Non-Contractual Liability (Tort Law)

ይህ ሀላፊነት በእንግሊዝኛው /vicarious liability/ የሚባለው ነው፡፡ የተደነገገውም ከ2124 እስክ 2136 ባሉት ቁጥሮች ስር ነው፡፡ ሀላፊነትን የሚያስከትለው ተግባር የተፈፀመው በአንዱ ሰው ሲሆን ተጠያቂ የሚሆነው ግን ሌላ ሰው ነው፡፡ ሀላፊነት የሚያስከትለውን ተግባር የሚያከናውኑት ሦስት ዓይነት ሰዎች ናቸው፡፡ እነሱም አካለ መጠን ያላደረሰ ልጅ፣ ሠራተኛ እና ደራሲያን /ፀሐፊዎች/ /authors/ ናቸው፡፡ ሠራተኛ የሚለው የመንግስት ሹም ሠራተኛ ወይም  ሌሎች ሠራተኞች ሊመለከት ይችላል፡፡ ለአካለ መጠን ላልደረሱ ልጆች ተፈፃሚነት ያላቸው  ከቁጥር 2124 እና 2125 ሲሆኑ ለሠራተኛ ደግሞ ከቁጥር 2126 እስከ 2134 ያሉት ናቸው ስለደራሲ ደግሞ ቁጥር 2135 ይደነግጋል፡፡ ለአካለመጠን ላልደረሰ ልጅ ሀላፊ የሚሆኑት ወላጆችና ሌሎች ሲሆኑ ለሠራተኛ ደግሞ መንግስት ወይም አሠሪ ይሆናሉ፡፡ ለደራሲ ሀላፊ የሚሆነው አሳታሚው ነው፡፡ በመጨረሻም አንድ ነጥብ ግልፅ እናድርግ፡፡  ሀላፊነት የሚያስከትለውን ተግባር የፈፀሙ ሰዎች አላፊ  ሳይሆኑ ሌሎች ሀላፊ ይሆናሉ ማለት ተግባሩን የፈፀሙት በጭራሽ ተጠያቂ አይሆኑም ማለት አይደለም፡፡ ይህን ያህል ለመግቢያ ካልን ቀጥለን ነጥቦችን ዘርዘር አድርገን ለመመልከት እንሞክር፡፡

 

አካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ቁጥር /2124 /

 

በቅድሚያ አንድ ነጥብ ግለፅ አናድርግ በፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2124 መሠረት አካለመጠን ያልደረሰ ልጅ ሀላፈነትን የሚያስከትል ሥራ የሰራ እንደሆነ በፍትሐብሔር በኩል ለተሠራው ሥራ አላፊ የሚሆነው አባት ነው በማለት ቅድሚያ አባትን ያስቀምጠዋል፡፡ ለዚህ የሚሰጠው ምክንያት አባት የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ግን የኢፌዳሪ ህግ መንግስትንም ሆነ አዲሱን የተሻሻሉ የቤተሰብ ህጐችን የሚፃረር ነው፡፡ ለምሳሌ በኢፌዳሪ ህግ መንግስት አንቀፅ 34 /1/ መሠረት ባል አና ሚስት በጋብቻ ዘመን እኩል መብት ሲኖራቸው በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀፅ 5ዐ  መሠረት በቤተሰብ አመራር ረገድ ባልና ሚስት እኩል መብት አላቸው፡፡ ይህም በመሆኑ ባልና ሚስት ልጆቻቸው በመልካም ስነምግባር እንዲታነፁ ተገቢ ትምህርት እንዲቀስሙና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጐች ሆነው እንዲያድጐ ለማድረግ መጣር  አለባቸው፡፡

 

ስለሆነም አካለመጠን ያልደረሰ ልጅ ሀላፊ በሚሆንበት ጊዜ አባትና እናት እኩል ሀላፊ መሆን አለባቸው እንጂ በመጀመሪያ ደረጃ አባት በሁለተኛ ደረጃ እናት መሆን የለባቸውም፡፡ ስለዚህ ይህ የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር ከኢፌዲሪ ሕገ መንግስትና ከተሻሻሉት የቤተሰብ ሕጐች አንፃር መቃኘት አለበት፡፡

 

ለአካለመጠን ያልደረሰ ልጅ ሀላፊ መሆንን በሚመለከት የኮመን ሎው አገሮችና የሲቪል ሎው አገሮች የተለያዩ አቋም አላቸው፡፡ በኮመን ሎው አገሮች ለአካለመጠን ላልደረሰ ልጅ አባትን ወይም እናትን ሀላፊ ለማድረግ በአባት ወይም በእናት በኩል ጥፋት መኖሩን ማረጋገጥን ይጠይቃል፡፡ በሲቪል ሎው አገሮች ግን አካለመጠን ያልደረሰ ልጅ ድርጊት ጉዳት ካደረሰ በወላጆች ዘንድ ጥፋቱ እንዳለ ይገመታል፡፡ ይህ ግምት ግን በተቃራኒ ማስረጃ ሊፈርስ የሚችል ግምት /ribufuble/ ነው፡፡

 

 

በእኛ ህግ ግን ሁለቱም አቋም ያለ ይመስላል፡፡ በቁጥር 2124 ስር አባት ወይም በ2125 /1/ ስር እናትን ሀላፊ ለማድረግ ጥፋትን ማረጋገጥ አያሰፈልግም፡፡ በቁጥር 2ዐ52 መሠረት ግን ወላጅን ወይም ሌላ አካለመጠን ያልደረሰ ልጅ አሳዳሪነት ወይም ጠባቂነት የተሰጠውን ሰው ሀላፊ ለማድረግ ጥፋትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

 

ሌላው ግልፅ መሆን ያለበት ነጥብ ደግሞ ወላጆች ወይም ሌሎች በቁጥር 2125 የተጠቀሱት ሰዎችና አካላት ሀላፊነት የፍትሐብሔር ሀላፊነት ብቻ ነው፡፡ አካለመጠን ያልደረሰው ልጅ የወንጀል ድርጊት ቢፈፅምና ቢረጋገጥበት ከ9 ዓመት በላይ ከሆነ በወንጀል ድርጊት ተጠያቂነቱ ወደ ሌሎች ሰዎች አይተላለፍም፡፡ በመጨረሻም ቁጥር 2124 አስመልክቶ በፍትሐብሔር ህግ አማርኛውና እንግሊዝኛ መሃል ልዩነት አለ፡፡

 

አማርኛው ልጁ ሀላፊነትን የሚያስከትል ሥራ የሰራ እንደሆነ በማለት የልጁ ሀላፊነት ከሥራ የሚመነጭ መሆኑን ሲደነግግ እንግሊዝኛው ግን /Where his minor child incurs a liability/ ስለሚል የልጁ ሀላፊነት ወይ ልጁ ጥፋተኛ በመሆኑ ሊመነጭ ይችላል ወይም ጥፋት ሳይኖርበት ጉዳት የሚያደርሱ ነገሮች ባለቤት በመሆኑ ሊመነጭ ይችላል፡፡ ሌሎች ለልጁ ሀላፊ ተብለው በህግ ይገለፁ እንጂ ልጁም ከሀላፊነት አያድንም፡፡

 

የመንግስት አላፊነት ቁጥር  /2126/

 

 

በቁጥር 2126 /1/ መሠረት የመንግስት ሹም ወይም ሠራተኛ በራሱ ጥፋት በሌላው ሰው ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ኪሣራውን ለመክፍል ይገደዳል፡፡ ይህ ጥፋት በሁለት አጋጣሚ ሊደረግ ይችላል፡፡ አንድ አጋጣሚ  የመንግስትን ሥራ ሲሠራ ሊሆን ይችላል፡፡ የግል ሥራውን ሲሠራም ሊሆን ይችላል፡፡ የመጀመሪያው ጥፋት የሥራ ጥፋት ሲሆን የተጐዳው ሰው ካሣ ከመንግስት ላይ ለመጠየቅ ይችላል፡፡ ሠራተኛው ያደረገው ጥፋት የግል ጥፋቱ የሆነ እንደሆነ ግን መንግስት ሀላፊነት አይኖርበትም //2126 /2/ እና /3// ፡፡

 

አንድ ጥፋት የሥራ ጥፋት ለመባል ምን ማሟላት እንዳለበት ቁጥር 2127 ስር ተዘርዝሯል፡፡

እነሱም፣

  1. ሥራው በስልጣኑ ልክ መሆን አለበት
  2. ቅን ልቦና መኖር አለበት
  3. ለሥራ ክፍል ይለዋል እንግሊዝኛው ግን /In the interest of the state/ ይለዋል፡፡

 

ከዚህ ውጭ በሆነው በማናቸውም ሌላ ጉዳይ ጥፋት ቢፊፅም ጥፋቱ እንደግል ጥፋት ሆኖ ይቆጠራል፡፡

 

ከላይ ያልናቸው ነጥቦችና ሀሳቦች በሙሉ ለክልል መንግስታት ሠራተኞችና ለህዝብ አገልግሎት በተቋቋሙ በህግ የሰውነት መብት በተሰጣቸው ድርጅቶች ሠራተኞችም ላይ ተፈፃሚ ይሆናሉ /2128/፡፡

 

የሰውነት  መብት  የተሰጣቸው  ድርጅቶች  አላፊነት ቁጥር  /2129/

 

እነዚህ ድርጅቶች  በእንግሊዝኛው  /Bodies corporate / የሚባሉ ናቸው  ምን  እንደሆኑ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 4ዐ4 ጀምሮ እስከ 482  ተደንግጓል፡፡ ቁጥር 457  ስር ለሠራተኞቻቸው  እነዚህ  የሰውነት መብት የተሰጣቸው  ድርጅቶች  ከውል  ውጭ  በሚደርስ አላፊነት እንዴት በአላፊነት ሊጠየቁ እንደሚችሉ  ተደንግጓል፡፡ ቁጥር  2129  እነዚሁኑ ሠራተኞች የማህበሩ  እንደራሲዎች ፣ ወኪሎች ወይም ደሞወዝተኞች  በማለት  ዘርዝሮ ያስቀምጣቸዋል፡፡

ቁጥር 457  እንደ ቁጥር 2129 እነዚህ ሠራተኞች  የተሰጣቸውን ሥራ በሚያከናውኑበት ጊዜ አላፊነት  የሚያስክትል ሥራ  የፈፀሙ  እንደሆነ በፍትሐብሔር የሚጠየቁት እነዚህ ማህበሮች  መሆናቸውን ይደነግጋል፡፡

 

በተመሳሳይ  ቁጥር 213ዐ አንድ ሠራተኛ  ሥራውን የሚሰራበት ጊዜ አላፊነትን የሚያስከትል ጥፋት  የሰራ እንደሆነ በፍትሐብሔር  በአላፊነት የሚጠየቀው አሰሪው  ነው በማለት ደንግጓል፡፡ ሥራውን በሚሠራበት ጊዜ  የሚለውንም ሐረግ 2132 ስር ሕጉ የሕሊና ግምት ወስዷል፡፡ በዚህ ቁጥር መሠረት ሠራተኛው  በሚሰራበት ቦታና  ጊዜ የጥፋት ተግባር የፈፀመ እንደሆነ ጉዳቱን ሥራውን በማከናወን ላይ  ሳለ እንደሰራው ይቆጠራል፡፡

ባለፈው  ክፍል ጥፋት ምን እንደሆነ የጥፋት  ዓይነቶችንና ጥፋት  በምን ላይ  ሊፈፀምና እንዴት  አላፊነትን  ሊያስከትል  እንደሚችል አይተናል፡፡ በዚህ ክፍል  ደግሞ  አንድ ሰው ጥፋት ሳይኖረው   እንዴት  ተጠያቂ  እንደሚሆን  እንመለከታለን፡፡ በእንግሊዝኛው  /Strict liability/ የሚባለው ነው፡፡ ስለጥፋት  ሳይኖር አላፊነትን የሚደነግጉት  ቁጥሮች  ከ2066 እስከ 2089 ያሉት ናቸው፡፡ እነዚህን ቁጥሮች  በንዑስ  ክፍሎች   ስንከፍላቸው፡፡

 

ቁጥር 2066-2070 ድረስ ያሉት አንድ ሰው የሚሰራው ስራ ምክንያት ሆኖ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት በማድረስ ተጠያቂ የሚሆንበት ሁኔታን ሲደነግጉ

 

በቁጥር 2071 -2076 ድርሰ ደግሞ እንሰሳት በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ለሚያደርሱት ጉዳት ባለእንሰሳው ተጠያቂ የሚሆንበትን ሁኔታ ይደነግጋሉ፡፡

 

እንዲሁም ከቁጥር 2077-2080  ድረስ ያሉት ደግሞ የህንፃ ባለቤቶች  በንብረት ወይም በሰው ላይ ለሚደርሱት  ጉዳት ተጠያቂ ስለመሆናቸው ይደነግጋሉ፡፡  መኪናዎች  ከቁጥር  2081-2084  ስር   5 ባለሞተር  ተሽከርካሪ ባለቤቶችና  ሌሎች  እንዴት ተጠያቂ  እንደሚሆኑ ሲደነግጉ  ቁጥር 2085 ስለተሰሩ  ዕቃዎችና  የሚያስከትሉት ተጠያቂነት ይደነግጋል፡፡ ቀጥለን እነዚህን  አፍታተን  አንድ ባንድ እንመለከትለን፡፡

 

ከሥራ ጋር  የተያያዘ አላፊነት

 

አስፈላጊ ሆኔታ /Necessity/  ቁጥር /2066/

 

በራስ  ወይም በሌላ  ሰው ላይ  ወይም  በራስ ንብረት ላይ ወይም  በሌላ  ሰው ንብረት  ላይ በእርግጠኝነት  ሊደርስ  ከሚችል አደጋ ለመከላከል  በሌለ ሰው  ላይ ሆን ብሎ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ጉዳት አደራሹ ተጠያቂ ይሆናል፡፡

 

በአስፈላጊ  ሁኔታ  ስር ሆኖ በሌላ ሰው ላይ  ጉዳት ማድረስ በኢፊዲሪ  የወንጀል ሕግ አንቀፅ 76  መሠረት ተጠያቂ አያደርግም፡፡ ሆኖም  ግን በፍትሐብሔር  ተጠያቂ  ያደርጋል፡፡  ምክንያት ሊሆን የሚችለው  በድርጊቱ ተበዳዩች /Victims/ መኖር  ነው፡፡  ሕግ ይህን  የሚያደርገው   አስፈለጊ  በሆነ  ሁኔታ  ስር ድርጊቱን ፈፅሞ  ጉዳቱን ባደረሰ እና  የተበዳዩ  ጥቅም መሃል  /balance/  ለመጠበቅ ነው፡፡ ሕግ  አድራጊውንና ጉዳት አድራሹን  ድረግትህ ጥፋት አይደለም ይበል እንጂ ካሣ  አትከፍልም አላለም፡፡

 

ሌላው መነሳት  ያለበት ጥያቄ  አንድ ሰው የሌላ ሰውንና  ንብረት በእርግጠኝነት ሊደርስ ከሚችል አደጋ በመከላከልና ጉዳት በማድረሱ እንዴት  ተጠያቂ  ሊሆን  እንደሚችል  ነው፡፡  ምናልባትም  ተበዳዩ  የሚያውቀው ጉዳት  ያደረሰበትን  እንጂ  ሰውነቱ ወይም እና ንብረቱ ከአደጋ የተጠበቀለትን  ሰው  ስላልሆነ  ይሆናል፡፡ ሆኖም  ግን  አደጋው እንዳይደርስ  የተከላከለው ሰው  በቁጥር  2162 ጥቅሙ  ወይም  ሰውነቱ ከአደጋ የጠበቀለትን ሰው መጠየቅ  ይችላሉ፡፡

 

በመጨረሻም  ከቁጥር 2066  ጋር  ቁጥር 2103ትን  አብረን  ማንበብ አለብን  በቁጥር 2066 መሠረት ጉዳት ለደረሰበት ሰው የካሣው  መጠን የሚወሰነው በ2091 መሠረት ሳይሆን  በቁጥር 2103  መሠረት በርትዕ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው በንብረት ላይ ለደረሰ አደጋ ነው፡፡

 

በሰው  አካል ላይ  ጉዳት  ስለማድረስ ቁጥር /2087/

 

ከዚህ ቀደም  ቁጥር  2038ን ስንወያይ  አንድን  ሰው  ያለፍላጉት  ብንነካ ጥፋተኛ  እንደሚያደርገን  ተመልክተናል፡፡ በዚህ  ቁጥር  መሠረት ግን  ጥፋተኛ  ለመባል  በተሰነካው ሰው ጉዳት ማድረሰ ቅደመ ሁኔታ እንዳል  ሆነ  ተልክተናል፡፡  በቁጥር  2067 መሠረት ተጠያቂ ለመሆን  አንድ ሰው  በሥራው  በሌላ ሰው ላይ ጉዳት  ማድረስ ቅደመ ሁኔታ ነው  ለዚህም  ነው ቁጥር  2087 /1/ አንደ ሰው በሠራው  ሥራ  በሌላ  ሰው አካል  ላይ ጉዳት ያደረሰ  እንደሆነ ኃላፊ ነው በማለት የደነገገው ፡፡

 

 

ሆኖም  ግን ጉዳቱ የደረሰው በሚከተሉት ምክንያት ከሆነ  ጉዳት  አድራሹ ተጠያቂ  አይሆንም፡፡

1.ሥራው  በሕግ የተፈቀደ  ወይም  የተያዘ ከሆነ ይህን በምሳሌ  እናስረዳ፡፡ ቁጥር  18 ስር  የሰው አካል የማይደፈር መሆኑ ተደንግጓል፡፡  ይህ ማለት ግን  አንድ  ሰው  በሕክምና ጥበብ  በኩል  ጉዳት የማያደርስበት  መሆኑ ከተረጋገጠ አካሉን አሳልፎ  ለመስጠት ይችላል፡፡ ለምሳሌ  አንድን  ኩላሊት አሳልፎ መስጠት  እንደሚቻል የሕክምና  ጥበብ  ይነግረናል፡፡ ይህን  ለማድረግ ግን  ኩላሊቱን  የሚሰጠው ሰውዩ ሰውነት መቀደድ  አለበት ይህም  ጉዳት  ያደርስበታል፡፡ ይህን ጉዳት  ያደረሰው  ቀዳጅ  ሐኪም  ግን ተጠያቂ  አይሆንም፡፡

2.ጉዳቱ  የደረሰው ራስን  ለመከላከል  ከሆነ ጉዳት አድራሹ አላፊ  አይሆንም፡፡ ለምሳሌ  አንድ  ሰው በጩቤ  ሌላውን ሰው  ለመውጋት ቢንደረደርና ሊወጋ በነበረው ሰው ጥቃት  ቢቆስል  ተከላካዩ   ለደረሰው  ጉዳት አላፊ  አይሆንም፡፡

3.አደጋው የደረሰው በተበዳዩ ጥፋት ምክንያት  ብቻ  ከሆነ  አድራጊው  አላፊ አይሆንም  እዚህ ነጥብ ላይ ግልፅ  መሆን ያለበት ለጉዳቱ ምክንያት የተጉጂው  ጥፋት ብቻ  መሆኑን  መንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የጉዳት አድራሹ  ምንም ዓይነት ሚና መኖር የለበትም፡፡

 

 

አደገኛ ሥራ ቁጥር / 2069/

 

   እዚህ ቁጥር ስር  አራት ዓይነት ሥራዎች ተዘርዝረዋል እነሱም፡፡

የሚፈነዱ ወይም  መርዝ የሚሆኑ ቅመማትን በሥራ  ላይ  መዋል ወይም  ማከማቸት፡፡

ከፍተኛ  ጉልበት  ያለው  የኤሌክትሪክ  መስመር  መዘርጋት፡፡

የመሬትን የተፈጥሮ  መልክ መለወጥ

በተለይ አደገኛ  የሆነ የኢንዱስትሪ ሥራ  ማካሄድ  ናቸው፡፡

 

አንዳንድ  ነጥቦችን  እናንሳ  የመጀመሪያው እነዚህ የተዘረዘሩት የሥራ  ዓይነቶች /Enumerative /  ወይስ  /Exhaustive/ ናቸው፡፡ የሚለው  አከራካሪ ነው፡፡

 

ሁለተኛው  ነጥብ እነዚህ ሥራዎች  ሊከለከሉ  አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ለአገር  ኢኮኖሚ ግንባታ  አስፈላጊ ናቸውና፡፡ ሶስተኛ  በእነዚህ  የሥራ ዓይነቶች  ላይ የተሰማሩትን  ወይም  ባለቤቶችን  ተጠያቂ  ለማድረግ   በመጀመሪያ  ሥራው  በሌላ  ሰው  ላይ አደጋ ያደረሰ መሆኑን  ማሳየት  ያስፈልጋል፡፡ በሌላ አባባል  በሥራውና  በደረሰው ጉዳት  መሃል  የምክንያትና ውጤት  ግንኙነት መኖሩን ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም ጥፋት መኖሩን  ማሳየት   አያስፈልግም፡፡  ይህም  በመሆኑ ቁጠር 2086  ስር እንደተደነገገው እላይ  ባስቀመጥናቸው ሥራዎች  ምክንያት አደጋ  በሚፈጥርበት ወይም  በሚደርስበት ጊዜ  የዚህ ሥራ  ባለቤቶች   አንዳች  ጥፋት  ያለደረጉ  መሆናቸውን  በማስረዳት ወይም የጉዳቱ  ምክንያት ሳይታወቅ በመቅረት ወይም ጉዳቱን  ለመከላከል አንችልም ነበር  ወይም ጉዳቱ  የደረሰው በሌላ ሶስተኛ  ወገን ጥፋት ነው በማለት  ከአላፊነት  ሊያመልጡ አይችሉም፡፡

 

አንድ  ነጥብ  እንጨምርና ወደሚቀጥለው  ቁጥር  እንሻገር  በዚህ ቁጥር  መሠረት የሥራው ባለቤቶች  አላፊ የሚሆኑት ጉዳቱ  የደረሰው  በሰው  ላይ  ሲሆን  ነው፡፡ በእነዚህ  ሥራዎች  ምክንያት በንብረት  ላይ  ጉዳት መድረሱ  ብቻውን  አላፊነትን አያስከትልም አላፊነትን ለማስከተል  በቁጥር  2070  መሠረት ከሚከተሉት አንዱ መሟላት  አለበት፡፡

 

1. በሥራው  ምክንያት   ጉዳት  ደረሰበት የተባለው  የጉረቤት ንብረት ሙሉ           በሙሉ  መውደም  አለበት ወይም

2. በጉረቤት ንብረት ላይ  ጉዳት የደረሰው የሥራው  ባለቤት በሰራው ጥፋት   መሆን አለበት

ስለሆነም  በሥራው  ምክንያት የጉረቤት ንብረት ዋጋ ቢቀንስ  የሥራው ባለቤት አላፊ  አይሆንም፡፡

 

በእጅ  የተያዘ  ነገር  ጉዳት ሲያደርስ

 

ባለፈው  ንዑስ ክፍል  ሰው  በሰራው  ሥራ  ምክንያት ጉዳት ሲያደርስ እንዴት አላፊ  እንደሚሆንና  መከላከያው  ምን  እንደሆነ  ተመልክተና፡፡ በዚህ ስር  አራት  ንዑስ  ክፍሎችን  እንመለከታለን እነሱም፣

1.እንሰሶች  ከ2071-2076

2.ሕንፃ 2077-2080

3.መኪናዎችና ባለሞተር፣ ተሽከርካሪዎች 2081-2084

4.የተሰሩ ዕቃዎች ናቸው፡፡

 

አንድ  ሁለት  ነጥቦችን  እናንሳና እያንዳንዱን  እንመልከት በአራቱም ላይ  ባለቤቶች ኃላፊ ናቸው፡፡  እንደገና  በ1፣2፣እና 3 ስር  ባለይዞታዎችም  አላፊ  ሊሆኑ  ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ  በአንደኛ እና በሶስተኛ  ስር  ተቀጣሪዎችም  አላፊ የሚሆኑበት  ሆኔታ አለ፡፡ በመጨረሻም ሕንፃው በሚያደርሰው  ጉዳት  ሕንፃውን  የሰራው  ኢንጅነር  አላፊ  ሊሆን  ይችላል፡፡

 

እንሰሳው  ላደረሰው ጉዳት  አላፊ  መሆን

 

አንድ እንሰሳ ለሚያደርስው  ጉዳት እንደሁኔታው  አላፊ  የሚሆኑት  የሚከተሉት ናቸው፡፡

 

1.የእንሰሳው  ባለሀብት፣

2.የእንሰሳው  ጠባቂ፣

3.እንሰሳውን  ለመጠበቅ የተቀጠረ ፣

 

የእንሰሳው  ባለሀብት ቀጥር /2071/

 

የእንሰሳው  ባለቤት በሁለት ሁኔታዎች  ስር አላፊ  ሊሆን ይችላል፡፡ የመጀመሪያ  ቁጥር 2071 ስር እንደተደነገገው  እንሰሳው  በርሱ ይዞታ ስር  ሆኖ  ድንገት በማምለጥ ወይም ያደርጋል  ተብሎ  ያልተጠበቀውን   ጉዳት  ሲያደርስ ኃላፊ ይሆናል፡፡ እንዲሁም  አንድ እንሰሳ በተያዥነት  የተረከበው  ሰው ዘንድ ወይም  ለባለሀብቱ  ወይም ለሌላ  ሰው  የሚሰራ ሰው  ይዞታ ስር ባለበት ጊዜ ጉዳት ቢያደርስ  ባለቤቱ ኃላፊ   ይሆናል፡፡ ከአላፊነት የሚያድነው  እንሰሳው  ይዞታው ስር  የነበረ ሰው  ጥፋት በመስራቱ  እንሰሳው ጉዳት  ካደረሰ ብቻ  ነው፡፡

 

 

የእንሰሳው  ጠባቂ ቁጥር /2072/

 

የእንሰሳ ጠባቂ የተባሎትን በሶስት  ከፍለን ማየት  እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው እንሰሳውን  ለግል  ጥቅሙ  የሚያውለው  ሲሆን  ሁለተኛው እንሰሳውን  በኪራይ    የተረከበ  ሲሆን  ሶስተኛው  ደግሞ  እንሰሳውን  ለመጠበቅ  ለመቀለብ ወይም  ደግሞ  በማናቸውም  ሌላ ዓይነት ሁኔታ እንሰሳውን  የተረከበና  በራሱ ጠባቂነት  ውስጥ  ያለ ነው፡፡ በእንዲህ  ያለ  ሁኔታ  እንሰሳው  ጉዳት ቢያደርስ  አላፊ  የሚሆነው  ይኸው  እንሰሳ በእጅ  የሚገኘው  ሰው ነው፡፡

 

ቀጥለን  አላፊነትን  እነዚህ  ሰዎች እንዴት   እንደሚወጡ  እንመለከታለን፡፡ እንሰሳው  ባለሀብቱ ይዞታ ስር  ባለበት ጊዜ  እንሰሳው  ጉዳት ሲያደርስ አላፊነቱን  የሚወጣው እንደ  እንሰሳው  ዓይነት  ይወስናል፡፡ እንሰሳው  የሰው አገልጋይ ከሆነ ቁጥር  2074 /1/ መሠረት  የዚህ እንሰሳ ባለቤት  የሆነው ሰው  እንስሳውን  ጉዳት ለደረሰበት ሰው  በመልቀቅ /ባለቤትነቱን  በማስተላለፍ/ ከአላፊነቱ ለመዳን ይችላል፡፡

 

ይህ  የሚሆነው  እንሰሳው  ጉዳት ያደረሰው  በግል ባለሃብቱ  ወይም በባለቤቱ ሥልጣን    ስር በሚተዳደር ሰው  ጥፋት ካልሆነ  ነው፡፡ በአንዳቸው ጥፋት ከሆነ  ግን  የአላፊነቱ መጠን  የእንሰሳውን ባለቤትነት  በማስተላለፍ ብቻ አይወሰንም፡፡

 

እንዲሁም  እንሰሳው  የቤት እንሰሳ ሳይሆን  የቤት አራዊት  ከሆነ ጠባቂው /holder/ የእንሰሳውን  ዋጋ በመክፈል አለፊነቱን ይወጣል /2075/  ጉዳት የደረሰው በጠባቂው  ጥፋት ከሆነ የእንሰሳውን  ዋጋ በመክፈል  አላፊነቱን  ይወጣል፡፡ ዋጋውም የሚሆነው  በቁጥር  2075 /1/ መሠረት ጉዳት በደረሰበት ጊዜ  የእንሰሳው  ዋጋ ነው፡፡

 

 

ከዚህ  የምንረዳው ቁጥር  2072/1/ እና ቁጥር  2155/1/ አብረን  ስናነብ  የእንሰሳው  ባለቤትና  የጠባቂው  አላፊነት  በአንድነትና በተናጥልም  /several and joint/ ማለት ነው፡፡  ስለሆነም  ቁጥር  2073  ስር  እንደተደነገገው አንድ  እንሰሳ  በሌላ  ሰው  ወይም ንብርት ላይ  ጉዳት  ቢያደርስ የእንሰሳው  ባለሃብት  እንሰሳው  ጉዳት  ያደረሰበትን ተበዳይ  ከካሣ  በኃላ  የእንሰሳው  ጠባቂ  የነበረውን ሰው  ሊጠይቅ  ይችላል፡፡ በመሆኑም  ጉዳት የደረሰበት ሰው  ባለሀብቱን እና  ጠባቂውን  ወይም  ከሁለቱ  አንዱን  መርጦ መክሰስ ይችላል፡፡

 

በመጨረሻ  እንሰሳት  በአዝዕርት  ላይ ወይም በሣር  ላይ ጉዳት  ሊያደርሱ ይችላሉ ፡፡ ይህ  በሚሆንበት ጊዜ  ቁጥር 2076 /1/ መሠረት ጉዳቱ  የደረሰበት ሰው  የእንስሳው  ባለሀብት  ወይም ጠባቂ እስኪክሰው  ድረስ  ጉዳት ያደረሱትን እንሰሳት በመያዥነት  ሊይዝ  ይችላል፡፡ እንዲሁም  ከእንስሳው  ግምት መጠን  በላይ  የሆነውን ጉዳት ለማስቀረት እንስሳውን  መግደል አስፈላጊ ሲሆን እንስሶቹን ለመግደል መብት አለው ለምሳሊ ውሻና  ድመት የመሳሰሉትን ማለት ነው፡፡  ጉዳቱ የደረሰበት ሰው  ጉዳት  ያደረሱትን  ወይም ሊያደርሱ  የነበሩትን  ቢይዝም ቢገድልም ለባለቤቱ  ሳይዘገይ ማሳወቅ አለበት ወይም  ባለቤቱን  ሳያውቅ  ለማግኘት  የሚችልበትን አስፈላጊውን  ማድረግ አለበት፡፡

 

ህንፃ

 

ህንፃዎች  ተደርምሰው ወይም ወድቀው አደጋ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ የመደርመሳቸው  ወይም የመውደቃቸው ምክንያት  ጥገና  ያለማግኘት  ሊሆን ይችላል ወይም  በመሬት መንቀጥቀጥ  ሊሆን  ይችላል፡፡  ተደርምሰው ወይም ወድቀው አደጋ ሲያደርሱ  ባለቤቱ  በቁጥር 2076 /1/ መሠረት አላፊ ይሆናል፡፡ የህንፃው ባለቤት  አላፊ  የሚሆነው  ምንም ጥፋት  ሳይኖርበት  ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ምናልባት  የህንፃው  ባለቤት  ከህንፃው ተጠቃሚ ነው ከሚል  ግምት ሊሆን ይችላል፡፡

 

ህንፃው  በሰው ላይ  ጉዳት ያደረሰው  ከመጀመሪያውኑ ህንፃውን የሰራው  ሰው  ሕንፃውን  በትክክል  ሳይሰራው  ሰለቀረ ይሆናል፡፡ይህ  በሚሆንበት ጊዜ  የህንፃው ባለቤት ለተጉጂው  ካሣ  ከፍሎ  ኢንጅነሩን መልሶ  መጠየቅ ይችላል /2077/2//በተመሳሳይ  ህንፃው ውስጥ የሚኖር  ሰው  ህንፃውን በፍትሐብሔር  ቁጥር ከ2953-2954 መሠረት  ማደስ  ሲገባው  ባለማደሱ ህንፃው  ወድቆ  ሌላ ሰው  ላይ ጉዳት  ቢያደርስ  የህንፃውን  ባለቤት ተጉጂው ከሶ  ህንፃው  ውስጥ  የሚኖርውን ሰው መጠየቅ እንደሚችል ቁጥር  2077/2/ ይደነግጋል፡፡ የጉዳቱ ምንጭ   የሌላ ሰው  ጥፋትም  ሊሆን  ይችላል፡፡ በዚህን   ጊዜም በተመሳሳይ  አጥፊውን  መጠየቅ ይችላል፡፡

 

ባለቤቱ  ጉዳት ያደረሰውን  እንዴት ሊክስ እንደሚችል  ቁጥር  2078  ይነግረናል አንዱ  መንገድ ለተጉዳው ሰው  ህንፃውን  በመልቀቅ ማለት የህንፃውን  ባለቤትነት  በማስተላለፍ  ነው፡፡ አንዳንድ  ጥያቄዎችን እናንሳ  ህንፃው ሙሉ በሙሉ ከወደመስ ይህ ቁጥር እንዴት ይተረጉማል? ጉዳቱ የደረሰበት ሰው  ቁጥር  2053ትን  በመተላለፍ ወደ ህንፃው  የገባ  ከሆነስ?

 

ከላይ የህንፃው ባለቤት ጉዳት ለደረሰበት ሰው ህንፃውን  በማስረከብ አላፊነቱን  እንደሚወጣ  ተመልክተናል፡፡  አላፊነቱ በዚህ ብቻ የሚያበቃው  ለጉዳቱ  ምክንያት የህንፃው ባለቤት ጥፋት ወይም  በእርሱ በሥልጣኑ  ስር የሚያሳድረው  ሰው ጥፋት  ያልሆነ  እንደሆነው  ነው  /2078/2// በሌላ  አባባል  ለጉዳቱ መድረስ  የህንፃው ባለቤት  ጥፋት  ምክንያት ከሆነ የካሣው  መጠን  ከህንፃው  ዋጋ በላይ  ሊሆን  ይችላል ማለት ነው ፡፡

 

የባለህንፃውን  ጥፋት  ለማስረዳት ቁጥር  2079ኝን  እንደምሳሌ  ልንወስድ  እንችላለን በዚህ  ቁጥር  መሠርት ከሌላ ሰው ቤት ምክንያት ጉዳት ይደርስብኛል ብሎ የሚሰጋ ሰው  የዚሁ አስጊ የሆነው  ህንፃ  ባለቤት  ይህ ጉዳት  ከመድረሱ በፊት  አስቀድሞ አስጊውን  ሁኔታ ለማስወገድ የህንፃውን ባለቤት አስፈላጊውን  እርምጃ  እንዲወስድ መጠየቅ ይችላል፡፡ ይህ  ማስጠንቀቂያ ተነግሮት  አስፈላጊውን  እምርጃ  የህንፃው ባለቤት  ሳይወስድ ቢቀርና በዚህም ምክንያት ጉዳት ቢደርስ  የህንፃው  ባለቤት  አላፊ  የሚሆነው  በአጥፊነት ነው፡፡ ይህ በሚሆንበት  ጊዜ  የህንፃው ባለቤት ህንፃውን  ወደ ተጐጂው  ለማስተላለፍ ብቻ አለፊነቱን መወጣት  አይችልም፡፡  አላፊነቱ  ከዚህም  ሊበልጥ ይችላል፡፡ ሕጉ  ይህን  መንገድ የመረጠው የህንፃውን  ባለቤት ለመቅጣትም  ጭምር ነው፡፡

 

በመጨረሻም ቁጥር 2080 መሠረት በአንድ ህንፃ  ውስጥ የሚኖር /occupier/ ከዚህ ህንፃ  እየወደቁ በሌላው ሰው ላይ ጉዳት ለማያደርሱት ተንቀሳቃሽ  ነገሮች  አላፊ ነው፡፡

 

 

መኪናዎችና ባለሞተር ተሽከርካሪዎች  በእንግሊዝኛ /Machines and motor vehicles/ ቁጥር / 2081/

 

መኪናዎች  ወይም  /Machines/ የተባሉት ቋሚ  ወይም  ተንቀሳቃሽ  ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በኢንዱስትሪ  ተተክለው ያሉ  ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ  ጫማ ለመስራት የሚያለግል ማሽን  ሊሆን ይችላል፡፡ መንገድ  ለመጥረግ  የምንጠቀምበት ቡልዶዘርም  ሊሆን  ይችላል፡፡ ውሃ  ከዋና ቦይ  ለመሳብ  የምንጥቀምበት የውሃ  መሳቢያ  ሞተርም ሌላ  ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ ለባለሞተር ተሽከርካሪዎች  /Vehicles/ ምሳሌ  ደግሞ የሰውና የጭነት ማመላለሻ  መኪናዎችን  መውሰድ  እንችላለን፡፡

 

መኪናዎችና  ባለሞተር  ተሽከርካሪዎች  ለሚያደርሱት ጉዳት  ባለቤት አላፊ ሊሆን ይችላል፡፡ ጠባቂ ወይም  ሠራተኛውም  አላፊ  ሊሆን ይችላል፡፡ የመኪናዎችና  የባለሞተር  ተሽከርካሪዎች  ለሚያደርሱት ጉዳት በቁጥር 2081 /1/ መሠረት ባለቤት አላፊ የሚሆነው  አደጋውን ያደረሰው ይህን  መኪና ወይም  ይህን ባለሞተር ተሽከርካሪ  ለማንቀሳቀስ ወይም  ለመንዳት  ያልተፈቀደለት ሰው  እንኳን ቢያሽከረክር  ወይም  ቢነዳም ነው፡፡  ሆኖም አደጋው  በደረሰ ጊዜ  መኪናው  ወይም ተሽከርካሪው  ተስርቆበት ከሆነና ይህንንም ማስረዳት  ከቻለ ባለሀብቱ አላፊ አይሆንም፡፡

 

በሌላ በኩል ደግሞ በቁጥር 2082/1/ መሠረት አንድ ሰው  ባለሞተር ተሽከርካሪውን  ወይም መኪናውን ለግል  ጥቅሙ ሲገለገልበት ወይም ሲጠቀምበት  ተሽከርካሪው  ወይም መኪናው ጉዳት ካደረሰ ለደረሰው ጉዳት  አላፊ ሊሆን የሚችለው  ይህ ሰው ነው፡፡

 

አንድ የመኪና ወይም የሞተር ተሽከርካሪ ባለቤት መኪናውን  ለማንቀሳቀስ ወይም  ለመንዳት ሠራተኛ ሊቀጥር ይችላል፡፡ ይህ  በሚሆንበት ጊዜ ጉዳቱ የደረሰው ግን   በሠራተኛው  ጥፋት ምክንያት ካለሆነ  በቁጥር 2082/2/ መሠረት አላፊ የሚሆነው ባለቤቱ ነው፡፡

 

ስለሆነም በመኪና ወይም በሞተር ተሽከርካሪ  ጉዳት የደረሰበት ሰው  ባለሀብቱን  ተጠቃሚውን  ወይም  ሠራተኛውን  በአንድነት ወይም በተናጥል በቁጥር  2155/1/ መሠረት  ሊከስ ይችላል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ በቁጥር 2083 /1/ መሠረት የመኪናው  ወይም  የባለሞተር  ተሽከርካሪው ባለቤት ለተጐጂው ካሣ ከከፈለ በኃላ  የከፈለውን ከጠባቂው መቀበል ይችላል፡፡ ከጠባቂው  የሚቀበለው የካሣ መጠን በቁጥር 2083/2/ ስር ተደንግጓል፡፡ ባለቤቱ  ጥፋት ካልሰራ ለምሳሌ  በ4ኛ  መንጃ ፍቃድ  የሚሽከረከረውን  ባለሞተር ተሽከርካሪን  3ተኛ  መንጃ ፍታድ  ያለው  ሰው እንዲያሽከረክር ባለቤቱ ቢያዝ ወይም ባለቤቱ ስልጣን  ስር ያለ ሰው ጥፋት ካልሰራ ለምሳሌ  ልጁ ባለቤቱ  ከጠባቂው  የሚቀበለው መጠን  የከፈለውን  ሙሉ ካሣ ነው፡፡

 

የተሽከርካሪዎች ግጭት ቁጥር /2084/

 

ሁለት ተሽከርካሪዎች ሊጋጡ  ይችላሉ፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ  አንዳቸው ጥፋት መስራታቸው  ካልተረጋገጠ በቀር ሁለቱም አሽከርካሪዎች ለጉዳቱ  አኩል አስተዋፅዎ  እንዳደረጉ የቆጠራል፡፡ይህ  በሚሆንበት ጊዜ ቁጥር  2084/2/  እንደደነገገው የእያንዳንዱ ተሽከርካሪ ባለሀብት  ወይም ለአደጋው  አላፊ  የሆነው  ሰው  በአደጋው  ምክንያት  ከደረሰው  ጉዳት ገሚሱን  ይከፍላል፡፡ የጉዳቱ መጠን ብር  1000 ከሆነ አያንዳንዳቸው  ብር 500 ይከፍላሉ  ማለት ነው፡፡

 

ነገር ግን አደጋው  የደረሰው በአንደኛው  መኪና ነጂ ስህተት  መሆኑ  በማስረጃ የተረጋገጠ እንደሆነ  /የትራፊክ  ፖሊስ ኘላን/ ስህተቱን  የሰራው አሽከርካሪ  ለአደጋው  ሙሉ በሙሉ  አላፊ  ይሆናል ወይም  ለአደጋው  ከግማሽ  በላይ  ተጠያቂ ሊሆን ይችላል፡፡

 

የተሰሩ ዕቃዎች ቁጥር /2085/

 

በእንግሊዝኛው /Manufactured goods / የተባሉ ናቸው  ሌላ አገር / Product liability/ የሚባለው ነው፡፡ ተጉጂው  ዕቃዎቹን  በመግዛት  ባለቤት የሆነ ሰው ነው፡፡ /የፍትሐብሔር ቁጥር 1143 እና 1186  በአንድ ላይ ተመለከቱ/ አላፊነቱ ደግሞ  የሚያርፈው  ዕቃዎቹን በሰራው ሰው  ላይ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያት ሊሆን  የሚችለው  የተሰሩ ዕቃዎች ጉደሎዎች / Defective / መሆናቸው  ነው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው  ታዲያ ተጉጂው  ዕቃውን  ከሰሪው እስካልገዛ  ድረስ ነው ይህ ከሆነ  ጉዳያቸው  የሚፈታው በውል  ሕግ መሠረት ነው፡፡

 

ሌላው  መሟላት ያለበት ሰሪው ዕቃውን የሰራው ለትርፍ  መሆን አለበት እንዲሁም ተጉጂው  አስፈላጊውን መደበኛ  ፍተሻ /Necessary customary examination/ ማድረግ አለበት፡፡ የተሰሩ ዕቃዎች  ምን እንደሆኑም መለየት አለብን፡፡ ለምሳሌ  እንጀራ  የተሰራ ዕቃ ነው፣ ጤፍ ግን  አለደለም ስለሆነም እንጀራን ለመሰራት የተወሰነ ሂደት / process /  እንደሚያስፈልግ ሌላም  ውጤት  የተሰራ  ዕቃ  ነው ለማለት በተወሰነ ሂደት  ውስጥ ማለፍ አለበት፡፡

 

አንዳንድ ነጥቦችን  እናንሳና  ወደ ሚቀጥለው  ቁጥር እንለፍ፡፡ አንድ ዕቃ ሰሪ የተመረዘ  ወይም  የተበከለ ዕቃ ሽጦ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ቢደርስ ዕቃ ሰሪው ተጠያቂ  የሚሆነው በጥፋተኝነት / Fault/ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዕቃው ላይ ያለው  ጉድለት በተራ ፍተሻ / Customary Examination / ሊገኝ  የሚችል  ሆኖ ሳለና ተጉጂው  ይህን ሳያደርግ  ቀርቶ ጉዳት ቢደርስበት  ዕቃ  ሰሪው ተጠያቂ  አይሆንም፡፡ እንደሁም  ተጉጂው  ዕቃው  የተሰራለትን ዓላማ  በመለወጥ / Change the  purpose/ ተጠቅሞ  ጉዳት ቢደርስበት ዕቃ  አምራቹ  ተጠያቂ አይሆንም  ለምሳሌ  ለፊት ቅባትነት የተሰራውን በምግብነት ብጠቀም  እንደማለት ነው፡፡

 

 

መከላከያ እና ሌሎች ነገሮች ቁጥር  2086 እና  2087

 

እስካሁን ድረስ የእንስሳ፣ የህንፃ፣ የባለ ተሽከርካሪ እና ባለመኪና ባለቤቶች እንዲሁም ዕቃ አምራቶች እንዴት አላፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተመልክተናል፡፡ እነዚህ ሰዎች ከአላፊነት ሊድኑ የሚችሉት ጉዳቱ የደረሰው በቁጥር 2086/2/ መሠረት በከፊልም ሆነ በሙሉ ከተበደዩ ጥፋት መሆኑን ሲረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ቁጥር 2086/1/ ስረ እንደተደነገገው አንደኛ ጥፋት አልሰራንም ፣ ወይም የጉዳቱ ምክንያት  አይታወቅም ወይም ጉዳቱን ለመከላከል  አይቻልም ነበር ወይም ጉዳቱ የደረሰው በሌላ ሶስተኛ ወገን ጥፋት ነው በማለት ከአላፊነት ሊያመልጡ አይችሉም፡፡

   

ሆኖም  ቁጥር 2087  ስር እንደተደነገገው ከእንስሳት፣ከህንፃ ፣ ከሞተር እና  ዕቃዎች አምራቶች ባለቤቶች  ሳይሆን የሌሎች ዕቃዎች ባለቤት የሆኑ   ሰዎችን  አላፊ  ለማድረግ ባለቤቶቹ  ወይም  በእነሱ ሥልጣን ስር  ያሉ  ሰዎች  ጥፋት መስራታቸውን ማረጋገጥ  ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ አንድ  ዛፍ  ተቆርጦም  ይሆን በሌላ  ምክንያት ወድቆ በአንዲት መኪና  ላይ ጉዳት ቢያደርስ የዛፍን ባለቤት  ወይም ዛፍ  ቆራጩን አላፊ  ለማድረግ  ባለቤቱ ወይም ዛፍ ቆራጩ  ጥፋት የሰራ መሆኑን ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡    እንዲሁም  ከእንሰሳ  ከህንፃ ፣ ከሞተር እና ከአደገኛ ኢንዱስትሪ  ባለቤቶች  እንዲሁም  ከዕቃ አምራቶች  ዘንድ ተቀጥሮ የሚሰራ ሰው  በእነዚህ ውስጥ ሲሰራ ጉዳት ቢደርስበት ከውል ውጪ  ያሉ  ደንቦችን  ጠቅሶ መከራከር  አይችልም 2088/1/ እንዲህ በሆነ ጊዜ ጉዳቱ የሚያደርስው ነገር የሚመራው  በተደረገው የውል  ደንብ መሠረት መሆኑን ቁጥር /2088/2// ይደነግጋል፡፡ 

 

በመጨረሻምአንድ ሰው በህንፃው፣ በእንስሳው፣ ወይም በሌላ ነገር ሲጠቀም ጉዳት ሊደርስበት ይችላል፡፡ በዚህን ጊዜ ተጐጂው ከውል ውጪ ሀላፊነት ደንቦችን በመጥቀስ መከራከር የሚችለው የእነዚህ ነገሮች ባለቤት በዚህ ግንኙነት አንዳች ጥቅም ካገኘም ወይም ባለሀብቱ ወይም ጠባቂው ጥፋት ከሠሩ ብቻ ነው፡፡

ውል  ከማድረግ  በፊት  የተደረገ ድርድር ቁጥር 2055

 

አንድ  ተዋዋይ  ውል  ገብቶ  በውሉ መሠረት ግደታውን  ሳይወጣ  ከቀረ በውሉ መሠረትና በውል ድንጋጌዎች  መሠረት  አላፊ  ይሆናል፡፡ ሆኖም  ግን  ውል ከመግባቱ በፊት አንደ ሰው  ሌላኛውን ወገን  ውል እንዲገባ ሊያግባባውና ውሉንና ከውሉ የሚያገኘውን  በማሰብ  ለወጪ  ሊዳርገው ይችላል፡፡ ይህን  ወጪ  ከወጣ  በኃላ  ግን አግባቢው ውል  ውስጥ  ላይገባ ይችላል፡፡ በዚህ  ጊዜ  አግባቢው  በቁጥር 2055 መሠረት ጥፋተኛ ይሆናል፡፡

 

በውል የገባውን  የግዴታ ቃል ስላለማክበር ቁጥር /2056/

 

የዚህ ርዕስ  ቁጥር ትክክል  አይመለስንም ምክንያቱም አንድ  ሰው  በውል የገባውን የግዴታ  ቃል  ያለማክበሩ  ጉዳይ  የሚዳኘው ከውል ውጨ  ሕግ አላፊነት ሳይሆን  የሚዳኘው  ቁጥር 2047/2/ ስር  እንደተመለከተው በውል አለመፈፀም  ድንጋጌዎች መሠረት ነው፡፡

 

ሁለተኛ  ደግሞ  ቀጥለን እንደምንመለከተው ሁለት ሌሎች  ተዋዋዩች  የመሠረቱትን ውል  ነው እንዳይተገበር  መሰናክል የሚሆነው ፡፡ ስለዚህ ርዕሱ  መሆን  ያለበት በተዋዋይ  ወገኖች  መሃል ጣልቃ  መግባት ነው፡፡

 

በቁጥር  2056 /1/ መሠረት  ሁለት ቀድሞ ውል የተዋዋሉ  ይኖራሉ፡፡ ሌላ  ሶስተኛ ወገን  ደግሞ ይህ ሁለቱ  ተዋዋይ  ወገኖች  የገቡት ውል  እንዳይተገበር  ከአንደኛው ተዋዋይ ጋር  ሌላ  ውል  ያደርጋል ፡፡ ሁለት ነጥቦች  ግልፅ  መሆን  አለባቸው፡፡ መጀመሪያ ሶስተኛው  ወገን  በሁለቱ ሰዎች  መሃል  ውል  መኖሩን  ማወቅ አለበት፡፡  የዚህ እውቀት  ከሌለው በዚህ ቁጥር  መሠረት ተጠያቂ አይሆንም  ሁለተኛ ነገር  ሶስተኛው  ወገን  በዚህ  ድርጊቱ ቀድሞ  በሁለት  ወገኖች  መሃል  የተደረገ ውል  እንዳይተገበር  ማድረግ  አለበት፡፡  እነዚህ  ሁለቱ ሁኔታዎች  ካሉ ነው ጥፋተኛ  የሚባለው፡፡  ውል  እንዳይተገበር  ሆኗል በዚህም  ጉዳት ደርሶብኛል የሚል  ወገን  ይህን እንዳይሆን  አስፈላጊውን  ጥንቃቄ  ማድረግ አለበት ይህን  አስፈላጊውን ጥንቃቄ  በቸልተኝነት  ሳያደርግ ከቀረ  በቁጥር 2056 /2/ መሠረት  የኃለኛው   ተዋዋይ ጥፋተኛ  አይሆንም፡፡

 

የማይገባ ውድድር  ቁጥር /2057/

 

የማይገባ  ውድድርን  ለማወቅ ጤናማ  ውድድርን  /fair competition/ ብናውቅ  አይከፋም፡፡ ጤናማ ውድድር  ሁለት ወይም  ከሁለት  የሚበልጥ  በተመሳሳይ  ሥራ  የተሰማሩ  ወገኖች  /ነጋዴዎች/ ለደንበኖቻቸው   የተሻለ አገልግሎት ወይም  ሸቀጥ /Services or goods / ለመስጠት ወይም ለመሸጥ የሚደረግ ውድድር ማለት ነው፡፡  ይህም በሚከተለው  መንገድ  ይገለፃል፡፡

 

  • የሸቀጦችን ዋጋ  በመቀነስ
  • ደረጃውን  የጠበቀ  ሸቀጥ  በማምረት
  • ደንበኛን  ሊያረካ  የሚችል  ግልጋሎት

 

በመስጠት እና  በሌሎችም፡፡   ሆኖም  ግን  ስለሌላኛው  ተወዳዳሪ ነጋዴ  ትክክለኛ  ያልሆነ  መረጃ  ማሳተም፣እንዲሁም  ሀሰተኛ ወሬ መንዛት፣ የሌላኛውን  ተወዳዳሪ የንግድ  ምልክት ወይም  አርማ /Trade name or trade mark/ ወይም  ተመሳሳይ  መያዥ  /container/ መጠቀም  የማይገባ ወይም  ጤናማ  ያለሆነ ውድድር  ስለሆነ ይህን  አደርጊ  በቁጥር  2057 መሠርት ጥፋተኛ  ይሆናል፡፡ ይህ በሚሆንበት  ጊዚ  ፍ/ቤት  ለተጉጂው  ካሣ  እንዲከፈል ከማዘዙም  በተጨማሪ  በቁጥር 2122 መሠረት ድርጊቱ  እንዲቆም ትዕዛዝ  ይሰጣል፡፡

 

የሌላውን  አስመስሎ ማስራት ቁጥር /2058/

 

በእግሊዝኛው /simulation/ የሚባለው ነው፡፡ በአጭሩ ማስመሰል በዚህም ሌላውን  ለጉዳት መዳረግ ነው፡፡ በከተማው  አባባል ቁጭ ይበሉ የሚባለው  ነው፡፡  ይህን በምሳሌ  እናስረዳ፡፡

 

አዲስ አበባ  ከተማ ቦሌ  መሄጃ መንገድ  ላይ የኢትዩጵያ  አየር መንገድ  አይሮኘላንን  በሚመስል መልክ  የተሰራ ካፍቴሪያ  ይገኛል፡፡  ስሙም ለንደን ካፌ  ይባላል፡፡ አንድ  ቀን  አንድ የከተማ  ጮሌ  ወደ ሐጂ  ለመጓዝ  የሚፈልጉ  የገጠር ሰዎችን  አገኘ እንበል ጉዳያቸውን ከጠየቃቸው  በኃላ ወደ ሐጂ  መጓዝ  እንደሚፈልጉ ገለፁለት  እንበል፡፡ ይህ  የከተማ ጮሌ ሰዎቹን  ወደ ተባለው  የአይሮኘላን  ምስል ወስዶ  ካፍቴሪያው ውሰጥ  ካስገባቸው በኃላ  ብሩን  አምጡ እኔ ከፍዬ  እስክመጣ  ድረስ አይሮኘላኑ ሞተሩን  ያግላል አሁንም እንደሚታዩት  እየጋለ ነው በማለት  የሻይና  ቡና መስሪያ ማሸኑ ሲሰራ  ያሳያቸዋል  እንበል፡፡  የገጠሩ ሰዎችም አመነውት ብራቸውን  ይሰጡታል፣ ጮሌውም “መጣሁ” ጠብቁኝ በማለት እዛው  ጥሏቸው  ሄደ እንበል፡፡ ቢጠብቁት አይመለስም፣ አስተናጋጅ  ትመጣና ምን ልታዘዝ ትላለች፡፡ ወደ ሐጂ  ለመብረር እዚህ  “አይሮኘላን” ውስጥ  አንደገቡ  ቲኬታቸውንም እየተጠባበቁ  መሆናቸውን ይነግሯታል፡፡ አስተናጋ²ም እውነተኛውን  ትነግራቸዋለች፡፡  ማስመሰል  በዚህም ሌላውን  መጉዳት ይህ ነው፡፡

 

ያልተስተካከለ  ወሬ ቁጥር  /2059

 

በዚህ  ቁጥር መሠረት አንድ  ሰው  ያልተስተካከለ  ወሬ /መረጃ/ በማሰተላለፍ ተጠያቂ አይሆንም፡፡ ተጠያቂ  ለመሆን  ሁለት  ነገሮችን  ማሟላት አለበት፡፡ የመጀመሪያ ሆን ተብሎ ወይም በቸልተኝነት  የተላለፈውን  መረጃ / information  /  የተቀበለው  ሰው ወይም  ሌላ ሰው  በመረጃው  መሠርት እንደሚተገብርና  /act/   ሁለተኛ  ደግሞ  በመረጃው  መሠረት /act/ ያደረገው ሰው  ላይ  ጉዳት እንደሚደርስበት ማወቅ አለበት፡፡ ለምሳሌ  ሰዎች  በአንድ አዳራሽ  ውስጥ ፊልም ወይም  ትያትር  እየተመለከቱ  እያለ  አንድ ተመልካች  እሳት  ሳይነሳ  ወይም ሳይኖር እሳት! እሳት!  እያለ  ቢጮህና  ይህንንም  በማድረጉ  ሰዎች  ትርምስመሳቸው እንደሚወጣና  አንዱ  በአንዱ  ላይ  ጉዳት እንደሚያደርስ እያወቀ  ይህን ያደረገ  እንደሆነ በቁጥር  2059/1/ መሠረት ጥፋተኛ  ይህናል፡፡

 

ይህ  ንዑስ  ቁጥር  ለተራ ሰው  ነው፡፡  ባለሞያ ከሆነ ግን  ከሞያው  ጋር በተያያዘ መስጠት  የሚገባው  መረጃ ትክክለኛ መሆን አለበት፡፡ በሰጠው መረጃ  ሰዎች  /act/ ማድረግና  ጉዳት ሊደርስባቸው  አይጠበቅም፡፡  ሞያው  ጋር በተያያዘ  አንድ ባለሞያ  ትክክለኛ  መረጃ አለመስጠት ብቻውን ጥፋተኛ  ያደርገዋል 2059/2/

 

 

ሆኖም  ግን አንድ  ሰው መልሶ ገንዘብ  መክፈል ስለሚችል  ገንዘብ እንደሰጠው ለማድረግ ሥራ ለማስገኘት  ስለችሎታው  መናገር  የንግድ ዕቃ  እንዲሰጠው  ስለዚህ ሰው  ችሎታ ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ  መስጠት  በፅሑፍ  ተደርጐ  ተፈርሞ  ካልተሰጠ በሰተቀር በቁጥር   2060  መሠረት  ተጠያቂ አይደለም፡፡ ይህን  አንድ ምሳሌ  በመውሰድ  ለማስረዳት  እንሞክር  የአንድ  ሰው  ዘመድ  የሆነችን  አንዲት ልጅ በቤት ሠራተኝነት  ለማስቀጠር  የተለያዩ  ምግቦችን የመስራት  ችሎታ አላት  በማለት ሥራ ቢያስገኝላት  ይህ ሰው ይህን  ትክክለኛ  ያልሆነ  መረጃ  የሰጠው  ለልጅቷ ሥራ ለማስገኘት  ብቻ ከሆነ ጥፋተኛ  አይባልም፡፡  ግን እነዚህን ትክክለኛ መርጃዎች  የሰጠ ሰው ቃሉን  በፅሑፍ አድርጐ  ፊርማውን ካኖረ  በቁጥር 2060/2/ መሠረት ተጠያቂ ይሆናል፡፡

ምስክሮች ቁጥር /2061/

ምስክሮች  አንድ  ነገር  መፈፀሙን  ወይም አለመፈፀሙን  /occurrence or non occurrence/ ወይም  አንድ  አድራጉት  መኖሩን  ወይም  አለመኖሩን  /the  existence or the non existence/ ሊመሰክሩ  ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ  የጋብቻ ስርዓት  መፈፀሙን  ወይም  አለመፈፀሙን ወይም ጋብቻ  መኖሩን  ወይም  አለመኖሩን  ሊመሰክሩ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ይህ የሰጡት  የምስክርነት ቃል  እርግጠኛ  /accuracy/ ስለመሆኑ አለፊዎች  ናቸው፡፡

 

ሰዎች  ይህን  በምስክሮች  የተሰጠውን  ቃል በመንተራስ  አንድ ነገር  ሊፈፅሙ  ይችላሉ፡፡ለምሳሌ  አንዲት ሴት ባለትዳር  ከሆነ ሰው ጋር  ምስክሮች   ትዳር የለውም  በማለታቸው  ትዳር ልትመሰርት ትችላለች፡፡  በዚህ አድራጉታቸው ለሴትየዋ  ኃላፊ  ይሆናሉ  በሌላ በኩል ደግሞ  እነዚሁ  ሰዎች  ይህን  የምስክርንት  ቃል የሰጡት  በቅን  ልቦና ከሆነና በሌላ ሰው  ተሳስተው  መሆኑን ካረጋገጡ  በዛ  ባሳሳቻቸው ሰው  ላይ  ክስ መመስረት ይችላሉ ፡፡ 2061/3/፡፡

 

ምክር ወይም  የአደራ ቃል /advice or  recommendation/ ቁጥር /2062/

 

አንድ ሰው  ለሌላ  ሰው አንድ  ነገር  እንዲያከናውን  ወይም እንዳያከናውን  ምክር ሊሰጠው  ይችላል፡፡ ለምሳሌ ጠንቋይ  ዘንድ  ቢሂድ  ከበሽታው  እንደሚድን ሊመክረው ይችላል፡፡ መካሪው  በዚህ  ብቻ  ከተወሰነ በቁጥር 2062  መሠረት  ጥፋተኛ አይደለም ሆኖም  ግን  ከዚህ ምክር አልፎ  ጠንቋዩ ዘንድ  ይዞት ብሄድና በዚህ  ምክንያት ምክር ተቀባዩ   ጉዳት ቢደርስበት መካሪውና መሪው  ጥፋተኛ ይሆናል፡፡

 

 

ስለ መያዝ /Distraint/ ቁጥር 2063

 

አንድ  ባለዕዳ  ዕዳውን  በጊዜ  ላይከፍል ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ   አበዳሪው  ባለዕዳው  ዕዳውን  እንዲከፍል ለማስገደድ  የባለዕደውን  ንብረት ሊይዝ  ይችላል፡፡ ለምሳሌ  የአንድ ሰው  ከብት ወደ ሌላ ሰው  ማሳ  ገብቶ አዝዕርቱን  ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ ይህ  በሚሆንበት ጊዜ   ባለእርሻው  ባለከብቱ ከብቶቹ ያደረሱትን ጉዳት እንዲከፍለው ለማድረግ  ከብቶችን  ሊይዝ ይችላል ይህ  ጥፋት አይደለም፡፡

 

ይህ  መያዝ ጥፋት  የሚሆነው  ባለዕዳው  ሊቀበል ከሚገባው  ገንዘብ ጋር  የተያዘው ንብረት   ከዕዳው  ሲበልጥ ነው በተጨማሪም  መያዙ  አስፈላጊ  ሳይሆን ሲቀር  ለምሳሌ  ከብቶቹ  ላጠÕት  ባለከብቱ  እንደሚከፍል  ዋስ  ቢጠራ መያዙ ያለአስፈላጊ  ይሆናል  ማለት  ነው፡፡ ይህ  በሚሆንበት  ጊዜ ያዡ ጥፋተኛ  ይሆናል፡፡

 

የፍርድ  ትዕዛዝ ስለመፈፀም ቁጥር /2064/

 

ሆኖም  ንብረት  በፍርድ  አስፈፃሚ  ሊያዝ  ይችላል፡፡ የተያዘው ንብረት ከዕዳው  ሊበልጥ ይችላል፡፡  ሆኖም  የፍርድ  አስፈፃሚው ጥፋተኛ  አይሆንም  ነገር ግን የሚከተሉት መሟላታቸውን እርግጠኛ  መሆን አለብን፡፡

 

የፍርድ  አስፈፃሚው  ንብረቱን የያዘው  የፍርድ ቤት ትዕዛዝ  ለማስፈፀም መሆን አለበት፡፡ በሌላ አካል የሚሰጥ ትዕዛዝ ለማስፈፀም  መሆን የለበትም ማለት ነው፡፡

 

ትዕዛዙ ትክክለኛ አሰራሩን  የያዘ ፎርም መሆን አለበት፡፡ ትዕዛዙ ትክክለኛ  ነው ለማለት ትዕዛዙ  የዳኛ ፊርማና  የፍርድ  ቤቱ  ማህተም  ሊኖረው  ይገባል ትዕዛዙ  በፅሑፍ  መሆን  አለበት፡፡

 

ስለሆነም ትዕዛዙ የዳኛውን ፊርማ  ያልያዘ ከሆነ  ወይም  የፍርድ  ቤቱን ትዕዛዝ ያልያዘ  ሆኖ  እያለ ንብረቱን ከያዘ  ፍርድ አስፈፃሚው ጥፋተኛ  ይህናል 2064/2/ በተጨማሪ  ፍርድ አስፈፃሚው  ከተሰጠው ትዕዛዝ  ውጭ  ከሆነ ለምሳሌ  በትዕዛዙ  ላይ  የተባለውን  ንብረት ሳይሆን  ሌላ ንብረት ከያዘ  ወይም  ተጨማሪ ንብረት ከያዘ  ወይም ትዕዛዙን  ሕግን ባለማክበር  የፊፀመ እንደሆነ ለምሳሌ  በፍትሐብሔር  ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት  ሊያዙ የማይችሎትን   ንብረቶች  ከያዘ ጥፋተኛ ይሆናል፡፡ 2064/2/

 

ስለ ይርጋ  ቁጥር /2065/

 

አንድ ሰው  በአንድ ጉዳይ ላይ  ክስ  ለመመስረት  የሚችለው  የይርጋ ጊዜው  ሳያልፍበት  ነው፡፡ ለምሳሌ  በውል የይርጋ ጊዜው  10 ዓመት  ነው፡፡ ስለሆነም  ባለገንዘቡ   በባለዕዳው  ላይ በ10 ዓመት ጊዜ  ውስጥ  ክስ መመስረት  አለበት፡፡  ይህን  ከላደረገ ክሱ  በይርጋ  ይታገድበታል፡፡ በሌላ በኩል  ባለዕዳው ዕዳውን  ባለመክፈሉ በቁጥር 2030  መሠረት ጥፋተኛ  ነው፡፡  ይህ ቁጥር  ተጠቀሱ  ክስ  ቢመሠረትበት ባለዕዳው  ቁጥር 2065ን  በመጥቀስ በይርጋ  ደንብ መክሰሰ ቀርቶልኛል  ብሎ  ቢከራከር ጥፋተኛ አይሆንም፡፡

የኢፊድሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 40 ስር   የግል ንብረት  ምን ማለት እንደሆነ ዘርዝሮ  ማንኛውም የኢትዩጵያ  ዜጋ  የግል  ንብረት  ባለቤት መሆኑ /መሆኗ እንደተከበረ  የሕግ  ጥበቃም  እንዳለው ደንግጓል፡፡ ይህ መብት  የመሸጥ፣  የመለወጥ፣ የማውረስ፣ ባለቤትነት የማዘወር  ወይም  የካሣ  ክፍያ  የመጠየቅ መብትን  ይጨምራል እንዲሁም  መሬት  የማይሸጥ  የማይለወጥ ቢሆንም በይዞታ  የመያዝና  የመጠቀም  መብት መኖሩን  በዚሁ  አንቀፅ ስር  ተደንግጓል፡፡

 

ስለሆነም በፍትሐብሔር  ሕግ ቁጥር 2053  መሠረት  አንድ ሰው  በሕግ ሳይፈቀድለትና የቤቱ ባለቤት ወይም ባለይዞታ እንዲሁም የመሬቱ ባለይዞታ ሳይፈቅድለትና  ያለመፍቀዱንም  በግልፅ  እየተናገረ  እላይ በተጠቀሰው  የቤት ሀብት  ወይም የመሬት ይዞታ ከገባ የገባው ሰው ጥፋተኛ ነው፡፡

 

አንድ ሁለት ነጥቦችን እናንሳ የመጀመሪያው በሕግ ሳይፈቀድለት እንግሊዝኛው /without due legal authority/ የሚለው  ነው፡፡

 

ለምሳሌ  አንድ  ፖሊስ  ከፍርድ ቤት የመበርበሪያ  ትዕዛዝ ይዞ  ቢመጣና  ለመበርበር ቤቱ  ውስጥ  ቢገባ አግባቡ በሕግ  ሳይፈቅድለት  አይባልም ፡፡  እንዲሁም አንድ ሰው  የወንጀል  ድርጊት ፈፀሞ ወደ  አንድ  ቤት ወይም  መሬት ቢገባና  ሌላ  ሰው ወይም  ፖሊስ  ተከትሎት  እዛ ቤት ወይም መሬት ቢገባ  አግባቡ በሕግ ሳይፈቅድለት ነው አይባልም፡፡  በዚህ ሁኔታ  ወደ ቤት ወይም መሬት የገባ ሰው  የባለቤቱ  ወይም  የበላይዞታው  ፍቃድ  ባይኖር እንኳን ጥፋተኛ  አይባልም፡፡

 

ሁለተኛው  ነጥብ  የማይፈቀድ  መሆኑን በግልፅ እየተናገረ የሚለው  ነው፡፡  ይህ ተቃውሞ  በቃል  ወይም በፅሑፍ  ሊሆን ይችላል፡፡ በማጠረስ ሊሆን  ይችላል? በሌላ  በኩል  ደግሞ  ወደ  መሬት ወይም ቤት  መግባቱ   የግድ በገቢው በራሱ መፈፀም  አለበት?  በቤት  እንሰሳ  አማካኝነት  ቢሆንስ?ግዑዝ  በሆነ  ነገርስ  ሊሆን ይችላል ?  ለምሳሌ እኔ ቤት የበቀለ ዛፍ ቅርንጫፍ  ወደ ጉረቤቴ  ቢያልፍስ?  ቆሻሻ  ወደ ሌላ  ሰው ቤት  ቢጣልስ? ዛሬ  ቴክኖሎጂው     በሪሞት  ኮንትሮል  በሚንቀሳቀስ  አንስተኛ  አሸንጉሊት  መኪና ወደ ሌላ  ሰው ቤት ወይም መሬት ቢገባስ? ሰልጣኖች  እስቲ  በእነዚህ  ጥያቄዎች  ላይ ተወያዩባቸው፡፡

 

ንብረት  ስለመደፈር ቁጥር /2054/

 

እላይ  የተመለከትነው  የማይንቀሰቀስ ንብረት  ነው በዚህ  ክፍል  ደግሞ  የምንቀሳቀስ  ንብረትን  አስመልክቶ ሕጉ  ምን  እንደሚል እንመለከታለን፡፡  እንደህ ዓይነት  ንብረትንም  አስመልክቶ  ቁጥር  2054  በሕግ  ሰይፈቀድለት የሚለውን ሐረግ  ይጠቀማል፡፡ ስለሆነም  ከላይ ለማስቀመጥ አንደሞከርነው አንድ  ፖሊስ  አንድን የሚንቀሳቀስ ንብረት በእግዚቢትነት  ለመያዝ  የፍርድ  ቤት  ትዕዛዝ ይዞ  ቢመጣና  ንብረቱን  ቢወስድ  ሕገ  ሳይፈቅድለት  ወሰደ  አያስኘውም፡፡ የግል ንብረቱ ወይም የባለይዞታው  ፍቃድ  እንኳን  ሳይኖር ቢወሰድ ጥፋተኛ  አያስብለውም፡፡

 

ሌላው ነጥብ አለመፍቀዱንም በመግለፅ ሲናገር የሚለውን በሌላ የፍትሐብሔር ቁጥር  ለማስረዳት ቁጥር  1148/2/ መሠረት አንድ ሰው እጅ ያደረገው ነገር በንጥቂያ  ከተወሰደበት  የተወሰደበትን ነገር መመለስ እንደሚችል  ይደነግጋል፡፡ ስለዚህ   እንዳይነጥቅ  የሚያደርገው ትግል  ነገሩ  እንዳይወሰድበት  አለመፍቀዱን  መግለጫ ነው  ስለሆነም  አንድ ሰው  የሌላን  ሰው  ተንቀሳቃሽ  ንብረት ሕግም  ሳይፈቅድለት ወይም  ባለቤቱ  ወይም  ባለይዞታው ሳይፈቅደለት  የወሰደ እንደሆነ  በቁጥር  2050 መሠረት ጥፋተኛ ነው፡፡

ይህ  ድርጊት በፍትሐብሔርም በወንጀል ሕግም ጥፋት ነው የወንጀል ሕግ ቁጥር 613ን  ተመልከቱ እነዚህ ቁጥሮች  በኘሬስና  ሀሳብን  በነፃ  የመግለፅ  ሕገ  መንግስታዊ መብት ላይ  የተደረጉ  ገደቦች ናቸው፡፡  በተመሳሳይ  ሁኔታ የኢፊዲሪ  ሕገ  መንግስት  አንቀፅ  39 /3/ ስር  የኘሬስና የሌሎች  መገናኛ  ብዙሃን  እንዲሁም የሥነ ጥበብ ፈጠራ ነፃነት መረጋገጡን  ደንግጉ  አንቀፅ  29/6/ ስር  የሰውን ክብርና  መለካም  ስም  ለመጠበቅ  ሲባል  ሕጋዊ ገደቦች  በእነዚህ  መብቶች  ላይ ሊደነገጉ ይችላሉ ይላል፡፡ ስለሆነም በዚህ ገደብ  አማካኝነት  ጥበቃ  የተደረገላቸው  መልካም ስምና ክብር ናቸው፡፡

 

ይህን  ያህል ለመግቢያ ካልን  አንዳንድ ነጥቦችን  አንስተን  እንወያይ  የስም  ማጥፋት  ድርጊት የሚፈፀምበት ሰው በሕይወት ያለ መሆን አለበት ይህም የሰም ማጥፋት  የሚደረገው  ስሙ የጠፋው ሰው  እንዲጠላ ወይም   እንዲዋረድ  ወይም  እንዲሳቅበትና  ብሎም  ስሙ  በጠፋው  ሰው ላይ  ሌላው እምነት  እንዳይኖረው  ለማድረግ  ወይም  መልካም  ዝናው  ወይም  የወደፊት  ዕድሉ እንዲበላሽ  ለማድረግ ነው፡፡ ይህን  ያደረገ  ጥፋተኛ  ነው፡፡

 

አንዳንድ  ምሳሌዎችን  እንውሰድ፡፡  አንድ ሰው በወንጀል  ሕግ  የሚያስቀጣ  ወንጀል ሳይፈፀም  ሰርቷል  ወይም  አንድን  የሕክምና ዶክተር  ችሎታ  እያለው  ችሎታ  የለውም  ማለት አንድን ነጋዴ  ሳይከስር   ዕዳውን  ለመክፈል  አይችልም  ማለት ተላላፊ በሽታ  ሳይኖርበት  እንዳለበት አድርጐ   ማውራት   ለስም  ማጥፋት እንደምሳሌ ልንወስዳቸው  እንችላለን፡፡ እንዲሁም ነገሩ  እውነት ሆኖም ሰውዬውን ለመጉዳት  ብለን ካደረግነው  ድርጊታችን  ጥፋት ይሆናል፡፡ /የወ.ሕግ  613/

 

አንድ  ቃል ወይም  አረፍተ ነገር  ስም ማጥፋት  ነው እንዲባል ቃሉ  ወይም  ዐረፍተ  ነገሩ  ለሶስተኛ  ሰው  ሊነገር  ይገባል፡፡  ለሶስተኛ  ሰው  ሳይሆን  ለራሱ  ለተበዳዩ ቀጥታ የተነገረ  እንደሆነ  ስም  ማጥፋት  ሳይሆን  ስድብ /insult/ ነው የሚሆነው፡፡

 

ስም የማጥፋት ድርጊት በቃል ሊሆን ይችላል፡፡ በፅሁፍና እንዲሁም በሌላ ዘዴ /ለምሳሌ ሌላ የኪነ ጥበብ ውጤት / ሊሆን ይችላል፡፡  ስም  ማጥፋት  አለ ለማለት  የግድ  የመጉዳት ሃሳብ   መኖር የለበትም፡፡ 2045 /1/ እንዲሁም  ቁጥር  2ዐ45/2/ ስር  እንደተደነገገው  በብድን  ስም  /group defamation/ የለም፡፡ ስለሆነም አንድ ሰው  ስም አጠፋ   ለማለት  በንግግሩ  ወይም  በፅሁፍ  የማንንም ሰው በተለይ ካልገለፀ በቀር ስም እንዳጠፋ አይቆጠርም፡፡  ሆኖም  ግን  ይህ አድራጉቱ ሌላ  ሰው እንዲጉዳ አስቀድሞ  ለመረዳት መቻሎ  ከተረጋገጠ  አላፊ  ሊሆን እንደሚችል  ቁጥር  2ዐ41/3/  ይደነግጋል፡፡

 

ቀጥለን  መከላከያዎችን  እንመለከታለን፡፡  የመጀመሪያው  መከላከያ  ቁጥር  2ዐ46 ስር የተደነገገው  የሕዝብን  ጥቅም  በሚነኩ ጉዳዩች  ላይ  አሳብን መግለፅ  ነው፡፡ ይህ  የተገለፀው  ሃሳብ  ሌላውን ሰው  በሕዝብ  ዘንድ  የሚያስወቅስ  እንኳን  ቢሆን  እንደስም  ማጥፋት  አይቆጠርም ሆኖም  ስም አጠፋ የተባለው ሰው ጠፋ   የተባለው  ሰው  ላይ  የሰጠው  አስተያየት  ሃሰት  መሆኑን በእርግጠኝነት  ካወቀ  ጥፋተኛ  ይሆናል፡፡

 

ሁለተኛው  መከላከያ  ደግሞ  የተነገረው  ነገር  እውነት መሆኑ ነው፡፡ ይህንንም በማስረጃ ማረጋገጥ አለበት  ሆኖም  ግን  የተባለው ነገር እውነት ቢሆንም  ስሙ  ጠፋ  የተባለውን ሰው  ሆን ብሎ  ለመጉዳት ቃሉን ወይም  ዓረፍተ  ነገሩን   የተናገረው  ተከሣሽ  ጥፋተኛ  ይሆናል፡፡ /በቁጥር 2ዐ47/

 

ሶስተኛ  መከላከያ  ደግሞ   የማይደፈር  መብት  በእንግሊዝኛው /immunity/ የሚባለው  ነው፡፡  ይህ መብት ለተወሰኑ  ሰዎች  የተሰጠ ነው  ለፖርላማ  አባላትና በፍርድ ቤት ፊት  ለሚከራከሩ ወገኖች፡፡  አንድ የፖርላማ አባል  በፖርላማ ውስጥ  በሚደረግ  ውይይት  ሀሳቡን  ሲገልፅ  ግለሰብን  አንስቶ ሊናገር  ይችላል፡፡  ይህ ግን  የፖርላማ አባሉን  በስም  ማጥፋት  ተጠያቂ ሊያደርግው አይችልም፡፡

 

በፍርድ  ሂደት ክርክርም  የሰዎች  ስም  ሊነሳ ይችላል ለፍትህ አሰጣጥ የግድ  ከሆነ ግለሰብ  ሊነሳ ይችላል፡፡  ይህን ያነሳ ተከራካሪ  በስም  ማጥፋት  ጥፋተኛ አይባልም፡፡

 

በተጨማሪም ቁጥር  2ዐ45/2/ ስር  እንደተደነገገው  በምክር ቤት ወይም በፍርድ  ቤት  የተደረገን ንግግርና ክርክር  እንዳለ /እንደወረደ እንደሚባለው/ የገለጠ  ሰውም በአላፊነት  ሊጠየቅ የሚችለው  ስሙ  በውይይቱ  ወይም በክርክሩ      የተነሳውን ሰውዬ  ለመጐዳት ብቻ አስቦ ከሆነ ብቻ ይሆናል፡፡

 

በመጨረሻም  የስም  ማጥፋት  ተግባር  በጋዜጣ  ላይ  ሊደረግ  ይችላል፡፡ ይህ  በሚሆንበት ጊዜ  ስም አጠፋ የተባለው ሰው  ፋጥተኛ  የሚሆነው፣

  • አንድን  ሰው  ለመጉዳት ብሎ  አስቦ ከሆነ
  • ይህንንም  የፈፀመው በከፍተኛ ቸልተኝነት ከሆነ
  • ወዲያውኑ መልሶ  ይቅርታ ካልጠየቀ ነው፡፡

 

በሌላ  አባባል  ስም  ማጥፋቱን  የፈፀመ አንድን  ሰው ለመጉዳት ሆን ብሎ  አስቦ  ሳይሆንና  በቸልተኝነት  ካልሆነ ይህንንም  ካደረገ  በኃላ  ወዲያውኑ  መልሶ  ይቅርታ  ከጠየቀ ጥፋተኛ  አይሆንም፡፡  2ዐ49/1/

ቁጥር 2ዐ49 /2/ እና /3/ የይቅርታው  አጠያየቅ  ጊዜ  እና በምን  ላይ መሆን  አለበት  የሚለውን  ይመልሳሉ፡፡  በንዑስ  ቁጥር  ሁለት  መሠረት ስም ማጥፋት  ድርጊቱ  የተደረገው  ከአንድ  ሳምንት  በበለጠ ጊዜ  በሚወጣ  ጋዜጣ  ላይ  ከሆነ  ይቅርታው  የግድ  የሚቀጥለው  ጋዜጣ  እስኪወጣ  መጠበቅ  የለበትም ይህ ከሆነ  ተበዳዩ  ይጉዳል፡፡  የጠፋውንም  ስምና ጉዳቱንም  ማስተካከል  የማይቻልበት  ደረጃ  ላይ  ሊደረስ  ይችላል፡፡ ስለዚህ  ይቅርታው  ተበዳዩ  በሚመርጠው  ጋዜጣ  ላይ  መውጣት  አለበት፡፡ ይህ ጋዜጣ  የበዳዩም  ሊሆን  ይችላል፡፡ የሌላ ሰወ  ጋዜጣም  ሊሆን ይችላል፡፡ ተበዳዩ  ጋዜጣ  ካልመረጠ በንዑስ  ቁጥር ሶስት  መሠረት  የስም  ማጥፋቱ ነገርና  የይቅርታው  መጠየቁ   የሚታተመው  ስምን ማጥፋቱ  በወጣበት ተከታይ ዕትም ላይ  ይሆናል፡፡

የኢፌዲሪ  ሕገ መንግስት  አንቀፅ 17 ስር  በሕገ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ማንኛውም ሰው ወንድም ሆነ ሴት ነፃነቱን/ቷን አያጣም /አታጣም ተብሎ ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም ንዑስ አንቀፅ ሁለት ስር ማንኛውም  ሰው  በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ሊያዝ እንደማይችል ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም ይህ የነፃነት መብት  ሕገ መንግስታዊ መብት ነው፡፡

 

ይህም በመሆኑ  ነው  የፍትሐብሔር  ቁጥር 2ዐ4ዐ/1/ አንድ ሰው ሕግ ሳይፈቀድለት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የሌላውን ሰው ነፃነት /ሕገ መንግስታዊ ነፃነት/የነካና አንደተፈቀደለት መጠን ካንዱ ቦታ ወደ ሌላው  እንዳይዘዋወር /የኢፌዲሪ ሕገ  መንግስት አንቀፅ 32/ ሰውየውን የከለከለ እንደሆነ ጥፋተኛ ነው በማለት የደነገገው፡፡

 

እዚህ ላይ  አንዳንድ  ነጥቦችን  እንመልከት የመጀመሪያው ሕግ  ሳይፈቀድለት የሚለው ነጥበ ነው፡፡ በሌላ  አባባል  አንድ ሰው  ሌላውን  ሰው ከቦታ  ቦታ  እንዳይዘዋወር መከልከል  ሕግ የፈቀደለት  ከሆነ  ጥፋተኛ  አይሆንም  ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ  የፍሐብሔር  ሕግ ቁጥር 265  እና በተሻሻለው  የቤተሰብ ሕግ /1992/  አንቀፅ  256  መሠረት አሳዳሪው አካለ  መጠን ያልደረሰውን ልጅ  መኖሪያ  ቦታ  የመወሰን ስልጣን  ብቻ ሳይሆን  አካለመጠን  ያላደረሰ ልጅ  ያለአሳዳሪው ፈቃድ  ያን ቦታ  ሊተው  አይችልም፡፡  ስለሆነም  አካለ መጠን  ያለደረሰው  ልጅ  ያን ቦታ ትቶ  የሄደ  እንደሆነ  አሳዳሪው  መኖሪያ  ቦታው  ላይ  እንዲመለስ ሊያስገድደው ይችላል፡፡ ስለዚህ  አካለመጠን  ያለደረሰውን ልጅ  የመዘዋወር ነፃነት  የመገደብ ስልጣን ለሞግዚቱ  አለው ማለት ነው፡፡

 

እንደተፈቀደለት የሚለው  ደግሞ   መብራራት ያለበት ሁለተኛው ነጥብ ነው፡፡ በእንግሊዝኛ / As he is  entitled to/ የሚለው  ነው፡፡ የእንግሊዝኛው የተሻለ  ይገልፀዋል፡፡ ይህ  ሐረግ  ቀጥታ  ሕግ  መንግስቱን ነው የሚያመለክተው የሕግ  መንግስቱ አንቀፅ 32 /1/ ይህን መብት ሲደነግግ

ማንኛውም  ኢትዩጵያዊ  ወይም  በሕጋዊ መንገድ  ሀገሪቱ  ውስጥ  የሚገኝ  የውጭ ዜጋ  በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወር እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነፃነት አለው”  ብሏል፡፡

 

ስለሆነም አንድ  ሰው  ሕግ  ሳይፈቅድለት  ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወር  የከለከለው ከሆነ ሕገ መንግስታዊ  መብቱን መንካት  መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

 

ሶስተኛው  ነጥብ  ደግሞ  መከልከሉ የግድ  ለረዥም ጊዜ መሆን የለበትም፡፡ በአማርኛው  ለተወሰነ ጊዜ  ይለዋል፡፡ እንግሊዝኛው ግን / Even for  a short time/ በማለት  ይገልፀዋል፡፡ ስለዚህ ይህ  መከልከል የግድ  ረዥም  ጊዜ  መሆን  የለበትም  ለአጭር ጌዜም  ቢሆን  ከልካዩን  ጥፋተኛ ያደርጋል፡፡ እንዲሁም   በተበዳይ /victim/ ሰውነት ላይ የግድ ጉዳት ማድረስ ይለበትም፡፡

 

 

መከላከያ  ቁጥር / 2ዐ42 እና 2ዐ43/

 

የመጀመሪያ  መከላከያ  ቁጥር  2ዐ42  ስር የተደነገገው  ነው፡፡ በዚህ ቁጥር መሠረት በሌላ ሰው  ነፃነት  ጣልቃ  የገባው  ሰው /ተከሣሽ/ ሁለት ነገሮችን  ማስረዳት ይጠበቅበታል፡፡

 

የመጀመሪያው ነፃነቱ የተነካበት ሰው  አንድ  የወንጀል  ድርጊት ሰርተዋል የሚለው  ነው፡፡ ድርጊቱ የወንጀል ድርጊት መሆን አለበት፡፡ በፍትሐብሔር  ሕግ  ተጠያቂ  ሊያደርግ የሚችል መሆን  የለበትም፡፡  ሁለተኛው  ነጥብ ደግሞ  የወንጀል  ድርጊቱን  ሰርቶአል  ብሎ  ለማሰብ የሚያስችለው  በቂ ምክንያት መኖሩን ማስረዳት አለበት፡፡ ይህን  በምሳሌ  እናስረዳ፡፡

 

አንድ  ሰው  በደም  የተበከለ ቢላዋ  ከደም  በተጨማለቀ እጁ  ይዞ   ቢገኝ  ይህን ሰው  ወንጀል ሰርተዋል ብሎ ለማሰብ በቂ ምክንያት  ሊሆን አይችልም  ሆኖም  ይህንኑ ሰው ሌሎች ሰዎች “ያዘው ያዘው” እያሉ  እየጮሁ  ቢያበሩት  እነዚህ ሁሉ  ተደምረው  ይህ ሰው  የወንጀል  ድርጊት ፈፅሟል  ብሎ  ለማሰብ በቂ ምክንያት ሊሆን  ይችላል፡፡ ስለሆነም ይህን ሰው  በቁጥጥር ስር ያለው ሰው  ጥፋተኛ  አይደለም ማለት ነው፡፡

 

ሌላ አንድ ምሳሌ  እንጨምር አንዲት የቤት እመቤት ባለቤቷን  በሌላ ሴት ትጠረጥረዋለች፡፡ እንበል አንድ ቀን ለቅሶ መሄዴ ነው  ብሎ  ሲወጣ በስውር ትከተለዋለች አባዋራውም  አንዲት  ጋለሞታ  ቤት ይገባና በሩ ይዘጋል ሚስትም  የተከረቸመውን በር እንዲከፍት  ብታንኳኳ  አይከፈትላትም በዚህ ጊዜ  በሩን ከኃላ  በቁልፍ ትቆልፍና ፖሊስ  ትጠራለች  ይህ ድርጊቷ ጥፋተኛ   አያሰኛትም ምክንያቱም  የመዘዋወር ነፃነቱ  የተነካበት /ባሏ/ ወንጀል  ሰርትዋል ብሏ ለማሰብ  በቂ  ምክንያት  /ከሌላ ሴት ጋር በሩን  መቆለፍ/ ስላላት ነው፡፡

 

ይህን  ወንጀል ሰርቷል ተብሎ  የተጠረጠረውን ሰው   አሳሪው  ወዴያውኑ  ለባለሥልጣኑ /ፖሊስ/ ማስረከብ ይኖርበታል፡፡ በምሳሌው ላይ የተጠቀሰችው  ሲትዩ በሩን  በቁልፍ  ከቆለፈች በኃላ  ወዲያውኑ  ፖሊስ  ጠርታለች፡፡ ደግሞ  የተጨማለቀውንም  ሰውዩ  ወዲያውኑ  ለፖሊስ  ማስርከብ  ያስፈልጋል፡፡  ይህ  ካልሆነ  ግን የዛን  ሰውዩ  የመዘዋወር ነፃነት የገደበው ሰው  በቁጥር 2ዐ42 /2/ መሠረት ጥፋተኛ ይሆናል፡፡

 

ሁለተኛው  መከላከያ  ቁጥር 2ዐ41  ስር  የተደነገገው ነው  በርግጥ ይህን ቁጥር  ለማስረዳት  እላይ   የገለፅነው   የአካለ  መጠን  ያለደረሰው  ልጅ  ሞግዚት ድርጊትን  መጠቀም  እንችላለን፡፡ ሆኖም  አንድ  ሌላ  ምሳሌ  እንውሰድ ፡፡

 

አንድ  ሰው  በሕግ  አግባብ  ቁጥጥር ስር  የዋለ  እንደሆነ የመዘዋወር  ነፃነቱ  ይገደባል፡፡  ይህንንም  የሚያስፈፅም  ሰው  ለምሳሌ  ፖሊስ  ጥፋት ሰራ  አይባልም  ሕግ  በሚፈቅድለት  አኳኋን  መሆን  እንዳለበት ቁጥር  2ዐ41     ይደነግጋል፡፡  በሌላ አባባል   በስልጣኑ  ስር  ያለን  ሰው  ማንገላታት የለበትም ነው  ይህ  እንደሆነም  የኢፌዲሪ  ሕገ መንግስት አንቀፅ  21  ስር

በጥበቃ  ስር ያሎና  በፍርድ  የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን  በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ  መብት አላቸው” 

 

በማለት  ደንግጓል፡፡ ስለሆነም  የመዘዋዋር ነፃነታቸው   የተገደበ ሰዎች   ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚነካ  ሁኔታ  መያዝ  የለባቸውም  ይህን የጣሰ ሰው  የተያዡን ሕገ  መንግስታዊ  መብት ስለሚነካ  ጥፋተኛ  ይሆናል፡፡

 

ሌላው  መነሳት ያለበት ነጥብ  ደግሞ ነፃነቱ  የተነካበት ሰው   ነፃነቱን በነካው  ሰው  ስልጣን  ስር ያለ  መሆን አለበት ይህ ስልጣን  ከሕግ  ወይም  ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ  ሊመነጭ  ይችላል፡፡  ሞግዚቱ አካለ  መጠን  ባለደረሰ ልጅ ላይ  ያለው  ስልጣን  የሚመነጨው ከሕግ  /የፍትሐብሔር  ሕገ ቁጥር 265 እና  የተሻሻለው የቤተሰብ  ሕግ ቁጥር 256/ ሲሆን የፖሊስ ደግሞ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወይም  ከሕግ የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡

 

በመጨረሻም ዋስ  የሆነ  ሰው  ዋስ የሆነለት ሰው  ሊጠፋ ነው የሚያስብል  መሰናዶ ማድረጉን  የሚያሳምን   በቂ  ምክንያት  ካለው የዚህን ሰው  ነፃነት  ቢነካበት ጥፋተኛ  እንደማይሆን  ቁጥር  2ዐ43  ይደነግጋል፡፡ ይህን ቁጥር በጥንቃቄ  መመልከት  የሚያሻ  ይመስለኛል፡፡  ምክንያቱም ቀድሞ  ግዞት   ከሚባል ፅንሰ  ሃሳብና  ተግባር ጋር  የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን   የሚልበት ምክንያት  አንድ ሰው  ለሌላ ሰው  ዋስ የሚሆነው ዋስ የተገባለት  ሰው ባንድ  በተወሰነ ቦታ እንዲኖር  ነው፡፡  ይህን  ዋስትና  የሚሰጠው  ደግሞ  ለመንግስት ባለስልጣናት  ነው፡፡  ስለዚህ  ዋሰ  የተገባለት  ሰው ዕዳ  ኖሮበት ወይም  የወንጀል  ድርጊት በመፈፀም  ተጠርጥሮ  ሳይሆን ዋስ የሚኮንለት  ባንድ በተወሰነ ቦታ እንዲኖር  ነው፡፡  በቀድሞ  ጊዜ  ሰዎች  ለንጉስ  ነገስቱ  የፖለቲካ  ተቀናቃኝ  ከሆኑ   ወደ ገጠር  ይወሰዱና  አንድ  አካባቢ  ብቻ  እንዲኖሩ  ለዚህም  ጠዋትና   ማታ  ፖሊስ  ጣቢያ  ሪፖርት   እንዲያደርጉ  ይደረጋሉ፡፡  ያን  ስፍራ  እንደማይለቁ ደግሞ   ዋስ  ይጠራሉ  ያ ዋስ  ነው እንግዲህ  ግዞተኛው  ቦታውን  ለቆ ለማምለጥ   መሰናዳቱን የሚያሳምን  በቂ ምክንያት  /ለምሳሌ  ዕቃዎችን  ያሰናዳ መንገድ  ለመሩት ከሚችሎ  ሰዎች  ጋር  ተነጋግሮ  ቀብድ  ከከፈለ ወዘተ/  ካለው  ይህ ሰው እንዳይንቀሳቀስ ሊያግደው  ይችላል፡፡  ይህን ማድረጉ ግን  ጥፋተኛ  አያደርገውም፡፡

 

ግዞት  ግን በአሁኑ  ጊዜ ቀርቷል፡፡ ሰዎች   ለፖለቲካ   አመለካከት  የመያዝ  ብቻ ሳይሆን ያን  አመለካከት  በሰላማዊ  መንገድ  የማራመድ  በነፃ የፖሊቲካ  ውድድር ተወዳድሮ  የመንግስት ስልጣን  የመያዝ  መብታቸው  በኢፊድሪ  ሕገ መንግስት  ተረጋግጧል፡፡  ይህን  በማድጋቸው   በግዞት በአንድ  ቦታ እንዲቆዩ  የሚደረጉበት ምክንያት  የለም፡፡ /በአንድ  ቦታ ለመቆየት ጥሩ  ምሳሌ  የሚትሆነን የበርማዋ ተወላጅ  የናቢል  ሰላም ተሸላሚዋ ሚስ ሳንሶዥ ናት ዛሬ ይህች   ፖለቲከኛ  በወታደራው ጁንታ ከቤቷ እንዳትወጣ /House  arrest ይሉታል ፈረጆች/   ተወስኖባታል፡፡ ምናልባት  ለዚህ አንድ  ሰው ዋሰ  እንዲሆኗት ጠርታ  እንደሆነና ዋስ   ልትጠሩ  መሰናዶ  ብታደርግ  ዋስ  የሆኗት ሰው  ከዛ ቤት እንዳትወጣ  ሊያደርጋት ይችላል፡፡ 

Page 1 of 2