መግቢያ
እንደሚታወቀው በኮንስትራክሽን ውሎች አፈጻጸም ወቅት መሀንዲሱ የሚጫወተው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ አንዳንዴም መሀንዲሱ በውኑ የመሀንዲስ አድራጎት የማይመስሉ ተግባራትን ሲያከናውን ይሰተዋላል፡፡ ይህም ነገሩ አጀብ! ቢያሰኝም እውነታው ግን ከዚህ የራቀ አይደለም፡፡
እርግጥ ነው መሀንዲሱ ብዙ አልፎ አልፎም እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ ተግባራትን የሚያከናውንበት ጊዜ አለ፡፡ ለአብነት ያህልም፡-የግንባታው ዲዛይነር፣ የአሰሪው ወኪል (employer’s agent)፣ አማካሪ (supervisor)፣ የሥራ ርክክብ አረጋጋጭ (certifier)፣ ብሎም አንዳንዴ አራጊ ፈጣሪ ገላጋይ ዳኛ ወይም ከፊል አስታራቂ (adjudicator or quasi-arbitrator) ሊሆን ይችላል፡፡
በነገራችን ላይ የመሀንዲሱ ሚና ከላይ በጠቀስናቸው ተግባራት ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በግንባታ ውሉ አፈጻጸም ወቅት አስቀድሞ ለፕሮጀክቱ አፈጻጸም የሚሆኑ ሥራዎን በራሱ አነሻሽነት (proactive works) ወይም ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ ለውሉ አፈጻጸም የሚሆኑ ተግባራት እና ሥራዎችን በአሰሪው ወይም ሥራ ተቋራጩ ትእዛዝ (reactive works) እንዲሁም በውሉ በግልጽ ተለይተው ባይሰጡትም ለፕሮጀክት አፈጻጸም አንድ መደበኛ መሀንዲስ ሊሰራቸው የሚችሉ ሥራወችን ሊያከናውን ይችላል፡፡
አንዳንዴም ባለሃብቶች የመገንባት ሃሳቡ ኑሯቸው ወደ ስራው ሊገቡ ሲሉ ዘርፈ ብዙ የቴክኒክ ችግሮች፣ የምርታማነት እና ንግድ ጉዳዮች እንዲሁም የሕግ መወሳሰብ ባለማወቃቸው ብሎም ከግምት ባለማስገባታቸው የተነሳ እክል ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ በሲቪል ምህንድስናው ዘርፍም ይህንን የባለሃብቱን ሃሳብ እና ስጋት ወደ እውነት ለመተግበር አማካሪ መሀንዲሱ ወይም መሀንዲሱየተባለውን ጉዳይ ሊፈጽምለት ይችላል፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው! መሀንዲሱም ሆነ አማካሪ መሀንዲሱ በውል የተጣለባቸውን ሥራወች ሲሰሩ ግልጽ የሆነ የጥቅም ግጭት (manifest conflict of interest) ሊከሰት ይችላል፡፡ እነዚህ የጥቅም ግጭቶችም በሥራው ላይ ከተፈጥሮ ሕግ እና ርትዕ(natural law and equity) አንጻር የፍትሃዊነት ጥያቄ ስለሚያስነሳ በጥልቀት እና በአንክሮ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