Font size: +
10 minutes reading time (2059 words)

የፍርድ ቤቶች በከፊል መዘጋት በማረምያ ቤት ከሚገኙ እስረኞች መብት አንጻር

የኮሮና (COVID-19) በሽታ አለም አቀፍ ችግር ሆኗል፡፡ በአለም ላይ ያሉ ሳይንቲስቶች በደረሱበት የምርምር ደረጃም በትክክል የሚተላለፍባቸው መንገዶች በሙሉ ተለይተው አይታወቁም፡፡ ነገር ግን በሽታው በሰዎች መካከል በሚኖር ቀጥተኝ (መጨባበጥ፤ መተቃቀፍ..) እና ቀጥተኛ ያልሆነ (አንድ ሰው የነካውን ግኡዝ ነገር ሌላ ሰው በመንካት …) አካላዊ ንክኪ እና የትንፋሽ ግንኙነት በቀላሉ የሚተላለፍ መሆኑ በትክክል ይታወቃል፡፡ ይህ ከሰዎች ባሕሪ ጋር በቀጥታ የተገናኘ የመተላለፍያ መንገዱ በሽታውን እጅግ አደገኛ እና አስፈሪ አድርጎታል፡፡ በሽታው ምንም አይነት ፈዋሽ መድሀኒት የሌለው መሆኑ እና ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍበት እና የሚሰራጭበት ፍጥነት በድምር ሲታይ ብሔራዊ ስጋት ተደርጎ እንዲወሰድ አድርጎታል፡፡ በበሽታው የተፈጠረው ብሔራዊ ስጋት ተራ ስጋት ሳይሆን ከፍተኛ እና ከባድ ስጋት ነው፡፡   

በሽታው ምንም አይነት ፈዋሽ መድሀኒት የሌለው ከመሆኑ አንፃር ያለው ብቸኛ መዳኛ መንገድ በበሽታው ላለመያዝ አስቀድሞ የሚደረግ የመከላከል ተግባራትን መፈፀም ብቻ ነው፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች ከበሽታው አስቀድሞ መከላከያ መንገዶች አድርገው በዋናነት የሚጠቅሷቸው ዘዴዎች አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እና ንፅህናን መጠበቅ ናቸው፡፡

አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የሚለው የመከላከያ ዘዴ ሰዎች በቤታቸው ተቀምጠው ራሳቸውን ከሌላው ሕብረተሰብ ከልለው እንዲቀመጡ ከማድረግ ጀምሮ በስራ፤ በትራንስፖርት እና በሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥም ቢያንስ የሁለት የትልቅ ሰው እርምጃ ርቀትን በማስጠበቅ እንዲንቀሳቀሱ እና አገልግሎት እንዲገኙ ማድረግን የግድ ይላል፡፡ ይህን በከተማ ብሎም በሀገር ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ እና ተግባራዊነቱን መከታተል እና መቆጣጠር ቀላል ተግባር አይደለም፡፡ በዚሕ መሀከል የሚፈፀም ትንሽ ስህተት ተቆጥሮ የማያልቅ የብዙ ሰዎችን ሕይወት የሚቀጥፍ ወይም አደጋ ላይ የሚጥል ውጤት ሊያስከትል ይችላል፡፡

የሕብረተሰብን ጤና መጠበቅ እና ከተላላፊ በሽታዎች የመከላከል ተግባር የመንግስት መደበኛ ስራ ነው፡፡ በዚሕ መሰረት የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 301/2006 አንቀጽ 5/2 መሰረት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ስጋቶችን አስቀድሞ የመለየት እና በቂ ዝግጅት በማድረግ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ በተገቢው ሁኔታ የመከላከል ሥልጣን እና ተግባር ተሰጥቶታል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 አንቀጽ 27 ንኡስ አንቀጽ 6 እና 7 መሰረት  የጤና ሚኒስቴርም ወረርሽኝ እና ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችሉ ስልቶችን የመቀየስ እና የሕብረተሰቡን ጤና ሊጎዱ የሚችሉ ሁኔታዎችን የመከላከል እርምጃዎችን የመውሰድ እንዲሁም ድንገተኛ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ አፋጣኝ እና ውጤታማ መፍትሔ የመስጠት ሥልጣን እና ተግባር ተሰጥቶታል፡፡

