በኢትዮጵያ በኢንተርኔት ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት እና ገደቡ

ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ለዲሞክራሲያዊ ማህብረሰብ መፈጠር የመሰረት ድንጋይ ነው፡፡ ይህ መብት በጣም ረጅም ጊዜ ያስቆጥረ የሰው ልጅ መብት ሲሆን በዘመናት መካከል በፈላጭቆራጭ ነገስታት እና መሪዎች ጫና ተደርጎበታል፡፡ ለአብነት ያህልም በጥንታዊ ባቢሎናዊያን የልዩነት ሃሳብ (being dissenter) መያዝ ወደ እቶን እሳት ያስጨምር እንደነበር ከመጽሃፈ ዳንኤል  ምዕራፍ 3 ንባብ መረዳት እንችላለን፡፡

ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት የፍልስፍና መሰረቱ ከጥንት ግሪካዊያን ስልጣኔ ጋር አብሮ ይነሳል፡፡ በተለየም የዴሞክራሲ ታሪካዊ ከተማ በሆነችው አቴንስ የመናገር ነጻነት ዋጋ ህይዎትን እስከወዲያኛው ሊያስነጥቅ የሚችል ነገር ነበር፡፡ በዚህ ረገድ የሶቀራጥስ የፍርድ ችሎት ለዘመናት እንደ የመናገር ነጻነት ጥሰት ተደርጎ በድርሳናት ይወሳል፡፡ (አርሊን ሳክሶንሃውስ፡2006፡102)

በአውሮፓዊያን የዕውቀት ስልጣኔ (enlightenment period) ጫፍ በነካበት ወቅት የመናገር ነጻነት አምባገነን መንግስታትን በሃሳብ ለመሞገት የሚስችል መሳሪያ ነበር፡፡ ለምሳሌ:- ባሮን ሞንተስኩ የተባለ የፈረንሳይ ፈላስፋ የመንግስት ስልጣን ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፍፃሚ እና ሕግ ተርጓሚ ተብሎ መከፈል እንዳለበት በጹሁፍ እና በቃል በማስተማሩ የማታ ማታ ሃሳቡ ተቀባይነት ሊያገኝ ችሏል፡፡ በኋላም እኤአ ከ 1789_1799 ዓ.ም በነበረው የፈረንሳይ አቢዮት የመናገር መብት የሰው ልጆች ትልቁ ነጻነት እንደነበር ታሪክ መዝግቦታል፡፡ በታላቋ ብሪታኒያ እና አሜሪካም የመናገር ነጻነት የሊብራል የፖለቲካ አስተሳሰብ እና ዴሞክራሲ እንዲያብብ በማስቻል ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ በተለይም እነዚህ አገራት ጆን ሚልተን፣ ጆን ስቱዋርት ሚልን ጨምሮ ጀምስ ማዲሰንን የመሰሉ ሃሳብን በነጻነት የመናገር መብት ተሟጋቾችን አፍርተዋል፡፡

ልክ እንደ ዘመነ ሶክራጥስ ሁሉ ዛሬም ሃሳብን በነጻ መግለጽ እንደ ጅማል ካሾጊ ህይዎትን እስክ ወዲያኛው ሊያስከፍል ይችላል፡፡ በአምባገነኖች ግፊት አገር እስጥሎ ስደተኛ ያደርጋል፤ ለእስር ብሎም ለተለያዩ እንግልቶች ይዳርጋል፡፡

ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ሲባል ግለሰቦች ሃሳባችውን መግለጽ፣ መረጃ ማግኘት፣ መጠየቅ እንዲሁም ለሌሎች የማካፈል መብትን ጨምሮ በፈለጉት መንገድ ማለትም በጽሁፍ፣ በንግግር፣ በምልክት፤ በኢንተርኔት ወይም በሌላ መንገድ በመጠቀም መልዕክት የማስተላልፍ መብት ነው፡፡

የዚህ ጹሁፍ አላማ በኢትዮጵያ በኢንተርኔት ሃሳብን በነጻ ስለመግልጽ መብት ምንነት፣ ገደቡ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ከዚሁ መብት አተገባበር ጋር በተያያዘ በተግባር ስልሚታዩ ችግሮች በጥቂቱ መዳሰስ ይሆናል፡፡

1. የመናገር ነጻነት ለምን አስፈለገ?

ምንም እንኳን በኢንተርኔት ሃሳብን በነጻ የመግልጽ መብት ከኢንተርኔት ቴክኖሎጂና መረጃ መረብ ጋር አብሮ የሚነሳ ቢሆንም ፤ ስለ አንኳር የመገናኛ ብዙሃን ዘዴዎች (mainstream mass media) ያሉ አስተሳሰቦች፣ ትርክቶች እና ክርክሮች ኢንተርኔትን በመጠቀም ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ላይም ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ለምን አስፈለገ ለሚለው ፍልስፍናዊ ጥያቄ አራት የሚደርሱ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ (ኤሪክ ባርኔይት፡2017፡6)

አንደኛ ሃሳብን በነጻ የመግልጽ መብት በሃሳብ ገበያ ውስጥ እውነት እንዲወጣ (discovery of truth)  ያደርጋል፡፡ ይህም ግልጽ ውይይት ማድረግ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ ከማስቻሉ በተጨማሪ እውነትን እንድንፈልግ ያደርጋል፡፡ ታዋቂው ፈላስፍ ጆን ስትዋርት ሚል እንደሚለው ከሆነ እውነት ለማህበረሰብ እድገትና ለውጥ በጣም አስፈላጊ እና ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብም በአሜሪካ የሕግ ስርዓት ከፍተኛ ቦታ ይስጠዋል ፡፡ በተለይም በሃሳብ ገበያ እውነት ነጥሮ ይወጣል የሚለው (marketplace of ideas’) አስተሳሰብ ነው፡፡ እኤአ በ1919 የአሜሪካ ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኛ ኦሊቨር ሆልምስ በአብራሃምስ እና ዩናይትድ ስቴትስ  መካከል በነበረው ክርክር እውነት በሚጋጩ ሃሳቦች መካከል በሃሳብ ገበያ ውስጥ ነጥሮ የሚወጣ እሳቤ እንደሆነ በፍርድ መዝገቡ አስፍሯል፡፡ ሆኖም ግን ይህ አመክንዮ ዘረኝነትን መሰረት አድርጎ በሚነሳ የጥላቻ ንግግር እንዲሁም ለግብረ ገብነት (morality) ተቃራኒ በሆኑ ንግግሮች ላይ ተግባራዊ አይደረግም፡፡

ሁለተኛ ሃሳብን በነጻ መግለጽ የግልሰቦችን የራስ ፍላጎት ያጎለብታል፡፡ ይህም የሚሆነው አንድ ሰው ከውስጥ የታመቀ እና ራሱን የቻል ነገር ለሌሎች አውጥቶ በማከፈሉ በጣም ንቁ ተሳታፊ ብሎም በአስተሳሰብ የበለጸጉ ግለሰቦች ከመፍጠሩ ባሻገር ሰፊውን የማህብረሰብ ክፍል እንደሚጠቅም መገንዘብ ይቻላል፡፡ (ቶም ካምቤል፡1994፡34)

ሦስተኛ ሃሳብን በነጻ መግለጽ ዜጎች በዴሞክራሲያዊ ሂደት ውስጥ እንዲሳተፋ ያደርጋል፡፡ ይህ አስተሳሰብም በጣም ተቀባይነት ያገኘ ሀሳብን በነጻ የመግልጽ መብት መጠበቅ ምክንያት (justification) ነው፡፡ (አሌክስአንድር ማይክልጆን ፡1948፡26)

የመጨረሻው ምክንያት ደግሞ መንግስትን በአሰራሩ እንድንተቸው በማስቻሉ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የመንግስትን አሉታዊ ጎኖች እያነሳን ነቅሰን በማሳየት በመጠራጠር ጭምር እንድንሄድ በማስቻሉ ነው፡፡ (ፍሬድሪክ ሸኧር1982፡85)

2. በኢትዮጵያ በኢንተርኔት ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ይዘት

አለም ወደ አንድ መንደር መምጣቷን ተከትሎ፤ ኢንተርኔት የመናገር ነጻነትን አውድ ያሰፋ ብሎም የቅየረ መሆኑን እየተመለከትን ነው፡፡ (አንድሪው ፑዲፋአት፡2016፡17)ኢንተርኔት የሰው ልጆችን አኗኗር በእጅጉ ቀይሯል ከእልት ተዕልት ግብይት እስከ ማህበራዊ ሚዲያ፤ከኤሌክትሮኒክ መልእክት እስከ ተንቀሳቃሽ የስልክ አገልግሎት ብቻ ነገሮች ሁሉ በኢንተርኔት የሚዘወሩበት (Internet of things) ሁኔታ ላይ ነን፡፡ (ጎርደን ግርሃም፡1999፡23)    

በኢትዮጵያ በኢንተርኔት ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት በህገ መንግስቱ አንቀጽ 29 (2) የሕግ መሰረት ያለው ሲሆን የመብቱ ባለቤትም ኢንተርኔትን በመጠቀም ሃሳብን መግለጽ፣ መረጃ የመጠየቅ፣ የመቀበል እና የማጋራት መብቶች አሉት፡፡ ይህ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ከዓለምአቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን (ICCPR) አንቀጽ 19 ጋር ተመሳሳይ በሚባል መልኩ መብቱን ደንግጓል፡፡ በኢንተርኔት ሃሳብን በነጻ የመግልጽ መብት ሁለት ገጽታዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ግለሰባዊ (individual dimension) ሲሆን ይህም ማነኛውም ሰው ሃሳቡን የመናገር፣ የመጻፍ እንዲሁም ለሌሎች ማጋራት መብት ሲኖረው ፤ ሁለተኛው ደግሞ ቡድናዊ (collective dimension) ገጽታ ሲሆን ማነኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን ሃሳብ መቀያየር፣ መለዋወጥ እንዲሁም መረጃ ከሌሎች ሰዎች መቀበል የሚችልበት አግባብ ነው፡፡ (የላቲን አሜሪካ አገራት የሰብዓዊ መብት ፍ/ቤት በ Compulsory Membership in an Association Prescribed by Law for the Practice of Journalism ምክረሃሳብ፡1985፡ከ30-32 ይመለከቷል፡፡ )

የመናገር መብት ለአገር ዴሞክራሲያዊ ግንባታ መሰረት ሊሆን የሚችል ሰፊ መብት ነው፡፡ አንዳንድ ጸሃፍት ይህንን መብት የዴሞክራሲ ኦክስጂን ነው ይሉታል፡፡ የተ.መ.ድ ሰብዓዊ መብት ኮሚቴ በጠቅላላ አስተያየት ቁ.34 በአንቀጽ 11/12 ላይ ሃሳብን በነጻ የመግልጽ መብት በጣም ሰፊ መብት እንደሆነና በውስጡም ብዙ ጉዳዮችን  ሊይዝ እንደሚችል አመልክቷል፡፡ እነዚህም፦

  • የፖለቲካ ትምህርት/political discourse/
  • በገለሰባዊ ወይም ህዝባዊ ጉዳዮች ሃተታ
  • ዘመቻና ቅስቀሳ/Canvassing /campaigning/
  • የሰብዓዊ መብት ውይይት/discussion of human rights/
  • ጋዜጠኝነት/journalism/
  • ባህላዊና ሥነ ጥበባዊ መገለጫዎች
  • ሃይማኖታዊ አስተምህሮ/ religious discourse/
  • የንግድ ማስታወቂያ እና
  • የሚክነክኑ እና ሊያስደነግጡ የሚችሉ አገላልጾች ለምሳሌ፡ ሰንደቅአላማ ማቃጠል (flag desecration)

ታዲያ ማንም ሰው እነዚህን መብቶች በሚጠቀምበት ጊዜ አብረው ሊወሰዱ የሚገባችው ገደቦችና ግዴታዎችን ማክበር ይጠበቅበታል፡፡ ይህ መብት ለግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ለመገናኛ ብዙሃን ጨምር ተሰጥቷል፡፡ በተለይም በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁ.590/2000 አንቀጽ 4 መሰረት የብዙሃን መገናኛ ተቋማት ሃሳብን በነጻ የመግልጽ መብት እንዳላቸው በግልጽ ይናገራል፡፡

     ሃሳብን በነጻ የመግልጽ መብት በህገ መንግስቱ እና በአዋጁ ብቻ ተወስኖ የሚቀር መብት ሳይሆን ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀቻችው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ሰምምነቶች ጭምር እውቅና ያገኘ መብት ነው፡፡ ለምሳሌ፦የሁሉንአቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግልጫ (Universal Declaration of Human Rights/UDHR/ እና የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች ዓለምአቀፍ ቃልኪዳን (International Covenant on Civil and Political Rights-ICCPR) የወል አንቀጽ 19 እንዲሁም የአፍሪካ የሰዎችና ህዝቦች መብት ቻርተር (African Charter on Human and Peoples’ Right-ACHPR አንቀጽ 9 ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ህገ መንግስቱም ይህንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሃሳብን በነጻ የመግልጽ መብት ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግጋት ጋር ተቃኝቶና ተጣጥሞ መተርጎም እንዳለበት በአንቀጽ 13 ላይ በግልጽ አመልክቷል፡፡

     ሲጠቃለልም በኢንተርኔት ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት የመረጃ መረብን በመጠቀም ሃሳብን በጽሁፍ፣ በምልክትና በምስል መግልጽ፤መረጃ መቀበል ብሎም ማጋራትን ይይዛል፡፡

3. የመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ግዴታ

የተ.መ.ድ የሰብዓዊ መብት ካውንስል እኤአ በ2012ዓ.ም ባወጣው ፈር-ቀዳጅ የውሳኔ ሃሳብ መሰረት አገራት ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን በተመለከተ ያለኢንተርኔት (offline) እንዲሁም በኢንተርኔት (online) ላይ የማክበር፣ የማስጠበቅ እና የማሟላት ግዴታ አለባቸው፡፡

     በዓለምአቀፍ ሰብዓዊ መብት ሕግ አስተምህሮ አገራት ሰብዓዊ መብቶችን በተመለከተ ሦስት ግዴታ ይጣልባቸዋል፡፡ (Asbjorn Eide:1987:67)እነዚህም፦ የማክበር (respect)፣ የማስጠበቅ (protect) እና የማሟላት (fulfill) ግዴታ ናቸው፡፡ የማክበር ግዴታ ሲባል የመንግስት አካላት (ሕግ አውጪው፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚው) ሃሳብን በነጻ የመገለጽ መብትን ከመጣስ መቆጠብ አለባቸው፡፡ ለምሳሌ፦መንግስት ሃሳብን በነጻ መግለጽን ለማፈን በሚል ኢንተርኔትን ከመዝጋት ( Internet Shutdown) ወይም በይነ መረቦችን (websites) ከማፈን መቆጥብ አለበት፡፡

     የመጠበቅ ግዴታ ሲባል መንግስት የመብቱን ባለቤቶች ከሦስተኛ ወገኖች ወይም መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጥቃት/ጉዳት መጠበቅ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፦ምንም እንኳን እኛ አገር የግል ኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢዎች (Internet Service Providers) በስፋት ባይኖሩም፤ እነዚህ አካላት የተጠቃሚዎችን መብት በመተላልፍ አቅርቦታቸውን ቢያቋርጡ ወይም ቢገድቡ መንግስት እንዲህ አይነት ጉዳዮችን እየተከታተለ መብቶች እንዲጠበቁ ማድረግ አለበት፡፡

     የማሟላት ግዴታ ደግሞ መንግስት አወንታዊ እርምጃዎች (positive measures) እንዲወስድ የሚያድርግ ሲሆን በተለይም በኢንተርኔት ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ጋር በተያያዘም መንግስት ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲኖር መንገዶችን ማመቻችት እንዲሁም የቴሌኮሚኒኬሽን ግብዓቶች እንዲሟሉ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግስት ብዝሃነት በኢንትርኔት ላይ እንዲሰፍን የተለያዩ ሃሳቦች (diversity of views) እንዲንሸራሸሩ መስራት አለበት፡፡

     ይህ በእንዲህ እንዳለ ምንም እንኳን መንግስት በዋናነት ሰብዓዊ መብቶችን በሚመለከት ከላይ ወደ ታች አላፊነት (vertical obligations) ቢኖሩበትም ፤ መንግስታዊ ያልሆኑ አካልትም የጎዮሽ አላፊነት (horizontal obligations) አለባቸው፡፡ የተ.መ.ድ ሰብዓዊ መብት ኮሚቴ በጠቅላላ አስተያየት ቁ.31 አንቀጽ 8 ላይ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ( non-State actors) ማለትም ድንበር ተሻጋሪ ኩባያዎች (Transnational Companies)፣ በይነ መንግስታዊ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች (Intergovernmental Organizations) ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGOs)፣ የሲቪክ ማህበራት (CSOs) እና ግልሰቦች ሰብዓዊ መብቶችን ማክበርና መጠበቅ አለባቸው፡፡ በእርግጥ ሁሉንአቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግልጫ (UDHR) መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ሰብዓዊ መብቶችን በሚመለከት የጎንዮሽ ግዴታ እንዳለባችው በአንቀጽ 30 አመላክቷል፡፡

     እኤአ በ2017 ዓ.ም የወቅቱ የተ.መ.ድ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መበት ልዩ ጸሀፊ ( the UN Special Rapporteur on Freedom of Expression )፡ ዳቪድ ኬየ በሪፖርቱ እንደገለጸው ከሆነ በኢንተርኔት ሃሳብን ከመግለጽ መብት ጋር በተያያዘ የሚታወቁ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት እንደ—የግል ቴሌኮም አቅራቢዎች፣ የኢንተርኔት አስተላላፊ ድርጀቶች ( Internet Exchange Points)፣ የኢንተርኔት ትስስር ይዘት አስተላላፊዎች ( Content Delivery Networks)፣ ኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢዎች (Internet Service providers)፣ የኢንተርኔት አከፋፋዮች ( Internet Intermediaries)፣ የፍለጋ ኦፕሬተሮች (search engines)፣ የጡመራ አገልግሎት ሰጪዎች (blogging services)፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተቋማት (social media platforms)፣ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች (online community) እና የግል ተቋማት (private contractors) ናቸው፡፡ ለምሳሌ፦ኢትዮጵያ ውስጥ የመብት ቡድኖች እንደሚከሱት ከሆነ አንድ ዜድ ቲ ኢ የተባለ የቻይና የቴሌኮም አቅራቢ ኩባንያ (ZTE Corporation) ለኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞች ቁጥጥር  በሚል ለስለላ (intrusive surveillance) አገልግሎት የሚሆን ዳታቤዝ (database) እንደተከለለት ይታወሳል፡፡

ታዲያ እንደዚህ አይነት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የመናገር ነጻነትን ሲጋፋ በምን የሕግ ማዕቅፍ ይግዛሉ የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ በዚህ ረገድ እኤአ በ2008ዓ.ም የተ.መ.ድ ልዩ ወኪል ጆን ሩጊ ያወጣቸው አሳማኝ መርሆዎች (John Ruggie Principles) ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ሥራቸውን በሚያከናወኑበት ወቅት ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር፣ ከጉዳት የመጠበቅ እና ለደረሱ ጥሰቶች ካሳ የመክፍል አላፊነት አለባቸው፡፡ እንዲሁም ኩባንያዎች በሚሰጡት አገልግሎት ምክንያት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚያደርሱብት ጊዜ የኩባንያ ማህበራዊ አላፊነት (Corporate Social Responsibility) እንደተጠበቀ ሆኖ ቅን አካሄድ (due diligence) በመከተል ጥሰቶችን መለየት፣ መከላከል፣ መካስ ብሎም ተጠያቂ መሆንን ይጨምራል፡፡  

4. ሕጋዊ ገደቦች (Legitimate Limitations)

ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት በዓለምአቀፍ ሰብዓዊ መብት ሕግ ግንዛቤ መሰረት ምንም እንኳ በውስጡ በርካታ መብቶችን ቢይዝም ፍጹም የሚባል መብት (absolute right) ግን አይደለም፡፡ ይህ ማለት መብቱ በመንግስት ሊገደብ ወይም ሊወሰን ይችላል፡፡ ለምሳሌ፦በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 29 (6) ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ሊገደብ እንደሚችልና ተገቢ ወሰኖች እንደሚደረጉበት እንዲህ በማለት ይደነግጋል፦

    

እነዚህ መብቶች ገደብ ሊጣልባቸው የሚችለው የሃሳብና መረጃ የማግኘት ነጻነት በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትለው በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤት ሊገታ አይገባውም በሚል መርህ ላይ ተመስርተው በሚወጡ ህጎች ብቻ ይሆናል ፡፡ የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰው ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል ሕጋዊ ገደቦች በእነዚህ መብቶች ላይ ሊደነገጉ ይችላል፡፡ የጦርነት ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች በሕግ የሚከለከሉ ይሆናል፡፡

 

በእርግጥ ይህ ህገ መንግስታዊ ገደብ በመጠኑም ቢሆን ከዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ስምምነቶች (ለምሳሌ፦የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች ዓለምአቀፍ ቃልኪዳን አንቀጽ 19 (3)) የሚመሳሰል ነገር አለው፡፡ ዳሩግን አንዳንድ ገደቦች በጣም ጥቅልና በዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግ ተቀባይነት የሌላቸው መስፍርቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ፦ ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡

     ታዲያ በኢንተርኔት ሃሳብን በነጻ የመግልጽ መብት ላይ የሚወሰዱ ገደቦች አራት የሚደርሱ ቅድመ ሁኔታዎች (quadruple tests) መከተል አለባቸው፡፡ እነዚህም፦ህጋዊነት (Legality) ፣ ቅቡል ዓላማ መኖር (Legitimacy)፣ አስፈላጊነት (Necessity ) እና ተመጣጣኝነት (Proportionality)ናቸው፡፡

  • ህጋዊነት (legality)ይህ መርህ ማነኛውም ገደብ በሕግ መገለጽ (prescribed by law/provided by law) አለበት ይላል፡፡ እንደ የተ.መ.ድ ሰብዓዊ መብት ኮሚቴ ጠቅላላ አስተያያት አንቀጽ 24/25 ከሆነ __ሕግ ማለት በግልጽ የወጣ እንዲሁም ለዜጎች በግልጽ ተደራሽ መሆን አለበት ይላል፡፡ በዚህ ረገድ አሻሚና ጥቅል ህጎች የህጋዊነት መርህን አያሟሉም፡፡ ለምሳሌ፦በኢትዮጵያ ከአመት በፊት በወርሃ የካቲት ታውጆ የነበረው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የህጋዊነት መርሆን አያሟላም፡፡ ለምን ቢባል የአዋጁ ድምጽ ቆጠራ በጣም አሻሚ እና የተጭበረበረ በመሆኑ ነው፡፡ እንዲሁም በአገር ደህንነት ሽፋን ለመንግስት ኢንተርኔትን ጨምሮ የሞባይል ዴታ እንዲቆልፍ ትልቅ ስልጣን ስለሚሰጥም ጭምር ነው ፡፡

እንዲሁም ከህጉ ተደራሽነትና ግልጽኝነት በተጨማሪ ስልገደቡ ትክክለኛነት በቂ፣ አፍጣኝ እና አስተማማኝ የፍ/ቤት ትችት ሊኖር ይገባል፡፡ (የጆሃንስበርግ መርሆዎች አንቀጽ 1 ይመለከቷል፡፡ )

  • ቅቡል ዓላማ መኖር (Legitimacy) ፦ ይህ መርህ ደግሞ ገደብ የሚወሰደው በግልጽ ህጉ ሊያሳካ የሚችላቸው ዓላማዎችን አስቀድሞ በማመላከት ነው፡፡ የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች ዓለምአቀፍ ቃልኪዳን አንቀጽ 19 (3) (ሀ)ና (ለ) ላይ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት በሚከተሉት ቅቡል ምክንያቶች ይገደባል፡፡ አንድም የሌሎችን መብት ለመጠበቅ ሲባል (ለምሳሌ፦በምርጫ ወቅት የመራጮችን መብት ለመጠበቅ ሲባል)፤ሁለትም የሌሎችን መልካም ስምና ዝና ለመጠበቅ ብሎም ብሄራዊ ደህንነት፣ የመንግስት ስርዓት ለማስጠበቅ (public order)፣ የህብረተሰብ ጤና ለማስከበር እና ግብረ ገብነትን ለመጠበቅ ሊሆን ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት በአንጻሩ የወጣቶችን ደህንነት ( the well-being of the youth) እንዲሁም የሰውን ክብር የሚነኩ (expression of opinion intended to injure human dignity) የሚሉና በዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግ ተቀባይነት የሌላቸው ምክንያቶችን አስቀምጧል፡፡
  • አስፈላጊነት (Necessity) ፦ የሚወሰዱ ገድቦች እጅግ አስፈላጊ (necessary) መሆን አለበት፡፡ ይህም ማለትም የሚወሰደው የመብት ገደብ እርምጃ አንገብጋቢ ማህበራዊ ጉዳዮች (pressing public or social need) ጋር መጣጣም አለበት፡፡ (የSiracusa Principles 1984, መርህ 10 ይመለከቷል፡፡ ) ይህንንም ጉዳይ እኤአ በ2014ዓ.ም የአፍሪካ የሰብዓዊና ህዝቦች መብት ፍ/ቤት ኢሳ ኮናቴ እና የቡርኪናፋሶ (የውሳኔ አንቀጽ 132) መንግስት መካከል በነበረው ክርክር ላይ የመናገር መብት እጅግ አስፈላጊ በሆኑ ምክንያቶች ሊገደብ እንደሚችልና የመብቱን ዋና ዓላማ ማክሸፍ ( necessity measures may not vilify the very purpose of the right) እንደሌለበት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ (በተጨማሪም Media Rights Agenda and Others v. Nigeria, ACmHPR 1998 69 ይመልከቱ፡፡ )
  • ተመጣጣኝነት (Proportionality)፦ መንግስት በኢንተርኔት ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን ሲገድብ ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ መሆን አለበት፡፡ ሊገኝ ከታሰበው ቅቡል ዓላማ አንጻር (ለምሳሌ፦ብሄራዊ ደህንነት) መብቱ በመገደቡ የአገር ደህንነት በተሻለ ሁኔታ ከተጠበቀ የግለሰቦች የመናገር መብት ይገደባል፡፡ ሆኖም ግን ይህ የተመጣጣኝነት መርህ ለአገራት ቅጥ ያጣ (exorbitant leverage) እና የተጋነነ ስልጣን (over-broad) በመስጠት የግለሰቦችን የመናገር መብት መገደብ (gag) አይገባም፡፡ ይህንንም ጉዳይ የአፍሪካ የሰብዓዊና ህዝቦች መብት ኮሚሽን በZimbabwe Lawyers for Human Rights & Associated Newspapers Republic of Zimbabwe (2009, para 176-78) ጉዳይ ላይ እንደሚከተለው ተመልክቶታል፡፡ “The principle of proportionality seeks to determine whether, by the action of the State, a fair balance has been struck between the protection of the rights and freedoms of the individual and the interests of the society as a whole. In determining whether an action is proportionate, the Commission will have to answer the following questions: (1) Was there sufficient reasons supporting the action? (2) Was there a less restrictive alternative? (3) Was the decision-making process procedurally fair? (4) Were there any safeguards against abuse?, and  (5) Does the action  destroy the very essence of the Charter rights in issue?” ኮሚሽኑም እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች አንድ ላይ በመመርመር በእርግጥም የጋዜጣው መዘጋት የመብት ጥሰት ነው በማለት ቋጭቷል፡፡

5. በአገራችን በአሁን ወቅት የሚስተዋሉ  ችግሮች

በኢትዮጵያ በአሁን ወቅት በኢንተርኔት ሃሳብን በነጻ ከመግልጽ ጋር በተያያዝ በርካታ ችግሮች በባለመብቶች (right holders) እና በመንግስት ሲፈጽሙ ይስታዋላል፡፡ ቁጥራዊ መረጃዎችንም ብንመለከት በኢትዮጵያ ከአጠቃላዩ የህዝብ ብዛት አንጻር ያለው የኢንተርኔት ተጠቃሚ በጣም ትንሽ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በህዳር 2011ዓ.ም ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ ወደ 17,870,000 ሚሊየን ህዝብ ይህም ከአጠቃላይ ህዝብ ውስጥ 16.4 ፐርሰንት ገደማ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል የኢንተርኔት ተጠቃሚ እንደሆነ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ፌስቡክ ( Facebook) የተባለውን ማህበራዊ ድህረ ገጽን የሚጠቀሙ ወደ 4,500,000 ሚሊየን ገዳማ ይጠጋል፡፡ እንዲያውም ኢትዮጵያ ውስጥ “ኢንተርኔት ማለት ፌስቡክ ማለት ነው”የሚለውን ትርክት ቁጥራዊ መረጃዎች ውድቅ ያደርጉታል፡፡

ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ላለው ፖለቲካዊ ለውጥ ፌስቡክ የተባለው ማህበራዊ ሚዲያ የቀዳሚነቱን ስፍራ ይይዛል፡፡ ታዲያ በጎ ነገር እንዳመጣው ሁሉ በኢንተርኔት ሃሳብን መግለጽ የሚከተሉትን ተግዳሮቶች ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ እነዚህም፦ የሃሰት ወሬዎች (Fake News)፣ የጥላቻ ንግግር (Hate Speech)፣ የኢንተርኔት መዘጋት (Internet Shutdown )፣ የሰንደቅ አላማ ትእይንት ፍክክር (vying for Flag parade) እና በታሪክ አተራረክ ላይ ያሉ አለመግባባቶች (historical facts denials)ተጠቃሽ ናቸው፡፡

) የሃሰት ወሬዎች (Fake News)

የሃሰት ወሬዎች በአገራችን ከባድ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እያስከተሉ ይገኛሉ፡፡ ይባስ በሎም ግለሰቦች በቁጣ ተነሳስተው ወደ ደቦ ፍርድ (mob justice) የሚያመሩበት አጋጣሚ አለ፡፡ በተለምዶው የሃሰት ወሬዎች (Fake news/Disinformation) የሚባሉት ያልተረጋገጡ፣ ወደ አልተፈለገ መንገድ የሚመሩ ሃሰት የሆኑ ዜናዎችን ለማለት ነው፡፡ በእርግጥ የትኛው የሃሰት ወሬ የትኛው ትክክለኛ ወሬ ነው ለማለት በጣም አስቸጋሪ (subjective) ቢሆንም ወሬው የመነጨበትን ጉዳይ ከሌሎች የዜና አውታሮች ወይም ምንጮች በማረጋገጥ መለየት ይቻላል፡፡ በቅርቡ እንኳን በፌስቡክ በተሰራጨ የተሳሳተ መረጃ በመነሳሳት በኦሮሚያ ክልል ሻሽመኔ ከተማ እንዲሁም አማራ ክልል አዲስ አለም ከተማ በሃሰት ወሬዎች የተመሩ ወጣቶች በንጽሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያ አድርሰዋል፡፡

     እኤአ በ2017ዓ.ም የተ.መ.ድ ሃሳብን በነጻ የመግልጽ መብት ልዩ ጽሃፊ ከአፍሪካ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ የደህንነትና ትብብር ማህበር ልዩ ጽሃፊዎች ጋር በጥምረት ባወጡት ሃሳብን በነጻ ስለመግለጽ እና የሃሰት ወሬዎች መግለጫ (Joint Declaration on Freedom of Expression and Fake News) ላይ እንደጠቆሙት አገራት የሃሰት ወሬዎች እንዲዛመቱ ማበረታታት፣ መደገፍ ወይም ማስተዋወቅ የለባቸውም፡፡ ስልሆነም አንድን መረጃ እንደ ወረደ ከምንቀበለው ቢያንስ በተመሳሳይ ጉዳይ ሌሎች አካላት ያሉትን ነገሮች ብናጤን የሃሰት ወሬዎችን መግታት ይቻላል፡፡

) የጥላቻ ንግግር (Hate Speech)

የጥላቻ ንግግር (hate speech) ሲባል አንድን ሰው ወይም ቡድን በጎሳው (ethnicity)፣ በሃማኖቱ ወይም ጾታው እንዲገለል የሚያደርጉ ንግግሮች ናቸው፡፡ የጥላቻ ንግግሮች በዋናነት መገለጫቸው የሚከተለው ነው፡፡ አንደኛ ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን ካላይ በተቀመጡት መስፈርቶች በማድረግ መሳዳብ ( Insult) ወይም ማዋረድ (humiliate)ነው፡፡ ሁለተኛ ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን በማንነታችው፣ ሃይማኖታችው እና ጾታችው ምክያት ከማህበረ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንዳይሳተፋ ማቀብን (boycott) የሚያበረታቱ ንግግሮች ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲሁም ግለሰቦችንና ቡድኖችን ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች መግለል (discrimination)  እንዲደርስ የሚያበረታቱ ንግግሮች ናቸው፡፡ ( Iginio Gagliardone & et al, UNESCO, 2015 ይመለከቷል፡፡ )

     የጥላቻ ንግግር ከአናዳጅ/አስቀያሚ ንግግር (offensive speech) እንዲሁም አደገኛ ንግግር ( dangerous speech) ይለያል፡፡ በተለይም አናዳጅ ንግግር የሚባለው አንድን ግለሰብ ወይም ቡድን ከላይ በተመለከቱ መስፈርቶች መሰረት በማድረግ ነውር የሆኑ ቃላቶችን (derogatory terms) ወይም የዳቦ ስሞችን እየሰጡ ማስቀየም ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ አደገኛ ንግግር የሚባለው አንድን ግለሰብ ወይም ቡድን በማንነቱ፣ ሃይማኖቱ ወይም ጾታው ምክንያት በማድረግ መጠነ ሰፊ (widespread) ጥቃት እንዲደርስበት ጥሪ የሚያደርግ ንግግር ነው፡፡ አደገኛ ንግግሮች በግለሰቦች ወይም ቡድኖች ላይ ከላይ በተቀመጡት ምክንያቶች መሰረት በማድረግ ዘረፋ (looting)፣ ብጥብጥ (riot)፣ መፈናቀል (displacement) ወይም ግድያ እንዲደርስባቸው ጥሪ ያደርጋል፡፡

     ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን የጥላቻ ንግግሮችን በብዛት መስማት የተለመደ ቢሆንም፤ እኤአ በ2016ዓ.ም የአኮክስፎርድና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች መቻቻል (Mechachal) በተሰኘ ፕሮጅክት ባጠኑት ጥናት ኢትዮጵያ ውስጥ በጥናቱ ናሙና ከተውሰዱት መካከል ኢንተርኔትን በመጠቀም 0.4 ፐርሰንት የሚደርሱ ንግግሮች የጥላቻ ንግግሮች ሲሆኑ አደግኛ ንግግሮች ደግሞ ወድ 0.3 ፐርሰንት ይይዛሉ፡፡ (ለዝርዝር ጉዳዮችና ምሳሌዎች የጥናቱን ግኝት እዚህ ተመልከቱ፡፡ )

     በዓለምአቀፋ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪድን አንቀጽ 20 (2) ላይ ብሄርን፣ ዘርን ወይም ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ የጥላቻና አደገኛ ንግግሮች በሕግ ጭምር መከልከል እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግም የኢትዮጵያ መንግስት የጥላቻና አደገኛ ንግግሮች ሕግ ለማውጣት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ የተ.መ.ድ ሰብዓዊ መብት ኮሚቴ በጠቅላላ አስተያየቱ ቁ.34 የመጨረሻ አንቀጽ እንዳመለከተው በሕግ መከልከል ያለባቸው በቃልኪዳኑ አንቀጽ 20 (2) በተመለከቱ ጉዳዮች ብቻ ሲሆን በሌሎች ጉዳዮች ግን በዚህ ጽሁፍ ክፍል አራት በተብራራው አራትዮሽ መስፈርት (quadruple tests) መሆን እንዳለበት ኮሚቴው ጠቁሟል፡፡

) የኢንተርኔት መዘጋት (Internet Shutdown )

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ2009 እስክ 2011ዓ.ም ባላው ጊዜ ውስጥ ቢያንስ ከስድስት ጊዜ በላይ ኢንተርኔት ተዝግቷል፡፡ በዚህ ሳቢያም የሚሊዮኖችን በኢንተርኔት ሃሳብን የመግለጽ መብት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ያፈነበትን ሁኔታ እናገኛለን፡፡ የዘረፉ ጠበብት እንደሚሉት የኢንተርኔት መዘጋት (Internet shutdown/blackout) ማለት ሆነ ተብሎ የኢንተርኔት እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክ መገናኛ ዘዴዎችን ለተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ወይም አካባቢዎች አገልግሎታቸው ተደራሽ እንዳይሆን (inaccessible) ወይም ግልጋሎት እንዳይሰጡ (unusable) ማዳረግ ነው፡፡

     አገራት ኢንተርኔትን በሚከተሉት ምክንያቶች ሊዘጉ ይችላሉ፡፡ አንደኛ የፈተና ኩረጃን (exam cheating) ለማስቀረት በፈተና ወቅት ሊወሰድ ይችላል፡፡ ለምሳሌ፦ኢትዮጵያ ውስጥ በሰኔ ወር 2008ዓ.ም ከዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በማህበራዊ ሚዲያዎች መለቀቅ ጋር በተያያዘ ኢንተርኔት ተዘግቶ እንደነበር ይታውሳል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከአገር ጸጥታ ጋር በተያያዘ በአስቸኳይ ጊዜ ወቅት የኢንተርኔት አገልግሎት ሊቋረጥ ይችላል፡፡ በአገራችን ከአመት በፊት በወርሃ የካቲት ታውጆ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የኢንተርኔት አግልግሎት ተቋርጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ህዝባዊ እምቢተኝነትን ለመቆጣጠር ( quelling sparking protests) ኢንተርኔት ሊዘጋ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ በአለፉት ጥቂት አመታት መደበኛ የብዙሃን መገናኛ ዘዴዎች በመንግስት ጫና እና ቁጥጥር ስር በመሆናችው ግለሰቦች የማህበራዊ ሚዲያን እንድ ትልቅና ዋነኛ አማራጭ በመውሰድ የሃሳብ ማንሸራሸሪያ መድረኮች ሲሆኑ፤ይህንን ተከትሎም ወጣቶች ያላችውን ቁጣ በተለያየ አደረጃጀት ማለትም__ቄሮ (ኦሮሞ)፣ ፋኖ (አማራ)፣ ዘርማ (ጉራጌ)፣ ዱኮ ሂና (አፋር) ወዘተ በሚሉ ስሞች መንግስት ላይ ጫና አሳድረዋል፡፡ ታዲያ እነዚህን አመጾች ለመቆጣጠር መንግስት ከወሰዳቸው እርምጃዎች ውስጥ አንዱ የኢንተርኔት መዝጋት ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢንተርኔት ምርጫን ልመቆጣጠር (managing elections) ሊዚጋ ይችላል፡፡ እንዲሁም ኢንተርኔት በመካላከያ ሃይሎች የሚቀርቡ የሥራ ማቆም አድማን ለመቆጣጠር (containing defense forces strike) ሲባል ሊዘጋ ይችላል፡፡

) የሰንደቅ አላማ ትእይንት ፍክክር (vying for Flag parade)

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚደግፉትን የፖለቲካ ቡድን አርማ ወይም ሰንደቅ አላማ በመያዝ ትዕንት ማድረገ የተለመደ ተግባር እየሆነ ነው፡፡ ሰንደቅ አላማ ማውለብለብ ወይም መስቀል (flag waving/hoisting) አንዱ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት መገለጫ ነው፡፡ በኢንተርኔትም በተለይ በማህበራዊ ሚዲያም ጭምር የሚደግፋትን ቡድን ሰንደቅ አላማ ማግዘፍ፣ ማግነን ብሎም ለሌሎች ሰዎች ማጋራት በስፋት ይስተዋላል፡፡ ታዲያ የኔ ብቻ ነው ትክክል፣ የሌላውን ሰንደቅ አውርዶ መስቅል እንዲሁም በሌሎች ሰዎች ንብረትና መብት ላይ ጣልቃ እየገቡ ሰንደቅ አላማ መስቀል ተገቢ አይደለም፡፡ ስለሆነም ወዳልተፈለገ ፉክክር ሳይገባ በሰልጠነ መንግድ መብታችንን መጠቀም የመብቱን ዓላማ ማሳካት ተገቢ ነው፡፡

) በታሪክ እውነታዎች ላይ ያሉ አለመግባባቶች (Historical facts denials)

በታሪካዊ እወነታዎች ላይ በሚሰጡ አሉታዊ አስተያየቶች ከባድ ውዝግቦች ሲነሱ ይስተዋላል፡፡ በቅርቡም CNN የተባለ የቴሌቪዥን ተቋም ስል አይሁዶች በናዚዎች መጨፍጨፍ ክህደትና ጸረ ሴማዊነት (holocaust denials and anti-Semitism)  በአውሮፓ  በሚል ሰፊ ምርመራዊ ዘገባ አውጥቶ ነበር፡፡ በዚህ ዳሰሳ መሰረትም 34 ፐርሰንት የሚሆኑ አውሮፓዊያን ስለአይሁዶች ጭፍጨፋ እንደማያውቁ አመልክቷል፡፡ በርካታ የአውሮፓ አገራትም የአይሁዶችን ጭፍጭፋ መካድን በሕግ እንደሚያስቀጣ ደንግገዋል፡፡

     ምንምእንኳ በኢትዮጵያ በታሪካዊ እውነቶች ላይ አለመግባባት ጉዳይ ብዙ ያልተለመደ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን አንዳንድ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የታሪክ አራዳዳችን በጣም የተራራቅ አንዳንዴም ጫፍ የረገጠ ነው፡፡ ለምሳሌ፦የአድዋ ድልን መካድ እንዲሁም የንጉስ ምኒልክን ሚና ማናናቅ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተም ሕግ የለንም፡፡

     የተ.መ.ድ ሰብዓዊ መብት ኮሚቴ በጠቅላላ አስተያየቱ ቁ.34 አንቀጽ 49 ላይ በታሪክ እውነታዎች ክህድትን የሚቀጡ ሕግጋት በተለይም አንደን ቡድን እንዲጠቃ ወይም እንዲገለል እስካላደረገ  ድረስ ሃሳብን በነጻ ከመግለጽ መብት ጋር እንደሚጣረሱ አስቀምጧል፡፡ (በጉዳዩ ላይ የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ በጠቅላላ ውሳኔ ቁ.550/93 በፋውሪስን እና ፈረንሳይ ይመለከቷል፡፡ )

መደምደሚያ

በኢንተርኔት ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ሲባል ኢንተርኔትን በመጠቀም ግለሰቦች ሃሳባችውን መግለጽ፣ መረጃ ማግኘት፣ መጠየቅ እንዲሁም ለሌሎች የማካፈል መብት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኢንተርኔት ሃሳብን የመግለጽ መብት የሚከተሉትን ተግዳሮቶች ይስተዋሉበታል፡፡ እነዚህም፦ የሃሰት ወሬዎች (Fake News)፣ የጥላቻ ንግግር (Hate Speech)፣ የኢንተርኔት መዘጋት (Internet Shutdown )፣ የሰንደቅ አላማ ትእይንት ፍክክር (vying for Flag parade) እና በታሪክ አተራረክ ላይ ያሉ አለመግባባቶች (historical facts denials)ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ከላይ ያሉትን ችግሮች ለመቀነስ የሚከተሉትን ምክረ ሃሳቦች አጋራለሁ፡፡ አንደኛ የሃሰት ወሬዎችን ለመከላከል ዜጎች በማነኛውም ጊዜ በጣም ንቁ በመሆን የዜናውን ምንጭ ብሎም ይዘት ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንዲህም ምንጊዜም ቢሆን አላፊነት ከራስ ስለሚጀምር አንድ ወሬ ሳይረጋገጥ ከማውራት በፊት ራስን መቆጠብ (self-regulation) መልካም ነው፡፡ ሁለተኛ መንግስታዊ ባልሆኑ ቡድኖች (non-State actors) መሪነት ሃሳብን በነጻ ከመግለጽ ጋር ተያይዘው ለሚደርሱ ችግሮች (በተለይ የስንደቅ አላማ ትዕይንት ፍክክር እንዲሁም የደቦ ፍርድ)፤ የሚመለከታቸው ቡድኖች ወይም ፖለቲካ ፓርቲዎች አላፊነት እንደሚያስከትል በማወቅ የሌሎችን ግለሰቦች መብት እንዲጠበቅ መስራት አለባችው፡፡ ሦስተኛ ከኢንተርኔት መዘጋት ጋር በተገናኘ መንግስት በተቻል መጠን የዜጎች በኢንተርኔት የመናገር ነጻነት እንዳይጣስ ጥንቃቄ ማድረግ እንዲሁም የመዝጋት እርምጃ ከመወሰዱ በፊት መብቱ የሚገደብባቸውን አራት መስፈርቶች መሟላታቸውን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በመጨረሻም ከጥላቻ ንግግሮች ጋር በተያያዘ መንግስት ሕግ ሲያወጣ  የዓለም አቀፋን የሲቪል እና የፖልቲካ መብቶች ቃልኪዳን አንቀጽ 19 (3) እና 20 መሰረት በማድረግ እና የንግግሮችን ዓይነት በባህሪ (አስነዋሪ/offensive፣ የጥላቻ/hate እና አደገኛ/dangerous) ለይቶ በመክፈል የመናገር መብትን በማይገድብ መልኩ ሕግ ቢረቀቅ መልካም ነው፡፡

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ሕገ-መንግሥታዊነት
Stolen Asset Recovery in Ethiopia: Critical Legal ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 29 March 2024