የወንጀልና ቅጣት ግሽበት፤ ቅጣት እንደ እንቁ እና ሌሎች ጉዳዮች ከወንጀል ኤኮኖሚክስ አንጻር ክፍል አንድ
የዚህ ጽሑፍ ርዕስ ምንም እንኳ የወንጀል ኤኮኖሚክስ ቢልም፤ እንዲሁም ይህ ጽሑፍ የተጠቀመባቸው የጥናትና ምሁራዊ ጽሑፎች የኖቤል ሎሬት ጌሪ ቤከር የጀመረውና በሌሎች ምሁራን የዳበረው የጥናት ክፍል የወንጀል ኤኮኖሚክስ በመባል ቢጠራም፤ በጽሑፉ የሚነሱት ዋና ዋና ነጥቦች በአጠቃላይ በቅጣት ለማስፈጸም የሚሞከርን ሕግን ይመለከታል፡፡ በመሆኑም ወንጀል ባይሆንም በአስተዳደራዊም ሆነ በሌላ ዓይነት ቅጣት የሚፈጸም ሕግን በዚህ የጥናት ዘርፍ በዳበሩ አስተሳሰቦች አንጸር መገምገም እንችላለን፡፡
ግለሰቦች ሕግን ለማክበርና ላለማክበር ሲወስኑ ብዙ ነገሮችን ግምት ውስጥ ያስገባሉ፡፡ (ይህ አስተሳሰብ ግለሰቦች ሕግን ሲጥሱ አስበውበት ነው ከሚል ይነሳል፡፡ በእርግጥ በደመነፍስ ወይም ያለእውቀት የሚፈጸም የሕግ ጥሰቶች አሉ፡፡) እንደ ኤኮኖሚክስ ባለሙያዎች አባባል፤ ሕጉን በመጣስ የሚገኘው ጥቅም ሕጉን በመጣስ ከሚያስከትለው ቅጣት ካነሰ ግለሰቦች ሕጉን ያከብራሉ፡፡ የሚያስከትለው ቅጣት የተባለው በሕጉ ላይ የተቀመጠው ቅጣት አይደለም፡፡ ይልቅስ ዜጎች የሚያወዳድሩት በሕጉ ላይ የተቀመጠው ቅጣት ሲባዛ በመያዝና በመቀጣት እድል ነው፡፡ ትክክለኛው ቀመር ይህ ነው፤
ሕግ በመጣስ የሚገኘው ጥቅም ≤ (በሕጉ የተቀመጠው ቅጣት X የመያዝና የመቀጣት እድል X ዲስካውንት ፋክተር) + ሕጉን ለመጣስ የሚወጣው ወጪ + (ኢመደበኛ ቅጣት X የመያዝና የመቀጣት እድል X ዲስካውንት ፋክተር)
ቅጣትን መጨመር፤ እስከ ምን ድረስ
በዚህ ቀመር መሠረት የሕግ መከበረን ለመጨመር ማድረግ ያለብን ነገሮችን ይጠቁማል፡፡ አንደኛውና እንደ ቀላል ተደርጎ የሚወሰደው በሕጉ የተቀመጠውን ቅጣት መጨመር ነው፡፡ አንድ ሕግ በሚገባ አልተተገበረም፤ ቅጣቱ የተከለከለውን ተግባር አልቀነሰውም፤ ተብሎ ሲታሰብ ሕግ አውጪዎችም ሆኑ የተለያዩ አካላት እንደ መፍትሔ አድርገው የሚወስዱት ቅጣትን መጨመር ነው፡፡ ለምሳሌ የመኪና አደጋ ጨምሯል ተብሎ ሲታሰብ፤ በተለይ አሰቃቂ አደጋን ተከትሎ ለትራፊክ ደንቦች ጥሰት የተቀመጡ ቅጣቶች እንዲጨምሩ ሃሳቦች ይቀርባሉ፡፡ አንዳንድ አሰቃቂ ጉዳት ያስከተሉ የሕግ ጥሰቶችን ተከትሎ በሕዝብ የሚቀርቡ የቅጣት ይጨመር ጥያቄዎች ይጨምራሉ፡፡ መንግሥታት ከዚህ ጫና ለመውጣት እና የሕግ ከበሬታን ለመጨመር እንደ ቀላል መንገድ አድርገው የሚወስዱት ቅጣትን መጨመር ነው፡፡ በርግጥ ቅጣትን መጨመር አንዱ መፍትሔ ቢሆንም ነገር ግን ይህ መፍትሔ ሊያመጣው የሚችል ጥቅም ውስን ነው፡፡ እንደውም ያልታሰበ አደጋን ያዘለ ነው፡፡ ቅጣትን መጨመር ይቻላል ነገር ግን እስከምን ድረስ የሚለውን ማየት ተገቢ ነው፡፡
በልማዳዊ የሕግ ባለሙያዎች ቅጣትን አስመልክቶ ሊከበር የሚገባው መርህ ተመጣጣኝነትን ይመለከታል፡፡ ከጥሰቱ ጋር የሚጣጣም ቅጣት መጣል አለበት ይላሉ፡፡ ነገር ግን ተመጣጣኝነት የሚለው መመሪያ እጅግ ጠቅላላ እና ደብሳሳ ነው፡፡ ለምሳሌ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 15 ያስቀመጠውን ድንጋጌ እንመልከት፤ "ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት አለው፡፡ ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን አያጣም፡፡" ከባድ ወንጀል የሚባሉት ምንድን ናቸው? የሞት ቅጣት ሕገ መንግሥቱን ይጥሳል ሊባል የሚችለው ለምን ዓይነት ወንጀሎች እንደ ቅጣት ሲደነገግ ነው? ሁለተኛውና ተያያዥ መመሪያ እና የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ተደርጎ የሚወሰደው ጨካኝና ያልተለመደ ቅጣትን ማስወገድ ነው፡፡ ለምሳሌ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 18 መመልከት ይቻላል፤
