በሰዎች የእለት ከዕለት መስተጋብር ዉስጥ ከሚፈጠሩ ነገሮች መካከል አንዱ ቅራኔ ነዉ። ቅራኔ ሲኖር ደግሞ የመረጃ ወይም ማስረጃ ጉዳይ አብሮ ይነሳል። በተለይ ለዳኝነት አካላት ማለትም ለፍርድ ቤት፤ ለግልግል እና ለመሳሰሉት በሚቀርቡ ክርክሮች ላይ ማስረጃን ወይም መረጃን የሚመለከቱ ጉዳዮች መነሳታቸዉ አይቀሬ ናቸዉ። እዚህ ላይ የመረጃ እና ማስረጃን ልዩነት መረዳት ተገቢ ነዉ። ማስረጃ አንድን አከራካሪ ፍሬ ጉዳይ ለማረጋገጥ ወይም ለማስተባበል የሚቀርብ ተጨባጭ ጉዳይ ሲሆን፤ መረጃ ግን አንድን ነገር ለማረጋገጥ ወይም ለማስተባበል የሚሰጥ መግለጫ (Information) ብቻ ነዉ። ሁሉም ማስረጃ የመረጃነት ባህሪ ያለዉ ሲሆን፤ ሁሉም መረጃ ግን ማስረጃ አይደለም። ማስረጃ ለፍትሕ አካል የሚቀርብ መረጃ ሲሆን፤ ይህ መረጃም ፍሬ ነገርን የሚመለከት ነዉ። ፍሬ ነገር ማለትም በፍርድ ቤት ወይም በሌላ የዳኝነት አካል ፊት አከራካሪ ሆኖ የወጣ እና የተያዘ ጭብጥን የሚመለከት ነዉ። ማስረጃ የሚቀርበዉም ይህንን አከራካሪ ጭብጥ ወይም ፍሬ ነገር ለማረጋገጥ ወይም ለማስተባበል ነዉ። የማስረጃ ሕግ ተፈጻሚነት የሚታየዉም በዚህ ጊዜ ነዉ።