Font size: +
9 minutes reading time (1738 words)

በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት የቀዳሚ ምርመራ ድንጋጌዎችና አተገባበራቸው አጭር ዳሰሳ

የወንጀል ክስን በማስረጃ አስደግፎ በማረጋገጥ እና ተከሳሽን ወደ ፍርድ ቤት በማቅረብ ጥፋተኛ ማስደረግ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ ትልቅ ጥረትና ድካም የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ አንድ ወንጀል ማህበረሰቡ ላይ ሲፈጸም ወንጀሉን የፈጸመን አካል ነቅሶ በማውጣት ለፍርድ በማቅረብ ማስቀጣት የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ አንድ መንግሥት የሕዝብን  ሥልጣን  ሲቀበል  የማህበረሰቡን  ሰላም  መጠበቅ ከሕዝቡ የተጣለበት  ግደታው  ነው፡፡ ይህንን ሰላም ለመጠበቅ  ደግሞ  ወንጀል  እንዳይፈፀም ይከላከላል፡፡ ከተፈፀመ በኋላ ፈፃሚውን ለሕግ ያቀርባል፣ ወንጀል ለመፈፀሙ ሊያሥረዱ የሚችሉ ማስረጃወችን አብሮ ያቀርባል፡፡

ቀዳሚ ምርመራም መንግሥት ወንጀል መፈፀሙን ለማሥረዳት የሚችሉ ማስረጃወችን የሚሰበስብበት አንዱ መንገድ ነው፡፡ ቀዳሚ ምርመራ ክስ ከመሰማቱ በፊት በፍርድ ቤት የሚደረግ የማስረጃ መስማት እና ለክስ መስማት የሚቀርበውን ጉዳይ የመለየት ሂደት ነው፡፡

የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት በሦስተኛ መጽሐፉ ከአንቀፅ 80 እስከ 93 ድረስ ስለ ቀዳሚ ምርመራ የሚያትቱ ድንጋጌዎች አካትቶ ይገኛል፡፡ ይህ ጽሑፍ የሚያተኩረው በሃገራችን ያለውን የሕግ ማዕቀፍ ይዘት እና የተግባር አሠራር የሚመለከት ነው፡፡ በአተገባበር ደረጃ ግድፈት አለባቸው ተብለው በጸሐፊው እይታ የታዩ ደንጋጌዎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ እስከተቻለ ድረስ የሕጉን መንፈስ እና በተግባር ምን እየተሠራ እንደሆነ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡

የቀዳሚ ምርመራ ጠቃሜታ

ቀዳሚ ምርመራ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ዐቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶ ጉዳዩን በሥረ ነገር ሥልጣን ደረጃ ማየት እና ማከራከር ለሚችለው ፍ/ቤት ከመቅረቡ ቀድሞ ወንጀሉ በተፈፀመበት አካባቢ ያለው  የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የሚያደርገው ምርመራ ነው፡፡ ይህ ቀዳሚ ምርመራ አደራጊ ፍ/ቤት ጉዳዩን አይቶ እና አከራክሮ ውሳኔ ለመስጠት ሥልጣን የለውም፡፡ ሆኖም ግን ወንጀሉ ከተፈፀመበት ቦታ ቅርበት አንጸር ማስረጃ ቶሎ አሰባስቦ ዱካው ሳይጠፋ በፍ/ቤት አስመዝግቦ መያዝ እና በኋላም ይህ ማስረጃ ጉዳዩን በሚሰማው ፍ/ቤት በማንኛውም ዓይነት ምክንያት ቀርቦ መመርመር ባይችል የተመዘገበውን እንደ ማስረጃ ማቅረብ ይችላል፡፡

ማስረጃ ሲባል ምስከር ብቻ የሚመስለው ማህበረሰብ ባለበት፤ የአብዛኛው ወንጀል ድርጊቶች ማስረጃ ሰው ብቻ በሆነበት እና ምስክሮች ፍ/ቤት  ቀርቦ ለመመስከር በቀጠሮ ቀን ያለመገኘት ችግሮች ራስ ምታት በሆነበት በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ወንጀል መፈፀሙን የሚያውቁት ሰዎች በሚገኙበት በቅርበት በሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ በማድረግ እና በመመዝገብ ለማስረጃነት ማቅረብ ተገቢ እና ለፍትሕ አስተዳደሩም ትልቅ ሚና አለው፡፡

በሥራ ላይ ባለው የ1954ቱ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት የቀዳሚ ምርመራን ጠቀሜታ በግልፅ አላስቀመጠም፡፡ ሆኖም ግን የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 144 ርእሱ በቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍ/ቤት ምስክሮች የሰጡት ቃል በማስረጃነት ሊቀርብ ስለመቻሉ ብሎም ምስክሮች ክሱን በሚሰማው ፍ/ቤት ቀርበው መስማት በተለያዩ ምክንያቶች ባልቻሉ ጊዜ በቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍ/ቤት ዘንድ የሰጡት የምስክርነት ቃል በችሎት ከተነበበ በኋላ ክሱን ሊያሥረዳ እንደሚችል አስቀምጧል፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ቀዳሚ ምርመራ በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር የሚጫወተው ሚና ማስረጃን ጠብቆ ለማቆየት የተዘጋጀ ዘዴ እንደሆነ ነው፡፡ በአዲሱ ረቂቅ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ የቀዳሚ ምርመራን ዓላማ በአንቀጽ 162 ሥር ደንግጎት ይገኛል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የቀዳሚ ምርመራ ዓላማ በምርመራ አካላት የተሰበሰቡ ጠቃሚ የሆኑ እና የማሥረዳት ዋጋቸው ከፍ ያለ ማስረጃወችን በአግባቡ ለመያዝ እና ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ነው በማለት በግልጽ አስቀምጦታል፡፡ ምንም እንኳን ቀዳሚ ምርመራ የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ ብቻ መዝግቦ ለማቆየት ያለመ ቢሆን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መልኩ ተጠርጣሪውን ይጠቅማል፡፡ ተጠርጣሪውን ጉደዩን አስቀድሞ በማወቅ ለመከላከል እንዲዘጋጅ ይረዳዋል፡፡ ተጠርጣሪው ሊከሰስ የሚችልበትን ወንጀል እና ዐቃቤ ሕግ ሊያቀርባቸው የሚችላቸውን ማስረጃወች ቀድሞ በማወቅ ለመከላከል ይጠቅመዋል፡፡                                                  

ቀዳሚ ምርመራ የሚደረግባቸው ወንጀሎች

ቀዳሚ ምርመራ የሚደረግባቸው ወንጀሎች የጋራ ባህሪያቸው ሁሉም ወንጀሎች በሥረ ነገር ሥልጣን  ደረጃ በከፍተኛው ፍ/ቤት ሆነው ምርመራው የሚካሄደው ግን በዝቅተኛው ፍ/ቤት መሆኑ ነው፡፡ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ቀዳሚ ምርመራን በከፍተኛው ፍርድ ቤት ለሚታዩ ወንጀሎች ላይ ብቻ ተወስኖ እንዲደረግ ያዛል፡፡ ቀዳሚ ምርመራ የሚደረግባቸው ወንጀሎችን በሁለት መክፈል ይቻላል፡፡

ግዴታ ቀዳሚ ምርመራ የሚደረግባቸው ወንጀሎች / አንቀጽ 80 (1)

አንደኛውና የመጀመሪያው የግዴታ የቀዳሚ ምርመራ መደረግ ያለበት የተፈጸሙት ወንጀሎች ከባድ የሰው ግድያ እና ከባድ ውንብድና ወንጀሎች ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ወንጀሎች መፈጸማቸው ሲታወቅ ነገሩ ለከፍተኛው ፍ/ቤት ከመሰማቱ በፊት ቀዳሚ ምርመራ የግድ መደረግ አለበት፡፡ እነዚህ ሁለት ወንጀሎች ተፈጽመው ቀዳሚ ምርመራ ላይደረግበት የሚችለው ብቸኛ ምክንያት ዐቃቤ ሕጉ ነገሩ ወድያውኑ በከፍተኛ ፍ/ቤት መታየት አለበት ብሎ ሲያምን እና ይህን ውሳኔ የከፍተኛው ፍ/ቤት ከተቀበለው የከፍተኛው ፍ/ቤት የቀዳሚ ምርመራው ፍ/ቤት እንዳይቀርብ መወሰን ይችላል፡፡ ከዚህ ምክንያት ውጭ ግን ቀዳሚ ምርመራ ሳይደረግ ጉዳዩ ለከፍተኛ ፍ/ቤት አይደርስም፡፡ ዐቃቤ ሕግ እነዚህን ሁለት ወንጀሎች በተመለከተ ምርጫው አንድ ነው፡፡ ይኸውም ለቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍ/ቤት ምርመራው እዲደረግለት አቤቱታ ማቅረብ፡፡ ዐቃቤ ሕግ በእነዚህ ሁለት ወንጀሎች ላይ ቀዳሚ ምርመራ እንዲደረግ አቤቱታ ማቅረብ ዐቃቤ ሕግ ሀላፊነቱ ነው፡፡

ምንም እንኳን የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 80(1) ላይ ከባድ የሰው ግድያ እና ከባድ ውንብድና ወንጀሎች ሲፈጸሙ ክስ ከመሰማቱ በፊት ቀዳሚ ምርመራ መደረግ እንዳለበት ቢያስቀምጥም የሥነ ሥርዓት ሕጋችን የማይመልሳቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ወንጀሉ ከባድ የሰው ግድያ ወይም ከባድ ውንብድና ሆኖ ዐቃቤ ሕግ ለከፍተኛው ፍ/ቤት ጉዳዩ ወዲያውኑ መታወቅ እንዳለበት ባያሳውቅ እና ቀዳሚ ምርመራ ሳይደረግ ቀርቶ ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶ ቢመጣ ምን ይሆናል ለሚለው ሕጋችን ምንም አይልም፡፡ ውጤቱ ምንም የሚሆን ከሆነ በእነዚህ ወንጀሎች ላይ ቀዳሚ ምርመራ ማድረግ እንደ ግዴታ ማስቀመጡ ፋይዳ ቢስ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተጠርጣሪው በቀዳሚ መርመራ አለመቅረቡን ክሱ በሚሰማበት ጊዜ እንደ መቃወሚያ ቢያቀርብ የፍ/ቤቱ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል ሕጋችን አያመለክትም፡፡

በዐቃቤ ሕግ ውሳኔ ቀዳሚ ምርመራ የሚደረግባቸው ወንጀሎች አንቀጽ 80(2)

በሁለተኛ ደረጃ በዐቃቤ ሕግ ውሳኔ ቀዳሚ ምርመራ የሚደረግባቸው ወንጀሎች ወንጀሎቹ ከከባድ ሰው ግድያ እና ከከባድ ውንብድና ወንጀሎች ውጭ ሆነው በሥረ ነገር ሥልጣን ደረጃ የከፍተኛው ፍ/ቤት ብቻ የሆኑ ወንጀሎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ሁለት ወንጀሎች ውጭ ሆነው በከፍተኛው ፍ/ቤት ሥልጣን ስር በሚገኙ ወንጀሎች ላይ ዐቃቤ ሕግ በአንቀጽ 38(ለ) መሠረት ካላዘዘ በስተቀር ለቀዳሚ ምርመራ ፍ/ቤት መቅረብ የለበትም፡፡ በዓቀቤ ሕግ ውሳኔ ቀዳሚ ምርመራ የሚደረግባቸው ወንጀሎች መፈጸማቸው በታወቀ ጊዜ ቀዳሚ ምርመራ በማድረግ የዐቃቤ ሕግን ውሳኔ መጠበቅ ግዴታ ነው፡፡ የእነዚህ ወንጀሎች የቀዳሚ ምርመራ እጣ ፋንታ የሚወሰነው በዐቃቤ ሕግ እጅ ነው፡፡ ዐቃቤ ሕግ ከወሰነው ምርመራው ይደረጋል፡፡ ካልተወሰነ ምርመራው አይደረግም፡፡ ስለሆነም የከፍተኛው ፍ/ቤት ቀጥታ ክሱን ሊሰማ ይችላል፡፡ ለእነዚህ ወንጀሎች ቀዳሚ ምርመራ ማድረግ ቅድመ ሁኔታ አይደለም፡፡

የቀዳሚ ምርመራ አጀማመር /አንቀጽ 83/

አንቀጽ 83 የሚደነግገው በዐቃቤ ሕግ ውሳኔ ቀዳሚ ምርመራ ስለሚደረግባቸው ወንጀሎች አጀማመር ብቻ ነው፡፡ በግዴታ የቀዳሚ ምርመራ መደረግ ያለባቸውን ወንጀሎች የቀዳሚ ምርመራ አጀማመር በተመለከተ የሥነ ሥርዓት ሕጉ የሚለው ነገር የለም፡፡ በአንቀጽ 80(2) መሠረት ዐቃቤ ሕግ ቀዳሚ ምርመራ መደረግ አለበት ብሎ ከወሰነ የውሳኔውን ግልባጭ ቀዳሚ ምርመራውን ለማድረግ ሥልጣን ላለው ፍ/ቤት ይልካል ይላል፡፡ ስለዚህ ዐቃቤ ሕግ እና ቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍ/ቤት በምርመራው ጉዳይ መግባቢያቸው የዐቃቤ ሕግ ውሳኔ ነው፡፡

የዐቃቤ ሕግ ውሳኔ ይዘቱ ምን መሆን እንዳለበት እና ቅርጹ ምን መምሰል እንዳለበት የሥነ ሥርዓት ሕጉ ድንጋጌ የለውም፡፡ ነገር ግን ውሳኔው በይዘት ደረጃ በትንሹ ወንጀሉ በከፍተኛ ፍ/ቤት የሥረ ነገር ሥልጣን ስር እንደሆነ መግለጽ መቻል አለበት፡፡ ይህንን የመወሰን ሥልጣን የተሰጠው ለዐቃቤ ሕግ ነው፡፡ ወንጀሉን ለማየት ሥልጣን ያለው የከፍተኛ ፍ/ቤት ነው ብሎ ካመነ ቀዳሚ ምርመራ እንዲደረግ ዝቅተኛውን ፍ/ቤት ይጠይቃል፡፡ በውሳኔ ግልባጩ መሠረት ፍ/ቤቱ ምርመራ የሚደረግበትን ቀን ወስኖ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች እንዲቀርቡ ትዛዝ ይሰጣል፡፡

ስለዚህ በሕጉ መንፈስ መሠረት በሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀፅ 88(ለ) መሠረት ዐቃቤ ሕግ ቀዳሚ ምርመራ መደረግ አለበት ብሎ ሲወስን ለቀዳሚ ምርመራ አድራጊው ፍርድ ቤት የሚልከው የዚህን ውሳኔ ግልባጭ ነው፡፡ ዐቃቤ ሕግ መደበኛ የክስ ማመልከቻ ፅፎ መቅረብ የለበትም፡፡ ዐቃቤ ሕግ ይዞ መቅረብ ያለበት ቀዳሚ ምርመራ መደረግ ያለበት መሆኑን የወሰነበትን የውሳኔ ግልባጭ ነው፡፡ በተግባር ግን የሚላከው የክስ ማመልከቻ እንጅ የውሳኔ ግልባጭ አይደለም፡፡ የሥረ ነገር ስልጣኑ የከፍተኛው ፍርድ ቤት በሆነ ወንጀል ላይ ቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት የክስ ማመልከቻ ተቀብሎ ምርመራ ማድረግ ተገቢነት የለውም፡፡ የቀዳሚ ምርመራው ዓላማ ማስረጃን ጠብቆ ማኖር እስከሆነ ድረስ የቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤትም ሆነ ዐቃቤ ሕግ መደበኛ የክስ አመሰራረት እና አከፋፈት ሥነ ሥርዓቶችን መከተል አይጠበቅባቸውም፡፡ በዐቃቤ ሕግ በኩል የሚቀርበው ቀዳሚ ምርመራ ይደረግልን ክስ አይደለም፡፡ ቀዳሚ ምርመራ ክስ ለማዘጋጀት ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ በአንቀፅ 109 መሠረት አንድ የክስ ማመልከቻ ለማዘጋጀት ዐቃቤ ሕጉ የፖሊስ ምርመራ መዝገብ ወይም የቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት መዝገብ ሊደርሰው ይገባል፡፡ ስለሆነም የቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት መዝገብ ለዐቃቤ ሕግ ክስ ለመመሥረት ግብዓት ነው፡፡

የቀዳሚ ምርመራው እንዲደረግበት የተወሰነው ሰው በእርግጥ በምርመራው ደረጃ ላይ እያለ ተከሳሽ ነው ወይ?

የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ በሦስተኛ መጽሐፍ ውስጥ ቀዳሚ ምርመራ እንዲደረግበት የተወሰነበትን ሰው ብዙ ቦታ ላይ ተከሳሽ እያለ ያስቀምጠዋል፡፡ የቀዳሚ ምርመራ ጊዜ ዐቃቤ ሕግ ለመክሰስ ወይም ላለመክሰስ አይወስንም፡፡

በተግባር ለቀዳሚ ምርመራ አዲራጊ ፍ/ቤት የሚቀርበው ማመልከቻ ዐቃቤ ሕግ ከሳሽ እና ምርመራው የሚካሄድበትን ሰው ደግሞ ተከሳሽ በማለት ነው የሚያቀርበው፡፡ በምርመራው  ደረጃ ላይ እያለ ተከሳሽ ሳይሆን ይህ ሰው ተጠርጣሪ ነው፡፡ የወንጀሉን መደበኛ ከስ ለማቅረብ የሚችለው ዐቃቤ ሕግ ነገሩን ለመስማት ለሚችለው ፍ/ቤት ቀርቦ ፍ/ቤቱ የክሱን ግልባጭ እስኪልክለት ድረስ ይህንን ሰው ተከሳሽ ብሎ መፈረጅ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ምርመራው እንዲደረግ የተወሰነበት ሰው ምርመራው ደረጃ ላይ እያለ ፍ/ቤት የሚቀርበው ተከስሶ ሳይሆን ከመከሰሱ በፊት ለምርመራ ነው፡፡

የቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍ/ቤት ሥልጣንና ተግባራት

የቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት የሚጠቀምበት በምርመራው ወቅት የቀረበውን የተሰማውን ማስረጃ የማሥረዳት አቅሙ ምንም ይሁን ምን ክሱን መስማት ለሚችለው ለከፍተኛው ፍ/ቤት መላክ ነው፡፡ ዐቃቤ ሕግ የቀዳሚ ምርመራው እንዲደረግ ለፍ/ቤት ሲያቀርብ ፍ/ቤቱ ምርመራው የሚፈጸምበትን ቀን በመወሰን ተጠርጣሪው የዐቃቤ ሕግ እና የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች በቀጠሮው ቀን እንዲቀርቡ ትእዛዝ ይሰጣል፡፡ ምንም ያህል የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ በቂ ባይሆን በእኛ ሀገር ቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍ/ቤት ተከሳሽን በነፃ ለመልቀቅ አይችልም (አንቀጽ85/2/)፡፡

ረቂቁ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ የቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍ/ቤት ሥልጣንን ዘርዝሮ በማስቀመጥ የምርመራ አድራጊ ፍ/ቤቱን ሥልጣን አስፍቶታል፡፡ (ይህንን መጋቢት 30 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀረበው ረቂቅ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ከአንቀጽ 177 እስከ 187 ተመልከት)

የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ አላላክ /አንቀጽ 91/

ቀዳሚ ምርመራ አድራጊው ፍ/ቤት ምርመራውን ሲያጠናቅቅ ነገሩ እንዲሰማ መዝገቡን ለከፍተኛው ፍ/ቤት መላክ አለበት፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጉ በዚህ ረገድ ግልጽ ቢሆንም በተግባር ግን ክፍተቶች አሉ፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀፅ 91 የምርመራው መዝገብ እንደት ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት እንደሚላክ የሚያትት አንቀፅ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ነገሩ በከፍተኛው ፍ/ቤት ለመሰማት የምርመራው ዋናው መዝገብ ሊደርሰው ይገባል፡፡ የምርመራ መዝገቡን ደግሞ ሊያገኝ የሚችለው የቀዳሚ ምርመራ አዲራጊው ፍ/ቤት መዝገብ ቤት እና የከፍተኛው ፍ/ቤት መዝገብ ቤት በሚያደርጉት ግንኙነት ነው፡፡ ምርመራው ከተጠናቀቀ በኋላ አንድ መዝገብ ከዳኛው እጅ ወጥቶ የሚቀመጠው በመዝገብ ቤት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ ግን የሚቀመጠው ምርመራውን ባደረገው ፍ/ቤት መዝገብ ቤት ሳይሆን በከፍተኛው ፍ/ቤት መዝገብ ቤት ነው፡፡

የምርመራ አድራጊ ፍ/ቤት መዝገብ ቤት ዋናውን መዝገብ እና ለፍርድ ቤት የሚቀርብ ማንኛውም መረጃ  ለከፍተኛው ፍ/ቤት መዝገብ ቤት ይልካል (አንቀፅ 91(1))፡፡ በተግባር እየተሰራ ያለው ግን በሕጉ መሠረት ነው ወይ ቢባል መልሱ አሉታዊ ነው፡፡ የምርመራው ዋናው መዝገብ ራሱ የምርመራ አድራጊው ፍርድ ቤት ንብረት አይደለም፡፡ አንድ ከዋናው መዝገብ ጋር ሌሎች ማንኛውም ዓይነት ፍርድ ቤት ሊቀርቡ የሚችሉ መረጃወች ይላካሉ፡፡ ሆኖም ግን በማንኛውም ዓይነት ምክንያት ለመላክ አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ ስለ መረጃዎቹ የሚገልፅ ዝርዝር በመላክ መረጃዎቹ በፖሊስ እጅ እንዲቆይ ማድረግ ይቻላል፡፡ የምርመራ መዝገቡ ሲላክ ከመዝገቡ በተጨማሪ መዝገቡ ስለያዛቸው ነገሮች ሊያብራራ የሚችል ዝርዝር አብሮ ይላካል፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀፅ 92(1) የዝርዝሩ ይዘት ምን መሆን እንዳለበት ዘርዝሮ አስቀምጧል፡፡

እንግድህ በዚህ መልኩ ዋናው መዝገብ እና ሌሎች መረጃዎች የደረሱት የከፍተኛው ፍ/ቤት መዝገብ ቤት ለዐቃቤ ሕግ እና ለተጠርጣሪው ሰው ገልብጦ መስጠት ሀላፊነት እንዳለበት አንቀፅ 91(3) በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ከዚህ በቀላሉ መረዳት የሚቻለው ዐቃቤ ሕግም ሆነ ተጠርጣሪው ሰው የምርመራውን መዝገብ የተመለከተ ማንኛውም ዓይነት ተገልብጦ ሊሰጣቸው የሚችል ማስረጃ ሊጠይቁት የሚገባው የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ነው፡፡ የምርመራ አድራጊው ፍርድ ቤት ዋናው መዝገብ እና ሌሎች መረጃዎች ከእነ ዝርዝር መግለጫቸው ከመላክ ያለፈ ሀላፊነት የለበትም፡፡ የምርመራ መዝገቡ ንብረትነት የምርመራ አድራጊው ፍርድ ቤት እስካልሆነ ድረስ ማንኛውም ዓይነት ማስረጃ ገልብጦ መስጠት አይጠበቅበትም፡፡ አላላኩን በተመለከተ በተግባር የምርመራው መዝገብ ተገልብጦ እንዲሰጠው ዐቃቤ ሕግ ምርመራ አድራጊውን ፍርድ ቤት ይጠይቃል ተገልብጦ ይሰጠዋል፡፡ ፖሊስ ደግሞ የምርመራ መዝገቡን ግልባጭ እና ሌሎች ማስረጃዎችን ለዐቃቤ ሕግ ይልካል፡፡ የምርመራው ዋናው መዝገብ በምርመራ አድራጊው ፍ/ቤት መዝገብ ቤት ተቀምጦ ይቀራል፡፡

ማጠቃለያ

ቀዳሚ ምርመራን የተመለከቱ ድንጋጌዎች ተቀርጸው በሥነ ሥርዓት ሕጉ ውስጥ የተካተቱ ቢሆንም ባለሙያዎች ብዙ ጊዜ ተግባር ላይ ስለማያውሏቸው አልፎ አልፎ በሚመጡ መዝገቦች ላይ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ድንጋጌዎች ሲገደፉ ይታያሉ፡፡

ቀዳሚ ምርመራን በተመለከተ ከሕጉ ይልቅ ልማድ የጎላበት ነው፡፡ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ አሠራር በሕጉ አግባብ ሊታረቅ ይገባል፡፡ የአሠራሩ ምንጭ ከልማድ ያለፈ ሕጋዊ መሠረት የለውም፡፡ ሕጉ በማያሻማ አኳኋን ተቀምጦ ባለበት ሁኔታ በተንጋደደ መልኩ መሥራት የሁሉም ባለሙያ ማለትም የዐቃቤ ሕግ፤ የፖሊስ እና የዳኛው ሃላፊነት ውድቀት ነው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የሰበር ፍርድ ያለማክበር ልማድና ውጤቱ
ዳኞች፣ ዐቃቤ ሕጎች፣ ጠበቆች እና ፖሊሶች ሊዘነጓቸው የማይገቡ የወንጀል ሥነ ሥ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024