Font size: +
27 minutes reading time (5435 words)

ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብትን በመተርጎም በኩል ስለታየው ችግር

ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት& ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግጋት እና በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የተካተቱት ሥነ ሥርዓታዊ መብቶች መሠረታዊ ዓላማ መርማሪ አካላት ያለበቂ ምክንያትና ሕጋዊ ሥርዓት የአንድን ሰው የነጻነት መብት እንዳይጥሱ ዋስትና እና ጥበቃ መስጠት ነው፡፡ የብዙ አገሮች ሕገ መንግሥት የአንድ ሰው በሕይወት የመኖር& የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ክቡርነት የመነጩ ሊደፈሩና ሊገሰሱ የማይችሉ መብቶች መሆናቸውን ያረጋገጣሉ@ መሠረታዊ መብቶቹ ተግባር ላይ እንዲውሉ ጥረት የሚደረግ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በሌላ በኩል የእነዚህን መብቶች አፈፃፀም የሚሸረሽሩ ወይም ዋጋ የሚያሳጡ የተለያዩ የወንጀል ድርጌቶች በዓለም ውስጥ በየደረጃው በስፋት ሲፈፀም ማየትና መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህ የማይጣጣም ሁኔታ ከልዩ ልዩ የጥቅም ግጭቶች& ከአመለካከት ልዩነት& ካለመቻቻልና ከመሣሰሉት መንስዔዎች የሚመነጭ ሊሆን ይችላል፡፡

በዓለም አቀፍ ሆነ በብሔራዊ ሕግጋት ዕውቅና ከተሰጣቸው መሠረታዊ መብቶች አንዱ በወንጀል የተከሰሰ ሰው ጉዳዩ ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት ታይቶ ጥፋተኛ መሆኑ እስካልተረጋገጠ ድረስ ከወንጀል ነፃ እንደሆነ የመቆጠር መብት ያለው መሆኑ ነው፡፡ ይህ መሠረታዊ መብት ዕውቅና ሊያገኝ የቻለው ንፁሀን ግለሰቦች በወንጀል በመጠርጠራቸው ወይም በመከሰሳቸው ብቻ ሊደርስባቸው የሚችለውን የተለያየ የመብት ጥሰት ለመግታት ነው፡፡

ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ የተያዘ ሰው በመሠረቱ የተጠረጠረበት ወንጀል በማስረጃ ከተረጋገጠበት ሊፈረድበት@ ማስረጃ ከሌለ ግን ሊፈታ ይገባል፡፡ ሆኖም መረማሪ ፖሊስ ወይም ዐቃቤ ሕግ ጉዳዩን እስኪያጣሩና ለፍርድ እስኪቀርብ ድረስ ታሣሪው በጥፋተኝነት የማይቀጣበት ወይም በፍጹም ነፃነት የማይለቀቅበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህም በዋስ የመለቀቅ መብት ነው፡፡ መንግሥት የሕብረተሰብን ሰላምና ፀጥታ የማስከበር እንዲሁም የግለሰብን መብትና ነፃነት የማክበር ሃላፊነት አለበት፡፡ መንግሥት የወንጀል ተግባር ፈጽመዋል በማለት በሚይዛቸው ሰዎች ላይ ሕግ ለማስከበር የሚፈጽመው ተግባር ሁለት ተፋላሚ የሆኑ ጥቅሞችን የሚያስታርቅና የሚያቻችል መሆን አለበት፡፡ የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሲባል በከባድ የወንጀል ተግባር የተጠረጠሩ ሰዎችን በፍርድ አደባባይ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ  ከፍርድ በፊት ማሰሩ ተገቢ ሲሆን በሌላ በኩል ተጠርጠረው የታሰሩ ሰዎች ንፁህ ሰዎች የሚሆኑበት እድል ሰፊ ስለሆነ ከፍርድ በፊት እንዳይታሰሩ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡  

የዋስትና መብት ታሪካዊ ዳራ በትንሹ 

የዋስትና መብት በወንጀል የተጠረጠረ ወይም የተከሰሰ ሰው& የተጠረጠረበት የወንጀል ጉዳይ ምርመራ እስኪጠናቀቅ ወይም ክሱ በፍርድ ቤት ታይቶ ውሣኔ እስኪያገኝ በሚፈለግበት ጊዜና ቦታ ለመቀረብ ግዴታ ገብቶ ወይም ግዴታውን የሚወጣለት ዋስ ጠርቶ ከእስር የሚለቀቅበት ወይም ከመታሰር የሚድንበት ሥርዓት መሆኑን ከዋስትና ድንጋጌዎች አጠቃላይ ይዘት መረዳት ይቻላል፡፡ የዋስትና ሥርዓቱ ሌላው ገጽታ መብትን ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን በመብት ተጠቃሚው በኩል ግዴታ መግባትን የሚጠይቅ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

የወንጀል ተግባር ፈፅሟል ተብሎ በጥርጣሪ የተያዘን ሰው ወደፍርድ አደባባይ አቅርቦ በወንጀል ሕግና ሥነ ሥርዓት መሠረት የመጨረሻ ውሣኔ እስኪያገኝ ድረስ በጊዜ ቀጠሮ በማረሚያ ቤት ከማቆየት ይልቅ የዋስ መብቱን ጠብቆ መልቀቅ ይሻላል የሚለው መሠረተ ሀሳብ በሁሉም አገሮች ተቀባይነት አግኝቶ ተግባር ላይ ከዋለ አያሌ ዘመን አልፏል፡፡ የተጠርጣሪዎችን የዋስ መብት በመፍቀድ መልቀቅ የተጀመረበትን ዘመን በግልጽ ለመናገር ባይቻልም አንዳንድ ጽሑፎች እንደሚጠቁሙት ለምሳሌ በእንግሊዝ አገር በጥንት ጊዜ የወንጀል ተግባር የፈፀሙ ሰዎችን አስረው የመጠበቅ ሥልጣን የነበራቸው ሼሪፎች ከዚህ ከፍተኛ ወጪ ከሚጠይቅ አስቸጋሪ የግል ሀላፊነት ለመዳን አቀደው የፈጠሩት ዘዴ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት አለ፡፡ በወቅቱ ዳኞች ከአንዱ አገር ወደሌላው አገር እየተዘዋወሩ ዳኝነት ይሰጡ ስለነበር ተጠርጣሪዎች ተራ ደርሷቸው ጉዳያቸው እስኪሰማ ድረስ ብዙ ጊዜ ሰለሚወስድና እስር ቤቶቹ ለጤና ምቹ ስላልነበሩ ብዙ እስረኞች ጉዳያቸው ውሣኔ ከማገኘቱ በፊት በእስር ላይ እንዳሉ ይሞቱ ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ አሳዛኝ ሁኔታ ሸሪፎች እስረኞችን በራሳቸዉ ዋስትና ወይም ፍርድ ቤት ሊያቀርባቸው በሚችል በሌላ ሰው ዋስትና ከአስር ይለቋቸው ነበር፡፡ ይህ እስረኞችን በዋስ የመልቀቀ ተግባር ይፈፀም የነበረው ለሸሪፎቹ በሕግና በመመሪያ በተሰጠ ሥልጣን ሳይሆን በራሳቸው ሀላፊነት ከእስረኞቹ ጋር በሚፈጽሙት ስምምነት ብቻ ነበር፡፡  

እስረኞችን በዋስ የመልቀቅ አሰራር ጠቃሚ መሆኑ ሰለታመነበት እስረኞች በምን ዓይነት ሁኔታ የዋስ መብታቸው ሊከበርላቸው እነደሚገባ የሚወስን ሕግ ወጣ በዚህ ሕግ መሠረት ዳኞች የእስረኞችን የዋስ መብት በመጠበቅ ለመልቀቅ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ እስረኛው በቀጠሮው ቀን ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ሊያስገድደው የሚችል የገንዘብ ወይም የንብረት ወይም የሰው ዋስ እንዲጠራ ይደረጋል፡፡ የተያዘ ሰው በቀጠሮ ቀን ሳይቀርብ ቢቀር ለዋስትና ማስከበሪያ የተያዘው ገንዘብ ወይም ንብረት ለመንግሥት ገቢ ይሆናል፡፡ የዋሶቹ ገዴታ የተያዘው ሰው በቀጠሮ ቀን ሳይቀርብ ቢቀር ለመንግሥት የዋስትናውን ገንዘብ ገቢ ማድረግ በመሆኑ ዋስ መሆን ይችሉ የነበሩት ሀብት ያላቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ በተለምዶ ባለርስቶች የበለጠ ተቀባይነት የነበራቸው ሲሆን ተከሳሹ እንዳይጠፋ ለማድረግም የማሰር ስልጣን ተሰጥቷቸዉ ነበር፡፡

በጊዜ ሂደት ተጠርጣሪዎችን በዋስ የመልቀቅ እና ያለመልቀቅ ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ሆነ፡፡ ተከሣሹ በቀነ ቀጠሮ ከመቅረብ ይልቅ ይጠፋል የሚል ጥርጣሬ ዋሱ ካደረበት አስሮ እንዲያቆየው ሥልጣን ይሰጠው ነበር፡፡ ተከሳሹ በቀጠሮ ቀን ሳይቀርብ ከቀረ ዋሱ ፍልጐ የማቅረብ ግዴታ ነበረበት፡፡ በኃላ ግን ዋሱን በዚህ መልክ ከማስጨነጭ ይልቅ ተከሳሹ ቢጠፋ ዋሱ የዋስትናውን ገንዘብ ለመንግሥት እንዲከፍል ብቻ የማድረግ አሰራር ተተካ፡፡

በዘመናዊ የሕግ አስተሳሰብ መሠረት በዋስ ለመልቀቅ ከሚያበቁ ምክንያቶች መካከል ጎልቶ የሚታየው ማንኛውም በወንጀል የተከሰሰ ሰው በፍርድ ቤት ገና የጥፋተኝነት ውሳኔ ሳየሰጥበት ሊቀጣ አይገባውም” የሚለው ነው፡፡ አስተዋይነት በተሞላው በዚህ ዘመናዊ የሕግ አስተሳሰብ መሠረት ወንጀል ሰርቷል በመባል የተከሰሰ ሰው በሕግ የተቋቋመ ፍርድ ቤት በሕጋዊ  መንገድ የተሰበሰቡ ማስረጃዎችን ሰምቶ የጥፋተኝነት ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስ ንጹህ ሰው እንደሆነ ይቆጠራል፡፡ እንዲህ ያለውን ሰው ጥፋተኛ መሆኑ ገና ሣይረጋገጥ በእስር ቤት እንዲቆይ ማድረግ ንፁሁን ሰው ያለጥፋቱ እንደመቅጣት ስለሚቆጠር በዋስ መልቀቅ የተሻለ አሠራር ሆኖ ተገኝቷል፡፡ 

ጉዳዩ ገና በመጣራት ወይም በቀጠሮ ላይ ያለ ተከሣሽ በዋስ ሊለቀቅ ይገባል የሚባለበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ተከሣሹ የመከላከያ አቤቱታውን እንዲያዘጋጅ እና  ማስረጃዎቹን እንዲያሰባስብ በቂ ጊዜና አመቺ ሁኔታ ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ ለምሳሌ ምስክሮቹን ለይቶ የሚያውቃቸው ራሱ ተከሣሹ ብቻ ሊሆን ስለሚችል አድራሻቸውን ፈልጎ ለማገኝተ እንዲችል& ሌሎች ማስረጃዎቹን እንዲያጠናቅርና ከጠበቃው ጋር እንደልቡ እየተገናኘ ስለክርክሩ ስትራተጂ እንዲቀይስ ከእስር መለቀቅ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ፍትሕን ለመጠበቅ ሲባል አንድ ተከሣሽ መከላከያውን በደንብ እንዲያዘጋጅ በቂ ዕድል ሊሰጠው ይገባል፡፡  እነዚህ ምክንያቶች አሳማኝ ቢሆኑም እንኳን ከባድ ወንጀል ሰርተዋል ተብለው ለሚከሰሱ ሰዎች በዋስ   ቢለቀቁ   ፍርድ ቤቱ  ጉዳዩን  ሰምቶ  ሊወስንባቸው  የሚችለውን ከባድ  ቅጣት   ከመቀበል   ይልቅ መጥፋቱንና ሐብታቸውን ማጣቱን ይመርጣሉ ተብሎ ስለሚገመት የዋስ መብት ይነፈጋቸዋል፡፡ በአሜሪካን ሀገር በሞት ከሚያስቀጡ ወንጀሎች በስተቀር በሌሎች በማናቸውም ዓይነት ወንጀሎች የሚከሰስ ሰው በዋስ የመለቀቅ መብት አለው@ ይሁን እንጂ በሞት በሚያስቀጡ ወንጀሎች የተከሰሱ ሰዎችንም ቢሆን ፍርድ ቤቱ አይጠፉም ብሎ ከገመተ በዋስ ሊለቃቸው ይችላል፡፡   

የዋስትና መብት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት እና በዓለም አቀፍ ሕጎች   

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ለተያዙ ሰዎች ከሚያረጋግጣቸው መብቶች ውስጥ የዋስትና መብት አንዱ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ 6፦

የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት አላቸው@ ሆኖም በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትና ላለመቀበል ወይም በገደብ መፍታትን ጨምሮ በቂ ዋስትና ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ ለማዘዝ ይችላል ”  በማለት ይደነግጋል፡፡ (ሠረዝ የተጨመረበት) 

ይህ ድንጋጌ የሚገልፀው በዋስ የመፈታት መብት በመርህ ደረጃ የማንኛውም የተያዘ ሰው መብት ሲሆን በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ግን ፍርድ ቤት በተያዙ ሰዎች የሚቀርብለትን በዋስትና የመለቀቅ ጥያቄ ሊነፍግ& ሊገድብ እንደሚችል ወይም በቂ የሆነ የዋስትና ማረጋገጫ አስቀርቦ የመፍቻ ትዕዛዝ ለመስጠት የሚችል መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም የዋስትና መብት መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት ቢሆንም ፍጹም መብት ሳይሆን በሕግ አግባብ ሊነፈግ የሚችል መሆኑን ነው፡፡ 

ኢትዮጵያ በዓለም ሕብረተሰብ አባልነቷ በየጊዜው የምታፀድቃቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ሕጎች አሉ፡፡ እነዚህ ስምምነቶችና ሕጎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያራምዱ ቢያንስ የማይጎዱ ቢሆንም ኢትዮጵያን ግዴታ ላይ የሚጥሉ ናቸው፡፡ ስለሰብአዊ መብቶች በየጊዜው እና በየደረጃው የፈረመቻቸው የቃል ኪዳን ውሎች በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9(4) እንደ ተመለከተው ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ሰምምነቶች ሁሉ ፓርላማ እንዳወጣቸው ተቆጥረው በአገር ውስጥ እንደ አገር ሕግ ተወስደው ተፈፃሚነት የኖራቸዋል፡፡  ኢትዮጵያ  ከተቀበለቻቸው  ዓለም አቀፍ  የሰብአዊ መብት  ስምምነቶች  መካከል  የሲቪል እና  የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን አንቀጽ 9(3) እና  በማንኛውም  ሁኔታ  ታስረው ወይም  ታግተው የሚገኙ  ሰዎችን መብት ለመጠበቅ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወጣ መመሪያ በመርህ/Principle/ 39 ላይ ዋስትና መንፈግና በእስር ማቆየት እንደመርህ መታየት እንደሌለበት የሚደነግጉ ናቸው፡፡ 

Anyone arrested or detained on a criminal charge shall be brought promptly before a judge or other officer authorized by law to exercise judicial power and shall be entitled to trial with in a reasonable time or to release. It shall not be the general rule that persons awaiting trial shall be detained in custody, but release may be subject to guarantees to appear for trial, at any other stage of the judicial proceedings, and, should occasion arise, for execution of the judgement.[Emphasis added]

Except in special cases provided by the law, a person detained on criminal charge shall be entitled, unless a judicial or other authority decides otherwise in the interest oF the administration of justice, to release pending trial subject to the conditions that may be imposed in accordance with the law. Such authority shall keep the necessity of detention under review.  [Emphasis added]

የተጠቀሱት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግጋትና መርሆዎች በግልፅ የሚያረጋግጡት የዋስትና መብትን እንደመርህ እንዲሁም በቅድመ ክስ መሰማት ወቅት የሚፈፀምን የማረፊያ ቤት እስራትን እንደ ልዩ ሁኔታ ወይም እንደ መጨረሻ አማራጭ የሚወሰድ መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡ የኢፌዲሬ ሕገ መንግሥት እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግጋትና መርሆዎች በወንጀል የተጠረጠረ ወይም የተከሰሰ ሰው የተጠረጠረበት ወይም የተከሰሰበት ጉዳይ በፍርድ ቤት ከመሰማቱ በፊት መታሰር  የሌለበት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በፍርድ ቤት የወንጀሉ ክስ ከመሰማቱ በፊት የተከሣሹን ነጻነት ለመጠበቅ የተፈለገበት ምክንያት የጥፋተኛነት ውሣኔ በፍርድ ቤት ከመሰጠቱ በፊት በተከሣሹ ላይ ቅጣት ላለመጣልና  ተከሣሹ  ለቀረበበት  ክስ  ያለአንዳች  መሰናክል  መከላከያ  እንዲያዘጋጅ  ለማስቻል  ነው፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 13(2) በምዕራፍ ሦስት የተዘረዘሩት መሠረታዊ  የመበቶች እና የነፃነቶችድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግጋት& ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች& ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ መተርጎም እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ ከድንጋጌዎቹ መረዳት የሚቻለው ዋስትና የማይፈቀድባቸውን ልዩ ሁኔታዎች በመደነገግ ረገድ ለሕግ አውጪው ሥልጣን የተሰጠው መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን ሕግ አውጪው የዋስትና መብትን በመገደብ የሚያወጣው አዋጅ ከሕገ መንግሥቱና ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግጋት ጋር የተጣጣመ እና የዋስትና መብትን በውስን አድማስ ከመገደብ አልፎ ዋናውን መብት የሚያሳጣና የሚንድ መሆን የለበትም፡፡

