ከዚህ ቀደም በሀገራችን ኢትዮጵያ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይን የሚገዙ ሕጎች እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ በ1955 ዓ.ም የወጣው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 210/1955፣ በ1968 ዓ.ም የወጣው የሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 64/1968፣ የሠራተኛ ጉዳይ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 85/1968፣ ስለአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ የወጣው አዋጅ ቁጥር 42/1985 እና አዋጅ ቁጥር 377/1996 የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከየካቲት 18 ቀን 1996 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ በግሉ ዘርፍ ያለውን የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነትና መስተጋብር እንደ ዋነኛ ምሰሶ በመሆን ሲያስተዳድር የነበረው ሕግ አዋጅ ቁጥር 377/1996 እና የዚህ አዋጅ ማሻሻያ ሕጎቹ አዋጅ ቁጥር 466/1997 እና አዋጅ ቁጥር 494/1998 ነበሩ፡፡ እነዚህ ሕጎች ከ14 አመታት በላይ በሥራ ላይ የዋሉ በመሆናቸው አሁን ካለው የማህበረሰብ እድገት ጋር የተጣጣሙ ባለመሆናቸው የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀን ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው 4ኛ አመት የሥራ ዘመን 48ኛ መደበኛ ስብሰባው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ረቅቅ አዋጅን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
ይህም ሕግ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ዓ.ም ሆኖ ነሐሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በሥራ ላይ ውሏል፡፡ ይህ አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ምን ምን ሀሳቦችን አካቶ ነው የተሻሻለው? ለሠራተኛው ምን ዓይነት ሕጋዊ ጥቅምና መብቶችን አካቷል? እንዲሁም የአሠሪ ግዴታና መብት ምን ይመስላል? የሚሉትን ጉዳዮች እና አዲሱን አዋጅ ከተሻረው የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 በማነፃፀር በወፍ በረር (Bird’s Eye View) እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡
አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ከዚህ ቀደም የነበረውን አዋጅ ከነ ማሻሻያዎቹ በመሻር እና የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጄንሲ አዋጅ ቁጥር 632/2001ን በአዲሱ አዋጅ ውስጥ በማካተት ነው በሥራ ላይ የዋለው፡፡