Font size: +
9 minutes reading time (1853 words)

ጥንቃቄ የሚፈልገው ዳኞችን የመሾም ሥርዓት

በማንኛውም አገር የመንግሥት አስተዳደር ከሕግ አውጪውና ከሕግ አስፈጻሚው እኩል የዳኝነት አካሉ አደረጃጀት፣ አወቃቀርና ጥንካሬ የሥርዓቱን ዴሞክራሲያዊነት ይወስናል፡፡ የዳኝነት አካሉ ገለልተኛና ነፃ ባልሆነ መጠን የሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊነት ዋጋ ያጣል፡፡ የዳኝነት አካሉ መሠረታዊ ሕገ መንግሥታዊ መርሆችን ለማስፈጸም፣ የዜጎች የሰብዓዊ መብቶች እንዲጠበቁና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ገለልተኛ፣ ግልጽ አሠራርን የሚከተልና ጠንካራ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ በ1987 ዓ.ም. የወጣው ሕገ መንግሥታችን በአንቀጽ 78 እና 79 እነዚህ መሠረታዊ የዳኝነት አካሉ መገለጫዎችን ደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ ከወጣ ከ25 ዓመታት በኋላም የዳኝነት አካሉ የአሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት አመርቂ እንዳልሆነ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይስማማሉ፡፡

ለዚህ ነው የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2015 ዓ.ም በሕዝብ ታማኝነት ያለው የዳኝነት አካል ለመሆን ራዕይ ይዞ የሚንቀሳቀሰው፡፡ ከ15 ቀናት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀው የዳኝነት ሹመት ጋር በተያያዘ በሕግ ባለሙያዎች በየዐውዱ የሚደረገው ክርክር የዚህ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ኃይለ ገብርኤል መሐሪ የተባሉ ጸሐፊ ሰኔ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በሪፖርተር ጋዜጣ የአስተያየት አምድ ‹‹ግልጽነት የጎደለው የዳኞች ምልመላ›› በሚል በጻፉት ጽሑፍ የተሾሙት ዳኞች ምልመላ በአጭር ጊዜ የተፈጸመ፣ በቂ ፈተናና ግምገማ ያልተደረገበት፣ የሕዝብ አስተያየት በአግባቡ ያልተወሰደበትና ግልጽነት የጎደለው እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ ጸሐፊውን ጨምሮ በፍርድ ቤቶች አካባቢ የሚታዩ ጠበቆችም የዳኞቹ አመላመልና ሹመት ጋር በተያያዘ ሊታዩ የሚገቡ ነጥቦች እንዳሉ ያምናሉ፡፡

የዳኞች አመላመልና አሿሿም የዳኝነት አካሉን ነፃነት ከሚያረጋግጡ ቅድመ ሁኔታዎች ዋናው ነው፡፡ ዳኞችም ከማንኛውም ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ነፃ በመሆን ፍትሕ እንዲሰፍን የሚሠሩት ምልመላውና አሿሿሙ ግልጽና ተጠያቂነት ሲኖረው ነው፡፡ የዳኞች አሿሿም የዳኝነት አካሉን ነፃነት ከሚያስገኙ የገለልተኝነት፣ የብቃት፣ የሃቀኝነትና የነፃነት እሴቶች ጋር እጅጉን ይቆራኛል፡፡ የዳኝነት አካሉ በኅብረተሰብ ውስጥ ተገቢውን ቦታ እንዲያገኝ በግልጽነት የዳኞችን የመሾም ሥርዓት ሊያከናውን ይገባል፡፡ ይህ የሚሳካው ደግሞ የዳኞች የአመራረጥና የአሿሿም ዘዴ፣ የሚመረጡ ዳኞች ዕውቀትና ልምድ በጥንቃቄና በኃላፊነት ሲከናወን ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ከዳኝነት አሿሿም ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ የሚፈልጉ አንዳንድ ነጥቦችን ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

የዳኝነት አሿሿም ዘዴዎች

የዳኝነት አሿሿም እንደ አገሮቹ የፖለቲካ ባህልና ማኅበራዊ እሴት ይለያያል፡፡ አንድ ወጥ የአሿሿም ሥርዓት የለም፡፡ ማንኛውንም የአሿሿም ሥርዓት የሚከተል አንድ አገር የዳኝነት አካሉ ነፃ እንዲሆን የአሿሿም ሒደቱ ግልጽና ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ግልጽነትና የሕዝብ ተሳትፎ በአሿሿም ካለ ጥራትና ብቃት ያላቸው የሕግ ባለሙያዎች ዳኛ ይሆናሉ፡፡ ኅብረተሰቡ በዳኝነት አካሉ ላይ ያለው መተማመን ይጨምራል፡፡

በተለያዩ አገሮች ተፈጻሚ የሚሆኑ የዳኝነት አሿሿም በደምሳሳው በሁለት ሊከፈል ይችላል፡፡ አንዱ በምርጫ የሚከናወን ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በመሾም ሥርዓት የሚከናወን ነው፡፡

ዳኞችን በምርጫ መሾም እንደማንኛውም የፓርላማ ምርጫ በሕዝብ ማስመረጥ ወይም በሕግ አውጪው አካል ማስመረጥን ይመለከታል፡፡ ዳኞች በቀጥታ ወይም በፖለቲካ ፓርቲዎች አቅራቢነት ሕዝቡ አስተያየት ሰጥቶባቸውና መርጧቸው የሚሾሙ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ የተወሰኑ ግዛቶች ይህ ዓይነት አመራረጥ ሥራ ላይ ይውላል፡፡ በሳውዝ ካሮሊና እና ቨርጂኒያ ተግባራዊ የሚሆነው አመራረጥ Legislative Appointment የሚባለው ሲሆን፣ የሕግ አውጪው አካል ከዜጎች ጋር በመተባበር በውስጡ ባቋቋመው ኮሚሽን አማካይነት ዳኞችን መርጦ ይሾማል፡፡ በካሊፎርኒያና በኒው ጀርሲ ተፈጻሚ የሚሆነው አሿሿም ደግሞ Executive Appointment የሚባለው ሲሆን፣ አስፈጻሚው ዳኞቹን መርጦ በሕግ አውጪው አካል ያሾማል፡፡

እንዲህ ዓይነት ዳኞችን በምርጫ የመሾም ዘዴ ዳኞች በመደበኛነት ለመረጣቸው አካል ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያስችል ሲሆን፣ አልፎ አልፎ ዳኞች ሕግም የማውጣት ድርሻ ስለሚኖራቸው በሕግጋቱ በሚገዛው ሕዝብ መመረጣቸውን ፍትሐዊ እንደሆነ የሚገልጹ አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ዓይነት የዳኝነት አሿሿም ዳኞች በብቃታቸውና በልምዳቸው ሳይሆን በፖለቲካ ታማኝነታቸው፣ በሙያቸው ሳይሆን በምርጫ ዘመቻቸው እንዲመረጡ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም መራጩ ሕዝብ ስለ ሙያው ያለው ዕውቀት አናሳ ስለሚሆን ብቁ ያልሆኑ ዳኞች ሊመረጡ ይችላሉ፡፡

ሁለተኛውና በብዙ የዓለማችን ክፍሎች ተግባራዊ የሚደረገው ዳኞች በአስፈጻሚው የመንግሥት አካል ተመርጠው በሕግ አውጪው አካል የሚሾሙበት ወይም የሚፀድቁበት ሁኔታ ነው፡፡ የዳኞች መረጣው ሙሉ በሙሉ በአስፈጻሚው የሚሠራ ከሆነ አስፈጻሚው ለራሱ የፖለቲካ ጥቅም ስለሚያውለው የዳኝነቱን ነፃነት ዋጋ የሚያሳጣ ይሆናል፡፡ አስፈጻሚው ከሕግ ባለሙያዎችና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተውጣጡ ገምጋሚዎች (Jurists and commentators) ሊታገዝ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ዓይነት የዳኞች አመራረጥና አሿሿም ሦስት መሠረታዊ ሒደቶች በጥንቃቄ ሊፈጸሙ እንደሚገባ ጸሐፍት ይገልጻሉ፡፡ እነዚህም በሕግ አውጪው አካል የማጽደቅ (Parliamentary Approval) የዳኝነት አካሉንና የሕግ ባለሙያዎችን የማማከር (Consultation with Judiciary and Legal profession) እንዲሁም ገለልተኛ ኮሚሽንን የመጠቀም (Use of an independent commission) ሒደት ናቸው፡፡

በፓርላማ የማጽደቅ ሒደት በመጀመሪያ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ለዳኝነት ዕጩ የሆኑትን ይመርጥና ፓርላማው ሲያፀድቀው ብቻ ዳኞቹ የሚሾሙ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ፕሬዚዳንቱ የፌደራል ዕጩ ዳኞችን ለሴኔቱ ያቀርባል ሴኔቱ ይሾማል፡፡ እንዲህ ዓይነት አሿሿም ሕግ አውጪው አስፈጻሚውን ለመቆጣጠር የሚያስችለው ሲሆን፣ በሒደቱም ሕዝቡ ዕጩዎችን በመገምገም እንዲሳተፍ ይረዳል፡፡ እንዲህ ዓይነት የአሿሿም ሥርዓት የራሱ ውስንነት አለው፡፡ ፓርላማው በዕጩ አመራረጥ ሒደቱ ስለማይሳተፍ አስፈጻሚው ለራሱ የፖለቲካ ዓላማ መሣሪያነት ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ በተለይ በፓርላማው ውስጥ ብዙ የአንድ ፓርቲ አባላት ከተገኙበት የአሿሿም ሥርዓቱ በፖለቲካ ደጋፊነት (Political Patronage) ዳኞች የሚሾሙበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡

በዳኞች አሿሿም የዳኝነት አካሉንና የሕግ ባለሙያዎችን ማማከር ነፃና ገለልተኛ ዳኞች እንዲሾሙ እንዲሁም በብቃትና በልምዳቸው የተመሰከረላቸው ዳኞች እንዲሾሙ ያስችላል፡፡ ዳኞች ለዳኝነት ብቁ የሆኑ ዕጩዎችን ለመገምገም፣ ዕጩው ዳኛ ለዳኝነት ብቁ የሚያደርግ ዕውቀትና ክህሎት እንዳለውና እንደሌለው ለመመዘን የተሻሉ ናቸው፡፡ የሕግ ባለሙያዎችንም ማማከር ጠቃሚነቱ የጎላ ነው፡፡ ከተለያዩ የሕግ ባለሙያዎች የተውጣጣ አካል የተመረጠው የሕግ ባለሙያ ፀባዩን፣ ችሎታውንና ለቦታው የሚመጥን መሆን አለመሆኑን ለመገምገም የሙያ ቅርበት ይኖራቸዋል፡፡ ይህ ዓይነት የማማከር ሒደት ብቁ ዳኞች እንዲመረጡ፤ ሕዝቡም በዳኝነት አካሉ ላይ ያለው መተማመን እንዲጨምር የማድረግ ውጤት ቢኖረውም የተወሰኑ ውስንነቶች አሉበት፡፡ አስፈጻሚው አካል ዳኞቹንና የሕግ ባለሙያዎቹን የሚያማክረው ለይስሙላ ከሆነ ወይም ባለሙያዎቹ የሚሰጡትን ምክር፣ ግምገማና አስተያየት ከመጤፍ የሚቆጥር ከሆነ ማማከሩ ትርጉም የለውም፡፡ በዚህ ረገድ የህንድ ሕገ መንግሥት ፕሬዚዳንቱ የጠቅላይና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሊሾም የፍርድ ቤቶቹን ፕሬዚዳንቶች ጨምሮ የፍርድ ቤቶቹን ዳኞች፣ የሕግ ባለሙያዎችን የከተማ ገዥዎችን የማማከር ግዴታ እንዳለበት በግልጽ ይደነግጋል፡፡

በብዙ የዓለማችን አገሮች ተቀባይነት ያለው አሠራር ገለልተኛ ኮሚሽን አቋቁሞ የዳኞችን ጥቆማ መቀበል፣ የመገምገምና ዕጩዎችን የመምረጥ አሠራር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ዳኞችን የሚመርጥ ገለልተኛ ኮሚሽን ወይም ኮሚቴ በካናዳ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በብዙ የአሜሪካ ግዛቶች፣ በአየርላንድ፣ በእስራኤል ወዘተ. ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ ኮሚሽኑ ወይም ኮሚቴው ከዳኞችና ከተለያዩ የሕግ ባለሙያዎች የሚውጣጣ ሲሆን፣ ዳኞችን የመምረጥ ወይም የመጠቆም ወይም ከተወሰኑ ዝርዝሮች ውስጥ አስፈጻሚው እንዲመርጥ የመጠቆም ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ የእንዲህ ዓይነት ኮሚሽን ውጤታማነት የሚወሰነው በአባላት ስብጥሩና በሚከተለው ሥርዓት ነው፡፡ ኮሚሽኑ ከዳኞች፣ ከታዋቂ የሕግ ባለሙያዎች፣ ከሕግ ምሁራን፣ ከኅብረተሰቡና ከፓርላማው የተወሰኑ ተወካዮችን ሊያካትት ይችላል፡፡ ኮሚሽኑ ውጤታማ ከሆነ ለዳኝነት አካሉ የሚመጥኑ ምርጥ ዕጩዎችን ያቀርባል፣ ለሕዝብ ያስገመግማል፡፡ ይህን በማድረጉም የአስፈጻሚውን ተፅዕኖ ይቀንሳል ሕዝቡ ለዳኝነት አካሉ የሚኖረውን መተማመን ይጨምራል፡፡ በዚህ ረገድ የአፍሪካዊቷ አገር የደቡብ አፍሪካ ምሳሌ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ ከ10 በላይ ባለድርሻ አካላት ዳኞች፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ ጠበቆች፣ የሕግ አስተማሪዎች፣ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ የፓርላማ አባላት ከአስፈጻሚው አካል ወዘተ. የሚውጣጡ ይሆናሉ፡፡ ይህ ኮሚሽን ለዳኝነት መወዳደር የሚፈልጉ የሕግ ባለሙያዎችን በሥራ ማስታወቂያ (Advertising Judicial Vacancy) ይጠራል፣ በግልጽ የተመረጡ ተወዳዳሪዎችን ቃለ መጠይቅ ያደርግና እንዲሾሙ ከሚፈለገው የዳኞች ቁጥር ሦስት ያህል ተጨማሪ ዕጩ በመጨመር ለፕሬዚዳንቱ ያስተላልፋል፡፡ ይህ ረዥም ጥብቅ የአመራረጥ ሒደት ለዳኞቹ ጥራትና ብቃት ዋስትና ይሰጣል፡፡

የዳኞች አሿሿም በአገራችን

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ነፃ የዳኝነት አካል ያቋቋመ ሲሆን፣ የፍርድ ቤቶችን ቅርጽና ሥልጣን በዝርዝር ደንግጓል፡፡ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባላት የፌዴራል ዳኞችን በተመለከተ ዕጩዎችን መልምሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያፀድቅ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይልካል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፌዴራል ዳኞች በተጨማሪ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትንና ምክትል ፕሬዚዳንትን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ያፀድቃል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የአባላትን ስብጥር፣ ሥልጣንና ተግባር የዳኞች አመላመል ዘዴና ተያያዥ ጭብጦችን የተመለከተ ድንጋጌዎች በዝርዝር አልያዘም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በዝርዝር የታዩት በፌዴራል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 24/1988 ሲሆን፣ ይህ አዋጅ የዳኞችን ተጠያቂነት ለማስፈንና የጉባዔውን ስብጥር ለማስፋት በሚል ዓላማ በአዋጅ ቁጥር 684/2002 እንዲተካ ተደርጓል፡፡ በአዋጁ መሠረት ይህ ጉባዔ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ጥያቄ ለፌዴራል ዳኝነት ቦታዎች ዕጩዎችን የመለየት፣ ብቁ የሆኑትን የመለየት፣ የፍርድ ቤት ሠራተኞችን ደመወዝ፣ አበልና ጥቅማጥቅም መወሰን፣ የሥነ ምግባር ደንብ፣ የዲሲፕሊን ክስ ሥነ ሥርዓት ደንብና የሥራ አፈጻጸም መመዘኛ መሥፈርት ማውጣትና ተግባራዊነቱን መከታተል ከሥልጣኑ የተወሰኑት ናቸው፡፡ የጉባዔው አባላት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ሦስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የፍትሕ ሚኒስትር የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች፣ ከጠበቆች፣ ከዳኞችና ከታዋቂ ግለሰብ የሚመረጡ ከእያንዳንዳቸው አንድ አንድ አባላት ይኖሩታል፡፡ የጉባዔው አባላት ቁጥርና ስብጥር በቀድሞው አዋጅ ከነበረው እንዲጨምር ተደርጓል፡፡

አዋጁ ለዳኝነት ለመሾም የሚያበቁ ሁኔታዎችን በተመለከተ ሰባት መሥፈርቶችን በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ በዳኝነት ሙያ ለመሰማራት ፈቃደኛ የሆነ፣ ዕድሜው ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከ25 ዓመት ያላነሰ፣ ለፌዴራል ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከ30 ዓመት ያላነሰ፣ ዕውቅና ካለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም በሕግ ትምህርት ቢያንስ በመጀመሪያ ዲግሪ በከፍተኛ ውጤት የተመረቀ፣ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ የሆነ፣ ጉባዔው በሚያደርግለት ቃለመጠይቅ፣ የማጣሪያ ፈተናና ሌሎች የባህርይ ምርመራዎች በዕውቀቱ፣ በታታሪነቱ፣ በሥነ ምግባሩ፣ በፍትሐዊነቱና በሕግ አክባሪነቱ መልካም ስም ያለው፣ የቅድመ ዕጩነት ሥልጠና የሚያጠናቅቅ፣ በጽኑ እስራት ተቀጥቶ የማያውቅ የሆነ በዳኝነት ቦታ ሊታጭ ይችላል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ከወጣ በኋላ በተለይ የመጀመሪያው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ከተቋቋመ በኋላ የተደረጉ ሹመቶችን ካስተዋልን የፌዴራል ሥርዓቱ የሚጠይቀውን የዳኞች ብዛት ከማሟላት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ከሕግ ትምህርት ቤት የተመረቁ የሕግ ምሁራን ያለብዙ ውጣ ውረዱ የሚሾሙበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. በ2004 የተሠራ የኢትዮጵያ የሕግና የዳኝነት ሴክተር ግምገማ ጥናት በጊዜው የነበሩት በዳኝነት አሿሿም ላይ የሚታዩትን ችግሮች እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፡፡

‹‹The new levers of decentralized federal/ state judicial systems introduced in the 1995 constitution created numerous new courts as well as enormous staffing demands. The remaining pool of legally – trained personnel was utterly insufficient to meet these demands. Consequently, professional qualifications were relaxed to meet immediate needs and to bring younger judges in to the new system who were unconnected with the prior regime.››  

በጊዜው በፌዴራል ሥርዓተ መንግሥት አወቃቀር የተፈጠረውን የዳኝነት ፍላጎት ለማሟላት በቁጥር አነስተኛ የነበሩትን የሕግ ተመራቂዎች በዝቅተኛ መሥፈርት በልጅነታቸው በመሾም በጊዜው የነበረውን ችግር ለመቅረፍ ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚያ ወቅት የነበሩት ዳኞች በብዙ መሥፈርት በብቃት የዳኝነት ሥራውን እንደተወጡት ቢታመንም፣ በጊዜው ከበቂ ሥልጠናና ልምድ ማነስ ጋር የሚታዩ ቅሬታዎች እንደነበሩ ይኼው ጥናት ይጠቁማል፡፡ ዳኞቹ በፍርድ ቤት ቆይታቸው እየበሰሉና ልምድ እያካበቱም ሲመጡ በጊዜው ይከፈል የነበረው ደመወዝ አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ ልምድ ያላቸው ዳኞች ወደ ጥብቅናው ዓለም ወይም ወደ ግል ሴክተሩ እየተቀላቀሉ የሕግ ምሩቃን ከሁለትና ሦስት ዓመታት በላይ በፍርድ ቤት የማያገለግሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህም የዳኞችን እጥረት እያስከተለ፣ የመዛግብት ብዛት እየጨመረ ፍርድ ቤቶች የኅብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካት አስቸግሯቸው ነበር፡፡

በጊዜው የነበረው የዳኝነት አሿሿምም ግልጽና ወጥ መሥፈርትና ሥርዓት የሌለው፣ የፌዴራል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የዳኞች አመራረጥና ዕጩ አቀራረብ ግልጽነት የጎደለው፣ የጥናት ማነስና የውሳኔ አሰጣጥ ተገማችነት አለመኖር በአጠቃላይ የፕሮፌሽናሊዝም እጦት በችግርነት እንደሚጠቀስ ከላይ የጠቀስነው የዓለም ባንክ የግምገማ ጥናት ይዘረዝራል፡፡

በአሁኑ ወቅት ተፈጻሚ የሆነው የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ማቋቋሚያ አዋጅ ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን አካቷል፡፡ የጉባዔውን አባላት ቁጥርና ስብጥሩን ማብዛቱ፣ ለዕጩ ዳኞች አስፈላጊ የሆነውን አነስተኛ ዕድሜ እንደ ፍርድ ቤቱ ዓይነት የተለያየ ማድረጉ፣ ለዳኝነት የሚፈለገው የትምህርት ደረጃ ወደ የመጀመሪያ ዲግሪ ከፍ መደረጉ፣ ዳኞች የሚመለመሉበትን በማስታወቂያ የመጥራት፣ ቃለመጠይቅና የማጣሪያ ፈተና እንዲኖር በማድረጉ ከቀድሞው ይለያል፡፡ በዳኞች አመራረጥና አሿሿም ላይ ትኩረት አደረግን እንጂ ሌሎች ልዩነቶችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ የዚህን አዋጅ ይዘት፣ አፈጻጸምና የዳኞችን አሿሿም በተመለከተ የሚነሱ ትችቶች አሉ፡፡ በዋናነት በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ለመጥቀስ እንደሞከርነው የዳኞች አመራረጥና አሿሿም ዓላማ የዳኞች ነፃነት በተግባር እንዲገለጥ፣ ብቁና ጥራት ያለው ዳኛ እንዲሾም እንዲሁም የዳኝነት አካሉ ከአስፈጻሚው አካል ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ የሕዝብ አመኔታው እንዲጨምር ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች የዕጩ ዳኞቹ አመራረጥና አሿሿም በበቂ ጊዜና የኅብረተሰብ ተሳትፎ እንዲሁም በጥንቃቄ ስለመከናወኑ ሥጋት አላቸው፡፡ ምንም የተቃዋሚ አባል በሌለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዳኝነት የሚቀርበው መሥፈርት፣ መራጩና ሿሚው ጥንቃቄ ካላደረገ የአስፈጻሚው ተፅዕኖ እንዳይሰፋ ሥጋት አለ፡፡ እስካሁን የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አሳልፎት፣ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ለሹመት ያቀረቡት ግን በምክር ቤቱ ተቀባይነት ያጣ ሹመት አለመኖሩን አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች ለጥንቃቄ ትኩረት ለማነሱ እንደማስረጃ ይጠቅሳሉ፡፡ የዳኝነት አሿሿም ከሦስቱ ዋና የመንግሥት አካላት አንዱን ክንፍ መሾም እንደመሆኑ በአፅንኦት ሊከናወን ሲገባ፣ የሕዝብ አስተያየት እየተደመጠበት በስፋት በውይይት ሊሆን ሲገባ  የሹመቱ አጀንዳ በሕዝቡ ውስጥ መነጋገሪያ እስኪሆን ድረስ የሕዝብ ተሳትፎ ማረጋገጥ አለመቻሉ ፈተና ሳይሆን አልቀረም፡፡ በአዲሱ አዋጅ ዳኞችን በፈተና የመምረጥ ሒደት እንደመሥፈርት ከመቀመጡ ውጭ ለዳኝነት ብቁ የሆነ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ማስገኘቱን በማስረጃ ማረጋገጥ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ከፈተናው እኩል ወይም ይልቅ የአመለካከት ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው ይመስላል፡፡ ፈተናውን ማን ነው የሚያወጣው? ይዘቱን በተመለከተ የተቀመጠ መመርያ (Guideline) አለ ወይ የፈተናው ይዘትስ ለዳኝነት ብቁ የመሆን ዕውቀትና ክህሎትን ይመዝናል ወይ? የሚለው ራሱን የቻለ ጥናት የሚፈልግ ነው፡፡ ኃይለ ገብርኤል መሐሪ፣ በጽሑፋቸው 700 ተፈታኞች በአንድ አዳራሽ፣ እርስ በርስ መኮራረጅ ባለበት ሁኔታ ‹‹ፈተና›› መደረጉን መሞገታቸው ለዚህ ነው፡፡ በጥሞና የፈተና መሥፈርትን ለገመገመው ዳኝነት ማንኛውም በሕግ የተመረቀ ሰው የሚሞክረው እንጂ ፍላጎት፣ ትጋት፣ ክህሎት፣ ቁርጠኝነት ያለው የሚያገኘው ለተገቢው ብቁ ባለሙያ ብቻ ክፍት የሆነ አያስመስለውም፡፡ ከዚህ ውጭ ሌሎች መሥፈርቶችም ላይ አንዳንድ የሕግ ምሁራን የሚያነሷቸው ትጋቶች አሉ፡፡ የ25 ዓመት የዕድሜ ገደብ ለአብዛኞቹ ተሿሚዎች ባልበሰሉበት ዘመን (የማኅበረሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ባልተረዱበት፣ የሚሰጡት ፍርድ በኅብረተሰቡ ውስጥ ሊኖረው የሚችለውን ውጤት በማይገምቱበት፣ በአግባቡ ጭብጥ ለመመሥረትና ለመመርመር ክህሎት ባልዳበረበት ዕድሜ) መሆኑ ጥራቱ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያደርግ መገመት አያስቸግርም፡፡ ለሁሉም ባይሠራ ለብዙኃኑ ሊሠራ ይችላል፡፡ ከፍተኛ ውጤት (ስንት መሆኑ በግልጽ በማይታወቅበት) የመሥፈርቱም አስፈላጊነት አከራካሪ በሆነበት መሥፈርቱን ማሟላት አስቸጋሪ መሆኑን የሚገልጹ አሉ፡፡

በአጠቃላይ ከላይ ያነሳናቸው ነጥቦች የዳኝነት አመራረጥና አሿሿም ላይ ሥርዓቱ የበለጠ እንዲሠራ፣ ነፃነትና የሕዝብ ታማኝነትን ለመጨመር በጥንቃቄ ሊሠራ እንደሚገባ አመላካች ነው፡፡  

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Victim Oriented Measures under Ethiopian Anti-Huma...
የኮንስትራክሽን መብቶች (Claims) ምንነት እና የሚስተዋሉ ችግሮች
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 21 November 2024