ስለ ዜግነት አዎጁ በፃፍኩት ጽሑፍ ላይ አቶ ግዛዉ ለገሰ የተባሉ የሕግ ባለሙያ የፃፉት ምላሽ ደርሶኝ ተመለከትኩት፡፡ (የአቶ ግዛው ለገሰ ጽሑፍን ለማግኘት ይህንን ይጫኑ፡፡ ) በመጀመሪያ ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ እንደመሆናቸውም ብሎም ጽሑፉን ያወጡት እሳቸው ስላልተስማሙበት የሕግ ጽሑፍ ምላሽ ለመስጠት እንደ መሆኑ አቶ ጀዋር መሐመድን ለመደገፍ አልፃፍኩትም ለማለት አቶ ጀዋር የራሱ ጉዳይ ብለው ጽሑፉን መጀመራቸው፤ በጽሑፉ ውስጥ ለተነሱ እያንዳንዱ ክርክሮች ተገቢውን የሕግ ክርክር ከማንሳት ይልቅ በአመዛኙ በተራ የአዋቃለሁ ባይነት ጉራ ተሞልተው እኩይ ሴራ የሚሉ ያልተገቡ ቃላቶች መጠቀማቸው ብሎም በጽሑፉ ውስጥ ለድምዳሜቸው ማስረጃ አድርገው ስላቀረቡት የሕግ ግምት (presumption of law) ምንነት ያሉት ነገር አለመኖሩ እና ሃሳባቸው ልክ ስለመሆኑ የሚደግፍ የሕግ አስተምሮ ሳይጠቅሱ በደፈናው የሕግ ግምት ያልገባው የሚል የወረደ ምላሽ መስጠታቸው ከሙያ ሥነ-ምግባር የወጣ ተራ ብሽሽቅ የመሰለ መውረድ ሆኖ አግንቼዋለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ የመጀመሪየው ጽሑፍ በግልፅ ዜግነትን መልሶ ስለማግኘት ላይ ብቻ አተኮሮ እንደተፃፈ በተገለፀበት ሁኔታ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ስለሌላቸው እንደ በሕግ ዜግነት ስለማግኘት የመሳሰሉ ለምላሹ ፋይዳ በሌላቸው ዝርዝሮች ላይ ማተኮራቸውም አስቀድመው ላልተስማሙበት ጽሑፍ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በቂ እድል ነፍጓቸዋል ጊዜያቸው አጥንቱን በመጋጥ ላይ መዋል ሲገባው መረቅ ለመጠጣት ውሏል፡፡
እንግዲህ ከዚህ ቀጥየ የአቶ ግዛው የክርክር ነጥቦችን በእኔ መረዳት በሕግ እና በክርክር መርሆች አይን ስሁት መሆናቸውን እንደሚከተለው አሰረዳለሁ፡፡ ትክክለኛው እና አሳማኙ ክርክር የማን ነው የሚለው መዳረሻ የአንባቢ እንጂ የጸሐፊዎች ባለመሆኑ እንደ አቶ ግዛው የኔ ሃሳብ የጉዳዩ ዳርቻ ነው የሚል ትዕቢት አይዳዳኝም፡፡ በጉዳዩ ላይ ስፅፍም የጉዳዩ ትኩረት ማግኘት ትኩረት ከመሳቡ ውጭ የተለየ አትኩሮት ለጉዳዩ እንደሌለኝ በቅንነት ስገልፅ ይህን ማመን ወይም መጠራጠር በእጃችሁ ነው፡፡
የአቶ ግዛው ጽሑፍ አልፋ እና ኦሜጋ በዜግነት አዋጁ ላይ የተጠቀሱት ሦስት ቅድመ ሁኔታዎች የሕግ ግምት በመሆናቸው ያለምንም የተለየ ሥርዓት ዜግነት ያሰጣሉ ቅድመ ሁኔታዎቹ አልተሟሉም ካለ ማስረጃ የማቅረብ ሃላፊነት (የማስረዳት ሸክም) የኮሚቴው ነው የሚል ነው፡፡