Font size: +
7 minutes reading time (1325 words)

ፍርድ ቤቶች የዘነጓቸው አንገብጋቢ የተገልጋይ መብቶች

ፍርድ ቤቶች ሐምሌ 30 ሥራቸውን ካጠናቀቁ አንድ ሳምንት ሆናቸው፡፡ በየዓመቱ በክረምቱ አጋማሽ ተዘግቶ በመስከረም መጨረሻ የሚከፈተው ፍርድ ቤት ክረምት ጭር ይላል፡፡ የተወሰኑ የወንጀል ችሎቶችና ተረኛ ችሎቶች ካልሆኑ በቀር ፍርድ ቤቱ ከመደበኛው ሥራ ይቀዘቅዛል፡፡ አዲስ ፋይል መክፈት፣ አስቸኳይ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ (ለምሳሌ እግድ) መስጠት፣ ከበድ ያሉ የወንጀል ጉዳዮች ከመመልከት ውጭ መደበኛ ቀጠሮ አይስተናገድም፡፡ በዚህ በክረምት ወቅት ችሎቶቹ አይሠሩም ማለት እንጂ አስተዳዳሪዎቹ፣ ስለ ፍርድ ቤቶቹ የተሻለ አሠራር፣ የዳኞች አቅም የማጎልበት ሥራ፣ ስለ ሥራቸውና አገልግሎት አሰጣጣቸው የሚቀርቡ ቅሬታዎችን የማስተካከል ሥራ ላይ ይጠመዳሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ፍርድ ቤቱ ልማዳዊ የፍርድ ቤት አሠራሮችን በማስቀረት፣ የዳኞችን ሥነ ምግባር በመቆጣጠር እንዲሁም ለተገልጋዮች ምቹ የሚሆንበትን ሥራ የሚያስብበት ወቅት በመሆኑ፣ በዚህ ጽሑፍ በፍርድ ቤቶች የተዘነጉ ግን ተገልጋዮችን እየጎዱ ባለ ልማዶችና አሠራሮች ላይ የተወሰነ ምልከታ ለማድረግ እንሞክር፡፡

የመፀዳጃ ቤቱ ነገር

መፀዳጃና ፍርድ ቤት ምን አገናኛቸው እንዳልይባል ከገጠመኝ ልጅምር፡፡ በልደታ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተገልጋዮች መግቢያ በቀኝ በኩል ባሉት የድሮ ሕንፃዎች ጀርባ ሰዎች ተጣድፈው ሲገቡ ቀልቤን ሳቡኝ፡፡ ገንዘብ ቤት ወይም ኮፒ ቤት የሚሄዱ ቢመስልም ፍጥነታቸው የሚያሯሩጥ ሰው ያለ ነው የሚመስለው፡፡ ቀረብ ብዬ አንድ ወዳጄን ‹‹ሰዎቹ የት እየሄዱ ነው?›› ብዬ ስጠይቀው፣ ‹‹የተፈጥሮ ግዴታ ወጥሯቸው›› በማለት ሰዎቹ የሽንት ወረፋ ለመያዝ እንደሚቻኮሉ ነገረኝ፡፡ ከፍርድ ቤት ቅጥር ውጭም ባለጉዳዮችና ጠበቆች ሳይቀሩ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፊት ለፊት ካለው ኒያላ ሆቴል ጀርባ ለሽንት ማዘውተራቸው የተለመደ ነው፡፡ ድንገት ተራቸው ደርሶ ከተጠሩ ‹‹ኒያላ ሆቴል ለሽንት ሄደው ነው›› ቢባል የሚረዳ ይኖር ይሆን? ፍርድ ቤቶቻችን በጤና መሥፈርት አንፃር ቢገመገሙ ኖሮ አሁን ካሉበት ደረጃ የባሱኑ ዝቅ ሊሉ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ በርካታ ባለጉዳይ የሚስተናገድበት ፍርድ ቤት ለባለጉዳዮች፣ ለጠበቆች፣ ለነገረ ፈጆች የሚሆኑ መታጠቢያ ቤቶችና የመፀዳጃ ቤቶች የላቸውም፡፡ አዲስ በተሠራው የልደታው ፍርድ ቤት ሕንፃ ሳይቀር ሽንት ቤት ባለመኖሩ ጠበቆችና ባለጉዳዮች ከፍርድ ቤት ውጭ በየካፌውና ሬስቶራንቱ ሲዞሩ ይውላሉ፡፡ በዚህ ዘመን ዘመናዊ ሕንፃዎች አይደሉም የገጠሩ ማኅበረሰብ እንኳን የመፀዳጃ ቤት እንዲያዘጋጅ በሚመከርበት ወቅት፣ ትናንሽ ግሮሰሪዎችና ካፌዎች እንኳን መፀዳጃ ቤት ለደንበኞቻቸው በሚያቀርቡበት ጊዜ ፍርድ ቤቶች ረዥም ሰዓት ለሚያስቆሙዋቸው ባለጉዳዮቻቸው የተፈጥሮ ግዴታቸውን የሚወጡበት ቦታ አለማዘጋጀታቸው ደንበኛ ተኮር እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ በሰኔ ወር በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በተዘጋጀ ጉባዔና የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር በሐምሌ አጋማሽ በፍትሕ ሚኒስቴር ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ጠበቆች ‹‹ኧረ የመፀዳጃ ቤቱን ነገር አደራ!!›› የሚል መልዕክት ለፍርድ ቤቶቹ አመራሮች አሰምተዋል፡፡ አንዳንድ ጠበቆች ከልምዳቸው እንደሚናገሩት ከፍተኛ ታዋቂነት ያላቸውና የውጭ ዜጎች ሳይቀሩ የመፀዳጃ ቤት ጥያቄ ባቀረቡ ጊዜ አለማስተናገዳቸው የፍርድ ቤቱን ገጽታ እንደሚያጎድፈው ይናገራሉ፡፡ ሕፃናትና ነፍሰ ጡሮች፣ አረጋውያንና የታመሙ ሰዎች በሚገኙበት ፍርድ ቤት ለአስቸጋሪ ሁኔታ የሚጠቅም መታጠቢያ ቤትና መፀዳጃ ቤት አለመኖሩ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ የድሮዎቹ ፍርድ ቤት ለዳኞች መፀዳጃ ቤቶችን ሲያዘጋጁ ባለጉዳዮቹንም አይዘነጉም ነበር፡፡ ለዚህ ነው በአዲስ ባልተተኩት የድሮ ሕንፃዎች ንጽህናቸው አጠያያቂ ቢሆንም፣ ለባለጉዳዮች ሽንት ቤቶች አዘጋጅተው የምናስተውለው፡፡ የሽንት ቤት ነገር የፍርድ ቤቶች አስተዳዳሪ አካል የክረምት የቤት ሥራ ይሆናል ብለን ተስፋ እናድርግ፤ ካልሆነ ጤና ጥበቃ የሽንት ቤቱን ጥያቄ በይግባኝ እንዳይመለከተው፡፡

ጊዜ ዋጋ የሚያገኘው መቼ ነው?

