ጸሐፊው በሚከታተለው አንድ የንግድ ችሎት ጉዳይ ጠበቃው የችሎቱን ዳኛ ያማርራል፡፡ የዳኛውን የችሎት አካሄድ እየተቸ በዕለቱ በሰጠው ፍርድ ጠበቃው ለጉዳዩ ጠቃሚ የሆነውን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ የሕግ ትርጉም የችሎቱ ዳኛ በፍርዱ አለማካተቱ፣ ለጉዳዩ አግባብነት ያለው መሆኑንና ይዘቱንም በፍርዱ ለማንፀባረቅ ፈቃደኛ አለመሆኑ እጅጉን አንገብግቦታል፡፡ እንደ ጠበቃው አነጋገር ‹‹ከሳሾች ባቀረቡት ክስ ለጉዳዩ አግባብነት ያለውን የሰበር ችሎት ቅጹን፣ የመዝገብ ቁጥሩንና ቀኑን አመልክተን አቀረብን፣ በቃል ክርክርም ይህንኑ በአጽንአት እንዲመዘገብልን አመለከትን፤›› ይላል፡፡ ውጤቱን ሲገልጽ ደግሞ ዳኛው በፍርዱ ሀተታውም ሆነ ትንታኔ የሰበር ችሎቱን ፍርድ አልገለጸም፣ የሰጠውም ፍርድ ሰበር ችሎቱ ከሰጠው አስገዳጅ ትርጓሜ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ በይግባኝ ከማሳረም ውጭ አማራጭ እንደሌለው ተናገረ፡፡
ከሰኔ 1997 ዓ.ም. ጀምሮ በአገራችን የሰበር ችሎት የሚሰጠው ትርጉም በሥር ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅ መሆኑ በሁሉም የሕግ ባለሙያዎች ዳኞችን ጨምሮ የታወቀ ነው፡፡ በተግባር ግን ጠበቃው የገጠመውን ዓይነት የፍርድ ቤቶች ልማድ ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡ አፈጻጸሙን በተመለከተ ግን አሁንም ያልጠሩ ወይም የማይፈጸሙ አሠራሮች መኖራቸውን የጠበቃው ተሞክሮ ያሳያል፡፡ ለመሆኑ የሥር ፍርድ ቤት ዳኞች የሰበር ሰሚ ችሎት የሰጣቸውን አስገዳጅ ፍርዶች ማወቅ (Judical notice መውሰድ) ይጠበቅባቸዋልን? የሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ፍርዶች ባልታተሙበት ሁኔታ አስገዳጅነት አላቸውን? አንድ የሥር ፍርድ ቤት ዳኛ የሰበር አስገዳጅ ፍርድ ተጠቅሶላት የማይቀበልበት ሁኔታ ይኖራልን? አስገዳጅ የሰበር ትርጉምን ወደ ጎን ማድረግ፣ አለመቀበል ወይም ከተሰጠው ትርጉም ተቃራኒ የሆነ ፍርድ መስጠት ዳኞችን በሥነ ምግባር አያስጠይቃቸውምን? የሚሉት ነጥቦች ምላሽ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ እነዚህን ነጥቦችና ከሰበር ችሎት ፍርድ አስገዳጅነት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ነጥቦችን ለማንሳት እንሞክራለን፡፡
አዋጅ ቁጥር 454/97 ዓላማውና ይዘቱ
ይህ አዋጅ በአንቀጽ 4 ላይ ‹‹የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ችሎት የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኝ የፌዴራል ወይም የክልል ፍርድ ቤት ላይ አስገዳጅነት ይኖረዋል፡፡ ሆኖም የሰበር ችሎቱ በሌላ ጊዜ በተመሳሳይ ጭብጥ የተለየ ትርጉም ሊሰጥ ይችላል፤›› ሲል ይደነግጋል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የሥር ፍርድ ቤቶች ሰበር ችሎቱ የሰጠውን የሕግ ትርጉም የመከተል፣ የመተግበር ግዴታ አለባቸው፡፡