እያመለጠ ያለን የጊዜ ቀጠሮ እስረኛ ተኩሶ መግደል በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ
አንድ ሰው ወንጀል በመስራት በመጠርጠሩና የተጠረጠረበት ወንጀል በሕጉ ዋስትና የማያስፈቅድ በመሆኑ ወይም በዋስትና ለመውጣት አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች እስኪከናወኑ ጊዜ ድረስ በእስር ላይ ሊቆይ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ እስረኛው በሕጉ የተፈቀደለት የሰብአዊ ክብር እንክብካቤና በሕይወት ለመቆየት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች በሙሉ እየተሟሉለት የፍርድ ሂደቱን የመከታተል መብት አለው፡፡ እስረኛው በፍ/ቤት ወንጀለኛ ተብሎ ያልተፈረጀ ይልቁንስ በህገመንግስቱ አንቀፅ 20/3/ መሠረት ንፁህ ሆኖ የመገመት መብት ያለው በመሆኑ ተገቢው ክብርና እንክብካቤ የሚገባው ነዉ፡፡
የዚህ ጽሑፍ መነሻ በአንድ በተጠረጠሩበት ወንጀል ምክንያት የታሰሩ ሰዎች የታሰሩበት እስር ቤት በራሳቸው ባልሆነ ጥፋት በእሳት እየተቃጠለ በመሆኑ ምክንያት ከሚነደው የእሳት ቃጠሎ ራሳቸውን ለማዳን ሲሉ በሕግ ወንጀልነቱ የተደነገገ ሌላ ወንጀል ፈፅመው ቢገኙ ለምሳሌ ከታሰሩበት እስር ቤት ለማምለጥ ቢሞክሩ የእስር ቤቱ ጠባቂ ይህን የማምለጥ ድርጊት ለማቆም የሚወስደው የግድያ ተግባር በወንጀል ሕጉ መሠረት ያለውን ህጋዊነት መፈተሽ ነው፡፡
ቅጣት አልባው ወንጀል
የወንጀል ሕግ በህብረተሰቡና በመንግሥት ጥፋት መሆናቸው የታመነባቸው ድርጊቶችን መፈፀም የሚያስከፍለው ዋጋ የተገለፀበት የወንጀል ድርጊቶች ሜኑ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ በወንጀል ሕጉ ወንጀል ተብሎ የተገለፀን ድርጊት መፈፀም ሁል ጊዜ አያስቀጣም፡፡ ወንጀል ያለቅጣት ምኑን ወንጅል ሆነ ቢያስብልም ማህበረሰቡ ወንጀል ብሎ የፈረጃቸው ድርጊቶች መፈፀም ወንጀል ቢሆንም ማህበረሰቡ ሊጠብቀዉ ለፈለገዉ ሌላ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተቀሜታ ሲባል ወንጀል ሁሉ አያስቀጣም፡፡
ወንጀል ነው ግን አያስቀጣም እንደማለት፡፡ ይህ የወንጀል ሕግ ወንጀል ብሎ ለደነገጋቸው ተግባሮች ያስቀመጠው ልዩ ሁኔታ ነው፡፡ እነዚህ ልዩ ሁኔታዎች በርካታ ቢሆኑም የተወሰኑት በአጭሩ ለማንሳት ያህል በሕግ የተመለከተውን የ9 ኣመት እድሜ ያልሞላ ህፃን ወንጀል ፈፅሞ ሲገኝ ፤በሕጉ ወንጀለኛዉ ትክክለኛ አዕምሮ የለውም የሚያስብል ምክንያት ሲኖር ፤በአንድ ሌላ ነገር ምክንያት ራሱን መቆጣጠር በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ወንጀል መስራት ሲኖር፤ በግዴታ ወንጀል ውስጥ መግባትና በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ መገኘትና ሌሎችንም ይጨምራል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ማብራራት የጽሑፍ አላማ ስላልሆነ ከተነሳው ርዕስ ጋር ተያያዥነት ስላለው በሕግ ወንጀል ቢሆንም እንደትክክለኛ ተግባር ስለሚቆጠረዉ በአስፈላጊ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ወንጅል ስለመስራት ማብራራት ተገቢ ነው፡፡
