መግቢያ
በዚህ የውድድር ዘመን አሰሪዎች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ወይም ምርት በጥራት እና በፍጥነት ለደንበኞቻቸው ማቅረብ ይገባቸዋል። ከዚህም ባለፈ አንዳንድ ሙያዎች በባህሪያቸው በአደራና እምነት ላይ የተመሰረቱ (positions of trust) ስለሆነ ሰራተኛው ለዚህ የሥራ መደብ የተገባ መሆን ይገባዋል። በመሆኑም አሰሪዎች መልካም ስማቸውን ጠብቀው የገበያ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ በቴክኖሎጂ እና በሰለጠነ የሰው ሃይል ተቋማቸውን ያጠናክራሉ። ሆኖም ግን የሰው ሃይል ቅጥር በሚፈፅሙበት ወቅት ከግለሰብ የግል ባህሪ እና በዲጅታል ቴክኖሎች መሳሪያዎች ሀሰተኛ ሰነድ ለማዘጋጀት ከመቼው ጊዜ በላይ ለመለየት በሚያስቸግር መልኩ ረቂቅ፣ በቀላሉ የሚገኝና ተግባር ላይ የሚውል በመሆኑ የቅጥር መስፈርቱን የማያሟላ እና ለስራው ትክክለኛና ተገቢ ያልሆነው ስራተኛ እንዲቀጥሩ በማድረግ ከገበያ ተወዳዳሪነት የሚያስወጣ የስጋት ተጋላጭነታቸውን አሳድጎታል።