የዋስትና ክርክር በሚሰማበት ጊዜ አስፈላጊ ከሆኑ ሁኔታዎች አንዱ የተያዘው ሰው ፈጽሞታል ተብሎ የተጠረጠረበት የወንጀል ዓይነት ነው፡፡ በአደገኛ ቦዘኔ በሚገባ ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው በዋስትና  አይለቀቅም ወይም በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በዋስ እንዲለቀቀቅ ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል@ ሆኖም የተከሰሰበት ወንጀል ከአስር ዓመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ በዋስትና መልቀቅ አይቻልም በተጨማሪም ማንኛውም የተያዘ ሰው የተከሰሰበት ወንጀል የሞት ቅጣትን ወይም አሰራ አምስት ዓመት ወይም በላይ የሆነ ጽኑ እስራት የሚያሰቀጣው ከሆነ በዋስትና ለመልቀቅ አይቻልም፡፡  እነዚህ ሕጎች የዋስትና ክስ በሚሰማበት ጊዜ ተጠርጥረው ለተያዙ ሰዎች እጅግ አስፈላጌና ወሣኝ ሁኔታዎች ሲሆኑ ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው አንድ ሰው ከእነዚህ ድንጋጌዎች በአንዱ ሥር በሚካተት ወንጀል በተከሰሰ ጊዜ ፍርድ ቤት ዋስትና የመፍቀድ ሥልጣን የለውም፡፡ እንደ ሕጎቹ ድንጋጌ ከሆነ የዋስትና መብትን ወዲያውኑ የነፍጋሉ@ ፍርድ ቤቶች የዋስትና መብትን እምቢ እንዲሉ ያስገድዷቸዋል፡፡ የእነዚህ ሕጎች ሕገ-መንግሥታዊነት የሕግ ባለሙያዎችን በሁለት የተለያዩ አቅጣጫ እያከራከረ ያለ ሲሆን ሁለቱም ለክርክራቸው ደጋፊና ዋቢ አድርገው የሚጠቅሱት የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 19(6) ላይ የተደነገገውን ነው፡፡ ለልዩነቱና ለክርክሩ መነሻ ምክንያት የሆነው በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች (In Exceptional Circumstances Prescribed By Law)  ከሚለው  የድንጋጌው  ይዘትና ኃይለ  ቃል  ውስጥ  ልዩ ሁኔታዎች ”  (Exceptional      Circumstances) ለሚለው ሐረግ በሚሰጠው ትርጉም ላይ የሚመሠረተ ነው፡፡ አንደኛውን አስተሳሰብ በሚያራምዱ የሕግ ባለሙያዎች እምነት ሕገ መንግሥቱ በዋስትና መብት ገደብ እንደሚደረግበት ቢደነግግም ይህ ገደብ በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትና ላለመቀበል ወይም በገደብ መፍታትን ጨምሮ በቂ ዋስትና ማረጋገጫ እንዲቀርብ ለማዘዝ ይችላል በሚል መልክ የተደነገገ በመሆኑ ገደቡ እንደጉዳዩ ዓይነት ፍርድ ቤት ውሣኔ የሚሰጥበት እንጅ ሕግ አውጪው አንድን የወንጀል ዓይነት ነጥሎ በማውጣት በዚህ ወንጀል የተጠረጠረ ወይም የተከሰሰ ዋስትና አይጠበቅለትም እንዲል ሥልጣን አይሰጠውም፡፡ ልዩ ሁኔታዎች ማለት ደግሞ ፍርድ ቤቶች እንደነገሩ ሁኔታ የእያንዳንዱን ተጠርጣሪ ወይም ተከሣሽ ግላዊ የአደገኝነት ሁኔታ& ያለፈ የሕይወት ታሪኩን& የወንጀሉን ከባድነትና ጊዜ ቀጠሮውን አክብሮ መቀረብ ወይም አለመቅረቡን ጉዳዩን ሲመረምሩ የሚያዩትና የሚደርሱበት እንጅ ቀድሞ በሕግ ሊወሰን የሚችል አይደለም፡፡ በመሆኑም የተጠቀሱት የአዋጁ ድንጋጌዎች ከሕገ መንግሥቱ በተቃራኒ የተቀመጡ በመሆኑ ፍርድ ቤቶች ዋስትናን በሚመለከት ሁኔታዎችን እየመረመሩ ውሣኔ እንዳይሰጡ የሚከለክሉ ስለሆነ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 19(6)& 20(3) እና 37(1) ይቃረናሉ፡፡ ስለሆነም ድንጋጌዎቹ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(1) መሠረት ተፈጻሚ እንዳይሆኑ ሊደረግ ይገባል በማለት የመከራከሪያ ሀሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡ 

ሁለተኛውን አስተሳሰብ በሚያራምዱ የሕግ ባለሙያዎች እምነት የተጠረጠሩ ወይም የተከሰሱ ሰዎች ከመርህ አኳያ በዋስ የመውጣት መብት የተከበረላቸው ቢሆንም ይህ መብት ፍፁማዊ መብት አይደለም፡፡ የተጠረጠሩ ወይም የተከሰሱ ሰዎች በዋስ የመለቀቅ ወይም ያለመለቀቅ ሁኔታ በሕግ የተወስነ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(6) ድንጋጌ ሕግ አውጪው የዋስትና መብትን የሚገድብ ሕግ ሲደነግግ አንድን የወንጀል ዓይነት ለይቶ በመደንገግ በዚህ ወንጀል የተጠረጠረን ወይም የተከሰሰን ሰው በዋስትና መልቀቅ አይቻልም  እንዲል  ሥልጣን  ይሰጠዋል፡፡ ሕግ  አውጪው  ልዩ ሁኔታዎችን  በሁለት አማራጮች ሊያውጅ  ይችላል@ በአንድ በኩል ዋስትና የሚያስከለክሉ የወንጀል ዓይነቶችን ለይቶ በመደንገግ ሲሆን (ለምሳሌ ቅጣቱ ቀላልም ይሁን ከባድ ወይም ዋስትና የሚያስከለክል ሁኔታ መኖር አለመኖሩ ግምት ውስጥ ሳይገባ በአደገኛ ቦዘኔ ወይም በአሸባሪነት ወንጀል የተከሰሰ የዋስትና መብት የለውም)@ በሌላ በኩል ደግሞ በማንኛውም ዓይነት ወንጀል ቢሆን ዋስትና ሊያስከለክሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን በዝርዝርና በግልጽ ለመደንገግ መብት ይሰጠዋል የሚል ነው (ለምሳሌ የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ አንቀጽ 67 ከ(ሀ-ሐ))፡፡ እንደነዚህ የመከራከሪያ ነጥብ ከሆነ በተለዩ የወንጀል ዓይነቶች የተጠረጠሩ ወይም የተከሰሱ ሰዎችን የዋስትና መብት ወዲያውኑ የሚነፍጉት ድንጋጌዎች ሙሉ በሙሉ ከኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 19/6/ ጋር የተጣጣሙ ናቸው በማለት ይከራከራሉ፡፡

ከላይ ያየናቸው የዋስትና መብትን ወዲያውኑ የሚነፍጉት ሕጎች በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ መብቶችን ይጥሳሉ የሚል አቤቱታ በተለያየ ጊዜ ለተለያዩ ፍርድ ቤቶች እና ለሕገ መንግሥት ጉዳዩች አጣሪ ጉባዔ ቀረበው የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ አስነስተው ነበር፡፡

ማሳያ-1 (Case-1)

በከሣሽ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙሰና ኮሚሽን እና በተከሣሽ እነ አሰፋ አብረሐ መካከል በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በወንጀል መዝገብ ቁጥር 7366 ህዳር 5 ቀን 1993 ዓ/ም በተደረገ ክርክር ተጠርጣሪዋቹ የተከሰሱት በሙስና ወንጀል ሲሆን ሕጉ የተያዙ ሰዎች ፈጽመውታል ተብሎ የተጠረጠሩበት ወንጀል የሙስና ወንጀል ከሆነ በዋስትናቸው ላይ ፍጹማዊ ክልከላ ያደርጋል፡፡ የተጠርጣሪ ጠበቆች ዋስትናን በግልጽ የሚከለክለው የሕግ ድንጋጌ ከኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 19/6/ ጋር የሚቀረን ነው በማለት ተከራከረዋል፡፡ በኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ በኩል የነበረው መከራከሪያ የተከሰሱትን ሰዎች በዋስ መልቀቅ ግልጽ የሆነ የሕግ ጥሰት ነው ያለ ሲሆን በተጨማሪም የተከሣሻቹ ጠበቆች ዋስትና የሚከለክለው ሕግ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም በማለት ያቀረቡት መከራከሪያ ተቀባይነት የለውም ምከንያቱም ሕገ መንግሥቱ የዋስትና ክልከላ በልዩ ሁኔታ ፈቀዶል በማለት ተከራክሯል፡፡ ክርክሩን ሲሰማ የነበረው ፍርድ ቤት በሙስና ወንጀሎች ጉዳይ ዋስትና የሚከለክለው ሕግ ግልጽ ስለሆነ ትርጉም አያስፈለገውም በማለት አስታውቋል፡፡ በመቀፀልም የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 19/6/ ሀሳብ ፍርድ ቤት በሕግ የተደነገጉትን ልዩ ሁኔታዎች መሠረት በማድረግ የዋስትና መብት መከልከል እንደሚችል ነው፡፡ ልዩ ሁኔታዎች የሚለው የሕገ መንግሥቱ እሳቤ በተለያዩ ሕጎች ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ለሙሰና ወንጀሎች ዋስትና የሚከለክል ልዩ ሕግ ወጥቷል፡፡ ስለሆነም በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች  ዋስትና የሚከለክለው የልዩ ሕግ አዋጅ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የልዩ ሁኔታዎች እሳቤ መስፈርት የሚያሟላ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ትንታኔውን ሲደመድም ሕጉ ግልጽ ስለሆነ ሕጉን ከመተግበር ውጭ አማራጭ የለም ያለ ሲሆን የተከሳሽ ጠበቆቹን የመከራከሪያ አቤቱታ መሰረተ ቢስ ነው በማለት ውድቅ አድርጐታል፡፡

ማሳያ-2(Case-2)

በሌላ ተመሳሳይ ጉዳይ በከሣሽ የፌዴራል ዐቃቤ ሕግና በተከሣሽ እነ ኢንጅነር ሐይሉ ሸዋል መካከል በወንጀል መዝገብ ቁጥር 34246 በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህዳር 4 ቀን 1997 ዓ/ም በተደረገ የዋስትና ክርክር ጉዳይ& ዋስትና ወዲያውኑ የሚከለክለው የሕግ ድንጋጌ ሕገ-መንግሥታዊ ጥየቄ አሰነስቶ ነበር፡፡ ዐቃቤ ሕግ በ1ኛ ክሰ የተከሰሱት ሰዎች የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥትና ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን በሀይል ለማፍረስ ሞክረዋል በማለት በወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ለ፣ 38፣ 34፣ 27/1/ እና አንቀጽ 258 መሠረት ክስ መስርቶባቸዋል፡፡ ተከሳሾቹ የተከሰሱበት ወንጀል በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ቅጣት ሊያስቀጣ እንደሚችል ግልጽ ነበር፡፡ ተከሳሾቹ ምንም እንኳን የወ/መ/ሥ/ሥ/ ሕ/ ቁጥር 63 የዋስትና መበታቸውን ወዲያውኑ የሚከለክል ቢሆንም ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄቸውን መርምሮ ለመወሰን ስልጣን እንዳለው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥትና ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች በመጥቀስ ተከራክረዋል፡፡ በተጨማሪም የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የዋስትና መብት በሕግ እንዲከለከል አልፈቀደም ስለሆነም ዋስትና ወዲያውኑ የሚነፍገው የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 63 ድንጋጌን ውድቅ እንዲያደርገው ፍርድ ቤቱን ለማሳመን ጥረዋል፡፡ ዓቃቢ ሕግ በበኩሉ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 19 /6/ መንፈስና ይዘት የዋሰትና መብት በሕግ መሠረት ሊከለከል አንደሚችል በመግለጽ እና የሕገ መንግሥት ጉዳዩች አጣሪ ጉባዔ በሕግ ዋሰትና መከለከል ሕገ-መንግሥታዊ ነው በማለት አስተያየተ መስጠቱን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱ ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ኮንፌሽን አንቀጽ 9/3/ እና የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 19/6/ ለጉዳዩ አግባብነት ያለው ለመሆኑ ገልጾል፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች አፈጻጸም የመንረዳው በዋስትና መለቀቅ መርህ ሲሆን ዋስትና መከልከል የጠቅላላው መርህ ልዩ ሁኔታ ነው በማለት ገልጾል፡፡ ፍርድ ቤቱ ዋስትናን በሕግ መከልከል አይቻልም የሚለውን መከራከሪያ ውድቅ በማድረግ መከራከሪያው ከኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 19/6/ እይታ ውሃ የሚቋጥር አይደለም ምክንያቱም የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ፍርድ ቤት በሕግ የተመለከቱ ሁኔታዎችን መሠረት በማድረግ ዋስትና እንዲከለክል በግልጽ ይፈቅድለታል በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡  

የውጭ ሀገር  ልምድ  /Foreign  Experience/

በዚህ ረገድ የሌሎች ሐገሮችን የሥነ-ሥርዓት ሕግና ልምድ  በምንቃኝበት ጊዜ አብዛኞቹ ሐገሮች ተከሣሽ የተከሰሰበትን የወንጀል ዓይነት ለዋሰትና ማስከልከል ብቸኛ ምክንያት ወይም መስፈርት አድርገው አይወስዱም፡፡

በካናዳ በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ዋስትና የሚያስከለክል አሳማኝ ምክንያት በሌለበት ሁኔታ የዋስትና መብታቸውን ያለማጣት መብት አላቸው፡፡ ተከሳሽ የተጠቀሰበትን ወንጀል መሠረት በማድረግ ብቻ የዋስትና መብት አይከለከልም፡፡ ከዚህ ይልቅ ዐቃቤ ሕግ የተከሣሽ የዋስትና መብት ተነፍጎ በማረሚያ ቤት እንዲቆይ አሰፈላጊ የሆነበትን ምክንያት በቅድሚያ ማስረዳት አለበት፡፡ ይህም ማለት ተከሣሽ  በየቀጠሮው  ፍርድ ቤት  እንዲቀርብ  ለማድረግ እስርቱ አስፈላጊ መሆኑን ወይም  የተከሣሽ በማረሚያ ቤት መቆየት ለሕዝብ ደህንነትና ጥበቃ አስፈላጊ መሆኑን ወይም ተከሣሽ በዋስ ቢለቀቅ ሌላ ወንጀል የሚፈጽም መሆኑን ዐቃቤ ሕጉ በተጨባጭ ማሳየትና ማስረዳት አለበት፡፡

በእንግሊዝ በዋስትና መለቀቅ መርህ ነው፡፡ ነገር ግን ተጠረጣሪው በግድያ ወንጀል፣ በግድያ ሙከራ  በአስገድዶ መድፈር፣ በአስገድዶ መድፈር ሙከራ ወይም በከባድ ግብረ ሥጋ ግንኙነት ወንጀሎች& በአንዱ ወንጀል ከተከሰሰ እና ቀደም ሲል በእንግሊዝ ውስጥ ከእነዚህ ወንጀሎች በአንዱ ጥፋተኛ ተብሎ የተፈረደበት ከሆነ& ተጠርጣሪው የዋስትና መብቱ ሊነፈግ እንደማይገባ ለፈርድ ቤቱ የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡ ተጠርጣሪው ያለበትን የማስረዳት ኃላፊነት በአግባቡ ከተወጣ ፍረድ ቤቱ በዋስትና ሊለቀው ይችላል፡፡ ይህ ነው ፍርድ ቤትን በዋስትና ጥያቄ ላይ የመጨረሻ ውሣኔ ሰጭ ነው የሚያሰኘው፡፡

በፈረንሳይ የወንጀሉ ከባድነት ለዋስትና ክርክር አስፈላጊ አይደለም፡፡ ዋስትና ከፍትሕ አስተዳደሩ ሰላም ጋር በተዛመዱ ምክንያቶች ብቻ ሊከለከል ይቻላል፡፡ ዳኞች ክሱ በፍርድ ቤት ከመሰማቱ በፊት የተጠርጣሪው መታሰር ለፍትሕ አስተዳደሩ ሰላም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኙት ዋስትና ሊከለክሉ ይችላሉ፡፡

ለጉዳዩ አግባብነት ያለው የደቡብ አፍሪካ ሕግ ዋስትና የሚከለክሉ ወንጀሎችን በዝርዝር አይደነግግም፡፡ በዋስትና ጥያቄ ላይ ውሣኔ ሲሰጥ ሕጉ ቅጣትን እንደ ብቸኛ መስፈርት አድርጎ አልደነገገም፡፡ በመርህ ደረጃ እያንዳንዱ ወንጀል የሚያስከትለው ቅጣት ግምት ውስጥ ሳይገባ ዋስትና ይፈቀዳል፡፡ ዋስትና ፍጹማዊ መብት ባለመሆኑ ምክንያት ዐቃቤ ሕግ የተጠርጣሪውን በዋስትና መለቀቅ ሊቃወም ይችላል፡፡ ተጠርጣሪው ለፍትሕ ጥቅም ሲባል በዋስትና እንዳይፈታ ዐቃቤ ሕግ ፍርድ ቤትን የማሳመን አላፊነት አለበት፡፡ ተጠርጣሪው ለፍትሕ  ጥቅም   ሲባል ዋስትና ሊከበርለት አይገባም የሚለው የዐቃቤ ሕግ መከራከሪያ ተጠርጣሪው በዋስትና ቢለቀቅ  ይጠፋል፣  ምርመራውን  ያደናቅፋል ወይም ምስክሮችን  ያባብላል& ሌላ ወንጀል በመፈጸም ጉዳት ያደርሳል የሚለውን ነጥብ ያሲዛል፡፡ ተጠርጣሪው በተወሰኑ ወንጀሎች ለምሳሌ በግድያ፣ በአስገድዶ መድፈር፣ በከባድ ውንብድና የእርሱ መታሰር የፍትሕ ፍላጎት እንዳልሆነ የማስረዳት ሸክሙን ከተወጣ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቱን ይጠበቅለታል፡፡

በአሜሪካ የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት አላቸው፡፡ ተጠርጣሪው የፈፀመውን ወንጀል ምክንያት በማድረግ ብቻ የተጠርጣሪውን ዋስትና ሊያሳጣ የሚችል ወንጀል የለም፡፡ የተከሣሽ በዋስ የመለቀቅ ወይም ያለመለቀቅ ውሣኔ መሠረት የሚያደርገው በሌላ ተጨማሪ ፍሬ ነገር ላይ ነው፡፡  ዳኞች ተከሣሽ ቀጠሮውን አክብሮ በችሎት ለመገኘቱ፣ ከውንጀል ምርመራ እንቅስቃሴ ጋር በተያይዞ መስናክል ላለመፍጠሩ እና ሌላ ወንጀል ላለመፈጸሙ ማረጋገጫ እንዲሰጥ በማድረግ በቅድመ ሁኔታ በዋስ ሊፈቱት ይችላሉ፡፡ ዳኞች  ቅድመ ሁኔታዎቹ በተጠርጣሪው የማይከበሩ  መሆኑን ባረጋገጡ ጊዜ ቀደም ሲል የፈቀዱትን ዋስትና በማንሳት በማረሚያ ቤት ሆኖ እንዲከራከር ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ የአሜሪካ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ አንድ ሰው በነፍስ ግድያ ወንጀል ቢጠረጠርም የተጠረጠረበትን ወንጀል መነሻ በማድረግ ብቻ በዋስትና መለቀቁን የሚከለክል አይደለም፡፡ በተጨማሪ The Federal Bail Reform Act of 1984 ተብሎ የሚጠራው ሕግ ተጠርጣሪው የተጠረጠረበትን ወንጀል መሠረት በማድረግ ብቻ ዋስትናውን እንዲያጣ አልደነገገም፡፡ ፍርድ ቤቱ የዋስትና ክርክር በሚሰማበት ወቅት ግምት ውስጥ ከሚያስገባቸው አያሌ መስፈርቶች አንዱ የወንጀሉ ዓይነት ነው፡፡

በሙስና  ወንጀል  ዋስትናን  የሚከለክለው  ሕግ ሕገ መንግሥትዊ አይደለም በማለት የቀረበ አቤቱታን በሚመለከት የተሰጠ የሕገ መንግሥት ትርጉም አስተያየት፡፡

የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ጉዳዩች አጣሪ ጉባዔ የፀረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጁን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 239/93 አንቀጽ 51(2) ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን ስለሆነ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን መሆኑን በማረጋገጥ ወደ ፌደሬሸን ምክር ቤት አቅርቦ እንዲያስወስንልን በማለት የቀረበለትን አቤቱታ ተመልክቶ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 84(2) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የሚከተለውን የሕገ መንግሥት ትርጉም ሃሣብ አቅርቧል፡፡

አቤቱታ አቅራቢዎች፦   

የዚህ አቤቱታ አቅራቢዎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በእስር የሚገኙ ሲሆኑ ሁሉም በፀረ ሙስና አዋጅ ዋስትና አይፈቀድላቸውም የተባሉ ናቸው፡፡ 

የቀረበው አቤቱታ ይዘት፦ 

አቤቱታ አቅራቢዎቹ የሙስና ወንጀል ፈጽማችኃል በሚል ጥርጣሪ ተይዘው በእስር ላይ የሚገኙ መሆናቸውንና የተጠረጠሩበት ጉዳይ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል እየተጣራ የሚገኝ ሲሆን& ጉዳዩ እስኪጣራ ድረስ በዋስ የመፈታት መብት ተነፍጎን በእስር ላይ እንገኛለን በማለት አመልክተዋል፡፡ 

የአቤቱታ  አቅራቢዎች  አቤቱታ  ይዘት  ዝርዝር  ሲታይ  ቀጥሎ  የተመለከቱትን  ነጥቦች  ያነሳል፡፡

1.     ምንም እንኳን የሙስና ወንጀል ፈጽማችኃል በሚል ክስ ቢቀርብብንም ጉዳያችንን በዋስ እንድንከታተል ልንከለከል የማይገባን ሆኖ ሳለ በፀረ-ሙስና ልዩ ሥነ-ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 239/1993 አንቀጽ 51(2) ድንጋጌ መሠረት የዋስትና መብት እንዳይፈቀድልን ተከልክሏል፡፡ ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ ዋስትናን በፍርድ ሊታይ የሚገባ ጉዳይ አድርጎ የደነገገው ከመሆኑም በላይ በዋስትና የመፈታት መብትን እንደ መርህ& አለመፈታትን እንደ ልዩ ሁኔታ አስቀምጦታል፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ ግን የአዋጁ አንቀጽ 51(2) በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው የዋስትና መብት አይኖረውም በማለት ፍርድ ቤት የዋስትና መብት እንዳይፈቀድ መደንገጉ ሕገ መንግሥቱ  ያረጋገጠውን  በዋስ  የመፈታት  እና  ከፍርድ  በፊት እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር መብትን የሚጥስ ነው፡፡ በመሆኑም የተጠቀሰው የአዋጁ ድንጋጌ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 19(6) እና 20(3) ይቃረናል፡፡                    

2.    የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(6) በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትና ላለመቀበል... የሚለው አባባል ሕግ አውጪው ዋስትና ሊከለከል የሚችልበትን ሁኔታ በሕግ ለይቶ እንዲያስቀምጥ እንጂ አንድን ወንጀል ነጥሎ በማውጣት በዚህ ወንጀል የተከሰሰ ዋስ ይከልከል በማለት ሕግ እንዲያወጣ ሕገ መንግሥቱ አይፈቀድም፡፡ ይሁን እንጂ የአዋጁ ድንጋጌ ከዚሁ በተቃራኒ የተቀመጠ በመሆኑ ፍርድ ቤቶች ዋስትናን በሚመለከት ሁኔታዎችን እየመረመሩ ውሣኔ እንዲሰጡ የሚከለክል ስለሆነ ይህ የአዋጁ ድንጋጌ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 37(1) ይቃረናል፡፡ 

3.    የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13 ንዑስ ቁጥር 1 እና 2 ማንኛውም ሕግ አውጪ& አስፈጻሚ እና የዳኝነት አካል በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት ሥር የተዘረዘሩትን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነጾች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዲታ ያለበት መሆኑን እና ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች መካከል አንዱ የሆነው የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል-ኪዳን አንቀጽ 9(3) በበኩሉ ዋስትና መንፈግና በእስር ማቆየት እንደመርህ መታየት እንደሌለበት የሚደነግግ ሲሆን የአዋጁ አንቀጽ 51(2) ግን ዋስትና መነፈግን እንደመርህ ተቀብሎ የተያዙ ሰዎች በዋስትና እንዳይፈቱ ያዛል፡፡ ይህ ደግሞ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 13 ይቃረናል የሚል ነው፡፡ 

አቤቱታ አቅራቢዎቹ አዋጅ ቁጥር 239/1993 አንቀጽ 51(2) ድንጋጌ ከፍ ሲል የተዘረዘሩትን የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች የሚጥስ በመሆኑ እና በአጠቃላይ የሕገ መንግሥቱን የበላይ ሕግነት የሚጋፋ ስለሆነ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ይባልልን በማለት ጠይቀዋል፡፡  

የሕገ መንግሥት ትርጉም  አስተያየት      

በዚህ ጉዳይ ላይ የቀረበውን የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ለመመልከት አግባብነት ያላቸው ሕጎች ድንጋጌዎች እና የአቤቱታ አቅራቢዎች አቤቱታ በዝርዝር ታይቷል፡፡ በዚህ ጉዳይ የሚነሳው መሠረታዊ ጭብጥ አዋጅ ቁጥር 239/1993 አንቀጽ 51(2) በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው የዋስትና መብት አይኖረውም በማለት የደነገገው ድንጋጌ ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ነው፡፡  

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ለተያዙ ሰዎች ከሚያረጋጋግጣቸው መብቶች ውስጥ የዋስትና መብት አንዱ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ (6) የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት አላቸው@ ሆኖም በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትና ላለመቀበል ወይም በገደብ መፍታትን ጨምሮ በቂ የዋስትና ማረጋገጫ እንዲቀርብ ለማዘዝ ይችላል በማለት ይደነግጋል፡፡ 

ይህ ድንጋጌ የሚገልፀው በዋስ የመፈታት መብት የማንኛውም የተያዘ ሰው መብት መሆኑን& በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ግን ፍርድ ቤት በተያዙ ሰዎች የሚቀርብለትን በዋስትና የመለቀቅ ጥያቄ ላለመቀበል እንደሚችል ወይም ደግሞ የተያዘውን ሰው በቂ የዋስትና ማረጋገጫ አቅርቦ በገደብ እንዲፈታ ለማዘዝ የሚችል መሆኑን ነው፡፡  

ኢትዮጵያ በተቀበለቸው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽንም ሆነ በሕገ መንግሥታችን የዋስትና መብት ከነፃነት መብት ጋር በቀጥታ የተቆራኘና የነፃነት መብትን በተለይ የወንጀል ክስ በፍርድ ቤት የተከሣሽ የግል ነፃነት (Pretrial Freedom) መከበር ያለበት መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ 

Every One has the right to liberty and security of person. No one shall be subjected to Aribitrary arrest or detention. No one shall be deprived of his liberty except on such grounds and in accordance with such procedures as established by Law.

በዚህ መሠረት ኮንቬንሽኑ የሚያረጋግጠው ማንም ሰው የነፃነት እና የደህንነት መብት ያለው መሆኑን& ማንም ሰው በጭፍን እንዲያዝ ወይም ተይዞ እንዲቆይ መደረግ የሌለበት መሆኑን እና በሕግ በተመለከቱ ምክንያቶች እና ሥነ ሥርዓቶች ካልሆነ በቀር ማንም ሰው የግል ነፃነቱን ማጣት የሌለበት መሆኑን ነው፡፡

ሕገ መንግሥታችንም በተመሳሳይ መልኩ በአንቀጽ 17 በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ማንኛውም ሰው ወንድም ሆነ ሴት ነፃነቱን አያጣም፡፡ ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ሊያዝ& ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም በማለት ይደነግጋል፡፡

ይህ ድንጋጌ የአንድን ሰው የግል ነፃነት ለመገደብ በሕግ የተደነገገ ሥርዓት መኖር እንዳለበት& በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ አንድን ሰው መያዝ ወይም ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ማሰር እንደማይቻል ይገልጻል፡፡ የዚሁ ድንጋጌ የእንግሊዝኛ ቅጅ ግን የአንድን ሰው የግል ነፃነት መገደብ የሚቻለው በሕግ በተደነገገ ሥርዓት መሠረት ብቻ ሳይሆን በሕግ በተደነገጉ ምክንያቶች ጭምር መሆን እንዳለበት የሚገልጽ ከመሆኑም በላይ ማንንም ሰው በጭፍን መያዝ (Arbitrary Arrest) የተከለከለ መሆኑን ይገልጻል፡፡ የሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 13(2) በምዕራፍ ሦስት ሥር የተዘረዘሩ መብቶችና ነፃነቶች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግጋት& ስምምነቶችና መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ መተርጎም የሚገባቸው መሆኑን ስለሚደነግግ ስለ ነፃነት መብት የሕገ መንግሥታችን የእንግሊዝኛውን ቅጅ የሚደነግገውን ድንጋጌ ኢትዮጵያ ከተቀበለቸው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ኮንቬንሽን ስለነፃነት መብት ከተደነገገው ድንጋጌ ጋር ስለሚቀራረብ በዚህ እረገድ ልንወስደው ይገባል፡፡

ከተጠቀሰው ኮንቬንሽንም ሆነ በሕገ መንግሥታችን የግል ነፃነት ለመገደብ ወይም ለማሳጣት የሚቻለው በሕግ በተደነገጉ ምክንያቶችና ሥነ-ሥርዓቶች ስለመሆኑ& የአንድን ሰው የግል ነፃነት ለመገደብ የመያዣ ምክንያቶችና የመያዣ ሥነ-ሥርዓቶች በሕግ በግልፅ ሊደነገጉ እንደሚገባ@ በሕግ ከተመለከተው ምክንያቶችና ሥነ-ሥርዓት ውጭ አንድን ሰው መያዝ ወይም ማሰር የተከለከለ መሆኑን እና በጭፍንነት የግል ነፃነትን ማሳጣት የተከለከለ መሆኑን እንረዳለን፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ (Human Rights Committee) በተጠቀሰው ኮንቬንሽን ስለ ጭፍንነት (Arbitrariness) የሚገልፀውን ሐረግ በሚመለከት የሰጠው ትርጓሜ Arbitrariness’ is not to be equated with ‘against the law’ but must Be Interpreted more broadly to include the elements of inappropriateness, injustice and lack of predictability such that remand in custody must not only be lawful but also reasonable in all circumstances.” የሚል ነው፡፡ በመሆኑም በጭፍን መያዝ የተከለከለ ነው የሚለው ሐረግ የአንድን ሰው የግል ነፃነት ለመገደብ በሕግ በግልጽ የተደነገጉ የመያዣ ምክንያቶችና ሥነ ሥርዓቶች መኖራቸውን ብቻ ሳይሆን እነዚህ በሕግ የተደነገጉ ነጻነትን ሊገድቡ የሚችሉ ሕጎች የማያዳሉ ፍትሐዊና ሊተነበዩ የሚችሉ መሆን የሚገባቸው መሆኑን ያመላክታል፡፡ የነጻነት መብት በወንጀል የተከሰሰን  ሰው  የተከሰሰበት ጉዳይ  በፍርድ ቤት  ከመሰማቱ  በፊት መታሰር (Pre-trial detention) የሌለበት መሆኑን ይገልጻል፡፡ በፍርድ ቤት የወንጀሉ ክስ ከመሰማቱ በፊት የተከሳሹን ነጻነት (Pre-trial freedom) ለመጠበቅ የተፈለገበት ምክንያት የጥፋተኝነት ውሣኔ በፍርድ ቤት ከመሰማቱ በፊት በተከሣሹ ላይ ቅጣት ላለመጣልና ተከሣሹ ለቀረበበት ክስ ያለአንዳች መሰናክል መከላከያ እንዲያዘጋጅ ለማስቻል ነው፡፡ ምንም እንኳ በአንድ በኩል ክስ ከመሰማቱ በፊት የተከሣሽን የግል ነጻነት መጠበቅ የሚያስፈልግ ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ተከሣሹ ቢለቀቅ ክሱ በሚሰማበት ወቅት ፍርድ ቤት ላይቀርብ ስለሚችል መንግሥት ተከሣሹን ለፍርድ ለማቅረብ ካለው ፍላጎት ጋር የተከሣሹ መብት መጣጣም ይኖርበታል፡፡ የዋስትና መብት በመሠረቱ የሚያነጣጥረው እነዚህን ሁለት ጥቅሞች (Interests) በማጣጣም ላይ ሲሆን የተለመደው መሠረታዊ ዓላማው ተከሣሽን የቀረበበት ክስ በፍርድ ቤት ከመሰማቱ በፊት በእስር በማቆየት ለመቅጣት ሳይሆን ክሱ በሚሰማበት ወቅት ፍርድ ቤት እንዲቀርብ በቂ ተያዥ (Guarantee) አምጥቶ ከእስር እንዲለቀቅ ለማድረግና ፍርድ ቤት በሚወስነው ማናቸውም ጊዜ ተከሣሹን ፍርድ ቤት የሚቀርብ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው፡፡ 

በሲቪልና በፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ኮንቬንሸንም ሆነ ሕገ-መንግሥታችን የነፃነት መብት በማናቸውም ሁኔታ የማይገደብ ለማናቸውም ለተያዙ ሰዎች ሁልግዜ መከበር ያለበት መብት አይደለም፡፡ እነዚህ ሕጎች ለተያዙ ሰዎች በዋስትና የመለቀቅ መብት ያላቸው መሆኑን የሚያረጋግጡ ቢሆኑም ውስን በሆኑ በሕግ በግልጽ በተደነገጉ ምክንያቶችና ሥነ ሥርዓቶች መሠረት ግን የተከሣሾችን የዋስትና መብት በመገደብ ተከሣሾቹ የተከሰሱበት የወንጀል ጉዳይ በፍርድ ቤት ከመሰማቱ በፊት በእስር እንዲቆዩ ለማድረግ ሕጎቹ ይፈቅዳሉ፡፡ የሕገ መንግሥታችንን አንቀጽ 16(6) እና 17 በማያያዝ ስናነበው በሕግ በተደነገጉ ምክንያቶችና ሥርዓቶች ካልሆነ በቀር ማንም ሰው ነፃነቱን ማጣት የሌለበት መሆኑን& ወይም ሳይፈረድበት መታሰረ የሌለበት መሆኑን& የዋስትና መብት ገደብየለሽ ሳይሆን በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ሊገደብ እንደሚችል& ሕግ አውጪው ልዩ ሁኔታዎች ናቸው በማለት በግልጽ በሚያውጃቸው ድንጋጌዎች መሠረት በተወሰኑ ጉዳዩች የአንድን ተከሣሽ የዋስትና መብት ፍርድ ቤት ላለመቀበል እንደሚችል ያስረዱናል፡፡ ሆኖም የዋስትና መብትን የሚገድብ ሕግ የነፃነት መብትንም ስለሚገድብ ሕጉ የዋስትና መብት የሚነፈግባቸውን ምክንያቶችና ሥርዓቶች በግልጽ የሚደነግግና ገደቡም በጭፍን ወይም በሚያዳላ ወይም ኢፍትሐዊ ወይም በማይተነበይ አኳኋን ሊፈፀም የማይገባ መሆኑን የሚያረጋግጥ መሆን አለበት፡፡ የዋስትና መብት በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች የሚገደበው በሁለት መንገድ ነው@ አንዱ መንገድ በማናቸውም የወንጀል ክሶች ላይ የዋስትና መብት ጥያቄ ተቀባይነት እንዳያገኝ ፖሊስ ወይም ዐቃቤ ሕግ ተቃውሞ ሊያቀርብባቸው የሚችልባቸውን ምክንያቶች ወይም ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄን ላለመቀበል የሚያስችሉትን የተወሰኑ ምክንያቶች በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ በግልጽ ዘርዝሮ መደንገግ ነው፡፡ ለምሳሌ በሐገራችን የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ ቁጥር 67 መሠረት በዋስትና ወረቀት የመልቀቅ ማመልከቻን መቀበል የማይቻለው፦  

ሀ/  በዋስትናው ወረቀት የተመለከቱትን ግዴታዎች አመልካቹ የሚፈጽም የማይመስል የሆነ እንደሆነ 

ለ/  አመልካቹ ቢለቀቅ ሌላ ወንጀል ይፈጽም የሆናል ተብሎ የሚገመት ሲሆን 

ሐ/  ምስክሮችን በመግዛት (በማባበል) ወይም ማሰረጃ የሚሆኑበትን ያጠፋ የሆናል ተብሎ የሚገመት ሲሆን ነው፡፡ በማለት ይደነግጋል፡፡ 

 

ሌላው መንገድ ደግሞ የዋስትና መብት የማያሰጡ ወንጀሎችን (Non-Bailable Offences) በመዘርዘር ማስቀመጥ ነው፡፡ ለምሳሌ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጋችን አንቀጽ 63(1) ማንኛውም የተያዘ ሰው የተከሰሰበት ወንጀል የሞት ቅጣትን ወይም አሥራ አምስት ዓመት ወይም በላይ የሆነ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣው ከሆነና ወንጀል የተፈፀመበት ሰው በደረሰበት ጉዳት የማይሞት የሆነ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ የዋስትና ወረቀት አስፈርሞ ለመልቀቅ ይችላል፡፡ በማለት የተደነገገው ድንጋጌ ሌላውን የዋስትና መብት የሚገደብበት መንገድ የሚያመለክት ነው፡፡ 

በዚህ ረገድ የውጭ ሀገር ልምድን ለማየት የዩናይትድ ስቴትስን ልምድ ስንወስድ የሚከተለውን እንረዳለን፡፡ በአሜሪካ ሁሉም የክልል መንግሥታት በከባድ ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች When the proof is evident or the presumption is great that the accused committed an offence የዋስትና መብት በፍርድ ቤት ሊገደብ እንደሚችል ይደነግጋሉ፡፡  

ሁሉም የአሜሪካ ክልሎች የግድያ ወንጀል የዋስትና መብትን የሚከለክል መሆኑን የሚደነግጉ ሲሆን& ከዚህም በተጨማሪ የተወሰኑ የክልል መንግሥታት የበታች ፍርድ ቤት ዳኞችን (magistrates) በከባድ ወንጀል ለተከሰሱ ሰዎች ወይም ከዚህ ቀደም በወንጀል ለተቀጡ ሰዎች የዋስትና መብት እንዲከለክሉ ያዛሉ፡፡ ሌሎች የተወሰኑ የአሜሪካ ክልል መንግሥታት ደግሞ የዋስትና መብት የማይከበርባቸውን የወንጀል ዓይነቶች በመዘርዘር ይደነግጋሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር በአሜሪካ በፌዴራል ደረጃ የወጣው the Federal Bail Reform Act Of 1984 ተብሎ የሚታወቀው ሕግ የማሕብረሰብን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የወንጀል ክስ በፍርድ ቤት ከመሰማቱ በፊት /Pre-Trial detention/ በተወሰኑ ከባድ ወንጀሎች የተከሰሱ ሰዎች የዋስትና መብትን ይከለክላል፡፡ የዋስትና መብትንና የነፃነት መብትን በሚመለከት ከላይ ያቀረብነውን ማብራሪያ መሠረት በማድረግ አሁን በያዝነው ጉዳይ ላይ የተነሳውን አዋጅ ቁጥር 239/1993 አንቀጽ 51(2) ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት ጋር ይቃረናል ወይ? የሚለውን መሠረታዊ ጭብጥ እንደሚከተለው መርምረነዋል፡፡ 

የማመልከቻ አቅራቢዎች መነሻ ክርክር ሕገ መንግሥቱ በዋስትና መብት ገደብ እንደሚደረግበት ቢደነግግም ይህ ገደብ በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትና ላለመቀበል ወይም በገደብ መፍታትን ጨምሮ በቂ የሆነ የዋስትና ማረጋገጫ እንዲቀርብ ለማዘዝ ይችላል በሚል መልክ የተቀመጠ በመሆኑ ገደቡ በየጉዳዩ ፍርድ ቤት ውሣኔ የሚሰጥበት እንጂ ሕግ አውጪው አንድን የወንጀል ዓይነት ለይቶ ዋስትና ያሳጣል እንዲል ሥልጣን አይሰጠውም የሚል ነው፡፡ ለዚሁ አስተያየት መሠረት ነው የተባለውም በአንቀጽ 19(6) በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ከሚለው የድንጋጌው ይዘት ልዩ ሁኔታዎች ለሚለው ኃረግ በሚሰጠው  ትርጉም  የሚወሰን  ነው፡፡  ልዩ  ሁኔታዎች  ማለት ደግሞ ፍርድ  ቤቶች እንደነገሩ ሁኔታ እያንዳንዱን ጉዳይ ሲመረምሩ የሚያዩት እና የሚደርሱበት እንጂ ቀድሞ በሕግ ሊወሰን የሚችል አይደለም፡፡ የዋስትና መብት በፍርድ ቤት የሚታይ (Justiciable Matter) በመሆኑ ሕግ አውጪው በፀረ ሙስና አዋጅ ያስቀመጠውን ዓይነት ድንጋጌ በሕግ እንዲያወጣ ሕገ መንግሥቱ አይፈቅድም የሚል ነው፡፡

የዋስትና መብት ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑና በመርህ ደረጃ የተያዙ ሰዎች በዋስትና የመፈታት መብትም ሕገ-መንግስታዊ ደረጃ ያገኘ መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ የዋስትና መብት እንደብዙዎቹ መብቶች ገደብ ሊደረግበት እንደሚችልም አከራካሪ አይደለም፡፡  ለቀረበው  አቤቱታ  መነሻ ምክንያት የሆነው የዋስትና መብት የሚገደበው በምን ዓይነት ሁኔታ ነው የሚለውን አስመልክቶ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 19(6) በሕግ በተደነገጉ ልዩ  ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትና  ላለመቀበል ወይም በገደብ መፍታትን ጨምሮ በቂ የዋስትና ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ለማዘዝ ይችላል በማለት ይደነግጋል፡፡

ከዚህ ድንጋጌ ሁለት አበይት ነጥቦችን ማየት ይቻላል፡፡  የመጀመሪያው ነጥብ ፍርድ ቤት የዋስትና ጥያቄ ሲቀርብለት ሁለት አማራጮች እንዳሉት ይገልጻል፡፡ ፍርድ ቤት የዋስትና ጥያቄውን አልቀበልም ሊል ይችላል፡፡ ዋስትና የሚፈቀድ ሲሆን ደግሞ ዋስትና ጠያቂው በገደብ እንዲፈታ ካለሆነ ደግሞ በቂ የዋስትና ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ሊጠይቀው ይችላል፡፡ 

ሁለተኛው ነጥብ ፍርድ ቤቱ ከላይ የተመለከቱትን አማራጮች ሊወስድ የሚችለው በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች መሠረት መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡ በመሆኑም የዋስትና ገደብ በማስቀመጡ ረገድ ሕግ አውጪው እና ፍርድ ቤቶች የየራሳቸው የሥራ ድርሻ እንዳላቸው ግልጽ ነው፡፡ እዚህ ላይ መታየት ያለበት ዋናው ነጥብ ሕግ አውጪው ዋስትና የማይፈቀድባቸውን ልዩ ሁኔታዎች እንዲደነግግ መብት ይሰጠዋል፡፡ ዋስትና መከልከል የመሠረታዊ መብት ገደብ በመሆኑ ሕግ አውጪውም ሆኑ ፍርድ ቤቶች በጥንቃቄ ሊያዩት እንደሚገባ ይታመናል፡፡ ሕግ አውጪው የሚያወጣው አዋጅ በሕገ መንግሥት የሰፈረውን መብት በተወሰነ ደረጃ ከመገደብ አልፎ ዋናውን መብት ማጥፋትና መናድ ስለማይችል የአዋጁ ድንጋጌዎች አቀራረጽ እና ትርጉም ግልጽ ሆኖ እንዲቀመጥ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ልዩ ሁኔታዎች በውስን አድማስ የሚፈፀሙ መሆናቸውን የሚጠቁም በመሆኑ ማንኛውም የዋስትና መብት የሚገድብ ሕግ በአፈፃፀም ገደብ የለሽ እንዳይሆን እያንዳንዱ ድንጋጌ በጥንቃቄ መቀረጽ ይኖርበታል፡፡ 

ከዚህ በመለስ ሕግ አውጪው የዋስትና መብትን የሚገድብ ሕግ ሲያወጣ አንድን ወንጀል ለይቶ ዋስትና አያሰጥም ከማለት ሊከለከል አይችልም፡፡ ሕግ አውጪው ልዩ ሁኔታዎችን በሁለት አመማራጮች ሊያስቀምጥ ይችላል& አንድም ዋስትና የማያሰጠውን የወንጀል ዓይነት ለይቶ ማስቀመጥ& አሊያም በየትኛውም ዓይነት ወንጀል ቢሆን ዋስትና ሊያስከለክሉ የሚችሉ ፍሬ ነገሮችን መዘርዘር ናቸው፡፡ በሕግ አውጪው ተለይቶ የተጠቀሰው ወንጀል የዋስትና መብት አያሰጥም መባሉ ዋስትናው በፍርድ ቤት የማይታይ (Non-Justiciable Matter) የሚያደርገው አይሆንም፡፡ ዞሮ ዞሮ ዋስትና ያስከለክላል የሚባለው ወንጀል ዋስትና ለመከልከል በቂ ፍሬ ነገሮች ቀርበዋል አልቀረቡም የሚለውን ነጥብ መመርመር ያለበት ፍርድ ቤቱ ነው፡፡ የሙስና ወንጀል ዋስትና አያሰጥም የሚል ሕግ ቢኖርም አንድ ሰው በሙስና ወንጀል ለመያዝ በቂ ምክንያት አለ ወይንስ የለም የሚለው ነጥብ በአሳሪው ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በፍርድ ቤት ሊታመንበት የሚገባ ነገርም መሆን አለበት፡፡ ሙስና ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን በመመለስም ፍርድ ቤቶች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ መገመት አግባብ ነው፡፡ ሕግ አውጪው በአዋጁ አፈፃፀም የሚገጥሙ ችግሮች ተመልክቶ መፍተሄ ማፈላለግ እንዳለበትም ይታመናል፡፡

ከዚህ ውጪ የሙስና አዋጅ ዋስትና የሚከለክል በመሆኑ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 19(6) የሚጥስ ነው ለማለት የሚቻል አይደለም፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ ለሕገ መንግሥት ትርጉም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መላክ ያለበት አይደለም በማለት ወስነናል፡፡

ማጠቃለያ

1.     ከዚህ በላይ ለማሳየት እንደተሞከረው የዋስትና መብትን ወዲያውኑ የሚከለክሉት ሕጎች ሕገ መንግሥታዊ ናቸው ወይስ አይደሉም? የሚለውን መሠረታዊ ሀሳብ በተመለከተ በዳኞች እና በሌሎች የሕግ ባለሙያዎች መካከል አንድ ወጥ የሆነ አመለካከትና መግባባት አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም፡፡

2.  የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 19(6) ድንጋጌ ኢትዮጵያ ተቀብላ ካፀደቀቸው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን አንቀጽ 9(3) እና በዓለማቸን ከፍተኛ ተጽዕኖ ያላቸው የሕግ ሥርዓቶች ካዳበሩት አሰራር አንጻር በመነሳት የተለያዩ ሀሳቦች እና የአተረጓጎም ልዩነቶች በዳኞች& በሕግ ባለሙያዎች መካከል የተፈጠረ መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል፡፡

3.  የዋስትና መብትን ወዲያውኑ የሚከለክሉት ሕጎች የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 19(6) ድንጋጌ የሚጥሱ እና በአጠቃላይ የሕገ መንግሥቱን የበላይ ሕግነት የሚጋፉ ስለሆነ ሕገ-መንግሥታዊ አይደሉም ይባልልን በማለት ለሕገ መንግሥት ጉዳዩች አጣሪ ጉባዔ አቤቱታ ቀርቦ የነበረ ሲሆን ጉባዔውም ዋስትና የሚከለክሉት ሕጎችና ደንቦች ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(6) ጋር የሚቃረኑ አይደሉም@ በመሆኑም ጉዳዩ ለሕገ መንግሥት ትርጉም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መላክ ያለበት አይደለም በማለት ውሣኔ ሰጥቷል፡፡ ይህ የሕገ መንግሥት ጉዳዩች አጣሪ ጉባዔ ውሣኔ በይግባኝ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ ያልተሻረ በመሆኑ እንደመጨረሻ ውሣኔ ሆኖ ይቆጠራል፡፡

4.  በመሠረቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፕብሊክ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 62(1) መሠረት ሕገ መንግሥትን የመተርጎም ሥልጣን ያለው አካል ሲሆን የዚህን አካል ሥልጣን እና ተግባር ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/ 1993 አንቀጽ 3(1) ሥርም ሕገ መንግሥትን የመተርጎም ሥራ የምክር ቤቱ መሆኑ በግልጽ ሰፍሯል፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 56(1) ሥር ደግሞ ምክር ቤቱ በቀረበለት ጉዳይ የሚሰጠው ውሣኔ የመጨረሻ ስለመሆኑ የተደነገገ ሲሆን በዚሁ ድንጋጌ ንዑስ-አንቀጽ 2 ድንጋጌ ሥርም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች ውሣኔውን የማክበር እና የመፈፀም ግዴታ ያለባቸው መሆኑ አስገዳጅነት ባለው መልኩ ተቀምጧል፡፡

5.  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥት ጉዳዩች አጣሪ ጉባዔ በመታገዝ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ በሚያስነሱ ጉዳዩች ላይ ውሣኔ ይሰጣል፡፡ የሕገ መንግሥት ጉዳዩች አጣሪ ጉባዔ የዋስትና መብትን ወዲያውኑ የሚከለክሉት ሕጎች ከሕገ መንግሥቱ ጋር አይቃረኑም በማለት የሰጠው ውሣኔ ለጉዳዩ የመጨረሻ ሲሆን በዳኞችና በሕግ ባለሙያዎች መከበርና መፈፀም ያለበት ስለመሆኑ ከድንጋጌዎቹ ይዘትና መንፈስ የመንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉም የሕግ ባለሙያ በጉባዔው ውሣኔ ይስማማል ማለት አይደለም፡፡  ውሣኔው በመሠረታዊ ባህሪውም ሆነ በውጤት ደረጃ የተለያየ ትርጉም በመስጠት ወጥነት የሌለው የሕግ አተረጓጎምና አፈጻጸም እንዳይኖር ለመከላከልና በሐገር ደረጃ አንድ ወጥ የሆነ የሕግ አተረጓጎም ለማስፈን እረድቷል ማለት ይቻላል፡፡

Download this with full citation here

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የአክሲዮን መያዣ አመሠራረትና የመያዣ ተቀባዩ መብቶች
አዲሱ የፀረ ሙስና ሕግ በግል ኩባንያወች ላይ ተፈፃሚነቱና የሕግ አንድምታው

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Tuesday, 23 July 2024