- Details
- Category: Property Law
የንግድ ምልክት (Trade Mark)
የንግድ ምልክት ማለት ምን ማለት እንደሆነ የንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 501/98 በአንቀፅ 2(12) ላይ፡-
የንግድ ምልክት ማለት የአንድን ሰው ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ከሌሎች ሰዎች ወይም አገልግሎቶች ለመለየት የሚያስችል የሚታይ ምስል ነው፡፡ ምልክቱ ቃላቶችን፣ ዲዛይኖችን፣ ፊደሎችን፣ ቁጥሮችን፣ ቀለሞችን ወይም የዕቃዎችን ወይም የመያዣዎቻቸውን ቅርፅ ወይም የእነዚህኑ ቅንጅት ሊይዝ ይችላል፡፡ በማለት ሲተረጉመው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ Wikipedia the free encyclopedia
Trade mark is a distinctive sign or indicator of some kind which is used by an individual, business organization or other legal entity to identify uniquely the source of its products and/or services to consumers, and to distinguish its products or services from those of other entities.
ሲል የንግድ ምልክት ምንነትን ይገልፃል፡፡ ስለሆነም የንግድ ምልክት ማለት የአንድን ምርት ወይ አገልግሎት ወይም ምንጭ (origin) በማስመዝገብ እንደ ብቸኛ መለያ (exclusive sign) ተወስዶ ሰዎች አንድን ምርት ወይም አገልግሎት ከሌላው ምርትና አገልግሎት ለመለየት የሚያገለግል ምልክት ሆኖ ማሳከር (confusion) የማስወገድ አላማ ያለው ነው፡፡
የንግድ ምልክት ህጋዊነት የሚመሰረተው ወይም ጥበቃ የሚያገኘው በምዝገባ እንደሆነ ከአዋጁ አንቀፅ 4፣ 5፣ 15 እና 16 መረዳት የሚቻል ሲሆን Wikipedia ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ የንግድ ምልክቶች የሚባሉ እንዴት ያሉ ምልክቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ልክ በአንቀፅ 2(12) እንደተዘረዘረው፡-
A trade mark is a type of intellectual property, and typically comprises a name, word, phrase, logo, symbol, image or combination of these elements.
በማለት የንግድ ምልክቶች ምን ዓይነት ሊሆኑ እንደሚችሉ መዘርዘሩ ህጋችን የቱን ያህል አለማቀፋዊ መመዘኛዎችን (international standards) ያሟላ እንደሆነ የሚያመለክት ነው፡፡
የንግድ ምልክት አላማም ዕቃ በማምረት እና በማከፋፈል ወይም አገልግሎት በመስጠት የንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች መልካም ስም እና ዝና ለማስጠበቅና በተመሳሳይ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች መካከል መሳከር (confusion) በማስወገድ የንግድ ስራ የነፃ ገበያ ስርዓትን መርህ ተከትሎ እንዲሄድና የሸማቾችን ምርጫ ማስጠበቅም ነው:: ብሄራዊ ጥቅም በተለይም የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ስትራተጂን እውን የማድረግ አላማም ያለው ነው፡፡ በመሆኑም ጤናማ፣ ነፃ ውድድርና በእውቀት ላይ የተመሰረተ የግብይት ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ ህጉ በሚያዘውና ግልፅ በሆነ የንግድ ምልክት ላይ ተመስርቶ ማምረትና አገልግሎት መስጠት ለአንድ ህብረተሰብ እድገት ቁልፍ መሳርያ ነው፡፡ በመሆኑም በነፃ ገበያ መርህ መሰረት ጤናማ የምርትና አገልግሎት ውድድር በማካሄድ ህብረሰተቡ ሰፊ አማራጭ አግኝቶ ለከፈለው ዋጋ የሚመጥን እቃ ወይም አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ የአዋጅ ቁጥር 329/95 የንግድ አሰራር መርህን የተከተለ መሆን ይኖርበታል፡፡
የንግድ ምልክት ምዝገባ
ለምዝገባ ብቁ መሆን የሚቻለው፤-
የንግድ ምልክት የአንድን ሰው ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ከሌሎች ሰዎች ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች በግልፅ ለመለየት የሚያስችል መሆን ለመመዝገብና ህጋዊ ጥበቃ ለማግኘት አንዱ መስፈርት ነው፡፡ (አንቀፅ 5(1) )
አንድ የንግድ ምልክት በጥቁርና ነጭ ወይም በከለር ቀለም ሊመዘገብ ይችላል:: በጥቁርና ነጭ ቀለም የተመዘገበ የንግድ ምልክት በማናቸውም የቀለሞች ቅንጅት ጥበቃ የሚደረግለት ሲሆን የንግድ ምልክቱ የተመዘገበው በከለር ቀለም ከሆነ ጥበቃ የሚደረግለት በተመዘገበው የከለር ቀለም ቅንጅት ብቻ ይሆናል፡፡ (አንቀፅ 5(2) )
አንድ ሊመዘገብ የሚችል የንግድ ምልክት የምልክቱ ልዩ ባህሪ የሚቀንስ ወይም የሌላ ሰውን መብት የሚጥስ እስካልሆነ ድረስ ጥበቃ ሊደረግላቸው የማይችሉ ክፍሎችን ሊይዝ ይችላል፡፡ (አንቀፅ 5(3) )
ለምዝገባ ብቁ ስለማይሆኑ የንግድ ምልክቶች በማስመልከት አዋጁ በአንቀፅ 6 ላይ የዘረዘራቸውን ስንመለከት ደግሞ:-
በአንቀፅ 5 የተዘረዘሩትን መስፈርቶች የማያሟላ ሲሆን ምልክቱ በንግድ ምልክትነት አይመዘግብም፣
ድምፅ ወይም ሽታን የያዘ የንግድ ምልክት አይመዘገብም፣
ከሌሎች ሰዎች ዕቃዎች ወይም አገልግልቶች ለመለየት የማያስችል ከሆነ የንግድ ምልክቱ አይመዘገብም፣
የህዝቡን ሰላምና ስነ-ምግባር የሚፃረር ሲሆን እንደዚሁ አይመዘገብም ፣
የዕቃዎች ወይም የአገልግሎቶች ዓይነቶች፣ ጥራት፣ ብዛት፣ ጠቀሜታ፣ ዋጋ ወይም የመነጨበትን ቦታ፣ የተመረተበት ወይም የሚቀርብበትን ግዜ ወይም ባህሪ ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣
የንግድ ምልክቱ የሚመለከታቸው ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች በሚመለከት ወይም በኢኮኖሚያዊ ወይም የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የተለመዱና በጋራ መግባብያ ቋንቋነት የሚያገለግሉ ምልክቶች ወይም መለያዎች ብቻ የያዘ የንግድ ምልክት ሲሆን፡፡
ከዕቃው ተፈጥራዊ ሁኔታ የመነጨ ወይም የአንድን ዕቃ ቴክኒካዊ ውጤት ለማግኘት አስፈላጊ የሆነን ወይም ዕቃው ላይ ከፍተኛ ዋጋ የሚጨምርን ቅርፅ ብቻ የያዘ የንግድ ምልክት::
የዕቃዎቹ ወይም አገልግሎቶቹ የመነጩበት ቦታ ወይም ዓይነትና ባህሪ በተለመከተ ህዝቡን ወይም የንግዱን ማህበረሰብ ሊያሳሳት የሚችል የንግድ ምልክት ሲሆን፡፡
ከአሁን ቀደም በተዘጋጀ ኦፊሴላዊ ምልክት የተመዘገበ የማንኛውም ሀገር መንግሰት፣ በይነ-መንግስታዊ ድርጅት ወይም በአለም አቀፍ ስምምነት የተቋቋመ ድርጅት፣ ወታደራዊ ምልክት፣ ሰንደቅ አላማ፣ ሌላ አርማ፣ ስም፣ ምህፃረ ቃል፣ የስም አህፅሮት መሰረት ያደረገ የንግድ ምልክት ሲሆን፡፡
የአመልካቹ የቤተዘመድ ስብ ብቻ የያዘ የንግድ ምልክት
ያለ ግለሰቡ ፈቃድ የአንድን በህይወት ያለ ግለሰብ ሙሉ ስም የያዘ የንግድ ምልክት ሲሆን በህግ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንድ አመልካች እንዲመዘገብለት የሚያቀርበው ምልክት የሶስተኛ ወገን መብት የሚነካ በሚሆንበት ግዜ አይመዘገብም:: ከዚህ አኳያ ህጉ የሶስተኛ ወገኖችን መብት በመጠበቅ የንግድ ምልክት እንዳይደረግ የሚከለክልባቸው ሁኔታዎች በአንቀፅ 7 ላይ የተዘረዘሩ ሲሆን እነሱም፤
ቀደም ሲል ከተመዘገበ የንግድ ምልክት ጋር ተመሳሳይ ሲሆንና ማሳከርን (confusion) የሚፈጥር ሲሆን፤
የንግድ ምልክቱ የአንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ የሆነ የሌላ ሰው እቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በሚመለከት የንግድ ምልክት ጋር አንድ ዓይነት ወይም ሊያሳስት በሚችል ደረጃ ተመሳሳይ ከሆነ ወይም ትርጉሙን ከያዘ፤
በባለቤቱ በፅሁፍ የተሰጠ ፈቃድ ሳይኖር የንግድ ምልክት ጥበቃ የሚደረግለትን የሌላ ሰው የስነ-ፅሁፍ ወይም ኪነ-ጥበባዊ መብት ወይም የሌላ ሰውን የፎቶግራፍ ወይም የዲዛይን መብት የያዘ ነው ተብሎ ሲታመን የንግድ ምልክቱ አይመዘግብም፡፡ ያለመመዝገብ ህጋዊ ውጤት እንደሚታወቀው የህግ ጥበቃ አለማግኘትና ከህግ ጋር በሚፃረርበት ግዜ ደግሞ ለፍ/ብሄርና ወንጀል ተጠያቂነት የሚዳርግ ነው፡፡
ምዝገባ የሚያስገኘው መብት
ባስመዘገበው የንግድ ምልክት የመጠቀም ወይም ሌላ ሰው እንዲጠቀበት የመፍቀድ መብትን ያስገኛል፡፡
ሌሎች ወገኖች የንግድ ምልክቱን በሚያሳስት መንገድ እንዳይጠቀሙና ህዝቡን እንዳያሳስቱ የማድረግ መብትን ያጐናፅፋል፡፡
-
- ሌሎች ሰዎች የባለቤቱን ጥቅምን በሚጐዳ አኳኃን እንዳይገለገሉበት የማድረግ መብት ይሰጣል፡፡
- ሌሎች መሰል ድርጅቶች ተመሳሳይ ምልክት ተጠቅመው ማሳከር በመፍጠር መብቱ እንዳይጐዱ ለማገድ የሚያስችል መብት ያስገኝለታል::
- የንግድ ምልክት ማሳከር (confusion) ተፈጥሯል ባለበት ግዜ ክስ የመመስረት መብት ይኖረዋል፡፡ (አንቀፅ 26)
የአንድ የንግድ ምልክት መመዝገብ ከፍ ብለን ያየናቸውን መብቶች የሚያስገኝ ቢሆንም መብቶቹ ያለገደብ የተሰጡ አይደሉም፡፡ በመሆኑም አንቀፅ 27 በምዝገባ የተገኙ መብት ገደብን በማስመልከት የንግድ ምልክቱን በመያዝ በእቃዎቹ ምንጭ ዓይነት ለውጥ ሳይደረግባቸው በማንኛውም አገር በመሸጥ ላይ ባሉ ሶስተኛ ወገኞች ላይ የንግድ ምልክቱ ባለቤት የመከልከል መብት አይኖረውም፡፡ እንዲሁም ሶስተኛ ወገኖች በቅን ልቦና ዕቃቸውን ወይም አገልግሎታቸውን ምንጭ በማያሳስት መንገድ ለማስተዋወቅ ወይም ለመረጃ አላማ እንዳይገለገሉበት የንግድ ምልክት ባለቤቱ መከልከል አይችልም፡፡ ይህ ማለት ግን ሶስተኛ ወገኖች በነዚህ ገደቦች ሽፋን በባለመብቱ ላይ ጉዳት እዲያደርሱ ህጉ ፈቅዷል ማለት አይደለም፡፡
የንግድ ምልክት በምዝገባ መብቶችን ሲያስገኝ ገደቦች ያሉበት እንደመሆኑ ሁሉ የንግድ ምልክቱ ምዝገባ ፈራሽ የሚሆንባቸው ሁኔታዎችና የምዝገባው ፈራሽነት ውጤት ምን እንደሆነም በህጉ ሽፋን ተሰጥቶታል፡፡ ምዝገባው ፈራሽ የሚሆነው በአዋጁ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ሳያሟሉ የቀሩ እንደሆነ ምዝገባው ፈራሽ ይሆናል፡፡ እንደዚሁም ምዝገባው በከፊል ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ላይ ከሆነ ባልተመዘገቡት ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ላይ የንግድ ምልክቱ በከፊል ፈራሽ ይሆናል፡፡(አንቀፅ 36) የምዝገባው ፈራሽነት ውጤትም ውሳኔው ተፈፃሚነት የሚኖረው የንግድ ምልክቱ ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ ነው፡፡ ይህም ማለት የምዝገባው ፈራሽነት ወደ ኃላ ተመልሶ ውጤት (retroactive effect) ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ የሶስተኛ ወገኖች መብትን ለመጠበቅ የንግድ ምልክቱ ፈራሽ ስለመሆኑ በአእምሮ ንብረት ጋዜጣ ወይም ሰፊ አገራዊ ስርጭት ባለው ጋዜጣ በማውጣት እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡ በዚህ መንገድ ፈራሽ የሆነ የንግድ ምልክት ባለቤት በፈቃድ ውል ምልክቱን የሰጠው አካል ይህን የንግድ ምልክት እንዲከፍል ያደረገው ገንዘብ ቢኖርም ይመለስልኝ ብሎ መጠየቅ ግን አይችልም፡፡ ስለዚህ የንግድ ምልክት ፈራሽ መሆን ሁለት ውጤቶች ያሉት ሲሆን እነሱም ወደ ኃላ ተመልሶ የመስራትና ለምዝገባው ሲባል የተከፈለ ገንዘብ ካለም የማይመለስ መሆኑ ናቸው፡፡ (አንቀፅ 37) ከፍ ብለን የተመለከትናቸው የምዝገባ ውጤቶች ወይም መብቶች፣ ገደቦቻቸው፤ ፈራሽነትና ውጤቱን ሲሆን የንግድ ምልክት ምዝገባ ሊታደስ፣ ሊተውና በጥቅም ላይ ባለመዋሉ ምክንያት ስለሚሰረዝበትና በዚህ መብት የመጠቀም በሙሉ ወይም በከፊል መብት በመስጠት ወይም ፈቃድ በመስጠት ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ ስለሚቻልበት ስርዓትም በህጉ (በአንቀፅ 20፣ 25፣ 34፣ 35፣ 28) ላይ በዝርዝር ተደንግገው የምናገኛቸው ናቸው፡፡ የንግድ ምልክት እንደሌሎች የአእምሮ ንብረቶች የራሱ የሆነ ፀንቶ የሚቆይበት ዘመን ያለው ሲሆን አንቀፅ 24 ይህን በማስመልከት "በዚህ አዋጅ ከአንቀፅ 35 እስከ 37 የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ የንግድ ምልክት ምዝገባ ፀንቶ የሚቆየው የምዝገባው መመልከቻ ከቀረበበት ቀን ጀምሮ ለሰባት ዓመታት ይሆናል " ሲል የሚደነግግ ሲሆን አንቀፅ 35 ጥቅም ላይ ያልዋሉ የንግድ ምክቶች ስለሚሰረዙበት ሁኔታ የሚደነግግ ህግ እንደመሆኑ መጠን አንድ የተመዘገበ የንግድ ምልክት በስራ ላይ ባልዋለበት ግዜ የግድ ፀንቶ የሚቆይበት 7 ዓመት መጠበቅ ሳያስፈልግ ሊሰረዝ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ በአንቀፅ 36 እንደዚሁ አንድ የተመዘገበ የንግድ ምልክት ፈራሽ ስለሚሆንበት ሁኔታ የሚደነግግ በመሆኑ በዚህም ሁኔታ ፀንቶ የሚቆይበትን 7 ዓመት መጠበቅ አስፈላጊ ያለመሆኑን ይገልፃል፡፡ አንቀፅ 37 ስለፈራሽነት ውጤት የሚደነግግ በመሆኑ የንግድ ምልክቱ ፀንቶ ባይቀጥልም በመፍረሱ ምክንያት የሚኖረው ውጤት ወደ ኃላ ተመልሶ እንዳልተመዘገበ እንደሚቆጠርና በምዝገባው ምክንያት የተከፈለው ገንዘብ የማይመለስ ስለመሆኑ የሚደነግግ በመሆኑ የአንቀፅ 24 ሐሳብ ፀንቶ የሚቆየው ለሰባት ዓመታት ቢሆንም በመሀል ግን የንግድ ምልክቱ ምዝገባ ሊሰረዝ፣ ፈራሽ ሊሆንና የፈራሽነት ውጤት ሊኖው እንደሚችል የሚደነግግ ነው፡፡
የንግድ ምልክት ምዝገባን በማስመልከት መዝጋቢው ፅ/ቤት በሰጠው ውሳኔ ያልተስማማ ወገን በይግባይ ስልጣን ወዳለው ፍ/ቤት መሄድ ይችላል:: ስለዚህ የንግድ ምልክት ባለቤትነት መብት በሶስተኛ ወገኖች ለሚደርስ ጥሰት የፍታብሄር መፍትሄ (civil remedies) እና የወንጀል ቅጣት (criminal sanctions) በማስከተል የፍታብሄርና የወንጀል ተጠያቂነት እንዲኖር በማድረግ ህግ ከፍተኛ የአእምሮ ንብረት መብት ጥበቃ የሚያደርግለት መብት ነው፡፡(አንቀፅ 17፣ 40 እና 41)
እስከ አሁን ያየናቸውን አጠር ባለ መንገድ ለማስቀመጥ የንግድ ምልክት እንደሁሉም የአእምሮ ንብረቶች ከምዝገባ በኃላ የሚገኝ የግዙፍነት የሌለው የንብረት መብት ሆኖ በሂደት ሊሰረዝ፣ ፈራሽ ሊሆን፣ ሊተውና ሊታደስ የሚችል መብትና ግዴታ ያለበት በመጨረሻም ከ7 ዓመት በኃላ ካልታደሰ መብቱ ቀሪ የሚሆንና ህግ የፍታብሄርና የወንጀል ጥሰት እንዳይገጥመው በፍትህ ስርዓቱ ከፍተኛ የሆነ ጥበቃ ተሰጥቶት የአገር ኢኮኖሚ ጤናማ በሆነ የግብይት ስርዓት ላይ እንዲመሰረትና የሸማቶችን መብት ከማሳከር (confusion) ነፃ በሆነ መንገድ በነፃ ፍላጐት ላይ የተመሰረተ የዕቃ ወይም የአገልግሎት ምርጫ እንዲካሄድ የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት ለኢኮኖሚ ልማቱ ስኬት የግብይት ስርዓቱ የነፃ ገበያ መርህን ተከትሎ እንዲሄድ የማድረግ አለማና ግብ ያለው ነው፡፡
የመብት ጥሰት መፍትሄዎች (Remedies)
የንግድ ምልክትን መሰረት በማድረግ ክርክር በሚነሳበት ጊዜ ፍ/ቤት እና የጉምሩክ ባለስልጣን ጊዜያዊ መፍትሄዎች ሊሰጡ እንደሚችሉና ዘላቂ መፍትሄም በፍ/ቤት ሊሰጥ እንደሚችል ይኸውም የፍ/ብሄር እና የወንጀል መፍትሔ ብሎ ማስተናገድ እንደሚቻል አዋጁ በግልፅ ይደነግጋል፡፡
የፍ/ብሄር መፍትሔ
በዚህ አዋጅ መሰረት በጊዜያዊ የፍ/ብሄር መፍትሔነት የሚወስዱት ጊዜያዊ እርምጃዎች ጉዳዩ እልባት እስኪያገኝ ድረስ የሚሰጥ ጊዜያዊ እግድ (interim injuction) ሲሆን ይኸውም አዋጁ በአንቀፅ 39(4) (ሀ)ላይ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ155 (1) ከተደነገገው በተሻለና ግልፅ በሆነ መንገድ እግድ ለመስጠት አደጋ ላይ የወደቀው ጥቅም በካሳ ሊሸፍን የማይችል ሲሆን፣ አደጋው የማይቀር መሆኑ ሲረጋገጥ፣ የክሱን ጥንካሬና ውሳኔ መስጠት በእያንዳንዱ ተከራካሪ ወገን ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በመመርመር እግድን መስጠት እንደሚቻል የሚደነግግ በመሆኑ በፍ/ቤት ስልጣን ላይ ልጓም ያበጀ ነው፡፡
የሁለቱ ተከራከሪዎች አቋም ተመሳሳይ በሚሆንበት ጊዜም ፍ/ቤት ጠለቅ ያለ ምርመራ (deep investigation) ማካሄድ እንዳለበት አዋጁ በአንቀፅ 39 (4) (ሐ) ላይ ግዴታ የሚጥል በመሆኑ በዚሁ አዋጅ የሚሰጥ እግድ ስለተጠየቀ ብቻ የሚሰጥ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
የንግድ ምልክት ክርክር በሚኖርበት ጊዜ ሌላው ሊወሰድ የሚችል መፍትሔ ንብረቱ ዋስትና ተደርጐለት ለ1ዐ ቀናት በጉምሩክ ተይዞ እንዲቆይ ማድረግ ሲሆን ከሳሽ ወይም መብቴ ተጣሰ በማለት አቤቱታውን ለጉምሩክ ባለስልጣን ያመለከተ ሰው በዚያ 10 ቀን ውስጥ ከፍ/ቤት ትዕዛዝ ካላመጣ በዋስትና የተያዘው ገንዘብ ገቢ ሆኖ ንብረቱ ለሌላው ወገን ይመለስለታል:: (አንቀፅ 42(1)) የዚህ ህግ ፋይዳም ባለመብቱ የእፎይታ ጊዜ(breathing time) አግኝቶ ጉዳዮን ወደ ፍርድ ቤት እንዲያቀርብና መመዘኛዎቹን አሟልቶ ከተገኘ ከፍ/ቤት የእግድ ትዕዛዝ በማውጣት በመብቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ጊዜ መስጠት ነው፡፡ ሌላው በአዋጁ ያለ ጊዜያዊ መፍትሔ ፍ/ቤት ከንግድ ምልክት ጋር በተያያዘ ምክንያት አንደኛው ወገን መብቴ ተጥሷል በማለት ያመለከተ እንደሆነ በአንቀፅ 39(1) (ለ) እና 39(5) መሰረት ለክርክር መነሻ የሆነው ንብረት በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 161(1) (ሀ) እና በወ/ሰ/ሰ/ህ/ቁ32 መሰረት እንዲበረብርና እንዲያዝ እንዲሁም እንዲታሰር ወይም እንዲታቀብ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ለፍ/ቤቱ ስልጣን የሚሰጥ በመሆኑ አንድ የንግድ ምልክት ባለቤት መብቱ እንዲሁ እንዳይጣስ የህግ ከለላ የሚሰጠውና በዘላቂነትም በፍ/ቤት ውሳኔ መብቱን እንዲያስከብር የሚያስችል ነው፡፡ እስካሁን ያየናቸው አንድ የንግድ ምልክት ባለቤት መብቴ ተጥሷል ባለበት ጊዜ ስለሚያቀርበው ክስና ጊዜያዊ መፍትሔ:: ቀጥለን ስለሚኖሩት ዘላቂ መፍትሔዎች (Final Remedies) እናያለን፡፡
አንዱ መፍትሔ በፍ/ ቤት ከሶ ለደረሰበት ጉዳት ካሳ እንዲያገኝ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው የንግድ ምልክት ባለቤቱን መብት መጣሱ ከታወቀ በዚያ ጊዜ ውስጥ ያገኘውን ትርፍ( Account of Profit) እንዲመለስ ማድረግ ሲሆን የዚህ ዓይነቱ መፍትሔ በአፈፃፀም ላይ አንድ ህገ ወጥ ስራን የሚሰራ ሰው የንግድ ሒሳብ ደብተር ይይዛል ተብሎ ስለማይገመት ስሌቱ ለማወቅ አስቸጋሪ የሆነ የመፍትሔ አገባበ ነው፡፡ ገንዘባዊ ጥቅም ካላቸው መፍትሔ በተጨማሪ ፍ/ቤት የእንዲታወቅ ፍርድ (declaratory judgment) በመስጠት የንግድ ምልክት መብት በሶስተኛ ወገኖች እንዳይጣስ ሊያደርግ ይችላል፡፡ አዋጁ በፍ/ብሄር መፍትሔነት ያስቀመጣቸው እግድ (injuction) እና ካሳ (compensation) ሲሆኑ በአንቀፅ 40(2) ያለው የካሳ አከፋፈል ስርዓት በፍ/ብ/ህ/ቁ 2091 ከተደነገገው ጉዳት ካሳ = የጉዳት መጠን ከሚለው መርህ ማፈንገጥ (deviation) የሚስተዋልበት ነው፡፡ ይኸውም የንግድ ምልክት መጣስን ተከትሎ የሚመጣ የካሳ አከፋፈል ስርዓት መሰረቱ ጉዳት (damage) መሆኑ ቀርቶ መብት ጥሷል የተባለው ሰው መጣሱ ከተረጋገጠ በዚያ ንግድ ምልክት ጥሶ በመነገድ ያገኘውን የተጣራ ትርፍ በሙሉ እንዲከፍል በማድረግ ወይም ፈቃድ ተሰጥቶት ቢነግድ ይከፈል ከነበረው ኪራይ(royalty) የሚበልጥ እንዲከፍል በማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም ስሌቱ “Compensation equals to damage” መሆኑ ቀርቶ የዚህ አዋጅ መርህ ለየት ባለ መንገድ ስለቱ “Compensation equal to net Profit or royalty +” ነው፡፡ በመሆኑም የንግድ ምልክት አዋጅ ቁጥር 501/98 የሚከተለው የካሳ አከፋፈል ክልሰ ሓሳብ (theory) ያለአግባብ መበልፀግን the theory of unlawful enrichment ክልስ ሐሳብ ሲሆን የፍ/ብሄር ህጉ የሚከተለው የጉዳት ካሳ አከፋፈል the theory of damages ክልስ ሓሳብን የተከተለ ነው::
ከዚህ በተጨማሪ አዋጁ በአንቀፅ 40(1) ላይ ልክ በፍ/ብሄር ህጉ አንቀፅ 2121 ላይ እንደተደነገገው ዘላቂ እግድ (permanent injuction) ሊሰጥ ስለሚችልበት ሁኔታ “ ተከሳሹ የመብት መጣስን ድርጊት እንዲያቆም ሊወሰን ይችላል በማለት ስለሚደነግግ ለባለ መብቱ ከፍተኛ የአእምሮ ንብረት መብት ጥበቃ የሚሰጥ ነው፡፡
የፍ/ብሄር መፍትሔን በማስመልከት ስለሚኖሩ ጥሰቶችና መፍትሄዎቻቸው እንደተገለፀው ሆኖ የንግድ ምልክት ባለቤቱን መልካም ስምና ዝናን (reputation of honor) እንዲመለሰልት ፍ/ቤት ፍ/ብ/ህ/ቁ 2120 እና ን/ህ/ቁ/134(2) (ሀ) በሚያዙት መሰረት በማስታወቂያ እንዲወጣና ህዝቡ እንዲያውቀው እንዲደረግ ለማዘዝ ስለሚችል የንግድ ምልክቱ ባለቤት በዚህ ራሱን መልሶ ወደ ገበያው በማስገባት ለበለጠ ጥቅም ሊሰራ የሚያስችለውን ሁኔታ እንዲመቻችለት ያደርጋል፡፡
የወንጀል ቅጣት
በመጨረሻም አዋጁ የንግድ ምልክት ጥሰትን መሰረት በማድረግ የፍ/ብሄር መፍትሄዎች እንደሚደነገግ ሁሉ በአንቀፅ 41 ላይ ወንጀልን በማስመልከት የንግድ ምልክት መብት ጥሷልተብሎ የተጠረጠረው ሰው ድርጊቱ መፈፀሙ ሲረጋገጥ በወ/ህ/ቁ 720 መሰረት ሆነ ብሎ የጣሰ ከሆነ ከ5 ዓመት በማያንስና ከ15 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡ ድርጊቱን የፈፀመው በቸልተኛነት ከሆነም ከአንድ ዓመት በማያንስና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡ አንዲሁም ወንጀሉን ለመፈፀም ያገለገሉ ቁሳቁሶችና መሳሪያዎችና መብት የተጣሰባቸውን ዕቃዎች መያዝ፣ መውረስና እና ማስወገድን ያጠቃልላል ሲል ይደነግጋል፡፡ ይህ የሚያሳየው የንግድ ምልክት መጣስ የቱን ያህል እንደሚያስቀጣ ብቻ ሳይሆን ህጉ ህዝቡ በህጋዊ የንግድ ምልክት ባልተጠቀሙ ግለሰቦች እንዳይታለልና ያልሆነ ዕቃ ወይም አገልግሎት በመግዛት ሊደርስበት ከሚችል ጉዳት ለመጠበቅ የቱን ያህል ክብደት እንደሰጠ ነው:: ከዚህ ህግ በስተጀርባ ያለው ህዝባዊ ፖሊስ ስግብግብ ነጋዴዎችን ከድርጊታቻው እንዲታቀቡ በማድረግ ህ/ሰቡን የነፃና ፍትሐዊ ግብይት ስርዓት ተጠቃሚ ማድረግም ጭምር ነው::