Font size: +
8 minutes reading time (1586 words)

በአደባባይ የሚፈጸም ብልግና እና የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ

የዛሬው ጽሑፍ የሚያጠነጥነው በወንጀል ሕግ ዙሪያ ነው፡፡ የወንጀል ሕግና የኅብረተሰቡ የሞራል አስተሳሰብ የጠበቀ ቁርኝት አላቸው፡፡ በአብዛኛው በኅብረተሰቡ እንደ ኃጢያት ወይም ነውር የሚቆጠሩ ድርጊቶች በወንጀል ሕግም የሚያስጠይቁ ናቸው፡፡ አመንዝራነት፣ ስርቆት፣ ስድብ፣ ግብረሰዶም ወዘተ. ኃጢያት ወይም ነው ብቻ ሳይሆኑ ወንጀልም ተደርገው በወንጀል ሕጉ እንደሚያስቀጡ ተመልክቶ እናገኛለን፡፡ ይሁን እንጂ ኃጢያት ወይም ነውር የሆነ ድርጊት ሁሉ ግን ወንጀል ላይሆን ይችላል፡፡ ዝሙት አዳሪነት ለዓብነት ብንመለከት ድርጊቱ ኃጢያት ወይም ነውር መሆኑ ባያጠያይቅም፣ በወንጀል ሕጋችን በመርህ ደረጃ የወንጀል ኃላፊነት የማያስከትል ድርጊት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

የወንጀልና የኃጢአት ግንኙነት ስፋት እንደ ኅብረተሰቡ የሞራል አስተሳሰብ የሚለያይ ስለሚሆን በሁሉም ዘንድ ተመሳሳይ መግባባት ላይኖር ይችላል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1957 በእንግሊዝ ሕግ ግብረ ሰዶም ሊኖረው የሚገባውን ቦታ በተመለከተ በጊዜው የቀረበው ሪፖርት (The Wolfeden Report) ሕግ የኅብረተሰቡን የሞራል አስተሳሰብ የማስከበር ወሰኑን በተመለከተ አከራካሪ ጽንሰ ሐሳቦችን አንስቷል፡፡ በዘመናት የሕግና የሞራል ግንኙነት የሚታዩበት ሁኔታ እየሰፋ ቢመጣም፣ በጊዜው በሪፖርቱ ተነስተው ሙግት የተደረገባቸው ግራና ቀኝ አስተሳሰቦች አሁንም አከራካሪነታቸውን አልለቀቁም፡፡ በሪፖርቱ እንደተገለጸው የሕግ ዓላማ የሕዝብን ሥርዓትና መልካም ሥነ ምግባር በማስጠበቅ ዜጎቹን ከሚጎዳ ነገር፣ ከብልግና እንዲሁም ከጥቃት መከላከል መሆኑ ተሰምሮበታል፡፡ ሆኖም ‹‹ሕጉ ይህንን ዓላማውን በማስፈጸም ሰበብ በግለሰቦች ግላዊ ሕይወት ጣልቃ በመግባት ወንጀልና ኃጢአት አንድ እስኪሆኑ ድረስ በሞራል አስተሳሰብ ላይ አቋም መውሰድ የለበትም፤›› ይላል ሪፖርቱ፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ ሪፖርት አቅራቢው በእንግሊዝ ሕግ ግብረ ሰዶም በአደባባይ ሲፈጸም እንጂ በፈቃድ በግል ሕይወት (In private) ሲፈጸም እንደዝሙት አዳሪነት ሁሉ ወንጀል ሊሆን አይገባም የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

 

ሪፖርቱን በመቃወም ሕግ የኅብረተሰብን ሞራል ሊያስከብር የሚገባበትን ሁኔታ ሰር ፓትሪክ ዴቭሊን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ እንደእርሳቸው አመለካከት፣ ኅብረተሰብ ሕግን እንደ መሣሪያ በመጠቀም የዜጎቹን ድርጊት መልካም ወይም ጎጂ በማለት የመፈረጅ ሥልጣን አለው፡፡ መንገደኛ ሰው (Reasonable man) ሥነ ምግባርን በተመለከተ የሚሰጠው አስተያየት ኅብረተሰቡን የሚወክልና ሕጉ ጥበቃ ሊሰጠው የሚገባ ስለመሆኑ ምሁሩ ይገልጻሉ፡፡ በዴቭሊን አስተሳሰብ

