- Details
- Category: Property Law
ይህ ዓይነት የአእምሮ ንብረት መብት ለኢትዮጵያ አዲስና ከወጣም ብዙ ዓመታትን ያላስቆጠረ መብት ነው፡፡ የዕፀዋት አዳቃዮች መብት ለማስጠበቅ የወጣው አዋጅ ቁጥር 481/98 አላማም በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ተመራማሪዎችና በልማዳዊ አሰራር ዝርያን የሚያዳቅሉ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የሰራቸው ውጤት ተጠቃሚዎች ለመሆን የሚያስችላቸውን ኢኮኖሢያዊ ጥቅም ለማስጠበቅና የቆየው የዝርያ መጠቀምና መለዋወጥ ልማዳዊ ስርዓታቸው እንዲቀጥል ለማድረግና የተሻለ ዝርያ በመጠቀም የተሻለ ምርት እንዲያመርቱ በማስቻል የልማት ስትራተጂውን ከግብ ማድረስ ነው፡፡
አዋጁ በርእስነት የተጠቀመባቸውን ሁለት ስለዕፀዋትና አዳቃዮች የሚሉትን ቃላት በትርጉም ክፍሉ አንቀፅ 2(6)” ዕፀዋት” የሚለውን ቃል” “ዕፀዋት ማለት እንሰሳ ያልሆነ እና በተፈጥሮ መራባት የሚችል ሕይወታዊ ሃብት ነው፡፡” ሲል ”አዳቃይ” ማለት
አዲስ የዕፀዋት ዝርያ አዳቅሎ ያወጣ ሰው ወይም
አዲስ የዕፀዋት ዝርያ አዳቅሎ ያወጣን ሰው ቀጥሮ ወይም ስራውን ተኮናትሮ ያሰራ ሰው ወይም በዚህ ንዑስ አንቀፅ “ ሀ ” ወይም “ ለ” የተጠቀሰ ሰው ወራሽ የሆነ ሰው ነው፡፡’
በማለት ፍቻቸውን ይሰጣል:: ከነዚህ ሁለት መብቱን የሚገልፁ ቃላት ትርጉም መረዳት የሚቻለው መብቱን ለማግኘት በማዳቀል የተገኘው ዘር አዲስ መሆን እንዳለበት፤ ሌላ ሰውን ቀጥሮ በማሰራት በሚገኘው አዲስ ዝርያ የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብትን ማግኘት እንደሚቻልና በመጨረሻም የግኝቱ ባለቤት ወራሽ መብቱን ሊያወርስ እንደሚችል ነው፡፡
በዚህ አዋጅ መሰረት አዳቃዮች የሚኖራቸው መብት ምንድ ነው? ብለን ያየን እንደሆነ በመብቱ ያለመከልከለ ወይም ከክልከላ ነፃ መሆን (Exemptions) እና ገደቦች (restrictions) እንደተጠበቁ ሆነው የዕፅዋት አዳቃዩ ሌሎች ሰዎች የተጠበቀን የተክል ዝርያ ወይም የዝሪያ አካል እንዲሸጡ፣ እንዲገዙ የመፍቀድና በማንኛውም መንገድ በሌላ ሶስተኛ ወገን የመብት ጥሰት ሲያጋጥም በመደበኛ ፍ/ቤት አቅርቦ የማስቀጣት መብቶች ናቸው ፡፡ እነዚህ መብቶች ፍፁም መብቶች (monopoly or absolute rights) ባለመሆናቸው ህጉ በአንቀፅ 6 ላይ ከክልከላ ነፃ የሆኑ ድርጊቶችን (exemptions) በዝርዝር አስቀምጧል::
በመሆኑም ለንግድ ስራ ሳይሆን ለሌላ አገልግሎት እንዲውል የማራባት፣ መዝራት ወይም መጠቀም በህግ የሚያስጠይቅ ተግባር አይደለም፡፡ ለምግብነት ወይም የዝሪያውን ማብቀል ወይም ማራባት ለሚያስከትሉ ሌሎች አገልግሎቶች እንዲውል መሸጥ አያስጠይቅም፡፡ ተተክለው በሚገኙበት ማሳ መይም በማናቸውም ሌላ ቦታ ላይ እንዳሉ መሸጥ፡፡ አዲስ ዝርያን ለማውጣት በመነሻ የተለያየነት (variety) ምንጭነት አድርጐ አንድ የተጠበቀን ዘር ወይም የዘር አካል መገልገል፡፡ በምግብነት በቤት ለመጠቀም ወይም በገበያ ለመሸጥ የተጠበቀውን ዝርያ መዝራት፡ ለቀጣይ ምርምር፣ ለትምህርት አገልግሎት ሲባል የሚደረግ ማዳቀል ከጂን ባንክ ወይም ከዕፅዋት ጀነቲክ ማዕከል ዝሪያውን ማግኘት በአዋጁ መሰረት የማያስከስሱ ግን ደግሞ ለንግድ ስራ እንዳይውሉ ለባለመብቱ ጥበቃ የሚሰጠው መብት ነው፡፡
የዕፅዋት አዳቃይ ባለቤት በመብቱ እንዳይሰራበት ሊደረግ ወይም ሊታገድ እንደሚችል በአንቀፅ 7 ላይ የተዘረዘሩ ሲሆኑ እነሱም፤
በዕፅዋት አዳቃዮች መካከል በሚደረግ ውድድር ምክንያት ችግር ሲፈጠር ወይም
ዝርያው በምግብ ዋስትና ፣ በስነ ምግብ (nutrition) ወይም ጤና ፍላጐቶች ወይም ብዝሀ ሕይወት (biological diversity) ላይ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያደርስ ሆኖ ከተገኘ
ለገበያ የሚውለው ዝሪያ አብዛኛው ከውጪ የመጣ ሲሆን ወይም
የአርሶ አደሩ ማህበረሰብ ለአንድ ለተወሰነ የተጠበቀ ዝሪያ ዘር ያለው ፍላጐት ያልተሟላ የሆነ እንደሆነ ናቸው፡፡
የዕፅዋት አዳቃይነት መብት ለማግኘት ያለው መስፈርት ምንድን ነው? አዋጁ ለዚህ መልስ የሚሰጥ ሲሆን አንድ የዘርፉ ተመራማሪ ወይም በልማዳዊ የማዳቀል ዘዴ መብቱ ይጠበቅልኝ ብሎ የሚያመለክት ሰው የዚህ መብት ባለቤት ተብሎ እውቅና በግርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር እንዲሰጠው ከተፈለገ ፤
የዕፀዋቱ ዝሪያ አዲስ መሆን ይኖርበታል ይኸውም በአዋጁ አንቀፅ 2(5) መለኪያ መሰረት ተገኘ የተባለው ዝርያ ማመልከቻው ባቀረበበት ዕለት መኖራቸው በህዝብ ከታወቁት ከሁሉም ሌሎች ዝርያዎች በግልፅ የሚለይና በተደረጉ ማራባቶች ምክንያት ዋና ዋና ባህሪያቱን ሳይለወጥ የሚቆይና በበቂ ሁኔታ ወጥ የሆነ አንድ ዓይነት ዝሪያ ወይም ተለይቶ የሚታወቅ ሕብረ-ዝሪያ (multi line) የሆነ እንደሆነና የዘር፣ ፍራፍሬ ወይም ወይን ዝሪያ በሆነበት ጊዜ ከ6 ዓመት በፊት ወይም ሌሎች ዝሪያዎችን የሚመለከት ሲሆን ማመልከቻው ከቀረበበት ዕለት 4 ዓመት በፊት ያልሸጠው ወይም ያላስተላለፈው መሆኑ ታይቶ እንደ አዲስ ዝርያ ተወስዶ ባለመብት ሊሆን ይችላል፡፡
መብቱን ለመስጠት የሚከለክል ምክንያት ከሌለ መብቱ ይሰጠዋል፡፡
መብቱ ቀደም ሲል ለሌላ ሰው ያልተሰጠ ሲሆን የሚሰጠው ይሆናል::
ቀደም ሲል የቀረበ ግን ደግሞ ያልተወሰነ ወይም ውድቅ ያልተደረገ የዕፀዋት አዳቃዮች ማመልከቻ የሌለ እንደሆነ ይታይለታል፡፡
ለመብቱ መከፈል ያለበትን ክፍያ የከፈለ እንደሆነ እውቅናው ይሰጠዋል::
ዝርያውን አዳቅሎ ለማውጣት ጥቅም ላይ የዋለን የጀነቲክ ሀብት አመልካቹ በተገቢው የአክብሮት ህግ (relevant laws on access to genetic resource) ያገኘው መሆኑ ሲረጋገጥ መብቱ ይሰጠዋል፡፡ ቀጥሎ መነሳት ያለበት ጉዳይ ይህ መብት ሊሰጥ የሚችለው ለማን ነው? የሚለው ሲሆን የዕፀዋት አዳቃዮች መብት ለኢትዮጵያዊም ሆነ የውጭ ዜጋ በአገር ውስጥ የተገኘ ይሁን በውጪ አገር መስፈርቱን ካሟላ ለአመልካቹ መብቱ ይሰጠዋል፡፡ ይኸውም በግለሰብ ደረጃ፣ በጋራ እና በድርጅት ሰም ሊሰጥ የሚችል ሲሆን እዚህ ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ሁለት የተለያዩ የዕፅዋት አዳቃዮች በተመሳሳይ ዝርያ መብቱ እንዲሰጣቸው በሚያመለክቱበት ጊዜ የቀደምትነት መብት የሚሰጠው ቀድሞ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ላመለከተው ሰው መሆኑን ነው፡፡
የዕፅዋት አዳቃይነት መብት በማስመልከት ምን ማለት እንደሆነ መብቱ ጥበቃ የሚደረግለት ለምን እንደሆነና ህጉ የሚያስቀምጣቸውን ከክልከላ ነፃ መሆን (exemptions) እና ገደቦች (restriction) እና ባለ መብት ለመሆን ያሉትን መመዘኛዎችና መብቱ ለማን ሊሰጥ እንደሚችል ተመልክተናል ቀጥለን የምናየው ደግሞ ይህ በህግ የሚቋቋም መብት እንዴት እንደሚተላለፍ፣ እንደሚተውና እንደሚሰረዝ ይሆናል፡፡ የዕፅዋት አዳቃዮች መብት በህግ ወይም በውል ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ የሚቻል ግዙፍነት የሌለው የአእምሮ የንብረት መብት ሲሆን መብቱ የሚተላለፈው በውል በሚሆንበት ጊዜ ውሉ በዕፀዋት አዳቃዮች መዝገብ ካልተመዘገብ ህጋዊ ውጤት አይኖረውም፡፡ አንድ ሰው የዕፅዋት አዳቃይነት መብት ካገኘ በኋላ ባለቤቱ በራሱ ፈቃድ መብቱን ትቻለሁ ብሎ ለሚኒስቴሩ በማመልከት መተው ይችላል፡፡ ህጉ ከዚህ ጋር ተያያዥነት ባለው መልኩ የሚደነግገው የተለየ ሁኔታ (exeption) ቢኖር በመብቱ ሳቢያ በፍ/ቤት ክስ ቀርቦበት ወይም ተከራካሪ ሆኖ ባለበት ጊዜ መብቱን ትቻለሁ ብሎ ለሚኒስቴሩ ቢያመለክትም ሚኒስቴሩ የፍ/ቤት ፈቃድ ሳያገኝ ማመልከቻውን ሊቀበል የማይችል መሆኑ ነው፡፡ የዕፅዋት አዳቃይነት መብት መሰረዝን በተመለከተ አንድ ሰው የባለቤትነት መብቱ ለሌላ ሰው በመስጠቱ ምክንያት ጥቅሜ ተነክቷል የሚል ወገን ሲያመለክት የማጣራቱ ስራ ለወደፊቱ በሚወጣው ደንብ መሰረት ተጣርቶ መብቱ ለመሰረዝ የሚያስችል ምክንያት ሲገኝ የነበረው መብት ይሰረዛል፡፡ እንደዚሁም ከተሰጠው በኋላ ዝርያው አዲስ ያለመሆኑ ሲረጋገጥ ወይም ከመስጠቱ በፊት ቢታወቅ ኖሮ አይሰጠውም ነበር የሚያሰኝ ምክንያት ሲገኝ መብቱ ይሰረዛል፡፡ ሌሎች የዕፅዋት አዳቃይነት መብት ሊያሰርዙ የሚችሉ ምክንያቶች እንደ መክፈል ያለበትን ገንዘብ የመክፈያው ቀን (due date) ከደረሰ በኋላ በ9ዐ ቀን ጊዜ ውስጥ ሳይከፍል መቅርት ወይም አንድን የተጠበቀን ዝሪያ ሳያድስ መቅረት መብቱን ሊያሰርዙ የሚችሉ ምክንያቶች በአዋጁ ተደንግገው የምናገኛቸው ናቸው፡፡
የዕፀዋት አዳቃዮች መብትን መሰረት በማድረግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 481/98 ለገበሬዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ልዩ ጥበቃ የሚሰጥ ነው::
ካመረቱት ዘር ዝርያውን ወይም የዝርያውን አካል የማስቀመጥ፣ የመለወጥ፣ የመጠቀምና የመሸጥ መብትን ይሰጣቸዋል፡፡
ከጄነቲክ ማዕከላትና የጂን ባንክ ዝርያን የማውጣትና የመጠቀም መብትንና
የተጠበቀ ዝርያን ዘርተው ካገኙት ምርት ዝርያን በጋራ የማስቀመጥ ፣ የመጠቀም፣ የማባዛትና የማዘጋጀት መብትን ይሰጣቸዋል:: ሆኖም ግን አንድን ዘር ወይም የዘርን አካል በዘር ኢንዱስትሪ ውስጥ ለንግድ በሆነ መጠን እንዲሸጡ አይፈቀድላቸውም፡፡
ይህ መብት እንደሌሎቹ የአእምሮ ንበረት መብቶች ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ በህግ የተደነገገ ሲሆን ጊዜው የመብቱ መሰረት የሆነውን ዝርያ መሰረት በማድረግ በሁለት የተከፈለ ነው:: ይሄውም መብቱ የተሰጠው ዓመታዊ ሰብሎችን መሰረት በማድረግ ከሆነ ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ ማመልከቻው ከቀረበበት ቀን አንስቶ ለቀጣይ 20 ዓመታት ነው፡፡ የመብቱ መሰረት ዛፎችን የወይን ተክሎችን ወይም ሌሎች ቋሚ ተክሎች በሚሆኑበት ጊዜ ደግሞ ይህ መብቱ ፀንቶ የሚቆየው ማመልከቻው ከቀረበበት ቀን አንስቶ ለቀጣዮቹ 25 ዓመታት ይሆናል:: ህጉ መብቱ ፀንቶ ባለበት ጊዜ የሚከሰቱ የመብት ጥሰቶችን መሰረት በማድረግ ባለ መብቶች ጉዳያቸውን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በማቅረብ በከሳሽነት፣ በተከሳሽነት ወይም በተከሳሽ ከሳሽነት ሊከራከሩና ፍርድ ቤት ካሳ ማስከፈልን ጨምሮ በቅጣት ከ6 ወር በማያንስ እስራትና ከብር አምስ ሺህ በማያንስ መቀጮ ሊቀጣ አንደሚችል የሚደነግግ ስለሆነ ለዜጐች ፈጠራ ስራ ዋስትና የሚሰጥ ነው፡፡
የዕፅዋት አዳቃዮች መብትን በማስመልከት የወጣው አዋጅ ቁጥር 481/98 በርካታ መብቶችን በማስጠበቅ ለህዝብ ጥቅም ሲባል ብቻ በመብቱ ከክልከላ ነፃ የሆኑ ሁኔታዎችንና ገዳቦችን በመዘርዘር ዜጐች ስርዓት ባለው መንገድ የግኝታቸው ባለቤትነት እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው:: ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማስጠበቅ የዘርፉ ተመራማሪዎችን በማበረታታት አገሪቱ ከዚህ የልማት አንድ አካል የሆነው ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችል ነው::
ስለዚህእስካሁን እያየናቸው የመጣን ዝርዝር ነገሮች የአእምሮ ንብረትን የሚመለከት አገራችን ከማንኛውም ጊዜ የበለጠና ዘመናዊ ህግ እንዳላት የሚያመላክትና ዜጎች በዚህ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዋስትና የሚሰጡ ናቸው :: ሆኖም ግን በአንድ አገር ፍትሓዊና ዘመናዊ ህግ መኖሩ ብቻ በራሱ ግብ ሊሆን ስለማይችል የህጎቹን አላማ ተገንዝበን ህብረተሰባዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አመረቂ ስራ በመስራቱ ሂደት የፍትህ አካላትና መላው ህ/ሰብ አበክረው ሊሰሩና ከጥሰት እነዚህን የአእምሮ ንብረቶችን አንደ ዓይን ብሌናቸው ሊንከባከቧችው ይገባል::
- Hits: 6917
- Details
- Category: Property Law
የንግድ ምልክት ማለት ምን ማለት እንደሆነ የንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 501/98 በአንቀፅ 2(12) ላይ፡-
የንግድ ምልክት ማለት የአንድን ሰው ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ከሌሎች ሰዎች ወይም አገልግሎቶች ለመለየት የሚያስችል የሚታይ ምስል ነው፡፡ ምልክቱ ቃላቶችን፣ ዲዛይኖችን፣ ፊደሎችን፣ ቁጥሮችን፣ ቀለሞችን ወይም የዕቃዎችን ወይም የመያዣዎቻቸውን ቅርፅ ወይም የእነዚህኑ ቅንጅት ሊይዝ ይችላል፡፡ በማለት ሲተረጉመው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ Wikipedia the free encyclopedia
Trade mark is a distinctive sign or indicator of some kind which is used by an individual, business organization or other legal entity to identify uniquely the source of its products and/or services to consumers, and to distinguish its products or services from those of other entities.
ሲል የንግድ ምልክት ምንነትን ይገልፃል፡፡ ስለሆነም የንግድ ምልክት ማለት የአንድን ምርት ወይ አገልግሎት ወይም ምንጭ (origin) በማስመዝገብ እንደ ብቸኛ መለያ (exclusive sign) ተወስዶ ሰዎች አንድን ምርት ወይም አገልግሎት ከሌላው ምርትና አገልግሎት ለመለየት የሚያገለግል ምልክት ሆኖ ማሳከር (confusion) የማስወገድ አላማ ያለው ነው፡፡
የንግድ ምልክት ህጋዊነት የሚመሰረተው ወይም ጥበቃ የሚያገኘው በምዝገባ እንደሆነ ከአዋጁ አንቀፅ 4፣ 5፣ 15 እና 16 መረዳት የሚቻል ሲሆን Wikipedia ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ የንግድ ምልክቶች የሚባሉ እንዴት ያሉ ምልክቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ልክ በአንቀፅ 2(12) እንደተዘረዘረው፡-
A trade mark is a type of intellectual property, and typically comprises a name, word, phrase, logo, symbol, image or combination of these elements.
በማለት የንግድ ምልክቶች ምን ዓይነት ሊሆኑ እንደሚችሉ መዘርዘሩ ህጋችን የቱን ያህል አለማቀፋዊ መመዘኛዎችን (international standards) ያሟላ እንደሆነ የሚያመለክት ነው፡፡
የንግድ ምልክት አላማም ዕቃ በማምረት እና በማከፋፈል ወይም አገልግሎት በመስጠት የንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች መልካም ስም እና ዝና ለማስጠበቅና በተመሳሳይ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች መካከል መሳከር (confusion) በማስወገድ የንግድ ስራ የነፃ ገበያ ስርዓትን መርህ ተከትሎ እንዲሄድና የሸማቾችን ምርጫ ማስጠበቅም ነው:: ብሄራዊ ጥቅም በተለይም የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ስትራተጂን እውን የማድረግ አላማም ያለው ነው፡፡ በመሆኑም ጤናማ፣ ነፃ ውድድርና በእውቀት ላይ የተመሰረተ የግብይት ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ ህጉ በሚያዘውና ግልፅ በሆነ የንግድ ምልክት ላይ ተመስርቶ ማምረትና አገልግሎት መስጠት ለአንድ ህብረተሰብ እድገት ቁልፍ መሳርያ ነው፡፡ በመሆኑም በነፃ ገበያ መርህ መሰረት ጤናማ የምርትና አገልግሎት ውድድር በማካሄድ ህብረሰተቡ ሰፊ አማራጭ አግኝቶ ለከፈለው ዋጋ የሚመጥን እቃ ወይም አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ የአዋጅ ቁጥር 329/95 የንግድ አሰራር መርህን የተከተለ መሆን ይኖርበታል፡፡
የንግድ ምልክት ምዝገባ
ለምዝገባ ብቁ መሆን የሚቻለው፤-
የንግድ ምልክት የአንድን ሰው ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ከሌሎች ሰዎች ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች በግልፅ ለመለየት የሚያስችል መሆን ለመመዝገብና ህጋዊ ጥበቃ ለማግኘት አንዱ መስፈርት ነው፡፡ (አንቀፅ 5(1) )
አንድ የንግድ ምልክት በጥቁርና ነጭ ወይም በከለር ቀለም ሊመዘገብ ይችላል:: በጥቁርና ነጭ ቀለም የተመዘገበ የንግድ ምልክት በማናቸውም የቀለሞች ቅንጅት ጥበቃ የሚደረግለት ሲሆን የንግድ ምልክቱ የተመዘገበው በከለር ቀለም ከሆነ ጥበቃ የሚደረግለት በተመዘገበው የከለር ቀለም ቅንጅት ብቻ ይሆናል፡፡ (አንቀፅ 5(2) )
አንድ ሊመዘገብ የሚችል የንግድ ምልክት የምልክቱ ልዩ ባህሪ የሚቀንስ ወይም የሌላ ሰውን መብት የሚጥስ እስካልሆነ ድረስ ጥበቃ ሊደረግላቸው የማይችሉ ክፍሎችን ሊይዝ ይችላል፡፡ (አንቀፅ 5(3) )
ለምዝገባ ብቁ ስለማይሆኑ የንግድ ምልክቶች በማስመልከት አዋጁ በአንቀፅ 6 ላይ የዘረዘራቸውን ስንመለከት ደግሞ:-
በአንቀፅ 5 የተዘረዘሩትን መስፈርቶች የማያሟላ ሲሆን ምልክቱ በንግድ ምልክትነት አይመዘግብም፣
ድምፅ ወይም ሽታን የያዘ የንግድ ምልክት አይመዘገብም፣
ከሌሎች ሰዎች ዕቃዎች ወይም አገልግልቶች ለመለየት የማያስችል ከሆነ የንግድ ምልክቱ አይመዘገብም፣
የህዝቡን ሰላምና ስነ-ምግባር የሚፃረር ሲሆን እንደዚሁ አይመዘገብም ፣
የዕቃዎች ወይም የአገልግሎቶች ዓይነቶች፣ ጥራት፣ ብዛት፣ ጠቀሜታ፣ ዋጋ ወይም የመነጨበትን ቦታ፣ የተመረተበት ወይም የሚቀርብበትን ግዜ ወይም ባህሪ ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣
የንግድ ምልክቱ የሚመለከታቸው ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች በሚመለከት ወይም በኢኮኖሚያዊ ወይም የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የተለመዱና በጋራ መግባብያ ቋንቋነት የሚያገለግሉ ምልክቶች ወይም መለያዎች ብቻ የያዘ የንግድ ምልክት ሲሆን፡፡
ከዕቃው ተፈጥራዊ ሁኔታ የመነጨ ወይም የአንድን ዕቃ ቴክኒካዊ ውጤት ለማግኘት አስፈላጊ የሆነን ወይም ዕቃው ላይ ከፍተኛ ዋጋ የሚጨምርን ቅርፅ ብቻ የያዘ የንግድ ምልክት::
የዕቃዎቹ ወይም አገልግሎቶቹ የመነጩበት ቦታ ወይም ዓይነትና ባህሪ በተለመከተ ህዝቡን ወይም የንግዱን ማህበረሰብ ሊያሳሳት የሚችል የንግድ ምልክት ሲሆን፡፡
ከአሁን ቀደም በተዘጋጀ ኦፊሴላዊ ምልክት የተመዘገበ የማንኛውም ሀገር መንግሰት፣ በይነ-መንግስታዊ ድርጅት ወይም በአለም አቀፍ ስምምነት የተቋቋመ ድርጅት፣ ወታደራዊ ምልክት፣ ሰንደቅ አላማ፣ ሌላ አርማ፣ ስም፣ ምህፃረ ቃል፣ የስም አህፅሮት መሰረት ያደረገ የንግድ ምልክት ሲሆን፡፡
የአመልካቹ የቤተዘመድ ስብ ብቻ የያዘ የንግድ ምልክት
ያለ ግለሰቡ ፈቃድ የአንድን በህይወት ያለ ግለሰብ ሙሉ ስም የያዘ የንግድ ምልክት ሲሆን በህግ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንድ አመልካች እንዲመዘገብለት የሚያቀርበው ምልክት የሶስተኛ ወገን መብት የሚነካ በሚሆንበት ግዜ አይመዘገብም:: ከዚህ አኳያ ህጉ የሶስተኛ ወገኖችን መብት በመጠበቅ የንግድ ምልክት እንዳይደረግ የሚከለክልባቸው ሁኔታዎች በአንቀፅ 7 ላይ የተዘረዘሩ ሲሆን እነሱም፤
ቀደም ሲል ከተመዘገበ የንግድ ምልክት ጋር ተመሳሳይ ሲሆንና ማሳከርን (confusion) የሚፈጥር ሲሆን፤
የንግድ ምልክቱ የአንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ የሆነ የሌላ ሰው እቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በሚመለከት የንግድ ምልክት ጋር አንድ ዓይነት ወይም ሊያሳስት በሚችል ደረጃ ተመሳሳይ ከሆነ ወይም ትርጉሙን ከያዘ፤
በባለቤቱ በፅሁፍ የተሰጠ ፈቃድ ሳይኖር የንግድ ምልክት ጥበቃ የሚደረግለትን የሌላ ሰው የስነ-ፅሁፍ ወይም ኪነ-ጥበባዊ መብት ወይም የሌላ ሰውን የፎቶግራፍ ወይም የዲዛይን መብት የያዘ ነው ተብሎ ሲታመን የንግድ ምልክቱ አይመዘግብም፡፡ ያለመመዝገብ ህጋዊ ውጤት እንደሚታወቀው የህግ ጥበቃ አለማግኘትና ከህግ ጋር በሚፃረርበት ግዜ ደግሞ ለፍ/ብሄርና ወንጀል ተጠያቂነት የሚዳርግ ነው፡፡
ምዝገባ የሚያስገኘው መብት
ባስመዘገበው የንግድ ምልክት የመጠቀም ወይም ሌላ ሰው እንዲጠቀበት የመፍቀድ መብትን ያስገኛል፡፡
ሌሎች ወገኖች የንግድ ምልክቱን በሚያሳስት መንገድ እንዳይጠቀሙና ህዝቡን እንዳያሳስቱ የማድረግ መብትን ያጐናፅፋል፡፡
-
- ሌሎች ሰዎች የባለቤቱን ጥቅምን በሚጐዳ አኳኃን እንዳይገለገሉበት የማድረግ መብት ይሰጣል፡፡
- ሌሎች መሰል ድርጅቶች ተመሳሳይ ምልክት ተጠቅመው ማሳከር በመፍጠር መብቱ እንዳይጐዱ ለማገድ የሚያስችል መብት ያስገኝለታል::
- የንግድ ምልክት ማሳከር (confusion) ተፈጥሯል ባለበት ግዜ ክስ የመመስረት መብት ይኖረዋል፡፡ (አንቀፅ 26)
የአንድ የንግድ ምልክት መመዝገብ ከፍ ብለን ያየናቸውን መብቶች የሚያስገኝ ቢሆንም መብቶቹ ያለገደብ የተሰጡ አይደሉም፡፡ በመሆኑም አንቀፅ 27 በምዝገባ የተገኙ መብት ገደብን በማስመልከት የንግድ ምልክቱን በመያዝ በእቃዎቹ ምንጭ ዓይነት ለውጥ ሳይደረግባቸው በማንኛውም አገር በመሸጥ ላይ ባሉ ሶስተኛ ወገኞች ላይ የንግድ ምልክቱ ባለቤት የመከልከል መብት አይኖረውም፡፡ እንዲሁም ሶስተኛ ወገኖች በቅን ልቦና ዕቃቸውን ወይም አገልግሎታቸውን ምንጭ በማያሳስት መንገድ ለማስተዋወቅ ወይም ለመረጃ አላማ እንዳይገለገሉበት የንግድ ምልክት ባለቤቱ መከልከል አይችልም፡፡ ይህ ማለት ግን ሶስተኛ ወገኖች በነዚህ ገደቦች ሽፋን በባለመብቱ ላይ ጉዳት እዲያደርሱ ህጉ ፈቅዷል ማለት አይደለም፡፡
የንግድ ምልክት በምዝገባ መብቶችን ሲያስገኝ ገደቦች ያሉበት እንደመሆኑ ሁሉ የንግድ ምልክቱ ምዝገባ ፈራሽ የሚሆንባቸው ሁኔታዎችና የምዝገባው ፈራሽነት ውጤት ምን እንደሆነም በህጉ ሽፋን ተሰጥቶታል፡፡ ምዝገባው ፈራሽ የሚሆነው በአዋጁ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ሳያሟሉ የቀሩ እንደሆነ ምዝገባው ፈራሽ ይሆናል፡፡ እንደዚሁም ምዝገባው በከፊል ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ላይ ከሆነ ባልተመዘገቡት ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ላይ የንግድ ምልክቱ በከፊል ፈራሽ ይሆናል፡፡(አንቀፅ 36) የምዝገባው ፈራሽነት ውጤትም ውሳኔው ተፈፃሚነት የሚኖረው የንግድ ምልክቱ ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ ነው፡፡ ይህም ማለት የምዝገባው ፈራሽነት ወደ ኃላ ተመልሶ ውጤት (retroactive effect) ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ የሶስተኛ ወገኖች መብትን ለመጠበቅ የንግድ ምልክቱ ፈራሽ ስለመሆኑ በአእምሮ ንብረት ጋዜጣ ወይም ሰፊ አገራዊ ስርጭት ባለው ጋዜጣ በማውጣት እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡ በዚህ መንገድ ፈራሽ የሆነ የንግድ ምልክት ባለቤት በፈቃድ ውል ምልክቱን የሰጠው አካል ይህን የንግድ ምልክት እንዲከፍል ያደረገው ገንዘብ ቢኖርም ይመለስልኝ ብሎ መጠየቅ ግን አይችልም፡፡ ስለዚህ የንግድ ምልክት ፈራሽ መሆን ሁለት ውጤቶች ያሉት ሲሆን እነሱም ወደ ኃላ ተመልሶ የመስራትና ለምዝገባው ሲባል የተከፈለ ገንዘብ ካለም የማይመለስ መሆኑ ናቸው፡፡ (አንቀፅ 37) ከፍ ብለን የተመለከትናቸው የምዝገባ ውጤቶች ወይም መብቶች፣ ገደቦቻቸው፤ ፈራሽነትና ውጤቱን ሲሆን የንግድ ምልክት ምዝገባ ሊታደስ፣ ሊተውና በጥቅም ላይ ባለመዋሉ ምክንያት ስለሚሰረዝበትና በዚህ መብት የመጠቀም በሙሉ ወይም በከፊል መብት በመስጠት ወይም ፈቃድ በመስጠት ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ ስለሚቻልበት ስርዓትም በህጉ (በአንቀፅ 20፣ 25፣ 34፣ 35፣ 28) ላይ በዝርዝር ተደንግገው የምናገኛቸው ናቸው፡፡ የንግድ ምልክት እንደሌሎች የአእምሮ ንብረቶች የራሱ የሆነ ፀንቶ የሚቆይበት ዘመን ያለው ሲሆን አንቀፅ 24 ይህን በማስመልከት "በዚህ አዋጅ ከአንቀፅ 35 እስከ 37 የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ የንግድ ምልክት ምዝገባ ፀንቶ የሚቆየው የምዝገባው መመልከቻ ከቀረበበት ቀን ጀምሮ ለሰባት ዓመታት ይሆናል " ሲል የሚደነግግ ሲሆን አንቀፅ 35 ጥቅም ላይ ያልዋሉ የንግድ ምክቶች ስለሚሰረዙበት ሁኔታ የሚደነግግ ህግ እንደመሆኑ መጠን አንድ የተመዘገበ የንግድ ምልክት በስራ ላይ ባልዋለበት ግዜ የግድ ፀንቶ የሚቆይበት 7 ዓመት መጠበቅ ሳያስፈልግ ሊሰረዝ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ በአንቀፅ 36 እንደዚሁ አንድ የተመዘገበ የንግድ ምልክት ፈራሽ ስለሚሆንበት ሁኔታ የሚደነግግ በመሆኑ በዚህም ሁኔታ ፀንቶ የሚቆይበትን 7 ዓመት መጠበቅ አስፈላጊ ያለመሆኑን ይገልፃል፡፡ አንቀፅ 37 ስለፈራሽነት ውጤት የሚደነግግ በመሆኑ የንግድ ምልክቱ ፀንቶ ባይቀጥልም በመፍረሱ ምክንያት የሚኖረው ውጤት ወደ ኃላ ተመልሶ እንዳልተመዘገበ እንደሚቆጠርና በምዝገባው ምክንያት የተከፈለው ገንዘብ የማይመለስ ስለመሆኑ የሚደነግግ በመሆኑ የአንቀፅ 24 ሐሳብ ፀንቶ የሚቆየው ለሰባት ዓመታት ቢሆንም በመሀል ግን የንግድ ምልክቱ ምዝገባ ሊሰረዝ፣ ፈራሽ ሊሆንና የፈራሽነት ውጤት ሊኖው እንደሚችል የሚደነግግ ነው፡፡
የንግድ ምልክት ምዝገባን በማስመልከት መዝጋቢው ፅ/ቤት በሰጠው ውሳኔ ያልተስማማ ወገን በይግባይ ስልጣን ወዳለው ፍ/ቤት መሄድ ይችላል:: ስለዚህ የንግድ ምልክት ባለቤትነት መብት በሶስተኛ ወገኖች ለሚደርስ ጥሰት የፍታብሄር መፍትሄ (civil remedies) እና የወንጀል ቅጣት (criminal sanctions) በማስከተል የፍታብሄርና የወንጀል ተጠያቂነት እንዲኖር በማድረግ ህግ ከፍተኛ የአእምሮ ንብረት መብት ጥበቃ የሚያደርግለት መብት ነው፡፡(አንቀፅ 17፣ 40 እና 41)
እስከ አሁን ያየናቸውን አጠር ባለ መንገድ ለማስቀመጥ የንግድ ምልክት እንደሁሉም የአእምሮ ንብረቶች ከምዝገባ በኃላ የሚገኝ የግዙፍነት የሌለው የንብረት መብት ሆኖ በሂደት ሊሰረዝ፣ ፈራሽ ሊሆን፣ ሊተውና ሊታደስ የሚችል መብትና ግዴታ ያለበት በመጨረሻም ከ7 ዓመት በኃላ ካልታደሰ መብቱ ቀሪ የሚሆንና ህግ የፍታብሄርና የወንጀል ጥሰት እንዳይገጥመው በፍትህ ስርዓቱ ከፍተኛ የሆነ ጥበቃ ተሰጥቶት የአገር ኢኮኖሚ ጤናማ በሆነ የግብይት ስርዓት ላይ እንዲመሰረትና የሸማቶችን መብት ከማሳከር (confusion) ነፃ በሆነ መንገድ በነፃ ፍላጐት ላይ የተመሰረተ የዕቃ ወይም የአገልግሎት ምርጫ እንዲካሄድ የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት ለኢኮኖሚ ልማቱ ስኬት የግብይት ስርዓቱ የነፃ ገበያ መርህን ተከትሎ እንዲሄድ የማድረግ አለማና ግብ ያለው ነው፡፡
የመብት ጥሰት መፍትሄዎች (Remedies)
የንግድ ምልክትን መሰረት በማድረግ ክርክር በሚነሳበት ጊዜ ፍ/ቤት እና የጉምሩክ ባለስልጣን ጊዜያዊ መፍትሄዎች ሊሰጡ እንደሚችሉና ዘላቂ መፍትሄም በፍ/ቤት ሊሰጥ እንደሚችል ይኸውም የፍ/ብሄር እና የወንጀል መፍትሔ ብሎ ማስተናገድ እንደሚቻል አዋጁ በግልፅ ይደነግጋል፡፡
የፍ/ብሄር መፍትሔ
በዚህ አዋጅ መሰረት በጊዜያዊ የፍ/ብሄር መፍትሔነት የሚወስዱት ጊዜያዊ እርምጃዎች ጉዳዩ እልባት እስኪያገኝ ድረስ የሚሰጥ ጊዜያዊ እግድ (interim injuction) ሲሆን ይኸውም አዋጁ በአንቀፅ 39(4) (ሀ)ላይ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ155 (1) ከተደነገገው በተሻለና ግልፅ በሆነ መንገድ እግድ ለመስጠት አደጋ ላይ የወደቀው ጥቅም በካሳ ሊሸፍን የማይችል ሲሆን፣ አደጋው የማይቀር መሆኑ ሲረጋገጥ፣ የክሱን ጥንካሬና ውሳኔ መስጠት በእያንዳንዱ ተከራካሪ ወገን ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በመመርመር እግድን መስጠት እንደሚቻል የሚደነግግ በመሆኑ በፍ/ቤት ስልጣን ላይ ልጓም ያበጀ ነው፡፡
የሁለቱ ተከራከሪዎች አቋም ተመሳሳይ በሚሆንበት ጊዜም ፍ/ቤት ጠለቅ ያለ ምርመራ (deep investigation) ማካሄድ እንዳለበት አዋጁ በአንቀፅ 39 (4) (ሐ) ላይ ግዴታ የሚጥል በመሆኑ በዚሁ አዋጅ የሚሰጥ እግድ ስለተጠየቀ ብቻ የሚሰጥ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
የንግድ ምልክት ክርክር በሚኖርበት ጊዜ ሌላው ሊወሰድ የሚችል መፍትሔ ንብረቱ ዋስትና ተደርጐለት ለ1ዐ ቀናት በጉምሩክ ተይዞ እንዲቆይ ማድረግ ሲሆን ከሳሽ ወይም መብቴ ተጣሰ በማለት አቤቱታውን ለጉምሩክ ባለስልጣን ያመለከተ ሰው በዚያ 10 ቀን ውስጥ ከፍ/ቤት ትዕዛዝ ካላመጣ በዋስትና የተያዘው ገንዘብ ገቢ ሆኖ ንብረቱ ለሌላው ወገን ይመለስለታል:: (አንቀፅ 42(1)) የዚህ ህግ ፋይዳም ባለመብቱ የእፎይታ ጊዜ(breathing time) አግኝቶ ጉዳዮን ወደ ፍርድ ቤት እንዲያቀርብና መመዘኛዎቹን አሟልቶ ከተገኘ ከፍ/ቤት የእግድ ትዕዛዝ በማውጣት በመብቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ጊዜ መስጠት ነው፡፡ ሌላው በአዋጁ ያለ ጊዜያዊ መፍትሔ ፍ/ቤት ከንግድ ምልክት ጋር በተያያዘ ምክንያት አንደኛው ወገን መብቴ ተጥሷል በማለት ያመለከተ እንደሆነ በአንቀፅ 39(1) (ለ) እና 39(5) መሰረት ለክርክር መነሻ የሆነው ንብረት በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 161(1) (ሀ) እና በወ/ሰ/ሰ/ህ/ቁ32 መሰረት እንዲበረብርና እንዲያዝ እንዲሁም እንዲታሰር ወይም እንዲታቀብ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ለፍ/ቤቱ ስልጣን የሚሰጥ በመሆኑ አንድ የንግድ ምልክት ባለቤት መብቱ እንዲሁ እንዳይጣስ የህግ ከለላ የሚሰጠውና በዘላቂነትም በፍ/ቤት ውሳኔ መብቱን እንዲያስከብር የሚያስችል ነው፡፡ እስካሁን ያየናቸው አንድ የንግድ ምልክት ባለቤት መብቴ ተጥሷል ባለበት ጊዜ ስለሚያቀርበው ክስና ጊዜያዊ መፍትሔ:: ቀጥለን ስለሚኖሩት ዘላቂ መፍትሔዎች (Final Remedies) እናያለን፡፡
አንዱ መፍትሔ በፍ/ ቤት ከሶ ለደረሰበት ጉዳት ካሳ እንዲያገኝ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው የንግድ ምልክት ባለቤቱን መብት መጣሱ ከታወቀ በዚያ ጊዜ ውስጥ ያገኘውን ትርፍ( Account of Profit) እንዲመለስ ማድረግ ሲሆን የዚህ ዓይነቱ መፍትሔ በአፈፃፀም ላይ አንድ ህገ ወጥ ስራን የሚሰራ ሰው የንግድ ሒሳብ ደብተር ይይዛል ተብሎ ስለማይገመት ስሌቱ ለማወቅ አስቸጋሪ የሆነ የመፍትሔ አገባበ ነው፡፡ ገንዘባዊ ጥቅም ካላቸው መፍትሔ በተጨማሪ ፍ/ቤት የእንዲታወቅ ፍርድ (declaratory judgment) በመስጠት የንግድ ምልክት መብት በሶስተኛ ወገኖች እንዳይጣስ ሊያደርግ ይችላል፡፡ አዋጁ በፍ/ብሄር መፍትሔነት ያስቀመጣቸው እግድ (injuction) እና ካሳ (compensation) ሲሆኑ በአንቀፅ 40(2) ያለው የካሳ አከፋፈል ስርዓት በፍ/ብ/ህ/ቁ 2091 ከተደነገገው ጉዳት ካሳ = የጉዳት መጠን ከሚለው መርህ ማፈንገጥ (deviation) የሚስተዋልበት ነው፡፡ ይኸውም የንግድ ምልክት መጣስን ተከትሎ የሚመጣ የካሳ አከፋፈል ስርዓት መሰረቱ ጉዳት (damage) መሆኑ ቀርቶ መብት ጥሷል የተባለው ሰው መጣሱ ከተረጋገጠ በዚያ ንግድ ምልክት ጥሶ በመነገድ ያገኘውን የተጣራ ትርፍ በሙሉ እንዲከፍል በማድረግ ወይም ፈቃድ ተሰጥቶት ቢነግድ ይከፈል ከነበረው ኪራይ(royalty) የሚበልጥ እንዲከፍል በማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም ስሌቱ “Compensation equals to damage” መሆኑ ቀርቶ የዚህ አዋጅ መርህ ለየት ባለ መንገድ ስለቱ “Compensation equal to net Profit or royalty +” ነው፡፡ በመሆኑም የንግድ ምልክት አዋጅ ቁጥር 501/98 የሚከተለው የካሳ አከፋፈል ክልሰ ሓሳብ (theory) ያለአግባብ መበልፀግን the theory of unlawful enrichment ክልስ ሐሳብ ሲሆን የፍ/ብሄር ህጉ የሚከተለው የጉዳት ካሳ አከፋፈል the theory of damages ክልስ ሓሳብን የተከተለ ነው::
ከዚህ በተጨማሪ አዋጁ በአንቀፅ 40(1) ላይ ልክ በፍ/ብሄር ህጉ አንቀፅ 2121 ላይ እንደተደነገገው ዘላቂ እግድ (permanent injuction) ሊሰጥ ስለሚችልበት ሁኔታ “ ተከሳሹ የመብት መጣስን ድርጊት እንዲያቆም ሊወሰን ይችላል በማለት ስለሚደነግግ ለባለ መብቱ ከፍተኛ የአእምሮ ንብረት መብት ጥበቃ የሚሰጥ ነው፡፡
የፍ/ብሄር መፍትሔን በማስመልከት ስለሚኖሩ ጥሰቶችና መፍትሄዎቻቸው እንደተገለፀው ሆኖ የንግድ ምልክት ባለቤቱን መልካም ስምና ዝናን (reputation of honor) እንዲመለሰልት ፍ/ቤት ፍ/ብ/ህ/ቁ 2120 እና ን/ህ/ቁ/134(2) (ሀ) በሚያዙት መሰረት በማስታወቂያ እንዲወጣና ህዝቡ እንዲያውቀው እንዲደረግ ለማዘዝ ስለሚችል የንግድ ምልክቱ ባለቤት በዚህ ራሱን መልሶ ወደ ገበያው በማስገባት ለበለጠ ጥቅም ሊሰራ የሚያስችለውን ሁኔታ እንዲመቻችለት ያደርጋል፡፡
የወንጀል ቅጣት
በመጨረሻም አዋጁ የንግድ ምልክት ጥሰትን መሰረት በማድረግ የፍ/ብሄር መፍትሄዎች እንደሚደነገግ ሁሉ በአንቀፅ 41 ላይ ወንጀልን በማስመልከት የንግድ ምልክት መብት ጥሷልተብሎ የተጠረጠረው ሰው ድርጊቱ መፈፀሙ ሲረጋገጥ በወ/ህ/ቁ 720 መሰረት ሆነ ብሎ የጣሰ ከሆነ ከ5 ዓመት በማያንስና ከ15 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡ ድርጊቱን የፈፀመው በቸልተኛነት ከሆነም ከአንድ ዓመት በማያንስና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡ አንዲሁም ወንጀሉን ለመፈፀም ያገለገሉ ቁሳቁሶችና መሳሪያዎችና መብት የተጣሰባቸውን ዕቃዎች መያዝ፣ መውረስና እና ማስወገድን ያጠቃልላል ሲል ይደነግጋል፡፡ ይህ የሚያሳየው የንግድ ምልክት መጣስ የቱን ያህል እንደሚያስቀጣ ብቻ ሳይሆን ህጉ ህዝቡ በህጋዊ የንግድ ምልክት ባልተጠቀሙ ግለሰቦች እንዳይታለልና ያልሆነ ዕቃ ወይም አገልግሎት በመግዛት ሊደርስበት ከሚችል ጉዳት ለመጠበቅ የቱን ያህል ክብደት እንደሰጠ ነው:: ከዚህ ህግ በስተጀርባ ያለው ህዝባዊ ፖሊስ ስግብግብ ነጋዴዎችን ከድርጊታቻው እንዲታቀቡ በማድረግ ህ/ሰቡን የነፃና ፍትሐዊ ግብይት ስርዓት ተጠቃሚ ማድረግም ጭምር ነው::
- Hits: 11568
- Details
- Category: Property Law
የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን በማስመልከት የወጣው አዋጅ ቁጥር 410/96 በአንቀፅ 2(8) ላይ "የቅጅ መብት ማለት ከአንድ ስራ የሚመነጭ የኢኮኖሚ መብት ሲሆን አግባብነት ባለው ጊዜ የሞራል መብቶችን ይጨምራል" በማለት ሲተረጉመው ተዛማጅ መብት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ደግሞ በአንቀፅ 2(14) ላይ " ተዛማጅ መብት ማለት ከዋኝ፣ የድምፅ ሪከርዲንግ ፕሮዲሰር፣ የብሮድካስቲንግ ድርጅት በስራው ላይ ያለው መብት ነው" በማለት ገልፆታል፡፡ እውቁ Wikipedia free encyclopedia በበኩሉ
Generally it is "the right to copy", but also gives the copy right holder the right to be credited for the work, to determine who may adapt the work to other forms, who may perform the work, who may financially benefit from it, and others.
በማለት የቅጂ መብት ለአእምሮ ንብረት ባለቤት የሚያስገኘውን መብት ሰፋ ባለመልኩ ተርጉሞት እናገኛለን፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋለ ያለብን ነገር የቅጂ መብት ሽፋን የሚሰጠው ሃሳብን (ideas) እና መረጃን (information) ሳይሆን የህግ ጥበቃ የሚሰጠው የቅጂውን መብት መሰረት በማድረግ ስለሆነ ጥበቃው ለሃሳቡና ለመረጃው ሳይሆን ለአፃፃፍ ቅርፅ (forms) ወይም አገባብ (manner) መሆኑን ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ የቀጅ መብት ተኩረት የሚያደርገውና ሽፋን የሚሰጠው ለሀሳቡ አገላለፅ አንጂ ሀሳቡ አንዳይጣስ ማድረግ አይደለም:: Copy right usually protects the expression of an idea not the idea itself. Thus, copy right does not prohibit a reader from freely using and describing that concept to others, it is only the particular expression of that process as originally described that is covered by copy right.
የቅጅና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ አላማ በአገራችን ያለውን የስነ-ፅሁፍ፣ የኪነ ጥበብ እና ሌሎች ተመሳሳይ የፈጠራ ስራዎች የህግ ጥበቃ እንዲያገኙ በማድረግ የአገራችንን ባህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሳይንሳዊና ቴክኒኖሎጂያዊ እድገት በማፋጠን አገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ማስቻል ነው፡፡ ይህን አብይ አላማ መሰረት በማድረግ አዋጁ ከአሁን ቀደም በፍታብሄር ህጉ ከቁጥር 1647- 1674 ባሉ ህጎች ለቅጅ መብት ተሰጥቶ የነበረን የጥበቃ ሽፋን በማስፋት አዳዲስ መሰረተ ሃሳቦችና መብቶች እንዲካተት ያደረገ ነው:: የማስተላለፍያ መንገዶቹ (transferability) እንዲሰፋ በማድረግ ተገቢ የሆነ ጥበቃ እንዲያገኙና ዋስትና አግኝተው ባለሙያዎቹ በልበ ሙሉነት እንዲሰሩ የማስቻል አላማን በመያዝ የወጣና በስራ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ከማንኛውም ግዜ በላይ በአደረጃጀትና አሰራር ተጠናክሮ በመሄድ ላይ ያለ የአእምሮ ንብረት መብት ጥበቃ ዘርፍ ነው፡፡ በቅጂ መብት ሽፋን የሚሰጣቸውን የአእምሮ ንብረቶች በማስመልከት Wikipedia ላይ ያየን እንደሆነ ፤
copy right may apply to a wide range of creative, intellectual, or artistic forms or "works" . . . can include, poems, theses, plays, other literacy works, moves, dances, musical composition, audio recordings, drawings, sculptures, photographs, software, radio and television broadcasts, and industrial designs, graphic designs.
በማለት የቅጅ መብት ጥበቃ የሚያገኙ ስራዎችን በመዘርዘር ሲያሰፍር በአገራችን የወጣው አዋጅ ቁጥር 410/96 ከዚህ ጋር በተቀራረበ መልኩ ጥበቃ ስለሚደረግላቸው የቅጅ መብት ማስገኛ ስራዎች በአንቀፅ 4(1) (ሀ) (ለ) ላይ የሚከሉት ፈጠራ ስራ ጥበቃ ይደረግላቸዋል በሚል ስር፤
ትርጉም፣ የማመሳሰል ስራ፣ ቅንብርና ሌላ የስራውን ዓይነት የሚቀይር ወይም የሚያሻሻል ስራ ወይም
በይዘት፣ በቅንብር፣ ወይም በአመራረጥ የተነሳ ኦርጅናል የሆነና በሚነበብ መሳርያ ወይም በሌላ መልክ ያለ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ የቅኔ ስብስብ ወይም ዳታቤዝን የመሳሰለ የስብስብ ስራ፡፡
በማለት የሽፋን አድማሱን ሲገልፅ የህግ ጥበቃ ለማግኘት ስለሚኖረው መስፈርት በማስመልከት ደግሞ በአንቀፅ 6(1) ላይ ማንኛውም የስራ አመንጪ የስራው አላማና ጥራት ከግምት ስውጥ ሳይገባ የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብት ሊያገኝ የሚችለው ስራው ወጥ ወይም ኦርጅናል ከሆነ፣ ከተቀረፀ ወይም ግዙፍነት ካገኘ ስራውን በማውጣት ምክንያት ብቻ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥበቃ እንደሚያገኝ ሲደነግግ ስራው የፎቶ ግራፍ ስራ በሚሆንበት ግዜ ደግሞ ከፍ ብለው ከተገለፁት መስፈርቶ በተጨማሪ ስራው የአንድ ስብስብ አካል ሲሆን ወይም በመፅሓፍ መልክ ሲታተሙ ወይም የስራ አመንጪውን ወይም ወኪሉን ስምና አድራሻ ሲይዙ እንደሆነ በአንቀፅ 6(2) (ሀ) (ለ) ላይ በግልፅ ሰፍሯል፡፡ ስለሆነም በአገራችን የአንድን ስራ ቅጂ መብት ለማግኘት የተጠቀመበት የአፃፃፍ ወይም የፎቶ አነሳስ ወይም የዘገባ ስርጭት ቅርፅ (form) ወይም አግባብ (manner) ኦርጅናል መሆንንና ስራዎቹ የፎቶና የብሮድካስቲን በሚሆኑበት ግዜ ደግሞ ኦጅናል ከመሆን በተጨማሪ በህጉ አንቀፅ 6(2) እና (3) የተዘረዘሩትን መስፈርቶች ሟሟላት እንዳላባቸው ህጉ ያስገድዳል፡፡
የቅጅና ተዛማጅ ስራዎች መብቶች
የቅጅ መብት ባለቤት ብቸኛ መብቶች (exclusive rights)
ቅጂዎችን ማባዛት ወይም እንደገና ማባዛትና መሸጥ፤
ወደ አገር ውስጥ ማስገባትና ከአገር ማውጣት፤
የመጀመርያውን ስራ የሚያጠናክሩ ስራዎችን መስራት፤
ስራውን ለህዝብ ማቅረብ፤
መብቱን ለሌሎች የማስተላለፍ፤
ስራውን በሬድዮና ቴሌቪዝን ማስተላለፍ ናቸው::
የቅጅና ተዛማጅ ስራ መብት የኢኮኖሚና የሞራል መብቶች በሚል ለሁለት ከፍሎ ማየት የሚቻል ሲሆን በአንቀፅ 19 ላይ ያለው ስለ ቅጂ ማሰራጨት መብትና በአንቀፅ 9 ላይ በግል አገልግሎት ስራ ስለማባዛት ያለው ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ የቅጂ ስራ የአእምሮ ንብረት ባለቤት የሚኖሩት የኢኮኖሚ መብቶችን በማስመልከት ህጉ በአንቀፅ 7 ላይ ማንኛውም የስራ አመንጪ ወይም የአንድ ስራ ባለቤት የሚከተሉትን ለመፈፀም ወይም ሌላ ሰው እንዲፈፅማቸው ለመፍቀድ ብቸኛ መብት ይኖረዋል በማለት ስራን የማባዛት፣ የመተርጐም፣ የማመሳሰል፣ የማቀናበር፣ ወይም ወደ ሌላ ዓይነት የመቀየር፣ በሽያጭ ወይም በኪራይ ኦርጅናል ስራን ወይም ቅጅውን የማከፋፈል፣ ኦጂናል ወይም ቅጂውን ከውጭ አገር የማስገባት፣ ኦርጅናል ወይም ቅጅውን ለህዝብ የማሳየት፣ ስራን በይፋ የማከናወን፣ ስራን ብሮድካስት የማድረግ ወይም በሌላ መንገድ የማሰራጨት መብቶች ይኖሩታል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆና ህጉ ለዚህ አጠቃላይ የቅጂ የኢኮኖሚ መብት ጥበቃ ሲሰጥ ለሁለም ክንዋኔዎች እንዳልሆነ በአንቀፅ 7(2) ላይ የሚደነግግ ሲሆን በ7(3) ላይ ደግሞ ዋናው አመንጪ ወይም ወራሾች ስለሚኖራቸው ኢኮኖሚያዊ መብት በደንብ እንደሚወሰን ደንግጓል፡፡ አንድ የቅጂ ወይም ተዛማጅ ስራ ባለቤት የሚኖሩት የኢኮኖሚ መብቶች ከፍ ብለው የተዘረዘሩት ሲሆኑ ባለቤቱ በነዚህ መብቶች ሊሰራባችው የሚችለው ወይም መብቱ ፀንቶ የሚቆየው እስከመቼ ነው? የሚለውን ጥያቄ አንስተን ስናይ የተለያዩ አገሮች የተለያየ የጊዜ ሰሌዳን ይጠቀማሉ ለምሳሌ በአሜሪካ መብቱ ፀንቶ የሚቆየው ከ50-70 ዓመት ሲሆን በየ 28 ዓመቱ መታደስን ይጠይቃል:: ከዚያ በኋላ የህዝብ ንብረት (public domain) ይሆናል :: በጣልያን ከሞተ በኋላ ለ6 ዓመት፤በፈረንሳይ ለ14 ዓመትና በስፔን ለ80 ዓመት መብቱ ፀንቶ የሚቆይበት ህግ አላቸው:: ወደኛ አገር ህግ ስንመጣ አዋጁ በአንቀፅ 20 ላይ
20(1) " ኢኮኖሚ መብቶች የስራ አመንጪው በሂወት በቆየበት ዘመንና ከሞተ በኃላ ለወራሾቹ እስከ ሃምሳ ዓመት ፀንተው ይቆያሉ፡፡"
20(2) " በጋራ የስራ አምንጪዎች የተሰራ ስራን በሚመለከት ጉዳይ የሃምሳ ዓመቱ ግዜ መቆጠር የሚጀምረው የመጨሻው የስራ አመንጪው ከሞተበት ቀን ጀምሮ ይሆናል፡፡"
20(3) " የስራው አመንጪ ከሞተ በኃላ የታተመ ስራ የሃምሳ ዓመት የጥበቃ ግዜ መቆጠር የሚጀምረው ስራው ከታተመበት ግዜ ጀምሮ ይሆናል፡፡"
20(4) " አንድ ከኦዲዮቪዥዋል ስራ ውጪ የሆነ ስብስብ ስራ አኮኖምያዊ መብት ፀንቶ የሚቆየው ስራው ከተሰራበት ወይም መጀመርያ ለህዝብ ከቀረበበት ወይም መጀመርያ ከታተመበት ጊዜ የመጨረሻ ከሆነ አንዱ ጀምሮ ለሃምሳ ዓመት ይሆናል፡፡"
20(5) " ስራው የአመንጪውን ሰም ካልያዘ ወይም በብእር ስም የታተመ ከሆነ የስራው አመንጪ የኢኮኖሚ መብት ፀንቶ የሚቆየው ስራው ከተሰራበት ወይም መጀመርያ ለህዝብ ከቀረበበት ወይም መጀመርያ ከታተመበት ጊዜ የመጨረሻው አንዱ ጀምሮ ለ50 ዓመታት ይሆናል፡፡"
20(6) " በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ (5) ከተመለከተው ግዜ በፊት የስራው አመንጪ ማንነት ከታወቀ ወይም የማያጠራጥር ከሆነ የዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ (1) እና (2) እንደሁኔታው ተፈፃሚ ይሆናል፡፡"
20(7) "በፎቶ ግራፍ ስራ ላይ ያሉ የኢኮኖሚ መብቶች ፀንተው የሚቆዩት ስራው ከተሰራበት ግዜ ጀምሮ ለሃያ አምስት ዓመት ይሆናል፡፡"
20(7) "በኦዲዮቪዥዋል ስራ ላይ ያለ ኢኮኖሚያዊ መብት ፀንቶ የሚቆየው ስራው ከተሰራበት ወይም ለህዝብ ከተሰራጨበት ግዜ የመጨረሻ ከሆነው አንዱ ጀምሮ ለሃምሳ ዓመታት ይሆናል፡፡"
ከዚህ አንቀፅ ድንጋጌዎች መገንዘብ የሚቻለው የኢኮኖሚ መብቶች ግዜው መቁጠር የሚጀምረው ሞትን ወይም የመጨረሻ ህትመትን ወይም ከሞት በኃላ ለሚወጣ ህትመት ህትመቱ ለመጀመርያ ግዜ ከወጣበት ግዜ ጀምሮ መሆኑን ነው፡፡
የቅጅና ተዛማጅ ስራዎች የኢኮኖሚ መብት እንደ ማንኛውም መብት ከባለቤቱ ወደ ሌላ ሰው ሊተላለፍ የሚችል መብት ነው፡፡ የሚተላለፈውም ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በማስተላለፍ ወይም ፈቃድ በመስጠት ሲሆን ውሉ መመስረት ያለበትም በፅሁፍ ነው፡፡ ይሄውም መብት በሚተላለፍበት ግዜ ፈቃድ የሰጠው ወይም የመብቱ ባለቤት የሚጠቀምባቸውን ቁሳዊ ነገሮች አያጠቃልልም፡፡ የመብት ማስተላለፊያው ሰነድ መብቱ የሚተላለፍበትን ጊዜ በግልፅ ካልያዘ የመብቱ ይተላለፍልኝ ጥያቄ መቅረብ የሚችለው በ10 ዓመት ግዜ ውስጥ ነው:: የፈቃድ ይተላለፍልኝ ጥቄያው ደግሞ በ5 ዓመት ግዜ ውስጥ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ በሌላ አነጋገር የተጠቀሰው ግዜ ካለፈ በኃላ የይተላለፍልኝ ጥያቄ ማቅረብ አይቻልም ማለት ነው፡፡ (አንቀፅ 23 እና 24) በዚህ መንገድ መብቱ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሳይገለገልበት ከቀረና በቅጅና ተዛማጅ መብት ባለቤት መብት ላይ ጉዳት ያደርስ እንደሆነ የስራው አመንጪ የመብቱን መተላለፍ ወይም ፈቃድ መስጠትን ሊሽረው ይችላል፡፡(አንቀፅ 25)
የስራው አመንጪ የኢኮኖሚ መብቶች ባለቤት ቢሆንም ባይሆንም የሞራል መብቶች አሉት፡፡ እነዚህም:-
ወቅታዊ ሁኔታን በብሮድካስት አማካይነት ለመዘገብ ባጋጣሚ ወይም በድንገት ከተካተተ ስራ ውጪ የስራ አመንጪነቱ እንዲታወቅ የመጠየቅ መብት አለው ፡፡ (አንቀፅ 8(1) (ሀ))
ሳይታወቅ የመቆየት ወይም የብእር ስም የመጠቀምና ክብሩንና መልካም ስሙን የሚያጐድፍ የስራ መዛባት፣ መቆራረጥ ወይም በሌላ መልክ መቀየርን የመቃወም መብት ይኖረዋል፡፡ (አንቀፅ 8(1) (ለ)(ሐ))
ስራን የማሳተም ሞራላዊ መብት ይኖረዋል፡፡ አንቀፅ 8(1) (መ))
አንድ የቅጅና ተዛማጅ ስራዎች ባለቤት በአንቀፅ 8 ላይ የተዘረዘሩትን የሞራል መብቶች ለወራሾች ወይም የስጦታ ተቀባዮች ካልሆነ በቀር በሂወት እያለ እነዚህን መብቶች ወደ ሌላ ሶስተኛ ወገኖች ሊያስተላልፋቸው የሚችል መብቶች አይደሉም፡፡ (አንቀፅ 8(2)) የሞራል መብት የሚወረስ ወይም በስጦታ የሚሰጥ ቢሆንም የስራው አመንጪ በሂወት ባለበትና መብቱ ፀንቶ ባለበት ግዜም ሆነ ወራሾች ወይም የስጦታ ተቀባዮቹ በመብቱ የተጠቃሚነት መብታቸውን ትተነዋል ብለው ለማመልከት ይችላሉ፡፡ የሞራል መብቶች ፀንተው የሚቆዩበት የኢኮኖሚ መብቶች ፀንተው ከሚቆዩበት ጊዜ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አንቀፅ 8(3) (4))
አንድን የቅጂ መብት የተሰጠበትን ንብረት ፍትሓዊ በሆነ መንገድ መገልገልን (fair use) በማስመልከት የተለያዩ አገሮች የተለያየ አሰራርን የሚከተሉ ቢሆንም አብዛኛዎቹ የሚሰሩበት መለክያን ወስደን ስናይ፤-
የተጠቀመበት አላማና ባህሪው (purpose & characterstic)
የቅጂ መብቱ ተፈጥሮ (nature)
ከስራው የቱን ያህል ነው የተወሰደው (what amount or propertion of the whole work was taken)
በቅጂ መብቱ ላይ በገበያ የሚኖረው ዘላቂ ውጤት (the effect of the use upon the the potential market for the value of the copyrighted work) የሚሉ ናቸው::
በካናዳ ለግል አገልግሎት አባዝቶ መጠቀም ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የተፈቀደ ሲሆን በአውስትራሊያ አባዝቶ መጠቀም የሚፈቀደው ለምርምር፤ ለጥናት፤ ተችቶ ለመፃፍ ፤ ለዜና ሪፖርትና የህግ ምክር አገልግሎት ለመስጠት ሲሆን ብቻ ነው:: በአሜሪካ ህግ 10 ቀጂ ማባዛት ለንግድ ስራ እንደተባዛ ይቆጠራል ከሚል በቀር ከዚያ በታች ማባዛት የተፈቀደ ስለመሆኑ በግልፅ የሚለው የለም:: የኢትዮጵያ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ህግም በአንቀፅ 9(1) ላይ አንድ ቀጂ (a single copy) ለግል አገልግሎት ሲባለ ማባዛት የሚፈቅድ ነው:: ስለዚህ የኢትዮጵያ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ህግ አለም አቀፍ መመዘኛ (International standards) ያሟላና ለስራ አመንጭነት መብት ጥበቃ የሚሰጥ ህገ-መንግስታዊ እውቅና የተሰጠው መብት ሆኖ እንደ ሌሎቹ የአእምሮ ንብረት መብቶች ሊተላለፍ የሚችልና የራሱ የሆነ ፀንቶ የሚቆይበት ዘመን ያለው የኢኮኖሚና የሞራል መብት የሚያስገኝ ንብረት ነው፡፡
የመብት ጥሰት መፍትሔዎች (Remedies)
የቅጅና ተዛማች መብቶች ለማስጠበቅ የወጣው አዋጅ ቁጥር 401/96 ሶስት ዓይነት መፍትሔዎችን የሚሰጥ ሲሆን እነሱም የፍ/ብሔር መፍትሔ፤ የደንበር ላይ እርምጃና የወንጀል ቅጣት ናቸው፡፡
የፍ/ብሄር መፍትሔ
የፍታብሔር መፍትሔን በተመለከተ ስልጣኑ የተሰጠው ለመደበኛ ፍ/ቤት ሰለሆን ፍ/ቤት የመብት ጥሰት ያለመሆኑን ከማረጋገጡ በፊትና ካረጋገጠ በኃላ ሊወስድ ከሚችለው እርምጃ ዓንፃር በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል:: ይሄውም ከመረጋገጡ በፊት ሊወሰድ የሚችለው በጊዚያዊነት የእግድ ትእዛዝ (interim injuction) መስጠት ሲሆን የመብት ጥስት መኖሩ ከተረጋገጠ ግን
ባለመብቱ ያወጣውን ወጭና ለደረሰበት ጉዳት ቁሳዊና ሞራላዊ ካሳ እንዲከፈለው ይወሰናል::
ያለ ባለመብቱ ፈቃድ እንዳይባዛ ወይም ከአገር ውጭ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ የተባለን ነገር ያስገባ ወይም ያሰራጨ ካለ እንዲወረስ ያዛል ::
ከቅጅ መብት ጋር የተያያዙ የሂሳብ መግለጫዎች ሰነዶች፤ የንግድ ስራ ለማከናወን የሚያስፈልጉ ወረቀቶችን ለመስራት የሚያገለግሉ መሳሪያዎችና እሽጉች እንዲያዙ ትእዛዝ ይሰጣል::
አመልካች ከካሳው በተጨማሪ ያለአግባብ በልፅጓል ሲል የከሰሰ እንደሆነ ፈቃድ ቢሰጠው ሊከፍል ይችል የነበረውን ያህል እንዲከፍለው ይወስናል ::
ባለቤቱ ከተጠርጣሪው የተገኘውን ትርፍ ብቻ እንዲከፈለው በጠየቀ ጊዜ እንዲከፍለው መወሰን፡፡ ተከሳሹ የተጠየቀው ትርፍ በሌላ ገበያ የተገኘ ሂሳብ ነው የሚል ከሆነ የማስረዳት ሸክም በተከሳሹ ላይ ይወድቃል፡፡
ይሄውም ለባለመብቱ የሚከፈለው ካሳ ለደረሰበት ጉዳትና በመጣሱ ሌላው ወገን ያገኘውን ትርፍ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይሆናል፡፡
የቅጅ መብት በመጣሱ ምክንያት የሚከፈል ሞራል ካሳ ከ 100.000 ብር ያላነሳ ሆኖ የደረሰውን ጉዳት መሰረት በማድረግ ይሆናል፡፡
ሆኖም ግን መብት የጣሰው ሰው ድርጊቱን የፈጸመው ባለማወቅ ወይም ሊያውቅ የሚችልበት በቂ ምክንያት የሌለው ከሆነ ፍ/ቤቱ ያገኝውን ትርፍ ብቻ እንዲመልስ ሊወሰን ይችላል፡፡
ቅጅዎችን ወይንም ጥቅሎቹን በቅጅ ባለመብቱ ላይ ጉዳት ሳያደርሱ ከንግድ እንቅስቃሴ ውጭ እንዲሆኑ ወይም እንዲወገዱ ወይም በሌላ ተገቢ አኳኋን እንዲጣሉ ለማዘዝ ይችላል፡፡ ይህ ቅጅዎችን በቅን ልቦና በያዘ 3ኛ ወገን ላይ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡ (አንቀጽ34)
የደንበር ላይ እርምጃ
በቅጅ ባለመብቱ በሚቀርብለት ማመልከቻ የጉምርክ ባለስልጣን ቅጅዎችን በቁጥጥር ስር ያደርጋል::
ይህን እርምጃ መውሰዱ ለአመልካቹ ወይም የዕቃው ባለቤት ወድያውኑ ያሳውቃል::
አመልካቹ በ10 ቀናት ውስጥ ህጋዊ ማስረጃዎችን ማቅረብ ካልቻለ እቃውን ለመያዝ የተወሰደው እርምጃ ይነሳል ፡፡
አመልካች ያቀረበው ማመልከቻ ህጋዊ መሰረት የሌለው ሲሆን በመያዙ ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂ ይሆናል::
በፍ/ቤቱ ትእዛዝ መሰረት የጉምሩክ ባለስልጣን መብት የጣሰን ዕቃ መውረስ ይችላል፡፡ (አንቀጽ35)
የወንጀል ቅጣት
የወንጀል ህጉ የበለጠ የሚያስቀጣ ካልሆነ በቀር ሆን ብሎ የቅጅ መብትን የጣሰ ሰው ከ 5 ዓመት ባላነሰ እና ከ10 ዓመት ባልበለጠ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡
የወንጀል ህጉ የበለጠ የሚያስቀጣ ካልሆነ በስተቀር በከፍተኛ ቸልተኝነት በዚህ አዋጅ ጥበቃ የተደረገላቸው የቅጅ መብቶችን የጣሰ ከሆነ ከ 1ዓመት በማያንስና ከ 5 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እሰራት ይቀጣል፡፡
አግባብነት ባለው ግዜ ወንጀሉን ለመፈጸም ያገለገሉዕቃዎችን መሳሪያዎችን መብት የጣሱ ዕቃዎችን መያዝ፤ መውረስና ማውደምን ይጨምራል፡፡ (አንቀጽ36)
ስለዚህ የኢትዮጵያ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ህግ አለም አቀፍ መመዘኛ (International standards) ያሟላና ለስራ አመንጭነት መብት ጥበቃ የሚሰጥ ህገ-መንግስታዊ እውቅና የተሰጠው መብት ሆኖ እንደ ሌሎቹ የአእምሮ ንብረት መብቶች ሊተላለፍ የሚችልና የራሱ የሆነ ፀንቶ የሚቆይበት ዘመን ያለውና የአኮኖሚና የሞራል መብት የሚያስገኝ ስራ ነው፡፡ የመብቱ ተጠቃሚዎች የፍታብሄር መፍትሄ የሚያገኝ መሆናቸው በተጨማሪ የመብቱ ጥሰት የወንጀል ተግባርን ያካተተ ከሆነ በወንጀል ተጠያቂ የማስደረግን መብት የሚያጐናፅፍ ነው፡፡
- Hits: 9695
- Details
- Category: Property Law
ህገ-መንግስታዊ መሰረቱ
የአእምሮ ንብረት ከድሮ ጀምሮ ሮማውያን የግለሰብ መብት (personal right) እና ግዙፍ መብት (real right) በሚል ከሚመድቧቸው የንብረት መብቶች በተጨማሪ ለየት ያለ መብት ሲሆን ስያሜውን በተመለከተ የተለያዩ ፀሓፍት የተለያየ አጠራር ሲጠቀሙ ይስተዋላል:: ለዚህም አንዳንዶቹ ግዙፍነት የሌለው መብት (incorporeal right) ሌሎቹ ደግሞ የአእምሮ ንብረት (inteiiectual property) በማለት ይጠሩታል:: ይህ ግን ምንነቱን የሚቀይር ባለመሆኑ በይዘት አንድ (semantic) ነው :: የአእምሮ ንብረት መብት ግዙፍነት የሌለው የንብረት መብት ሲሆን አገሮች ይህን የንብረት መብት ከሚከተሉት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ፖሊሲ በመነሳት በህገ-መንግስታቸውና ከዚያ በታች ባሉ ህጐቻቸው ጥበቃ በመሰጠት በልማት መሳርያነት ሲገለገሉበት የሚገኝ የንብረት መብት ነው፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት ለአእምሮ ንብረት የተሰጠው የህግ ማእቀፍ ስንመለከት በአንቀፅ 51(19) ላይ "የፈጠራና የድርሰት መብቶችን ይፈቅዳል፣ ይጠብቃል" ሲል መንግስት ለአእምሮ ንብረት መብት መከበር የሚኖረውን ሃላፊነት መሰረት በማድረግ ሲደነግግ በአንቀፅ77(5) ላይ ደግሞ "የፈጠራና የኪነጥበብ መብቶችን ያስጠብቃል" በማለት ይደነግግል፡፡ ከነዚህ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች መገንዘብ የሚቻለው በአገራችን ኪነ ጥበብ፤ ድርሰትና የቴክኖሎጂ እድገት ከፍ እንዲል በማድረግ ዜጐች በአገሪቱ ማሕበረ ኢኮኖሚ ለውጥና እድገት ላይ ያላቸውን ሚና ከወትሮው በተሻለ መንገድ እንዲጫወቱ በማስቻል በሰፊው የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ የማድረግ አላማ ያለው መሆኑ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ከፍ ብሎ ከተጠቀሱት የህገ-መንግስት ድንጋጌዎች ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ የአእምሮ ንብረት መብት በፈጠራ (patent) እና በኪነ-ጥበብ ስራ ወይም ድርሰት (copy right) ብቻ የታጠረ የንብረት መብት ነውን? የሚል ሲሆን የአእምሮ ንብረት መብት ከፈጠራ መብት (patent) እና የድርሰትና ወይም የኪነ ጥበብ ንብረት መብት(copy right) በተጨማሪ የኢንዱስትሪ ንድፍ (Industrial design)፣ የንግድ ምልክትና (Trade marks)፣ የእፅዋት አዳቃዮች መብት(plant breeders right) የሚያካትት በመሆኑ የህገ-መንግስቱ ህጋዊ ሽፋን ጠበብ ያለ ነው ብሎ መረዳት የሚቻል ቢሆንም የነዚህ መብቶች ጥበቃ ከህገ-መንግስቱ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ፖሊሲዎችና ስትራተጂዎች በመነጩ ሌሎች ህጐች የህግ ሽፋንና የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብቶች ጥበቃ የተደረገላቸው በመሆኑ የዜጐች መብቶች ለአደጋ የተጋለጡበት ሁኔታ በአገሪቱ የፍትህ ስርዓት የለም ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡
የአእምሮ ንብረት መብት ጥበቃ ከሌሎች የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህግ-መንግስት ድንጋጌዎች አንፃር ሲታይም ነፃ ሃሳብ የመያዝና የመግለፅ ዲሞክራሲያዊ መብት አንፃር በአንቀፅ 29(2) ‘’ማንኛውም ሰው ያለምንም ጣልቃ ገብነት ሃሳቡን የመግለፅ ነፃነት አለው:: ይህ ነፃነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በፅሑፍ ወይም በህትመት፣ በስነ-ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሃሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጫት ነፃነቶችን ያካትታል፡፡’’ በማለት ስለሚደነግግ ዜጎች ይህን መብታቸውን ተጠቅመው ለሚሰሩትና ለሚያወጡት የአእምሮ ንብረት መብት ህጋዊ ጥበቃ አግኝተው የልማቱ ተዋናይ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ነው:: መንግስትም በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 89(1) መሰረት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሃገሪቱ የተጠራቀመ ዕውቀትና ሀብት ተጠቃሚዎች የሚሆኑበት መንገድ የመቀየስ ሃላፊነት ያለበት በመሆኑ ይህን ህገ መንግስታዊ ኢኮኖሚያዊ መርህ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ አዋጆችን አውጥቶ ከማንኛውም ግዜ በበለጠ የአእምሮ ንብረት መብትን የሚያስጠብቅ አሰራርና አደረጃጀት ዘርግቶ ለዘላቂ ልማት ስትራተጂ ስኬት በዚ መስክ ሊገኝ የሚችለውን ውጤት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡
በመሆኑም የአእምሮ ንብረት መብት መረጋገጥና አለመረጋገጥ በአንድ አገር የኢኮኖሚና ማህበራዊ እንዲሁም ዲሞክራሲ ስርአት እድገት ያለው ፋይዳን መሰረት በማድረግ የህግ ሽፋን የሚሰጠው የንብረት መብት እንደመሆኑ መጠን በፍትህ አካላት ዘንድም በየጊዜው የሚቀርቡላቸውን ጉዳዮች በአግባቡ በማስተናገድ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 13(1) የተጣለባቸውን የማክበር እና የማስከበር ግዴታቸውን እንዲወጡ የሚያስችላቸው ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡
የአእምሮ ንብረት ዓይነቶች
የፈጠራ ስራ (patent)
የፈጠራ ስራ ማለት ምን ማለት ነው? የአእምሮ ንብረት ለማስጠበቅና በስርዓቱ እንዲመራ ለማድረግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 123/1987 በአንቀፅ 2(5) ላይ "ፓተንት ማለት የፈጣ ስራን ለማስጠበቅ የሚሰጥ መብት ሲሆን የፈጠራ ስራውን ከአንድ ምርት ወይም የምርት ሂደት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡" በማለት ሲተረጉመው በአንቀፅ 2(3) ላይ ደግሞ " ፈጠራ ማለት በቴክኖሎጂ መሰክ ለአንድ የተወሰነ ችግር ተግባራዊ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል የፈጠራ ሰራተኛ ሃሳብ ነው " በማለት የፈጠራን ምንነት ይገልፃል፡፡
እውቁ Wikipedia, the free encyclopedia በድረ ገፁ ላይ የፈጠራ ስራን (patent) እምብዛም በአዋጁ ከተሰጠው ትርጉም ባልተለየ መልኩ እንዲህ ሲል ተረጉሞት እናገኘዋለን፡፡
The term patent usually refers to a right granted to any one who invents or discovers process, machine, article of manufacture, or composition of matters, or any new and useful improvement there of.
ከነዚህ የተቀራረቡ ትርጓሜዎች መገንዘብ የሚቻለው የፈጠራ መብት (patent right) የሚመነጨው አንድ ሰው በአእምሮው ከሚፈጥረው አዲስና ጠቃሚ ምርት ወይም ግኝትና አዲስ ባይሆንም በሌላ ሰው ፈጠራ ተሰርቶ በስራ ላይ የቆየን ነገር በማሻሻል የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችለው ተጨማሪ የፈጠራ ስራ በማከልና በማሻሻል እንደሆነ ነው፡፡ በመርህ ደረጃ የፈጠራ መብት አዲስ በመፍጠር ወይም ያለውን በማሻሻል ሊገኝ የሚችል የአእምሮ ንብረት መብት እንደሆነ መገንዘብ ቢቻልም የአገራችንን ህግ ያየን እንደሆነ ግን የዚህ ዓይነት መብት የሚሰጠው በአዋጁ አንቀፅ 40(1) መሰረት ለአገልግሎት ሞዴል (ለአነስተኛ የፈጠራ ስራ) ካልሆነ በስተቀር በፓተንት መብትነት አንድን ቀደም ሲል የነበረን የፈጠራ ስራ አሻሽሎ በመስራት የአእምሮ ንብረት መብት ማግኘት እንደሚቻል የሚደነግግ አይደለም፡፡ የዚህ ዓይነት ልዩነት በብዙ አገሮች ህግም ያለ ነው:: ለምሳሌ በአሜሪካ የፓተንት ህግ አንድን ሰው ፈጠራ አሻሽሎ መስራት እንደ መብት ጥሰት ተወስዶ የፍ/ብሄር ተጠያቂነትን የሚስከትል ሲሆን በአውስትራልያ ህግ ተጨማሪ የፈጠራ ስራ መስራት ማለትም አሻሽሎ ማውጣት የተፈቀደ ነው::
በአገራችን የፈጠራ ስራን ለማስጠበቅ የወጣው አዋጅ ቁጥር 123/1987 አላማዎችን ስንመለከት የፈጠራ ስራ አእምራዊ ንብረት መብት የአንድን ሰው በፈጠራው ስራ መገልገልን (Use or practice) መብት የሚጐናፀፍ በመሆኑ በዋና አላማነት ይዞት የሚነሳው ሌሎችን ያለ ባለመብቱ ፈቃድ እንዳይገለገሉበት መከልከል (excluding others) ነው:: ከዚህ በተጨማሪ
1.ለአገር ውስጥ ፈጣሪዎች (local inventors) ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የአገሪቱን የቴክኖሎጂ እድገት በማፋጠን የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲንና ስትራተጂን ከግብ ለማድረስ የሚያስችል ስራን የመስራት አላማ ያለው ነው ፡፡
2.ከአገር ውስጥ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች በተጨማሪ ከውጪው ዓለም የቴክሎጂ ሽግግር እንዲኖር የሚያስችል ምቹ ሁኔታን በመፍጠር አገሪቱ ከዚህ ተጠቃሚ እንድትሆን በማድረግ ዘርፉ ለሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ስኬት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት የማስቻል አላማን በመያዝ የወጣ ህግ ለመሆኑ ከአዋጁ መግብያና ከዝርዝር ህጐቹ መረዳት እንችላለን፡፡ በመሆኑም የአገር ውስጥ ፈጠራን በዋና የልማት መሳርያነት በመጠቀም ከውጪው ዓለም መውሰድ ያለብንን ተሞክሮ መበውሰድ ጠንካራ፣ ዘላቂና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚን መገንባት መሰረት ያደረገ የኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ እድገት ማምጣት እንደግብ የያዘም ነው፡፡ የፓተንት መብት መጠበቅ አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ አንስተን ስናይ አገሮች የፓተንት መብት እንዲጠበቅ የሚያደርጉባቸው ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም ዋና ዋናዎቹን ወሰደን ያየን እንደሆነ:-
ለኢኮኖሚ እድገት ያለው አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ ስለሆነ ከዚህ ተጠቃሚ ለመሆን በማሰብ፤
መብቱ በመጠበቁ ሰዎች ፈጠራቸውን እንዲያወጡና ህዝቡ ከዚህ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል፤
ተመራማሪዎች ወደ ውድድር እንዲገቡና ኩባንያዎች ከዚህ የፈጠራ ስራ ውድድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻልና በቀላል ዋጋ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ፤
ኩባንያዎች የፈጠራ ስራውን ገዝተው ማምረት ሲጀምሩ በሌላ የሚፈበረክ ከሆነ አደጋ ላይ ሊጥላቸውና ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ ሊከታቸው ስለሚችል የፓተንት ህግ ከሌለ ደፍረው የፈጠራ ስራን ሊገዙ ስለማይችሉ የህጉ መኖር እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ነው:: ስለዚህ በአንድ አገር የፈጠራ ህግ ሲወጣ የራሱ አላማዎችና ምክንያቶች ያሉት ነው::
ጥበቃ የሚሰጣቸውና የማይሰጣቸው የፈጠራ ስራዎች
በመቀጠል የፈጠራ ስራ መብት (patent right) የሚሰጠው እንዴት ላለ ፈጠራ ነው? የሚለውን ስናይ ይህ መብት ለሁሉም እንደማይሰጥ አዋጁ በአንቀፅ 3 ላይ በዝርዝርና ለይቶ የሚያሳይ መልኩ የደነገገውን ወስደን ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ አንድ የፈጠራ ስራ የህግ ጥበቃ እንዲያገኝ ከተፈለገ ቀጥሎ ያሉትን መስፈርቶች አሟልቶ መገኘት ይጠበቅበታል::
1.አዲስነት - አንድ የፈጠራ ስራ አዲስ ነው የሚባለው በቀደምት ጥበብ ያልተሸፈነ ሲሆን ነው፡፡ ቀደምት ጥበብ ማለት የፈጠራ ስራውን በተመለከተ ማመልከቻ ከገባበት ወይም እንደአግባቡ ከቀዳሚው ቀን በፊት በየትኛውም የአለም ክፍል በተጨባጭ በሚታይ ህትመት ወይም በቃል ወይም ጥቅም ላይ በማዋል ወይም በሌላ ማናቸውም መንገድ የተገለፀ ነገርን ያጠቃልላል (አንቀፅ 3(2))
2.ፈጠራዊ ብቃት - አንድ የፈጠራ ስራ ፈጠራዊ ብቃት አለው የሚባለው ከሚመለከታቸው ጋር አግባብነት ካለው ቀደምት ጥበብ አንፃር ሲታይ በመስኩ ተራ እውቀት ላለው ሰው ግልፅ ያልሆነ እንደሆነ ነው፡፡ (አንቀፅ 3(4))
3.ኢንዱስትሪያዊ ተግባራዊነት - አንድ የፈጠራ ስራ ኢንዱስትሪያዊ ተግባራዊነት አለው የሚባለው በዕዳ ጥበብ፣ በግብርና፣ በማህበራዊ አገልግሎቶችና ሌላ ማናቸውም መስክ ሊሰራ ወይም ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ሲሆን ነው (አንቀፅ 3(5))
በመሆኑም አንድ የፈጠራ ስራ የህግ ጥበቃ አግኝቶ ፈጣሪ ነኝ የሚለው ሰውም በመብቱ ተጠቃሚ ለመሆን ስራው እነዚህን ከፍ ብሎ የተዘረዘሩትን ህጋዊ መስፈርቶች (legal requirements) ማሟላት የግድ ይላል፡፡
የፈጠራ ስራ ጥበቃ የማይደርግላቸው ስራዎች በአዋጁ አንቀፅ 4 ላይ ተዘርዝረው ያሉት ሲሆኑ እነሱም፤
የህዝቡን ሰላም ወይም ስነ-ምግባር የሚፃረሩ ፈጠራዎች፤
የእፅዋት ወይም የእንስሳት ዓይነቶች ወይም የእፅዋት ወይም የእንስሳት ውጤቶችን ለማስገኘት በስነ-ህይወት ዘርፍ የሚከናወኑ ስራዎች፤
ጨዋታዎችን ለማካሄድ ወይም የንግድና የኢንዱስትሪ ስራዎችን ለማከናወን የተዘጋጁ ስልቶች፣ ደንቦች፣ ዜዴዎች እንዲሁም የኮምፒዩተር ፕሮግራም፤
ግኝቶች፣ ሳይንሳዊ ቲዎሪዎች (theories) እና የቅመራ ዘዴዎች፤ (mathematical methods)
ሰውን ወይም እንስሳትን በቀዶ ጥገና ወይም በቴራፒ ህክምና ዘዴዎች ለማከም እንዲሁም የሰዎችን ወይም እንስሳትን በሽታ ለመመርመር የሚረዱ ዘዴዎች የፈጠራ መብት ጥበቃ የማይሰጣቸው ክንዋኔዎች ተደርገው ነው የሚወሰዱት፡፡ ይህ ማለት ግን የሰዎችን ወይም የእስሳትን በሽታ ለመመርመር የሚረዱ ዘዴዎችን በጥቅም ላይ ለማዋል የሚያገለግሉ ውጤቶች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ (አንቀፅ 4(2) ስለዚህ ህጉ ለፈጠራ ስራ የህግ ጥበቃ ለመስጠትም ላለመስጠትም በመለክያነት የሚገለገለው የፈጠራ ስራው የህዝብን ጥቅም ያስጠብቃል ወይስ አያስጠብቅም? በግል የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት ሊያዝ የሚችል ነው ወይስ አይደለም? የሚሉትን መስፈርቶች የሚጠቀም ነው::
የፈጠራ ስራ መብትና ይዘት
የፓተንቱ ይዘት ባለቤቱ በፈጠራው ላይ ያለውን ብቸኛ መብት የሚያረጋግጥና ሌሎች በደንብ ቁጥር 12/89 አንቀፅ 14 እና ቀጥሎ ባሉ ድንጋጌዎች መሰረት ዝርዝር ነጥቦችን የያዘ መሆን አለበት፡፡ (የአዋጁ አንቀፅ 15) አንድን የፈጠራ ስራ የስራ የፓተንት ባለ መብት የተሰጠውን ፈጠራ ለመፈብረክ ወይም በሱ ለመገልገል ወይም በሌላ ማናቸውም መንገድ ለመጠቀም መብት ይኖረዋል፡፡ ሶስተኛ ወገኖችን የባለ ፓተንቱ ፈቃድ ሳያገኙ ፓተንት በተሰጠው ፈጠራ ለመፈብረክ አይችሉም፡፡ ሶስተኛ ወገኖች ተጠያቂ ሊሆኑ የማይችሉት የፓተንት መብት (patent right) ለፈጣሪው የተሰጠው ከሆነ ብቻ ነው፡፡ (አንቀፅ 22(1) እና 23) ይህ ሰው ያለእርሱ ፈቃድ ፓተንቱን የሚፃረር ወይም መብቱን ሊነካ የሚችል ድርጊትን በሚፈፅም ማናቸውም ሰው ላይ በፍ/ቤት ክስ የመመስረት መብት አለው:: መብቱ ያልተረጋገጠለት ሰው የኔ ፈጠራ ስራ ነው በሚል ብቻ ግን በሶስተኛ ወገኞች ላይ ክስ ማቅረብ አይችልም፡፡ የፈጠራው ባለቤት የፓተንት መብት የማግኘትና በሶስተኛ ወገኖች ሊመጣ ከሚችል መጣስ ህጋዊ ጥበቃ እንደሚደረግለት ሁሉ ግዴታም ያለበት ነው:: ይሄውም ባለፓተንቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ፈጠራውን ስራ ላይ የማዋል ወይም በርሱ ፈቃድ ሌሎች ሰዎች ፈጠራውን ስራ ላይ እንዲያውሉ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ (አንቀፅ 27)
የፓተንት መብት የሚሰጠው እንዴት ነው? የሚለውን አንስተን ስናይ በመርህ ድረጃ መብቱ የሚሰጠው ለፈጠራ ሰራተኛው ሲሆን የፈጠራ ስራው በሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች በጋራ ሆነው አንድን የፈጠራ ስራ ካከናወኑ የጋራ የፓተንት መብት ይኖራቸዋል፡፡ ሁለት የተለያዩ ሰዎች ተመሳሳይ የፈጠራ ስራ ስርቻለሁ በማለት በሚቀርቡበት ጊዜ የፈጠራው ባለቤት የሚሆነው አስቀድሞ ማመልከቻ ያስገባው ነው:: (አንቀፅ 11(1) ) ይሄውም ህጉ first to file rule and right of priority በመርህ ደረጃ የሚከተል ነው:: ፓተንት የሚሰጠውም በአዋጁ አንቀፅ 14 መሰረት ኮሚሽኑ ፓተንት ስለመስጠቱ በኦፊሴል ጋዜጣ በማሳወቅ ፤ የፓተንቱን ሰርትፍኬትና የፓተንቱን ቅጂ ለአመልካቹ በመስጠት፤ በመመዝገብና ክፍያ ለሚያስፈፅም አካል የፓተንቱን ቅጂ በመስጠት ነው:: የፓተንቱ ይዘትም ባለፓተንቱ በፈጠራው ላይ ያለውን ብቸኛ መብት የሚያረጋግጥና በደንቡ መሰረት ሌሎች ነገሮችን ያካተተ ይሆናል::(አንቀፅ 15 ) በኢትዮጵያ የፓተንት መብት የሚሰጠው ለተፈጥሮና የህግ ሰው ሲሆን በአሜሪካ አገር የዚህ ዓይነት መብት የሚሰጠው ለተፈጥሮ ሰው ብቻ ነው:: በኛ አገር የአሰጣጥ ስነ-ስርአቱ ምን ይመስላል? የሚለውን ስንመለከት ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በቀር አንድ ሰው ተቀጥሮ በሚሰራበት ግዜ ለሚገኘው የፈጠራ ስራ የፓተንት መብቱ የሚሰጠው ለቀጣሪው ነው:: የቅጥሩ ሁኔታ ከፈጠራ ስራው ግንኙነት የሌላው ወይም ከቅጥር ወይም የአገልግሎት ውል ጋር ግንኙነት በሌለው መንገድና የቀጣሪው ወይም የአሰሪውን ሃብት፣ መረጃ፣ ማምረቻ ወይም የአገልግሎት መስጫ ማተሪያል ወይም መሳርያ ሳይጠቀም የፈጠራ ስራውን ያከናወነው ከሆነ ግን የፓተንት መብቱ የሚሰጠው ለፈጣሪው ወይም ለተቀጣሪው ወይም ለአገልግሎት ሰጪው ነው፡፡ ከፍ ብሎ የተጠቀሱት እንዳሉ ሆነው የቀጣሪውን መሳርያ በመጠቀምና የተቀጣሪው የግል አስተዋፅኦ ታክሎበት ለሚገኝ የፈጠራ ስራ ተቃራኒ ስምምነት ከሌለው በስተቀር እኩል ድርሻን መሰረት በማድረግ የሁለቱ ማለትም የቀጣሪውና የተቀጣሪው የጋራ ንብረት ይሆንና የፓተንት መብቱ በጋራ ይሰጣል፡፡(አንቀፅ 7) ስለዚህ የፈጠራ ስራ ባለቤትነት ይዘቱ የፈጠራውን ብቸኛ ባለመብትነት የሚያረጋግጥ ሰነድ ሲሆን የዚህም ውጤት በሶስተኛ ወገኖች ላይ ተፈፃሚነት እንዲኖረው በማድረግ የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት ጥበቃ እንዲያገኝ ማስቻል ነው፡፡ የፈጠራ ስራ ባለቤትነት መብት (patent) የሚሰጠው አንድም ለፈጣሪው ለራሱ ወይም ይህን ስራ እንዲያከናውን የተቀጠረ ወይም አገልግሎት የሚሰጥ በሆነበት ግዜ ፓተንቱ የሚሰጠው ለቀጣሪው መሆኑንና ተቃራኒ ስምምነት ከሌለና ለፈጠራ ስራው የሁለቱም አስተዋፅኦ ካለበት ደግሞ ፓተንቱ የሚሰጠው ለሁለቱም በጋራ ባለቤትነት እንዲያገግል በሚያስችል አገባብ ይሆናል፡፡
የባለፓተንት መብት ገደቦች
የፓተንት መብት የአእምሮ ንብረት መብት እንደመሆኑ መጠን የፈጠራ ስራው ባለቤት በዚህ መብቱ ብቸኛ ባለቤት በመሆን ሶስተኛ ወገኖች ያለሱ ፈቃድ በዚህ የፈጠራ ስራ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ የመከልከል ውጤት ያለው መብት (negative right) ነው:: ሆኖም ግን ይህ መብት በህግ ገደብ (limitation) የማይደረግበት የንብረት መብት (monopoly right) ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ በመሆኑም በአዋጁ አንቀፅ 25 ላይ የተወሰኑ ገደቦች ተጥሎበታል:: እነዚህም፡-
ሀ. ንግድ ነክ ባልሆኑ ተግባሮች ያለፈጣሪው ፈቃድ ቢገላገሉበት በህግ አያስጠይቅም፡፡
ለ. ፓተንት የተሰጠበት ፈጠራ ለሳይንሳዊ ምርምርና ሙከራዎች ዓላማ አገልግሎት ብቻ እንዲውል ማድረግ የተፈቀደ ነው ፡፡
ሐ. በባለፓተንቱ ወይም በሱ ፈቃድ ኢትዮጵያ ውስጥ በገበያ ላይ ከዋሉ ፓተንት የተሰጣቸው ሸቀጦች ጋር በተያያዘ መልክ የሚከናወኑ ድርጊቶች::
እንዲሁም በአንቀፅ 25(2) ላይ
የህዝብን ጥቅም በተለይም የብሄራዊ ደህንነት፣ የምግብና የጤና ወይም የሌሎች ብሄራዊ የኢኮኖሚ ዋና ዘርፎች የልማት ፍላጐት ለመጠቀም ኮሚሽኑ ያለባለፓተንቱ ፈቃድ የመንግስት ድርጅት ወይም ኮሚሽኑ የሚሰይመው ሶስተኛ ወገን ለባለፓተንቱ ተገቢውን ክፍያ በመፈፀም ፈጠራውን አንዲጠቀም ሊወሰን ይችላል፡፡ የካሳ ክፍያውን በሚመለከት ኮሚሽኑ በሰጠው ውሳኔ ላይ ወደ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሊባልበት ይችላል::
ሲል ይደነግጋል፡፡ የነዚህ ድንጋጌዎች አላማ በህገ-መንግስቱ እውቅና የተሰጠውን የፈጠራ ጥበቃ በመርህ ደረጃ የባለቤትነት መብቱ የፈጣሪው ሰው የራሱ ወይም ከአንድ በላይ በሚሆኑበት ግዜ የጋራ እንደሆነ በመቀበል ለህዝብ ጥቅምና አገር ደህንነት ሲባል ግን በዚህ የአእምሮ ንብረት መብት ላይ ገደብ (Limitation) ሊጣልበት እንደሚችልና ይህም በሚሆንበት ግዜ ባለፓተንቱ ካሳ የማግኘት መብት እንዳለው ማረጋገጥ ነው፡፡
የፓተንት መቋረጥ፣ መተውና መሰረዝ
የፓተንት መብት ፀንቶ የሚቆይበት ግዜ ጥበቃ ለማግኘት የቀረበው ማመልከቻ ከተመዘገበበት ቀን አንስቶ ለአስራ አምስት ዓመታት ቢሆንም በተለያየ ምክንያት የመብቱ መቋረጥ፣ መተው፣ መሰረዝ ሊከሰት ይችላል፡፡ የፓተንት መብት ሊቋረጥ የሚችለው ባለመብቱ ፓተንቱን የተወ መሆኑን ለኮሚሽኑ በፅሑፍ ሲያሳውቅና የመብት ማቆያ ክፍያ በተወሰነው የግዜ ገደብ ውስጥ ያልተፈፀመ ሲሆን ነው፡፡ይሄውም የመብቱ መቋረጥ ሊከሰት የሚችለው በፍላጐትና ግዴታን በአግባቡ ባለመፈፀም ምክንያት እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ የፓተንት መብት መተው ሊከሰት የሚችለው ደግሞ በፍላጐት ላይ ተመስርቶ የሚመጣ ሲሆን የክንውኑ ስነ-ስርዓትም ባለፓተንቱ መብቱን መተውን ለኮሚሽኑ ሲያሳውቅና ኮሚሽኑ ይህን የመተው ሁኔታ በመመዝገብ አትሞ ሲያወጣው ነው፡፡ ባላፓተንቱ መብቱን ትቻለሁ በሚልበት ግዜ መብቱ ለሌላ ሶስተኛ ወገን በውል ከተሰጠ በኃላ ከሆነ የሚኖረው ስነ-ስርዓት የመተው ጥያቄው ተቀባይነት የሚያገኘው ሌላው ተዋዋይ ወገን ስምምነቱን ሲሰጥ ብቻ ነው:: ይህም የሆነበት ምክንያት መብቱ በውል የተላለፈለት ሰው ጥቅም (third party interest) ለመጠበቅ እንደሆነ መገመት ቢቻልም ስምምነቱን በማይሰጥበት ጊዜ ስለሚኖረው ስነ-ስርዓት ህጉ በግልፅ የሚለው ነገር የለም፡፡ ከአጠቃላይ የድንጋጌው ይዘት ለመረዳት እንደሚቻለው ግን ይህ መብት ፀንቶ ለሚቆይበት ግዜ በውል የፓተንት መብት የተላለፈለት ሰው በፓተንቱ እየተገለገለበት ሊቆይ እንደሚችል ነው፡፡ የፓተንት መብትን መሰረዝ የሚመለከትም ቀጥለው የምናያቸው መስፈርቶች በሙሉ ወይም በከፊል ከተሟሉ ፍ/ቤት ፓተንቱን ሊሰርዘው ይችላል፡፡ (አንቀፅ 34፣35 እና 36) ይሄውም
ሀ. ፓተንት የተጠየቀበት ነገር በአዋጁ ቁጥር 123/89 አንቀፅ 3 እና 4 መሰረት ፓተንት ሊሰጥበት የማይችል ሆኖ ሲገኝ፡፡
ለ. ፈጣሪው በሚበቃ መጠን ግልፅና ሙሉ በሆነ መልክ ባለመገለፁ በመስኩ ለሰለጠነ ሰው በተግባር ለመተርጐም የማያስችል ሲሆን ነው ፡፡
ፓተንቱ ሲሰረዝ የዚህ የፓተንት መብት መሰረዝ ህጋዊ ውጤትም ወደ ኃላ ተመልሶ በሚሰራ ውጤት (retroactive effect) ይኖረዋል፡፡ ለዚህም ነው አንቀፅ 37(2) "በከፊል ወይም በሙሉ የተሰረዘ ፓተንት ዋጋ ቢስ ሆኖ የሚቆጠረው ፓተንቱ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ይሆናል’’ ሲል የሚደነግገው፡፡
ስለዚህ አጠር ባለ መልኩ ሲታይ የፓተንት መብት ለአንድ ወይም ከዚያ በላይ ለሆኑ ፈጠራ ስራ ባለቤቶች የሚሰጥ የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብት ሆኖ ህገ-መንግስታዊና ከዚያ በታች ባሉ አዋጆችና ደንበች ጥበቃ የተደረገለትና ወደ ሶስተኛ ወገን ሊተላለፍ የሚችል ግዙፍነት የሌለው የንብረት መብት ነው፡፡ የፓተንት መብት ጥበቃ የሚያገኘው ለ15 ዓመት ሆኖ የዚህ መብት ዋናው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታም ሶስተኛ ወገኖች ያለባለፓተንቱ ፈቃድ እንዳይገለገልበት መከልከል ነው፡፡ ፓተንት ግዙፍነት የሌለው የንብረት መብት ቢሆንም በአንድ ወቅት ተፈጥሮ ለ15 ዓመት ህጋዊ ውጤት ኖሮት ማንነቱን ሊያጣ ወይም ቀሪ ሊሆን የሚችል ወይም በመሃል እክል ገጥሞት ሊሰረዝ ወይም ሊቋረጥ ወይም በነፃ ፈቃድ ሊተው የሚችል የአእምሮ ንብረት መብት ነው፡፡
የአስጋቢ ፓተንት (patent of introduction)
የአስገቢ ፓተንት የሚሰጠው ለማን ነው? የአስገቢ ፓተንት የሚሰጠው በውጭ አገር የፓተንት ፈቃድ ለተሰጠውና የጥብቃ ጊዜው ላላለፈበት እንዲሁም በኢትዮጵያ ፓተንት ላልተሰጠው የፈጠራ ስራ መግለጫ ለሰጠና ሙሉ ሓላፊነት ለሚወስድ ማንኛውም የአስገቢ ፓተንት ሊሰጠው ይችላል:: (አንቀፅ 18) የአስገቢ ፓተንት መመዘኛዎችም ለፈጠራ ፓተንት ከሚጠይቁት መመዘኛዎች ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም የአስገቢ ፓተንት መሰረቱ የውጭ ፓተንት እንደመሆኑ መጠን የአስገቢ ፓተንት ፈቃድ እንዲሰጠው የሚያመለክት ሰው የውጭውን ፓተንት ቁጥር፣ ቀንና ምንጭ ወይም ዝርዝር መረጃውን የማያውቅ ከሆነ የሚገኝበትን ምንጭ መጠቆም ይኖርበታል፡፡ (አንቀፅ 19(1) (2)
የአዋጁ አንቀፅ 11(2) የእንካ ለእንካ መርህ (principle of reprocity) እንደተጠበቀ ሆኖ የአስገቢ ፓተንት አመልካች በአንቀፅ 11(2) የተጠቀሰው አንድ ዓመት ግዜ ከማለቁ በፊት የውጭው ፓተንት ባለቤት ማመልከቻ ካላቀረበ ወይም የአስገቢ ፓተንት ባለቤቱ በዚህ አዋጅ አንቀፅ 21 ማለትም የአስገቢው ፓተንት መብት ፀንቶ የሚቆይበት ግዜ መሰረት ፈጠራው ስራ ላይ መዋሉን ማረጋገጥ ካልቻለ ወይም ዓመታዊውን ክፍያ መፈፀም ካልቻለ የአስገቢ ፓተንቱ ዋጋ ቢስ ወይም ህጋዊ ውጤት የሌለው እንደሆነ ይቆጠራል፡፡ (አንቀፅ 20(1)) ይሄም በሚመለከተው አካል ጠያቂነት የአስገቢ ፓተንት መብቱ በአዋጁ አንቀፅ 36 መሰረት በፍ/ቤት የሚሰረዝ ይሆናል፡፡
የአስገቢ ፓተንት መብት ፀንቶ የሚቆየው የአስገቢ ፓተንት ከተሰጠ ከሶስት ዓመት በኃላ በየዓመቱ በስራ ላይ የዋለ መሆኑ የማረጋገጥ ግዴታና ዓመታዊ ክፍያ የመክፈል ግዴታው እንደተጠበቀ ሆኖ የአስገቢ ፓተንቱ ፀንቶ የሚቆየው እስከ አስር ዓመት ሊደርስ ይችላል፡፡ (አንቀፅ 21) የዚህ ዓይነት የፓተንት መብት መፍቀድ አላማው የውጭ ፓተንት የተሰጠን ፈጠራ ስራ በኢትዮጵያ እንዲገባ በመፍቀድ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖርና ከዚህ ዘርፍ ልናገኝ የምንችለውን ጥቅም አሟጦ በመጠቀም ለልማት በማዋል በዘርፉ የአሰራር፣ አደረጃጀትና የሰው ሃይል ብቃት እንዲጨምር ማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም ወሳኙ የአገር ውስጥ እድገት ቢሆንም ለውጭውም ቢሆን ተገቢ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አሁን ዓለማችን ከደረሰችበት የግሎባላይዘሽን ዘመን አኳያ ሲታይ በእጅጉ አስፈላጊና ተገቢም ነው ፡፡
የአገልግሎት ሞዴል (Utility model)
በአዋጅ ቁጥር 123/87 እና ደንብ ቁጥር 12/89 ለአነስተኛ የፈጠራ ሰዎች የሚሰጣቸው ጥበቃ የአገልግሎት ሞዴል ሰርትፍኬት እንደሆነ ከአዋጁ አንቀፅ 38 እና ከደንቡ አንቀፅ 39 መረዳት የሚቻል ሲሆን እንደ ፓተንት መብት ሁሉ የአገልግሎት ሞዴል በህግ ጥበቃ የሚደረግላቸውና የማይደረግላቸው የፈጠራ ስራዎችን ያካተተ ነው፡፡
በአገልግሎት ሞዴል ሰርተፍኬት ጥበቃ የሚደረግላቸው የአዲስነትና የኢንዱስትሪያዊ ተግባራዊነትን መስፈርቶች የሚያሟሉ አነስተኛ ፈጠራዎች በአገልግሎት ሞዴል ሰርተፍኬት ጥበቃ ይደረግላቸዋል መመዘኛዎቹም፡፡
አዲስነት - አንድ አነስተኛ የፈጠራ ስራ አዲስ ነው የሚባለው ማመልከቻው በተመዘገበበት ቀን ኢትዮጵያ ውስጥ በታተሙ ፅሑፎች ላይ ቀደም ሲል ያልተገለፀ ወይም ለህዝብ ያልቀረበ ወይም በይፋ ጥቅም ላይ ያልዋለ ከሆነ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የፈጠራ ስራው ማመልከቻ ከመመዝገቡ ከ6 ወራት በፊት መገለፁና ጥቅም ላይ መዋሉ አዲስነቱ አያስቀረውም (አንቀፅ 39(1) (2))
ኢንዱስትሪያዊ ተግባራዊነት - አንድ የፈጠራ ስራ ኢንዱስትሪያዊ ተግባራዊነት አለው የሚባለው በዕደ ጥበብ፣ በግብርናና በማህበራዊ አገልግሎቶችና ሌላ በማናቸውም መስክ ሊሰራ ወይም ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ሲሆን ነው፡፡ (አንቀፀ 3(5))
የአገልግሎት መዴል ጥበቃ የሚሰጠው ለ5 ዓመት ሲሆን አነስተኛ የፈጠራ ስራው በኢትዮጵያ ውስጥ ስራ ላይ የዋለ ከሆነ ለተጨማሪ 5 ዓመት ይታደሳል፡፡ (አንቀፅ 44(1)) አነስተኛ የፈጠራ ስራን መብት የሚያስጠብቀው የአገልግሎት ሞዴል ከፓተንት ጋር ሲነፃፀር ቀላል፣ ውድ ያልሆነና ፈጣን የፈጠራ ስራ ማስጠበቅያ መንገድ በመሆኑ ብዙዎች ሊገለገሉበት የሚችል የፈጠራ ስራ ማስጠበቀያ ነው፡፡
ቀደም ሲል እንደተገለፀው በአገልግሎት ሞዴል ጥበቃ የሚደረግላቸው የአነስተኛ የፈጠራ ስራዎች የመኖራቸው ያህል ጥበቃ የማይደረግላቸውም አሉ፡፡ እነዚህም፡-
ፓተንት የተሰጠበት ወይም የህዝብ ንብረት የሆነን ነገር የቀድሞ ይዘት፣ ጠባይ ወይም ተግባር ቀይሮ በአጠቃቀሙ ወይም በታለመለት ተግባር መሻሻልን የሚያስከትል ካልሆነ በቀር በቅርፅ፣ በመጠን ወይም በማተሪያል መልክ የሚደረግ ለውጥ የአገልግሎት ሞዴል ጥበቃ አይደረግለትም፡፡ (አንቀፅ 40(1))
የታወቁ ንጥረ ነገሮችን ጥንቅር ተመሳሳይ ተግባር ባላቸው ሌሎች የታወቁ ንጥረ ነገሮች የመተካትና ይህም በሚገኘው ጥቅም ወይም አሰራር ላይ ምንም ዓይነት መሻሻል የማያስገኝ ሲሆን፡፡ (አንቀፅ 40(2))
ለህዝብ ሰላምና ስነ-ምግባር ተፃራሪ የሆኑ አነስተኛ ፈጠራዎች ከሆኑ የአነስተኛ የፈጠራ ስራ መብት ማስጠበቅያ የሆነው የአገልግሎት ሞዴል ሰርተፍኬት አይስጥም፤ የሚደረግላቸው ጥበቃም አይኖርም፡፡ (አንቀፅ 40(3))
ስለዚህ የአገልግሎት ሞዴል ሰርተፊኬት ለአነስተኛ የፈጠራ ስራዎች መብት ማስጠበቅያ ተብሎ የሚሰጥ የፈጠራ መብት ሲሆን ጥበቃ የሚሰጣቸውና የማይሰጣቸው የአነስተኛ ፈጠራ ስራዎች በህግ ተለይተዋል:: ይህ መብት ፀንቶ የሚቆየው ለአምስት ዓመት ሲሆን የፈጠራ ስራው በአገር ውስጥ በስራ ላይ የዋለ መሆኑ ሲረጋገጥ ለተጨማሪ አምስት ዓመት ሊታደስ ይችላል:: የጥሰት መፍትሔን (remedies) በሚመለከት በአሜሪካን አገር የፍ/ብሄር ተጠያቂነትን ብቻ የሚያስከትል ሲሆን በፈረሳይና አውስትራሊያ የወንጅል ተጠያቂነትን የሚያስከትል ነው:: በኛ አገር ህግም የፍታብሄር ተጠያቂነት ከውል ውጭ ባለ ሃላፊነት በአንቀፅ 2027ና ቀጥለው ባሉ ድንጋጌዎች በወንጀል ደግሞ በወ/ህ/ቁ 721 የሚያስጠይቅ ነው::
ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ (Industrial Designs)
የኢንዱስትሪ ንድፍ ማለት ምን ማለት ነው? የኢንዱስትሪ ንድፍ ማለት የመስመሮች ወይም የቀለሞች ቅንጅት ወይም ከመስመሮችና ከቀለሞች ጋር የተያያዘ ወይም ያልተያያዘ ባለሶስት ገፅታ ቅርፅ ሲሆን ቅንጅቱ ወይም ቅርፁ ለኢንዱስትሪ ወይም ለዕደ ጥበብ ውጤቶች ልዩ መልክ የሚሰጥና በኢንዱስትሪ ወይም ዕደ-ጥበብ ለሚመረት ምርት እንደ ንድፍ የሚያገለግል ነው፡፡ ሲል በአንቀፅ 2(2) ላይ ሲተረጉመው እውቁ Wikipedia free encyclopedia በህጋችን ከተሰጠው ትርጉም እምብዛም ባልተለየ መልኩ
Industrial design rights are Intellectual property rights that protect the visual design of objects that are not purely utilitarian. An Industrial design consists of creation of shapes, configurations or composition of patterns or color or combination of patterns and color in three-dimensional form containing aesthetic value.
የሚል ትርጉም ሰጥቶታል፡፡
ጥበቃ የሚደረግላቸውና የማይደረግላቸው ንድፎች
በኢንዱስትሪ ንድፍ የንብረት ባለቤትነት መብት እንደሌሎች የአእምሮ ንብረቶች የህግ ጥበቃ የሚደረግላቸውና የማይደረግላቸው የኢንዱስትሪ ንድፎች ያሉ ሲሆን ጥበቃ የሚደረግላቸውን የተመለከትን እንደሆነ የሚከተሉትን መመዘኛዎች ያሟሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል::
እውቅና ስለማይኖረው ጥበቃ ሊደረግለት አይችልም፡፡ (አንቀፅ 46(3))
ቴክኒካዊ ውጤቶችን ለማግኘት ብቻ ለሚውሉ ማናቸውም ነገሮች በዚህ አዋጅ ለኢንዱስትሪያዊ ንድፎች የሚሰጠው ጥበቃ አይሰጣቸውም፡፡ (አንቀፅ 46(4))
የኢንዱስትሪ ንድፍ መብት እንዴት ይረጋገጣል? የኢንዱስትሪ ንድፍ መብት የሚረጋገጠው በምዝገባ ሲሆን የምዝገባው ውጤትም የኢንዱስትሪ ንድአዲስነት - አንድ የኢንዱስትሪ ንድፍ አዲስ ነው የሚባለው የንድፉ ዋና ዋና ባህርያት በኢትዮጵያ ወይም በውጪ ከታወቁ ተመሳሳይ ንድፎች የተለየና ከምዝገባ ቀን ወይም እንደ አግባቡ ከቀዳሚው ቀን በፊት ባለው አንድ ዓመት ግዜ ውስጥ ያልተገለፁ ሲሆን ነው፡፡ በንድፎቹ መካከል ያሉ የተለዩ ገፅታዎች ልዩነት በጥቃቅን ዝርዝሮች ከሆነ ተመሳሳይ ናቸው ተብለው ይወሰዳሉ፡፡ (አንቀፅ 46(2) (ሀ))
ተግባራዊ ተፈፃሚነት - አንድ የኢንዱስትሪ ንድፍ ተግባራዊ ተፈፃሚነት አለው የሚባለው ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ምርቶችን በተደጋጋሚ ለማውጣት በሞዴልነት ለማገልገል የሚችል ሲሆን ነው፡፡ (አንቀፅ 46(2) (ለ))
የኢንዱስትሪ ንድፍ ህጋዊ ጥበቃ የማይደረግላቸው ንድፎችን ስንመለከት ደግሞ
ለህዝብ ሰላም ወይም ስነ-ምግባር ተፃራሪ የሆነ ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ከሆነ አይመዘገብም፡፡ ካልተመዘገበ ደግሞ ህጋዊ ፍ ሰርተፍኬት ባለቤት በንድፉ ለመሰራት ወይም ለመልገል ወይም በሌላ ማናቸውም አኳኃን ለመጠቀም ብቸኛ መብት እንዲኖረው ማስቻል ነው፡፡ (አንቀፅ 49) ይህን መብት ለማግኘት የሚቀርብ ማመልከቻ የኢንዱስትሪ ንድፉን ያቀፈ ምርት ናሙና ወይም የንድፉን ስእላዊ አምሳያና ንድፉ ሊያገለግል የታቀደውን የምርት ዓይነት መያዝ ይኖርበታል:: ከማመልከቻው ጋር የተመደበውን ክፍያ ይከፍላል:: ከዚህ በኋላ የቀረበው ንድፍ ተመርምሮ ተቀባይነት ካገኘ የኢዱስትሪ ንድፍ ምዝገባ ምስክር ወረቀት ይሰጠዋል ይሄውም
የንድፍ ስራው የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ መሆኑን
የኢንዱስትሪ ንድፉን ቀዳሚነት
የኢንዱስትሪያዊ ንድፉን ሰራተኛ ማንነትና ባለቤቱ በኢንዱስትሪዊ ንድፉ ያለውን ብቸኛ መብት ይይዛል::
በመብቱ ተጠቃሚ ለመሆን ምዝገባ ወሳኝ ነው:: ኮሚሽኑ የቀረበለት ማመልከቻን በማስመልከት በሚሰጠው ውሳኔ አመልካቹ ካልተስማማው የውሳኔው ቅጂ ከደረሰው ቀን ጀምሮ በ60 ቀን ውስጥ ይግባኙን ወደ ፍ/ቤት ማቅረብ ይችላል:: ስለዚህ በአገራች ሆነ በሌሎች አገሮች የኢንዱስትሪ ንድፍ ህግ ለፈጠራ ስራ ጥበቃ የሚሰጥ ቢሆንም ለሁሉም የኢንዱስትሪ ንድፎች ልዩነት በሌለው መንገድ (indiscrimnatlly) ጥበቃ የሚሰጥ ህግ ግን አይደለም::
መብቱ ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ
የአንዱስትሪ ንድፍ የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብት እንደሌሎቹ የአእምሮ ንብረት መብቶች ፀንቶ የሚቆይበት ግዜ ያለው ነው:: አገሮች እንደየ ፍትሕ ስርዓታቸው የተለያየ መብቱ ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ አላቸው:: ለምሳሌ በካናዳ 10 ዓመት፤ በጃፓን 15 ዓመት፤ በአሜሪካ 14 ዓመት በእንግሊዝ የተመዘገበና ያልተመዘገበ የሚል አሰራር ስለሚከተሉ የተመዘገበ ከሆነ 25 ዓመት ያልተመዘገበ ከሆነ ደግሞ ለ15 ዓመት ፀንቶ ይቆያል:: በኢትዮጵያም የምዝገባ ማመልከቻው ከተመዘገበበት ቀን አንስቶ ለ5 ዓመት ፀንቶ የሚቆይ ሲሆን ይህ የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ በኢትዮጵያ ውስጥ ስራ ላይ እየዋለ መሆኑ ሲረጋገጥ ደግሞ የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ መብት ለተጨማሪ ሁለት አምስት ዓመታት ሊራዘም ይችላል፡፡ (አንቀፅ 50(1)) ይህም የይራዘምልኝ ማመልከቻ የማብቅያ ግዜው ከመድረሱ በፊት ዘጠና ቀን አስቀድሞ በማመልከት ሊከናወን ይገባል ካልሆነ አይታደስም ፡፡ (አንቀፅ 50(2))
ስለዚህ የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ የባለቤት መብት የሚሰጠው ለንድፍ ፈጣሪ ሲሆን ጥበቃ የሚሰጣቸው ንድፎች ለአገር ልማት ከሚያበረክቱት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፋይዳ አንፃር እየታዩ ሲሆን በይዘታቸውና አላማቸው የህዝቡን ሁለንተናዊ እድገት ወደ ኃላ የሚጐትቱ የኢንዱስትሪ ንድፎች የማይመዘገቡና ከሶስተኛ ወገኖች ጥሰት ለመከላከል ማንኛውም ዓይነት የህግ ጥበቃ የማይደረግላቸው መሆኑን ከአዋጅ ቁጥር 123/1987 ድንጋጌዎችና ደንብ ቁጥር 12/89 አንቀፅ 40 እና ቀጥለው ያሉ ድንጋጌዎች ልንረዳው የምንችል እውነታ ነው፡፡ በመሆኑም የኢንዱስትሪ ንድፍ ህግ እንደሌሎች የአእምሮ ንብረቶች ስርዓት ባለው መንገድ እየተመራ ለአገር ልማት እንዲውል የማድረግ ህዝባዊ አላማን መሰረት ያደረገ ነው ፡፡
- Hits: 14124
Page 1 of 7