በኢትዮጵያ የክስረት ሕግ ነጋዴ ከሰረ የሚባለው መቼ ነው? ከክሥረት ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን ከወንጀል ሕጉ አንፃር

የንግድ ሥራ ኢትዮጵያውያን ከ 11 ኛው ምዕት አመት በፊት ባህር አቋርጠው ድንበር ሳይገድቧቸው ቤትና ሀገር ያፈራውን ከሌላው ለሙሙላትና ለመቀያየር አሁን የምንጠቀምበት አይነት ገንዘብ ከሌለበት ጊዜ ጀምሮ ንግድን ስራዬ ብለው ሲሰሩት ነበር። ረጅም ጉዞ በሚደረግብት የጥንቱ ንግድ ግን ሁሉ አልጋ በአልጋ አልነበረም። ያላሰቡት ሽፍታ ከመንገድ ሁሉን ከነጋዴው መዝረፍ፣ የተቀየሩት ንብረቶች ፈላጊ በማጣት ነጋዴውን አትራፊ ከመሆን ይልቅ አክስሮት፣ ለአባዳሪዎች እንግልትና ሲሳይ ይዳርገው ነበር። የከሰረ ነጋዴ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚቆጠረው በስራው የገጠመው ዕድለቢስነት በመሆን ሳይሆን መቅሰፍት የወረደበት ተደርጎ ነው። የከሰረን ነጋዴ በጎሪጥ መመልከት፣ ብድር እንኳ ቢጠይቅ ማንም የማያበድረው በመሆኑ የተነሳ አንዴ ወድቆ የማይነሳ ምሳር የበዛበት የሚሆንበት አጋጣሚ አለ።

የንግድ ተቋማት ክስረት ተፈጥሯዊ መሆኑን የተረዱት ቀዳማዊ ሀይለስላሴ አስቀድመው በመክሰር የሚገጥሙ ፈተናዎችን ለመቅረፍ በሚል የክስረት ህግን ከ 1960 በፊት ያወጡ ሲሆን የመጀመሪያው የክስረት ህግን በመያዝ የወጣው የ 1928 ህግ ሲሆን በማስከተልም በ 1933 የንግድ ድርጅቶችን የሚገዛ ህግ ሲወጣ በዚያውም ውስጥም ለማካተት የተሞከረ ሲሆን በዚያው አመት የክስረት ህግን ለመግዛት በሚል 93 አንቀፃችን የያዘ ህግ ሊወጣ ችሏል። ይህን ህግ በ 1960ዎቹ በድጋሚ በማሻሻል ቢያወጡም እንዳሰቡት ሳይሆን ቀርቶ ህጉን የሚጠቀሙበት እስካሁን ጊዜ ድረስ አናሶች ናቸው። በህግ የደነገጉት የክስረት ህግ በነጋዴና በንግድ ተቋማት ላይ የሚሰራ ቢሆንምና ኢቲዮጲያዊ ነጋዴም የሚከስርበት ዕድል እያለው ስለምን ህጉን ለመጠቀም አልተቻለም የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም።

በንግድ ተቋማት እንቅስቃሴ ላይ የዘመነ ደርግ ዘመን የጣለው ገደብና እንዳይሰሩ መደረግ የክስረት ህግን በዚህ ወቅት ለመጠቀም አላስቻለም። ይህ አመክንዮ በዋናነት አግባብነቱ በደርግ ወቅት ብቻ ህጉ ሊሰራበት እና በተፈለገው መጠን አገልግሎት ላይ እንዳይውል ምክንያት የሆነበትን የሚያመለክት ነው። ህጉ በህግ ባለሙያዎችና በሚከስሩ ነጋዴዎች ጭምር እስከዚህም አለመታወቅም ላለመተግበሩ እንደ አንድ ምክንይት ነው። [1] ህጎች በሚገባ ለመተግበርና ፍርድ ቤትም እንዲጠቀምባቸው የህግ ባለሙያዎችና በህጉ ተጠቃሚ የሚሆኑ ሰዎች ስለህጉ በሚገባ ማወቅ አለባቸው ። ይህ ግን አንዳልሆነ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ተቋማት ያረጋገጡት ነው። ሌላውና የክስረት ህግ ጥቅም ላይ በሚገባ እንዳይውል ትልቁን ድርሻ የተጫወተው በሀገሪቱ

ያለውና ለባንኮች ንብረትን በመያዝ የመሸጥ ህግ ነው። ይህ ህግ ባንኮች ላበደሩት ገንዘብ መክፈል ሳይቻል ሲቀር በመያዣነት የያዙትን ንብረት እንዲሸጡ ያደርጋቸውል፡፤ህጉ በብዙ መልኩ ከንግድ ህጉ የክስረት ድንጋጌዎች የተለየ ሲሆን ይህ ሁነትም ህጉን በሚገባ ላለመጠቀም እንደ አንድ ምክንያት ነው። ይህ ፅሁፍ ስለ ክስረት ምንነት፣ -የክስረት ህግ አላማዎች፣ ነጋዴ ከሰረ የሚባለው መቼ ነው፣ ፍርድ ቤቶች የድርጅቶችን መክሰር የሚወስኑት ምን ሲሟላ ነው፣ የክስረት ህግ አተገባበር በኢቲዮጲያ፣ ክስረትና ወንጀል ከወንጀል ህጉ አንፃርን የኢቲዮጲያ የንግድ ህግ እና ሌሎች ህጎች ላይ በመመስረት መነሻ የሚሆን ምልከታ የሚያሳይ ነው።

ስለመክሰር በጥቂቱ

ኖሮ የማይሞት የለም እንደሚባለው ነግዶ ማትረፍ ወይም መክሰር የንግድ ተፈጥሯዊ ገፅ ነው። መክሰር የነጋዴ ብቻ ነው ብለው ካሰቡ በየቤቱ ያለውን የሰውን የኑሮ ገበና በሚገባ አልተረዱም ማለት ነው።