ፍርድ ቤቶች በማሻሻያ ካመጡዋቸው ለውጦች አንዱ እያንዳንዱ ጉዳይ የሚፈጀውን ጊዜ በመወሰን ባለጉዳዮች ሙሉ ጊዜያቸውን ፍርድ ቤት እንዳያሳልፉ ቀጠሮ በቀን ብቻ ሳይሆን በሰዓትና በደቂቃ ጭምር መስጠት ነው፡፡ ይህ አዲስ አሠራር ለተወሰነ ጊዜ ከሠራ በኋላ ወደ ቀድሞው የልምድ አሠራር ተመልሷል፡፡ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት የተቀጠረ ባለጉዳይ 5፡45 ወይም 6፡30 ሊጠራ ይችላል፤ ዕድል ካልቀናውም ከሰዓት በኋላ ተመልሰህ ና ሊባል ይችላል፡፡ አንዳንዴ የችሎት አስተናጋጆች ሳይቀሩ 3፡00 ሰዓት ተቀተርክ ማለት በሰዓቱ ትስተናገዳለህ ማለት አይደለም እያሉ በድፍረት መናገር ጀምረዋል፡፡ ይህ የልማድ አሠራር ማሻሻያውን የሻረና የባለጉዳዮችን በተለይም የጠበቆችን ጊዜ የሚገድል ነው፡፡ ጠዋት የተቀጠረ ጠበቃ ጋዜጣ ሲያነብ፣ ሲያወራ፣ ሲቆም፣ ሲቀመጥ፣ ሲገባ፣ ሲወጣ ውሎ ዳኞች ለምሳ ከመውጣታቸው በፊት ተጠርቶ አልመረመርነውም ሌላ ቀጠሮ ሰጥተናል ማለት እየተለመደ ነው፡፡ ጠበቆች ሌላ ባለጉዳይ የሚያማክሩበትን፣ የማኅበራዊ ሕይወታቸውን የሚመሩበትንና ሙያቸውን የሚያዳብሩ ምርምሮችን የሚያከናውኑበትን ሰዓታት በፍርድ ቤት ያለ ጥቅም እያዋሉት ነው፡፡ በፍርድ ቤቶች የተጀመረ ማሻሻያ መልሶ ወደ ቀድሞው ልማዱ የሚሄድ ከሆነ ማሻሻያው ለምን አስፈለገ? ለምን በብዙ በጀትና የሰው ኃይል ታቀደ? በተለይ ፍርድ ቤቶች ለመዝጋት በተቃረቡበት የሐምሌ የመጨረሻ ሳምንታት ቀጠሮዎች ከሰዓታት መዘግየት ብቻ አይደለም ለሚቀጥለው ዓመት ቀጠሮ የማስፈንጠር ልማድ ያለ እስኪመስል ባለጉዳዮችና ጠበቆች ሲያማርሩ ይደመጣል፡፡ ‹‹ሰበር ለየካቲት ቀጠረኝ›› ‹‹ከፍተኛ ጥር አሽቀነጠረው›› ‹‹ፍርድ ቤቱ ያለ ታህሳስ አጀንዳዬ ክፍት አይደለም አለ›› ወዘተ. የሚሉ ሮሮዎች በፍርድ ቤቶች ጉዳይ የሚከታተሉ ጠበቆች ሮሮ ሆኗል፡፡ ቀጠሮዎች ሲሽቀነጠሩ የዳኛውንም ክፍያ በዚያው መጠን ያራዝመዋል፣ የደንበኛውንም ጭቅጭቅ እንዲሁ ይጨምረዋል፡፡ ብዙ ዳኞች እየተሾሙ ባለበትና የኅብረተሰቡ የንግድ ልውውጥ ከቀድሞው በተወሳሰበና በፍጥነት በሚከናወንበት ሁኔታ ፍርድ ቤቶች ለጊዜ ተገቢውን ዋጋ ካልሰጡ ማኅበራዊ ተቋምነት ምን ላይ ነው? ኔልሰን ማንዴላ ‹‹We must use time wisely and forever realize that the time is always ripe to do right›› ጊዜን በጥበብ በመጠቀም ሁልጊዜ ትክክል ነገር ለመሥራት እንጠቀምበት የሚለው አስተማሪ ንግግር ፍርድ ቤቶቻችን በክረምት ወቅት ለሚያደርጉት ለውጥ መነሻ እንደሚሆን ተስፋ ማድረግ ሞኝነት አይባልም፡፡

የዳኛ ማስቻያና የተገልጋዩስ ማረፍያ ከወዴት አለ?

የአራዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚገኝበት የሰባራ ባቡሩ ሕንፃን በችሎት ቀን ላስተዋለ ይህ ነገር ይገባዋል፡፡ በአዲሱ ልደታ በሚገኘው የፍርድ ቤት ሕንፃ የተስተናገደም ባለሙያ መጨናነቁን አስተውሎት ይሆናል፡፡ ፍርድ ቤቶች በግልጽ የማስቻል ግዴታ አለባቸው፡፡ በግልጽ ችሎት መዳኘት የዜጋ መብት ነውና፡፡ በግልጽ ከተዳኘ የተጠያቂነትና የግልጽነት መርሆች ይተገበራሉ፤ የፍርድ ቤት ትችት ይዳብርና የፍርድ ጥራት ይመጣል፡፡ በቂ የማስቻያ ቦታ ከሌለ ግን የዜጋውም መብት፣ የዳኞቹም ግዴታ አይተገበርም፡፡ አሁን አሁን የማስቻያ ቦታ ባለመኖሩ፣ ወይም ለሁሉም ችሎቶች በቂ ባለመሆኑ ወይም ጠባብ በመሆኑ ሕዝቡ በየፍርድ ቤቱ ኮሪደር ሲተራመስ ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡ አራዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሕንፃ  ኮሪደር፣ ደረጃና ቢሮ በር ላይ የሚጠብቁ ባለጉዳዮች ብዛት ከማረሚያ የሚመጡ ባለጉዳዮችን ለማሳለፍ አያስችልም፣ የሚያስችሉ ዳኛዎችን ይረብሻል፡፡ ከማስቻያው ቢሮ ጠባብነት አንፃር ኮሪደርና ደረጃ ላይ አለመቆም አማራጭ አይደለም፡፡ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 7ኛ፣ 8ኛ እና 9ኛ ችሎት አንድ ማስቻያ ብቻ ስላላቸው አንዱ ሲያስችል አንዱ በቢሮ ማስተናገድ፣ ባለጉዳዮች ፀሐይና ዝናብ ላይ መቆም የተለመደ ሆኗል፡፡ በቅርብ ጊዜ የተሠራው የልደታ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሕንፃም የማስቻያው ቦታ ጠባብ ነው፣ የባለጉዳይ ማረፊያ የለውም፣ መስኮት የሌላቸውና ዝናብ የሚገባባቸው ክፍሎች እንኳን መኖራቸው ይነገራል፡፡ በዚህ ሕንፃ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለሕፃናትና ለአረጋውያን የሚሆን አሳንሰር አለመኖሩ ለደንበኛ ምቹ ባለመሆን ቀዳሚ ያደረገው ሲሆን፣ በምን ስሌት የሕንፃው ዲዛይን እንደተነደፈም ጥያቄ የሚፈጥር ሆኗል፡፡ ፍርድ ቤቶች መብት የሚጠየቅባቸው፣ የተበደሉ ተስፋ አርገው የሚመጡባቸው፣ ፍትሕ የሚሠራባቸው፣ የሕግ ምሁራን እውቀታቸውንና የክርክር ጥበባቸውን የሚያሳዩበት ቦታ እንደመሆኑ በቂ የማስቻያ ቦታና የባለጉዳዮች ማረፊያ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በክረምት የፍርድ ቤቱ አስተዳደር በሚያቅደው አሠራር ዳኞች በቂ የማስቻያ ሥፍራ፣ ባለጉዳዮች ምቹ ማረፊያ ያገኙ ይሆን? መስከረም ሲጠባ የምንመለከተው ይሆናል፡፡