ማንኛውም ሰው ጭካኔ በተሞላበት፤ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝና ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው፡፡
ማንኛውም ሰው በባርነት ወይም በግዴታ አገልጋይነት ሊያዝ አይችልም፡፡ ለማንኛውም ዓላማ በሰው የመነገድ ተግባር የተከለከለ ነው፡፡
ማንኛውም ሰው በኃይል ተገዶ ወይም ግዴታን ለማሟላት ማንኛውንም ሥራ እንዲሠራ ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 "በኃይል ተገዶ ወይም ግዴታን ለማሟላት" የሚለው ሐረግ የሚከተሉትን ሁኔታዎች አያካትትም፤
(ሀ) ማንኛውም እስረኛ በእስራት ላይ ባለበት ጊዜ በሕግ መሠረት እንዲሠራ የተወሰነውን ወይም በገደብ ከእስር በተለቀቀበት ጊዜ የሚሠራውን ማንኛውም ሥራ፤
(ለ) ማንኛውም ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናው የማይፈቅድለት ሰው በምትክ የሚሰጠውን አገልግሎት፤
(ሐ) የማኅበረሰቡን ሕይወት ወይም ደህንነት የሚሰጋ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ወይም አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ የሚሰጥ ማንኛውንም አገልግሎት፤
(መ) በሚመለከተው ሕዝብ ፈቃድ በአካባቢው የሚፈጸመውን ማንኛውም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ የልማት ሥራ፡፡
በኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች አመለካከት መሠረት ቅጣት ውድ ኃብት ነው፡፡ የሚያልቅና የማይታደስ ኃብት ነው፡፡ በመሆኑም በቁጠባ መጠቀም አለብን፡፡ ከዚህ በታች የበለጠ ተብራርቷል፡፡
በጓሮ ያለ ጸበል ልጥ መንከሪያ ይሆናል
ቅጣት በበዛ ቁጥር፤ በጣም የተለመደ ከሆነ፤ ተፈሪነቱም ይቀንሳል፡፡ ቅጣት የሚያስፈራራው ሲለመድ ሳይሆን በቁጠባ ስንጠቀምበት ነው፡፡ ለምሳሌ በሆነው ባልሆነው የሚማታ፤ የሚጋረፍ አባት ከተወሰነ በኋላ ዱላው ማስፈራራቱን ያቆማል፡፡ ዱላው ይለመዳል፡፡ በአንጻሩ ዱላውን አልፎ አልፎ የሚጠቀም፤ በሆነው ባልሆነው የማይቆጣ አባት እንኳን ዱላውን አንስቶ ይቅርና ትንሽ ድምጹን ከፍ ሲያደርግ ልጆቹ በፍርሃት ይርበደበዳሉ፡፡ ይህ አባባል በታሪክ አጋጣሚም ተፈትሽዋል፡፡ ለምሳሌ የናዚ መንግስት እንግሊዝን በቀላሉ ለመቆጣጠር በማለት የእግረኛ ጦር ሳይልክ የእንግሊዝ ከተሞችን ሌትና ቀን በቦንብ ይደበድብ ነበር፡፡ አላማው ሕዝቡን አማረን በራሱ መንግስት ላይ እንዲነሳ ማድረግ እንችላለን፤ በኋላም የእግረኛ ጦር ስንልክ ሕዝቡ እያጨበጨበ ይቀበለናል የሚል ነው፡፡ ነገር ግን የናዚ መንግስት ያሰበው አልተሳካም፡፡ በአንግሊዝ ከተሞች የሚወድቀው ቦንብ በበረታና በበዛ ቁጥር የእንግሊዛዊያን ጥንካሬም አልበገር ባይነትም በዛው ልክ ይበረታና ይጨመር ጀመረ፡፡ የናዚ አውሮፕላኖች መምጣታቸውን እና ዜጎች ወደ ቦንብ መጠለያቸው እንዲሄዱ የሚያመለክተው ጡሩንባ ቢነፋም የሚደነግጠው ሰው እጅግ ትንሽ ሆነ፡፡ ይልቅስ የናዚ የጦር አውሮፕላኖች ቦንብ ሲጥሉ የተጎዱ ሰዎችን በመሸከም እርዳታ የሚሰጠው የከተማ ነዋሪ በዛ፡፡
