ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብትን በመተርጎም በኩል ስለታየው ችግር

 

መግቢያ

ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት& ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግጋት እና በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የተካተቱት ሥነ ሥርዓታዊ መብቶች መሠረታዊ ዓላማ መርማሪ አካላት ያለበቂ ምክንያትና ሕጋዊ ሥርዓት የአንድን ሰው የነጻነት መብት እንዳይጥሱ ዋስትና እና ጥበቃ መስጠት ነው፡፡ የብዙ አገሮች ሕገ መንግሥት የአንድ ሰው በሕይወት የመኖር& የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ክቡርነት የመነጩ ሊደፈሩና ሊገሰሱ የማይችሉ መብቶች መሆናቸውን ያረጋገጣሉ@ መሠረታዊ መብቶቹ ተግባር ላይ እንዲውሉ ጥረት የሚደረግ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በሌላ በኩል የእነዚህን መብቶች አፈፃፀም የሚሸረሽሩ ወይም ዋጋ የሚያሳጡ የተለያዩ የወንጀል ድርጌቶች በዓለም ውስጥ በየደረጃው በስፋት ሲፈፀም ማየትና መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህ የማይጣጣም ሁኔታ ከልዩ ልዩ የጥቅም ግጭቶች& ከአመለካከት ልዩነት& ካለመቻቻልና ከመሣሰሉት መንስዔዎች የሚመነጭ ሊሆን ይችላል፡፡

በዓለም አቀፍ ሆነ በብሔራዊ ሕግጋት ዕውቅና ከተሰጣቸው መሠረታዊ መብቶች አንዱ በወንጀል የተከሰሰ ሰው ጉዳዩ ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት ታይቶ ጥፋተኛ መሆኑ እስካልተረጋገጠ ድረስ ከወንጀል ነፃ እንደሆነ የመቆጠር መብት ያለው መሆኑ ነው፡፡ ይህ መሠረታዊ መብት ዕውቅና ሊያገኝ የቻለው ንፁሀን ግለሰቦች በወንጀል በመጠርጠራቸው ወይም በመከሰሳቸው ብቻ ሊደርስባቸው የሚችለውን የተለያየ የመብት ጥሰት ለመግታት ነው፡፡

ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ የተያዘ ሰው በመሠረቱ የተጠረጠረበት ወንጀል በማስረጃ ከተረጋገጠበት ሊፈረድበት@ ማስረጃ ከሌለ ግን ሊፈታ ይገባል፡፡ ሆኖም መረማሪ ፖሊስ ወይም ዐቃቤ ሕግ ጉዳዩን እስኪያጣሩና ለፍርድ እስኪቀርብ ድረስ ታሣሪው በጥፋተኝነት የማይቀጣበት ወይም በፍጹም ነፃነት የማይለቀቅበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህም በዋስ የመለቀቅ መብት ነው፡፡ መንግሥት የሕብረተሰብን ሰላምና ፀጥታ የማስከበር እንዲሁም የግለሰብን መብትና ነፃነት የማክበር ሃላፊነት አለበት፡፡ መንግሥት የወንጀል ተግባር ፈጽመዋል በማለት በሚይዛቸው ሰዎች ላይ ሕግ ለማስከበር የሚፈጽመው ተግባር ሁለት ተፋላሚ የሆኑ ጥቅሞችን የሚያስታርቅና የሚያቻችል መሆን አለበት፡፡ የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሲባል በከባድ የወንጀል ተግባር የተጠረጠሩ ሰዎችን በፍርድ አደባባይ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ  ከፍርድ በፊት ማሰሩ ተገቢ ሲሆን በሌላ በኩል ተጠርጠረው የታሰሩ ሰዎች ንፁህ ሰዎች የሚሆኑበት እድል ሰፊ ስለሆነ ከፍርድ በፊት እንዳይታሰሩ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡  

Continue reading
  15333 Hits