Font size: +
11 minutes reading time (2215 words)

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን - የሴቶች ጥቃት ችግር - ሴቶች

እንኳን ለአለማቀፍ የሴቶች ቀን አደረሳችሁ። ዛሬ የመጣሁበት ዋነኛ ምክንያት ከዚህ ቀን ማለትም ከአለማቀፍ ሴቶች ቀን እና አለማቀፍ ነጭ ሪቫን ቀን አከባበር ጋር በተያያዘ ሁል ግዜም በአይምሮዬ የሚመላለሱ ጥያቄዎች ስላሉኝ እነሱን ለማንሳት እና ከጉዳዩም ጋር ተያይዞ ከስራ እና በሕይወት የተረዳኋቸውን አንዳንድ ነጥቦች ለማካፈል ነው።

በእርግጥ ሁሉም ችግሮች እንደየደረጃቸው እና ጥልቀታቸው በጥናት የሚለዩ መሆኑን አምናለሁ። ይሁን እና ጥናትም ለማድረግ ችግሩ ባለቤት ሊኖረው የሚገባ ስለመሆኑ ደግሞ የምንግባባበት ነው ብየ አስባለሁ። ይህ እንዳለ ሆኖ ጥናትም ለማድረግ ቢሆን መጀመርያ ላይ መነሻ ሊኖረን የሚገባ ነው። ለዚህም ነው ከዚህ ጉዳይ ጋር በተገናኘ በግል ያስተዋልኳቸው አንዳንድ ነጥቦችን ባጋራችሁ እንወያይበታለን ብዬ ያሰብኩት። ስለሆነም ምናልባት ጉዳዩን በጥልቀት ባለመረዳት የማነሳቸው ሀሳቦች የተሳሳቱ ከሆኑ ይቅር እንድትሉኝ እና በሀሳብ እንድትሞግቱኝ በሀሳቤ የምትስማሙም ከሆነ ደግሞ እኔ ጉዳዩን ካየሁበት አቅጣጫ በተጨማሪ ያላችሁን ልምድ እና ግንዛቤ ብትጨምሩበት ምናልባትም በጉዳዩ ላይ ቀጣይ ጥናት ለማድረግ የሚያስብ ሰው ካለ ጽሁፉን በመነሻነት እንኳ ሊጠቀምበት ይችላል ብዬ አስባለሁ።

በዚሁ መሰረት ሀሳቤን ጥያቄ በመጠየቅ ልጀምር እስኪ። የመጀመርያው ጥያቄየ በተለምዶ የሴቶች እኩልነት እና የሥርዓተ ጾታ እኩልነት ሲባል እንሰማለን አይደል። የእነዚህ ሁለት ትልልቅ ጽንሰ ሀሳብቦች ልዩነትና አንድነት ምንድነው? አንዱ በሌላው ውስጥ የሚካተት ነው? ወይስ የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው? የተለያዩ ከሆኑ ለምንድነው ከዚህ ጋር በተገናኘ በሚዘጋጁ ትልልቅ መድረኮች ሳይቀር የሴቶች እኩልነትን ከሥርዓተ ጾታ እኩልነት ጋር እየደባለቅን የሚነሳው?

ይህ ቀን ማለትም የሴቶች ቀን በዚህ ስም ማለት የሴቶች ቀን ተብሎ መከበሩን ምን ያህል ትቀበሉታላችሁ? ይህንን የጠየኩት አንዳንድ ቀኑ መከበር ያለበት መሆኑን የሚያምኑ ነገር ግን ስያሜው ሊስተካከል ይገባል ብለው የሚያምኑ ሴቶች ወይም ሰዎች ስለገጠሙኝ ነው።

የሥርዓተ ጾታ እኩልነት እንበለው የሴቶች እኩልነት እነዚህ ሁኔታዎች በራሳቸው ግብ ናቸው? ወይስ የግቡ ሂደት? ግብ ናቸው የምንል ከሆነ የታወቁ ሂደቶቹ ምን ምን ናቸው? ለምንስ ሲተገበሩ አናይም? አይ ግብ አይደሉም የምንል ከሆነ የእነዚህ ጽንሰ ሀሳቦች ግቦች ምንድናቸው? ለምንስ አይተገበሩም?

እሺ ምናልባትም ጉዳዩ የጽንሰ ሀሳብ ነው የምንል ከሆነ እና ይህንን ሳይንሱ ይመልሰዋል ለዚህ ምን አሳሰበሽ የምትሉ አትጠፉም። ጉዳዩ ወዲህ ነው። ሁልጊዜም አይምሮዬ አንድ ጥያቄ ይጠይቀኛል። ይኸውም የሴቶች እኩልነትን አስመልክቶ በአለም አቀፍ ደረጃ የተተገበሩ ፖሊሲዎች ህጎች እና እንቅስቃሴዎችን ትተን በሀገራችን እንኳ ከባለፉት ሰላሳ አመታት ጀምሮ ያለውን እንቅስቃሴ የምናውቀው ነው።

ሀገራችን ኢትዮጵያ የሴቶችን እኩልነት ና እኩል ተጠቃሚነት ለመረጋገጥ እራሱን የቻለ የሴቶች ፖሊሲ ቀርጻ በህገ መንግስቷ ሳይቀር የሴቶች እኩልነትን እንደ አንድ የሰብአዊ መብት ደንግጋ ትገኛለች። ይህንን መብት የሚያስፈጽሙ እና አና የሚከታተሉ መንግስታዊም ሆኖ መንግስታዊ ያልሆኑ እንደ አሸን የፈሉ ተቋማትም በሀገራችን እንዳሉ የምናውቀው ነው።

ይሁን እና አሁንም ድረስ ያውም ከድሮው በባሰ መልኩ ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች አሉን። ትልልቅ የመንግስት እና የህዝብን ኃላፊነት የተሸከሙ ነገር ግን በባሎቻቸው የሚደበደቡ፣ በአባት ወንድሞቻቸው የሚደፈሩ ሴቶች እህቶች እና እናቶች አሉን። አሁንም ድረስ ሀሳባቸውን ለመግለጽ የሚፈሩ እኔ አልችል ይሆን? ብለው በራሳቸው የማይተማመኑ ሴት እህቶች አሉን። አሁንም ድረስ ለብቻቸው በመንገድ ለመሄድ የሚፈሩ ብቻቸውን ትምህርት ቤት የማይላኩ ሴቶች አሉን። አሁንም ድረስ የንጽህና መጠበቅያ ሞዴስ አጠቃቀምን የማያውቁ ቢያውቁም የመጠቀም የማይችሉ ሴት እህቶች አሉን። እናም የኔ የማያርፈው አይምሮ ሁል ጊዜም ለምን እያለ ይጠይቃል። ለምን እንዲህ ሆነ? ለምን?

ካላችሁ ልምድ ምናልባትም በጥናት የተረጋገጡ የምትሏቸው ምላሾች እንዳላችሁ አምናለሁ። ለምሳሌ የህጉ ክፍተት፣ በአጥፊው ላይ የሚጣለው ቅጣት አነስተኛ መሆኑ፣ የህጉ እና የፖሊሲው አፈጻጸም ከፍተት፣ በቂ የሆነ ጉዳዩን የሚመለከት ተቋም አለመኖት፣ አሁን ላይ ባሉን በተቋማት መካከል ያለ አነስተኛ የሆነ ቅንጅት ወይም የቅንጅቱ አለመኖር፣ ለጉዳዩ በቂ ትኩረት አለመስጠት እና የመሳሰሉትን እንደ ምክንያት ወይም ለጥያቄዬ እንደ ምላሽ ልትጠቅሱልኝ እንደምትችሉ አውቃለሁ። በእርግጥ የተጽኖአቸው ደረጃ በጥናት የሚለይ ሆኖ እነዚህ እያንዳቸው ጉዳዮች ለችግሩ አስተዋጽኦ የላቸውም ብዬ እኔም አላምንም።

ነገር ግን አሁን ላይ ለችግሩ ዋነኛ ምክንያት ምንድነው ብላችሁ ብትጠይቁኝ ምላሼ እኛው ሴቶች ሚና ከእነዚህ ጉዳዮች ያልተናነሰ መሆኑን ነው የምነግራችሁ። እንዴት አትሉኝም?

ቀድሞ በነበርኩበት ተቋም በሴቶች እና ህጻናት ክፍል ባለሙያነት እሰራ ነበር። ይህም ሁኔታ በጉዳዩ ላይ አንቱ የተባሉ ሰዎችን እና አሉ የተባሉ ተቋማትን እንዳውቅ እንድተዋወቅ እረድቶኛል። ከሞላ ጎደል ከእያንዳንዱ ተቋማት ጋር በእነዚሁ የበአል አከባበር ጋር በተገኘ በሚዘጋጁ መድረኮች ላይ የመገኘት እድሉም ነበረኝ። በብዙዎቹ መድረኮች ላይ እሳተፍ ሀሳብ እሰጥም ነበር። በተለይም እኔም እራሴ ለችግሩ ዋነኛ መንስኤ ነው ብዬ አምናቸው የነበሩት ከላይ የዘረዘርከዋቸው ነጥቦች ስለነበሩ ለችግሮቹ መፍትሄ የሰጠሁ እስኪመስለኝ ድረስ በጉዳዮቹ ላይ ሀሳብ እሰጥባቸው ነበር። ይሁን እና ያየኋቸው እና ተገነዘብኳቸው ጉዳዮች በሙሉ ያስረዱኝ እና ያስገነዘቡኝ አንዳንድ ነገሮች አሉ።

አንደኛው እኛ ሴቶች ለችግሮቹ መኖር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የየራሳችን ሚና እንዳለን ነው። ለምሳሌ ያክል አብዛኞቻችን ሴቶች እንችላለን እያልን እንገልጻለን። እንደውም ይህ የአንድ ሰሞን የበአሉ መሪ ቃል እንደነበረም አስታውሳለሁኝ። ባልሳሳት " ሴት ልጅ ትችላለች" የሚል ነበር መሰለኝ። በነገራችን ላይ ምንድነው የምትችለው? ምግብ ማብሰል?፣ ቤተሰቧን መንከባከብ? የቤት ውስጥ ስራ መስራት? ወይስ ምን?

እርግጠኛ ነኝ ይህ ትችላለች የሚለው ቃል ለእነዚህ አይነት ጉዳዮች ታስቦ የተደረገ አይደለም። ምክንያቱም እነዚህ ስራዎች በዋነኛነት የሴቶች ኃላፊነት ናቸው ተብሎ በእኛ በሴቶቸ ጭምር ስለሚታመን ትችላለች እየተባልን ያለነው ለእነደዚህ አይነት ስራዎች እንዳልሆነ የምናውቀው ነው። ይልቁንም ይህ ትችላለች የሚለው ነገር የመጣው ሴት ትላልቅ የሚባሉ በተለይም በህብረተሰቡ ዘንድ የወንድ ሀላፊነት ተብለው የተለዩ ከቤት ውጪ የሚሰሩ እና ገቢ የሚያስገቡ ስራዎችን ሴትም መስራት እና ኃላፊነትን መወጣት ትችላለች ለማለት የታሰበ ነው።

ይሁን እና በዋነኛነት የሴት ስራዎች ናቸው ተብለው በህብረተሰቡ ዘንድ የተለዩ ስራዎችንም በአግባቡ የሚሰሩ ወንዶችም እንዳሉ የምናውቀው ነው። ይሁን እና ለእነዚህ ስራዎች ወንዶች አንድም ቀን ወንዶች ይችላሉ የሚል ሞቶን ሲያስተጋቡ አይታዩም። ሁሉም ስራ እኩል ነው። ማንኛውም ስራ ወንድም ይስራው ሴት ያው ስራ ነው። ስለዚህም ስራውን ችለን እስከሰራነው ድረስ እችላለሁ ብሎ መፎከርን ምን አመጣው። ዋናው ጉደይ መቻላችን አይደል። ከቻልን ደግሞ ቻልን ነው። መናገር ሳይሆን የሚጠበቅብን መቻላችንን ማሳየት እንጂ። እኔ መኪና ካለኝ መኪናው የኔ ነው። ተናገርኩም አልተናገርኩም በቃ መኪናው የኔ ነው። ባለመናገሬ መኪናው የኔ ከመሆን አይቀር። እንዴት አውሮፕላን የምታበር ሴት ባለችበት አለም እና ሀገር ሴቶች አውሮፕላን ማብረር ይችላሉ ብለን እንፎክራለን። ይህ እኮ በራሱ ለራሳችን አንችል ይሆን? ከሚል ፍርሀት አለመላቀቃችን ያሳብቅብናል። ከቻልን በቃ ቻልን ነው። ዝም ብሎ እየሰሩ መኖር፡፤

