ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የሚወጡ ሕጎች ተከሳሽ የተከሰሰበትን ወንጀል ያመነ ከሆነ ወይም ስለተፈፀመው ድርጊት ስለተባባሪዎቹ ሚና ጠቃሚ መረጃ ከሰጠ ከፍርድ ውሳኔ በፊት ሥልጣን ያለው ክፍል ከክሱ ነፃ ሊያደርገው እንደሚችል ደንግገው ይታያሉ፡፡ በተለይ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ሥራ ላይ የዋሉ ስምምነቶችና ተቀባይነት ያገኙ መግለጫዎች በተደራጁ ወንጀሎች ዙሪያ የሚወጡ ሕጎች በተባባሪዎች ላይ በቂ መረጃ የሚሰጥ ተከሳሽን ከክሱ ነፃ የሚደረግበትን ሥርዐት ሊዘረጉ እንደሚገባ ያመለክታል፡፡ እነዚህን መሰል ድንጋጌዎች በወንጀል በቀረበ ክስ ላይ ጥፋተኝነትን ማመንና (Plea of guilt) ለፍርድ ሂደቱ ተባባሪ ሆኖ መገኘት ከወንጀል ተጠያቂነት ነፃ እስከመሆን ሊደርስ የሚችል የቅጣት ቅናሽ እንደሚያስገኝ የሚያሳዩ ሲሆኑ በሌሎች ሀገሮች በስፋት የሚሠራበትን የጥፋተኝነት ድርድር “Plea bargain” ጽንሰ ሃሳብ የሚያንፀባርቁ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
በኮመን ሎው የሕግ ሥርዐት ውስጥ ለሚዘወተሩ የሕግ መርሆዎች የተሟላ ትርጉም በማስቀመጥ የሚታወቀው ብላክስ የሕግ መዝገበ ቃላት የጥፋተኝነት ድርድርን በሚከተለው ሁኔታ ተርጉሞታል፡፡
Plea bargains is the Process by which the accused and the prosecutor a criminal case workout a mutually satisfactory disposition of the case subject to court approval; it involves the defendants pleading guilty to a lesser offence or to only one or some of the courts of a multi-count indictment in return for a lighter sentence then that possible for a graver charge.
ይህ ወደ አማረኛ ሲመለስ
የጥፋተኝነት ድርድር ማለት ተከሳሹና ዐቃቤ ሕጉ በተከሳሹ ላይ የቀረበው የወንጀል ጉዳይ ሁለቱንም በሚስማማ /በሚጠቅም/ መንገድ ፍፃሜ እንዲያገኝ የሚደራደሩበት ሂደት ሲሆን በሁለቱ መካከል የተደረሰው ስምምነት በፍርድ ቤት የሚፀድቅ ሆኖ ተከሳሹ /ከቀረቡት ክሶች ውስጥ/ ቀላል በሆነው ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን በማመን የሚቀጣበት እና ከከባዱ ወንጀል ነፃ የሚሆንበትን ወይም የተከሰሰበት ከባድ ወንጀል ሲያስቀጣው ከሚችለው ባነሰ ቅጣት ለመቀጣት ሲል ከአንድ ድርጊት ከመነጩ ክሶች ውስጥ አንዱን ወይም ከፊሎቹን መፈፀሙን በማመን የሚቀጣበትን ሁኔታ የሚጠቀልል ነው የሚል ግርድፍ ትርጉም ይኖረዋል፡፡