አስፈላጊ ሁኔታን (necessity) አንድ ሰው በሁለት መጥፎ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ አንዱን የተሸለውን መጥፎ ለመምረጥ የሚገደድበት ቅፅበት ብሎ መግለፅ ይቻላል ፈረንጆቹ /the lesser evil/ የሚሉት መሆኑ ነው፡፡ አስፈላጊ ሁኔታ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 75 ላይ በሚገባ የተብራራ ሲሆን በዚህ የሕጉ ንባብ መሠረት አንድ ሰው የራሱን ወይም የሌላን ሰው መብት በቅርብ ከሚደርስ ከባድ የሆነ አደጋ ለማዳን አደጋውን በሌላ መንገድ ማስወገድ የማይቻል በመሆኑ አድራጊው ከሁኔታው ጋር ተመጣጣኝ የሁኑ ዘዴዎችን በመጠቀመ ሌላ ወንጀል ፈፅሞ የሚደርስበትን ወይም የሚደርስን አደጋ ቢያስቀር አይቀጣም፡፡ በመሆኑም ይህ ሁኔታ ማህበረሰቡ አንድን ድርጊት ወንጀል ብሎ ቢፈርጀውም ነገር ግን ወንጀል ተብሎ ከተደነነገ ድርጊት ይበልጥ የከበረ ተቀባይነት ያለው ሌላ የተሸለ መብትን ለመጠበቅ ሲባል የተፈፀመ ወንጀል በመሆኑ እንደ ትክክለኛ ተግባር ሕጉ ይቀበለዋል ማለት ነው፡፡
ስለዚህ በሕጉ መመዘኛ መሠረት አንድ የወንጀል ድርጊት የተፈፀመው በአድራጊዉ ጥፋት ያልመጣ ከባድ የሆነን አደጋ ለማስቀረት አደጋው አይቀሬና በሚፈፀመው ወንጀል ካልሆነ በቀር በሌላ መንገድ ሊቀር የማይችል የወንጀል ድርጊቱ የሚያደርሰው ጉዳት ሊደርስ ከነበረው ጉዳት ጋር ተመጣጣኝ እስከሆነ ጊዜ ድረስ አያስቀጣም ማለት ነው፡፡
በዚህ መመዘኛ እና ፍሬ ነገር መሠረት በአንድ እስር ቤት ውስጥ በጊዜ ቀጠሮ ምክንያት የታሰረ እስረኛ የታሰረበት እስር ቤት ወይም ክፍል በእሳት በመቃጠሉ ምክንያት ከታሰረበት ቦታ ለማምለጥ መሞከር የሚያስቀጣ ድርጊት ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ነጥብ ስንመለከት አንድ እስረኛ በሕግ አግባብ ከታሰረበት ቦታ ሊያመልጥ ከሞከረ ወይም ካመለጠ ወንጀል ሲሆን በወ/ህ/ቁ 461 መሠረትም የሚቀጣው ከ6 ወር በማይበልጥ እስራት ሲሆን እንዲሁም ይህ ገና በተጠርጣሪዉ መፈፀም አለመፈፀሙ ባልተረጋገጠ ወንጀል በእስር ላይ የሚገኝ ሰው(ወንጀለኛ ሆኖ ቢፈረድበትም የሚያመጣው ለውጥ ባይኖርም) የታሰረበት እስር ቤት ወይም ክፍል በከፍተኛ ቃጠሎ እየነደደ መሆኑን ካወቀ ከፍ ሲል እንደተገለፀዉ ሁለት መጥፎ ሁኔታዎች ውስጥ መውደቁ አይቀሬ ነው፡፡ ይሄውም ህይወቱ አደጋ ውስጥ ስለሆነ ከዕሳት ቃጠሎው ማምለጥ አለበት ወይም ህይወቱን ለማዳን ከቃጠሎው ለማምለጥ ከፍ ሲል የተገለፀውንና በወ/ህ/ቁ 461 ላይ ወንጀል ሆኖ የተደነገገውን የወንጀል ድርጊት ለመፈፀም ይገደዳል፡፡ እነዚህ ሁለት መጥፎ ነገሮች ቢሆኑም ሁለቱም ግን እኩል መጥፎ ሁኔታዎች አይደሉም በመሆኑም ከሁለቱ መጥፎ ሁኔታዎች ከፍ ሲል ባስቀመጥነው የአስገዳጅ ሁኔታ መመዘኛዋች መሠረት ከሁለቱ አንዱን መምረጥ አለበት፡፡ አደጋ ላይ ያለው መብት የተጠርጣሪዉ በህይወት የመኖር መብት ሲሆን ይህ መብት እሳት ቃጠሎ በሚባል ከባድ አደጋ ውስጥ በመሆኑ ከእስር በማምለጡ ከሚጣሰው የወ/ህ/ቁ 461/ከዕስር ማምለጥ/ ጋር ሲነፃፀር ድርጊቱ ተመጣጣኝ የሚባል ነው ማለት ይቻላል፡፡ ተጠርጣሪዉ የእሳት ቃጠሎን ሸሽቶ ከማምለጥ ውጭ ህይወቱን መታደግ አይችልም ከእሳት ቃጠሎው ህይወቱ ሊድን የሚችለው ደግሞ የታሰረበትን እስር ቤት ለቆ ሲወጣ ብቻ ነው ይህን በማድረጉ ወንጀል ፈፅሟል ይሁን እንጂ ተጠርጣሪ የግዜ ቀጠሮ እስረኛ እንጂ ወንጀለኛ ባለመሆኑ (ወንጀለኛ ቢሆንም ለውጥ የማያመጣ ቢሆንም)፤ የተጠርጣሪው ከእስር ማምለጥ በህይወት ከመኖሩ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ጉዳት በመሆኑ፣ አይደለም የእስር ቤቱን ጥሎ መውጣት እንዳይወጣ እንቅፋት በሆነበት ሰው ላይ እርምጃ ቢወስድ እንኳ በሕጉ ተመጣጣኝ ድርጊት ተብሎ የሚወሰድ ተግባር እስከወሰደ ጊዜ ድረስ የዚህ እስረኛ ድርጊት በሕጉ መመዘኛ መሠረት ወንጀል የሆነ ነገር ግን የማያስቀጣ ትክክለኛ ተግባር ይሆናል፡፡
በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ህይወቱን ለማዳን ከእስር እያመለጠ ያለን ሰው በመግደል የማስቆም ህጋዊነት
ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው ጥያቄ ከፍ ሲል በተገለፀው አግባብ ህይወቱን ከመጣበት ከባድ የእሳት ቃጠሎ ለማዳን ከእስር እያመለጠ ያለን እስረኛ ተኩሶ የገደለ የእስር ቤት ጠበቂ ድርጊት በሕጉ መሠረት ተገቢ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ ይሆናል፡፡
ከፍ ሲል እንደገለፅነው የእስረኛው ህይወት ከፍተኛ አደጋ ላይ ነው እንዲሁም ከእስር ማምለጡ ከእስረኛው ህይወት ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ ጉዳት ነው ታዲያ ይህ የእስር ቤት ጠባቂ እያመለጠ ያለውን እስረኛ ተኩሶ ከመምታትና የአካል ወይም የህይወት ጉዳት ከማድረስ ባነሰ ሁኔታ የማምለጥ ተግባሩን ለዚያዉም የእስረኛውን ህይወት የእሳት አደጋው በማይጎዳዉ ሁኔታ በሌላ አማራጭ ማስቆም ቢችልም ተኩሶ በመግደል ወይም የአካል ጉዳት እንዲደርስበት በማድረግ እስረኛው ማስቆም ግን ከእስር በማምለጡ ምክንያት በማህበረሰቡ ላይ ከሚደርሰው ጉዳት ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ ድርጊት ነዉ፡፡
ፍርዱን በመጠባበቅ ላይ ያለን እስረኛ መግደል ትርፍ የሌለዉ ኪሳራ ሲሆን በፍርድ ነፃ ቢባል አንድ ንፁህ ሰው ከሚታሰር አስር ወንጀልኛ ነፃ ይውጣ በሚል መርህ ውስጥ የአንድን ንፁህ ሰው ህይወት መቅጠፍ በመሆኑ ድርጊቱ የአንድን ንፁህ ሰዉ ህይወት በግፍ መውሰድ ነዉ፡ በሌላ መልኩ ከጅምሩ ተጠርጣሪዉ የታሰረዉ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኝ በፈፀመዉ ወንጀል እንዲቀጣ እና ከዚህም ራሱ እስረኛዉ እና ማህበረሰቡ ተምረዉ ከወንጀል እንዲቆጠቡ በማድረግ ማህበረሰቡን ከወንጀል መከላከል በመሆኑ ተጠርጣሪዉ ወንጀለኛ ቢሆን እንኳ አስቀድሞ ከፍርድ በፊት የተገደለ በመሆኑ የሞተ ሰው ከስህተቱ ሊማር ስለማይችል ሌላዉን ማህበረሰብም ጥፋተኛ መባሉ ባልተረጋገጠ ሰዉ ማስተማር የማይቻል በመሆኑ ተጠርጣሪውን በማሰር ሊፈፀም የታሰበዉ የወንጀል ሕጉ መሰረታዊ አላማ ተሰነካክሎ የቀረ በመሆኑ ድርጊቱ ተራ ወንጀል ብቻ ሳይሆን የወንጀል ሕጉን አላማ እና ማህብረሰቡ በወንጀል ሕጉ መርሆች በኩል እንዲሳኩ የሚፈልጋቸውን መሰረታዊ ጥቅሞች ያስቀረ ድርጊት በመሆኑ በፍፁም ተገቢነት ያለዉ ድርጊት አይደለም፡፡
ከ6 ወር በማይበልጥ እስራት ለሚያስቀጣ የወንጀል ድርጊት የሰው ህይወት ከማጥፋት ከእስር ማምለጡ እጅግ የሚሻል በመሆኑ በመግቢያ እንደገለፅኩ በህገመንግስቱ ንፁህ መሆኑ የተገመተ ሰው በአስገዳጅ ሁኔታ ከእስር በማምለጡ ህይወቱን እንዲያጣ ማድረግ ሊታረም የማይችል ስህተት በመሆኑና ምናልባት በተጠረጠረበት ወንጀል ያለፍርድ እንደተቀጣ ምስኪን የሚቆጠር በመሆኑ በየትኛው መመዘኛ የእስር ቤት ጠባቂው ድርጊት ተመጣጣኝ ሊባል የማይችል በመመዘኛው መሠረት ከፍ ያለ አደጋን ለማስቀረት ሲባል የተፈፀመ ባለመሆኑ ድርጊቱ በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ የተፈፀመ ነው ለማለት አይቻልም ይልቁንስ አንድ የአስገዳጅ ሁኔታን ለመጠቀም መብት ያለው ሰው በሕጉ ከተቀመጠው መመዘኛ በመውጣት ወይም አስፈላጊ ሁኔታ በመባል የሚታወቀው ሁኔታ ከሚፈቅደው የሁኔታ ወሰን በመውጣት ወንጀል መፈፀም በወ/ህ/ቁ 76 መሠረት አድራጊው ከቅጣት አይድንም ምክንያቱም ድርጊቱ ያልተመጣጠነ ድርጊት ከመሆኑ ባሻገር ሕጉ የአንድን እስረኛ ማምለጥ ለመከላከል የእስረኛውን ህይወት ከመቅጠፍ ይልቅ የእስረኛ ማምለጥ ድርጊት ቢፈፀም እንደሚሻለው በወ/ህ/ቁ 76 በግልፅ አማርኛ በነገሮች አካባቢ በአደጋው ላይ የሚገኘው መብት /በያዝነው ጉዳይ ከእስር ማምለጥ/ መሰዋእት ማድረግ (እስረኛዉ እንዲያመልጥ መተው) አስፈላጊ መሆኑ ሲገመት ይህ መብት ማለትም ከእስር ማምለጡ እንዳይፈፀም መከላከል የሚያስቀጣ ወንጀል ይሆናል ምንም እንኳ በሕጉ ይህ ሁኔታ እንደ አንድ መሰረታዊ የቅጣት ማቅለያ ቢመለከተውም የሚያስቀጣ ወንጀል ከመሆን አይቀርም፡፡
መደምደሚያ
በአጠቃላይ እጅግ አነስተኛ ለሆነ አደጋ /ከእስር ማምለጥ/ ከፍ ያለ አደጋን /የእስረኛውን ህይወት መቅጠፍ/ መፈፀም የሚያስቀጣ ወንጀል ሲሆን በተለይም በሕገ መንግሥቱ ንፁህ ሆኖ የመገመት መብት ያለውን ሰው የእስረኛው ጥፋት ባልሆነ ሌላ ምክንያት በደረሰ ከባድ አደጋ ምክንያት ህይወቱን ከሞት ለመታደግ እያመለጠ ያለን እስረኛ ከአንድ ሞት ሲተርፍ በሌላ ሞት መቀበል ተገቢ ድርጊት ባለመሆኑ ድርጊቱ በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 76 መሠረት ወንጀል ነው፡፡ በተጨማሪም የፍትሐብሔር ሃላፈነት የሚያስከትል ሲሆን ይህን ድርጊት የተፈፀመበት ማረሚያ ቤትም በጠርጣሪዉም ሆነ በፍትሕ ላይ ለተፈፀመዉ ድርጊት ሀላፊነት አለበት፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments