መግቢያ
ኢንቨስትመንት ቃሉ እንግሊዝኛ ሲሆን አሁን አሁን ግን በአማርኛ ሥነ ጽሑፍም በጣም እየተለመደ በመምጣቱ የአማርኛውን አቻ ቃል ማለትም “ምዋዕለ-ንዋይ” የሚለው መጠሪያ እስከሚዘነጋ ድረስ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በየእለቱ ይነገራል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት አዋጅ ቁ.769/2005 ሳይቀር መዋዕለ ንዋይ ከማለት ይልቅ ኢንቨስትመንት የሚለውን ቃል ሙሉ በሙል ተጠቅሟል፤ ስለዚህ በዚህ ረገድ አንባቢውን ግራ ላለማጋባት ሲባል ጸሐፊው ኢንቨስትመንት የሚለውን ቃል ለመጠቀም ተገዷል፡፡ የዚህ ጹሑፍ ዓለማ ለምን ምዋዕለ-ንዋይ የሚለው ቃል ኢንቨስትመንት እየተባለ ተጠራ የሚለው ጉዳይ ባይሆንም አገር በቀል መጠሪያዎችን መጠቀም እንድንለምድና እንድናዳብር አስተያየት ለመጠቆም ነው፡፡
የአንድ ሃገር ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተፈለጊ እና ሳቢ የሚያደርጋት የዘረጋችው ሃገራዊ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ነው፡፡ ሆኖም ግን ምቹ የሕግ እና የፖሊሲ ማዕቀፍ መኖሩ ብቻ ፍሰቱን እንዲጨምር ላያደርግ ይችላል፡፡ ለምን ቢባል በተግባር የወጡት ፖሊሲዎች እና ሕጎች በአስፈጻሚው አካል ዘንድ የመተግበራቸው ሁኔታ ስለሚያጠያይቅ ጭምር ነው፡፡ እነዚህ አስተዳደራዊ ሥነ ሥርዓቶች ነጻ የኢንቨስትመንት ፈቃድ በሰጡ አገራት ጭምር ከፍተኛ ስጋት ያጭራሉ፡፡ በብዙ ሃገራትም በርካታ ኢንቬስተሮች የሚያቀርቡት ስሞታ እና እሮሮ በተለይም አሰልቺ ከሆኑ አሰራሮች (hectic bureaucracy) መኖር ጋር ይያያዛል፡፡
እርግጥ ነው ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ጥሩ የሕዝብ ግንኙነት ወይም የገበያ ጥናት ባለሙያዎች መኖራቸው መልካም ተግባር ነው፡፡ በተለየም ቢዝነስ ተኮር የሕዝብ ዲፕሎማሲ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ተግባር ነው፡፡ ታዲያ በዚህ የማስተዋዋቅ ተግባር የተመሰጡ የውጭ ኢንቬስተሮች የተባለችውን አገር ሄዶ ሁኔታውን ለማየት ከመቼው ጊዜ ልባቸው ይነሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ የሚሄዱበት አገር አስተዳደራዊ ችግር በስፋት የሚታይበት ከሆነ ኢንቬስተሩ አስቀድሞ ስለሁኔታው ሊወስን ይችላል፡፡ ለአብነት ያህልም ኢንቬስተሩ/ሯ ወደ ተባለው አገር ለማምራት ቪዛ ተይቀው በጣም አሰልቺ ነገር ቢገጥማቸው ከራስ ተሞክሮ ውሳኔ ሊዎስኑ ይችላሉ፡፡ (ፍራንክ ሳደር፡እኤአ 2003፡2)
የተባለውን እሰቸጋሪ ውጣ ውረድ አልፈውም ወደ አገር ቤት ሲገቡ ከሌሎች ቀደምት ኢንቨስተሮች ተሞክሮ በመውሰድ ሊያውጡ የሚችሉትን ወጪ፣ መዘግየት፣ የመንግስት ምላሽ እና ለችግሮች የሚሰጠውን መልስ ከግምት በማስገባት አስቀድመው ትረፍና ኪሳራ (cost-benefit analysis) በመስራት የተባለው አስተዳደራዊ ችግር ይኖራል ብለው ካመኑ ልክ እንደ ሌሎች ተጎጂ ላለመሆን ባመጣቸው እግር ወደ መጡበት አገር ይመለሳሉ፡፡
ሌላው ጉዳይ ፈቃድ ሰጭው አካል የቀረበለትን ማመልከቻ ቶሎ መልስ ካልሰጠበት፣ ግለጸኝነት የሚጎድለው ከሆነ እና በጣም ሰፊ የሆነ ፈቅደ ስልጣን (discretionary power) የሚስተዋል ከሆነ ለሌላ ብልሹ አሰራር ማለትም ጉዳይን በቶሎ ከፍሎ ማስፈጸም (practice of “speed payments”) ተግባር አምርቶ ኢንቨስተሮች ፈቃድ ለማግ ኘት ሲሉ መደለያ እና ማግባቢያ ገንዘብ ለነቀዙ ባለስልጣናት ወይም ወኪሎች እንዲከፍሉ ሊገደዱ ይችላል፡፡