ፍትሕን የሚዳስሱ ሰዎች ነገርስ?

በሁሉም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚነበብ አንድ የጋራ ማስታወቂያ ፍትሕን የሚደልሉ ሰዎችን ነገር ይመለከታል፡፡ በፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ጉዳይ እናስፈጽማለን፣ ዳኛ እናውቃለን፣ ፍርድ እናሰጣለን የሚሉ ደላሎች በመኖራቸው እንዲጠቁሙን፣ በፍርድ ቤት ሠራተኞች ላይ ያያችሁትን የሥነ ምግባር ጉድለት በተጠቀሰው ስልክ ቁጥር አሳውቁ የሚሉ ማሳሰቢያዎች አሁንም አሉ፡፡ ፍትሕን የሚደልሉ ሰዎች መኖራቸው በፍርድ ቤቱ አመራር ሳይቀር ታውቆ በገሃድ ለማስታወቂያ በቅቷል፡፡ ጸሐፊው ያናገራቸው ጠበቆችም ‹‹ጥብቅና አያዋጣም፣ ድለላ ሆኗል፣ በተወሰኑ ሰዎች ኔትዎርክ ሥር ወድቋል!!›› በሚል በሙያቸውና በሕግ ሥርዓቱ ሲያማርሩ መስማት ተለምዷል፡፡ የጠበቃ የሕግ ዕውቀቱና የሙግት ክህሎቱ የማይፈተንበት፣ ሕግ ባለሙያዎች በኅብረተሰቡ ውስጥ አንገታቸውን ቀና አድርገው የማይሄዱበት፣ ሕግ ሙያን ከሙስናና ጉቦ ጋር ብቻ የሚያያዝበት ዘመን የሆነው በእነዚህ በፍትሕ ደላሎች ሳይሆን እንዳልቀረ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ በፍርድ ቤት የተለጠፈውን የፍትሕ ደላላ መፈለጊያ ማስታወቂያ ያነበበ ባልንጀራዬ ጉዳይ ጉዳዩ (ደላላው) መረቡ ከፍርድ ቤት ውጭ መሆኑን በመጠቆም የፍርድ ቤቱን በቅጽሩ ደላላ የመፈለግ ጥረት ይተቻል፡፡ በእርግጥ የፍትሕ ደላሎቹና ባለጉዳዮቹ የሚገናኙት፣ የሚስማሙትና የሚቀባበሉት ከፍርድ ቤት ውጭ እንደመሆኑ መጠን ሰፊ ዘመቻ የሚፈልግ ቢሆንም በፍርድ ቤቶቹ የተለጠፈው ማስታወቂያም ፍርድ ቤቱ የያዘውን አቋም ሕዝቡ ይረዳበታል፤ ሲገኝም ደላላው ይጠመድበታል፡፡ ስኳር ለለመደ ዳኛ፣ ፋይል ለሚደብቅ የችሎት ጸሐፊ፣ ሥልጣኑን ለክፉ ለሚጠቀም ኃላፊ፣ ወዘተ. ጥሩ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ሆኖም ከማስታወቂያ መለጠፍ ባለፈ የዳኞችን ሥነ ምግባር ደንብ በተጨባጭ መፈጸም፣ ዳኞች ለሙያ ሥነ ምግባራቸውና ለህሊናቸው እንዲታመኑ የሥነ ምግባር ሥልጠናዎችን መስጠት፣ ጠበቆችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላትን የሚያካትት ኔትወርክ መዘርጋት፣ የባለጉዳዮችን አስተያየትና ጥቆማ በሙሉ ጊዜው የሚቀበልና የሚመረምር ኮሚቴ ማዋቀር ከፍርድ ቤቶቹ የሚጠበቅ ሥራ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶቻችን የዳኞች ነፃነትንና ተጠያቂነትን በጥንቃቄ ተግባር ላይ ካዋሉ የፍትሕ ደላላ ቦታ አይኖረውም፡፡ ነፃነታቸው ተጠያቂነታቸውን እንዳያስቀረው፣ ተጠያቂነታቸው ነፃነታቸውን እንዳያጠበው በጥንቃቄ ከተሠራ ለውጥ ይመጣል፡፡ የፍትሕ ደላሎችን ማጥፋት የሚቻለው በፍርድ ቤት ጥረት ብቻ ባለመሆኑ  የጠበቆች ማኅበርም አባላቱን በአግባቡ በማወቅ፣ በመመዝገብ፣ የሥነ ምግባር ደንብ በመቅረጽ (ከሕጉ በተጨማሪ)፣ በማሠልጠን፣ ጥፋተኛን በማጋለጥና ከአባልነት በመሠረዝ ጭምር የራሱን ጥረት ካላደረገ ሕግን እንደ ሙያ ከሥነ ምግባር ጋር መያዝ ብርቅ እንዳይሆን ሥጋት አለ፡፡ የፍትሕ ደላሎች የሕግ ባለሙያውንና የፍትሕ ሥርዓቱን ሥም ከማርከስ ባለፈ ገንዘብ፣ ሀብት፣ ዘመድ ወይም ሌላ መመኪያ ሳይኖራቸው ሕግንና የሕግ ሥርዓቱን ብቻ መከታ አድርገው መብታቸውን ለጠየቁና ለሚጠይቁ ባለጉዳዮች እጅጉን ይጎዳልና በዚህ ክረምት ይታሰብበት፡፡

ከላይ የዘረዘርናቸው ነጠቦች ማሳያ እንጂ ፍርድ ቤቶቻችንን ያሉባቸውን ተግዳሮቶች በምሉዕነት የሚዳስሱ አይደሉም፡፡ ያነሳናቸው ነጥቦች በቀጥታ ከሕግ አተረጓጎምና ከፍርድ ቤት የሕግ ኃላፊነት ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡ የማይያያዙ የሚመስሉትም ሥራው ላይ ተፅዕኖ ያደርጋሉ፡፡ ችግሮቹ ፍርድ ቤቶች ሥራቸውን በአግባቡ በመሥራት ሕዝባዊ ተቋማት እንዳይሆኑ እያሰናከሏቸው ካሉ ምክንያቶች የተወሰኑት ናቸው፡፡ ችግሮቹ በአብዛኛው በአስተዳደራዊ መፍትሔዎች፣ ለምሳሌ መፀዳጃ ቤቶች፣ መጠለያ፣ ችሎት ማስቻያ ቤቶችን በማመቻቸት እንዲሁም ዳኞች ባለጉዳዮችን በተገቢው ጊዜና በሥነ ምግባር እንዲያስተናግዱ የሚያደርግ ሥርዓት በመፍጠር ሊቀረፉ ይችላሉ፡፡ በዚህ በክረምት ወቅት (በፍርድ ቤቶች የዕረፍት ወራት) የፍርድ ቤት አመራሮች እነዚህን ነገሮች በተጨባጭ ለመፍታት ይሠራሉ ብለን እናምናለን፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

እንዴት ያለባለቤቱ ሙሉና ነጻ ፈቃድ የተላለፈን ንብረት ማስመለስ፤ የተቋቋመን የ...
በቀጠሮ ቀን ፍርድ ቤት ያለመቅረብ ውጤቶች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 13 November 2024