Font size: +
19 minutes reading time (3737 words)

ድጋፍ የተሳነው እና እየተዘነጋ የመጣው የኮንስትራክሽን ውሎች አማራጭ የግጭት አፈታት

ግጭት የሰው ልጅ ወደ ምድር ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ  የነበረ፣ ያለ እንዲሁም በእልት ተዕለት የማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ ሊከሰት የሚችል አለመግባባት ወይም ልዩነት ነው፡፡ ይህም አለመግባባት በጊዜና በሚገባ ካልተፈታ፣ በማህበረሰብ ውስጥ ከፍተኛ ስጋትና አለመረጋጋት ሊፈጥር ይችላል፡፡ ይህንንም ተግዳሮት ለማስቀረት በማሰብ አብዛኛውን ጊዜ የመንግስት ባህላዊ ተግባር (traditional functions of government) በመባል የሚታወቀው ማለትም ቋሚ የሕግና ፍትሕ ሥርዓት በመገንባት ለሚነሱ ቁርሾዎች መላ ሊያገኙበት የሚችልበትን ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ ይህም ሊሆን የሚችልበት አንዱ መንገድ መደበኛ ፍርድ ቤቶችን ወይም አማራጭ የግጭት መፍቻ መንገዶችን በየደረጃው በማቋቋምና ለሚነሱ ግጭቶች በጊዜ መፍትሄ በመስጠት ሊሆን ይችላል፡፡

“In business as in life, you don’t get what you deserve, you get what you negotiate.”

Dr.Chester L. Karrass

በዓለምአቀፍም ሆነ በአገር ወስጥ የሕግ ሥርዓት አስተማማኝና በቂ የግጭት አፈታት ሥርዓት መኖር በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም መሆኑ በህብረተሰቡ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ኑሮ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ከማምጣቱ ባሻገር ተጠባቂ የሕግ ሥርዓት (Predictable legal system) እንዲኖረን ያደርጋል፡፡

የግጭት አፈታት ሲባልም በግራ ቀኝ በኩል የሚመጣ ማነኛውም ግጭት ወይም አለመግባባት ለመፍታት የሚተገበር ሥነ-ስርዓት ሲሆን ይህም በመደበኛው የፍርድ ሂደት ወይም በአማራጭ የግጭት አፈታት (alternative dispute resolution) መንገድ ሊከናወን ይችላል፡፡

ሆኖም ግን መደበኛ ፍ/ቤቶች ካላቸው የሥራ ጫና፣ የጉዳይ መረጣ እንዲሁም ተደራሽነት ውሱኑነት ሳቢያ የሚከሰቱ ግጭቶችን ተቀብለው ላይመለከቱ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ ዓይኖች ሁሉ ወደ አማራጭ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ያመራሉ፡፡

አማራጭ የግጭት አፈታት የሚባለው ከመደበኛ ፍ/ቤት ውጭ ግጭትን ለመፍታት በማሰብ የሚተገበሩ መንገዶች ናቸው፡፡ አማራጭ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ስንልም ከመደበኛ ፍ/ቤትና ከአስተዳደር ፍ/ቤቶች ውጭ ያሉ በርካታ የግጭት መፍቻ ሥልቶች ያቀፈ ማለት ነው፡፡

መደበኛ ፍ/ቤቶች በሌሉበት በጥንት ዘመን አብዛኛውን ጊዜ በባህላዊ መንገድ ግጭቶች የሚፈቱበት መንገድ ነበር፡፡  ይህም አካሄድ ለበርካታ አመታት ሲሰራበት ቆይቷል፡፡ አሁንም ቢሆን የዚህ መሰሉ አካሄድ ወደ ከተሞች አካባቢ እየቀነሰ ቢመጣም አብዛኛውን ጊዜ በገጠራማ አካበቢዎች ይሰራበታል፡፡ በተለይም ደግሞ አማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ባላቸው አንጻራዊ ጥቅም በመደበኛ ፍ/ቤቶች ሳይቀር ተከራካሪዎቹ ጉዳያቸውን በዚህ መንገድ እንዲፈቱ ጭምር ምክረ ሃሳብና ትዕዛዝ የሚሰጡበት ሁኔታ አለ፡፡  

አማራጭ የግጭት አፈታት የተባለበትም ምክንያት የመደበኛ ፍ/ቤትን ተክተው በአማራጭነት በቀረቡ መንገዶች በመሆናቸው ነው ለምሳሌ የሁለትዮሽ ድርድር፣እርቅ፣ሽምግልና ወዘተ በማምራት የግራ ቀኙ ተከራካሪ ወገኖች ጉዳይ መፍትሄ የሚገኝበት ዘዴ ስለሆነ ነው፡፡ ለአብነትም የዓለምአቀፍ የንግድ ም/ቤት ማቋቋሚያ ሕግ መግቢያ ላይ የአማራጭ የግጭት አፈታት አስፈላጊነትን ጠቆም አድርጎ ለማቅረብ ይሞክራል፡፡

የንግድ ግጭቶችንና ልዩነቶችን ለመፍታት ሰላማዊ የግጭት አፈታት አይነተኛ መፍትሄ ይጫወታል፡፡ ይህም በፍርድ ቤት ክርክር ወቅት ወይም በሽምግልና እንዲሁም በሌላ በሦስተኛ ወገን በታገዘ የግጭት አፈታት ሕግጋት ሊከናወን ይችላል፡፡

በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን አማራጭ የግጭት አፈታት (construction alternative dispute resolution) በይፋ የተዋወቀው በ1952ዓ.ም በወጣው የፍትሐብሔር ሕግ ነበር፡፡ ሆኖም ግን የኮንስትራክሽን ባለሙያዎችን ጨምሮ በሕግ አማካሪዎች ዘንድ ትኩረት መሳብ የጀመረው በቅርቡ ነው፡፡  አማራጭ የግጭት አፈታት አሰፈላጊነቱ ብሎም አዋጭነቱ እየታመነበት የመጣበትም ምክንያት “የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ” እንዲሉ በግጭት አፈታት ሂደቱ ውስጥ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ከዳኝነት እስከ ተከራካሪነት በጥልቀት ስለሚሳተፋበት ጭምር ነው፡፡

እርግጥ ነው የግንባታ ሂደት ፈርጀ ብዙ እንዲሁም መጠነ ሰፊ ሥራዎች የሚከናወኑበት እንቅስቃሴ ነው፡፡ በተለይም በውስጡ የያዛቸው በርካታ ተቋማዊ ሁነቶች በራሳቸው አለመግባባት አንዳንዴም ግጭት ሲፈጥሩ ይስተዋላል፡፡ በተለይ በርካታ የውል ግንኙነቶች መኖራቸውን ተክትሎ በተለይ በአሰሪው(ባለቤቱና) እና በሥራ ተቋራጩ፣ በአሰሪው እና በአማካሪው፣ በሥራ ተቋራጩ እና በአማካሪው፣ በሥራ ተቋራጩ እና በንዑስ ሥራ ተቋራጩ፣ በባለቤቱና ንዑስ ተቋራጮች አለፍ ሲልም በንዑስ ሥራ ተቋራጮች መካከል በርካታ ጠቅላላና ዝርዝር ውሎች መኖራቸውን ተከትሎ የተለያዩ አለመግባባቶች ሲከሰቱ ይታያል፡፡ እዚህ ላይ ሊታወቅ የሚገባው ነገር ለገጭቶች መከሰት እንደምክንያትነት የሚነሳው የግንኙነቶችና ውሎች መብዛት ሳይሆን የፕሮጀክት ሥራ-አመራር (project management) መዛባት እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜ ውሎች የሚነደፋበት አግባብ በቀጥታ ከቀደሙ ውሎች በመገልበጥ በሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡ ከግንባታ ውልች ግንኙነት አንጻር የኮንስትራክሽን ግጭቶችና አለመግባባቶች ምንጮች በሚከተሉት አበይት ጉዳዮች ሊጠቃለሉ ይችላሉ፡-

አንደኛ ከጊዜ አንጻር የሚነሱ ጉዳዮች በተለይ ሥራ ተቋራጩ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ባለማጠናቀቁ ምክንያት ተጨማሪ ጊዜ በመጠየቁ ብሎም ሌሎች ውል የወሰዱ አካላት ቅር በመሰኘታቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛም ከፕሮጀክት ገንዘብ አከፋፈል ጋር የተያያዙ አለመግባባቶች ናቸው፡፡ ይህም የሚሆነው ሥራ ተቋራጩ ለሰራቸው ተጨማሪ ሥራዎች የሚጠይቀው የገንዝብ መብት ጥያቄ (claim) አሊያም ደግሞ የማካካሻ ገንዝብ ጉዳይ ጋር ይያያዛል፡፡ በተለይ በገሃድ የሚታዩ የጥራት ደረጃዎች ጉደልት አሰሪውን እንቅልፍ ሊነሳውና ወደ ግጭት ሊቆሰቁሰው ይችላል፡፡ ይህም በዋናነት ከተበላሸ የግብዓት አጠቃቀም ወይም የሥራ አፈጻጸም ጋር ይገናኛል፡፡

በአጠቃላይ አማራጭ የግጭት አፈታት ጠቀሜታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ በኮንስትራክሽን ዘርፍም አዋጭነቱ እየታመነበት እና አብዛኝውን ጊዜም በግንባታ ውሎች ላይ ስለ ግጭት አፈታት የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በአማራጭ የግጭት መፍቻ መንገዶች  ጉዳዮች እንዲያልቁ ጭምር ተዋዋዮች የተየቡበት (የወጠኑበት) ስለሆነ ነው፡፡

1.    የኮንስትራክሽን ግጭት አፈታት አጠቃላይ ምልከታ

አብዛኛውን ጊዜ የኮንስትራክሽን ውሎች ውስብስብ መሆናቸውን ተከትሎ ግጭቶት መከሰታቸው የሚደንቅ ነገር አይደለም፡፡ በሌላ አባባል በዘርፋ በርካታ ባለድርሻ አካላት ማለትም ባለቤቱ፣ ቀራጺው፣ መሀንዲሱ፣ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ፣ ሥራ ተቋራጩ፣በርካታ ንዑስ ተቋራጮች፤የእቃ እና ግብአት አቅራቢዎች፣ የመድን ሰጪ ድርጅቶች፣ ባንኮች፣ አበዳሪ ተቋማት…ወዘተ በአብዛኛውም እነዚህ ባለድርሻ አካላት አንድም በቀጥታ የፕሮጀክቱ ሰራተኞች አሊያም የሌላ ድርጅት ተቀጣሪዎች ሆነው መሳተፋቸውን ተከትሎ የተለያዩ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላል፡፡  እነዚህም በሥራው መዘግየት፣ ያልተጠበቀ ወይም የታሰበበት ተጨማሪ ሥራ፣ የተበላሸ ሥራ(defective work)፣ የወጪ መጨመር፣ አደጋ በመከሰቱ ምክንያት የግንባታው የአሰራር ጉድለት መኖር፣ የመረጃ ፍሰቱ መዘገይት፣ የግንባታ ሰነድ አተረጓጎም ችግር፣ሌሎች ያለተጠበቁ ከአቅም በላይ (force majeure events) ሁነቶች በኮንስትራክሽን አፈጻጸም ወቅት መከሰት ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህም ችግሮች በአግባቡ ካልተፈቱና ካልተስተናገዱ፤ከፍተኛ የሆነ አልመግባባት ውስጥ ሊያስገባ ይቻላል፡፡ በዚህም ሳቢያ የተነሱት ቁርሾዎች ወደ ሙግትና ክርክር ሲያመሩ ይስተዋላል፡፡

2.   በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ  አማራጭ  የግጭት  አፈታት እና የፕሮጀክት ሥራ አመራር

በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ጉዳይ ወደ ለየለት ግጭት እንዳያመራ ከተፈለገ ብቁ የሆነ የፕሮጀክት ሥራ አመራር እንዲሁም የውል አስተዳደር ያስፈልጋል፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ጠንካራ የሆኑ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጆች ያስፈልጋሉ፡፡ ለምን ቢባል የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጆች ተራ አለመግባባቶች አድገው ወደ ግጭት እንዳያመሩ፣የሥራ ግንኙነት መስመር እንዳይሻክር፣በፕሮጀክት ርክክብ ጊዜ እና ጥራት ላይ ቅራኔ እንዳይኖር ብሎም ወደ ግጭት አፈታት ተሂዶ ሊወጣ የሚችለውን ገንዘብ አስቀድሞ እንዲቀር በማድረግ ረገድ የሚጫወቱት ሚና የጎላ በመሆኑ ነው፡፡

ሌላው የፕሮጅክት ሥራ አመራር ሰዎች ሚና ሊሆን የሚችለው በተለይ አስቀድመው የፕሮጀክት ሥራ አለመግባባት ሊነሳባቸው የሚችሉ ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣት እና በእቅድ ተጠንቅቆ በማካተት ምናልባት የግጭትን መከሰት ሊቀንሱ ይችላሉ በዚህም የተነሳ ሁሉንም የሚጠቅም የተሳካ የፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ ሊደረስ ይችላል፡፡

የውል አስተዳደር ሰዎች ግጭት እንዳይከሰት በማድረግ ረገድ የጎላ ሚና ሊጫዎቱ ይችላሉ፡፡ በተለይ በውሉ የሰፈረው ቃል ያልማንም ጣልቃ ገብነት ሕግንና ህሊናን መሰረት አድርገው የሚያከናውኑ ከሆነ አለመግባባትን መቀነስ ይቻላል፡፡ ለምን ቢባል በተለመደው የላቲን ብሄል “pacta sunt servanda” ወደ አማርኛው ስንመልሰው “ሰው በቃሉ ይታሰራል ” እንዲሉ ውልን የሚያስተዳድሩ አካላት ውሉ ላይ በሰፈረው ፍሬ ነገር በመመራት ፕሮጀክትን ማስተዳደር ከቻሉ አስቀድሞ የግጭት ቀዳዳን መድፈን ይቻላል፡፡

በአጠቃላይም በኮንስትራክሽን ግጭት አፈታት ያስፈለገበት ምክንያት በተደጋጋሚ የሚከተሉት ችግሮች በመከሰታቸው እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡  እነዚህም፡-

  • የውል መጣስ
  • በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ክፍያ አለመፈጸም
  • የመረጃ ፈሰቱ በቂ አለመሆኑ
  • የግንባታ ዲዛይን፣መዘርዝሮች፣ፕላኖች እና ስዕሎች ጉድለት መኖር
  • የፕሮጀክት አደጋዎች
  • የሥራ ቦታ ደህንነት ጉድለት
  • ያለበቂ ትዕዛዝ የፕሮጀክት ሥራው መቀየር
  • ፕሮጀክት የማስተዳደርና የመምራት አቅም ክፍተት
  • ሥራውን በቅንጅት አለመስራት ናቸው፡፡

በቅርብ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ በፕሮጀክት ሥራ አፈጻጸም ወቅት ግጭት ሊያስከትሉ የሚችሉ ዋና ዋና ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡፡

፩-በአንድ ወገን ብቻ የሚዘጋጁ ውሎች/One-Sided contracts/:-በአንድ ወገን ብቻ የሚዘጋጁ ውሎች የአንድን ወገን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል የሚነደፉ ውሎች ናቸው፡፡ በዚህ ሳቢያ በሌላኛው ወገን ላይ አሉታዊ ጉዳቶች ከማስከተሉ ባሻገር ያልተጠበቁ ሁነቶችን ሊያስተናግዱ ይችላሉ፡፡ እርግጥ ነው አንድ ወግን የሚያዘጋጃቸው ውሎች የሚዛናዊነት ጥያቄ ያስነሳሉ፡፡ ሆኖም ግን አሁን አሁን በሙያ ማህበራት የሚዘጋጁ ወጥ ውሎች(Standard conditions of contract) መምጣት ጋር ተያይዞ እንዲህ ዓይነት ችግር ሊያስቀር ይችላል፡፡ በመሰረቱ አንድ ወገን የሚያዘጋጃቸው ውሎች (adhesive contracts) በኮንስትራክሽን ኢንዲስትሪ በጣም ሥር እየሰደዱ መጥተዋል፡፡ ሆኖም ግን በትርጉም ወቅት መጣርስ ቢመጣ ላዘጋጃቸው ወገን መሆን ቀርቶ ውል ለተቀበለው ሰው በሚጠቅም መልኩ ሊተረጎሙ እንደሚችል ከፍ/ህ/ቁ 1738 ንባብ መረዳት እንችላለን፡፡

፪-የፕሮጀክት ርክክብ ሥርዓት የመምረጥ ችግር፡-ለፕሮጀክት የሚመረጡ የርክክብ ሥርዓት ዘዴዎች አንዳንድ ጊዜ በይዘት፣በጊዜ፣ገንዘብ እና የአላፊነት መውሰድ ጋር ተያይዞ አለመግባባትን ሊፈጥር ይችላል፡፡ በተለይም ባለቤቱ ሊገነባው ያሰበው ህንጻ በቶሎ ተፈጽሞለት ከተባለው ግንባታ ሊገኝ የሚችለውን የኢኮኖሚ ጥቅም ሊያሰላ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ባለቤቱ የሚገነባው ህንጻ በጥር አልቆ ታችኛውን ፎሎር ለሱቅ፣በግንቦት ደግሞ መካከለኛውን ክፍል ለቢሮ እንዲሁም ቀሪውን ደግሞ በመስከረም ለት/ቤትነት አገልግሎት የሚውል በማለት የኪራይ እቅድ ሊያወጣ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ ከእቅዱ ጋር ተስማሚ የሆነ የፕሮጀክት ግንባታ ርክክብ ሊመርጥ ይችላል፡፡ በዓለምአቀፍም ሆነ በአገር ውስጥ ፕሮጀክቶች የሚታወቁ የፕሮጀክት የርክከብ ዓይነቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሀ/ ዲዛይን-ጨረታ-ግንባታ (Design-Bid-Build (DBB)):-ይህ ዓይነቱ መንገድ በጣም የተለመደ ባህላዊ የግንባታ ርክክብ መንገድ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ባለቤቱ አስቀድሞ ከመሀንዲሱ ጋር አሊያም ከአርክቴክቱ ጋር በመነጋገር የግንባታ ንድፈ-ሃሳብ ያቀርባል፡፡ ከዚያም ወደ ጨረታ ይገባና በጣም ዝቅተኛ የግንባታ ሃሳብ ላቀረበ ሰው ሥራው ይሰጣል፡፡ ሆኖም ግን በተግባር በዚህ መንገድ የሚሰሩ ግንባታዎች ጋር የሚነሳው የግጭት ቁርሾ ከጥራት እንዲሁም ጊዜ ጋር ይገናኛል፡፡

ለ/ ዲዛይን-ጨረታ-ግንባታ-እና የግንባታ ሥራ አመራር (Design-Bid-Build with Construction Management (DBB with CM):-በዚህ ጊዜ ደግሞ ባለቤቱ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ በመቅጠር የፕሮጀክት ሥራ አመራርን ዕውቀትን በመጠቀም ሥራው በአግባቡ እየሄደ መሆኑን ለንዑስ ተቋራጮች እንደ አስፈላጊነቱ ጥሪ በማድረግ ሥራው እንዲሰራ የሚደረግበት አግባብ ነው፡፡

ሐ/ ዲዛይን-ግንባታ(Design-Build (DB):-ባለቤቱ ያቀደውን የግንባታ ንድፈ-ሃሳብ ከመሃንዲሱ ጋር በመሆን ወደ ተግባር የሚገባበት መንገድ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ዘዴ በአብዛኛውን ጊዜ ፕሮጀክቱ በፍጥነት እንዲገነባ (fast-track delivery system) እና የባለቤቱን ፍላጎት ሊያሟላ ይችላል፡፡

መ/ ገነባ-ሥራ አስጀመረ-አስተላለፈ (Build-Operate-Transfer (BOT):-ይህ ዓይነቱ ሥርዓት ደግሞ በተለይ ለትልልቅ ፕሮጀክቶች በተለይ መንግስት በኮንሲሽን ውሎች (concession contracts) የሚመጡ የግንባታ ውሎች ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሥራ ተቋራጩ ራሱ ዲዛይን አውጥቶ፣ገንብቶ፣ሥራ አሰርቶ ቢበላሽ ጠግኖ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለባለቤቱ የሚያስተላልፍበት መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ፡-የኢትዮጵያ አዲስ-አዳማ ፈጣን መንገድ ተጠቃሽ ነው፡፡

ሠ/ የተቀናጀ የፕሮጀክት ርክክብ (Integrated Project Delivery (IPD):-ይህ ደግሞ የፕሮጀክት ተሳታፊዎች በቅንጅት እና ውጤት ተኮር ሂደት እንዲሳተፉ የሚያደርግ ነው፡፡

ወደ ተናሳሁበት ጉዳይ ስመለስ ባለቤቱ ከላይ ከተጠቀሱት መንገዶች ውስጥ ለፍላጉቱ ማሳኪያ የሚሆን የርክክብ ዘዴ ካልመረጠ አለመግባባቶችና ግጭቶች መከሰታቸው አይቀሬ ነው፡፡  

፫-የፕሮጀክት ዲዛይን ችግር፡-ይህ ድግሞ ሊከሰት የሚችለው ያልተሟላ፣ የተሳሳተ እና የተበላሸ የዲዛይን ፕላን በሚዘጋጅበት ወቅት ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ያልተጠበቀ ፕሮጀክት ወጪ እና መዘግየት ብሎም ግጭት ሊያስከትል ይችላል፡፡

፬-የሳይት ሁኔታዎች፡- አብዛኛውን ጊዜ ሥራው በጨረታ ውድድር ለአሸናፊዉ ከተሰጠ በኋላ ሥራ ተቋራጩ ፕሮጀክቱን የሚያከኛውንበት ቦታ እጅግ አደጋች ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ባለቤቱ ተጨማሪ ክፍያ የማይሰጥ ከሆን ወደ አለመግባባት ሊያመሩ ይቻላል፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት የግጭት መንስኤዎች እንደማሳያ እንጂ ሌሎች ለፕሮጀክት አፈጻጸም ግጭት መነሻ የሚሆኑ የመልካም አስተዳደር እና በተለይ በመንግስት ዉሎች ድግሞ መንግስታዊ ጫናዎች ሊከሰቱ እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል፡፡

የኮንስትራክሽን ግጭት አፋታት ሲባልም በዋናነት ሊያካትት የሚችልው ጉዳይ በመደበኛ መንገድ አሊያም የአማራጭ መፍቻ መንገዶችን ነው፡፡ ታዲያ ካላይ የተባሉት ነገሮች በሚከሰቱበት ጊዜ አማራጭ ግጭት አፈታት ዘዴዎችን በመጠቀም የፕሮጀክት አለመግባባትንና ግጭትን ልንቀንስ እንችላለን፡፡

3.  የግጭት አፈታት ዓይነቶች

በአንድ አገር የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የተለያዩ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ሊኖሩ ይችላል፡፡ በጣም በሰለጠኑ አገራት መደበኛ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ጨምሮ አማራጭ የግጭት መፍቻ መንገዶችን በመጠቀም ለሚነሱ ግጭቶች እልባት ይሰጣል፡፡ አንዳንድ አገራት ደግሞ በባህላዊ መንገድ በአካባቢያቸው በሚገኝ የግጭት መፍቻ ተቋም ወይም ግለሰብ በማምራት ጉዳያቸውን ሊፈቱ ይችላሉ፡፡

በዚህ ጹሁፍም ሁለት ዓይነት የግጭት መፍቻ መንገዶችን ማለትም መደበኛ እና አማራጭ የተባሉትን የግጭት አፈታት ዘዴዎች እንመለከታለን፡፡

3.1. መደበኛ መንገድ

መደበኛ የግጭት አፈታት መንገድ የሚባለው ተከራካሪ ወገኖች ጉዳያቸውን ለመፍታት በማሰብ  በሕግ ለተቋቋመ ፍ/ቤት ወይም የአስተዳደር ችሎት በመሄድ የሚፈቱበት መንገድ ነው፡፡ በአገራችንም የዚህ አይነቱ የግጭት አፈታት ዘዴ በዘመናዊ መንገድ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ-መንግስት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በከተሞች አካባቢ እስካሁን ድረስ የግጭት አፈታትን የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ ጥቅም ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ-መንግስት የመደበኛ መንገድ ግጭት አፈታትን በማስመልከት በአንቀጽ 78 እና 79 ላይ ልዩ ሽፍን ሰጦት እናገኛለን፡፡ በተለይም አንቀጽ 78(4) ላይ እንዲህ የሚል ዐ/ነገር እናገኛለን፡፡

 “የዳኝነት ሥልጣንን ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ወይም በሕግ የመዳኘት ሥልጣን ከተሰጠው ተቋም ውጭ የሚደረግ፣ በሕግ የተደነገገ የዳንነት ሥርዓት የማይከተል ልዩ ፍርድ ቤት ወይም ጊዜዊ ፍርድ ቤት አይቋቋምም፡፡ ’'

ይህም ማለት መደበኛ የግጭት አፈታት በመጀመሪያ ደረጃ በፍርድ ቤቶች (regular courts) ሊከናወን ይችላል፡፡ አሊያም በሕግ የመዳኘት ሥልጣን በተሰጣቸው ተቋማት (Administrative Tribunals) ሊሆን ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓትም ፍርድ ቤቶች በፌዴራልም ሆነ በክልል ሲቋቋሙ በሦስት እርከን ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህም ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የመጀመሪያ ደረጃ(ወረዳ) ፍርድ ቤት ናቸው፡፡

በሕግ የመዳኘት ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት የሚባሉት ደግሞ የአስተዳደር ነክ ጉዳዮችን የማየት ሥልጣን የተሰጣቸው ተቋማት ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡-የግብር ይግባኝ ኮሚሽን፡ በግብር አወሳሰን ለሚነሱ ቅሬታዎችን የመዳኘት ሥልጣን አለው፡፡ እንዲሁም የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድም ከሠራተኞች የሥራ ሁኔታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የመመርመር ሥልጣን አለው፡፡

መደበኛ የገጭት አፈታት የሚከተሉት ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ በተለይም በመደበኛ ፍርድ ቤት አንድ ጉዳይ የሚታይ ከሆነ የግጭት አፈታቱ በጥብቅ ሥነ-ሥርዓት(formal procedure) ይከናወናል፡፡

እንዲሁም የኃይል ሚዛን እንዲመጣጠን በማድረግ ረገድ የመደበኛ መንገድ ግጭት አፈታት ቀላል የማይባል አስተዋጽዖ አለው፡፡ ለምን ቢባል ተከራካሪዎች በአማራጭ መንገድ ጉዳያቸውን ለመፍታት ከሄዱ አንደኛው ወገን የመደራደር አቅሙን በመጠቀም/exerting unequal bargaining power/ ሄደቱን ጥላ ሊያጠላበት ይችላል፡፡

ሌላው የመደበኛ መንገድ የግጭት አፈታት ጠቀሜታ የካበተ የሕግ እውቀት መኖር ነው፡፡ በአብዛኛው ጊዜ የመደበኛ ፍ/ቤት ዳኞች በሕግ እውቀታቸው እንዲህም አተረጓጎማቸው ከፍተኛ ልምድና ክህሎት ያላቸው ናቸው፡፡ ሆኖም ግን በአማራጭ የግጭት አፈታት ላይ የሚሰማሩ ዳኞች በሙያቸው ጭምር የሕግ እውቀት የሌላቸው በሌሎች ዘርፎች የተመረቁ ባለሙያዎች ሊሆኑ ይችላል፡፡ ለምሳሌ፡-በኮንስትራክሽን ጉዳዮች በግልግል ፍ/ቤቶች የሚታየው አንዱ ገላጋዮቹ የሲቪል ምህንድስና ወይም ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ምሩቃን ሲሆኑ ይታያል፡፡ በዚህ ሳቢያ ምንም እንኳን ለዘርፉ ቅርበት ቢኖራቸውም ሕግን በመተርጎም እንዲሁም አጠቃላይ የሕግ እውቀት ስለሌላቸው አንዳንድ የሕግ ስህተቶች ሲፈጽሙ በተግባር ይስተዋላል፡፡

በመደበኛ የግጭት አፈታት የቀደሙ ፍርዶች በተከታይ ወሳኔዎች ላይ የአስገዳጅነት ሕግ/precedent system/ ተጠቃሽነት ሃይል አላቸው፡፡ ይህም በተለይ በኮመን ሎ (common law) አገራት ላይ ሲስተዋል ይታያል፡፡ በአንጻሩ ድግሞ በአማራጭ መንገድ የግጭት አፈታት በተለይም በግልግል ዳኝነት የቀደሙ ውሳኔዎች ለትክክለኛ ትርጉም አሰጣጥ አስፈላጊ ቢሆኑም አስገዳጅ ግን አይደሉም፡፡

በመጨረሻም በመደበኛ ፍ/ቤት የተሰጡ ፍርዶች ለማስፈጸም አይከብድም፡፡ ሆኖም ግን በአማራጭ መንገድ የግጭት አፈታት ከግልግል በስተቀር ፍርዶችን ማስፈጸም በጣም ከባድ ነው፡፡

3.2. አማራጭ መንገድ

አማራጭ የግጭት አፈታት የሚባለው ደግሞ ከስሙም እንደምንረዳው ግጭት በሚከሰትበት ጊዜ ከመደበኛ የግጭት አፈታት ማለትም ከፍ/ቤት ወይም አስተዳደራዊ ተቋማት ውጪ የሚደረግ የአለመግባባቶች መፍቻ መንገድ ነው፡፡

በአጠቃላይ የአማራጭ የግጭት አፈታት መንገድ የሚከተሉትን ዘዴዎች ሊይዝ ይችላል፡፡ እነዚህም፡-የሁለትዮሽ ድርድር (negotiation) ፣የሦስተኛ ወገን ድርድር (mediation)፣የዕርቅ ስምምነት(Conciliation)፣ የቅድመ ግጭት ግምገማ(early neutral evaultion)፣ ሚኒ ትሪያል(mini trial)፣ የማግባባት ዳኝነት(adjudication) እና ግልግል(arbitration) ናቸው፡፡

አሁን አሁን በኮንስትራክሽን ዘርፍም በአብዛኛው አማራጭ የግጭት መፍቻ መንገዶች በሥራ ላይ ናቸው፡፡ ለዚህ መሆን እንደምክንያትነት የሚጠቀሱት የሚከተሉት ናቸው፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ አማራጭ የግጭት አፈታት መጠቀም ጊዜ እንዲሁም ወጪ ቂጣቢ ነው፡፡ ለምን ቢባል በመደበኛው መንገድ ለምሳሌ በፍርድ ቤት አንድ ጉዳይ ከክስ አከፋፈት እስከ አፈጻጸም ደረስ በትንሹ ከአንድ እስከ ሶስት ዓመት ይፈጃል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ አንድ ጉዳይ በአማራጭ የግጭት መፍቻ መንገድ ከታየአፈጻጸሙን ጨምሮ በወራት እድሜ ሊጠናቀቅ ይችላል፡፡

ሌላው የመደበኛ ፍርድ ቤት ወጪ በአንጻራዊነት ከአማራጭ መንገዶች ከፍ ያለ ነው፡፡ በ1935 ዓ.ም በወጣው የፍ/ቤቶች ዳኝነት ገንዘብ አከፋፈል ደንብ መሰረት ለምሳሌ፡-አንድ የኮንስትራክሽን ውል ክርክር የክሱ ጥያቄ 1,000,000(አንድ ሚሊየን) ብር ቢሆን የፍርድ ቤት ክፍያ 33,500(ሰላሳ ሶስት ሺ አምስት መቶ) ብር ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን በአማራጭ መንገድ ጉዳዩ ለምሳሌ በተባለው ገንዘብ መጠን ልክ ጉዳዩ ወደ አዲስ አበባ ንግድና የዘርፉ ማህበራት ም/ቤት የግልግል ማዕከል ቢሄድ 11,050(አስራ አንድ ሺ ሃምሳ) ብር ይከፍላል፡፡ ይህም ከመደበኛ ፍ/ቤቶች ክፍያ አንጻር በአንድ ሦስተኛ እጅ ያነሰ ነው፡፡

ሌላው የአማራጭ መንገድ የግጭት አፈታት ጠቃሜታ ለግራ ቀኝ ተከራካሪዎች የሚጠቅም ውሳኔ(win-win) ከመድረሱ ባሻገር በተከራካሪዎች መካከል የቀደመ ግንኙነታቸውን በተሻለ መልኩ እንዲኖር ያደርጋል እንዲሁም ለወደፊተ ለሚነሱ ግጭቶች መፍትሄ የማምጣት አቅም አለው፡፡

አማራጭ የግጭት አፈታት በተለያዩ መስፈርቶች ሊፈረጅ ይችላል፡፡ በዋናነት ግን በሦስት መስፈርቶች ተነስተን ልንፈርጀው እንችላለን፡፡ እነዚህም፡-በስምምነት አካሄድ ፣በውሳኔ አሰጣጥ አካሄድ እና በምክር አሰጣጥ አካሄድ ሊሆን ይችላል፡፡

የግጭት አፈታትን በስምምነት አካሄድ እንደሚከተለው ልንመድበው እንችላለን፡፡ እነዚህም የሁለትዮሽ ድርድር (negotiation)፣ የሦስትኛ ወገን ድርድር (mediation)፣ ማመቻቸት (facilitation) እና ሚኒ ትሪያል(mini-trial) ናቸው:: ለምን ቢባል የሁሉም አካሄድ በመጨረሻ ለፍሬ የሚበቃው በሥነ-ሥርዓቱ በተካፈሉ ሰዎች ስምምነት ነው፡፡ በአጭሩ ተሳታፊዎቹ ከስምምነት ካልደረሱ ሂደቱ ዋጋ የለሽ ያደርገዋል፡፡

የግጭት አፈታትን በውሳኔ አሰጣጥም ልንፈርጀው እንችላለን፡፡ ለምሳሌ፡-ግልግል፡፡ በዚህ አካሄድም ግራ ቀኝ ተከራካሪዎች ለሦስተኛ ወገን ጉዳያቸውን አቅርበው ገላጋዩ በሚሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ለአለመግባባቱ እልባት የሚያፈላልጉበት መንገድ ነው፡፡

ሌላው የምክር አሰጣጥ አካሄድን መሰረት በማድረግ ልንከፍለው እንችላለን፡፡ በዚህ ጊዜም ባለጉዳዮች የግጭታቸውን ዝርዝር ሁኔታ ለሦስተኛ ወገን አማካሪ በማቅረብ አለመግባባታቸውን በሚቀርብላቸው የምክር እና የውሳኔ ሃሳብ ሊፈቱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ፡-የሦስተኛ ወገን ገለልተኛ አስተያየት (neutral case evaluation)፣ አጣሪ (fact finding or investigation) ወይም የባለሙያ አስተያየት(expert opinion) ናቸው፡፡

4.  በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የተለመዱ አማራጭ የግጭት አፈታት መንገዶች

በ 2005 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ስለአማራጭ የግጭት አፈታት ምንም ያለው ነገር የለም፡፡ በዚህም ሳቢያ በመንግስት ፖሊሲ ቀራጺያን ዘንድ ጉዳዩ ድጋፍ እየተሳነው እና እየተዘነጋ ያለበትን ሁኔታ እናገኛለን፡፡

የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በቅጽ 9 በሰ/መ/ቁ 38794 በእነ አቶ ሙከሚል መሐመድ እና አቶ ሚፍታህ ከድር መካከል በነበረው ክርክር ላይ በአገራችን የተለመዱትንየአማራጭ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን አስመልክቶ በገጽ 174 ላይ በጥልቀት ተመልክቷል፡፡

“በመሠረቱ አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች ተብለው በአብዛኛው ከሚታወቁት መንገድች መካከል ድርድር /conciliation/፣ እርቅ /mediation/ ግልግል /arbitration/ እና ስምምነት /Negotiation/ የሚጠቀሱ ሲሆን በሀገራችን ከሚሠሩት የሽምግልና ዓይነቶች ውስጥ ድርድር፣ ግልግልና እርቅ ይገኙበታል፡፡ ”

ጸሀፊውም በኮንስትራክሽን ውሎች የሚታወቁትን የግጭት መፍቻ መንገዶች በተለይም የሁለትዮሽ ድርድር (negotiation)፣ የዕርቅ ስምምነት እና ግልግልን እንደሚከተለው አቅርቧል፡፡

4.1.      የሁለትዮሽ ድርድር (Negotiation)

ጸሐፊው የእንግሊዝኛው አቻ ቃል ማለትም ‘negotiation’ የሚለው አቻ የአማርኛ ቃል በማጣቱና የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጠቀመበት ቃል ‘ስምምነት’ የሚል በመሆኑ ይህም የቃሉን ትክክለኛ አመክንዮዊ ትርጉም (logical semantic) ያልተከተለ በመሆኑ ‘የሁለትዮሽ ድርድር’ የሚለውን ተጠቅሟል፡፡

የሁለትዮሽ ድርድር የሚባለው ግራ ቀኝ ተከራካሪዎች ያለምንም ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት በራሳቸው አነሳሽነት ጉዳያቸውን በንግግር፣ ወይይት ወይም ድርድር የሚፈቱበት መንገድ ነው፡፡ በጽሁፋ መግቢያ ላይም ታዋቂው የቢዝነስ ሙያ ሊቅ ዶ/ር ቸስተር ያለው አባባል የሚያስረዳው በንግድ ዓለም ማንም ሰው ቢሆን የፈለገውን ሳይሆን የተደራደረውን ያገኛል በማለት ያስረዱት ለዚህ ነው፡፡

የሁለትዮሽ ድርድር ከእለት ትእለት እንቅስቃሴያችን እስከ ትልልቅ ግብይቶች አለመግባባቶችን የምንፈታበት መንገድ ነው፡፡ የሁለትዮሽ ድርድር በኮንስትራክሽን ውሎች ለሚደርሱ ግጭቶች አንዱ መፍትሄ ነው፡፡ ለምሳሌ፡-ዓለምአቀፋ የአማካሪ ማሀንዲሶች ማህበር ወጥ ውል(FIDIC) ስለግጭት አፈታት በሚመለከተው ክፍል ላይ ሰላማዊ የግጭት አፈታት በሚል (amicable dispute resolution) የሁለትዮሽ ድርድር ሊኖር እንደሚችል ይናገራል፡፡ /አንቀጽ 20(5) ይመለከቷል፡፡ /

እኤአ በ2011 የወጣው የፌዴራል መንግስት ግዥ ኤጄንሲ (Public procurement Agency) ወጥ የጨረታ ሰነድ አንቀጽ 24(2) ላይ የሁለትዮሽ ድርድርን አስመልክቶ የሚከተለውን አስቀምጧል፡-

[T]he Public Body and the Supplier shall make every effort to resolve amicably by direct informal negotiation any disagreement, controversy or dispute arising between them under or in connection with the Contract or interpretation thereof.”

ከድንጋጌው የምንረዳውም በመንግስት የግንባታ ውሎች ላይ ጨረታ አሸንፈው  አቅራቢ ሆነው የሚገቡ ሥራ-ተቋራጮች ከተባለው መንግስታዊ ተቋም ጋር አለመግባባቶች እና ግጭቶች በሚነሱበት ወቅት በሰላማዊ መንገድ ማለትም በሁለትዮሽ ድርድር እንዲፈቱ ይናገራል፡፡

4.2.     የዕርቅ ስምምነት (Conciliation)

የዕርቅ ስምምነትየሚባለው ደግሞ የሁለትዮሽ ድርድር በሌላ ሶስተኛ ወገን እየታገዘ አለመግባባቶች በአስታራቂ ሶስተኛ ወገን የሚፈቱበት ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የግጭት መፍቻ መንገድ በኮመን ሎ(Common law) የሕግ ስርዓት በሚከተሉ አገራት እንደእነ አሜሪካ የሶስተኛ ወገን አደራዳሪ(mediation) በሚል በሥራ ላይ ውሏል፡፡ በፍትሐብሔር ህጋችንም የዚህ ዓይነቱ አካሄድ ከአንቀጽ 3318-3324 ተመልክቷል፡፡

የፌዴራሉ ሰበር ሰሚ ችሎትምበሰ/መ/ቁ 38794 ከላይ በተጠቀሰው ክስ ስለ ዕርቅ ስምምነትን በጨረፈታ እንደሚከተለው ለማየት ሞክሯል፡-

“ድርድር /conciliation/ የሚባለው የሽምግልና ዘዴ 3ኛ ወገን ባለበት ግራ ቀኙ ወገኖች የሚደራደሩበት መንገድ ሲሆን 3ኛ ወገን ከመታዘብ በስተቀር በድርድሩ ጣልቃ አይገባም በፍ/ብ/ህ/ቁ. 3318-3324 የተመለከቱት ዴንጋጌዎችም የሚገዙት ይህንኑ ነው፡፡ ”

ከዚህ አባባልም የምንረዳው ነገር የዕርቅ ስምምነት በሚደረግበት ጊዜ አስታራቂው (Concilator) ጉዳዩን በማግባባት ይመራል እንጂ አስገዳጅ ውሳኔ አይሰጥም፤ ይህም በፍ/ህ/ቁ 3322(2) ላይ በግልጽ ተመልክቷል፡፡

4.3.    የዘመድ ዳኝነት/ግልግል (Arbitration)

የዘመድ ዳኝነት የሚባለው ደግሞ ተከራካሪዎች ጉዳያቸው እልባት እንዲያገኝ ለሦስተኛ ወገንገላጋይ ዳኛ አቅርበው የሚፈቱበት መንገድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 3325 ላይ ግልግልን በተመለከተ እንዲህ የሚል ዐ/ነገር ሰፍሮ እናገኛለን፡፡ የግልግል ስምምነት ማለት ተዋዋይ ወገኖች ያንድን ክርክር ዉሳኔ ለአንድ የዘመድ ዳኛ ለሆነዉ ለአንድ ለሦስተኛ ሰዉ አቅርበዉ የዘመድ ዳኛዉ ዉል በሕግ አግባብ መሰረት ይህንኑ ክርከር ለመቁረጥ የሚያደርገዉ ዉል ነው፡፡ ስለዚህ በግልግል ሂደት ገላጋይ ሆኖ የሚመረጠዉ ሦስተኛ ወገን ወይም ተቋም አስገዳጅ የሆነ ዉሳኔ መስጠት ይችላል፡፡ በኢትዮጵያም የዚህን መሰል አግልግሎት በተደራጀ መልኩ የሚሰጡ የተወሰኑ የግልግል ተቋማት አሉ፡፡ ለምሳሌ፡ የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፋ ማህበራት ም/ቤት፡፡

ሌላው ደግሞ የግልግል ዳኝነት ውል እነደመሆኑ መጠን ግራቀኙ ተዋዋይ ወገኖች የውል ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡ /የፍ/ሕ/ቁ 3225-3226 ይመለከቷል፡፡ /የግልግል አካሄድም በፍትሐብሔር ሕጉ ከአንቀጽ 3325-3346 ባሉ ድንጋጌዎች ይመራል፡፡

በኢትዮጵያ የግልግል ዳኝነት ሂደት ውስጥ የሚነሳው ሌላው ትልቁ ጥያቄ የመንግስት እና አስተዳደር ውሎች በግልግል ይፈታሉ ወይስ አይታዩም የሚል ነው? በመሰረቱ የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 315(2) እንዲህ የሚል ቃል አስቀምጦ እናገኛለን፡፡

“በግልግል እንዳይወሰን በሕግ የተከለከለ ጉዳይ ወይም በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 3131 እንደተነገረው ያለ ጉዳይ ሲሆን ለግልግል ዳኝነት አይቀርብም፡፡ ”

ለመሆኑ በአንቀጽ 3131 ላይ የሰፈረው ድንጋጌ ምንድን ነው? በዋናነት የመንግስት መ/ቤቶች የሚያደርጓቸው የአስተዳደር ውሎች ናቸው፡፡ በፍትሐብሔር ሕጉ የአስተዳደር ውሎች ተብለው የሚታወቁት፡-

፩-የመንግስት ኮንሲሽዮን ውሎች (የፍ/ሕ/ቁ 3207-3243)

፪-የመንግስት ኮንስትራክሽን ውሎች (የፍ/ሕ/ቁ 3244-3296) እና

፫-የመንግስት አቅርቦት ውሎች (የፍ/ሕ/ቁ 3297-3306) ናቸው፡፡

ሆኖም ግን የመንግስት ኮንስትራክሽን ውሎችን የተመለከቱ የፍትሐብሔር ሕጉ ድንጋጌዎች   የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት ግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁ 649/2001 ከወጣ በኋላ ተፈጻሚነቱ የተገደበ ነው፡፡

እኤአ በ2011 የወጣው የፌዴራል መንግስት ግዥ ኤጄንሲ ወጥ የጨረታ ሰነድ አንቀጽ 24(6) ግጭቶች በግልግል ሊፈቱበት የሚችልበትን ሥነ-ሥርዓት እንደሚከተለው ደንግጎ እናገኘዋለን፡፡

“Only those Public Bodies that are allowed by law to proceed to arbitration can do so.”

በሕግ ወደ ግልግል እንዲያመሩ የተፈቀደላቸው የመንግስት አካላት የግልግል አካሄድን መከተል ይችላሉ፡፡ በእርግጥ የጨረታ ሰነዱ ተፈቀደላቸው የመንግስት አካላት እነማን ናቸው ሚለውን ግልጽ አላደረገም፡፡ የግልግል አካሄድም ለተፈቀደላቸው አካላት ብቻ ከሆነ የተባለው አንቀጽ ተፈጻሚነት በጣም የተገደበ ያደርገዋል፡፡

ወደ ተነሳንበት ጥያቄ ስንመለስ ግልግል ውል እንደመሆኑ መጠን ተዋዋይ ወገኖች በውላቸው መርጠውት ያሉባቸውን አለመግባባቶች በግልግል ውል ሊፈቱ ይችላሉ፡፡ ዳሩ ግን የመንግስት ውሎች በሚሆኑበት ጊዜ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 315(2) በተመለከተው መሰረት ምንም እንኳ የሥነ-ሥርዓት ህጎች የአንድን አገር ወሳኝ ፖሊሲ ይይዛሉ ተብሎ ባይጠበቅም የአስተዳደር ውሎች ለግልግል እንዳይቀርቡ ክልከላ አድርጓል፡፡ ይህንን ጉዳይም የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅጽ 2 በመ/ቁ/16896በዘምዘም ኃ/የተ/የግል ማህበር እና በሊባቡር ዞን ት/ቢሮ መካከል በነበረው ክርክር የአስተዳደር ውሎች በግልግል ሊፈቱ እንደሚችል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ሆኖም ግን ውሳኔው ሁሉን ፈዋሽ አይደለም፡፡

ሌላው ጉዳይ የኮንስትራክሽን ውልን አስመልክቶ የሚነሳን ክርክር በግልግል ዳኝነት እንዲያይ በውሉ ላይ የተሰየመው አካል በከሰመ (በጠፍ ወይም በተዘጋ) ጊዜ ክርክሩ በማን ሊታይ ይገባል? የሚለውን ነጥብ ነው፡፡

ይህንን በተመለከተ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ቅጽ 14 በሰ/መ/ቁ 80722 ላይ በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ አገልግሎት ድርጅት እና ዲአምሲ ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግል ማህበር መካከል በነበረው ክርክር ላይ ትርጉም ለመስጠት ሞክሯል፡፡ በዚህም መሰረት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3336(1) ላይ አንድ የዘመድ ዳኛ ሆኖ የተመረጠ ወገን የሞተ ወይም ችሎታ ያጣ እንደሆነ በእርሱ ምትክ ሌላ ዳኛ የሚመረጥ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ሆኖም ግን ተከራካሪዎች መስማማት ካልቻሉ የግልግል ስምምነቱ ቀሪ እንደሚሆን ከፍ/ህ/ቁ 3337 ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱም የሚከተለውን የፍርድ ሀተታ ሰጥቷል፡-

“ግራቀኙ መስከረም 04 ቀን 1999 ዓ.ም ካደረጉት የግንባታ ውል የመነጨውን ክርክር አይቶ ሊወስንላቸው የሚችለውን የግልግል ዳኛ/ተቋም/ የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወይም እርሱ የሚወክለው አካል ብለው ሰይመዋል፡፡ ሆኖም ግን ክርክሩ በተነሳበት ጊዜ ይህ የግልግል ዳኛ የግልግል ዳኝነት ተግባሩን ማከናወኑን በማቆሙ ምክንያት ሁለቱም ወገኖች እንደነበራቸው ሀሳብ አሁንም ጉዳያቸውን በግልግል ተመልክቶ ሊያይላቸው የሚችለውን ወገን ሁለቱም ወገኖች በጋራ ስምምነት ከሚሰየሙ በቀር፤ ጉዳዩን ተመልክቶ ሊወስን የሚችልን የግልግል ተቋም ወይም አካል ፍ/ቤት የመወሰን ሥልጣን የለውም፡፡ በስምምነት ለይተው ያመለከቱ ወይም የመረጡ በመሆኑ በዚህ አኳኋን የተመረጠው የግልግል ዳኛ /ተቋም የግልግል ተግባሩን ማከናወን ማቆሙ ከተረጋገጠ ይህንኑ የግልግል ዳኛ /ተቋም/ ተክቶ የግልግል ዳኝነት ተግባሩን ሊያከናውን የሚችል ሌላ አካል ለመሰየም የሁለቱ የጋራ ስምምነት የግድ አስፈላጊ መሆኑን፣ ይህ ስምምነት ካልተገኘ ግን ጉዳዩን በግልግል ዳኝነት ለመጨረስ ያደረጉት ስምምነት ቀሪ ሊሆን እንደሚገባበ ፍ/ብ/ሕ/ቁ 3337 በግልፅ በመደንገጉ ለጉዳዩ ቀጥተኛ ተፈፃሚነት ያለው ይኸው ድንጋጌ በመሆኑ ነው፡፡ ”

በግልግል የተሰጡ ውሳኔዎች ልክ እነደመደበኛ ፍ/ቤት ውሳኔዎች ይፈጸማሉ፡፡  ይህም በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 350-357 መሰረት ባለው ድንጋጌ ይመራል፡፡ ይህም ገላጋዩ ሊከተለው የሚገባ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ስለመሆነ የፍ/ህ/ቁ 3345 ንባብ ያስረዳል፡፡

በመጨረሻም በኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ቁ.621/2001 መውጣትን ተከትሎ በርካታ የአማራጭ ግጭት መፈቻ ተቋማት የተዘጉበት ጊዜ አለ፡፡ ይህም በተለይ በአዋጁ አንቀጽ 2(2) ላይ ያለው አፋኝ ክልከላ ነው፡፡ አንድ ማህበር የገቢ ምንጩ 90% በላይ ከአገር ውስጥ ማድረግ አለበት በዚህ ሳቢያ የገቢ ምንጫቸውን ከባህር ማዶ ያደረጉ ማህበራት የዕልት ተዕለት ሥራቸውን ለማከናወን ይቸገራሉ፡፡ ከዚህ ሕግ መውጣት በኋላ ሰለባ የሆኑ ተቋማት አሉ፡፡ ለምሳሌ፡-ፈረጀ ብዙ ዓላማዎችን ሰንቆ የተነሳው የኢትዮጵያ የግልግል እና ዕርቅ ማዕከል(Ethiopian Arbitration and Concilation Centre) አንዱ ነው፡፡ ምክንያቱም ከላይ ለማብራራት እንደተሞከረው የእነዚህ ማዕከላት መብዛት ፈርጀ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ የሌሎች የአፍሪካ አገራት ተሞክሮም የሚያሳየን ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡ ለምሳሌ፡-ናይጀሪያ 6(ስደስት) የግልግል ማዕከላት አላት፣ደቡብ አፍሪካ ደግሞ 5(አምስት) እንዲሁም ግብጽ 3(ሦስት) የግልግል ነክ ተቋማት አላቸው፡፡ በአንጻሩ ኢትዮጵያ ‘አንድ ለእናቱ’ የሆነ ብቸኛ ተቋም አላት ይህም የአዲስ አበባ የንግድ እና ዘርፋ ማህበራት ም/ቤት የግልግል ማዕከል ብቻ ነው፡፡ ታዲያ ፈጣን የኮንስትራክሽን፣ ኢንቨስትመንት እና ንግድ ዕድገት በተከታታይ የምታሰመዘግብ አገር እንዴት የኮንስትራክሽን ግጭቶችን በሚመለከት የግልግል ተቋማት መትከል ይሳናት? ስለዚህ መንግስት ይህንን ጉዳይ በጥልቀት ዝርዝር ጥናት በማስጠናት ሊሰራበት ይገባል፡፡

5.     ማጠቃለያ

የኮንስትራክስሽን ኢንዱስትሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከማደጉ ጋር ተያይዞ የተለያዩ አለመግባባቶችና ግጭቶች ሲከሰቱ ይስተዋላል፡፡  በዚህም ጊዜ በቂ የሆነ የግጭት አፈታት ሥነ ሥርዓት መደንገግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም አንድም በመደበኛ መንገድ በፍ/ቤት አሊያም በአማራጭ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪም አማራጭ የግጭት አፈታት ዘዴ እጅግ የታወቀና የተለመደ ነው፡፡  አማራጭ የግጭት አፈታት ዘዴ ከወጪ፣ተደራሽነት፣አሳታፊነት እና የቀደመ ግንኙነትን ጠብቆ ከማቆየት አንጻር ከመደበኛ ፍ/ቤቶች ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ የአማራጭ የግጭት አፈታት መንገድ የሚከተሉትን ዘዴዎች ሊይዝ ይችላል፡፡ እነዚህም፡-የሁለትዮሽ ድርድር (negotiation)፣ የሦስተኛ ወገን ድርድር (mediation) ወይም የዕርቅ ስምምነት (Conciliation)፣ የቅድመ ግጭት ግምገማ (early neutral evaluation)፣ ሚኒ ትሪያል (mini trial) ፣ የማግባባት ዳኝነት (adjudication) እና ግልግል (arbitration) ናቸው፡፡ በተለይ የግልግል ሥነ-ሥርዓት በጣም የተለመደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ገላጋይ ተቋማትን (arbitration centers) ማጠናከር የኮንስትራክሽን የግጭት አፈታትን የተሳለጠ ያደርገዋል፡፡ ለምን ቢባል በአገራችን የግልግል ተቋማት አንድንዶቹ እየተዘጉ ሌሎች ደግም ከአቅም ጋር ተያይዞ አገልግሎት መስጠት ያቆሙበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለሆነም የኮንስትራክሽን የግጭት አፈታትን ይበልጥ ለማጠናከር መንግስት በተለይ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የሙያ ማህበራት በመደገፍ ሊሰራ ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የበጎ አድራጎት እና ማህበራት አዋጅ አሰፈላጊ ጥናት ተደርጎ ቢሻሻል ጥሩ ነው፡፡ እንዲሁም በ2005ዓ.ም የተዘጋጀውን ፖሊሲ ዝርዝር ጥናት በማድረግ አሻሽሎ ስለ ግጭት አፈታት አስፈላጊነትበፖሊሲ አቅጣጫነት ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Note on Invalidation of Suspect Transaction under ...
ስለ ሸሪኣ ፍርድ ቤቶች መልስ የሚሹ ጉዳዮች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 15 June 2024