- Details
- Category: Non-Contractual Liability (Tort Law)
የሌላን ሰው ነፃነት ስለመንካት ቁጥር 2040
የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 17 ስር በሕገ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ማንኛውም ሰው ወንድም ሆነ ሴት ነፃነቱን/ቷን አያጣም /አታጣም ተብሎ ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም ንዑስ አንቀፅ ሁለት ስር ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ሊያዝ እንደማይችል ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም ይህ የነፃነት መብት ሕገ መንግስታዊ መብት ነው፡፡
ይህም በመሆኑ ነው የፍትሐብሔር ቁጥር 2ዐ4ዐ/1/ አንድ ሰው ሕግ ሳይፈቀድለት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የሌላውን ሰው ነፃነት /ሕገ መንግስታዊ ነፃነት/የነካና አንደተፈቀደለት መጠን ካንዱ ቦታ ወደ ሌላው እንዳይዘዋወር /የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 32/ ሰውየውን የከለከለ እንደሆነ ጥፋተኛ ነው በማለት የደነገገው፡፡
እዚህ ላይ አንዳንድ ነጥቦችን እንመልከት የመጀመሪያው ሕግ ሳይፈቀድለት የሚለው ነጥበ ነው፡፡ በሌላ አባባል አንድ ሰው ሌላውን ሰው ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወር መከልከል ሕግ የፈቀደለት ከሆነ ጥፋተኛ አይሆንም ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የፍሐብሔር ሕግ ቁጥር 265 እና በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ /1992/ አንቀፅ 256 መሠረት አሳዳሪው አካለ መጠን ያልደረሰውን ልጅ መኖሪያ ቦታ የመወሰን ስልጣን ብቻ ሳይሆን አካለመጠን ያላደረሰ ልጅ ያለአሳዳሪው ፈቃድ ያን ቦታ ሊተው አይችልም፡፡ ስለሆነም አካለ መጠን ያለደረሰው ልጅ ያን ቦታ ትቶ የሄደ እንደሆነ አሳዳሪው መኖሪያ ቦታው ላይ እንዲመለስ ሊያስገድደው ይችላል፡፡ ስለዚህ አካለመጠን ያለደረሰውን ልጅ የመዘዋወር ነፃነት የመገደብ ስልጣን ለሞግዚቱ አለው ማለት ነው፡፡
እንደተፈቀደለት የሚለው ደግሞ መብራራት ያለበት ሁለተኛው ነጥብ ነው፡፡ በእንግሊዝኛ / As he is entitled to/ የሚለው ነው፡፡ የእንግሊዝኛው የተሻለ ይገልፀዋል፡፡ ይህ ሐረግ ቀጥታ ሕግ መንግስቱን ነው የሚያመለክተው የሕግ መንግስቱ አንቀፅ 32 /1/ ይህን መብት ሲደነግግ
“ማንኛውም ኢትዩጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወር እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነፃነት አለው” ብሏል፡፡
ስለሆነም አንድ ሰው ሕግ ሳይፈቅድለት ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወር የከለከለው ከሆነ ሕገ መንግስታዊ መብቱን መንካት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ሶስተኛው ነጥብ ደግሞ መከልከሉ የግድ ለረዥም ጊዜ መሆን የለበትም፡፡ በአማርኛው ለተወሰነ ጊዜ ይለዋል፡፡ እንግሊዝኛው ግን / Even for a short time/ በማለት ይገልፀዋል፡፡ ስለዚህ ይህ መከልከል የግድ ረዥም ጊዜ መሆን የለበትም ለአጭር ጌዜም ቢሆን ከልካዩን ጥፋተኛ ያደርጋል፡፡ እንዲሁም በተበዳይ /victim/ ሰውነት ላይ የግድ ጉዳት ማድረስ ይለበትም፡፡
መከላከያ ቁጥር / 2ዐ42 እና 2ዐ43/
የመጀመሪያ መከላከያ ቁጥር 2ዐ42 ስር የተደነገገው ነው፡፡ በዚህ ቁጥር መሠረት በሌላ ሰው ነፃነት ጣልቃ የገባው ሰው /ተከሣሽ/ ሁለት ነገሮችን ማስረዳት ይጠበቅበታል፡፡
የመጀመሪያው ነፃነቱ የተነካበት ሰው አንድ የወንጀል ድርጊት ሰርተዋል የሚለው ነው፡፡ ድርጊቱ የወንጀል ድርጊት መሆን አለበት፡፡ በፍትሐብሔር ሕግ ተጠያቂ ሊያደርግ የሚችል መሆን የለበትም፡፡ ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ የወንጀል ድርጊቱን ሰርቶአል ብሎ ለማሰብ የሚያስችለው በቂ ምክንያት መኖሩን ማስረዳት አለበት፡፡ ይህን በምሳሌ እናስረዳ፡፡
አንድ ሰው በደም የተበከለ ቢላዋ ከደም በተጨማለቀ እጁ ይዞ ቢገኝ ይህን ሰው ወንጀል ሰርተዋል ብሎ ለማሰብ በቂ ምክንያት ሊሆን አይችልም ሆኖም ይህንኑ ሰው ሌሎች ሰዎች “ያዘው ያዘው” እያሉ እየጮሁ ቢያበሩት እነዚህ ሁሉ ተደምረው ይህ ሰው የወንጀል ድርጊት ፈፅሟል ብሎ ለማሰብ በቂ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም ይህን ሰው በቁጥጥር ስር ያለው ሰው ጥፋተኛ አይደለም ማለት ነው፡፡
ሌላ አንድ ምሳሌ እንጨምር አንዲት የቤት እመቤት ባለቤቷን በሌላ ሴት ትጠረጥረዋለች፡፡ እንበል አንድ ቀን ለቅሶ መሄዴ ነው ብሎ ሲወጣ በስውር ትከተለዋለች አባዋራውም አንዲት ጋለሞታ ቤት ይገባና በሩ ይዘጋል ሚስትም የተከረቸመውን በር እንዲከፍት ብታንኳኳ አይከፈትላትም በዚህ ጊዜ በሩን ከኃላ በቁልፍ ትቆልፍና ፖሊስ ትጠራለች ይህ ድርጊቷ ጥፋተኛ አያሰኛትም ምክንያቱም የመዘዋወር ነፃነቱ የተነካበት /ባሏ/ ወንጀል ሰርትዋል ብሏ ለማሰብ በቂ ምክንያት /ከሌላ ሴት ጋር በሩን መቆለፍ/ ስላላት ነው፡፡
ይህን ወንጀል ሰርቷል ተብሎ የተጠረጠረውን ሰው አሳሪው ወዴያውኑ ለባለሥልጣኑ /ፖሊስ/ ማስረከብ ይኖርበታል፡፡ በምሳሌው ላይ የተጠቀሰችው ሲትዩ በሩን በቁልፍ ከቆለፈች በኃላ ወዲያውኑ ፖሊስ ጠርታለች፡፡ ደግሞ የተጨማለቀውንም ሰውዩ ወዲያውኑ ለፖሊስ ማስርከብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የዛን ሰውዩ የመዘዋወር ነፃነት የገደበው ሰው በቁጥር 2ዐ42 /2/ መሠረት ጥፋተኛ ይሆናል፡፡
ሁለተኛው መከላከያ ቁጥር 2ዐ41 ስር የተደነገገው ነው በርግጥ ይህን ቁጥር ለማስረዳት እላይ የገለፅነው የአካለ መጠን ያለደረሰው ልጅ ሞግዚት ድርጊትን መጠቀም እንችላለን፡፡ ሆኖም አንድ ሌላ ምሳሌ እንውሰድ ፡፡
አንድ ሰው በሕግ አግባብ ቁጥጥር ስር የዋለ እንደሆነ የመዘዋወር ነፃነቱ ይገደባል፡፡ ይህንንም የሚያስፈፅም ሰው ለምሳሌ ፖሊስ ጥፋት ሰራ አይባልም ሕግ በሚፈቅድለት አኳኋን መሆን እንዳለበት ቁጥር 2ዐ41 ይደነግጋል፡፡ በሌላ አባባል በስልጣኑ ስር ያለን ሰው ማንገላታት የለበትም ነው ይህ እንደሆነም የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 21 ስር
“በጥበቃ ስር ያሎና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት አላቸው”
በማለት ደንግጓል፡፡ ስለሆነም የመዘዋዋር ነፃነታቸው የተገደበ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚነካ ሁኔታ መያዝ የለባቸውም ይህን የጣሰ ሰው የተያዡን ሕገ መንግስታዊ መብት ስለሚነካ ጥፋተኛ ይሆናል፡፡
ሌላው መነሳት ያለበት ነጥብ ደግሞ ነፃነቱ የተነካበት ሰው ነፃነቱን በነካው ሰው ስልጣን ስር ያለ መሆን አለበት ይህ ስልጣን ከሕግ ወይም ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊመነጭ ይችላል፡፡ ሞግዚቱ አካለ መጠን ባለደረሰ ልጅ ላይ ያለው ስልጣን የሚመነጨው ከሕግ /የፍትሐብሔር ሕገ ቁጥር 265 እና የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ቁጥር 256/ ሲሆን የፖሊስ ደግሞ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወይም ከሕግ የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡
በመጨረሻም ዋስ የሆነ ሰው ዋስ የሆነለት ሰው ሊጠፋ ነው የሚያስብል መሰናዶ ማድረጉን የሚያሳምን በቂ ምክንያት ካለው የዚህን ሰው ነፃነት ቢነካበት ጥፋተኛ እንደማይሆን ቁጥር 2ዐ43 ይደነግጋል፡፡ ይህን ቁጥር በጥንቃቄ መመልከት የሚያሻ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ቀድሞ ግዞት ከሚባል ፅንሰ ሃሳብና ተግባር ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን የሚልበት ምክንያት አንድ ሰው ለሌላ ሰው ዋስ የሚሆነው ዋስ የተገባለት ሰው ባንድ በተወሰነ ቦታ እንዲኖር ነው፡፡ ይህን ዋስትና የሚሰጠው ደግሞ ለመንግስት ባለስልጣናት ነው፡፡ ስለዚህ ዋሰ የተገባለት ሰው ዕዳ ኖሮበት ወይም የወንጀል ድርጊት በመፈፀም ተጠርጥሮ ሳይሆን ዋስ የሚኮንለት ባንድ በተወሰነ ቦታ እንዲኖር ነው፡፡ በቀድሞ ጊዜ ሰዎች ለንጉስ ነገስቱ የፖለቲካ ተቀናቃኝ ከሆኑ ወደ ገጠር ይወሰዱና አንድ አካባቢ ብቻ እንዲኖሩ ለዚህም ጠዋትና ማታ ፖሊስ ጣቢያ ሪፖርት እንዲያደርጉ ይደረጋሉ፡፡ ያን ስፍራ እንደማይለቁ ደግሞ ዋስ ይጠራሉ ያ ዋስ ነው እንግዲህ ግዞተኛው ቦታውን ለቆ ለማምለጥ መሰናዳቱን የሚያሳምን በቂ ምክንያት /ለምሳሌ ዕቃዎችን ያሰናዳ መንገድ ለመሩት ከሚችሎ ሰዎች ጋር ተነጋግሮ ቀብድ ከከፈለ ወዘተ/ ካለው ይህ ሰው እንዳይንቀሳቀስ ሊያግደው ይችላል፡፡ ይህን ማድረጉ ግን ጥፋተኛ አያደርገውም፡፡
ግዞት ግን በአሁኑ ጊዜ ቀርቷል፡፡ ሰዎች ለፖለቲካ አመለካከት የመያዝ ብቻ ሳይሆን ያን አመለካከት በሰላማዊ መንገድ የማራመድ በነፃ የፖሊቲካ ውድድር ተወዳድሮ የመንግስት ስልጣን የመያዝ መብታቸው በኢፊድሪ ሕገ መንግስት ተረጋግጧል፡፡ ይህን በማድጋቸው በግዞት በአንድ ቦታ እንዲቆዩ የሚደረጉበት ምክንያት የለም፡፡ /በአንድ ቦታ ለመቆየት ጥሩ ምሳሌ የሚትሆነን የበርማዋ ተወላጅ የናቢል ሰላም ተሸላሚዋ ሚስ ሳንሶዥ ናት ዛሬ ይህች ፖለቲከኛ በወታደራው ጁንታ ከቤቷ እንዳትወጣ /House arrest ይሉታል ፈረጆች/ ተወስኖባታል፡፡ ምናልባት ለዚህ አንድ ሰው ዋሰ እንዲሆኗት ጠርታ እንደሆነና ዋስ ልትጠሩ መሰናዶ ብታደርግ ዋስ የሆኗት ሰው ከዛ ቤት እንዳትወጣ ሊያደርጋት ይችላል፡፡