Font size: +
10 minutes reading time (2050 words)

በፍርድ ከሄደች በቅሎየ ያለፍርድ የሄደች ጭብጦየ (ለውጥ የሚሹ የፍርድ ቤት ጉዳዮች)

ፍርድ ቤት የበደል ስር የሚቆረጥበት ፤ ተበዳይ የሚካስበት፤ አጥፊ የሚቀጣበትና መንግስት ከህግ በታች መሆኑ የሚረጋገጥበት መድረክ ነው፡፡ ፍርድ ቤት ፍትህ ከረቂቅነት ከፍ ብላ የምትታይ ፣ የምትሰማ እና የምትዳሰስ ህልው መሆኗ የሚታወቅበት አደባባይ ነው፡፡ ፍርድ ቤት የሰለጠነ ህዝብ የኔ የሚለውን ህግ የሚያስከብርበት መሳሪያ ነው፡፡ ህይወቱ ፣ ንብረቱና የኔ የሚላቸው እሴቶቹ ሁሉ ጥበቃ ያላቸው ስለመሆኑ የሚተማመንበት ዋሱ ነው ፍርድ ቤት፡፡

የምትታሰረው ፣ የምትፈታው፣ ከአታላዮች ገንዘብህን የምታስመልስው፣ ስሜ አስጠላኝ ልቀይር ፣ ትዳር ከበደኝ ልፋታ ካልክ መሄጃህ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ሞት የሚፈርደብህ፣ ቀሪ ዘመንህን በአንድ የተከለለ የቆርቆሮ ግቢ ውስጥ በጥበቃ ስር ሆነህ እንድታሳልፍ የምትገደደውም በፍርድ ቤት ነው፡፡ ተበድያለሁ ልካስ ፣ በድሏል ይቀጣ ፣ የመናገር ነፃነቴ ይከበር ፣ የመዘዋወር መብቴ ተገደበ ብለህ የምትጮህውም ፍርድ ቤት ነው፡፡ ክብሬ ተንክቷል ልከበር ፣ ስሜ ጠፍቷል ይታደስ ፣ ገንዘቤ ተወስዷል ይመለስ ማለት የምትችለውም በዚያው ነው፡፡ አርእስቱን የተቀኘው ባለቅኔም በፍርድ ከሄደች ብዙ ዋጋ ከምታወጣው በቅሎው ይልቅ ያለፍርድ የሄደችው በሳንቲም የምትተመነው ጭብጦው የቆጨችው ያለፍርድ በዘፈቀደ የሚደረግ ድርጊት የፍትህ መዛባት የፍርድ መጓደል አድርጎ ስለሚመለከተው ነው፡፡


ታዲያ ይህን ሁሉ ማድረግ የሚችሉት ፍርድ ቤቶቻችን እነዚህን ጉዳዮች በጊዜው ፣ በእኩል እና ያለአድሎ ለመፈጸም በሚያስችላቸው ቁመና ላይ ይገኛሉ? በርግጥስ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚታመን ሲቀጣም ሲፈታም ልክ ነው የሚባል ፍርድ ቤት ገንብተናል? ፍትህ ለሁሉም በግዜው ተደራሽ ሆኗል?