ከዚህ የምንማረው ዱላ ሲበዛ ተፈሪነቱም ይቀንሳል፡፡ የቅጣት ትልቁ ጥቅም ያጠፋን ሰው በመቅጣት እንዳይደገመው ማድረግ ሳይሆን ቅጣቱን መጠቀም ሳይኖርብን ሰዎች በፍርሃት ብቻ እንዲያከብሩት ማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም የቅጣት ትልቁ ሃይል ፍራቻው ላይ ነው፡፡ የቅጣቱ ህመም ላይ አይደለም፡፡ ሕሙንማ የተቀጣው ሰው ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ፍርሃቱ ግን ሁሉንም ይመለከታል፡፡ ታዲያ ትልቁ አደጋ ቅጣቱ ሲበዛ፤ የተለመደ ሲሆን፤ ተፈሪነቱም ልክ እንደ ናዚ ቦንብ ይቀንሳል፡፡
ቅጣት ወጪ አለው
ቅጣት የራሱ ወጪ አለው፡፡ ይህ ወጪ እንደ ብክነት ሊወሰድ ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ካሳ እንዲከፍል ቢታዘዝና ለሌላ ሰው ቢከፍል ከሀገር ሀብት አንጻር የሚቀንሰው ነገር የለም፡፡ ካንድ ኪስ ወደ ሌላ መግባት ነው ውጤቱ፡፡ ነገር ግን አብዛኛው ቅጣት የሀገርን ሀብት በቅጣቱ ልክ ይቀንሳል፡፡ በመሆኑም በቁጠባ መጠቀም የግድ ይላል፡፡
ሰላጣ የሰረቀን በሞት መቅጣት?
ቅጣት እየጨመረ ሲሄድ በእያንዳንዱ ተጨማሪ ቅጣት የሚገኘው ጥቅም (የሕግ ከበሬታን መጨመር) እየቀነሰ ነው፡፡ ልክ ብርቱካን በመብላት የምናገኘው እርካታና ጥቅም ከእያዳንዷ ተጨማሪ ብርቱካን እየቀነሰ እንደሚሄደው፡፡ ቅጣትን ካንድ ዓመት ወደ ሁለት ዓመት በመጨመር የምናገኘው የሕግ ከበሬታና የቅጣት ተፈሪነት፤ ቅጣትን ከ23 ዓመት ወደ 24 ዓመት በመጨመር ከምናገኘው ይበልጣል፡፡ በሁለቱም ቅጣቱ የጨመረው በአንድ ዓመት ቢሆንም፤ ጥቅሙ ግን እጅግ ይለያያል፡፡ እንደውም አንዴ 23 ዓመት የተቀጣ ሰው ቅጣቱ በአንድ ዓመት እንዳይጨምርብኝ በሚል ያን ያህል አይሰጋም፤ አይጠነቀቅም፡፡ ለዛም ነው የሚጣልበትን ቅጣት ሳያውቅ በፊት ለዳኛውና ፍርድ ቤቱ ከበሬታውን እና ፍራቻውን ለማሳየት የማያደርገው የሌለው አንድ ተከሳሽ፤ ፍርድ ቤቱ ለምሳሌ 23 ዓመት እንደፈረደበት ካወቀ በኋላ ግን ለዳኛውም ሆነ ለፍርድ ቤቱ ያለው ፍራቻ ጠፍቶ፤ በንቀት የሚሞላውና አንዳንዴም የሚሳደበው ምንም አንኳ ይህ ባህሪው በእርግጠኝነት ተጨማሪ አንድ ዓመት ሊያስቀጣው እንደሚችል ቢያውቅም፡፡ ነገር ግን ይህ ለከሳሽ የተፈረደበት እስር አንድ ዓመት ከሆነ፤ ምንም እንኳ ፍርድ ቤቱና ዳኛው ኢፍትሐዊ ሆኑ ብሎ በሙሉ ልቡ ቢያምንም፤ ዳኘውን እና ፍርድ ቤቱን ለማንጓጠጥ ይፈራል፡፡ ዳኛን በማንጓጠጥ ምክንያት የሚጣል የአንድ ዓመት ተጨማሪ እስር ሁለት የተለያዩ ተከሳሾች ላይ ያለው ውጤት የተለያያ ነው፡፡
ቅጣት እየጨመረ ሲሄድ በእያንዳንዱ ተጨማሪ ቅጣት የሚገኘው ጥቅም መቀነሱ ብቻ ሳይሆን፤ እጅግ ከበዛ በብዙ ቅጣት የሚያስቀጣን ጥፋት የፈጸመ ሰው ተጨማሪ ጥፋት ላለማጥፋቱ እርግጠኛ መሆን አንችልም፡፡ ለምሳሌ በግ መስረቅ በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ከሆነ፤ አንዴ በግ የሰረቀ ወይም ሊሰርቅ የሞከረ ሰው በግ ከመስረቅ አልፎ ተጨማሪ ከባድ ወንጀሎች ሊሠራ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የበጎቹን እረኛና አይተውኛል ብሎ ያሰባቸውን በሙሉ ለመግደል ሊበረታታ ይችላል፡፡ ምክኒያቱም ተጨማሪ ወንጀል ቢሰራ ዞሮ ዞሮ ቅጣቱ ሞት ነው፡፡ እንደውም እነዚህን ወንጀሎች በመፈጸም በበግ ስርቆት የመያዝና የመቀጣት እድሉንም ሊቀንስ ይችላል፡፡