የተዛባ አመለካከት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሉም እያልኩኝ አይደለም። ግን ለእነሱም ቢሆን መቻላለችንን በመንገር ሳይሆን አመለካከታቸውን የምንቀርፈው መቻላችንን በማሳየት ብቻ ነው። መቻላችን ልምድ ወይም ተግባር እስከሆነ ድረስ ልክ እንደወንዶች መቻል ተወስዶ ሴቶች ይችላሉ ሳይሆን ሁሉም ሰዎች ይችላሉ ወደሚል ተግባር የሚቀየር ይሆናል።

ሌላው ለምንስ የኛ ተብለው የተለዩ ስራዎችን እናሳንሳለን። ያውም ሰፊ ጊዜን እና ጉልበታችንን እያፈሰስንባቸው የምንሰራቸውን ስራዎችን ከቤት ውጪ ካለው ስራ እኩል ባለማየት እንደውም በማሳነስ ሁል ጊዜም እችላለሁ እያልን የምናስተጋባው ከቤት ውጪ ለሚሰሩ ስራዎች ብቻ ነው። ይህን ስል የቤቱ ስራ ለሴቶቸ የተተወ ነው ብዬ የማምን ሆኜ አይደለም። ይሁን እና የቤቱ ስራ የሴቶች ስራ ነው ከተባለ ግን ይህንን ስራ ልንኮራበት ከቤት ውጪም ካለው ስራ እኩል መሆኑን ልንተማመንበት የሚገባ ሆኖ ሳለ መቻላችንን ሁል ግዜም ከቤት ውጪ ለሚሰሩ ስራዎች ማድረጋችን በራሱ ለቤት ውስጥ ስራ አናሳ አመለካከት በራሳችን በመፍጠር በተዘዋዋሪ መንገድ በአመለካከት እኩል ላለመሆናችን ድርሻችንን እየተወጣን አይደለም ወይ ብዬ አምናለሁ።

አንዲት ሴት የቢሮ ስራ ባይኖራት እና የቤት እመቤት ብትሆን ይህንን መግለጽ የሚገባት በኩራት ሆኖ ሳለ እኛ ግን የቤት እመቤትነትን አሳንሰን በማየት ስራሽ ምንድነው ተብለን ስንጠየቅ ስራ የለኝም በማለት እንገልጻለን። ይህ በራሱ እኛም ለችግሮቹ መኖር የራሳችንን ድርሻ በተዘዋዋሪ መንገድ እየተወጣን አይደለም ወይ ያስብሉኛል።

ሌላው ደግሞ አንዳንድ ሴቶች የራሳቸው ወይም የግላቸው የሆነን ጉድለታቸውን ለመሸፈን ሴትነታቸውን ሲጠቀሙ አያለሁ። እንዴት አትሉም። ለምሳሌ እኔ ካለሁበት መንግስታዊ ኃላፊነት አንጻር ሲታይ ስራዬን በአግባቡ እና በብቃት ከሰራሁኝ ልመሰገን ስራየን ግን በአግባቡ ካልሰራሁ ልወቀስ የሚገባኝ ስለመሆኑ እውነት ነው። ስራየን ባለመስራቴ ምክንያት ስወቀስ የተወቀስኩት ሴት በመሆኔ ነው ብለን የራሳችንን ጉድለት ወይም ድክመት በሴትነታችን የምንሸፍን ብዙዎች ነን። በነገራችን ላይ ወቀሳውም ሆነ ምስጋናው ከያዝነው ኃላፊነት ጋር እንጂ ከጾታችን ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። ስንመሰገን ችለናል ስንወቀስ ደግሞ ሴት ስለሆንን ነው ብለን የምናስብ እና በዚህም ተከልለን የምንኖር ከሆነ በአመለካከት ረገድ እኩል መሆናችንን አለማመናችን ነው ለኔ የሚያሳየኝ። በነገራቸን ላይ ይህንን ነገር አንድ የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊ የነበሩ ሴት አመራር ከስራቸው ጋር በተገናኘ ለተነሳባቸው ትችት ምላሽ ሲሰጡ "እንዲህ የተባልኩት ሴት በመሆኔ ነው እንጂ ቦታው ላይ ያለው ወንድ ቢሆን ኖሮ ተቺው እንዲህ የማለት ድፍረት አይኖረውም ነበር" ሲሉ ሰምቻለሁ።

ይገርመኛል አንዳንዶቻችን ጭራሽ በፈተና አንደኛ ወጥተን እያለ ሴት ስለሆንን ብቻ ያችን መከረኛ ሶስት ነጥብ እንዲጨመርልን የምንፈልግ ነን። እንግዲህ በሴትነታችን ሁሌም የልዩ መብት ተጠቃሚ እንድንሆን የምንፈልግ ከሆነ እኛ እራሱ መቻላችንን መቼ አመንን ያስብለኛል። ስለዚህም የኛው የሴቶች የአመለካከት ችግር በራሱ አሁንም ድረስ ችግሩ ዘልቆ እንዲኖር አስችሎታል ብዬ አስባለሁ። እነዚህ ነጥቦች በዋናነት ከአመለካከት ችግር ጋር በተያያዙ የማያቸው የኛው ሰቶች ክፍተቶች ናቸው።

ሌላው የኛው የሴቶች ችግር ሆኖ ያገኘሁት ደግሞ ችግሮቹን ለመፍታት የምንሄድባቸው መንገዶች ላይ ነው። የመጀመርያው አንዳንድ መንገዶቹ እውነተኛ እና የሴቶቹን ችግር በእርግጥም ለመፍተታ የሚፈልጉ ሆንው አላገኘዋቸውም። ሴቶችዬ እንዴት አትሉም? እንደምታውቁት ከሴቶች ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተለያዩ መድረኮች ይዘጋጃሉ። በተለይም አንዲት ሴት ጥቃት ደርሶባት ከሆነማ በየቦታው "ፍትህ ለእከሊት" የሚሉ መድረኮች ግፋም ሲል ሰልፎች በብዛት ይታያሉ። ይሁን እና እነዚህ መድረኮች የአንድ ሰሞን መድረኮች እንጂ ዘላቂነት ያላቸው ሆነው አላየሁም። እንደነገርኳችሁ በብዛት መድረኮቹ ላየ ተሳትፌ የማውቅ እንደመሆኑ መጠን በቀጣይ ምን እናድርግ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲደረግ እና አቅጣጫ ሲቀመጥ እንዲሁ የኃላፊነት ክፍፍል ሲደረግ አላየሁም።

እንደውም መድረኮቹ ላይ የሚቀርቡ ጥናት መሰል ጽሁፎችም ሆኑ ፕሮግራሞች እጅግ የተደጋገሙ ከመሆናቸው የተነሳ በቦታው ያልነበረ ሰው እንኳ ስለጉዳዩ አውቃለሁ እንዲል የሚያስችሉም ናቸው። እንዴት አንድ ሴክተር ሰላሳ አመት ሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ ስለ ወንጀል ቅጣት ማነስ ጽሁፍ ያቀርባል? ያውም በመንግስት ላይ ጫና መፍጠር እና መደራደር የሚችል አቅም የፈጠሩ ሴቶች ባሉበት ሀገር እተደጋገመ የወንጀል ቅጣት ለችግሩ መባባስ በየ አመቱ በምክንያትነት ይቀርባል? ይህ መሆኑ በራሱ ችግሩን ለመቅረፍ እየሄድንበት ያለው መንገድ እውነተኛ አለመሆኑን የሚያን ነበር። እውነተኛ ቢሆን ኖሮ ለምሳሌ ለወንጀሉ ቅጣት ማነስ ለችግሩ መባባስ የራሱ ሚና ቢኖረው በየአመቱ በምናዘጋጀው መድረክ ላይ ቅጣት አነሰ በማለት ከመደስኮር ይልቅ በመፍትሄው ላይ እናተኩ ነበር። መድረኮቻችንም የአንድ ሰሞን መድረኮች ብቻ ሆነው አይቀሩም ነበር። ሀሳቦቻችን ቀን በመሰየም ማክበር ላይ አያተኩሩም ነበር፡

እንደምታውቁት መንግስት ልዩ ትኩረት የሰጣቸው የወንጀል አይነቶች አሉን። ለምሳሌ የሽብር ወንጀሎች፣የሙስና ወንጀሎች፣በገቢዎች እና በጉምሩክ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። መንግስት እነዚህ የወንጀል አይነቶች በሀገር እና በኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሱትን ጫና በመረዳት ከመደበኛው የወንጀል ህግ ወጥተው በራሳቸው ልዩ ህግ እንዲመሩ አድርጓል። አዋጆቹም ጸድቀው ስራ ላይ መዋላቸውን ሁላችንም የምናውቀው ነው። ሴቶች ማለት የህብረተሰቡ ግማሽ ክፍሎች ናቸው ሲባል እሰማለሁ። ሀገር ናቸውም ይባላል። እሰይ ይሁን። ነገር ግን ይህን የህብረተሰቡን ግማሽ በመሆነው ክፍል ላይ የሚፈጸምን ወንጀል በተመለከተ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ጉዳዩን በተለየ ህግ እንኳ እንዲመራ እንዲያደርግ እኛ ሴቶች ከመንግስት ኃላፊዎች እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር ቁርጥ በሆነ አቋም ስንደራደር አንታይም። አድርገን ቢሆን እንኳ አሁንም ድረስ ለውጥ አለመኖሩ ግፊታችን አናሳ ወይም በቂ አለመሆኑን ከሚያሳይ በቀር ሌላ የሚባል አይሆንም።

ሌላው ያስተዋልኩት ነገር በየመድረኮቻችን የሚነሱ ሀሳቦች ዘመናችንን የሚመጥኑ አለመሆናቸውን ነው። አሁን እማ ጭራሽ "እባካችሁ አትግደሉን" ወደ ማለት መድረኮቻችን ተሸጋግረዋል። ሴቶችዬ ይህ በእኔ እምነት መብትን መለመን ነው። በነገራችን ላይ በሂወት የመኖር መብት የሁሉም ሰው ልጅ መብት ነው። ማንም ማንንም የመግደል መብት የለውም። ስለሆነም አተግደሉኝ በማለት በየአመቱ በጥቃት ምክንያት ሂወታቸውን የሚያጡ ፣ አካላቸው ለሚጎዳ እና ስነልቦናቸው ለሚቃወስ ሴት እህቶቻችን መፍትሄ አይመጣም። ይህ አባባልስ ለህብረተሰቡ ምንድነው የሚያስተላልፈው መልእክት? እራሳችንን መጠበቅ አለመቻላችንን? ወይስ ምን? እኔ ይህ ጤናማ የሆነ አካሄድ ነው ብዬ አላምንም።

የእነዚህ መድረኮች ግብስ ምንድነው? እንዳልኳችሁ መድረኮቹ በየ አመቱ የሴቶችን ቀን እና የነጭ ሪቫንን ቀን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ አካላት ሲዘጋጁ ይታያል። እንዲሁም ጥቃት የደረሰባት እና በህዝቡ ዘንድ የታወቀች ወይም "ታዋቂ ሰው የሚያውቃት" ሴት እህት ባለች ሰሞን ከላይ እንዳልኳችሁ በየቦታው ብዛት ያላቸው ጥቃቱን የሚያወግዙ መድረኮች በሴቶች እና ጉዳዩን በሚያቀነቅኑ አካላት ሲዘጋጁ ይታያል። ይህ ሁኔታ እኔ እንኳ ጉዳዩን ማስተዋል ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ሲታይ በጣም በተደጋጋሚ የሚደረግ አሁን አሁን እማ እንደ ፋሽን ወይም ስታይል የሚቆጠር አካሄድ እየሆነ መጥቷል። ይህም መድረኩን ማዘጋጀት ብቻ እንደ ግብ እተቆጠረ እንዳይሆን በጣም ያሰጋኛል። ምክንያቱም መድረኩ መዘጋጀቱ ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ የለም። ለውጥ ቢያመጣማ ኖሮ ጥቃቱ አሁን ላይ በተባባሰ መልኩ ሁኔታውን እቀየረ ባልመጣ ነበር።

ሌላው ያስተዋልኩት ነገር ደግሞ በመድረኮቹ ላይ የሚነሱት ሀሳቦች በመሬት ላይ ያለውን ችግር ፈቺ ሳይሆኑ ህብረተሰባችን አሁን ካለበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር በተለይም የገጠሪቷን ኢትዮጵያ ሴቶች ከግምት አስገብተን ስናያቸው " ሌግዠሪ" የሚባሉት አይነት ናቸው። ሴቶችዬ ለምን የሞዲስ ዋጋ 60 ብር (ስልሳ ብር) ገባ ብላችሁ ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ? ይህ ዋጋ ማለት አሁን ካለንበት የድህነት ሁኔታ አንጻርስ ለአንዲት ምስኪን የገጠር ሴት ምን ማለት እንደሆነ ይገባን ይሆን? አይመስለኝም። ምክንያቱም እኛ ይህንን ተላልፈን እኮ የቃላት መረጣ ላይ ደርሰናል። ለወንድ ሲሆን "አውሮፕላኑ መጣ" ለሴት ሲሆን ደግሞ "ባጃጇመጣች" ለምን ይባላል በማለት መድረኮቻችን ተጨናንቀዋል።

ሴቶችዬ "ቡና አለም " ተባለ "ቡናዋ አለች" ለገጠሪቷ ሴት የሞዲስ ዋጋን አይቀንስም። ይህ እንዳለ ሆኖ ይህንን ጉዳይ እንደ ችግር የሚያየው ምንያህሉ የሴቶች ክፍል ነው የሚለውን ቤት ይቁጠረው።

ሌላው ያስተዋልኩት ነገር መድረኮቻችን የአንድ ሰሞን ከመሆናቸውም በላይ ያተኮሩት ጉዳዮቹን መነካካት ላይ እንጂ ችግሮቹን በመፍታት ላይ አለመሆኑን ነው። ለሚደርስብን ጥቃት ዋናው ምክንያት ለድርጊቱ የሚጣለው ቅጣት አናሳነት ነው ብለን በችግርነት ለይተን ስናበቃ ይህንን በማስተካከል ከግብ ሳናደርስ "በጋብቻ ውስጥ የሚፈጸም ማስገደድ" በወንጀልነት ሊፈረጅ ይገባል የሚል አጀንዳ ደግሞ እናነሳለን። ሲጀምርስ መቼ ከጋብቻ ውጪ የተፈጸመብንን ማስገደድ ተከታትለን እና ጉዳዩን ተጋፍጠን እልባት ሰጠንና ነው ሌላ ያውም ከስንት አንድ ጊዜ የሚፈጸምን ጉዳይ አጀንዳ አድርገን የምንወያየው? ይገርመኛል በጣም። በእንደዚህ አይነት መድረኮች ለይ የምንሳተፍ ሴቶች እነማን ነን? በመድረኮቹ ላይ የምንሳተፈው የምር ጉዳዩ አሳሳቢ ሆኖ ነው? ወይስ አሳስቦን ነው? አይመስለኝም። ግባችን መድረኩን ማዘጋጀት ስለሆነ እንጂ። ግባችን በቦታው ተጋባዥ ሆኖ ተገኝቶ እርስ በእርሳችን "ስለለበስነው ብራንድ ልብስ እና ስለተቀባነው ብራንድ ሽቶ" መተማማት ስለሆነ እንጂ። በእርግጥ የህ ሁኔታ ሁሉም የመድረኩ ተሳታፊዎችን የሚገልጽ አይደለም። ዞሮ ዞሮ ግን መድረኮቻችን የሚዘጋጁበት አላማም ሆነ ግብ ያው በመሆኑ አሁንም ድረስ ስር ነቀል ለውጥ በሴቶች መብትም ሆነ አመለካከት ላይ አምጥተዋል ብዬ አላምን።

በመጨረሻም ይህ የግል ገጠመኜ ነው። ከአንድ አምስት አመት በፊት በከተማችን ካለ አንድ ትልቅ ሆቴል ውስጥ በአገራችን ካሉ የሴቶች መብት ተሟጋች ድርጅቶች መካከል አንዱ የሖነው አሁን በስም የማልጠቅሰው ተቋም ባዘጋጀው መድረክ ላይ ተጋባዥ ሆኜ ተገኝቼ ነበር። በተለምዶ ፊት ለፊት ያሉ ወንበሮች ለተናጋሪዎች እና ለልዩ እንግዶች የሚያዙ በመሆኑ የተቀመጥኩት ከኃላ በኩል ካሉ ወንበሮች መካከል በአንዱ ነበር። ከፊት ለፊቴ በሴቶች መብት ጋር በተገናኘ በሀገራችን ቴሌቪዢን ጣብያዎች በእየእለቱ የሚታዩ ሁለት ታዋቂ እንስቶች ተቀምጠዋል። እኔ እራሴ ሳድግ እንደነሱ እሆናለሁ ብዬ የማስባቸው አይነት ናቸው። እነዚህ ሁለት ሴቶች ግን ፊት ለፊት ወንበር ላይ ያልተቀመጡበት ምክንያት በወቅቱ ጥያቄ ፈጥሮብኝ ነበር። ይሁን እና ወድያው ለጥያቄ መልስ አገኘሁኝ።

የሆነው ምን መሰላችሁ ከትንሽ ደቂቃ ቦኃላ በእነዚህ ሁለት ሴቶቸ ደረጃ ያለች አንዲት ታወቂ ሴት ዘንጣ ማለት በሚቻል መልኩ ወደ ክፍሉ ገብታ በቀጥታ ፊት ለፊት ወዳሉት ወንበሮች በማምራት ተቀመጠች። እነዚህ ከኔ ፊት ተቀምጠው የነበሩ ሴቶች ያቺ ሴት ከፊት ለፊታቸው አልፋ እንደሄደች እርስ በእርሳቸው ማውራት ጀመሩ። ምን የተባባሉ ይመስላቹኃል? እንዴ ይህንን ሽቶ እና ቀሚስ ገዛችው እነዴ? ሊፒስቲኳን እነኳ ያኔ ለስብሰባ ፓሪስ በሄድን ጊዜ የገዛችው ነው የሚሉ ጉዳዮችን እያነሱ ያወራሉ። እኔ በጣም ደነገጥኩኝ። በፍጹም አልጠበኩም ነበር። ወድያው የመድረኩ አዘጋጅ ተነጋሪዋን የመክፈቻ ንግግር እንድታደርግ ጋበዘ። በጭብጨበ ወደ መድረኩ ወጣች። ከዛም ስለመድረኩ አስፈላጊነት ስለሴቶች መብት የመሳሰሉትን እየጠቃቀሰች ንግግር ስታደርግ ሴቶችዬ ምን ቢሉ ጥሩ ነው። እያሽሟጠጡ "አሁን ጉዳዩ የገባት እና የምታምንበት አትመስልም"።

ለኔ ይህ ጉዳይ ብዙ ነገር እንዳገናዝብ አድርጎኛል። ይኀውም ምንድነው አሁን ላሉት ችግሮቻችን መባባስ ካሉት ውጫዊ ምክንያቶች ባልተናነሰ መልኩ የኛም ጉድለት ሚና ያለው መሆኑን።

ይህ የግል ምልከታየ ነው። እንዳልኳችሁ ሁሉም ቸግር በጥናት የሚፈታ ነው። ቢሆንም ግን እከዝያው ድረስ ግን እኛ እራሳችን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የችግሮቹ አባባሾች ልንሆን አይገባንም ለማለት ነው። አመሰግናለሁ። በድጋሚ እንኳን ለአለማቀፉ ሴቶች ቀን አደረሰን አደረሳችሁ።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ስለ ወንጀል ተጎጂዎች - የአዲስ ዕይታ አስፈላጊነት በረቂቁ የወንጀል ሕግ የሥነ...
የግልግል ስምምነት /Arbitration Agreement/ እና የፍርድ ቤቶች ሥል...
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024