 

‹‹What makes a society of any sort is community of ideas, not only political ideas but also ideas about the way its members should behave and govern their lives, these latter ideas are its morals.››

 

ስለዚህ ሕግ የግለሰብን ነፃነት የመጨረሻው ጥግ ድረስ ሲጠብቅ የኅብረተሰቡንም ህልውና ለቅፅበት ሳይዘነጋ መሆኑን ምሁሩ ይገልጻሉ፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግም አገርን መድፈር ወንጀል ሆኖ የሚያስጠይቀውን ያህል በግልም ሆነ በአደባባይ የሚፈጸም ግብረ ሰዶም በወንጀል ሊያስጠይቅ ይገባል፡፡ የሁለቱም ዓላማ የኅብረተሰብን ህልውናና ቀጣይነት ማረጋገጥ በመሆኑ፡፡

 

ጸሐፊው ይህን ክርክር በመግቢያነት የተጠቀመው ያለ ያለምክንያት አይደለም፡፡ አገራችን ሁለተኛውን ዘመናዊና የተደራጀ የወንጀል ሕግ እ.ኤ.አ. በ1957 ዓ.ም. (ከ1930 በኋላ ማለት ነው) ስታወጣ፣ እነዚህ አስተሳሰቦች በወቅቱ ተፅዕኖ ስለማድረጋቸው ስቴቨን ሎዌንስቲን ስለ ኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ጥናት እንዲረዱ ባዘጋጁት መጽሐፍ ላይ ገልጸውታል፡፡ በ1997 ዓ.ም. የወጣው አዲሱ የወንጀል ሕግ እ.ኤ.አ. በ1957 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ የተካ ሲሆን፣ ወንጀልና የሞራል እሳቤዎችን ግንኙነት በማስቀመጥ ረገድ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ይዘት አላቸው፡፡ በወንጀል ሕጋችን የኅብረተሰቡን የሞራል አስተሳሰብ የሚያስጠብቁ የተለያዩ ድንጋጌዎች ተቀምጠዋል፡፡ ግብረ ሰዶም በአደባባይም ይፈጸም በግል፤ በሴትም ይፈጸም በወንድ በወንጀልነት ተፈርጆ በጽኑ እስራት የማስቀጣቱ ነገር አንዱ ማሳያ ነው፡፡ አመንዝራነት፣ አስገድዶ መድፈር (አንቀጽ 620) በእንስሳት ላይ የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም (አንቀጽ 633)፣ በዘመዳሞች መካከል የሚፈጸም ግብረ ሥጋ (654) በሕጋችን ከሞራል አመክንዮ አንፃር በወንጀልነት መፈረጃቸውን ልብ ይሏል፡፡ ያም ሆኖ በ1997 ዓ.ም. የወጣው አዲሱ የወንጀል ሕግ ሞራላዊ እሴቶችን በመጠበቅ ረገድ የተወሰኑ ክፍተቶች አሉበት፡፡ በዚህ ጽሑፍ ከእነዚህ ወንጀሎች ክፍል የሚመደበውን በመልካም ጠባይ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በሰሞኑ ከሚነሱ ነጥቦች አንፃር በመቃኘት የሕጎቻችንን አቋም ለመፈተሽ እንሞክራለን፡፡

 

በአደባባይ የሚፈጸም ብልግና

 

በወንጀል ሕጉ በአደባባይ የሚፈጸም ብልግና በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ግለሰቦች በአደባባይ ብልግና ለመፈጸም ቢፈልጉ እንኳን ሕጉ አይፈቅድላቸውም፡፡ ሕጉ ከግለሰቦች ነፃነት ይልቅ የኅብረተሰብን ሞራል የመጠበቅ ዓላማ አለው፡፡ ይህን መሠረት አድርጎ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 639 ‹‹ማንም ሰው አስቦ ሕዝብ በሚያዘወትርበት ቦታ ወይም በሕዝብ ፊት የግብረ ሥጋ ድርጊትን ወይም ለመልካም ጠባይ ወይም ለመልካም ሥነ ምግባር በብርቱ ተቃራኒ የሆነውን ማናቸውንም ሌላ ጸያፍ ድርጊት የፈጸመ ወይም በአኳኋን ያሳየ እንደሆነ ከሦስት ወር እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከአንድ ሺሕ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፤›› ሲል ይደነግጋል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የተወሰኑ ነጥቦችን መመልከት እንችላለን፡፡

 

ድርጊቱ ብልግና መሆን አለበት

 

ብልግና የሚባለውን ሕጉ በግልጽ ለማመልከት ሞክሯል፡፡ በዋናነት የተጠቀሰው በሕዝብ ፊት የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም ነው፡፡ ይህ የብልግናው ጥግ ሲሆን ከዚያ መለስ ለመልካም ጠባይ ወይም ሥነ ምግባር በብርቱ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶችም ሊካተቱ ይችላሉ፡፡ የሕጉ የእንግሊዝኛው ቃል ‹‹Public indecency›› ‹‹Obscene act›› የሚሉ ቃላትን ስለሚጠቀም ማንኛውም ኅብረተሰቡ ከተቀበለው የሞራል አስተሳሰብ ጋር የማይሄድ ድርጊት (አካልን ማጋለጥ፣ ብልግናን በምልክት መግለጽ) ወዘተ. በወንጀሉ ሥር የሚወድቅ ይሆናል፡፡ በእንግሊዝኛው ትርጉም ‹‹Obscene›› የሚለው ‹‹Indecent›› ከሚለው ቃል የከበደ ከሥነ ምግባር ጋር የሚፃረር ጸያፍ ድርጊትን ይገልጻል፡፡ ቶም ሉዊስ የተባለ የእንግሊዝ የሕግ ምሁር የሁለቱን ድርጊቶች ልዩነት የፍርድ ቤት ጉዳይን በመጥቀስ በምሳሌ እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡

 

‹‹It is easier to illustrate than define and illustrate it thus. For a male bather to enter the water nude in the presence of ladies would be indecent, but it would not necessary be obscene. But if he directed the attention of a lady to a certain member of his body his conduct would certainly be obscene››

 

በዚህ ገለጻ መሠረት ብልግናው የተለያየ ደረጃ ሊኖረው እንደሚችል ማሰብ ይቻላል፡፡ የብልግና ድርጊቱ ወንጀል እንዲሆን ፈጻሚው አስቦ ሊያደርገው የሚገባ ሲሆን፣ አፈጻጸሙም በድርጊት ወይም በአኳኋን በማሳየት ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ በአገራችን አንዳንድ ባህሎች እርቃን መሄድ፣ በአደባባይ ግንኙነት መፈጸም፣ እንደ ባዕድ አገር መሳሳም ወዘተ. ለመባለግ ስለማይፈጸሙ በወንጀል እንደማያስጠይቅ መገንዘብ ይቻላል፡፡

 

የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 640 እና 641 ተጨማሪ የብልግና ድርጊቶችን ይዘረዝራሉ፡፡ ብልግናው በጽሑፍ፣ በፊልም፣ በምሥል፣ በሥዕል፣ በቴአትር፣ በሲኒማ፣ በሬዲዮ፣ በቪዲዮ፣ በቴሌቪዥን ወዘተ. ጭምር ሊካተቱ ይችላሉ፡፡ እነዚህን ድርጊቶች የያዙ ነገሮችን ያዘጋጀ፣ ያስገባ፣ የሸጠ፣ ለሕዝብ ያሳየ፣ ያከራየ ወዘተ. ሁሉ በወንጀሉ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ያም ሆኖ ወሲብን ወይም ፍትወት ሥጋን ለመቀስቀስ ያልታሰቡ በባህሪያቸው በሞላ ሥነ ጥበባዊ፣ ሥነ ጽሑፋዊ፣ ወይም ሣይንሳዊ የሆኑ ሥራዎች እንደጸያፍ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች እንዲሆኑ ሊቆጠሩ አይችልም፡፡ (642) በወንጀሉና በተፈቀዱ ሥራዎች መካከል ያለውን መስመር የመለየት ኃላፊነት የዳኞች ይሆናል፡፡ በሌሎች አገሮች የዳበሩ አስተምህሮዎችና ትርጉሞች በመኖራቸው መለየቱ አስቸጋሪ ላይሆን ይችላል፡፡ በእኛ አገር ግን መስመሩን ማስመር ፈታኝና በዳኞች ግላዊ አተያይ ላይ መውደቁ አይቀርም፡፡ ወግ አጥባቂ የሆነ ሰው ጉዳዩን ከተመለከተው ልዩ ሁኔታው መጥበብ ካለበትም የበለጠ ሊቀጭጭ ይችላል፡፡

 

በሕዝብ ፊት ወይም ሕዝብ በሚያዘወትርበት ቦታ

 

የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 639 ተፈጻሚ የሚሆነው የብልግና ድርጊቱ በአደባባይ ተፈጽሞ ሲገኝ ነው፡፡ ከሕዝብ ተሰውሮ፣ በግል ሕይወት የሚፈጸመውን ጸያፍ ድርጊት ሁሉ የመግዛት ሐሳብ ሕጉ የለውም፡፡ በዚህ ሰሞን በቢግ ብራዘር አፍሪካ የተነሳው የእውነታ ማሳያ (Reality show) ጉዳይ አከራካሪነቱ ከዚሁ የሚመነጭ ነው፡፡ በአንድ በኩል ጉዳዩ የተፈጸመው በግል ሕይወት (In private life) በመሆኑ በአደባባይ አልፈተጸመም የሚል ሙግት አለ፡፡ የዝግጅቱ ተሳታፊዎች በግል የሚኖሩትን እውነተኛ ሕይወት በአንድ የተገደበ ቦታ እንዲኖሩት ሁኔታዎችን ያመቻቸ በመሆኑ ብልግናው በሕዝብ ፊት የተደረገ አለመሆኑን በማንሳት ይከራከራሉ፡፡ ይህን የሚያራምዱ ወገኖች ተጠያቂነቱን ከፈጻሚዎቹ ወደ ነጋሪዎቹ (አሳይዎቹ) ያሸጋግሩታል፡፡ መጠየቅ ካለበት ለሕዝብ እንዲደርስ ያደረገው የመገናኛ ብዙኀን እንጂ ተሳታፊዎቹ አይደሉም ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ግን ተሳታፊዎች ላይ ማዕከል ያደረጉ ትችቶች በማቅረብ ለሕዝብ በቀጥታ እንደሚተላለፍ በታወቀ መርሐ ግብር የብልግናን ድርጊት መፈጸም ወንጀሉን በሕዝብ ፊት መፈጸም ነው ይላሉ፡፡ የቀጥታ ሥርጭቱ እያንዳንዱ ቤት በቴሌቪዥን፣ በኢንተርኔትና በሌላ መንገድ እንደሚደርስ አውቆ የሚፈጸመው በሕዝብ ፊት መፈጸሙን አውቆ ውጤቱን የተቀበለ ነው የሚል ሙግት አለ፡፡ እነዚህ ወገኖች ፈጻሚዎቹ ከመገናኛ ብዙኅኑ ጋር በጣምራ በኃላፊነት ሊያስጠይቅ ቢችል እንጂ አንዱን ወንጀለኛ ሌላው ነፃ አያደርገውም የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ ጉዳዩ በብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ መሠረትም የሚታይበት ሁኔታ አለ፡፡ አዋጁ ከሞራል ጋር የሚቃረን መርሐ ግብር እንዳይተላለፍ የሚከለክል ድንጋጌ አለው፡፡ የአዋጁን አንቀጽ 30-31 ይመለከቷል፡፡

 

ብልግናው በሕዝብ በፊት ተፈጽሟል የሚል መደምደሚያ ላይ ቢደረስ እንኳን የወንጀል ኃላፊነቱ ከፍርድ ቤት ሥልጣን (Jurisdiction) ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ተጨማሪ ሙግት ማስከተሉ አይቀርም፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 11 የወንጀል ሕጉን ጂኦግራፊያዊ አፈጻጸም ሲደነግግ ሕጉ ተፈጻሚ የሚሆነው ወንጀሉ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ (በየብሱ፣ በአየሩና በውኃ አካላቱ) የተፈጸመ ሲሆን ነው፡፡ በዚህ መነሻነት የሰሞኑን ጉዳይ ከተመለከትነው በባዕድ አገር የተፈጸመ የብልግና ተግባር በኢትዮጵያ ስለሚዳኝበት አሳማኝ ነጥብ ማግኘት አስቸጋሪ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሕጉ በልዩ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ ከግዛቷ ውጭ የሚደረግ ወንጀል በኢትዮጵያ ሊታይ የሚችልበትን ሁኔታ በአንቀጽ 13 ቢደነግግም፣ ወንጀሎቹ በመንግሥት ደኅንነት፣ አንድነት፣ ተቋማት፣ ጥቅምና በገንዘቡ ላይ ለሚፈጸሙት በመሆኑ ለዚህ ጉዳይ አግባብነት አይኖረውም፡፡

 

የሆኖ ሆኖ ብልግናው ወይም ጸያፍ ተግባሩ በወንጀል እንዲያስጠይቅ በሕዝብ ፊት መፈጸሙ በአሳማኝ ሁኔታ ሊረጋገጥ የሚገባው ሲሆን፣ የተፈጸመውም በኢትዮጵያ ግዛት ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ግን ውግዘት ካለ የሕግ ሳይሆን የባህልና የሞራል መሆኑ አይቀርም፡፡

 

የቅጣቱ ነገር

 

በአደባባይ የሚፈጸም ብልግና በቀላል እስራት ወይም በገንዘብ መቀጮ ሊያስቀጣ ይችላል፡፡ ቀላል እስራቱ ከሦስት ወር እስከ አንድ ዓመት የሚያስቀጣ ሲሆን፣ መቀጮው ከ1000 ብር አይበልጥም፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው አካለ መጠን ባልደረስ ልጅ ፊት ከሆነ ቅጣቱ ከስድስት ወር እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት ይሆናል፡፡ ሕጉ ያስቀመጠው ቅጣት በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ በአማራጭነት መሆኑ ወንጀሉን ቀላል ያደርገዋል፡፡ በኅብረተሰብ ሞራል ላይ የተፈጸመ ጸያፍ የብልግና ወንጀል በ1000 ብር ብቻ እንዲቀጣ ማድረግ የሞራሉን ዋጋ ማሳነስ ነው፡፡ የፍትሐ ብሔር የሞራል ካሳ በ1952 የፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 2116(3) መሠረት አንድ ሺሕ ብር ብቻ መሆኑ ሊደንቀን አይገባም፡፡ ከ50 ዓመት በፊትም አሁንም የሞራል ዋጋው አንድ ሺሕ ብር ብቻ መሆኑ ሕጉ ለሞራል ጥበቃ የሰጠውን አነስተኛ ቦታ አመላካች ነው፡፡

 

ወንጀል፣ ኃጢአት፣ ነውር

 

የሦስቱ ጽንሰ ሐሳቦች ግንኙነት በአገራችን ያለውን ትስስር በግርድፉ ለተመለከተ በጊዜ ሒደት ልዩነታቸው እየሰፋ መምጣቱን ያስተውላል፡፡ በድሮው ዘመን ሁሉም ኃጢአቶች ባይሆኑም አብዛኛዎቹ ነውሮች በወንጀልነት በሕግ የተፈረጁበት ሁኔታን እናስተውላለን፡፡ በአደባባይ የሚፈጸም የብልግና ወንጀል የሦስቱ ግንኙነት የሰመረበት መሆኑን መመስከር እንችላለን፡፡ ድርጊቱ ኃጢአትና ነውር ብቻ ሳይሆን ወንጀል ሆኖ ያስቀጣል፡፡ ሕግ የኅብረተሰቡን የሞራል ሁኔታ (Public morality) የሚያከብርና የሚያስከብር ሊሆን ይገባዋል፡፡ በመነሻችን እንደገለጽነው እንደ አንድ ማኅበረሰብ ያስተሳሰረን የፖለቲካ ውህደት ብቻ ሳይሆን የሞራል አስተሳሰብ ውህደት ነው፡፡ የሞራል መስፈርቶችን የሚሸረሽር ሕግ ከበዛ አብሮነታችንንም መሸርሸሩ አይቀርም፡፡ በዚህ ረገድ የወንጀል ሕጉ ግብረ ሰዶምን መከልከሉ፣ አመንዝራነትን ወንጀል ማድረጉ፣ ብልግናን መቅጣቱ ወዘተ. የሚያስመሰግነው ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የወጡ ሕጎች ሞራልን በመጠበቅ ረገድ ያላቸው ጥንካሬ የቀድሞውን ያህል መሆኑን መመስከር ዳገት መሆኑ አይቀርም፡፡ ጽንስ ማስወረድ መፈቀዱ (ወይም የመፈቀድ ያህል ላልቶ በሕጉ መካተቱ)፣ የአጎትና የአክስትን ልጅ ማግባት የሚፈቅድ የቤተሰብ ሕግ መፅደቁ፣ ማኅበራዊ ተቋም የሆነውን ጋብቻን በተራ ስምምነት ለማፍረስ የሚያስችል የሕግ መሠረት መጣሉ ወዘተ. የተወሰኑ ማሳያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ከኅብረተሰቡ የሞራል አስተሳሰብ ጋር የተጣመሩ በመሆናቸው የሕጉ ዕውቅና ሲነፈጋቸው በኅብረተሰቡ ላይ የሚያመጣው አሉታዊ አስተዋጽኦ ነጋሪ አይፈልግም፡፡ አሁን አሁን የአገሮችን የሕግ ይዘት ታሪካቸው፣ ባህላቸውና የሞራል አስተሳሰባቸው ሳይሆን የሌሎች ተሞክሮ፣ በሰብዓዊ መብት ስም የሚገቡ ባዕድ ሐሳቦችና የገንዘብ ድጋፍ የሚወስናቸው መሆኑን በዕለት ተዕለት ኑሮአችን እናስተውላለን፡፡ የታወቀ የሞራል ኮድ የሌለው ሕዝብ ደግሞ የማይቀበለው ባዕድ ሐሳብ ስለማይኖር ጉዳቱ ሰፊ ነው፡፡

 

ስለዚህ ብልግናን የሚያወግዝ ሕግ መኖሩ የሕጉ ጥሩ ጐን ነው፡፡ ባህላቸውን ዘንግተው በአደባባይ ጸያፍ ድርጊትን ለሚፈጽሙ ተገቢ ዋጋ መዘጋጀቱን ሕጉ ያበስረናል፡፡ የቅጣቱ ማነስ አሳሳቢ ቢሆንም፣ የድንጋጌው መኖር ያጽናናል፡፡ የወንጀል ሕግ ተጠያቂነት ከኅብረተሰብ ውግዘት በላይ የሚታይ ተጨባጭ ውጤት አለው፡፡ ብልግናን ወንጀል ያደረገ ሕግ ግን ሌሎችንም ከኅብረተሰቡ ሞራል ጋር የሚቃረኑ ድርጊቶች ለመግዛት/ለማስተዳደር ጉልበት ሊያንሰው አይገባም፡፡ ለዝሙት አዳሪነት፣ ለጽንስ ማቋረጥ፣ በጋብቻ ላይ ጋብቻ ወዘተ. ትርጉም ያለው አቋም ቢያዝ ሕጉ ኅብረተሰባዊ መሠረት ይኖረዋል፡፡ አፈጻጸሙም በጥንቃቄ ሊጠናና ሊዳብር ይገበዋል፣ በየአደባባዩ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉት ድርጊቶች ሃይ ባይ ይፈልጋሉ፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Regional Systems in Pursuing International Crimina...
In Response to the comment given by a Fitsum Yifra...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 24 July 2024