ከእነዚሕ ድንጋጌዎች በቀላሉ መረዳት እንደሚቻለው እንደ ኮሮና (COVID-19) ያሉ ተላላፊ በሽታዎችን በተመለከተ መንግስት የሕብረተሰብን ጤና ለመጠበቅ የሚከተለው ስትራቴጂ የሕብረተሰብን ጤና አደጋ ላይ ከሚጥሉ ስጋቶች የመከላከል ስልትን ማእከል ያደረገ ዘዴን ነው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ መንግስት የኮሮና (COVID-19) በሽታን የሕክምና ባለሙያዎች ምክረ ሀሳብን መሰረት ባደረገ ሁኔታ የመከላከል ስልትን ማእከል ያደረጉ የመከላከል ተግባራትን በሕብረተሰቡ እንዲፈጸሙ የማስተማር፤ የማሳወቅ እና እንደሁኔታው የማስገደድ ተግባራትን ማከናወኑ መደበኛ የመንግስት ስራውን እከናወነ መሆኑን ያሳያል፡፡ 

ነገር ግን የኮሮና (COVID-19) በሽታ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍበት እና የሚሰራጭበት ፍጥነት እጅግ ፈጣን (Exponential) በመሆኑ እና ይህን የአደጋ ስጋት ለማስወገድ የሚከናወነው የመከላከል ተግባር የሕብረተሰቡን መደበኛ ኑሮ የሚያናጋ እና ብዙ ውዝግቦችን የሚያስነሳ ከመሆኑ አንጻር እንዲሁም በሽታው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውስን ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ የመከላከሉ ተግባር በመደበኛ የመንግስት ስራ ሊከናወን የሚችል አይደለም፡፡  

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 መግቢያ ላይ ኮሮና (COVID-19) በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እየተሰራጨ እና ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለ ወረርሽኝ በመሆኑ እና በመደበኛ የመንግስት አሰራር ሥርዓት ስርጭቱን መከላከል እና መቆጣጠር የማይቻል ስለሆነ የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማውጣት አስፈላጊነት በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1189/2012 መፅደቁን ተከትሎ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 ማስፈፀምያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 456/2012 መግቢያው ላይ የደንቡን መውጣት አስፈላጊነት ሲገልፅ ደንቡ የወጣው የመከላከል ስራውን ለማከናወን አስፈላጊ የሆኑ የመብት እገዳዎችን እና እርምጃዎችን ለመወሰን መሆኑን ይገልጻል፡፡  

የኮሮና (COVID-19) በሽታን የመከላከል ተግባራት በተለይ በሕክምና ባለሙያዎች ከሚሰጡት ምክረ ሀሳቦች አንጻር ሲታይ የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚገድብ እና በእንቅስቃሴ ጊዜያትም ሰዎች በራሳቸው ፍላጎት ከሚጠቀሟቸው አልባሳት በተጨማሪ አስገዳጅ የሆኑ የፊት መሸፈኛ ማድረግን እና አካላዊ ርቀትን መጠበቅን አስገዳጅ የሚያደርጉ እንዲሁም እነዚሕን ጥንቃቄዎች በቀላሉ መፈፀም በማይቻልባቸው አካባቢዎች እንዳይገኙ ማስደደድን እና አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ የማያስችሉ አገልግሎት መስጫዎችን አገልግሎት እንዳይሰጡ መዝጋትን የሚጠይቅ በመሆኑ ይህን ለመፈጸም ሲባል በሕገመንግስቱ ሕጋዊ ጥበቃ ከሚደረግላቸው መሰረታዊ መብቶች ውስጥ የሚገደቡ መብቶች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ ምክንያት ብቻ በሕመንግስቱ የተረጋገጡ መብቶች በሙሉ የሚታገዱ አይደሉም፡፡ ይልቁንም የሚታገዱት መብቶች የትኞቹ እንደሆኑ እና በምን መጠን እንደሚታገዱ የሚወሰነው በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ መሆኑ በሕገመንግስቱ አንቀጽ 93/4 ሀ እና ለ መሰረት በግልጽ ተደንግጓል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸምያ በማውጣት በመሰረታዊ መብቶች ላይ ገደብ ለማድረግ ያለው ስልጣን ልቅ ወይም ያልተገደበ ስልጣን አይደለም፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ አዋጅ በመታወጁ ምክንያት ገደብ የሚደረግባቸው በሕገመንግስቱ የተረጋገጡ መብቶች የትኞቹ እንደሆኑ እና ገደብ የሚደረግባቸውም በምን መጠን እንደሆነ በሚወስንበት ጊዜ መመዘኛ አድርጎ ሊወስደው የሚገባው ዋናው ነጥብ የአስቸኳይ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ (ኮሮና በሽታን) ለማስወገድ አስፈላጊ የሆኑት ገደቦች የትኞቹ እንደሆኑ በመለየት እና የገደቡ መጠንም በዚሑ እሳቤ ምን ያሕል እንደሆነ በመወሰን ነው፡፡ እዚሕ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህን የመብት ገደብ ሲያደርግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ነገር ለማስወገድ ከሚያስፈልገው የመብት ገደብ በላይ ገደብ ቢያደርግ ይህን በምን መንገድ ማረም እና ማስተካከል ይቻላል የሚለው ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ይህ ጥያቄ ከዚሕ ፅሁፍ አላማ ውጭ ስለሆነ አንባቢ በራሱ መንገድ ምላሽ እንዲሰጠው በማድረግ አልፈንዋል፡፡

የኮሮና በሽታን የመከላከሉ ተግባር በዋናነት የሰዎች እንቅስቃሴን እና ግንኙነትን መገደብን ማእከል ያደረገ ነው፡፡ በዚሕም ምክንያት የኮሮና (COVID-19) በሽታን ለመከላከል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈጸም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚወጣው የማስፈጸምያ ደንብ ገደብ የሚያደርግባቸው መብቶች የበሽታውን ስርጭት ለማቆም ወይም ለመቀነስ በሚያስችል መጠን የሰዎች እንቅስቃሴን እና ግንኙነትን መገደብን ማእከል ያደረገ እና የእነዚሕ ገደቦችን ማስከበር እና ማስፈጸም የሚቻልበትን እንዲሁም ከገደቦቹ እና በበሽታው ከሚደርሱ ጉዳቶች ጋር በተያያዘ ሊፈጠሩ የሚችሉ ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶችን ለማስወገድ ወይም ለመቀነስ የሚቻልባቸውን ዝርዝር ጉዳዮችን የሚመለከት እንዲሆን ይጠበቃል፡፡  

በዚሕ መሰረት የኮሮና (COVID-19) በሽታን ለመከላከል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈጸም የወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 456/2012 የመብት ገደቦች መደረጉን እና የተገደቡት መብቶች ምን ምን እንደሆኑ በዝርዝር ይገልጻል፡፡ ገደብ የተደረገባቸው መብቶችም የተከለከሉ ተግባራት በሚል ርእስ ስር በደንቡ አንቀፅ 3 ንኢስ አንቀፅ 1 እስከ 27 ድረስ በተቀመጠ ዝርዝር ተገልጸዋል፡፡  

ከነዚሕ ገደብ የተደረገባቸው መብቶች ውስጥ የዚሕ ፅሁፍ አላማ የሆነው በማረምያ ቤት የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን እና ታራሚዎችን የሚመለከተው ክልከላ ነው፡፡

በማረምያ ቤት ያሉ እስረኞች የተከሰሱ እና የታሰሩ ሰዎች በመሆናቸው በሕገመንግስቱ አንቀጽ 20 ላይ ስለተከሰሱ ሰዎች የተገለፁት መብቶች እና በአንቀጽ 21 በጥበቃ ስር ስላሉ እና በፍርድ ስለታሰሩ ሰዎች የተገለፁት መብቶች ይመለከቷቸዋል፡፡ በሕገመንግስቱ አንቀጽ 20 መሰረት አንድ ተከሳሽ ሲከሰስ በመደበኛ ፍ/ቤት በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ በግልፅ ችሎት ጉዳዩ የመስማት መብት፤ በሕግ በተገለፀ ስርአት ጉዳያቸው በዝግ ችሎት መታየት ያለበት ካልሆነ በስተቀር በግልፅ ችሎት የመዳኘት፤ የክሱን ኮፒ የማግኘት እና የክሱን ዝርዝር የመረዳት፤ የቀረበበትን ምስክር የመጠየቅና የቀረበበትን ማስረጃ የማየት እንዲሁም የመከላከያ ማስረጃዎቹ እንደቀርቡለትና እንዲሰሙለት የመጠየቅ መብት አለው፡፡

ተከሳሹ መከራከሪያውንና መከላከያ ማስረጃውን እንዲያዘጋጅ እና በዚሕ ሒደት ውስጥ ከጠበቃው የሙያ ድጋፍና የምክር አገልግሎት እንዲያገኝ የማድረግ ፤ በፍርድ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ በተሰጠው ፍርድ ላይ ተፈፅሟል የሚለውን የሕግና የፍሬ ጉዳይ ስህተት በይግባኝ እንዲታረም የማድረግ መብት አለው፡፡ ከዚህ አንፃር ይግባኝ በወንጀል ጉዳዩች ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና የተሰጠው መብት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 21 መሰረት አንድ ሰው በእስር ላይ ባለበት ጊዜ ከትዳር ጓደኟው፤ ከቅርብ ቤተሰቡ፤ ከጓደኟው፤ ከሐይማኖት አማካሪው፤ ከሐኪሙ እና ከሕግ አማካሪው ጋር የመገናኘት እንዲሁም እንዲጎበኘው እድል የማግኘት መብት አለው፡፡

እነዚሕ መብቶች በሕገመንግስቱ የተረጋገጡ መብቶች በመሆናቸው ገደብ ሊደረግባቸው የሚችለው በሕገመንግስቱ በተገለፀው ስርአት ብቻ ነው፡፡ በሕገ መንግስቱ የተዘረጋው ብቸኛ ስርአት ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ ነው፡፡

ከዚሕ አንጻር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈፀም በወጣው ደንብ ቁጥር 456/2012 ላይ በማረምያ ቤት ያሉ ሰዎችን በተመለከተ የተደረገውን ገደብ ስንመለከት በደንቡ በተራ ቁጥር 9 ላይ “ማንኛውንም ታራሚን ወይም ተጠርጣሪን በአካል በመገኘት በማረምያ ቤት ወይም በፖሊስ ጣቢያ በመገኘት መጎብኘት ክልክል ነው፡፡” የሚለው ክልከላ ብቻ መደንገጉን እንረዳለን፡፡   

በዚሕ ደንብ መሰረት በማረምያ ቤት ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች እና ታራሚዎች ገደብ የተደረገባቸው ከቤተሰቦቻቸው፤ ከትዳር ጓደኞቻቸው፡ ከሐይማኖት አባቶቻቸው፤ እና ከሐኪሞቻቸው ጋር ለመገናኘት ባላቸው መብት ላይ ብቻ ነው፡፡ እስረኞች ከጠበቆቻቸው ጋር የመገናኘት መብታቸው አልተገደበም፡፡ ይልቁንም በደንቡ አንቀጽ 4/14 መሰረት የፖሊስ እና የማረምያ ቤት ተቋማት ታሳሪዎች ከጠበቆቻቸው ጋር የሚገናኙበትን ሁኔታ የማመቻቸት ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

ከዚሕ ውጭ ያሉ በማረምያ ቤት በእስር ላይ የሚገኙ እስረኞች በሕ መንግሰቱ ጥበቃ በሚደረግላቸው መብቶቻቸው በሙሉ ላይ ገደብ አልተደረገባቸውም፡፡ በተለይ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በተፋጠነ ሁኔታ እንዲታይላቸው ለማድረግ ያላቸው መብት በማናቸውም ሁኔታ አልተገደበም፡፡ ደንቡ እስረኞች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይ ለማድረግ ባላቸው መብት ላይ ገደብ ያላደረገ ከመሆኑ በተጨማሪ እንደ ፍርድ ቤት ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሰራተኞቻቸውም ሆኑ አገልግሎት ተቀባዮች አካላዊ ርቀቶቻቸውን እንዲጠብቁ በማድረግ እና ተጨማሪ ጥንቃቄ ተግባራትን በማከናወን አገልግሎቱ እንዲሰጥ የማድረግ ኃላፊነትን በመስርያቤቶቹ ኃላፊዎች ላይ የሚጥል በመሆኑ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ የፌደራል ማረምያ ቤት፤ እና ጠቅላይ ዐ/ሕግ ተቀናጅተው በመስራት እስረኞቹ አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው ጉዳያቸው እንዲታይ ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ የመፍጠር ኃላፊነት አለባቸው፡፡

አሁን ባለው እውነታ ግን በማረምያ ቤት ያሉ እስረኞች ፍርድ ቤቶች በከፊል በመዘጋታቸው ምክንያት የፍርድ ሒደታቸው በመጀመርያ ደረጃ ክርክር ደረጃም ሆነ በይግባኝ ደረጃ ታግዶ ይገኛል፡፡

የችሎቶች በከፊል መዘጋት በእስር ላይ ያሉ ሰዎች ክርክሮቻቸውን የማቅረብ፤ የቀረበባቸውን ምስክር የመስማት እና መስቀለኛ ጥያቄ የማቅረብ፤ የመከላከያ ምስክር የማሰማት፤ ማስረጃ የማቅረብ፤ ፍርድ የማግኘት እና ይግባኛቸውን የማሰማት እና የመከራከር ሕገመንግስታዊ ጥበቃ ያላቸው መብቶቻቸው መታገድን አስከትሏል፡፡ ፋይሎቻቸው እነሱም ሆኑ ጠበቆቻቸው በሌሉበት እንዲቀጠር እና ያለምንም የፍርድ ሒደት በእስር ላይ እንዲቆዩ አድርጓቸዋል፡፡ ይህን ከእስረኞች አንጻር ስንመለከተው ሊመለስም ሆነ በማናቸውም ሁኔታ ሊካስ የማይችል ከባድ ጉዳትን ያስከተለ ተግባር ነው፡፡

እነዚሕ መብቶች በማረምያ ቤት ያሉ እስረኞች ሕገመንግስታዊ መብቶች በመሆናቸው በሕገመንግስቱ መሰረት ገደብ ሊደረግባቸው የሚችለው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብቻ ከመሆኑ አንጻር የፍርድ ቤቶቹ መዘጋትን ከሕገመንግስቱ እና በሌሎች ሕጎች ከተሰጡ ስልጣኖች አንፃር መመርመር የግድ ያስፈልጋል፡፡  

በፍርድ ቤቶች ያለው የፍርድ ሒደት የታገደው ክብርት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መጋቢት 09 ቀን 2012 ዓ/ም እና መጋቢት 23 ቀን 2012 ዓ/ም በሰጡት “መግለጫ” ነው፡፡ መግለጫው በሕግ ያለው ደረጃ እና አስገዳጅነት ምንድን ነው የሚለው አከራካሪ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ፕሬዚዳንቷ በመግለጫው ላይ በግልጽ እንዳስቀመጡት ፍርድ ቤቶችን በከፊል የመዝጋት ውሳኔውን የሰጠው የፌደራል ፍርድ ቤቶች አመራር ነው፡፡

በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 የፌደራል ፍርድ ቤቶች አመራር የሚባል ግልጽ የሆነ በሕግ የተዘረጋ አደረጃጀት የለም፡፡ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 16 መሰረት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እና የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በጋራ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሰብሳቢነት የተለያዩ ውሳኔዎችን የሚሰጡበት አሰራር አለ፡፡ ከዚሕ በተጨማሪም በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 31 እና ተከታዮቹ መሰረት የተለያዩ ስልጣኖች ያሉት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባኤ የሚባል አደረጃጀት አለ፡፡ በነዚሕ በሁለቱም አደረጃጀቶች ችሎቶችን በከፊል ለመዝጋት ስልጣን የተሰጠው አካል የለም፡፡  

ፍርድ ቤቶች በከፊል የተዘጉት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሚያዝያ 08 ቀን 2012 ዓ/ም ከመታወጁ በፊት ከመጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ/ም ጀምሮ ነው፡፡ እዚህ ላይ የፍርድ ቤቶቹን መዘጋት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመታወጁ በፊት እና በኋላ ብለን ለይተን ብንምለከተው ሁለት ገጽታ ያለው መሰረታዊ ስህተት እናያለን፡፡

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመታወጁ በፊት ፍርድ ቤቶችን በከፊል የመዝጋቱ ተግባር በማረምያ ቤት ያሉ እስረኞች ባሏቸው መሰረታዊ እና ሕገመንግስታዊ ጥበቃ የሚደረግላቸው መብቶቻቸው ላይ ገደብ የሚያደርግ ተግባር ከመሆኑ አንፃር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባልታወጀበት ሁኔታ በእስረኞች ሕገመንግስታዊ መብት ላይ ገደብ የሚያደርግ ውሳኔ መስጠቱ ከሕገመንግስቱ ጋር የሚጣረስ ተግባር ሆኖ እናየዋለን፡፡

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላም ሕገመንግስታዊ ጥበቃ በሚደረግላቸው መብቶች ላይ ገደብ የተደረገባቸው መብቶች የትኞቹ እንደሆኑ እና በምን መጠን ገደብ እንደተደረገባቸው የሚወሰነው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ ብቻ መሆኑ እየታወቀ እና በዚሕ መሰረት የወጣው ደንብ በእስረኞቹ የመዳኘት እና የፍርድ ሒደት መብት ላይ ገደብ አለማድረጉ ግልፅ ሆኖ ባለበት ሁኔታ በደንቡ ገደብ ባልተደረገባቸው መብቶች ላይ በራስ ስልጣን ገደብ አድርጎ ታራሚዎች ያላቸውን ሕገመንግስታዊ ጥበቃ በሚደረግላቸው መብት እንዳይጠቀሙ ማገድም መሰረታዊ ስህተት ነው፡፡

የችሎቶች በከፊል መዘጋት የበሽታውን ሥርጭት ለመከላከል ወይም ለመገደብ ከሚኖረው ጥቅም አንፃርም ሊመዘን እና ሊመረመር ይገባል፡፡ ከዚሕ አንጻር ችሎቶች በከፊል የተዘጉበትን ምክንያት ስንመለከት ትክክለኛውን መረጃ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መግለጫ ላይ በቀላሉ ማየት ይቻላል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለችሎቶቹ በከፊል መዘጋት ምክንያት ያደረገው የኮሮና (COVID-19) በሽታ ለመከላከል በሕክምና ባለሙያዎች የተሰጠው ምክር አካላዊ መራራቅን የሚጠይቅ በመሆኑ እና አሁን ባሉት ችሎቶች ይህን የሕክምና ባሙያዎች ምክር ማስጠበቅ የማይቻል መሆኑን ነው፡፡ ፀሐፊው ለሁሉም ችሎቶች በቂ ግንዛቤ ያለው በመሆኑ የጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራሮችን ስጋት ምክንያታዊ ስጋት መሆኑን በትክክል ይገነዘባል፡፡

ነገር ግን የጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራሮች የእስረኞችን ሕገመንግስታዊ መብት ከማገድ በተሻለ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም ወይ የሚለውን ማየት ተገቢ ነው፡፡ በኮሮና (COVID-19) ምክንያት የተፈጠረው ችግር አካላዊ ርቀቶችን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአንድ ችሎት ውስጥ የሚገቡት ተከሳሾች መጠን እና አቀማመጣቸውን እንዲሁም የዳኞችን አቀማመጥ በማስተካከል በቀላሉ ሊፈታ የሚችል ችግር ነው፡፡ በተለይ አብዛኛዎቹ የፍትሐ ብሔር ችሎቶች በተመሳሳይ ዝግ በመሆናቸው እነዚሕን አዳራሾችም መጠቀም ይቻላል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ፍርድ ቤቶቹ በከፊል ከመዘጋታቸው በፊት ባሉት ቀናት በዚሕ ሁኔታ አስተናግዶናል፡፡ ይህን ተሞክሮ በመውሰድ እና ሁሉም ችሎቶች ይህ ተሞክሮ የጎደለውን ሞልተው እና አስተካክለው ከችሎታቸው ልዩ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣምም አድርገው የፍርድ ሒደቱን በማስቀጠል የእስረኞችን ችግር በቀላሉ መፍታት ይቻል ነበር፡፡

ሌላው እና ፈፅሞ ትኩረት የተነሳው ነጥብ በኮሮና (COVID-19) ምክንያት የፍርድ ሒደቱ ተቋርጦ አንድን ሰው በእስር ላይ እንዲቆይ የማድረግ ተግባር ሕጋዊነት ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ሰው በእስር ላይ እንዲቆይ ከተደረገ ከእርሱ ፈቃድ ውጭ ብዙ መብቶቹ በሕግ ወይም በፍርድ ቤት ትእዛዝ ተገድበው የሚገኙ በመሆኑ የተፋጠነ ፍርድ የማግኘት መብቱ ሊከበርለት ይገባል፡፡ ከዚሕ አንፃር የአንድን እስረኛ የፍርድ ሒደት አግዶ ያለምንም የፍርድ ሒደት በእስር እንዲቆይ ማድረግ በማናቸውም መመዘኛ ሕጋዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህን ከኮሮና (COVID-19) በሽታን ስርጭት ለመከላከል ከሚከናወን ተግባር አንጻር ስንመለከተውም የፍርድ ሒደቱን ከማገድ ውጭ ያሉ የመፍትሔ አማራጮችን መከተል እየተቻለ በእስረኛው ላይ ሊመለስ እና ሊካስ የማይችል የፍርድ ሒደትን የማገድ አማራጭ መከተል ፍትሐዊ አይሆንም፡፡  

በማናቸውም ምክንያት ይህ በሽታ እስኪወገድ ድረስ የፍርድ ሒደቱን ማስቀጠል የማይቻል ከሆነ ለዚሑ ልዩ ሁኔታ አግባብነት የሚኖረውን ሕግ በማውጣት ወይም የጠቅላይ ዐ/ሕግ ስልጣንን በመጠቀም የበሽታው መወገድ እስኪረጋገጥ ድረስ ክሱን በማቋረጥ እስረኞቹ ከእስር እንዲለቀቁ ማድረግ እና በሽታው መወገዱ ሲረጋገጥ ወደ ነበሩበት ሁኔታ ተመልሰው የፍርድ ሒደታቸው የሚቀጥልበትን ሁኔታ በመፍጠር እና ለዚሕም እስረኞቹ ተገቢውን ዋስትና እንዲሰጡ በማድረግ ከእስር በመልቀቅ የበሽታውን ስርጭት መከላከልም ሆነ የእስረኞችን መብት ማስከበር ይቻላል፡፡  

በአጠቃላይ በአንድ በኩል የኮሮና (COVID-19) በሽታ ስርጭትን የመከላከል ተግባርን በሌላ በኩል ደግሞ የእስረኞችን ሕገመንግስታዊ መብትን አክብሮ ማስከበርን ሚዛን ላይ አስቀምጦ በማየት የእስረኞች መብት በተከበረበት እና በእስረኞች መብት ላይ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስ የኮሮና (COVID-19) በሽታን መከላከል የሚቻልበትን ፍትሐዊ የመፍትሔ አማራጭ ተግባራዊ ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡   

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

The New Investment Proclamation No. 1180/2020: A B...
አንዳንድ ጉዳዮች ስለ ሕገ-መንግሥት እና ፍርድ (ትርጉም)

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Sunday, 08 September 2024