- Details
- Category: Non-Contractual Liability (Tort Law)
ከውል ውጪ የአላፊነት ምንጮች
ከውል ውጭ የሆኑ የአላፊት ምንጨች ሶስት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ጥፋት ነው፡፡ ሁለተኛው የአንድ ሰው እንቅስቃሴ /Activity/ ወይም በእጅ የያዘው ወይም ንብረቱ የሆነ ነገር ነው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ አላፊ የሆኑለት ሰዉ በጥፋት ምክንያት ወይም በሕጉ መሠረት አላፊ መሆን ነው፡፡ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2ዐ77 /1/ የመጀመሪያውን አንድ ሰው በራሱ በኩል ምንም የገባው ግዴታ ሳይኖር በራሱ ጥፋት በሌላው ሰው ላይ ጉዳትን ካደረሰ አላፊ ነው ይላል፡፡ በዚህ ድንጋጌ ቁጥር ስር የሚመደበት ከቁጥር 2ዐ28 እስከ ቁጥር 2ዐ65 ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ቁጥሮች በአራት ንዑሳን ክፍሎች ከፍለን በዝርዝር እንመለከታለን፡፡
ቁጥር 2ዐ27/2/ ደግሞ ሁለተኛውን ምንጭ ሲደነግግ አንድ ሰው በሕጉ ላይ እንደ ተመለከተው በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችለው ሥራ ከሠራ /ከቁጥር 2ዐ66-ቁጥር 2ዐ76/ ወይም በእጅ የያዘው ነገር /ከቁጥር 2ዐ77-ቁጥር 2ዐ85/ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ካደረሰ አላፊ ይሆናል ይላል፡፡
ሶስተኛው ምንጭ ሲደነገግ በጥፋት ምክንያት /በቁጥር 2ዐ28-2ዐ65/ ወይም በሕጉ መሠረት ሲኖር ሌላ ሰው ለፈፀመው አድራጐት በሕጐ አላፊነት አለበት የተባለው ሰው አላፊ ነው ይላል፡፡
በእነዚህ ንዑስ ቁጥሮች ውስጥ ከወዲሁ መብራራት ያለባቸው ሀረጐች አሉ፡፡ በቁጥር 2ዐ28/1/ ስር አንድ በራሱ በኩል ምንም የገባው ግዴታ ሳይኖር የሚል ሀረግ አለ፡፡ ይህ ሀረግ የምያነሳው እላይ በውልና ከውል ውጨ አላፊነት ሕጉች ልዩነት ስንወያይ የግዴታዎች ምንጨች ይለያያሉ ያለውን ነው የሚያጠናክረው፡፡ በሌላ አባባል በውል ሕግ መሠረት ለአላፊነት ምንጩ የተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ሲሆን ከውል ውጭ አላፊነት መሠረቱ ግን የተዋዋይ ወገኖች ውል ሣይሆን ሕግ ነው ማለት ነው፡፡
ስለሆነም በ2ዐ28/1/ መሠረት አላፊ ለመሆን አጥፊው ጥፋት ቢሰራ አላፊ እሆናለሁ በማለት ግዴታ መግባት የለበትም፡፡ አላፊ ለመሆን የሚያስፈልገው ጥፋት መስራት በጥፋት ደግሞ ጉዳት ማድረስ ለጉደቱ ደግሞ የተፈፀመው ጥፋት ምክንያት መሆን ናቸው፡፡ንዑስ ቁጥር ሁለት ስር ደግሞ በሕጉ ላይ እንደተመለከተው የሚል ሀረግ አስፈላጊነት አንድ ሰው በሰራው ሥራ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት በማድረስ አላፊ የሚሆነው ሕግ አላፊ ይሆናል ሲል ነው፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ቁጥር 2ዐ7ዐ ነው፡፡ በዚህ ቁጥር መሠረት ሥራ ብቻውን አላፊነትን አያስከትልም፡፡ ሥራው ጥፋት ያለበት መሆን አለበት፡፡ ያን ጊዜ ብቻ ነው በሥራው ምክንያት ጉዳት ያደረሰ ሰው አላፊ የሚሆነው፡፡
በጥፋት ላይ ስለተመሠረተ አላፊነት
ይህ አላፊነት የተደነገገው በፍተሐብሔር ሕግ ቁጥር 2ዐ28-2ዐ65 ድረስ ባሉት ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንደገና በሁለት ይከፈላል፡፡ ከቁጥር 2ዐ28-2ዐ37 ድረስ ያሉት ጠቅላላ ደንቦች በሚል ስር የተመደቡ ሲሆን ከ2ዐ38-2ዐ65 ድረስ ያሉት ደግሞ ልዩ ሆኔታዎች በሚለው ስር ተመድበዋል፡፡
በጥፋት ላይ የተመሠረተ አላፊነትን በሶስት ክፍሎች ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ የመጀመያው ከሰው ሰውነት ጋር በተያያዙ መብቶች ላይ የተደረገ ጥፋት ብለን መመደብ እንችላለን፡፡ በመጨረሻም በንብረትና በኢኮነሚያዊ መብት ጋር በተያያዘ የተደረገ ጥፋት ማለት እንችላለን፡፡ ሶስተኛ ደግሞ ሌሎች ብለን መመደብ እንችላለን፡፡
ከሰው ሰውነት ጋር በተያያዘ መብቶች ላይ የተደረገ ጥፋት
በሞያ ሥራ ላይ የሚደረግ ጥፋት /2ዐ31/
ይህ የጥፋት ዓይነት በሞያተኛ የሚፈፀም የጥፋት ዓይነት ነው፡፡ ስለሆነም ሞያ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ የተለየ ስልጠና ክህሎት እና እውቀት የሚያስፈልገው ክወና /activity/ ሞያ ይባላል፡፡ ለምሳሌ መኪና መንዳት ሞያ ነው፡፡ ድንጋይ በባሬላ ማጓጓዠ ወይም ከጭነት መኪና ላይ በርበሬ መጫን ወይም ማራገፍ ሞያ አይባልም፡፡
ሞያ የራሱ የሆነ ሕጉች ወይም መመሪያዎች አሉት፡፡ እነዚህ ሕጐች በፅሑፍ የተቀመጡ ወይም ያልተፃፋ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የመኪና መንዳት ሞያ ሕጐች በፅሁፍ ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህን የተፃፋ ሕጐች እያንዳንዱ አሽከረካሪ አውቋቸው በዛው መሠረት መኪናውን ማሽከርክር አለበት፡፡ የሞያው ሕጐች /rules/ ማየት ያስፈልጋል ለዚህም ይመስላል ቁጥር 2ዐ35 /1/ ስር አንድ ሰው በሕግ ላይ በትክክል ተገልጾ የተመለከተውን ልዬ ድንጋጌ ልዬ ደንብና ስርዓት የጣሰ እንደሆነ ጥፋተኛ ነው በማለት የደነገገው በፅሑፍ ካልሆነ ግን ባለሞያ ጠርተን መሰማት የግድ ይላል፡፡
ሞያን አስመልክቶ ቁጥር 2ዐ3ዐ /2/ ስር የተቀመጠው ትክክለኛ አእምሮ /reasonable man/ ያለው ሰው ተብሎ የቀመጠው ትክክለኛ አአምሮ ያለው ባለሞያ ማለት መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም፡፡
የመጉዳት ሃሳብ ቁጥር 2ዐ32
ይህ ቁጥር ዋና መሠረተ ሀሳብ / Intention / ነው ስለሆነም አንድን ሰው በዚህ ቁጥር መሠረት ጥፋተኛ ለማድረግ ሀሳብ /Intention/ መኖሩን ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም ንዑስ ቁጥር /1/ ስር በማሰብ የሚል ቃል ሲኖር ንዑስ ቁጥር /2/ ስር ደግሞ እያወቀ የሚል ቃለ እናግኛለን፡፡ ስለሆነም የጤነኛ አአምሮ መኖርን ይጠይቃል ማለት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ቁጥር 2ዐ3ዐ /3/ ለዚህ ቁጥር አግባብንት ያለው አይመስልም፡፡
በዚህ ቁጥር ንዑስ ቁጥር 1 እና 2 ያሉ ልዩነቶችን እንመልከት፡፡ የመጀመሪያው ልዩነት ንዑስ ቁጥር /1/ ስር አንድ ሰው ሆን ብሎ ድርጊቱን የሚፈፀመው የግል ጥቅሙን ለመፈለግ አይደለም፡፡ በንዑስ ቁጥር ሁለት ስር ድርጊቱን የሚያከናውነው የራሱን ጥቅም ሲፈለግ ነው፡፡ ስለሆነም በንዑስ ቁጥር አንድ ስር ዋና አለማው የግል ጥቅም ማግኘት ሳይሆን ሌላውን መጉዳት ነው፡፡ በንዑስ ቁጥር 2 ስር ግን ዋናው ግብ የራስን ጥቅም ማግኘት ነው፡፡ ሌላው ከንዑስ ቁጥር ሁለት ጋር ተያያዞ መነሳት ያለበት ጥፋት ፈፀመ የተባለው በዚህ ንዑስ ቁጥር መሠረት ተጠያቂ ለማድረግ የደረሰው ጉዳት ከተገኘው ጥቅም ብልጫ ያለው መሆን አለበት ሌላው ነጥብ ደግሞ ጉዳቱን ያደረሰው ድርጊት በሕግ የተፈቀደ ድርጊት መሆን አለበት፡፡
በስልጣን ያለአግባብ መጠቀም ቁጥር 2ዐ33
በዚህ ቁጥር ስር ሁለት የስልጣን ዓይነቶችን እናገኛለን፡፡ አንደኛው ዓይነት ስልጣን የግለሰብ ጥቅምን ለመጠበቅ /Interest of a given private individual/ የተሰጠ ሥልጣን ሲሆን ሁለተኛው ዓይነት ደግሞ ለጠቅላላው ጥቅም እንዲያገለግል / In the interest of the public/ የተሰጠው ስልጣን ነው፡፡ ለመጀመሪያው ዓይነት ስልጣን ምሳሌ የሚሆነን በተለያየ ምክንያት ችሎታ ያጡ ሰዎችን ጥቅም ለመጠበቅ ለአሳዳሪውና ለሞግዚት የተሰጠ ስልጣን ሲሆን ለሁለተኛው ደግሞ ዳኛና ዓቃቢ ሕግ ያላቸው ስልጣን ምሳሌ ሌሆን ይችላል፡፡
እንዲሁም የትኛውም ዓይነት ስልጣን ይሆን አንድ ሰው የተሰጠውን ስልጣን ለግል ጥቅሙ የሠራበት እንደሆነ በስልጣን ያለአግባብ መጠቀም አለ እንላለን፡፡ በሁሉተኛው የስልጣን ዓይነት የመንግስት ሠራተኛው በሹመት ያገኘውን ስልጣን ለተለየ ሰው ጥቅም ካዋለውም በስልጣኑ ያለ አግባብ ተጠቅሟል ይባላል፡፡ ሁለቱም ዓይነት በስልጣን ያለ አግባብ መጠቀም ጥፋት ነው፡፡
የዚህን ቁጥር ንዑስ ቁጥር ሁለትን አስመልክቶ አንዳንደ ነጥቦችን ግልፅ እናድርግ የመጀመሪያው ግለሰቡ የመንግስት ሠራተኛ መሆን አለበት፡፡ የመንግስት ሠራተኛ ማለት በአዋጅ ቁጥር 262/1994 አንቀፅ 2/1/ ስር ከ ሀ - ሠ ያሉትን ሳይጨምር በመንግስት መሥሪያ ቤት ውሰጥ በቋሚነት ወይም በጊዜያዊነት ተቀጥሮ የሚሰራ ሰው ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ ስልጣኑ የተሰጠው ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል መሆን አለበት የስልጣኑ /Public interest/ ምንጭ ደግሞ ሹመት ወይም ሥራው / Powers conferred up on him….. by his office / መሆን አለበት፡፡
ስለ መብቶች ግብ ቁጥር /2ዐ34/
ንብረቶች ኢኮነሚያዊና ማህበራዊ ግቦች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ የአንድ ቤት ኢኮነሚያዊና ማህበራዊ ግብ የመኖሪያነት ወይም አከራይቶ ኪራይ መሰብሰብ ሊሆን ይችላል፡፡ የአንዲት ሚኒባስ ኢኮነሚያዊና ማህበራዊ ግብ ሰዎችን በማጓጓዝ ገቢ ማግኘት ሊሆን ይችላል፡፡
የቤቱ ባለቤት ቤቱን ላይኖርበት፣ ላያከራየው ቆልፎ ሊያስቀምጠው ይችላል፡፡ የሚኒባሱም ሰውዩ ሚኒባሷን ሳይጠቀምባት ሊያቆማት ይችላል፡፡ ባለንብረቶቹን ይህን ለምን አደረጋችሁ ብሎ የሚጠይቃቸው የለም፡፡ በንብረት ያለመጠቀም መብት ከንብረት መብቶች አንዱ ነውና፡፡ ለዚህ ይመስላል ቁጥር 2ዐ34 አንድ ሰው የተሰጠውን በሥራ ላይ ያዋለበት ሁኔታ ከኢኮነሚክና /የቁጠባ ዘዴ/ ከማህበራዊ አሰተዳደር ጋራ ተስማሚ አይደለም በማለት መንቀፍ አይቻልም በማለት የደነገገው፡፡
ሆኖም በዚህ ቁጥር መግቢያ ላይ ከዚህ በላይ ባሉት ቁጥሮች የተመለከቱት ደንጋጌዎች ሳይነኩ የሚል ሀሪግ አለ፡፡ ይህን ሀረግ እላይ ያስቀመጥነውን አንድ ምሳሌ በመውሰድ እናስረዳ፡፡ የትራንስፖርት እጥረት አለ አንበል፡፡ አቶ ዘበርጋ ሚኒባሱን ምንም ዓይነት ብልሽት ሳይኖርባት አቆማት አንበል አንድ ግምት መውሰድ እንችላለን፡፡ አቶ ዘበርጋ ሚኒባሷን ያቆማት ሆን ብሎ ጐዳት ለማድረስ /Injure/ ነው በማለት ነው፡፡
ሌላም ምሳሌ እንውሰድ የአዲስ አበባ ሚኒባስ ታክሲዎችና አንዳንድ ግለሰቦች ከግንቦት 1997 ዓ.ም ምርጫ ማግስት ለተወሰኑ ቀናት ሚኒባስአቸውን እንዳይሰሩ አድርገው ነበር አንዳንድ ግለቦችም ሱቅአቸውን ዘግተው ነበር በአዘቦት ቀን /Normal days/ ቢሆን ኖሮ ያ ድርጊታቸው አይነቀፍም ነበር፡፡ ግን በዛን ጊዜ ያ ድርጊት የተደረገው ሆን ብሎ ጉዳት / Intention to injure 2032/ ስለሆነ መንግስት ሥራ ካልጀመሩ የሥራ ፍቃዳቸው እንደሚነጥቃቸው አስጠነቀቃቸው፡፡ መንግስት ይህን ያደረገው የባለንብረቶቹ ድርጊት መብታቸውን በሥራ ላይ ያዋሉበት ሁኔታ ከኢኮነሚክስና ከማህበራዊ አስተዳዳር ጋራ ተስማሚ ስላልነበረ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ድርጊቶቹ የተፈፀሙት ሆን ብሎ በሌሎች ላይ ጉዳት ለማደረስ ተብሎ ስለነበረ ነው፡፡
ሕግን ስለመጣስ ቁጥር /2ዐ35/
አንድ ሰው አታድርግ የተባለውን በማድረግ / Commission / ወይም አድርግ የተባለውን ባለማድረግ / Omission / ሕግን ሊጥስ ይችላል፡፡ በዚህ ቁጥር የተጣሰው ድንጋጌ / Law / ልዩ ደንብ / decree / ወይም ስርዓት /Administrative regulations / ሊሆን ይችላል፡፡ በአማርኛውና በእንግሊዝኛው መካከል ስለሚታየው አለመጣጣም አሁን ምንም አንልም ይልቅ አንድ ሶስት ነጥቦችን እናንሳ፡፡
የመጀመሪያ የተጣሰው ሕግ /specific/ መሆን አለበት በሌለ አባባል /General/ አጠቃላይ መሆን የለበትም፡፡ ማለት ለትርጉም የተጋለጠ መሆን የለበትም፡፡ ይህን በምሳሌ እናስረዳ ይህን የምናደርገው ቁጥር 1758 እና ቁጥር 2323 በማወዳዳር ነው፡፡ ቁጥር 1758 /1/ የሚደነግገው ስለባለዕዳ ነው፡፡ ባለዕዳው ሻጭ ወይም ገዥ ሊሆን ይችላል፡፡ አካራይም ወይም ተከራይም ሊሆን ይችላል፡፡ ቁጥር 2323 ግን ስለገዥው ነው የሚደነግገው፡፡ በቁጥር 1758 ትም በቁጥር 2323 ትም ስለ አደጋ /risk/ ነው የተደነገገው ግን ቁጥር 1758 ከቁጥር 2323 ጋር ሲነፃፀር አጠቃላይ ሲሆን ቁጥር 2323 ግን ልዬ /Specific/ ነው፡፡ ስለሆነም ቁጥር 1758 ለትርጉም የተጋለጠ ነው፡፡
ሌላው ስለቁጥር 2ዐ35 ማንሳት የሚገባን ነጥብ የተጣሰው ሕግ /explicit / መሆን አለበት፡፡ /Implicit/ መሆን ይለበትም፡፡ ማለትም ግልፅ መሆን አለበት ሶስተኛ ነጥብ ደግሞ ጥፋቱ በሌሎች ከውል ውጨ አላፊነትን በሚደነግጉት ቁጥሮች የሚስተናገድ ከሆነ ቁጥር 2ዐ35 ን እንጠቀምም፡፡ በመጨረሻም ከተዋዋዩች ወገኖች መሃል አንዱ በውሉ መሠረት ግዴታውን ባይፈፀም ምንም እንኳን ግዴታውን አለመፈፀሙ ሕግን መጣስ ቢሆንም ቁጥር 2ዐ37 ሥር እንደተደነገገው አንድ ሰው በአንድ ውል ምክንያት የመጣበትን ግዴታ ሳይፈፅም በቀረ ጊዜ የውል አለመፈፀም ደንብ ብቻ ተፈፃሚ ይሆንበታል፡፡
የበላይ ትዕዛዝ ቁጥር 2ዐ36
የበላይ ትዕዛዝን አስመልክቶ ሶስት የተለያዩ መነሻዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ሁሌም ሕግን ብቻ ታዘዝ የሚለው ሲሆን ይህ ማነሻ ሁሌም ሰው ሕግን ያውቃል የሚለውን ግምት መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ይህ መነሻ በትልቋ ቢሪታኒያ ተቀባይነት አለው፡፡ ይህ መነሻ ውይይትን ስለሚጋብዝ ተግባራዊ መሆኑ /በተለይም በሠራዊቱ ውስጥ/ አጠያያቂ ነው ለማለት ይቻላል፡፡
ሁለተኛው መነሻ ደግሞ ሕግን እርሳው አለቃህን ብቻ ታዘዝ የሚል ነው፡፡ ይህ ደግሞ አለቆች ሕግን በደንብ ያውቃሉ የሚል ግምትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ /ስለሆነም አለቆች በሕጉ መሠረት ትዕዛዝ ይሰጣሎ፡፡
ይህ መነሻ በሠራዊቱ ውስጥ ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ በሰው እና በንብረት ላይ በደረሰው ስቃይና ውድመት ይህ መነሻ ተተችቷል፡፡ ምክንያቱም ወታደሮች በሰው ልጅ ላይ በዛን ጦርነት ጊዜ የደረሰውን እለቂትና ግፍ የፈፀምነው ከላይ ትዕዛዝ ስለተሰጠን ነው፡፡ በማለታቸው ነበር፡፡
ሶሰተኛው መነሻ ሕጉንም ትዕዛዙንም ታዘዝ የሚለው ነው፡፡ ይህ መነሻ ነው ቁጥር 2ዐ36 ሥር የተንፀባረቀው በዚህ ቁጥር መሠረት በመጀመሪያ ትዕዛዙን በሚሰጠውና ትዕዛዙን በሚቀበለው መሃል የአለቃና አመንዝራ ግንኙነት ሊኖር ይገባል፡፡ ይህም ግንኙነት /Superiority in authority / እንጂ /Superiority in rank/ ላይ የተመሠረቱ መሆን የለበትም፡፡ ይህን በምሳሌ እናስረዳ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ባለ አንድ ጀነራልና በፖሊስ ውስጥ ባለ አንድ ተራ ፖሊስ መሃል ያለ ግንኙነት / Superiority in rank/ እንጂ /Superiority in authority/ አይደለም፡፡ በዚህ ምሳሌ መሠረት ጀነራሉ ለፖሊሱ ትዕዝዝ ቢሰጠው ትዕዛዙ ሕግ ወጥ ይሆናል ምክንያቱም ቁጥር 2ዐ36/2/ እንደደነገገው ትዕዛዝ ሰጪው /ጀነራሉ/ ለፖሊሱ ትዕዛዝ የመስጠት ስልጣን ስለሌለው ነው፡፡
እንዲሁም አለቃው /Superiority in authority / እንኳን ቢኖረው ትዕዛዙ የአመፅ ጠባይ ካለው ትዕዛዙ አሁንም ሕግ ወጥ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም የሰጠው ትዕዛዝ አስወቃሽ ማለትም ተጠያቂነትን የሚያስከትል ከሆነ ትዕዛዙ ሕገ ወጥ ይሆናል፡፡
ለማጠቃለል ትዕዛዝ ተቀባዩ ማለት ምንዝሩ በእሱ እና ትዕዛዙን በሰጠው መሃል ያለው ግንኙነት / Superiority in rank / እንጂ / Superiority in authority /የሌለ መሆኑን እያወቀ ትዕዛዙን ተቀብሎ ተግባራዊ ካደረገ ወይም /Superiority in authority / ቢኖርም ትዕዛዙ የአመፅ ጠባይ ያለው መሆኑን ወይም አስወቃሽነቱን እያወቀ ሰርቶት እንደሆነ ትዕዛዙን ፈፃሚው ጥፋተኛ ይሆናል /2ዐ36 /2/
ቁጥር 2ዐ36 /2/ ትዕዛዙን ለተገበረ ሰው መከላከያ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ትዕዛዙን ፈፃሚው ጥብቅ በሆነ በመንግስታዊ ወይም በወታደራዊ ዲስኘሊን ምክንያት በተሰጠው ትዕዛዝ ለመከራከር ወይም ያንን የታዘዘውን እንጂ ሌላ ነገር ለማድረግ በማይችልበት ሆኔታ ውስጥ ከመገኘት የተነሳ ከሆነ ጥፋት የለበትም ስለሚል ነው፡፡
ግን ጥፋት ባይኖርበትም አላፊ ከመሆን ላይድን ይችላላ፡፡ ምክንያቱም ምንም እንኳን በአስፈላጊ ሁኔታ /Under necessity/ ስር ማለት አስገዳጅ በሆነ ሆኔታ ስር ያን ቢፈፅምም በቁጥር 2ዐ66 /1/ መሠረት አላፊ ይሆናል፡፡ ምናልባትም በቁጥር 2ዐ37/1/ መሠረትም አላፊ ማድረግ ይቻላል፡፡ ግን አንድን ሰው በአንድ በኩል ጥፋት የለበትም በሌላ በኩል ደግሞ አላፊ ማድረግ ሰሜት ላይሰጥ ይችላል፡፡ ለደረሰው ጉዳት ሌላ አማራጭ ልንፈልግ ይገባል፡፡ ምናልባት ትዕዛዝ ስጪውን በቁጥር 2ዐ35 እና በወንጀል ሕግ መሠረት ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል፡፡
የውል አለመፈፀም ቁጥር /2ዐ37/
አንድ ሰው በገባው ውል መሠረት ግዴታውን አለመፈፀሙ ከውል ውጭ አላፊነት ስር ጥፋተኛ አያስኘውም፡፡ ከሣሽ ለክሱ መሠረት ማድረግ ያለበት ስለውል አለመፈፀም የሚደነግጉትን ድንጋግዎች ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን የትኛውን /ከውል ውጨ ወይስ የውል/ ድንግጌ ነው ለክሳችን መነሻ ማድረግ ያለብን የሚለው አስቸጋሪ የሚሆንበት ሁኔታ ያጋጥመናል፡፡
ይህን በምሳሌ እናስረዳ በቁጥር 2533 መሠረት ሠራተኛው የሥራ ውል ካለቀ በኃላም ቢሆን በሥራው ጊዜ ያወቃቸውን የአሰሪውም ምስጢሮች መጠበቅ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ሠራተኛው ይህን ቁጥር ጥሶ ቢገኝ ተጠያቂ የሚሆነው በየትኛው ሕግ መሠረት ነው፡፡ በውሉ መሠረት ነው፡፡ እንዳንል ውል ተቋርጧል፡፡ ቁጥር 2ዐ35 ትን እንዳንጠቀም ደግሞ ቁጥር 2ዐ37 ይከለክለናል፡፡ ምናልባት ቀጥሉ ባለው መንገድ መከራከር እንችላለን፡፡ ውል ቢቋረጥም ሕግ ግን ሠራተኛው የአሰሪውን ሚሰጢር እንዳያወጣ ግዴታ ጥሎበታል፡፡ ስለሆነም ሠራተኛው ሚስጥሩን ቢያወጣ ግልፅ የሆነን ሕግ አንደጣሰ ተቆጥሮ በቁጥር 2ዐ35 መሠረት ተጠያቂ ልናደርገው እንችላለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ምንም እንኳን በአጠቃላይ ውል ቢቋረጥም ምስጢር ያለማውጣት ግዲታ ግን ይቆያል / Persist/ ስለሆነም ሚስጢር ሲያወጣ ያለማድረግ ግዴታን / Obligation not to do/ እንደጣሰ ተቆጥሮ በውል ሕግ ቁጥር መሠረት ተጠያቂ ልናደርግው እንችላለን፡፡