ይህ ዓይነት የአእምሮ ንብረት መብት ለኢትዮጵያ አዲስና ከወጣም ብዙ ዓመታትን ያላስቆጠረ መብት ነው፡፡ የዕፀዋት አዳቃዮች መብት ለማስጠበቅ የወጣው አዋጅ ቁጥር 481/98 አላማም በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ተመራማሪዎችና በልማዳዊ አሰራር ዝርያን የሚያዳቅሉ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የሰራቸው ውጤት ተጠቃሚዎች ለመሆን የሚያስችላቸውን ኢኮኖሢያዊ ጥቅም ለማስጠበቅና የቆየው የዝርያ መጠቀምና መለዋወጥ ልማዳዊ ስርዓታቸው እንዲቀጥል ለማድረግና የተሻለ ዝርያ በመጠቀም የተሻለ ምርት እንዲያመርቱ በማስቻል የልማት ስትራተጂውን ከግብ ማድረስ ነው፡፡

አዋጁ በርእስነት የተጠቀመባቸውን ሁለት ስለዕፀዋትና አዳቃዮች የሚሉትን ቃላት በትርጉም ክፍሉ አንቀፅ 2(6)” ዕፀዋት” የሚለውን ቃል” “ዕፀዋት ማለት እንሰሳ ያልሆነ እና በተፈጥሮ መራባት የሚችል ሕይወታዊ  ሃብት ነው፡፡”  ሲል ”አዳቃይ” ማለት

አዲስ የዕፀዋት ዝርያ አዳቅሎ ያወጣ ሰው ወይም

አዲስ የዕፀዋት ዝርያ አዳቅሎ ያወጣን ሰው ቀጥሮ ወይም ስራውን ተኮናትሮ ያሰራ ሰው ወይም  በዚህ ንዑስ አንቀፅ “ ሀ ” ወይም “ ለ” የተጠቀሰ ሰው ወራሽ የሆነ ሰው ነው፡፡’

በማለት ፍቻቸውን ይሰጣል:: ከነዚህ ሁለት መብቱን የሚገልፁ ቃላት ትርጉም መረዳት የሚቻለው መብቱን ለማግኘት በማዳቀል የተገኘው ዘር አዲስ መሆን እንዳለበት፤ ሌላ ሰውን ቀጥሮ በማሰራት በሚገኘው አዲስ ዝርያ የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብትን ማግኘት እንደሚቻልና በመጨረሻም የግኝቱ ባለቤት ወራሽ መብቱን ሊያወርስ እንደሚችል ነው፡፡

 

በዚህ አዋጅ መሰረት አዳቃዮች የሚኖራቸው መብት ምንድ ነው? ብለን ያየን እንደሆነ በመብቱ ያለመከልከለ ወይም ከክልከላ ነፃ መሆን (Exemptions) እና ገደቦች (restrictions) እንደተጠበቁ ሆነው የዕፅዋት አዳቃዩ ሌሎች ሰዎች የተጠበቀን የተክል ዝርያ ወይም የዝሪያ አካል እንዲሸጡ፣ እንዲገዙ የመፍቀድና በማንኛውም መንገድ በሌላ ሶስተኛ ወገን የመብት ጥሰት ሲያጋጥም በመደበኛ ፍ/ቤት አቅርቦ የማስቀጣት መብቶች ናቸው ፡፡ እነዚህ መብቶች ፍፁም መብቶች (monopoly or absolute rights) ባለመሆናቸው ህጉ በአንቀፅ 6 ላይ ከክልከላ ነፃ የሆኑ ድርጊቶችን (exemptions) በዝርዝር አስቀምጧል::

በመሆኑም ለንግድ ስራ ሳይሆን ለሌላ አገልግሎት እንዲውል የማራባት፣ መዝራት ወይም መጠቀም በህግ የሚያስጠይቅ ተግባር አይደለም፡፡ ለምግብነት ወይም የዝሪያውን ማብቀል ወይም ማራባት ለሚያስከትሉ ሌሎች አገልግሎቶች እንዲውል መሸጥ አያስጠይቅም፡፡  ተተክለው በሚገኙበት ማሳ መይም በማናቸውም ሌላ ቦታ ላይ እንዳሉ መሸጥ፡፡  አዲስ ዝርያን ለማውጣት በመነሻ የተለያየነት (variety) ምንጭነት አድርጐ አንድ የተጠበቀን ዘር ወይም የዘር አካል መገልገል፡፡ በምግብነት በቤት ለመጠቀም ወይም በገበያ ለመሸጥ የተጠበቀውን ዝርያ መዝራት፡  ለቀጣይ ምርምር፣ ለትምህርት አገልግሎት ሲባል የሚደረግ ማዳቀል  ከጂን ባንክ ወይም ከዕፅዋት ጀነቲክ ማዕከል ዝሪያውን ማግኘት በአዋጁ መሰረት የማያስከስሱ ግን ደግሞ ለንግድ ስራ እንዳይውሉ ለባለመብቱ ጥበቃ የሚሰጠው መብት ነው፡፡

 

የዕፅዋት አዳቃይ ባለቤት በመብቱ እንዳይሰራበት ሊደረግ ወይም ሊታገድ እንደሚችል በአንቀፅ 7 ላይ የተዘረዘሩ ሲሆኑ እነሱም፤

በዕፅዋት አዳቃዮች መካከል በሚደረግ ውድድር ምክንያት ችግር ሲፈጠር ወይም

ዝርያው በምግብ ዋስትና ፣ በስነ ምግብ (nutrition) ወይም ጤና ፍላጐቶች ወይም ብዝሀ ሕይወት (biological diversity) ላይ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያደርስ ሆኖ ከተገኘ

ለገበያ የሚውለው ዝሪያ አብዛኛው ከውጪ የመጣ ሲሆን ወይም

የአርሶ አደሩ ማህበረሰብ ለአንድ ለተወሰነ የተጠበቀ ዝሪያ ዘር ያለው ፍላጐት ያልተሟላ የሆነ እንደሆነ ናቸው፡፡

የዕፅዋት አዳቃይነት መብት ለማግኘት ያለው መስፈርት ምንድን ነው? አዋጁ ለዚህ መልስ የሚሰጥ ሲሆን አንድ የዘርፉ ተመራማሪ ወይም በልማዳዊ የማዳቀል ዘዴ መብቱ ይጠበቅልኝ ብሎ የሚያመለክት ሰው የዚህ መብት ባለቤት ተብሎ እውቅና በግርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር እንዲሰጠው ከተፈለገ ፤

የዕፀዋቱ ዝሪያ አዲስ መሆን ይኖርበታል ይኸውም በአዋጁ አንቀፅ 2(5) መለኪያ መሰረት ተገኘ የተባለው ዝርያ ማመልከቻው ባቀረበበት ዕለት መኖራቸው በህዝብ ከታወቁት ከሁሉም ሌሎች ዝርያዎች በግልፅ የሚለይና በተደረጉ ማራባቶች ምክንያት ዋና ዋና  ባህሪያቱን ሳይለወጥ የሚቆይና በበቂ ሁኔታ ወጥ የሆነ አንድ ዓይነት ዝሪያ ወይም ተለይቶ የሚታወቅ ሕብረ-ዝሪያ (multi line) የሆነ እንደሆነና የዘር፣ ፍራፍሬ ወይም ወይን ዝሪያ በሆነበት ጊዜ ከ6 ዓመት በፊት ወይም ሌሎች ዝሪያዎችን የሚመለከት ሲሆን ማመልከቻው ከቀረበበት ዕለት 4 ዓመት በፊት ያልሸጠው ወይም ያላስተላለፈው መሆኑ ታይቶ እንደ አዲስ ዝርያ ተወስዶ ባለመብት ሊሆን ይችላል፡፡

መብቱን ለመስጠት የሚከለክል ምክንያት ከሌለ መብቱ ይሰጠዋል፡፡

መብቱ ቀደም ሲል ለሌላ ሰው ያልተሰጠ ሲሆን የሚሰጠው ይሆናል::

ቀደም ሲል የቀረበ ግን ደግሞ ያልተወሰነ ወይም ውድቅ ያልተደረገ የዕፀዋት አዳቃዮች ማመልከቻ የሌለ እንደሆነ ይታይለታል፡፡

ለመብቱ መከፈል ያለበትን ክፍያ የከፈለ እንደሆነ እውቅናው ይሰጠዋል::

ዝርያውን አዳቅሎ ለማውጣት ጥቅም ላይ የዋለን የጀነቲክ ሀብት አመልካቹ በተገቢው የአክብሮት ህግ (relevant laws on access to genetic resource) ያገኘው መሆኑ ሲረጋገጥ መብቱ ይሰጠዋል፡፡ ቀጥሎ መነሳት ያለበት ጉዳይ ይህ መብት ሊሰጥ የሚችለው ለማን ነው? የሚለው ሲሆን የዕፀዋት አዳቃዮች መብት ለኢትዮጵያዊም ሆነ የውጭ ዜጋ በአገር ውስጥ የተገኘ ይሁን በውጪ አገር መስፈርቱን ካሟላ ለአመልካቹ መብቱ ይሰጠዋል፡፡  ይኸውም በግለሰብ ደረጃ፣ በጋራ እና በድርጅት ሰም ሊሰጥ የሚችል ሲሆን እዚህ ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ሁለት የተለያዩ የዕፅዋት አዳቃዮች በተመሳሳይ ዝርያ መብቱ እንዲሰጣቸው በሚያመለክቱበት ጊዜ የቀደምትነት መብት የሚሰጠው ቀድሞ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ላመለከተው ሰው መሆኑን ነው፡፡

 

የዕፅዋት አዳቃይነት መብት በማስመልከት ምን ማለት እንደሆነ መብቱ ጥበቃ የሚደረግለት ለምን እንደሆነና ህጉ የሚያስቀምጣቸውን ከክልከላ ነፃ መሆን (exemptions) እና ገደቦች (restriction) እና ባለ መብት ለመሆን ያሉትን መመዘኛዎችና መብቱ ለማን ሊሰጥ እንደሚችል ተመልክተናል ቀጥለን የምናየው ደግሞ ይህ በህግ የሚቋቋም መብት እንዴት እንደሚተላለፍ፣ እንደሚተውና እንደሚሰረዝ ይሆናል፡፡  የዕፅዋት አዳቃዮች መብት በህግ ወይም በውል ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ የሚቻል ግዙፍነት የሌለው የአእምሮ የንብረት መብት ሲሆን መብቱ የሚተላለፈው በውል በሚሆንበት ጊዜ ውሉ በዕፀዋት አዳቃዮች መዝገብ ካልተመዘገብ ህጋዊ ውጤት አይኖረውም፡፡  አንድ ሰው የዕፅዋት አዳቃይነት መብት ካገኘ በኋላ ባለቤቱ በራሱ ፈቃድ መብቱን ትቻለሁ ብሎ ለሚኒስቴሩ በማመልከት መተው ይችላል፡፡  ህጉ ከዚህ ጋር ተያያዥነት ባለው መልኩ የሚደነግገው የተለየ ሁኔታ (exeption) ቢኖር በመብቱ ሳቢያ በፍ/ቤት ክስ ቀርቦበት ወይም ተከራካሪ ሆኖ ባለበት ጊዜ መብቱን ትቻለሁ ብሎ ለሚኒስቴሩ ቢያመለክትም ሚኒስቴሩ የፍ/ቤት ፈቃድ ሳያገኝ ማመልከቻውን ሊቀበል የማይችል መሆኑ ነው፡፡ የዕፅዋት አዳቃይነት መብት መሰረዝን በተመለከተ አንድ ሰው የባለቤትነት መብቱ ለሌላ ሰው በመስጠቱ ምክንያት ጥቅሜ ተነክቷል የሚል ወገን ሲያመለክት የማጣራቱ ስራ ለወደፊቱ በሚወጣው ደንብ መሰረት ተጣርቶ መብቱ ለመሰረዝ የሚያስችል ምክንያት ሲገኝ የነበረው መብት ይሰረዛል፡፡  እንደዚሁም ከተሰጠው በኋላ ዝርያው አዲስ ያለመሆኑ ሲረጋገጥ ወይም ከመስጠቱ በፊት ቢታወቅ ኖሮ አይሰጠውም ነበር የሚያሰኝ ምክንያት ሲገኝ መብቱ ይሰረዛል፡፡  ሌሎች የዕፅዋት አዳቃይነት መብት ሊያሰርዙ የሚችሉ ምክንያቶች እንደ መክፈል ያለበትን ገንዘብ የመክፈያው ቀን (due date) ከደረሰ በኋላ  በ9ዐ ቀን ጊዜ ውስጥ ሳይከፍል መቅርት ወይም አንድን የተጠበቀን ዝሪያ ሳያድስ መቅረት መብቱን ሊያሰርዙ የሚችሉ ምክንያቶች በአዋጁ ተደንግገው የምናገኛቸው ናቸው፡፡

 

የዕፀዋት አዳቃዮች መብትን መሰረት በማድረግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 481/98 ለገበሬዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ልዩ ጥበቃ የሚሰጥ ነው::

ካመረቱት ዘር ዝርያውን ወይም የዝርያውን አካል የማስቀመጥ፣ የመለወጥ፣ የመጠቀምና የመሸጥ መብትን ይሰጣቸዋል፡፡

ከጄነቲክ ማዕከላትና የጂን ባንክ ዝርያን የማውጣትና የመጠቀም መብትንና

የተጠበቀ ዝርያን ዘርተው ካገኙት ምርት ዝርያን በጋራ የማስቀመጥ ፣ የመጠቀም፣ የማባዛትና የማዘጋጀት መብትን ይሰጣቸዋል:: ሆኖም ግን አንድን ዘር ወይም የዘርን አካል በዘር ኢንዱስትሪ ውስጥ ለንግድ በሆነ መጠን እንዲሸጡ አይፈቀድላቸውም፡፡

 

ይህ መብት እንደሌሎቹ የአእምሮ ንበረት መብቶች ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ በህግ የተደነገገ ሲሆን ጊዜው የመብቱ መሰረት የሆነውን ዝርያ መሰረት በማድረግ በሁለት የተከፈለ ነው:: ይሄውም መብቱ የተሰጠው ዓመታዊ ሰብሎችን መሰረት በማድረግ ከሆነ ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ ማመልከቻው ከቀረበበት ቀን አንስቶ ለቀጣይ 20 ዓመታት ነው፡፡ የመብቱ መሰረት ዛፎችን የወይን ተክሎችን ወይም ሌሎች ቋሚ ተክሎች በሚሆኑበት ጊዜ ደግሞ ይህ መብቱ ፀንቶ የሚቆየው ማመልከቻው ከቀረበበት ቀን አንስቶ ለቀጣዮቹ 25 ዓመታት ይሆናል::  ህጉ መብቱ ፀንቶ ባለበት ጊዜ የሚከሰቱ የመብት ጥሰቶችን መሰረት በማድረግ ባለ መብቶች ጉዳያቸውን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በማቅረብ በከሳሽነት፣ በተከሳሽነት ወይም በተከሳሽ ከሳሽነት ሊከራከሩና ፍርድ ቤት ካሳ ማስከፈልን ጨምሮ በቅጣት ከ6 ወር በማያንስ እስራትና ከብር አምስ ሺህ በማያንስ መቀጮ ሊቀጣ አንደሚችል የሚደነግግ ስለሆነ ለዜጐች ፈጠራ ስራ ዋስትና የሚሰጥ ነው፡፡

 

የዕፅዋት አዳቃዮች መብትን በማስመልከት የወጣው አዋጅ ቁጥር 481/98 በርካታ መብቶችን በማስጠበቅ ለህዝብ ጥቅም ሲባል ብቻ በመብቱ ከክልከላ ነፃ የሆኑ ሁኔታዎችንና ገዳቦችን በመዘርዘር ዜጐች ስርዓት ባለው መንገድ የግኝታቸው ባለቤትነት እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው:: ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማስጠበቅ የዘርፉ ተመራማሪዎችን በማበረታታት አገሪቱ ከዚህ የልማት አንድ አካል የሆነው ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችል ነው::

 

ስለዚህእስካሁን እያየናቸው የመጣን ዝርዝር ነገሮች የአእምሮ ንብረትን የሚመለከት አገራችን  ከማንኛውም ጊዜ የበለጠና ዘመናዊ ህግ እንዳላት የሚያመላክትና ዜጎች በዚህ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዋስትና የሚሰጡ ናቸው :: ሆኖም ግን በአንድ አገር ፍትሓዊና ዘመናዊ ህግ መኖሩ ብቻ በራሱ ግብ ሊሆን ስለማይችል የህጎቹን አላማ ተገንዝበን ህብረተሰባዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አመረቂ ስራ በመስራቱ ሂደት የፍትህ አካላትና መላው ህ/ሰብ አበክረው ሊሰሩና ከጥሰት እነዚህን የአእምሮ ንብረቶችን አንደ ዓይን ብሌናቸው ሊንከባከቧችው ይገባል::