የኮንስትራክሽን መብቶች (Claims) ምንነት እና የሚስተዋሉ ችግሮች
ማንኛውም ሰው በማህበራዊ ኑሮ ውስጥ በሚገጥመው መስተጋብር የተለያዩ ጥያቄዎች ወይም መብቶች (Claims) ሊኖረው ይችላል፡፡ ከዚህ ንድፈ ሃሳብ በመነሳት ታዲያ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውም በርካታ የመብት ጥያቄዎች መነሳታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው! እንደሚታወቀው የግንባታ ዘርፍ ብዙ ባለድርሻ አካላትን ማሳተፋ ብቻ ሳይሆን የሚገርመው በተለያየ ሙያ ያሉ ሰዎች መሳተፋቸውም ጭምር ነው፡፡ ይህም በመሆኑም በርካታ የመብት ጥያቄዎች መነሳታቸው የግድ ነው፡፡ ከዚህ ብሂል በመነሳት አንዳንዶች ከውል በመነጨ ጉዳይ የውል የመብት ጥያቄ ሲያነሱ ሌሎች ደግሞ ሕጉ አስቀድሞ ባስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ መሠረት ውል ሳይኖር አላፊነት በመኖሩ ምክንያት መብታቸውን ከውል ውጭ ሲጠይቁ ይስታዋላል፡፡
ምናልባት በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ለሚነሱ አለመግባባቶች እና ቁርሾዎች እንደ ምክንያትነት የሚነሣው የመብቶች ጥያቄ ጉዳይ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ቅድሚያውንም የሚወስዱት በተለይም ከሥራ ርክክብ መዘግይት እንዲሁም ከውል መለወጥ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በሃገራችንም ምንም እንኳን ልማዱ በዓለም አቀፍ ሥራ ተቋራጮች በርከት ቢልም ቅሉ፤ የሃገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮችም ቢሆን አሁን አሁን የተለያዩ የኮንስትራክሽን የመብት ጥያቄዎች ሲያስተጋቡ ይስተዋላል፡፡
በዋናነትም ለነዚህ የኮንስትራክሽን መብት ጥያቄዎች መበራክት እንደ መነሻነት የሚቆጠሩት አንድም የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ውስብስብነት፣ የክፍያ መጠኑ ከፍተኛ መሆን እንዲሁም አሁን አሁን ሥራ ተቋራጮችም ሆነ ባለቤቶች ወደ ክስ እና ሙግት ሥነ ሥርዓት ልማድ ማድረግ እንደ ምክንያትነት ይወሰዳሉ፡፡
በመጨረሻም አቅራቢው በዚህ አጭር ጽሑፍ የኮንስትራክሽን መብት ጥያቄዎችን ምንነት ብሎም ፍረጃ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፍ/ቤቶች ልማድ በሚከተሉት ክፍሎች በአጭሩ ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡
1. የኮንስትራክሽን መብቶች ምንነት
የኮንስትራክሽን መብቶች ከተለያየ ምንጮች ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ከውል፣ ከውል ውጪ እንዲሁም ከሕግ ሊመነጩ ይችላሉ፡፡ በነገራችን ላይ የመብት ጥያቄ (Claim) ማለት ምን ማለት ነው?
Black’s law dictionary 9th edition የሚከተለውን ትርጉም ሰጥቶት እናገኛለን፡፡ “claim is the aggregate of operative facts giving rise to a right enforceable by a court.” የመብት ጥያቄ ማለት በፍርድ ቤት ሊፈጸም የሚችል በፍሬ ነገሮች የተደገፈ መብት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ቪሰንት ስሚዝ የተባሉ ምሁር (civil Engineering Claims,1989) በሚለው መጽሐፋቸው የመብት ጥያቄ (Claim) የሚለውን ቃል እንደሚከተለው አብራርተውታል፡-
[C]laims are a general term for the assertion of a right to money, property or a remedy… [Sic] In relation to construction industry, claims means, a demand by a contractor for extension of time or for an extra payment of an item of work carried out by him on behalf of the employer for which a readily identifiab መሠረት ባለእዳው ውል ካልተፈጸመለት ሦስት መፍትሔዎች አሉት፡፡ /የፍ/ሕ/ቁ አንቀጽ 1771 ይመለከተዋል/
1) ውሉን በግድ ስለማስፈጸም /Forced Perfle amount cannot be ascertained under the term of contract.”
እንደ ስሚዝ ገለጻ ከሆነ የመብት ጥያቄ የሚባለው ባጠቃላይ የገንዘብ፣ የንብረት እንዲሁም የካሳ ጥያቄ የሚስተናገድበት ሥርዓት መሆኑን ከገለጸ በኋላ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውም ሥራ ተቋራጩ አሰሪውን ለተጨማሪ ሥራው ተጨማሪ ገንዘብ እንዲሁም ጊዜ እንዲጨመርለት የሚጠይቅበት መንገድ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡
ከላይ ለመግለትጽ እንደሞከርነው የመብት ጥያቄ የሚባለው አንድ ሕጋዊ የሆነን ነገር የምንጠይቅበት ሥርዓት መሆኑን አይተናል፡፡ እንደ ሲርስ ክላፍ (2008) እይታ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ የኮንስትራክሽን የመብት ጥያቄዎች የሚነሱት ከመጠን በላይ ያልተጠበቀ ወጪ ሲያጋጥም፣ ሥራው ያለአግባብ ሲሰራ፣ የሕጉ መወሳሰብ (legal entanglement) እንዲሁም የተለያዩ ሥራ ተቋራጮች አሉታዊ እንቅስቃሴዎችን እንደ ምክንያትነት ያነሳሉ፡፡ የሚገርመው ነገር አልፎ አልፎ የመብት ጥያቄዎች በባለሃብቶች እና ማህንዲሶች ዘንድ በአይነ ቁራኛነት ሲስተዋል እናያለን ለምን ቢባል ይህ መንገድ አብዛኛውን ጊዜ የሥራ ተቋራጮች በመብት ጥያቄ ሽፋን አስቀድመው ያላነሷቸውን መብቶች ወይም ስህተቶች መሸፈኛ ስትራቴጂ ስለሆነ ጭምር ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የግንዛቤ እጥረት እንጅ እንደ ትክክለኛ አመክንዮ አይወሰድም ለምን ቢባል እንደሚታወቀው የመብት ጥያቄ የኮንስትራክሽን ሂደት አንኳር አካል ከመሆኑ በላይ ጥሩ የሚባል የመብት ጥያቄ እና የግጭት አፈታት ሥርዓት መኖር ለጥሩ ምህንድስና ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው ንግድም ሰናይ ነው፡፡
የኮንስትራክሽን መብት ጥያቄ (Claim) በምን ምክንያት ሊነሳ ይችላል፡፡ በዚህ ጹሑፍ አቅራቢ እምነት የሚከተሉት መነሻዎች በመላ ምትነት አቀርባለሁ፡-
ሀ) አንድም የኮንስትራክሽን ውል በአሰሪውና በራሱ ደቀ መዛሙርት (የአሰሪው ወኪሎች) በፍጥነት ሲዘጋጅ ብዙ ጉዳዮችን በማወቅም (intentional) ይሁን ባለማወቅ (negligence) ሊተውት ይችላሉ፡፡
ለ) ሁለትም አሰሪዎችም በገቡት ውለታ መሠረት ላይገኙ እና ግዴታቸውንም ላይወጡ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ከላይ የተሰነዘሩት መላምቶች ምንያህል እውነት ናቸው የሚለውን በሚቀጥሉት ንዑሳን ርዕሶች እናያለን፡፡
2. የኮንስትራክሽን መብቶች ጥያቄ ፍረጃ (Construction Claim’s Classification)
የተለያዩ የሕግ፣ የኮንስትራክሽን ሥራ አመራር እንዲሁም የሲቪል ምህንድስና ድርሳናት እንደሚጠቁሙት ከሆነ የኮንስትራክሽን መብት ጥያቄን በአምስት ዘርፍ ይፈርጇችዋል፡፡ እነዚህም ከውል የሚመነጩ መብቶች /Contractual claims/፣ ከውል ውጭ የሚመነጩ መብቶች /Tort claims/፣ ተገቢ መብቶች /Quantum Meruit claims/፣ የርህራሄ መብት ጥያቄዎች /Ex-gratia Claims/ እና የአጸፋ መብት ጥያቄ /Counter claims/ ናቸው፡፡
ስለ እያንዳንዱ ዓይነት የመብት ጥያቄ ምንነት በአጭሩ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ሀ) ከውል የሚመነጩ መብቶች/Contractual claims/ ፡-አብዛኛውን ጊዜ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ለሚነሱ የመብት ጥያቄዎች የአንበሳውን ድርሻ (lion’s share) የሚወስዱት ከውል ሚመነጩ የመብት ጥያቄዎች ናቸው፡፡
ለመሆኑ ከውል የሚመነጩ መብቶች እንዴት ይፈጠራሉ? በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪም የውሎች መጣስ አንድም ከሥራ ተቋራጩ በኩል ወይም ደግሞ ከአሰሪው ወገን ሊመጣ ይችላል፡፡ ለአብነት ያህልም ሥራ ተቋራጩ አስፈላጊ ግብአቶችን ሳያሟል ጨረታውን አሸንፎ ወደ ሥራ ቢገባና በተፈለገው ጊዜ አለማጠናቀቁ፤በሌላ በኩል አሰሪውም በውሉ በተመለከተው ጊዜ የመስሪያ ቦታውን አለማስረከቡ እና መሰል ችግሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግም ስለውል በጠቅላላው ከአንቀጽ 1675-2026 ድረስ እንደተመለከተው አንድ ባለመብት ባለዳውን በውል የተቀመጡ ግዴታወች ካልፈጸመለት ውል እንዲፈጸምለት፣ ውሉን እስከመሰረዝ አልፎ ተርፎም ካሳ መጠየቅ ይችላል፡፡
በፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 1731 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው በህጋዊ መንገድ በተዋዋዮች ዘንድ የተመሰረተ ውል ሕግ ነው፡፡ ይህም ሰው በቃሉ ይታሰራል ከሚለው ዓለም አቀፍ መርሆ/”Pacta sunt servanda”/(አንቀጽ 26 የቬና የሥምምነቶች ሕግ ስምምነት ተመልክቷል) የመጣ ከመሆኑም በላይ ተዋዋዮች ውላቸውን የሕጉን ገደብ ሳያልፋ ከተዋዋሉ የሚያስገድዳቸው መሆኑን ጭምር ያስገነዝበናል፡፡ ስለዚህ በኮንስትራክሽን ውልም ውል ሰጭው ባለቤት(አሰሪው) እና ሥራ ተቋራጩ(ኮንትራክተሩ) የሚያደርጉት ውል በፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 1731 መሠረት ገዢ እና የተዋዋዮች ሕግ ነው፡፡ በኮንስትራክሽን ውልም አጠቃላይ የውል ሥምምነቶች (General conditions of contract)፣ ልዩ የውል ሥምምነቶች (Special conditions of contract) እንዲሁም ሌሎች የማሻሻያ ውሎች ሊስማሙ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም የመብት ጥያቄን ጨምሮ አለመግባባት ቢነሳ ለተዋዋይ ወገኖች ውሎች ቀድሚያ ይሰጣል፡፡
የኮንስተራክሽን ውል ልዩ ውል ቢሆንም በፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 1676 በተመለከተው መሠረት የፍትሐብሔር ውል ሕግ ድንጋጌወች ተፈጻሚነታቸው እሙን ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ታዲያ አንድ ሥራ ተቋራጭ የመብት ጥያቄ (Claims) ቢያነሳ ወደ ውል ይፈጸምልን ድንጋጌወች በማምራት ከአንቀጽ 1740-1762 የውል አፈጻጸሙን መጠየቅ ይቻላል፡፡
ምንግዜም የመብት ጥያቄ ሲነሳ መብት ጠያቂወች መዘንጋት የሌለባቸው ነገር መጀመሪያውኑ ውል በሚመሰርቱበት ወቅት የገቡበትን ወጥ ውል መሠረት ማድረግ አለባቸው፡፡ ለምሳሌ በFIDIC፣ World Bank standard conditions of contract ወይም በሥራ እና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወጥ ውል መሠረት ሊዋዋሉ ይችላሉ ዳሩ ግን የመብት ጥያቄ (Claims) ሲያነሱ የተዋዋልነው በየትኛው ወጥ ውል ነው ሚለውን ጥያቄ ግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል ተዋዋይ ወገኖች ወደ ውሉ ዝም ብለው ቢያመሩ እንዲሁም የሚገዙበትን ሕግ ካላመለከቱ የፍትሐብሔር ሕግ ድንጋጌወች እንደ ክፍተት ማሙያነት (default-gap filling role) ያገለግላል፡፡
በኢትዮጵያ ፍትሐብሔር ሕግ ስለውል በጠቅላላው አንደተመለከተው ባለመብቱ በውሉormance/
2) ውሉን የመሰረዝ /Cancellation/
3) የጉዳት ካሳ መጠየቅ /Damages or compensation/
እዚህ ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነጥብ ከውል የሚመነጩ የመብት ጥያቄዎች (Claims) በይርጋ (ይርጋ፡ማለት ጊዜ በማለፋ መብት ቀሪ የሚሆንበት ሥርዓት ነው፡፡) ይታገዳሉ ወይ የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ነው፡፡ ይህም በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 1845 በግልጽ እንዳስቀመጠው ከውል ይፈጸምልኝ ጋር የተያያዙ የመብት ጥያቄዎች በአስር(10) አመት ውስጥ ካልተነሱ በይርጋ እንደሚታገዱ መረዳት ይቻላል፡፡
ለ) ከውል ውጭ የሚመነጩ መብቶች/Tort claims/፡- ይህ ዓይነቱ የመብት ጥያቄ ደግሞ የሚመነጨው ከውል ውጭ ኃላፊነት በመኖሩ ነው፡፡ ይህም አስቀድሞ ሕጉ ባስቀመጣቸው ምክንያቶች እንዲሁም አንድን ድርጊት ጥፋት ነው ብሎ በመፈረጁ እንደሆነ ወይም ጥፋት ሳይኖርም አላፊነት ሊኖር እንደሚችል መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ከውል ውጭ አላፊነት በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 2027 ላይ እንደተመለከተው ከሦስት ምንጮች ሊመጣ ይችላል፡፡
i. በጥፋት ላይ የተመሠረት አላፊነት (የፍ/ሕ/ ከአንቀጽ 2028-2065)፡- ይህም የሚሆነው አንድ ሰው በሌላ ሰው አካል ወይም ንብረት ላይ ሆን ብሎ (intentional) ወይም በቸልተኝነት (negligence) ጉዳት ካደረሰ ኃላፊነት አለበት፡፡ (የፍ/ሕ/ አንቀጽ 2029)ለምሳሌ አንድ ሥራ ተቋራጭ ህንጻውን በሚገነባበት ወቅት የሌላን ሰው ንበረት ለግንባታ ግባኣትነት ቢጠቀም (በፍ/ሕ/ቁ 2054) መሠረት ከውል ውጭ አላፊ ይሆናል፡፡ ይህ በመሆኑም የንብረቱ ባለመብት የሆኑ ሰዎች ከውል ውጭ የመብት ጥያቄ (Tort claims) ሊያነሱ ይችላሉ፡፡
ii. ጥፋት ሳይኖር አላፊ መሆን (የፍ/ሕ/ ከአንቀጽ 2066-2089)፡- ይህ ደግሞ ሕጉ አስቀድሞ የህብረተሰቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል ምንም እንኳን በጉዳዩ ባለቤት ዘንድ ጥፋት ባይኖርም ጥፋት ብሎ የሰየማቸው ድርጊቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያንድ ሕንጻ ባለቤት ወይም ባለይዞታ ሕንጻው ያደርሳል ተብሎ ያልታሰበ ድንገተኛ ነገር ቢያደርስም ይህ ሕንጻ በሚያደርሰው ጉዳት አላፊ ነው፡፡ (ፍ/ሕ/ቁ/2077 ተመልክቷል፡፡ )
iii. ለሦስተኛ ወገን አላፊ በመሆን (የፍ/ሕ/ ከአንቀጽ 2124-2136)፡- የዚህ ዓይነቱ አላፊነት ደግሞ ሌሎች ለፈጸሙት ድርጊት ተጠያቂነት የሚያስከትል (Vicarious liability) ነው፡፡ አንድ ድርጅት የቅጥር ውል ፈጽመው በስሩ ለሚሰሩ ሰራተኞች ተጠያቂነት ሊኖርበት ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ልክ በፍ/ሕ/ቁ 2134 እንደተመለከተው ሙሉ ኃላፊነት ወስደው የሚሰሩ ሰራተኞች ለሚያደርሱት ግን አሰሪው ተጠያቂነት የለበትም፡፡ ለምሳሌ አንድ ኮንትራክተር የተለያየ ሥራ ለማሰራት በማሰብ በራሳቸው የስራ መሪነት የሚሰሩ ሰራተኞች ቢቀጥር እና ጥፋት ቢያደርሱ ተጠያቂነት የለበትም፡፡
ሐ) ተገቢ መብቶች /Quantum Meruit claims/፡- እንደሚታወቀው የኮንስትራክሽን ውል በአፈጻጸም ወቅት ያለተገመተ ነገር ሊያስከትል ይችላል፡፡ በዚሁ ምክንያት ሥራ ተቋራጩ ያልገመተው ኪሳራም ጭምር ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ ተገቢ የሚባለው የመብት ጥያቄ የሚነሳው ሥራ ተቋራጩ ፕሮጀክቱን አሸንፎ ወደ ስራ ከገባ በኋላ በውሉ መሠረት እንዳይፈጽም ችግር ቢገጥመውና አሰሪውም ችግሩን ከግምት አስገብቶ ተመጣጣኝ እና ሚዛናዊ ማስተካከያ ቢደርግለት የዚህ አይነቱ ጥያቄ ከዚህ ዘርፍ ይመደባል፡፡ ይህም አሰራር ከላቲኑ “quantum meruit’ ትርጓሜውም “what one has earned/reasonable value of service/ እንደ ማለት ነው፡፡ አንዳንዴም የዚህ ዓይነቱ የመብት ጥያቄ ተዋዋይ ወገኖች ስለዋጋ እና ተያያዥ ጉዳዮች የለየለት ስምምነት ሳያደርጉ ቢቀሩ እና አሰሪው ለኮንትራክተሩ የሚገባውን ክፍያ ሊፈጽም ይችላል፡፡
በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግ በተለይም አንቀጽ 3032(1) ላይ አንደተቀመጠው ተቋራጩ ከሚሠራው ሥራ እንዲቀነስ በአሠሪው ተጠይቆ ከሠራና የሥራ ለውጡ የተቋራጩን ወጪ ከቀነሠለት በውሉ ተወስኖ ከነበረው ዋጋ ላይ እንዲቀነስለት አሠሪው ተቋራጩን ለመጠየቅ ይችላል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አሠሪው በጠየቀው የሥራ መለዋወጥ ምክንያት የሥራ ተቋራጩን ወጪ የሚያበዛ ወይም ተጨማሪ ሥራ የሚያስከትል ወይም አላፊነቱን የሚያከብድበት ከሆነ ለተጨማሪው ሥራ ዋጋውና የሚከፈለው አበል ተጨምሮ እንዲከፈለው አሠሪውን ለመጠየቅ ይችላል፡፡ ከድንጋጌው የምንረዳው የሥራ ለውጥ በሚኖርበት ወቅት አስፈላጊ እና ተገቢ መብቶች /quantum meruit/ በኮንትራክተሩ ወይም አሰሪው እንደሁኔታው ሊነሳ ይችላል፡፡
መ) የርህራሄ መብት ጥያቄዎች /Ex-gratia Claims፡-የዚህ ዓይነቱ የመብት ጥያቄ ደግሞ ከሰብዓዊነት ወይም ከርህራሄ ይመነጫሉ፡፡ ለዚህም ነው አንድ ሰው ምንም ዓይነት የሕግ አላፊነት ሳይኖርበት ለሌላው ወገን በችሮታ ክፍያ የሚሰጠው በተለይም ባለእዳው ባለመብቱ ከባድ ችግር ተጋርጧል/facing hardships/ ብሎ የሚያስብ ከሆነ ነው፡፡
ስለሆነም ሥራ ተቋራጩ ይህን ዓይነት የመብት ጥያቄ ሲያነሳ ለከባድ ችግር መዳረጉን ማስረዳት ይኖርበታል፡፡
ሠ) የአጸፋ መብት ጥያቄ /Counter claims ፡- የአጸፋ መብት የሚባለው ደግሞ ባለመብቱ አንድ መብቱን አንስቶ በሚጠይቅበት ወቅት ባለእዳውም በአጸፋው ሌላ የመብት ጥያቄ ቢያነሳበት የዚህን ጊዜ ጉዳዩ ይነሳል፡፡
በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግም ስለማቻቻል (set-off) የተቀመጡት ድንጋጌወች አላማቸው የአጻፋ መብትን ለማሳካት ይመስላል፡፡ /የፍ/ብ/ሕ ቁ 1831/ ዳሩ ግን ስለ ማቻቻል(set-off) የተቀመጡት ድንጋጌወች ሁኔታ ከአጸፋ መብት (Counter claim) ጋር በይዘትም ሆነ በምንነት ይለያያሉ፡፡
በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪም የዚህ አይነት የመብት ጥያቄ እየተሰራበት ያለ አካሄድ ነው፡፡ ለምሳሌ ሥራ ተቋራጩ ያለተከፈለውን ውዝፍ ክፍያ ሲጠይቀው በለሃብቱ (አሰሪው) በአጻፋው የአጸፋ መብት (Counter claim) በመጠቀም የሥራውን ማሻሻያ ቅናሽ ክፍያ እንዲከፍለው ሊጠይቀው ይችላል፡፡
በመጨረሻም የአጸፋ መብት (Counter claim) በሥነ ሥርዓት ህጎቻችንም የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ በፍትሐብሔር ሥነ ስርዓት ሕግ አንቀጽ 30 በግልጽ እንደተመለከተው አንድ ከሳሽ ክስ በሚያቀርብበት ወቅት ተከሳሹ የተከሳሽ ከሳሽነት (Counter claim) ማንሳት እንደሚችል መረዳት ይቻላል፡፡
3. ከመዘግየት የሚመነጩ የኮንስትራክሽን የመብት ጥያቄዎች
በዚህ ክፍል ውስጥ የምንመለከተው ደግሞ ከመዘግየት (delay) የሚመነጩ የመብት ጥያቄዎች ምን፣ ማን እና እንዴት ሊነሱ እንደሚችሉ እንዲሁም አስቀድሞ ችግሮችን ለይቶ ከጉዳዩ ጋር ተያያዘ በተቻለመጠን የመፍትሄ አቅጣጫ ይጠቁማል፡፡ እንደሚታወቀው የኮንስትራክሽን የመብት ጥያቄዎች በተለያየ ምክንያት ሊነሱ ይችላሉ፡፡ እነዚህንም መንስኤዎች ነቅሶ ማውጣት እና መለየት አንዱ ከመብት ጥያቄ ጋር የሚነሱ ችግሮችን መላ ለማበጀት ወሳኝ ነው፡፡
በጠቅላላው ግን የኮንስትራክሽን የመብት ጥያቄ ከሚከተሉት ምክንያቶች ሊመነጭ ይችላል፡-
- የግንባታው ሄደት መዘግየት (delay) እና ውሉ በጊዜው አለመፈጸሙ፣
- የግንባታው በቂ ግብአት አለመሟላት
- የመደበኛው አየር ጠባይ መዛባት
- በባለቤቱ ጠያቂነት ወይም በሥራ ተቋራጩ የሚደረጉ ተደጋጋሚ ለውጦች
- የግንባታ ሳይቱ ደካማ ሥራ አመራር መኖር እና ቁጥጥር ማነስ
- ሥራው ለመጸም አዳጋች መሆን
- በቂ ያልሆኑ የግንባታ ፕላኖች እና መገለጫወች
- በግንባታ ሂደት ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች አስፈላጊ የሆኑ መረጃወችን በወቅቱ አለመግለጽ
- በኮንስትራክሽን ፕሮጀክት አፈጻጸም ወቅት የሚነሱ ግጭቶች
- የግንባታ ውሉ ባንደኛው ወገን መቋረጡ
- ሥራው እንደ ጨረቃ ቤት አሰራር በጣም ፈጣን ሲሆን
- ሥራውን በእቅድ እና በቅንጅት አለመሄድ እና
- እንዲሁም ተዋዋዮች በትብብር እና በህብረት አለመምራት ናቸው፡፡
የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት በሚፈጸምበት ወቅት ለሚነሱ የተለያዩ መዘግየቶች (delays) እና ክርክሮች የሚነሱ ሁለት ፍልስፍናዊ (Construction jurisprudence) አስተሳሰቦች አሉ፡፡ እነዚህም፡-The Concept of Float/ የማረጋጋት ጽንሰ ሃሳብ እና The Concept of Acceleration/ የማፍጠን ጽንሰ ሃሳብ ናቸው፡፡
I. The Concept of Float/የማረጋጋት ጽንሰ ሃሳብ፡- በዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሠረትም ኮንትራክተሩ በፕሮጀክቱ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዳይጨርስ የሚደርገው የሚያረጋጋ ጊዜ/ slack time/ መኖሩ ነው፡፡ ዳሩ ግን ይህ በሚሆንበት ጊዜ የግንባታ ሂደቱ ረጋ ብሎ በመቆየቱ የተነሳ መዘግየት ይከሰታል፤ በዚህም የተነሳ ኮንትራክተሩ ለሚነሱ የመብት ጥያቄዎች አላፊነት አለበት፡፡
ባሪ ብራምብል (2000፡10) የተባሉ የዘርፋ ጸሀፊ የማረጋጋት ጽንሰ ሃሳብን እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡-
[C]onsequently, float time allows a construction project to absorb some delays in the construction schedule. However, when the float is used up, the work at issue returns to the critical path, and the delay which was absorbed by the float may result in construction claims and the need for one party to compensate another for any resulting costs associated with the delay.”
በመጨረሻም የማረጋጋት ጽንሰ ሃሳብ በሚተገበርበት ወቅት ሥራ ተቋራጩ አስቀድሞ ፕሮጀክቱ የሚዘገይበት ጊዜ እንዲሁም ጥቅምና ጉዳት (costs/benefits analysis) ማስላት አለበት፡፡ ምክንያቱም በጣም የተጋነነ የእፎይታ ጊዜ ሥራ ተቋራጩን የበለጠ ወጪ ያስወጣዋል፡፡
II. የማፍጠን ጽንሰ ሃሳብ/The Concept of Acceleration/፡-ይህ ጽንሰ ሃሳብ የሚያስገነዝበው ደግሞ ኮንትራክተሩ ወይ በቀጥታ በራሱ አነሳሽነት ከግንባታ የጊዜ ሰሌዳው በፊት ሥራውን ቢያጠናቅቅ ወይም በአሰሪው (ባለቤቱ) ጉትጎታ እና ትእዛዝ የፕሮጀክቱን ሥራ ከታቀደው ጊዜ በፊት ቀድሞ ቢያጠናቅቅ የማፋጠን ጽንሰ ሃሳብ የሚነሳ ይህን ጊዜ ነው፡፡
በተለየም በባለቤቱ ትእዛዝ የግንባታ ሥራውን ፍጥነት በሚያከናውንበት ወቅት ሥራ ተቋራጩ ግዴታውን ሊየከብድበት ይችላል፡፡ ለምሳሌ ተጨማሪ ሰራተኛ ሊቀጥር ይችላል፣ ትርፍ ሰዓት ሊሰራ ይችላል (work overtime)፣ ተጨማሪ ምክር እና ግብኣት ሊጠይቀው ይችላል፡፡
በመጨረሻም ሥራ ተቋራጩ በባለቤቱ ትእዛዝ ሥራውን በፍጥነት ለመጨረስ ሲል ለሚደርስበት ጉዳት የመብት ጥያቄ (acceleration claim) ማንሳት ይቸላል፡፡
በኮንስትራክሽን አፈጻጸም ወቅት አንድ ግንባታ ዘገየ (delayed) የሚባለው መቼ ነው?
የኮንስጥራክሽን ግንባታ ዘገየ የሚባለው አንድም በታሰበው የጊዜ ልክ እንዲሁም በውሉ በተቀመጠው መሠረት የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል አለመጠናቀቁ አሊያም በቀደመው የጊዜ ስሌት ላይ በውል ከተቀመጠውን የሥራ መጠን በላይ ሥራ እንዲሰራ እቅድ መምጣቱ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት መዘግየት በተለያየ ምክንያት ቢነሳም በዋናነት ግን ከመዘግየት የሚመነጩ ምክንያቶች እንደሚከተለው ይከፈላሉ፡፡
በዚህም መሠረት የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት መዘግየትን በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ አነዚህም ከተዋዋይ ወገኖች ውጭ በሚደርስ መዘግየት፣ በባለቤቱ ምክንያት የሚደርስ መዘግየት እና በሥራ ተቋራጩ ምክንያት የሚደርስ መዘግየት ናቸው፡፡
ሀ) ከተዋዋይ ወገኞች ውጪ የሚደርስ መዘግየት፡- የዚህ ዓይነት መዘግየት የሚፈጠረው ከተዋዋይ ወገኖች ማለትም ከባለቤቱ እና ሥራ ተቋራጩ ቁጥጥር ውጪ ወይ በሦስተኛ ወገኖች እንቅስቃሴ አሊያም በተፈጥሮ አደጋ ሊሆን ይችላል፡፡
መዘግየቱ ተፈጠረው ከተዋዋይ ወገኖች ውጪ ሲሆን ጊዜ መራዘሙ (excusable delay) የታመነ ነው፡፡ ምክንያቱም ሥራ ተቋራጩን ወይም ባለቤቱን የእፎይታ ጊዜ ስለሚሰጣቸው ነው፡፡ ለመሆኑ በተዋዋይ ወገኖች ውጪ የሚደርስ መዘገይት የሚባለው መቼ ነው?
§ ከባድ የአየር ጠባይ ሁኔታ
§ ሥራ ማቆም አድማ
§ የተፈጥሮ አደጋ እንደ ጎርፍ፣ማዕበል፣ርዕደ መሬት መከሰት
§ የመንግስት ባለስልጣናት ተግባር በተለይ መዘጋጃ ቤት እና ፍቃድ ሰጭ አካላት
§ የእግዚአብሄር ምኣት እና ቁጣ
ስለሆነም ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ አንዱ ነገር ተከስቶ በፕሮጀክቱ ላይ መዘግየት ቢያስከትል አንደኛው ወገን ለሌላኛው ወገን ካሳ የሚከፍልበት መንገድ የለም፡፡ /non-compensable/ ለምን ቢባል ከሁለቱም ወገኖች ቁጥጥር ውጪ ስለሚሆን ነው፡፡
ለ) በባለቤቱ ምክንያት የሚደርስ መዘግየት፡- መዘግየቱ የመነጨው ከአሰሪው (ባለቤቱ) ከሆነ ለሥራ ተቋራጩ የእፎይታ ተጨማሪ ጊዜ መስጠት እንዲሁም በመዘገይቱ ምክንያት ሥራ ተቋራጩ ላወጣቸው ወጪወች ካሳ የመክፈል አላፊነት አለበት፡፡ በባለቤቱ ምክንያት የሚደርስ መዘገየት የሚባለው መቼ ነው?
- ከመጠን በላይ የዲዛይን ለወጥ ትዕዛዝ መስጠት
- የተሳሳተ ወይም ከደረጃ በታች የሆነ ፕላን
- የባለሃብቱ ጣልቃ ገብነት
- ሣይቱን ሥራውን ለሚሰራው አካል ክፍት አለማድረግ
- የመስሪያ ፍቃድ አለማግኘት
- የተለየ ስራ በሚያገኝበት ጊዜ ከሥራ ተቋራጩ ጋር አለመተባበር
- አማካሪ ማህንዲሱ በተፈለገው ጊዜ ያለውን የዲዛይን ስዕሎች(drawings) አለማቅረብ እንዲሁም አለማጽደቅ ናቸው፡፡
በመሆኑም ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ አንዱ ነገር ተከስቶ በፕሮጀክቱ ላይ መዘግየት ቢያስከትል አንደኛው ወገን ማለትም ባለቤቱ ለሥራ ተቋራጩ በመዘግየቱ ምክንያት ላወጣው ወጪ ተጠያቂ /compensable/ ነው፡፡
ሐ) በሥራ ተቋራጩ ምክንያት የሚደርስ መዘግየት፡- በሥራ ተቋራጩ ምክንያት የሚደርስ መዘግየት ባለቤቱ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጥ አይገደድም እንዳውም ሥራ ተቋራጩ በተባለው ጊዜ ካላጠናቀቀ ሥራ ተቋራጩ ላደረሰበት የመዘግየት ጉዳት የመብት ጥያቄ (claim) መጠየቅ ይችላል፡፡
የሚከተሉትም ሁነቶች መከሰት መዘግየቱን በሥራ ተቋራጩ ትክሻ እንዲወድቅ ያደረገዋል፡-
· የሥራ ተቋራጩ ፕሮጀክት የመምራት አቅም ማነስ እና ሥራ አመራር ችግር
· ደካማ ሥራ ማካሄድ
· ለግንባታው የሚውሉ ግበኣቶችን በጊዜ አለማዘዝ እና አለማቅረብ
· የሰራተኛ እና የአቅርቦት ችግር
· ሌሎች በኮንትራክተሩ ጥፋት የሚነሱ ችግሮች ናቸው፡፡
4. የዓለም አቀፋ የአማካሪ ማሃንዲሶች ማህበር ወጥ ውል /FIDIC/ ይዞታ
የዚህ ወጥ ውል አንቀጽ 20 መሠረት ሥራ ተቋራጩ በውሉ አግባብ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜ ይገባኛል የሚል እንደሆነና ወይም ተጨማሪ ክፍያ ይከፈለኝ ብሎ የሚያምን እንደሆነ፤ሥራ ተቋራጩ ለማህንዲሱ አስቀድሞ የመብት ጥያቄውን (claim) ምክንያቱን ወይም ሁኔታውን በመግለጽ ማሳወቅ አለበት፡፡ ከዚህ ድንጋጌም የምንረዳው ነገር ቢሆን በመጀመሪያ ደረጃ ሥራ ተቋራጩ የመብት ጥያቄ የሚያነሳው እና የሚያቀርበው ለፕሮጀክቱ ማህንዲስ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ለምን ቢባል በፕሮጀክት አፈጻጸም ወቅት ማህንዲሱ የባለቤቱ ተወካይ እንደሆነ ስለሚገመት ነው፡፡
ሌላው ሥራ ተቋራጩ ለማህንዲሱ የመብት ጥያቄውን በምን ያህል ጊዜ ማስታወቅ አለበት የሚለው ነጥብ ማየቱ አስፈላጊ ነው? በFIDIC ወጥ ውል መሠረት ሥራ ተቋራጩ በተቻለ መጠን ወዲያውኑ ለማሃንዲሱ ማሳወቅ አለበት፤ይህ ባይሆን ግን ሥራ ተቋራጩ ጉዳዩን ባወቀ ወይም ማወቅ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ በሀያ ስምንት (28) ቀናት መቅረብ አለበት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ሥራ ተቋራጩ የማስታወቅ ግዴታውን ባይወጣ ምንድን ነው ውጤቱ የሚለው ጉዳይ ማየቱ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም በሚሆንበት ጊዜ በ FIDIC ወጥ ውል መሠረት ሁለት መፍትሄወች አሉ፡፡ እነዚህንም ከሥራ ተቋራጩ ጥቅም አንጻር አሉታዊ እና አወንታዊ ብለን ማየት እንችላለን፡፡
በዚህም መሠረት በአሉታዊ ጎን የሚወሰደው ሥራ ተቋራጩ በሃያ ስምንት(28) ቀናት ውስጥ የማስታወቅ ግዴታ እያለበት ሳያደርግ ቢቀር የመብት ጥያቄው ቀሪ ይሆንበታል፡፡ ሆኖም ግን ሥራ ተቋራጩ በአወንታዊ መልኩ ሊያነሳ የሚችለው ነገር ቢኖር በግልጽ በውላቸው ላይ ሌላ ዓይነት ማስታወቂያ እና የመብት ጥያቄውን ሊያሰደግፍበት የሚችለው ሰነድ የማቅረብ መብት ካለው ብቻ ነው፡፡ ይህን ዓይነቱን አወንታዊ መንገድ ሥራ ተቋራጩ በሚያቀርብበት ጊዜ ጊዜው በአስራ አራት(14) ቀናት አድጎ ከሃያ ስምንት(28) ቀናት ወደ አርባ ሁለት ቀናት ይሄዳል፡፡
5. በኢትዮጵያ ፍ/ቤቶች ያለው ልማድ
በኢትዮጵያ ፍ/ቤቶች ስለ ኮንስትራክሽን የመብት ጥያቄ (construction claims) በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተለያዩ ፍርዶች ተሰጥተዋል፡፡ በነገራችን ላይ አብዛኛው የኮንስትራክሽን የመብት ጥያቄዎች በአማራጭ የሙግት ሂደት(Alternative dispute resolution) በማለቃቸው የተነሳ ብዙ ጊዜ በመደበኛ ፍ/ቤቶች ሲቀርቡ አይስተዋሉም፡፡ ጸሃፊው የመረጃ እና የጊዜ ውሱኑነት ስላለበት የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ልማድ ብቻ ለማቅረብ ተገዷል፡፡ በዚህም መሠረት የተመረጡ ውሳኔወችን ከመብት ጥያቄ (claims) አንጻር እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
· ከውል የሚመነጩ የመብት ጥያቄዎች(Contractual claims) በተመለከተ በቅጽ 12 በመዝገብ ቁ.56252፤በተስፊዬ አበበ ሥራ ተቋራጭ እና በተጠሪ ማዕረጉወርቁሥራተቋራጭ በነበረው ክርክር አመልካቹ ያነሳው የመብት ጥያቄ ተገቢነት የለውም ለምን ቢባል የመንግስት መስሪያ ቤት ጋር የሚደረግ የንዑስ ተቋራጭነት ውል በተመለከተ አሰሪው ሳይፈቅድ ለሌላ ተቋራጭ አሳልፎ መስጠት እንደማይቻል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
· ስለ ውል የቀረበ የመብት ጥያቄ በሌላ ውሳኔው ማለትም በቅጽ 14 ገጽ 90 በመዝገብ ቁ.71972፤በአቶ ካሳሁን አያሌው እና የምስራቅ ጎጃም ጎዛመን ወረዳ ጤና ጽ/ቤት መካከል በነበረው ክርክር የሥራ ተቋራጩ ከሥራው ባለቤት ጋር የተደረገውን የግንባታ ሥራ ውል፣ፕላኖች፣ግንባታ ዲዛይን አይነቶች፣ የዋጋና የሥራ ማስታወቂያ መሠረት ግንባታውን የማካሄድ ግዴታ ያለበት በመሆኑ የሥራው ባለቤት በግንባታ ውል ሰነዱ ላይ ከተመለከተው ውጪ በተጨማሪነት በባለቤቱ ፈቃድና ትዕዛዞች ለተሰሩ ሥራወች ክፍያ ለመክፈል አልገደድም በሚል የሚያቀርበው ክርክር ተቀባይነት የሌለው ስለመሆኑ እና በህጉ አግባብ በባለቤቱ የተሰጡ ተጨማሪ የሥራ ትዕዛዞች የሥራ ውል አካል ተደርገው የሚወሰዱ ስለመሆኑ፡፡ [የፍ/ብ/ህ/ቁ.3244,3225,(1)(2),3152(1),3266(1),3263,3265(3)] ከዚህ ውሳኔም የምንረዳው ነገር ቢኖር ተጨማሪ ሥራ መስራት የመብት ጥያቄ (Contractual claims) ለማቅረብ እንደሚያስችል መገንዘብ ያሻል፡፡
· ስለ ከውል ውጭ አላፊነት የመብት ጥያቄ አስመልክቶ ሰበር ሰሚው ችሎት በቅጽ 18 ፡ በመዝገብ ቁጥር 106147፤ እሸት ኢንጂኔሪንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር እና አቶ ፈንታየ፡ ቢያድግልኝ መካከል በነበረው የፍትሃ ብሄር ክርክር ስለ ከውል ወጭ አላፊነት የመብት ጥያቄ(tort claims) አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡ በዚህም ውሳኔ እንደተመለከተው “በአንድ ንዑስ የሥራ ተቋራጭ ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ ሰራተኛ ለሚደርስበት ጉዳት ዋናው ሥራ ተቋራጭ ከውል ውጭ አላፊነት የሚጠየቅበት የሕግ አግባብ የሌለ ስለመሆኑ እና የመበት ጥያቄው ተቀባይነት እንደሌለው ጭምር ፍርዱ ያስረዳል፡፡”
6. የሚስተዋሉ ችግሮች እና የመፍትሄ ሃሳቦች
የመብት ጥያቄ (claim) በሚነሳበት ወቅጥ አልፎ አልፎ ለጠብ መጋበዝ፣ ጥል እና መልካም ግንኙነትን ማደብዘዝ በተደጋጋሚ የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ተግዳሮቶች አስቀድሞ ለመከላከል የሚከተሉትን ሃሳቦች አቀርባለሁ፡-
- የመብት ጥያቄ መቼም ቢሆን ለዘላለም ማስወገድ አይቻልም ሆኖም ግን ሥራ ተቋራጮችም ሆኑ አሰሪዎች (ባለቤቶች) ውላቸውን በሚየደርጉበት ወቅት የሕግ አማካሪ ጋር ተገናኝተው ቢመካከሩ መልካም ነው፡፡ ለምን ቢባል ብዙውን ጊዜ ወጥ ውሎች (standard conditions of contract) በየጊዜው ስለማይሻሻሉ ህጸጽ መገኘቱ የታመነ ነው፡፡
- ሌላው በተግባር ካጋጠሙ የፍ/ቤት ጉዳዮች በመነሳት የፕሮጀክት ባለቤቶች በተቻለ መጠን የሥራ ትዕዛዝ ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ ከመገባቱ በፊት ቢያደርጉ መላካም ነው፡፡ አለበለዚያ ግን የመብት ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም፡፡
- አንዳንድ ጊዜ ቢሆንም ባለቤቶች በጨረታ ዋጋው ዝቅ ያለ ከመፈለግ አንጻር በቂ አቅም ከሌለው ሥራ ተቋራጭ ጋር ውል የሚገቡበት ሁኔታ አለ ስለሆነም በተቻለ መጠን በግንባታው ኢንዳስትሪ የካበተ ልምድ ካላቸው ይህ ባይሆን እንኳን ሥራውን ለመወጣት አቅም ያላቸው ሥራ ተቋራጮች መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
7. ማጠቃለያ
የሰው ልጅ በማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ የተለያዩ የመብት ጥቄወች (claims) ሊኖረው ይችላል፡፡ የመብት ጥያቄውም መሰረቱ ውል እና ከሕጉ ሊመነጭ ይችላል፡፡ ከውል በመነጨ ጉዳይ የውል የመብት ጥያቄ ሲያነሱ ሌሎች ደግሞ ሕጉ አስቀድሞ ባስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ መሠረት ውል ሳይኖር አላፊነት በመኖሩ ምክንያት መብታቸውን ከውል ውጭ ሲጠይቁ ይስታዋላል፡፡
ሌላው ነገር ተዋዋይ ወገኖች የሚነሱ የመብት ጥያቄዎች በአግባቡ ለማስተዳደር ያመቻቸው ዘንድ አስቀድመው ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ በተለይም የሚገቡበት ወጥ ውል ስልመብት ጥያቄ በግልጽ ማመለከት ይኖርበታል፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments