Font size: +
16 minutes reading time (3189 words)

ከሠራተኞች መብት አንጻር ትኩረት የሚሹ የግንባታ ደህንነት አንዳንድ ነጥቦች

ለመስፋፋትና፡ ለመመቻቸት፤

ተድላና፡ ደስታ፡ ምቾት፡ ለማግኘት፤

እንረዳው በጣም፡ መነሻ እርካባችን፤

ሠራተኞች ናቸው፡ መቆናጠጫችን፡፡

ከበደ ሚካኤል (ዶ/ር) ታሪክና ምሳሌ፡ 1999 ዓ.ም ‘የሠራተኞች ዋጋ’ ገጽ 54-56

መግቢያ

ሠራተኞች በሥራ ወቅት በደህንነት ጉድለት ምክንያት የተለያዩ አደጋዎች እና ጉዳቶች ሲያጋጥሟቸው ይሰተዋላል፡፡ ይህንንም ችግር ለመቀነስ የተለያዩ የሕግ፣ የህብረተሰብ ጤና እና ማህበራዊ ግንዝቤ ሥራዎች ሲሞከሩ ይታያል፡፡ በተለይም እኤአ ከ1919 ዓ.ም ጀምሮ የዓለምአቀፉ የሥራ ድርጅት (International Labour Organization/ILO) መቋቋምን ተከትሎ በርካታ ከሠራተኛ የሥራ ደህንነት ጋር የተያያዙ መርሆዎች እያደገ መምጣቱ አይዘነጋም፡፡

ይህንንም ተከተሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተ.መ.ድ) ጠቅላላ ጉባዔ እኤአ በ1948 ባወጣው ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (Universal Declaration of Human Rights-UDHR) የሥራ ላይ ደህንነት አንዱ የሠራተኞች መብት እነደሆነ ደንግጓል፡፡

የግንባታ ሥራ በራሱ እጅግ ውስብስብ ከመሆኑ ባሻገር በርካታ ሥራዎች በጉልበት የሚከናወኑ (labour intensive) በመሆናቸው ብሎም ከሥራው ባህሪ አንጻር ፈረጅ ብዙ የሥራ ክንውን የሚካሄድበት ስለሆነ በደህንነት ጉደለት ምክንያት በርካታ አደጋ እና ስጋት ሲያጋጥም ይሰታዋላል፡፡

እንደ ዓለምአቀፉ የሥራ ድርጅት (ILO) ሪፖርት ከሆነ በዓለምአቀፍ ደረጃ በየአመቱ በግንባታ ወቅት ቢያንስ 60ሺ ሠራተኞች ከደህንነት ጉደለት ጋር በተያየዘ ለሞት የሚዳርጉ ወይም ከባድ የአካል ጉዳት አደጋዎች እንዳሚያጋጥማቸው ጠቁሟል፡፡ ይህም ማለት በየአስር ደቂቃው ውስጥ አንድ ከባድ አደጋ ይደርሳል እንደማለት ነው፡፡ ሪፖርቱም በተለይ ከአጠቃላይ የሥራ ላይ አደጋዎች ውስጥ 17 ፐርሰንት ይህም ከስድስት አደጋዎች ውስጥ አንዱ የሚሆነው ገዳይ አደጋ በግንባታ ዘርፍ እንደሆነ ያትታል፡፡

የግንባታ ደህንነት ሲባል አንድ የግንባታ ፕሮጀክት ከጥንስሱ እስከ ፍጻሜው ድረስ በሚካሄዱ መጠነ ሰፊ የግንባታ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሊደረጉ የሚገባቸው እንዲሁም ሊወሰዱ የሚችሉ ጥንቃቄዎች የሚይዝ አሰራር ነው፡፡

የግንባታ ደህንነትን በተመለከተም በ2005ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ በግልጽ እንደሚያስቀምጠው የኮንስትራክሽን ሥራ ደህንነት ጉዳይ ከኢንዱስትሪው ዕድገት ጋር ተያይዞ በትይዩ ትኩረት የሚሠጠው ቁልፍ ስራ መሆን እንዳለበት ይናገራል፡፡ በፈጻሚ አካላት የሚስተዋለው በፕሮጀክት ሳይቶች የሥራ አካባቢ ደህንነት ፖሊሲ ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ የሚወጣው ወጪና የሚመደበው ጊዜ እንደተጨማሪ ወጪ አድርጐ የመመልከት እሳቤ በመሠረታዊነት መቀየር እንዳለበትና ለስራ አካባቢ ሰራተኞች ጤንነትና ደህንነት ጥበቃ የሚወጣ ወጪ የግንባታ ወጪ በመሆኑ ትርፍ እንዳልሆነ አጥብቆ ያሳስባል፡፡

በኮንስትራክሽን ስራ አከባቢዎች መደረግ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች ባለመወሰዳቸው ምክንያት የሚደርሱ ከቀላል እስከ ከባድ የንብረትና ህይወት መጥፋት ጉዳቶች መከላከል ያሻል፡፡ እነዚን የመሰሉ አደጋዎች ለመከላለል የሚያስችል በግንባታ ሂደት መወሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄ በቂ ስልጠናና አፈጻጸሙን መከታተል የዋናው ስራ አካል ተደርጎ መፈጸም ይኖርበታል፡፡ የኮንስትራክሽን አካባቢ ደህንነት /Construction Site safety/ የግንባታ ሂደቱ ጥራት፣ ቅልጥፍና እና ውጤታማነት መረጋገጥ ወሳኝ እርምጃ ተደርጐ መወሰድ ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ በሀገራችን የኮንስትራክሽን ሥራ እንቅስቃሴ ደህንነት ማስፈን ፖሊሲው አጉልቶ ያስቀመጠበትን ሁኔታ መገንዘብ ጠቃሚ ነው፡፡

