Font size: +
25 minutes reading time (5026 words)

ዳኞች፣ ዐቃቤ ሕጎች፣ ጠበቆች እና ፖሊሶች ሊዘነጓቸው የማይገቡ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ መርህዎች

መንግሥት የሃገርን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ እና የማስጠበቅ እንዲሁም የሕዝቦቹን እና የነዋሪዎቹን መሠረታዊ የግለሰብና የቡድን ነፃነት መብት እና ጥቅም የማክበርና የማረጋገጥ ግንባር ቀደም ኃላፊነትና ሚና አለበት፡፡ ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት ከሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል በግልጽ በሚመራ ሥርዓት የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ማዕቀፍን መዘርጋትና ማቋቋም አንዱና ዋነኛው ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ማዕቀፍን ከሚያቋቁሙ ምሰሶዎች መካከል የወንጀል ሕግ፣ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ እና የማስረጃ ሕግ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡

በአንድ ዘርፍ የወንጀል ሕግ ስለወንጀል ምንነት፣ ዓይነት እና ስለሚያስከትለው ቅጣት አስቀድሞ በግልጽ በመደንገግ ወይም ማስጠንቀቂያ በመስጠት፣ ዜጎች ስለወንጀል ምንነት እና ስለሚያስከትለው ጉዳት እንዲያውቁት እና እንዲረዱት ያደርጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝ ወንጀል ፈፃሚዎችን በሕግ ፊት በማቅረብ ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲያገኙ ብሎም እንዲታረሙ፣ ሌላ ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠቡ፣ ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑና እንዲታረሙ የማድረግ ሥርዓትን ይከተላል፡፡ በሌላ ዘርፍ ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝ በማን፣ እንዴት፣ መቼ ወዘተ... እንደተፈፀመ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ማስረጃዎች የሚሰበሰብበት፣ ለፍርድ ቤት የሚቀርብበት፣ የማስረጃዎቹ ዓይነት፣ ክብደት እና ብቃት የሚመዘንበት ሥርዓት እንደየሃገሩ ተጨባጭ ሁኔታ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ወይም በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ እና በማስረጃ ሕግ ይደነገጋል፡፡

የወንጀል ሕግ እነዚህን እና መሰል ጉዳዮችን ሲደነግግ ሁለት ተፋላሚ ጥቅሞችን በማመዛዘንና ግምት ውስጥ በማስገባት መሆን ይኖርበታል፡፡ በአንድ በኩል የሕብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ የወንጀል ድርጊት ፈፃሚዎችን ለፍርድ አቅርቦ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ሲሆን በሌላ በኩል ቅጣቱ የሚፈፀመው በአጥፊ ሰዎች ላይ ብቻ አንደሚሆንና እነዚህም ቢሆኑ ለጥፋታቸው ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት እንዲያገኙ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ነው፡፡ መንግሥት እነዚህን ሁለት ተፋላሚ ፍላጎቶችን አጣጥሞ የወንጀል ሕጉን ትርጉም ባለው መልኩ ለማስፈፀም የሚያስችል ውጤታማ፣ ቀልጣፋ፣ ሚዛናዊ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ተደራሽ እና ከፍተኛ የሕዝብ አመኔታ ያለው አሠራር መዘርጋት ይኖርበታል፡፡

ከላይ ከተጠቀሰው አንፃር ኢትዮጵያ የነበሩትን የባህላዊና የሃይማኖታዊ የወንጀል ሥርዓቶችን ሙሉ በሙሉ ለመተው እና በምዕራባዊያን የሕግ ፍልስፍናዎች እና ልምዶች ላይ የተመሠረተ ዘመናዊ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ለመገንባት ከወሰነች ከ1950ዎቹ ወዲህ የተለያዩ የወንጀል ሕጎችን በመደንገግና የተለያዩ የፍትሕ ተቋማትን በማቋቋም እነዚህን ሕጎች እያስፈፀመች የምትገኝ ሃገር ነች፡፡ በ1950ዎቹ ከተደነገጉ ሕጎች መካከል በ1949 ዓ.ም የታወጀው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ እና ይህንን ሕግ ለማስፈፀም በ 1954 ዓ.ም የተደነገገው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ-ሥርዓት በዋናነት የሚጠቀሱ ሲሆኑ እነዚህ ሁለቱን ሕጎች ጨምሮ በሌሎች ዋና (SUBSTANTIVE) እና ሥነ-ሥርዓት ሕጎች ውስጥ በተለያዩ ክፍሎችና ድንጋጌዎች የተካተቱ የዘመናዊ የማስረጃ ሕግ መርሆዎችንና ሥርዓቶችም እንዲሁ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡

በ1949 ዓ.ም የታወጀው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በወቅቱ ካለው ብሔራዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዕድገትና ፍላጎቶች ጋር የሚጣጣም ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን አሁን ከደረስንበት ዘመን አዳዲስ አስተሳሰቦች፣ የቴክኖሎጂ ዕድገቶችና የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ፅንሰ ሃሳቦች ጋር የሚጣጣም ሆኖ ባለመገኘቱ ላለፉት 48 ዓመታት ሲያገለግል የነበረው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በ 1997ቱ የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ ተሻሽሏል፡፡ በአንፃሩ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና በየሕጎቹ ውስጥ ተበታትነው የሚገኙትን የማስረጃ ሕጎች ስንመለከት ከተወሰኑ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ /ለምሳሌ የፀረ ሙስና፣ የጉሙሩክ እና የፀረ ሽብርተኝነት ወንጀሎችን አስመልክቶ/ ከተደረጉ ጥቂት ለውጦች በስተቀር ላለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት መሠረታዊ ማሻሻያ ሳይደረግባቸው በመስኩ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሔ እየተሰጠባቸውና እየተሰራባቸው ያሉ ሕጎች ናቸው፡፡

የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓትም ለረጅም ጊዜያት ማሻሻያ ሳይደረግለት እስከ አሁን ድረስ በሥራ ላይ በመቆየቱ የተነሳ በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ምንም አሉታዊ ተፅዕኖ አላስደረም ብሎ መደምደም የማይቻል ሲሆን ይህንኑ ጉዳይ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልኩ ለመገምገምና አግባብነት ያላቸውን ዘላቂ መፍትሔዎች ለማቅረብ እንደመነሻ የሚያገለግሉ መሠረታዊ የጥናት እና ምርምር ሥራ ማካሔድ የግድ ይላል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ በዘመናዊ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሊዘነጉ የማይገባቸው የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ መርሆችን ለመዳሰስ ነው፡፡

የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ መሠረታዊ መርሆዎች

የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ እንደማንኛውም ሕግ የራሱ የሆኑ መሠረታዊ መርህዎች አሉት፡፡ እነዚህ መርህዎች የወንጀል ሕጎችን (Substantive and Procedural laws) ዓላማና ግቦች ለማሳካት ሲባል የሚከናወኑ ተግባራት የሚመሩባቸው ሲሆኑ በዋናነት የሚመነጩት አግባብነት ካላቸው የሕገ-መንግሥት እና የዓለም አቀፍ ሕግ ድንጋጌዎች እንዲሁም በዓለም አቀፍ ተቀባይነት ካላቸው የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር የአሠራር ሥርዓቶች ነው፡፡ በዚህም መሠረት በመስኩ ያሉ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት መርህዎች በርካታ ቢሆኑም ለዚህ ጽሑፍ ዓላማ ይጠቅማሉ ተብለው የታመነባቸው እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

1. ደህንነትና ሰላም የማስጠበቅ መርህ (Principle of protection)

ደህንነትና ሰላም የማስጠበቅ መርህ አንዱና ዋነኛው የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ መርህ ሲሆን በቀጥታ ከወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ዓላማ ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ የዚህ መርህ ዋና ይዘት የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ዓላማ የመንግሥት፣ የሕዝብና የግለሰቦችን ደህንነትና ሰላም ማስጠበቅ መሆን አለበት የሚል መሠረታዊ ሀሣብ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ በወንጀል ጉዳዮች ላይ የሚሰጡ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓቶችን የሚገዛ እንደመሆኑ መጠን ንፁሐን ከአጥፊዎች በአግባቡ የሚለዩበት፣ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙት ከፈፀሙት ጥፋት ጋር ተመጣጣኝ ቅጣት የሚያገኙበት፣ ለጥፋታቸው ኃላፊነት መውሰዳቸው የሚረጋገጥበት እና በወንጀሉ የተፈጠሩትን ችግሮች በማስወገድ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ የሕብረተሰቡንና የመንግሥትን ደህንነትና ሰላም ማስጠበቅ መቻል አለበት፡፡ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ እነዚህ ተግባራት ሲከናወኑ ፍትሐዊና ሚዛናዊ በሆነ አካሔድ እንዲመሩ በማድረግ ሕብረተሰቡንና መንግሥትን ከወንጀል ድርጊት ስጋትና ፍርኃት መጠበቅ መቻል አለበት፡፡

ይህ ሕግ የሕብረተሰቡንና የመንግሥትን ደህንነትና ሰላም ሲያስጠብቅ ሁለት ተፋላሚ ጥቅሞችን በማመዛዘን መሆን ይኖርበታል፡፡ በአንድ በኩል የመንግሥትና የሕብረተሰብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የወንጀል ሕግ የሚተላለፉ ግለሰቦችን ውጤታማ፣ ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋ እና አስተማማኝ በሆነ ሂደት (reliable screening) በሕግ ፊት አቅርቦ አራሚና አስተማሪ የሆነ ቅጣት እንዲያገኙ በማድረግ፤ በሌላ በኩል ቅጣቱ በንፁሐን ሰዎች ላይ ሳይሆን በአጥፊ ሰዎች ላይ ብቻ እንዲፈፀም ብርቱ የጥንቃቄ እርምጃዎች ማስቀመጥ ይጠበቅበታል፡፡ በተጨማሪ ቅጣቱ በአጥፊ ሰዎች ላይ ብቻ የሚፈፀምበት ሂደትም ቢሆን የአጥፊውን ሰብዓዊ ክብር እና ማንነት በማይጐዳ ሁኔታ መሆኑን የሚያረጋግጥበት ሥነ-ሥርዓት ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡

በዚህ መርህ መሠረት የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ዋና ተልዕኮ እነዚህን ተፋላሚ ፍላጐቶችን አጣጥሞና አቻችሎ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ዓላማን ተዓማኒነትና ተቀባይነት ባለው መልኩ ማስፈፀም የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ፍላጐቶች በሚፈለገው ደረጃ (Optimal standard) ተጣጥሞና ተቻችሎ ውጤታማ፣ ፍትሐዊና ቀልጣፋ በሆነ አሠራር የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ዓላማና ግቦች ማሳካት ከተቻለ የሕዝብና የመንግሥት እንዲሁም የግለሰቦች ደህንነትና ሰላም ማስጠበቅ ይቻላል የሚል ጠንካራ እምነት አለ፡፡

2.   የሕገ-መንግሥታዊነት መርህ (Principle of Constitutionality)

ይህ መርህ እጅግ በጣም መሠረታዊና ቁልፍ ከሆኑ መርህዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ሲሆን ይዘቱም በብዙ መልክ ሊገለጽ ይቻላል፡፡ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ውስጥ የአንድን ሃገር ሕገ-መንግሥትና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ማንፀባረቅ መርህ ከሚገለጽበት መንገድ አንዱ ነው፡፡ ይህም ማለት የሥነ-ሥርዓት ሕጉ ይዘት በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የተደነገጉ እና ለወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ አግባብነት ያላቸው ጉዳዮችን በተሟላ ሁኔታ ለማስፈፀምና ተቋማዊ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ መቃኘት አለበት ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ በሥነ-ሥርዓት ሕጉ ውስጥ የሚካተቱ ማናኛውም ድንጋጌዎች ከሕገ-መንግሥት የመነጩና ሕገ-መንግሥታዊ መሠረት ከሌላቸው ተፈፃሚ ሊሆኑ አይገባም ማለት ነው፡፡

መርሁ በመሠረቱ በማንኛውም በሕግ የበላይነት በሚመራ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ለሚተገበሩ ሕጐች ሁሉ የሚሠራ ቢሆንም ለወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ግን የተለየ ትርጉም አለው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የሃገራችንን ሕገ-መንግሥት ጨምሮ የዘመናዊ ሕገ መንግሥቶች ዋነኛ አካል የሆነው የሰብዓዊና የዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች አብዛኛዎቹ ድንጋጌዎች በቀጥታ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ አማካይነት ተፈፃሚነት የሚያገኙ በመሆናቸው ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የተካተቱት የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች መሠረታቸው የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች እንደመሆኑ መጠን የሕገ-መንግሥታዊነት መርህ ለወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ዓለም አቀፋዊ ትርጉም እንዳለው መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሌላው መረዳት የሚያስፈልገው ቁምነገር ይህ መርህ በባህርይው ጠቅላይ (grand) መርህ እንጂ ዝርዝር መርህ አለመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ዋና መርህ ውስጥ የሚጠቃለሉ በርካታ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ መርህዎች አብዛኛዎቹ ከተጠርጣሪዎች ወይም ከተከሳሾች ሕገ-መንግሥታዊ መብቶች ጋር ተያይዘው ያሉ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት በሕገ-መንግሥታዊነት መርህ ውስጥ የሚጠቃለሉ ዋና ዋና መርህዎችን ቀጥሎ ጠቅለል ባለ መልኩ እናያለን፡፡

2.1 ጥፋተኛ ሆኖ ያለመቆጠር መብት (Presumption of Innocence)

ጥፋተኛ ሆኖ ያለመቆጠር መብት ከሕገ-መንግሥታዊ መርህዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ሲሆን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 20/3/ ሥር የተከሰሱ ሰዎች በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር መብት አላቸው ተብሎ በግልጽ ተመልክቷል፡፡ ጥፋተኛ ሆኖ ያለመቆጠር መብት ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት በተጨማሪ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች፣ ስምምነቶችና ቃል ኪዳን ሠነዶች ዕውቅና ያገኘ መብት ነው፡፡ ጥፋተኛ ሆኖ ያለመቆጠር መብት ሁለት ዋና ዋና አንጓዎች (elements) አሉት፤ የመጀመሪያው ተከሳሹ በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ የሚቀጣው ከሳሹ አካል (ዓቃቤ ሕግ) ተከሳሹ የተከሰሰበትን ወንጀል መፈፀሙን በማስረጃ ካረጋገጠ ብቻ ነው የሚል ሲሆን ሁለተኛው የተከሳሹ ጥፋተኝነት የሚረጋገጥበት ደረጃ (Standards of proof) ከፍና ጠበቅ ያለ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ እነዚህን አንጓዎችን አስመልክቶ በተለያዩ የሕግ ሥርዓቶች የተለያየ አሠራር ቢኖርም የመጀመሪያውን አንጓ በተመለከተ በሁሉም ዘንድ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ የሆነ ግንዛቤ አለ፡፡ ሁለተኛውን አንጓ በተመለከተ ግን እንደየሕግ ሥርዓቱ የተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ የአንግሎ ሳክሰን የሕግ ሥርዓት “ከበቂ ጥርጣሬ በላይ” (beyond any  reasonable doubt) የሚለውን የጥፋተኝነት ማረጋገጫ ደረጃ የሚጠቀሙ ሲሆን ሲሆን የሲቪሊያን የሕግ ሥርዓት ደግሞ “ተጠርጣሪው/ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመፈፀሙ ችሎቱን ወይም ዳኞችን አጥጋቢና በቂ በሆነ ሁኔታ ሊያሳምን በሚችል ደረጃ” (established to the satisfaction of the court” or” established sufficiently”) መሆን አለበት የሚሉ ናቸው፡፡

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው “ጥፋተኛ ሆኖ ያለመቆጠር መብት” ለወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ መርህ የሆነውን ያህል ለማስረጃ ሕግም መርህ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ሌላው ጉዳይ ይህ መርህ ትርጉምና ተፈፃሚነት የሚያገኘው ሃገራት በሚከተሉት የሕግ ሥርዓት ዓይነት ላይ በመመሥረት ነው፡፡ ምንም እንኳ በእኛ ሃገር ሕግ ውስጥ በግልፅ ያልተፃፈ ቢሆንም የሃገራችን ፍርድ ቤቶች “ከበቂ ጥርጣሬ በላይ” የሚለውን የጥፋተኝነት ማረጋገጫ ደረጃ የሚጠቀሙበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከጥፋተኛ ሆኖ ያለመቆጠር መብት መርህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ጉዳይ ከሳሹ አካል (ዐቃቤ ሕግ) የተጠርጣሪውን ጥፋተኝነት ሲያረጋግጥ ሁሉንም የወንጀሉን ፍሬ ነገሮች (elements of crime) በተቀመጠው የማረጋገጫ ደረጃ መሠረት ማረጋገጥ ይጠበቅበታል የሚለው ነው፡፡

በአጠቃላይ “ጥፋተኛ ሆኖ ያለመቆጠር መብት” መርህ አንዱና መሠረታዊ የሕገ-መንግሥታዊነት መርህ መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ መርህ ተግባራዊ የሚሆነው በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ በመሆኑ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ይህንን መርህ በግልፅ በመደንገግ ወደ ተግባር የሚቀየርበትን ሥርዓት ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡

2.2 ላለመናገር መብት (Right to silence)

ይህ መርህ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ስምምነቶችና ቃል ኪዳኖች ውስጥ ዕውቅና ያለው መብት ሲሆን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ከተረጋገጠላቸው መሠረታዊ መብቶች አንዱ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ላለመናገር መብት እንዳላቸው በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 19/2/ በግልፅ ተደንግጐ ይገኛል፡፡

ይህ ሕገ-መንግሥታዊ መብት ቀደም ሲል ከተጠቀሰው “ጥፋተኛ ሆኖ ያለመቆጠር መብት” ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ሲሆን ዋና ዕሳቤውም ተጠርጣሪው ወንጀል መፈፀሙን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ማስረጃዎች መሰብሰብ ያለባቸው ተጠርጣሪው በራሱ ላይ ከሚሰጠው ውጪ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ በመሆኑም የወንጀል ምርመራ አካላት የተፈፀመውን ወንጀል ለማረጋገጥ የሚያስችል ማስረጃ ለመሰብሰብ ራሱን የቻለና ተጠርጣሪውን ማዕከል ያላደረገ አሠራር መዘርጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ የተጠርጣሪዎች መብት በውስጡ ብዙ ዝርዝር ጉዳዮችን ያቀፈ ሲሆን ተጠርጣሪዎች ከተጠረጠሩበት የወንጀል ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለሚጠየቁት ማንኛውም ጥያቄ መልስ እንዲሰጡ እንደማይገደዱ፣ ተጠርጠሪዎች ወይም የተከሰሱ ሰዎች በራሳቸው ላይ በምስክርነት እንዲቀርቡ ሊገደዱ እንደማይገባቸው፣ ተጠርጣሪዎች ወይም ተከሳሾች እነዚህን መብቶች እንዳላቸው የማወቅ መብት እንዳላቸው፣ ማንኛውም አካል ተጠርጣሪውን ማንኛውንም ዓይነት ጥያቄ ከመጠየቁ በፊት ተጠርጣሪዎች ስለሚኖራቸው መብት በሚገባቸው ቋንቋ በበቂ ሁኔታ የማስረዳት ግዴታ እንዳለበት ወዘተ ዋና ዋናዎቹ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተጠርጣሪዎች በፍርድ ቤት ጉዳያቸው በሚሰማበት ወቅት ማንኛውም አካል ለሚጠይቃቸው ማንኛውም ዓይነት ጥያቄ መልስ እንዲሰጡ እንደፈማይገደዱ እና ለተጠየቁት ጥያቄዎች መልስ ባለመመለሳቸውም የተነሣ ማንኛውም አካል ተጠርጣሪዎችን አስመልክቶ አሉታዊ አስተያየት ከመስጠት መቆጠብ እንዳለበት ላለመናገር መብት ጋር ተያይዘው የሚነሱ መብቶች ናቸው፡፡

ከላይ ከተዘረዘሩት መረዳት የሚቻለው ላለመናገር መብት በሁሉም የወንጀል ፍትሕ ሂደት ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆን ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ተጠርጣሪ በወንጀል ተጠርጥሮ እጁ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ ጉዳዩ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ መብቱን ሊጠቀምበት ይችላል፡፡

2.3 የሕግ ምክር የማግኘት መብት (Right to Legal Council)

ከወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ መርህዎች መካከል አንዱና አስፈላጊው የተጠርጣሪዎች የሕግ ምክር የማግኘት መብት ሲሆን በሃገራችን የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥም ሕገ-መንግሥታዊ መሠረት ያለው ነው፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 20/5/ ውስጥም በግልፅ እንደተመለከተው ተጠርጣሪዎች ወይም የተከሰሱ ሰዎች በመረጡት የሕግ ጠበቃ የመወከል ወይም ጠበቃ ለማቆም አቅም በማጣታቸው ፍትሕ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታ ሲያጋጥም ከመንግሥት ጠበቃ የማግኘት መብት አላቸው፡፡  በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባገኙ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር አሠራሮች መሠረት የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱን ፍትሐዊነት፣ ሚዛናዊነት እና ተደራሽነት ለማረጋገጥ ሲባል መሟላት ከሚገባቸው አስፈላጊ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ተጠርጣሪዎች ይህንን መብት መጠቀም መቻላቸው ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡፡

በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ከከሳሾቻቸው ጋር በእኩል ደረጃ ከመብቶቻቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ ተጠርጣሪዎች በመረጡት የሕግ ጠበቃ መወከል መቻላቸው ነው፡፡ በመሆኑም ተጠርጣሪዎች ወይም ተከሳሾች በሕገ-መንግሥትና በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከተረጋገጡላቸው መብቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ለማረጋገጥ እና የወንጀል ፍትሕ ሂደቱን ፍትሐዊ፣ ሚዛናዊ፣ ተደራሽና አሳታፊ ለማድረግ ከተፈለገ እነዚህ ሰዎች የሕግ ምክር በሚፈለገው ጊዜ፣ ቦታና ጥራት ማግኘታቸውን ማረጋገጥ የግድ ይላል፡፡ በዚህም መሠረት የተከሰሱ ሰዎች የዚህ መብት ተጠቃሚ መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት በዋናነት የመርማሪ አካል፣ የዐቃቤ ሕግ እና የፍርድ ቤቶች ቢሆንም ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሕግ አውጪውና የሕግ አስፈፃሚ አካላትም የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡

የሕግ ምክር የማግኘት መብት ዘርፈ-ብዙ እና የራሱ የሆነ መገለጫዎች ያሉት ቢሆንም በዋናነት የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

1.     ንኛውም በወንጀል ድርጊት ተጠርጥሮ የተያዘ ወይም የታሰረ ሰው ከተያዘበት ወይም ከታሰረበት ጊዜ ጀምሮ በማንኛውም የፍርድ ሂደት ወቅት እሱ ከመረጠው የሕግ አማካሪ ምክርና ድጋፍ የማግኘት ወይም ከተመሠረተበት ክስ ራሱን ለመከላከል በመረጠው ጠበቃ የመወከል መብት እንዳለው፤

2.    በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ከተመሠረተባቸው ክስ ራሳቸውን ለመከላከል ጠበቃ ለማቆም የገንዘብ አቅም የሌላቸው መሆኑ ከተረጋገጠ ከመንግሥት ጠበቃ የማግኘት መብት እንዳላቸው፤

3.    ማንኛውም የሕግ አስከባሪ አካል ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ምክንያት ሰዎችን በሚይዝበት ወይም በሚያስርበት ጊዜ ተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ የማግኘት መብት እንዳላቸው በሚገባቸው ቋንቋ የማስረዳትና ጠበቃ በቀላሉ ለማግኘት እንዲችሉ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ግዴታ እንዳለበት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡

2.4 የዋስትና መብት (Right to Bail)

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 19/6/ በግልጽ እንደተደነገገው የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት ሕገ-መንግሥታዊ ሲሆን የተያዙ ወይም የተከሰሱ ሰዎችን መብት ከማስከበር አኳያ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያ ጠቀሜታው ሌሎች ሕገ-መንግሥታዊ መብቶችን ማስከበር መቻሉ እና በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ሰዎች ሊታሰሩ አይገባም ከሚለው የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ጋር የተቆራኘ መሆኑ ነው፡፡ የግለሰቦች ነፃነት እንዳይሸረሸር እና ከፍርድ በፊት ያለአግባብ እንዳይታሰሩ በዋስ የመፈታት መብታቸውን ያስጠብቃል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ እና የተከሰሱ ሰዎችም ቢሆኑ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ከሆነ በሕግ በተለየ ሁኔታ የተጠረጠሩበት ወንጀል የዋስትና መብት የሚያስከለክል ካልሆነ በስተቀር በዋስ የመለቀቅ መብት አላቸው፡፡ በመሆኑም የዋስትና መብት ለሌሎች ሕገ-መንግሥታዊ መብቶች መሠረት ነው ለማለት ይቻላል፡፡

ሌላኛው ጠቀሜታው በወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው በዋስ ሲለቀቅ ከተከሰሰበት ክስ ራሱን ለመከላከል የሚያስችለውን ማስረጃ ለማሰባሰብ እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለማድረግ የተሻለ ነፃነት ያገኛል፡፡ በዚህም ሂደት የፍትሕ አካላት ውነትን ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት ያግዛል፡፡ በሌላም በኩል የተያዘን ሰው በዋስ መልቀቅ በማረሚያ ቤት ያለውን የእስረኞች መጨናነቅ ለመቀነስ የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ይህ ደግሞ በዋስ ሊለቀቁ ለማይችሉና ማረሚያ ቤት ለሚቆዩ ሌሎች እስረኞች አንፃራዊ የሆነ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፡፡

በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩትን ሰዎች በሕግ አግባብ በዋስ መልቀቅ ከፍርድ ሂደት በኋላ በነፃ ሊለቀቁ የሚችሉ ሰዎች በሞራላቸውና ቁሳዊ ሀብታቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በመቀነስ የዜጎችን ሰብዓዊ ክብር እና ቁሳዊ ጥቅሞችን ለመጠበቅ አንዱ ዘዴ ነው፡፡ አንድ ሰው ዋስትና ተነፍጎ ለረጅም ጊዜ እስር ላይ ከቆየ በኋላ በመጨረሻ ነፃ ነህ ተብሎ ሲለቀቅ ሊተካ የማይችል ከፍተኛ ጉዳት ይደርስበታል፡፡ ስለሆነም እንዲህ ዓይነቱ የመብት መጣበብ እንዳይፈጠር በተለየ ሁኔታ በሕግ እስካልተከለከለ ድረስ አማራጭ መፍትሔው ሰዎች ለጉዳያቸው ውሳኔ እስኪያገኙ ድረስ በዋስ ከእስር ውጭ እንዲቆዩ ማድረግ ነው፡፡

በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች በዋስትና የሚፈቱበት አሠራሮች የተለያዩ ናቸው፡፡ እነዚህ አሠራሮቸ የሚመሠረቱት የዋስትና ጥያቄ የቀረበበት የወንጀል ጉዳይ ከባድነት፣ የተጠርጣሪው የወንጀል ሪከርድ እና የግል ፀባይ፣ በዋስትና ጥያቄ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ፣ በሕህዝብ ጥቅም ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ፣ ተጠርጣሪው በዋስትና ቢለቀቅ በተፈለገ ጊዜ ፍርድ ቤት ተመልሶ ሊቀርብ የሚችል ስለመሆኑ ወይም ሌላ ወንጀል ሊፈፅም የሚችል ስለመሆኑ፣ ምስክሮችን በማስፈራራት እና ማስረጃዎችን በማጥፋት በፍትሕ አሰጣጥ ሂደት ላይ ዕክል ሊፈጥር የሚችል ስለመሆኑ እና በመሳሰሉት ሁኔታዎች ላይ ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ከታዩና ከተመዘኑ በኋላ ከተወሰኑ ሁኔታዎች ጋር ግለሰቡ በዋስ ሊለቀቅ ይችላል፡፡ እነዚህን በራስ ዋስትና (own recognizance)፣ የዋስትና መብት ፀንቶ በሚቆይበት ጊዜ ለተወሰነ የመንግሥት አካል በቋሚነት ሪፖርት እንዲያደርግ (supervised release)፣ ወደተወሰኑ ሥፍራዎች እንዳይደርስ፣ ከአንዳንድ ድርጊቶች (ለምሳሌ ከመጠጥ) እንዲቆጠብ፣ ከተጎጂ ወይም ከምስክር ጋር እንዳይገናኝ፣ የተወሰነ ገንዘብ እንዲያሲዝ፣ የተወሰኑ ሰዎችን በተያዥነት እንዲያቀርብ (third party custody) እና በመሳሰሉት ሁኔታዎች ሊለቀቅ ይችላል፡፡ ከላይ የተጠቀሱ ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት የዋስትና መብት ፍፁም እንዳልሆነ በአንቀጽ 19/6/ ከተቀመጠው ድንጋጌ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚህም መሠረት በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት የዋስትና ጥያቄዎችን ላለመቀበል ይችላል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች የሚከተሉትን ዋና ዋና ጉዳዮች መሠረት ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ እነዚህም፡-

 ·        የወንጀል ዓይነቶች (ለምሳሌ የሽብርተኝነት ወንጀል)፤

·        የወንጀል ዓይነትና የቅጣት መጠን (ለምሳሌ የሙስና ወንጀል ሆኖ ከአስር ዓመት በላይ የሚያስቀጣ)፤

·        የቅጣቱ ጣራ (ለምሳሌ በሞት የሚያስቀጣ ከሆነ)፤

·        የተጎጂዎች ዓይነት (ለምሳሌ ሕፃናት እና ሴቶች  ከሆኑ)፤

·        የወንጀል እና የተጎጂዎች ዓይነት (ለምሳሌ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሆኖ ተጎጅዋ ከ13 ዓመት በታች ከሆነች) እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

 በአጠቃላይ የዋስትና ጥያቄ ሕገ-መንግሥታዊ መብት እንደመሆኑ መጠን ዋነኛው የሥነ-ሥርዓት ሕግ መርህ ነው፡፡

3.   የሕጋዊነት መርህ (Principle of legality)

የሕጋዊነት መርህ እጅግ በጣም ወሳኝ ከሆኑ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ መርህዎች አንዱ ነው፡፡ የዚህ መርህ ዋና ይዘት ማንም ሰው አስቅድሞ በግልጽ ወንጀል ነው ተብሎ ባልተደነገገ ድርጊት፣ ወይም ድርጊቱ አስቅድሞ ወንጀል ነው ተብሎ ባልታወጀ ድርጊት፣ ወይም ድርጊቱ በተፈጸመበት ጊዜ ድርጊቱ ወንጀል ባልሆነበት፣ ወይም ወደኋላ ሔዶ ድርጊትን ወንጀል ነው በሚል የወንጀል ሕግ ሊቀጣ ወይም ሊከሰስ አይችልም የሚለውን የወንጀል ሕግ መርህ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በሌላ አኳኋን ይህ መርህ ማንም ሰው ወይም የመንግሥት አካል ከሕግ በላይ እንዳልሆነ የሚያስረግጥ መርህ ነው፡፡ ይህም ማለት በአንድ በኩል ሕጉን አላውቅም በማለት የሚቀርብ መከላክያ ሁሉ ውድቅ እንደሚሆን ሲያመላክት በሌላ በኩል ዐቃቤ ሕግ ወይም ፖሊስ ወይም የመንግሥት አካል ዜጎችን ያለግልጽ ሕግና ሥነ-ሥርዓት እንዳይያዙ ወይም በደል እንዳይደርስባቸው የሚያስገድድ መርህ ነው፡፡ በግልጽ ወንጀል ነው ተብሎ የተደነገገን ድርጊት በግልጽ ሰውየው ይወቀውም አይወቀውም ማንም ሰው ወይም የመንግሥት አካል ሊያከብረው የሚገባ መሆኑን መርሁ ያመለክታል፡፡

 4.   የፍትሐዊ ዳኝነት መርህ (Principle of fair trial)

የፍትሐዊ ዳኝነት መርህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካገኙ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ መርህዎች መካከል አንዱ ሲሆን ዋና ዓላማው ዜጐች በሕግ ከተደነገገው ውጪ እንዲሁ በዘፈቀደ ነፃነታቸውንና ንብረታቸውን እንዳያጡ የሕግ ጥበቃ ለማድረግ ታስቦ የተቀመረ የሕግ ፅንሰ ሀሳብና አሠራር ነው፡፡ የፍትሐዊ ዳኝነት መርህ ትርጉም እጅግ በጣም ሰፊና ውስብስብ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት መርሁ የሚመሠረተው በሦስት የሕግ መሠረቶች ላይ ሲሆን እነሱም፡-

1.     በሕገ-መንግሥት እና በሌሎች የሃገር ውስጥ ሕጎች፤

2.    በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችና ቃል ኪዳን ሠነዶች እና

3.    በዓለም አቀፍ ባህላዊ የሕግ ዕሴቶችና ልምዶች (Norms of Customary International Laws) ናቸው፡፡

በአንድ ሃገር የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ የፍትሐዊ ዳኝነት መርህዎች በአግባቡ መካተት አለመካተታቸውን ለመገምገም ከላይ የተጠቀሱትን ምንጮችንና መሠረቶችን መተንተንና መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የፍትሐዊ ዳኝነት መርህ ትርጉሞች የሚመሠረቱት የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ሃገር በሚከተለው የሕግ ሥርዓት ዓይነት ላይ በመመርኮዝ ነው፡፡

በዚህም መሠረት በሃገራችን የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የፍትሐዊ ዳኝነት መርህ በተሟላ መልኩ መኖር አለመኖሩን ለመመርመርና ለመረዳት የሃገራችንን ሕገ-መንግሥት ጨምሮ ሌሎች ሕጐቻችንን፣ የፍርድ ቤቶቻችን ውሳኔዎችና ልምዶችን በዝርዝር መፈተሽ የግድ ይላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሃገራችን የፈረመቻቸውንና ያፀደቀቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እንዲሁም የዓለም አቀፍ ባህላዊ የሕግ ዕሴቶችና ልምዶችን በጥልቀት መፈተሽ የግድ ይላል፡፡

የፍትሐዊ ዳኝነት መርህ የሁሉም የወንጀል ፍትሕ አካላት የአሠራር ሥርዓትን የሚመለከት በመሆኑ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ መሠረታዊ አካል መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህ መርህ የፍትሐዊ ዳኝነት መርህ የወንጀል ጉዳይ ላይ ምርመራ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የምርመራ አካሔድ፣ የክስ አመሠራረት፣ የክርክርና የውሳኔ አሰጣጥ አሠራሮችን እንደሁም በይግባኝና በሰበር አቤቱታ ቀርቦ የሚታይበትና የሚወሰንበት ሂደት ላይ ተግባራዊ የሚሆን የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ መርህ ነው፡፡

በዘህም መሠረት ለዚህ ጽሑፍ ዓላማ ሲባል የፍትሐዊ ዳኝነት መርህን ለመረዳት የወንጀል ፍትሕ ሂደቱን በሦስት ክፍል ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ አነዚህም፡-

·        ከክስ በፊት ተግባራዊ የሚሆኑ የፍትሐዊ ዳኝነት መርህዎች (Pre-Trial-Principles)፤

·        በክስ መሰማት ሂደት ላይ ተግባራዊ የሚሆኑ የፍትሐዊ ዳኝነት መርህዎች (The Hearing Principles) እና

·        ከውሳኔ በኋላ ተግባራዊ የሚሆኑ የፍትሐዊ ዳኝነት መርህዎች (Post-Hearing Principles) ናቸው፡፡

 ሀ. ከክስ በፊት ተግባራዊ የሚሆኑ የፍትሐዊ ዳኝነት መርህዎች (Pre Trial Principles)

 በዚህ ሂደት ላይ ተግባራዊ የሚሆኑ የፍትሐዊ ዳኝነት መርህዎች በርካታ ቢሆኑም ዋና ዋናዎቹን ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡

 1.     ከሕግ ውጭ በዘፈቀደ ያለመያዝና ያለመታሰር (The Prohibition on Arbitrary Arrest and detention) 

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 16 እና 17 በግልጽ እንደተመለከተው ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ሊያዝ፣ ክስ ሣይቀርብበት ወይም ሣይፈረድበት ሊታሰር እንደማይገባውና የአካል ደህንነት መብቶች እንዳሉት ተደንግጓል፡፡

 2.     የእስር እና የክስ ምክንያትን የማወቅ መብት (The Right to know the reason for arrest)

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት መሠረት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተያዙ ሰዎች የቀረበባቸውን ክስ ምክንያት በዝርዝር ወዲያውኑ በሚገባቸው ቋንቋ የማወቅ መብት እንዳላቸው በአንቀጽ 19/1/ የተደነገገው ሲሆን የሚይዛቸውም አካል የተያዙ ሰዎች ይህንን መብት እንዳለቸው የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡

3.  የሕግ ምክር የማግኘት መብት (The Right to legal council)

ይህንን መርህ አስመልክቶ በዚህ ጽሑፍ ከታች በዝርዝር ከተቀመጠው በተጨማሪ ተከሳሾች ከጠበቆቻቸው ጋር የሚያደርጉት ምክርና ግንኙነት በምንም መልኩ ሊጠለፍ (interception) እና ሊመረመር (censorship) አይገባም፡፡ በመሆኑም ተከሳሾችና ጠበቆች የሚያደርጉት ንግግር ሚስጥራዊ መሆን ይኖርበታል፡፡

4.  ወዲያውኑ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት (The Right to a prompt appearance before a judge to challenge the lawfulness of arrest and detention) 

ይህንን አስመልክቶ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 19/3/ እንደተደነገገው የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አላቸው፡፡ ይህም ጊዜ ሰዎች ከተያዙበት ቦታ ፍርድ ቤት ለመምጣት አግባብ ባለው ግምት የሚጠይቀውን ጊዜ አይጨምርም፡፡ ወዲያውኑ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ በተጠረጠሩበት ወንጀል ለመታሰር የሚያበቃ ምክንያት ያለ መሆኑን ተለይቶ እንዲገለፅላቸው (በሚረዱት ቋንቋ) መብት አላቸው፡፡

 5.     በሰብዓዊነትና በርህራሔ የመያዝ መብት (The prohibition of torture and the right to human condition during pretrial detention)

 

በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 18/1/ እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢ-ሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ…የመጠበቅ መብት አለው፡፡ ይህ መርህ የዓለም አቀፍ ባህላዊ ሕግ እሴቶችና ልምዶች (Jusco gens) መሠረት ያለው ነው፡፡

 6.     ከውጪ ዓለም ጋር የመገናኘት መብት (The prohibition on incommunicado detention) 

በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች ከትዳር አጋሮቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከኃይማኖት አባቶቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘትና ለመጎብኘት ዕድል የማግኘት መብት እንዳላቸው በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 21 ሥር ተመልክቷል፡፡

 ለ. በክስ መስማት ሂደት ላይ ተግባራዊ የሚሆኑ የፍትሐዊ ዳኝነት መርህ (The Hearing Principle) 

ይህ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ከደረሰ በኋላ ተግባራዊ የሚሆን የፍትሐዊ ዳኝነት መርህ አካል  ሲሆን በውስጡ በርካታ ጉዳዮችን የያዘ ነው፡፡ በዋናነት በሕግ ፊት በእኩልነት የመታየት፣ ለሕዝብ ግልፅ በሆነ ችሎት የመዳኘት፣ ነፃና ገለልተኛ በሆነ ዳኝነት የመዳኘት፣ ጥፋተኛ ሆኖ ያለመቆጠር፣ ቀልጣፋ ዳኝነት የማግኘት፣ የቀረበባቸውን ማስረጃ የመመልከት፣ የቋንቋ ትርጉም የማግኘት፣ በራስ ላይ ምስክር ሆኖ ያለመቅረብ፣ በአንድ የወንጀል ድርጊት በድጋሚ ያለመቀጣት መብቶች እና ሌሎችን አካቶ የያዘ ነው፡፡ ከላይ የተዘረዘሩ በክስ መስማት ሂደት ላይ ተግባራዊ የሚሆኑ የፍትሐዊነት መርህዎች የሕገ መንግሥቱ እና የዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ያላቸው ናቸው፡፡

 . ከውሳኔ በኋላ ተግባራዊ የሚሆኑ የፍትሐዊ ዳኝነት መርህ (Post Hearing Principles)

ይህ የፍትሐዊ ዳኝነት መርህ ክፍል በመጀመሪያ ደረጃ የቀረበውን ክስ ፍርድ ቤቱ ሰምቶና መርምሮ ውሳኔ ከሰጠበት በኋላ ባሉ ሂደቶች ላይ ተግባራዊ የሚሆን ነው፡፡ በዚህም መሠረት በሃገራችን የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮችን ማንሳት የሚቻል ሲሆን እነሱም የይግባኝ መብት፣ ለሰበር ችሎት አቤቱታ የማቅረብ እና በወንጀል ጉዳይ የፍትሕ መጓደል (Miscarriage of justice) ምክንያት ለደረሰው ጉዳት ካሣ የማግኘት መብቶች ናቸው፡እነዚህን ጉዳዮች አስመልክቶ የይግባኝ መብትና ለሰበር አቤቱታ ማቅረብ ለሃገራችን አዲስ ሀሳቦች አይደሉም፡፡ በሃገራችን ለረጅም ጊዜ ሲሠራባቸው የነበሩ በመሆናቸው ብዙም እንግዳ አሠራር ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በወንጀል ጉዳይ የፍትሕ መጓደል ምክንያት ለደረሰው ጉዳት ካሣ የማግኘት መብት ለሃገራችን ፍትሕ ሥርዓት እንግዳ ሀሳብና አሠራር ቢሆንም በዓለም አቀፍ ሕጐችና ስምምነቶች እንደ አንዱ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት መርህ ተደርጐ የሚወሰድ ነው፡፡ ለአብነት በዓለም አቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ውስጥ (International Convention on Civil and Political Rights) ይህንን መብት አስመልክቶ የሚከተለው ተደንግጓል፡፡    

“When a person has by a final decision been convicted of a criminal offence and subsequently his conviction has been reversed or has been pardoned on the ground that a new or newly discovered fact shows conclusively that there has been a miscarriage of justice, the person who suffered punishment as a result of such conviction shall be compensated according to law, unless it is proved that the non-disclosure of the unknown fact in time is wholly or partly attributable to him.”  

ከዚህ ስምምነት ድንጋጌ እና ከሌሎች ሃገሮች አሠራር መረዳት የሚቻለው ጉዳት ለደረሰበት ሰው ካሣ የሚከፈለው የሚከተሉት ፍሬ ነገሮች ሲሟሉ ብቻ ነው፡፡ እነሱም፡-

 ·        ጉዳት ያደረሰው ውሳኔ የመጨረሻ ውሳኔ ሲሆን (finality of decision)፤

·        ሥልጣን ያለው አካል ውሳኔው የፍትሕ መጓደልን በማስከተሉ ምክንያት የሻረው ከሆነ፤

·        ካሣ የሚጠይቀው ሰው ለፍትሕ መጓደሉ ምንም ዓይነት አስተዋፅኦ እንዳላደረገ ከተረጋገጠ፤ እና

·        በተጓደለ ፍትሕ አካሔድ በተወሰነው ውሳኔ ምክንያት የተላለፈው ቅጣት ጉዳት ካደረሰ ብቻ ነው፡፡

 5.   የቀልጣፋ እና የፈጣን ዳኝነት መርህ (Principle of speedy trial)

ሌላኛው የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ መርህ የምርመራና የፍርድ ሂደቱ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ግልጽ መሆን አለበት የሚል ሲሆን “የዘገየ ፍትሕ እንደተከለከለ ይቆጠራል” የሚለው የሕግ ልሂቃን አባባል ይህንን መርህ በደንብ የሚያብራራ ነው፡፡ የተያዘ ወይም የተከሰሰ ሰው የተጠረጠረበት ወይም የተከሰሰበት ወንጀል በተቻለ ፍጥነት ተጣርቶ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለህዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት እልባት ካላገኘ የተከሳሾች ሕጋዊ መብት ጥሰት ያስከትላል የሚል ዕሳቤ ያለው ነው፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት ድንጋጌዎችም ይህንኑ የሚደግፉ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

በተለይ በወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘና በእስር ቆይቶ ነፃነቱን ለማግኘት ለሚከራከር ተከሳሽ የምርመራና የክስ ሂደት ቀልጣፋና ፈጣን መሆን የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው፡፡ የተከሰሰበት ጉዳይ በማስረጃ እስኪረጋገጥ ድረስ ለብዙ ጊዜያት በእስር ሆኖ ሲከራከር የቆየ ተከሳሽ በክርክሩ የመጨረሻ ሂደት በነፃ የሚለቀቅበት በርካታ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ በምርመራ ሰበብ በጊዜ ቀጠሮ ሲጉላላ የቆየ ተጠርጣሪ ለክስ ምክንያት የሚሆን ማስረጃ አልተገኘም በሚል ሰበብ ክስ ሳይመሠረትበት በየእስር ቤቱ የሚማቅቅበት ሥርዓት ምን ያህል ጎጂ እነደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ስለሆነም ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው በመደበኛ ፍርድ ቤት ክስ የቀረበባቸው ሰዎች ጉዳያቸው በተቻለ መጠን ቀልጣፋና ፈጣን በሆነ አካሔድ ተሰምቶ መወሰን አለበት፡፡ ይህ መርህ ሕገ-መንግሥታዊ ዕውቅና ያለው ሲሆን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 20/1/ ውስጥም እንደተመለከተው የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በኋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ ለሕዝቡ ግልፅ በሆነ ችሎት ተሰምቶ ፍርድ እንዲሰጣቸው መብታቸው መሆኑን ይደነግጋል፡፡

ቀልጣፋና ፈጣን ዳኝነት በዋናነት የተከሳሹ መብት ቢሆንም የተጐጂዎችና የሕብረተሰቡ ጥቅሞችንና ፍላጐቶችን የሚጠብቅ ነው፡፡ ተከሳሹ በተቻለ ፍጥነት የተከሰሰበት ጉዳይ ዕልባት እንዲያገኝለት የሚፈልገውን ያህል ተጐጂዎችም ይፈልጋሉ፡፡ ሕብረተሰቡም ቢሆን ጉዳዩ በተራዘመ ቁጥር የህዝብ እና የመንግሥትን ወጪና ጉልበት የሚያባክን በመሆኑ ቶሎ ዕልባት እንዲያገኝ ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም የቀልጣፋ እና የፈጣን ዳኝነት መርህ እጅግ በጣም ጠቃሚና ወሳኝ የሥነ-ሥርዓት ሕግ መርህ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

የቀልጣፋ እና የፈጣን ዳኝነት መርህ ብዙ ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን የሚከተሉትን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነሱም የፍርድ ቤት የአጀንዳ አያያዝ፣ የቀጠሮ አሰጣጥና አከባበር፣ ጉዳዮች የሚጀመሩበትና የሚጠናቀቁበት የጊዜ ሠሌዳ፣ የዳኞች፣ የዐቃቢያነ ሕግና የምስክሮች አቀራረብና የሠዓት አከባበር፣ ጉዳዩ የሚሰማበት የጊዜ ሰሌዳ ተገማችነት (certainty of trial dates)፣ በሕግና በፍሬ ነገሮች ላይ ለሚነሱ ክርክሮች ብያኔ ወይም ትዕዛዝ የሚሰጥበት ፍጥነት፣ ለዳኞች፣ ለዐቃቢያነ ሕግ እና ለመርማሪ አካላት ሥራዎች በሕጉ የተቀመጠላቸው የጊዜ ገደቦች፣ በተቀመጠው የጊዜ ገደቦች የመጠቀም ብቃትና ፍላጐት፣ ካልተጠቀሙ የተቀመጠ መፍትሔ፣ የመዝገብና የጉዳዮች አያያዝ ሥርዓቶችና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

6.  የአሳታፊነት መርህ (Principle of participation)

ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለበት ሃገር የሚገኝ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ምንጊዜም ቢሆን የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ ያለሕብረተሰቡ ተሳትፎ ውጤታማ የሆነ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ሊኖር  አይችልም፡፡ በዚህም መሠረት የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ የፍትሕ ሥርዓቱን ዓላማና ግቦች ለማሳካት ከሚረዱት ዋነኛ መሣሪያዎች አንዱ የህብረተሰቡ ተሳትፎ በመሆኑ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ሲረቀቅም ሆነ ፀድቆ ሥራ ላይ ሲውል የአሳታፊነት መርህን በሚያረጋግጥ መልኩ መሆን አለበት፡፡

የአሳታፊነት መርህ ሁለት ገፅታዎች አሉት፡፡ አንደኛው በወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩ ውስጥ አጠቃላይ ሕብረተሰቡ ያለው ተሳትፎ ሲሆን ሁለተኛው በወንጀል ጉዳይ ላይ የተለየ ፍላጐትና ድርሻ ያላቸው አካላት ያላቸውን ተሳትፎ የሚመለከት ነው፡፡ በወንጀል ጉዳዮች ላይ የተለየ ፍላጐትና ድርሻ ያላቸው አካላት በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የተለየ ሚና የሚጫወቱ አካላት በመሆናቸው ከአጠቃላይ የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ባላነሰ ሁኔታ ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡

ሕብረተሰቡ ወንጀል በመጠቆም፣ አጠቃላይ የፍትሕ አካላት ሥራዎችን በመከታተልና በመተቸት እንዲሁም ከእነዚህ አካላት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች በመተባበር ለፍትሕ ሥርዓቱ መጐልበትና መጠናከር ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ ከሕብረተሰቡ ጐን ለጐን የተለያዩ የመንግሥት አካላት በወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩ ውስጥ ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡ ለምሳሌ ወንጀልን በመጠቆም፣ የተፈፀመውን ወንጀል አስመልክቶ የባለሙያ ድጋፍ በማድረግ፣ በፍርድ ቤቶችና በሌሎች አግባብነት ባላቸው አካላት የሚወሰኑ ውሳኔዎችን በማስፈፀምና በመፈፀም እና በመሳሰሉት ሁኔታዎች በወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩ ውስጥ መሳተፍ መቻል አለባቸው፡፡

የተጐጂዎችና የተጐጂ ቤተሰቦች እንደዚሁም የምስክሮችና የወንጀል ጠቋሚዎች ተሳትፎ እጅግ በጣም ወሳኝ ሚና አለው፡፡ እነዚህ አካላት ማስረጃዎችን በመስጠት፣ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ በአሠራር ሂደቶች ላይ ባሉት ጉድለቶች ላይ አቤቱታዎችን በማቅረብና የማስተካከያ እርምጃ በሚመለከተው አካል እንዲወሰድ በማድረግ እና በመሳሰሉት ጉዳዮች የሚሳተፉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡

ተጠርጣሪውም በተመሳሳይ መልኩ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩ ውስጥ ሰፊ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ አስፈላጊ የሆኑ ማስረጃዎች በፈቃደኝነት የሚሰጥበት ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ በሐሰት የቀረቡ ማስረጃዎችን በማጋለጥ የፍትሕና እውነት ማፈላለግ ጥረቶችን መርዳት አለበት፡፡ በዚህ ረገድ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት በቂ የሆነ ሥርዓቶችን የዘረጋ በመሆኑ ከተጠርጣሪው የሚጠበቀው በእነዚህ ሥርዓቶች መሠረት የሚፈለግበትን መወጣት መቻል ነው፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱ ውጤታማ እንዲሆን የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ተቋማት የሆኑት የመርማሪ አካላት፣ የዐቃቤ ሕግ፣ የተከላከይ ጠበቆች፣ የፍርድ ቤቶች፣ የማረሚያ ቤቶችና ሌሎች የፀጥታ አካላት የተሟላ ቅንጅታዊ አሠራር ድጋፍ የሚረጋገጥበት ሥርዓት መኖር የግድ ይላል፡፡ የፍርድና ከፍርድ ሂደቶች ጋር ተያይዞ ያሉ አሠራሮች ለሕብረተሰቡ ግልፅ እና ክፍት መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን ግልፅነት በመጠቀም ሚዲያዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎች ጉዳዮችን ለመከታተልና ለመመልከት የሚፈልጉ የሕብረተሰቡ ክፍሎች በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ መሳተፍ መቻል አለባቸው፡፡

7.   የግልፅነት፣ የተገማችነት እና የወጥነት መርህዎች (Principles of clarity, predictability and consistency) 

የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት በተጠቃሚው ሕብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነትና ሕጋዊነት (legitimacy) የሚኖረው የሕጐቹ፣ የተቋሞቹ አሠራሮች ግልፅ፣ ተገማችና ወጥነት ሲኖረው ብቻ ነው፡፡ እነዚህ መርህዎች በአጠቃላይ የፍትሕ ሥርዓት እሴቶች (values) ቢሆኑም ለወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ግን የተለየ ትርጉም አላቸው፡፡ የሕብረሰቡ አባላት የሆኑት ዜጐች ወንጀል ሲፈጽሙ በሕጉ አግባብ ነፃነታቸውንና ንብረታቸውን ሊያጡ የሚችሉት በዚህ የወንጀል ፍትሕ ሂደት እንደመሆኑ መጠን ለሕብረተሰብና ለግለሰቦች አሠራሩ ግልፅ፣ ተገማች እና ወጥነት ሊኖረው ይገባል፡፡

እነዚህ መርህዎች በዋናነት የሚከተሉትን ጉዳዮች በውስጣቸው የያዙ ናቸው፡፡ እነሱም የወንጀል ፍትሕ አካላትን የአሠራር ግልፅነት፤ በወንጀል ጉዳዮች ላይ የሚሰጡ ውሳኔዎች፣ ትዕዛዞችና ብይኖች ግልፅነት፣ ተገማችነት እና ወጥነትን፤ በሚሰጡ ውሳኔዎችና በአፈፃፀማቸው መካከል ያለው ግንኙነትና ልዩነት፤ በቀረበው የክስ አቤቱታ እና አቤቱታውን ለማረጋገጥ በተሰበሰቡና በቀረቡ ማስረጃዎችና ክርክሮች መካከል ያለውን ግንኙነት፤ በተያዙ ጭብጦችና በተሰጡ የመጨረሻ ውሳኔዎች መካከል ያለውን ልዩነት፤ የቅጣት አሰጣጥ፣ አፈፃፀም፣ ተገማችነትና ወጥነት፤ ለሕግና ለፍሬ ነገር የሚሰጡ ትርጉሞችና የአተረጓጐም መርህዎች ግልፅነት፣ ተገማችነትና ወጥነት፤ በይግባኝና በሰበር የሚታዩና የሚወሰኑ ውሳኔዎች ምክንያታዊነት፣ ተገማችነት፣ ወጥነት እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት አንዱና ዋነኛው ተልዕኮም የወንጀል ፍትሕ ሂደት ግልፅ፣ ተገማችና ወጥ መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡

8.   የተደራሽነት መርህ (Principles of accessibility)

የተደራሽነት መርህ ሕገ-መንግሥታዊ ዕውቅና ያለው ሲሆን በቀጥታ ከዲሞክራሲና ከመልካም አስተዳደር መርህች ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ ዜጐች በጾታ፣ በኃይማኖት፣ በዕድሜ፣ በዘር፣ በማሕበራዊ ሕይወት፣ በትምህርትና በሌሎች ምክንያቶች ልዩነት ሳይደረግባቸው በፍርድ ሊወሰን የሚችለውን ጉዳይ (Justiciable matter) ለፍርድ ቤት የማቅረብና ውሳኔ የማግኘት መብት ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለው፡፡ በመሆኑም በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ፍትሕ የማግኘት መብት ለተወሰኑና ለሚችሉ የሕብረተሰቡ ክፍሎች (ለምሳሌ ለተማሩ፣ ሀብት ላላቸው፣ ተሰሚነት ላላቸው ወዘተ) ብቻ  የተሰጠ ስጦታ ሳይሆን ለሁሉም የሕብረተሰቡ አባላት (ለድሆች፣ ለሴቶችና ሕፃናት፣ ለአረጋዊያንና ለአካል ጉዳተኞች፣ ላልተማሩትና ለአጠቃላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች) የተረጋገጠና ተግባራዊ መሆን ያለበት መብት ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ይህንን መብት በማያሻማ ሁኔታ ለሁሉም የሕብረተሰባችን ክፍሎችና ግለሰቦች ያረጋገጠ በመሆኑ ይህንን መርህ በግልፅና በዝርዝር ተቋማዊና ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ በመሥራት የዜጐችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ዓላማው መሆን አለበት፡፡

የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱን አስመልክቶ ይህንን መርህ ተግባራዊ ለማድረግ በብዙ መልኩ የሚሰራ ቢሆንም አንዱና ዋነኛው መንገድ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ አማካይነት የወንጀል ፍትሕ ሂደት የሚመራበትን ሥርዓት መዘርጋት በመሆኑ ይህንን መርህ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ተግባራዊና ተቋማዊ ለማድረግ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ በዚህም መሠረት በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተደራሽነት መርህን አስመልክቶ የሚዳሰሰው ጉዳይ ከወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች ቀጥለን እንመለከታለን፡፡

    ሀ. ሕጐችና የአሠራር ሥርዓቶች

የወንጀል ፍትሕ ሂደቱን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ ከተፈለገ ዜጐች በሕግ የተረጋገጠላቸውን መብቶቻቸውን ለማወቅና ለማስጠበቅ እንዲችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ዋነኛውና ሊሰራ የሚገባ ሥራ ነው፡፡ የዜጐች መብቶችና ግዴታዎች ተደንግገው የሚገኙት በሕጐች፣ በአሠራር ሥርዓቶች እና በሚወሰኑ ውሳኔዎች ውስጥ በመሆኑ እነዚህ ሕጐች፣ ውሳኔዎችና የአሠራር ሥርዓቶች ለሁሉም የሕብረተሰቡ ክፍሎች በቀላሉ ተደራሽ መሆን አለባቸው፡፡ በዚህም መሠረት የወንጀል ፍትሕ ሂደቱን አስመልክቶ የሚወጡ ሕጐች፣ የሚወሰኑ ውሳኔዎችና የሚዘረጉ የአሠራር ሥርዓቶች ለሁሉም የሕብረተሰቡ ክፍሎች በቀላሉ የሚገኙና (physically accessibile) ለመረዳትም አስቸጋሪ ያልሆኑ መሆን አለባቸው፡፡

ከዚህ አንፃር የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ የሚጫወተው ሚና በጣም ወሳኝ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን እንደ ምሳሌም የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች የተከሰሱበት የሕግ መሠረት፣ ድንጋጌዎች እና ክሱ ያለውን ሕጋዊ ውጤቶች የሚረዱበትና ራሳቸውን የሚከላከሉበትን ሁኔታዎች፣ በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች አግባብነት ባላቸው ሕጐች ያላቸውን መብቶች የሚያውቁበትንና ከመብቶቹ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ፣ በወንጀል ጉዳዮች ላይ የተለየ ሕጋዊ ጥቅሞች ያላቸው የተለያዩ ሰዎች (ተከሳሽ፣ ተጐጂ፣ ምስክሮች ወዘተ..) ጉዳያቸውን ለመከታተልና ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ ይረዳቸው ዘንድ ከጉዳዩ ጋር ተያይዘው ያሉ የአሠራር ሥርዓቶችን (አዋጆች፣ ደንቦች፣መመሪያዎች የውስጥ አሠራሮች) ከሚመለከታቸው አካላት ጠይቀው የሚረዱበትን አሠራሮች፣በወንጀል ፍትሕ ሂደቱ ውስጥ የሚወሰኑ ውሳኔዎች፣ የሚተላለፉ ትዕዛዞችና ብይኖች የሚመለከታቸውን አካላት በሚፈለገው ጊዜና ጥራት የሚደርሱበትን አሠራሮችንና ውሳኔዎች የሚዘጋጁበትና የሚሰራጩበትን ይዘትና ቅርፅን ያካትታል፡፡

 

 ለ. የወንጀል ፍትሕ ሂደት ተቋማትን በተመለከተ

የወንጀል ፍትሕ ሂደቱን በቀላሉ ተደራሽ ከሚያደርጉ ተግባራት መካከል የወንጀል ፍትሕ ሂደቱን ተቋማት ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ሦስት ገፅታዎች አሉት፡፡ አንደኛው እነዚህን ተቋማት በአካል ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው የፍትሕ ተቋማቱ በአካል (physically) ለሕብረተሰቡ ቅርብ ቢሆኑም የሚፈለገውን አገልግሎት ለመስጠት ግን ምቹ የማይሆኑበት ሁኔታ አለ፡፡ ከዚህ አንፃር የፍትሕ ተቋማቱ ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ የሚሰጡት አገልግሎት ደረጃውን የጠበቀና ለሁሉም የሕብረተሰቡ ክፍል ተደራሽ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሦስተኛው በፍትሕ ተቋማቱ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች የተለያዩ የሕብረተሰቡ ክፍሎችን ለማስተናገድ የሚያስችላቸው የዕውቀት፣ የሥነ ምግባርና የቋንቋ የመሳሰሉ ክህሎቶች ሊኖራቸው ይገባል፡፡

     ሐ. የወጀል ፍትሕ ሂደቱ ወጪዎችን ከመቀነስ አንፃር

የወንጀል ፍትሕ ሂደት በቀላል ወጪና በከፍተኛ ጥራት መሠራት የሚችልበት ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ዜጐች ፍትሕ የማግኘት መብታቸው ተረጋግጧል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ በሌላ አባባል ዜጐች መብቶቻቸውን ለማስከበር የሚያወጡት ወጪ ከሚያገኙት ገቢ አንፃር መክፈል የማይችሉት ከሆነ ዜጐች ከመብቶቻቸው ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ አይገመትም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት መብትን ለማስከበር የሚያስፈልገው ወጪ ከፍ ባለ ቁጥር ብዙው የሕብረተሰቡ ክፍል ትክክለኛና ሕጋዊ መብት እንኳን ቢኖረው ወጪውን ለመሸፈን ባለመቻል ብቻ ሕገ ወጥና ተቀባይነት ለሌለው በደልና አሠራር ተጋላጭ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ፍትሕ የማግኘት መብትን ተግባራዊ ለማድረግ መብቶችን ለማስከበር የሚጠየቀው ወጪ ሕጋዊና ተመጣጣኝ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በዚህም መሠረት በወንጀል ፍትሕ ሂደቱ ውስጥ መብቶችን ለማስከበር የሚወጡ ወጭዎችን ከመቆጣጠርና ከመቀነስ አንፃር የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ወሳኝ ሚና አለው፡፡ ለምሳሌ የወንጀል ፍትሕ ሂደቱ በተንዛዛ ቁጥር ወጪው ይጨምራል፡፡ በወንጀል ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ጥራታቸው ዝቅተኛ ከሆነ ተበዳዩ በውሳኔው ስለማይረካ ለይግባኝ፣ ለሰበር አቤቱታዎች እና ተመሳሳይ ሂደቶች ተጨማሪ ወጪ ይዳረጋል፡፡   በፍትሕ አካላት የሚሰጡት ውሣኔዎች ተገማችና ታማኝነት ከሌላቸው እንደሙስና ያሉ ሕጋዊ ያልሆኑ አሰራሮች እንዲስፋፉ የራሱ የሆነ አሰተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

መ. በወንጀል ፍትሕ ሂደት ውስጥ ለሚታዩ አንዳንድ ጉዳዮች ልዩ ትኩረት መስጠትን በተመለከተ

በወንጀል ፍትሕ ሂደቱ ውስጥ የሚታዩ አንዳንድ የወንጀል ጉዳዮች ከተጐጂዎቹ ወይም ከተጠርጣሪዎቹ ልዩ ማሕበራዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች የተነሳ ልዩ ትኩረት ሊደረግባቸው ይችላል፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ ጉዳዮች በወንጀል ፍትሕ ሂደቱ የሚስተናገዱበት አሠራር የተደራሽነት መርህችን በተከተለ አኳኋን መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ በወንጀል ፍትሕ ሂደቱ ውስጥ በማንኛውም ደረጃ በሚከናወኑ ተግባራት የወጣት ወንጀል አድራጊዎች፣ የወንጀል ተጐጂ ሕፃናት፣ የወንጀል ተጠርጣሪ/ጥፋተኛ ወይም ተጐጂ የሆኑ ሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞች እና በሕብረተሰቡ ውስጥ ተጋላጭ የሆኑ ሌሎች የሕብረተሰቡ ክፍሎችን ፍላጐትና የተለዩ ሁኔታዎች ተገቢውን ትኩረት ማግኘታቸውን መረጋገጥ አለበት፡፡ ይህንና ሌሎች ጉዳዮችን አስመልክቶ የሚሰሩ ሥራዎች የተደራሽነት መርህዎች በተከተለ መልኩ ካልሆነ ብዙም ውጤት አይኖራቸውም፡፡ 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት የቀዳሚ ምርመራ ድንጋጌዎችና አተገ...
የ‹‹ያስቀርባል … አያስቀርብም›› እንቆቅልሽ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024