Font size: +
28 minutes reading time (5615 words)

የኢትዮጵያና የግብፅ ውጥረት በናይል ወንዝ፡ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ፀጋ የተከበበች ውብ ሀገር ብትሆንም በድህነት አዘቅት ውስጥ ተዘፍቃ የምትኖር፤ ባደጉ ሀገራት ተረፈ ምርትና የአየር ብክለት ገፈት ቀማሽነት፤ በሚጠጣ ንጹህ ውኃ እጥረት ተጠቂነት የምትነሳ ሀገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ በመአድን፣ በለም መሬት፣ በእንስሳት፣ በውኃ ኃብት እንዲሁም በሌሎች አላቂና አላቂ ያልሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች ባለፀጋ መሆኗን የሚካድ ባይሆንም በተፈጥሮ የታደለችውን ኃብት ጥቅም ላይ ከማዋል ረገድ ግን እምብዛም አይደለችም፡፡ ሜዳዋንና ተራሯን የሚሸፍን የተፈጥሮ ዝናብ እየተቀበለች ይህ ዝናብ አፈሯንና ወርቋን ጠራርጎ በመውሰድ ለጎረቤት ሀገራት ነፃ ስጦታና ችሮታ እንዲሆን ከመፍቀድ ውጪ የልማት መንገዱን አልተገለጠላትም፡፡ ወንዞች በደራሽ ውኃ ተጥለቅልቀው የገበሬ ማሳ የጎርፍ ሲሳይ ሲያደርጉ ማየት ክረምት በመጣ ቁጥር የምንገነዘበው መራራ እውነት ነው፡፡ አባይን የሚያክል ግዙፍ የውሀ ኃብት ከጉሮሮዋ እየፈለቀቁ የራሳቸው ከርሰ ምድር ሲሞሉ ኢትዮጵያ  የበይ ተመልካች ሆና መኖሯን ግርምት ይፈጥራል፡፡

ናይል የሚባለው የአለም ረዥሙ ወንዝ ላይ ያለው ውኃ 85%ቱ የኢትዮጵያ ነው፡፡ ይሁንና ከ50% በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ኑሮውን በኩራዝ መብራት ይመራል፡፡ ይህ ክስተት ወገብን ይቆርጣል፡፡ ”ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” እንዲሉ ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ 5% እንኳን አስተዋፅኦ ሳታደርግ በምስራቅም በምእራብም የዚሁ ወንዝ ብቸኛ አለቃ ነኝ በማለት በሌሎች የናይል ተፋሰስ ሀገራት ላይ የምትሰነዝረው ዛቻና ማስፈራርያ የሚያስገርም ነው፡፡ የናይል ወንዝ ብቸኛ ባለቤት እንደሆነች በመግለፅ አሁናዊ ተጠቃሚነቷን የሚነካ ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴ የደም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ እንደሆነች በተለያዩ አጋጣሚዎች ስትገልፅ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ የግብፅ ሽለላና ቀረርቶ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት በግዛታዊ ክልሏ ውስጥ በሚገኝ በጥቁር አባይ ላይ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ጀምራ ከ70% በላይ ማድረሷን ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል ይህ ግድብ ለግብፅ ራስ ምታት እንደሆነባት፤ኢትዮጵያ የያዘቸውን የልማት መንገድ ለማደናቀፍም ያልፈነቀለችው ድንጋይ እንደሌለ፤በቀጣይም የማትቆፍረው ጉድጓድ እንደማይኖር ኢትዮጵያውያን የምንገነዘበው እውነት ነው፡፡ የናይል ወንዝ በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል የፈጠረውን ውጥረት በተለያዩ ወቅቶች የውጭና የሀገር ውስጥ ሚድያዎች ርእሰ ዜና በመሆን የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ቀልብ መሳብ የቻለ፤አሁንም ውጥረቱ በስምምነት ያልተቋጨ ክስተት ሆኖ ቀጥሏል፡፡

ስለአባይ ግድብ እና ኢትዮጵያ በአንድ በኩል ስለግብጽ እና ተከታዮቿ ደግሞ በሌላ በኩል የሚዳስስ አጭር ጽሑፍ ለማቅረብ እየተንደረደርኩኝ ነው፡፡ በዚሁ አጭር ጽሑፍ በናይል ወንዝ ላይ የግብጽና የኢትዮጵያ አቋም ምን ይመስላል፤ከሕግ አንፃርስ እንዴት ይታያል፤በናይል ወንዝ ላይ በተፋሰስ ሀገራት መካከል ፍትሀዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት ይኖር ዘንድ ምን መደረግ አለበት የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አካትቷል፡፡

 

2) የናይል ወንዝ የማን ነው

ናይል የአለም ረዥሙ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ሆኖ 11 ተፋሰስ ሀገራትን የሚያቋርጥ  ነው፡፡ የወንዙ ላዕላይ ተፋሰስ ሀገራት የሚባሉት ኢትዮጵያ፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳና ኬንያ፤የመሀል ተፋሰስ ሀገራት ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ሩዋንዳና ብሩንዲ፤የታሕታይ ተፋሰስ ሀገራት ደግሞ ሱዳን እና ግብጽ ናቸው፡፡ የናይል ገባር ወንዞች ነጭ ናይል፣ ሰማያዊ ናይል(አባይ) እና አትባራ ወንዞች ናቸው፡፡ ነጭ አባይ ከታንዛንያ፣ ኡጋንዳና ኬንያ ድንበሮች አካባቢ ከሚገኘው ከቪክቶርያ ሀይቅ ተነስቶ ወደ ናይል ወንዝ የሚቀላቀል ሆኖ 15% አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ሰማያዊ ናይል(አባይ) ደግሞ ከጣና ሀይቅ የሚነሳና 70% አካባቢ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሲሆን አትባራ የተባለው ወንዝ ደግሞ በተከዘና በሰቲት ወንዝ ገባሪነት ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ ተነስቶ በሱዳን በኩል አድርጎ ናይልን የሚቀላቀልና 15% አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው፡፡ ሰማያዊ ናይል(ጥቁር አባይና አትባራ)ከኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ተነስተው ኴርቱምን አቋርጠው ግብፅ የሚገቡና 85% የናይል የውሀ ይዘት የሚሽፍኑ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ሰማያዊና ነጭ ናይል  በደቡባዊ የሱዳን ክፍል በሚገኘው ኳርቱም አካባቢ ይገናኙና ተያይዘው ወደ ግብፅ ሲና በረሀ በመክነፍ ሜዲትራንያን ባህርን ይቀላቀላሉ፡፡

 

3) ናይልና ጥቅሙን

የናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት ወንዙ የኢኮኖሚያዊ እድገት መሰረት እንደሆነ በማመን በዚሁ ተፈጥሮ ኃብት ተጠቃሚ ለመሆን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች ጀምረዋል፡፡ የናይል ወንዝ ለቀጠናው ሀገራት የእርሻና የመስኖ ማልሚያ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ የውኃ አቅርቦትና የአሳ ልማት፣ የቱሪዝም መስህብና የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን በመገንዘብ ሀገራቱ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብተዋል፡፡ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫን በዋነኛነት የመስኖ ስራዎችን ደግሞ በመጠኑ ለማስፋፋት ታላቁ የህዳሴ ግድብን በመገንባት ላይ ነች፡፡ ታንዛንያም ለሚጠጣ ንጹህ ውሀ አላማ በቪክቶርያ ሀይቅ ላይ የጀመረችው የልማት እንቅስቃሴ ተጠቃሽ ነው፡፡ በምድረ በዳ ላይ የምትኖረውና የናይል ወንዝ የደህንነት ጉዳይ አድርጋ የምትመለከተው ግብፅ እነዚህን የሌሎች ሀገራት እንቅስቃሴዎች በአይነ ቁራኛ ትመለከታቸዋለች፡፡ ይህ የግብጽ አቋም በአንድ በኩል፤የሌሎች ተፋሰስ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መብት ደግሞ በሌላ በኩል የፈጠረውን ውጥረት በቀጠናው ላይ ግጭት እንዳይወልድ የአካባቢው ማህበረሰብ ስጋት ሲሆን በተለይም ደግሞ በግብፅ መሪዎች በኩል የጦርነት ታምቡር ሲደለቅና የቀረርቶ ዘፈን ሲሰማ የነገሮችን አቅጣጫ ወዴት ያመሩ ይሆን የሚል ጥያቄ በእያንዳንዳችን አእምሮ መመላለሱ የማይቀር ነው፡፡

 

4) ኢትዮጵያ ለምን ከአባይ ርቃ ቆየች

የናይል ወንዝ የውኃ ይዘት 85%ቱ የኢትዮጵያ ኃብት መሆኑን ከፍ ሲል ተመልክተናል፡፡ ግብፅ ይህን ቁልቁል የሚፈስላትን ሄያጅ ወንዝ ሁለት እጆቿን ዘርግታ እየተቀበለች በሲናይ በረሃ ላይ  “የውኃ ባንክ” ክፍታ በማጠራቀም ከአለም ቀዳሚ የከርሰ ምድር ውኃ ሀብታም ለመሆን በቅታለች፡፡ ይሁንና ለናይል ወንዝ አንድ ብርጭቆ የሚሞላ የውሀ አስተዋጽኦ እንኳን አታደርግም፡፡ በተቃራኒው ኢትዮጵያ አንድ ብርጭቆ ውኃ እንኳን ቀድታ እንዳትጠጣ እድል ሳታገኝበት ግብፅ የአንበሳው ድርሻ በመውሰድ የናይል ወንዝ ብቸኛ ተጠቃሚ ሆና ቆይታለች፡፡ ይህ ለምን ሊሆን ቻለ?ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ ያላት የበላይነትስ ከምን የመነጨ ነው ለሚለው ጥያቄ የጀርባ ምክንያቶችን ስንመለከት፤

አንደኛ ኢትዮጵያ በሀይድሮሎጂና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሰለጠነ ባለሙያ አልነበራትም፡፡ በውኃ ሕግ እንደ ግብፅ በአግባቡ የተማረ፣ የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት ነበረባት፤አሁንም ቢሆን በአንፃራዊነት የተሻለ ሁኔታ መኖሩን የማይካድ ቢሆንም በሚያስፈልገው ደረጃ ይህ ችግር ተቀርፏል ማለት አያስደፍርም፡፡ ምናልባትም ጥቂት ሙህራን ቢኖርም በውሀ ጉዳይ ላይ ጽሑፍ ማቅረብ፣ መፈላሰፍና ምርምር ማድረግ ፍላጎት ያላቸው አይደለም፡፡ በአባይ ወንዝ ላይ ቁጭ ብለን ግጥምና ዜማ እየደረስን ከመዝፈን ውጪ አንድም ስራ መስራት ሳንችል ለዘመናት ዘልቀናል፡፡ የውሀ ፖለቲከኞቻችና እና የሕግ ምሁሮቻችን ከዘፋኞቻችን የተሻለ ስራ አልሰሩም፤ያለፉት መንግስታትም እንዲሁ፡፡ በአባይ ጉዳይ ላይ ከተሰጠው የሕግ እና/ወይም የፖለቲካ ትንታኔዎች በላይ በአማርኛ የተዘፈኑ ዘፈኖች በአንጻራዊነት ብዙ ናቸው፡፡ በመሰረቱ የኛ የሕግ ፍልስፍና ያላደገ፣ በቋንቋችን እንኳን የፈለግነውን የሕግ ትንታኔ የማናገኝበት ነው፡፡ በውሀ ሕግ ላይ ሲሆን ደግሞ ችግሩ የባሰ ነው፡፡ ግብፆች በተቃራኒው ከውኃ ጋር ተያይዞ ያላቸው የሕግና የፖለቲካ እውቀት “አፍ መፍቻ ቋንቋቸው” ነው ማለት ይቻላል፡፡ በናይል ወንዝ ላይ የሚከናወነው ስምምነትና ውል ተራ ከሆነውን የእንግሊዘኛ ቃላት አመራረጥ ጀምረው እስከ የውሉ አቀራረፅና ይዘት በብልጫና በድል መቺነት የበላይነታቸውን እንዲያረጋግጡ በጥንቃቄና በተቆጣጣሪነት መንፈስ መንቀሳቀስ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማእቀፍ ስምምነት ያልፈረመችበትና ያላፀደቀችበት ምክንያት ማየት በቂ ይመስለኛል፡፡ በአጠቃላይ ከውሀና  ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ያላቸው እውቀት ከኢትዮጵያውያን ጋር የሚወዳደር አይደለም፡፡ በግብፅ ሕግ ያላጠና ተራ ዜጋውም አለም አቀፍ የውሀ ሕግ ሲተነትንና የምርምር ጽሁፍ ሲያቀርብ፤በአንፃሩ በኢትዮጵያ ተራ ዜጋው ይቅርና ሕግ ያጠና ምሁርም የሚጠበቅበት ዜግነታዊ ግዴታውን ሲወጣ አይስተዋልም፡፡ ስለሆነም ስነልቦናዊ የእውቀት ውግያው ግብጽ በናይል ወንዝ ላይ ያላትን የበላይነት ማስቀጥያ መንገድ አድርጋ ታየዋለች፡፡

ሁለተኛው በኢትዮጵያ የተረጋጋ የኢኮኖሚ እድገትና የፖለቲካ አስተዳደር አለመኖር ነው፡፡ ከኢኮኖሚ አንጻር ስናየው ኢትዮጵያ ዜጎቿን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ስለሆነ ይህ አስከፊ የሆነ የዜጎች የድህነት ኑሮ ለማስወገድ በተለይም የዜጎች ከእጅ ወደ አፍ የሆነ አሰልቺ ኑሮን ለማላቀቅ በትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ሳይሆን በጥቃቅንና አነስተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ተጠምዳ እንድትኖር አስገድዷታል፡፡ በሌላ አነጋገር የአባይ ወንዝ የሚያክል ትልቅ ሀገራዊ የተፈጥሮ ኃብት ለማልማት የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ አቅም አልገነባችም፡፡ በዚሁ ምክንያትም በእቅፏ የያዘችው ትልቅ የድህነት ማስወገጃ ኃብት አይን አይኑን ከመመልከት ውጪ ሌላ አማራጭ ሳትወስድ ለዘመናት ዘልቃለች፡፡ በፖለቲካ ረገድ ስናየውም የውጭ መዋእለ ንዋይ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀስበት ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር አልነበረም፤ኢትዮጵያውያን የውጪ ጠላት ተባብረው ከማንበርከክ ረገድ ለአለም አርአያ ቢሆኑም በውስጥ ጉዳያቸው ላይ ግን እርስበእርሳቸው ተዋድደውና ተፋቅረው ከነበሩበት ዘመን በላይ እርስበእርሳቸው በጥርጣሬና በአይነቁራኛ እየተያዩ የእርስበእርስ ጦርነትና ውግያ ላይ ያሳለፉትን ዘመን ይበልጣል፡፡ ይህ ሁኔታ ለግብጽ የሚያስደስታት ብቻ ሳይሆን ሁለት እጆቿ በመዘርጋት ድጋፍ የምትሰጥበት ሁኔታ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ “መሸጥ የለመደ እናትን ያስማማል” እንዲሉ ተራና ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ የሀገራቸውን የሉአላዊነት ክብር አሳልፈው ለመስጠት ከግብጽ ጋር እየተደራደሩ ትልቁ የአባይ ግድብ በግብፅ ፓውንድ እየለወጡ ለስብእናቸውና ለሀገራዊ ክብራቸው ሳይሆን ለሆዳቸውና ለስልጣናቸው ያደሩ የሀገር ውስጥ አማጽያን ቡድኖች እንደነበሩም ታሪክ መዝግቦት ያለፈ ነጭ እውነት በመሆኑ እኛም እነሱንም የሚክዱት አይሆንም፡፡ ይህ ኢትዮጵያ በጀመረችውን ልማት ወደ ኃላ እንዲጎተት በማድረግ ለግብጽ ትልቅ የድል ሜዳ በመሆን ሲያገለግላት ቆይቷል፤አሁንም ከዚሁ አደገኛ ተግባር ነጻ ስለመሆናችን በእጅጉ እጠረጥራለሁኝ፡፡

ሶስተኛ ግብጽ በቀጠናው ላይ ከፍተኛ ወታደራዊ የበላይነትና የተሻለ አለምአቀፋዊ የዲፕሎማሲ ተፅእኖ የመፍጠር አቅምን የሚመለከት ነው፡፡ ይህ ወታደራዊ የበላይነትና አለምአቀፍ ፖለቲካዊ ተሰሚነት በናይል ተፋሰስ ሀገራት ላይ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ተጽእኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው፡፡ ግብፅ በአረብ ሀገራት የአለቃነት ማእርግ ተሰጥቷት ይህን አለቃነቷን በምእራባውያን ሀገራት ላይም የጠነከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲኖራት አስችሏታል፡፡ ምእራባውያን ሀገራትም ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች የናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት ይልቅ በግብፅ ላይ የተሻለ ጂኦ-ፖለቲካዊ ጥቅም አላቸው፡፡ በቅኝ ገዢዎች ሲደረጉ የነበሩ የግብፅ ጥቅም-መር ስምምነቶች እንደተጠበቁ ሆኖው በቅርቡ በትልቁ የህዳሴ ግድብ አስመልክተው ግብፅና ኢትዮጵያ የከፈቱትን “የስምምነት መድረክ አዳራሽ”ውስጥ እነ አሜሪካም በታዛቢነት ገብተዋል የሚል ዜናዎች መስመታችን ተከትሎ፤በኃላም አሜሪካ ታዛቢ ብቻ ሳልሆን የውሉ አርቃቂና ቀንደኛ አደራዳሪ ነኝ በማለት የኢትዮጵያ መብትን የሚገድብ አቋም በመያዝ ለግብፅ ያሳየችው ግልፅ የሆነ ውግንናን መመልከት በቂ ማስረጃ  ይመስለኛል፡፡ በዚሁ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት በቀጣይም በውጭ ሀገራት ተፅእኖ ስር እንዳይወድቅ በመርህ ላይ የተመሰረተና ሚዛኑን የጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ማጎልበት ይጠበቅበታል፡፡ ምናልባትም አላስፈላጊ ጣልቃገብነትንና እጅ ጥምዘዛን ሊደቀንበት የሚችል ፈታኝ ጊዜ ቢገጥመው እንኳን ራሱንና የሀገሩን ብሄራዊ ጥቅምን በማስቀደም በህዝቡና በልአላዊ ግዛቱን የሚፈፀምበት የቅኝ ገዢዎች አእምሮአዊና ቁሳዊ ወረራን ለመከላከል በሚችልበት ፖለቲካዊ ቁመናና አቅም ላይ ሆኖ መዘጋጀት ይኖርበታል የሚል የእግረ መንገዴን ምክረ ሀሳቤ ነው፡፡ ግብፅ በአለም አቀፍ ደረጃ የነበራትና ያላትን ተሰሚነትን እንደ መልካም አጋጣሚና እድል በመውሰድ የምእራባውያንና የአረብ ሀገራት ከጎኗ እንዲሰለፉ ከማድረጓ በላይ በአለም አቀፍ ተቋማት ላይ ለኢትዮጵያ ብድርና እርዳታ እንዳይሰጡ እንደ መሰናከል ሆና መቆየቷ እንረዳለን፡፡ እነ አለም ባንክና አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም ይቅርና እዚሁ በአፍሪካ የሚገኘው የአፍሪካ ልማት ባንክ እንኳን ብድር ከልክሎናል፡፡

ይሁንና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ መለስ ዜናዊ ግዙፉ የአባይ ሀይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ በመጋቢት 24 ቀን 2004 አ.ም በይፋ እንዲጀመር ያደረጉ ሲሆን ግንባታው ከ70% በላይ መጠናቀቁና በሚቀጥለው ክረምት የውሀ ሙሌት ስራ እንደሚጀምር በመንግስት ሚዲያዎች ይነጋራል፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፤ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በኢትዮጵያውያን አቅም የሚገነባ በመሆኑ ከዜጎች የኑሮ መጎሳቆል ጋር ተደማምሮ የሚፈጥረው ጊዚያዊ የገንዘብ እጥረት የሚናቅ ባይሆንም በመጨረሻ ግን ግድቡ ወደ መገባደዱ እየደረሰ መሆኑ ሲታይ እጅጉን የሚያስደስት ነው፡፡ አቶ መለስ “በአባይ ጉዳይ ቤይጂንግ ወይም ዋሽንግተን ሄደን ይግባኝ የምንልበት ጉዳይ ሳይሆን በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ቤት እየገባን ይግባኝ የምንልበት ነው” ማለታቸውን የሚታወስ ሲሆን የዚህ ንግግር መሰረታዊ ይዘት በሁለት መልኩ ማየት ይቻላል፡፡ አንደኛው በአባይ ዙርያ ለምናከናውነው ማንኛውም አይነት የልማት እንቅስቃሴ ከማንም የውጭ ሀይል ብድርና እርዳታ ሳንጠይቅ በህዝባችን አቅም እናከናውናለን ማለት ሲሆን ሁለተኛው መልእክቱ ደግሞ የሀገራችን ኃብት የሆነውን የአባይ ወንዝ ላይ ያሻንን ለማድረግ ማንንም የውጭ ሃይል ማማከር ሆነ መጠየቅ አያስፈልገንም፡፡ በአባይ ወንዝ ላይ ፈቃጅና ከልካይ ነኝ ለሚል የውጭ ሃይል የምንሰግድበት አንድም ምክንያት የለም ማለታቸው ነበር፡፡

 

5) የግብፅ አቋምና አለም አቀፍ የሕግ ተቀባይነቱ፡-

5.1) በናይል ላይ የተፈፀሙ ስምምነቶች   

በናይል ዙርያ ላይ የተከናወኑ ውሎችና ስምምነቶች በዋነኛነት በቅኝ ገዢዎች የተከናወኑ ሲሆን ግብጽን ማእከል ያደረጉና ሌሎች ተፋሰስ ሀገራትን የሚያገሉ ብሎም ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ የናይል ወንዝ የቅኝ ገዢዎች ቀልብና ፍላጎት መሳብ የጀመረው ከ19ኛ መክዘ ጀምሮ ነው፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ እንግሊዝ የናይል ወንዝን አጠቃቀምና አጠባበቅን በማስመልከት ስምንት ስምምነቶችን ተፈራርማለች፡፡ እንግሊዝ ለምን ይህን ያህል ስምምነት በናይል ወንዝ ላይ መዋዋል አስፈለጋት የሚለውን ጥያቄ ስናይ እንግሊዝ የግብፅ ቅኝ ገዥ ስለነበረች በአንድም በሌላ መንገድም የራሷን ጥቅም እያሰከበረች ነበር፡፡ ሌሎች የቅኝ ገዥ ሀገራትም በናይል ወንዝ ዙርያ ሲያከናውኑዋቸው የነበሩት ስምምነቶች የራሳቸውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና የእነዚህ ስምምነቶች ትሩፋቶች የግብፅ ብሄራዊ ጥቅም ብቻ የሚያስከብሩና የሌሎች ተፋሰስ ሀገራት ጥቅም ታሳቢ ያላደረጉ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ከ1891 እስከ 1959 ድረስ በናይል ወንዝና ገባሪዎቹ ላይ የተከናወኑ ስምምነቶች እንደሚከተለው እንያቸው፡፡

 

የ1891 የጣልያንና የእንግሊዝ ስምምነት     

ይህ ስምምነት የግብፅን ጥቅም ላለመንካት ሲባል ጣልያን በአትባራ ወይም ተከዜ ወንዝ ላይ ግድብ እንደማትሰራ ከእንግሊዝ ጋር የተዋዋለችበት ነው፡፡ በውሉ አንቀፅ 3 ላይ እንደሰፈረው ጣልያን የናይል ገባር ወንዝ የሆነውና ከአዲስቷ የቅኝ ተገዥ ኤርትራ ግዛት ላይ የሚነሳውን አትባራ ወንዝ ላይ የመስኖ ወይም የውኃውን ፍሰት የሚቀንስ ማንኛውም አይነት ስራ እንደማትሰራ ከእንግሊዝ ጋር ውል ማድረጓን ያሳያል፡፡ ጣልያን ከሃፀይ ዮውሀንስ መስዋእትነት በኃላ እ.ኤ.አ. ከ1890-1941 የኤርትራ ቅኝ ገዥ እንደነበረች የሚታወስ ሲሆን ይህ ውል ፍፁም ኢ-ፍትሀዊና በምን አገባኝ ስሜት የተፈፀመ መሆኑን መገመት የሚከብድ አይደለም፡፡

 

የ1901 የእንግሊዝና የጣልያን ስምምነት

ይህ ስምምነት ከደቡባዊ አስመራ ተነስቶ አትባራ ወንዝን የሚገብርና በመጨረሻም ወደ ናይል የሚቀላቀል ጋሽ/መረብ  ወንዝን በማስመልከት በእንግሊዝና በጣልያን መካከል የተከናወነ ሲሆን ይዘቱም ኤርትራ በመልካም የጉርብትና መርህ ላይ ተመስርታ በወንዙ ላይ የመጠቀም መብት እንዳላት እውቅና የሚሰጥ በመሆኑ ከሌሎች የቅኝ ገዢዎች ስምምነቶች በተሻለ ሁኔታ ፍትሀዊና የአሁኗ ኤርትራን መብት የማይጎዳ ነው ይባላል፡፡

 

የ1902 የእንግሊዝና የኢትዮጵያ ስምምነት

ይህ ስምምነት ግንቦት 15 ቀን 1902 እ.ኤ.አ የሱዳን ቅኝ ገዥ በነበረችው በእንግሊዝ እና በኢትዮጵያ መካከል የተከናወነ የአዲስ አበባ የድንበር ስምምነት ነበር፡፡ ይሁንና በዚሁ ስምምነት አንቀጽ 3 ላይ መነሻቸው ከኢትዮጵያ ያደረጉ የናይል ገባሪ ወንዞችን የሚመለከት የውኃ ስምምነት ይዘትም ተካትቶበታል፡፡ በስምምነቱ መሰረት ንጉስ ሚኒሊክ በግዛቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የእንግሊዝና የሱዳን መንግስታት ፈቃድ ሳያገኝ የአባይን ወንዝ ፍሰትን ማስቆም የሚችል ማንኛውም አይነት ስራ እንዲሰራ የማይፈቅድ መሆኑን የተስማማበት ውል ነበር፡፡ ይህ ውል የኢትዮጵያ መንግስት ሳይገደድና በራሱ ፍላጎት ስምምነቱን የፈረመበት በመሆኑ ኢትዮጵያ የምትገደድበት ውል ነው የሚል በግብፅ በኩል ክርክር ይነሳል፡፡

የስምምነቱ አንቀፅ 3 የእንግሊዝኛና የአማርኛ ቅጂዎች በተከታታይ እንደሚከተለው እንያቸው፡፡

“His Majesty the Emperor Menelik II, King of kings of Ethiopia, engages himself towards the Government of His Britannic Majesty not to construct or allow to be constructed, any works across the Blue Nile, Lake Tana or the Sobat, which would arrest the flow of their waters into the Nile except in agreement with his Britannic Majesty’s Government and the Government of the Sudan”.

ጃንሆይ ዳግማዊ ምንይልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ከጥቁር አባይና ከባህረ ፃና ከሰባት ወንዝ ወደ ነጭ ዐባይ የሚወርደውን ውሀ ከእንግሊዝ ጋር አስቀድመው ሳያስማሙ ወንዝ ተዳር እዳር የሚደፍን ስራ እንዳይሰሩ ወይም ወንዝ የሚደፍን ስራ ለመስራት ለማንም ፈቃድ እንዳይሰጡ በዚህ ውል አድርገዋል፡፡

ይህ ውል የኢትዮጵያ ሉአላዊነትን የሚነካ አወዛጋቢ ይዘት ያለው ቢመስልም አሁንም ግን ህጋዊነቱን ውድቅ ለማድረግ የሚጠቅሙ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑንም በብዙ የውሀ ሕግ ልሂቃኖች የሚታመንበት ነው፡፡ ለምሳሌ አንደኛ ውሉ በእንግሊዝም ሆነ በኢትዮጵያ አልፀደቀም ወይም Ratify አልተደረገም፡፡ ይሁንና ከዚህ ጋር ተያይዞ በወቅቱ የሁለትዮሽ ሆነ የባለብዙ ወገን ስምምነቶችን ማጽደቅ የሚችል የተለየ ተቋም ባልነበረበት ሁኔታ ስለ ውሎችን መፈረም እንጂ ስለማፅደቅ የሕግ ክርክር ሆኖ መነሳት የለበትም የሚል የመልሶ ማጥቃት ክርክርም ይነሳል፤ምክንያቱም እንደአሁኑ ዘመን የስልጣን ክፍፍል የሚደግፍ ህጋዊ መርህ ባልነበረበት በተለይም ደግሞ ሕግ አውጪ፣ ሕግ አጽዳቂና ሕግ ትርጓሚ ራሱ ንጉሱ በሆነበት ሁኔታ የሁለትዮሽ ስምምነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካልፀደቀ ተቀባይነት የለውም የሚለውን ክርክር ውሀ የሚያነሳ አይደለም በማለት ይከራከራሉ፡፡ ሁለተኛ በእንግሊዘኛውና በአማርኛው መካከል የቃላት አለመጣጣምና የትርጉም መጣረስ አለበት፤በአማርኛው ቅጂ የኢትዮጵያ መንግስት የማሳወቅ ግዴታ የገባው እንግሊዝን ብቻ ሲሆን በእንግሊዘኛው ቅጂ ላይ ግን ሱዳንም ተጨምራለች፡፡ ይህ የአማርኛ ቅጂ የኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎት መገለጫ ነው ተብሎ የሚታሰበው እንግሊዝ ሱዳንን ትታ እስክትሄድ ድረስ የሚቆይ ጊዚያዊ ግዴታ መግባቱን ነው፤ለዚሁ ማሳያም በውሉ አንቀፅ 4 ላይ “ለቅቆ እስኪሄዱ” የሚል የአማርኛ ቃልና “Removed” የሚል የእንግሊዘኛ ቃል እናገኛለን፡፡ በሌላ በኩል ውኃውን Arrest ወይም Block ማድረግን ወይም ሙሉ በሙሉ ማስቆምን እንጂ ማንኛውም አይነት ተጠቃሚነትን የሚከለክል ውል አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ የውሉ የአማርኛ ቅጂ ከእንግሊዘኛው በተሻለ ሁኔታ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብር ቢሆንም የውሉ የእንግሊዘኛው ቅጂም ኢትዮጵያ ወንዟን ከመጠቀም የማይከለክላትና እንግሊዝ ሱዳንን ለቃ ከሄደች በኃላም የውሉ ተፈፃሚነትን የሚያበቃ በመሆኑ ኢትዮጵያ በአሁን ጊዜ ይህን ውል የምትቀበልበት የሕግ ምክንያት የለም፡፡ ግብፅም የውሉ 3ኛ ወገን እንጂ ፈራሚ ባለመሆኗ ይህን ውል በማንሳት መከራከር አትችልም፡፡

 

የ1906 የበልጂየም እና የእንግሊዝ ስምምነት

ይህ ስምምነት ግንቦት 09 ቀን 1906  እ.ኤ.አ በበልጂየም(ኮንጎን በመወከል) እና በእንግሊዝ መካከል  የተከናወነ ሆኖ በዚሁ ስምምነት በአንቀፅ 3 ላይ በግልፅ እንደተመለከተው የኮንጎ መንግስት ከሰምሊኪ ወይም ከልሳንጎ ወንዝ ወደ አልበርት ሀይቅ የሚወርደውን ውሀ ከሱዳን መንግስት ጋር አስቀድሞ ሳይስማማ የውሀውን ይዘት የሚቀንስ ስራ እንዳይሰራ ወይም ውሀውን የሚቀንስ ስራ ለመስራት ለማንም ፈቃድ እንዳይሰጥ በዚህ ውል አድርገዋል የሚል ነበር፡፡ ይህ ስምምነት የኮንጎ ህዝብ ከናይል ወንዝ ላይ የመጠቀም መብቱን የሚከለክል፤የሀገሪቱ ብሄራዊ ጥቅምን የሚጎዳ በበልጅየም ፍላጎት ብቻ የተፈረመ ሲሆን የታችኞች ተፋሰስ ሀገራትን ብቻ የሚጠቅም ኢ-ፍትሀዊ ስምምነት በመሆኑ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡

 

የ1906 የእንግሊዝ፣ የጣልያንና የፈረንሳይ ስምምነት

ይህ ስምምነት በእንግሊዝ፣ ጣልያንና ፈረንሳይ መካከል በሎንደን የተከናወነ የሶስትዮሽ ስምምነት(Tripartite Agreement) ሲሆን በዚሁ ስምምነት አንቀፅ 4(a)ላይ እንደተመለከተው ፍፁም ግዛታዊ አንድነት ላይ በመመስረት የኢትዮጵያ መብትን ገታ በማድረግ በአንድ በኩል፤ጣልያን በሶማሊያና በኤርትራ ላይ ያላትን የቆየ ጥቅምን በማስጠበቅ በሌላ በኩል፤የእንግሊዝና የግብጽ ጥቅም በናይል ወንዝ ለማረጋገጥ ሶስቱም ሀገራት የተስማሙበት ነው፡፡ ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ በልአላዊ ግዛቷ ላይ በሚገኝ የውሀ ኃብት እንዳትጠቀም ሙሉ ለሙሉ ያገለላት በመሆኑ በውሀዋ ላይ እንድትገለገል ሊያሰቆማት የሚችል የውጭ ሃይል እንደሌለና ስምምነቱንም በኢትዮጵያ ተቀባይነት እንደማይኖረው በግልፅ ለሀገራቱ አሳውቃለች፡፡  

 

የ1925 የእንግሊዝና የጣልያን ስምምነት

በ1919 እ.ኤ.አ እንግሊዝ በጣና ሀይቅ ላይ ግድብ እንድትሰራ የኢትዮጵያ ይሁንታ እንድታገኝ ጣልያን ድጋፏን የምትሰጥ መሆኗን የሚገልፅ የስምምነት ማእቀፍ በእንግሊዝና በጣልያን መካከል ተከናወነ፡፡ ይህን ስምምነትን ተከትሎ በ1925 እ.ኤ.አ.ግብፅና ሱዳን በነጭና ሰማያዊ ናይል (ጥቁር አባይ) እንዲሁም በሌሎች የናይል ገባሪ ወንዞች ላይ የውሀ ስራዎችን ለመስራት ቅድሚያ መብት እንዳላቸውና ሌሎች ሀገራት የወንዙን የውሀ ይዘት የሚቀንስ ማንኛውም አይነት ስራ እንደማይሰሩ በመግለፅ ጣልያንና እንግሊዝ የማስታወሻ ልውውጥ አደረጉ፡፡ ይህ የደብዳቤ ልውውጥን ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው ተቋውሟን ገልፃለች፤ቅሬታዋን በወቅቱ ለነበረው የአለም መንግስታት ድርጅት (League of Nations) አስታውቃለች፡፡

 

የ1929 የእንግሊዝ እና የግብፅ ስምምነት

ይህ ስምምነት ሱዳንን እና ሌሎች በእንግሊዝ ስር የነበሩ ቅኝ ተገዢዎችን(ኡጋንዳ፣ ኬንያና ታንዛንያን)በመወከል በእንግሊዝ እና በግብፅ መካከል የተከናወነ ሆኖ የናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራትን ሊጎናፀፉት የሚገባቸውን ተፈጥሮአዊና ፍትሀዊ የውኃ ኃብት ተጠቃሚነትን እውቅና የማይሰጥ ፍፁም የሁለትዮሽ ስምምነት ነበር፡፡ ይህ ስምምነት ሱዳንን የተወሰነ ድርሻ ብቻ እንዲሰጣት በማድረግ ግብጽና እንግሊዝ ብቻቸውን የናይል ወንዝ ተጠቃሚ እንደሆኑ በተለይም ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ በብቸኝነት የመወሰንና ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን(Veto Power)እንደላትና ይህ መብትም ካለምንም ጣልቃ ገብነት የሚቀጥል መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የግብፅ ፈቃድ ሳይታከልበት በናይልን ሆነ ናይልን በሚገብሩ ወንዞች ላይ ምንም አይነት የመስኖ ሆነ የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት ለመስጠት የሚችል ግንባታ በሌሎች ተፋሰስ ሀገራት መከናወን እንደሌለበት ማእቀብ የሚጥል ነበር፡፡

 

የ1952 የእንግሊዝና የግብፅ ስምምነት(The Owen Falls Agreement)

የኡጋንዳ ቅኝ ገዥ በነበረችው በእንግሊዝና በግብፅ መካከል የተከናወነ ሆኖ የስምምነቱ ይዘትም በአንድ በኩል ኡጋንዳ ለኤሌክትሪክ ሃይል አመንጪነት የሚውል ግድብ ለመገንባት የሚያስችል ህጋዊ መእቀፍ ለማግኘት፤በሌላ በኩል ደግሞ ግብፅ በናይል ላይ የነበራትን የተቆጣጣሪነትና የአለቃነት ስልጣን አስጠብቆ ለማስቀጠል በማለም የተፈፀመ ነበር፡፡ ይኸውም ግብፅ ካልፈቀደች ምንም አይነት ስራ መስራት እንደማይቻል እውቅና ለመስጠት በማሰብ የተከናወነ ይመስላል፡፡

 

የ1959 የግብጽና የሱዳን ስምምነት

ይህ ስምምነት በዩናይትድ አራብ ሪፓብሊክ ግብጽና በሱዳን ሪፓብሊክ መካከል የተከናወነ ሲሆን የ1929 ስምምነት ተቀጥያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ከፍተኛው የናይል ውኃ የግብጽ እንደሆነ እውቅና የሚሰጥ ስምምነት ነበር፡፡ በዚሁ ስምምነት አንቀጽ 4 ላይ በግልጽ እንደተመለከተው 55.5 ቢሊዮን ኩቢክ ሜትር ለግብጽ፣ 18.5 ቢሊዮን ኩቢክ ሜትር ለሱዳን በመስጠት ቀሪው 10 ቢሊዮን ኩቢክ ሜትር ደግሞ የአከባቢው የኢኮሎጂካዊ ሚዛን ለመጠበቅ ወደ ሰሃራ ምድረ በዳ እንዲተን በመስማማት ኢትዮጵያ በብርጭቆ እንኳን ውኃ የምትቀዳበት መብት ያላገኘችበት አስገራሚ ውል ነበር፡፡ ይህ ስምምነት ሌሎች ተፋሰስ ሀገራትን ያገለለና ፍፁም የሁለትዮሽ ውል ስለነበር በኢትዮጵያ ተቀባይነት እንደሌለው ተደጋግሞ ተገልጿል፡፡

 

5.2) ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ መብቶች

ግብጽ የናይል ወንዝን ከአምስት ሺህ በላይ አመታት በቀደምትነት ስትጠቀምበት እንደቆየች የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡ ኑሮዋን፣ ድህንነቷን፣ ጉሮሯንና የህዝቧ ህልውና መሰረት ያደረገው በናይል ወንዝ ላይ ነው፡፡ ሄሮዶቱስ የተባለ ግሪካዊ የጥንት ፀሃፊ ግብፅ የናይል ስጦታ ነች ብሎ ነበር፤ግብፅም ይህን ትለዋለች፡፡ ይህ ማለት ግን ናይል የግብፅ “የግል ስጦታ” ነው ማለት ባለመሆኑ ናይል የአስራ አንድ ተፋሰስ ሀገራት “የጋራ ስጦታ” መሆኑን ማመን ያስፈልጋል፡፡ በ1855 ዓ.ም አካባቢ ኢስማኤል ፖሻ  የተባለው የግብጽ ገዢም ‘ግብጽ አባይ ናት፣ አባይም ግብጽ ናት’ በሚል እሳቤ በአባይ ሸለቆና በቀይ ባህር አቅጣጫ የግብፅን ግዛት ለማስፋፋት ቢያቅድም በኢትዮጵያውያን ጎራዴ መክሸፉን በታሪክ ተመዝግቧል፡፡

በሌላ በኩል ግብፅ በመጀመርያዎች 20ኛ መክዘ አከባቢ በናይል ወንዝ ላይ ከፍተኛ የእርሻ ስራዎች ማከናወን የጀመረችበት ጊዜ ስለነበር “በቀደምትነት የመጠቀም” ህጋዊና ታሪካዊ መብቷን የሚያጠናክሩ የተለያዩ ስምምነቶችን ማደራጀት የጀመረችበት ነበር፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች በግብፅ ላይ ጂኦ-ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት እያሳደጉ የመጡ የምእራባውያን ሀገራትም ትኩረታቸውን በናይል ላይ ማድረግ ጀመሩና በአንድም በሌላ መንገድም ግብፅ የሚጠቅሙና ሌሎች ተፋሰስ ሀገራትን የሚጎዱ የተለያዩ ስምምነቶችን ፈፀሙ፡፡ ግብጽም እነዚህን ስምምነቶችና ተራ የሆነ የንብረት ሕግ መሰረት በማድረግ ናይልን ቀድሜ የያዝኩትና ከጥንት ጀምሮ ስጠቀምበት ስለነበር አስቀድሜ ከያዝኩት ኮታ ከተነካብኝ ወዮላችሁ ማለት ጀመረች፡፡ የግብፅ አቋም ፍጹማዊ የግዛት አንድነት ከሚል ኃልዮት ጋር የሚያያዝ ሲሆን በዚሁ መሰረትም የራስጌ ሀገራት የግብፅ የውሀ ድህንነትና በቀደምትነት የመጠቀም መብትን በሚነካ መልኩ የናይል ወንዝን ሊጠቀሙበት አይችሉም የሚል “አልቦ ድምር ጨዋታን”(Zero-Sum Game)ታቀነቅናለች፡፡ የቅኝ ገዢዎች ስምምነቶችንም እየመዘዘች እንደመከራከርያ ዱላ ትጠቀምባቸዋለች፡፡

 

5.3) ጉልህ ጉዳትን ያለማድረስ ግዴታ (No Significant Harm Principle)

በመሰረቱ ድንበር ተሻጋሪ በሆኑ ወንዞች ላይ ሁለት መሰረታዊ መርሆዎች እያደጉና የአለም አቀፍ ልማዳዊ ሕግ መገለጫ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ በአንድ በኩል ፍትሀዊና ምክንያታዊ የመጠቀም መብት በሌላ በኩል ደግሞ መሰረታዊ ጉዳት ያለማድረስ ግዴታ ናቸው፡፡ እነዚህ  መርሆዎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለመጓጓዣነት የማያገለግሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ለማስተዳደር ባወጣው አለምአቀፍ ስምምነት(1997) በአንቀጽ 5 እና 7 ላይ እንደቅደም ተከተላቸው ተደንግገዋል፡፡ ዝቅ ብለን እንደምናየው እነዚህ መርሆዎች የአለምአቀፍ ልማዳዊ ሕግ መገለጫ(Declaratory of International Customary Law) ተብለው የሚወሰዱ መሆናቸውን ልብ ይበሉ፡፡ ግብፅ የናይል ወንዝ የታችኛው ተፋሰስ ሀገር እንደመሆኗ መጠን ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ ግዴታ የሚለው መርህን እያነሳች ትከራከራለች፡፡ ሆኖም ግብፅ የናይል ወንዝን ኢ-ምክንያታዊ በሆነ መንገድና ከሚገባት በላይ ጥቅም ላይ በማዋል በራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉልህ ጉዳት እያደረሰች ነው፤የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ሚዛናዊና ምክንያታዊ የተጠቃሚነት መብታቸውን አግታለች በማለት ኢትዮጵያም መከራከር ትችላለች፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን በኮንቬንሽኑ አንቀጽ 10(2) ላይ እንደተደነገገው ማንኛውም አይነት የውሀ አጠቃቀም በአንድ በኩል ፍትሃዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነትን ተግባራዊ በማድረግ በሌላ በኩል ደግሞ በሌሎች ተፋሰስ ሀገራት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ መሆን አለበት፡፡

ወደ ቀደመ ነገሬን ስመለስ በአለም አቀፍ የውኃ መሄጃ ስምምነት(International Watercourse Convention)አንቀጽ 7 ላይ እንደሰፈረው ማንኛውም ሀገር በግዛቷ ላይ የሚገኘውን ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ የታችኞች ተፋሰስ ሀገራትን ጥቅምና ህልውና አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ መጠቀም አትችልም፡፡ ይህ ማለት ኢትዮጵያ ምንም እንኳን የአባይ ወንዝ በግዛቷ ስር ቢገኝም ወንዙን ሙሉ በሙሉ መዝጋትና ወደ ታሕታይ ሀገራት የሚያደርገውን ፍሰት ማስቆም ግን አትችልም፤ምክንያቱም ይህ ድርጊት የግብፅን ጉሮሮ የሚዘጋ በመሆኑ አደገኛ ጉዳት(significant harm)ያስከትላል፡፡ ኢትዮጵያ ሆነ ግብፅ የስምምነቱ አባል ሀገራት አይደሉም፡፡ ይሁንና መሰረታዊ ጉዳት ያለማድረስ ግዴታ በሀገራት ልምድ (State practice)ቅቡልነት ያገኘ፣ አለም አቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት(International Court of Justice) ትርጉም የሰጠበትና አለም አቀፍ የልማድ ሕግ ደረጃን ያገኘ በመሆኑ ኢትዮጵያም ይህን አለም አቀፍ ግዴታ ታከብራለች፡፡ ለምሳሌ በ1849 “የኮርፉ ቻነል” በማለት በሚታወቀው ጉዳይ ላይ አለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ማንኛውም ሀገር በግዛቷ ስር እያወቀች የሌሎች ሀገራት መብትን የሚጎዳ ተግባር እንዲፈፀም ማድረግ ወይም ማስደረግ አትችልም በማለት ግልጽ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ይህ አለምአቀፍ መርሆ ወደ አባይ ግድብ ስናመጣው በግብጽ ላይ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይቅርና የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በጎርፍና በደለል እንዳይጎዱ የሚያግዛቸውና ሌሎች የጋራ ጥቅሞችን እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን የሚነገርለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በጋራ ባደራጁዋቸው የቴክኒክ ባለሙያዎችም ቢሆን የአባይ ግድብ በግርጌ ተፋሰስ ሀገራት ላይ የሚያደርሰው መሰረታዊ ጉዳት ስለመኖሩ ያቀረቡት ግኝት የለም፡፡ በመሰረቱ ግን የላይኞች ተፋሰስ ሀገራት በግዛታቸው ስር የሚገኝ ውኃን ሲጠቀሙ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው “ተገቢውን እርምጃ” እንዲወስዱ ሊገደዱ ይችሉ ይሆናል እንጂ ምንም አይነት ጉዳት እንዳይደርስ ብለው እጃቸውንና እግራቸውን አጣጥፈው ቁጭ እንዲሉ አይገደዱም፡፡ ህገ ወጥ ጉዳት እንዳያደርሱ መጠንቀቅ አለባቸው ማለት ፈፅመው ጉዳት ማድረስ የለባቸውም ማለት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያም ግብጽን “በእጅጉ ሊጎዳ” በሚችል መልኩ የአባይ ውኃን መጠቀም አትችልም ማለት ፍትሀዊ ተጠቃሚነቷን ትነፈጋለች ማለት አይደለም፤ተጠቃሚነቷ ፍትሀዊ እስከሆነ ድረስ በግብጽ ላይ ለሚደርስ ጉዳት ተጠያቂ ልትሆን አትችልም፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ የአባይ ግድብ ስትሰራ የግብጽ የቀደመ የውኃ ተጠቃሚነት ሊቀንስ ይችላል፡፡ ዋና መሰረታዊ ጉዳይም ግብጽ አስቀድማ የተቆጣጠረችው የናይል ውሀ ለሌሎች ተፋሰስ ሀገራት ልታካፍል ይገባል የሚል በመሆኑ ከዚህ በፊት ስትጠቀመው የነበረውን የውኃ ኮታ ልክ ላታገኝ ትችላለች፡፡ ስለሆነም ሚዛናዊ እና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት ጉልህ ጉዳት ካለማድረስ ግዴታ ቅድሚያ ይሰጧል፡፡

 

6) የኢትዮጵያ አቋምና አለም አቀፍ የሕግ ተቀባይነቱ

6.1) ስምምነቶቹና ኢትዮጵያ ምንና ምን ናቸው ?

የናይል ትልቁ ድርሻ አመንጪ ኢትዮጵያ ነች፤የናይል ወንዝ የውኃ ይዘት ጥቁር አባይ የሚልከው ውኃ ካልታከለበት ምንም ነው፡፡ ይሁንና ግብፅ የናይል ወንዝ ውኃን አከፋፋይና ከልካይ አድራጋ ራሷን በመሾም “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” እንዲሉ ውሀውን በበርጭቆ እንኳን ሳታስቀር ጥርግርግ አድርጋ መውሰድ ትፈልጋለች፡፡ በናይል ወንዝ ላይ “አዲስ ስምምነት” እንዲሮር አትፈልግም፤እንዲኖር ከተፈለገም በቅኝ ገዢዎች የተከናወኑ ስምምነቶችና ውሎች ሙሉ እውቅና ተሰጥቶዋቸው የአዲሱ ስምምነት አካል ሆኖው መካተት አለባቸው በማለት እርባና ቢሶችና መርህ ላይ መሰረት ያላደረጉ ክርክሮች ታነሳለች፡፡

በመሰረቱ ግብጽ የናይል ወንዝ አለቃ፣ አከፋፋይና ከልካይ አድርጎ የሾማት አካል እንደሌለ፤ናይል የተፋሰሱ የጋራ ኃብት እንጂ የግብፅ “የግል ንብረት” እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ የግብፅ አቋም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅምን በእጅጉ የሚቃረን በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ፈፅሞ የማይቀበለው ከመሆኑ በላይ አለምአቀፍ ማህበረሰቡም ለናይል ተፋሰስ ሀገራት ሰላምና ደህንነት ሲል ሊኮንነው ይገባል፡፡ የአፍሪካ ህብረት የስምምነት ሰነድ ከአንቀጽ 3 እና 4 ላይ መገንዘብ እንደሚቻለውም የህብረቱ መሰረታዊ አላማዎችና መርሆዎች የአህጉሪቱ ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የአባል ሀገራት አንድነትና ትብብርን ማስጠበቅ ከመሆኑ ባሻገር ሀገራት በልአላዊ ግዛታቸው የሚገኝን ተፈጥአዊ ኃብት በመጠቀም የህዝቦች ኢኮኖሚያዊ እድገትን የማረጋገጥ ግዴታንና መብትን እውቅና የሚሰጡ ጭምር ናቸው፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር  አንቀጽ 1 እና 2 ላይም በተመሳሳይ መልኩ የድርጅቱ መሰረታዊ አላማዎችና መርሆዎች የተደነገጉ ሲሆን በአባል ሀገራት መካከል በሁሉም መስኮች እኩልነትን ማረጋገጥ፤እንዲሁም አለምአቀፍ ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅን ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በዚሁ መሰረት ሀገራት የጋራ ፀጋቸውንና ሀብታቸውን በጋራና በእኩልነት የመጠቀም መብት አላቸው፡፡ ግብፅ የናይል ወንዝ ብቸኛ ባለቤት ነኝ በማለት የቀጠናውን ሰላምና ደህንነት እንድትበጠብጥ ሆነ ፍትሀዊ የተፈጥሮ ኃብት ክፍፍልን የሚቃረን ህገ ወጥ ተግባር እንድትሰራ ፈቃድ ማግኘት የለባትም፡፡ ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ ታሪካዊ፤ተፈጥሮአዊና የቀደምትነት የባለቤትነት መብት አለኝ በማለት የምትከራከረው በጉዳዩ ላይ መብት ከሌላቸው ቅኝ ገዢዎች ጋር የተዋዋለቻቸውን ያረጁ እና ከዘመኑ ጋር የማይሄዱ ስምምነቶችንና ውሎችን እየመዘዘች ነው፡፡ ይህ የግብጽ የተለመደው አሰልቺ ክርክር በአለምአቀፍ ልማዳዊ ሕግ የማይታወቅ ነው፡፡ የግብፅ ብቸኛ አማራጭ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የመከባበርና የመተባበር መስመርን መከተል መሆን አለበት፡፡

ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ የተፈፀሙት ስምምነቶችና ውሎች የላይኞቹ የአባይ ተፋሰስ አገራትን ሙሉ በሙሉ ያገለሉና የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅምን ታሳቢ ያላደረጉ በመሆናቸው አልቀበላቸውም በማለት በግልጽ ስትቃወም ቆይታለች፡፡ ታንዛንያና ኬንያም እነዚህ ስምምነቶች ተቀባይነት እንደሌላቸው ከቅኝ ገዥ ሀገራት ነፃነታቸውን በተጎናፀፉበት ማግስት ጀምሮው በመሪዎቻቸው በኩል አሳውጀዋል፡፡ የታንዛንያው መሪ ጁሊየስ ኑረሬ ማንኛውም አይነት የቅኝ ገዢዎች ስምምነቶች በታንዛንያ ላይ ተፈፃሚነት እንደሌለው በግልጽ አውጇል፡፡ ”ኒይረሬ ቀኖና” እየተባለም ይታወቃል፡፡ ይሁንና በስምምነቶቹ ላይ አስተያየታቸው ሳይሰጡ እስከአሁን ዝምታን የመረጡ የላዕላይ ተፋስስ ሀገራትም አሉ፡፡ ለምሳሌ ሩዋንዳና ኡጋንዳ፡፡ እነዚህ ሀገራት በናይል ወንዝ ላይ ጠንካራ አቋም ማራመድ ያልቻሉበት ምክንያት ከናይል ወንዝ በላይ ሌሎች ጂኦግራፊካዊና ፖለቲካዊ ብልጫ ባላቸው የተፈጥሮ ኃብት የተከበቡ ከመሆኑ በላይ ግዙፍ ፕሮጀክት ለመስራት የሚያስችል አቅምም አላሳደጉም፡፡

ሲጠቃለል በካይሮና በሎንደን መካከል ወይም በካይሮና በካርቱም መካከል የተከናወኑ ውሎች ለኢትዮጵያ ምንም ናቸው፤አዲስ አበባ ያልተሳተፈችበት ማንኛውም አይነት ስምምነት ከአንድ ሺህ በላይም ቢደረደረርና የግብጽ ቤተመንግስት ቢሞላው በኢትዮጵያ ላይ ውጤት የለውም፡፡ በቬና ቃልኪዳን የስምምነት ሕግ አንቀጽ 11 እና 34 ላይ  እንደተመለከተው በሀገራት መካከል የሚከናወን ማንኛውም አይነት ስምምነት ፍላጎቷ ባልገለፀች በሌላ ሶስተኛ ሀገር ላይ ተፈጻሚነት የለውም፡፡ በተለይም የስምምነቱ አንቀጽ 34 ድንጋጌ ስንመለከተው በአንድ ውል ላይ ነፃ ፍላጎቷን ካልገለፀች የምታገኘው መብት ሆነ የሚጣልባት ግዴታ አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያ ከላይ የተገለጹት ስምምነቶች አታውቃቸውም፤የስምምነቱ አካልም አይደለችም፡፡ ስለሆነም ስምምነቶቹና ውሎቹ በኢትዮጵያ ላይ ተፈጻሚነት የላቸውም፡፡

 

6.2)  ፍጹማዊ የግዛት ሉአላዊነት ኃልዮት፤

በመርህ ደረጃ አንድ ሀገር በግዛት ክልሏ ላይ ፍፁም የሆነ የሉአላዊነት ስልጣን አላት፡፡ አባይ የግዛትና የሉአላዊነት መገለጫ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ህዝብ ፖለቲካዊ ልእልና አንፃርም መታየት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ በግዛቷ ስር የሚገኝ ማንኛውም አይነት የተፈጥሮ ኃብትን የማንም ፈቃድ ሳትሻ የመጠቀም መብት አላት፡፡ በአንድ ወቅት አሜሪካ በግዛቷ ስር የሚገኘውን “ሪያ ግራንዲ” የተባለውን ወንዝ ሚክሲኮን በሚጎዳ መልኩ ተጠቅማለች የሚል ክስ ሲቀርብባት ሉአላዊነቴን የማስከበር ስራ ነው የሰራሁኝ እንጂ የጣስኩት አንድም አለም አቀፍ ሕግ የለም የሚል መከራከሪያ ነጥብ አቅርባ ነበር፡፡ ይህ ከፍጹማዊ የግዛት ሉአላዊነት ኃልዮት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ሆኖ “የሀርሞን ቀኖና” የሚል ስያሜ አግኝቶ ነበር፡፡ የላይኞች ተፋሰስ ሀገራት በግዛታቸው ስር የሚገኝን ወንዝ ሲጠቀሙ የታችኞች ተፋሰስ ሀገራትን ታሳቢ የማድረግ ግዴታ እንደሌለባቸው የሚያትት ነው፡፡ ሆኖም ይህ ኃልዮት እንደ የአካባቢ ጥበቃና ወንዞች የመሳሰሉ ድንበር ተሻጋሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከአለም አቀፍ ሕግ አንጻር ተቀባይነት የሌለውና ከዘመኑ ጋር ሊሄድ የማይችል እምነት ነው፡፡ ሀገራት የተገደበ ግዛታዊ ሉአላዊነትን ቅድሚያ የሚሰጡበት ሁኔታ እያደገ በመምጣቱ በአሁን ጊዜ ተቀባይነቱን እየቀነሰ መጥቷል፡፡

ኢትዮጵያም ይህን “የሀርሞን እምነት” የመረጠችው አይመስልም፤ኢትዮጵያ ያስቀደመችው የድርድርና የመተባበር መርሆ በመሆኑ የተገደበ የግዛት ሉአላዊነትን የምትደግፍ ነች ማለት ይቻላል፡፡ አለም አቀፍ የልማድ ሕግ ደረጃ ካገኙ የውሀ ህጎች አንጻር ሲታይም  ትክክለኛ አቋም ይህ ነው፡፡ እስካሁን በስራ ላይ የሚገኘው የኢ.ፌ.ድ.ሪ.መንግስት የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራተጂ ላይ እንደተገለፀው በግሎባላይዜሽን ማእቀፍ ውስጥ አገራዊ ጥቅማችንና ደህንነታችን ለማስጠበቅ የሚያስችል የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደህንነት ፖሊሲ መቅረፅ ያለብን በድንበራችን ታጥረን ሳይሆን አለም አቀፋዊውን ትስስር ጠበቅ አድርገን ይዘንና አቅፈን የምንሰራበት አቅጣጫ የሚያሳየን ፖሊሲ መሆን እንዳለበት ከዚያም አልፎም ጠቅሞ በመጠቀም፣ ሰጥቶ በመቀበል፣ በድርድርና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ እንጂ በተናጠል ጥቅምን ለማስጠበቅ በመሞከር የሚፈፀም ፖሊሲ መሆን የለበትም፡፡ በዚሁ መሰረትም የአባይ ወንዝ በግዛታችን ስር ስለሚገኝ ብቻ ከአለም ማህበረሰቡ ተነጥለን በወንዞቻችን ስር መሽገን፣ የድርድር በሮቻችንን ዘግተንና አለም አቀፋዊ ትስስርን ችላ ብለን የምናሳካው ሀገራዊ ጥቅም አይኖርም፡፡

 

6.3) አባይ የሰብአዊ መብቶች መተግበርያ መንገድ ስለመሆኑ፤

የናይል ወንዝ የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ተፈጥሮአዊ ጸጋ በመሆኑ ኢትዮጵያ ከፍፁም ግዛታዊ ሉአላዊነት መርሆ ጋር የሙጥኝ የምትልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ የአባይ ወንዝ የሰብአዊ መብት ጉዳይም ጭምር ነውና፡፡ የናይል የተፋሰስ ሀገራት የጋራ ፀጋቸውና ሀብታቸውን እየተገለገሉ በድህነት ተዘፍቆ የሚማቅቅ ህዝባቸውን የተሻለ ኑሮ እንዲኖረው የማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡ የሲቪልና የፖለቲካዊ አለምአቀፍ ቃልኪዳን እንዲሁም የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና ባህላዊ አለምአቀፍ ቃልኪዳን የጋራ አንቀጽ 1(2) ላይ እንደተደነገገው ሁሉም ህዝቦች በጋራ ጥቅም ላይ የተሰረተ አለምአቀፍ የኢኮኖሚ ትብብር ግዴታቸውንና አለምአቀፍ ሕግን አክብረው የተፈጥሮ ሀብታቸውን ለራሳቸው ጉዳይ በነፃነት መጠቀም ይችላሉ፡፡ በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን አንድ ህዝብ ለኑሮው አስፈላጊ የሆኑትን የራሱን ጥቅሞች አይነፈግም፡፡ በተጨማሪም የሰብአዊ መብቶች ሁሉ-አቀፍ መግለጫ አንቀጽ 22 ላይ እንደሰፈረ ሀገራት የኃብት ሁኔታቸውን ታሳቢ በማድረግ የሰዎች የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና ባህላዊ መብቶችን የማሟላትና የኑሮ ዋስትና ማረጋገጥ ያለባቸው ሲሆን በኢ.ፌ.ድ.ሪ.ህገ መንግስት አንቀፅ 43 መሰረትም የኢትዮጵያ ህዝቦች የማያቋርጥ እድገት የማግኘት መብታቸውን እውቅና አግኝቷል፡፡ መንግስት የሀገሪቷ አጠቃላይ ኃብት መሰረት በማድረግ የዜጎች እድገትና መሰረታዊ ፍላጎቶች የማሟላት ግዴታ አለበት የተባለበት የጀርባ ምክንያት ቁጠባዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች የሰው ልጅ ሰብአዊና ተፈጥሮአዊ መብቶች ተደርገው የሚወሰዱ በመሆናቸውም ነው፡፡ ሁሉም ሀገሮች የተፈጥሮ ሀብታቸውን ጥቅም ላይ በማዋል የዜጎቻቸው ማህበረ-ቁጠባዊ ፍላጎት የመመለስ፣ የልማት ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ እንዲሁም ሰብአዊ መብትን የማክበርና የማስከበር ግዴታ አለባቸው፡፡

 

6.4) ፍትሀዊና ምክንያታዊ አጠቃቀምን ተግባራዊ የማድረግ መብት

ኢትዮጵያ የመረጠችው የመፍትሔ መንገድና በናይል ወንዝ ላይ የያዘችው አቋም አለምአቀፋዊ ቅቡልነት ያለው ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀምን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ ሙሉ ለሙሉ ተፈጥሮአዊ ፍሰቱን አስቆመዋለሁኝ የሚል አቋም አንድም ቀን አንፀባርቃ አታውቅም፤ፍላጎቷም በኮንቬንሽኑ አንቀፅ 5 መሰረት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲኖር ነው፡፡ ፍትሀዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነትን(equitable and reasonable Utilization)ተግባራዊ ለማድረግ ታሳቢ መደረግ ያለባቸው ሁኔታዎች በኮንቬንሽኑ አንቀጽ 6(1)(a-g) ላይ የተመለከቱ ሲሆን በዚሁ መሰረትም የሀገራቱ ጂኦግራፊ፤ሃድሮግራፊክ፣ ሃይድሮሎጂክ፣ ኢኮሎጂካል፣ የአየር ንብረትና ሌሎች ተፈጥሮአዊ ነገሮች፤በተፋሰስ ሀገራት የሚገኝ ህዝብ ከውኃው ጋር ያለው ትስስርን፤የተፋሰስ ሀገራቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎትን፣ የአንድ ሀገር የውሀ ተጠቃሚነት በሌላኛው ተፋሰስ ሀገር ላይ ያለው ተፅእኖ፤በጥቅም ላይ የዋለ የውሀ መጠንና ክብት የውሀ አቅም፤የውሀ ኃብትን ለመቆጣጠር፣ ለመጠበቅ፣ ለማልማት ያለው ኢኮኖሚያዊ አዋጪነት፤እንዲሁም ጥቅም ላይ ከዋለ ወይም እንዲውል ከታቀደው በተሻለ ሁኔታ ሌላ አማራጭ የውኃ ምንጭ መኖርን ታሳቢ በማድረግ መሆን አለበት፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ኢትዮጵያን በእጅጉ የሚደግፉ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከ110 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በመያዝ ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ከመሆኑ በላይ ቀጣይነት ባለው የህዝብ ብዛት መጨመር ምክንያት እያጋጠማት ያለው የአየር ንብረት ለውጥ አስጊ ነው፤ኢትዮጵያ የናይል ውኃ ከፍተኛ ባለድርሻ ከመሆኗ በላይ የሀገር ውስጥ ትልቁ ሀብቷም አባይ ሆኖ እያለ ከወንዙ ምንም ሳትጠቀም የልማት ተጠቃሚነት መብትን የዘመናት የዜጎቿ ጥያቄ ሆኖ ዘልቋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትገኝበት መልከአ ምድራዊ ሁኔታ የአባይ ወንዝን ለኤሌክትሪክ ሃይል አመንጪነት አመቺ ሆኖ እያለ ይህን እድል መጠቀም ሳትችል መቆየቷን፤የዜጎቿ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎት በእጅጉ እያደገ መምጣቱ እና ሌሎች ምክንያቶች ተደማምረው የአባይ ወንዝን አለመጠቀም በማይቻልበት ጊዜ ላይ ደርሳለች፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ባፀደቁት የኳርቱም ሰነድ እየተባለ በሚታወቀው የመርሆዎች መግለጫ(Principles of Declarations) ላይም ይህ መርህ ተካቷል፡፡   

አለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ማንኛውም አይነት የሄያጅ ውኃ አጠቃቀም ሚዛናዊና ምክንታዊ በሆነ የአጠቃቀም መርሆ በመመስረት መሆን እንዳለበት “ጋብቺኮቮ ናጊማሮስ የውሀ ፕሮጀክት ጉዳይ” ላይ በሰጠው ውሳኔ በግልጽ ያሰፈረ ሲሆን ይህ የሚያሳየው ፍትሀዊና ምክንያታዊ የውሀ አጠቃቀም መርሆ የዓለም አቀፍ የልማድ ሕግ ደረጃን ማግኘቱን ነው፡፡ ምንም እንኳን ፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን ምክረ ሃሳብ በራሱ አስገዳጅ አለመሆኑን ግልጽ ቢሆንም ይህንን መርህ ጨምሮ ከላይ የተመለከትናቸው ሌሎች መርሆዎች የዓለም አቀፍ የልማድ ሕግ ደረጃን በማግኘታቸው ይህ ትርጉም ህጋዊ ተቀባይነት እንደሚኖረው ግን የሚያከራክር አይደለም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ መለስ ዜናዊ በግብጽ ቴሌቭዥን በተደረገላቸው ቃለ መጠይቅ ላይ “የግብጽ የህልውና መሰረት ናይል እንደሆነ ኢትዮጵያ ትረዳለች፡፡ ሆኖም የናይል ወንዝ የውሀ ይዘት 85%ቱ የኢትዮጵያ በመሆኑ ከዚሁ ሀብቷ መጠቀም እንደምትችል ግብፅም በተመሳሳይ መልኩ ማወቅ አለባት፡፡ ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ ከሌሎች ተፋሰስ ሀገራት ጋር እኩል የውሀ ድርሻ ማግኘት አለብኝ በማለት ሳይሆን እየጠየቀች ያለችው ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መከፋፈል አለብን፤ግብጽም አሁን የምጠቀምበትን የውሀ ኮታ የሚነካብኝ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ጉዳት ያስከትልብኛልና አልቀበለውም የሚለው ያረጀ አቋሟን እንደገና መመርመር አለባት” በማለት ተናግረው ነበር፡፡ የግብጽ ምልከታ ኢትዮጵያ ከያዘችው አቋም በእጅጉ ተቃራኒና መታረቅ የማይችል ነው፤የክርክሯ ትኩረትም መሰረታዊ ጉዳት ያለማድረስ ግዴታ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ነው፡፡ በግብፅ አቋምና አረዳድ “ጉዳት ያለማድረስ መርሆ” ማለት አሁን በበላይነት የያዘችውን የውኃ ኮታ አለመንካት ማለቷ ነው፡፡ የግብፅ የቀድሞ ፕሬዚዳንት መሃመድ ሙርሲ አሁን ከምንጠቀምበት የናይል ወንዝ ላይ የጠብታ ውኃ የሚቀነስብን ከሆነ ደማችን የመጨረሻ አማራጭ አድርገን እንጠቀማለን ሲል ይፋዊ መግለጫ መስጠቱን ይታወሳል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ”ውኃ ከደም ይወፍራል” የሚለውን የኢትዮጵያውያን ብሂል እንዲያውቀው ባይገደድም እንኳን ግብፅ “አስራ ስድስት” ጊዜ በኢትዮጵያ የተደቆሰችበት ታሪካዊ የጦርነት ግጥሚያዎችን ፈፅሞ እንደማይረሳው ግን እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡ የአብድል ፈታህ አልሲ ሲ መንግስትም በናይል ላይ የሚያራምደውን ፖለቲካ ይረዳው ዘንድ  ይህን ታሪክ እያስታወሰ መሆን አለበት።

 

7) መፍትሔው፡- አሁናዊ ድርድርና ስምምነት

የናይል ወንዝ አጠቃቀምን፣ ማልማትን፣ መንከባከብን፣ መጠበቅን፣ መቆጣጠርን አስመልክቶ ሁሉንም ተፋሰስ ሀገራት የሚያስማማ፣ የሚያዋህድና የሚያስተባብር ወጥ የሆነ ቀጠናዊ ሕግ የለም፡፡ ግብፅ ሀገራዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ ከሱዳንና ከቅኝ ገዢዎች ጋር ካደረገችው የሁለትዮሽ ስምምነት(Bilateral agreements) ውጪ የናይል ወንዝን የሚያስተዳድር የባለ ብዙ ወገን የስምምነት ማእቀፍ(Multilateral agreements) መፍጠር አልተቻለም፡፡ ሆኖም ግን የናይል ወንዝ ፍትሀዊ አከፋፈል፣ አጠቃቀምና አለማምን የሚስተዳድር ወጥና አለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ህጋዊና ተቋማዊ ማእቀፍ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም በናይል ወንዝ ላይ ለሚነሳው ማንኛውም አይነት አለመግባባትን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚችል የሕግ እና የተቋም ማእቀፍ ከሌለ የቀጠናው ግጭት መቀስቀሻና ደም ማፈሳሻ ሊሆን እንደማይችል እርግጠኛ መሆን  አይቻልም፡፡

ይህ በመሆኑም በናይል ወንዝ ላይ የውኃ አከፋፈል፣ አስተዳደርና አመዳድብን ለማስተዳደር እንዲሁም በውኃ ምክንያት ግጭት እንዳይፈጠር ለመከላከል የሚያስችል ህጋዊና ተቋማዊ ማእቀፍ ለመመስረት አስፈላጊ መሆኑን በተፋሰስ ሀገራት መካከል የጋራ መግባባት የተደረሰበት ጉዳይ በመሆኑ እ.ኤ.አ ከ1960ዎች ጀምሮ የናይል ወንዝ ተፋሰስ ትብብርን የሚያጠናክሩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፡፡ ለምሳሌ ወንድማማችነት፣ ቴክኒካዊ የትብብር ኮሚቴ እና ሌሎች ተያያዥ እንቅስቃሴዎች ተጠቃሾች ቢሆኑም ይህ ነው የሚባል የረባ ውጤት አላስመዘገቡም፡፡ ይህን ተከትሎ በሀገራቱ የጋራ ጥረትና ትብብር የናይል ተፋሰስ እንቅስቃሴ(Nile Bazine Initiative) በ1999 እ.ኤ.አ እንዲመሰረት ሆኗል፡፡ ከኤርትራ የታዛቢነት ተሳትፎ ውጪ ሌሎቹ ሁሉም የናይል ተፋሰስ ሀገራት የዚሁ እንቅስቃሴ አባል ናቸው፡፡ ይህ እንቅስቃሴ በ2010 እ.ኤ.አ “የኢንቴቤ ስምምነት” የሚባል የናይል ተፋሰስ የትብብር ማእቀፍ ስምምነትን(Nile Basine Cooperatve Framework Agreement) መውለድ የቻለ ቢሆንም እስከአሁን አልጸደቀም፡፡

ስምምነቱን ለማጸደቅ ኢትዮጵያ፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያና ብሩንዲ የፈረሙ ቢሆንም እስካሁን ስምምነቱን ያፀደቁት ግን ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳና ታንዛንያ ብቻ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ይህን የትብብር ስምምነት በአዋጅ ቁጥር 797/2005 መሰረት አጽድቃ የህጎቿ አካል አድርገዋለች፡፡ ኬንያና ኡጋንዳ ስምምነቱን ለማፅደቅ ፈቃደኛ እንደሆኑ ገልፀው የነበረ ቢሆንም እስካሁን ሊያጸደቁት አለመቻላቸው አቋማቸውን ለማወቅ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክና ኤርትራ ለናይል ወንዝ ያላቸው አስተዋጽኦ አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ በናይል ፖለቲካ ላይ በመሪነት የመተወን ፍላጎት ያላቸው አይመስልም፣ በዚሁ ምክንያትም በስምምነት ማእቀፉ ላይ አለፈረሙም፤አላጸደቁትም፡፡ ብሩንዲ የስምምነቱን ፈራሚ ብትሆንም ከማጸደቅጋር ተያይዞ ያላት አቋም ግልጽ አላደረገችም፡፡ ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን እንዳወጀች ብዙ ሳትቆይ የእንቅስቃሴው አባል ሆናለች፡፡ የስምምነቱ ማእቀፉን እንደምትፈርምና እንደምታጸድቀውም የገለፀች ሲሆን በውስጧ ባለው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት እስካሁን አላፀደቀችውም፡፡ በመሆኑም ስምምነቱን እንድታጸድቅ የኢትዮጵያ ያላሳለሰ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ ግብፅና ሱዳን ካላቸው “ከእኔ በላይ ንፋስ” አይነት ፍፁም ከሆነ የግለኝነት ስሜትና ስግብግብነት ምክንያት በስምምነት ሰነዱ ላይ አልፈረሙም፤አላጸደቁትም፡፡

ግብፅ ይህን ስምምነት ለማጽደቅ ያልተስማማችበት መሰረታዊ ምክንያት ከዚህ ቀደም በቅኝ ገዢዎች የተከናወኑ ስምምነቶች ላይ የሰፈሩ የግብፅ የውሀ ድህንነት፣ ድርሻና ኮታ የሚነካብኝ ስምምነት ነው፤ይህን ስምምነት መፈረም ካለበኝ አሁናዊ የውኃ ተጠቃሚነቴን( Status qua) እንደማይነካብኝ በስምምነቱ ውስጥ መካተት አለበት ባይ ነች፡፡ በተጨማሪም የራስጌ ሀገራት ሊያከናውኑት ያቀዱትን ስራና እርምጃ ለግርጌ ሀገራት የማሳወቅ ግዴታ ሊካተትበት ይገባል በማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የማይሆንና ፍፁም በተፋሰስ ሀገራቱ መካከል የሚያቀራርብ አቋም አይደለም፡፡ ይህ የግብጽ ፍላጎት ሁሉም የራስጌ ሀገራት አልተቀበሉትም፡፡ የሱዳን ምክንያት ግብጽ የምታነሳቸውን መቃወሚያዎች እንደምትጋራ በተለጣፊነት ደረጃ ሀሳብ ብትሰጥም ግልፅ ነው ማለት ግን አይቻልም፤የሱዳን ተቀያያሪ አቋም በስምምነት ማእቀፉን የምትወስነው ውሳኔ ተገማች እንዳይሆን ያደርጓል፡፡ በቅርቡ በነበረው የአረብ ሀገራት ስብሰባ ኢትዮጵያን የሚቃወም ውሳኔ ሲታላለፍ ሱዳን በብቸኝነት የተቃውሞ ድምጿን እንዳሰማች የምናስታውሰው ነው፡፡ ስለሆነም የሱዳን የመጨረሻ ውሳኔ ጊዜው ሲደርስ የምናየው ይሆናል፡፡ ያም ሆነ ይህ ይህን ስምምነት ስድስት አገራት ከፈረሙትና ካፀደቁት በናይል ተፋሰስ ሀገራት ላይ አስገዳጅ ሕግ  ስለሚሆን ግብፅ ብቻዋን ተገትራ መቅረቷን የማይቀር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማእቀፍ ስምምነት እንዲጸድቅ አበክራ ልትሰራበትና ሌሎች የፈረሙና ያልፈረሙ ቀሪ ተፋሰስ ሀገራትን የማሳመን ስራ መስራት አለባት፡፡ በመሰረቱ ይህ ስምምነት ከሞላ ጎደል አለም አቀፍ የውኃ መሔጃ ሕግ መርሆዎች የሚባሉት አካትቶ የተቀረፀ የሕግ ማእቀፍ ሲሆን በዚሁ መሰረትም የሀገራት ትብብርን በማጠናከር እንዲሁም ፍፁም ግዛታዊ አንድነትና ግዛታዊ ሉአላዊነትን በማቻቻል የተገደበ የግዛት ሉአላዊነት እንዲኖር በማድረግ፤በአንድ በኩል የላይኞች ተፋሰስ ሀገራት በታችኞች ተፋሰስ ሀገራት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርሱ ግዴታ የሚያስገባ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ቅንልቦና መሰረት ያደረገ የጋራ የሆነ ሚዛናዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነትን እንዲኖር እውቅና የሚሰጥ ነው፡፡

 

8) ማሰርያ

ኢትዮጵያ አባይን የሚያክል ትልቅ ወንዝ ይዛ የኩራዝ መብራት የምተጠቀምበት አንድም ምክንያት የለም፤የአባይ ወንዝ የራሷንና የዜጎቿን የመብራት ጥያቄን የምትመልስበት ብቻ አይደለም፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበትና ድህነቷን የምታስወግድበት ትልቅ መሳርያዋ ነው፡፡ የአባይ ወንዝ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚያዊ እድገት ማሳለጫ መንገድ ብቻም አይደለም፤የአባይ ወንዝ ለኢትዮጵያ የክብሯ፣ የሉአላዊነቷና የግዛቷ ማስከበርያ መንገድም ነው፡፡ የአባይ ወንዝ የህዝብ ኃብት ነው፤ነዳጅ ነው፤ፓውንድ/ዶላር ነው፤ሚሳይል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ድህነቷን አሽቀንጥራ ለመወርወርና ኢኮኖሚያዊ እደገቷን ለማረጋገጥ በሚዛን ትጠቀምበታለች፡፡ የግብፅን ህልውና በማይፈታተን መልኩ፣ ግብፅን በውኃው ላይ የመጠቀም መብቷን በእጅጉ በማይጎዳ አኳኃን አለም አቀፍ የውሀ ሕግን ባገናዘበ መልኩ ፍትሀዊና ምክንያታዊ የመጠቀም መብቷን ታረጋግጣለች፡፡ ይህ ደግሞ በትልቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ብቻ ላያቆም ይችላል፡፡

በመሆኑም በግብጽና ኢትዮጵያና መካከል ያለውን ውጥረት ለመፍታት የሚያስችል ገዢና አስገዳጅ ስምምነት በመፍጠር አብረው የሚለሙበትና የሚያድጉበት ባህል መስፈን አለበት፡፡ ሁለቱም ሀገራት ለዚሁ መዘጋጀት ካልቻሉ የቀጠናው ሰላም እና ደህንነት አስጊ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ በናይል ዙርያ ከግብፅ ጋር ለመስማማትና ለመደራደር በሯን ክፍት ማድረግ ችላለች፡፡ ትልቁ የውሀ ይዘት ከግዛቷ እንደሚመነጭ እያወቀችም ቢሆን በናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል ፍትሀዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት እንዲኖር ፍላጎቷ እንደሆነ በተደጋጋሚ አይተነዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያ የማንም አለምአቀፍ የውሀ ሕግ ስምምነነትና ተቋም ፈራሚ ወይም አባል ሀገር ባትሆንም እንኳን አለም አቀፍ ልማዳዊ የውሀ ሕግ ደረጃ ባገኙ መርሆዎች እንድትመራ ያላት ፍላጎት ማሳያ እንቅስቃሴ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡ ይኸውም ኢትዮጵያ ከግብፅ የተሻለ ኃላፊነት እንደሚሰማት የሚያስገነዝቡ መልካም እርምጃዎች ስትወስድ ቆይታለች፣ አሁንም እየወሰደች ትገኛለች፡፡ ለምሳሌ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማእቀፍ ስምምነት (NBCFA) በማጽደቅና እንዲፀድቅ ትግል በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያ የማይናቅ ስራ እየሰራች ቆይታለች፡፡    

ስለሆነም ግብጽ መከተል ያለባት ብቸኛ መንገድ በቅኝ ገዢዎች የተጎናፀፈችውን የፊታውራሪነት መአርግ በመርሳት ከተፋሰስ ሀገራትና ከኢትዮጵያ ጋር በቅን ልቦና መደራደርና መተባበር ብቻ ነው፡፡ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ምክንያታዊና ሚዛናዊ ተጠቃሚነት፣ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ ግዴታና ሌሎች አለምአቀፍ የውኃ ሕግ መርሆዎች መሰረት በማድረግ ከመደራደርና ከመተባበር ውጪ አማራጭ የላቸውም፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ኢትዮጵያ በሉአላዊ ግዛቷ ስር የሚገኘውን የአባይ ወንዝ አለም አቀፍ ልማዳዊ ተቀባይነት ባገኙ መርሆዎች መሰረት የውሀ ሀብቷን እንዳትጠቀምና ህዝቦቿን ከድህነት እንዳታላቅቅ የሚያስቆማት አንድም የውስጥ ሆነ የውጭ ኃይል አለመኖሩን ግብፅ ሆነ ከግብፅ ጋር የተሰለፉ ኃይሎች ሊያውቁት ይገባል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

PROBLEMS WITH THE ‘GENEROUS DIRECTIVE’: DIRECTIVE ...
A Brief Note on Ethiopia’s Tax Privileges to ease ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 23 November 2024