Font size: +
13 minutes reading time (2662 words)

ስለጥፋተኝነት ድርድር (Plea Bargain) አንዳንድ ነጥቦች

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የሚወጡ ሕጎች ተከሳሽ የተከሰሰበትን ወንጀል ያመነ ከሆነ ወይም ስለተፈፀመው ድርጊት ስለተባባሪዎቹ ሚና ጠቃሚ መረጃ ከሰጠ ከፍርድ ውሳኔ በፊት ሥልጣን ያለው ክፍል ከክሱ ነፃ ሊያደርገው እንደሚችል ደንግገው ይታያሉ፡፡ በተለይ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ሥራ ላይ የዋሉ ስምምነቶችና ተቀባይነት ያገኙ መግለጫዎች በተደራጁ ወንጀሎች ዙሪያ የሚወጡ ሕጎች በተባባሪዎች ላይ በቂ መረጃ የሚሰጥ ተከሳሽን ከክሱ ነፃ የሚደረግበትን ሥርዐት ሊዘረጉ እንደሚገባ ያመለክታል፡፡ እነዚህን መሰል ድንጋጌዎች በወንጀል በቀረበ ክስ ላይ ጥፋተኝነትን ማመንና (Plea of guilt) ለፍርድ ሂደቱ ተባባሪ ሆኖ መገኘት ከወንጀል ተጠያቂነት ነፃ እስከመሆን ሊደርስ የሚችል የቅጣት ቅናሽ እንደሚያስገኝ የሚያሳዩ ሲሆኑ በሌሎች ሀገሮች በስፋት የሚሠራበትን የጥፋተኝነት ድርድር “Plea bargain” ጽንሰ ሃሳብ የሚያንፀባርቁ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

በኮመን ሎው የሕግ ሥርዐት ውስጥ ለሚዘወተሩ የሕግ መርሆዎች የተሟላ ትርጉም በማስቀመጥ የሚታወቀው ብላክስ የሕግ መዝገበ ቃላት የጥፋተኝነት ድርድርን በሚከተለው ሁኔታ ተርጉሞታል፡፡

Plea bargains is the Process by which the accused and the prosecutor a criminal case workout a mutually satisfactory disposition of the case subject to court approval; it involves the defendants pleading guilty to a lesser offence or to only one or some of the courts of a multi-count indictment in return for a lighter sentence then that possible for a graver charge.

ይህ ወደ አማረኛ ሲመለስ

የጥፋተኝነት ድርድር ማለት ተከሳሹና ዐቃቤ ሕጉ በተከሳሹ ላይ የቀረበው የወንጀል ጉዳይ ሁለቱንም በሚስማማ /በሚጠቅም/ መንገድ ፍፃሜ እንዲያገኝ የሚደራደሩበት ሂደት ሲሆን በሁለቱ መካከል የተደረሰው ስምምነት በፍርድ ቤት የሚፀድቅ ሆኖ ተከሳሹ /ከቀረቡት ክሶች ውስጥ/ ቀላል በሆነው ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን በማመን የሚቀጣበት እና ከከባዱ ወንጀል ነፃ የሚሆንበትን ወይም የተከሰሰበት ከባድ ወንጀል ሲያስቀጣው ከሚችለው ባነሰ ቅጣት ለመቀጣት ሲል ከአንድ ድርጊት ከመነጩ ክሶች ውስጥ አንዱን ወይም ከፊሎቹን መፈፀሙን በማመን የሚቀጣበትን ሁኔታ የሚጠቀልል ነው የሚል ግርድፍ ትርጉም ይኖረዋል፡፡

ብላክስ መዝገበ ቃላት ያስቀመጠው ጥቅል ትርጓሜ ሲተነተን የጥፋተኝነት ድርድር አራት ቁልፍ ሃሳቦችን መያዙን መረዳት ይቻላል፡፡ እነርሱም፤ ዐቃቤ ሕግና ተከሳሹ ስምምነት የሚያደርጉ መሆኑን፣ ስምምነቱ በፍርድ ቤት የሚፀድቅ መሆኑ፣ ስምምነቱ ለዐቃቤ ሕጉና ለተከሳሹ ጥቅም ያለው መሆኑ እንዲሁም ዐቃቤ ሕጉና ተከሳሹ የሚያደርጉት ስምምነት በተከሳሹ ላይ የቀረበውን ክስ ወደ ውሳኔ ለማድረስ የሚረዳ መሆኑ የሚሉ ናቸው፡፡ ጽንሰ ሀሳቡን የበለጠ መረዳት ይቻል ዘንድ እያንዳንዳቸው አጠር አድርጎ መመልከቱ ተገቢ ሆኖ ይታያል፡፡

ሀ. በዐቃቤ ሕግና በተከሳሽ መካከል ስለሚደረግ ስምምነት

የጥፋተኝነት ድርድር ሥርዐት በዐቃቤ ሕግና በተከሳሽ መካከል በሚደረጉ ሁለት መሠረታዊ ድርድሮች /ስምምነቶች/ ላይ የቆመ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህም ተከሳሽ በቀረበበት ክስ ላይ የሚደረግ ስምምነት /ድርድር/ (charge bargaining) እና ተከሳሹ በሚጣልበት ቅጣት ላይ የሚደረግ ስምምነት /ድርድር/ (sentence bargaining) በሚል ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ተከሳሽ በቀረበበት ክስ ላይ የሚደረግ ድርድር ዐቃቤ ሕጉ በተከሳሹ ላይ ሊያቀርባቸው ከሚችለው በርካታ ክሶች ውስጥ በአንዱ ወይም በተወሰኑት ጉዳዮች ብቻ ክስ ለመመሥረት ወይም ካቀረባቸው ክሶች ውስጥ አንዱን ወይም የተወሰኑትን ለማንሳት የሚስማማበት ክሶች ውስጥ ያነሰ ቅጣት ያስቀጣኛል ብሎ ያመነበትን አንድ ወይም የተወሰኑ ክሶች ላይ ጥፋተኝነቱን ለማመን የሚስማማበት ሂደት ነው፡፡ በኮመን ሎው ሥርዐት ሕግ ተከታይ ሀገሮች ተከሳሹ በቀረበበት ክስ ጥፋተንነቱን ለማመን የሚያደርገው ድርድር በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ መሆኑን በቀጥታ የሚያምንበት (Straight guilty plea) ሲሆን ሁለተኛ የቀረበበትን ክስ የማይቃወም መሆኑን በመግለጽ (nolo contedre plea) የሚስማማበትን ነው፡፡ በሁለቱ ጥፋተንነት የማመን መንገዶች መካከል የጎል ልዩነት ባይኖርም ሁለተኛው ዐይነት ጥፋተኝነት የማመን መንገድ ተከሳሹ ከተከሰሰበት የወንጀል ጉዳይ ጋር ተያይዞ በቀጣይነት በሚቀርብ የፍታብሔር ከስ ላይ ጥፋቱን ያመነ መሆኑን ለማስረዳት በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል አለመሆኑ ነው፡፡

በሌላ በኩል ተከሳሹ በሚጣልበት ቅጣት ላይ የሚደረግ ድርድር (sentence bargaining) በቅጣት ቅነሳና ጥፋትን በማመን ዙሪያ ላይ የሚደረግ ድርድር ሲሆን ዐቃቤ ሕጉ ተከሳሹ በቀረበበት ክስ ላይ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ቅጣትን በተመለከተ ምንም የመፋረጃ ሃሳብ ላለማቅረብ ወይም ፍርድ ቤቱ ያቀረበውን ቅጣት ላለመቃወም ወንጀሉ ከሚያስቀጣው ዝቅተኛውን ወይም ከከፍተኛ ያነሰ ቅጣት እንዲቀጣ ለመጠየቅ ወይም አንድ የተወሰነ ቅጣት እንዲቀጣ ለመጠየቅ የሚስማማበት ድርድር ሲሆን በተለዋጩ ተከሳሹ ከቀረቡበት ወይም ከሚቀርቡበት ክሶች ውስጥ በሙሉ ወይም በከፊል ጥፋተኝነቱን ለማመን የሚስማማበት ሂደት ነው፡፡

ተከሳሽ በሚጣልበት ቅጣት ላይ የሚደረግ ድርድር ተከሳሹ ጥፋተኝነቱን በፍርድ ቤት ለማመን የሚስማማበት ሁኔታ ሲሆን በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዐት ቁጥር 134 ከተመለከተው ጥፋተኝነት የማመን ሃሳብ ጋር ሲነፃጸር የመጀመሪያው በድርድር የተገኘ ሲሆን ሁለተኛው በራስ አነሳሽነት የተፈፀመ በመሆኑ (blind plea of guilt) እንዲሁም የመጀመሪያው በፍርድ ቤት ተቀባይነት ካገኘ ግራ ቀኙ ማስረጃ ማስቀረብና መሰማት ሳያስፈለግ ቅጣት ወደ መወሰን በቀጥታ የሚወሰድ ሲሆን ሁለተኛው ፍርድ ቤቱ እንደነገሩ ሁኔታ ተጨማሪ ማስረጃ ማዳመጥ ሥልጣን የሚሰጠው በመሆኑ ልዩነት እንዳላቸው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

በዐቃቤ ሕግና በተከሳሽ መካከል የሚደረገው ድርድር ተከሳሽን ምስክር ከማድረግ ጋር ተያያዥነት እንዲኖረው የሚደረግበት ጊዜም ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ ብዙ ሀገሮች ማስረጃ በቀላሉ የማይገኝባቸው የተደራጁ ወንጀሎችን ለመከላከልና አጥፊዎችን ለመቅጣት ከብዙ ተከሳሾች መካከል በተለይ በወንጀሉ ድርጊት ውስጥ ውስን ተሳትፎ ያለውንና ጠቃሚ መረጃ ሊሰጥ የሚችለውን ሰው በሌሎች ላይ እንዲመሰክር የሚያደርጉበትን ሥርዐት ዘርግተው ይታያሉ፡፡ በዚህ መሰሉ ድርድር ዐቃቤ ሕጉ ተከሳሹ ከቀረበበት ክስ ነፃ ለማድረግ የሚስማማ ሲሆን ተከሳሹ በበኩሉ ወንጀሉን ግብረ አበር በመሆን በፈፀሙ ሌሎች ሰዎች ላይ ለመመስከር ይስማማል፡፡

ከፍ ሲል በተጠቀሱ በዐቃቤ ሕግና በተከሳሹ መካከል የሚደረጉ የድርድር ዓይነቶች ላይ ዐቃቤ ሕግ የተከሳሹን ሚስጥር ለመጠበቅ እና ሌሎች ጉዳዮች ለመፈፀም ሚስማማ ሲሆን ተከሳሹም ድርድሩን ከተቀበለ ጉዳዩ በሙሉ ችሎት ቢታይ የሚጠቅማቸው እንደ ምስክር አቅርቦ መስቀለኛ ጥያቄ የማቅረብ ወዘተ. የመሳሰሉ ከክስ በፊት ያሉ ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ተጥሰውብኛል በሚል ይግባኝ እንዲያቀርብ የሚስማማበት ይሆናል፡፡

ለ. ስምምነቱ ለዐቃቤ ሕጉና ለከሳሹ ጠቃሚ ስለመሆኑ

የኢፌዴሪ የወንጀል ፖሊሲ ይዘት ቅጣትን ለመቀነስ ጥፋትን ማመን ዐቃቤ ሕግና ተከሳሹ በጋራ የሚጠቀሙበት ሥርዐት እንደሆነ አመላክቷል:: እዚህ ላይ ዐቃቤ ሕጉም ሆነ ተከሳሹ ከሥርዐቱ የሚያገኙት ጥቅም ምንድነው የሚል ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ ይሆናል፡፡

በተከሳሽ ላይ የሚቀርቡ ክሶችን አስመልክቶ በሚደረግ ድርደር (Charge bargaining) ላይ ተከሳሹ ከተከሰሰበት ወንጀል በተወሰኑት ላይ ጥፋተኛ መሆኑን ሲያምን ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የተወሰኑት ክስ ሊቀርብባቸው በሚገቡ ገዳዮች ላይ ክስ እንደሚያቀርብ፣ በተከሳሹ ላይ ከቀረቡ የተወሰኑትንም እንደሚያነሳ ግዴታ ይገባል፡፡

በዚህ ድርድር ተከሳሹ ጥፋተኛ መሆኑን ባመነባቸው ክሶች ላይ ፍርድ ቤቱ በቀጥታ ወደ ቅጣት የሚሄድ በመሆኑ ድርድር ዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከማሰባሰብ እንዲሁም ጉዳዩን ለረዥም ጊዜ ከመከታተልና በተለይም ከትርጣሬ በላይ (beyond reasonable doubt) ከማስረዳት አስቸጋሪ ሥራ ይድናል፡፡ ከዚሁ በተጨማሪ በድርድሩ መሠረት በተከሳሹ ላይ የቀረቡ ክሶችን በማንሳቱ ወይም ክስ ሳይመሠረት መቅረቱ /ተከሳሽ ባመነበት ወንጀል አስቀጥቶ/ ክስቹ ቢመሠረቱ ወይም ባይነሱ ኖሮ ከሚያሰማራው በርካታ የሰው ኃይልና ከሚያባክነው ጊዜ የሚድን ሲሆን ወጪውንም በዚሁ መልክ ይቀንሳል፡፡ በተከሳሽ ላይ የሚቀርብ ቅጣትን አስመልክቶ በሚደረገው ድርድር (sentence bargaining) ተከሳሹ የቅጣት ቅናሽ ለማግኘት ሲል በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ እንደሆነ መስማማቱ ለዐቃቤ ሕጉም ከፍ ሲል የተገለጸውን ተመሳሳይ ጥቅም የሚያስገኝለት ይሆናል፡፡

ተከሳሹ በግብረ አበርነት የፈፀመው ወንጀል ውስጥ ተሳታፊ በመሆኑ ሰዎች ላይ እንዲመሰክር የሚያደርገው ስምምነት ዐቃቤ ሕግ በተለይ በማስረጃ እጦት ምክንያት ጥፋተኞችን ለሕግ በማቅረብ እንዳይፈረድ የሚያጋጥመውን እንቅፋት የሚያስወግድ በመሆኑ ግዴታውን በአግባቡ እንዲወጣ የሚያስችለው አሠራር እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በሌላ በኩል ተከሳሹ የሚቀርብበት ክስን አስመልክቶ በሚደረግ ድርድር የተወሰኑ የወንጀል ክሶች የሚነሱለት ወይም በተወሰኑ ጉዳዮች ክስ የማይመሠረትበት በመሆኑ በፍርድ ሂደት ከሚያጋጥሙት የተለያዩ የመብት መጣበቦች /የጊዜ ቀጠሮ/ የሚድን ሲሆን ክሱ ቢመሠረት ወይም ባይነሳ ኖሮ ሊቀጣ ከሚችለው ቅጣትም የሚድን ይሆናል፡፡

ሐ. ስምምነቱ በፍርድ ቤቱ የሚፀድቅ መሆኑ

የጥፋተኝነት ድርድር ሥርዐት ዐቃቤ ሕጉ እና ተከሳሹ የቀረቡትን ክሶች በክስ ብዛት ወይም በቅጣት መጠንና ዐይነት በሚያደርጓቸው የተለያዩ ስምምነቶች /ድርድሮች/ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ከፍ ሲል ተመልክተናል፡፡ እነዚህ ስምምነቶች በተከሳሹ ላይ ሊሳድሩ የሚችሉትን ተገቢ ያልሆነ ተፅዕኖ (inducement) ለመቀነስ በፍርድ ቤት ክትትል እንዲደረግባቸው የማድረጉ አሠራር በሰፊው ሲሰራበት ይስተዋላል፡፡

ይሁንና ፍርድ ቤቱ በስምምነቱ ላይ የሚያደርገው ክትትል ወይም ቁጥጥር እንደስምምነቱ ዐይነት ይለያያል፡፡ በተከሳሽ ላይ የሚቀርብ ክስ፣ (charge bargaining) ክስ ማንሳትን ወይም ክስ አለመመሥረትን የሚያጠቃልል ከመሆኑ አንፃር ለዐቃቤ ሕግ የተሰጠ ሥልጣንን የሚመለከት በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የሚሰራው ቀሪ ሥራ ተከሳሹ ጥፋተኝነቱን ያመነው ያለተፅዕኖ መሆኑን በማረጋገጥ ላይ የተወሰነ ይሆናል፡፡

በአብዛኛዎቹ የኮመን ሎው ሕግ ሥርዐት ተከታይ ሀገሮች በዐቃቤ ሕግና በተከሳሽ መካከል የሚደረጉ ድርድሮች ተከሣሹ በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ እንደሆነ የተስማማበትን ስምምነት ለማጽደቅ ፍርድ ቤት የሚቀርብ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ተከሳሹ ጥፋተኛ እንደሆነ ቃሉን ከመስጠቱ በፊት የስምምነቱን ዋና ሃሣብ የተረዳው መሆኑን፣ ድርድሩ ሲካሔድ ተከሳሹ በጠበቃ የተወከለ ስለመሆኑ፣ ጥፋተኝነቱን ያመነው በፈቃደኝነትና ያለ ተጽዕኖ መሆኑን፣ ክሱንና የሚጣልበትን ቅጣት መረዳቱን፣ ጤንነቱ የተሟላ መሆኑን፣ በፍርድ ቤት ምስክሮች ጠርቶ መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ፣ ጉዳዩን በፍርድ ቤት እንዲታይ የማድረግ ወዘተ…. መብቶቹን እንደማይጠቀምባቸው መረዳቱን፣ ለክሱ መንስዔ የሆኑ ሥረ-ነገሮችን መገንዘቡን ወዘተ…..ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

በሌላ በኩል በተከሣሽ ላይ የሚጣል ቅጣትን አስመልክቶ የሚደረግ ድርድር (sentence bargaining) ተከሣሹ የቀረበበትን ክስ ባያምን ኖሮ ሊቀጣ የሚችለው ከባድ ቅጠት ዝቅ ለማድረግ ሲባል የሚደረግ ስምምነት እንደሆነ ከፍ ሲል ተመልክተናል፡፡ ቅጣት የሚወሰነው በፍርድ ቤት በመሆኑ ስምምነቱ በፍርድ ቤት ተቀባይነት የማያገኝ ከሆነ ተከሣሹ የታሰበውን የቅጣት ቅናሽ ማግኘቱ አጠራጣሪነቱ ግልጽ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለማስወገድ አብዛኛዎቹ የኮመን ሎው ሕግ ሥርዓት ተከታይ ሀገሮች ተዋዋይ ወገኖች ድርድሩን በጽሑፍ በማድረግ ጉዳዩ ከመታየቱ በፊት ለፍርድ ቤቱ የሚያስቀርቡበትን ሥርዐት ዘርግተው ይታያሉ፡፡ የድርድር ሃሣቡን የተቀበለው ፍርድ ቤትም ተከሳሹ (ጠበቃው) ጥፋተኛ መሆንን ቃሉን በፍርድ ቤቱ ፊት ከመስጠቱ አስቀድሞ ስምምነቱን ለማጤን ፈቃደኛ መሆን አለመሆኑን ለተከሣሹና ለዐቃቤ ሕጉ ያሳውቃል፡፡ ስምምነቱን ለማጤን ፈቃደኛ በሆነ ጊዜ በገደብ በተጣለ ቅጣትና በቅድመ የቅጣት ምርመራ (sentence investigation) ላይ የቀረበውን ሪፖርት በዝግ ችሎት ይገመግማል፡፡ ከዚሁ በተጨማሪ ተከሣሹንና የግል ተበዳዩን ጨምሮ ማንኛውም ሰው ችሎት ቀርቦ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ መጠየቅ ይችላል፡፡ ፍርድ ቤቱ ስምምነቱን ያልተቀበለው ከሆነ ምክንያቱን ጭምር በመግለጽ ስምምነቱን እንዲያሻሽሉ ለተከሳሽና ለዐቃቤ ሕጉ ያስታውቃል፡፡ ፍርድ ቤቱ ስምምነቱን የተቀበለው ከሆነ ከፍኛውን ቅጣት፣ ክሱ ብዙ በሆነ ጊዜ ለእያንዳንዳቸው የሚጣለው ከፍተኛ ቅጣት ወዘተ….. በግልጽ ወስኖ ተከሣሽና ዐቃቤ ሕጉ እንዲያውቁ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

ዐቃቤ ሕግና ተከሣሹ የድርድር ሃሳቡን አስቀድመው ለፍርድ ቤቱ ያላቀረቡ ከሆነ ጉዳዩ የቀረበለት ፍርድ ቤት በስምምነቱ እንደማይገደድ ወዲያውኑ የሚያሳውቅ ሲሆን ቅጣቱ ከስምምነቱ ባፈነገጠ ጊዜም ስምምነቱን ማፍረስ እንደሚችል ለተከሣሹ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡

መ. ስምምነቱን ክሱ ውሣኔ እንዲያገኝ አጋዥ ስለመሆኑ

የኢፌዴሪ የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ የጥፋተኝነት ድርድር ሃሣብ በተከሣሹ ላይ የቀረበውን ክስ ፍፃሜ እንዲያገኝ ዐቃቤ ሕጉና ተከሣሹ የሚደራደሩበት ሂደት እንደሆነ ያመለክታል፡፡

ተከሣሹ በቀረበበት ክስ ላይ የሚደረግ ድርድር (charge bargaining) በተከሣሹ ላይ ከቀረቡት ክሶች መካከል ጥቂቶቹ በዐቃቤ ሕጉ የሚነሱበት ቀሪዎቹ ደግሞ ተከሣሹ ጥፋተኝነቱን ለማመን የተስማማበት ወይም ዐቃቤ ሕጉ በተከሣሹ ላይ የተወሰነ ክስ ሳያቀርብ በመተው በቀሪዎቹ ላይ ክስ አቀርቦ ተከሣሹ ጥፋተኝነቱን ለማመን የተስማማት ወይም ዐቃቤ ሕግ በተከሣሹ ላይ የተወሰነ ክስ ሳያቀርብ በመተው በቀሪዎቹ ላይ ክስ አቅርቦ ተከሣሹ ጥፋተኝነቱን ለማመን የሚስማማበት እንደሆነ ከፍ ሲል ተመልክተናል፡፡

ተከሣሹ ፍርድ ቤት በመቅረብ ድርጊቱን መፈጸሙን ያመነባቸው ጉዳዮች ያለተጨማሪ ሥነ ሥርዐትና የማስረጃ ምዘና ወዲያውኑ የቅጣት ውሣኔ የሚተላለፍ ሲሆን ዐቃቤ ሕጉ ክስ ሳይመሠርት የተዋቸው ወይም ከተመሠረቱ በኋላ ያነሳቸው ጉዳዮችም ከፍርድ ሂደት ውጪ ስለሚሆኑ በፍጥነት ውሣኔ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

ተከሣሽ በሚጣልበት ቅጣት ላይ የሚደረግ ድርድርም (sentence bargains) ተከሣሹ ክሱን ባያምን ኖሮ የሚጣልበትን ከፍተኛ ቅጣት ዝቅ የሚደረግበት፣ በተለዋጩ በተወሰኑ ወንጀሎች ጥፋተኛ መሆኑን የሚስማማበት በመሆኑ እነዚህን መሰል ጉዳዮች በተመሣሣይ ሁኔታ ያለተጨማሪ ሥነ ሥርዐት /ማለትም የተከሣሹን ጉዳዮች በተመሣሣይ ሁኔታ፣ ከተገቢ ጥርጣሬ በላይ ማረጋገጥ/ በተሻለ ፍጥነት የቅጣት ውሳኔ የሚሰጥባቸው ሁኔታዎች እንደሆኑ ግልጽ ነው፡፡

የጥፋተኝነት ድርድር ላይ የሚቀርቡ የድጋፍ ወይም የተቃውሞ ሃሣቦች

የጥፋተኝነት ድርድር መርህ በተለይ የኮመን ሎው የሕግ ሥርዐት በሚከተሉ ብዙ ሀገሮች ሥር የሰደደና በስፋት እየተሰራበት ያለ ቢሆንም በመርሁ ላይ ያለው የምሁራን አመለካከት አሁንም ድረስ ያልጠራና ግማሹን በድጋፍ ከፊሉን በተቃውሞ ጐራ ያሳለፈ ሆኖ ይታያል፡፡

ከድጋፍ ጐራ የተሰለፉት ብዙዎቹ ምሁራን የፍትሕ አካለት የሰው ኃይልና የማቴሪያል ዐቅም በየጊዜው የእተመናመነ በመሄድ ላይ በመሆኑ ለወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩ ውጤታማነት ጥፋትን በድርድር የማመን መርህ አስፈላጊና ጠቃሚ እንደሆነ ይመከራሉ፡፡ ጊውን ማን የተባው ፀሐፊ የአሜሪካንን የሕግ ሥርዐት በዋቢነት በመጥቀስ ሲከራከር በዚሁ ሃገር ለውሣኔ ከበቁ ከባድ የወንጀል ጉዳዮች ውስጥ 90% ያህሉ ውሣኔ ያገኙት የጥፋተኝነት ድርድር መርህን ሥራ ላይ በማዋል እንደሆነ ጽፏል፡፡ ይህንኑ ሃሣብ የሚያጠናክረው ዐቃቤ ሕግ ማንሀንተን “ውሣኔ ካገኙ የወንጀል ጉዳዮች ውስጥ 5% ያህሉን ጥፋትን የጥፋተኝነት ድርድር መርህን ሳንከተል ለመወሰን ብንሞክር በከፍተኛ የሥራ ጫና ውስጥ መውደቃችን የግድ ይሆናል፤ ይህንን ቁጥር ወደ 10% ከፍ ካደረግን የፍትሕ ሥርዐቱ ጨርሶውኑ ይቆማል” በማለት የጥፋተኝነት ድርድር መርህ የወንጀል ጉዳዮች በፍጥነት እንዲታዩ የሚረዳ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የጥፋተኝነት ድርድር መርህ ሌላው ጥቅም ሚዛናዊ ፍትሕ ከመስጠት ጋር ይገናኛል፡፡ በዚህ ረገድ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት መርሁ ሕጉ ብዙ ወንጀሎችን ወይም ወንጀለኞችን በአንድ ጐራ በመመደብ የሚጥለውን ቅጣት ፍርድ ቤቱ በቅርብ በማጤን ጥፋተኛውን ማዕከል ያደረገ ቅጣት ለመወሰን ያስችለዋል፡፡ ከዚሁ በተጨማሪ በዐቃቤ ሕግና በተከሣሹ መካከል የሚደረገው ድርድር ብዙ ጊዜ የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶችን ለመረዳት የሚያግዝ ይሆናል፡፡

በአንዳንድ የኮመን ሎው ሕግ ሥርዐት ተከታይ ሀገሮች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የጥፋተኝነት ድርድር መርህ የፍርድ ሂደቱን ለማጥፋጠን ክሱ የሚወስደውን ጊዜ እንደሚያሳጥሩ፣ የተንዛዛ ይግባኝ እንዳይኖር የሚረዱ እንደሆነ ታውቋል፡፡ መርሁ የሕግ አስፈፃሚ አካላት የፍትሕ ሂደቱን እንዲፋጠን እገዛ ላደረገው ተከሣሽ ቅጣት በመቀነስ ርህራሄ እንዲያሳዩ መንገድ የሚያመቻች ሲሆን ጥፋተኛው በፍጥነት እንዲታረም አጋጣሚን የሚፈጥር እንደሆነ እነዚሁ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

በዚሁ መሠረት ዋስ ያጣ ወይም በራሱ ዋስትና ለመለቀቅ ያልቻለ ወይም በሕግ ዋስተና የተከለከለ ተከሣሽ ድርድሩን በመቀበል ጥፋተኝነቱን ያመነ ከሆነ እንደወንጀሉ ሁኔታ በነፃ ሊለቀቅ ወይም በገደብ ለኅብረተሰቡ አግልግሎት እንዲሰጥ ግዴታ ተጥሎበት ሊለቀቅ ይችላል፡፡ ተከሣሹ በተደጋጋሚ ችሎት በመቅረብ የተከሣሽነት ስሜት ከሚያስከትለው የመሳቀቅ ስሜት ለመዳን ጥፋተኝነትን በድርድር የማመንና ቅጣትን የመቀነስ መርህ እንደመፍትሔ ተጠቅሷል፡፡ ተከሣሹ ድርድሩን በመቀበሉ ምክንያት ሊያስከስሱት የሚችሉ ከባድ ወንጀሎችን ማስወገድ ወይም ከተከሰሰ በኃላ እንዲነሱ ማድረግ ከከባድ የወንጀል ሪኮርድ ውስጥ እንዳይመዘገብ ያስችለዋል፡፡ ድርድሩን የተቀበለ ተከሣሽ ለጠበቃ የሚያወጣውን ወጪ ማስቀረት የሚችል ሲሆን የኅብረተሰቡን ትኩረት በሚስቡ ወንጀሎች በመከሰስ ሳቢያ የሚመጣውን መገለልም ሊያስወግድ ይችላል፡፡

የጥፋተኝነት ድርድር መርህ ከዳኞችና ከዐቃቢያነ ሕግ የሥራ አካሄድ አንፃር የራሱ ጥቅም እንዳለው ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ በዚሁ መሠረት ዋስትና አጥተው በፍርድ ቤት የሚቆዩትን ሰዎች እንደሁኔታው እንዲለቀቁ ወይም የተፋጠነ ውሳኔ እንዲያገኙ በፍርድ ሂደት የሚጠፋውን ረዥም ጊዜ በማሳጠር ውዝፍ ጉዳዮችን እንዲወገዱ ወዘተ… ድርሻ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡ ዐቃቤ ሕጉ በተመሣሣይ መልኩ የተከሣሹን ጥፋተኝነት በተፋጠነ ሁኔታ ለማረጋገጥ፣ ውዝፍ ጉዳዮችን በቶሎ ለማየት ክስ የመሠረተባቸው ጉዳዮች በርግጠኝነት የሚያስቀጡ መሆናቸውን ለመረዳት፣ ማስረጃ ያልተገኘላቸው ጉዳዮች ሲገጥመው አንዱን ተከሣሽ ምስክር አድርጐ ጥፋተኞችን ለመፋረድ የመርሁ ተፈፃሚነት ጠቃሚነት እንደለው ተመልክቷል፡፡

የጥፋተኝነት ድርድር መርህን በተመለከተ በርካታ ነቀፌታዎች የሚሰነዘሩ ሲሆን ከነዚህም መካከል ጥቂቶቹ፤

ተከሣሹ ወንጀሉን አለመፈጸሙን ቢያውቅም ከእስር ቤት ቶሎ ለመውጣት ሲል ጥፋቱን እንዲያምን ሊያነሳሳው ይችላል፤

ከድርድሩ የሚገኘው ውጤት ተከሣሹ ወይም የተከሣሹ ጠበቃ ባለው የመደራደር ብቃትና ዕውቀት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ተመሣሣይ ወንጀል የተፈጸመ ነገር ግን የላቀ የድርድግ ዕውቀት ያለውን ጠበቃ መቅጠር የሚችል ተከሳሽ ከድርድሩ የተሻለ ጥቅም የሚያስገኝለት ይሆናል፤

የጥፋተኝነት ድርድር ተከሣሹ በራሱ ላየ እንዲመሰክር የተስፋ ቃል መስጠት /የእሥራት ቅናሽ/ በመሆኑ ከተከሣሹ በራሱ ላይ ላለመመስከር ያለውን ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚጋፋ ይሆናል፤

የሕግ አስፈፃሚ አካላት ሕገ መንግሥቱን በመጣስ በተከሣሹ የሚፈጽሟቸው ተግባራት በመርሁ ተግባራዊነት ሳቢያ ገሀድ ሳየወጣ የሚቀርበት በርካታ አጋጣሚ ተስተውሏል፤

መርሁ ዐቃቤ ሕግ የሕዝብ ደህንነትን አሳልፎ እንዲሰጥ አጋጣሚን የሚፈጥርና በወጤቱም የወንጀል ሕግ ዓላማን የሚጥስ ይሆናል፤

መርሁ ድርድሩን ተቀበለ ተከሣሽ ያነሰ ቅጣት እንዲቀጣ፣ ድርድሩን ያልተቀበል ተከሣሽ ሕገ መንግሥታዊ መብቱን በመጠቀሙ የበለጠ ቅጣት እንዲቀጣ የሚያደርግ በመሆኑ ተገቢነት የለውም፤

የግል ተበዳዩን ፍትሕ የማግኘት መብት ያለገናዘበና ግልጽነት የጐደለው ነው፤

ወዘተ…..የሚሉ ይገኙበታል፡፡

የጥፋተኝነት ድርደርን በተመለከተ ከፍ ሲል የተመለከቱት ተቃውሞዎች ቢቀርቡም ሥርዓቱ ሥር ከሰደደበት የኮመን ሎው የሕግ ሥርዐት ወደ ሲቪል ሎው የሕግ ሥርዐት እይተወሰደ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ፈረንሣይ፣ ስፔይን፣ ጀርመን፣ ጣሊያንና ፖርቹጋል ሥርዐቱን በሕጋቸው ውስጥ አካትተው ይገኛሉ፡፡

ውጤት

ዐቃቤ ሕጉና ተከሣሹ ከፍ ሲል በተመለከተው መሠረት የተለያዩ ድርድሮችን እንደሚያደርጉና ተከሣሹ ጥፋተኝተቱን በፍርድ ቤት ካመነ በኋላ ስምምነቶቹ አስገዳጅ እንደሚሆኑ አይተናል፡፡ ቀጣዩ ጥያቄ እነዚህ ስምምነቶች በፍርድ ቤቶችና በተለያዩ አካላት ላይ ያላቸው ውጤት ምን ይሆናል የሚለው ነው፡፡

ጠቅለል ባለ አነጋገር በተከሣሹ ላይ የቀረበ ክስ አስመልክቶ የተደረሰ ስምምነት (charge bargaining) በተፈጸመ ጊዜ ፍርድ ቤቶች ስምምነቱን የማስፈጸም ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡ ሆኖም ስምምነቱ የተደረሰው ተከሳሹ ላይ የሚጣልን ቅጣት አስመልክቶ ከሆነ ፍርድ ቤቶች በስምምነቱ የማይገደዱ በመሆኑ ስምምነቱ ላይ ከተመለከተው የተለየ ቅጣት ሊወሰኑ ይችላሉ፡፡

ዐቃቤ ሕግ በተከሣሹ ላይ የቀረበ ክስን ወይም የሚጣልበትን ቅጣት አስመልክቶ ከተከሣሹ ጋር ያደረጋቸው ስምምነቶች የሚፀኑትና ውጤት የሚኖራቸው ተከሣሹ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኛ መሆኑን ካመነ በኋላ ሲሆን ፍርድ ቤቱ የተከሣሹን የጥፋተኝነት ቃል ከመቀበሉ በፊት ስምምነቶቹ የተፈፃሚነት ኃይል የሌላቸው በመሆኑ ዐቃቤ ሕጉም ሆነ ተከሣሹ ስምምነቶቹን ለመፈጸም አይገደዱም፡፡

ዐቃቤ ሕጉ ወይም ተከሣሹ ስምምነቱን ለመፈጸም ፈቃደኛ ባልሆኑ ጊዜ ወይም ከስምምነቱ ውጪ በፈጸሙ ጊዜ ተከሣሹ ምን መፍትሔ ይኖረዋል የሚለው ቀጣይነት የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በስፋት የሚሰራበት አካሄድ ስምምነቱን የጣሰው ወገን እንደስምምነቱ እንዲፈጽም ማድረግ ሲሆን ተጐጂው ወገን ይኸው እንዲፈጸምለት ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል፡፡ በአንድ ጉዳይ ተከሣሹ የሚጣልበትን ቅጣት አስመልክቶ የመፋረጃ ሃሣብ ከመስጠት ለመታቀብ ያለበትን ግዴታ በመጣስ ወንጀሉ የሚያስቀጣውን ከፍተኛ ቅጣት እንዲቀጣ በዐቃቤ ሕጉ የቀረበ ጥያቄን ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

ጥፋትን በድርድር የማመንና ቅጣትን የመቀነስ ስምምነትን በመቃወም ስለሚቀርብ ይግባኝ

ተከሣሹ በቀረበበት ክስ ወይም በሚጣልበት ቅጣት ወይም በሌላ ጉዳይ ላይ ከዐቃቤ ሕጉ ጋር ተደራድሮ ጥፋቱን ለማመን ከተስማማና ስምምነቱም ፍርድ ቤት በመቅረቡ ውጤት ካገኘ ተከሣሹ በስምምነቱ ቅር የተሰኘ ቢሆንም ስምምነቱን የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት ከፍ ሲል ተመልክተናል፡፡ ይሁንና ተከሣሹ ቅሬታ ያደረበት በሚከተሉት ሶስት ምክንያቶች በሆነ ጊዜ በብዙ የኮመን ሎው ሕግ ሥርዐት ተከታይ ሀገሮች ይግባኝ እንዲያቀርብ ይፈቀድለታል፡፡

እነዚህም ምክንያቶች፤

ስምምነቱ ከተከሣሹ ፈቃደኝነት ውጪ ተፈጽሟል ወይም ተከሣሹ ስምምነቱ የሚያስከትለውን ውጤት ሳያውቅ ፈጽሟል፤

ዐቃቤ ሕጉ ስምምነቱን ጥሷል ወይም ፍርድ ቤቱ እንደስምምነቱ አልወሰነም፤

ስምምነቱ ሕገ ወጥ ብርበራን በመሳሰሉ የተከሣሹን መብት በሚጥሱ ድርጊቶች ተጥሷል፤

የሚል አቤቱታን መሠረት ያደረጉ ሲሆኑ እንደሁኔታው ለበላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ የሚቀርቡ ናቸው፡፡

ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ይግባኙን መሠረት አድርጐ ስምምነቱን ውድቅ ባደረገ ጊዜ ተከሣሹ የተጣለበት ቅጣት ለጊዜው ታግዶ ክርክሩ እንደገና የሚጀመር ሲሆን ከክስ በኋላ ያሉት ሂደቶች በመደበኛ ሁኔታ ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡ በዚህም መሠረት ዐቃቤ ሕጉ ማስረጃ እንደገና ማቅረብና ተከሣሹ ከጥርጣሬ ውጪ ጥፋተኛ መሆኑን ማስረዳት የሚጠበቅበት ሲሆን ተከሣሹ በስምምነቱ ምክንያት የተገደቡበት ከክስ በፊት ያሉት መብቶቹን መጠቀም ያስችለዋል፡፡

የጥፋተኝነት ድርድር ከኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር አንፃር ያለው እንድምታ

የጥፋተኝነት ድርድር ለኢትዮጵያ የሕግ ሥርዐት እንግዳ በመሆኑ በተፈፃሚነቱ ላይ ያለው ጥቅምና ያስከተለውን ችግር ተንተርሶ ዝርዝር ነጥቦችን ማንሳት የሚቻል አይሆንም፡፡ የሕግ መርሁ በተለይ በስፋት ሥራ ላይ በዋለበት በኮመን ሎው የሕግ ሥርዐት ውስጥ የወንጀል የፍትሕ አስተዳደር ቀልጣፋ ከማድረግ አንፃር ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ብዙዎቹ የሲቪል ሎው ሕግ ሥርዐት ተከታይ ሀገሮችም መርሁ በተለይ የተፋጠነ ፍትሕ ከመስጠት አንፃር ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ የሕጐቻቸው አካለ ካደረጉት ውለው አድረዋል፡፡

በሀገራችን የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ እንደችግር ከሚጠቀሱ ጉዳዮች ውስጥ የተፋጠነ ፍትሕ ያለማግኘት ሲሆን በዚህ ዙሪያ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ የጥፋተኝነት ድርድር ጽንሰ ሃሳብና ዝርዝር ሥነ ሥርዐት በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ ቦታ እንዲኖረው ለማስቻል ታኅሳስ 2003 የጸደቀው የኢፌዴሪ የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ ወስጥ ሃሳቡ እንዲካተት ተደርጓል፡፡

በፖሊሲ ሰነዱ የጥፋተኛነት ድርድርን ለማካሄድ የዓቃቤ ሕግን ውሳኔ የሚፈለግ ሲሆን የተጠርጣሪውን ወይም የተከሳሹን ነፃ ፈቃድና ፍላጎት መሠረት ያደረገ መሆን እንዳለበት ተመልክቷል፡፡ ድርድሩ በተከሳሹ ወይም በተጠርጣሪው ነፃ ፍላጎትና በሕጋዊ አግባብ የተደረገ መሆኑን ለማረጋገጥ የማፅደቅ ኃላፊነት የፍርድ ቤት ሚና መሆኑን ፖሊሲው ውስጥ ተመልክቷል፡፡

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ስለአስተዳደር ሕግ አንዳንድ ነጥቦች
ተጨማሪ ማስታወሻ፡‘መንግስት ወይም ለሕዝብ አገልግሎት የቆመ መስሪያ ቤት ላይ’ ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 30 October 2024