የኢትዮጵያ የይቅርታ ሕግ አንዳንድ ነጥቦች
“…ይቅርታ ይደረግልን አዲስ የኢትዮጵያ ባህል ነው፡፡”
የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕ/ት ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማሪያም
መግቢያ
ይቅርታ በእለት ተእለት እንቅስቃሴችን ውስጥ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው እና ለማኅበራዊ ህይወታችንም ጥሩ መሆን እንዲሁም መልካም መስተጋብር ጉልህ ሚና እንደአለው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
ለማስረጃ ያህል ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታወች ላይ መገፋፋት ብሎም ቀለል ያሉ ጉዳቶች /Tolerable trespass/ በፍ/ሕ/ቁ 2039(ሠ) እንደተቀመጠው በአብዛኛው በይቅርታ የሚታለፉ ጉዳዮች ናቸው፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በማኅበራዊ ህይወት ውስጥ የሚከሰቱ በይቅርታ የሚታለፉ መስተጋብሮችን መዳሰስ ባይሆንም ይቅርታ ምን ያህል ዋጋ ያለው ነገር መሁኑን ጠቆም ለማድረግ ነው፡፡
ይቅርታ በአለማችን ጥቅም ላይ ዋለ የሚባልበት ጊዜ ረዘም ያለ ሲሆን በጥንታዊ ሮማዊያን ሥልጣኔ በተለይ ደግሞ በጁሊየስ ቄሳር የሥልጣን ዘመን በሰፊው ምኅረት በሚል ስያሜ ይሠራበት ነበር ይህም ይቅርታ በሮሜ ግዛት ወንጀል ለፈጸመ ሰው የሚደረግለት ምኅረት/Clemency/ ወይም ርህራሄ ነበር፡፡ ይቅርታ /Pardon/ በዘመናዊ መንግሥት በታሪክ ተመዝግቦ የሚገኘው ግን በአንግሎ ሳክሶን ዘመን በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ በወቅቱ የነበረውን ዘፈቀዳዊ አሠራር ብሎም ተራና ተልካሻ ምክንያቶች ለመቅረፍ ታዲያ የእንግሊዝ ፓርላማ እ.ኤ.አ በ1389 ከባድ ወንጀል፤ የወንጀሉን ዝርዝር እና የጥፋቱ ዝርዝር ተጽፎ ካልቀረበ ይቅርታ አንዳይደረግ በወቅቱ አዋጅ ታውጆ ነበር፡፡
ይቅርታ በወንጀል ሕግ ፍልስፍና /Penal jurisprudence/ ላይም ከፍተኛ ሽፍን ያለው ሲሆን ይኸውም አንድ ሰው ወንጀል ሰርቶ ከተፈረደበት ፍርድ በሙሉ ወይም በከፊል አግባብ ባለው አካል ቀሪ ሲሆንለት ነው፡፡
ዛሬ ዛሬ በአብዛኛው የዓለም ሀገራት ይቅርታ ተግባራዊ የሚደረገው ግለሰቦች በህብረተሰቡ ዘንድ ጥሩ አክብሮት እንዲሁም ተሰሚነት ሲኖራቸው ወይም የሚገባቸው ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ይቅርታ በሀሰት ተፈርዶባቸው ለታሰሩና ይቅርታ ይደረግለን ብለው ለሚጠይቁ ሰዎች እንደሆነ አንዳንድ ጹሑፎች ይጠቁማሉ፡፡
በተቃራኒው ደግሞ ከአንዳንድ ሀገራት ተሞክሮ እንደምንረዳው ይቅርታ ማድረግ ጥፋትን እንደማመን ይቆጠራል ስለሚባል (pardon tantamount admission of guilt)፤ ይቅርታ የሚነፈግበት ሁኔታ አለ ይህም በአሜሪካን በታወቀ የፍርድ ቤት ጉዳይ Burdick v. United states ተረጋግጧል፡፡
በመጨረሻም በዚህ ጽሑፍ የይቅርታ ትርጉም፤ የሌሎች ሀገራት ልምዶች እንዲሁም የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ እና የይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁ.840/2006 ዓ.ም በስፋት እናያለን፡፡
የይቅርታ ትርጓሜ
ይቅርታ የሚለው ቃል ሣህል ከሚለው ከግዕዙ ስርወ ቃል የተገኘ ሲሆን ይቅር በለን ወይም ምኅረት ስጠን ማለት ነው፡፡ የእንግሊዘኛው አቻ ቃል “ፓርደን/Pardon/” ሲሆን ፔርዱኔሬ/perdonare/ ከሚለው ላቲን የመጣ ሲሆን የቀጥታ ትርጓሜውም በነጻ መሳናበት ወይም በወንጀል ጥፋተኛ የሆነ ሰው ቅጣቱን መተው ወይም ተግባራዊ አለማድረግ ብሎም ምኅረት ማድረግን ይጨምራል፡፡
በተመሳሳይ ይቅርታ ሚለውን ቃል ታዋቂው Black’s law dictionary 9ኛ ዕትም ላይ“Pardon is the act or an instance of nullifying punishment or other legal consequence of a crime.” በማለት ትርጉም ለመስጠት ይሞክራል፡፡ ይህም ማለት ይቅርታ ቅጣትና ሌሎች የወንጀል ቱርፋቶችን እንደሚያስቀር ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ የይቅርታ አሰጣጥ እና አፈጻጸም ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁ. 840/2006 በአንቀጽ 2(1) እንዲሁም የቀድሞው አዋጅ ቁ. 395/1996 አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ ይቅርታ የሚለውን ቃል እንደሚከተለው ትርጉም ሰጥቶት ይገኛል፡፡
“ይቅርታ ማለት የቅጣት ፍርድ በሙሉ ወይም በከፊል ቀሪ እንዲሆን ወይም የቅጣት ፍርዱ አፈጻጸምና ዓይነት ቀለል ተደርጎ እንዲፈጸም ማድረግ ነው፡፡”
ከአዋጁ ትርጓሜ እንደምንረዳው ይቅርታ አንድም የቅጣት ፍርድን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ቀሪ የማድረግ ኃይል ሲኖረው በሌላ በኩል ይቅርታ የቅጣት ፍርድን ቀነስ አድርጎ ወይም ዝቅ አድርጎ መፈጸምን ይጨምራል፡፡
በዚህ አጋጣሚ አቶ ሙሉጌታ አያሌው የተባሉ የሕግ ባለሙያ “የይቅርታ አሰጣጥ ሁኔታ በኢትዮጵያ 2004 ዓ.ም ” በሚለው ጽሑፋቸው ላይ ይቅርታን አስመልክቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተደነገገው የይቅርታ አሰታጥና ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁ. 395/1996 የይቅርታ ጥያቄን ትርጉም በመስጠት ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ይናገራሉ፤ ይሁን እንጂ ሌሎች ሕጎቻችን ማለትም፤ የኢህዴሪ/ደርግ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 86(መ)፤ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 71(7)፤ አዲሱ የወንጅል ሕግ አንቀጽ 229 እና የቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 239 የወንጀል ድርጊት ፈጽሞ ፍርድ የተላለፈበት ሰው ይቅርታ ሊደረግለት የሚችል መሆኑን ከማሰቀመጥ ባለፈ ትርጉም እንዳላስቀመጡ በጽሑፋቸው ይጠቁማሉ፡፡
የይቅርታ አሰጣጥ ዋና ዓላማ የህዝብ፤ የመንግሥትን እና የታራሚወችን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል መንግሥት ጥፋተኞች በጥፋታቸው የተጸጸቱና የታረሙ መሆኑን በማረጋገጥ ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቅለው አምራች ዜጋ ማድረግ ነው፡፡ (አዋጅ ቁ.840/2006 አንቀጽ 3 ይመለከተዋል)
ይቅርታ፤ ምኅረት፤ አመክሮ እና መሠየም አንድነታቸው እና ልዩነታቸው
እንደሚታወቀው ይቅርታ፤ ምኅረት እና አመክሮ እንዲሁም መሠየም በተለምዶ አንድ ተደረገው በልማደድ የሚነገሩበት ሁኔታ አለ፡፡ አራቱንም አንድ የሚደርጋቸው ነገር ቢኖር አንድ ጥፍተኛ ወንጀል ከፈጸመ በኋላ ጥፋቱን የሚስቀሩ ወይም የሚቀንሱ መንገዶች ናቸው፡፡
ወደ ልዩነታቸው ስናመራ በመጀመሪያ ደረጃ ምኅረት ወንጀልን ከመጀመሪያው የሚያስቀር ሲሆን ይቅርታና አመክሮ ግን ቅጣትን ብቻ የሚያስቀሩ ሲሆን መሠየም ደግሞ መልካም ስማቸውን የሚያስመልሱበት መንገድ ነው፡፡ ሁለተኛ ምኅረት በአብዛኛው የሚሰጠው በሕግ አውጪው ሲሆን፤ ይቅርታ በሕግ አስፈጻሚው፤ ዳሩ ግን አመክሮ እና መሠየም ደግሞ የቅጣት ውሳኔውን በሰጠው ፍርድ ቤት ወይም ሕግ ተርጓሚው ነው፡፡
ሦስተኛ ምኅረት ሲደረግ ወጤቱ የጥፍተኛነት ስም አብሮ ይሰረዛል (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 230(2))፤ ይቅርታ ግን የጥፋተኝነት ስም በወንጀለኞች መዝገብ አብሮ ይያዛል (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 229(2))፤ አመክሮ ደግሞ የሚስከትለው ውጤት ታራሚው ጥሩ ምግባር ካሳየ ከቅጣቱ ሲሶ ወይም አንድ ሦስተኛ ተቀንሶለት የሚለቀቅበት አግባብ ነው፡፡ በሌላ በኩል መሰየም የሚባለው ደግሞ ወንጀለኛው የቀድሞ መልካም ስሙን የሚስከብረለት እና የጥፍተኛ ስሙ የሚፋቅለት ነው፡፡(የወንጀል ሕግ አንቀጽ 232)
በመጨረሻም ከምኅረት በስተቀር ይቅርታም ሆነ አመክሮ ብሎም መሰየም በአብዛኛው ተግባራዊ የሚደረጉት በቅድመ ሁኔታወች እና የመንግሥት አካላት በሚያወጡት መመሪያ መሠረት ነው፡፡
ይቅርታ መስጠት ሕገ መንግስታዊ ነውን?
ይቅርታ በኢትዮጵያ የሕግ ስርዓት ሕገ መንግሥታዊ እውቅና ማግኘት የጀመረው በ1923 ዓ.ም በወጣው ሕገ መንግሥት ነበር፡፡ በወቅቱም ለንጉሱ በአንቀጽ 16 ይቅርታ እንዲያደርጉ ሕገ መንግስቱ ፈቅዶላቸው ነበር፡፡
እንዲሁም የኢህዴሪ/ደርግ ሕገ መንግሥትም በተመሣሣይ የሪፖፕሊኩ ፕሬዝዳንት ይቅርታ እንደሚያደርጉ በአንቀጽ (86(2)መ) ተመልክቷል፡፡
ሆኖም በአንድ ወቅት የብሔራዊ ሸንጎ ም/ቤት ስብሰባ ላይ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሲናገሩ “…ካጠፋ በኋላ ይቅርታ ይደረግልን አዲስ የኢትዮጵያ ባህል ነው፡፡” ይላሉ ብለዋል፡፡ ከዚህ የፕሬዝዳንቱ ንግግር የምንረዳው ሀገሪቱ ውስጥ የይቅርታ ባህል እና ልማድ እየተለመደ መምጣቱን ነው፡፡
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ሕገ መንግሥቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተለያዩ ጉዳዮችን እውቅና ሰጥቷል፡፡
የተለያዩ ሰባዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነ ጻነቶች (የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 14-44 ይመለከተዋል) እንዲሁም የመንግሥት አወቃቀር፤ የሥልጣን አወቃቀር እና ክፍፍል (አንቀጽ 45-52 ይመለከተዋል) ወዘተረፈ ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡
ሕገ መንግሥቱ ስለ ሰብዓዊ መብቶች በሚደነግገው ክፍል ስለ ይቅርታ በማያሻማ መልኩ እንደሚከተለው ደንግጓል፡-
አንቀጽ 28
በስብዕና ላይ ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች
1. ኢትዮጵያ ባፀደቀቻቸው ዓለምአቀፍ ስምምነቶችና በሌሎች የኢትዮጵያ ሕጎች በሰው ልጅ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑትን ወንጀሎች የሰው ዘር የማጠፍት ፤ያለፍርድ የሞት ቅጣት የመውሰድ ፤ በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር፤ወይም ኢ-ሰብአዊ የድብደባ ድርጊቶችን በመፈጸሙ ሰወች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገድም፡፡በሕግ አወጪው ክፍልም ሆነ በማነኛውም የመንግሥት አካል ውሳኔወች በምኅረት ወይም ይቅርታ አይታለፋም፡፡
2. ከዚህ በላይ የተደነገገው ዕንደተጠበቀው ሆኖ፤ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተጠቀሱትን ወንጀሎች ፈጽመው የሞት ቅጣት ለተፈረደባቸው ሰዎች ርዕሰ ብሄሩ ቅጣቱን ወደ እድሜ ልክ ጽኑ እስራት ሊያሻሽለው ይችላል፡፡
ከላይ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ተቃራኒ ምንባብ (acontrario) መገንዘብ እንደሚቻለው አንድም ኢትዮጵያ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና በሌሎች የኢትዮጵያ ሕጎች በሰው ልጅ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑትን ወንጀሎች የሰው ዘር የማጠፍት፤ ያለፍርድ የሞት ቅጣት የመውሰድ፤ በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር፤ ወይም ኢ-ሰብዓዊ የድብደባ ድርጊቶችን ውጪ ያሉ ወንጀሎችን የፈጸሙ ሰዎች በይቅርታ ወይም በምኅረት ሊታለፋ ይችላሉ፡፡
በሌላ በኩል በቁጥር 28 ንዑስ አንቀጽ ሁለት በግልጽ እንደተጠበቀው በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተጠቀሱትን ወንጀሎች ፈጽመው የሞት ቅጣት ለተፈረደባቸው ሰዎች ርዕሰ ብሄሩ ቅጣቱን ወደ እድሜ ልክ ጽኑ እስራት ሊያሻሽለው ይችላል፡፡ ይህም ማለት ከሞት ፍርድ ወደ ዕድሜ ልክ እስራት መቀየር በራሱ ቅጣትን ዝቅ ማድረግ ስለሆነ ከይቅርታ ጽንሰ ሀሳብ አኳያ እንደ ይቅርታ ይቆጠራል፡፡እንዲሁም ከይቅርታ አሰጣጥ ና አፈጻጸም ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁ. 840/2006 አንቀጽ 2(1) አንጻር ፕሬዝዳንቱ/ርዕሰ ብሔሩ ፍርዱን ከሞት ወደ እድሜ ልክ መቀየሩ በራሱ የቅጣት ፍርዱ አፈጻጸም ና ዓይነት ቀለል አደርጎ እንዲፈጸም ማድረግ ስለሆነ እንደ ይቅርታ ይቆጠራል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ስለ ሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር/ፕሬዝዳት በሚናገረው ክፍል በምዕራፍ ሰባት ላይ በአንቀጽ 71(7) በግልጽ ስለ ይቅርታ እንደሚከተለው ድነግጓል፡፡
አንቀጽ 71
የፕሬዝዳንቱ ሥልጣንና ተግባር
…(7) በሕግ መሠረት ይቅርታ ያደረጋል፡፡
ይህም ማለት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት በህጉ መሠረት ይቅርታ እንደሚያደርጉ ህገ-መነግስቱ በማያሻማ መልኩ ይደነግጋል፡፡ “በሕጉ መሠረት” የሚለው ሕገ መንግሥታዊ ሀረግ የሚያጠይቀው ሥለ ይቅርታ የሚዘከሩ ሌሎች ሕጎችን ማለትም ሕገ መንግሥቱን ተከትለው የወጡ እንደ የወንጀል ሕግ እና የይቅርታ አሰጣጥ እና አፈጻጸም ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁ. 840/2006 ለማለት ነው፡
በተመሳሳይ እኤአ በ1996 የወጣው የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት ቁጥር 84(2)(በ) ላይ የሪፖሊኩ ፕሬዝዳንት ለወንጀለኞች ይቅርታ ሊያደረግ እንደሚችል ይጠቁማል፡፡
እንዲሁም በአሜሪካም ይቅርታ በፌዴራል መንግሥት ላይ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ይቅርታ እንሚያደረጉ በአሜሪካ ህገ-መንግሥት አንቀጽ 2 ክፍል 2 ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡
ስለሆነም ከላይ ጠቆም ለማድረግ እንደሞከርሁት ይቅርታ መስጠት የሕገ-መንግሥት መሠረት (Constitutional-backup) ያለው እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ይቅርታ እና የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ
የወንጀል ሕግ ዓላማው ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የአገሪቱን መንግሥት፤ የህዝቦቿን፤ የነዋሪውን ሠላም ድህንነት፤ መብት እና ጥቅም ማስጠበቅ እና ማረጋገጥ ሲሆን ግቡም ወንጀል እንዳይፈጸም መከላከል ሲሆን ይህን የሚያደርገው ስለወንጀሎች እና ስለቅጣታቸው በቅድሚያማስጠንቀቂያ በመስጠት የተሠጠው ማስጠንቀቂያ በቂ ባልሆነ ጊዜ ወንጀለኞች ተቀጥተው ሌላ ወንጀል ከመፈጸም እንዲቆጠቡና ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑ ወይም እንዲታረሙ በማድረግ ወይም ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ እርምጃወች እንዲፈጸሙባቸው በማድረግ ነው፡፡ (የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 1 ይመለከተዋል)፡፡
የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ በጠቅላላው ክፍል በክፍል ሦስት በአንቀጽ 229 ላይ ለይቅርታ ትልቅ ትርጉም ሰጥቶት እናገኛለን፡፡
አንቀጽ 229 ይቅርታ
1) በሕግ በሌላ አኳኃን ካልተደነገገ በቀር በፍርድ የተወሰነ ቅጣት ሥልጣን በተሰጠው አክል በሙሉ ወይም በከፊል በይቅርታ ሊቀር ወይም ዓይነቱ አነስተኛ በሆነ ቅጣት ሊለወጥ ይችላል፡፡
የከባድነታቸው ደረጃ ማናቸውም ቢሆን በዋነኝነትም ሆነ ወይም በተጨማሪ ተፈጻሚ ለሚሆኑ ቅጣቶችና የጥንቃቄ እርምጃወች ይቅርታ ሊሰጥ ይችላል፡፡
2) የይቅርታ አሰጣጡ ሁኔታ በሕግ በተደነገገው መሠረት ይሆናል፤ የቅርታን የሚሠጠው ሁኔታነና ገደብ ይወሠናል፡፡
3) ይቅርታ ሲሰጥ በተቀጭው ላይ የተወሠነው ፍርድ ከሚየስከተለው ውጤት ጋር በወንጀለኞች መዝገብ ላይ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
ከላይ በወንጀል ሕጉ በግልፅ እንደተቀመጠው ይቅርታ በፍርድ የተወሠነ ቅጣትን በሙሉ ወይም በከፊል ቀሪ የማድረግ እንዲሁም አነስ ባለ ቅጣት ሊለወጥ እንደሚችል እሙን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የከባድነታቸው ደረጃ ማናቸውም ቢሆን በዋነኝነትም ሆነ ወይም በተጨማሪ ተፈጻሚ ለሚሆኑ ቅጣቶች ብሎም የጥንቃቄ እርምጃወች ይቅርታ ሊሰጥ ይችላል፡፡
የወንጀል ሕጉ ሌሎቸ ጉዳዮችንም ስለሚዳስስ የይቅርታን ጉዳይ በአንድ አንቀጽ ብቻ የተመለከተው ሲሆን ዝርዝሩም በሕግ እነደሚወሰን ጭምር በንዑስ ቀጥር 2 አንቀጽ 129 ላይ አመላካች ሀረግ አስቀምጦ አልፏል፡፡ይህንን ንዑስ አንቀጽ ለማስፈጸም የይቅርታ አሰጣጥ እና አፈጻጸም ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁ. 840/2006 ሥራ ላይ ውሏል፡፡ ስለ አዋጁ ምንነት እና ዝርዝር በቀጣዩ ክፍል እንመለስበታለን፡፡
በመጨረሻም የወንጀል ሕጉ የይቅርታን ውጤት ያተተ ሲሆን፤ ይቅርታ የተደረገለት ወንጀለኛ ስሙ ከጥፋተኞች መዝገብ እንደማይፋቅ ጭምር ነው ሕጉ በአንክሮ የሚነግረን፡፡ (የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 229(2) ሀለተኛ ሀረግ ይመለከተዋል፡፡)
የይቅርታ አሰጣጥ እና አፈጻጸም ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁ. 840/2006
ይቅርታን በተመለከተ የሀገራችን የሕግ ማዕቀፍ እጅግ ዘግይቶም ቢሆን በልዩ ሕግ መታየት ከጀመረ አሥርት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ የመጀመሪያው የአትዮጵያ የይቅርታ ሕግ ተብሎ የሚጠራው የይቅርታ አሰጣጥና ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁ. 395/1996 ሲሆን በነበረበት አንዳንድ የአፈጻጸም ክፍተቶች በመነሳት በአዲሱ የይቅርታ አሰጣጥ እና አፈጻጸም ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁ. 840/2006 ተሸሯል፡፡ (አንቀጽ 27 አዲሱ አዋጅ ተመለከተዋል፡፡)
አዲሱ የይቅርታ አሰጣጥና አፈጻጸም ሥነ ሥርዓት አዋጅ ለሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በይቀርታ ጉዳዮች ከፍተኛ ሥልጣን ይሰጣል፡፡ (አንቀጽ 5 ይመለከተዋል)
ከዚህ በተጨማሪ አዋጅ በአንቀጽ 6 ላይ የይቅርታ ቦርድ እንደሚቋቋም ይጠቁምና በአንቀጽ 7 ላይ ደግሞ የይቅርታ ቦርድ አባላትን ዝርዝር ይናገራል፡፡ በዚህም አዲሱ አዋጅ የቦርዱን አባላት ስብጥር ቀድሞ ከነበረው አምስት ወደ ዘጠኝ ከፍ በማድረግ ከተለያዩ ዘርፎችጭማሪ ማድረጉ ጥሩ እርምጃ ነው፡፡
የይቅርታ ቦርድ በአዋጁ አንቀጽ 9 እንደተመለከተው የሚከተሉት ስልጣኖች ተሰጠውታል፡-
I. የሚቀርብለትን የይቅርታ ጥያቄ በመመርመር በቅድመ ሁኔታ ወይም ያለቅድመ ሁኔታ ተመስርቶ ይቅርታ እንዲሰጥ ለፕሬዝዳንቱ የውሳኔ ሀሳብ ያቀርባል፡፡
II. ለይቅርታ አሰጣጥ አስፈላጊ የሆኑና ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘቡ መስፈርቶች ማውጣት
III. እንደ አስፈላጊነቱ ክሱን የተከታተለው ዐቃቤ ሕግ አካል ማነኛውም ባለሥልጣን ወይም ግለሰብ በአካል በመቅረብ በጽሑፍ ሀሳብ እንዲያቀርብ የማድረግ፡፡
ሌላው ጉዳይ በዚህ አጋጣሚ መነሳት ያለበት ነገር የይቅርታ ቦርድ ጽ/ቤት የት እና በምን መሥሪያ ቤት ሥር ይገኛል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህም ጥያቄ አዋጁ በአንቀጽ 13 ላይ መልስ አስቀምጧል፤ የይቅርታ ቦርድ ጽ/ቤት በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር ይደራጃል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ይቅርታ አንዴት ይሠጣል? የሚለው ጥያቄ ትኩረት የሚሻ ነጥብ ነው፡፡ ይቅርታ የሚሰጠው “የይቅርታ ይደረግልኝ ጥያቄ” ሲቀርብ ነው፡፡ በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የመጨረሻ የቅጣት ፍርድ የተሰጠበት ማነኛውም ሰው የይቅርታ ጥያቄውን ራሱ ወይም ባለቤቱ፤ በቅርብ ዘመዱ፤ በወኪሉ፤ ወይም ጠበቃው፤ በፍትሕ ሚኒስቴር ወይም በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አማካኝነት የይቅርታ ይደረግልኝ ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ (አንቀጽ 15 አዋጁ ይመለከተዋል፡፡) የይቅርታ ጥያቄ በቅርብ ዘመድ ሊቀርብ ይችላል እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ የቅርብ ዘመድ ማን ነው፤ ነገርግን አዋጁ መልስ አይሰጥም፡፡ በመሆኑም የቅርብ ዘመድ ከቤተሰብ ህጉ አንፃር ስናየው የሥጋ ወይም የጋብቻ ዘመድ ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡
የይቅርታ ጥያቄ መቅረቡ ብቻ ይቅርታ አያሰጥም ለምን ቢባል በህጉ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታወች መሟላት አለባቸው፡፡ ይህም በአንቀጽ 20 ላይ በግልጽ እንደተመለከው መሟላት ያለባቸው ነገሮች፡-
I. የይቅርታ ጠያቂው አደገኝነት
II. የወንጀሉ ክብደት እና የይቅርታ ጠያቂው በማረፊያ ቤትና በማረሚያ ቤት የቆየበት ጊዜ፤
III. የይቅርታ ጠያቂው ከዚህ ቀደም ይሰራበት ከነበረው መስሪያ ቤት፤ ይኖርበት ከነበረው አካባቢ ማህበረሰብ፤ ከቤተሰብ፤ ከሐኪሙ ወይም ከሌሎች አግባበብነት ካላቸው አካላት የተሰባሰቡ መረጃወች፤
IV. ይቅርታ ጠያቂው ለወደፊቱ በሠላም ለመኖር የሚሳየው ባህሪ፤ ብሎም ጥፋቱን አምኖ የተጸጸተ መሆኑ እና ከተጎጂ ቤተሰቦች ጋር ያደረገው ዕርቀ ሰላም
V. የይቅርታ ጠያቂው የቤተሰብና የጤንነት አቋም እና የዕድሜ ሁኔታ፡፡
ከላይ የተቀመጡት ቅድመ ሁኔታወች በቀድሞው የይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ያለተካተቱ ሲሆን በዚህም የተለያዩ ተግዳሮቶች ቦርዱን በተግባር ገጥመውታል፡፡ ይህምንንም ጉዳይ አቶ ሙሉጌታ አያሌው እንደጻፋት “በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ የይቅርታ መስፈርት ያልተዘጋጀ ሲሆን ወደፊት የሁሉንም ክልሎች መስፈርት በማየትና ለሁሉም ወጥ የሆኑትን በመለየት መስፈርት ለማዘጋጀት በፌዴራል ይቅርታ ቦርድ ጽ/ቤት በኩል ዕቅድ ተይዞ እየተሰራበት ይገኛል፡፡ በአዲሱ አዋጅ ግን አንቀጽ 20 ላይ በተቀመጡት መስፈርቶች የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡
በመጨረሻም አዋጁ የይቅርታን ውጤት የተመለከተው ሲሆን በይቅርታ ውሳኔው በግልጽ ካልተመለከተ በስተቀር የይቅርታ ውሳኔው በፍርድ ቤት ውሳኔ የተሰጡትን ቅጣቶች በሙሉ የሚስቀር ይሆናል፡፡ ነገር ግን የይቅርታ ውሳኔው ከወንጀል የሚመነጩ የፍትሐ ብሄር ኃላፊነቶችን የሚያስቀር አይደለም፡፡ (አንቀጽ 22 ይመለከተዋል)
ይቅርታ እና የሌሎች ሀገራት ልምድ
ሀ. አሜሪካ
በአሜሪካን አገር ይቅርታ የሚሰጠው በፕሬዚዳንቱ ሲሆን ይህም በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 2 ክፍል 2 ላይ የተመለከተ ሲሆን የውሳኔ ሀሳብ የሚያቀርበው በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥር የተዋቀረው እና የተደራጀው የይቅርታ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ (Office of the Pardon Attorney) ነው፡፡
በአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በፍትህ ሚኒስቴር ሥር የተደራጀ ቢሆንም ከወንጀል ፍትህ አስተዳደር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ሥልጣን ያለው ይኸው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ (Attorney General) ነው፡፡
በፕሬዝዳንቱ የሚደረገው ይቅርታ በማነኘውም ጊዜ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን በፍትሕ ሚኒስቴር የሚሰጠው ይቅርታ ተግባራዊ የሚደረገው ይቅርታ ጠያቂው ከቅጣት በኋላ አምስት አመት በመታገስ ነው፡፡
አሜሪካ የፌዴራል ሥርዓት ተከታይ አገር በመሆኗ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ይቅርታ የማድረግ ሥልጣን በፌዴራል ጉዳዮች ዙሪያ ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ክፍለ ሀገራት/ ክልሎች (States) በራሳቸው ግዛት ይቅርታ የማድረግ ሥልጣን አላቸው፡፡
ለ. ደቡብ አፍሪካ
ልክ እንደ አሜሪካ ሁሉ በደቡብ አፍሪካ የሕግ ስርዓት ይቅርታ በህገ-መንግስቱ ለሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የተሠጠ ሥልጣን ነው፡፡ይህም ሥልጣን በአብዛኛው በልዩ ሁኔታወች የሚሰራ ሥልጣን እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡
በደቡብ አፍሪካ የሕግ ሥርዓት ይቅርታ የሚሰጠው ቀላል በሚባሉ ወንጀሎች ነው፡፡ እንዲሁም ይቅርታ ጠያቂው ጥፍተኛ ከተባለ አንስቶ አሥር (10) አመት መታገስ ይኖርበታል፡፡ነገር ግን በከባድ ወንጀሎች ላይ ይቅርታ አይሰጥም፡፡
ሐ. ፈረንሳይ
በፈረንሣይ አገር ይቅርታ የሚሰጠው በፕሬዚዳንቱ ሲሆን በፍትህ ሚኒስቴር ሥር የተዋቀረው የወንጀል ጉዳዮች እና የይቅርታ ዳይሬክቶሬት (Directorate of Criminal Affairs and Pardons) የውሳኔ ሀሳቡን አዘጋጅቶ ያቀርባል፡፡ የይቅርታ ጠያቂው ማመልከቻ ተቀባይነት ካገኘ ቅጣቱን በሙሉ ወይም በከፊል ማስቀረት ወይም ከባድ ቅጣት ወደ ቀላል መለወጥ የሚቻል ሲሆን የተከሳሹ የፍትሐብሔር ተጠያቂነት ግን ይቅርታ አይደረግለትም፡፡
ይቅርታ በሚሰጥበት ጊዜም የይቅርታ ውሳኔው በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት፤መቅላይ ሚኒስቴር ና የፍትህ ሚኒስቴር ሚንስትር እንዲሁም ሌሎች የተሳተፋ ሚንስትሮች መፈረም አለበት፡፡
መ. ሕንድ
በሕንድ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 72 በግልፅ እንደተቀመጠው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ይቅርታ የማድረግ ወይም በተለይ የሞት ቅጣት የተላለፈበትን ዝቅ ባለ እንዲቀጣ የመወሰን ሥልጣን አለው፡፡
ይህም ሥልጣን በተመሣሣይ ለሀገረ-ገዢወች /Governors of states/ በአንቀጽ 161 ላይ ተሰጧል፡፡ ነገር ግን እንደሚታወቀው ህንድ አህዳዊ የሕግ ስርዓት ተገከታይ ሀገር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ክልሎች የራሳቸው የሆነ ሕግ የላቸውም፡፡ ስለሆነም የሀገረ-ገዢወች የይቅርታ ሥልጣን ቀላል በሚባሉ ወንጀሎች ሲሆን በከባድ ወንጀሎች ግን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሥልጣን ብቻ ነው፡፡
ማጠቃለያ
ይቅርታ ለማህበረሰብ በሰላም መኖር የማይናቅ ሚና አለው፡፡ በሀገራችን ወንጀል ፈጽመው ይቅርታ የሚያገኙበትን ሥርዓት በመዘርጋት የይቅረታ አሰጣጥ እና ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁ. 395/1996 ፈር ቀዳጅ ነው፡፡ ሆኖም ግን በተግባር ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታትና የበለጠ በተጠናከረ መልኩ ሕግ ማውጣት በማስፈለጉ እንደገና በአዋጅ ቁ. 840/2006 ተተክቷል፡፡
በአዋጁ እንደተመለከተውም ይቅርታ የሚደረገውም የይቅርታ ይደረግልኝ አቤቱታ ሲቀርብ መሆኑ እሙን ነው፡፡
በመጨረሻም በአብዛኛው የዓለም ሀገራት በይቅርታ ጉዳይ የበላይ እና የመጨረሻ ሥልጣን ያለው የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ወይም ፕሬዝዳንት ነው፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments