- Details
- Category: Non-Contractual Liability (Tort Law)
ሰውነትን ስለ መጉዳት ቁጥር /2038/
የኮመን ሎው አገሮች /Battery/ ይሉታል፡፡ ሲቪል ሎው አገሮች ደግሞ /Physical assault/ የሚሉት ነው፡፡ በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 14 መሠረት ማንኛውም ሰው ሰበዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት አለው፡፡ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብትን ይህን ቁጥር ማለት 2ዐ38ን እና ቀጣዩን ቁጥር ማለት ቁጥር 2ዐ4ዐ ስንወያይ እናነሳቸዋለን፡፡ እነዚህ ሐገ መንግስታዊ መብቶች ላልናቸው ቁጥሮች መሠረቶች ናቸው፡፡
ስለሆነም የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 16 እንደሚደነግገው ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ ሕገ መንግስታዊ መብት አለው፡፡ ይህ መብት በፍትሐብሔር ሕገ ቁጥር 2ዐ38 እንደተደነገገው አንድ ሰው ሳይፈቅደ ሰውነቱ ያለመነካት መብትንም ይጨምራል፡፡ ስለሆነም አንድ ሰው ሆን ብሎ ሌላው ሰው ሳይፈቅድ ሌላውን ሰው ከነካ ነኪው ጥፋተኛ ነው፡፡ ይህ ቁጥር የሚነግረን አንድ ሰው በሰውነቱ ላይ አዛዥ ራሱ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 14 ስር ለማንኛውም ሰው ሰብዓዊነት አፅንዎት የሰጠው ይህን የፍታብሔር ቁጥር አስመልክቶ አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ፡፡ የመጀመሪያው የሌላን ሰው ሰውነት የሚነካው ሰው ንኪኪውን የሚያደርገው ሆን ብሎ /Intentionally/ ነው፡፡ ሁለተኛ የተነኪው ፍላጐት የለም፡፡ ስለሆነም ነኪው የነኪውን ሰውነት ተገዶ ቢነካ ወይም በቸልተኝነት ቢነካ የተነኪው ፍላጐት በይኖርም እንኳን ጥፋተኛ አይሆንም፡፡
በተጨማሪ ደግሞ ነኪውን ጥፋተኛ ለማድረግ የተነካው ሰው ላይ ጉዳት መድረስ የለበትም፡፡ ሌላው መነሳት ያለበት ነጥብ የሌላን ሰው ሰውነት የሚነካው ሰው መንካቱን የግድ በቀጥታ ማድረግ አይጠበቅበትም እንዲሁም ድርጊቱን ለመፈፀም ሕይወት ያለው ነገር ወይም የሌለው ነገር መጠቀም ይችላል፡፡
በምሳሌ እናስረዳ ጫልቱ ዛፍ ስር ጥላ ፍለጋ ተቀምጣለች እንበል፡፡ መሐመድ ዛፋን ሆን ብሎ በማነቃነቅ የዛፍ ቅጠሎች እና ፍሬዎች በጫልቱ ላይ እንዲወድቅ ቢያደርግ በቁጥር 2ዐ38/2/ መሠረት ተጠያቂ ይሆናል፡፡ መሐመድ ጫልቱን ለመንካት እዚህ ጋ የተጠቀመው ሕይወት ያለውን ነገር ቀጥታ ባልሆነ መንገድ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አቶ ጊግሶ ውሻ አልጥኖ ውሻው የሌላን ሰውነት እንዲነካ ሆን ብሎ ቢያደርግ አቶ ጊግሶ ጥፋተኛ ይባላል እንዲሁም በሩቅ ቁጥጥር በሚደረግበት አሸንጐሊት የሌላን ሰው ያለፍላጉት መንካትም ጥፋተኛ ያደርጋል፡፡ ቀጥለን መከላከያዎችን እንመለከታለን፡፡
በቂ ምክንያት ቁጥር /2ዐ39/
በዚህ ቁጥር ስር አራት ንዑስ ቁጥሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ሀ ስር ያለው ሲሆን እንዲህ ይነበባል፡፡
“ከሣሹ በአአምሮ ግምት ሊያስበው የማይችል መሆኑ የታወቀ እንደሆነ “
ይህን በምሳሌ ለማስረዳት እንሞክር ፋጡማና ከድር የአንድ ክፍል ተማሪዎች ጓደኛሞች ናቸው እንበል፡፡ ሁለቱ ጓደኛሞች ሁልጊዜ ሲገናኙ ይጨባበጣሉ ይላፋሉ እንበል በመሃል ፋጡማ ወደ እስልምና ትምህርት የሚሰጥበት ትምህርት ቤት መሄድ በመጀመሯ ሊጋቡ የሚችሉ ወንድና ሴት ባልና ሚስት ካልሆኑ ሰውነታቸው መነካካት ይለበትም የሚል ትምህርት ተማረች እንበል፡፡ አንድ ጠዋት ከድር ከኃላዋ መጥቶ አይኗን ቢይዛትና ፋጡማ በቁጥር 2ዐ38 መሠረት ክስ ብትመሠርት ከድር ቀድሞ ከነበራቸው ግንኙነት አንፃር ፋጡማ የእሱን አድራጉት እንደምትቃወም በአእምሮው ግምት ሊያሰበው የማይችል መሆኑን ካስረዳ ጥፋተኛ መሆኑ ይቀርለታል፡፡
ሁለተኛው የመከላከያ ነጥብ አንድ ሰው የራሱን ወይም የሌላን ሰው ከአደጋ ለመከላከል ወይም በደንቡ መሠረት ንብረቱ የሆነውን ወይም በይዞታው ስር ያለን ንብረት ለመከላከል በሚደረግ ትንንቅ የሊላን ሰው ሰውነት ቢነካ ጥፋተኛ መባሉ ይቀርለታል፡፡ ለምሳሌ አንድ ጐረምሳ አንዲትን ልጅ የሐይል ጥቃት ሊያደርስባት ፈልጐ ጐረምሳውን ገላጋይ ቢይዘው ገላጋዩ ጥፋተኛ አይባልም፡፡ እንዲሁም የፍትሐብሔር ቁጥር 1148/2/ ስር እንደተደነገገው በእጁ ያደረገውን ነገር በንጥቂያ ወይም በስውር የተወሰደበት እንደሆነ ነገሩን በግፍ /በጉልበት/ ሲወሰድ ከተገኘው ወይም ይዞ ሲሸሸ ከተያዘው ነጣቂ ላይ ወዲይውኑ በጉልበት ለማስለቀቅ የተወሰደበትን ነገር ለመመለስ ስለሚችል ይህን ለማድረግ የነጣቂውን ወይም የሌላውን ሰውነት የግድ መንካት ስለሚኖር ነኪው ጥፋተኛ አይሆንም፡፡
በቁጥር 2ዐ39 /ሐ/ ስር ያለው መከላከያ በአሁኑ ጊዜ ተገቢነት ያለው አይመስለንም፡ በሁለት ምክንያት የመጀመሪያው በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 36/1//ሠ/ ስር እንደተደነገገው ህፃናት በአካላቸው ከሚፈፀም ወይም ከጭካኔና ኢሰብአዊ ከሆነ ቅጣት ነፃ የመሆን መብት አላቸው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ይህ የመከላከያ ንዑስ ቁጥር የሚያመለክተው የፍትሐብሔር ቁጥር 267/2/ ነበር፡፡ በዚህ ንዑስ ቁጥር መሠረት አሳዳጊው ቀለል ያሉ የሰውነት ቅጣቶችን አካለ መጠን ባለደረሰ ልጅ ላይ ለመፈፀም ይችላል፡፡ ሆኖም ግን የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት በህፃናት ላይ ማንኛው ዓይነት የሰውነት ቅጣት እንዳይፈፀም ይከለክላል፡፡ በተለይ እንግሊዝኛው “ To be free of corporal punishment” ይላል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የወጣውም አዲሱ የተሻሻለው የቤሰተብ ሕግም እላይ የጠቀስነውን ቁጥር 267/2/ ትን አንቀፅ 258/2/ ስር አሳዳሪው አካለመጠን ለልደረሰው ልጅ መልካም አስተዳደግ ተገቢነት ያለውን የዲስፒሊን እርምጃ ለመውሰድ ይችላል፡፡ በማለት ተክቶታል፡፡ ከዚህ ሁሉ የምንረደው በልጅ ላይ የሚፈፀም ቅጣት ጥፋት እንደሆነና መከላከያ እንደማይሆን ነው፡፡ ለልጅ ያልነው ነገር ሁሉ ለተማሪም ለአሽከርመ /ለሠራተኛ/ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ለተማሪ እና ሠራተኛ ስውነት ላይ ቅጣት መፈፀም ኢ-ሕገመንግስታዊ ስለሆነ እንደመከላከያ ሊያገለግል አይችልም፡፡
ሶስተኛው የመከላከያ ነጥብ አንድ ዕብድ በራሱ ወይም በሌላ ሰው ላይ እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል በሚደረግ ጥረት የሚፈጠር መንካት ነው፡፡ ለምሳሌ የፍትሐብሔር ቁጥር 342 ስር አንድ ሰው ዕብደቱ በግልፅ የታወቀ ነው የሚባለው አብረውት የሚኖሩት ወይም ቤተዘመዶቹ የተባለው ሰው መዘዋወር ላይ ገደብ ሲያደርጉ ነው፡፡ የዚህ ገደብ ማድረጊያ አንዱ መንገድ ዕብዱን ሰው በገመድ ማሰር ነው፡፡ ይህ ድርጊት የግድ ዕብድ የተባለው ሰው ሰውነት መንካትን ይጋብዛል፡፡ በዚህ ሁኔታ ስር ነኪው ጥፋት ሰርቷል አይባልም፡፡ አንድ ነጥብ እናክል፡፡ ይህ መንካት የሚፈቀደው አደገኛ ዕብዱን አደጋ እንዲያደርስ በሌላ አኳኃን ለመከላከል ካልተቻል ነው፡፡ ለምሳሌ ሐኪም እንዲያስተኛው ብሎም እንዲረጋጋ የሚይደርገው መድሃኒት አዞለት እያለ ያን መድሃኒት እንዲወስድ ማድረግ ሲገባን ያን ሳናደርግ ከቀረን እንደ ማለት ነው፡፡ በመጨረሻም ዕብዱ ማንኛውም ተራ ዕብድ ሳይሆን አደገኛ ዕብድ መሆን አለበት፡፡ ይህን የምናረጋግጠው አደገኛ ዕብድ ነው የተባለው ከፈፀማቸው የቀድሞ ተግባሮችና ጉዳቶች በመነሳት ወይም አዋቂ በማስመስከር ሊሆን ይችላል፡፡
የመጨረሻው መከላከያ ደግሞ ትክክለኛ አእምሮ ያለው ሰው /reasonable man/ ትክክለኛ ነው ብሎ የሚገምተው ከሆነ ድርጊቱ እንደጥፋት አይቆጠርም፡፡