Font size: +
8 minutes reading time (1664 words)

ማቀባበል (Facilitating Act of Bribery)

(ለጉቦኞች አይላላኩ፤ ከተላኩ ዘብጥያ ይላካሉ!)

ይህ አጭር ጽሑፍ በማወቅም ባለማወቅም የወንጀል አድራጊዎች ተልእኮ የሚያስፈጽሙ ሰዎች እንዲጠነቀቁ ለማስቻል በግርድፉ የቀረበ ነው፤ ጥልቀት ያለው ትንተና እንዳይጠብቁ። ጽሑፉ ሰዎች የቆሸሸ ገንዘብ የሚያቀባብሉበት እጃቸው፣ እንዲሁም የጉቦኞች የገንዘብ መላላኪያ የሚያደርጉት የባንክ ሂሳብ ቁጥራቸው አደገኛ መዘዝ ይዞባቸው እንዳይመጣ ሊጠነቀቁ ይገባል የሚል መልእክት ለማስተላለፍ፣ ምናልባትም ለማስጠንቀቅ የቀረበ የሕጉ አጭር መግለጫ ነው። ለሕግ ሙያተኞች ፈጽሞ ጥቅም የለውም ማለት ባይቻልም ዓይነተኛ ጥቅሙ ግን ከሙያው ዓለም ውጪ ላለው ለተራው ማኅበረሰብ ነው። ጽሑፉ ስለማቀባበል የሙስና ወንጀል ውስን የግንዛቤ ማስጨበጫ ነጥቦችን በመያዝ ተዘጋጅቷል። ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንምና ይነበብ።

ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና ባሕላዊ መስተጋብሮችን የሚያቀላጥፉ ሕጋዊ ደላሎች እንዳሉ ሁሉ የአንድ ማሕበረሰብ ሰላማዊ ኑሮን የሚያውኩ የመንግሥትና የሕዝብ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅምን የሚጎዱ ሕገ ወጥ ደላሎችን ማየትም የተለመደ ነው። በጉቦ መሥጠት ሆነ መቀበል ወንጀል ውስጥም አቀባባዮች የሚባሉ ሦስተኛ ወገኖች አሉ፤ የጉቦ ተላላኪዎች። እነዚህ ሦስተኛ ወገኖች 'የወንጀል ደላሎች' ወይም 'የጉቦ ወኪሎች' ብለን ልንጠራቸው እንችላለን። የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 27፣ እነዚህን 'የጉቦ ወኪሎች' 'አቀባባዮች' በማለት ይሰይማቸዋል።

 

በመርሕ ደረጃ አቀባባዮች ከሌላ ሰው ጉቦ ወይም ጥቅም ተቀብለው ለሌላ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ የሚያስተላልፉ ናቸው። ይሁንና ጉቦ ሰጪ ከሚባለው ግለሰብ ገንዘብ ወይም ሌላ ማንኛውም ጥቅም ሳይቀበሉ ለዚሁ ግለሰብ ጥቅም ሲባል ከራሳቸው ኪስ አውጥተው ለጉቦ ተቀባይ ሊሰጡ ይችላሉ። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እነዚህ ግለሰቦች ጥቅሙን በቀጥታ ለራሳቸው ለማዋል በማሰብ ባይሆንም በራሳቸው ፍላጎት ከእነ ሙሉ እውቀታቸው በድርጊቱ ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ከተገኙ ጉቦ ሰጪውና ጉቦ ተቀባዩ የሃሳብ አንድነትና ጥምረት እንዲፈጥሩ የሚያደርጉ የጉቦ ደላላዎች በመሆናቸው 'የጉቦ ተወካዮች፣ 'ተላላኪዎች፣' 'አቀባባዮች፣' 'አስተላላፊዎች' ወይም 'አገናኞች' የሚል ስያሜ ማግኘታቸው ትክክል ይሆናል።

 

