ወይኖን ግረፈው ኳሊ እንዲሰማህ፤ የወንጀል ኢኮኖሚክስ ክፍል ሁለት
1. የመያዝና የመቀጣት እድል፤ ማጅራት መቺዎችን እና ቤት ሰርሳሪዎችን ከተማን በማጽዳት እንዋጋቸው፤ ወይኖን ግረፈው ኳሊ እንዲሰማህ እና ሌሎችም አሳቦች
1.1 አጠቃላይ
ማስታወሻ ለአንባቢ፤ ይህ በወንጀል ኤኮኖሚክስ ዙሪያ የጻፍኩት ሁለተኛው ጽሑፌ ነው፡፡ የመጀመሪያውን ክፍል እዚህ ማግኘት ይቻላሉ:: አሳቦቼን ለማስረዳት ስል አንዳንዴ ተጓዳኝ ጉዳዮችን እያነሳው ባወራም፤ የዋናው ሃሳብ ፍሰት አይዛባም የሚል ዕምነት አለኝ፡፡
በመጀመሪያው የጽሑፉ ክፍል የተቀመጠው ቀመር ሌላኛው አካል የመያዝና የመቀጣት እድልን መጨመር ነው፡፡ ለማስታወስ ያህል ቀመሩ ይህ ነው፤
ሕግ በመጣስ የሚገኘው ጥቅም ≤ (በሕጉ የተቀመጠው ቅጣት X የመያዝና የመቀጣት እድል X ዲስካውንት ፋክተር) + ሕጉን ለመጣስ የሚወጣው ወጪ + (ኢመደበኛ ቅጣት X የመያዝና የመቀጣት እድል X ዲስካውንት ፋክተር)
በሕጉ የተቀመጠውን ቅጣት ስኬታማነት ከሚወስኑት ጉዳዮች አንደኛው የመያዝና የመቀጣት እድል ነው፡፡ አንድ ሰው ሕግ ጣሰ ማለት ይያዛል፤ ይቀጣል ማለት አይደለም፡፡ የመያዝና የመቀጣት እድሉ ከመቶ መቶ አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ እንዲሆንም አይገባም፡፡ መቶ ከመቶ ከማይሆንበት ምክኒያት ግለሰቡ ሕግ መጣሱን የሚያስረዳና በፍርድ ቤት ወይም የዳኝነት ሥልጣን በተሰጠው አካል ተቀባይነት የሚኖረው በቂ ማስረጃ በማጣት ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ይህን መረጃ ተጨማሪ ማስታወቅ፤ መረጃው የተሰበሰበበትም ሥርዓት አደጋ ውስጥ ስለሚከት ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ምንም እንኳ ይህን መረጃ መሰብሰብ ቢቻልም መረጃውን በመሰብሰብ የሚወጣው ወጪ ከሚገኘው ጥቅም ስለሚበልጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ክፍል በጽሑፉ ሦስተኛ ወይም አራተኛ ክፍል እመለስበታለው፡፡
መንግሥት የሕግ ጥሰትን ለማወቅና ሕግ የጣሱትን ለማስቀጣት ሲል ፖሊሶችን ለክትትል ያሰማራል፤ በተለያዩ አጋጣሚዎችና ሁኔታዎችም ምርመራን እና ክትትልን ያከናውናል፡፡ ፖሊሶችን ማሰመራቱ አንድም ግለሰቦች ሕግ እንዳይጥሱ ለማድረግ፤ ሌላም ጥሰው የተገኙነትን ለማወቅና ለመመርመር ነው፡፡ ከፖሊሶች በተጨማሪ የተለያዩ አስተዳደር ተቋማት ክትትል፤ ፍተሻና፤ ምርመራ በሕግ በተቀመጡ አግባቦችና ሁኔታዎች ያከናውናሉ፡፡ እንዲሁም የሕግ ጥሰትን ለመከታተልና ለመመርመር የተለያዩ ቴክሎሎጂዎችን ይጠቀማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተበዳይ ወገኖች ወይም ሕግ ስለመጣሱ የሚያውቁ ሰዎች በሚሰጡት ጥቆማ፤ አቤቱታና፤ ማስረጃ ይደገፋል፡፡
የአንድ ሕግን ተከባሪነት ለመጨመር የመያዝና የመቀጣት እድልን መጨመር ይጠቅማል፡፡ ይህም ተጨማሪ ፖሊሶችን መቅጠርና ማሰማራትን፤ የተለያዩ ቴክሎሎጂዎችን መጠቀምን፤ እንዲሁም ዜጎችና ተበዳዮች መረጃ ሰጪዎችና ምስክሮች እንዲሆኑ ማበረታታትን ይጨምራል፡፡ በዚህ አኳኋን የመያዝና የመቀጣት እድልን መጨመር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህ ራሱን የቻለ ወጪ አለው፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙ ጊዜ አንድን ሕግ በተመለከተ አቤቱታ ሲበረታ የመያዝና የመቀጣት እድልን ከመጨመር ይልቅ፤ ቅጣትን መጨመር ቀላል መስሎ ይታያል፡፡ ይህ ግን አግባብነት ላይኖረው እንደሚችል ከዚህ በፊት ባሉት የጽሑፉ ክፍሎች አይተናል፡፡
የመያዝና የመቀጣት እድልን ለመጨመር የሚረዱ የተለያዩ ዓይነት ስልቶች አሉ፡፡ አንደኛው የሕግ ጥሰትን በቀላሉ ሊያውቁ የሚችሉት በድርጊቱ የተጎዱ ወይም የተካፈሉ ወይም ደግሞ ምስክር የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ለሕግ አስፈጻሚዎች መረጃ እንዲሰጡና ምስክር እንዲሆኑ የተለያዩ ማበረታቻዎችን እና አመቺ ሁኔታዎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በአንጻሩ እነዚህ ወገኖች መረጃና ምስክር መስጠታቸው ለተለያዩ ውጣ ውረዶች፤ የጥቅም ጉዳቶችና፤ ጥቃቶች የሚያጋልጣቸው ከሆነ ግን የመያዝና የመቀጣት እድል እጅል ሊቀንስ ይችላል፡፡
1.2 የመቀጣትና የመያዝ እድል ከፍተኛ እንደሆነ ዜጎች እንዲሰማቸው ማድረግ፤ የተሰበረ መስኮት ፖሊሲ
1.2.1 ግለሰቦች ራሽናል ናቸው፤ የሚፈልጉትን ያውቃሉ?
ከላይ እንደተብራራው የመያዝና የመቀጣት እድልን መጨመር በራሱ ሰፊ ሥራና ወጪ የሚጠይቅ ነው፡፡ በሌላ በኩል ዘመናዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የመያዝና የመቀጣት አድልን በተጨባጭ ብዙ ከፍ ማድረግና እጅግ ከፍተኛ ወጪ ማውጣት ሳያስፈልግ፤ ዜጎች ግን የመያዝና የመቀጣት እድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ እንዲሰማቸው ማድረግ ይቻላል፡፡ በአንጻሩ አንዳንድ አሠራሮች ዜጎች ሕግ ቢጥሱ የመያዝና የመቀጣት እድላቸው ከእውነታው ያነሰ መስሎ ስለሚታያቸው ሕግ ለመጣስ ሊደፋፈሩ ይችላል፡፡ ይህ ለምን ሆነ እንዴትስ የሕግ ከበሬታን (ይህን ሃሳብ ግምት ውስጥ አስገብትን) ማሻሻል ይቻላል የሚሉትን ጉዳዮች እስቲ ትንሽ እንፈትሻቸው፡፡
የኒዮ-ኢኮኖሚክስ አስተሳሰብ የሚጀምረው ግለሰቦች ራሽናል ናቸው ከሚል ግምት ነው፡፡ ስለ ነጻነት እና ስለ ምርጫ ያላቸው አቋምም ከዚሁ ግምት ነው የሚመነጨው፡፡ በአማርኛ ራሽናል የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል ከመተርጎም ይልቅ፤ ቃሉ ሁለትና ከዛ በላይ የሚሆኑ ተያያዥ ሃሳቦችን ያጨቀ ስለሆነ፤ እነዚህን ሃሳቦች ማየቱ የበለጠ ይጠቅማል፡፡
በመጀመሪያ የግለሰብ ራሽናሊቲ የሚጠቁመው አንደኛው ሃሳብ ግለሰቦች ምን እንደሚፈልጉ አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ከግለሰቡ በላይ ስለሱ ፍላጎት የሚያውቅ ሰው የለም፡፡ ከራስ ያወቀ ቡዳ ነው፡፡ ጀረሚ ቤንታም ግለሰቦች የሁለት ማስተር ተገዥ ናቸው ይለናል፤ የደስታና ሰቆቃ፡፡ ደስታቸውን ለመጨመር ሰቆቃቸውን ለመቀነስ ዘወትር ይሰራሉ፡፡ ምንም እንኳ ይህን በአጠቃላይ ስለሰው ልጆች በጠቅላላው መናገር ቢቻልም፤ እያንዳንዱ ግለሰብ ምን እንደሚፈልግ፤ ምን ዓይነት ነገር ደስታውን በምን ያህል እንደሚጨምርለት እና በምን ያህል ደግሞ ሰቆቃውን እንደሚቀንስለት ከሱ በላይ የሚያውቅ ሊኖር አይችልም ይለናል፡፡ ከዚህ አስተሳሰብ በመነሳት፤ የኒዮ ሊብራል አባት የሚባለው ሚልቶን ፍሪድማን የመንግሥት ሃላፊነት ትንሽ መሆን አለበት በሚል የሚሟገተው፤ መንግሥት ማለት ለሌላ ሰው ጥቅምና ደህንነት የሌላን ሰው ሃብት የሚያስተዳድር በመሆኑና፤ የራሱ ያልሆነውን ሃብት ለሌላ በመጠቀም ረገድ የእውቀት ውስንነት ይኖራል--የሚሰራለት ሰው ምን ዓይነት ነገር በምን ዓይነት መጠን ደስታውን እንደሚጨምርለትና ሰቆቃውን እንደሚቀንስለት ማወቅ አይችልምና፡፡ የሚከተለውን አባባል ከሚልቶን ፍሪድማን መጽሐፍ ቀንጭቤ አቅርቤአለው፡፡
At the dawn of the new era all seemed well. The people to be benefited were few; the taxpayers available to finance them, many—so each was paying a small sum that provided significant benefits to a few in need. As welfare programs expanded, the numbers changed. Today all of us are paying out of one pocket to put money—or something money could buy—in the other.
A simple classification of spending shows why that process leads to undesirable results. When you spend, you may spend your own money or someone else’s; and you may spend for the benefit of yourself or someone else. Combining these two pairs of alternatives gives four possibilities summarized in the following simple table:
|
On Whom Spent |
|
Whose Money |
You |
Someone Else |
Yours |
I |
II |
Someone Else’s |
III |
IV |
Category I in the table refer to your spending your own money on yourself. You shop in a supermarket, for example. You clearly have a strong incentive both to economize and to get as much value as you can for each dollar you do spend.
Category II refers to your spending your own money on someone else. You shop for Christmas or birthday presents. You have the same incentive to get full value for your money, at least as judged by the tastes of the recipient. You will, of course, want to get something the recipient will like—provided that it also makes the right impression and does not take too much time and effort. (If, indeed, your main objective were to enable the recipient to get as much value as possible per dollar, you would give him cash, converting your Category II spending to Category I spending by him).
Category III refers to your spending someone else’s money on yourself—lunching on an expense account, for instance. You have no strong incentive to keep down the cost of the lunch, but you do have a strong incentive to get your money’s worth.
Category IV refers to your spending someone else’s money on still another person. You are paying for someone else’s lunch out of an expense account. You have little incentive either to economize or to try to get your guest the lunch that he will value most highly. However, if you are having lunch with him, so that the lunch is a mixture of Category III and Category IV, you do have a strong incentive to satisfy your own tastes at the sacrifice of his, if necessary.
All welfare programs fall into either Category III—for example, social security which involves cash payments that the recipient is free to spend as he may wish; or Category IV—for example, public housing; except that even Category IV programs share one feature of Category III, namely, that the bureaucrats administering the program partake of the lunch; and all the Category III programs have bureaucrats among their recipients.
In our opinion these characteristics of welfare spending are the main source of their defects.
…. The bureaucrats spend someone else’s money on someone else. Only human kindness, not the much stronger and more dependable spur of self-interest, assures that they will spend the money in the way most beneficial to the recipients. Hence the wastefulness and ineffectiveness of the spending.
ሚልቶን ፍሪድማን
ከዚህ በላይ ከተቀመጠው የሚልቶን ፍሪድማን አባባል ጋር በአጠቃላይ እስማማለው፡፡ የማልስማማው በተሰመረበት ክፍል ላይ ነው፡፡ ብክነትን የሚያስወግደው፤ ውጤትን የሚያልቀው የግል ጥቅም ብቻ ነው የሚለውን በብዙ መልኩ መሞገት ይቻላል፡፡ ከጉዳዩ ጋር በደንብ ስለማይያያዝ ለጊዜው እንተወው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ይህ ነው፤ በኒዮ ሊብራሎች አስተሳሰብ አንድ ሰው ምን እንደሚፈልግ፤ ምን በምን ያህል ደስታውን እንደሚጨምርለት፤ በምን ያህል ደግሞ ሰቆቃውን እንደሚቀንስለት፤ ከእሱ በላይ የሚያውቅ አይኖርም የሚለው አስተሳሰብ የኒዮ-ሊብራል ፓለቲካል ኢኮኖሚ አስተሳሰብ መሠረት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ነው ሚልቶን ፍሪድማን የመንግሥትን የዌልፌር ሚና የሚቃወመው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ነው ኒዮ ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች የእቃ ስጦታን ሃብት አባካኝ ነው በሚል የሚኮንኑት፡፡ አንዳንድ ጥናቶች የሚያሳዩት ሰዎች በስጦታ ላገኙት እቃ የሚሰጡት ዋጋ ስጦታ ሰጪው ካወጣው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ከመቶ 20 እጅ ይቀንሳል፡፡ በመሆኑም ይሉናል፤ የእቃ ስጦታ ከመስጠት ይልቅ፤ ገንዘቡን ሰጥተው፤ ግለሰቡ የፈለገውን ቢገዛበት ይሻላል፡፡
ግለሰቦች ራሽናል ናቸው የሚለው አስተሳሰብ፤ ግለሰቦች የሚፈልጉትን ያውቃሉ ብቻ ሳይሆን ከእነሱ በላይ የሚያውቅ የለም የሚለውን ይጨምራል፡፡ ከዚህ በተጫማሪ ወይም ይህ በመሆኑ የተነሳ ደግሞ፤ ግለሰቦችን መገመት ይቻላል፡፡ ወይም ግለሰቦች ተገማች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከበለስና ከብርቱካን ብርቱካንን ከመረጠ፤ እንዲሁም ከብርቱካን እና ከሙዝ ብርቱካንን ከመረጠ፤ ይህ ሰው ከበለስና ሙዝ በለስን ይመርጣል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከዚሁ ጋር የሚያያዘው ደግሞ አንድ ሰው በለስን የሚወድ ከሆነ፤ ከአንድ በለስ ሁለት በለስ ይመርጣል ተብሎ ይገመታል፡፡ ለጊዜው ግለሰቦች የሚፈልጉትን ያውቃሉ ለሚለው አስተሳሰብ የሚቀርቡ ሙግቶችን ወደ ጎን እንተዋቸው፡፡
1.2.2 ግለሰቦች ራሽናል ናቸው፤ መምረጥ፤ መገምገም ይችላሉ
ሰዎች ራሽናል ናቸው የሚለው አስተሳሰብ አጭቆ የያዘው ሁለተኛው ሃሳብ ሰዎች መምረጥ ይችላሉ የሚለውን ነው፡፡ ከብዙ አማራጮች ውስጥ፤ ከፍላጎታቸው አንጻር አንዱን ወይም ከዛ በላይ የሆኑትን ገምግመው መምረጥ ይችላሉ፡፡ ይህ አባባል ግለሰቦች መገምገም ይችላሉ፡፡ የግንዛቤ ችግር የለባቸውም፡፡ ለምርጫቸውና ግምገማቸው እስካገዘ እና ከወጪው የበለጠ ጥቅም የሚያመጣ እስከሆነ ድረስ የሚያስፈልጋቸውን መረጃ ይሰበስባሉ፡፡ ከተሰበሰቡት መረጃዎች አንጻር ከተለያዩ አማራጮች የሚፈልጉትን ይመርጣሉ፡፡ ተያያዥ አሳብ የሆነው ምርጫ ሲበዛ ግለሰቦች የበለጠ ተጠቃሚ ናቸው የሚለው ነው፡፡
1.2.3 ግለሰቦች ራሽናል ናቸው፤ ረሳቸውን መቆጣጠር ይችላሉ
ሰዎች ራሽናል ናቸው የሚለው አስተሳሰብ አጭቆ የያዘው ሶስተኛው ሃሳብ ግለሰቦች ራሳቸውን መቆጣጠር ይችላሉ፡፡ የማይበጃቸውን አያደርጉም፡፡ ደስታቸውን በአጠቃላይ የሚጨመረውን እንጂ በአፍታ ደስታቸውን ጨምሮ ለረጅም ጊዜ ግን ሰቆቃቸውን የሚጨመረውን ነገር አይደርጉትም፡፡ ግለሰቦች ሞግዚት አያስፈልጋቸውም የሚለው ነው፡፡
1.2.4 ግለሰቦች ራሽናል ናቸው?
ሰዎች ራሽናል ናቸው የሚለው አስተሳሰብ ለረጅም ዘመናት አውራ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከዚህም በመነሳት ተቋማት፤ ፓሊሲዎችና ሕግጋት ተቀርጸዋል፡፡ ግለሰቦች ራሽናል ናቸው የሚለው አስተሳሰብ ግለሰቦች ተገማች ሆነው እንዲታሰቡ አድርጓል፡፡ ግለሰቦች ራሽናል እና ተገማች ባይሆኑማ ኖሮ እንዴት ነው ተቋማት፤ ፓሊሲዎችና ሕግጋት የሚቆሙት? ግለሰቦች ተገማች ብቻ ሳይሆኑ በብዙ የሕይወት መስኮች ተገማችነትን ይመርጣሉ፡፡
የራሽናሊቲን ግምት የሚሞግቱም ቢሆኑ ከዚሁ አስተሳሰብ እኩል እድሜ አላቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተጠራጣሪዎች የሚያቀርቡት ሙግት ከአምስትና ስድስት አሥር ዓመታት ወዲህ ሙግታቸውን የሚደግፉ የሙከራ ጥናቶችና ግኝቶች መጠራቀም ጀምረዋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የቴክኖሎጂ አድገት ባመጣው ጸጋ ስለአንጎል አሰራር ያለን እውቀት እየጨመረና እየተስተካከለ መጥቷል፡፡ እነዚህ ግኝቶች ግለሰቦች ራሽናል ናቸው የሚለውን አስተሳሰብ ሙሉ ለሙሉ ባያፈርሱትም፤ እንዲሁም ሰዎች ተገማች አይደሉም የሚለውን ግንዛቤ ባይደረምሱትም፤ በተወሰነ ደረጃ የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥተዋል፡፡ በመሆኑም አሁን ግለሰቦች ሁልጊዜ ራሽናል ናቸው የሚለው አስተሳሰብ ግለሰቦች በአብዛኛው ራሽናል ናቸው በሚለው ተተክቷል፡፡
ራሽናል ባልሆኑ ጊዜስ ለሚለው ደግሞ መልሱ ግለሰቦች ተገማች በሆኑ መልኩ ኢራሽናል ናቸው የሚለው ነው፡፡ ግለሰቦች ኢራሽናል ናቸው ሲባል፤ አንዳንዴ (ተገማች በሆኑ ሁኔታዎች) የሚፈልጉትን አያውቁም፤ ወይም መምረጥ አይችሉም (የማይፈልጉትን፤ የማይበጃቸውን ይመርጣሉ)፤ ወይም ራሳቸውን መቆጣጠር አይችሉም ወደሚለው ይመራናል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ይህን ሙሉ ለሙሉ ለማስረዳት አይቻልም፡፡ ሆኖም ከጽሑፉ ዓላማ አንጻር አንዳንድ ነገሮችን ብቻ መጨመር ይቻላል፡፡
ግለሰቦች የሚፈልጉትን እንደማያውቁና መምረጥ መቻላቸውን እንድንጠራጠር ከሚያደርጉን ነገሮች አንደኛው ግለሰቦች ምን ያህን ምርጫቸው በሚፈልጉት ሳይሆን በምርጫው አቀራረብ እንደሚወሰን የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ምሳሌዎች፤
- በአንድ ድርጅት ውስጥ ያሉ ሠራተኞች የቁጠባ እድል በቀጣሪያቸው ቀረበላቸው፡፡ ከደመወዛቸው 10 ከመቶ ከሚሆነውን በተዘጋጀው ፕሮግራም ከቆጠቡ፤ ቀጣሪው ጨምሮላቸው 13 ከመቶ ያደርገዋል፡፡ ምርጫው የሠራተኞቹ ነው፡፡ ድርጅቱ በዚህ ፕሮግራም መሳተፍ የሚፈልጉ የድርጅቱ ሠራተኞች ኪሳብ ክፍል እየሄዱ ፈቃደኝነታቸውን የሚገልጽ ፎርም ላይ እንዲፈርሙ አስታወቀ፡፡ ይህን የቁጠባ ሃሳብ ሌላ ድርጅትም ለሠራተኞቹ አቀረበ፡፡ ከመጀመሪያው ቀጣሪ የሚለየው ሁለተኛው ቀጣሪ ለሠራተኞቹ የሰጠው ማስታወቂያ እንዲህ የሚል ነው፤ ሁሉም ሠራተኛ በዚህ የቁጠባ ፕሮግራም ለመሳተፈ እንዲፈልግ ታስቦ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ከደመወዛቸው ይቆረጣል፤ ነገር ግን የማይፈልግ ካለ የደመወዝ ቀን ከመድረሱ በፊት ሒሳብ ክፍል በመሄድ በተዘጋጀው ፎርም ላይ አለመፈለጉን ለመግለጽ ይፈርም፡፡ በሁለቱም ድርጅቶች የቀረቡት ምርጫዎች ተመሳሳይ ናቸው፤ የመቆጠብና ያለመቆጠብ፡፡ መቆጠብ የሚኖረው ውጤትም ተመሳሳይ ነው፤ 10 ከመቶ ከቆጠቡ 13 ከመቶ እንደቆጠቡ ይቆጠራል፡፡ በሁለቱ ድርጅቶች የሚሠሩት ሠራተኞች ተመሳሳይ ናቸው ብለን ካሰብን እና እነሱም ራሽናል ናቸው ብለን ካሰብን፤ በሁለቱም ድርጅቶች የቆጠቡት ሰዎች በመቶኛ ብዙ መለያየት የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም ተመሳሳይ ምርጫ ስለቀረበላቸው፡፡ ልዩነቱ ምርጫው የተገለጸበት መንገድ ነው፡፡ በመጀመሪያው ድርጅት መቆጠብ የሚፈልግ መፈረም አለበት፡፡ በሁለተኛው ድርጅት መቆጠብ የማይፈልግ ነው የሚፈርመው፡፡ ልዩነቱ የዲፎልት ምርጫው ላይ ነው፡፡ በመጀመሪያው ድርጅት የዲፎልት ምርጫው አለመቆጠብ ነው፡፡ በሁለተኛው ድርጅት ዲፎልት ምርጫው መቆጠብ ነው፡፡ በሁለቱም ሠራተኞቹ የመምረጥ ነጻነት አላቸው፡፡ በሚገረም ሁኔታ በተመሳሳይ ሁኔታዎች የተሰበሰቡ ማስረጃዎችና የተሰሩ ሙከራዎች የሚያሳዩት ምንም እንኳ በይዘት ምርጫዎቹ ተመሳሳይ ቢሆኑም፤ ውጤታቸው ግን መለየቱ ነው፡፡ ዲፎልት ምርጫው መቆጠብ ሲሆን፤ ብዙ ሰው ይቆጥባል፡፡ ዲፎልት ምርጫው አለመቆጠብ ከሆነ ግን ብዙ ሰው አይቆጥብም፡፡ ይህ ግለሰቦች የሚፈልጉትን ያውቃሉ፤ የሚበጃቸውን መምረጥ ይችላሉ፤ ራሳቸውን መቆጣጠር ይችላሉ የሚለውን ግምት ጥያቄ ውስጥ ይከታል፡፡
- ሁለት ዓይነት አማራጭ ቀዶ ጥገናዎችን እንውሰድ፡፡ ቀዶ ጥገናዎቹ የሚከተለው የስኬት ሪከርድ አላቸው፡፡ የመጀመሪያውን ቀዶ ጥገና ካደረጉ ሰዎች መካከል 95 ከመቶ የሚሆኑት ቀዶ ጥገናውን ካደረጉ በኋላ ለአሥር ዓመታት በጥሩ ጤና ይኖራሉ፡፡ ሁለተኛውን ቀዶ ጥገና ካደረጉ ሰዎች መካከል 5 ከመቶ የሚሆኑት ቀዶ ጥገናውን ባደረጉ በአሥር ዓመታት ውስጥ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ አንድ በሽተኛ እነዚህ ሁለት ምርጫዎች ቢቀርቡል የትኛውን ትመርጣለህ? ምርጫዎቹ በመሠረቱ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ልዩነቱ ምርጫዎቹ የተገለጹበት ቋንቋ ነው፡፡ ራሽናል የሆኑ የተለያዩ ሰዎች በሁለት ተከፍለው፤ ለአንደኛው ቡድን አንደኛው መረጃ፤ ለሁለተኛው ቡድን ሁለተኛው መረጃ ቢቀርብላቸው ምርጫቸው ተመሳሳይ መሆን አለበት፡፡ ነገረ ግን የተለያዩ ጥናቶች ይህ እንደማይሆን ያሳያሉ፡፡ ሁለተኛው መረጃ የቀረበላቸው ሰዎች ቀዶ ጥገናውን የበለጠ ይፈሩታል፡፡
- አንድ ሱሪ ለመግዛት ገበያ የወጣ ሰው የመጀመሪያው ሻጭ የሱሪውን ዋጋ 3000 ብር ቢለውና፤ ሌላኛው ሻጭ ተመሳሳይ ሱሪን 2500 ቢለው፤ ምንም እንኳ እንዲህ ዓይነት ሱሪን ከ2000 ብር በላይ ላለመግዛት ከቤቱ ቢወጣም ሱሪውን በ2500 የመግዛት እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡
እንዲሁም ሰዎች መረጃዎችን ሳይሆን አጭር-አቋራጭን፤ ልምድን፤ ሌሎች ሰዎችን የመሳሰሉትን አይተው እንደሚወስኑ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡ ምሳሌ
- ምን ያህን ግለሰቦች ለንብረታቸው የእሳት አደጋ ኢንሹራንስ ይገዛሉ የሚለው በእሳት አደጋ የመጠቃት እድል ይወሰናል፡፡ ነገር ግን ግለሰቦች ተጨባጭ መረጃን ሳይሆን የሚያዩት፤ ስለ እሳት አደጋ ሲያስቡ የመጣቃት አድላችን ምን ያህል ነው ብለው ያምናሉ የሚለው ነው፡፡ በአንድ ወቅት እጅግ ከፍተኛ አደጋ ያደረሱ ከፍተኛ አደጋዎች ከተከሰቱ ምንም እንኳ በእሳት አደጋ በመጠቃት አማካኝ እድል ባይጨመርም፤ ስለ አደጋው ብዙ የሰሙ፤ ያዩ፤ ያነበቡ ሰዎች ኢንሹራንስ የመግዛት እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡
ግለሰቦች ራሽናል ናቸው ሆነ ግለሰቦች ተገማች በሆነ መልኩ ኢራሽናል ናቸው የሚሉት አስተሳሰቦች ለተቋም፤ ፓሊሲና ሕግ ቀረጻ እጅግ በጣም ብዙ ትምህርቶች ይሰጣሉ፡፡ ሁሉንም በዚህ ጽሑፍ መተንተን አይቻልም፡፡ በሌሎች ጽሑፎች እመለስበታለው፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ግን አግባብነት ያላቸውን አሳቦች በዚህ ጽሑፍ የተለያዩ ክፍሎች በተደጋጋሚ እመለስበታለው፡፡
1.2.5 የወንጀል ሕግ ከግለሰቦች ራሽናሊቲ የሚማረው ትምህርት
ግለሰቦች ራሽናል ናቸው የሚለው አስተሳሰብ የወንጀል ኢኮኖሚክስ መሠረት ነው፡፡ ለዛም ነው ከዚህ በፊት ባሉት የጽሑፉ ክፍሎች ቅጣት በመጨመር እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ወንጀልን መቀነስ ይቻላል የተባለው፡፡ እንዲሁም በግ የሰረቀ ሰው በሞት የሚቀጣ ከሆነ፤ አንዴ በግ የሰረቀ ሰው እረኛውንም ሊገለው ይችላል የሚለው ሙግት የቀረበው፡፡
ግለሰቦች ራሽናል መሆናቸው የሚሰጠን ሌላኛው ትምህርት ግለሰቦች በሕግ የተቀመጠን ቅጣት ብቻ ሳይሆን ግምት ውስጥ የሚያስገቡት የመያዝና የመቀጣት አድላቸውን ጭመር መሆኑን ነው፡፡ በሕግ የተቀመጠው ቅጣት 1000 ብር ቢሆን እና የመያዝና የመቀጣት እድሉ 10 ከመቶ ከሆነ አንድ ግለሰብ ግምት ውስጥ የሚያስገባው ቅጣት 1000 ብር ሳይሆን 100 ብር ነው፡፡ ሌላኛው ጉዳይ ግለሰቦች የመያዝና የመቀጣት እድላቸውን ለማወቅ እንደ ማንኛውም ጉዳይ ተጨባጭ መረጃዎችን ይሰበስባሉ፡፡ ይህን እድላቸውን በትክክል ለማወቅ ሲሉ ተጨማሪ መረጃ መሰብሰብ ያለው ወጪ ከሚሰጣቸው ጥቅም አንጻር ትንሽ እስከሆነ ድረስ መረጃ ይሰበስባሉ ማለት ነው፡፡
በተጨማሪም ግለሰቦች በ10 ከመቶ እና በ12 ከመቶ መካከል ያለውን የመያዝ እድል ጠንቅቀው ያውቁታል የሚለው ግምትም ከዚሁ አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው፡፡
1.2.6 የወንጀል ሕግ ከግለሰቦች ተገማች የራሽናሊቲ ድክመቶች የሚማረው ትምህርት
በአንጻሩ ግለሰቦች ተገማች በሆነ መልኩ ራሽናል አይደሉም የሚለው አስተሳሰብ ለወንጅል ሕግ አቀራረጽና ለሕግ አስከባሪ አካላት የሚኖሩ አንድምታ አለ፡፡ አብዛኛውን ጉዳይ ወደፊት እንመለስበታለን፡፡ ካሁኑ ጉዳይ ጋር የሚያያዘው ግለሰቦች እንዴት የመያዝና የመቀጣት እድልን እንደሚረዱ ነው፡፡ ራሽናል የሆኑ ሰዎች ለውሳኔዎቻቸው የሚያስፈልጉ መረጃዎችን በሙሉ ይሰበስባሉ፡፡ ተጨማሪ መረጃ መሰብሰብ የሚያመጣው ተጨማሪ ወጪ መረጃውን በመሰብሰብ ከሚገኘው ጥቅም እስካነሰ ድረስ የሚተውት ተጨማሪ መረጃ አይኖርም፡፡ እነዚህ አስተሳሰቦች ሰዎች ራሽናል ናቸው ከሚለው ይፈሳሉ፡፡
ነገር ግን ከዚህ ክፍል በፊት እንዳየነው ሰዎች መረጃዎችን ሳይሆን አጭር-አቋራጭን፤ ልምድን፤ ሌሎች ሰዎችን የመሳሰሉትን አይተው እንደሚወስኑ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ፤ በአይምሮ ተገኝነት የሚባለውን ጉዳይ ማየት ይቻላል፡፡ አንድ መረጃ በአካል ተገኝ ነው ማለት በአይምሮ ተገኝ ነው ማለት አይደለም፡፡ በቀላሉ ለማስቀመጥ ያህል መረጃው አለ፤ ነገር ግን መረጃው በታሸገበት ፓስታ ምክንያት መረጃው የሚጠቅማቸው ሰዎች መረጃውን በአካል ቢያገኙትም ላይገባቸው ወይም በሚፈለግበት ጊዜ ላያስታውሱት ይችላሉ፡፡ የታሸገበት ፓስታ ስንል መረጃው የተገለጸበት ቋንቋን ይጨምራል፡፡ መረጃውን የሚጠቀመው ሰው የሚናገረው ቋንቋ አማርኛ ብቻ ከሆነ እና መረጃው ግን የተጻፈው ግን በወፍ ቋንቋ ከሆነ ሰውየው ይህን መረጃ አይጠቀምበትም ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ተመራማሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች ጥናት ቢሰሩምና፤ ለፓሊሲ ጠቃሚ የሚሆን እውቀት ወይም መረጃ ቢያገኙም፤ መንግሥት (ፓሊሲ አውጪዎች) ግን የእነሱን ጥናቶች ችላ እንደሚሏቸውና እንደማይጠቀሙባቸው ያማርራሉ፤ ይከሳሉ፡፡ እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ ግን እነዚህ ተመራማሪዎች ልብ ሊሉት የሚገባው ነገር ፓሊሲ አውጪዎችን ቢሆን ሰዎች ናቸው፤ በገባቸውና ባስታወሱት ልክ ነው ውሳኔ የሚሰጡት (በሌላ ጽሑፍ ወደዚህ ጉዳይ ተመልሼ እመጣለው)፡፡ በመሆኑም ለምንድን ነው ያልተጠቀሙበት ብለው ይጠይቁ፡፡ ተጨማሪ ሥራ ስለሚቀረው ሊሆን ይችላል፡፡ ጥናቱና ውጤቱ በአካል ቢገኙም (ለምሳሌ ታትመው ወተዋል እንበል)፤ በጉዳዩ ላይ ከሰለጠነ ሰው ውጭ ያለ ሰው ጥናቱን አንብቦ ይረዳዋል ወይ፤ መረጃው በአካል ብቻ ሳይሆን በአይምሮ ተገኝ ነው ወይ የሚሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ አለባቸው፡፡ አንደኛ እኛ አገር ጥናትና ሳይንስ በእንግሊዘኛ ነው የሚሰራው፤ ፓሊሲ አውጪዎችና መንግሥት ግን የሚሰሩት በአማርኛ፤ በኦሮምኛ፤ በትግሪኛ እና በመሳሰሉት ቋንቋዎች ነው፡፡ ሁለተኛ እንግሊዘኛ ብንረዳም፤ የተለያዩ የጥናት መስኮቸ የየራሳቸው የእንግሊዘኛ ቋንቋ አላቸው (የቴክኒክ ቋንቋ)፡፡ በመሆኑም የሚቀረው ሥራ ጥናቱን የመተርጎም፤ በቀላሉና በሚገባ ቋንቋ ጥናቱን መልሶ የማሸግና፤ የጥናቱ ውጤትም ሥራ ላይ እንዲውል የማስተዋወቅ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ በአጭሩ የማሻሻጥ ሥራ ይጠይቃል፡፡ ያለበለዚያ ያወቀ ብቻ ይግዛው፤ ይጠቀምበት ነው የሚሆነው፡፡ ማንንም ዓይነት ሸቀጥ ያወቀ፤ የገባው ብቻ ይግዛው አይልም ነጋዴ፤ ጥቅሙን ያስረዳል፤ ያሽሽጣል፡፡ የእውቀት/የሳይንስ/የመረጃ ድለላ/ማስተዋወቅ ያስፈልጋል፡፡ በሌሎች አገሮች እነዚህን ተጨማሪ ሥራዎች የሚሰሩ ተቋማት በብዛት አሉ፤ ቲንክ ታንክስ ይባላሉ፡፡ በአብዛኛው አዲስ ግኝት ፍለጋ ላይ ሳይሆን፤ የመረጃ እሸጋ፤ ድለላ፤ ማሻሻጥ፤ እና ማስተዋወቅ ላይ ነው የሚጠመዱት፡፡
አንድን መረጃ የመረዳትና የማወቅ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ መረጃውን በሚፈለገው ጊዜ ማስታወስ መቻልና አለመቻልን ይመለከታል፡፡ ለምሳሌ የኮካኮላን ምርት በዓለም ላይ ለማስተዋወቅ በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ለማስታወቂያ ይወጣል፡፡ ማጋነን ካልሆነ አሁን በአለም ላይ ኮካኮላን የማያውቅ አለና ነው ይህ ሁሉ ሃብት የሚባክነው? ጉዳዩ የማወቅና ያለማወቅ ሳይሆን የማስታወስና ያለማስታወስ ነው፡፡ ሰዎች ውሳኔ የሚወስኑት በአካል በሚገኙ መረጃዎች ተመስርተው ሳይሆን፤ በአይምሮ ከሚገኙ መረጃዎች ተመስርተው ነው፡፡ በተጨማሪም ሰዎች ውሳኔ የሚወስኑት በአይምሮ በሚገኙ መረጃዎች ተመስርተው ሳይሆን፤ በሚያስታውሷቸው መረጃዎች ተመስርተው ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ ምን ያህል ሰዎች ኮካ ኮላን ያውቁታል ሳይሆን፤ ጥማታቸውን ለማርካት ሲፈልጉ ምን ያህል ኮካ ኮላን ያስታውሱታል ነው፡፡ በቀላሉ የሚታወሰው ደግሞ በቅርብ ቀን ያየነውን፤ ያነበብነውን፤ የሰማነውን ነው፡፡ ለዛ ነው ኮካ ኮላ በተደጋጋሚ ያን ያህል ሃብት እያወጣ ማስታወቂያ የሚሠራው፡፡ ይህ ማስታወቂያ መረጃ የመስጠት ዓላማ ሳይሆን ያለው የማስታወስ ዓላማ ነው ያለው፡፡ (መረጃና መንግሥት ከኢኮኖሚክስ አንጻር በሚል በሌላ ጊዜ በሌላ ጽሑፍ የመመለስ አሳብ አለኝ)
ሌላኛው ጉዳይ ግለሰቦች አንድ አሳብ ስለገባቸውና ስላስታወሱት ብቻ ይጠቀሙበታል ማለት አይደለም፡፡ ግለሰቦቹ በአሳቡ ማመን አለባቸው፡፡ እንዴት የሚለው ጥያቄ ሰፊ ትንተና ያስፈልገዋል፡፡ ኒዮ-ሊብራሊዝም የአሳብ ተቀባይነት የሚወሰነው የተለያዩ አሳቦችና አሳቦቹን የሚደግፉ ማስረጃዎች በነጻነት ለገበያ ቀርበው፤ በአሳቦቹ መካከል በሚኖር ውድድር የበለጠ ተቀባይነት ያገኘው አሸናፊ ሆኖ ይወጣል፡፡ ተቀባይነት የሌለው ደግሞ ይከስማል ይላሉ፡፡ በዚህ አስተሳሰብ መሠረት አሸንፎ የሚወጣው ብዙና ሳይንሳዊ መረጃ ያለው አሳብ ነው፡፡ የዚህ አስተሳሰብ መሰረቱ ግለሰቦች አንድን አሳብ የሚቀበሉት በአሳማኝ በቂና ሳይንሳዊ መረጃ ሲደገፍ ብቻ እንደሆነ ማመን ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ሰዎች ራሽናል ናቸው ከሚል ይመነጫል፡፡ ነገር ግን ሰዎች አሳቦች የሚመርጡት መረጃን መሠረት አድርገው ነው የሚለው አስተሳሰብ ሁል ጊዜ ትክክል አይደለም፡፡ እንደማንኛውም ምርጫ ሰዎች አንድን አሳብ የሚደግፉት የአሳቦቹ ምርጫ ከቀረበበት ፍሬም፤ ተመሳሳይ ሰዎች ምንን መረጡ ከሚል፤ እና ከመሳሰሉት አንጻር ነው፡፡ ዋናው ነጥብ ሰዎች እንዲያስታውሱት ብቻ ሳይሆን እንዲያምኑበትም ያስፈልጋል፡፡
ወደ የመያዝና የመቀጣት እድልም ስንመጣ ያው ነው፡፡ ጉዳዩ በተጨባጭ፤ ሳይንሳዊ መረጃዎች የመያዝና የመቀጣት እድል ምን ያህን እንደሆነ ያሳያሉ ሳይሆን፤ ዜጎች የመያዝና የመቀጣት እድል ምን ያህል ነው ብለው ያምናሉ፤ ያስታውሳሉ የሚለው ነው፡፡ መረጃዎች የሚያሳዩት ሳይሆን ግለሰቦች የሚያምኑትና የሚያስታውሱትን ነው ዋናው ጉዳይ፡፡ የመያዝና የመቀጣት እድል ምን ያህል እንደሆነ መረጃዎች የሚያሳዩት፤ ዜጎች የመያዝና የመቀጣት እድላቸው ምን ያህል እንደሆነ ከሚያምኑትና ከሚያስታውሱት፤ ይበልጥም፤ ሊያንስም ይችላል፡፡ ከበለጠ፤ ምንም እንኳ መንግሥት የመያዝና የመቀጣት እድልን በተግባር ለማሳደግ ተጨማሪ ወጪ ቢያወጣም፤ ዜጎች ግን ይህን ለውጥ ካለመረዳታቸው ወይም ካለማስታወሳቸው የተነሳ ወንጀል ሊቀንስ አልቻለም ማለት ነው፡፡ እንዲሁም መረጃዎች የሚያሳዩት ዜጎች ከሚያምኑትና ከሚያስታውሱት ያነሰ ከሆነ፤ መንግሥት በቀላል ወጪ ወንጅልን በቀላሉ ቀንሷል ማለት ነው፡፡
ለዚህ ማሳያ የሚሆነኝና የተሰበረው መስኮት ፓሊሲ ተብሎ ስለሚጠራው ጉዳይ ትንሽ ልበል፡፡ በአንድ ወቅት የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ሩዲ ጂሊዋኒ የተከተሉት ፓሊሲ መጠሪያ ነው፡፡ ከንቲባው በጣም ቀላልና የሚታዩ የሕግ ጥሰቶችን እየተከታተሉ ከተቻለ ወዲያው እንዲቀጡ፤ አጥፊው ካልታወቀም እየተከታተሉ ጥፋቱን ማከም፤ ማስተካከል የሚል ፓሊሲ መከተል ጀመሩ፡፡ ቀይ መብራት የሚጥስ እግረኛ እዛው ተይዞ ቅጣቱን ይከፍላል፡፡ ቆሻሻ የሚጥል ሰው ወዲያው ይቀጣል፡፡ የሰከሩ ጎረምሶች ሌሊት የሰበሯቸው መስኮቶች ካሉ፤ ጠዋቱኑ ይጠገናሉ ወይም ይቀየራሉ፡፡ አንዳንድ ቡድኖች በባቡሩች፤ በግድግዳዎችና በሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች በቀለም የሚጽፉቸውን ጽሑፎች ወይም የሚስሏቸውን ሥዕሎች የሚያጠፉ ቡድኖች ተመደቡ፤ ለዚህም በጀት ተመደበ፡፡ የኛ አገር ሰው አስመሳይ፤ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ሊላቸው ይችላል ከንቲባውን፡፡ ነገር ግን ከትንሽ ጊዜ በኋላ የተገኘው ውጤት ሌላ ነው፡፡ ከንቲባው ትኩረት አድርገው የሰሩባቸው የሕግ ጥሰቶች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ዓይነት ከፍተኛ ወንጀሎችም ቁጥራቹ ሊቀንስ ችሏል፡፡ ልብ በሉ፤ እነዚህን ከፍተኛ ወንጀሎች በተመለከተ ከንቲባው ያደረጉት ለውጥ ባይኖርም እንኳ፤ የሚታዩ ጥፋቶችን በመቅጣትና ይህንንም ሌሎች እንዲያዩት በማድረጋቸው የተነሳ ነዋሪዎች ማንኛውንም ዓይነት ጥፋት ቢያጠፉ የመያዝና የመቀጣት እድላቸው መረጃው ከሚያሳየው በላይ ነው ብለው እንዲያምኑ አድርጓቸዋል፡፡ በመሆኑም ወንጀል ሊቀንስ ችሏል፡፡ ማጅራት መቺዎችን የመቀነስ ሥራ የፓሊስ ብቻ ሳይሆን፤ የጽዳትና ቁንጅና ቢሮም፤ የትራፊክ ፓሊስም ነው፡፡ የአገሬ ሰው ሲተርት ወይኖን ግረፈው ኳሊ እንዲሰማህ ይላል፡፡
1.3 ሕግን አለማክበርና አለማስከበር ተላላፊ በሽታ ስለሆን ማክበርና ማስከበር የማይቻልን ወይም ያልታሰበን ሕግ መጀመሪያውኑ አለማውጣት ይሻላል?
ሎን ፉለር የሚባለው ጸሐፊ “The Internal Morality of the Law” በሚለው መጽሐፉ መንግሥት ራሱ የማያከብረውና ሌሎች እንዲያከብሩት ለማድረግ የማያስፈጽመው ሕግ ባይወጣ ይሻላል፡፡ ምክንያቱም ይለናል ይህን ሕግ አለማክበርና አለማስፈጸም ወደ ሌሎቹም ይተላለፋልና፡፡
ሎን ፉለር አንድን ሕግ አለማክበርና አለመፈጸም ወደ ሌሎቹ ይተላለፋልና የማይከበርና የማይፈጸም ከሆነ ባይወጣ ይሻላል፡፡ ከወጣ ደግሞ ሊከበርና ሊፈጸም ይገባል፡፡ ነገር ግን ሎን ፉለር ይተላለፋል ቢልም እንኳ እንዴት እንደሚተላለፍ አያብራራም፡፡
እንደ እኔ እምነት የመተላለፊያው መንገድ ሁለት ናቸው፤
አንደኛ ባለቤቱ ያላከበረውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም ይባላል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ያላከበረውን ሕግ እንዴት ዜጎች ያከብሩታል የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ የሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው የሕግ ትርጉም በማንኛው ፍርድ ቤት አስገዳጅ ነው ይላል አንድ አዋጅ፡፡ ይህ በራሱ የሚያስነሳው ጥያቄ አለ፡፡ ይህን የሕግ ድንጋጌ ለማስከበርና ለማስፈጸም የሚረዳው ምንድን ነው? አንድ ፍርድ ቤት የሰበርን ችሎቱ የሰጠውን የሕግ ትርጉም ወደ ጎን በማለት የራሱን ትርጉም ቢሰጥ ችሎቱ ወይም ዳኛው ምን ይደርስበታል? የተቀመጠ ቅጣት ወይም ሽልማት ከሌለ ይህ ድንጋጌ ሊፈጸም የማይችል ሕግ በመሆኑ እንደ ሎን ፉለር አባባል ባይወጣ ይሻል ነበር?
ሌላው ጉዳይ እራሱ ሰበር ሰሚ ችሎቱ የማያከብረውን የሕግ ትርጉም እንዴት ሌሎቹ ሊያከብሩት ይቻላቸዋል፡፡ ሰበር ሰሚው የራሱን የሕግ ትርጉም እንደማያከብረው ማስረጃዎች ቢኖሩም አሁን ከተነሳውበት ጉዳይ ጋር ስለማይያያዝ ለጊዜው ልተወው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ባለቤቱ ያላከበረውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም የሚለው ነው፡፡
ሁለተኛ ዜጎች ሕግን ለማክበርና ላለማክበር ሲወስኑ ብዙ ነገሮችን ግምት ውስጥ ያስገባሉ፡፡ እንደ ኤኮኖሚክስ ባለሙያዎች አባባል፤ ሕጉን በመጣስ የሚገኘው ጥቅም ሕጉን በመጣስ ከሚያስከትለው ቅጣት ካነሰ ግለሰቦች ሕጉን ያከብራሉ፡፡ የሚያስከትለው ቅጣት የተባለው በሕጉ ላይ የተቀመጠው ቅጣት አይደለም፡፡ ይልቅስ ዜጎች የሚያወዳድሩት በሕጉ ላይ የተቀመጠው ቅጣት ሲባዛ በመያዝና በመቀጣት እድል ነው፡፡ የመያዝና የመቀጣት እድል መቶ በመቶ አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፤ እንዲሆንም መሥራት አይገባም፡፡ ሕጉን የጣሰ ሁሉ ይያዛል፤ ማስረጃ ይገኝበታል፤ ይቀጣል ማለት አይደለም፡፡ ለዛ ነው ይህ እድል ግምት ውስጥ የሚገባው፡፡
የመያዝና የመቀጣት እድል ስናወራ ሁለት ነገር መለየት አለብን፡፡ አንደኛው ትክክለኛው/እርግጠኛው እድል ሲሆን፤ ሁለተኛው ሰዎች የመያዝ እድላቸው ብለው የሚያምኑት ነው፡፡ እላይ ከተቀመጠው ቀመር አንጻር አግባብነት ያለው ሰዎች የመያዝ እድላቸው ምን ያህል ነው ብለው የሚያምኑት እንጂ፤ ተጨባጭ እውነታው ነው፡፡ ለዛ ነው ሲሲቲቪ ካሜራ ምንም እንኳ የማይሠራ ቢሆንም ሰዎች የመያዝ እድላችን ከፍተኛ ነው ብለው እንዲያምኑ የሚያደርጋቸው፡፡
ሁለተኛው ነጥብ ግለሰቦች የመያዝ እድላቸውን ሲያመዛዝኑ፤ አንድን የተለየን ሕግ ቢጥሱ የመያዝና የመቀጣት እድላችን ምን ያህል ነው ብለው ሳይሆን በአጠቃላይ በአማካኝ ሕግ (ማንኛውንም) ሕግ ቢጥሱ የመያዝና የመቀጣት እድላቸውን የሚያሰሉት፡፡ በመሆኑም በተግባር ሊያከብረውን ሊያስከብረው የማይፈልገውን ሕግ መንግሥት አውጥቶ ቁጭ ቢያደርገው በአጠቃላይ ዜጎች የመያዝና የመቀጣት እድላችን ብለው የሚያስቡትን ይቀንሰዋል፡፡ ይህ ደግሞ ያንን የማይከበረውን ሕግ ብቻ ሳይሆን ሌሎቹንም ሕጎች እንዲጥሱ ያበረታታቸዋል፡፡
ስለዚህ ቁም ነገሩ ልናከብረውን ልናስከብረው የማንችለውን ወይም የማንፈልገውን ሕግ ባናወጣው ይሻላል፡፡ ተላላፊ በሽታ ስለሆነ፡፡
ከዚህ ተጸራሪ የሆኑ ሙግት የሚያቀርቡ ምሁራን አሉ፡፡ ሕግ ባይፈጸምም ኤክስፕረሲቭ ዋጋ አለው ይላሉ፡፡ ይህ ዋጋው ወይም ዓላማው ደግሞ መንግሥትና ሕብረተሰቡ ምን ያህን አንድን ተግባር ወይም ባህሪ እንደሚጸየፉት ማሳወቅ ነው፡፡ ይህን ማሳወቅ ማውጣቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ ባይተገበርም ይላሉ፡፡ ለምሳሌ ከእንሰሳት ጋር ወሲባዊ ግንኙነት መፈጸም እንደ ወንጀል ይቆጠራል በኛ ሃገር ሕግ፡፡ ይህን ሕግ ማስፈጸም አስቸጋሪ ቢሆንምና ባይከበርም እንኳ ዞሮ ዞሮ ሕብረተሰቡ ምን ያህል ተግባሩን እንደሚጸየፈው ስለሚያሳይ መኖሩ (ምንም እንኳ መንግሥት ይህን ወንጀል እየተከታተለ ባይተገብረውም) ጥሩ ነው ይላሉ፡፡ ሕግ ኤክስፕሬሲቭ ጥቅም አለው የሚሉ ሰዎች ከሚጠቅሷቸው አንደኛው ምሳሌ ስዊዘርላንድን ይመለከታል፡፡ የስዊዝ ግዛቶች አብዛኞቹ ማንም እድሜው የደረሰ ዜጋ ምርጫ ላይ እንዲሳተፍ ያስገድዳሉ፡፡ አንድ ዜጋ ካልመረጠ ከአንድ ዶላር ያልበለጠ ቅጣት ይጥላሉ፡፡ ቅጣቱ ትንሽ ሆኖም ብዙ ጊዜ ይህን ቅጣት የማስፈጸም ሥራ አይሰራም፡፡ በአንድ ወቅት የተወሰኑት ግዛቶች ይህን ሕግ ሻሩት፡፡ ማለትም መምረጥም ሆነ አለመምረጥ የግለሰቡ ምርጫ ነው፡፡ የሕጎቹ መሻር ለምርጫ በሚወጣው ሕዝብ ቁጥር ላይ ለውጥ ሊኖራቸው አይገባም፤ ምክኒያቱም ቅጣቱ ትንሽ ነው፤ በዛ ላይ የመከሰስና የመቀጣት እድሉ ዜሮ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ነገር ግን በተጨባጭ የታየው ጉዳይ የሕጉን መሻር ተከትሎ የሚመርጠው መራጭ መቀነሱ ነው፡፡ እናም ይላሉ እነዚህ የሕግ ምሁራን ምንም እንኳ፤ ሕጉ የጣለው ቅጣት ትንሽ ቢሆንም ወይም የመከሰስና የመቀጣት እድሉ ዜሮ ሊባል ቢችልም እንድ ሕግ በሰዎች ባህሪና ውሳኔ ላይ ውጤት ሊኖረው ይችላል፡፡ ይህን የሚያደርገው ሕጉ ኤክስፕሬስ የሚያደርገው አገራዊ አቋም በመኖሩና ሰዎች ከዚህ አቋም ማፈንገጥ ስለማይፈልጉ ነው፡፡
እናንተ ምን ትላላቹ? ቀላል የሚመስል ጥያቄ ጀምሬ ነገሩ ተወሳሰበ፡፡ እዚህ ላይ ላቁምና ምናልባት በሌላ ጽሑፍ ሕግ ኤክስፕሬሲቭ ጥቅም አለው የሚሉትን ምሁራንና አቋማቸው እላይ ከተገለጸው የተላላፊነት በሽታ ሃሳብ ጋር እንዴት ይታረቃል የሚለውን ለማየት እሞክራለው፡፡
(ክፍል ሦስት ይቀጥላል፤ በክፍል ሦስት የሚከተሉትን ጉዳዮች እዳስሳለሁ፤
- የሕግ ጥሰትን ለመከታተል፤ ለመፈተሸና ለመመርመር የሚመደብ ሃብትን እንዴት መጠቀም ይገባል
- የመያዝና የመቀጣትን እድል ለመጨመር ሲባል የሕግ ማስከበር ሥራን በተወሰነ ደረጃ ፕራይቬታይዝ ማድረግ
- ወንጀለኛ መቀጣቱ ብቻ ሳይሆን ሲቀጣም መታየት አለበት፤ የቴሌቪዥኑ የፓሊስ ፕሮግራም
- የፍትሕ ሥርዓቱ ሙስና ችግር
- የወንጀልና ቅጣት ፌዴራሊዝም
- ከቅጣትና ሽልማት ማን ይሻላል
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments