የኮንስትራክሽን ዋስትና ምንነትና በተግባር የሚስተዋሉ የሕግ ክፍተቶች - ክፍል 1
ይህ ጹሑፍ በ6ኛው የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ “የኮንስትራክሽን ዋስትና ሕጎች እና የገንዘብ ተቋማት አሰራር” በሚል አውደ ጥናት ላይ ለውይይት የቀረበ ነው፡፡ ዋስትና በውል አፈጻጸም ወቅት እንደተጨማሪ ግዴታ የሚቆጠር በሕግ ፊት ሊጸና የሚችል (juridical act) ተግባር ነው፡፡ በአለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ በአለማችን ከኢኮኖሚያዊ እድገት ጋር ታያይዞ ዋስትና (security) የመጠቀም ልማድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጧል፡፡
ሆኖም ግን እኤአ ከ2007 ዓ.ም በኋላ ከዓለም ኢኮኖሚ መዳከም ጋር ተያይዞ የዋስትና ጥቅም በአግባቡ የታየበት ብሎም አሰፈላጊነቱም ጭምር ጥያቄ ምልክት ውስጥ የገባበት ጊዜም አይዘነጋም፡፡
ዋስትና መልኩ ይለያይ እንጂ በተግባር አገልግሎት ላይ መዋል የጀመረው እእኤ ከ2750ዓ.ዓ ገደማ ጀምሮ ነበር፡፡ በወቅቱም ዋስትናው ጥሬ ገንዘብ እንደመያዣነት በማቅረብ ነበር፡፡ በተለይ ስለ ሰው ዋስትና (surety) ሕግጋት እና መርሆዎች በተመለከተ ጥናታዊ ሮማዊያን እኤአ በ150ዓ.ም ገደማ ያዘጋጁት ተጠቃሽ ነው፡፡ (ጄፈሪ በርተን፡2000፡9) ከዚያም የሦስተኛ ወገን ዋስትና ወደ ማቅረብ የተሄደበትም ጊዜ ነበር፡፡ ዘመናዊ የፋይናንስ ተቋማት ማደግን ተክትሎ በዋናነት ለዓለምአቀፍ የሽያጭ ግብይቶች ክሬዲ (letters of credit) እየተስፋፋ የመጣበትን ሁኔታ እናገኛልን፡፡
በውል አፈጻጸም ወቅት የተለያዩ ዋስትናዎች ሊተገበሩ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ፡-የግምጃ ቤት ሰነድ (treasury bill)፣ ማገቻ (bond)፣ በቅድመ ሁኔታ የሚሰጡ ዋስትናዎች (conditional guarantees)፣ ያለቅድመ ሁኔታ የሚሰጡ ዋስትናዎች (on demand guarantees)፣ የጨረታ ማሰከበሪያ ዋስትና (Bid security)፣ የቅድመ ክፍያ ዋስትና፣ የሰው ዋስትና (suretyship)፣ የንብረት ዋስትና (pledge or mortgage)፣ ራሳቸውን የቻሉ የብድር ሰነዶች ወይም ክሬዲት (Standby letters of credit) ወዘተ በመባል ይታወቃሉ፡፡
አብዛኛውን ከላይ የተባሉት የዋስትና ሰነዶች በገንዘብ አበዳሪ ተቋማት እና ኢንሹራንስ ድርጅቶች ይዘጋጃሉ፡፡ ነገር ግን የሰው እና የንብረት ዋስትና ግን በግራ ቀኝ ተዋዋይ ወገኖች በራሳቸው አሊያም በሌላ ሦስተኛ ወገን አላፊነት ሊከናወኑ ይችላል፡፡
በውል አፈጻጸም ወቅት የዋስትና መኖር በተዋዋዮች ዘንድ ከፍተኛ መተማመን እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ሌላው የውሉን አፈጻጸም ተጠባቂ (predictable) እንዲሆን ያደርጋል፡፡ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪም አንድ የፕሮጀክት ባለቤት ሥራው በተያዘለት ጊዜ እንዲያልቅ በማሰብ የፕሮጀክት አፈጻጸም ዋስትና አስፈላጊነት ትዝ ካለው፤ ለፕሮጅቱ የሚመቸውን የዋስትና ዓይነት ማለትም የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትና፣ በገንዘብ አበዳሪ ተቋማት የሚዘጋጅ ዋስትና ወይም ክሬዲ አንዳንዴ ደግሞ የፕሮጀክቱን ክፍያ ገንዘብ በፐርሰንት መያዝ (retention) እንዲኖር ሊያስብ ይችላል፡፡ የሆነው ሆኖ እነዚህ የዋስትና መንገዶች ተመሳሳይ ዓላማ አላቸው፡፡ ይህም በተዋዋዮች መካከል መተማመን እና ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎች (risk) በመቀነስ ግብይትን ማፋጠን ነው፡፡ ዳሩ ግን እያንዳንዳቸው የራሳቸው ባህሪይ አላቸው ብሎም በአፈጻጸም እና አተገባበር የተለያዩ ናቸው፡፡ ስለሆነም አሰፈላጊነታቸው መታየት ያለበት እንደየ ፕሮጀክቱ አካሄድ፣ መጠን እና ጊዜ ሊሆን ይቻላል፡፡
በዓለምአቀፍ ደረጃ ባሉ ግብይቶችም የዋስትና ሰነዶች በጣም የተለመዱ ናቸው፡፡ በተለይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተ.መ.ድ) የዋስትና ወረቀቶች እና ክሬዲ ሥምምነት (UN Convention on Independent Guarantees and Standby Letter of Cedit) በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ዓለምአቀፍ ሥምምነት እኤአ በ1995 በአሜሪካዋ የኒዮርክ ከተማ ለሥምምነት ክፍት የሆነ ሲሆን 8 (ስምንት) አገራት በመፈረምና በማጽደቅ ተቀብለውታል፡፡ ኢትዮጵያ ግን የዚህ ሕግ ፈራሚ አገር አይደለችም፡፡ ሆኖም ግን ይህ ሥምምነት በዓለምአቀፉ የንግድ ሕግ ኮሚሽን (United Nations Commission on International Trade Law/UNCTRAL) እንደመዘጋጀቱ መጠን ዋስትናን በተመለከተ በቀጣይ አገራት ለሚያዘጋጇቸው ዝርዝር ህጎች በሞዴልነት እንደመነሻ ሊያገለግል ይችላል፡፡ በተለይ ስምምነቱን የፈረሙ አገራት በዓለምአቀፍ ደረጃ ሊሚያከናውኗቸው የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ላይ ዋስትናን በተመለከተ ይህ ሕግ ተፈጻሚ ነው፡፡
ሌላው ዋስትና ሲነሳ ምንጊዜም ቢሆን አብሮ የሚነሳው የመድን ውል (insurance) ነው፡፡ ዋስትናም (security/guarantee) ሆነ መድን አንድ የሚያደርጋቸው ነገር አለ፡፡ ይህም ሁለቱም ባለመብቱን ሊደርስ ከሚችል አደጋ በመከላከላቸው ነው፡፡ ሆኖም ግን በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ሁለቱም የተለያየ የሕግ ውጤት ያላቸው ተግባራት ናቸው፡፡ በተለይ በዋስትና ተግባር ዋስ የሚሆነው ግለሰብ የሚጠበቅበት ግዴታ ቢኖር ባለእዳው ለባለገንዘቡ በውል መሰረት ካልከፈለ ወይም መክፋል ካልፈለገ በሕግ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን ጠብቆ በባለእዳው እግር ተተክቶ ዕዳውን ሊወጣ የሚችልበት ሁኔታ ነው፡፡ በአንጻሩ ግን መድን የገባ ሰው መደበኛ የሆነ አረቦን (premium) መክፈል እንደተጠበቀ ሆኖ መድን በተገባለት ጉዳይ ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን ይፋ ማድረግን ጨምሮ የመድን ጥቀም (insurable interest) ሊኖረው ግድ ይላል፡፡
በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪም ከላይ የጠቀስናቸው የዋስትና ዓይነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ አስፈላጊነታቸው እየታመነበት ስለመጣ በፕሮጀክት አፈጻጸም ወቅት ሲተገበሩ ይታያል፡፡
1. የዋስትና ምንነት
ዋስትና በይዘትም ሆነ በዓይነት መለያየቱን ተከትሎ የተለያዩ ትርጓሜዎችን ሊይዝ ይችላል፡፡ ዋስትና (Security) የሚለው ቃል የመጣው ‘securitat’ ከሚለው የላቲን ቃል ሲሆን ትርጉሙም ለዕዳ ማስከበሪያ የሚጠየቅ ገንዘብ እንደሆነ ያሳያል፡፡ በጽንሰሃሳብ ደረጃ ዋስትና ሰፋ ያለ ትርጉም ሊይዝ ይችላል፡፡ ለአብነት ያህልም የተለያዩ መዝገበ ቃላቶች የተለያየ ትርጉም ሲሰጡት ይታያል፡፡
ሜሪያም ዌብስተር መዝገበ-ቃላት (Merriam Webster dictionary) ዋስትና የሚለውን ቃል ግዴታን ለመወጣት ተብሎ የሚሰጥ፣ የሚቀመጥ ወይም የሚያዝ ነገር በማለት ይተረጉመዋል፡፡
[S]ecurity as something given, deposited or pledged to make certain the fulfillment of an obligation.”
በሌላ በኩል ኦክስፎርድ ኮንሳይስ መዝገበ ቃላት (Oxford Concise Dictionary) 10ኛ ዕትም ዋስትና የሚለውን ቃል ለብድር ማስከበሪያ ወይም ለግዴታ መወጫ ሊሆን የሚችል መያዣ ወይም ዋቢነት ሲሆን የገንዘብ ብድር መኖርን የሚያሳይ ወረቀት፣ አክሲዮን (stock)፣ የግምጃ ቤት ሰነድ እና ሌሎች ባለቤትነትን ሊያረጋገጡ የሚችሉ ተላላፊ ሰነዶች ናቸው፡፡
ሌላው የብላክስ ሎ መዝገበ ቃላት (Black’s Law dictionary) 9ኛ ዕትም ላይ ዋስትናን ከብድር ጋር የተያያዘ ግዴታን ለመፈጸም የሚያገልግል መያዣ በማለት ያስቀምጠዋል፡፡
[S]ecurity means collateral given or pledged to guarantee the fulfillment of an obligation...[sic]...especially the assurance that a creditor will be repaid any money or credit extended to a debtor.”
የተ.መ.ድ የዋስትና ሥምምነት ሕግ ዋስትና የሚለውን በእንግሊዘኛው ‘Security’ ከማለት ይልቅ ‘undertaking’ በማለት በአንቀጽ 2 ላይ ሰፋ ያለ ትርጉም ሲሰጠው እናያለን፡-
“an undertaking is an independent commitment, known in international practice as an independent guarantee or as a stand-by letter of credit, given by a bank or other institution or person (“guarantor/issuer”) to pay to the beneficiary a certain or determinable amount upon simple demand or upon demand accompanied by other documents, in conformity with the terms and any documentary conditions of the undertaking, indicating, or from which it is to be inferred, that payment is due because of a default in the performance of an obligation, or because of another contingency, or for money borrowed or advanced, or on account of any mature indebtedness undertaken by the principal/applicant or another person.”
በዚህም ዓለምአቀፍ ሕግም ዋስትና ማለት ራሱን የቻለ ግዴታ ሲሆን ይህም በባንክ፣ በገንዘብ ነክ ተቋማት ወይም በግለሰቦች ሊሰጥ የሚችል በተለይም እንደነገሩ ሁኔታ በቅድመ-ሁኔታ አሊያም ያለቅድመ ሁኔታ ተበዳሪው እዳውን መወጣት ካለመቻሉ ጋር ተያይዞ አሊያም ሌሎች ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን ታሳቢ በማድረግ የሚከናወን የዋስትና ወረቀት ወይም ራሱን የቻለ ክሬዲ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህ የተ.መ.ድ ሕግ በአንቀጽ 1 እንደተመለከተው የተፈጻሚነት ወሰኑ አንድም በዓለም አቀፍ ግብይቶች ላይ ሲሆን ሁለትም በፈራሚ አገራት ብቻ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሕግጋት ውስጥም ስለ ዋስትና የተመለከቱ አንዳንድ የተበታተኑ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡-በ2001ዓ.ም የወጣው የፌዴራል መንግስት የፋይናንስ አስተዳድር አዋጅ ቁ.648/2001 ዋስትና የሚለውን ቃል የዋስትና ሰነድ በሚል በአንቀጽ 2 (20) ላይ እንደሚከተለው ይተርጉመዋል፡-
“የዋስትና ሰነድ ማለት የፋይናንስ ቃልኪዳን ወይም የፋይናንስ ግዴታን ለመፈጸም የሚሰጥ ወይም የሚያዝ ማነኛውም ሰነድ ሲሆን፣ የግምጃ ቤት ሰነድን፣ የተስፋ ሰነድን እና ቦንድን ይጨምራል፡፡ ”
ዳሩ ግን የአዋጁ ትርጓሜ የዋስትና ዓይነቶችን ከመዘርዘር ውጪ ዋስትና በምን ሁኔታ ሊሰጥ ይችላል የሚለውን ጉዳይ ግልጽ አላደረገም፡፡
ከላይ ከተመለከቱት የዋስትና ትርጓሜዎች የምንረዳው ነገር ቢኖር ዋስትና ቀዳማዊ ግዴታ ሳይሆን የእዳ ማስከበሪያ ተለጣፊ ግዴታ ነው፡፡ በሌላ አባባል የዋስትና ውል ደባል ውል (accessory contract) ነው፡፡ ይህም ሲሆን ዋሱ ባለዕዳው ለገባው ግዴታ ማለትም ባለእዳው ካልከፈል በደባልነት የሚጠየቅበት ሥርዓት ነው፡፡
በአጠቃላይ ካደጉ አገራት የሕግ ፍልስፋና (developed countries jurisprudence) እና ንጽጽራዊ ጥናት (comparative study) አንጻር ዋስትና የሚለው ቃል በጣም ሰፋ ያለ እና በይዘትም በርካታ ነገሮችን በውስጡ አቅፎ የሚይዝ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የፍይናንስ ወረቀቶች እንደ አክሲዮን፣ የግምጃ ቤት ሰነድ፣ ቦንድ፣ የንግድ ማህበራት የሚያወጧቸው የብድር ወረቀቶች (debentures)፣ ተላላፊ የገንዘብ ሰነዶች፣ የኢንቨስትመንት ውሎች፣ ከማዕድን ማውጣት ጋር የተያያዙ ያለተከፋፈለ የወለድ መብት ወዘተ ሊያጠቃልል ይችላል፡፡
2. የዋስትና ዓይነቶች
ዋስትና አብዛኛውን ጊዜ በገንዘብ አበዳሪ ተቋማት እንደ ባንክ፣ ማይክሮ ፋይናንስ ይሰጣል፡፡ አለፍ ሲልም በመድን ድርጅቶች ጭምር የሚወጣበት ጊዜ አለ፡፡ ዋስትና በተለያየ የሕግ ማዕቀፍ ይመራል፡፡ በአገራችንም በተበታተነ መልኩ ቢሆንም ዋስትናን የሚገዙ ሕጎች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡-የፍትሐብሔር ሕጉ ስለ ሰው ዋስትና ብሎም ስለ ንብረት ዋስትና በዝርዝር ይደነግጋል፡፡ የንግድ ሕጉ ደግሞ ስለ ሰነድ ዋስትና እንዲሁም የባሕር ሕጉ ስለ ንብረት ዋስትና በተመሳሳይ ዘርዘር ያሉ ጉዳዮችን ተመልክቷል፡፡
ጸሐፊውም ዋስትና የሚለው ቃል ፈርጀ ብዙ ከመሆኑ አንጻር እንዲሁም አሁን አሁን እያደገ የመጣውን የኮንስትራክሽን ዋስትና በጥልቀት ለመረዳት ያስችል ዘንድ ዋስትናን ከሚሰጠው ጠቀሜታ እና ባህሪ አንጻር በአራት አብይት ክፍሎች በመፈረጅ ለመዳሰስ ሞክሯል፡፡ እነዚህም የሰው ዋስትና፣ የንብረት ዋስትና፣ የፋይናንስ ዋስትና እና የኮንስትራክሽን ዋስትና ናቸው፡፡
2.1. የሰው ዋስትና (Personal security/Suretyship)
የሰው ዋስትና የሚባለው አንድ ባለዕዳ ከባለገንዘቡ ጋር ላለበት የውል አፈጻጸም ሌላ ሦስተኛ ወገንን በዋስነት (surety/guarantor) የሚቀርብበት የዋስትና ዓይነት ነው፡፡ የሰው ዋስትና በፍትሐብሔር ሕጋችንም የታወቀ ነው፡፡ በተለይ የፍ/ህ/ቁ 1920 የሚከተለውን ደንግጓል፡-
“ለግዴታው አፈጻጸም ዋስ የሚሆነው ባለዕዳው ግዴታውን ያለፈጸመ እንደሆነ ለባለገንዘቡ ይህንን ግዴታ ሊፈጽም ይገደዳል፡፡ ”
ከዚህ ድንጋጌም የሚከተሉትን የሰው ዋስትና ባህሪያት መዘርዘር እንችላለን፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የዋሱ ግዴታ ቀዳማዊ ሳይሆን ተከታይ ነው፡፡ ሁለተኛም የዋሱ ግዴታ የሚጀምረው ዋናው ባለዕዳ መክፈል ካልቻለ ነው፡፡
በዋናነት የሰው ዋስትና መሠረታዊ ጥቅም በባለገንዘቡ እና ባለእዳው መካከል ያለውን ግብይት ታዓማኒ ማድረግ ነው፤ ለምን ቢባል ባለገንዘቡ በልበ-ሙሉነት ወደ ውሉ ስለሚገባ ጭምር ነው፡፡ ስለ ሰው ዋስትና ጥቂት ነጥቦችን ለመጨመር ያህል የዋስትና ግዴታው ግልፅ መሆን አለበት፡፡ ኃላፊነቱም ግዴታ ከተገባለት እዳ ወሰን ለማለፍ እንደማይቻል እና ለአፈፃፀሙ ግዴታ የተገባለት የእዳ መጠን ወይም የገንዘብ ልክ በዋስትና ውሉ ካልተገለፀ ዋስትናው ፈራሽ ይሆናል፡፡ /የፍ/ህ/ቁ 1922 ይመለከቷል፡፡ ይህንንም ጉዳይ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቅጽ 19 ላይ በሰ/መ/ቁ 104061 በእነ አቶ ፍቅሬ ግርማ እና አቶ ደስታ ጫምሶ መካከል በነበረው የፍትሐብሔር ክርክር ላይ የሰጠው ውሳኔ ማስታዎስ እንችላለን፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ገና ለወደፊት ሊደርስ ለሚችል ግዴታ አፈጻጸምም ዋስ ለመሆን እንደሚቻል ነገር ግን በግልፅ ለምን ያህል እዳ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚቻል በግልፅ በውሉ ላይ መስፈር ያለበት እንደሆነ የፍ/ህ/ቁ 1925 ያስረዳል፡፡ ይህም ጉዳይ በፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅጽ 16 በሰ/መ/ቁ 94837 በእነ አቶ ልዑል ዘወዴ እና አጀመራ የወርቅ ግብይት ኃ/የተ/የግ/ማህበር መካከል በነበረው የፍትሐብሔር ክርክር ውሳኔ ማነበብ ጠቃሚ ነው፡፡
ሌላው ስለሰው ዋስትና በተመለከተ አጨቃጫቂው ነጥብ ዋሱ ዋስ የሆነበት ጉዳይ ለምሳሌ፡-ተቀጣሪው ሰራተኛ የንብረት ክፍል አላፊ ሆኖ ለሚያደርሰው አላፊነት በሚል ነው ነገር ግን ተቀጣሪው የገንዘብ ክፍል አላፊ ቢሆን እና ገንዘብ ቢያጎድል፣ የዋሱ አላፊነት እሰከምን ድረስ ነው? የሚል ነው፡፡
እርግጥ ነው የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 1928 ላይ በግልጽ እንዳስቀመጠው በባለዕዳው እና ባለገንዘቡ መካከል የሚደረግ የውል መለወጥ የዋሱን ግዴታ ሊያብስበት እንደማይችል በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ዳሩ ግን በቅርቡ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በቅጽ 20 ላይ በሰ/መ/ቁ 107542 በእነ አቶ ሶፎኒያስ ኃ/ማርያም እና ካልዲስ ኮፊ ኃ/የተ/የግል ማህበር መካከል በነበረው ክርክር አመልካቹ ያቀረቡትን የውል መለወጥ ክርክር ውድቅ አደርጎ የዋስትና ውል ግዴታ ሰራተኛው ተቀጥሮ በሚያገልግልበት ወቅት ለሚያደርሰው የገንዘብና የንብረት መጥፋትና መጉደል ነው በማለት የፍ/ህ/ቁ 1933 (1) እና 1897 በመጥቀስ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ በመሰረቱ ዋሱ ከባለዕዳው ጋር ያለበት የአንድነትና ጣምራ ተጠያቂነት በማስረጃ የሚረጋገጥ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ግን ፍርድ ቤቱ የፍ/ህ/ቁ 1928 አለማየቱ የዋስትናን ትርጉም አላግባብ እንዲለጠጥ ያደርጋል፡፡ ሌላው ዋስትና በጣምራ (joint guarantee) ከባለዕዳው ጋር ሊሰጥ ይችላል፡፡ /የፍ/ህ/ቁ 1933 ተመልክቷል፡፡ /በዚህ ጊዜም ዋሱና ባለዕዳው በአንድነትና ሳይከፋፈል አላፊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ /የፍ/ህ/ቁ 1897/
በአጠቃላይ የዋሱ ግዴታ የሚጀምረው ባለዕዳው ግዴታውን መወጣት ካልቻለ ነው፡፡ ሆኖም ግን ዋሱ አስቀድሞ የተለያዩ መከላከያዎችን ሊያነሳ እንደሚችል በተለይም ዋሱ በተከሰሰ ጊዜ ከባለዕዳው ጋር ተከራከር የማለት መብት (benefit of discussion) እንዲሁም የባለዕዳውን ንብረት ለባለገንዘቡ የመምራትና የማሳየት መብት (asset discussion) አለው፡፡ /የፍ/ህ/ቁ 1935 እና 1936/
2.2. የንብረት ዋስትና (Real security)
ሌላኛው በፍትሐብሔር ሕጉ ዋስትናን የተመለከተው ጉዳይ የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት በዋስትናነት ማቅረብ የሚችልበት መንገድ ሲሆን ይህም በአጠቃላይ የንብረት ዋስትና በመባል ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ ፍትሐብሔር ሕግም የንብረት ዋስትናን በተመለከተ በርካታ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ የንብረት ዋስትናም ሲባል በእጅ ያለ ንብረት መያዣ (Lien)፣ የሚንቀሳቀስ ንብረት መያዣ (Pledge)፣ የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ (Mortgage) እና ወለድ አገድ (Antichresis) ናቸው፡፡
በአንዳንድ ድርሳናት ዘንድ በእጅ ያለንብረት (lien) እንደ ንብረት ዋስትና ይቆጠራል፡፡ ለምን ቢባል አንድ ግለሰብ ለአንድ ጉዳይ ማስፈጸሚያ በሚል የተረከባቸውን ንብረቶች በተለይም ደግሞ ለቀጣሪው (ባለገንዘቡ) ጥቅም በሚሆንበት ጊዜ ያዡ ተገቢ የአገልገሎት ክፍያም ሆነ ጥቅማጥቅሞች ካለተከፈለው የያዘውን ንብረት እንደ ገንዘብ ማስከበሪያ ማድረግ ስለሚያስችለው ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ ዋስትና በኢትዮጵያ ሕግጋትም እውቅና የተሰጠው ነው፡፡ ለምሳሌ፡-ወኪል ሆኖ የወካዩን ተግባር ያከናወነ ሰው ክፍያ ካልተከፈለው በውክልና ወቅት የተረከበውን ንብረት ሊይዝ ይችላል፡፡ /የፍ/ህ/ቁ 2224 ይመለከቷል፡፡ /በእጅ ያለ ንብረትን በመያዣነት መያዝን በተመለከተ ሌሎች በርካታ የፍትሐብሔር ድንጋጌዎች አሉ፡፡ እነዚህም አንቀጽ 1946፣ 1971፣ 1973፣ 1990፣ 2247፣ 2320፣ 2726፣ 2794 እና 2846 ናቸው፡፡
ሁለተኛው ዓይነት የንብረት ዋስትና ደግሞ የሚንቀሳቀስ ንብረት ዋስትና (pledge) ነው፡፡ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ባለዕዳው ለውል አፈጻጸም ሲል ለባለገንዘቡ አንድን የሚንቀሳቀስ ንብረት በመያዣነት የሚሰጥበት ዘዴ ነው፡፡ ለምሳሌ፡-አንድ ሰው ከአንድ አበዳሪ 10,000 (አስር ሺ) ብር ቢበደር እና ለብድሩ ደግሞ አንድ ቴሌቪዥን እንደዋስትና ቢያቀርብ የዚህ መሰሉ ዋስትና በዚህ ክፍል ይመደባል፡፡ በፍትሐብሔር ሕጉም ከአንቀጽ 2825-2874 ባሉ ድንጋጌዎች ይመራል፡፡
ሦስተኛው ዓይነት የንብረት ዋስትና ደግሞ የማይንቀሳቀስ ንብረት ዋስትና (mortgage) ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ ዋስትና ምንጩ ውል፣ ሕግ አሊያም ደግሞ የፍርድ ውሳኔ ሊሆን እንደሚችል ከፍ/ህ/ቁ 3041 ቀጥተኛ ንባብ መገንዘብ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ፡- አንድ ሰው ያለውን ቪላ ቤት አስይዞ ከባንክ አንድ ሚሊየን ብር ቢበደር በማይንቀሳቀስ ንብረት ዋስትናነት ይመደባል፡፡ አሁን አሁን የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣን በተመለከተ ያሉ አንዳንድ ድንጋጌዎች የተሻሻሉበትን ሁኔታ ማየት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ፡-ባለገንዘቡ በዋስትና የያዘውን ንብረት የእዳ መክፍያ ጊዜው በማለፋ ምክንያት ለመያዝም ሆነ መሸጥ አይችልም ሲል የፍ/ህ/ቁ 3060/ በግልጽ ያስረዳል፡፡ ዳሩ ግን በባንክ በመያዣ ስለተያዘ ንብረት በሚመለከት በወጣው አዋጅ ቁ.97/1990 አንቀጽ 3 መሰረት ባንኮች በመያዣነት የተቀበሉትን ንብረት ባለዕዳው በውል መሰረት በተባለው ጊዜ መክፈል ካልቻለ የ30ቀን ማስጠንቀቂያ በመስጠት ንብረቱን በሃራጅ የመሸጥ መብት ወይም ለራሳቸው ስመ ንብረቱን ማስተላለፍ ስልጣን አላቸው፡፡
ስለማይንቀሳቀስ ንብረት ዋስትና ሲነሳ የማይረሳ አንድ ነጥብ አለ፡፡ ይህም ለምሳሌ አንድ በዋስትና የተያዘ ባለ ሁለት ፎቅ ህንጻ ዋስትናው ከተሰጠ በኋላ ማሻሻያ ተደርጎበት ባለአራት ፎቅ ቢሆን በዚህ ጊዜ ንብረቱ በሚሸጥበት ጊዜ የቀዳሚነት መብት (preferential right) ማን ይሰጠው? የንብረት መያዣ ባለመብት (mortgagee) ወይስ ህንጻውን የገነባው ሥራ ተቋራጭ? ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የፍ/ህ/ቁ 3067 ግልጽ ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡ በዚህም መሠረት ሥራ ተቋራጮች የቀዳሚነት መብት አላቸው፡፡
ሌላው በ1952ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ባሕር ሕግ (Martime Code) አንቀጽ 30 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች እንደሚያስረዱት መርከብን እንደ ማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ መስጠት ይቻላል፡፡ በተመሳሳይም በንግድ ሕጉ መሠረት የንግድ መደብርንም (business) በመያዣነት መጠቀም ይቻላል፡፡
አራተኛው ዓይነት የንብረት ዋስትና ደግሞ ወልድ አገድ (Antichresis) ይባላል፡፡ ወልድ አገድ የሚባለው ደግሞ ባለዕዳው ግዴታውን ለመፈጸም ማረጋገጫ በማድረግ ለባለገንዘቡ የማይንቀሳቀሰውን ንብረት የሚያስረክብበት ውል ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ ዋስትና በውል ብቻ ይቋቋማል፡፡ /የፍ/ህ/ቁ 3119/ ወልድ አገድ ከማይንቀሳቀስ ንብረት ዋስትና (Mortgage) ለየት የሚያደርገው አበዳሪው በተበዳሪው ንብረት የመጠቀም እና የመገልገል መብት አለው፤ኪራይም አይከፍልም በዚህ ጊዜ ታዲያ በአበደረው ገንዘብ ላይ ወለደ (interest) አይታሰብም ለዚህም ይመስላል ወልድ አግድ የተባለው ይህም በአንቀጽ 3124 ላይ በግልጽ ተመልክቷል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ዋስትና ደግሞ በፍትሐብሔር ሕጉ ከአንቀጽ 3117-3130 ባሉት ድንጋጌዎች ይመራል፡፡
2.3. የፍይናንስ ዋስትና (Financial security)
የፍይናንስ ዋስትና ሲባል የዋስትና ሰነዱንም ሆነ የዋስትናውን ዓይነት የፍይናንስ ተቋማት እንደ ባንክ፣ ማይክሮ ፍይናንስ ተቋማት እና መድን ድርጅቶች የሚያወጧቸው በመሆናቸው ነው፡፡
በ 2005ዓ.ም የወጣው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ አንቀጽ 3.1.6 ላይ ስለ ፍይናንስ ተቋማት ዋስትና አስፈላጊነት እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡
“ኢንሹራንስ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የተሰማራ አንድ ተቋም ሊሸከመው የሚከብደውን አደጋ (Risk) በጋራ በመሸከም የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቱን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል አቅም የሚፈጥር ነው፡፡ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የተሰማሩ ተቋማት ሊያጋጥማቸው የሚችለውን አደጋ ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ከስራው ጋር የተያያዙና ዋስትና የሚፈልጉ ጉዳዮች በቅድሚያ ውል ገብቶ መፈጸም ላይ የግንዛቤ ክፍተት በስፋት ይስተዋላል፡፡ ”
ከዚህ የፖሊሲ አቅጣጫ የምንረዳው የፍይናንስ ዋስትና አሰፈላጊ መሆኑ አያጠራጥርም ዳሩ ግን የፋይናንስ ተቋማት የሚሰጡትን ዋስትና በተመለከተ ግን ግልጽ የግንዛቤ እጥረት አንዳለ ነው፡፡
የፍይናንስ ተቋማት ዋስትና ከሌሎች የዋስትና ዓይነቶች በአንጻራዊነት ለየት የሚያደርጋቸው የሚሰጡት ዋስትና አስተማማኝ መሆኑ ነው፡፡ ይህም እነዚሁ ተቋማት በገንዘብ ረገድ ጠንካራ (creditworthiness) ከመሆናቸው ጋር ይያያዛል፡፡ ለምሳሌ ባለዕዳው ዕዳውን መክፍል ካልቻለ እና የዕዳውን ዋስትና ከፍይናንስ ተቋማት ከወሰደ ባለገንዘቡ ከእነዚህ ተቋማት በቀላሉ ገንዘቡን ሊያገኝ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል የፍይናንስ ተቋማት ዋስትና የራሱ የሆኑ ችግሮች አሉበት፡፡ ለምሳሌ፡- የፍይናንስ ዋስትና በችሮታ (gratitious) የተመሠረተ ሳይሆን ለዚሁ ተግባር ተብሎ የሚጠየቅ ክፍያ ወይም ኮሚሽን ይኖራል፡፡ በዚህ ሳቢያ ከሰው ዋስትና አንጻር ሲታይ የፍይናንስ ዋስትና በክፍያ ላይ (security in consideration) መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ሌላው ደግሞ የፍይናንስ ዋስትናን አስቸጋሪ የሚደረገው ባለዕዳው ከተባለው የገንዘብ ተቋም ጋር ያለው ግንኙነት ነው፡፡ በተለይ በተባለው ተቋም ትንሽ የቁጠባ ገንዘብ ካለው አሊያም ደግሞ የተጠየቀው ገንዝብ ከፍተኛ በሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡
በፍይናንስ ተቋማት የሚዘጋጁ የዋስትና ዓይነቶች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን በጣም የሚታወቁት ሦስቱ ናቸው፡፡ እነዚህም፡- ክሬዲ (letters of credit) ፣ በሁኔታ ወይም ያለ ቅድመ ሁኔታ የሚሰጡ የዋስትና ወረቀቶች (guarantees) እና የውል አፈጻጸም ዋስትና (performance bonds) ናቸው፡፡
2.3.1.ክሬዲ (Letter of Credit)
በክሬዲ ባለዕዳው ባንክ በመቅረብ የተወሰኑ ሁኔታዎችን በመጠበቅ በሰነዱ ተጠቃሚ ለሆነ ሰው ገንዘብ የሚከፍልበት የዋስትና ሰነድ ነው፡፡ ክሬዲ አብዛኛውን ጊዜ በዓለም አቀፍ የንግድ ግብይቶች ተፈጻሚ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ገዥው ከአቅራቢያው ከሚገኘው ባንክ በቂ ተቀማጭ ገንዘብ ሊኖረው ግድ ይላል፡፡ ከዚያም ከባህር ማዶ ለሚያስመጣው ዕቃ የክሬዲ ሰነድ እንዲዘጋጅለት ይጠይቃል፡፡ የተዘጋጀውንም ሰነድ ለሻጩ ይልክለታል፡፡ ከዚያም ሻጩ ደግሞ ወደ መርከብ ወይም አውሮፕላን የጫነበትን ሰነድ (shipment document) ለባንኩ ወይም ገዥው ይልካል፡፡
በዚህ ጊዜ ክሬዲው አንድም የመክፍያ መንገድ ሆኖ ያገለግላል፡፡ አሊያም ደግሞ ለግብይቱ እንደ ዋስትና ማስከበሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ፡- አንድ ነጋዴ ከውጭ አገር ለሚያስመጣው ምርት በአቅራቢው ከሚገኝ ባንክ ቀርቦ የክሬዲ ወረቀት እንዲወጣለት ቢጠይቅ፣ ሺያጩም ተገቢውን ጊዜ ጠብቆ ዕቃውን በመርከብ ቢለክልት፤ በግዥ እና ሻጭ መካከል ባለ ውል የክፍያው መንገድ በክሬዲ ወረቀት ነው ተብሎ ከተስማሙ ባንኩም የተባለውን ገንዘብ ለሻጭ ይልካል፡፡
ክሬዲ የፍይናንስ ዋስትና የሚሆነው ባአንድ በኩል ሻጩ በውል ለሸጠው እና ላስረከበው ዕቃ በውሉ መሰረት ክፍያው እሰከሚፈጸምለት ድረስ የሚይዘው ሰነድ በመሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩልም ገዥው ሻጩ ስጋት እንዳይገባው በማሰብ ሰነዱን ከባንክ አውጥቶ ለውል ማስፈጸሚያነት በማቅረቡ ነው፡፡
ክሬዲ በኢትዮጵያ ንግድ ሕግም የታዋቀ የክፍያ መንገድ እንዲሁም የፍይናንስ ዋስትና (financial security) ነው፡፡ በተለይም የን/ሕ/ቁ 959-967 ያሉ ድንጋጌዎች የክሬዲ ሰነድ ዋስትና ወረቀትን የሚመለከቱ ናቸው፡፡
በተግባርም ስናየው ለምሳሌ፡-የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (Commercial bank of Ethiopia) በወጪ እና ገቢ ንግዶች ላይ ከሚሰጣቸው ዋስትና አገልግሎቶች አንዱ የክሬዲ ሰነድ ነው፡፡
2.3.2.በሁኔታ ወይም ያለቅድመ ሁኔታ የሚሰጡ ዋስትናዎች (Conditional or unconditional Guarantees)
የፍይናንስ ተቋማት በተዋዋዮች መካከል ለሚኖር ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ በቅድመ ሁኔታም ይሁን ያለቅድመ ሁኔታ ዋስ የሚሆኑበት መንገድ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ! የተባለው የፍይናንስ ተቋም አንደኛው ወገን በውሉ መሰረት ግዴታውን ሳይወጣ ቢቀር በገባው ውል መሰረት የሚጠየቅበት ሁኔታ ነው፡፡ የፍይናንስ ተቋሙ ዋስ እንደመሆኑ መጠን ደንበኛው (ለምሳሌ፡ሥራ ተቋራጩ) በውል ያለበትን ግዴታ መወጣቱን በማስመልከት ሊገባ ይችላል፡፡
ልክ እንደ ሰው ዋስትና ሁሉ የፍይናንስ ተቋማት ዋስትና ወረቀት በሚሰጥበት ጊዜ ዋሱ (ባንክ) ደንበኛው (ተበዳሪው) ያለበትን ግዴታ በጊዜ ካልተወጣ በውሉ መሰረት ባንኩ ለተጠቃሚው (ባለገንዘቡ) የሚከፍልበት መንገድ ነው፡፡
ነገር ግን በውል ባለገንዘቡ እና ባለዕዳው ባደረጉት የውል አፈጻጸም ዋሱ (ባንክ) አላፊነት ቀዳማዊ ነው ብለው ከተስማሙ የፍይናንስ ዋሰትናው ባንኩን ያልቅድመ ሁኔታ (unconditionally) እና እንደተጠየቀ (upon demand) እንዲከፍል ያስገድደዋል፡፡ የዚህ ዓይነቱ የባንኮች ተጠያቂነት አሰራር በአብዛኛው በኤሲያ አገራት ይሰራበታል፡፡
ለምሳሌ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሌሎች ንግድ ባንኮች ውስጥ የሚከተሉት የዋስትና ዓይነቶች ይሰጣሉ፡-የጨረታ ሰነድ ዋስትና (bid bond)፣ የውል አፈጻጸም ዋስትና (Performance bond)፣ ቅድመ ክፍያ ዋስትና፣ የብድር ዋስትና (loan guarantee)፣ የዋና ገንዘብ መያዣ ዋስትና (retention guarantee) እና የጉምሩክ ቀረጥ ዋስትና ናቸው፡፡
ሌላው ዓይነት ዋስትና ደግሞ የገንዘብ ዋስትና ግዴታ ሰነድ (financial guarantee bond) ነው፡፡ ይህ የዋስትና ሰነድም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በመድን ድርጅቶች ሲሰራበት የነበረ የዋስትና ሰነድ ነው፡፡ ይህን ሰነድ የያዘ ባለገንዘብ ባለዕዳው ግዴታውን ባልተወጣ ጊዜ ከአበዳሪው ባንክ ቀርቦ የተባለውን ገንዘብ ተጠቃሚ የሚያደርግ (Payable on demand) ሰነድ ነው፡፡ ዳሩ ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመድን ድርጅቶ ሊደርስባቸው ከሚችል ኪሳራ ለመጠበቅ በሚል በመመሪያ ቁ.24/2004 መከልከሉ የሚታወስ ነው፡፡
በተለይም ከመመሪያው መግቢያ አንቀጽ 1 ላይ መገንዘብ እንደሚቻለው እኤአ ከ2004ዓ.ም በፊት የመድን ድርጅቶች የገንዘብ ዋስትና ግዴታ እና ያለቅድመ ሁኔታ የሚሰጡ ሰነዶችን ያወጡ ነበር፡፡ ይህም ጉዳይ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በቅጽ 13 በሰ/መ/ቁ 36935 በአፍሪካ ኢንሹራንስ አ.ማ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መካከል በነበረው ክርክር መድን ድርጅቶች ከክልከላው በፊት የገንዘብ ዋስትና ሰነድ (financial guarantee bond) ማውጣት እንደሚችሉ ትርጉም ለመስጠት መክሯል፡፡ ዳሩ ግን የመድን ድርጅቶች አስተማማኝ ጥበቃ ለማድረግ እና በኢትዮጵያ የጠለፋ መድን (re-insurance) ካለመኖር ጋር ተያይዞ ከላይ የተጠቀሱትን የዋስትና ዓይነቶች ማውጣት እንደማይቻል የመመሪያው አንቀጽ 2 ግልጽ ንባብ ያስረዳል:: ሆኖም ከድንጋጌው ተቃራኒ ንባብ (acontrario) መረዳት እንደሚቻለው መድን ድርጅቶች በቅድመ ሁኔታ የተመሰረተ የዋስትና ሰነድ (conditional insurance bond) ከማውጣት አይከለከሉም፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments