- Details
- Category: Property Law
- Hits: 9146
የንብረት አገልግሎት ስለ ሌላ የማይንቀሳቀስ ንብረት ጥቅም በአንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚጣል ግዴታ ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1359) የንብረት አገልግሎት መሰረቱ (subject matter) የማይንቀሳቀስ ንብረት ሲሆን የመብቱ ምንጮች (sources) ህግ፣ ውልና ተፈጥራዊ አቀማመጥ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የንብረት አገልግሎት መብት ቀደም ሲል እንደ አላባ መብት በሚንቀሳቀሱ ንብረቶችና ግዙፍነት በሌላቸው እንደ ፈጠራ፣ የቅጅ መብትና፣ የኢንዱስትሪ ንድፍ በመሳሰሉ ንብረቶች ላይ ሊመሰረት አይችልም፡፡ የንብረት አገልግሎት መብት ሊመሰረት የሚችለው ግዙፍነት ባለው የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ነው፡፡
የንብረት አገልግሎት በፍ/ብሄር ህጉ ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1359 እስከ 1385 ባሉ ድንጋጌዎች የሚገዛ ሆኖ በጐረቤታሞች መካከል የመቻቻል፣ የመረዳዳት መሬቶቻቸውንና ግንባታዎቻቸውን የተሻለ ጥቅም ሊሰጥ በሚችል መልኩ እንዲገለገሉበት የሚያስችል መብት በመሆኑ ለሰዎች መልካም ግንኙነት ያለው ፋይዳ እጅግ የጐላ ነው፡፡ ይህ መብት ሰውን በመከተል ሊፈፀም የሚችል መብት (real right) ሲሆን በዋናነት መሰረቱ መሬት ነው፡፡ ይሄውም የንብረት አገልግሎት ግዴታ ያለበት የማይንቀሳቀስ ንብረት የግዴታ አገልጋይ (Servient tenament) ባለቤት በንብረቱ ላይ ያለውን መብት ለአገልግሎት ተቀባዩ (Dominant tenament የማይንቀሳቀስ ንብረት ጥቅም ሲባል መብቱ የሚገደብበት ዓይነት የንብረት አገልግሎት ወይም በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ያለ ግንኙነት ነው፡፡
የንብረት አገልግሎት መብት የሁለት የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችና የሁለት የተለያዩ ሰዎች መኖርን ታሳቢ የሚያደርግ ቢሆንም እነዚህ ሁለት የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ሁሉ ግዜ ጥግ ለጥግ (contiguous) ወይም ተጓዳኝ (adjacent) መሆን አለባቸው ማለት ግን አይደለም፡፡ ይህም ማለት የተወሰነ ርቀት ኖራቸውም እንደ እንሰሳትን ውሃ ማጠጣት (watering animals) ግጦሽ፤ (pasture) እንጨት መቁረጥ (cutting wood) ወይም እይታ (view) ወ.ዘ.ተ. ባሉ ሁኔታዎችም የንብረት አገልግሎት ሊመሰረት ይችላል፡፡ የንብረት አገልግሎት በግዴታ አገልጋይ (Servient tenement) የባለቤትነት መብት ላይ ተፅእኖ የሚፈጥር ነው፡፡ ለምሳሌ የንብረት አገልግሎቱ የማለፊያ መንገድን መሰረት ያደረገ በሚሆንበት ግዜ ከመሬቱ ቀንሶ ለመንገድ የሚሆን መሬት እንዲሰጥ:: የንብረት አገልግሎቱ የእይታ መብት (right to view) በሚሆንበት ግዜ ደግሞ ግርዶሽ የሚፈጥር ግንባታ ከማካሄድ እንዲቆጠብ ይገደዳል፡፡ የንብረት አገልግሎት አስፈላጊነት መለኪያው ለአገልግሎት ተቀባዩ (dominant tenament) ምን ያህል ጠቃሚ ነው የሚል ነው፡፡ አንድ ሰው ለሌላ ሰው የግዴታ አገልጋይ (Servient tenement) እንዲሆን የሚገደደው የንብረት አገልግሎት ተቀባዩ (Dominant tenement) የማይንቀሳቀስ ንብረት ያለ እንደዚያ ያለ አገልግሎት የማይንቀሳቀስ ንብረቱ ጥቅም ላይ የማይውል መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የንብረት አገልግሎት ግንኙነት ሊመሰረት አይችልም፡፡ በመሆኑም የንብረት አገልግሎት የሚሰጠው ለመሬቱ እንጂ ለሰው አይደለም፡፡ ሌላው መስፈርት በግዴታ አገልጋዩና በንብረት አገልግሎት ተቀባዩ መካከል የተፈጥሮ ትስስር (natural relationship) መኖር አለበት፡፡ የንብረት አገልግሎት መብት ከማይንቀሳቀሰው ንብረት ተለይቶ አገልግሎት ላይ ሊውል የማይችል የዋናው መብት ተጨማሪ (accessory) ነው፡፡ ይህ መብት በተፈጥሮ ቀጣይነት ያለው (perpetual) ሲሆን መሰረቱ ውል (convention) ወይም ህግ ነው፡፡ የመበቱና ግዴታው መሰረት ውል በሚሆንበተ ጊዜ ተዋዋዮች ግዴታው የሚቆይበትን ጊዜ በውላቸው ላይ በማስፈር ሊሰማሙ ይችላሉ፡፡ መብቱና ግዴታው የሚመነጨው ከህግ በሆነበት ጊዜ ደግሞ ህጉ በሚያዘው መሰረት ይፈፀማል፡፡ የንብረት አገልግሎት የግዴታ አገልጋይ ያለበትን ግዴታ ልዋጭ በመስጠት (redemption) ካልሆነ በስተቀር ካሳ (indemnity) በመስጠት ቀሪ ሊያደርገው አይችልም::
የንብረት አገልግሎት ዓይነቶች (Kinds of Servitude)
የንብረት አገልግሎት ዓይነቶች ሶስት ሲሆኑ እነሱም፡፡
Øአንደኛው ተፈጥራዊ የንብረት አገልግሎት (natural servitude) የሚባለው ሲሆን መነሻው የንብረት አገልግሎት ተቀባዩ (dominant tenament) እና የንብረት አገልግሎት ግዴታ አገልጋይ (servient tenament) ጆግራፍያዊ አቀማመጥን መሰረት ያደረገ እንደ በዝቅተኛ ቦታ ያለ ሰው ውሃ የማግኘት መብት ወይም እንደ በሁለት ማሳዎች ድንበር ወይም አጥር ባሉ ነገሮች ላይ የሚመሰረት የንብረት አገልግሎት ዓይነት ነው፡፡ ይህም የጆግራፊ አቀማመጣቸው የግዴታ አገልግሎት መሰጠትን የግድ ሲል ህግ በራሱ እውቅና (recognition) የሚሰጠው መብት ነው፡፡
Øሁለተኛው ህጋዊ የንብረት አገልግሎት (legal servitude) የሚባል ሲሆን ይህ ዓይነት የንብረት አገልግሎት ህግ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የሚፈጥረው ነው፡፡ ይህ የሚከሰተው መውጫ መግብያ የሌለው መሬት (enclave land) በሚኖርበት ግዜ ህግ መውጫ መግብያ እንዲኖረው ሲያስገድድ ወይም የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የቴሌ፣ የጋዝ መስመር ዝርጋታ ሲኖር በሌላው መሬት ላይ የዝርጋታ ስራው እንዲከናወን ህግ ሲያስገድድ የሚኖር የንብረት አገልግሎት ዓይነት ነው፡፡
Øሶስተኛው በውል የሚመሰረት የንብረት አገልግሎት (conventional or juridical servitude) የሚባለው ሲሆን የዚህ ዓይነት የንብረት አገልግሎት በሁለት እና ከሁለት በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል በሚደረግ ስምምነት የሚመሰረት ወይም አንድ ሰው በግሉ (unilaterially) እንደ ኑዛዜ ባለ ሁኔታ ሊመሰረት የሚችል ነው፡፡ ከፍ ብለን ካየናቸው ሁለት የንብረት አገልግሎት ዓይነቶች የሚለየው የዚህ ዓይነት ንብረት አገልግሎት ህጋዊ ውጤት እንዲኖረውና በተዋዋዮች መካከል በፍ/ህ/ቁ/1731 መሰረት ህግ ሆኖ እንዲያገለግል ከተፈለገ ውሉ በፅሁፍ መሆንና ስልጣን በተሰጠው አካል በፍ/ብ/ህ/ቁ 1723 መሰረት መመዝገብ ይኖርበታል ፡፡ ካልሆነ ግን የአስገዳጅነት ውጤት አይኖረውም::
የንብረት አገልግሎት አተገባበር (Servitude in Modes of Exercise)
vግልፅና ግልፅ ያልሆነ የንብረት አገልግሎት (apparent and non-apparent servitude) ግልፅ የንብረት አገልግሎት የሚባለው የሚገለፀው በሚታዩ ስራዎች (visible works) እንደ መስኮት፣ መዝጊያ፣ ሰርጥ (channel) እና ከመሬት በላይ የተዘረጋ ባምቧ ባሉ ዓይነቶች ነው፡፡ ግልፅ ያልሆነ የንብረት አገልግሎት በመሬት ላይ የሚታይ እንደ ያለመገንባት ወይም ከተወሰነ ከፍታ በላይ ያለመገንባት ባሉ ሁኔታዎች የሚገለፅ የንብረት አገልግሎት ነው፡፡ በሁለቱም የንብረት አገልግሎቶች መካከል ያለው ልዩነት ግልፅ በሆነው የንብረት አገልግሎት በይዞታ ለ10 ዓመት በእጅ በማቆየትና ግብር በመክፈል (usucaption) የንብረት አገልግሎት መብት ማግኘት የሚቻል ሲሆን ግልፅ ባልሆነው የንብረት አገልግሎት በዚህ መልኩ መብትን ማግኘት አይቻልም፡፡
vቀጣይነት ያለውና ቀጣይነት የሌለው የንብረት አገልግሎት (continuous and discontinuous servitude) ቀጣይነት ባለው የንብረት አገልግሎት መብቶቹ ስራ ላይ ለማዋል የሰውን ጣልቃ ገብነት የማይጠይቁና አንድ ግዜ ከተዘረጉ በኋላ በራሳቸው ግዜ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ የውሃ ቧንቧ (pipes of water) የቆሻሻ ማስወገጃ (sewerage) እና አለመገንባት (not to build) ወይም ከተወሰነ ከፍታ በላይ አለመገንባት (not to build beyond a certain height) ያሉት ናቸው፡፡ ቀጣይነት የሌለው የንብረት አገልግሎት የሚባለው በመብቱ ለመገልገል የሰውን ጣልቃ ገብነት ወይም አንቀሳቃሽነት የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህም እንደ የመንገድ መብት (the right to way)፣ ውሃ መቅዳት (drawing water)፣ ግጦሽ (pasture) እና ከመሬት እንደ ድንጋይና መአድን ማውጣት (extracting minerals) ወ.ዘ.ተ. ያሉት ናቸው፡፡
vአዎንታዊና አሉታዊ የንብረት አገልግሎት (positive and negative servitude)
አዎንታዊ የንብረት አገልግሎት (positive servitude) በግዴታ አገልጋዩ (servient tenement) መሬት ላይ ገብቶ ሲገለገል የሚከሰት የንብረት አገልግሎት ሲሆን በግዴታ አገልጋዩ የንብረት ባለቤትነት ጣልቃ የመግባት (interference) ውጤትን የሚያስከትል ቢሆንም ከተገልጋዩ መብት አኳያ ሲታይ እንደ አዎንታ የሚወሰድ ነው፡፡
አሉታዊ የንብረት አገልግሎት (negative servitude) የሚባለው የግዴታ አገልጋይ (servient tenement) በሌላኛው የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ጫና ሳይፈጥር (without imposition) በባለቤቱ ተፈጥራዊ የባለቤትነት መብት (inherent ownership right) ተፅእኖ ላለመፍጠር በመብቱ ላይ ገደብ ሲጣልበት የሚከሰት እንደ ከተወሰነ ከፍታ በላይ ያለመገንባት ወይም ጭራሽ ያለመገንባት የሚገለፅ በግዴታ አገልጋይ ላይ ገደብ የሚጥል በመሆኑ ከግዴታ አገልጋዩ የባለይዞታነት መብት አንፃር ሲታይ አሉታዊ ተብሎ የሚወሰድ ነው፡፡
ስለዚህ የንብረት አገልግሎት መብት በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ብቻ የሚመሰረት ሆኖ ከዜጐች በንብረት የመገልገል መብት ጋር ትስስር ያለው በግዴታ አገልጋይ የባለቤትነት መብት ላይ በመጠኑም ቢሆን ተፅእኖ የሚያሳርፍ ግንኙነት ነው፡፡ ይህ የንብረት አገልግሎት ከአላባ ጋር በንፅፅር ሲታይ ልዩነታቸው የአላባ መሰረቶች የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ግዙፍነት ያላቸው ንብረቶችና ግዙፍነት የሌላቸው ንብረቶች ሲሆኑ የንብረት አገልግሎት መሰረት የማይንቀሳቀስ ንብረት ብቻ መሆኑ አንዱ የሚለያቸው ነጥብ ነው፡፡ ሌላው ልዩነታቸው አላባ በግዚያውነት የሚተላለፍ እና ከንብረቱ ተለይቶ (independently) ሊተላለፍ የሚችል መብት ሲሆን የንብረት አገልግሎት ከማይንቀሳቀስ ንብረት ተለይቶ ሊሰራበት የማይችልና ዘላቂ ግንኙነትን የማስከተል ውጤት ያለው በመሆኑ የንብረቱ መከፋፈል ሊያስቀረው የማይችል ነው፡፡ እንደዚሁም የንብረት አገልግሎት የሚኖረውም ለባለቤቱ ጥቅም ሲባል ሳይሆን መብቱ የሚኖረው ለሌላ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት መብትና ጥቅም ሲባል ነው፡፡ የአላባ መብት ግን ለባለቤቱ ጥቅም ሲባል የሚደረግ ሊሆን ይችላል፡፡ የአላባ መብት ጉዳይ (object) የማይንቀሳቀስ፣ የሚንቀሳቀስና ግዙፍነት የሌለው የንብረት ባለቤትነት መብት ሲሆን የንብረት አገልግሎት ጉዳይ (object) ግን የማንቀሳቀስ ንብረት በተለይ የመሬት ባለይዞታነት መብት ነው፡፡ የንብረት ባለቤትነት መብት ለብቻው ሊተላለፍ የሚችል ሲሆን የንብረት አገልግሎት ግን ከማንቀሳቀስ ንብረቱ ተነጥሎ (dismemberedly) ሊተላለፍ (assign) ወይም ሊከበር (attach) የሚችል ባለመሆኑ በሁለቱም መካከል ልዩነት አለ፡፡
- Details
- Category: Property Law
- Hits: 9426
የአላባ መብት ከአንድ ግዙፍነት ያለው የሚንቀሳቀስ ወይም የማይንቀሳቀስ ንብረት ወይም ግዙፍነት ከሌለው የባለቤትነት መብት ተቀንሶ በንብረቱ ለመገልገል (usus) ወይም ፍሬውን የመሰብሰብና መውሰድ (fructus) መብት በመስጠት የሚቋቋም የንብረት ግንኙነት ነው፡፡ ይሄውም አንድ ሰው ካለው የባለቤትነት መብት ቀንሶ ለሌላ ሰው የሚያስተላልፈው መብት ነው፡፡ አንድን ንብረት በአላባ የማስተላለፍ መብት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 40/1/ ". . . ወይም በሌላ መንገድ የማስተላለፍ መብቶችን ያካትታል" በሚለው ስር የሚወድቅ ህገ-መንግስታዊ ሽፋን የተሰጠው መብት ነው፡፡ አላባ ከፍ/ብ/ህጉ አንፃር ሲታይም ከቁጥር 1309-1358 ባሉ ድንጋጌዎች ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶት የምናገኘው በንብረት የመገልገል ወይም ፍሬው የመሰብሰብና የመውሰድ ወይም ሁለቱ መብቶች አንድ ላይ ተዳብለው ልናገኛቸው የምንችል የንብረት ማስተላለፍያ አገባብ ነው፡፡
የአላባ መብት መሰረቱ (subject matter) ግዙፍነት ያላቸው (corporeal things) የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችና ግዙፍነት የሌላቸው (incorporeal things) እንደ ቅጅ መብትና ፈጠራ ያሉ የንብረት መብቶች ናቸው፡፡ (በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1204/1/፣ 1126፣ 1309/1/ /2/ እና 1347 እና ቀጠቀዮቹ) የአላባ መብት ምንጭ (source) ውል፣ ኑዛዜ ወይም ሕግ ሊሆን ይችላል፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ 1184 እና 1185) የአላባ መብት መሰረት የሚንቀሳቀስ ንብረት በሆነ ግዜ ተጠቃሚው ንብረቱን በእጅ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1186/1/) የአላባ መብት መሰረቱ የማይንቀሳቀስ ንብረት በሚሆንበት ግዜ ግን የአላባ መብት ምንጭ የሆነው ውል ወይም ኑዛዜ መመዝገብ ስለሚኖርበት በይዞታው ስር በማድረግ ብቻ የአላባ ተጠቃሚነትን መብት ሊያገኝ አይችልም፡፡ (በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1184 እና 1185) በኢትዮጵያ ፍ/ብሄር የፍትህ ስርዓት የአላባ መብት ከህግ የሚመነጨው ከማይንቀሳቀስ የውርስ ሃብት ጋር በተያያዘ መንገድና፣ ለአካለ መጠን ባላደረሰ ልጅና ሞግዚቱ ወይም በባልና ሚስት መካከል ያለን ግንኙነት መሰረት በማድረግ ሲሆን የሚተላለፍበት ስርዓትም በማግኘት (acquisition, Possession etc.) በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1310 እና 1311 ላይ በተደነገገው መሰረት ነው፡፡
የንብረት ባለቤትነት መብት (ownership right) ሶስት መሰረታዊ መብቶችን ማለትም የሌሎችን መብት ሳያውኩ (ሳይነኩ) (without impairing any one’s right) እንደፈለጉ ማድረግ (abusus right) በንብረት የመገልገልን (usus) እና ፍሬውን የመሰብሰብና የመውሰድ (fructus) መብቶችን የሚያጐናፅፍ ሲሆን የአላባ መብት የንብረቱ ባለቤት (owner) የባለቤትነት መብቱን (ownership right or abusus right) ለራሱ በማስቀረት የተቀሩትን ሌሎች ሁለት መብቶች ማለትም በንብረቱ የመገልገልና (right of using) እና ፍሬውን ሰብስቦ የመውሰድ (enjoying the thing) ለአላባ ተጠቃሚው በማስተላለፍ የሚገኝ መብት ነው፡፡ የአላባ መብት ተጠቃሚው በሂወት አስካለ ድረስ ሊገለገልበት የሚችል መብት እንጂ እንደሌሎቹ የንብረት መብቶች ወደ ተወላጆቹ ወይ ወላጆቹ በውርስ ሊተላለፍ የሚችል መብት አይደለም፡፡ይህ ማለትም አንድ ሰው በንብረት ያላውን የባለቤትነት መብቱን ተጠቅሞ የአላባ መብት ለሌላ ሰው በኑዛዜ መስጠት የሚችል ቢሆንም ይህ የአላባ ተቀባይ በሚሞትበት ጊዜ ይህን የአላባ መብቱ ለወራሾቹ በኑዘዜ ማሰተላለፍ አይችልም ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1322(1)) አንዱ የአላባ መብት ማስገኛ መንገድ ውል እንደምሆኑ መጠን የአላባ መብት በአላባ ሰጪና ተቀባይ መካከል በሚደረግ ስምምነት የሚቋቋም የንብረት መብት በሚሆንበት ጊዜ በተዋዋዮቹ መካከል በርካታ መብቶችና ግዴታዎች (bundle of rights and duties) ያሉበት ነው፡፡
የአላባ ተጠቃሚ መብትና ግዴታ
Øበአላባ የተሰጠውን መብት ለመገልገል ንብረቱን በራሱ ወይም በወኪሉ አማካይነት በይዞታው ስር ማድረግና በዚህ መብቱ ለመስራት በባለቤቱ፣ በወራሾቹ ወይም ንብረቱን በእጃቸው ላይ ባደረጉ 3ኛ ወገኖች ላይ የባለይዞታነት ክስ (possessory action) የመመስረት መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1311 እና 1341)
Øየማይንቀሳቀስው ንብረት ለህዝብ ጥቅም ሲባል በመንግስት በሚወሰድበት ግዜ የአላባ ተጠቃሚው በመልቀቅ ምክንያት የተሰጠውን ካሳ የማግኘት መብት ይኖረዋል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1319(2))
Øየአላባ ተቀባዩ ያለውን መብት መሰረት በማድረግ የመድን ሽፋን የመግዛትና ካሳ የማግኘት መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1320 እና ን/ህ/ቁ 654)
Øፍ/ብ/ህ/ቁ.1311 የአላባ ተጠቃሚው የአላባ ንብረቱን በቁጥጥር ስር ማደረግ አለበት ሲል እንደሚደነግግ ሁሉ የአላባ ተጠቃሚው ይህን የአላባ መብት የሚያገኘው ከህግ ከሆነ መብቱን የሚያገኘው ወድያውኑ (automatic) ነው፡፡ መብቱ የመነጨው ከውል በሆነ ጊዜ ስመምነቱ እንደተፈፀመ፣ በውርስ ከሆነም ውርሱ ሲከፈት፤ በኑዛዜ ከሆነ ደግሞ የውርስ ንብረት የማጣራቱ ስራ እንዳለቀ የአላባ መብቱን ያገኛል፡፡
Øየአላባ መብቱ መሰረት የሆነው ነገር የፍጆታ እቃ (consumable good) ከሆነና ሳይጐዳ በመብቱን ሊሰራበት የማይችል በሆነ ግዜ የንብረቱ ባለቤት ይሆናል፡፡ ይህ ማለትም በአላባ የተሰጠውን ንብረት እንደፈለገ ያረገዋል(will have the right to dispose) ማለት ነው:: ለምሳሌ፡- የአላባ መብቱ የተሰጠው በወይን ላይ ከሆነ ወይኑን የመጠጣት፣ የድንጋይ ከሰል ከሆነ በድንጋይ ከሰሉ የመገልገልና የመጨረስ፣ ገንዘብ ከሆነም ገንዘቡን ወደ ሌላ የማስተላለፍ መብት ይኖረዋል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1327(1))
Øየአላባ መብቱ የተሰጠው ፍሬ ለመሰብሰብ ከሆነ የአላባ ተቀባዩ የተፈጥሮ ፍሬዎች (natural fruits) እንደ ጥጃዎች (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1171 እና 1328(1)) ፣ ሲቪል ፍሬዎች (civil fruits) እንደ ኪራይ፤ ወለድ ወይም የተጣራ ትርፍ (interests, arrears or dividends) (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1331 እና 1347) እና የኢንዱስትሪ ውጤቶች (periodical products) (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1170/2/ እና 1333) የመሰብሰብ መብት ይኖረዋል፡፡
Øየአላባ መብቱ በሚቋረጥበት ግዜ ባልበሰሉ ሃብቶች ወይም የአላባ መብቱ በሚቋረጥበት ግዜ ባልበሰሉ ነገሮች (pre-mature things) ሲበስሉ ወይም ውሉ ሲቋረጥ የበሰሉ ካሉ የአላባ ተጠቃሚው እንደሆኑ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ 1328(1))
Øየአላባ ንብረቱ ለምሳሌ እንደ ቤተ መፅሐፍ ፣ ፈረስና የቤት እቃ ያለ ሲሆን የአላባ ተጠቃሚው ይህንን ንብረት ለሌላ 3ኛ ወገን በኪራይ (lease) የመስጠት መብት ይኖረዋል፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1331)
Øበአላባ የተሰጠን ንብረት መሬት ወይም ቤት ሲሆን ከተኸራየ በኋላ የገዛ ወይም በዋስትና የያዘ ሰው ቢኖሩም ለሚቀጥሉት 3 ዓመታት የአላባ ተጠቃሚው በአላባ መብቱ ይሰራበታል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1332(2))
Ø
Øአላባ ተቀባዩ የዋስትና (mortgage) ዋናው እዳ (principal debt) የመክፈል ግዴታ የለበትም፡፡ የከፈለ እንደሆነ ግን አላባ ሰጪውን ገንዘቡ እንዲመልስለት የመጠየቅ መብት አለው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1340 (2))
Øየማይንቀሳቀስ ንብረት ማስለቀቅንና የመድህን ካሳ ክፍያን መሰረት በማድረግ በሚነሱ ክርክሮች መብት አለኝ ብሎ በክርክሩ ውስጥ ልግባ የማለት መብት አለው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ.1311 ፤1341፣ ን/ህ/ቁ. 654 እና ፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 33(2))
Øበአላባ በተሰጠው ንብረት ላይ ሌላ ተጨማሪ ነገር የሰራው ካለ በአንድ ዓመት ግዜ ውስጥ ነቅሎ የመውሰድ መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1346(2))
Øበአላባ የተሰጠው ንብረት ከእጁ ወይም ከይዞታው ከወጣ እንዲመለስለት ወይም ሁከቱ እንዲወገድለት የባለ ይዞታ ክስ (possessry action) የመመስረት መብት አለው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ.1149፡ 1311፡1341 እና ፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 33(2))
Øበአላባ የተሰጠው ንብረት ቢወድምም የአላባ ተጠቃሚው በትራፊው ወይም በቀሪው ዎና (ruins) መገልገል ይችላል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1344)
Øበአላባ የተሰጠውን ንብረት የመስጠትና የኪራዩን ገቢ የመስብሰብ መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1331) ስለዚህም የአላባ ግንኙነት እጅግ በርካታ መብቶችን ሊያስገኝ የሚችል የንብረት ግንኙነት እንደሆነ ከንብረት ህጉ ይዘት ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ከግዴታ አንፃር ሲታይም የሚከተሉት ግዴታዎች የሚስተዋሉበት ነው፡፡
vበአላባ የተሰጠውን ንብረት ደረጃውን ጠብቆ በቅን ልቦና የማስተዳደርና የተቋቋመበትን አላማ መሰረት በማድረግ በአላባ መብቱ የመገልገል ግዴታ አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1312 ፣ 1326 ፤ 1328 እና 1330)
vእንደ የጣራ ማፍሰስ፣ መለስተኛ የግንብ መሰንጠቅ፣ የቀለም ቅብ ያሉ ተራ የጥገና ስራዎች የመስራት ግዴታ አለው፡፡ የአላባ መብቱ የተገኘው በውርስ (inheritance) ሲሆን የአላባውን ንብረት ዕዳ ወይም ወለድ የመክፈል ግዴታና መደበኛ ወጪ እንደ ግብር ያሉ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ ይህ የግብር መክፈል ግዴታ በመፈፀም ላይ ያለ የአላባ ተጠቃሚ ለተከታታይ 15 ዓመታት ቢከፈልም በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1168 በመያዝና መገልፈገል ብቻ (usucaption) የባለቤትነት መብት እንዲያገኝ አያደርገውም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1313 እና 1314)
vየአላባ ውሉ ሲቋረጥ የአላባው ንብረት በሂደት የሚመጣውን መጥፋትና መበላሸት (loss and deterioration) ሳይጨምር እንደነበረው ለባለቤቱ የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1317 ፣ 1326፤ 1327(2) ፣1343 ፤ 1346 እና 2027)
vየአላባ ተጠቃሚ በአላባ የተሰጠውን ንብረት በሚንቀሳቀስ ንብረት ዋስትና (pledge)፣ በማይንቀሳቀስ ንብረት ዋስትና (mortgage)፣ በንብረት አገልግሎት (servitude) ወይም ለሌላ ሰው በአላባ የመሰጠት ወይም የማስተላለፍ መብት ቢኖረውም ይህን መብቱን በስራ ላይ በሚያውልበት ግዜ የባለቤቱን መብት መጉዳት (impair) የለበትም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1318 እና 1324)
vየአላባ መብት ቀሪ በሚሆንበት ግዜ የንብረቱን ዋጋ ሳይሆን ንበረቱን በዓይነት ማለትም በአላባ የተሰጠውን ንብረት የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1321)
vበአላባ የተሰጠው ንብረት በሶስተኛ ወገኖች እጅ ሲገባወይም የጣለቃ መግባት (interference) ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ለባለቤቱ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1342)
vበአላባ የተሰጡት እንስሳት በሚሆንበት ግዜና ከእነዚህ የተወሰኑት በአደጋ ወይም በበሽታ ያለቁ እንደሆነ የነዚህን ምትክ ከሚወለዱት የመተካት ግዴታ አለበት፡፡ እነዚህ እንሰሳት በጠቅላላ በአደጋው ወይም በበሽታው ካለቁ ግን ቆዳቸውን የማስረከብ ወይም የቆዳውን ዋጋ ለባለቤቱ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1345)
vመሰረታዊ ለውጥ ያለማድረግ ግዴታ ይኖርበታል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1330)
vንብረቱን የማቀብ (preserve) ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1309)
vለንብረቱ ለማስተዳደር፡ ፍሬውን ለማግኘትና ለመጠቀም የሚያስፈልገውን ወጪና ወለድ የመሸፈን ግዴታ አለበት፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ.1313) ስለዚህ አንድ የአላባ ተጠቃሚ በርካታ መብቶች እንዳሉት ሁሉ ግዴታዎችም ያሉበት ነው፡፡
የአላባ ሰጪ መብትና ግዴታ
ü የአላባ ውል ግዜው ሲያልቅ ንብረቱን የመረከብ መብት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1322 እና 1327)
ü በአላባ መብትነት በሰጠው ንብረትና በመብቱ ላይ ተፅእኖ (jeopardy) አለ ባለ ግዜ ፍርድ ቤት ጣልቃ ገብቶ መብቱ እንደነበረው እንዲደረግለት የመጠየቅ መብት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1324)
ü ልዩ ወጪዎች እንዲከፍል በሚጠየቅበት ግዜና ይህን ወጪ የአላባ ተጠቃሚው በብድር መልክ የማይሰጠው ከሆነ በአላባ ሰጥቶት ከነበረው ንብረቱ ገሚሱን በመሸጥ እዳውን የመክፈል መብት፡፡
ü በአላባ የሰጠውን ንብረት በዋስትና (mortgage) የመስጠት መብት፡፡
ü በአላባ ተጠቃሚው ዋስትና (Securities) እንዲሰጠው የመጠየቅ መብት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1324)
ü የአላባ ተቀባዩን መብት ሳይጋፋ በንብረቱ የማዘዝ መብት አለው ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1323)
ü የባለቤትነት መብቱን መሰረት በማድረግ የመድን ዋስትና የመግዛትና የመድን ሽፋን የተሰጠው አደጋ እውን ሲሆን (whenever the risk materialises) ካሳ የማግኘት መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1320)
ü በአላባ ከተሰጠው ንብረት ጋር ያለአግባብ የተላለፈ ንብረት ካለ የማስመለስ መብት፡፡
ü ለአላባ ተቀባይ እንዲሆን ከተወሰነው በላይ ፍሬ ወይም ትርፍ ከተገኘ የመውሰድ መብት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1328(2) እና 1348)
ü በአላባ በተሰጠው መሬት ውስጥ የተቀበረ ገንዘብ (treasure) ከተገኘ ባለቤት በመሆኑ የመውሰድ መብት፡፡( ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1329)
ü የአላባ ተጠቃሚው በተሰጠው ንብረት ላይ ሌላ ተጨማሪ ስራ ሰርቶ ከሆነ የአላባ መብቱ ከተቋረጠ ግዜ ጀምሮ በአንድ ዓመት ግዜ ውስጥ ንብረቱን ለማንሳት ካልጠየቀ አላባ ሰጪው የዚህ ተጫማሪ ስራ ባለቤት ይሆናል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1346/2/ ) ከግዴታ አንፃር ሲታይም የሚከተሉት ግዴታዎች ይኖሩታል፡፡
በአላባ የሰጠውን ንብረት ለአላባ ተጠቃሚው የማስረከብ ግዴታ አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1321)
የአላባ ውሉ በፅሑፍ እንዲሆንና እንዲመዘገብ የማድረግ ግዴታ አለው፡፡
በአላባ የተሰጠው ንብረት ጥገና ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ሲሆን ወጪውን የመሸፈን ግዴታ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1338)
የጦርነት መዋጮ፣ የሰራዊት ሰፈር፣ ቆሻሻ ማስወገጃ ወጪ ወይም ረግረጐች የማድረቅ የመሳሰሉ ልዩ ወጪዎች (extra ordinary charges) የመክፈል ግዴታ የአለባ ሰጪው ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.
በመደበኛ አገልግሎት ምክንያት ዋጋው ቢቀንስ (depreciation caused by ordinary wear and tear) የንብረትን ማሽቆልቆል መሰረት በማድረግ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚደረግ ወጪ ቢኖር የመሸፈን ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1326 )
የአላባ ግንኙነት ቀሪ ስለመሆን
የአላባ ተጠቃሚው በውሉ ያሉትን ግዴታዎች የጣሰ አንደሆነ የአላባ መብቱ ቀሪ ይሆናል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1318 (3) እና 1324)
የአላባ ተጠቃሚው ሲሞት የአላባ መብት በውርስ የሚተላለፍ መብት ባለመሆኑ ምክንያት ቀሪ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን የአላባ ተጠቃሚነት መብቱ የተሰጠው ለባልና ሚስት በጋራ በሆነ ጊዜ የአንደኛው መሞት የአላባ ተጠቃሚነቱን መብት ሙሉ ለሙሉ ቀሪ አያደርገውም፡፡ በሌላ አነጋገር በሂወት ካለው ስው ጋር የአላባ ግንኙነቱ ይቀጥላል ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1322)
የአላባ ውሉ ግዜ ሲያልቅ በአላባ ተጠቃሚ የመሆን መብቱ ቀሪ ይሆናል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1322)
የአላባ መብት ተጠቃሚነት መብት የተሰጠበት ነገር እንደ ጥሬ ገንዘብ ባሉ አላቂ ነገሮች (consumable goods) ሲሆንና ሲያልቁ የአላባ መብት የተቋቋመበት ውል ቀሪ ይሆናል፡፡
የአላባ ተጠቃሚው በራሱ ፍላጐት በግልፅ የአላባ ተጠቃሚነት መብቱን ሲተው (express waiver) (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1323(2))
በአላባ የተሰጠው ንብረት ሙሉ ለሙሉ ሲወድም የአላባ ጥቅም መሰረት (subject matter of the usufract) በሌለበት ሁኔታ መብቱ ሊኖር ስለማይችል የአላባ ግንኙነቱን እንዲቀር ያስገድዳል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1319፣ 1343) ስለዚህ የአላባ ግንኙነት እንደ ሁሉም በህግ ፊት ዋጋ ያለው ተግባር ወይም ከህግ የሚመነጭ መብት በአንድ ወቅት ሊቋረጥ የሚችል ግንኙነት ነው፡፡ ይህ ግንኙነት በመቋረጡ የሚኖረው ውጤትም፡-
vከአላባ ተጠቃሚው ጋር የተደረጉ ውሎች ውጤት አልባ (extinguished contracts) ይሆናሉ፡፡
vበአላባ የተሰጠው ንብረት የማይንቀሳቀስ ንብረት በሆነበት ግዜና ተከራይቶ ወይም በዋስትና ተሰጥቶ ከቆየ የውሉ ግዜ በማለቁ ብቻ የአላባ መብቱ ቀሪ ሊሆን ስላማይቻል 3ኛ ወገኞች ለሶስት ዓመት የግድ መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡
ስለዚህ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ የአላባ መብት ግዙፍነት ባላቸው የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ እንዲሁም ግዙፍነት በሌላቸው የንብረት መብቶች ላይ ሊመሰረት የሚችል ህገ-መንግስታዊ እውቅና የተሰጠው የዜጐች በንብረት የመገልገል፤ፍሬ የመሰብሰብንና መውሰድን መብት የሚያጎናፅፍ ከውል ፤ ከህግ ወይም ከኑዛዜ የሚመነጭ ግንኙነት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ከውል፤ ከህግና ከኑዛዜ የሚመነጩ በርካታ የአላባ ተጠቃሚና አላባ ሰጪ መብቶችና ግዴታዎች የሚስተዋሉበት ንበረትን መሰረት ያደረገ ግንኙነት ነው፡፡ ይህ ግንኙነት እንደሁሉም ህግ ፊት ዋጋ ያላቸው ተግባራት (juridical acts) ወይም ከህግ የሚመነጩ መብቶች (legal rights) ተመስርቶ ቆይታው ይርዘም ይጠር ሰዎች በመብቱና ግዴታው ሲሰሩበት ከቆዩ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ቀሪ የሚሆን ንብረትን መሰረት ያደረገ ግንኙነትም ነው፡፡
- Details
- Category: Property Law
- Hits: 8296
ሁለተኛው የጋራ ባለሃብትነት ግንኙነት ልዩ የጋራ ባለሃብትነት ሲሆን የዚህ መብት መሰረት (subject matter) የጋራ ግንብ፤ አጥር፡ አፓርትማ ወ.ዘ.ተ. ሊሆን ይችላል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1209(1)) ሰዎች በዚህ ዙርያ የሚኖራቸውን መብት በማስመልከት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 40(7) ማንኛወም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ ወይም ለሚያደርገው ቋሚ ንብረት ወይም ለሚያደርገው ቋሚ መሻሻል ሙሉ መብት አለው፡፡ . . ." በማለት ሁለት በአዋሳኝ የሚገናኙ ሰዎች በጋራ መሬታቸው ለሚገነቡት ግንብ፡ አጥር ወይም አፓርትማ የጋራ ባለቤትነት መብት እንዳላቸው በማረጋገጥ ይህን መብታቸውን የመሸጥ የመለወጥ የማውረስና የመሬቱ ተጠቃሚነት ሲቋረጥ ንብረቱን የማንሳት ባለቤትነቱን የማዛወር ወይም የካሳ ክፍያ የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ህገ-መንስታዊ እውቅና የተሰጠው የንብረት መብት ነው፡፡ ልዩ የጋራ ባለሃብትነት ከንብረት ህግ አኳያ ሲታይ መብቱም ሆነ ግዴታው የሚመነጨው የጋራ ግንብ፣ አጥር፣ ኮሪደር (በረንዳ) ወ.ዘ.ተ. በሚጠቀሙ አጐራባች ባለሃብቶች መካከል ከሚደረግ ውል ወይም የህግ ግምት ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1259 ፤ 1281 እና 1282) ከዚህ ውልና የህግ ግምት የንብረት ህግ ሊመነጩ የሚችሉ የልዩ የጋራ ባለሃብቶች መብቶችና ግዴታዎች ያሉ ሲሆን መብቶችን በቅድሚ ስንመለከት ፡-
የልዩ የጋራ ባለሃብቶች መብትና ግዴታ
የጋራ ግንብ (common wall) ፣ አጥር፣ መውጪያና መግብያ (ኮሪደር) የሚኖራቸው ሰዎች ከተጋሪው ጋር አብሮ ለመስራትና ለመገልገል የመደራደርና አብሮ ሰርቶ አብሮ የጋራ ንብረት በሆነው ነገር የጋራ የባለቤትነት መብት እንዲኖራቸው ማድረግ ይችላሉ፡፡ አንደኛው ወገን ይሁንታ ካልሰጠ ለማስገደድ ባይቻልም ሌሎቹ ተጐራባቶች የጋራ የሆነው ግንብ፣ አጥር፣ ኮሪደር ብቻቸውን ሆነው በጋራ መሬቱ ላይ የመገንባትና የንብረቱ ባለቤት የመሆን መብት አላቸው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1278 እና 1279(2))
ተገንብቶ የቆየ የጋራ ግንብ በከፊል ወይም በሙሉ በሚፈርስበት ግዜ አንደኛው ተጋሪ ሌላኛውን እንስራው ብሎ መጠየቅ ያለበት ቢሆንም ሌላው ተጋሪ ይሁንታን ካልሰጠ አንደኛው ወገን እንደገና ሊገነባውና የባለቤትነት መብቱ ለብቻው እንዲሆን በማድረግ ያለውን የጋራ ነው የሚል የህግ ግምት እንዲቀር ያደርጋል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1200 እና 1201፣ 1279) እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ ብቸኛ ባለቤት የሚሆነው በራሱ መሬት ላይ ሲገነባው ነው ወይስ በእንቢተኛው ተጋሪ መሬት ላይም ሲገነባ ብቸኛ ባለቤት መሆን ይችላል? የሚል ነው:: ህጉ ለዚህ በፍ/ብ/ሀ/ቁ 1279(2) ላይ የሚሰጠው ግልፅ መልስ ስላለ ብዙ የሚከራክር አይደለም ፡፡
በጋራ የሚገለገሉበት ህንፃ በጋራ መሬት ላይ ያረፈ ነው ተብሎ የመገመትና የጋራ ሃብታቸው እንደሆነ ተደርጎ የመገመት መብት አላቸው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1200(1) 1281፤)
የጋራ ባለሃብቶቹ ማህበር (syndicate) የማቋቋም፣ አስተዳዳሪ የመምረጥ፣ በሐራጅ እንዲሸጥ የመጠየቅና በማህበር ሰብሰባዎች ላይ ድምፅ የመስጠትና በውሳኔው ካልተስማሙ ይግባይ ብለው ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት የመሄድ መብት አላቸው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1293፣1295፣ 1298፣ 1303፣ 1304፣ 1305)
ልዩ የጋራ ሃብቱን ለማደስ ወይም እንደገና ለመገንባት የወጣውን ወጪ ከሌሎቹ የጋራ ባለሃብቶቹ በውል ወይም ከውል ውጭ በክስ የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1306፣ 1308 እና 1297)
የልዩ ባለሃብቶች ግዴታዎችን በተመለከተ ያየን እንደሆነም ፡-
የልዩ የጋራ ባለሃብቶች መብትና ግዴታ የሚወሰነው ውል በፅሑፍ የማድረግ ግዴታ አላቸው፡፡ ይህን ፎርም ተከትለው ስምምነቱን ካልፈፀሙ ግን ህጋዊ ውጤት አይኖረውም ወይም ዋጋ አልባ (void) ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1283)
ውሉ ንብረቱ በሚገኝበት(situs) የውል መዝጋቢ (notary) ወይም የፍርድ መዝገብ (court registry) መቀመጥና ወራሾች፣ የወደፊት ገዢዎች፣ ወኪሎች፣ የግብር ባለስልጣንና ዋስትና የተሰጣቸው ባለሀብቶች (secured creditors) እንዲያዩት በሚችል አኳኃን መቀመጥ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1284)
የጋራ ባለሃብቶቹ ህንፃው የተሰራበትን አላማና የተጋሪዎችን መብት የማክበር ግዴታ አላቸው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1290 እና 1291)
መብትን ማስከበር እንዳለ ሁሉ ግዴታዎችን የመሸከም ግዴታ ስለሚኖርባቸው ልዩ የጋራ ሃብቱን እንዳለ ጠብቆ የማቆየት፣ የማደስ እና የማስተዳደር ግዴታ አላቸው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1292)
ልዩ የጋራ ሃብት ከሆነ ንብረት ከፊሉ ቢፈረስና ማኅበሩ እንዲሰራ ቢወስን
ልዩ የጋራ ባለሀብትነት ቀሪ ስለመሆን
ልዩ የጋራ ባለሃብትነት መብት መሰረቱ የባለሃብቶቹ ውል ሲሆን ይህ ሰምምነት እንደሁሉም ህግ ፊት ዋጋ ያላቸው ተግባራት በአንድ ወቅት ተወልዶ ተጋሪዎች በመብታቸው ሲሰሩበት ከቆዩ በኃላ ቀሪ የሚሆኑባቸው ሁኔታዎችም አሉ፡፡ ከነዚህም ጥቂቶችን ወስደን ያየን እንደሆነ፡-
§የጋራ ባለሃብቱ የነበረውን የባለቤትነት መብት (ownership right) በሽያጭ ወደ ሌላ ሰው ሲያስተላለፍ መብቱ ወደ ገዢው የሚተላለፍ ቢሆንም ከሻጭ አኳያ ሲታይ ግን በሽያጭ ውሉ አማካይነት በጋራ ንብረቱ ላይ የነበረውን መብት ስለሚያጣ መብቱ ቀሪ ይሆናል ፡፡
§የጋራ ባለሃብቱ ሲሞት በጋራ ንብረቱ ላይ የነበረው መብትና ግዴታ ወደ ወራሾች የሚተላለፍ ቢሆንም ከሟቹ አንፃር ሲታይ ግን በሞት ምክንያት ውሉ ቀሪ ይሆናል፡፡
§ልዩ የጋራ ሃብቱ ያረፈበት መሬት ለህዝብ ጥቅም ተብሎ ሲለቀቅ የጋራ ባለሃብቶቹ መብት በመሬቱ ላይ ባሰፈሩት ግንባታ ላይ ስለሚመሰረት በሚለቁበት ግዜ የመልቀቂያ ካሳ የማግኘት ህገ-መንግስታዊ መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በንብረቱ የነበራቸው የጋራ ባለሃብትነት መብት ግን ቀሪ ይሆናል፡፡
§መልሶ እስካልተገነባ ድረስ በጋራ ሃብቱ ላይ ጠቅላላ (total destruction) በሚያጋጥምበት ግዜ ለውሉ መመስረት ምክንያት የሆነው ንብረት ስለማይኖርና በሌለ ንብረት ላይ የጋራ ባለቤትነት መብት ሊመሰረት ስለማይችል የንብረት መብታቸው ቀሪ ይሆናል፡፡
ስለዚህ የጋራ የባለሃብትነት መብት መሰረት ግዙፍነት ያላቸው የሚንቀሳቀሱ ወይም የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች እና ግዙፍነት የሌላቸው ንብረቶች ናቸው፡፡ የመብቱ ዓይነት ተራ የጋራ ባለሃብትነት መብት ይሁን ልዩ የጋራ ባለሃብትነት መብት መሰረታቸው አሁን ባለው የፍ/ብሄር ፍትህ ስርዓት ዓይን ሲታይ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ-መንግስት አንቀጽ 40(1) (7)፣ 31 እና 89(1) ላይ የተደነገጉት ህገ-መንግስታዊ መርሆች መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ህገ-መንግስቱ ከመውጣቱ በፊት የነበረውን የፍ/ብሄር ህግ እነዚህን የህገ-መንግስቱን መርሆች መሰረት አድርገን መተርጎምና በስራ ላይ ማዋል የለብንም ማለት እንዳልሆነ ግልፅ ሊሆን ይገባል ፡፡ ከፍ ብለን እንዳየነው በፍ/ ብሄር ህጉም ቢሆን እምብዛም ከህገ-መንግስታዊ መርሁ ባልተቃረነ ወይም ባልራቀ መልኩ የንብረት መብት ጥበቃ ተደርጐላቸው የምናገኛቸው በርካታ የጋራ የባለሃብትነት መብቶችና ግዴታዎች አሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው የፍ/ብሄር ህጉ እነዚህ መብቶችና ግዴታዎች የሚተዳደሩበት ስርዓትና በመጨረሻም ቀሪ የሚሆኑበት ሁኔታ ያካተተ አስከሆነ ድረስና ህገ-መንግስቱን መሰረት በማድረግ የወጣ አዲስ የንብረት ህግ እስኪኖረን ድርስ ያለውን ህግ ከህገ-መንግስቱ ጋር አጣጥመን በስራ ላይ ማዋል ያለብን መሆኑ ነው ፡፡ የጋራ ባለሀብትነት መብት የንብረት መብት እንደመሆኑ መጠን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት ከወጣ በኋላ በሌሎች የንብረት ነክ ህጎችም ተካቶ የምናገኘው መብት መሆኑን ከፍ ብለን ካየናቸው አዋጆች መረዳት የሚቻል ቢሆንም ካለንበት ህገ መንግስታዊ ስርዓት ጋር የተጣጣመና የተሟላ የንብረት ህግ የሚኖረን ግን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት መርሆችን መሰረት ያደረገ አዲስና ወጥ የሆነ የንብረት ህግ ሲታወጅ ነው፡
ልዩ የጋራ ባለሃብትነት (Special joint ownership)
ሁለተኛው የጋራ ባለሃብትነት ግንኙነት ልዩ የጋራ ባለሃብትነት ሲሆን የዚህ መብት መሰረት (subject matter) የጋራ ግንብ፤ አጥር፡ አፓርትማ ወ.ዘ.ተ. ሊሆን ይችላል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1209(1)) ሰዎች በዚህ ዙርያ የሚኖራቸውን መብት በማስመልከት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 40(7) ማንኛወም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ ወይም ለሚያደርገው ቋሚ ንብረት ወይም ለሚያደርገው ቋሚ መሻሻል ሙሉ መብት አለው፡፡ . . ." በማለት ሁለት በአዋሳኝ የሚገናኙ ሰዎች በጋራ መሬታቸው ለሚገነቡት ግንብ፡ አጥር ወይም አፓርትማ የጋራ ባለቤትነት መብት እንዳላቸው በማረጋገጥ ይህን መብታቸውን የመሸጥ የመለወጥ የማውረስና የመሬቱ ተጠቃሚነት ሲቋረጥ ንብረቱን የማንሳት ባለቤትነቱን የማዛወር ወይም የካሳ ክፍያ የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ህገ-መንስታዊ እውቅና የተሰጠው የንብረት መብት ነው፡፡ ልዩ የጋራ ባለሃብትነት ከንብረት ህግ አኳያ ሲታይ መብቱም ሆነ ግዴታው የሚመነጨው የጋራ ግንብ፣ አጥር፣ ኮሪደር (በረንዳ) ወ.ዘ.ተ. በሚጠቀሙ አጐራባች ባለሃብቶች መካከል ከሚደረግ ውል ወይም የህግ ግምት ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1259 ፤ 1281 እና 1282) ከዚህ ውልና የህግ ግምት የንብረት ህግ ሊመነጩ የሚችሉ የልዩ የጋራ ባለሃብቶች መብቶችና ግዴታዎች ያሉ ሲሆን መብቶችን በቅድሚ ስንመለከት ፡-
የልዩ የጋራ ባለሃብቶች መብትና ግዴታ
የጋራ ግንብ (common wall) ፣ አጥር፣ መውጪያና መግብያ (ኮሪደር) የሚኖራቸው ሰዎች ከተጋሪው ጋር አብሮ ለመስራትና ለመገልገል የመደራደርና አብሮ ሰርቶ አብሮ የጋራ ንብረት በሆነው ነገር የጋራ የባለቤትነት መብት እንዲኖራቸው ማድረግ ይችላሉ፡፡ አንደኛው ወገን ይሁንታ ካልሰጠ ለማስገደድ ባይቻልም ሌሎቹ ተጐራባቶች የጋራ የሆነው ግንብ፣ አጥር፣ ኮሪደር ብቻቸውን ሆነው በጋራ መሬቱ ላይ የመገንባትና የንብረቱ ባለቤት የመሆን መብት አላቸው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1278 እና 1279(2))
ተገንብቶ የቆየ የጋራ ግንብ በከፊል ወይም በሙሉ በሚፈርስበት ግዜ አንደኛው ተጋሪ ሌላኛውን እንስራው ብሎ መጠየቅ ያለበት ቢሆንም ሌላው ተጋሪ ይሁንታን ካልሰጠ አንደኛው ወገን እንደገና ሊገነባውና የባለቤትነት መብቱ ለብቻው እንዲሆን በማድረግ ያለውን የጋራ ነው የሚል የህግ ግምት እንዲቀር ያደርጋል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1200 እና 1201፣ 1279) እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ ብቸኛ ባለቤት የሚሆነው በራሱ መሬት ላይ ሲገነባው ነው ወይስ በእንቢተኛው ተጋሪ መሬት ላይም ሲገነባ ብቸኛ ባለቤት መሆን ይችላል? የሚል ነው:: ህጉ ለዚህ በፍ/ብ/ሀ/ቁ 1279(2) ላይ የሚሰጠው ግልፅ መልስ ስላለ ብዙ የሚከራክር አይደለም ፡፡
በጋራ የሚገለገሉበት ህንፃ በጋራ መሬት ላይ ያረፈ ነው ተብሎ የመገመትና የጋራ ሃብታቸው እንደሆነ ተደርጎ የመገመት መብት አላቸው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1200(1) 1281፤)
የጋራ ባለሃብቶቹ ማህበር (syndicate) የማቋቋም፣ አስተዳዳሪ የመምረጥ፣ በሐራጅ እንዲሸጥ የመጠየቅና በማህበር ሰብሰባዎች ላይ ድምፅ የመስጠትና በውሳኔው ካልተስማሙ ይግባይ ብለው ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት የመሄድ መብት አላቸው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1293፣1295፣ 1298፣ 1303፣ 1304፣ 1305)
ልዩ የጋራ ሃብቱን ለማደስ ወይም እንደገና ለመገንባት የወጣውን ወጪ ከሌሎቹ የጋራ ባለሃብቶቹ በውል ወይም ከውል ውጭ በክስ የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1306፣ 1308 እና 1297)
የልዩ ባለሃብቶች ግዴታዎችን በተመለከተ ያየን እንደሆነም ፡-
የልዩ የጋራ ባለሃብቶች መብትና ግዴታ የሚወሰነው ውል በፅሑፍ የማድረግ ግዴታ አላቸው፡፡ ይህን ፎርም ተከትለው ስምምነቱን ካልፈፀሙ ግን ህጋዊ ውጤት አይኖረውም ወይም ዋጋ አልባ (void) ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1283)
ውሉ ንብረቱ በሚገኝበት(situs) የውል መዝጋቢ (notary) ወይም የፍርድ መዝገብ (court registry) መቀመጥና ወራሾች፣ የወደፊት ገዢዎች፣ ወኪሎች፣ የግብር ባለስልጣንና ዋስትና የተሰጣቸው ባለሀብቶች (secured creditors) እንዲያዩት በሚችል አኳኃን መቀመጥ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1284)
የጋራ ባለሃብቶቹ ህንፃው የተሰራበትን አላማና የተጋሪዎችን መብት የማክበር ግዴታ አላቸው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1290 እና 1291)
መብትን ማስከበር እንዳለ ሁሉ ግዴታዎችን የመሸከም ግዴታ ስለሚኖርባቸው ልዩ የጋራ ሃብቱን እንዳለ ጠብቆ የማቆየት፣ የማደስ እና የማስተዳደር ግዴታ አላቸው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1292)
ልዩ የጋራ ሃብት ከሆነ ንብረት ከፊሉ ቢፈረስና ማኅበሩ እንዲሰራ ቢወስን
ልዩ የጋራ ባለሀብትነት ቀሪ ስለመሆን
ልዩ የጋራ ባለሃብትነት መብት መሰረቱ የባለሃብቶቹ ውል ሲሆን ይህ ሰምምነት እንደሁሉም ህግ ፊት ዋጋ ያላቸው ተግባራት በአንድ ወቅት ተወልዶ ተጋሪዎች በመብታቸው ሲሰሩበት ከቆዩ በኃላ ቀሪ የሚሆኑባቸው ሁኔታዎችም አሉ፡፡ ከነዚህም ጥቂቶችን ወስደን ያየን እንደሆነ፡-
§የጋራ ባለሃብቱ የነበረውን የባለቤትነት መብት (ownership right) በሽያጭ ወደ ሌላ ሰው ሲያስተላለፍ መብቱ ወደ ገዢው የሚተላለፍ ቢሆንም ከሻጭ አኳያ ሲታይ ግን በሽያጭ ውሉ አማካይነት በጋራ ንብረቱ ላይ የነበረውን መብት ስለሚያጣ መብቱ ቀሪ ይሆናል ፡፡
§የጋራ ባለሃብቱ ሲሞት በጋራ ንብረቱ ላይ የነበረው መብትና ግዴታ ወደ ወራሾች የሚተላለፍ ቢሆንም ከሟቹ አንፃር ሲታይ ግን በሞት ምክንያት ውሉ ቀሪ ይሆናል፡፡
§ልዩ የጋራ ሃብቱ ያረፈበት መሬት ለህዝብ ጥቅም ተብሎ ሲለቀቅ የጋራ ባለሃብቶቹ መብት በመሬቱ ላይ ባሰፈሩት ግንባታ ላይ ስለሚመሰረት በሚለቁበት ግዜ የመልቀቂያ ካሳ የማግኘት ህገ-መንግስታዊ መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በንብረቱ የነበራቸው የጋራ ባለሃብትነት መብት ግን ቀሪ ይሆናል፡፡
§መልሶ እስካልተገነባ ድረስ በጋራ ሃብቱ ላይ ጠቅላላ (total destruction) በሚያጋጥምበት ግዜ ለውሉ መመስረት ምክንያት የሆነው ንብረት ስለማይኖርና በሌለ ንብረት ላይ የጋራ ባለቤትነት መብት ሊመሰረት ስለማይችል የንብረት መብታቸው ቀሪ ይሆናል፡፡
ስለዚህ የጋራ የባለሃብትነት መብት መሰረት ግዙፍነት ያላቸው የሚንቀሳቀሱ ወይም የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች እና ግዙፍነት የሌላቸው ንብረቶች ናቸው፡፡ የመብቱ ዓይነት ተራ የጋራ ባለሃብትነት መብት ይሁን ልዩ የጋራ ባለሃብትነት መብት መሰረታቸው አሁን ባለው የፍ/ብሄር ፍትህ ስርዓት ዓይን ሲታይ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ-መንግስት አንቀጽ 40(1) (7)፣ 31 እና 89(1) ላይ የተደነገጉት ህገ-መንግስታዊ መርሆች መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ህገ-መንግስቱ ከመውጣቱ በፊት የነበረውን የፍ/ብሄር ህግ እነዚህን የህገ-መንግስቱን መርሆች መሰረት አድርገን መተርጎምና በስራ ላይ ማዋል የለብንም ማለት እንዳልሆነ ግልፅ ሊሆን ይገባል ፡፡ ከፍ ብለን እንዳየነው በፍ/ ብሄር ህጉም ቢሆን እምብዛም ከህገ-መንግስታዊ መርሁ ባልተቃረነ ወይም ባልራቀ መልኩ የንብረት መብት ጥበቃ ተደርጐላቸው የምናገኛቸው በርካታ የጋራ የባለሃብትነት መብቶችና ግዴታዎች አሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው የፍ/ብሄር ህጉ እነዚህ መብቶችና ግዴታዎች የሚተዳደሩበት ስርዓትና በመጨረሻም ቀሪ የሚሆኑበት ሁኔታ ያካተተ አስከሆነ ድረስና ህገ-መንግስቱን መሰረት በማድረግ የወጣ አዲስ የንብረት ህግ እስኪኖረን ድርስ ያለውን ህግ ከህገ-መንግስቱ ጋር አጣጥመን በስራ ላይ ማዋል ያለብን መሆኑ ነው ፡፡ የጋራ ባለሀብትነት መብት የንብረት መብት እንደመሆኑ መጠን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት ከወጣ በኋላ በሌሎች የንብረት ነክ ህጎችም ተካቶ የምናገኘው መብት መሆኑን ከፍ ብለን ካየናቸው አዋጆች መረዳት የሚቻል ቢሆንም ካለንበት ህገ መንግስታዊ ስርዓት ጋር የተጣጣመና የተሟላ የንብረት ህግ የሚኖረን ግን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት መርሆችን መሰረት ያደረገ አዲስና ወጥ የሆነ የንብረት ህግ ሲታወጅ ነው፡
- Details
- Category: Property Law
- Hits: 8519
የጋራ ባለሃብትነት ምንድን ነው? የጋራ ባለሃብትነት መብት በመሰረቱ በሁለት እና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል በሚደረግ ውል የሚቋቋምና የሚገዛ የጋራ ንብረት ባለሃብትነት መብት ወይም ከህግ በሚመነጭ የጋራ ባለሃብትነት የሚቋቋም የንብረት መብት ነው፡፡ የጋራ ባለሃብትነት መብት ከፍታብሄር ህግ አኳያ ሲታይ በሁለት ማለትም ተራ የጋራ ባለሃብትነት (Ordinary joint ownership) እና ልዩ የጋራ ባለሃብትነት (Special joint ownership) በሚል ሊከፈል ይችላል፡፡ ተራ የጋራ ባለሃብትነት መብት መሰረቱ (Subject matter) ግዙፍነት ያላቸው የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችና ግዙፍነት የሌላቸው የንብረት መብቶች እንደ የፈጠራ መብት (patent right) ፣ የቅጂ መብት (copy right) እና የኢንዱስትሪ ንድፍ (Industrial design) ያሉ የንብረት መብቶችን መሰረት በማድረግ ሊሚቋቋም የሚችል የንበረት መብት ነው፡፡ የጋራ ባለሃብቶቹ ይህን የንብረት መብታቸውን ንብረቱ የማይንቀሳቀስ ንብረት በሚሆንበት ግዜ በዋስትና (mortgage) ፣ የንብረት አገልግሎት (Servitude) ፣ አላባ በመስጠት (usufruct) ወይም የቀደምትነት መብት (pre-emptive right) አለኝ በማለት በጋራ ሃብቱ ላይ ያላቸውን መብት ሊሰሩበት የሚያስችላቸው የንብረት መብት ነው፡፡ ንብረቱ የሚንቀሳቀስ በሚሆንበት ግዜም በዋስትና (pledge) በአላባ (usufract) ወ.ዘ.ተ. በመስጠት በጋራ ሃብቱ ላይ ያላቸውን መብት ሊሰሩበት ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን በሁለትና ከዚያም በላይ ባሉ ሰዎች መካከል የጋራ ባለሃብትነት ግንኙነት አለ ብሎ ለማለት የሚኖረው መስፈርት የጋራ ባለሃብቶች ነን በሚሉት ሰዎች መካከል የባለቤትነት ጥቅም (ownership interest) ያላቸው ሰዎች መሆንና የጋራ ባለሃብትነታቸው በተመሳሳይ ንብረት ላይ የተመሰረተ መሆን ይኖርበታል፡፡(the joint ownership must exist over the same thing) እነዚህን ሁለት መመዘኛዎች ካላሟሉ ግን የጋራ ባለሃብቶች ሊባሉ አይችሉም፡፡ ለምሳሌ አንድ የንብረት ባለቤት (owner) እና የአላባ ተጠቃሚ (usufractuary) የሆነ ሰው በአንድ ንብረት ላይ የጋራ ባለሃብቶች (joint owners) ሊሆኑ አይችሉም፡፡የዚህ ምክንያትም አንደኛው በንብረቱ ያለው የሰፋ የባለቤትነት መብት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በንብረት ላይ ያለው መብት ጠበብ ያለ የአላባ መብት ስለሆነ በንብረት ላይ ያላቸው መብት የተለያየ አስከሆነ ድረስ የጋራ ባለሀብትነት (joint ownership) ሊመሰርቱ አይችሉም፡፡ ስለሆነም የጋራ ባለሀብትነት ግንኙነት አለ ብሎ ለማለት የባለቤትነት መብትንና ይህ መብት በዚያ ተለይቶ በታወቀ ንብረት ላይ ያለ የጋራ መብት መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
የጋራ ባለሃብቶች መብቶች (Rights of Joint Owners)
የጋራ ባለሃብትነት መብት ከውል ወይም ከህግ ሊመነጭ ይችላል፡፡ ይሄውም ስምምነቱን መሰረት ከሚያደርገው ሰነድ ወይም በጋራ ባለሃብቶች መካከል የተደረገ ስምምነት ባይኖርም እንኳ ህግ በራሱ ግዜ ያንን ንብረት የጋራ ሃብት በሚያደርግበት ግዜ ሊመሰረት ይችላል፡፡ ለምሳሌ በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 አንቀጽ 62 መሰረት የሚታይ የባልና የሚስት የጋራ ሃብት በሚሆንበት ጊዜ፣ የውርስ ንብረት እስከ ሚከፋፈል ድረስ ያለው የጋራ ባለሃብትነት መብት (የፍ/ብ/ህ/ቁ.1060-1064) ወይም በማቀላቀል ወይም በማዋሃድ መሰረት የተገኘ በጋራ ባለሃብትነት መብት በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1183 ወይም ከፍ/ብ/ህ/ቁ. 1257-1277 ባሉ ድንጋጌዎች መሰረት የሚገዛ የጋራ ባለሃብትነት መብት በሚኖርበት ግዜ መብቱ የመነጨው ከህግ ይሆንና ሰዎቹ የጋራ ባለሃብቶች ይሆናሉ፡፡ ከዚህም በመነሳት የጋራ ባለሃብቶች ከንብረት ህጉ አኳያ ሊኖራቸው የሚችል የጋራ እና የተናጠል መብቶችንና ገዴታዎችን በዝርዝር ስናይ፡-
- Øየጋራ ሃብቱን በማስመልከት የተደረገ ስምምነት ከሌለ በስተቀር የጋራ ባለሃብቶች የጋራ ንብረት በሆነው ንብረት ላይ እኩል የባለቤትነት መብት (equal ownership right) አላቸው ተብሎ የህግ ግምት (legal presumption) ስለሚወሰድ በጋራ ሃብቱ ላይ ያላቸውን ድርሻ ከመሬት በስተቀር የመሸጥ ወይም መሬትን ጨምሮ በሌላ ንብረት ላይ በዋስትና የማስያዝና የመከፋፈል መብት ይኖራቸዋል፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ 1259፤ 1267፤ 1271 እና 1272) እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ፍ/ብ/ሀ/ቁ 1260 ለምን በአላባ የመስጠት መብትንስ አላከተተም? የሚል ጥያቄ ሲሆን ለዚህ በመልስነት ወይም በመከራከርያነት ሊነሳ የሚችለው ሃሳብ የእንግሊዝኛው የፍታብሄር ህግ ቅጂ "dispose" የሚል ቃልን በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1260(1) ላይ ሲለሚጠቀም እና በአላባ መስጠት የሚለውን መብት በዚሁ ውስጥ በውስጠ ታዋቂነት አካቷል የሚል ሓሳብን በማንሳት ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1260(1) ለአንድ የጋራ ሃብት ባለድርሻ የአላባ መብትን የሰጠው ስለሆነ ድርሻውን በአላባ ለሌላ ሰው ማስተላለፍ ይችላል የሚለው መከራከርያ ነው፡፡ ሌላው የመከራከሪያ ወይም የአተረጓጐም ስልት አንድ የጋራ ባለሃብት በድርሻው ያለውን ባለቤትነት መብት (ownership right) መሰረት በማድረግ ለሌላ ሰው የአላባ መብት ሰጠ ማለት በጋራ ሃብቱ ላይ ያለውን መብት በከፊል ለሌላ ሰው አስተላለፈ ማለት ስለሆነ ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1260(1) በአለባ የመስጠት መብትንም አካቷል ተብሎ መተርጐም አለበት የሚል ነው፡፡ አዘጋጁም በነዚህ ሃሳቦች ይስማማል፡፡ ለዚህም በምክንያትነት ሊጠቀስ የሚችለው የባለቤትነት መብት ያለው ሰው የሌላውን ሰው መብት ሳይነካ በንብረቱ ላይ እንደፈለገ የማዘዝ፤ (abusus or jus disponendi) በንብረቱ የመገልገል (usus or jus utendi) እና ፍሬውን የመሰብሰብና የመጠቀም(fructus or jus fruendi) መብቶች ስለሚኖሩትና አላባ ግን ከባለቤትነት መብት በጠበበ መልኩ በንብረቱ የመገልገልን ወይም ፍሬውን ሰብሰቦ የመውሰድን ወይም ሁለቱን መብቶች አዳብሎ ሊይዝ የሚችል በመሆኑ ፍ/ብ/ህ/ቁ.1260(1) ደግሞ ሶስቱን መብቶች ባካተተ መልኩ የሚደነግግ ከመሆኑ አንፃር ሲታይ በአላባ የመስጠትንም መብት ያካተተ ነው ብሎ መተርጐሙ የህጉን አላማ የበለጠ የሚያሳካል አተረጓጎም ስለሆነ ነው፡፡
- Øበጋራ ሃብቱ የመገልገል ወይም ፍሬውን የመሰብሰብ መብት አላቸው፡፡ ይሄውም የጋራ ሃብቱ የተፈጥሮ ፍሬ (natural fruit)፣ ሲቪል ፍሬ (Civil Fruit) የኢንዱስትሪ ፍሬ (Industrial fruit) ወይም ምርት (product ) ሊሆን ይችላል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1170፣ 1171፡ 1264 እና 1333) ስለሆነም የጋራ ሃብቱ ከሚያፈራው ፍሬ እንደየደረጃቸው ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው፡፡
- Øየጋራ ባለሃብቶቹ አንድን ባለድርሻ ነኝ የሚልን ሶስተኛ ወገን ሊከፈለው የሚገባውን በመክፈል ከጋራ ባለሃብትነቱ ለማስወጣት የሚያስችል የጋራ መብት (Concurrent right ) አላቸው፡ በዚህ ጊዜ ድርሻው ለመግዛት ገንዘብ ማዋጣት ያለባቸው ሲሆን በየድርሻቸው መጠን (pro rata basis) ማዋጣትና ገንዘቡን ለባድርሻው መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1261 እና 1386-1409)
- Øከጋራ ባለሃብቶቹ መካከል አንዱ በጋራ ሃብቱ ላይ ያለውን ድርሻ ለመሸጥ በሚፈልግበት ግዜ ከጋራ ባለሃብቶቹ አንዱ ለሱ እንዲሸጥለት የቀደምትነት መብቱን መሰረት በማድረግ ሊያስገድደው ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን በገበያ ዋጋው እንጂ ከዚያ ባነሰ ዋጋ እንዲሸጥለት ሊያስገድደው ይችላል ማለት አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር የጋራ ባለሃብቱ ድርሻ እገዛለሁ በሚልበት ግዜ የሻጩን በንብረቱ ተጠቃሚ የመሆን መብት መሰረት በማድረግ የተደነገጉ ድንጋጌዎችን በማይጥስ መንገድ መሆን ይኖርበታል፡፡ (ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 40(1)፣ ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1261 እና 1386)
- Øበአንድ በጋራ ሃብትነት የተያዘ ንብረት ላይ ድርሻ ያለው ሰው ድርሻውን ለመተው ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ይህን መብቱን መሰረት በማድረግ የነበረኝን ድርሻ ትቻለሁ በሚል ሰበብ ከመተዉ በፊት የዚህ የጋራ ሃብት ወጪዎችም ሆኑ እዳዎች ከመክፈል ወይም ለመከፈሉ ሃላፊ ከመሆን አይድንም፡፡ የተቀሩት የጋራ ባለሃብቶች ይህን የተተወን ድርሻ በእኩል የመካፈል መብት ያላቸው ሲሆን በራሱ ፈቃድ ድርሻውን ትቻለሁ ያለ የጋራ ባለሃብት ተመልሶ በድርሻየ የጋራ ባለሃብት ልሁን ብሎ መጠየቅ አይችልም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1262፣ 1164)
- Øበጋራ ሃብቱ ላይ ድርሻ ያለው ሰው የሌሎችን ባለድረሻዎች መብት ሳይጥስ የጋራ ሃብቱ ለታለመለት አላማ እንዲውል የማድረግ መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1263)
- Øየጋራ ባለሃብቶቹ የጋራ ንብረታቸውን የማስተዳደርና ይህንን መሰረት በማድረግ ድምፅ የመስጠትና ውሳኔ የማሳለፍ መብት አላቸው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1265 እና 1266 )
- Øአንድ የጋራ ሃብት ባለ ድርሻ የጋራ ሃብቱ ሊደርስበት ከሚችል ሙሉ (total) ወይም ከፊል (partial) ጥፋት (loss) ለማዳን ሲል ያወጣውን ወጪ ከጋራ ባለሃብቶቹ የመጠየቅ መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1268)
ብዙውን ግዜ ከዚህ መብት ጋር ተያያዥነት ባለው መልኩ የሚነሳው ጥያቄ ከአደጋ ለመከላከል ወጪውን የጠየቀው ስራ ውጤታማ ባይሆንና የጋራ ሃብቱ ቢወድም ሌሎቹ የጋራ ሃብት ባለድርሻዎች ይህን ወጪ የመተካት ግዴታ አላቸውን? የሚል ሲሆን ሌላውም የጋራ ሃብቱ በሙሉ ወይም በከፊል ከአደጋው ቢተርፍም ለዚህ ሲባል በአንደኛው ባለድርሻ የወጣው ወጪ ከጋራ ሃብቱ ዋጋ የበዛ በሚሆንበት ግዜስ የጋራ ባለሃብቶቹ ይህን ወጪ የመሸፈን ግዴታ አላቸውን? የሚሉ ናቸው፡፡ በመጀመርያው ጥያቄ ዙሪያ የሚንሸራሸሩት ሃሳቦች የጋራ ሃብቱን ለመከላከል የወጣው ወጪ መታየትና መመዘን ያለበት ከድል (success) አንፃር ሳይሆን ከአላማው (purpose) አንፃር መሆን ይኖርበታል:: ፍ/ብ/ህ/ቁ.1268 ቢሆንም የንብረቱ ከአደጋ ወይም ከጉዳት ስለመከላከልና ለዚህ ሲባል ስለሚወጣ ወጪ እንጂ ስለውጤቱ የሚለው ነገር ስለሌላ የመከላከሉ ግብ መምታት እና አለመምታት ወጪውን ከመሸፈንና ካለመሸፈን ጋር አያይዘን ማየት የለብንም የሚል ነው፡፡ ለዚህ የመራከሪያ ሃሳብ እንደማጠናከሪያ የሚነሱት ሌሎች ሓሳቦችም ንብረቱን ካላተረፈው ወጪውን አንሸፍንም የሚል አካሄድ መከተል የጋራ ሃብቱ እየጋየም ቢሆን በግሉ አውጥቶ የሚከላከል ሰው ስለማይኖር የጋራ ባለሃብቶች ችላ እንዲሉ ስለሚያደርግ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዘን ይቸላል የሚል ነው፡፡ ሌላውም አንድን በአደጋ ግዜ ረጋ ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ በሆነበት ግዜ የጋራ ሃብቱን ለማዳን ሲል አስፈላጊ የሆነውን ወጪ ያወጣ ባለድርሻ ወጪውን አንተካም ብሎ ማለት ምክንያታዊ አይደለም (unreasonable) የሚል ነው፡፡ የሁለተኛውን ጥያቄ በማስመልከት የሚሰነዘረው አስተያየትም የጋራ ንብረቱን ከአደጋ ለመከላከል የወጣው ወጪ ከጋራ ሃብቱ ዋጋ በላይ ቢሆንም ለዚህ የወጣን ወጪ የጋራ ባለሃብቶቹ መተካት አለባቸው የሚል ሲሆን ለዚህም በምክንያትነት የሚሰነዘረው አስተያየት የጋራ ሃብቱን ለመከላከል የወጣው ወጪ በመብዛቱ ብቻ እንዳላስፈላጊ ወጪ (unnecessary expense) መታየት የለበትም፡፡ የፍታብሄር ህጉ ይህን የሚያስብ ቢሆን ኑሮ አሁን እያነሳን ያለውን የባለ ድርሻው መብት በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1268 ያላስፈላጊ ወጪ የሚላቸውን ነገሮች በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1269 ለብቻ ባላስተናገዳቸው ነበር የሚል አስተያየት ነው፡፡ ሌላው ከባለድርሻው መብት ጋር ተያያዥነት ባለው መልኩ አንድ ግልፅ መሆን ያለበት ጉዳይ ግን አንድ ባለድርሻ ይህንን ለማድረግ ስልጣን ሳይኖረውና አስፈላጊ ባልሆነ ጊዜ ወጪ አድርጎ የጋራ ሃብቱን ኢኮኖሚያዊ ዋጋ ከፍ እንዲል፤ (increase the economic value) እይታው እንዲያምር፤ (increase the appearances) ወይም የሃብቱ ጠቃሚነት እንዲጨምር (increase the usefulness) ቢያደርግም ወጪውን ሌሎች ባለድርሻዎች እንዲተኩለት መጠየቅ የማይችል መሆኑ ነው ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1269(1)) አንደዚሀ ያለ ድርጊት የፈፀመ ባለድርሻ ያለው አማራጭም ንብረቱን ቀድሞ ወደ ነበረበት መመለስ (restoration) ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1269(2))
- Øየጋራ ባለሃብትነቱ የተመሰረተው በባለ ድርሻዎቹ ስምምነት በሆነ ግዜ የጋራ ባለሃብት ለመሆን በነፃ ፍላጐት ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ መጠን ባለድርሻው ከጋራ ባለሃብትነቱ ለመውጣትም (to withdraw) ነፃ ነው፡፡ በእርግጥ ከባለድርሻዎቹ አንዱ ሽጠን እንካፈል ሲል ሌሎቹ ደግሞ በዓይነት እንካፈል የሚል መከራከሪያ በመያዝ ከአንድ ስምምነት ላይ ላይደርሱ ይችላሉ ፡፡ እንደዚህ በሚሆንበት ጊዜ ፍ/ቤት ጉዳያቸውን በማየት ወቅቱ ለመሸጥ አመቺ ነው ባላለበት ጊዜ የከፍፍል ጥያቄውን ከስድስት ወር ላልበለጠ ጊዜ ሊያረዝመው ይችላል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1271) የሚከፋፈለው ነገር የማይንቀሳቀስ ንብረት በሚሆንበት ግዜም የጋራ ንብረቱ፤
-
- ከተቋቋመት አላማ ውጭ እንዳይሆን
- ክፍፍሉ የጋራ ሃብቱን ኢኮኖሚያዊ ዋጋ የሚቀንሰው እንዳይሆን
- በቀጣይ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ከፍተኛ የሆነ ችግር የማይፈጥር መሆኑን ታሳቢ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1272) የጋራ ባለሃብትነት መብት ከስምምነት ሊመነጭ እንደሚችል የተገለፀ ቢሆንም የጋራ ሃብቱን መሰረት ያደረገ ስምምነት ባይኖርም ህግ በራሱ የጋራ ሃብት እንደሆኑ ግምት የሚወስድባቸው እንደ አጥር፣ የጋራ ግንብና ኮሪደር ያሉ እንዳሉ ልንገነዘብ ይገባል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1281(1) (2)
የጋራ ባለሃብቶች ግዴታዎች (Duties of Joint Owners)
የጋራ ባለሃብትነት እንደሁሉም ህግ ፊት ዋጋ ያላቸው ተግባራት (juridical acts) ከስምምነት የሚመነጩ መብቶች እንዳሉት ሁሉ ግዴታዎችም እንዲሚኖሩት ይታወቃል፡፡ የጋራ ባለሃብትነቱ የመነጨው ከህግ በሚሆንበት ግዜም እንደዚሁ ከህጉ የሚመነጭ የጋራ ባለሃብቶች መብትና ግዴታ ይኖራል፡፡ ከንብረት ህጋችን አንፃር የጋራ ባለሃብቶችን ግዴታዎች ስንመለከት፡-
በአንድ የጋራ ሃብት ላይ ድርሻ ያለው ተጋሪ የጋራ ሃብት በሆነው ንብረት የመገልገል መብት (physical enjoyment) ቢኖረውም በዚህ መብቱ በሚሰራበት ግዜ ንብረቱ ከተቋቋመበት አላማ ውጭ ሊገለገልበትና (shall not convert the purpose for which it was destined) የሌሎቹን ባለድርሻዎች በጋራ ንብረቱ የመገልገል መብትን በሚፃረር መንገድ (shall not impair their use rights) ሊገልገልበት አይገባም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1263)
የጋራ ባለሃብቶቹ ከውሳንያቸው ለሚመነጭ ያልተጠበቀ ውጤት (consequence) ሃላፊ የመሆን ግዴታ አላቸው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1267)
በባለድርሻው አማካይነት በጋራ ሃብቱ ላይ ለደረሰ ጉዳት ከባሰ ውድመት ለማዳን ሲባል በጥፋት የወጣው ወጪ አስፈላጊ ወጪ (necessary expense) ቢሆንም ጥፋቱን የፈፀመው ባለድርሻ ወጪውን የመሸፈን ግዴታ አለበት፡፡ እንዲሁም ወጪው አላማ የሌለው (purposeless) ከሆነም ወጪውን የመሸፈን ግዴታ የሚወድቀው የዚህ ዓይነት ወጪ ባደረገው ባለድርሻ ላይ ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1268(2) )
የጋራ ባለሃብቶቹ በጋራ ሃብቱ አማካይነት በሶስተኛ ወገኖች ሂወትና ንብረት ለሚያደርሱት ጉዳት ሃላፊዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ ተራ የጋራ ባለሃብትነት ከውል ወይም ከህግ ሊመነጭ የሚችል የንብረት መብትና ግዴታ ያለበት በሰዎች መካከል የሚፈጠር ግንኙነት ነው፡፡
የጋራ ሃብትን ስለማስተዳደር (Acts of management)
የጋራ ሃብትን ማስተዳደር ማለት በፍ/ብ/ህ/ቁ.1265 ያለውን አባባል ከፍ/ብ/ህ/ቁ.2204 ጋር አስተሳስረን ስንመለከተው የጋራ ሃብቱን ማቀብ (to preserve or maintain) ማለት ነው ብለን ልንተረጉመው እንችላለን:: ይህን ዘርዘር ባለ መልኩ ስናየው ደግሞ የጋራ ሃብትን ማስተዳደር የጋራ ሃብቱን ከሶስት ዓመት ላልበለጠ ግዜ ማከራየት፣ የተገኘውን ገቢ በሌላ ስራ ላይ ማዋል (investing the income) ምርትንና፣ የሚበላሹ ነገሮችን መሸጥን እንዲሁም በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1266 የተዘረዘሩትን የጋራ ባለሃብቶች ሙሉ ድምፅ በማግኘት ሲወሰን የጋራ ሃብቱን መሸጥ (to dispose of) ፣ በዋስትና (mortgage or pledge) በኣላባ (usufruct) መስጠትና የጋራ ሃብቱ የተቋቋመበትን አላማ መለወጥ እንደ አስተዳደራዊ ስራ የሚወሰዱ ናቸው፡፡ እንዲሁም በፍ/ብ/ህ/ቁ.1266 ከተዘረዘሩት ነገሮች ውጭ በፍ/ብ/ህ/ቁ.1265 ስር በሚወድቁ ጉዳዮች ላይ የጋራ ባለሃብቶቹ በድምፅ ብልጫ ውሳኔ ያገኘን ጉዳይ እንዲተገበር ማድረግ እንደ አስተዳደራዊ ስራ (act of management) ሊወሰድ ይችላል፡፡ የጋራ ባለሃብትነቱ መብት መሰረት ውል በሚሆንት ጊዜ ውሉ በፅሑፍ ሆኖ ተዋዋይ ወገኖች ስለሚኖራቸው መብት፤ ግዴታና የንብረቱ አስተዳደር ምን መሆን እንዳለበት መግለፅ ይኖርበታል:: (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1277ን ከ1282 እና 1283) የጋራ ባለሃብትነት የሚመነጨው ከህግ በሚሆንበት ግዜም የጋራ ባለሃብቶቹ መብትና ግዴታ የሚመነጨው ይህን መብት ከሚያስገኘው ወይም ግዴታን ከሚጥለው ህግ ነው፡፡
የማይንቀሳቀስ ንብረት የጋራ ባለሃብቶች ከመጀርያው የጋራ ሃብቱን አስተዳደር መሰረት በማድረግ የሚፈጠሩትን ያለመግባባቶች በድርድር (arbitration) ለመፍታት ሊሰማሙ ይችላሉ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1275 እና 3307-3346) ባለድርሻዎቹ ሳይስማሙ ከቀሩ ፍ/ቤት አስተዳደሪ ሊሾምላቸው ይችላል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1273) ስለሆነም የጋራ ሃብት የማስተዳደር ስልጣን ከውል ወይም ከሕግ ሊመነጭ የሚችል ሆኖ በጋራ ባለሃብቶች መካከል ያለመስማማት ማለትም ሙሉ ድምፅ (unanimous vote) ወይም አብላጫ ድምፅ (majority vote) መሰጠት ባለባቸው ጉዳይ የሚፈለገውን ድምፅ ሳይሰጡ የቀሩ እንደሆነ ጉዳያቸውን በመመስረቻ ውላቸው ባስቀመጡት የችግር አፈታት መንገድ እልባት እንዲያገኝ ይደርጋል፡፡ ይህ በማይሆንበት ጊዜ ደግሞ ፍርድ ቤት በሚሰጠው ውሳኔ እልባት የሚያገኝ ይሆናል ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1265፤1266 እና1277(2) )
የጋራ ባለሃብትነት ቀሪ ስለመሆን
የጋራ ባለሃብትነት መብትና ግዴታ እንደ ሁሉም በህግ ፊት ዋጋ ያለው ተግባር ከውል ሊመነጭና ባለ መብቶቹ ሲሰሩበት ከቆዩ በኃላ ይህ መብትና ግዴታ ቀሪ የሚሆንበት ማለትም ህግ ፊት ዋጋ ሊያጣ የሚችልበት ጊዜ አለ፡፡ መሰረቱ ህግ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ህግ አውጪው ህጉን በሚለውጥበት ጊዜ መብቱ ህጋዊ መሰረት (legal standing) የሚያጣበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በዚህም መሰረት የጋራ ባለሃብትነት ቀሪ የሚሆኑባቸው መንገዶች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹን ውስደን ያየን እንደሆነ፡-
ü የጋራ ባለሃብቱ ድርሻውን ለሌሎቹ ባለድርሻዎች በነፃ ፈቃዱ ሲተው (surrender) (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1262)
ü የጋራ ሃብቱ ክፍፍል ሲደረግበት፡፡ (partition) (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1264)
ü ድርሻየን ትቻለሁ ሲል፡፡ (renunciation) (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1268(3))
ü ተቃራኒ ስምምነት ቢኖርም የሚንቀሳቀስ ንብረት ሲሆንና የጋራ ባለሃብቱ በሚያቀርበው ጥያቄ ንብረቱ በግልፅ ሓራጅ ሲሸጥ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1271)
ü የጋራ ሃብቱ የማይንቀሳቀስ ሆኖ ተቃራኒ ስምምነት ከሌለና ለመከፋፈል የማይቻል ከሆነ ወይም ንብረቱን መሸጥ ተስማሚ አይደለም ተብሎ በፍርድ ቤት ካልተወሰነ በስተቀር የጋራ ሃብቱ ሲሸጥ ወይም ሲከፋፈል የጋራ ባለሃብትነቱ ቀሪ ይሆናል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1272-1274)
ü የጋራ ባለሃብቶቹ በራሳቸው ስምምነት ውላቸው እንዲቀር ሲያደርጉ ወይም ህጉ በሚያዘው መሰረት የጋራ ሃብቱ ክፍፍል ሲጠናቀቅ፡፡ ለምሳሌ የጋራ ሃብቱ የውርስ ሃብት በሚሆንበት ጊዜ በፍ/ብ/ህ/ቁ1079(1) መሰረት የንብረቱ ክፍፍል ሲጠናቀቅ፡፡
ü የጋራ ባለሃብትነት ቀሪ በሚሆንባቸው ሌሎች ሁኔታዎች ቀሪ ሲሆን፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1188-1192)
ü ለጋራ ባለሃብትነት መብት መኖር መሰረት የሆነው የጋራ ንብረት ሲወድም ግንኙነቱ ቀሪ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1304)
ü
ስለዚህ ተራ የጋራ ባለሃብትነት (ordinary joint ownership) ከውል ወይም ከህግ የሚመጣ ንብረትን መሰረቱ በማድረግ የሚፈጠር መብትንና ግዴታን ያዘለ ግንኙነት ነው፡፡ በመሆኑም በህገ-መንግስቱና ከዚያ በታች ባሉ ሌሎች ህጐች ጥበቃ የተደረገለትና በአንድ ወቅት የጋራ ባለሃብቶቹ በመብታቸው ሲሰሩበት ከቆዩ በኃላ ቀሪ የሚሆን ወይም መብቱም ሆነ ግዴታው ተፈፃሚነት ሊያጣ የሚችል የኢኮኖሚ ትስስር ነው፡፡