አንድን ጥፋት በተመለከተ በሕግ ቅጣትን ስንደነግግ፤ አላማችን የሚከተለው መሆን አለበት፡፡ አንደኛ፤ ማንም ዜጋ ይህን ጥፋት ለመፈጸም እንዳያስብ ማድረግ፡፡ ሁለተኛ፤ ጥፋቱን ለመፈጸም ካሰበም፤ ሃሳቡን እንዲቀይር እድል መስጠት ነው፡፡ ለምሳሌ ጥፋት ለመፈጸም ያሰበ ሰው፤ ማሰቡ እንደፈጸመው ተቆጥሮ ለጥፋቱ በተቀመጠው ቅጣት ልክ የሚያስቀጣው ከሆነ፤ በማሰብ ብቻ አይመለስም፡፡ ማሰቡ የሚያስቀጣው ከሆነ እንደውም ለምን ሃሳቡን ይቀይራል? ወንጀል ለመፈጸም ማሰብ ብቻውን አያስቀጣም፤ ግን ለምን? በተለምዶ የሚሰጠው መልስ የሰውን ሃሳብ ማወቅ ስለማይቻል፤ እንኳን ሰው ሰይጣንም ቢሆን የሰውን ሃሳብ አያውቀውም ስለሚባል ነው፡፡ ይህ አጥጋቢ ምክኒያት አይደለም፤ ምክኒያቱም የወንጀል ሕግ ስለ ተከሳሹ ሃሳብና እውቀትም ይመለከታል፡፡ ታዲያ እንኳን ሰው ሰይጣንም የሰውን ልቦና ሊያውቅ የማይቻለው ከሆነ፤ የወንጀል ሕግ ስለ ቸልተኝነት፤ እውቀት፤ ፍላጎትና ሃሳብ ለምን ይደነግጋል፡፡ ይልቅስ አጥጋቢው ምክኒያት እንደ እኔ እምነት ይህ ነው፤ ወንጀል ለመስራት ማሰብ ብቻ ማስቀጣት የለበትም ምክኒቱም አሳቢው አሳቡን እንዲለውጥ ስለምንፈልግ ነው፡፡
የወንጀል ሕግ ዓላማ፤ ሰዎች ወንጀልን እንዳይፈጽሙ ማስታወቅና ማስፈራራት ከሆነ፤ ወንጀልን አንድ ሰው ለመፈጸም በማሰቡ ብቻ የሚቀጣ ከሆነ፤ ይህ ሰው በተለያየ ምክኒያት አንዴ ሃሳቡ አይምሮው ውስጥ ከገባ በኋላ፤ ከመፈጸም ወይም ከመሞከር ወደ ኋላ አይልም፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ የወንጀል ሕግ ወንጀል እንዲሰራ እያበረታታም አይደል? ሶስተኛ፤ ሃሳቡን ሳይቀይር ጥፋቱን ለመፈጸም መዘጋጀት ጀምሮ ከሆነም፤ ለዚህ ሰው ቢቻል ዝግጅቱን እንዲያቆም፤ ዝግጅቱን ጨርሶ ከሆነም ቢቻል ጥፋቱን እንዳይሞክረው፤ ሞክሮት ከሆነ እና በተለያየ ምክኒያት ካልተሳካለት፤ እንዳይጨርሰው ወይም ድጋሚ እንዳይሞክረው ወይም ካሰበው ያነሰ ጥፋት ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ሕጉ እድል መስጠት አለበት፡፡ አራተኛ፤ ግለሰቡ የተባለውን ጥፋት ፈጽሞት ከሆነ፤ በዚያው እንዲበቃው፤ ተጨማሪ ሌላ ተመሳሳይ ወይም የከፋ ጥፋት እንዳይፈጽም ማድረግ የሕጉ አላማ ነው፡፡
በግ የሰረቀ ሰው በዚያው እንዲበቃው፤ የሰው መግደል ወንጀል እንዳይፈጽም ማድረግ አለብን፡፡ ይህን ለማከናወን የሚጠቅመን በሕጉ ለሰው ግድያ የተቀመጠው ቅጣት ብቻ አይደለም፤ እንደውም ከሱ በተጨማሪ ለበግ መስረቅ እና ለሌሎች ዓይነት አነስተኛ ጉዳት ያላቸው ወንጀሎች የምናስቀምጠው ቅጣትም ናቸው የሚጠቅሙን፡፡ ለእነዚህ አነስተኛ ጉዳት ላላቸው ወንጀሎች የምንደነግገው ቅጣት፤ የዚህ ቅጣት አላማ እነዚህ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ማስታወቅና ማስፈራራት ብቻ ሳይሆን፤ ከዛም አልፎ ከእነሱ የባሱ ሌሎች ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ማድረግ ነው፡፡
በአጭሩ፤ ቅጣት አላቂና የከበረ ኃብት ነው፡፡ ይህን ኃብት አንድን ወንጀል ለመቅጣት በተጠቀምንበት ቁጥር፤ ከዛ የከበዱ ወንጀሎችን የምንቀጣበት ኃብት እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ በመሆኑም በቁጠባ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ የአቴንስ ንጉስ የነበረውና ሕግ ሰጪው እየተባለ የሚጠራው ድራኮ በአወጣው ሕግ ጥቃቅን የሚባሉ ጥፋቶችንም ሳይቀር በሞት ቅጣት እንዲቀጡ ደንግጎ ነበር፡፡ ከዛም ነው ድራኮኒያን ሕግ የሚለው አገላለጽ የመጣው፡፡ እናም ለምን ሰላጣ መስረቅን የመሰለ ጥፋት ልክ እንደ ሰው መግደል እኩል የሞት ቅጣት እንደደነገገ ሲጠየቅ፤ ሰላጣ መስረቅ አጸያፊና የማይፈለግ ተግባር በመሆኑ ሞት ይገባዋል፤ ሰው መግደል ከዚያ የሚበልጥ አጸያፊ ቢሆንም ከሞት የበለጠ ሌላ ቅጣት ማግኘት ስላልቻልኩ በሞት እንዲያስቀጣ ደንግጌያለው በሚል መልሷል፡፡
ጉዳዩ ይህ ነው፤ ድራኮ ሰላጣ የሰረቀን ሰው በሞት በመቅጣቱ የተነሳ፤ ሰው መግደልን የሚቀጣበት ቅጣት አጣ፡፡ ያለውን ቅጣት አሟጦ ጨረሰ፡፡ በዚህ አካሄድ ለሰው ግድያ ወንጀል ምንም ዓይነት ቅጣት እንዳልተቀመጠ ያህል ነው፡፡ ሳናስበው ሰው ግድያን እያበረታታን ነው፡፡ አንድን ጥፋት በምን ያህን መቀጣት እንዳለበት በሕግ ስንደነግግ፤ ማሰብ ያለብን ምን ያህል ያንን ጥፋት ሰዎች እንዳይፈጽሙት ማስታወቅና ማስፈራራት እንደፈለግን ብቻ ሳይሆን፤ ምን ያህል ከዛ የባሰ ጥፋት እነዚህ ሰዎች እንዳይፈጽሙ ማስታወቅና ማስፈራራት እንደምንፈልግም ነው፡፡ ሕግ አውጭው አካል ለአንድ የተወሰነ ጥፋት፤ የቅጣትን መጠን መወሰን ያለበት፤ የዛን ጥፋት ባህሪይና መዘዝ ብቻ በማየት ሳይሆን፤ ሌሎች ከዚህ ጥፋት ያነሱና የከፉ ጥፋቶችን በማነጸጸር መሆን ይገባዋል፡፡
ክልከላ እና ቅጣት ሲበዛ የሕዝብ ድጋፍን እና ተቃውሞን ይጨምራል
አንድን ጥፋት በተመለከተ የተጣለው ቅጣት በሕዝብ ዘንድ አላግባብ የበዛ ነው የሚል ግምት ካሳደረ፤ ዜጎች ስለሕጉ ያላቸውን አስተሳሰብ ይበርዘዋል፡፡ በመሆኑም በፈቃዳቸው፤ የሕጉን ፍትሃዊነት በመቀበል ሕግን የሚያከብሩ ግለሰቦችን ቁጥር ይቀንሳል፡፡ እንዲሁም መረጃ በመስጠትና በሌላ መልኩ ለሕጉ መፈጸም ትብብር የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር ይቀንሳል፡፡ በሌላ ክፍል በሰፊው እንመለስበታለን፡፡
ክልከላ እና ቅጣት ሲበዛ የመንግስት ሙስናን ይጨምራል
ክልከላ እና ቅጣት ሲበዛ ሕጉን ለማስፈጸም ሃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ለሙስና የመጋለጥ እድላቸውን ይጨምረዋል፡፡ ይህ ምንም እንኳ የሕጉን ውጤታማነት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ባይኖረውም፤ በአጠቃላይ የሕግ ስርአቱ ግን ከፍተኛ ጉዳት ይጥላል፡፡ አንድን ሕግ በልዩነት የማስፈጸም ሃላፊነት የተሰጣቸው ሕግ አስፈጻሚዎች ለሕጉ የተቀመጠውን ቅጣት እንዲጨመርና፤ ይህም ሕጉ የታሰበለትን አላማ ላለማሳካት እንደሚጠቅም ሲሞግቱ መጠራር አለብን፡፡
ክልከላ እና ቅጣት ሲበዛ የሕግ አስፈጻሚውን ኃብት በመበታተን የቅጣትን ውጤታማነት ይቀንሳል
ሌላኛው ጉዳይ የሕግ አስፈጻሚውን ኃብት በመበታተን የቅጣትን ውጤታማነት ይቀንሳል፡፡ ይህ እንዴት ይሆናል የሚለውን በሌላ ክፍል እንደመለስበታለን፡፡
ቅጣት መጨመር ማህበራዊ ተጽእኖዎችን በመቀነስ ድርጊቱን ሊያብሰው ይችላል
ቅጣት መጨመር ማህበራዊ ተጽእኖዎችን በመቀነስ ድርጊቱን ሊያብሰው ይችላል፡፡ አንዳንድ ነገሮችን ለመቆጣጠር ከሕግ ይልቅ ማህበራዊ ተቋማት የበለጠ ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ድርጊቱን በመቅጣት ለመቆጣጠር መሞከር፤ ድርጊቱን ከማህበራዊ ተቋማት አድማስ ውጭ በማድረግ በተቃራኒው ድርጊቱ ሊብስ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በአንድ የእስራኤል ትምህርት ቤት የተከሰተውን ነገር ማየት ይቻላል፡፡ በተወሰኑ ጣቢያዎች አስቀድሞ በተነገረ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ጧት ጧት እየዞር ተማሪዎችን በአውቶብስ ትምህርት ቤቱ ያጓጉዛል፡፡ ነገር ግን በአንድ ጣቢያ አንድ ወላጅ ልጆቹን ይዞ በተባለው ጊዜ ካልተገኘ፤ አውቶብሱ ለተወሰነ ጊዜ ቆሞ ሰለሚጠብቅ ለሚቀጥለው ጣቢያ ያለውን የጊዜ ሰሌዳ ያዛባዋል፡፡ ትምህርት ቤት በተፈለገው ሰአት አየደርስም፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ሲባል፤ የትምህርት ቤቱ አስተዳደር እንደዘገዩበት መጠን ወላጆች ላይ ቅጣት መጣል ጀመረ፡፡ ሃሳቡ መዘግየትን መቀነስ ነበር፡፡ ይልቅስ ይህ አሰራር መዘግየትን አብሶት አረፈው፡፡ ለምን እና እንዴት የሚለውን በሌላ ክፍል እንመለስበታለን፡፡
ቅጣትን ማእከላዊና አንጻራዊ በሆነ መልኩ መወሰን
ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ምክኒያቶች የአንድን ወንጀል ወይም ጥፋት ቁጥር ለመቀነስና የሕጉን ውጤታማነት ለማሳደግ፤ የተደነገገውን ቅጣት መጨመር ያሰብነውን አላማ ላያሳካልን ይችላል፡፡ እንደውም በተቃራኒው የቅጣትን አጠቃላይ ተፈሪነት ሊቀንስብን እና ከታሰበው ውጭ ሌሎች የከፉ ወንጀሎችን ወይም ጥፋቶችን ሊጨመር ይችላል፡፡ በመሆኑም መንግስታት፤ እጅግ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ የተፈጸመን ወንጀል ተከትሎ በሚቀሰቀስ ሕዝባዊ ቁጣና ጫና ምክኒያት ለወንጀሉ የተቀመጠን ቅጣት ከመጨመራቸው በፊት በጥንቃቄ ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡ ቅጣትን መጨመር፤ በሕግ ልንጠብቃቸው የምንፈልጋቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደውም ለከፋ ጥቃት ሊያጋልጣቸው ስለሚችል፡፡
ሌላው ከዚህ በላይ ከተደረገው ውይይት መረዳት የምንችለው ጉዳይ በተለያዩ ሕጎች ሰለሚደነገጉ ቅጣቶች ነው፡፡ የፌዴራል መንግስቱን የተለያዩ ሕጎች መውሰድ ይቻላል፡፡ ዋነኛው የወንጀል ሕግ ነው፡፡ ይህ ሕግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው የወጣው፡፡ ለተለያዩ ዓይነት ጥፋቶች የተለያዩ ዓይነት ቅጣቶች ይደነግጋል፡፡ አንዳንድ ዓይነት ወንጀሎችን በመውሰድ ከዚህ በላይ ከተነሱት ነጥቦች አንጸር መገምገም ቢቻልም፤ ለጊዜው ትኩረት ማድረግ የምፈልገው በሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም እንዲህ ይቀርባል፡፡ ከወንጀል ሕጉ በተጨማሪና ከዛ በኋላ በወጡ ሕጎች ተጨማሪ ጥፋቶችን ቅጣቶች ተደንገገዋል፡፡ እነዚህን ቅጣቶች ሲደነግግ መንግስት ከወንጀል ሕጉ አንጸር በጥንቃቄ በመመርመርና በመገምገም ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ይህን ላለማድረጉ፤ የሚያወጣቸው ሕጎች ያሳብቃሉ፡፡ ለምሳሌ በብዙ አዋጆች የተለመደውና ቅጣትን የሚመለከት ድንጋጌ እንዲህ ይላል፤ "በወንጀል ሕግሕጉ ከፍ ባለ ቅጣት የሚያስቀጣ ካልሆነ በቀር…. በዚህ አዋጅ ያሉትን ድንጋጌዎች የተጸረረ ሰው በዚህ ይቀጣል"፡፡
አዳዲስ ሕጎች ሲወጡ፤ ከነባር የሕግ ክምችት አንጻር ተፈትሸውና ተገምግመው መሆን አለበት፡፡ አንዱ የሰራውን ሌላኛው በማወቅም ይሆን ባለማወቅ ማፍረስ ሳይገባው ማፍረስ የለበትም፡፡ ለዛም ነው አዲሱ ሕግ መነካት የሌለባቸውን ነባር ሕጎች እንዳይሸረሽርና እንዳያፈርስ ለመቆጣጠር ሲባል ሕጉን ከነባር ሕጎች አንጻር መፈተሸ ያለብን፡፡ ይህ ሆኖ እያለ ሁሉም አዋጆች ሊባል በሚችል መጠን የሚያካትቱት ድንጋጌ እንዲህ ይላል፤ "ከዚህ አዋጅ ጋር የሚጻረር ማንኛውም ሕግ ዋጋ የለውም" ይላል፡፡ ይህም ሆነ ከዚህ በላይ የተጠቀሰው ድንጋጌ የሚያሳዩት ነገር አዲስ ሕግ ሲወጣ ሕጉን ከነባር ሕጎች አንጻር አለመፈተሹ ነው፡፡ ይህ ፍተሸ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፤ አዲሱ ሕግ የትኛውን ሕግ ዋጋ አልባ እንዳደረገ በግልጽ ማስቀመጥ ይቻል ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት ድፍን እና ጥቅል ድንጋጌዎች ፍተሻው እንዳልተከናወነ ያሳዩናል፡፡ ከዛም አልፎ ሕግ አውጪውና አርቃቂው ማድረግ የፈለጉትን የማያውቁ ያስመስላቸዋል፡፡ ሕግ መሻርን ለሕግ አውጪው አሳልፎ ለሕግ ተርጓሚው የሚሰጥ ነው፡፡ በትርጉም ልዩነት የተነሳም አንዱ ፍርድ ቤት አንድ ሕጋዊ ድንጋጌ ከኋላ በመጣ አዋጅ ተሸሯል ሲል፤ ሌላ ፍርድ ቤት ደግሞ ተመሳሳይን ድንጋጌ አልተሸረም እንዲል ቀዳዳ ይከፍታል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ አንድ አዋጅ በወንጀል ሕጉ ከፍተኛ ቅጣት ካልተቀመጠ በስተቀር የሚል አገላለጽ ሲጠቀም፤ ሕግ አውጭው አካል ይህን አዋጅ ሲያወጣ ከነበር ሕጎች አንጻር እንዳልገመገመው ያሳያል፡፡ ሕግ አውጭው አካል ሃሳቡ አዲስ ወንጀል መፍጠር ወይም ደግሞ ለነባር ወንጅል ቅጣትን መጨመር እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ሕግ አውጭው አካል ምን ለማድረግ እንደፈለገም ግልጽ አይደለም፡፡ አዲስ ዓይነት ወንጀል ወይም ተጨማሪ ቅጣት በቂ ጥንቃቄና ምርመራ ሳያደርግ በአዋጅ እየፈጠረ ነው፡፡ በቂ ጥንቃቄና ምርመራማ አድርጎ ቢሆንማ እንዲህ ዓይነት ድፍን እና ጥቅልል ድንጋጌ ማካተት ባላስፈለገው ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት አሰራር ወንጀልና ተጨማሪ ቅጣት በፍርድ ቤቶች በትርጉም እንዲፈጠር በር የሚከፍት ነው፡፡ በፍርድ ቤቶች መካከል የሚኖረው የትርጉም ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ ሕግ አውጭው አዲስ ዓይነት ወንጀል መፍጠር ፈልጎ ከሆነስ፤ ለምን በግልጽ የተፈጠረውን ወንጀል አያስቀምጠውም? በደፈናው ይህን አዋጅ የተጸረረ ተግባር የፈጸም የሚል ድንጋጌን ከማካተት ይልቅ፡፡
የዚህ ዓይነት ድንጋጌዎች ዋነኛ ኃጢያት ግን ይህ ነው፤ የቅጣትን ውጤታማነት በእጅጉ የመቀነስ ውጤት አላቸው፡፡ ሕግ አውጭው በአዋጁ ቅጣትን ሲደነግግ እንኳን ሌሎች ነባር ሕጎችን ሊያይ ይቅርና፤ ዋነኛ የሚባለውን የወንጀል ሕግን እንኳ አልፈተሸም፡፡ ይህ በመሆኑ በሃገራችን የቅጣት መጠን አንጻራዊ በሆነ መልኩ ሳይሆን በዘፈቀደ በተበጣጠሰ ሁኔታ መወሰኑን ነው፡፡ ይህ ሲሆን ቅጣትን በቁጠባ ስለመጠቀማችን ምንም ማረጋገጫ የለንም፡፡ ቅጣትን በቁጠባና በጥንቃቄ ሳንጠቀም ስንቀር ደግሞ የቅጣት ውጤታማነት ከዚህ በላይ በተብራሩት ምክንያቶች እጅግ ይሸረሸራል፡፡ ቅጣት ውድ፤ ኢፍትሐዊ እና አነስተኛ ውጤታማነት ያለው መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ እንደውም ልንቀንሳቸው የምንፈልጋቸውን ተግባራት ከመቀነስ ይልቅ ላለማበረታታችን ዋስትና የለንም፡፡
ችግሩን የበለጠ የሚያከብደው ቅጣቶች በተበጣጠሰ ሁኔታ በደንብና በመመሪያ መውጣታቸው ነው፡፡ ይህ አንጻራዊ ግምገማን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ በደንብና በአዋጅ የሚደነገግ ቅጣትን አንጻራዊ በሆነ ሁኔታ ለመፈተሸ ይቀላል፡፡ ምክኒያቱም ሁሉም ደንቦች በጠቅላይ አቃቢ ሕጉ ቢሮና እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተፈትሸው ስለሚወጡ፡፡ ከዛ በላይ ደግሞ አዋጆች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይመረመራሉ፡፡ ይህ ተጨማሪ የምርመራ እድል እያለ ግን፤ ቅጣቶች በአንጻራዊና ማእከላዊ በሆነ መልኩ ላለመውጣታቸው ከላይ የተጠቀሱት ዓይነት ድንጋጌዎች ያሳብቃሉ፡፡ ለማእከላዊና አንጻራዊ ውሳኔ የማይመቸው ቅጣት በመመሪያ ሲወሰን ነው፡፡ በመመሪያ የሚወሰኑ ቅጣቶችን ጥፋቶች ወንጅል ናቸው ወይስ አስተዳደራዊ ጥፋቶችና ቅጣቶች የሚለውን ወደ ጎን እንተወውና፤ ዋናው ነጥብ እዚህ ላይ በተበጣጠሰ ሁኔታ እና ያለ አንጻራው ግምገማና ውሳኔ አዲስ ጥፋትን እና ቅጣትን ወይም ተጨማሪ ቅጣትን በሕግ (በአዋጅ፤ በደንብ፤ በመመሪያ) መደንገግ የቅጣትን አጠቃላይ ሃይል የሚሸረሽር አሰራር ነው፡፡
እንደውም አዲስ ጥፋትን እና ቅጣትን ወይም ተጨማሪ ቅጣትን በመመሪያ የመደንገግ አሰራር ሙሉ ለሙሉ ሊቀር ይገባል፡፡ አንዳንድ መስሪያ ቤቶች ለሚሰበስቧቸው ክፍያዎች የሕግ መሠረቱ የሚጣለውና የክፍያው መጠን የሚወሰነው በአዋጅና ደንብ ነው፡፡ በመመሪያ የመሰበስቧቸውን የተለያዩ ክፍያዎች አይወስንም፡፡ ለክፍያ ይህ ከሆነ ለምን ለጥፋትና ቅጣት ተመሳሳይ አሰራር አንከተልም፡፡ ዋጋን መንግሥት አንጻራዊና ማዕከላዊ በሆነ መንገድ ካልወሰነ/ካልተመነ የዋጋ ግሽበትን እና ኢፍትሐዊ ውጤትን ሊያመጣ ይችላል፡፡ እንዲሁም ቅጣትን እና ጥፋትን ማእከላዊና አንጻራዊ በሆነ መንገድ ካልወሰነ፤ የቅጣትና የጥፋት ግሽበትን እንዲሁም ኢፍትሐዊ አሰራርን ያመጣል፡፡
የፌዴራል መንግሥቱ ሃላፊነቱን ለመወጣት ከሚጠቀምባቸው መሳሪያዎች አንዱ ቅጣት ነው፡፡ ቅጣት አላቂና ውድ ከመሆኑ የተነሳ እና በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ከሚያመጣው አሉታዊ ተጽአኖ አንጻር አጠቃቀሙን ማእከላዊ በሆነ መንገድ በጥንቃቄ መምራት ያስፈልጋል፡፡ ይህን በቶሎ ካልተደረገ ግን፤ ለተለያዩ ጥፋቶች የሚጣሉት ቅጣቶች አንጻራዊ በሆነ መልኩ ባለመደልደሉ የተለሳ፤ መንግስት ሊዋጋቸው የሚፈልጋቸው ተግባራት ሊራቡና ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይችላሉ፡፡ አንዱ የሰራውን ሌላኛው ይንደዋል፡፡ የቅጣት አሰራር የሚስከትለውን ወጪ መቆጣጠር አይቻልም፡፡ የሚያስቀጡ ድርጊቶች ከመብዛታቸውና ቅጣት ከመብዛቱ የተነሳ፤ ዜጎች ለቅጣትና ለመንግስት ያላቸው ከበሬታና ፍርሃት ይቀንሳል፤ ተቃውሞና ንቀትን ያስፋፋል፡፡ የተለያዩ መንግስታዊ ድርጅቶች የሚያከናውኗቸውን የኮሚኒኬሽን ስራዎች፤ የግዢና ሽያጭ ስራዎች፤ የመንግስ ሰራተኞች የቅጥርና ሌሎች ጉዳዮች ማእከላዊ በሆነ ፓሊሲና ማዘዣ ጣቢያ መምራት ካስፈለገ፤ የቅጣት አጠቃቀምን ማእከላዊ በሆነ ፓሊሲና ማዘዣ ጣቢያ መምራት የበለጠ ያስፈልጋል፡፡
(ይቀጥላል)
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments