የግል አቤቱታ የማቅረብ መብት በጠቅላላው

የሥነ-ሥርዓት ሕግ ሰዎች መሠረታዊ የሆኑ የፍትሕ አቤቱታዎች ሲቀርቡ የሚመሩበትን እና መብቶች ጥቅሞችና ግዴታዎች በሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት የሚወስኑበትንና ተፈፃሚ ሊሆኑ የሚችሉበትን ሥርዓት የሚያሳይ ጽንሰ ሀሳብ ነው። የሥነ-ሥርዓት ሕግ መብቶች ጥቅሞችና ግዴታዎች በምንና እንዴት ባለ አኳኋን ወደ ተግባር ሊፈፀሙ እንደሚችሉ የሚዘረዝር የሕግ ክፍል ነው። የእነዚህን መብቶች ጥቅሞችና ግዴታዎች ይዘትና አይነት ተንትኖ የሚያቀረበው የሕግ ክፍል መሠረታዊ ሕግ (Substantive Law) ተብሎ የሚጠራ ነው። መሠረታዊ ሕግ የሰው ልጆችን መብቶች ጥቅሞችና ግዴታዎች በግልፅ የሚደነግግ በመሆኑ ጠቀሚታው ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል። ይሁን እንጅ እንዚህ ዝርዝር መብቶችና ግዴታዎች በተግባር ተፈፃሚ እንዲሆኑ ካልተደረገ የመኖራቸው ጉዳይ ትርጉም የለሽ ይሆናል ማለት ነው። እነዚህ መደበኛና ልዩ መብቶች ጥቅሞችና ግዴታዎች እንዲፈፀሙ የማድረጉ ሐላፊነት የሥነ-ሥርዓት ሕግ ቢሆንም ውጤታማ የሥነ-ሥርዓት ሕግ ከሌለ ግን መብቶችንና ግዴታዎችን የማስፈፀሙ ዓላማ እረብ የለሽ ይሆናል። ለዚህም ነው የሥነ-ሥርዓት ሕግ ከመሠረታዊው ሕግ ባላነሰ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው የሚባለው።

በግልፅ መረዳት እንደሚቻለው ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ የሥነ-ሥርዓት ሕግ ያለው አስተዋፆ በጣም ከፍተኛ ነው። የሥነ-ሥርዓት ሕጉን ዓላማና መንፈስ መከተል ተከትሎም ተፈፃሚ ማድረግ በራሱ ፍትሕን ማረጋገጥ ነው የሚሆነው። የፍትሕ ጉዳይ ‹‹የትም ፍጪው ዱቂቱን አምጭው›› የምንለው ነገር ሣይሆን ከመነሻው እስከ መዳረሻው ያለውን ሂደትና ሥርዓት በመከተልና በመተግበር የሚገኝ ፍርድ ስለሆነ የሥነ-ሥርዓት ሕጎችን እውቀት ማሳደግ ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ ቁልፍ ሚና አለው።

የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥዓት የወንጀል ጉዳዩች የሚመሩበት የሚከሰሱበት የሚዳኙበት የሚቀጡበትን  ሥርዓቶች  የሚገዙ ደንቦች  ናቸው።  ይህም  ትንሽ  የማይባሉትን የመሠረታዊ ወይም የዋና መብቶች ደረጃ አግኝተው በሕገ-መንግስት እና  በዓለም-አቀፍ  ኮቬናንቶች ጥበቃና  አውቅና  ያገኙትን የተከሣሾች የሥነ-ሥርዓት መብቶች ያካትታል። 

የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት መሠረታዊ ዓላማ የወንጀል ሕጉ በተግባር የሚፈፀምበትን ሥርዓት መዘርጋት ነው። ንፁሐን ባልፈፀሙት ወንጀል ተስበው እንዳይከሰሱ ወይም እንዳይቀጡ የሚደረገው እንዴት ነው? ወንጀል ፈፃሚዎች ለፈፀሙት የወንጀል ተግባር የጃቸውን እንዲያገኙ ለፍርድ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ሕግ አስፈፃሚ አካላት የንፁሐንን መብት እንዳይጥሱ ምን መደረግ አለበት? በወንጀል ሕጉ ላይ የተዘረዘሩትን ወንጀሎች ለመፈፀሙ በበቂ ማስረጃ የተረጋገጠበት ፍርደኛ እንዲፈፀም የታዘዘው ቅጣት ወይም ሌላ የጥንቃቂ እርምጃ ተግባራዊ የሚሆነው በምን አይነት ሁኔታ ነው? ለሚሉትና ለሌሎችም ጥያቄዎች መልስ የሚሰጠው የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት ነው።

የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት የወንጀል ድርጊት ከተፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ በወንጀል ድርጊት ፈፃሚው ላይ ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት ተገቢው ፍርድ እስኪሰጥበት ድረሰ በየደረጃው መከናወን የሚገባቸውን ልዩ ልዩ ሥነ-ሥርዓቶች የሚገልፅ ነው። የወንጀል የሥነ-ሥርዓት ሕግ ወንጀል አድራጊው ከእዝቡ ውስጥ በጥንቃቂ ተለይቶ  የሚወጣበትንና ለፍርድ የሚቀርብበትን እንዲሁም ንፁሐን ያለአግባብ እንዳይታሰሩና እንዳይጉላሉ ሊወሰድ የሚገባውን ጥንቃቂ ይገልፃል። ሕግ እንዲከበርና ወንጀለኞች ለፈፀሙት ወንጀል ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲያገኙ ለሚደረገው ጥረት የፖሊስ፣ የዐቃቤ ሕግና የዳኞች ሚና ወሳኝ ነው። የፖሊስ ቁልፍ ተግባር ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከልና ተፈፅሞ  በሚገኝበት  ጊዜም  ወንጀሉን  ማን  እንደፈፀመው  የሥነ-ሥርዓት ሕጉ በሚፈቀደውና በሚያዘው መሠረት መመርመርና የምርመራ መዝገቡን ሥልጣን ላለው ዐቃቤ ሕግ ማስረከብ ነው። የዐቃቤ ሕግ ተግባርና ሥልጣን ደግሞ ፖሊስ የምርመራ ስራውን በሥነ-ሥርዓት ሕጉ መሠረት ማከናወኑን መቆጣጠር፣ ወንጀል ፈፅሟል በተባለው ሰው ላይ አግባብ ያለው የክስ ማመልከቻ ማዘጋጀት፣ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ማቅረብና ጉዳዩ በሚሰማበት ጊዜ ፖሊስ ያጠናቀረውን ማስረጃ በሥርዓት ለችሎቱ እያቀረበ ማስረዳት ነው። የዳኛም ተግባር ዐቃቤ ሕግና ተከሣሽ ያቀረቡትን ክስና መልስ ከቀረበው ማስረጃና ለጉዳዩ አግባብነት ካለው ሕግ ጋር አገናዝቦ በገለልተኝነት ተገቢውን ፍርድ መስጠት ነው። እነዚህ ሕግ የማሰፈፀምና የመተርጎም ኋላፊነት የተጣለባቸው አካላት የሥነ-ሥርዓት ህጉ በሚያዘው መሠረት ኋላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። በመሰረቱ ማንኛውም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሕይወቱን ነፃነቱንና ንብረቱን ማጣት የለበተም። ሥርዓቱን ባለጠበቀ ሁኔታ ተመርምሮና ተሟግቶ የተፈረደበት ሰው ፍትሕ እንደተጓደለበት ይቆጠራል። በሕግ የተቀመጠው ሥርዓት ሥለተጣሰም ፍርዱ ይሻራል።

ለዚህም ነው ‹‹ሥነ-ሥርዓት ሕጉን ጥሶ ንፁሐን ሰዎችን ከማንገላታት ይልቅ ወንጀለኛው ሣይያዝ ቢቀር ይሻላል›› የሚለውን የሕግ መርዕ ሕግ አስፈፃሚ አካላት ዘወትር የስራቸው መመሪያ ሊያደርጉት የገባል የሚባለው። ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሣኔ እስካለሰጠበት ድረስ እንደ ንፁሕ ሰው የመቆጠር መብት አለው። የሰው ልጅ በሳይንስና በቴክኖሎጄ በመጠቀበት በዚህ ዘመን ዐቃቤ ሕግ ወንጀል ፈፅሟል በማለት ክስ በመሰረተበት ሰው ላይ ጥፋተኛነቱን በማያጠራጥር ማስረጃ አረጋግጦ መርታት አለበት እንጅ ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ ክስ የቀረበበት ወገን ንፀሕነትህን አስረዳ ተብሎ ሊገደድ አይገባም። ተከሣሽ በሚንቀለቀል የእሳት ነበልባል ውስጥ አቋርጦ በማለፍ፣ ከአናብስት ጋር ታግሎ በማሸነፍ ወይም ከከሣሽ ባላጋራው ጋር በመፋለም ንፀሕነቱን ያረጋግጥ የነበረበት ያ የኡሪት ዘመን ካከተመ ብዙ ዘመን ሆኗል። የአሁኑ ሰው የክስተቶችንና የሁኔታዎችን ምክንያትና ውጤት (Cause and Effect Relationship)መርምሮና አመዛዝኖ  ከሳይንሣዊ ድምዳሜ ላይ መድረስ አለበት እንጅ ምክንያት በሌለው ጭፍን አስተሣሰብ ሊመራ አይገባውም።

የግል አቤቱታ የማቅረብ መብት በጠቅላላው

በጥንት ሮማውያን አሠራር መሠረት ማንም ሰው የወንጀል ተግባር ፈጽሟል በሚለው ወንጀለኛ ላይ ክስ ለማቅረብ መብት ነበረው። አንድ የወንጀል ድርጊት ተፈጽሞ የግል ተበዳዩ ወይም የግል ተበዳዩ የቅርብ ዘመዶች በወንጀለኛው ላይ ክስ ለማቅረብ አለመፈለጋቸው ሌሎች ግለሰቦች በተፈፀመው ወንጀል ክስ ለማቅረብ ያላቸውን የከሣሽነት መብት አያሣጣቸውም ነበር። እንደ እንግሊዝ ባሉ የኮመን ሎው የሕግ ሥርዓትን በሚያራምዱ አገሮች የግል ተበዳዩች በወንጀል ክርክር ያላቸው የተፋራጅነት ድርሻ ዛሬም ቢሆን ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። የአሜሪካ የወንጀል የሥነ-ሥርዓት ሕግ በብዙ መልኩ ምንጩ ከሆነው የእንግሊዝ ሕግ ጋር ተመሳሳይ ነው። የወንጀል ክስን የማቅረብ መብት በመርህ ደረጃ የግል ተበዳዩች እንደሆነ ዛሬም ይታመናል። ነገር ግን ከበድ ባሉ ወንጀሎች ዋነኛው ባለቤት መንግስት ነው። የሲቪል ሎው የሕግ ሥርዓትን ወደሚከተሉት የአውሮፓ አገራት ታሪክ ስንመለስ ምንም እንኳ የሕግ ሥርዓታቸው የተመሠረተው በጥንቱ የሮማውያን የሕግ ፍልስፍና ላይ ቢሆንም በኋለኛው የሮማውያን ዘመን እየጎላ የመጣውና በምንግስት አስተዳደራዊ መስሪያ ቤቶችና የዳኝነት አካላት መሀል ያለውን ልዩነት አስቀርቶ በአንድ ወጥ አሰራር የወንጀልን ክስ አቀራረብ ከግል ተበዳዩቹ እጅ አውጥቶ በቀጥታ ወደ መንግስት እጅ የማዛወርን ውጤት ያስከተለው ሂደት በብዙ የአውሮፓ አገሮችም ተቀባይነት እያገኘ መጣ። ከዚህም ጋር ተያይዘው ከዚህ በፊት የማይታወቁ እንደማሰቃየት (torture)፣ ማስረጃን ከተከሣሹ መሰወር፣ ክስን በሌለበት መስማት፣ ወዘተ የመሰሉ የምርመራ ዘዴዎችና እነዚህን ዘዴዎች የሚያስፈጽሙ ተቋማት ተፈጠሩ።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፍትሕ አስተዳደር ከመመስረቱ በፊት በነበሩት ጊዜያት የወንጀል ክስ አቤቱታ የሚቀረበው በግል  ተበዳዩ  ወይም በእርሱ የቅርብ ዘመዶች አማካኝነት ነበር። የወንጀል ክስ አቤቱታ የሚቀረበው፣ ማስረጃ የሚፈለገው፣ ምስክሮች የሚያቀርበው፣ ወንጀል ፈፃሚ ነው የተባለ ሰው ታድኖ እንዲያዝ የሚደረገውና አንዳንዴም በዳኛ የተሰጠው ፍርድ ራሱ ይፈፀም የነበረው በግል ተበዳዩ ወይም በቅርብ ዘመዶቹ ነበር። ቀደም ባሉት ዘመናት የወንጀል ክስ በማን መቅረብ አለበት በሚለው አስተሳሰብ ላይ ሁለት አይነት ክርክሮች ነበሩ።

አንደኛውን አስተሳሰብ በሚያራምዱ የሕግ ሊቃውንት እምነት ወንጀል በዋነኛነት በግል ተበዳይ ሳይሆን የጠቅላላውን ማዕበረሰብና መንግስት ጥቅም ደህንነትና እልውና ላይ የሚፈፀም ጠንቀኛ ድርጊት ስለሆነ የወንጀልን ክስ በባለቤትነት ተረክቦ እፍፃሚ ማድረስ ያለበት እራሱ መንግስት መሆን አለበት የሚሉ ናቸው። በዚሁ እሳቤ መሰረት በምንግስት አካላት ክትትል እና ምርመራ የወንጀል ክስ ለዳኞች የሚቀርብበትና ዳኞችም ቢሆኑ ወንጀል መፈፀሙን ለማረጋገጥ ጠንካራ የማጣራት ሥራ የሚሰሩበት አካሄድ ነው። ይህም በብዙ የሕግ ጥናቶች  ‹‹Inquisitorial System Of Prosecution ›› እየተባለ የሚታወቀው አሰራር ነው።

በሁለተኛው አመለካከት ደግሞ ወንጀል ምንም እንኳን በእብረተሰቡ ወይም በአባላቱ ላይ የሚፈፀም ሕገ-ወጥና ተገቢ ያለሆነ ድርጊት ቢሆንም የምንግስት ሚና በዳይና ተበዳይ ናቸው የሚባሉትን ወገኖች በገለልተኝነት አይቶ ተገቢውን ማድረግ በመሆኑ ክሱ ሊቀርብ የሚገባው በተበዳዩ ወይም በእርሱ የቅርብ ዘመዶች ተፋራጅነት ነው። የመንግስትም ድርሻ ከዚህ እሰጣ እገባ ውስጥ እውነትን አንጥሮ ፍትሕ መስጠት ነው የሚሉ ሀሳቦች ለብዙ ምዕተ-ዓመታት ሲንፀባረቁ ቆየተዋል። ለዚህ ለሁለተኛው

አካሄድ መሠረት የሆነው በግል አቤቱታ መነሻነት የሚቀርበውን የወንጀል ክስ አመሠራረት የሚደግፈው የጥንቱ የሮማውያን የሕግ መርሆ ነው። የግል ተበዳዩች የሚያቀርቧቸው የወንጀል ክሶችም በዚህ አይነት ለንግስታቱ ወይም እነርሱ የዳኝነት ሥልጣን ለሚሠጡዋቸው ሰዎች እያቀረቡ ይታይ ነበር። ማስረጃ የማፈላለጉ የማቅረቡና በሚያቀርበው ማስረጃ ክሱን የማስረዳቱ ሸክም የሚወድቀው በራሱ በተበዳዩ ጫንቃ ላይ ነበር። በዚህ እሳቤ መነሻነት የወንጀል ጉዳይ በአመዛኙ በግለሰቦች በተለይም በግል ተበዳዩች ተፋራጅነት ለፍርድ ቤት የሚቀርብበት ሄደት ‹‹ Accusatorial System of Prosecution ›› እየተባለ የሚታወቀው ሥርዓት ነው።

በግል አቤቱታ ብቻ የሚያስቀጡ ወንጀሎች

የግል ባህሪ ያላቸው ወንጀሎች የተፈፀመበት ሰው ስለነዚህ ወንጀሎች ጉዳይ ለምርማሪ አካላት ሲመለክትና ወንጀል የፈፀመበት ሰው እንዲቀጣለት ሲጠይቅ የግል አቤቱታ ይባላል። የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 1 ላይ እንደተመለከተው የወንጀል ሕግ ዓላማ ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የአገሪቱን መንግስት የሕዝቦቹን የነዋሪዎቹን ሰላም ደህንነት ሥርዓት መብትና ጥቅም መጠበቅና ማስጠበቅ ነው። የወንጀል ሕግ ይህን ዓላማውን ተፈፃሚ የሚያደርገው ስለ ጠቅላላው ጥቅም በሚል ሕገወጥነቱና  አስቀጭነቱ በሕግ የተደነገገውን ድርጊት ፈጽሞ በተገኘ ሰው ላይ ነው። የወንጀል ድርጊት ሊፈጸም የሚችለው በሕግ የተከለከለውን በማድረግ (by Commission) ወይም በሕግ የታዘዘውን ባለማድረግ (by Omission) ነው። ስለዚህ ማንም ሰው በሕግ የተከለከለውን በማድረጉ ወይም በሕግ የታዘዘውን ባለማድረጉ ለጠቅላላው ማሕበራዊ ኑሮ በኋላፊነት ያስጠይቀዋል ማለት ነው። 

መንግስት በእዝብ ስም ሆኖ ለዜጎች ተወክሎ የወንጀልን ክስ እንዲያቀርብና ተከራክሮ እንዲያስቀጣ ዓላፊነት ሊወድቅበት የቻለው በዚህ ምክንያት ነው። ዳሩ ግን የጠቅላላውን ሕዝቦችና ነዋሪዎች ስላምና ፀጥታ የማያውኩ ወንጀሎች አሉ። እነዚህ ቀለል ያሉ ወንጀሎች ከሕብረተሰቡ ጥቅምና ደህንነት ይልቅ የተበዳዩን ግለሰብ ጥቅምና  ደህንነት ብቻ የሚመለከቱ  እንዲሁም የወንጀሉ አፈፃፀም የመጨረሻ ውጤት ከተጎዳው ሰው ጥቅምና ደህንነት በላይ ተሻግሮ በመንግስትና በነዋሪዎች መብትና ጥቅም ላይ ጉዳት አያስከትልም። ምንም እንኳን በጠቅላላው ተበዳዩ ቢስማማም ባይስማማም የወንጀል መርምራና ክስን መከታተል የመንግስት ኋላፊነት ቢሆንም በግል አቤቱታ ብቻ የሚያስቀጡ ወንጀሎች ከሕብረተሰቡ ጥቅምና ደህንነት ይልቅ የተበዳዩን ግለሰብ ጥቅምና ደህንነት የሚመለከቱ በመሆናቸው በሕጉ ልዩ ክፍል በተለይ በሚደነግገው መሠረት እንደዚህ ያለውን ክስ የግል ተበዳዩ ወይም ስለእርሱ ሆኖ የመክሰስ መብት ያለው ሰው7  የክስ አቤቱታውን ካላቀረበ በቀር በዐቃቤ ሕግም ቢሆን ክስ ሊቀርብ አይችልም።

የግል  ተበዳይ  በዳዩ  ተከሶ  በፍርድ  አደባባይ  እንዲቀጣለት  አቤቱታ  በቅድሚያ እንዲያቀርብ  ያስፈለገበት  ምክንያት  አንደኛ  ወንጀሉ የጠቅላላውን  የሕዝብ   ጥቅም  ስለማይጎዳ፤  ሁለተኛ  የግል ተበዳዩ  ምርመራ  እንዲጣራለትና ክስ

እንዲቀርብለት ስምምነቱን በአቤቱታው ሳይገልጽ በተከሣሽ ላይ ክስ ቢቀርብ በግል ተበዳዩ ማሕበራዊ ኑሮ ላይ ጉዳትን ስለሚያስከትልበት ነው። የግል ተበዳይ ሚስጥር አድርጎ ለመያዝ የሚፈልገው ጉዳይ ከእሱ ስምምነት ውጭ  ሙግቱ በፍርድ ቤት በሕዝብ ፊት በአደባባይ ቢሰማበትና ቢታወቅበት ሊደርስበት የሚችለው ጉዳት፣ የተፈፀመበት ወንጀል ካደረሰብት  ጉዳት ይልቅ ከፍተኛ ሊሆን ስለሚችል ነው። ለምሳሌ የግል ተበዳይ ባል ከሌላ ሰው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ቢፈጽምም የግል ተበዳይ በተፈፀመባት ያመንዝራነት ወንጀል ባሏን ከሳ ከማስቀጣት ይልቅ ይቅርታ አድርጋለት በትዳር አብሮ መቀጠልን ልትመርጥ ስለምትችል ነው። በግል አቤቱታ አቅራቢነት የወንጀል ምርመራ ሊጀመር ወይም ክስ ሊቀርብ የሚችለው በግል ተበዳዩ ፍላጎት ብቻ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። 

ጠቋሚው ሳይታወቅ በሚቀርብ የወንጀል ክስ እና በግል አቤቱታ አቅራቢነት ብቻ በሚያስቀጣ ወንጀል መካከል ግልጽ ልዩነት ያለ ሲሆን ጠቋሚው ሳይታወቅ በሚቀርብ የወንጀል  ክስ ማንም ሰው ማንነቱን ደብቆና  ሸሸጎ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ስለወንጀሉ አፈፃፀም በመረጃ መልክ ክስ ለምርማሪ አካላት የሚያቀርብበት ሥርዓት ነው። እንዲሁም ምርማሪ አካላት ከማይታወቅ ጠቋሚ የቀረበውን የወንጀል ጥቋማ መነሻ በማድረግ የወንጀል ምርመራ መጀመር ያለባቸው በግል አቤቱታ አቅራቢነት በሚያስቀጣ ወንጀል  (Compliant)  ላይ  ሳይሆን  ከፍ  ያለ የሕግ ጥሰት በሚፈፀምበት የወንጀል ክስ (Accusation) ላይ ብቻ መሆን አለበት። የማይታወቅ ጠቋሚ በግል አቤቱታ አቅራቢነት በሚያስቀጣ ወንጀል ላይ የሚያቀረበውን ጥቆማና ክስ ምርማሪ አካላት መቀበል የለባቸውም። ምክንያቱም  በወንጀል ሕግ አንቀጽ 212  መሠረት  በግል አቤቱታ  በሚያስቀጣ   ወንጀል   የግል ተበዳዩ  ወይም  ስለእርሱ ሆኖ የመክሰስ መብት ያለው ሰው የክስ አቤቱታውን ካላቀረበ  በቀር  በዐቃቤ ሕግም ቢሆን ክስ ሊቀርብ አይችልም ተበሎ ከተደነገገው መሠረታዊ ሕግ ጋር ስለሚጋጭ ነው። በምርማሪ አካላት ሁልጊዜ መረሳት የሌለበት ነገር በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ አንቀጽ 13 መሠረት በግል አቤቱታ  የሚያስቀጣ  ወንጀል በተፈጸመ ጊዜ የመጀመሪያውን የወንጀል ምርመራ ለመቀጠል የግል  ተበዳዩ  አቤቱታ  ማቅረቡ  መሟላት  ያለበት  ቅድመ  ሁኔታ  መሆኑን  ነው።

በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ ልዩ ክፍል ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ድንጋጌዎች ‹‹ማንም ሰው - - - - - ወንጀል የፈፀመ እንደሆነ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት በ- - - - - ቀላል እስራት ወይም መቀጮ ይቀጣል››  ሲሉ ይደነግጋሉ።  በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስቀጣ ወንጀል ከሌላ በማንኛውም ሰው አቅራቢነት ከሚያስቀጣ ወንጀል ጋር በጣምራ /በተደራራቢነት/ ቢፈጸምና የግል አቤቱታ አቅራቢ ባይኖር ምርማሪ አካላት በማንኛውም ሰው አቅራቢነት በሚያስቀጣ ወንጀል ብቻ ነው ምርመራ ማጣራት ያለባቸው። ፍርድ ቤት እንደተደራራቢ ወንጀል በመቁጠር ለቅጣት ማክበጃ ሕጋዊ ምክንያት አድርጎ መውሰድ አይችልም።

የተፈፀመው ወንጀል የእጅ ተፍንጅ ወንጀል (Flagrant Offence) የሆነ እንደሆነ መጀመሪያ በግል ተበዳዩ አቤቱታ ካልቀረበ በስተቀር የፍርድ ቤት የመያዣ ትህዛዝ ሳይኖር አጥፊው የሚያዝ አይመስልም። እጅ ተፍንጅ የተፈፀመ ወንጀል የሚባለው አድራጊው ወንጀሉን ሲሰራ የተያዘ ሲሆን ወይም ለመስራት ሲሞክር ወይም የወንጀሉን ሥራ እንደፈፀመ ወዲያውኑ የተያዘ ሲሆን ነው። ወንጀል አድራጊው የወንጀሉን ሥራ ከፈፀመ በኋላ ወዲያውኑ ሲሸሽ ምስክሮቹ ወይም ሕዝቡ የተከታተሉት ወይም የሕዝቡ ጩሆትና እሪታ የተሰማ እንደሆነ ወንጀሉ የእጅ ተፍንጅ መሰል (Quasi-Flagrant) እንደሆነ ይቆጠራል በማለት ይደነግጋል። ከድንጋጌው መረዳት የሚቻለው እጅ ተፍንጅ ወንጀል ማለት አንድ ሰው ወንጀሉን በመፈፀም ላይ እንዳለ ወይም ለመስራት ሲሞክር ወይም ወንጀሉ ከተፈፀመ በኋላም ለድርጊቱ እጅግ ቅርብ በሆነ ጊዜና ሁኔታ ሲያዝ ነው። 

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 21 ንዑስ-አንቀጽ 1 ‹‹ በአንቀጽ 19 እና 20 በተዘረዘሩት ወንጀሎች መሠረት ወንጀሉ የክስ አቤቱታ ሳይቀርብ ክስ ሊቀርብበት የማይችል ካልሆነ በቀር ክስ ወይም የክስ አቤቱታ እንዲቀርብበት አስፈላጊ ሳይሆን ክስ ለማቅረብ ይቻላል። የዚሁ አንቀጽ ንዑስ-አንቀጽ 2 እንደዚህ ያለው ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ፍርድ ቤት የሚሰጠው የመያዣ ትህዛዝ ሳይኖር በአንቀጽ 49ና በተከታዩቹ  አንቀጾች መሠረት ወንጀለኛውን ለመያዝ ይቻላል ›› ተብሎ ተመልክቷል። ከንዑስ-አንቀጽ(1) የሕግ ድንጋጌ መንፈስና ይዘት መገንዘብ የሚቻለው የእጅ ተፍንጅ ወይም የእጅ ተፍንጅ  መሰል ወንጀሎች በተፈጸፀሙ ጊዜ ወንጀሉ በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስቀጣ ወንጀል ከሆነ ተበዳዩ በፍላጎቱ አቤቱታ ካላቀረበ በቀር ዐቃቤ ሕግ የወንጀል ክስ ሊያቀርብ የማይችል ሲሆን ነገር  ግን የተፈፀመው ወንጀል በማንኛውም ሰው አቅራቢነት የሚያስቀጣ ወንጀል ከሆነ፣ ጠቋሚ ወይም የግል ተበዳይ  የክስ  አቤቱታ  ሳያቀርብ  ዐቃቤ  ሕግ  የወንጀል  ክስ  ለማቅረብ  ይችላል።

በሌላ በኩል በንዑስ-አንቀጽ (2) ውስጥ ‹‹ እንደዚህ ያለው ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ . . . . ››  የሚለው የሕጉ ሐይለ ቃል ስለ እጅ ተፍንጅ ወይም የእጅ ተፍንጅ መሰል ወንጀሎች ወይም ባልታወቀ ጠቋሚ ወይም የክስ አቤቱታ አቅራቢ ሳይኖር ክስ ሊቀርብባቸው የሚችለውን ክሶች ማለቱ ለመሆኑና ላለመሆኑ ግልጽነት የሚጎለው ስለሆነ ድንጋጌው ለተለያየ ትርጉም በር የከፍታል። የእጅ ተፍንጅ ወንጀል በተፈጸመ ጊዜ የወንጀል ድርጌት ፈጻሚውን እጅ ተፍንጅ በመያዝ ክሱ በፍርድ ቤት መሰማት ሊጀመር ይችላል። ነገር ግን ተፈጸመ የተባለውን የወንጀል አይነት መለየት አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም የተፈጸመው የእጅ ተፍንጅ ወንጀል በግል አቤቱታ አቅራቢነት ብቻ የሚያስቀጣ ወንጀል ሲሆን ያለ ፍርድ ቤት ትህዛዝ (Arrest Without Warrant) ወንጀለኛው እንዲያዝና እንዲቀጣ ማድረግ በግል አቤቱታ አቅራቢነት ለሚያስቀጣ ወንጀል ተበደልኩ ባይ (ከሣሽ) በመጀመሪ አቤቱታ ካላቀረበ በዐቃቤ ሕግም ቢሆን ክስ ሊቀርብ አይችልም ተበሎ ከተደነገገው መሠረታዊ ሕግ ጋር የሚፋለስ ይሆናል። ሌላው የእጅ ተፍንጅ ወንጀል ሲፈጸም ወንጀለኛው ያለ ፍርድ ቤት ትህዛዝ እንዲያዝ የተደረገበት ዋና ምክንያት የሕዝብ ሰላምና ደሕንነት በባሰ ሁኔታ ሳይታወክ ወንጀለኛውን ወዲያውኑ ለመያዝ እንዲቻል ታስቦ ነው። ሆኖም በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስቀጣ ወንጀል በተፈጸመ ጊዜ የሕዝብን ሰላምና ጸጥታ አይታወከም። በአጠቃላይ በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስቀጣ የእጅ ተፍንጅ ወንጀል በተፈጸመ ጊዜ ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትህዛዝ ወንጀለኛው እንዲያዝ ማድረግና መፍቀድ በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስቀጡ ወንጀሎች የተለዩበትንና የቆመበትን የሕግ መርህ ትርጉም  አልባ  ያደረገዋል።  

በግል አቤቱታ የሚያሰቀጣ የእጅ ተፍንጅ ወንጀል የፈጸምን ወንጀለኛ በቀላሉ ለመያዝ እንዲያመች በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 14 በተገለጸው መሠረት አቤቱታ በጽሁፍ ማቅረብ አያስፈልግም። መርማሪ አካላት የግል ተበዳዩ በቃሉ

ያቀረበውን አቤቱታ በኋላ በጽሑፍ መዝግቦ ከመርመራ መዝገቡ ውስጥ ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል። የወንጀል ሕግ አንቀጽ 211(1)ና 212ን በጋራ አጣምረን ስናነብ በግልጽ መረዳት የምንችለው የግል አቤቱታ መቅረቡ የሚያስከትለው የሕግ ውጤት  መርማሪ አካላት ምርመራ እንዲ ጀምሩና ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሰርቱ ማድረግ ነው። ስለዚህ በግል አቤቱታ አቅራቢነት   የሚያስቀጣ ወንጀል በተፈጸመ ጊዜ በፍርድ ቤት ተከራክሮ የቅጣት ውሣኔ ለማሰጠት የሚችለው በመርህ ደረጃ ዐቃቤ ሕግ ቢሆንም በሕግ በተለየ ሁኔታ በግልጽ ተደንግጎ ሲገኝ የግል ተበዳይ የወንጀል ክስ የማቀረብ መብት እንዳለው መረዳት ይቻላል።

በቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 217 ስያሜ ‹‹ በግል ከሣሽ አቤቱታ ስለሚቀርብ የወንጀል ክስ » የሚል የነበረ ሲሆን ከግለሰቦች የግል አቤቱታ ሊቀርብ ከሚችል በቀር በቀጥታ የወንጀል ክስ ለማቅረብ ስለማይቻል ስያሚው ተሰርዞ በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 212 « በግል አቤቱታ ብቻ የሚያስቀጡ ወንጀሎች » በሚል ድንጋጌ ተተክቷል። በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስቀጣ ወንጀል በተፈጸመ ጊዜ የግል ተበዳዩ የግል ክስ በፍርድ ቤት አቀርቦ የወንጀል ሙግቱን በኋላፊነት ተከታትሎ ሊፈጽም ይችላል። ይህ ሊሆን የሚችለው ዐቃቤ ሕግ ተከሣሽን ጥፋተኛ ለማደረግ የሚያስችል በቂ የሆነ ማስረጃ የሌለ ስለሆነ ክስ አይቀርብም የማለት ውሣኔ ሲሰጠ ነው። ዐቃቤ ሕግ በተቻለው መጠን የግል ተበዳይ መብት ጠባቂና ደጋፊ ሆኖ ይሰራል። የግል ተበዳዩ በወንጀል ጉዳይ የግል ክስ ለማቅረብ የሚችለው ይህ አፈፃፀም ሊጠበቅ በማይችልበት ሁኔታና ጊዜ ብቻ ነው። ስለዚህ በግል አቤቱታ ብቻ የሚያስቀጡ ወንጀሎች የግል ተበዳዮች ፍትሕ ለማገኝት ጉዳዩን በሚያንቀሳቅሱበት ጊዜ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 213ና በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 13ና ተከታዩቹ መሠረት ክሱን መከታተል ይኖርባቸዋል። አካለ መጠን ያለደረሰ ወጣት የፈፀመው ወንጀል ከአስር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ወይም በሞት የሚያስቀጣ ካልሆነ በቀር በዐቃቤ ሕግ ክስ ሊመሠረትበት አይችልም። 

የቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 218 ስያሜ ‹‹ የክስ አቤቱታ የማቅረብ ተገቢ መብት ›› የሚል ሲሆን የግል ጠባይ ባላቸው ወንጀሎች የግል አቤቱታ ማቅረብ የሚችሉት በሕጉ መሰረት ችሎታ ያላቸው ሰዎች መሆናቸውንና ተበዳዩቹ ችሎታ የሌላቸው  ሲሆኑ  ሕጋዊ  ወኪሎቻቸው ወይም  ሞግዚቶቻቸው  እንዲሆኑ የሚደነግግ ነበር። ሌላው የቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 219 ስያሜ « በሕብረት የሚቀርብ የክስ አቤቱታ » የሚል ሲሆን የግል ጠባይ ያለው ወንጀል ቁጥራቸው ከአንድ በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ በሚፈጸምበት ጊዜ እያንዳንዳቸው በግል ወይም ሁሉም በሕብረት አቤቱታ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ይደነግግ ነበር። ሌላው የቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 221 ስያሜ «የቀረበውን ክስ ስለመተው » የሚል ሲሆን ከሣሽ የግል አቤቱታ ካቀረበ በኋላ ክሱ እንዳይቀጥል ማድረግ እንደሚችል የሚገልጽ ነው። በሌላ አነጋገር ከሣሽ በወንጀል አድራጊው ላይ የተጀመረው ምርመራ እንዲቋረጥ ወይም ፍርድ ቤት እንዳይፈረድበት የሚያደርግ የእርቅ ማመልከቻ ጽፎ ማቅረብ እንደሚችል ይደነግግ ነበር። ሌላው የቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 222 ስያሜ  «ክስ የማይከፋፈል ስለመሆኑ » የሚል ሲሆን የግል ጠባይ ባለው ወንጀል ተካፋዮቹ ከአንድ በላይ ሲሆኑ ከእነርሱ መካከል በአንዱ ላይ ብቻ የግል

አቤቱታ ማቅረብ ሁሉንም እንደመክሰስ የአንዱን ክስ መተው ደግሞ የሁሉንም ወንጀል አደራጊዎች ክስ እንደመተው የሚቆጥር  ድንጋጌ ነበር። ሆኖም ከላይ የተመለከቱት ድንጋጌዎች በይዘታቸው ሥነ-ሥርዓት ነክ ሕጎች ስለሆኑ ትክክለኛ ቦታቸው ከወንጀል ሕጉ (Substantive Law) ይልቅ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ (Procedural Law) ለመሆኑ ታምኖበት በአዲሱ የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ ውስጥ ሳይካተቱ ቀርተዋል ። ነገር ግን ከላይ የተመለከቱት ድንጋጌዎች እረቂቁ የወንጀል የሥነ-ሥርዓት ሕግ ታውጆ ተፈፃሚ ሲሆን አብረው ተግባራዊ የሆናሉ ቢባለም እስካሁን የሥነ-ሥርዓት ሕጉ ያልወጣ በመሆኑ የሕግ ማዕቀፎቹ በወንጀል የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ክፍተት ፈጥረዋል ወይም የነበራቸው ሚና ቀሪ ሆኗል ማለት ይቻላል።

በወንጀል ሕግ አንቀጽ 213 መሠረት ማንም ሰው የግል አቤቱታ ማቅረብ ያለበት ተበዳዩ የወንጀሉን ድርጊት ወይም የወንጀል አድራጊውን ማንነት ካወቀበት ቀን ጀምሮ እስከ ሦስት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። ተበዳዩ የግል አቤቱታውን ለማቅረብ ያልቻለው የግል አቤቱታ ለማቅረብ በማያስችል ጉልሕ በሆነ ምክንያት ካልሆነ በቀር ይህ ጊዜ ካለፈ የግል አቤቱታ ለማቅረብ እንዳለፈለገ ይቆጠራል። ተበዳዩ የግል አቤቱታውን ለማቅረብ ያልቻለው በበቂ ምክንያት ከሆነ ጊዜው መቁጠር የሚጀምረው ያጋጠመው ችግር ከተወገደበት ጊዜ ጀምሮ ነው። ነገር ግን ወንጀሉ ቀላል ቢሆንም ድርጊቱ የተፈፀመው በመንግስት ሐብትና ንብረት ላይ ሲሆን ክሱ የመንግስት ክስ ስለሚሆን የይርጋው ጊዜ አቆጣጠር የተለየ የሆናል። የወንጀል ክስ የማቀረቢያ ዘመን መቁጠር የሚጀምረው መቼ ነው፣ የይርጋ ዘመኑ መቁጠር የሚያቋረጠው በምን ሁኔታ ነው የሚለው ፍሬ-ነገር አከራካሪ የነበረ ሲሆን ጉዳዩ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቀርቦ ውሣኔ ያገኘ በመሆኑ በማሳያነት ቀርቧል።

ማሳያ-1(Case-1) 

በአመልካች እነ ሀይላይ ተክሉ ሁለት ሰዎች እና በተጠሪ የመቀሌ ከተማ ሰሜን ምድብ ዐቃቤ ሕግ መካከል በሰበር መዝገብ ቁጥር 77097 በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጥቅምት 20 ቀን 2005 ዓ/ም በተደረገ የወንጀል ክርክር ጉዳይ ዐቃቤ ሕግ በአመልካቾች ላይ ያቀረበው ክስ የክስ ማቀረቢያ ጊዜ በይርጋ ይታገዳል ወይስ አይታገደም የሚለው ጭብጥ የሕግ ክርክር አስነስቶ ነበር። ዐቃቤ ሕግ አመልካቾችን ጨምሮ በ 8 ተከሳሾች ላይ ነሐሴ 11 ቀን 2002 ዓ/ም ያቀረበው ክስ፡ ተከሳሾች በትግራይ መንገዶች ባለሥልጣን የመኪና ግዥ የጨረታ የቴክኒክ ኮሚቴ ሆነው ሲሰሩ መሥሪያ ቤቱ ያወጣውን ባለ 11 ቴክኒካል መስፈርቶችን ወደ ጎን በመተው ከተጠየቀው መለኪያ በታች ያቀረበውን ሐግቤስ የተባለው ተወዳዳሪ ድርጅት ቅናሽ ዋጋ አቅርቧል በሚል ጨረታውን እንዲያሸንፍ አድርገው መስፈርት ያላሟላ መኪና እንዲገዛ በማድረጋቸው መኪናው የሚፈለገውን አገልግሎት ሳይሰጥ የተበላሸ በመሆኑ መንግሥት አስፈላጊ ያልሆነ ወጪ እንዲያወጣ በማድረግ በወ/ሕ/አንቀጽ 420/2/ የተደነገገውን በመተላለፋቸው ተከሰዋል የሚል ነው፡፡

ተከሳሾችም ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ፡- ከሳሽ ጠቅሶ ያቀረበብን የወንጀል ህግ አንቀጽ 420 /2/ በእስራት የሚያስቀጣ ሲሆን የእስራት ጊዜውም በወንጀል ህግ አንቀጽ 106(1) ሥር እንደተደነገገው ከአስር ቀን እስከ ሶስት ዓመት በመሆኑና የቀላል እስራት ይርጋ ዘመንም በወ/ህ/አንቀጽ 217(1)(ሠ) መሰረት አምስት ዓመት በመሆኑ ከሳሽ የወንጀሉ ድርጊት ተፈጽሟል በማለት በክሱ ከጠቀሰበት 29/04/1997 ጀምሮ ክሱ እስከቀረበበት እስከ 11/12/2002 ዓ/ም ድረስ አምስት ዓመት ከስምንት ወር ያለፈ በመሆኑ ክሱ በይርጋ የሚታገድ ነው ሲሉ ተከራከረዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ የቀረበውን የይርጋ መቃወሚያ በተመለከተ በሰጠው መልስ፡- ተከሳሾች የተከሰሱበት ወንጀል እስከ ሶስት ዓመት የሚያስቀጣ ቢሆንም ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው የታወቀው በ29/04/1997 ዓ/ም ሳይሆን በ14/04/2001 ዓ.ም. ነው፡፡ በክሱ የተጠቀሰው ቀን 29/4/1997 ዓ.ም. ተከሳሾች የሚሰሩበት መ/ቤት ጨረታ ያወጣበት ሲሆን ጉዳዩ የታወቀበት 14/04/2001 ዓ.ም. በመሆኑ ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ሲቆጠርም የይርጋ ጊዜው ያላለፈ ስለሆነ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ተቀባይነት የለውም ሲል ተከራክሯል፡፡ የወረዳው ፍርድ ቤትም ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾች ወንጀሉን የፈጸሙት በ29/04/1997 ዓ/ም ሲሆን የወንጀሉ ድርጊት የታወቀው ደግሞ በ14/4/2001 ዓ/ም ነው ቢልም የክልሉ ኦዲተር ለክልሉ ፍትሕ ቢሮ በ24/9/2001 ዓ.ም. የጻፈው ደብዳቤ በ14/4/2001 ዓ/ም መሆኑን አይገልጽም፣ በክሱ ወንጀሉ ተፈጽሟል የተባለው በ29/04/1997 ዓ/ም በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ ክሱን መመስረት የሚገባው በ29/04/1997 ዓ/ም ነው፣ ተከሳሾች የተከሰሱበት ወንጀልም እስከ ሶስት ዓመት ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን ከአንድ ዓመት በላይ የሚያስቀጣው ቀላል እስራትም የይርጋው ዘመን አምስት ዓመት በመሆኑ ወንጀሉ ከተፈጸመበት ከ29/04/1997 ዓ/ም ጀምሮ ክሱ እስከቀረበበት ድረስም ያለው ጊዜ ሲቆጠር ከአምስት ዓመት በላይ ስለሆነ ክሱ በወ/ህ/አንቀጽ 216 (ሠ) መሰረት በይርጋ የሚታገድ ነው ብሏል፡፡ 

ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት የመቀሌ ከተማ ማዕከላዊ ፍርድ ቤትም ይግባኝ ባይ ያቀረበውን ይግባኝ በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/195(1) መሰረት በመሰረዙ ይግባኝ ባይም በሥር ፍርድ ቤቶች ብይን ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በሚል የሰበር አቤቱታውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበ ሲሆን ችሎቱም የግራ ቀኙን ወገኖች ካከራከረ በኋላ በሰጠው ፍርድ፡- በዚህ ጉዳይ ወንጀሉ ተፈጽሟል የተባለው በ29/04/1997 ዓ.ም. በመሆኑ ክሱ እስከቀረበበት እስከ 11/12/2002 ዓ/ም ያለው ጊዜ የሚቆጠር ነው፡፡ ሆኖም አመልካቾች ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ፖሊስና ዐቃቤ ህግ ምርመራ ማጣራት የጀመሩት በ14/04 2001 ዓ.ም. መሆኑን የምርመራ መዝገቡ የሚሳይ ሲሆን የምርመራው መጀመር የይርጋውን መቆጠር የሚያቋርጥ ስለመሆኑ የወንጀል ህግ አንቀጽ 221 ስለሚደነግግ አመልካች ያቀረበው ክስ የክስ ማቅረቢያ ጊዜ ያላለፈበት በመሆኑ በይርጋ የሚታገድ አይደለም በሚል የስር ፍርድ ቤቶችን ብይን ሽሯል፡፡

አመልካቾችም በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈጽሟል ሲሉ የሰበር አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡ ሲሆን በዋናነት የጠቀሱዓቸው የቅሬታ ነጥቦችም፡- ፖሊስ በተጠርጣሪዎች ላይ ምርምራ ለማድረግ ከፍርድ ቤት የመያዣ ወይም የብርበራ ትዕዛዝ ሳያገኝ የምርምራ መቅደም በ14/04/2001 ዓ/ም መክፈቱን በመግለጹ ብቻ የይርጋ መቆጠርን ያቋርጠዋል በሚል ሰበር ሰሚው ችሎት መወሰኑ በወ/ህ/አንቀጽ 219 እና 221 የተደነገገውን የሚቃረን ነው፣ ፖሊስ በአመልካቾች ላይ ምርመራ ጀምሯል ሊባል የሚችለውም በጉዳዩ ላይ የተከሳሽነት ቃላችንን እንድንሰጥ ደብዳቤ ከተጻፈልን ከ27/05/2002 ዓ.ም. ጀምሮ ስለሚሆን ወንጀሉ ተፈጸመ ከተባለበት ከ29/04/1997 ዓ/ም ጀምሮ ደብዳቤው እስከተጻፈበት ድረስም ያለው ጊዜ ሲቆጠር አምስት ዓመት ያለፈው ስለሆነ ክሱ በይርጋ የሚታገድ ነው የሚሉ ናቸው ፡፡ ተጠሪው በበኩሉ በጉዳዩ ላይ መልሱን እንዲያቀርብ ታዞ መጥሪያ የደረሰው ቢሆንም ቀርቦ መልስ ያልሰጠ በመሆኑ መልስ የመስጠት መብቱ ታልፏል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም፡- በአመልካቾች ላይ የቀረበው ክስ በይርጋ የሚታገድ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል፡፡ ዐቃቤ ሕግ አመልካቾች የተጣለባቸውን የስራ ኃላፊነት ባለመወጣት በመንግሥት ጥቅም ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል በወንጀል ህግ አንቀጽ 420(2) ሥር ክስ ያቀረበባቸው ሲሆን በዚህ ድንጋጌ ጥፋተኞች ሆነው ቢገኙ ሊወሰንባቸው የሚችለው ቀላል እስራቱና መቀጮው በህጉ እስከተወሰነው ከፍተኛው ቅጣት ሊደርስ እንደሚችል ከድንጋጌው መገንዘብ የሚቻል ነው፡፡ ቀላል እስራትም ከአስር ቀን እስከ ሶስት ዓመት የሚያስቀጣ መሆኑን የወንጀል ህግ አንቀጽ 106(1) የሚደነግግ ሲሆን በወንጀሉ ከባድነት የተነሳ በህጉ ልዩ ክፍል ተደንግጎ ሲገኝ ወይም በቀላል እስራት የሚያስቀጡ ተደራራቢ ወንጀሎች ሲኖሩ ወይም ወንጀለኛው በተደጋጋሚ ሲቀጣ ቀላል እስራቱ አስከ አምስት ዓመት ሊደርስ እንደሚችል የድንጋጌው 2ኛው ፓራግራፍ ያመለክታል፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ ቀላል እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል የክስ ማቅረቢያ የይርጋ ዘመን አምስት ዓመት መሆኑ በወንጀል ህግ አንቀጽ 217(1)(ሠ) ስር የተደነገገ ሲሆን የይርጋ ዘመኑም መቆጠር የሚጀምረው ጥፋተኛው የወንጀሉን ድርጊት ከፈጸመበት ቀን አንስቶ ስለመሆኑ የወንጀል ህግ አንቀጽ 219(2) ይደነግጋል፡፡ ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ አመልካቾች ወንጀሉን ፈጽመዋል በሚል በክሱ የተጠቀሰው 29/04/1997 ዓ/ም ሲሆን ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ክሱ እስከቀረበባቸው እስከ 11/12/2002 ዓ/ም ያለው ጊዜ ሲቆጠርም የክስ ማቅረቢያው አምስት ዓመት ማለፉ ግልጽ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ወንጀሉ ተፈጽሟል የተባለው በ29/04/1997 ዓ/ም ቢሆንም ወንጀሉ መፈጸሙ የታወቀውና ፖሊስ ምርመራ እንዲያጣራባቸው የተደረገው በ14/4/2001 ዓ/ም ስለመሆኑ በስር ፍርድ ቤቶች በተደረገው ክርክር የተረጋገጠ ፍሬ ነገር ነው፡፡ ፖሊስ በአመልካቾች ላይ ከ14/04/2001 ዓ/ም ጀምሮ ምርመራ ማድረጉ እስከተረጋገጠ ድረስም በወንጀል ህግ አንቀጽ 221 እንደተደነገገው የይርጋ ዘመኑን መቆጠር የሚያቋርጠው ሆኖ ይርጋው እንደ አዲስ መቆጠር የሚጀምር ይሆናል፡፡ በመሆኑም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በአመልካቾች ላይ ፖሊስ ምርመራ ማጣራት የጀመረው በ14/4/2001 ዓ/ም በመሆኑ ክሱ በወ/ህ/አንቀጽ 221 መሰረት በይርጋ የሚታገድ አይደለም በሚል የሰጠው ፍርድ የህግ ስህተት ያልተፈጸመበት በመሆኑ ፀንቷል ሲል ውሣኔ ሰጥቶ ጉዳዩን ቋጭቶታል።

የግል አቤቱታ ከቀረበ በኋላ መርማሪ አካላት በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ አንቀጽ 22ና ተከታዩቹ መሠረት የወንጀል ምርመራቸውን ያከናውናሉ። ከመርማሪ አካላት የሚቀርበውን የምርመራ ውጤት መነሻ በማድረግ ዐቃቤ ሕግ አጠራጣሪ በሆኑ ጉዳዩች ምርመራ እንዲቀጥል ያዛል ወይም ካልመሰለው የፖሊስ የምርመራ መዝገቡን በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ ቁጥር 39  መሠረት ይዘጋል።  ዐቃቤ ሕግ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ ሲዘጋ የዘጋበትን የውሣኔ ግልባጭ ለበላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ለግል ተበዳይ ያለ እንደሆነ እና ምርመራውን ላደረገው ፖሊስ መላክ አለበት (አንቀጽ 39/3/)። ዐቃቤ ሕጉ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ አንቀጽ42 መሠረት የሚከለክለው ሌላ ነገር ከሌለ በቀር አያስከስስም የማለት ውሣኔ ይሰጣል። ዐቃቤ ሕግ ክስ ሊያቀርብ የሚችለው የግል ተበዳይ ክስ እንዲቀርብለት የፈለገ እንደሆነ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ የግል ተበዳዩ ክሱ እንዲቋረጥ ቢፈለገ ይህን መብቱን ተፈፃሚ ለማድረግ የሚደግፈው የሕግ ማዕቀፍ የለም። በሌላ በኩል የግል ተበዳዩ ክሱ እንዲቋረጥ ያቀረበውን አቤቱታ ተከሣሽ በመቃወም ክሱ መቋረጥ የለበትም በማለት መከራከር የሚችል አይመስልም። ተከሣሽ በክሱ መቋረጥ ምክንያት መዝገቡ ከሚዘጋ ይልቅ ተከራክሮ በፍርድ አደባባይ ነፃ መባልን ቢፈልግ ክሱ እንዳይቋረጥ የሚያደርግበት የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ ተገቢነት የለውም።   

በሰንጠረዥ 3 ፎርም 5ን መሠረት በማድረግ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 43 በሚያዘው መሠረት ዐቃቤ ሕግ ክስ አይቀርብም ያለበት ውሣኔ በጽሁፍ ሆኖ  ከነ ሕጋዊ ምክንያቱ የግል ክስ ለማቅረብ መብት ለተሰጣቸው ሰዎች መግለጽ አለበት። ዐቃቤ ሕግ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 42/1/ ከ(ለ) እስከ (መ) የተመለከቱትን ድንጋጌዎች መነሻ በማድረግ በግል አቤቱታ በሚያስቀጡ ወንጀሎች ላይ ክስ ላያቀርብ ይችላል። በዚህ ጊዜ ልክ እንደሌላው የወንጀል ክስ ውሣኔው የመጨረሻ ስለሚሆን የግል ተበዳይ የግል ክስ ማቅረብ አይችልም። ዐቃቤ ሕግ ተከሣሽን ጥፋተኛ ለማድረግ በቂ ማስረጃ የለም በማለት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 42(1)(ሀ) መሠረት  ክስ ለማቅረብ ባይፈልግ የግል ተበዳይ የግል ክስ የማቅረብ መብት አለው። የግል ተበዳይ የግል ክስ ለማቅረብ የሚችለው በቅድሚያ ዐቃቤ ሕጉ ክስ አላቀርብም በማለት የሰጠው ውሣኔ እና የግል ክስ እንዲያቀርብ በጽሁፍ የፈቀደለትን ማስረጃ ሲይዝ ነው። ይህ የጽሁፍ ማስረጃ ይዘቱ የሚገልፀው ዐቃቤ ሕግ በተፈፀመው ወንጀል ክስ አለማቅረቡን እና የግል ከሣሽ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 44(1) መሠረት በራሱ ሙግቱን ሊመራና ይህንንም ሲፈጽም ለሚደርስበት የኪሣራ ወጪ ኃላፊነቱን የሚወስደው እራሱ መሆኑን ነው።  እንዲሁም  የግል  ከሣሽ  በክስ ማመልከቻው ተከሣሽ  ተላልፎታል  በማለት  የጠቀሰው ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ፍቃድ ከሰጠው ወንጀል ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ማረጋገጥ አለበት። ይህ ሲባል ግን ዐቃቤ ሕግ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 113(1) መሠረት ባማራጭ የሚቀርቡ ክሶችን ከማቅረብ የሚያግደው ነገር የለም። ሁሉም ወንጀሎች ግን በግል አቤቱታ የሚያስቀጡ መሆን አለባቸው። ስለዚህ የግል ክስ ለማቅረብ የሚፈቅደው ማስረጃ ተከሣሽ ባማራጭ በሚያስከስሰው ወንጀል ላይ ገደብ የሚጥል መሆን የለበትም።  

Download this Article with full Citation

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የኮንስትራክሽን መብቶች (Claims) ምንነት እና የሚስተዋሉ ችግሮች
Status and Application of Juvenile Related Interna...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 28 March 2024