ፀሃፊው ለጥያቄዎቹ የሚሰጠው ምላሽ ከፁሁፉ አርእስት ጋር አንድ እና ያው ነው፡፡ ይህ ፅሁፉ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ክብርት ፕሬዝዳንቷ ከመሾማቸው ቀደም ብሎ ለንባብ ለማብቃት ታስቦ በመሃል ክብርት ፕሬዝዳንቷ በመመረጣቸው የፅሁፉ ፋይዳ ከትችት ወደ ቸግር ተቋሚነት ከፍ ብሏል፡፡ የትላንቱ የፍርድ ቤት ዘመን አጥፍቶም ሆነ አልምቶ አልፏል፡፡ ለለውጥ የተሾሙት እና የሚሾሙት አዲስ ሀይሎች የትላንቱን ችግር መፍትሄ ማፈላለጊያ በማድረግ አዲስ ዘመን እንደሚያነጉ ይታመናል፡፡
ይህ ፅሁፍ መንግስት ለፍርድ ቤቶች ትኩረት ከመንፈጉ የተነሳ፣ በተበላሸ አስተዳደር ምክንያት ፣ ለሙግት ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮች ፍርድ ቤቶችን በማጨናነቃቸው ሳቢያ ፣ ለነሱም ትኩረት እና ምስጋና ሳይቸራቸው በሚቻላቸው መጠን በችግሮቹ መሀል ያላቸውን የሰጡ ለሀቅ እና ለፍትህ የቆሙ ዳኞችን አይመለከትም፡፡ ይልቁንስ በዚህ ችግር መሃል የቻሉትን አድርገዋል እና ምስጋናየ ይድረሰቻው፡፡ ይልቁንም ፅሁፉ ለችግሮቹ ዋና ምክንያት የሆኑትን የትኩረት ማጣት፣ የአስተዳደር ብልሽት እና ስሁት የሆኑ የፖሊሲ ጉዳዬች ላይ ያተኩራል፡፡


ዳኛ መሆን የሚገባው ማን ነው፡፡


ዳኝነት ፍትህ ስጋ ለብሳ ነፍስ ዘርታ ህልው እንድትሆን የሚያስችላት እስትንፋሷ ነው፡፡ ያለዳኝነት ፍትህ የመፅሀፍ ላይ ተረተረት የማትዳሰስ መንፈስ ትሆናለች፡፡ ዳኛ ደግሞ የዳኝነት አጋፋሪው የፍትህ የመንበሯ ንጉስ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሰው ከፍ ሲል ለተገለፀው አባባል የሚመጥን ስብዕና ፤ እውቀት እና ክህሎት እንዲኖረው ይጠበቃል፡፡ ለፍትህ እንደተሰጠው ትርጉም ይሕ ስብዕና ያለውን ሰው ማግኘት ቀላል ጉዳይ እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ ይህ ሰው እንደ ስፓይደር ማን በፊልም አለም ያለ ጀግና ካልሆነ በቀር ምድራዊው ሰው ፍትህን በስሟ ልክ ሊሰጠን አይቻለውም፡፡ ነገር ግን ሰውነት የተሸለውን ለማድረግ መጣር ነውና ለዚህ ስብዕና የቀረበ ዳኛ ማግኘት ግድ ነው፡፡ የፍርድ ስራ የሕይወት ልምድን ፣የማህበረሰቡስብን ስነልቦና ማወቅን ፣ ህግን እንደወረደ ሳይሆን ፍትህንና ርትዕን ሊያሳካ በሚችል መንገድ መተርጎምን ፣ ትግስትን ፣ ከአድሎ መፅዳትን፣ ሁሉን እኩል ማየትን የሚጠይቅ ክህሎትም እውቀትም ነው፡፡ ይህን ሰው ከህግ ትምህርት ቤት የተመረቀን ወጣት አምጥቶ በመሾም ማግኘት ይቻላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በፍርድ ቤቶቻችን የተለመደው የዳኝነት አመራረጥ ስረዓት በአብዛኛው ከትምህርት ቤት የተመረቁ ብሎም ጥቂት የሚባል የስራ ልምድ ያላቸውን የህግ ባለሙያዎች አምጥቶ በመቅጠር ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ነገር ግን ሰው አብዝቶ በሚፈተንበት በእጅ በመሄድ ያሹትን ማድረግ በሚቻልበት ፤ የፖለቲካው ፣ የማህበራዊ ግንኙነት ፣ የንግድ እና የጥቅም ትስስስር አሻጥር በሞላበት የፍትህ ስረአት ይህን መቋቋም የሚችል አቅም ፣ ልምድ ፣ ክህሎት እና እውቀት ያላው ዳኛ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ከፍ ሲል እንደተገለፀው የፍርድ ስራ የህግ እውቀት ብቻ ሳይሆን የህይወት ልምድና የማህበረሰቡን ስነልቡና ማወቅን የሚጠይቅ ክህሎትም ጭምር ነው፡፡ ለፍርድ ስራ እውቀቱንም ክህሎቱንም ከትምህርት ቤትም ከግዜም የተማሩ ባለልምዶች ፤ ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ጉዳያቸው ያልሆነ በፍርድ ስራ ላይ በሚያሳዩት ብቃት ክብርን ማግኘት የሚሹ ሰዎችን ማሰባሰብ የሚፈልግ ይመስለኛል፡፡ በሀገራችን ፍርድ ቤቶች ግን እውነታው ከዚህ በተቃራኒ ሲሆን በህግ እውቀታቸው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ በበርካታ የስራ ልምዳቸው የተነሳ የፍርድ ስራን የሚያውቁ ባለሙያወችም ሆነ ሙሁራን የሚገኙት ከፍርድ ቤት ውጭ ነው፡፡


በስራ እና በህይወት ልምዳቸው የተነሳ የክርክር ሴራን የተነቀቁ ፣ የህይዎት ክህሎትን ያዳበሩ ፣ በትምህርትም ሆነ በልምድ የተሻሉ ጠበቆች በአንድ ከትምህርት ቤት ተመርቆ ከወጣ የህግ ምሩቅ ፊት የሚያደርጉት ክርክር ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይመስለኝም፡፡ ቀደም ሲል የህግ ምሩቃን እጥረት የነበረ በመሆኑ እና ከፍ ሲል የተገለፀው አይነት እውቀት እና ክህሎት በገበያው ላይ እንደልብ በማይገኝበት ጊዜ ይህን ማድረጉ ትክክል ነበር ሊባል ይችላል፡፡ ዛሬ ግን በርካታ የህግ ምሩቃን ከየዩንቨርሲቲዉ እንደ አሸን በፈሉበት በዚህ ግዜ የዳኝነት አመራረጥ ስረአት ከልምድ ወደ ፍርድ (from bar to court) ሊሆን ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡ በርግጥ እነዚህ ሰዎች ባለቸው ትምህርት እና የስራ ልምድ የተነሳ ካሉበት የተሻለ ኑሮ አነስተኛ ደመወዝ ወደ ሚከፈልበት የፍርድ ስራ ማምጣት ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡


ፍርድ ቤት የተከበረ እና ተገቢው እውቅናና ክብር የሚሰጥበት ቦታ ሊሆንም ይገበዋል፡፡ ዳኞች ባለስልጣኖች ብለን ከምንገልፃቸው የአስፈፃሚ መስሪያቤት ሀላፊዎች የሚበልጥ እንጅ የሚያንስ ሚና ስለሌላቸው ተገቢውን ጥቅማጥቅም እንዲከበርላቸው በማድረግ ቦታው የሚመጡበት እንጅ የሚሄዱበት እንዳይሆን ማድረግ ይገባል፡፡ ምናልባትም እነዚህ ሰዎች በአመዛኙ የኢኮኖሚ ጥያቄያቸውን የመለሱ በመሆናቸው ከፍረድ ቤት የሚፈልጉት ገንዘብ ሳይሆን ክብርን ሊሆን ስለሚችል ዳኝነትን እውቀቱም ልምዱም ክህሎቱም ባላቸው ዳኞች የሚመራና የተከበረ እንዲሆን በመስራት ሰዎቹን ወደ ዳኝነት ስራው መጥራት የሚቻል ይመስለኛል፡፡


አንድ ዳኛ ከታች ወደ ላይ የሚያድግበት ስረአትም ቢሆን በዘፈቀደ እና አንዱን ከሌላው በመሻሉ በመለየቱ በህግ እውቀት እና ክህሎቱ ስለበለጠ ባለጉዳዮችን ባግባቡ በማስተናገድ የተመሰገነ በመሆኑ እንዳልተመረጠ ለማወቅ የዳኝነት አመራረጥ ስረአቱን በማየት በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ በተለይ በነበረበት ፍርድ ቤት ባለጉዳይ በማንጓጠጥ ከህግም ከርትዕም የራቀ ውሳኔ በመስጠቱ በበላይ ፍርድ ቤት የተተቸ ዳኛ ለበለጠ ሹመት ሲታጭ ማየት የተለመደ መሆኑ የዳኝነት ሹመት ተገቢው ጥንቃቄ እና ትጋት የማይፈፀምበት ተግባር የነበረ መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡


ስራውንም ሰሪውንም የማይመጥን አሰራር፡፡


ከፍ ሲል እንደገለፅኩት በፍረድ ቤቶቻችን ላይ የሚታየው ችግር በአመዛኙ የአስረዳደር እና የትኩረት ማነስ ችግር ነው፡፡ ታዲያ በአንድ ችሎት የሚስተናገድ ሰላሳ እና አርባ መዝገብም በቀን የሚያይን ዳኛ በመዝገብ ቁልል ተከቦ ከእያንዳንዱ ባለጉዳይ ጋር ተጨቃጭቆ ሁሉም የኔ ቁስል ከሱ ይበልጣል የሚል አቤቱታ እያቀረበበት አስተዳደረዊውን ችግር እንደራሱ ችግር እያየ እንዲህ የሆነው ለዚህ ነው እንዲያ የሆነው ደግሞ ለዚያ ነው እያለ ሲውል እደማየት ያለ የሚያምም ነገር የለም ፡፡ ለዚያውም ስራውን የማይመጥን ደመወዝ እየተቀበለ ወቀሳ እንጅ ምስጋና የሌለውን ስራ እየሰራ፡፡ እዚህ ሀገር ህግ ተርጓሚውም ህግ ፈፃሚውም እኩል ቢቋቋሙም ህግ ተርጓሚው ተረስቷል መኪና ቤት ጥቅማጥቅም የሚባሉ ጉዳዮች የአስፈፃሚው እንጅ የተርጓሚው ጉዳዮች አልሆኑም፡፡


በመሆኑም የማህበራዊ ግንኙነቱ የኢኮኖሚውም ሆነ የፖለቲካ ጉዳዩ ማንጸሪያ ፍርድ ቤቶች በመሆናቸው የፍረድ ስራ ለሚሰሩ ዳኞች ስራቸውን የሚመጥን ጥቅም ፤ ክብራቸውን የሚመጥን ትኩረት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከኢኮኖሚ ጉዳያቸው ጋር የሚታገሉ ዳኞችንና ትኩረት የተነፈገው ፍርድ ቤት ይዘን የዳኝነት ነፃነት ልናስከብር አንችልም፡፡ የፍረድ ስራ ከኢኮኖሚያዊ ጥያቄህ ጋር እየታገልክ ከፈረድክበት ወንበዴ ጋር እየተጋፋህ የሚሰራ ስራ አለመሆኑ ታውቆ አስቸኳያ መፍትሄ ያስፈልገዋል፡፡
ስለ አንድ ነገር ብዙ ማወቅ ወይም ስለ ብዙ ነግር ጥቂት ማወቅ፡፡


በፍድር ቤቶቻችን ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር እዚህ ሀገር የሚያስከብረው ስለ አንድ ነገር ብዙ ማወቅ ሳይሆን ስለብዙ ነገር ጥቂት ማወቅ ነው፡፡ በሀገራችን የፍትህ ስረአትም ስለብዙ ነገር ጥቂት እንጅ ስለአንድ ነገር ብዙ ማወቅ እንብዛም ነው፡፡ ጠበቃው ፣ ዳኛው ፣ አቃቤ ህጉም ሆነ ሌላው የህግ ሙያተኛ ስለብዙ ነገር ጥቂት የማወቅ ግዴታ ወስጥ ወድቋል ይህም በአንድ ጉዳይ ላይ ከሌላው በላቀ ሁኔታ የጉዳዩን ብልት የተነቀቀን ሰው ማግኘትን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ እንዲህ አይነት ሰው ቢገኝ እንኳ ተገቢው ትኩረት እና እድል ስለማይሰጠው እውቀቱ የጋን ውስጥ መብራት ሆኖ የመቅረት እድሉ ሰፊ ነው፡፡


በመሆኑም ችሎቶች በዘረፍ በዘረፍ የንግድ ፣ የኮንስትራክሽን ፣ የቤተስብ ፣ የውርስ እየተባሉ እንደተከፈሉት ሁሉ ዳኞቻችንም የውርስ ፣ የቤተሰብ፣ የንግድ ዳኛ እየተባሉ በዘርፉ ልምድና እውቀት ያዳበሩ ሆነው እነዲሰሩ ለማድረግ ተገቢው ሊፈፀም ግድ ነው፡፡


እንዲሁም ሙስናን ለመከላከል ይሁን ምክንያቱ ምን እንደሆነ የማልረዳው ዳኞችን በየአመቱ ከአንድ ችሎት ወደ አንድ ችሎት መቀያየር ከሚያበጀው ይልቅ የሚፈጀው ስለሚበልጥ ሊተኮርበት የሚገባ አሰራር ነው፡፡ አንድን የክርክር ጉዳይ ያዳመጠ ፣ ለክርክሩ ተገቢነው ያለውን ትእዛዝ በመስጠት ክርክሩን የመራ ፣ የተከራካሪዎቹን ስሜት እና አኳኋን ሲያይና ሲሰማ የነበረን ዳኛ አንስቶ ጉዳዩን ሲከታተል ያልነበረ አዲስ ዳኛ መዘግብ ብቻ አይቶ እንዲወስን ወይም ከቆመበት እንዲቀጥል ማድረግ የዳኝነት ስራ በአይንም ፣ በጆሮም ፣ በልብም የሚገባ ጥበብ መሆኑን ካለመረዳት የመጣ ይመስለኛል፡፡ ተከራካሪዎች በክርክራቸው ፣ በስሜታቸው ፣ ባሰሟቸው ምስክሮቻቸው በዳኛው ልብ ውስጥ ያስቀመጡት ሙሉ ስሜት እና እውነት ወደ ወረቀት ሙሉ በሙሉ ሊውርድ ስለማይችል በዳኛው ልብ ውስጥ እንደቀረ እንዲቀር በማድረግ ለተዛባ ፍርድ የሚዳርግ ብሎም የመዝገብ ጥናት በሚል አዲሱ ዳኛ ለሚወስደው ግዜ ለተራዘመ የቀጠሮ ምክንያት ከሚሆን በቀር ፋይዳው እንብዛም ነው ፡፡


የተራዘመ ቀጠሮ (ከመክሰስ መከሰስ)


በአሁኑ ግዜ ከመክሰስ መከሰስ ይሻላል የሚል የህብረተሰብ እሮሮ አብዝቶ መሰማቱ የሚያሳየው ከመበ'ደል መበደል ከመቀ'ማት መቀማት ከመጭበርበር ማጭበርበር የሚሻል መሆኑን የሚጠቁም አስደንጋጭ አነጋገር ነው፡፡ ምክንያቱም ተበደልኩ ብሎ የሚከስ ተበዳይ በፍርድ አደባባይ ተሟግቶ ፍትህ ለማግኘት ጉልበቱን ፣ ገንዘቡንና ግዜውን የሚያባክን በመሆኑ ይህን ማለቱ እውነት አለው፡፡ ከዚህ ግዜ ብኋላም በፍርዱ ሳይረካ ከፍርድ አደባባይ የሚገለልበት አጋጣሚ ብዙ በመሆኑ ቢፈረድለትም ከወሰደው ግዜ ፣ ካወጣው ገንዘብ እና ካፈሰሰው ጉልበት አኳያ ከፍርድ ይልቅ ጉልበት እንደሚሻል ስለሚረዳ ከመክሰስ መከሰስን ይመርጣል፡፡ አንድ የወንጀልም ሆነ የፍታብሄር ጉዳይ ሶስት አመት እና ከዚያ በላይ የሚወስድ በተለይም በእያንዳንዱ አመት ከሶስት እና አራት ግዜ በላይ ሳይቀጠር በጥበቃ የሚያሳልፈው ግዜ ለባለጉዳዩ መማረር አይነተኛ መክንያት ነው፡፡ ይርጋ በሚባል ስረአት በግዜ ክሰስ ብለህ በግዜ ፍርድ አለመስጠት ደግሞ የማይታረቅ ተቃርኖ ነው፡፡


በሌላ በኩል ባለሙያዎች የፍርድ ስራን በችኮላ መከወን ፍትህን ያዛባል ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ መሰረተ ሀሳቡ ትክክል ነው፡፡ ይሁን እንጅ ፍርድቤቶቻችን የተጠቀሰውን ግዜ የሚወስዱት የያዙትን አንድ መዝገብ ለመስራት ሳይሆን ባለባቸው የስራ ጫና እና የመዝገብ ፈሰት የተነሳ በሚሰጡት የተራራቀ ቀጠሮ እና ተደጋግመው በሚሰጡ የማይፈቱ የቀጠሮ መለወጫ ችግሮች የተነሳ በመሆኑ የፍትህ ስረአቱ ችግር የተቻኮለ ፍርድ ሳይሆን የፍርድ መዘግየት ነው፡፡


አመታቶችን አስቆጥሮ በዚህ መንገድ ከፍርድ አደባባይ የተገፋ ተበዳይ ደግሞ ነገ የበዳይን ጫማ ለመልበስ ወደኋላ እንደማይል ማሰብ አይከብድም፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቶቻችን አንድን ጉዳይ በግዜ ለማጠናቀቅ መላው ምንድ ነው? የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ እና በትክክል ሊመልሱ ግድ ነው፡፡


ለፍርድ ስራ የማይመቹ አሰራሮች እና የማስቻያ ስፍራዎች፡፡


ፍትህ የሚለካው በፍትህነቱ ብቻ ሳይሆን ፍትህ በሰፈነበት ወይም በተሰጠበት መንገድም ጭምር ነው፡፡ ይህ መንገድ ደግሞ የሙግት ስረአቱን ፤ የዳኞች ባለጉዳይን የሚያስተናግዱበትን አግባብ ፤ ክርክር የሚደረግባቸው የችሎት መድረኮች ምቾትን ይመለከታል፡፡ ፍርድ ቤቶች የሌሎችን መብት እንዲከበር ለማድረግ የተቋቋሙ ተቋማት እንደመሆናቸው በአሰራራቸው ፣ በባለጉዳይ አያያዝ ፣ ለሰራተኛው እና ለተገልጋዩ ምቹ ከመሆን አኳያ ከማንም የላቁ ሆነው መገኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡


በአሁኑ ግዜ በየፍርድ ቤቶቻችን የሚታዩ ጉዳዮችን ለአብነት ብናነሳ ፍርድ ቤቶቻችን በዚህ ረገድ ገና ከኋለኛው ሰልፍ እንዳሉ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ጊዜ ገንዘብም ህይወትም በሆነበት ዓለም ሁለት ሰአት ተኩል እንድትቀርብ የሚል ካልቀረበ በነጻነቱ በገንዘቡ ላይ የሚጣል ቅጣት እንዳለ የሚያመለክት ትእዛዝ ለባለ ጉዳዩ የላከ ፍርድ ቤት ከቀኑ አምስት ሰዓት ላይ ጉዳዩን ማስተናገድ በየትኛውም መንገድ ተገቢ አሰራር አይሆንም፡፡ ባለጉዳዩ ጥሎት የመጣው ኢኮኖሚያው ማህበራዊ ጉዳይ ያለው እንደመሆኑ ያለአንዳች ስራ በጥበቃ ማሳለፍ ባለጉዳዩን ብቻ ሳይሆን ባለጉዳዩ ጥሎት የመጣውን ኢኮኖሚያዊ ወይም ማህበራዊ ጉዳይ ጭምር የሚጎዳ ተግባር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተደጋጋሚ በብዙ ሰዎች ላይ ሲደረግ ሀገራዊ ጉዳቱ ማንም ያልተረዳው ተገቢው ትኩርት የተነፈገው ክስረት ነው፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የያዘው ጉዳይ ለሚሰራበት ጊዜ ተካፍሎ ጉዳዮች በተመደበላቸው ግዜ እንዲጠናቀቁ ለማድረግ ጥረት ሊደረግ ይገባል፡፡


ተሰደብኩ ተዋረድኩ ብሎ መብቱን ሊጠይቅ ሊያስከብር በመጣ ባለጉዳይ ላይ በእብሪት ፣ በቁጣ እና በማሸማቀቅ የሚደረግ የችሎት አውድ ፍርድ ቤቱን የማይመጥን ሊታገሱት የሚችሉት ተግባር አይደለም፡፡ ዳኛ ቻይ አስተዋይ እና አመዛዛኝ ሊሆን የሚገባው በመሆኑ በችሎት የሚከሰቱ ፈታኝ ሁኔታዎችን የሚያስተናግደበት ጥበብ ሊላበስ ይገባዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ ዳኞች የሚሰሩት ጥፋጥ ካለ መከታተል የሚያስችል ስረአትም መዘርጋት የሚገባ ይመስለኛል፡፡


አንድ ባለጉዳይ ወደ ተቋምህ ለአገልግሎት ሲመጣ አንተ በተቋሙ ያልህን ምቾት ያህል እንኳ እንዲሰማው ማድረግ ባትችል ቢያንስ መሰረታዊ የሆኑ ፍላጎቶቹን ልታሟላ ይገባል፡፡ ጧት ጠርተህው ማታ የምታስተናግደውን ባለጉዳይ ቢያንስ ቁጭ ብሎ እንዲጠብቅ ማረፊያ ማዘጋጀት ግድ ነው፡፡ በየፍርድ ቤቱ መቆም ህመም የሚሆንባቸው ታማሚዎች አቅመ ደካሞች ባሉበት ሁኔታ ይህን ችግር አለማስተዋል እና በዝምታ ማለፍ መሰረታዊ ግድፈት ነው፡፡ የፍርድ ቤት ሽንት ቤቶች በቁልፍ ቆልፈህ እየተጠቀምክ ባለጉዳይ የሚተነፍስበት ሽንት ቤት መከልከል ህግን ከሚያስከብር ተቋም የሚጠበቅ አይደልም፡፡


ግልፅ እና ምቹ ችሎት


የተለየ ምክንያት ከሌለ በቀር የሙግት ስረአቱ በግልፅ በአደባባይ መደረግ እንዳለበት ህግ ያዛል፡፡ ይሕ ህግ ባለበት ሙግቱን በዳኞች ቢሮ እና አስር ሰው እንኳን መያዝ በማይችሉ ማስቻያዎች ማስቻል ህግን መጣስ ሙግት በአደባባይ እንዲሆን የተፈለገበትን አላማም መሳት ነው፡፡ ሙግት በአደባባይ በህዝብ ፊት ሲፈጸም አንተም ትታረማለህ ሌላውም ይማራል የሚለው ንግግር እንዲሁ ለማለት የሚባል ንግግር ሳይሆን በርግጥም ለስረአቱ መሻሻል የሚያዋጣው አብርክቶ ከፍ ያለ ነው፡፡ የአደባባይ ሙግት የዳኞች መለኪያ ሚዛንም ነው፡፡ የሙግት አመራር ጥበብህ ፣ የእውቀትህና ክህሎትህ እንዴትነት ማወቅ የሚቻለውም ሙግት በየስርቻው ሳይሆን በአደባባይ ሲደረግ ነው፡፡ በመሆኑም ክርክሮች በርከት ያለ ሰው በግልፅ እና ምቹ በሆነ የችሎት አዳራሽ እንዲደረጉ ተገቢው ሁሉ ሊፈፀም ግድ ነው፡፡ ፍርድ ሲታይ እና ሲሰማ የፍርድ ቤቶች ተጠያቂነት ለማስፈን ቀላል ይሆናል፡፡


ፍርድ ቤቶች የሁሉም ናቸው ሲባል የሁሉም ናቸው ማለት ነው በዚህ ሁሉም ውስጥ ታዲያ አካል ጉዳተኞች ሴቶች አቅመ ደካሞችም አሉ እነዚህ ሰዎች በልካቸው ማስተናገድ የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለው ጥያቄ መሰረታዊ ብቻ ሳይሆን ህግም እንዲከበር የሚያዘው ግዴታ ነው፡፡ በአሁኑ ግዜ በአመዛኙ ፍርድቤቶቻችን የሚያስችሉባቸው የችሎት ስፈራዎች አይደለም ከፍ ሲል ለተገለፁት የህብረተሰቡ ክፍሎች ይቅርና ለሌላው ማህበረሰብም የሚመቹ አይደሉም፡፡ በተለይ በኪራይ በተለያየ ቦታ ለፍርድ ስራ የዋሉ ህንፃዎች ለፍርድ ስራ የማይመቹ የአገልጋዩንም የተገልጋዩንም ምቾት የማይጠብቁ በግዴለሽነት ለግብር ይውጣ የተከወኑ ተከራዩን ሳይሆን አከራዩን ማእከል ያደረጉ ስፍራዎች ይመስላሉ፡፡ በተለይ ለእነዚህ ህንፃዎች ኪራይ የወጣው ገንዘብ አስቀድሞ ታቅዶ በአላማ ስራው ተከውኖ ቢሆን ኖሮ ፍርድቤቶቻችን የቤት እንጅ የመሬት ችግር ስለሌለባቸው በየፍርድቤቶቹ ግቢ ወይም በሌላ ተስማሚ ቦታ በቀላሉ የሚሰሩ ቤቶችን በመገንባት ዘላቂ የሆነ ጥቅም መስጠት የሚችሉ ቤቶችን ማግኘት በተቻለ ነበረ፡፡

ትለብሰው የላት ትከናነበው አማራት


ለፍረድ ቤቶች ትኩረት አልተሰጠም የተባለውን ያህል ፍርድ ቤቶቹም የሚመደብላቸውን በጀት የሚጠቀሙበት መንገድ የሚያስገርም ነው፡፡ ክርክር የሚገለብጥ ፀኃፊ የለም ፤ የክርክር መቅረጫ ትርንስክራይበር ተበላሽቷል የሰው ሀይል እጥረት አለ በሚሉ ምክንያቶች ሶስት አራት ግዜ ቀጠሮ በሚሰጥበት ፍርድ ቤት አነስተኛ ወጭ የሚጠይቁ ነገርግን ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጡ የፍትህ ስራውን የሚያቀላጥፉ መሳሪያዎች ተትተው ውድ የሚባሉ መኪናዎችን መግዛት ፣ ግቢን በኮንክሪት መሙላት፣ ሰራተኛውን ዩኒፎርም ማልበስ የመሳሰሉ ስራዎችን ማየት ተገቢ መስሎ አይሰማኝም በርግጥ ሁሉም ቢሟላ እሰይው ነገርግን ሁሉን ማድረግ በማያስችል የማያወላደ በጀት ውስጥ ቅድሚያ ማግኘት የሚገባቸውን ቸግሮች ቅድሚያ አለመስጠት ተገቢ ባለመሆኑ ሊታረም የሚገባው አካሄድ ነው፡፡


መደምደሜ


መደምደሚያው እኒህን ዘመን ተሸግረው ተከባለው የመጡ ችግሮችን መደምደም ነው፡፡

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በኢትዮጵያ የክስረት ሕግ ነጋዴ ከሰረ የሚባለው መቼ ነው? ከክሥረት ጋር የተያያ...
ስለ ንብረት የዋጋ ግምት ጥቂት ነጥቦች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024