እጅ ነስቶ ከጓደኛና ከዘመድ ከተበደሩ በኋላ መክፈል ባለመቻላቸው ወይም በሌላ ምክንያት የወሰዱትን የማይመልሱ ብዙ ናቸው። ለመክፈል እጅ አጥሯቸው መክፈል ሳይችሉ የቀሩ በየቀኑ ባለው ማህበራዊ ህይወታችን የምንመለከታቸው ብዙ ናቸው። ይህ እጅ ማጠር ወይም በንግድ አለም የምንገባቸውን የንግድ ግዴታዎች መወጣት አለመቻል ነጋዴውን ከሰረ ለማለት እንደመነሻ ነው። በንግድ አለም ነግዶ ማትረፍ ወይም መክሰር የስራው ባህሪ ነው። መክሰር ከንግድ ጋር በተያያዘ ለገባንባቸው ግዴታዎች የሚያስፈልገንን ገንዘብ አለመኖር ሲሆን በዚህ ረገድ የሚነሳውና አጠያያቂ የሚሆነው እነዚህ ከንግድ ጋር የተያያዙ ግዴታዎች ምንድናቸው የሚለው ነው። በቀላሉ መረዳት እንደሚቻለው እነዚህ ግዴታዎች ነጋዴው ከስራው ጋር ባልተያያዘ በግል ግንኙነቱ የሚመጡበትን ግዴታ የማይጨምር መሆኑን ነው። በንግድ ህጋችን እነዚህ ከንግድ ጋር የተያያዙ ግዴታዎችን(commercial commitments) በመዘርዘር ባያስቀምጥም ከአንሲትራል የክስረት ህግ(UNCITRAL፡Legislative Guide on Insolvency Law) መነሻ የሆኑ ዝርዝሮችን ግን መመልከት ይቻላል። በንግድ ህጉ ላይ ከተመለከቱት የክስረት ድንጋጌዎች ውስጥ መክሰር የንግድ ዕዳን ካለመክፈል ጋር የተያያዘ መሆኑን ከበርካታ ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል። ይህ ሁኔታ በተለይ የክስረት ህጉ በነጋዴዎችና የንግድ ስራ በሚሰሩ ድርጅቶች ላይ ነው የሚሰራው ብሎ የተፈፃሚነት ወሰን ከመደንገጉ ጋር በተያያዘ ጥብቅ መስፈርት መሆኑን መረዳት ይቻላል። ከዚህ የድንጋጌዎች መንፈስ መረዳት የሚቻለው ከንግዱ ጋር ያልተያያዙ ዕዳዎችን አለመክፈል ከስሯል የሚለውን ለመወሰን እንደመስረት አለማገልገሉን ነው። ህጉ በዚህ መልኩ መስፈርት ቢያስቀምጥም ነገር ግን የትኛቹ ዕዳዎች ናቸው ከንግድ ጋር የተያያዙት የትኛቹ ናቸው ከንግድ ዕዳ ውስጥ የማይካተቱት የሚለውን በግልፅ ያስቀመጠበት ሁኔታ የለም። ከአንሲትራል የክስረት ህግ ካስቀመጣቸው ዝርዝሮች መካከል ውስጥ በዝርዝሩ የተመለከቱት የንግድ ግዴታን አለመወጣት ወይም ከነዚህ ግዴታ የሚመጣውን የገንዘብ ጥያቄዎች መክፈል አለመቻል ለነጋዴው እንደመክሰር ይቆጠር ይሆናል።

የክስረት ህግ አስፈላጊነትና አላማዎች

የክስረት ህግ አስፈላጊነት ከማየታችን በፊት በክስረት ህግ ለከሰረ ነጋዴ የሚሰጡ የመፍትሔ ተግባራቶችን መመርመር ያሻል። የንግድ ግዴታውን መወጣት ባልቻለ ነጋዴ ላይ በተናጥል ዕዳ ያለባቸው ጠያቂዎች ገንዘብ የሚጠይቁበት ዕድል ያለ ሲሆን ይህም የሚሆነው በፍትሐብሔር ስነ ስርአት ህጉ በመጠቀም ነው የሚሆነው። በዚህ የህግ ስርአት ዕዳ ጠያቂዎች መብታቸውን የሚያስከብሩ ከሆነ በነጋዴ ግለሰቡ ላይ በርካታ ክሶች የሚመሰረቱበት በመሆኑ የተነሳ ፋታ የሚያሳጠው በመሆኑ የገንዘብ አቋማቸው ስር ያልሰደደባቸ  ነጋዴዎች ከንግዱ አለም በቀላሉ የሚወጡ ሲሆን ይህም እዳ ጠያቂዎችን ከባለዕዳው ገንዘብ ለመጠየቅ የሚሯሯጡበትን ሁኔታ በመፍጠርና የቀዳሚነት መብት ያላቸው ዕዳ ጠያቂዎች የተሻለ መብት እንዲያገኙ ያደርጋል። ይህ የህግ መንገድ በቀላሉ ከመፍረስ መትረፍ የሚችሉ ንግዶችን በቀላሉ ከገበያ እንዲወጡና ንብረታቸውም ለባለገንዘቦች የሚሰጥበትን ሁኔታ ይፈጥራል። የክስረት ህግ ምንም እንኳን በቀዳሚነት አላማ የሚያደርገው ከባለዕዳው ገንዘብ ለሚጠይቁ ባለገንዘቦች ወደ አንድ እንዲሰባሰቡ በማድረግ ክሳቸውን በጋራ እንዲከፍቱ በማድረግ የተናጥል ሩጫን በማስቀረት ሁሉም ባለገንዘቦች ገንዘባቸውን እንዲያገኙ ማድረግ ነው። በህጉ ገንዘብ ለባለመብቶች የሚሰጠው በስነ ስርአት ህጉ ወይም በባንክ ንብረትን ይዞ በመሸጥ ህግ በተመለከተው አግባብ ብቻ አይደለም። በፍትሐብሔር ስነ ስርአትና በመሰል የህግ ስርአት ዕዳ የሚከፈለው የባለዕዳውን ንብረት በመሸጥና ለባለመብቶች በማከፋፈል ነው። ነገሩ በኢቲዮጲያ የክስረት ህግ ግን በልዩነት ሌሎች ለባለገንዘቦች ገንዘብ የሚከፈልበትንም መንገዶችን ጭምር ይዟል።

ነጋዴውን ከሰረ ብሎ ለመደምደም በምንም ሁኔታ ያለበትን የንግድ ግዴታ መክፈል የማይችልበት ሁኔታ ላይ ሲሆን ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ነጋዴ ግን አንዳንድ ጊዜ ከሰሮ ንብረቱ ተሸጦ ለባለገንዘቦች ከሚከፋፈል ይልቅ ቢኖር ለህብረተሰቡ የሚጠቅም በሂደትም ለባለመብቶች የሚሆን ገንዘብ ያመነጫል ተብሎ ከታሰበ ነጋዴውንና የንግድ ስራውን መጠገንና በስራ እንዲቆይ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር የክስረት ህጉ በአማራጭ ያስቀመጠው መንገድ ነው። በዚህ ወቅት ወደ መሞት እየሄደ ያለ ድርጅት ወይም ነጋዴ ለማትረፍ የሚያስችሉ መድሀኒት በመስጠት ነጋዴውንና ድርጅቱን ለማትረፍ የሚጣርበት ይሆናል። ድርጅቱን እንዲሰራ በማድረግ፣ እንዲያመርት በማድረግ በዚያውም የባለዕዳውን ገንዘብ መክፈል የሚቻልበት ሁኔታ በክስረት ህጉ መሰረት ይፈጠራል። በዚህም የባለገንዘቦችን፣ የከሰረውን ነጋዴ፣ የሰራተኛውንና የመንግስትን የህዝቡን  ጥቅም ማስጠበቅ ይቻላል።

በክስረት ህግ በሌላ አማራጭነት ለከሰሩ ነጋዴዎች የተቀመጠም መፍትሔ አለ። ይህኛው አማራጭ ባለዕዳውና ባለገንዘቦች ስምምነት ያደርጋሉ። የስምምነቱ ይዘት በመጠኑም ቢሆን ለባለዕዳው ዕዳ በመተውና በተቀረውም የባለዕዳውና ከፊል ንብረት በመሸጥ ዕዳ መክፈልና ድርጅቱንና የሚቀጥልበትን ሁኔታ የሚፈጠርበት ሁኔታ ነው። ይህ መንገድ በሌሎች የህግ መንገዶች ባለገንዘቦች ገንዘብን ለማግኘት ከሚጠቀሙበት የህግ መንገድ የተለየ ነው።

ሌላኛው በህጉ ያለውና ከዚህ በላይ ከተመለከቱት መንገዶች ውጭ ያለው መጥፎ አማራጭ የባለዕዳውን ንብረት በመሸጥ ለባለገንዘቦች መስጠት ነው። ይህ አማራጭ ለባለገንዘቦች ያለው ጥቅም ከፍተኛ በመሆኑ የተነሳ በጣሙን የሚፈለግ ነው። በዚህ መንገድ ድርጅቱ ተሸጦ ዕዳውን በመክፈል ከገበያ የሚወጣ ሲሆን ይህ አማራጭ እንደሀገር ተፈላጊው መንገድ አይደለም። የሀገራችን የክስረት ህግ ይህንን መጥፎ አማራጭ እንደመጀመሪያ መንገድ የተከተለ የሚያስመስል ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው ምክንያትም ድርጅትን መሸጥና ለባለመብቶች ክፍያን መፈፀም ከመፍትሔዎቹ ሁሉ በክስረት ህጋችን በመጀመሪያ የተቀመጠ ሲሆን ይህ አይነቱ አቀማመጥ ደግሞ በህግ አተረጓገም መርህ መሰረት  በቅድሚያ እንዲተገበር የተፈለገ ነው ለማለት የሚያስችል በመሆኑ ነው። ነገር ግን በርካታ የህግ ፀሀፍት ይህ አቀማመጥ የተከሰተበት ዋናው ምክንያት ይህን የንግድ ህግ ክፍል ሁለት የተለያዩ ሰዎች ያረቀቁት ከመሆኑ አንፃር በአጋጣሚ የተከሰተ ነው እንጂ የህግ አውጭዎችን ትክክለኛ ሀሳብ አያሳይም በሚል የሚያነሱ ሲሆን በተቃራኒው ህጉ የሚመርጠው በሌሎች የሀገሪቱ ህጎችም ለአብነትም በባንክ የክስረት ህግ የተመረጠው ቀዳሚው መንገድ ድርጅቱን ማቋቋም ነው የሚል ነው። ከነዚህ በኢቲዮጵያ የክስረት ህግ ከተቀመጡ አማራጮች በመነሳት የክስረት ህግ አላማዎች ምን እንደሆነ በግርድፉም ቢሆን መረዳት የሚቻል ቢሆንም የህጉን አላማዎች ግን ጠቅልሎ መረዳት አያስችለንም። የህጉን አላማ ጠንቅቆ ማወቅ ህጉን ለመቶርጎም የሚረዳ ከመሆኑ ባለፈ የንግዱን ማህበረሰብ ህጉን በማወቅ ለወደፊቱ ለመጠቀም የሚረዳ ስለሆነ የክስረት ህጉንና አለማቀፍ የክስረት ህጎችን በመዳሰስ አላማውን እንደሚከተለው ይዘረዘራሉ።

1ኛ) የቅንጅት ችግርን ይፈታል

የክስረት ህግ የገንዘብ ባለመብቶች በተናጥል ገንዘባቸውን ለማግኘት መሯሯጣቸውን በማስቀረት ባለመብቶችን ወደ አንድ በመሰብሰብ ተናጥላዊ ሩጫን ያስቀራል። ተናጥላዊ ሩጫ ጉዳቱ ለባለገንዘቦች ብቻ ሳይሆን ለባለዕዳውም ጭምር ነው። ባለዕዳዎች ለበርካታ የባለገንዘቦች ክርክር ከመዳረግም ባለፈ ያለጊዜያቸው ንብረታቸው ተሸጦ ከገበያ እንዲወጡ ያደርጋል። የክስረት ህግ ይህን ችግር ለመቅረፍ በሚል ባለገንዘቦችን ወደ አንድ በመሰብሰብ አነርሱን የሚወክል ተወካይ በመመደብ መብትና ጥቅማቸውን በጋራ የሚያስጠብቅ ስርአትን በመዘርጋት ተበታትኖ መሄድን ያስቀራል። የከሰሩ ነጋዴዎች ሂደታቸውን በክስረት ህጉ የሚቀጥሉ ከሆነ ሌሎች በተናጥል የሚያቀርቡትን ክስ ከማቅረብ የሚያግዳቸው ይሆናል። ጊዜያቸው የደረሱም ሆነ ወደፊት የሚደርሱ ዕዳዎች ወደ አንድ በማምጣት በጋራ እንደባለዕዳዎቹ አይነት የሚከፈልበት ሁኔታ ይፈጠራል። ዕዳዎቹ የሚከፈሉበት መንገድ የተለያየ ቢሆንም በዚህ መንገድ ገንዘብ ጠያቂዎችን በመሰብሰብ ዕዳዎች የሚከፈሉበት ሁኔታ በክስረት ህጉ የታሰበ አላማ ነው።

2ኛ)  ኢኮኖሚው የተረጋጋና እንዲያድግ ያደርጋል

ባስገራሚ ሁኔታ የክስረት ህግ ለኢኮኖሚው መረጋጋትና ማደግ እንዴት ይጠቅማል የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ከኢኮኖሚ ማደግና መረጋጋት ጋር በተያያዘ ኩነቱን በጥልቀት ከመመልከት በፊት የክስረት ህጉ በዋናናት ተግባራዊ የሚደረገው በንግድ ተቋማት ላይ መሆኑን ልብ ሊሉ ይገባል። የግሉ ዘርፍ የንግድ ተቋማት ከጊዜ ወደ ጊዜ በኢኮኖሚው ያላቸው ተሳትፎ ከፍ እያለ መጥቷል። የንግድ ተቋማት በስራቸው ከሚያገጥማቸው ትልቁ ፈተና ውስጥ ዋናው የፋይናንስ ችግር ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ የንግዱ ማህበረሰብ ገንዘብ ከተለያዩ የገንዘብ ምንጮች የሚበደሩ ሲሆን ይህን ገንዘብ መክፈል ሳይችሉ ሲቀሩ በፍጥነት ከስረዋል ተብለው ንብረታቸው ተሸጦ ድርጅቶችን መዝጋት ያለው ጉዳት እጅጉን ከፍተኛ ነው። መክሰር የድርጅቶች ገንዘብ ማጠር ሲሆን ይህም የዘርፉ አንድ ዕጣ ፈንታ ነው። ድርጅቶች ሲታመሙ ፈዋሽ መድሀኒት ሰጥቶ እንዲያገግሙ መሞከር ከመግደል እንደሚሻል እሙን ነው። የክስረት ህግ የህንን ዕድል ለድርጅቶች በመስጠት ረገድ ያለው አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ ነው። በቀላሉ ቢደገፉ ለመዳን የሚችሉ ድርጅቶችን በመደገፍና በማዳን በቀጣይ እዳቸውን የሚከፍሉበትንና ሌሎች የባለድርሻ አካላት ጥቅምን በማስጠበቅ ለኢኮኖሚው አስፈላጊና አዎንታዊ ሚና ያላቸውን የግል ዘርፉን ይጠብቃል። ድርጅቶች በመክሰራቸው የተነሳ በቀላሉ ከገበያ እንዳይወጡና ኢኮኖሚውም የተረጋጋ እንዲሆን ያደርጋል።

3ኛ) በመሸጥና በማቋቋም መሀል መመዛዘንን ይፈጥራል (striking balance between liquidation and reorganization)

በክስረት ዕጣ ፈንታ ውስጥ የገቡ ነጋዴዎችና የንግድ ስራዎች መጨረሻቸውን ከመደምደሙ በፊት በርካታ አማራጭ ያላቸው ሲሆን እነዚህን አማራጮች እንደሁኔታው በመጠቀም መመጣጠንን መፍጠር ያስፈልጋል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ህመሙ ፀንቶበት ሊሞት የተቃረብን ሰው ምንም ተስፋ እንደሌለው እየታወቀ ታማማዊን ለማዳን መሞከር ምንም አይነት ፋይዳ የለውም። በንግድ አለምም ገንዘብ ማጠርና የንግድ ድርጅቱ ወይም ነጋዴው የንግድ ግዴታውን መወጣት አለመቻሉ መታመሙን የሚያሳይ ሲሆን ህመሙ የማይፈወስ አይነት ከሆነ የድርጅቱን ንብረት በማጣራት መሸጥ ተገቢ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ ህመሙ(የገንዘብና የካፒታል አጥረቱ) ያለበትን ድርጅት ህመሙ በቀላሉ መድሀኒት የሆነውን ገንዘብ በመስጠት መፈወስ ከተቻለ የድርጅቱን ንብረት እንዳለ በማቆየት፣ ደግፎ ዕዳውን እንዲከፍልና ህብረተሰቡንም በተለያየ መልኩ እንዲጠቅም ማድረግ ይቻላል። የክስረት ህግ ከሌሎች ህጎች በተለየ መልኩ የድርጅቱን የህመም ጥልቀት በመለየት ስለሚያስፈልገው መድሀኒት አይነት በመወሰን የማመዛዘን ስራ ይሰራል።

4ኛ) በተመሳሳይ ደረጃ ያሉ ባለገንዘቦችን መብት በእኩል ማስጠበቅ

በንገድ ከከሰረ ባለዕዳ ገንዘብ የሚያበድሩ ባለዕዳዎች በደረጃቸው በእኩል ደረጃ ላይ የሚገኙ አይደሉም። አንዳንድ ባለገንዘቦች ገንዘብ ሲያበድሩ ለገንዘባቸው የሚሆን ማስያዢያ የሚዙ ሲሆን ሌሎች ባለዕዳዎች በተቃራኒውም ለሚያበድሩት ገንዘብ መያዣ የማያሲዙበት ሁኔታ ነው ያለው። ምንም እንኳን ሁሉም ባለገንዘቦች ወደ አንድ ማዕቀፍ ገብተው መብታቸውን በጋራ የሚያስከብሩ ቢሆንም በውጤት ደረጃ ከሚገኘው የባለዕዳው ንብረት ግን እንደየባለመብቶቹ የመብት ደረጃ በተመሳሳይ ደረጃ የሚገኙት እንደሚጠይቁትና እንደተረጋገጠው የገንዘብ መጠን የድርሻቸውን ከመውሰድ ባለፈ የደረጃቸው መጠን የተለያየ የሆኑ ባለመብቶችን እኩል ሆነው ከባለዕዳው ንብረት በእኩል የሚካፈሉ አይሆኑም። ይህን ታሳቢ በማድረግ የክስረት ህግም ለባለመብቶች ደረጃ በመስጠት በደረጃው ቀዳሚዎች የሆኑት እንደቅደም ተከተላቸው በዕዳቸው መጠን ልክ የድርሻቸውን እንዲያገኙ ሆኗል። (ስለባንገዘቦች የቀደሚነት መሰል የክፍፍል ስርአት ወደ ፊት የምንመለከተው ይሆናል)

5ኛ) መክሰር በፍጥነት፣ በውጤታማነት እና ያለመድልዎ የገንዘብ ባለመብቶችን መብት እንዲፈፀም ያደርጋል

በክስረት ህግ መሰረት ሁሉም ባለመብቶች በአንድ ጥላ ስር በመምጣት ለመብታቸው መጠበቅ የሚሰራ ተወካይ በመመደብ ይህም ተወካይ የባለዕዳውን ንብረት በተቻለ አቅም ካለበት ቦታ ሁሉ በመሰብሰብና በማስተዳደር ባለመብቶች ሊያገኙ የሚችሉትን የንብረት መጠን ከፍ በማድረግ ረገድ ውጤታማነቱ ከፍተኛ ነው። የውጤታማነቱ ሌላው መለኪያ ደግሞ በተለይም ድጋፍ መደረግ ያለባቸውን የንግድ ተቋማትን በመደገፍ በቀላሉ ከገበያ ከሚወጡ ይልቅ በይበልጥ ለኢኮኖሚው ጠቃሚ እንዲሆኑም ያደርጋል። ነገር ግን ቢደገፉም ውጤታማ የማይሆኑ ድርጅቶች ንብረተቸውን በመሸጥ ከገበያ እንዲወጡ በማድረግ ለሌላ ይበልጥ ውጤታማ ሊያስደርጉ በሚችሉ የኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ እንዲውሉ የማድረግ አስተዋፅኦ አለው። መያዣ ያለውም ሆነ የሌለው ባለገንዘብ በክስረት ህግ ሂደት ላይ ተሳታፊ የሚሆን ሲሆን ይህም ከሌሎች መንገዶች በተሻለ መንገድ ሁሉንም ተሳታፊና አድሎ የማያደርግ እንዲሆን አስችሎታል። እነዚህ ዋና ዋናዎቹ የክስረት ህግ አላማዎች ሲሆን ከዚህም በዘለለ በንብረት መሰብሰብ፣ ማከፋፈል በመሰል ከመክሰር ጋር በተያያዙ ተግባራት ግልፅነት በመፍጠር፣ በግልፅነትም መረጃ ለተለያዩ አካላት እንዲሰራጭ በማድረግ፣ ለሁሉም ባለመብቶች በለመብት ስለመሆናቸው ዕውቅና በመስጠትና ደረጃ ማውጣት  የህጉ አላማ ነው።

ከሰረ የሚባለው መቼ ነው

የኢቲዮጲያ የክስረት ህግ በንግድ ህጋችን አምስተኛ መፀሀፍ ከአንቀፅ 968 ጀምሮ ባሉት ድንጋጌዎች ሰፍሮ የሚገኝ ነው። በክስረት ህጉ አንቀፅ 968 የህጉ የተፈፃሚነት ወሰን የተደነገገ ሲሆን የክስረት ህጉ የተፈፃሚነት ወሰን ለነጋዴዎች ብቻ እንደሆነ ከንባቡ መረዳት ይቻላል። ህጉን በዚህ መልክ ወሰን ማበጀት በተለይም በሲቪል ሎው ሀገሮች ለአብነትም እንደፈረንሳይ ባሉት ሀገሮች የተለመደ ነው። ክስረት ከነጋዴ ጋር የተያየዘበት ዋናው ምክንያት በጥንት ጊዜ የገንዘብ ብድርን በዋናነት የሚያገኙት ነጋዴዎች መሆናቸው ሲሆን አሁን ላይ ግን የገንዘብ ብድር ነጋዴ በሆነም ባልሆነም ሰው የሚወሰድ ስለሆነ  አሁን አሁን እነኚህ ህጎች እየተሻሩና የክስረት ህጎች ነጋዴ የሆነንና ያልሆነንም መሸፈን የጀመሩበት ሁኔታ ነው ያለው። የንግድ ህጉ የክስረት ህግ ለነጋዴዎች የሚሰራ ከሆነ ማን ነው ግለሰብ ነጋዴ የሚለውን ከንግድ ህጉ አንቀፅ አምስት ላይ መረዳት ይቻላል። በዚህ መሰረት ነጋዴ የሚባሉት ስራቸውን በመደበኛነት ገቢና ትርፍ ለማግኘት ሲሉ በአንቀፁ ላይ የተዘረዘሩትን ስራዎች የሚሰሩትን ያጠቃልላል። ከንግድ ድርጅቶች አንፃር በህጉ የሚሸፈኑት የንግድ ስራ የሚሰሩ ድርጅቶች ሲሆን የእሽሙር ማህበር ግን ከዚህ ማዕቀፍ ውጭ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። ከንግድ ህጋችን ድንጋጌዎች መረዳት እንደሚቻለው የንገድ ድርጅቶች(business organization)  ስድስት ሲሆኑ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርና የሽርክና ማህበር (Private limited company and share company) በመሰረታቸው እንደ ንግድ ድርጅት(commertial by its nature) እንደሆኑ የተቆጠረ ስለሆነ ምንም እንኳን ስራቸው የንግድ ስራ ተብለው የተዘረዘሩትና ባይሆንም በክስረት ህግ ውስጥ የሚጠቃለሉና ህጉ የሚሰራባቸው ናቸው። ሌሎች የንግድ ድርጅቶችን በተመለከተ ( ordinary partenesrship,general and limited partenership) ግን በተግባራቸው ወይም በመመስረቻ ፅሁፋቸው በንግድ ህጉ አንቀፅ አምስት የተመለከተውን ስራ የሚሰሩ ከሆነ እጅ ሲያጥረቸው በንግድ ህጉ የተመለከተው የክስረት ህግ የሚሰራባቸው ይሆናል። የእሽሙር ማህበር(joint venture) የክስረት ህጉ የማይሰራባቸው ሲሆን በኢቲዮጵያ ህግ ግን የእሽሙር ማህበር ምን እንደሆነ  ግልፅ አይደለም። ብዙውን ጊዜ የእሽሙር ማህበር በንግድ መዝገብ ያልተመዘገበ ተብሎ የሚታሰብ ቢሆንም ይህ አስተሳሰብ ግን ሌሎች የሀገሪቱን ህግ ከተመለከተን በኋላ ሊሆን እንደማይችል የሚታሰብ ነው። የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አዋጅ ቁጥር 686(ማሻሻያውን ጨምሮ) ማንኛውም የንግድ ስራ ፍቃድ እንደሚያስፈልገው እና በንግድ መዝገብ መመዝገብ እናዳለበት የደነገገ ሲሆን ይህን ሳያደርግ ማንም ሰው የንግድ ስራ ቢሰራ በወንጀል እንደሚጠየቅ የደነገገ ሲሆን ይህ አዋጅን ከንግድ ህጉ ጋር አነፃፅረን ስንመለከተው የእሽሙር ማህበር የሚባል የንግድ ድርጅት በሀገራችን ውስጥ ሊኖር እንደማይችል ነው። ይህም በመሆኑ የእሽሙር ማህበር ምን ማለት ነው የሚለውን የንግድ ህጉንና ሌሎች የሀገሪቱን ህጎች በመመልከት ድጋሚ ማጤን ያሻዋል። አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የእሽሙር ማህበር የሚባሉት በንግድ መዝገብ ውስጥ ገብተውና የንግድ ፍቃድ አውጥተው በሚሰሩ ድርጅቶች ውስጥ ከንግድ ስራው ጋር ከተመዘገቡ አስተዳዳሪዎች ጋር በውስጥ ስምምነት ስራ ለመስራት የሚዋዋሉና የዚያ የንግድ ድርጅት አካል የሚሆኑ ሰዎችን ወይም ድርጅቶችን የሚገልፅ ነው የሚሉ አሉ። ለምሳሉ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በ 20 ሰዎች ተቋቁሞ ስራ ቢጀመርና ከነዚህ 20 ሰዎች ውጭ ሌሎች ግለሰቦች በመነገድ ስራ ማንነታቸው እንዳይታወቅ የሚፈልጉ ሰዎች ከሀያዎቹ ሰዎች ጋር በመስማማት ማንነታቸው ተደብቆ ነገር ግን በዚያ የንግድ ድርጅት ስራ ውስጥ ነጋዴ በመሆን የሚሳተፉ ቢሆን ለነዚህ ግለሰቦች የእሽሙር ድርጅት ተቋቋሟል ልንል እንችላለን።

ከዚህ የህጉ የተፈፃሚነት ወሰን በመነሳት ነጋዴ ከሰረ የሚባለው መቼ ነው የሚለውን መቃኘት ያሻል። ስለ ነጋዴ መክሰር በመርህ ደረጃ የሚያበስረው ፍርድ ቤት ነው። ፍርድ ቤት ነጋዴው ከንግድ ጋር ተያይዘው የሚመጡበትን ክፍያ መክፈል ሲያቆም ከሰረ በማለት በማፅናት ክስረትን ያረጋግጣል ። ከዚህ በመነሳት የሁለቱ መስፈርት መሟላት ብቻ ነው ነጋዴን ከሰረ ለማለት የሚያስችሉት። ከዚህ በዘለለ ግን ነጋዴው የንግድ ግዴታውን መክፈል አለመቻሉ ብቻ በራሱ ከሰረ ለማለት በቂ አይደለም( የንግድ ህጉ አንቀፅ 970(1)። ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት ባለዕዳ የሆነን ሰው ለመጠበቅ ታስቦ ነው። በቀላሉ የንግድ ግዴታውን መክፈል ሳይችል ሲቀር ከሰረ የሚባል ከሆነ ብዙ ነጋዴዎች ከስራ አለም ይወጣሉ ። ይህ እንዳይሆን ፍርድ ቤት የመወሰን ስልጣን እንዲይዝ በማድረግ የነጋዴውን የፋይናንስ ችግሩ ስር የሰደደና ሊመለስ የማይችል መሆኑን እንዲያረጋግጡ በማድረግና በህጉ የተመለከቱትን የመፍትሔ እርምጃዎች እንደሁኔታው እንዲወስዱ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው። ምንም እንኳን በመርህ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ክፍያ መክፈል ያልቻለን ነጋዴ ስለመክሰሩ ቢያውጁም በውስን ሁኔታ ግን ስለመክሰር ከሚወስኑ ፍርድ ቤቶች ውጭ ያሉ ሌሎች የወንጀል ፍርድ ቤቶች ስለነጋዴ ክፍያ ማቆሙን እያወቀ ወንጀል በሚሰሩ ነጋዴዎች ላይ ስለመክሰሩ የመክሰር ፍርድ ከሚሰጠው ፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይጠባበቁ የወንጀል ቅጣት ሊጥሉ ይችላሉ ( በቀጣይ በዚሁ ፅሁፍ ሁለተኛው ክፍል ላይ በሰፊው ይዳሰሳል) ። እንግዲህ በመርህ ደረጃ በህግ ስለመክሰር ውሳኔ የሚሰጠው ፍርድ ቤት ነጋዴው ክፍያ መክፈል አይችልም ለማለት የሚችለው መቼ ነው። የነጋዴውና የነጋዴው ድርጅት ከንግድ ጋር በተያያዘ የሚመጡ ክፍያዎችን መክፈል አይችሉም ለማለት ሶስት ማወቂያ መንገዶች አሉ እነርሱም

  • የካሽ ፍሎው ቴስት( cash flow test)
  • የባላንስ ሺት ቴስት( balance sheet test)
  • ካፒታል አሎኬሽን ቴስት ( capital allocation test) በመባል ይታወቃሉ።

1ኛ) የካሽ ፍሎው ቴስት ( cash flow test)

ነጋዴው ከንግድ ጋር በተያያዘ የሚመጡበትን ክፍያ መክፈል አልቻለም ብሎ ለመወሰን ያለበትን የፋይናነስ ችግር ለማጤን ከምንጠቀምባቸው ዘዴዎች አንደኛውና የመጀመሪያው መንገድ ይህ ነው። የህ መንገድ በተለያየ መጠሪያ ይጠራል። በተለያየ ሁኔታ ቢጠራም በትርጉምና በአተገባበር ረገድ ግን ሁሉም አንድ አይነት ውጤት ነው የሚሰጡት። በዋናነት በዚህ መንገድ ነጋዴው ክፍያውን አቁሟል ለማለት በተለየ ሁኔታ ነጋዴው በባለገንዘቦች ለሚጠየቅ ጊዜው የደረሰን ዕዳ ለመክፈል የሚያስችል የገንዘብ አቅም አለው ወይስ የለውም የሚለውን በመመርመር በሚገኘው ውጤት ላይ የሚንተራስ ነው። ነጋዴው በዚህ መሰረት የደረሰ ዕዳን ለመክፈል የሚያስችል የሚከፈል ገንዘብ ከሌለው እየከሰረ ነው ለማለት ይቻላል። መንገዱ በቀላሉ በወቅቱ ያለውን የገንዘብ አቅም ላይ በመንተራስ ክስረት የሚወሰንበት በመሆኑ የተነሳ ለባለገንዘቦች ጥቅም የቀረበ መንገድ ወይም ዘዴ ነው ይባላል። ይህ መንገድ ሁለት የተዛመዱ መለኪያዎች ያሉት ሲሆን አንደኛው አሁን ላይ የደረሰን ዕዳ በዕጅ ካለ ገንዘብና ጊዜያዊ ንብረቶች መሸፈን ሳይቻል ሲቀር ነጋዴው ከስሯል የምንልበት ሲሆን ሁለተኛው መንገድ አሁን ላይ የደረሱና ወደፊት የሚደርሱ ዕዳዎችን መክፈል ሳይቻል ሲቀር መክሰርን የምንወስንበት መንገድ ነው። ምንም እንኳን ዘዴው በቀላሉ ባለገንዘቦች ሊያስረዱ የሚችሉት ቢሆንም፣ ክፍያ መክፈል ያለመቻልን የሚያሳይ የሰነድና መሰል ማስረጃ በማቅረብ መክፈል አለመቻልን ማሳየት ቢቻልም እና በዚህም ባለዕዳው ገንዘቡን እናዳያሸሽ የሚያደርገው ቢሆንም በጣም ቀላል መንገድ በመሆኑ የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ባለገንዘቦች ከድርጅቱ ወይም ከነጋዴው ገንዘብ ከመቀበል አላማ ውጭ የነጋዴውን ስም ለማጥፋትና ከገበያ እንዲወጣ ለማድረግ ለአላግባብ አላማ ሊጠቀሙበት የሚችሉበት ዕድል አለ። በቀላሉ የደረሰን ዕዳ መክፈል ባለመቻሉ የተነሳ ብቻ ከስሯል በማለት ክስ መመስረት በጣም በርካታ ተቋማትን ከንግድ አለም የማውጣትና እንዳይሰሩ ከማድረጉም ባለፈ በትክክልም የነጋዴውን ወይም የንግድ ድርጅቶችን የገንዘብ አቅም ወይም መክፈል የመቻልና ያለመቻል የሚያሳይም አይደለም። በዚህም ይህን መንገድ በራሱ ብቻ መጠቀም ከላይ ከተመለከተው ችግር አንፃር አግባብ አይመስልም።

2) የባላንስ ሺት ቴስት (Balance sheet test)

ሁለተኛው መንገድና ብዙን ጊዜም የባለዕዳውን ትክክለኛ የገንዘብ አቋም ያሳያል የሚባለው መንገድ ይህኛው ነው። በዚህ መንገድ የድርጅቱን ወይም የነጋዴውን የመክፈል ማቆም  ለመመርመር  የድርጅቱን አጠቃላይ ንበረት ከዕዳው ጋር በማነፃፀር እዳው ከፍ ያለ ከሆነ ድርጅቱ ከስሯል የምንልበት ነው። የድርጅቱን ንብረት አሁን ካለው የገበያ ዋጋ ጋር መሰረት በማድረግ በመመዘን፣ ድርጅቱ ወደ ፊት ከተለያዩ ሰዎች የሚቀበለውን የገንዘብና መሰል ዕዳ በማከል ይህ የድርጅቱ አቅም ድርጅቱ ካለበትና ከሚከፍለው ከንግድ ጋር የተያያዙ ዕዳዎች አንፃር ሲታይ ያነሰ ከሆነ ድርጅቱ ከስሯል ወደ ሚል መደመደሚያ ይወስዳል። የድርጅቱ ዕዳዎች በሁኔታ ላይ የተመሰረተ፣ ወደፊት የሚመጠና ልካቸው የሚታወቅና፣ መጠኑ የሚታወቅና ያለሁኔታ የተመሰረተ ሊሆን ይችላል። የህ ዘዴ በተሻለ ሁኔታ የድርጅቱን የገንዘብ አቋም ለማወቅ የሚረዳ ቢሆንም ከህፀፅና ከችግር ግን የፀዳ አይደለም። በዋናነትም በባለዕዳው መረጃዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑ(የድርጅቱን አቋም የሚያሳየውን ደብተር የሚያመጣው ባለዕዳው በመሆኑ)፣ የደርጅቱን አቋም ለማወቅ በባለሙያ የሚታገዝ በመሆኑና ይህም ወጪው እጅግ ከፍተኛ መሆን፣ ስራው በባህሪው ረጅም ጊዜ የሚፈጅ መሆኑ እና መሰል ችግሮች የዘዴው ህፀፃች ሊባል የሚችል ነው። ይህ መንገድ በተለምዶው የድርጅቱ የገንዘብ አቅም ከዕዳው ማነስን እንደመስፈርት የመጠቀም ልምድ ቢኖርም በአንዳንድ ልዮ ሁኔታዎች ግን የሁለቱን መሰረቶች ንፅፅር ከማየት ባለፈ በሌላ በማንኛውም መንገድ ዕዳ ከሀብት(አሴት) ሊበልጥ የማይችል መሆኑን በተጨማሪነት መረጋገጥ የሚኖርበት ሁኔታ አለ።

3 )ካፒታል አሎኬሽን ቴስት (capital allocation test)

በዚህ መንገድ የነጋዴን ወይም የነጋዴ ድርጅት መክሰርን ለማረጋገጥ ድርጅቱ ለተቋቋመበት አላማ የሚሆን የገንዘብ አቋም አለው ወይስ የለውም የሚለውን መመርመር ያሻል። ድርጅቱ የንግድ ድርጅት ከሆነ የንግድ ስራ ለመስራት ወይም መሰል ተግባር ለመከወን እንደሚቋቋም ይገመታል። ይህን የተቋቋመበትን አላማ ደግሞ ለመከወን ገንዘብ ያስፈልገዋል ። ያለው የድርጅቱ ካፒታል የተቋቋመበትን አላማ ለመከወን የማያስችል ከሆነ ድርጅቱ ከሰረ ልንል እንችላለን።

 የንግድ ድርጅቶች ከንግድ ክፍያ ጋር በተያያዘ ክፍያ አቁመዋል ብሎ ለመወሰን ካላይ የተመለከቱት ሶስት መንገዶች ወሳኝ መሳሪያዎች ሲሆኑ የኢቲዮጵያ ህግ የትኛውን መንገድ ነው የተከተለው የሚለውን ስንመረመር በዋናነት የንግድ ህጉን አንቀፅ 969፣ 971፣ 973ን መመልከት ያሻል። የንግድ ህጉ አንቀፅ 971 ባለዕዳው በንግድ ስራው ያሉበትን ግዴታዎች ለመክፈል አለመቻሉን በሚገልፁ ማንኛውም ሁኔታዎችና፣ ስራዎች፣ ወይም ሰነዶች የእዳ መክፈል መቋረጥ ሊታወቅ ይችላል በሚል ተደንግጓል። ይህ በማንኛውም ሁኔታ የሚለው አገላለፅ ከአንቀፅ 973(ለ) ጋር ተጣምሮ ሲታይ ባለው የጊዜው የገንዘብ አቅም ሁኔታን ዕዳና ካለመክፈል ጋር በማነፃፀርም መክሰርን ማሳየት ይቻለል የሚል መደምደሚያ ሊያዝ ይችላል። ይህ ብቻውን ግን በቂ አለመሆኑን በአንቀፅ 970(1) ላይ የተገለፀ በመሆኑ የካሽ ፍሉው ቴስት መንገድን  ከሁለተኛው(ከባላንስ ሺት ቴስት) መንገድ ጋር በማጣመር መታየት ያለበት መሆኑን መገመት የሚቻል በመሆኑ በኢቲዮጵያ ህግም መክሰርን ለማረጋገጥ በካሽ ፍሎው ቴስትና የባላንስ ሺት ቴስት ጥምርታዎች የሚወሰን መሆኑን ነው።

በሁለተኛው ክፍል የዚህ ፅሁፌ የክስረት ህግን ከወንጀል ህጉ አንፃር በማየት በተለይም መክሰር ሳይረጋገጥ ከመክሰር ጋር የተያያዙ ወንጀሎች ቢኖሩና በነዚህ ክሶች ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በሚቀርብበት ጊዜ ልክ እንደሌሎች የፍትሐብሔር ክርክር ያለባቸው ወንጀሎች ክሱ ክስረት በፍትሐብሔር ችሎት እስኪረጋገጥ በሚል የማይቆም ስለመሆኑ በዝርዝር የምመለከተው ይሆናል።

በክፍል ሶስት የአቲዮጵን የኢንቨስትመንት ህግንና(የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነቶችን ጨምሮ)፣ ጠንካራ የክስረት ህግ በተለይም ድንበር ተሻጋሪ የክስረት ህግ(cross border bankruptcy law) ኢንቨስትመንትን ከማበረታት አንፃር ያለውን ፍይዳ መዳሰስና በዚህ መስክ የኢቲዮጵያ የክስረት ህግ ስላለበት ክፍተት በዝርዝር የምመለከተው ይሆናል።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ደረሰኝ አለመቁረጥ እና የወንጀል ተጠያቂነት
በፍርድ ከሄደች በቅሎየ ያለፍርድ የሄደች ጭብጦየ (ለውጥ የሚሹ የፍርድ ቤት ጉዳ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 01 May 2024