የ‹‹ያስቀርባል … አያስቀርብም›› እንቆቅልሽ

ዶ/ር ትዝታ በፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ጉዳዩዋን ለመከታተል በችሎት ታድማለች፡፡ በሥር ፍርድ ቤት በቤቷ ላይ ያለአግባብ ፍርድ ተሰጥቷል ብላ ስላመነች የተማረ ጠበቃ የይግባኝ አቤቱታ ጽፎላት ጉዳይዋን በራሷ ትከታተላለች፡፡ እንደ እርሷ አስተሳሰብ ጉዳይዋን ከእርሷ ይልቅ የሚረዳው የለም በሚል ከዳኛ ፊት ቀርባ ለማስረዳት ጓጉታለች፡፡ በዛሬው ቀጠሮ ይህ ሐሳቧ እንደሚሳካላት በውጭ የሚያማክራት ጠበቃ ነግሯታል፡፡

መዝገቡ ለዛሬ በቀጠሮ ያደረው ቀደም ሲል ረዳት ዳኛ ፊት ቀርባ ስለጉዳዩ ካሳሰበች በኋላ የይግባኝ አቤቱታውን ለመስማት በሚል ነው፡፡ ችሎት ተቀምጣ የምትሰማው የዳኛው ድምፅ ‹‹አያስቀርብም ብለናል!›› ‹‹አያስቀርብም›› የሚሉ አጭርና መርዶ ነጋሪ ቃላት ናቸው፡፡ የእሷ ጉዳይ ገና ያልተሰማ በመሆኑ እንዲህ ያለውን ፍርድ ዛሬ እንደማትሰማው አምናለች፡፡ የሕግ አማካሪዋም ልቧን አጽንቶላታል፡፡ ተራዬ እስኪደርስ በሥር ፍርድ ቤት ተፈጸመ የተባለውን ስህተት ለማስረዳት ከማስታወሻዬ ላይ ነጥቦቹን ተራ በተራ በወፍ በረር ልቃን ብላ ጀምራለች፡፡ ከተመሰጠችበት ንባብ ያናጠባት በዳኛው የተጠራው ስሟ ነበር፡፡
‹‹ዶ/ር ትዝታ በረደድ›› ብለው ዳኛው ሲጠሩ ከመቅጽበት ከዳኛው ፊት ተገተረች፡፡ ዳኛው ማንነቷን ካረጋገጡ በኋላ ‹‹ይግባኙ አያስቀርብም ብለናል፤›› ሲሏት በደንብ አልሰማቻቸውም፡፡ ‹‹እህ እህ ምን አሉ?›› ብላ ስትጠይቅ ‹‹አያስቀርብም ተዘግቷል፣ ጨርሰናል፤›› አሏት፡፡ ‹‹ይግባኜ አልተሰማም፣ ረዳቱ ነው ያናገረኝ፣ እርስዎን ዛሬ ማየቴ ነው… ለውሳኔ አልተቀጠረም… መዝገቡ የሌላ እንዳይሆን …›› ብዙ ለማለት ብታስብም ባህላዊው የፍርድ ቤት ፍርኃት አላስችላት አለ፡፡ ከእሷ በፊት የተስተናገዱት አቀርቅረው እንደወጡ እሷም በቁሟ አቀረቀረች፡፡ ከዳኛው ፊት እንደቆመች ዳኛው ሌላ ባለጉዳይ ማስተናገድ ቀጠሉ፡፡
በዚህ መነሻ ነበር ከችሎት ስትወጣ ጨዋታ የጀመርነው፡፡ ‹‹አያስቀርብም›› ማለት ምንድነው? በምን ምክንያት ነው? የማያስቀርበውስ እንዴት ነው? ዳኛው ይግባኜን አይሰሙም እንዴ? የሚሉትንና እኔ መልስ ልሰጣት የማልችላቸውን ጥያቄዎች ያዥጎደጎደችው፡፡ ሕጉ የሚለውን፣ ዳኛው ሊፈጽሙት ይገባ የነበረውን ሥርዓት ብነግራት ይባሱኑ ትበሳጫለች በማለት በቀልድ ነገሯን ለማጣጣል ጥረት አደረግኩ፡፡
እናንተ ሐኪሞችስ በማይነበብ ጽሑፍ ለበሽታህ መድኃኒቱ ይሄ ነው ብላችሁ ብጣቂ ወረቀት ትሰጡ የለም እንዴ? አልኳት፡፡ ዶ/ር ትዝታም መለሰች ‹‹እንዴ እኛ እኮ ደማችሁን ለክተን፣ ሙቀታችሁን አይተን፣ የሚሰማችሁን በዝርዝር ሰምተን፣ ደምና ሰገራ፣ ኤክስሬይና ራጅ ተመልክተን ነው፤ ከጻፍነውም በኋላ የመድሃኒት ባለሙያ የማይነበበውን አንብቦ ተገቢውን መድሃኒት ይሰጣችኋል አለች›› በልቤ ‹‹ልክ ነሽ›› አልኩ፡፡ እንዲያውም የመደመጥ መብት በሐኪሞች የተሻለ ይተገበራል፡፡ በእኛ አገር ሐኪሞች ከዳኞች ይልቅ ደንበኛቸውን ይሰማሉ፣ ጊዜ ይሰጣሉ፣ ሰፊ ምርመራም ያከናውናሉ አልኩ፡፡ እርሷንም እንድትጽናና ነግሬያት የነጋሪት ጋዜጣ ወደ መግዣው ሱቅ በመሔድ ከእሷና ከሐሳቧ ሸሸሁ፡፡

የ‹‹ያስቀርባል - አያስቀርብም›› ነገር ግን የሕግ ዕውቀቱ የሌላቸውን ቀርቶ ለሕግ ባለሙያዎችም በአግባቡ የሚገባ ወይም የተረዳ አይመስለኝም፡፡ ፀሐፊው በፍርድ ቤቶች አካባቢ ከገጠሙት ጉዳዮችና በችሎት ከሚያስተውለው ተግባር አንፃር ‘አያስቀርብም እንቆቅልሽ፣ ያስቀርባል ሎተሪ’ እየሆነ መምጣቱን አስተውሏል፡፡ የ‹‹አያስቀርብም›› ልማድ በሰበር ችሎት ሳይቀር የሚስተዋል ቢሆንም፣ በዚህ ጽሑፍ በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የታዘብኩትን አጠር አድርጌ ለመቃኘት እሞክራለሁ፡፡ ተሞክሮው በጎ የተሠራውን፣ ጊዜ ወስዶ መዝገብ መርምሮ በምክንያት ወይም ያለምክንያት አያስቀርብም የሚሉትን ተሞክሮዎች ስለማይመለከት የአሠራር ክፍተት ባለባቸው ላይ ማተኮሩ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አያስቀርብም በሕጉ ያለውን ቦታ፣ ከዳኛው የሚጠበቀውን ሥርዓት፣ በተግባር የሚታዩ ክፍተቶችን፣ የክፍተቶቹን አንድምታ በመቃኘት የሚስተካከልበትን መፍትሔ ለመጠቆም እሞክራለሁ፡፡

ስለ ይግባኝ መብትነት

አንድ ሰው በሥር ፍርድ ቤት ፍርድ አሰጣጥ ቅር ሲሰኝ ይግባኝ የመጠየቅ መብት አለው፡፡ የሥር ፍርድ ቤት በፍሬ ነገር ወይም በሕግ ጉዳይ ወይም በሥነ ሥርዓት አካሔድ የፈጸመው ስህተት እንዲታረምለት የበላይ ለሆነው ፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብ መብት አለው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የወንጀል ጉዳዮችን በተመለከተ በግልጽ የተከሰሰ ሰው የይግባኝ መብት እንዳለው ቢደነግግም (አንቀጽ 20(6)) መብቱ በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ላይም የፀና ነው፡፡ ፍትህ የማግኘት መብት ((አንቀጽ 37)ን ይመለከቷል) በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት የማቅረብ፣ ውሳኔ የማግኘትና በውሳኔው ቅር ከተሰኘም ይግባኝ የመጠየቅ መብትን እንደሚያጠቃልል ዓለም አቀፍ ስምምነት አለ፡፡ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 320ም ከሳሽ/ተከሳሽ በፍትሐብሔር ፍርድ ቤት በተወሰነበት የመጨረሻ ፍርድ ላይ ይግባኝ ለማለት ይቻላል በማለት ለይግባኝ የሕግ መሠረት ጥሏል፡፡ ፍርድ ቤቶች በየደረጃው የመዋቀራቸው አንዱ ምክንያት የይግባኝ መብትን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሰጠው ፍርድ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ፍርድ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረብ እንዲቻል ሕገ መንግሥቱ ፍርድ ቤቶችን በደረጃ አዋቅሯል፡፡ የፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጆች የይግባኝ ሥልጣንን በየደረጃው በመስጠት የግለሰቦች የይግባኝ መብት ተግባራዊ የሚሆንበትን አደረጃጀት ቀርጸዋል፡፡ ይግባኝ የራሱ ዓላማ አለው፡፡ ሁሉም ዳኛ ምሉዕ ነው፣ በትክክል ይሠራል የሚል ግምት ሙሉ በሙሉ ስለማይወሰድ ዳኛው የፈጸመው ስህተት የሚታረምበት ሥርዓት ተበጅቷል፡፡ ዳኛው ሰው በመሆኑ፣ ከዕውቀትና ከልምድ ማነስ፣ አለዚያም በሙስናና ብልሹ አሠራር የተሳሳተ ፍርድ ሊሰጥ ስለሚችል ይግባኝ የማረሚያ፣ የማስተካከያ፣ ሥርዓት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

የዳኞች አሿሿምም ዕውቀትና ልምድን መሠረት ያደረገ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ በከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚያስችል ዳኛ፣ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ካለው የተሻለ ዕውቀትና ልምድ አለው የሚል ግምት ስላለ በሥር ፍርድ ቤት የተፈጸሙ ስህተቶችን ለማረም የሚያስችል ብቃት ይኖረዋል፡፡ በዚህ መነሻነት ነው ግለሰቦች በሥር ፍርድ ቤት በተሰጠ ፍርድ ላይ ይግባኝ ለማቅረብ ሕጉ የሚፈቅድላቸው፡፡ ያም ሆኖ ይግባኝ ማለት የሚፈቀደው በመጨረሻ ፍርድ ላይና የሥር ፍርድ ቤት ስህተቱን ለማረም፣ ለማጣራት ወይም እንደገና ለማጣራት ባልቻለ ጊዜ ነው፡፡ ይግባኝ የሚባልባቸው ጉዳዮች በሥር ፍርድ ቤት በተፈጸመ የፍሬ ነገር ወይም የሕግ ጉዳይ ላይ ሲሆን፣ ይግባኙ በሥነ ሥርዓት ሕጉ በተዘጋጀው ፎርምና ሕጉ በሚፈቅደው ይግባኝ የመጠየቂያ ጊዜ ውስጥ ሊቀርብ ይገባል፡፡

የ‹‹አያስቀርብም›› የሕግ መሠረት

ያስቀርባል - አያስቀርብም የሚሉት በፍርድ ቤቶች የተለመዱ ቃላት በሥነ ሥርዓት ሕጉ በግልጽ ተመልክተው አናገኛቸውም፡፡ በፍርድ ቤቶች ልማድ የዳበሩና በሒደት ትርጉማቸው ለሁሉ የተረዳ የሥነ ሥርዓት ደረጃዎች ግን ሆነዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የይግባኝ አቤቱታ ቀርቦለት አቤቱታውን ተመልክቶ፣ የሥር ፍርድ ቤትን ፍርድ መርምሮ ይግባኝ ባዩን ከሰማ በኋላ የሚሰጠው የማጣሪያ ሥርዓት ‹‹ያስቀርባል- አያስቀርብም›› ብይን ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ይግባኝ ከሚሰማበት ሥርዓት ይለያል፡፡ ይግባኝ የሚሰማው የይግባኝ አቤቱታ ባልተሰረዘ ጊዜ ዳኛው ለመልስ ሰጪ መጥሪያ ልኮለት ሲቀርብ ግራ ቀኙን የሚሰማበት ሥርዓት ነው፡፡ ያስቀርባል - አያስቀርብም ግን በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 327 ድንጋጌ ሥር ይወድቃል፡፡
‹‹ይግባኝ ባዩ ያቀረበው የይግባኝ ማመልከቻ የተመሠረተው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሰጠው የፍርድ መዝገብ ላይ ብቻ ሆኖ … ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ነገሩ የሚሰማበትን ቀነ ቀጠሮ ወስኖ ይግባኝ ባዩ ወይም ጠበቃው የሚያቀርቡትን ክርክር ከሰማ በኋላ የመጀመሪያው ደረጃ ፍርድ ቤት ፍርድ የሰጠበትን የመዝገብ ግልባጭ መርምሮ ጉድለት የሌለበት መሆኑን ከተረዳው፣ መልስ ሰጪን ሳይጠራ ይግባኙን ዘግቶ አቤት ባዩን ሊያሰናብት ይችላል፡፡››

ይህ ድንጋጌ ለ‹‹አያስቀርብም›› የሕግ መሠረት ይሰጣል፡፡ ዳኛው ግን የቀረበለትን ይግባኝ አያስቀርብም ከማለቱ በፊት ሊፈጽም የሚገባው ሥርዓት በግልጽ ተመልክቷል፡፡ መጀመሪያ ይግባኙ በሥር ፍርድ ቤቱ የመጨረሻ ደረጃ ላይ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ይግባኝ ባዩ ሌላ ማስረጃ እንዲታይለት ወይም ሌሎች ምስክሮች እንዲሰሙለት አለመጠየቁም ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ይግባኝ ባዩ ማስረጃ እንዲቀርብለት ከጠየቀ ፍርድ ቤቱ ስለ ማስረጃው አግባብነትና ስለአቀራረቡ በሥነ ሥርዓት ሕጉ ላይ የተመለከቱትን ሥርዓቶች ሊከተል ይገባል፡፡ ሁለተኛው የይግባኝ ማመልከቻው ለፍርድ ቤቱ እንደቀረበ ፍርድ ቤቱ ነገሩ የሚሰማበትን ቀነ ቀጠሮ ወስኖ ይግባኝ ባዩ ወይም ጠበቃው የሚያቀርቡትን ክርክር ሊሰማ ይገባል፡፡ ይህ ሥርዓት እጅጉን አስፈላጊና በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ሊታለፍ የማይገባው ነው፡፡ ይህን ሥርዓት ሳይፈጽሙ በደፈናው አያስቀርብም ማለት ሕገመንግሥታዊና የሰብዓዊ መብት የሆነውን የመሰማት መብት መንፈግ ነው፡፡ በጥቅምም ደረጃ አቤት ባዩ ክርክሩን ካላሰማ ፍርድ ቤቱ የይግባኙን ነጥቦችና በሥር ፍርድ ቤት ላይ ያለውን ቅሬታ ሊገነዘበው አይችልም፡፡ ድንጋጌው በሦስተኛ ደረጃ የሚያስቀምጠው ዳኛው ይግባኙን ከአመልካቹ ከሰማ በኋላ የሥር ፍርድ ቤትን መዝገብ ግልባጭ መርምሮ መደምደሚያ ላይ ይደርሳል፡፡ በዚህ ጊዜ የሥር ፍርድ ቤት አካሄድ፣ ማስረጃ አሰማም፣ ጭብጥ አያያዝ፣ የፍሬ ነገርና የሕግ ትንታኔ ወዘተ. ጉድለት የለበትም ብሎ ካመነ ‹‹አያስቀርብም›› በሚል ይግባኙን ሊሰርዘው ይችላል፡፡

ጉድለት እንዳለው ካመነም ‹‹ይግባኙ ያስቀርባል›› በማለት ለመልስ ሰጪው መጥሪያ በመላክ ግራ ቀኙን የሚሰማበትን ቀጠሮ ይይዛል፡፡ ፍርድ ቤቱ ያስቀርባል ሲል በየትኞቹ ነጥቦች ላይ መሆኑን በግልጽ ማመልከት የሚጠበቅበትን ያህል አያስቀርብም ሲልም የተሻለ አሳማኝ ምክንያት ካለው ይህንኑ በግልጽ ቢያሰፍር ፍትሐዊና አሳማኝ ይሆናል፡፡ በተግባር ግን በሕጉ በተቀመጠው መሠረት ‹‹ያስቀርባል - አያስቀርብም›› በአግባቡ ለመፈጸሙ ሁልጊዜ ምስክርነት ማግኘት ያስቸግራል፡፡

በተግባር የሚስተዋሉ ችግሮች

‹‹አያስቀርብም›› ተብለው የተዘጉ መዛግብትን በጥሞና ካልመረመሩ፣ ጥናት አጥንቶ ሁሉን የሚወክል መደምደሚያ እስካልሰጡ ድረስ በተግባር የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚዳስስ ጽሑፍ የግል ተሞክሮ ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡ የግል ሲባል በችሎት ታድመን የሰማነው፣ በያዝነው ጉዳይ የሚያጋጥመን ወይም ሌሎች የሕግ ባለሙያዎች የነገሩን ነው፡፡ ለዚህ ጽሑፍ የተወሰኑትን እናንሳ፡፡

አንደኛ፡- ይግባኙን ከአቤት ባዩ ወይም ከጠበቃው ሳይሰሙ በደፈናው አያስቀርብም በማለት መዝገብን መዝጋት ዋነኛው ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑ ሁለት ጉዳዮችን እንጥቀስ፡፡ በአንድ የንግድ ኩባንያ የፍትሐብሔር ክርክር ጉዳይ የባለአክሲዮንነት መብትና ዳይሬክተሮች ያለጠቅላላ ጉባዔ ፈቃድ ስለሚከሰሱበት ሁኔታ በሥር ፍርድ ቤት በተሰጠ ፍርድ ላይ ይግባኝ ቀረበ፡፡ በችሎቱ የተሰየሙት ዳኛ ዝርዝሩን ጠየቁ፡፡ ጠበቃውም በዝርዝር አስረዳ፡፡ ዳኛው ያስቀርባል አያስቀርብም በሚለው ጭብጥ ላይ ብይን ለመስጠት የአንድ ወር ቀጠሮ ሰጡ፡፡

በቀጠሮው ዕለት ብይን ለመስማት ባለጉዳዮቹ ችሎት ሲገኙ ዳኛው ተቀይረው ሌላ ሴት ዳኛ ተሰይመዋል፡፡ ጉዳዩ ጥሬ ሆነ፡፡ ዳኛዋ ይግባኙን አልሰሙትም፡፡ የቀድሞውም ዳኛ የመዘገቡት ካለ ነጥቦቹን በአግባቡ ስለመረዳታቸው ፈጣሪ ይወቅ፡፡ ዳኛዋም ባለጉዳዮቹን ጠበቃችሁን በሚቀጥለው ቀጠሮው ቀርበው ይግባኙን እንዲያስረዱ ንገሩ በማለት ቀጠሮ ተለወጠ፡፡ በተለወጠው ቀጠሮ ቀን ጠበቃው ቢቀርቡም መስማት አያስፈልግም ብይኑን እየሠራን ነው በማለት በአዳሪ ‹‹አያስቀርብም›› በሚል መወሰኑ ተሰማ፡፡
ዳኛዋ ይግባኙን ባልሰሙበት ሁኔታ የትኞቹን ጭብጦች በምን ምክንያት አያስቀርብም እንዳሉ ከመዝገቡ መረዳት አልተቻለም፡፡ በሌላ ጉዳይ ዳኛው ለይስሙላ የይግባኝ አቤቱታውን በአጭሩ እንዲገልጽ አድርገው ከተወሰነው ፍርድ ግልባጭ ጋር ስለመመርመራቸው ሳይገልጹ ወዲያው አያስቀርብም ተባለ፡፡ ባለጉዳይን ሳይሰሙ፣ ቢሰሙም በጥሞና አዳምጦ ስለአግባብነቱ ከሕጉና ከቀድሞው መዝገብ ጋር ሳይመረምሩ የመዝገብ ብዛት ለመቀነስ በዕለቱ ‹‹አያስቀርብም›› ብሎ ባለጉዳይ ማሰናበት ሌላው በተግባር የሚስተዋል ችግር ነው፡፡ 

ሁለተኛ፡- ይግባኝ ቀርቦ ይግባኙን ከአቤት ባዩ ወይም ከጠበቃው ሳይሰሙ፣ አንዳንድ ጊዜም በአግባቡ ሰምቶ ያስቀርባል አያስቀርብም በሚለው ጭብጥ ላይ ብይን ሳይሰጡ ቀጠሮዎችን መለወጥ ይታያል፡፡ ጸሐፊው ያነጋገራቸው ጠበቆች ይግባኙ እንደተሰማ ወይም በሚቀጥለው ቀጠሮ ሊሰጥ የሚገባው ብይን እንደ ልማድ ሆኖ በቀጠሮዎች ይታጀባል፡፡ አንዳንድ ዳኛ ይታመማል፣ እክል ይገጥመዋል ወይም ስብሰባ ይበዛል፡፡ አንዳንዴ አልተመረመረም ተብሎ ቀጠሮ ይለወጣል፡፡ በተስፋ ቀጠሮ ሲከታተል የሚኖር ባለጉዳይ አንድ ቀን ሳያስበው ‘አያስቀርብም’ የሚል የመርዶ ብይን ይሰማል፡፡ የተነሣው የሕግ ጭብጥ ውስብስብ ሆኖ ወይስ መዛግብት በዝተው ወይስ በመራዘሙ የሚጠቀም አካል ኖሮ የሚለው በየጓዳው ካልሆነ በአደባባይ መልስ አይገኝለትም፡፡

ሦስተኛ፡- ምክንያት አለመግለጽ፡፡ ዳኛ የሚሰጠው ፍርድ ፍትሐዊ፣ ተጠያቂነት ያለውና ሁሉንም የሚያስማማ መሆኑ የሚታወቀው በሚሰጠው ብይን፣ በያዘው አቋም ምክንያቱን ሲያሰፍር ነው፡፡ በሌሎች አገሮች የሕግ ሥርዓት ውስጥ ይህ የተለመደ ወግ ነው፡፡ በእኛ አገር ግን እንኳን የመጀመሪያ ይግባኝ የሚመለከተው ፍርድ ቤት በሰበር ችሎት አናስተውልም፡፡ ምክንያት አለመስጠት የፍርድ ቤቶች ነባር አቋም ሆኖ ያለ ጥያቄና ያለጠያቂ ቀጥሏል፡፡ በዚህ ረገድ የአስተዳደር ውሳኔ ከፍርድ ቤት ብይን ስላለመሻሉ መከራከር የሚችል ደፋር የሕግ ምሁር መኖሩ ያጠራጥራል፡፡ አስተዳደራዊ አካል ለእያንዳንዱ የሚቀርብለት ይግባኝ ፍሬ ነገሩን፣ የደረሰበትን መደምደሚያና ምክንያቱን መግለጹን በዕለት ተዕለት የሥራ ተሞክሮ እናስተውላለን፡፡ ፍርድ ቤቶች የሥራ ጫና ቢበዛባቸውም ፍርዳቸው የሕዝብ ሰነድ እንደመሆኑ አጠር ያለ ምክንያት እንኳን ለአቋማቸው አመክንዮ ቢገልጹ የተሻለ ነበር፡፡

አራተኛ፡- ወጥነት አለመኖር፡፡ ተመሳሳይ ጉዳዮች በተለያዩ የይግባኝ ችሎቶች በመቅረባቸው ብቻ አንዱ ያስቀርባል፣ ሌላው አያስቀርብም ሲባል መስማት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የቱ ትክክል ነው፣ የትኛው ተሳስቷል የሚለውን ለመገምገም ምክንያት የተገለጠበት ብይን መመልከት የተለመደ አይደለም፡፡ ለተጠያቂነት፣ ለፍርድ ትችትም የማይመች አሠራር በመሆኑ የተለያዩ ዳኞች በተመሳሳይ ጭብጥ የተለያየ አቋም ሲይዙ ይስተዋላል፡፡

አምስተኛውና የመጨረሻው ያስቀርባል አያስቀርብም ለሚለው ጭብጥ መነሻ የሚሆነውን ሙግት ከሚያከናውኑ ረዳት ዳኞች ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡ በመሠረቱ ረዳት ዳኞች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያልተሾሙ፣ ዳኞችን በቢሮ ውስጥ ከሚረዱ በቀር በአደባባይ በችሎት መሰየም፣ አቤቱታንም መስማት የሚችሉ አይደሉም፡፡ በተግባር ግን ከእያንዳንዱ ያስቀርባል አያስቀርብም ክርክር ጀርባ ረዳት ዳኞች መኖራቸውን እናስተውላለን፡፡

ለአብነት ከሰሞኑ የተወሰነ አንድ የይግባኝ መዝገብን እንመልከት፡፡ መዝገቡ ከሥራ ክርክር ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ረዳት ዳኛው በቢሮው የባለጉዳዩን ይግባኝ ከጠበቃው ሰማ፡፡ የሰማውንም እንዲሁ መዘገበው፡፡ ተለዋጭ ቀጠሮ ሲሰጥም ‘ዳኛ ጋር ቀርባችሁ ይግባኙን እንደገና ይሰሙታል’ በማለት ባለጉዳዩን አሰናበተ፡፡ በተለዋጭ ቀጠሮ ጠበቃው ይግባኙን ለማሰማት በችሎት ሲገኝ ዳኛው የተለመደውን ‘አያስቀርብም’ የሚለውን ድምፅ አስተጋቡ፡፡ ለመሆኑ በዚህ ጉዳይ የሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 327 በሚፈቅደው መልኩ ይግባኙ ተሰምቷል? ረዳት ዳኛው ይግባኙን ቢሰማውም ፍርድ ቤቱ ይግባኙን ሰምቶታል ለማለት ቀደም ብለን በገለጽነው ምክንያት አይቻልም፡፡ ረዳት ዳኛውም ዳኛው ደግመው በችሎት ይሰሟችኋል እንጅ ያስቀርባል - አያስቀርብም ብይን ይሰጣሉ አላለም፡፡ ያልተሾሙ ረዳት ዳኞች ይግባኝ የሚሰሙ ከሆነ፣ የዳኞች ቁጥር ለምን አነሰ? እንዲፈርሙስ ለምን አይደረግም? ከሙስና እና ብልሹ አሠራር አንፃርስ ክፍተት ቢገኝ ተጠያቂው ማነው? በረዳቶቻቸው ምክንያት በሙስና ተጠርጥረው የታገዱ ዳኞችን ጉዳይ አልሰማንምን?

የችግሮቹ አንደምታ

የ‹‹ያስቀርባል - አያስቀርብም›› ተግባራዊ ችግሮች አንድምታ ሰፊና አደገኛ ነው፡፡ የተወሰኑትን ለመጥቀስ የሰበር ሰሚ ችሎት ላይ ካለው ጫና መነሳት እንችላለን፡፡ በአሁኑ ወቅት በፌዴራል ሰበር ከሚቀርቡ ጉዳዮች ብዛት አንፃር ችሎቱ ሌላ የይግባኝ ሰሚ ችሎት እንዲሆን ያደረገው ይመስላል፡፡ የሥር ፍርድ ቤቱን ፍርድ በአግባቡ ሳይመረምሩ በማጽናት፣ ወይም ያለምክንያት አያስቀርብም በማለት መዛግብት ሽቅብ እንዲፈሱ አድርገዋል፡፡

አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር በሕግ ትምህርት ቤት 50ኛ ዓመት በዓል ላይ ጽሑፍ ሲያቀርቡ የሰበር ችሎት አሠራር ችግር ውስጥ በመግባቱ የፍርድ ቤቶች ደረጃና የመዛግብት ብዛት የፒራሚድ ቅርጽ (ሦስት ጎን) ሊይዝ ሲገባው የዋርካ ገጽታ ይዟል ብለዋል፡፡ ከሥር ፍርድ ቤት ወደ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሚሄዱ ጉዳዮች ሊያንሱ ሲገባ፣ እየጨመሩ ሄደዋል፡፡ ይህ ጤናማ አይደለም፡፡ ለዚህ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ያለ በቂ ምርመራ አያስቀርብም ተብለው የሚዘጉ መዛግብት ናቸው፡፡ ለዚህ ነው የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት 18 ከሚሆን ጥራዝ (ቮልዩም) ውስጥ አብዛኛውን ከሥር ፍርድ ቤት የተወሰነው በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በይግባኝ ሳይታረሙ ለመጡ ጉዳዮች አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ለመስጠት የተገደደው፡፡

ሁለተኛው አንድምታ ከያስቀርባል አያስቀርብም ጋር የተያያዙ ችግሮች መበራከት የይግባኝ መብትን ዋጋ ያሳጣል፡፡ ያስቀርባል አያስቀርብም በአንድ በኩል የአቤት ባዩን ሕገ መንግሥታዊ የይግባኝ መብት የማይሸረሽር በሌላ በኩል ያለአግባብ ጊዜ ለመግዛት የሚመጡ ይግባኞችን ለመግታት ሚዛናዊ ሆኖ ካልተተገበረ አደገኛ ይሆናል፡፡ ከላይ የተመለከትናቸው ተግባራዊ ክፍተቶች ይግባኝ መብት መሆኑ እንዲዘነጋና አያስቀርብም ማለት የፍርድ ቤቶች ግዴታ እንዳያደርገው ሥጋት አለ፡፡

ሦስተኛው ያለምክንያት አያስቀርብም በማለት መዛግብትን መዝጋት፣  የቀጠሮ ጊዜ ማብዛትና በተመሳሳይ ጉዳዮች የተለያዩ አቋሞች የሚንፀባረቁ ከሆነ የፍርድ ቤቶች አሠራር ተገማች እንዳይሆን፣ ፍርድ ቤቶች በኅብረተሰቡ ያላቸው አመለካከት ዝቅ እንዲልና አሠራሩ ለሙስናና ለብልሹ አሠራር የተጋለጠ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ታስቦ ለሚሠራ የዳሰሳ ጥናትም ፍንጪ ሰጪ ጥናት ለማካሄድ አያስችልም፡፡

እንደ መፍትሔ

ችግሩን ማወቅ ግማሽ መፍትሔ ነው እንዲሉ ፍርድ ቤቶች የተጠቆሙት ችግሮች ተንሰራፍተው መኖራቸውን ጥናት በማድረግ ሊረዱት ይችላሉ፡፡ ትንሽ የሥነ ሥርዓት ግድፈት መሠረታዊ መርህን ታጠፋለች፡፡ በቸልተኝነት ያስቀርባል ወይም አያስቀርብም የሚባሉ መዛግብት የአቤት ባዩን የይግባኝና የመሰማት መብት፣ የፍርድ ቤቶችን መልካም ስም ያጎድፋሉ፡፡ መጽሐፍ ‹‹ጥቃቅን ቀበሮዎች የወይን እርሻውን እንዳያጠፉት አጥምዷቸው፤›› እንደሚል ለፍትሕና ለሕግ ሥርዓት ልዕልና የሚጨነቅ አካል መለስ ብሎ የይግባኝ አቤቱታ አቀራረብ፣ አሰማምና ምርመራን ሊመለከተው ይገባል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የአሠራር መመሪያ ማዘጋጀትና ጠንከር ያለ ቁጥጥር ማድረግ ልማዱ እንዲሰበርና ዳኞች እያንዳንዱን ጉዳይ በጥንቃቄ እንዲመለከቱት ያስችላል፡፡ ችግሩ መፍትሔ ካላገኘ ግን እነ ዶ/ር ትዝታን የመሰሉ ባለጉዳዮች ብቻ ሳይሆኑ እንጀራቸው ፍርድ ቤት የሆነ ጠበቆችና ነገረ ፈጆች በፍርድ ቤት ላይ ያላቸው መተማመን ይቀንሳል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ዳኞች፣ ዐቃቤ ሕጎች፣ ጠበቆች እና ፖሊሶች ሊዘነጓቸው የማይገቡ የወንጀል ሥነ ሥ...
ሰበር በአዲስ አበባ ፍርድ ቤት ሥልጣን ላይ ያሰመረው ቀጭን መስመር

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Monday, 20 May 2024