በዚህ አጭር ጹሁፍ ጸሀፊው የሥራ ድህንነት በሚል ጠቅላላ ሀሳብ በመነሳት የግንባታ ሥራ ደህንነት ላይ በማተኮር ከዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ህግ አንጻር የመንግስት ግዴታ እንዲሁም የሥራ ተቋራጮች ሚና በመዳሰስ ብሎም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በመጠቆም እና የማጠቃለያ ሃሳቡን ያቀርባል፡፡

  1. የግንባታ ሥራ ደህንነት ጽንሰ ሃሳባዊ ዳርቻ

የግንባታ ደህንነት በፕሮጀክት አፈጻጸም ወቅት በተለያየ ጊዜ ሊፈጸም ይችላል፡፡ ግንባታው የሚከናወንበት ቦታ ከታወቀ በተለይም ዲዛይን ሲነደፍ፣ መሰረቱ በሚወጣበት ጊዜ፤በግንባታ ወቅት እንዲሁም ድህረ ግንባታ ጊዜ ሊሆን ይችላል፡፡

የግንባታ ደህንነት ሲባል በግንባታ ወቅት የሚወሰዱ በርካታ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ጨምሮ የጤናና ደህንነትን ሊጠብቁ የሚችሉ በቅድሚያ ሊተገበሩ የሚገባቸው (proactive measures) ወይም ከድርጊት በኋላ የሚወሰዱ (reactive measures) ናቸው፡፡ (John Murdoch & Will Hughes: 2000: 253)

የግንባታ ሥራ ድህንነት በተመለከተ ብላክስ ሎ መዝገበ ቃላት (Black’s Law dictionary 9th ed p.1184) የግንባታ ሥራ ድህንነት ከማለት ይልቅ የሥራ ላይ ደህንነት በማለት ትርጉም ለመስጠት ይሞክራል፡፡ በዚህም መሰረት የሥራ ላይ ደህንነት በጠቅላላው የሥራ ቦታን ለሞት ወይም ከባድ አካለዊ ጉዳት ከሚያደርሱ የሚታወቁ አደጋዎች መጠበቅ ነው፡፡ “keep (ing) the workplace free from recognized hazards that cause or are likely to cause death or serious physical harm to employees.” ሆኖም ግን ይህ ዓይነት ትርጓሜ አንድም የታወቁ አደጋዎችን ባለመለየቱ ምክንያት ጥቅልነት (broadness) ይታይበታል አሊያም ደግሞ ሊወሰዱ የሚገባቸውን የደህንነት መንገዶች አያሳይም፡፡

በአንጻሩ ደግሞ እኤአ በ1988ዓ.ም የዓለምአቀፉ የሥራ ድርጅት (ILO) ያወጣው የግንባታ ደህንነት እና ጤና ስምምነት (Construction safety and health convention no.167) የግንባታ ደህንነትን በተመለከተ (ከአንቀጽ 13-34) በዝርዝር ከመደንገጉ ባሻገር በግንባታ ወቅት የሚወሰዱ ያላቸውን አነስተኛ እርምጃዎች (minimum measures) ለማስቀመጥ ይሞክራል፡፡ እነዚህም፡ -

  • ለግንባታ ሠራተኞች ከግንባታ በፊት ስለ ጥንቃቄ እርምጃዎች በቂ የሆነ ስልጠና እና መረጃ መስጠት ብሎም የሚደርሱ ጉዳቶችን ወይም አደጋዎችን በጊዜ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ማደረግ ያስፈልጋል፡፡
  • የሥራ ቦታ ደህንነት መጠበቅ፣
  • ተገቢ የሆነ እንደመሰላል ያለ ለግንባታ ሥራ የሚያግዝ መወጣጫና መሰላል መስራት (scaffolds and ladders) ፣
  • በአግባቡ የተተከሉ እንዲሁም የሚሰሩ የዕቃ ማንሻ እና ማቀበያ መሳሪያዎች (lifting appliances and gear) መጠቀም ፣
  • በግንባታው አካባቢ ያለውን የአካባቢ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሳይገድቡ ተገቢ የሆኑ ማሽኖች፣ ማጓጓዣ መሳሪያዎች እና ቁሳቁሶች መጠቀም (transport, earth-moving and material handling equipment) ፣
  • የሠራተኞችን የሥራ ብቃት መለኪያ መርሆችን (ergonomic principles) መሰረት ባደረገ መልኩ የሚተከሉ ማሽኖችን እና በተግባር የተሞከሩ መሳሪያዎችን መጠቀም፣
  • የከፍታ ላይ ሥራዎች በተለይ ገመድ መሰል መቋጠሪያ በመታጠቅ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በሠራተኛው ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ተገቢ ጥንቃቄ ማድረግ፣
  • የቁፋሮ ሥራዎች፣ የጉድጓድ፣ የከርሰ-ምድር እንዲሁም የዋሻ ሥራዎች በሚከናወኑበት ጊዜ አንድም ከፍርስራሽ አደጋዎች ለመጠበቅ ተገቢ ድጋፍና ከለላ የሚያደርግ መሳሪያ መጠቀም አሊያም በቂ የሆነ አየር (ventilation) አንዲኖር የሚያስችሉ፤ከድንገተኛ የተፈጥሮ ጋዝ እና ውሃ መታፈን ለመከላከል የሚስችሉ ነገሮችን ማድረግ፣
  • የድልድይና ትላልቅ የከርሰ-ምድር ግንባታዎች በሚሰራበት ወቅት የውሃ ማገቻ መሳሪያ (caisson) እና ውሃ ሳይገባ ሳጥን መሰል የውሃ አጥር በመገንባት (cofferdam) ጥንቃቄ በተሞላው መልኩ ሥራውን ማከናወን፣
  • ከውሃ በላይ በሚሰሩ ግንባታዎች እነዲሁም የነበረ ግንባታ በሚፈርስበት ወቅት ተገቢ የሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ፣
  • እንደ አስፈላጊነቱ ተንቀሳቃሽ የሆነ የመብራት፣ የኤሌትሪክ ኋይል እንዲሁም ለእሳት አደጋ መከላከያ የሚሆኑ መሳሪዎችን በሚገባ ጥቅም ላይ ማዋል፣
  • በመጨረሻም አልባሳትን ጨምሮ ሌሎች የግል ደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎች እንደ የደህንነት ኮፍያ (safety helmet) መጠቀም፤አደጋ በደረሰ ጊዜም የመጀመሪያ የህክምና አገልግሎት (first aid) መስጠትን ጨምሮ የምግብ አቅርቦት ተያያዥ ማህበራዊ መድህን (welfare) እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡

በእርግጥ የግንባታ ሥራ ድህንነት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በውስጡ ያለተፈቱ (nebulous) እና ቅቡል ያልሆኑ ጉዳዮችን ጥቅል በሆነ መልኩ ያስቀመጠበትን ሁኔታ እናገኛለን፡፡ ዳሩግን ከላይ ከተቀመጡት እርምጃዎች የግንባታ ሥራ ደህንነትን ጽንሰ ሃሳብን በመጠኑም ቢሆን ለመረዳት ያግዛሉ፡፡ እንዲሁም ስምምነቱ የማዕቀፍ ስምምነት (framework convention) እንደመሆኑ መጠን አገራት ይህንኑ እንደ መነሻ በመውሰድ የተሻሉ ዝርዝር የደህንነት ህግጋት ያወጣሉ በሚል ነው፡፡

ሌላው ጉዳይ ከላይ የተዘረዘሩት የግንባታ ላይ የጥንቃቄ እርምጃዎች እንደግንባታወቹ መጠን፣ ዓይነት እና ጊዜ አተገባበራቸው ሊለያይ ይችላል፡፡

ይህ ዓለምአቀፍ ህግ እስከዛሬ ድረስ 31 አገራት በመፈረም እና በማጽደቅ የህጋቸው አካል አድርገውታል፡፡ በአንጻሩ ኢትዮጵያ ግን የዚህ ስምምነት ፈራሚ አገር አይደለችም፡፡

  1. የግንባታ ደህንነት በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ ያለው ይዞታ

በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ የግንባታ ደህንነትን በተመለከተ ዝርዝር ህግ አልወጣም፡፡ ሆኖም ግን ከሥራ ጋር በተያያዘ እንደ ሠራተኞቹ የቅጥር ግንኙነት (employment relationship) የተለያዩና የተበታተኑ ህጎች እናያለን፡፡ ለምሳሌ፡ -በ1952ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ {tip title="ቊ 2548 መሠረቱ" content="(1) የሠራተኛውን ሕይወት ሙሉ ሰውነቱን ጤንነቱንና የሕሊና (የሞራል) ክብሩን በመጠበቅ ረገድ አሠሪው ለሥራው ልዩ ሁኔታዎች ተገቢ የሆኑትን ጥንቃቄዎች ሁሉ ማድረግ አለበት፡፡
(2) በልማድና በቴክኒክ ሥራዎች መሠረት በዚሁ ግብ ለሥራው ማካሄጃ ቦታዎችን ማቋቋምና አስፈላጊ መሣሪያን በተለይ ማደራጀት አለበት፡፡"}ፍትሃብሄር ህግ አንቀጽ 2548{/tip} ላይ አሰሪዎች ለሠራተኞቻቸው አካላዊ ደህንነት ተገቢ የሆነ የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው በቀደምትነት ይደነግጋል፡፡ በእርግጥ የሥራ ግንኙነትን የተመለከተው የፍትሃብሄየር ህግ ተፈጻሚነቱ ውስን የሆነበትን ሁኔታ መጠቆም ይቻላል፡፡

አሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁ.377/1996 አንቀጽ 92-93 የግንባታ ሥራን ጨምሮ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው የደህንነት ጥንቃቄ እርምጃዎችን አስቀምጧል፡፡ በእርግጥ አብዛኛውን ጊዜ የግንባታ ሥራ ሠራተኞች በጊዜያዊነት ከመቀጠራቸው ጋር ተያይዞ የጥንቃቄ እርምጃዎች በአግባቡ ሲተገበሩ አይስተዋልም፡፡ ሆኖም ግን የአሰሪና ሠራተኛ አዋጁ የሥራ ላይ ደህንነት የአሰሪዎች አንዱ ግዴታ መሆኑን በአንቀጽ 12 (4) ላይ በማያሻማ መልኩ አስቀምጧል፡፡ ይህንን ገዴታም ተላልፎ የተገኘ አሰሪ የወንጀል ህግ ላይ ያሉ ልዩ ሁኔታዎች እነደተጠበቀ ሆነ በመቀጮ ይቀጣል፡፡ (የአዋጁ አንቀጽ 184 (2) ይመለከቷል፡፡ )

በ2001ዓ.ም የወጣው የሕንጻ አዋጅ ቁጥር 624 ከመግቢያው ጀምሮ በርካታ የግንባታ ላይ ደህንነትን የተመለከቱ ጉዳዮችን ይዟል፡፡ በተለይም የሕንጻ አዋጅ ተቀዳሚ ዓላማ ህንጻ በሚገነባበት ወይም በሚታደስበት ጊዜ የሕዝብ ደህንነት እንዲጠበቅ ብሄራዊ ዝቅተኛ መመዘኛዎችን (national minimum standards) በመደንገግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የግንባታ ላይ ሠራተኞች የሂደቱ መሪ ተዋንያን በመሆናቸው በቂ ጥበቃ ሊደርግላቸው ይገባል፡፡

በተለይም የሕንጻ አዋጁ በአንቀጽ 31 (1) ላይ ስለ ግንባታ ደህንነት እንዲህ በማለት ያስቀምጣል፡ -

“ማነኛውም ግንባታ በግንባታው አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን፣ የግንባታ ሠራተኞችን፣ የሌሎች ግንባታዎችን ወይም ንብረቶችን ደህንነት በማያሰጋ መንገድ ዲዛይን መደረግና መገንባታ ይኖርበታል፡፡ ”

ይህ ድንጋጌ በግልጽ እንደሚያስረዳው በግንባታ ወቅት ሊወሰዱ ከሚገባቸው ጥንቃቄዎች አንዱ የግንባታ ሠራተኞች ደህንነት እንደሆነ ነው፡፡ ዳሩ ግን የእንግሊዝኛው ቅጂ የግንባታ ሠራተኞች ደህንነት በሚል ለይቶ አላስቀመጠም፡፡ አንቀጽ 31 (1) እንግሊዘኛ ቅጂ እንዲህ ይነበባል፡ - “any building shall be designed and constructed in such a way that it shall not impair the safety of people moving around, other constructions and properties.” በእርግጥ የአማርኛው ቅጂ ገዥነት ቢኖረውም የአዋጁ አጠቃላይ መንፈስ እንዲሁም የግንባታ ደህንነት ዋና ዓላማና ጥቅም (object and purpose) በመውሰድ አዋጁ የግንባታ ሠራተኞችንም ደህንነት ያጠቃልላል ብለን መተርጎም (teleological interpretation) ይቻላል፡፡ ሌላው ደግሞ አዋጁን ተከትሎ የወጣው የሕንጻ ደንብ ቁጥር 243/2003 አንቀጽ 29 (5) (ሠ) ላይ በሁለቱም ቅጂዎች እንደተመለከተው ለግንባታ ሠራተኞች ተገቢው የደህንነት ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ በግልጽ ይነገራሉ፡፡

የሕንጻ አዋጁም ከግንባታ ደህንነት ጋር የተያያዙ ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ፡ -ዲዛይኖች የደህንነት ደንቦችን ጠብቀው መዘጋጀት እንዳለባቸው ከ አንቀጽ 30 (2) ግልጽ ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡ ሌላው ከኤሌክትሪክ ገመድ ዝርጋታ ጋር በተያያዘ መወሰድ ስላለባቸው የድህንነት ጥንቃቄዎች ከአዋጁ አንቀጽ 35 ላይ መገንዘብ ይቻላል፡፡

በግንቦት 2003ዓ.ም የወጣው የሕንጻ መመሪያ በተለይም ደግሞ የግንባታ ሠራተኞችን ደህንነት በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮችን ከአንቀጽ 44-45 አስቀምጣል፡፡ የሚገርመው ደግሞ መመሪያው የደህንነት አላፊነት የአስሪዎች ወይም ሥራ ተቋራጮች ድርሻ ብቻ አይደለም፡፡ ሠራተኞችም ጭምር የሚጠበቅባቸው ግዴታዎች አሉ፡፡ እነዚህም፡ -በሥራ ቦታ ድህነነትን በሚያሰጋ መልኩ አስካሪ መጠጥ ፣ አላስፈላጊ ዝላይ፣ ሩጫ፣ ቀልዶች እና ግብግብ ከመሳተፍ መቆጠብን ጨምሮ የደህንነት አልባሳትንና ቁሳቁሶች በአግባቡ መጠቅም እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ (የመመረያው አንቀጽ 44 ተመልክቷል፡፡ )

በመጨረሻም የሕንጻ አዋጁ የደህንነት ደረጃዎችን ሳይጠብቁ የዲዛይን ወይም አማካሪ መሀንዲስነት አገልግሎት በሚሰጡ ሰዎች ላይ እነደነገሩ ሁኔታ በወንጀል ወይም በአስተዳደራዊ ቅጣት ተጠያቂ የሚያደርግበትን አሰራር አስቀምጧል፡፡ በዋናነት አዋጁ በአንቀጽ 54 (1) ላይ ድርጊቱ ሆነ ተብሎ (intentional) በሚፈጸምበት ወቅት ከ አምስት እስከ አስራአምስት አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም ከብር ሠላሳ ሺ እስከ ሃምሳ ሺ በሚደርስ መቀጮ እንደሚያስቀጣ ይደነግጋል፡፡ የሕንጻ ደንቡ በተለይም በአንቀጽ 44 ላይ የሕንጻ ደህንነትን ሳይጠብቁ ህንጻ መገንባት እንደ ህንጻው ደረጃ ከ3ሺ እስከ 5ሺ ብር አስተዳደራዊ መቀጮ እንደሚያስጠይቅ ይናገራል፡፡

  1. የግንባታ ሠራተኞች የሥራ ቦታ ደህንነት መብቶች

በዓለምአቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ህግ አስተምህሮ ሰብዓዊ መብትን የሚመለከቱ ግዴታዎች በሁለት ክፍል ሊፈረጁ ይችላል፡፡ እነዚህም፡ - ከስምምነት የሚመነጩ እና ከቻርተር የሚመነጩ ግዴታዎች ናቸው፡፡

3.1.  ከስምምነት የሚመነጩ ግዴታዎች (Treaty based)

ከስምምነት የሚመነጩ ግዴታዎች የሚባሉት በዓለምአቀፍ ደረጃ ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ አጠቃላይ ወይም ወሱን ጉዳዮችን ለመግዛት የተደነገጉ ቃልኪዳኖች (covenants) ወይም ስምምነቶች (conventions) ናቸው፡፡

የሠራተኞች መብትንም በተመለከተ እኤአ በ1966ዓ.ም የወጣው ዓለምአቀፍ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ቃልኪዳን (International Covenant on Economic, Social and Cultural Rights/ICESCR) ከአንቀጽ 6-8 ባሉ ድንጋጌዎች ሰፊ ትኩረት ሰጥቶታል፡፡ በተለይም በአንቀጽ 6 ማንም ሰው በፈለገውን የሙያ መስክ ሥራ መስራት መብት እንዳለው አስቀምጧል፡፡ እንዲሁም የተለያዩ የሠራተኛ ማህበራትን (trade unions) መመስረትን ጨምሮ የመደራጀት መብትን በአንቀጽ 8 ተመልክቶታል፡፡

ከሥራ ድህንነት ጋር በተያያዘም ቃልኪዳኑ በአንቀጽ 7 እንዲህ በማለት ያስቀምጣል፡ - “The States Parties to the present Covenant recognize the right of everyone to the enjoyment of just and favourable conditions of work which ensure, in particular (…) Safe and healthy working conditions.” ይህም ማለት ስምምነቱን የፈረሙ አገራት የሥራ ላይ ድህንነትና ጤንነትን ጨምሮ ለሠራተኞቻቸው ተገቢ እና የሚመች አጠቃላይ የሥራ ሁኔታ የመፍጠር ግዴታ አለባቸው፡፡

እንደ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች ኮሚቴ፡ ጠቅላላ አስተያየት ቁጥር 18 (CESCR General Comment No.18) ከሆነ ከዓለምአቀፍ ሰብዓዊ መብት አንጻር የሠራተኞች መብት ሁለት ገጽታ አለው፡፡ የመጀመሪያ ግለሰባዊ ገጽታ ሲሆን ይህም ሠራተኞች ምቹ እና ተሰስማሚ የሥራ ሁኔታ ባለበት አካባቢ መስራትን ጨምሮ በአጠቃላይ በፈለጉበት የሥራ መስከ የመሰማራትን ይጨምራል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በህብረት ተደራጅቶ የመስራት (collective dimension) ነው፡፡

ሌሎች ከስምምነት የሚመነጩ ዓለምአቀፍ ግዴታዎችም የሠራተኞች መብትን በሚመለከት ከሚገዙት ጉዳይ ጋር እያዛመዱ አስቀምጠዋል፡፡ ለማስረጃ ያህል፡ -ዓለምአቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን (International Covenant on Civil and Political Civil Rights -ICCPR) ስለ ተገዶ ሥራ ስለመስራት በአንቀጽ 8 (3) (ሀ) ፣ ማነኛውንም ዓይነት ዘረኝነት ለማስቀረት የወጣ ዓለምአቀፍ ስምምነት (International Convention on the Elimination of All Forms of Racial Discrimination-CERD) በአንቀጽ 5 (ሠ) (i) ፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ማነኛውም ዓይነት መገለል ለማስቀረት የወጣ ስምምነት (Convention on the Elimination of All Forms of Discrimination against Women-CEDAW) በአንቀጽ 11 (1) (ሀ) ፣ የሕጻናት መብቶች ስምምነት (Convention on the Rights of the Child-CRC) አንቀጽ 32 እንዲሁም በውጭ አገር ፈልሰው የሚሰሩ ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው መብቶች ጥበቃ ስምምነት (International Convention on the Protection of the Rights of All Migrant Workers and Members of Their Families-CMW) በአንቀጽ 11፣ 25-26፣ 40፣ 52 እና 54 ላይ በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡

ኢትዮጵያም በውጭ አገር ፈልሰው የሚሰሩ ሠራተኞችን ከሚለከተው ዓለምአቀፍ ስምምነት በስተቀር ሌሎች ከላይ የተዘረዘሩትን ሁሉንም ስምምነቶችን ፈርማ አባል ሆናለች፡፡

3.2.  ከቻርተር የሚመነጩ ግዴታዎች (Charter based)

ከቻርተር የሚመነጩ ግዴታዎች ሲባል ደግሞ የአንድ ዓለምአቀፍ ተቋም መመስረቻ ወይም ማቋቋሚያ ሕግን በአባልነት በመቀበል ወይም ተቋሙ በጊዜ ሂደት የሚያዎጣቸውን ልዩ ልዩ ስምምነቶች፣ ደንቦችና አሰራሮች በመቀበል ይሆናል፡፡

እኤአ በ1945ዓ.ም የወጣው የተ.መ.ድ ቻርተር-UN charter ምንምእንኳን ጥቅል የሆኑ ውሱን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ቢይዝም፤ስለ ከቻርተር የሚመነጩ ግዴታዎች ሲታሰብ በቀዳሚነት ይነሳል፡፡

ሥራ እና ሠራተኞችን በተመለከተ ከተ.መ.ድ ከመምጣቱ ጊዜ በፊት ማለትም በተባበሩት መንግስታት ማህበር (league of Nations) ጊዜ ጀምሮ የተቋቋመው ዓለምአቀፉ የሥራ ድርጅት (ILO) በርካታ ስምምነቶችን እና ምክረ ሃሳቦችን (recommendations) ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ የILO መመስረቻ ህገ-መንግስት-ILO constitution መግቢያ ላይ የሠራተኞች ደህንነት ጉዳይ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ይህ ዓለምአቀፍ ተቋም ሥራና ሠራተኛን በተመለከተ ሁሉንአቀፍ መለኪያዎችን ከማውጣት (standard setting) እስከ ዝርዝር ህግጋት እና ምክረ ሃሳቦች እስከመሰንዘር ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ለአብነት ያህልም፡ - ከሠራተኞች ደህንነትና ጤንነት ጋር በተያያዘ እኤአ በ1981ዓ.ም ያወጣው የሥራ ቦታ ድህንነትና ጤንነት ስምምነት (Occupational Safety and Health Convention No. 155) ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህም ስምምነት ውስጥም በርካታ የጥንቃቄና የመከላከያ እርምጃዎችን ስለመውሰድ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

ከግንባታ ሠራተኞች ጋር በተያያዘም ለዘርፋ የሚመች ልዩ ስምምነት ማለትም ከስምንት አመት በኋላ የግንባታ ደህንነት እና ጤና ስምምነት (Construction safety and health convention no.167) በሚል ማውጣቱ አይዘነጋም፡፡ በተለይም የስምምነቱ አንኳር ነጥቦች እንዴት መፈጸም እንዳለባቸው በውሳኔ ሃሳቡ (Safety and Health in Construction Recommendation, No. 175) ተዘርዝሯል፡፡

በመጨረሻም ሌሎች አህጉራዊ ቻርተሮች እና ስምምነቶችም ጭምር የሠራተኞች መብቶችን በተለይም የሥራ ቦታ ደህንነትን በተመለከተ ድንጋጌዎችን ይዘዋል፡፡ ለምሳሌ፡ -የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብት ቻርተር (African Charter on Human and Peoples’ Rights-ACHPR) አንቀጽ 15 ተጠቃሽ ነው፡፡

  1. የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ግዴታ

4.1.  የመንግስት ግዴታ

የሠራተኞች መብት በማስከበር ረገድ አገራት የተለያዩ ስምምነቶችን በመፈረም ግዴታ ገብተዋል፡፡ ታዴያ! አገራት ምን ዓይነት ግዴታ ይጣልባቸዋል?

በመሰረቱ የሠራተኞች መብት የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ መብት በመሆኑ የአገራት አላፊነት እና ግዴታ አቅም በፈቀደ መጥን እና ቀስ በቀስ ማሳካት (progressive realization) የሚል ነው፡፡ (ICESCR አንቀጽ 2 (1) ተመልክቷል፡፡ )ይህ ማለት ግን አገራት በአስቸኳይነት የሚወስዷቸው እርምጃዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ፡ -የሥራ ላይ ደህንነትን ያለአድሎ መፈጸም ጊዜ ወሰድ ባለመሆኑ ለነገ የማይባል ተግበር ነው፡፡

ልክ እንደሌሎች ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ፡ የሠራተኞች መብትም በመንግስት ላይ ሦስት ግዴታዎች ይጥላል፡፡ እነዚህም፡ - የማክበር፣ የመጠበቅ እና የማሟላት አላፊነት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ግዴታ የማክበር (obligation to respect) ሲሆን ይህም መንግስት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሠራተኞች መብት ከመጣስ መቆጠብ ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ፡ -ተገዶ የመስራት (forced labour) መከልከል ወይም ሁሉም ሠራተኛ በሥራው ላይ እንዲሁም የድህንነት መሳሪያዎች እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ከሚያደርግ አሰራር መቆጠብ ሊሆን ይችላል፡፡

ሁለተኛው ግዴታ ደግሞ የመጠበቅ (obligation to protect) ሲሆን መንግስት ሠራተኞች በሌሎች አካላት ማለትም ሦስተኛ ወገኞች ጣልቃ ገብነት ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከል አላፊነትን ይመለከታል፡፡ ለምሳሌ፡ -በግል የግንባታ ድርጅቶች እና ሥራ ተቋራጮች ተቀጥረው የሚሰሩ ሠራተኞች ተገቢ የህግ ጥበቃ እንዲያገኙ ማስቻል ሊጠቀስ ይችላል፡፡

ሦስተኛው ግዴታ ደግሞ የማሟላት (obligation to fulfill) ሲሆን ይህም መንግስት ሠራተኞችን ለመጠበቅ በሚል የሚወስዳቸው አወንታዊ እርምጃዎች (positive commitments) ናቸው፡፡ በሌላ አባባል መንግስት መብቱ እንዲከበር ከመቀስቀስ ጀምሮ ተገቢ ሕግ የማውጣት፣ አስተዳደራዊ እርምጃዎች የመውሰድ፣ የበጀት ድጋፍ የማድረግ፣ የፍትህ ተቋማት ዘርግቶ መብቱ በሚጣስበት ጊዜ እንዲከበር ማድረግን ጨምሮ ሌሎች ተዛማጅ ግዴታዎችን መወጣት ናቸው፡፡

ሌላው የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች ቃልኪዳንን የፈረሙ አገራት ሊያከብሯቸው የሚገቡ ዝቅተኛ ቁልፍ ግዴታዎች (minimum core obligations) አሉ፡፡ እነዚህም፡ -በተለይም ልዩ ጥበቃ የሚደርግላቸው ቡድኖች (marginalized groups) ሠራተኞች በቂ የሆነ የሥራ ዕድል መፍጠር እንዲሁም በየጊዜው የሚሻሻል እና የሚከለስ አገርአቀፍ የሠራተኞች የሥራ ሁኔታ ይህም የሠራተኞችን ደህንነት ጨምሮ ዕቀድ መተለም ይገኙበታል፡፡

ወደ አገራችንም ስንመለስ ከላይ ያሉትን ዓለምአቀፍ ግዴታዎች ለመወጣት በሚስችል አግባብ መንግስት የተለያዩ እርምጃዎች መውሰድ ይኖርበታል፡፡ በተለይም ደግሞ የግንባታ ዘርፍ በአገሪቱ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ በግንባታ ወቅት የሚስተዋሉ ግልጽ የድህንነት (safety standards) አለመሟላት እና በተደጋጋሚ አለመከበር መንግስት በተለይ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በሚገባ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል::

በእርግጥ መንግስት በ2005ዓ.ም ያወጣው የኮንስትራክሽን ኢንዲስትሪ ልማት ፖሊሲ በክፍል 5.9.2 ላይ የግንባታ ሠራተኞች ድህንነት በዘላቂነት መጠበቅ እንዳለበት ሦስት አብይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡ - የመጀመሪያው በኮንስትራክሽን ሥራ አካባቢ በሰዎች ጤናና ደህንነት ላይ አደጋ የማይጥሉ የመሳሪያዎች እንቅስቃሴና ሥራ አካባቢ እንዲፈጠር ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዲዛይንና ግንባታ ሂደቶች አስገዳጅ የስራ ላይ ደህንነት ማረጋገጫ ስርዓት መገንባት ሲሆን ፤ የመጨረሻው ደግሞ በኮንስትራክሽን ወቅት የሚለቀቁ ሙቀት፣ ጨረር፣ ድምፅ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ መርዛማ ውህዶች ቁጥጥር ማድረግ ይገኙበታል፡፡ ከላይ ያሉትን የፖሊሲ አቅጣጫዎች ለማስፈጸም የሚረዱ ዝርዝር ዕቅዶችን (strategies ) ያስቀምጣል፡፡ እነዚህም፡ -የሥራ ለይ ደህንነት ቁጥጥር ሥርዓት አስገዳጅ እንዲሆን ማድረግ፣ ደህንነት መጠበቂያ አልባሳትንና መሣሪያዎች አቅርቦት እንዲቀላጠፍ መደገፍ፣ ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ተቀናጅቶ በጋራ መስራት እና የግንባታ አካባቢ ስራተኞች ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ መተግበር ናቸው፡፡

ዳሩ ግን ከሰብዓዊ መብት አንጻር የግንባታ ደህንነት ማረጋገጥዝቀተኛ ቁልፍ ግዴታ በመሆኑ መንግስት ይህንን ጉዳይ አስገዳጅ ከማድረግ ባለፈ በዓለምአቀፍ የሥራ ድርጅት (ILO) ህግጋት መነሻነት ዝርዝር የደህንነት መመሪያዎች እና የፖሊሲ መተገበሪያ ስልቶችን ማውጣት ይኖርበታል፡፡

4.2.  መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት (Non-state Actors) ግዴታ

በመርህ ደረጃ የሰብዓዊ መብት ግዴታዎች ተፈጻሚነት በዋናነት የሚያነጣጥረው ስምምነቱን በተቀበሉ አገራት ላይ ነው፡፡ ሆኖም ግን ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት የሰብዓዊ መብትን እንዲያከብሩ ግዴታ የለባቸውም ማለት አይደለም፡፡

     በተለይም የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች ኮሚቴ፡ ጠቅላላ አስተያየት ቁጥር 18 አንቀፅ 52 እንዲህ የሚል ዐ.ነገር ያስቀምጣል፡ -

[W]hile only States are parties to the Covenant and are thus ultimately accountable for compliance with it, all members of society - individuals, local communities, trade unions, civil society and private sector organizations - have responsibilities regarding the realization of the right to work. (…) Such measures should recognize the labour standards elaborated by the ILO and aim at increasing the awareness and responsibility of enterprises in the realization of the right to work.” ይህም ማለት አገራት የሠራተኞችን መብትና ደህንነት በማክበር፣ በመጠበቅ ብሎም በማሟላት ረገድ የቀደሚነት ግዴታ ቢኖርባቸውም ሌሎች በዘርፋ ተዋንያን የሆኑ አካላት የተባለውን መብት የሚጥለውን ግዴታ በመወጣት አላፊነት አለባቸው፡፡ በተለይም ሥራ ተቋራጮች፣ ንዑስ ሥራ ተቋራጮች እንዲሁም በአማካሪነት የሚሰሩ ድርጅቶች የግንባታ ሠራተኞችን ደህንነት በማክበር፣ በመጠበቅ እና በማሟላት ረገድ የበኩላቸውን ሚና መጫዎት ይኖርባቸዋል፡፡

በቅርቡም የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች ኮሚቴ በጠቅላላ አስተያየት ቁጥር 24 (2017) የሠራተኞችን መብት በማስከበር ረገድ መንግስት የንግድ ድርጅቶችን ለምሳሌ:- ድንበር ተሻጋሪ የግንባታ ሥራ ተቋራጭ ድርጅቶችን (transnational construction companies) የመቆጣጠር አላፊነት እንዳለበት አሳስቧል፡፡

በመጨረሻም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚዘጋጁ የግንባታ ወጥ ውሎች (standard conditions of contract) የግንባታ ደህንነት እንዲጠበቅ በግዴታነት ያስቀምጣሉ፡፡ ለምሳሌ፡ -ዓለምአቀፉ የአማካሪ መሀንዲሶች ማህበር ወጥ ውል (FIDIC 1999) በአንቀጽ 4.8 ላይ በግልጽ እንደሚያስቀምጠው ሥራ ተቋራጮች አስፈላጊ የሆኑ የግንባታ ደህንነት ደንቦችን ማክበር አለባቸው እንዲሁም በግንባታ ቦታው ላይ በሚሰራው ሥራ ምክንያት በሠራተኞችና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ተገቢ ጥንቃቄ መወሰድ እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡

  1. ትኩረት የሚሹ ነጥቦች

በመሠረቱ የግንባታ ደህንነት ከሠራተኞች መብት አንጻር ብቻ ሳይሆን ከግንባታ ህግ እንዲሁም በአጠቃላይ ከህዝብ ድህንነት (public safety) ሊታይና ሊተነተን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ይህ የግንባታ ሠራተኞች የደህንነት ጉዳይ የመብት ጥያቄም (human rights question) ነው፡፡ ለምን ቢሉ አንድም የሠራተኞች የሥራ መብት ሲባል ደህንነታቸውን ስለሚጨምር ነው፡፡ ሁለትም የሥራ ደህንነት ባለመጠበቁ ምክንያት በዕየለቱ የሚደርሱ ሞትና ሌሎች የአካል ጉዳቶች ሠራተኛ በመሆን ከሚገኘው መብት በተጨማሪ ሌሎች በህይወት የመኖር መብትን እና የአካል ደህንነትን መብትን አደጋ ላይ ስለሚጥል ነው፡፡

ታዲያ የግንባታ ደህንነት ጉዳይ የመብት ጥያቄ መሆኑ እየታወቀ፤ በተቃራኒው አሁን ያለው ትርክታዊ አስተምህሮ (narrated discourse) በግንባታ ሂደት ውስጥ ደባል ወይም ሁለተኛ ጉዳይ (ancillary commitment) ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ስለዚህ የግንባታ ደህንነት ባለመጠበቁ ምክንያት በሠራተኞች ላይ ለሚደርሱ የመብት ጥሰቶች ሠራተኞች በተናጠል ወይም በቡድን በመሆን አግር ውስጥ በሚገኙ የፍትህ ተቋማት ተገቢ የፍትህ ጥበቃ እንዲሁም ሌሎች አስተዳደራዊ መፍትሄዎችን መጠየቅ ይችላሉ፡፡ በተለይም የሠራተኛ ማህበራት እና ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አንደዚህ ዓይነት የመብት ጥሰት በሚኖርበት ጊዜ ጉዳዮችን በማጥናት የሠራተኞችን መብት በማስጠበቅ ረገድ የጎላ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይም አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እንዲሁም በቂ ካሳ እንዲከፈል አስፈጻሚ አካላት የበኩላቸውን ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በመጨረሻም የአገር ወስጥ የፍትህ ሥርዓት በቂ በማይሆንበት ጊዜ ደግሞ የአግር ውስጥ አሠራርን በሚገባ እስከመጨረሻ እርከን አሟጦ ተጠቅሞ (exhaustion of local remedies) በአህጉራዊ ደረጃ ለተቋቋሙ የፍትህ አካላት ለምሳሌ፡ -የአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝቦች መብት ኮሚሽን ወይም ለተ.መ.ድ የሥምምነት አካላት (UN treaty bodies) እንደየነገሩ ሁኔታ በግልም ሆነ በቡድን የሚቀርብበት አሰራር ማቅረብ ይቻላል፡፡

መደምደሚያ

የግንባታ ደህንነት ሲባል በግንባታ ወቅት የሚወሰዱ በርካታ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ጨምሮ ጤናና ደህንነትን ሊጠብቁ የሚችሉ በቅድሚያ ሊተገበሩ የሚገባቸው ወይም ከድርጊት በኋላ የሚወሰዱ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህልም ከግንባታ ሥራ በፊት ለሠራተኞች መውሰድ ስላለባቸው የአልባሳት እና ሌሎች የጥንቃቄ እርምጃዎች ትምህርት ሊሆን ይችላል፡፡ የግንባታ ደህንነት ጉዳይ የግንባታ ሕግ ወይም የህዝብ ድህንት ብቻ አይደለም፡፡ ለረጅም ጊዜ ትኩረት ቢነፈገውም ቢያንስ የሠራተኞች አንዱ ቁልፍ መብት በመሆኑ ከሰብዓዊ መብት አንጻርም ተገቢው ትኩረት ሊሠጠው ይገባል፡፡

ይህ የሠራተኞች አንዱ መብት ከሆነ ደግሞ መብቱ በሚጣስበት ጊዜም በአገር ውስጥ፣ አህጉራዊ ወይም በዓለምአቀፍ ደረጃ ባሉ የፍትህ አካልትና ኮሚሽኖች ጉዳቹን በማቅረብ እልባት ሊያገኙበት የሚችልበትን አሰራር አለ፡፡

በመጨረሻም በኢትዮጵያ የግንባታ ህግጋት እንዲሁም ፖሊሲ ያሉት የግንባታ ደህንነት አሰራር ከዓለምአቀፉ የሥራ ድርጅት የግንባታ ሥራ ደህንነት ህግ ተሞክሮ ቢወስዱ ወይም መንግስት ሥምምነቱን በመፈረም የኢትዮጵያ የህግ አካል ቢያደርገው መልካም ነው፡፡ ሲጠቃለልም የግንባታ ደህንነት ጉዳይ ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር አብሮ ሊዘምን ስለሚገባው ያሉትን ህጎች እና ፖሊሲዎች በየጊዜው በማሻሻል በዘርፋ ያለውን ስጋት መቀነስ የሚቻልበትን ሁኔታ መዘርጋት ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡፡

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Making Extraordinary Power Part of the Ordinary Di...
The obligation of Developing Countries towards cli...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 05 October 2024