እነዚህ 'አቀባባይ' ግለሰቦች የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ እንዲሆኑ የግድ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ይሁንና እነዚህ አቀባባዮች የሕዝብና የመንግሥት ጥቅም የሚነካ ስራ የሚሰሩ በመሆናቸው በሙስና ወንጀል እንዲጠየቁ ማድረጉ አስፈላጊ ነው፡፡ በጉቦ ወንጀል ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች ማለትም ጉቦ ሰጭ እና ጉቦ ተቀባይ መሳተፋቸውን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሚያቀባብሉ ሌሎች ሦስተኛ ወገኖችም ተገኙ ማለት ነው፡፡

 

የተለያዩ ሀገራት አቀባባዮች ልክ የጉቦ ሰጪና ተቀባይ ያህል አደገኞች በመሆናቸው በሙስና ወንጀል ሊጠየቁ ይገባል በሚል እሳቤ በሕጎቻቸው ላይ እንዲካተቱ አድርገዋል። በተቃራኒው በመሀል ሆነው የሚያቀባብሉ ወይም ለጉቦ መሰጣጠት ሂደቱን የሚያመቻቹ ሰዎች በሙስና ወንጀል ተጠያቂ የሚያደርግ የሙስና ወንጀል ሕግ ወይም ድንጋጌ የሌላቸው ሀገራት አሉ። ወደ ኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ስንመጣ፣ አቀባባዮች በሙስና ወንጀል ይጠየቃሉ። በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት የማቀባበል ወንጀልን ለመጀመርያ ጊዜ በወንጀልነት የተፈረጀው በኢፌድሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 429 ላይ ሲሆን ድንጋጌው ከእስራኤል ሕግ በቀጥታ የተወሰደ ነበር።[1]

 

አቀባባዮች በጉቦ ሰንሰለት ውስጥ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታሉ። እከሌን አውቀዋለሁ፤ እኔ ጉዳይህን እጨርሳለሁ፣ በአቋራጭ እንጂ በሕግ ጠብ የሚልልህ አንድም ነገር ስለማይኖር በሌላ መንገድ አስተዋውቃሃለሁ፤ አገናኝሃለሁ በማለት ትክክለኛውን አሰራር የሚያዛቡ፤ ፍትሕን እንዲጓደል ግንባር ቀደም ሆነው የሚሰሩ አገናኝ ሰዎች በየትኛውም የመንግሥት ተቋማትና አገልግሎት ሂደት ውስጥ አዘውትረን የምናገኛቸው ናቸው።ስለዚህም በጉቦ ሰጪና ተቀባይ መካከል እንደ ድልድይ ሆነው የሚያገለግሉት እነዚህን ሰዎች መቅጣት አስፈላጊ ነው።[2]

 

በኢፌድሪ የሙስና ወንጀሎች ሕግ አዋጅ ቁጥር 881/2007 መሰረትም በጉቦ ሰጪና በጉቦ ተቀባይ መካከል መሰላል ሆነው የሚያገለግሉ ሕገ ወጥ ደላሎችን ጨምሮ በማንኛውም መንገድ የጥቅም መቀያየርን የሚያቀላጥፉ፣ የሚያመቻቹና የሚያገናኙ ግለሰቦችን በሙስና ወንጀል ተጠያቂ ናቸው።በዚሁም መሰረት ለመንግሥት ወይም ለሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ የሚሰጥ ጉቦን፣ ዋጋ ያለውን ነገር፣ ጥቅም ወይም ሌላ አገልግሎት መቀበል ወይም የእራስን አካውንት ለእንደዚሁ ዓይነት ተግባር ለማቀባበያነት ማዋል ወይም ሁኔታዎችን ማመቻቸትና መደለል ሕገ ወጥ ነው። ከላይ በጠቀስነው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 27 ላይ ስለአቀባባዮች ተከታዩን ድንጋጌ እናገኛለን።

 

"ማንኛውም ሰው ለራሱ ማናቸውንም ዓይነት ጥቅም ባያገኝም እንኳ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሥራን ለሚያከናውን ሰው ጉቦ ለመስጠት ገንዘብ፣ ዋጋ ያለው ነገር፣ አገልግሎት ወይም ሌላ ዓይነት ጥቅም ከሌላ ሰው የተቀበለ እንደሆነ፤ ወይም የራሱን የባንክ ሂሳብ እንደዚህ ዓይነት ጉቦ ለማቀባበል ያዋለ እንደሆነ፤ ወይም ጉቦ እንዲሰጣጡ ሁኔታዎችን ያመቻቸ፣ ያገናኘ፣ ያስማማ ወይም የደለለ እንደሆነ፤ እንደነገሩ ሁኔታ በቀላል እስራት እና በመቀጮ፣ ወይም ከሦስት ዓመት እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከሦስት ሺህ ብር እስከ አሥር ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡"[3]

 

ማቀባበልን አንዳንዶች እንደ ገቢ ማስገኛ የሚያከናውኑት የድለላ ስራ ሲሆን ይህ ድንጋጌ ግን ገንዘብ ለራሱ ሳይቀበል ይህን ተግባር የሚፈጽም ሰው ጭምር ለመቅጣት ያገለግላል። ስለሆነም ወንጀል አድራጊው ገንዘቡን ከሌላ ሰው ተቀብሎ ወይም የራሱን የባንክ ሂሳብ እንደዚህ ዓይነት ጉቦ ለማቀባበል በማዋል ድርጊቱን የሚፈጽመው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

 

ከዚህ ጋር ተያይዞ ማንኛውም ሰው በወንጀል የተከሰሰውን ሌላውን ሰው ከወንጀል ተጠያቂነት ለማስመለጥ ካለው ፍላጎት ከወንጀል አድራጊው 5,000 (አምስት ሺህ) ተቀብሎ ጉዳዩን ሲከታተለውና በወንጀል አድራጊው ላይ ክስ ለመመስረት በዝግጅት ላይ ለነበረው ዓቃቤ ሕግ ገንዘቡን ያቀባበለ እንደሆነ፣ ድርጊቱ የጉቦ ማቀባበል ወንጀልን የሚያቋቍም ተግባር ነው ሲል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅጽ 13፣ በሰ/መ/ቁ 78793 ላይ የሰጠውን አስገዳጅ ትርጉም ከነሙሉ ይዘቱን መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡[4]

 

ስለዚህም በጉቦ መቀበል ሆነ በጉቦ መስጠት ወንጀል ውስጥ አቀባባዮች የሚባሉ ሦስተኛ ወገኖች በተጨባጭ መሳተፍ የሚችሉበት ዕድል መኖሩን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ ከሰጠው ውሳኔ መገንዘብ ይቻላል ማለት ነው፡፡ በተለይም ጉቦ የሚቀበሉ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች ጉቦውን በቀጥታ ራሳቸው ከተቀበሉ በሕግ ቁጥጥር ስር የመዋልና የመያዝ እድላቸው እንደሚሰፋ ስለሚገነዘቡ ጉቦውን በሦስተኛ ወገን በኩል እንዲደርሳቸው ማመቻቸትን ይመርጣሉ፡፡

 

ጉቦ ሰጪዎችም ቢሆኑ ጉዳያቸው ለያዘላቸው የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ በቀጥታ ጉቦውን ከሰጡ ፍትሕን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት መንግሥታዊ ወይም ሕዝባዊ አገልግሎት በገንዘባቸው እየገዙ መሆናቸውን እንዲነቃባቸው ስለማይፈልጉ በአቀባባይ በኩል በተዘዋዋሪ መስጠትን ሊመርጡ ይችላሉ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ጉቦ ሰጪም ሆነ ጉቦ ተቀባይ ሳያምኑበት አቀባባዮች በራሳቸው ወትዋችነት፣ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ወይም ፍላጎት የጉቦ መሰጣጠት ሂደትን ሊያመቻቹ ወይም ሊያቀላጥፉ ይችላሉ፡፡

 

ከላይ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቀባባዮችን አስመልክቶ የተሰጠው ውሳኔ ስንመለከተውም፣ የጉቦ ወንጀሉን የተፈፀመው በዓቃቤ ሕጉ አነሳሽነትና መልካም ፈቃድ ሳይሆን አቀባባዩ በወንጀል ሲፈለግ ከነበረው ጉቦ ሰጪው ጋር በመነጋገርና በመተማመን ጉቦውን ተቀብሎ ክስ የማቅረብ ሥልጣንና ኃላፊነት የነበረበት ከሳሽ ወገን ዓቃቤ ሕግን በማሳመን፤ ውሳኔው ላይም ተጽዕኖ በማሳደርና ፍትሕን በገንዘብ ለመግዛት ጥረት ማድረጉን ግንዛቤ ወስደናል።

 

ስለዚህም ለድርጊቱ መፈጸም መሰረት የሆነው ዋናው ነገር ሌላውን ሰው ከሕግ ተጠያቂነት ለማዳን ስለመሆኑ ከተረጋገጠ አቀባባዩ ከሕግ ተጠያቂነት እንዲያመልጥ ከተፈለገው ግለሰብ ገንዘብ ስለመቀበሉ ያለመረጋገጡ የጉቦ ማቀባበል ድርጊትን አያቋቁምም ወደሚለው መደምደሚያ መድረስ አይቻልም። ይልቁንም ዋናውን መታየት ያለበት የድርጊት ፈጻሚው ፍላጎት (Motive) ነው። መሰረታዊ ነገሩ በወንጀል የሚታደወንን ሰው በሕግ እንዳይጠየቅ ከመነጨው ፍላጎት ሕገ ወጥና የሚያስቀጣ ድርጊት እያወቀ ያደረገ ስለመሆኑ በማስረጃ ማረጋገጥ ነው።

 

ከፍ ሲል እንደተገለጸው፣ ጉቦን የሚያቀባብሉ ሦስተኛ ወገኖች የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ እንዲሆኑ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ አይደለም፡፡ ይሁንና አቀባባዮች ሆነው የሚሰሩ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች አይኖሩም ማለት አይደለም፡፡ አቀባባዮቹ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ አይደሉም ሲባል ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም ማለት እንጂ ከጉዳዩ ጋር ባልተያያዘ በሌላ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ተቀጥረው የሚሰሩ ከሆነ በአቀባባይነት ሊጠየቁ አይችሉም ማለት አይደለም፡፡

 

ስለሆነም የጉቦው ምክንያት ከሆነው ጉዳይ ጋር ምንም ዓይነት የስራ ግንኙነት የሌላቸው ተራ ሰዎች የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች ባለመሆናቸው በጉቦ መቀበል ወንጀል በቀጥታ ባይከሰሱም በድርጊታቸው ግን የሕዝብ ጥቅም የሚመለከት ስራ የሚሰሩ በመሆናቸው ሊጠየቁ ይገባቸዋል።

 

በሌላ አነጋገር በመሀል ሆነው የሚያቀባብሉ ወይም ለጉቦ መሰጣጠቱን የሚያመቻቹ ሰዎች የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች ሆኑም አልሆኑም በሙስና ወንጀል ተጠያቂ ናቸው፡፡ ይሁንና የጉቦው ምክንያት ከሆነው ጉዳይ ጋር ተያይዞ ኃላፊነት ያለባቸው የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች ሆነው የማቀባበል ስራ የሰሩ እንደሆነ ጉቦውን ከተቀበለው የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ጋር በዋና ወንጀል አድራጊነትና ተካፋይነት በጉቦ መቀበል የሙስና ወንጀል በእኩል ይከሰሳሉ እንጂ በማቀባበል የሙስና ወንጀል ለብቻቸው የሚከሰሱበት ምክንያት አይኖርም፡፡

 

በሌላ በኩል፣ ከፍ ሲል እንደተገለጸው፤ በጉቦ ተቀባዮችና ሰጪዎች መካከል አቀባባዮች የሆኑ ሰዎችን በማቀባበል ወንጀል ለመጠየቅ ጥቅም አግኝተዋል ወይስ አላገኙም ወደሚለው መለኪያ መሄድ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ጉቦ መስጠትም ሆነ ጉቦ መቀበል ትክክለኛ ፍትሕን በማዛባት፣ እኩልነትንና የሕግ የበላይነትን በመናድ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ በመሆናቸው እነዚህን ወንጀሎች እንዲፈጸሙ የሚያቀላጥፍ፣ የሚያመቻች ወይም የሚያስፈፅም ማንኛውም 'የጉቦ ወኪል' ወይም 'የሕገ ወጥ ጥቅም አቀባባይ' ለራሱ ጥቅም ባያገኝም እንኳን በመንግሥት፣ በሕዝብና በሌሎች ግለሰቦች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ግን ጉቦውን ከሚቀበለውና ከሚሰጠው ጋር ተለይቶ ሊታይ አይችልም።

 

የሙስና ወንጀል መሰረታዊ ዓላማ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ሕገ ወጥ ጉዳትንም ለመከላከል ጭምር መሆኑን ሊሰመርበት ይገባል። ስለዚህም ማንኛውም ሰው ጉቦ ከአንድ ጉቦ ሰጪ ተቀብሎ ለአንድ ጉቦ ተቀባይ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛን ለመስጠት በማሰብ ዋጋ ያለውን ነገር፣ ጥቅም ወይም ሌላ አገልግሎት መቀበል ወይም የእራስን አካውንት ወይም የሂሳብ ቁጥር ለማቀባበያነት ማዋል ወይም ሁኔታዎችን ማመቻቸትና መደለል፤ ወይም ከጉቦ ሰጪው በቀጥታ ጥቅሙን ባይቀበልም እንኳን ለአንድ ተመሳሳይ ዓላማ ከራሱ ኪስ አውጥቶ ለጉቦ ተቀባዩ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛን መስጠት ራሱ የቻለ የማቀባበል የሙስና ወንጀል ማቋቋሚያ ፍሬ ነገር በመሆኑ ይህ አቀባባይ ያገኘሁት ጥቅም ስለሌለ ክስ ሊቀርብብኝ አይገባም የሚል መከላኪያ ማቅረብ አይችልም።

 

ይሁንና አቀባባዩ ወይም የጉቦ ወኪሉ ይህን የማቀባበል ተግባር የፈፀመው እያወቀ መሆን አለበት፡፡ የማቀባበል ወንጀል በቸልተኝነት አያስቀጣም፤ ሕጉ ማቀባበሉ በቸልተኝነት ከተፈጸመ ወንጀል ነው በማለት የደነገገው ነገር የለም። ለምሳሌ አንድ ሰው ከእውቅናው ወይም ከፈቃዱ ውጪ የቅርብ ዘመዱ፣ ጓደኛው ወይም የሚያውቀው ሌላ ማንኛውም ሰው በጉቦ የሚቀበለውን ገንዘብ ወደ አካውንቱ እንዲገባለት ያደረገ እንደሆነ ወይም ጉቦውን የሚሰጠው ሰው ወደ ተቀባዩ ሂሳብ ቁጥር በቀጥታ ሳይሆን ወደዚሁ አቀባባይ ግለሰብ ሂሳብ ቁጥር ውስጥ እንዲያስገባ ጉቦ ሰጪውን በነገረው መሰረት የገባለት እንደሆነ ግለሰቡ በማቀባበል የሙስና ወንጀል ለመክሰስና ለማስቀጣት ሕጋዊ፣ ምክንያታዊ እና ፍትሐዊ አይሆንም።

 

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ግለሰቡ የባንክ ሂሳብ ቁጥሩን እያወቀ ወይም ሆነ ብሎ ለጉቦ ማቀባቢያ ዓላማ እንዲውል የፈቀደ ስለመሆኑ በማስረጃ የማረጋገጥ ግዴታ አለበት፡፡ ዓቃቤ ሕግ በመርሕ ደረጃ ማንኛውም ዓይነት የወንጀል ክስ ሲያቀርብ በኢፌድሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 23(2) ላይ የተመለከቱትን ሕጋዊ፣ ግዙፋዊና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተው የተገኙ ስለመሆናቸው የማረጋገጥ ሕጋዊ ግዴታና ሃላፊነት እንዳለበት ይታወቃል። ወደ ማቀባበል የሙስና ወንጀል ስንመለስ፣ የማቀባበል ተግባር የፈጸመ ማንኛውም ሰው ለራሱ ጥቅም ስለ ማግኘት አለማግኘቱ ወንጀሉን በማቋቋም ወይም በማስቀረት ረገድ ተጽእኖ አይኖረውም። ማቀባበሉ እያወቀና በራሱ ሙሉ ፍላጎት ስለመፈጸሙ በማስረጃ ከተረጋገጠ ጥቅም አገኘ ወይስ አላገኘም ወደሚለው መመዘኛ መሄድ አስፈላጊ አይደለም። ይሁንና የማቀባበል ተግባሩ የፈጸመው እያወቀና ፍላጎትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ማረጋገጥ ካልቻለ በማቀባበል የሙስና ወንጀል ለመጠየቅ የሚቻል አይደለም። አቀባባዩ ጉቦ ተቀባይና ጉቦ ሰጪ ጉቦ እንዲሰጣጡ ሁኔታዎችን ያመቻቸ፣ ያገናኘ፣ ያስማማ ወይም የደለለ እንደሆነ የሚለውን የሕጉ አነጋገር ከድርጊቱ ራሱ ለማረጋገጥ ቀላል በመሆኑ የወንጀል አድራጊው የሃሳብ ክፍል በማስረዳት ረገድ የሚያጋጥም ፈተና ላይኖር ይችላል። ይሁንና ዓላማው ምን እንደሆነ ሳይታወቅ የገንዘብ ማቀባበል ድርጊት የፈጸመ ወይም የሂሳብ ቁጥሩ ለእንደዚሁ ዓይነት ዓላማ የዋለ እንደሆነ ይህ ተግባር ለምን እንደፈጸመው በማስረጃ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

 

ለምሳሌ አንድ ሰው አንድ የቅርብ ጓደኛው ብድር ተበድሬ ነበርና ለእከሌ አድርስልኝ ብሎ እንዲያደርስለት የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ በእምነት አስረክቦት ብድር ነው በሚል ግምት ይህን ገንዘብ ለተባለው ሰው ቢያደርስ በማቀባበል ወንጀል እንዲከሰስና እንዲቀጣ ማድረግ ተገቢ አይደለም። በተጨማሪም በሂሳብ ቁጥሩ ውስጥ ገንዘብ የገባለት ሰው የጉቦ ውጤት ቢሆንም እንኳን ይህ የጉቦ ውጤት የሆነው ገንዘብ የገባለት ግን ከራሱ እውቅና ውጪ ከሆነ በማቀባበል ወንጀል መክሰስና መቅጣት የሕጉን መንፈስ የተከተለ አይሆንም። ግለሰቡ ንጹሕነቱን እንዲያስረዳ የማይገደድ በመሆኑ ዓቃቤ ሕግ የማቀባበል ተግባሩን የተፈጸመው ወይም ሂሳብ ቁጥሩን ለማቀባብያ ዓላማ እንዲውል የተደረገው ተከሳሹ እያወቀ መሆኑ የሚያስረዱ አመላካች ወይም ፍንጭ ሰጪ ማስረጃዎች ሳይይዝ ክስ መመስረት የለበትም፡፡

 

በተጨባጭ ሁኔታም የባንክ ሂሳብ ቁጥሬን ለዚሁ ዓላማ ስለመዋሉ አላውቅም ነበረ የሚል መከላኪያ ማስረጃ በማቅረብ በነፃ የሚለቀቁ ተከሳሾች ብዙ ናቸው፡፡ በዚሁም ምክንያት ዓቃቤ ሕግ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 27 ን በመጥቀስ የሚመሰርተው ክስ እጅግ አናሳ ነው።

 

[1] የኢፌድሪ የተሻሻለው ወንጀል ሕግ ሐተታ ዘምክንያት ቁጥር 429

[2] ዝኒ ከማሁ፣ የወንጀል ሕግ ሐተታ ዘምክንያት

[3] የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 27

[4] የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ፣ቅጽ 13፣ ሰ/መ/ቁ 78793፣ ሰኔ 21 ቀን 2004፣ ከገፅ 320-323 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በኢትዮጵያ ስላሉ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች አንዳንድ ጉዳዮች
ተገዶ የመያዝን ሕጋዊነት ለማጣራት የሚቀርብ ክስ (Habeas corpus) እና ...

Related Posts

 

Comments 1

Abebe
Guest - tarhibit (website) on Monday, 05 December 2022 07:52

nice!

nice!
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 18 September 2024