በሀገራችን እጅግ አሳሳቢ እና አነጋጋሪ ከሆኑት የወንጀል ድርጊቶች መካከል በአሽከርካሪዎች የሚፈጸመው ወንጀል ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል ለማለት ይቻላል፡፡ ከትራፊክ ፖሊስ ዕለታዊ ሪፖርት በየዕለቱ እንደምንሰማው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ እንኳን ያለበትን ሁኔታ ብንመለከት በንብረትና በሰው ላይ፣ ቢያንስ በአንደኛው ላይ አደጋ ሳይደርስ የዋለበት ቀን የለም ለማለት ይቻላል፡፡ የአደጋ ዜናው በ24 ሰዓት፣ በወርና በዓመት ስሌት ሲነገር ስንሰማው እጅግ አሳሳቢ ነገር ነው፡፡ በትርፊክ ፖሊስ የዘወትር ሪፖርት እንደምንሰማውም ብዙውን ጊዜ አደጋው የደረሰው ለእግረኛ ቅድሚያ መከልከል በአሽከርካሪ ጥፋት መሆኑን መዘገቡ የተለመደ ነው፡፡
በዚህ ጽሁፍ ፍተሻ የምናደርግባቸው ነጥቦች አሽከርካሪ አጥፍቷል ወይም በቸልተኝነት ወንጀል ፈጽሟል የሚባለው መቼ ነው; የወንጀል ድርጊቱን ለመከላከል/ለመቀነስ እግረኞችስ ምን ዓይነት ግዴታ አለባቸው; አደጋውን እያባባሱ ያሉት ዋና ዋና ሁኔታዎች ምንድን ናቸው; የሕግ ስርዓታችንና በፍርድ ቤቶች የተሰጠው ቦታስ ምን ይመስላል; የሚሉትንና ተያያዥነት ያላቸውን ነጥቦች ናቸው፡፡
ወደ ዝርዝር ነጥቦች ከመግባታችን በፊት ጭብጡን በፍርድ ቤቶች በታዩና ፍርድ በተሰጠባቸው ጉዳዮች ለመደገፍ ይቻል ዘንድ በቅድሚያ ሶስት ዐቃቤ ህግ የወንጀል ክስ ያቀረበባቸውንና ፍርድ ቤት ፍርድ የሠጠባቸውን ናሙና ጉዳዮችን በአጭሩ እንመልከት፡፡
ጉዳይ አንድ፡ ጊዜው ነሐሴ ወር 2002 ዓ.ም ነው፡፡ በ70ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙት አዛውንት ከኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ለሥራ ጉዳይ በማለት ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡ አዛውንቱ ሥራ ያሉትም በመንገድ ላይ ገንዘብ ለምኖና አጠራቅሞ ወደመጡበት መመለስ ነበር፡፡ ሥራቸውንም በተክለሃይማኖት አካባቢ ባለው አስፋልት ላይ ቀኑን እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ከግራ ወደቀኝ በመመላለስ በትጋት ሲያከናውኑ መዋል ጀመሩ፡፡ የልመና ገንዘቡም በዋናነት ከአሽከርካሪዎች እየተሰበሰበና እየተጠራቀመ ነው፡፡ ይሁንና በአንዲቷ ጎደሎ ቀን ከአንዱ አሽከርካሪ ሳንቲም ተቀብለው በሌላኛው ተሽከርካሪ ተከልለው መንገዱን ከቀኝ ወደ ግራ ሲያቋርጡ ከአንድ የጭነት ተሽከርካሪ አይሱዙ ጋር ይጋጩና ከአስፋልቱ ላይ ይወድቃሉ፡፡ አዛውንቱም የሰበሰቡትን ገንዘብ የት እንዳስቀመጡት ሳይናገሩና እንዳሰቡትም ወደ መጡበት ሳይመለሱ እንደወጡ ቀሩ፡፡ የትራፊክ ፖሊስ የአዛውንቱ ሞት በአሽከርካሪ ጥፋት ለእግረኛ ቅድሚያ መከልከል የተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ ፕላኑን አዘጋጅቶና ሪፖርቱን ጽፎ ጉዳዩን ለዐቃቤ ህግ አስተላለፈ፡፡ ዐቃቤ ህግም በሪፖርቱ መሠረት ክሱን በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 543/2/ ተላልፎ በቸልተኝነት ሰው መግደል የወንጀል ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቀረበ፡፡
ጉዳይ ሁለት፡ ጊዜው በስድስተኛው ወር በ2002 ሲሆን አሽከርካሪዋ ሴት ነች፡፡ አሽከርካሪዋ ባለቤቷ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ የነበራቸውን ጅምር ቤት በመሸጥ ሁለት ህጻናት ልጆቿን ለማሳደጊያ ይሆናት ዘንድ በማሰብ አንድ ትንሽ ላዳ ታክሴ በመግዛት ሹፌር ቀጥራ ገቢ ማግኘት ጀመረች፡፡ ሴትዮዋ ያላት የመንጃ ፈቃድ 2ኛ ሆኖባት እንጅ 3ኛ ቢሆን ኖሮ ታክሲዋን ራሷ በማሽከርከር ገቢዋን የተሻለ የማድረግ ሀሳቡ ነበራት፡፡ ሀሳቧን ከግብ ለማድረስም 3ኛ ደረጃ አሽከርካሪነት የሙያ ፈቃድ ለማግኘት ልምምድ ጀመረች፡፡ ነገር ግን ልምምዱ በተፈቀደላቸው አሰልጣኞችና የመለማመጃ ተሸከርካሪዎች ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ከዚህ አልፎ በራሷ ታክሲ እና በሹፌሯ አለማማጅነት ልምምዷን በኮተቤ አስፋልት ቀጠለች፡፡ ይሁንና እንኳን በ3ኛ ደረጃ መንጃ ፈቃድ የሚነዳውን ተሸከርካሪ ማሽከርከር ይቅርና ችሎታዋ በ2ኛ ደረጃ ለሚሽከረከረውም አጥጋቢ አልነበረምና ከኋላ በተከተላትና ድምጹን በሰማቸው ከባድ ተሸከርካሪ ምክንያት በድንጋጤ ከመንገዱ በመውጣት በከባድ ቸልተኝነት የመንገዳቸውን ቀኝ ጠርዝ ይዘው ይጓዙ ከነበሩት ሴት ህጻናት ተማሪዎች መካከል በአንዷ ላይ የሞት አደጋ፣ በሁለቱ ላይ የአካል ጉዳት አደጋ በማድረስ ግቢ ጥሳ በመግባት በንብረትም ላይ ጉዳት የማድረስ ድረጊት ይፈጸማል፡፡ የትርፊክ ፖሊስም አደጋው የደረሰው ከመንጃ ፈቃድ ደረጃ ውጭ ደንብ በመተላለፍ፣ በአሽከርካሪ ጥፋት ለእግረኛ ቅድሚያ መከልከል የተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ ፕላኑን አዘጋጅቶና ሪፖርቱን ጽፎ፣ አለማማጁንም ከምስክሮች መካከል አድርጎ (እያለማመደ የነበረ መሆኑን ክዷል) ጉዳዩን ለዐቃቤ ህግ አስተላለፈ፡፡ ዐቃቤ ህግም በሪፖርቱ መሠረት ክሱን በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 543/2/ እና 559/2/ ተላልፎ በቸልተኝነት ሰው መግደል እና የአካል ጉዳት ማድረስ እንዲሁም በመንጃ ፈቃዱ ደንብ በመተላለፍ ሦስት የወንጀል ክሶችን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቀረበ፡፡