- Details
- Category: Non-Contractual Liability (Tort Law)
- Hits: 7935
ከውል ውጨ አላፊነት ሕግ ሁለት ዋና ዋና ዓላማች አሉት እነሱም የተጉዳ ሰው እንዲ ካስ ማድረግና በዳይ ወይም ሌላ ሰው ተመሳሳይ ድርጊት ከመፈፀም እንዲቆጠብ ማድረግ ነው፡፡ በእንግሊዝኛው / Compensation and Deterrence/ የምንለው ነው፡፡ ስለሆነም ከውል ውጨ አላፈነት ሕግ በዋናነት የቅጣት ዓላማ የለውም፡፡ ይህ በዋናነት የወንጀል ሕግ ዓላማ ነው፡፡ በርግጥ ከውል ውጨ አላፊነት ሕግም በሚወስናቸው ዳጐስ ያሉ የካሣ ክፍያዎች /Exemplary damages / የቅጣት ዓላማ /Punitive function / ሊኖረው ይችላል፡፡
መቆጠብ /Deterrent/
የዚህ ፅንሰ ዓላማ በዳይ ባህርዩውን እንዲለውጥና ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈፅም ማድረግ ነው፡፡ በሁለት መንገድ በዳይን ድጋሚ እንዲህ ዓይነት እንዳይፈፅም ማድረግ ይቻላል፡፡ አንደኛው ለተበዳዩ ገንዘብ እንዲከፍል በማድረግ ነው፡፡ ይህን ሲያደርግ በዳይ ገንዘቡን የሚከፍለው ከሀብቱ ላይ ቀንሶ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለእሱ ሀብት ጉዳት ነው፡፡ ሁለተኛ ስሙና ዝናው እየተሸረሸረ መምጣቱ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በሞያው አማካኝነት ግልጋሎት የሚሰጥ ሰው ለምሳሌ የሕክምና ዶክተርና የሕግ ባለሞያ በቸልተኝነት በደንበኛቸው ላይ ጉዳት ካደረሱ ይህ በወደፊት የሞያ ሕይወታቸው ላይ ትልቅ ጉዳት አለው፡፡ ሌላ ደንበኛ አያገኙም ማለት ነው ፡፡
ካሣ /Compensations /
ከውል ውጨ አላፊነት ሕግ ዋና ዓላማ ተበዳይ በበዳይ እንዲካስ ማድረግ ነው፡፡ ይህም ብዙ ጊዜ የሚሆነው በዳይ ለተበዳይ ገንዘብ እንዲከፍል በማድረግ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ይህ ካሣ በበዳይ ለተበዳይ በአንድ ጊዜ እንዲከፈል ይደረጋል፡፡ ተበዳዩች ብዙውን ጊዜ ካሣ እንዲከፈላቸው ከፍርድ ቤት ውጨ በድርድር ይጨርሳሉ፡፡ አንዱ ምክንያት የፍርድ ሂደቱ ረዥም ስለሆነ ሊሆን ይችላል፡፡ የሚከፈለው የካሣ መጠን ብዙ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ ሁለተኛ ካሣው ሲከፈል በአንዴ መከፈሉ ጥቅም ቢኖረውም ካሣው በሚከፈልበት ጊዜ የገንዘቡ ዋጋ ቀንሶ ሊሆን ይችላል፡፡ በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ተበዳዩች ጉዳያቸውን ብዙውን ጊዜ በድርድር ከፍርድ ቤት ውጪ እንዲጨርሱ ሊገደዱ ይችላሉ፡፡
ከውል ውጪ አላፊነት ሕግ ወሰን
የሰዎችን መብት የሚጠብቁ ሊሎች ሕጉችም አሉ፡፡ የውል ሕግና የወንጀል ሕግ እንደ ምሳሌ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ ሆኖም ከውል ውጨ ያለ አላፊነት ሕግ በአንድ በኩል የውልና የወንጀል ሕግ በሌላ በኩል ልዩነት አላቸው፡፡ የውል ሕግንና ከውል ውጨ አላፊነት ሕግን ብንወስድ የግዴታዎቹ ምንጨች የተለያዩ ናቸው ፡፡ ከውል ውጨ አላፊነት ምንጩ ሕግ ነው፡፡ የውል ኃላፊነት ምንጭ ደግሞ የተዋዋዩች ፍላጉት /Consent/ ነው፡፡ በውል ግንኙነት የመሠረቱት ሰዎች አላፊነት የርስ በርሳቸው ሲሆን ከውል ውጨ አላፊነት ግን በሁሉም ሰው ነው፡፡ ሌላም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የይርጋ ጊዜንና ክስ የሚመሰረትበትን ቦታ ወዘተ….
አንዳንዴ ጊዜ አላፊነቱ ከውል ውጨ ነው ወይስ በውል የሚመነጭ የሚለውን ለመለየት አስቸጋሪ የሚሆንበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ቀዳጅ ሐኪም ቀዶ ጠገና ሲያከናውን በተካሚ ሆድ ውስጥ የደም መጥረጊያ ጥጥ ረስቶ የታካሚውን ሆድ ቢሰፋ የቀዳጅ ሐኪሙ አላፊነት ከውል ነው የሚመነጨው ወይስ ከውል ውጨ ተመሳሳይ የሆኑ ሌሎች ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በተመሳሳይ ሆኔታም ከውል ውጨ እና የወንጀል ሕግ ይለያያሉ፡፡ አመዳደባቸው አንዱ በ Civil Law ሲመደብ ሌላኛው በ Public Law ስር ይመደባል፡፡ ተከራካሪ ወገኖችም እንዲሁ ይለያሉ፡፡ በወንጀል ሕግ አንዱ ተከራካሪ ወገን ሕዝብን ወክሎ መንግስት /በዐቃቢ ሕግ አማካኝነት/ ሲሆን ከውል ውጭ አላፊነት ተከራካሪ ወገኖች ግን ሁለቱም ሲቨሎች ናቸው፡፡ የወንጀል ሕግ ክርክር ውጤቱ ምናልባት እስር ሊሆን ይችላል፡፡ ከውል ውጨ ክርክር ግን እስር ሳይሆን ካሣ መክፈል ነው፡፡ የወንጀል ሕግ ክርክር ውጤቱ ወደ ሌላ ሶስተኛ ሰው አይተላለፍም ሆኖም ከውል ውጭ ክርክር ውጤት ወደ ወራሾች ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ብዙ ሌሎች ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ምክንያትና በጉዳት መሃል ያለ ግንኙነት
ምክንያት በከሣሹ ቸልተኝነትና በከሳሹ ላይ በደረሰው ጉዳት መሃል የሚገኝ አካላዊ ግንኙነት ነው፡፡ ሕግ ይህ ግንኙነት መኖሩን ለማረጋገጥ “ but for “ የሚለውን መርህ / test/ ይጠቀማል፡፡ በዚህ መርህ መሠረት የመጀመያው ጭብጥ / Issues/ የሚሆነው የተከሣሹ ማድርግ ወይም አለማድረግ /Commission or omission / ነው ወይ ከሣሽ ላይ ጉዳት ለማድረስ ምክንያት የሆነው? የሚል ይሆናል፡፡ ይህን ጭብጥ ለመፍታት የሕግ ባለሞያዎች የሚጠቀሙበት መርህ / test / “But for “ የሚለውን ነው በከሣሹ ላይ የደረሰው ጉዳት የተከሣሹ ማድረግ ወይም አለማድረግ ባይኖር ኖሮ ጉዳቱ አይደርስም ነበር፡፡ እንደማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል የተከሣሹ ማድረግ ወይም አለማድረግ ባይኖርም ጉዳቱ ይደርስ ነበር የሚል መደምደሚያ ላይ የሚያደርስን ሁኔታ ካጋጠመን የተከሳሹ ማድረግ ወይ አለማድረግ ለጉዳቱ ምክንያት አይደለም፡፡ማለት ነው እንላለን፡፡
በእውነተኛ ዓለም የሆነውን በመውሰድ ይህን ነጥብ እናስረዳ አንድ የሌሊት ተረኛ የጥበቃ አባል ምግብ ይበላና ማስታወክ ይጀምራል፡፡ በዚሁ ምክንያት ወደ ሆስፒታል ሲሄድ ተረኛ ሐኪም ምንም እርዳታ ሳያደርግለት ወደ ቤቱ እንዲመለስና ጠዋት የግል ሐኪሙ ዘንድ እንዲቀርብ ይመክረዋል ጥበቃው ለንጋት ሳይበቃ ይሞታል፡፡ የሟች ሚስት ተረኛ ሐኪሙንና ሆስፒታሉን በቸልተኝነት ትከሣለች ጉዳዩ የቀረበለት ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ማስረጃ ከሰማ በኃላ የከሣሽን ጥያቄ ባለመቀበል ተከሣሾችን በነፃ ያሰናብታል፡፡ ለዚህ ውሣኔም መሠረት ያደረገው በአንድ ባለሞይ /Expert/ የተሰጠውን የምስክርነት ቃል ነው፡፡ በዚህ ባለሞያ የምስክርነት ቃል መሠረት ጠባቂው ሆስፒታል በደረሰበት ጊዜ የተረኛው ሐኪም ምንም ዓይነት እርዳታ ከሞት አያድነውም የሚል ነበር፡፡ ስለሆነም የሐኪሙ እርዳታ ያለማድረግ /Omission/ ለጥበቃው አባል ሞት ምክንያት አልነበረም ማለት ነው፡፡
ይህ ውሣኔ መሠረት ያደረገው ዘመኑ የደረሰበትን ሳይንሳዊ ግኝት ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ዳኞች ለውሣኔአቸው ሳይንሳዊ ግኝትን መሠረት ላያደርጉ ይችላሉ፡፡ ይህን ደግሞ በገሃዱ ዓለም የሆነው በመውሰድ ለማስረዳት እንሞክር፡፡
አንድ የኤሊትሪክ ሠራተኛ የኤሊትሪክ ምሰሶ ላይ ወጥቶ ሲሰራ ወድቆ ይሞታል፡፡ የሟች ባለቤት ባሌ የሞተው አሰሪው ለጥንቃቂ የሚያስፈልገውን መከላከያዎችና መሣሪያዎች ባለመስጠቱ ነው በማለት ክስ መሠረተች፡፡ ዳኞች የሟች የቀድሞ ተግባር እንደሚያስረዳው መከላያዎች ተስጥቶት የማይጠቀምባቸው ስለነበር የመከላከያ መሳሪያዎች በአሰሪው ለሠራተኛው መስጠቱ ሟችን ከመሞት አያድነውም ነበር የሚል ምክንያት በመስጠት የከሣሽን ክስ አልተቀበሉትም በሌላ አባባል የአሰሪው የመከላከያ መሳሪያዎችን አለመስጠት ለሠራተኛው ሞት ምክንያት አይደለም ማለት ነው፡፡ ቢሰጠውም ስለማይጠቀምበት ከመሞት አይድንም ነበር፡፡ እንደ ማለት ነው፡፡ መከላከያው ዕቃ ቢሰጠው ኖሮ “ But for “ መመዘኛ ተቀባይነት አላገኘም ማለት ነው፡፡
የከሣሽ የማስረዳት ሸክም
ጉዳት የደረሰበት ከሣሽ ለጉዳቱ ምክንያት የተከሣሽ ማድረግ ወይም አለማድረግ መሆኑን የማስረዳት አላፊነት አለበት፡፡ በአንዳንድ ሁኒታ ይህን ማስረዳት ከባድ ላይሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ዘበርጋን የጫላ መኪና ቢገጨውና ጉዳት ደርሶበት ዘበርጋ ለጉዳቱ ምክንያት በጫላ መኪና መገጨት መሆኑን ማሰረዳት ላይከብደው ይችላል፡፡ ሆኖም ይህን ማስረዳት ቀላል የማይሆንበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ይህንንም በምሳሌ እናስረዳ፡፡
አንድ ጡብ ማምረቻ ፋብሪካ ውስጥ የሚሰራ ሠራተኛ በቆዳ በሽታ ይይዘዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ይህ በሽታ ሊይዘኝ የቻለው ሥራ ስጨርስ ወዲያውኑ ገላዬን እንድታጠብ የሚያሰችለኝ የገላ መታጠቢያ አሰሪው ባለማዘጋጀቱ ነው የሚል ነበር፡፡ በዚሁ ምክንያት ሠራተኛው ገላውን ቤቱ ደርሶ ነበር የሚታጠበው በዚህ ጊዜ አቧራው ከገላው ጋር አብሮ ስለሚቆይ የቆዳ በሽታ አስከትሎበታል፡፡ የሚል ክርክር ነበር ያነሳው ዳኞቹም ያነሱትና የመለሱት ጭብጥ የገላ መታጠቢያ ያለመኖር የቆዳው በሽታ ምክንያት ነው ወይም የሚል ነበር ሳይንስ በዛን ጊዜ በደረሰበት የዕድገት ደረጃ ይህን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ለመመለስ አይችልም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ዳኞች በእርግጠኝነት የገላ መታጠቢያው ቢኖር ኖሮ የቆዳው በሽታ እንዳይከሰት ማድረግ ይቻል ነበር ብሎ ለመደምደም ባይቻልም ያለመኖሩ ግን የበሽታውን መከሰት ዕድል /Probability/ ከፍ ስለሚያደርግው ከሣሽ ይህን ካስረዳ ይበቃል በማለት ወስነዋል፡፡
ዳኞቹ ከአንድ በላይ ካሎ ምክንያቶች አንዱን በመውሰድ ነው ለከሣሽ የወሰኑት በሌላ በኩል ዳኞች ብዙ ምክንያቶች በሚኖሩበት ጊዜ ከምክንያቶቹ በእርግጠኝነት ለጉዳቱ መድረስ አንዱ መሆኑን ማረጋገጥ ካልተቻለ ለከሣሽ መወሰን እንደማይቻል የወሰኑበት ሁኒታ አለ፡፡ ይህንንም በደረሰ ጉዳት እናስረዳ፡፡
አንድ ህፃን ዘጠኝ ወር ሳይሞላው ይወለዳል፡፡ በዚሁ ምክንያት ልዩ እንክብካቤ በሚሰጥበት ክፍል እንዲቆይ ይደረጋል፡፡ በቆይታው ተጨማሪ ኦክሲጂን ያስፈልገው ነበረና ይሄው ይሰጠዋል፡፡ የተሰጠውም ኦክሲጄን መጠን ነበረው ለህፃኑ የተሰጠው የኦክሲጂን መጠን ከልኩ ያለፈ ነበር፡፡ ህፃኑም በመጨረሻ አይኑን ያጣል፡፡ አይነስውረ ይሆናል፡፡ ማለት ነው፡፡ የህፃኑ ወላጆች ሆስፒታሉንና ኦክሲጂን የሰጠውን ዶክተር ይከሳሉ፡፡ ማስረጃዎች ሲቀርቡ ለህፃኑ መታወር የኦክሲጂን ከመጠን ማለፍ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ይህ ምክንያት ደግሞ ለህፃኑ ዓይን መጥፋት ምክንያት መሆኑን ማረጋገጥ አስካልተቻለ ድረስ ተከሣሾችን ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም በማለት ዳኞች ወስኑ፡፡
- Details
- Category: Non-Contractual Liability (Tort Law)
- Hits: 7770
ከውል ውጪ ያለ አላፊነት ሕግ ማለት ሕግ መንግስቱ ጥበቃ ባደረገላቸው የሰዎች የንብረት እና የሰውነት መብቶች ላይ ጉዳት ሲደርስ ጉዳቱን ያደረሱ ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች እንዲክሱ የሚያስገድድ ሕግ ነው፡፡
ጥበቃው በሶስት መንገድ ሊደረግ ይችላል፡፡ አንዱ ጉዳቱን ያደረሱ ሰዎች ጉዳቱን ለደረሰባቸው ሰዎች በገንዘብ መልክ ካሣ እንዲከፈሉ በማድረግ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲሁም ከአድራጐታቸው እንዲቆጠቡ ፍ/ቤት ትዕዛዛ በመስጠት ሊሆን ደችላል፡፡ በእንግሊዝኛው injunction የምንለው ነው እና በሶስተኛ ደረጃ ጉዳቱን በዓይነት እንዲክሱ በማድረግ ሊሆን ይችላል፡፡ በእንግሊዝኛው /Restitution/ የምንለው ማለት ነው፡፡ ሕግ እነዚህን ጥበቃዎች በሙሉ የሚያደርገው በፍርድ ቤቶች አማካኝነት መሆኑ ሊጤን ይገባል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ ባለመብቶቹ በራሳቸው መብታቸውን እንዲያስከብሩ ስልጣን ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ በፍትጠብሔር ሕግ ቁጥር 1149 ስር እንደ ተደነገገው፡፡
መርህዎች
ከውል ውጪ ያለ አላፊነት ሕግ መርሆዎችን በሚቀጥለው ክፍል በሰፊው እንመለከታለን፡፡ በአሁኑ ግን አጠር ባለ መልኩ ለመግቢያ የሚሆኑንን እንወያይ፡፡ አንድን ሰው በዚህ ሕግ ሥር አላፊ ለማድረግ አራት ዋና ዋና ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡ የመጀመሪያው አንድን ድርጊት ማከናወን በእንግሊዝኛው /Act/ የምንለው ሲሆን ሌላው ያለ ማከናወን በእንግሊዝኛው / omission / የምንለው ነው በሁለተኛ ደረጃ ይህ ማከናወን ወይም ያለማከናወን ጉዳት በእንግሊዝኛው /Damage / የምንለውን ማድረስ አለበት፡፡ በሶስተኛ ደረጃ በደረሰው ጉዳትና በድርጊቱ መሃል ምክንያታዊ ግንኙነት / Casual relationship/ ሊኖር ይገባል፡፡ በአራተኛ ደረጃ ይህ የደረሰው ጉዳት በሕግ እውቅና ያገኘ መሆን አለበት፡፡ /A kind of harm recognized as attracting legal liability / የምንለው ነው፡፡
ከላይ ያስቀመጥነውን በምሳሌ እናስረዳ፡፡ አቶ ጫላ ጥንቃቄ በጉደለው መልኩ መኪና እየነዳ ከዋናው መንገድ ወጥቶ እግረኞች በሚንቀሳቀሱበት ላይ በመውጣት አቶ መሐመድ ላይ ጉዳት አደረሰ እንበል፡፡ ድርጊቱ የአቶ ጫላ መኪና ያለጥንቃቄ መንዳት ሲሆን ጉዳቱ በአቶ መሐመድ የጉን አጥንት መሰበር ነው፡፡ ለዚህ ጉዳት ምክንያት ደግሞ የአቶ ጫላ መኪናውን በጥንቃቄ አለመንዳት ነው፡፡ ማለትም የአቶ ጫላ ጥፋት /fault/ ነው፡፡ ስለሆነም አቶ ጫላ አቶ መሐመድን ሊከስ አላፊነት አለበት ማለት ነው፡፡
በአንዳንድ ሁኔታዎች ስር ግን ጉዳትም ደርሶ ጉዳት አድራሹ ተጠያቄ የማይሆንበት ብሎም ጉዳት የደረሰበትን የማይካስበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ በምሳሌ እናስርዳ፡፡ አንድ የጫማ ችርቻሮ ንግድ የሚነግድ ነጋዲ ሃይሊ ገብረሥላሴ መንገድ ላይ አለ እንበል፡፡ ሚደቅሳ አጠገቡ ተመሳሳይ ጫማ ንግድ ከፍቶ ጫማዎቹን በርካሽ ሸጠ እንበል በዚሁ ምክንያት የመጀመሪያው ነጋዴ ከስረ እንበል፡፡
በዚህ ምሳሌ ጉዳት አለ፡፡ ጉዳቱም የጫማ ቤቱ ንግድ መዘጋት ነው፡፡ ለጉዳቱም ምክንያት የሚደቅሳ አጠገቡ ሌላ ተመሳሳይ ጫማ ቤት መክፈትና ጫማዎችን በርካሽ መሸጥ ነው፡፡ ለደረሰው ጉዳት /ኪሣራ/ ግን ጫላ ተጠያቂ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ጉዳቱ በሕግ እውቅና ያገኘ አይደለም እና ነው፡፡ ይህ በላቲን /damnum sine injuria / ይባላል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳት ሳይደርስ ካሣ የሚከፍልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ኡከን ኡከች ጣሂር ሳይፈቅድለት የጣሂርን መሬት ቢያቋርጥ ኡከን ኡከች መሬት ላይ ምንም ጉዳት ሳይደርስ ጣሂር ተጠያቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ በላቲን / injuria sine damno/ ይባላል፡፡ ጉዳት መኖሩን ማስረዳት ሳያስፈልግ አንድን ሰው ተጠያቂ ማድረግ እንደ ማለት ነው፡፡
ሕግ ጥበቃ የሚያደርግላቸው ጥቅሞች /መብቶች/ / Interests /
ሕግ ጥበቃ የሚያደግላቸው መብቶችን ከላይ ሕግ መንግስቱ ጥበቃ ያደረገላቸው ብለን ካስቀመጥናቸው መብቶች አንፃር በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያዎቹ ከአንድ ሰው ሰውነት ጋር የተያያዙ መብቶች ሲሆኑ ሁለተኛ ከንብረት ከምጣኔ ሀብት ጋር የተያያዙ መብቶች ናቸው፡፡ በእንግሊዝኛው / Personal property / እና / economic interest/ የሚባሉት ናቸው፡፡ ሶስተኛ ደግሞ ሌሎች ብለን መመደብ እንችላለን፡፡
ከሰውነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው መብቶች
ከላይ በክፍል አንድ ስር የኢፊዲሪ ሕገ መንግስት እውቅና የሰጣቸውና ጥበቃ ያደረገላቸውን መብቶችን አይተናል፡፡ ከእነሱም መሃል ከሰውነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው መብቶች አንዱን ክፍል ይይዛሎ፡፡ ሕግ መንግስቱን መነሻ በማድረግ ከውል ውጨ አላፊነት ሕግ እነዚህን መብቶች ይዘረዝራል፡፡
እነዚህ ከሰውነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው መብቶች በተለያየ መንገድ ክልከላና ጥበቃ ተደርጉላቸዋል፡፡ አንድ ሰው የሌላን ሰው ሰውነት ያለተነኪው ፈቃድ መንካት አይችልም፡፡ ቢነካ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ እንዲሁም በሌላ ሰው ሰውነት ላይ ጥቃት መፈፀም አይችልም፡፡ ከላይ ማንም ሰው ከቦታ ቦታ መዘዋወር ሕገ መንግስታዊ መብቱ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ከሕግ አግባባ ውጨ አንድ ሰው የሌላውን ሰው የመዘዋወር ነፃነት ቢገደብ ገዳቢው ተጠያቂነት አለበት እንዲሁም አንድ ሰው ስብዕናውና መልካም ስሙ ያለመነካት መብት አለው፡፡ ስብእናው እና መልካም ስሙ ሲነካ ይህን ፈፃሚውን በስም ማጥፋት /defamation/ ሊጠይቀው ይችላል፡፡
የንብረት እና የምጣኔ ሀብት መብቶች
ይህ መብት በሌላ ሰው ይዞታ ላይ ሁከት መፍጠርን፣ተንቀሳቃሽ የሆነ ንብረትን ያለ አግባብ መያዝን ያካትታሉ፡፡ እንዲሁም ሕገ ወጥ የሆኑ የንግድ ተግባራትን / Un law ful business practice/ እዚሁ ክፍል ስር ይመደባሉ፡፡ ለምሳሌ ሕገ ወጥ የሆነ የንግድ ውድድር /Unfair competition/ እንደ ማለት ነው፡፡
የአእምሮ ሁኔታ ከውል ውጨ በሚደረስ አላፊነት ስር /The Mental Element In Tort/
ከውል ውጪ ኃላፊነት ምንጨች ሶስት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ጥፋት ነው፡፡ ሁለተኛው በይዞታ ስር ወይም የራስ የሆነ ንብረት ወይም አንድ ሰው ከሚያከናውነው ምጣኔ ሐብታዊ እንቅስቅሴ የሚመነጭ በእንግሊዝኛው /Strict liability/ የምንለው ነው፡፡ ሶስተኛ ደግሞ ለሌሎች ተጠያቂ ከመሆን የሚመነጭ ኃላፊነት ነው፡፡ በእንግሊዝኛው /Vicarious liability/ የምንለው ነው፡፡ ከሶስቱ አላፊነቶች /the mental element/ አስፈላጊ የሚሆነው በጥፋት ላይ ለተመሠረተ ብቻ ነው፡፡ ለተቀሩት ሁለቱ የአእምሮ ሁኔታን ማስረዳት አስፈላጊ አይሆንም፡፡
በጥፋት ላይ የተመሠረተ አላፊነት ታሪክ እንደሚያስረዳው ይህ ተጠያቂነት /Develop/ የተደረገው አዳጊ ኢንዱስትሪዎችን ለማገዝ ሰዎች የእነዚህን ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ለደረሰው ጉዳት አላፊ ለማድረግ ጥፋትን ማስርዳት የግድ እንዲል ሆነ፡፡ በተጨማሪም ጥፋተኞች እንዲቀጡ የግድ አስፈላጊ ሆነ፡፡ በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች በጥፋት ላይ የተመሠረተ አላስፈላጊ ተቃውሞ በሌላ በኩል ደግሞ አንድን ባለ ኢንዲስትሪ ተጠያቂ ለማድረግ ጥፋትን ማስረዳት የግድ ማለቱ በኢንዱስትሪ ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞች በሥራ ላይ ጉዳት ሲደርስባው ካሣ እንዳይከፈላቸው አደረገ፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥፋትን ማረጋገጥ ሳያስፈልግ አላፊነት እንዲኖር ተደረገ፡፡ ይህም /Strict liability / የሚባለው ነው፡፡ አሁን /State of mind/ ዓይነቶችን እንመለከታለን፡፡ ከውል ውጨ ላለ አላፊነት ሁለት ዓይነት /State of mind/ አሉ እነሱም /intention and negligence ናቸው፡፡
Intention
Intention/ አንድ ነገር ሆነ ብሎ አስቦ ማድረግ /አለማድረግ/ ነው፡፡ ይህን Intention ቀጥሎ ባለው ሁኔታ ማየት እንችላለን፡፡
የመጀመሪያው አንድ ሰው በሕግ የተከለከለን ውጤት ለማምጣት ፍላጉት ሲኖረውና ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ይህንኑ ውጤት /For see/ ሲያደርግ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ሥር ሶስት መሟላት ያለባቸው ነጥቦች አሉ ለማለት ነው፡፡ የመጀመሪያው ውጤቱ በሕግ የተከለከለ መሆን አለበት ሁለተኛ ይህን ውጤት ለማምጣት ፍላጉት መኖር አለበት ሶስተኛ ውጤቱን አስቀድሞ ማየት መቻል / for see it/ አለበት፡፡
Negligence
Negligence ብዙ ትርጉሞች ሊኖሩት ይችላሉ ፡፡ አንዱ /Careless behavior/ የምንለው ነው፡፡ በዚህ ስር ፍ/ቤት ግንዛቤ የሚወሰደው የአድራጊውን ድርጊት /Conduct/ ነው፡፡ ለአንድ ሰው የሌሎች ሰዎች ደህንነት ምንም ቁም ላይሰጠው ይችላል፡፡ ሆኖም ምንም ጉዳት እስካላደረሰ ድረስ ተጠያቂ ላይሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የተቻለውን ያህል ጥረት አድርጉም /ጉደቱ ቢደርስ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ እዚህጋ መመዘኛው ነባራዊ መመዘኛ / Objective Standard/ የምንለው ነው፡፡ ፍ/ቤቱ በዚሁ ሁኔታ ስር አንድ / reasonable man / የተጠያቂው ቦታ ላይ ቢሆን ኖሮ የሚያደርገውን ነው እግምት ውስጥ የሚከተው፡፡ ስለሆነም የእያንዳንዱ ግለሰብ አለመቻል አይደለም እግምት ውስጥ የሚገባው፡፡
ይህን በምሳሌ እናስረዳ፡፡ ለይኩን ለማጅ አሽከርካሪ ነው እንበል፡፡ መምህሩ ደግሞ ደርበው ይባላል እንበል፡፡ ለይኩን በልምምድ ላይ አያለ በቸልተኝነት ደርበው ላይ ጉዳት ቢያደርስ ለይኩን ላደረሰው ጉዳት ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ለይኩን የሚመዘነው በለማጅነቱ ሳይሆን ብቃት ባለው በአማካይ አሽከርካሪ /Average Competent Driver/ ሚዛን ነው፡፡
- Details
- Category: Property Law
- Hits: 6711
ይህ ዓይነት የአእምሮ ንብረት መብት ለኢትዮጵያ አዲስና ከወጣም ብዙ ዓመታትን ያላስቆጠረ መብት ነው፡፡ የዕፀዋት አዳቃዮች መብት ለማስጠበቅ የወጣው አዋጅ ቁጥር 481/98 አላማም በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ተመራማሪዎችና በልማዳዊ አሰራር ዝርያን የሚያዳቅሉ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የሰራቸው ውጤት ተጠቃሚዎች ለመሆን የሚያስችላቸውን ኢኮኖሢያዊ ጥቅም ለማስጠበቅና የቆየው የዝርያ መጠቀምና መለዋወጥ ልማዳዊ ስርዓታቸው እንዲቀጥል ለማድረግና የተሻለ ዝርያ በመጠቀም የተሻለ ምርት እንዲያመርቱ በማስቻል የልማት ስትራተጂውን ከግብ ማድረስ ነው፡፡
አዋጁ በርእስነት የተጠቀመባቸውን ሁለት ስለዕፀዋትና አዳቃዮች የሚሉትን ቃላት በትርጉም ክፍሉ አንቀፅ 2(6)” ዕፀዋት” የሚለውን ቃል” “ዕፀዋት ማለት እንሰሳ ያልሆነ እና በተፈጥሮ መራባት የሚችል ሕይወታዊ ሃብት ነው፡፡” ሲል ”አዳቃይ” ማለት
አዲስ የዕፀዋት ዝርያ አዳቅሎ ያወጣ ሰው ወይም
አዲስ የዕፀዋት ዝርያ አዳቅሎ ያወጣን ሰው ቀጥሮ ወይም ስራውን ተኮናትሮ ያሰራ ሰው ወይም በዚህ ንዑስ አንቀፅ “ ሀ ” ወይም “ ለ” የተጠቀሰ ሰው ወራሽ የሆነ ሰው ነው፡፡’
በማለት ፍቻቸውን ይሰጣል:: ከነዚህ ሁለት መብቱን የሚገልፁ ቃላት ትርጉም መረዳት የሚቻለው መብቱን ለማግኘት በማዳቀል የተገኘው ዘር አዲስ መሆን እንዳለበት፤ ሌላ ሰውን ቀጥሮ በማሰራት በሚገኘው አዲስ ዝርያ የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብትን ማግኘት እንደሚቻልና በመጨረሻም የግኝቱ ባለቤት ወራሽ መብቱን ሊያወርስ እንደሚችል ነው፡፡
በዚህ አዋጅ መሰረት አዳቃዮች የሚኖራቸው መብት ምንድ ነው? ብለን ያየን እንደሆነ በመብቱ ያለመከልከለ ወይም ከክልከላ ነፃ መሆን (Exemptions) እና ገደቦች (restrictions) እንደተጠበቁ ሆነው የዕፅዋት አዳቃዩ ሌሎች ሰዎች የተጠበቀን የተክል ዝርያ ወይም የዝሪያ አካል እንዲሸጡ፣ እንዲገዙ የመፍቀድና በማንኛውም መንገድ በሌላ ሶስተኛ ወገን የመብት ጥሰት ሲያጋጥም በመደበኛ ፍ/ቤት አቅርቦ የማስቀጣት መብቶች ናቸው ፡፡ እነዚህ መብቶች ፍፁም መብቶች (monopoly or absolute rights) ባለመሆናቸው ህጉ በአንቀፅ 6 ላይ ከክልከላ ነፃ የሆኑ ድርጊቶችን (exemptions) በዝርዝር አስቀምጧል::
በመሆኑም ለንግድ ስራ ሳይሆን ለሌላ አገልግሎት እንዲውል የማራባት፣ መዝራት ወይም መጠቀም በህግ የሚያስጠይቅ ተግባር አይደለም፡፡ ለምግብነት ወይም የዝሪያውን ማብቀል ወይም ማራባት ለሚያስከትሉ ሌሎች አገልግሎቶች እንዲውል መሸጥ አያስጠይቅም፡፡ ተተክለው በሚገኙበት ማሳ መይም በማናቸውም ሌላ ቦታ ላይ እንዳሉ መሸጥ፡፡ አዲስ ዝርያን ለማውጣት በመነሻ የተለያየነት (variety) ምንጭነት አድርጐ አንድ የተጠበቀን ዘር ወይም የዘር አካል መገልገል፡፡ በምግብነት በቤት ለመጠቀም ወይም በገበያ ለመሸጥ የተጠበቀውን ዝርያ መዝራት፡ ለቀጣይ ምርምር፣ ለትምህርት አገልግሎት ሲባል የሚደረግ ማዳቀል ከጂን ባንክ ወይም ከዕፅዋት ጀነቲክ ማዕከል ዝሪያውን ማግኘት በአዋጁ መሰረት የማያስከስሱ ግን ደግሞ ለንግድ ስራ እንዳይውሉ ለባለመብቱ ጥበቃ የሚሰጠው መብት ነው፡፡
የዕፅዋት አዳቃይ ባለቤት በመብቱ እንዳይሰራበት ሊደረግ ወይም ሊታገድ እንደሚችል በአንቀፅ 7 ላይ የተዘረዘሩ ሲሆኑ እነሱም፤
በዕፅዋት አዳቃዮች መካከል በሚደረግ ውድድር ምክንያት ችግር ሲፈጠር ወይም
ዝርያው በምግብ ዋስትና ፣ በስነ ምግብ (nutrition) ወይም ጤና ፍላጐቶች ወይም ብዝሀ ሕይወት (biological diversity) ላይ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያደርስ ሆኖ ከተገኘ
ለገበያ የሚውለው ዝሪያ አብዛኛው ከውጪ የመጣ ሲሆን ወይም
የአርሶ አደሩ ማህበረሰብ ለአንድ ለተወሰነ የተጠበቀ ዝሪያ ዘር ያለው ፍላጐት ያልተሟላ የሆነ እንደሆነ ናቸው፡፡
የዕፅዋት አዳቃይነት መብት ለማግኘት ያለው መስፈርት ምንድን ነው? አዋጁ ለዚህ መልስ የሚሰጥ ሲሆን አንድ የዘርፉ ተመራማሪ ወይም በልማዳዊ የማዳቀል ዘዴ መብቱ ይጠበቅልኝ ብሎ የሚያመለክት ሰው የዚህ መብት ባለቤት ተብሎ እውቅና በግርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር እንዲሰጠው ከተፈለገ ፤
የዕፀዋቱ ዝሪያ አዲስ መሆን ይኖርበታል ይኸውም በአዋጁ አንቀፅ 2(5) መለኪያ መሰረት ተገኘ የተባለው ዝርያ ማመልከቻው ባቀረበበት ዕለት መኖራቸው በህዝብ ከታወቁት ከሁሉም ሌሎች ዝርያዎች በግልፅ የሚለይና በተደረጉ ማራባቶች ምክንያት ዋና ዋና ባህሪያቱን ሳይለወጥ የሚቆይና በበቂ ሁኔታ ወጥ የሆነ አንድ ዓይነት ዝሪያ ወይም ተለይቶ የሚታወቅ ሕብረ-ዝሪያ (multi line) የሆነ እንደሆነና የዘር፣ ፍራፍሬ ወይም ወይን ዝሪያ በሆነበት ጊዜ ከ6 ዓመት በፊት ወይም ሌሎች ዝሪያዎችን የሚመለከት ሲሆን ማመልከቻው ከቀረበበት ዕለት 4 ዓመት በፊት ያልሸጠው ወይም ያላስተላለፈው መሆኑ ታይቶ እንደ አዲስ ዝርያ ተወስዶ ባለመብት ሊሆን ይችላል፡፡
መብቱን ለመስጠት የሚከለክል ምክንያት ከሌለ መብቱ ይሰጠዋል፡፡
መብቱ ቀደም ሲል ለሌላ ሰው ያልተሰጠ ሲሆን የሚሰጠው ይሆናል::
ቀደም ሲል የቀረበ ግን ደግሞ ያልተወሰነ ወይም ውድቅ ያልተደረገ የዕፀዋት አዳቃዮች ማመልከቻ የሌለ እንደሆነ ይታይለታል፡፡
ለመብቱ መከፈል ያለበትን ክፍያ የከፈለ እንደሆነ እውቅናው ይሰጠዋል::
ዝርያውን አዳቅሎ ለማውጣት ጥቅም ላይ የዋለን የጀነቲክ ሀብት አመልካቹ በተገቢው የአክብሮት ህግ (relevant laws on access to genetic resource) ያገኘው መሆኑ ሲረጋገጥ መብቱ ይሰጠዋል፡፡ ቀጥሎ መነሳት ያለበት ጉዳይ ይህ መብት ሊሰጥ የሚችለው ለማን ነው? የሚለው ሲሆን የዕፀዋት አዳቃዮች መብት ለኢትዮጵያዊም ሆነ የውጭ ዜጋ በአገር ውስጥ የተገኘ ይሁን በውጪ አገር መስፈርቱን ካሟላ ለአመልካቹ መብቱ ይሰጠዋል፡፡ ይኸውም በግለሰብ ደረጃ፣ በጋራ እና በድርጅት ሰም ሊሰጥ የሚችል ሲሆን እዚህ ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ሁለት የተለያዩ የዕፅዋት አዳቃዮች በተመሳሳይ ዝርያ መብቱ እንዲሰጣቸው በሚያመለክቱበት ጊዜ የቀደምትነት መብት የሚሰጠው ቀድሞ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ላመለከተው ሰው መሆኑን ነው፡፡
የዕፅዋት አዳቃይነት መብት በማስመልከት ምን ማለት እንደሆነ መብቱ ጥበቃ የሚደረግለት ለምን እንደሆነና ህጉ የሚያስቀምጣቸውን ከክልከላ ነፃ መሆን (exemptions) እና ገደቦች (restriction) እና ባለ መብት ለመሆን ያሉትን መመዘኛዎችና መብቱ ለማን ሊሰጥ እንደሚችል ተመልክተናል ቀጥለን የምናየው ደግሞ ይህ በህግ የሚቋቋም መብት እንዴት እንደሚተላለፍ፣ እንደሚተውና እንደሚሰረዝ ይሆናል፡፡ የዕፅዋት አዳቃዮች መብት በህግ ወይም በውል ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ የሚቻል ግዙፍነት የሌለው የአእምሮ የንብረት መብት ሲሆን መብቱ የሚተላለፈው በውል በሚሆንበት ጊዜ ውሉ በዕፀዋት አዳቃዮች መዝገብ ካልተመዘገብ ህጋዊ ውጤት አይኖረውም፡፡ አንድ ሰው የዕፅዋት አዳቃይነት መብት ካገኘ በኋላ ባለቤቱ በራሱ ፈቃድ መብቱን ትቻለሁ ብሎ ለሚኒስቴሩ በማመልከት መተው ይችላል፡፡ ህጉ ከዚህ ጋር ተያያዥነት ባለው መልኩ የሚደነግገው የተለየ ሁኔታ (exeption) ቢኖር በመብቱ ሳቢያ በፍ/ቤት ክስ ቀርቦበት ወይም ተከራካሪ ሆኖ ባለበት ጊዜ መብቱን ትቻለሁ ብሎ ለሚኒስቴሩ ቢያመለክትም ሚኒስቴሩ የፍ/ቤት ፈቃድ ሳያገኝ ማመልከቻውን ሊቀበል የማይችል መሆኑ ነው፡፡ የዕፅዋት አዳቃይነት መብት መሰረዝን በተመለከተ አንድ ሰው የባለቤትነት መብቱ ለሌላ ሰው በመስጠቱ ምክንያት ጥቅሜ ተነክቷል የሚል ወገን ሲያመለክት የማጣራቱ ስራ ለወደፊቱ በሚወጣው ደንብ መሰረት ተጣርቶ መብቱ ለመሰረዝ የሚያስችል ምክንያት ሲገኝ የነበረው መብት ይሰረዛል፡፡ እንደዚሁም ከተሰጠው በኋላ ዝርያው አዲስ ያለመሆኑ ሲረጋገጥ ወይም ከመስጠቱ በፊት ቢታወቅ ኖሮ አይሰጠውም ነበር የሚያሰኝ ምክንያት ሲገኝ መብቱ ይሰረዛል፡፡ ሌሎች የዕፅዋት አዳቃይነት መብት ሊያሰርዙ የሚችሉ ምክንያቶች እንደ መክፈል ያለበትን ገንዘብ የመክፈያው ቀን (due date) ከደረሰ በኋላ በ9ዐ ቀን ጊዜ ውስጥ ሳይከፍል መቅርት ወይም አንድን የተጠበቀን ዝሪያ ሳያድስ መቅረት መብቱን ሊያሰርዙ የሚችሉ ምክንያቶች በአዋጁ ተደንግገው የምናገኛቸው ናቸው፡፡
የዕፀዋት አዳቃዮች መብትን መሰረት በማድረግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 481/98 ለገበሬዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ልዩ ጥበቃ የሚሰጥ ነው::
ካመረቱት ዘር ዝርያውን ወይም የዝርያውን አካል የማስቀመጥ፣ የመለወጥ፣ የመጠቀምና የመሸጥ መብትን ይሰጣቸዋል፡፡
ከጄነቲክ ማዕከላትና የጂን ባንክ ዝርያን የማውጣትና የመጠቀም መብትንና
የተጠበቀ ዝርያን ዘርተው ካገኙት ምርት ዝርያን በጋራ የማስቀመጥ ፣ የመጠቀም፣ የማባዛትና የማዘጋጀት መብትን ይሰጣቸዋል:: ሆኖም ግን አንድን ዘር ወይም የዘርን አካል በዘር ኢንዱስትሪ ውስጥ ለንግድ በሆነ መጠን እንዲሸጡ አይፈቀድላቸውም፡፡
ይህ መብት እንደሌሎቹ የአእምሮ ንበረት መብቶች ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ በህግ የተደነገገ ሲሆን ጊዜው የመብቱ መሰረት የሆነውን ዝርያ መሰረት በማድረግ በሁለት የተከፈለ ነው:: ይሄውም መብቱ የተሰጠው ዓመታዊ ሰብሎችን መሰረት በማድረግ ከሆነ ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ ማመልከቻው ከቀረበበት ቀን አንስቶ ለቀጣይ 20 ዓመታት ነው፡፡ የመብቱ መሰረት ዛፎችን የወይን ተክሎችን ወይም ሌሎች ቋሚ ተክሎች በሚሆኑበት ጊዜ ደግሞ ይህ መብቱ ፀንቶ የሚቆየው ማመልከቻው ከቀረበበት ቀን አንስቶ ለቀጣዮቹ 25 ዓመታት ይሆናል:: ህጉ መብቱ ፀንቶ ባለበት ጊዜ የሚከሰቱ የመብት ጥሰቶችን መሰረት በማድረግ ባለ መብቶች ጉዳያቸውን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በማቅረብ በከሳሽነት፣ በተከሳሽነት ወይም በተከሳሽ ከሳሽነት ሊከራከሩና ፍርድ ቤት ካሳ ማስከፈልን ጨምሮ በቅጣት ከ6 ወር በማያንስ እስራትና ከብር አምስ ሺህ በማያንስ መቀጮ ሊቀጣ አንደሚችል የሚደነግግ ስለሆነ ለዜጐች ፈጠራ ስራ ዋስትና የሚሰጥ ነው፡፡
የዕፅዋት አዳቃዮች መብትን በማስመልከት የወጣው አዋጅ ቁጥር 481/98 በርካታ መብቶችን በማስጠበቅ ለህዝብ ጥቅም ሲባል ብቻ በመብቱ ከክልከላ ነፃ የሆኑ ሁኔታዎችንና ገዳቦችን በመዘርዘር ዜጐች ስርዓት ባለው መንገድ የግኝታቸው ባለቤትነት እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው:: ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማስጠበቅ የዘርፉ ተመራማሪዎችን በማበረታታት አገሪቱ ከዚህ የልማት አንድ አካል የሆነው ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችል ነው::
ስለዚህእስካሁን እያየናቸው የመጣን ዝርዝር ነገሮች የአእምሮ ንብረትን የሚመለከት አገራችን ከማንኛውም ጊዜ የበለጠና ዘመናዊ ህግ እንዳላት የሚያመላክትና ዜጎች በዚህ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዋስትና የሚሰጡ ናቸው :: ሆኖም ግን በአንድ አገር ፍትሓዊና ዘመናዊ ህግ መኖሩ ብቻ በራሱ ግብ ሊሆን ስለማይችል የህጎቹን አላማ ተገንዝበን ህብረተሰባዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አመረቂ ስራ በመስራቱ ሂደት የፍትህ አካላትና መላው ህ/ሰብ አበክረው ሊሰሩና ከጥሰት እነዚህን የአእምሮ ንብረቶችን አንደ ዓይን ብሌናቸው ሊንከባከቧችው ይገባል::
- Details
- Category: Property Law
- Hits: 11202
የንግድ ምልክት ማለት ምን ማለት እንደሆነ የንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 501/98 በአንቀፅ 2(12) ላይ፡-
የንግድ ምልክት ማለት የአንድን ሰው ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ከሌሎች ሰዎች ወይም አገልግሎቶች ለመለየት የሚያስችል የሚታይ ምስል ነው፡፡ ምልክቱ ቃላቶችን፣ ዲዛይኖችን፣ ፊደሎችን፣ ቁጥሮችን፣ ቀለሞችን ወይም የዕቃዎችን ወይም የመያዣዎቻቸውን ቅርፅ ወይም የእነዚህኑ ቅንጅት ሊይዝ ይችላል፡፡ በማለት ሲተረጉመው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ Wikipedia the free encyclopedia
Trade mark is a distinctive sign or indicator of some kind which is used by an individual, business organization or other legal entity to identify uniquely the source of its products and/or services to consumers, and to distinguish its products or services from those of other entities.
ሲል የንግድ ምልክት ምንነትን ይገልፃል፡፡ ስለሆነም የንግድ ምልክት ማለት የአንድን ምርት ወይ አገልግሎት ወይም ምንጭ (origin) በማስመዝገብ እንደ ብቸኛ መለያ (exclusive sign) ተወስዶ ሰዎች አንድን ምርት ወይም አገልግሎት ከሌላው ምርትና አገልግሎት ለመለየት የሚያገለግል ምልክት ሆኖ ማሳከር (confusion) የማስወገድ አላማ ያለው ነው፡፡
የንግድ ምልክት ህጋዊነት የሚመሰረተው ወይም ጥበቃ የሚያገኘው በምዝገባ እንደሆነ ከአዋጁ አንቀፅ 4፣ 5፣ 15 እና 16 መረዳት የሚቻል ሲሆን Wikipedia ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ የንግድ ምልክቶች የሚባሉ እንዴት ያሉ ምልክቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ልክ በአንቀፅ 2(12) እንደተዘረዘረው፡-
A trade mark is a type of intellectual property, and typically comprises a name, word, phrase, logo, symbol, image or combination of these elements.
በማለት የንግድ ምልክቶች ምን ዓይነት ሊሆኑ እንደሚችሉ መዘርዘሩ ህጋችን የቱን ያህል አለማቀፋዊ መመዘኛዎችን (international standards) ያሟላ እንደሆነ የሚያመለክት ነው፡፡
የንግድ ምልክት አላማም ዕቃ በማምረት እና በማከፋፈል ወይም አገልግሎት በመስጠት የንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች መልካም ስም እና ዝና ለማስጠበቅና በተመሳሳይ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች መካከል መሳከር (confusion) በማስወገድ የንግድ ስራ የነፃ ገበያ ስርዓትን መርህ ተከትሎ እንዲሄድና የሸማቾችን ምርጫ ማስጠበቅም ነው:: ብሄራዊ ጥቅም በተለይም የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ስትራተጂን እውን የማድረግ አላማም ያለው ነው፡፡ በመሆኑም ጤናማ፣ ነፃ ውድድርና በእውቀት ላይ የተመሰረተ የግብይት ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ ህጉ በሚያዘውና ግልፅ በሆነ የንግድ ምልክት ላይ ተመስርቶ ማምረትና አገልግሎት መስጠት ለአንድ ህብረተሰብ እድገት ቁልፍ መሳርያ ነው፡፡ በመሆኑም በነፃ ገበያ መርህ መሰረት ጤናማ የምርትና አገልግሎት ውድድር በማካሄድ ህብረሰተቡ ሰፊ አማራጭ አግኝቶ ለከፈለው ዋጋ የሚመጥን እቃ ወይም አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ የአዋጅ ቁጥር 329/95 የንግድ አሰራር መርህን የተከተለ መሆን ይኖርበታል፡፡
የንግድ ምልክት ምዝገባ
ለምዝገባ ብቁ መሆን የሚቻለው፤-
የንግድ ምልክት የአንድን ሰው ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ከሌሎች ሰዎች ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች በግልፅ ለመለየት የሚያስችል መሆን ለመመዝገብና ህጋዊ ጥበቃ ለማግኘት አንዱ መስፈርት ነው፡፡ (አንቀፅ 5(1) )
አንድ የንግድ ምልክት በጥቁርና ነጭ ወይም በከለር ቀለም ሊመዘገብ ይችላል:: በጥቁርና ነጭ ቀለም የተመዘገበ የንግድ ምልክት በማናቸውም የቀለሞች ቅንጅት ጥበቃ የሚደረግለት ሲሆን የንግድ ምልክቱ የተመዘገበው በከለር ቀለም ከሆነ ጥበቃ የሚደረግለት በተመዘገበው የከለር ቀለም ቅንጅት ብቻ ይሆናል፡፡ (አንቀፅ 5(2) )
አንድ ሊመዘገብ የሚችል የንግድ ምልክት የምልክቱ ልዩ ባህሪ የሚቀንስ ወይም የሌላ ሰውን መብት የሚጥስ እስካልሆነ ድረስ ጥበቃ ሊደረግላቸው የማይችሉ ክፍሎችን ሊይዝ ይችላል፡፡ (አንቀፅ 5(3) )
ለምዝገባ ብቁ ስለማይሆኑ የንግድ ምልክቶች በማስመልከት አዋጁ በአንቀፅ 6 ላይ የዘረዘራቸውን ስንመለከት ደግሞ:-
በአንቀፅ 5 የተዘረዘሩትን መስፈርቶች የማያሟላ ሲሆን ምልክቱ በንግድ ምልክትነት አይመዘግብም፣
ድምፅ ወይም ሽታን የያዘ የንግድ ምልክት አይመዘገብም፣
ከሌሎች ሰዎች ዕቃዎች ወይም አገልግልቶች ለመለየት የማያስችል ከሆነ የንግድ ምልክቱ አይመዘገብም፣
የህዝቡን ሰላምና ስነ-ምግባር የሚፃረር ሲሆን እንደዚሁ አይመዘገብም ፣
የዕቃዎች ወይም የአገልግሎቶች ዓይነቶች፣ ጥራት፣ ብዛት፣ ጠቀሜታ፣ ዋጋ ወይም የመነጨበትን ቦታ፣ የተመረተበት ወይም የሚቀርብበትን ግዜ ወይም ባህሪ ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣
የንግድ ምልክቱ የሚመለከታቸው ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች በሚመለከት ወይም በኢኮኖሚያዊ ወይም የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የተለመዱና በጋራ መግባብያ ቋንቋነት የሚያገለግሉ ምልክቶች ወይም መለያዎች ብቻ የያዘ የንግድ ምልክት ሲሆን፡፡
ከዕቃው ተፈጥራዊ ሁኔታ የመነጨ ወይም የአንድን ዕቃ ቴክኒካዊ ውጤት ለማግኘት አስፈላጊ የሆነን ወይም ዕቃው ላይ ከፍተኛ ዋጋ የሚጨምርን ቅርፅ ብቻ የያዘ የንግድ ምልክት::
የዕቃዎቹ ወይም አገልግሎቶቹ የመነጩበት ቦታ ወይም ዓይነትና ባህሪ በተለመከተ ህዝቡን ወይም የንግዱን ማህበረሰብ ሊያሳሳት የሚችል የንግድ ምልክት ሲሆን፡፡
ከአሁን ቀደም በተዘጋጀ ኦፊሴላዊ ምልክት የተመዘገበ የማንኛውም ሀገር መንግሰት፣ በይነ-መንግስታዊ ድርጅት ወይም በአለም አቀፍ ስምምነት የተቋቋመ ድርጅት፣ ወታደራዊ ምልክት፣ ሰንደቅ አላማ፣ ሌላ አርማ፣ ስም፣ ምህፃረ ቃል፣ የስም አህፅሮት መሰረት ያደረገ የንግድ ምልክት ሲሆን፡፡
የአመልካቹ የቤተዘመድ ስብ ብቻ የያዘ የንግድ ምልክት
ያለ ግለሰቡ ፈቃድ የአንድን በህይወት ያለ ግለሰብ ሙሉ ስም የያዘ የንግድ ምልክት ሲሆን በህግ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንድ አመልካች እንዲመዘገብለት የሚያቀርበው ምልክት የሶስተኛ ወገን መብት የሚነካ በሚሆንበት ግዜ አይመዘገብም:: ከዚህ አኳያ ህጉ የሶስተኛ ወገኖችን መብት በመጠበቅ የንግድ ምልክት እንዳይደረግ የሚከለክልባቸው ሁኔታዎች በአንቀፅ 7 ላይ የተዘረዘሩ ሲሆን እነሱም፤
ቀደም ሲል ከተመዘገበ የንግድ ምልክት ጋር ተመሳሳይ ሲሆንና ማሳከርን (confusion) የሚፈጥር ሲሆን፤
የንግድ ምልክቱ የአንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ የሆነ የሌላ ሰው እቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በሚመለከት የንግድ ምልክት ጋር አንድ ዓይነት ወይም ሊያሳስት በሚችል ደረጃ ተመሳሳይ ከሆነ ወይም ትርጉሙን ከያዘ፤
በባለቤቱ በፅሁፍ የተሰጠ ፈቃድ ሳይኖር የንግድ ምልክት ጥበቃ የሚደረግለትን የሌላ ሰው የስነ-ፅሁፍ ወይም ኪነ-ጥበባዊ መብት ወይም የሌላ ሰውን የፎቶግራፍ ወይም የዲዛይን መብት የያዘ ነው ተብሎ ሲታመን የንግድ ምልክቱ አይመዘግብም፡፡ ያለመመዝገብ ህጋዊ ውጤት እንደሚታወቀው የህግ ጥበቃ አለማግኘትና ከህግ ጋር በሚፃረርበት ግዜ ደግሞ ለፍ/ብሄርና ወንጀል ተጠያቂነት የሚዳርግ ነው፡፡
ምዝገባ የሚያስገኘው መብት
ባስመዘገበው የንግድ ምልክት የመጠቀም ወይም ሌላ ሰው እንዲጠቀበት የመፍቀድ መብትን ያስገኛል፡፡
ሌሎች ወገኖች የንግድ ምልክቱን በሚያሳስት መንገድ እንዳይጠቀሙና ህዝቡን እንዳያሳስቱ የማድረግ መብትን ያጐናፅፋል፡፡
- ሌሎች ሰዎች የባለቤቱን ጥቅምን በሚጐዳ አኳኃን እንዳይገለገሉበት የማድረግ መብት ይሰጣል፡፡
- ሌሎች መሰል ድርጅቶች ተመሳሳይ ምልክት ተጠቅመው ማሳከር በመፍጠር መብቱ እንዳይጐዱ ለማገድ የሚያስችል መብት ያስገኝለታል::
- የንግድ ምልክት ማሳከር (confusion) ተፈጥሯል ባለበት ግዜ ክስ የመመስረት መብት ይኖረዋል፡፡ (አንቀፅ 26)
የአንድ የንግድ ምልክት መመዝገብ ከፍ ብለን ያየናቸውን መብቶች የሚያስገኝ ቢሆንም መብቶቹ ያለገደብ የተሰጡ አይደሉም፡፡ በመሆኑም አንቀፅ 27 በምዝገባ የተገኙ መብት ገደብን በማስመልከት የንግድ ምልክቱን በመያዝ በእቃዎቹ ምንጭ ዓይነት ለውጥ ሳይደረግባቸው በማንኛውም አገር በመሸጥ ላይ ባሉ ሶስተኛ ወገኞች ላይ የንግድ ምልክቱ ባለቤት የመከልከል መብት አይኖረውም፡፡ እንዲሁም ሶስተኛ ወገኖች በቅን ልቦና ዕቃቸውን ወይም አገልግሎታቸውን ምንጭ በማያሳስት መንገድ ለማስተዋወቅ ወይም ለመረጃ አላማ እንዳይገለገሉበት የንግድ ምልክት ባለቤቱ መከልከል አይችልም፡፡ ይህ ማለት ግን ሶስተኛ ወገኖች በነዚህ ገደቦች ሽፋን በባለመብቱ ላይ ጉዳት እዲያደርሱ ህጉ ፈቅዷል ማለት አይደለም፡፡
የንግድ ምልክት በምዝገባ መብቶችን ሲያስገኝ ገደቦች ያሉበት እንደመሆኑ ሁሉ የንግድ ምልክቱ ምዝገባ ፈራሽ የሚሆንባቸው ሁኔታዎችና የምዝገባው ፈራሽነት ውጤት ምን እንደሆነም በህጉ ሽፋን ተሰጥቶታል፡፡ ምዝገባው ፈራሽ የሚሆነው በአዋጁ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ሳያሟሉ የቀሩ እንደሆነ ምዝገባው ፈራሽ ይሆናል፡፡ እንደዚሁም ምዝገባው በከፊል ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ላይ ከሆነ ባልተመዘገቡት ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ላይ የንግድ ምልክቱ በከፊል ፈራሽ ይሆናል፡፡(አንቀፅ 36) የምዝገባው ፈራሽነት ውጤትም ውሳኔው ተፈፃሚነት የሚኖረው የንግድ ምልክቱ ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ ነው፡፡ ይህም ማለት የምዝገባው ፈራሽነት ወደ ኃላ ተመልሶ ውጤት (retroactive effect) ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ የሶስተኛ ወገኖች መብትን ለመጠበቅ የንግድ ምልክቱ ፈራሽ ስለመሆኑ በአእምሮ ንብረት ጋዜጣ ወይም ሰፊ አገራዊ ስርጭት ባለው ጋዜጣ በማውጣት እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡ በዚህ መንገድ ፈራሽ የሆነ የንግድ ምልክት ባለቤት በፈቃድ ውል ምልክቱን የሰጠው አካል ይህን የንግድ ምልክት እንዲከፍል ያደረገው ገንዘብ ቢኖርም ይመለስልኝ ብሎ መጠየቅ ግን አይችልም፡፡ ስለዚህ የንግድ ምልክት ፈራሽ መሆን ሁለት ውጤቶች ያሉት ሲሆን እነሱም ወደ ኃላ ተመልሶ የመስራትና ለምዝገባው ሲባል የተከፈለ ገንዘብ ካለም የማይመለስ መሆኑ ናቸው፡፡ (አንቀፅ 37) ከፍ ብለን የተመለከትናቸው የምዝገባ ውጤቶች ወይም መብቶች፣ ገደቦቻቸው፤ ፈራሽነትና ውጤቱን ሲሆን የንግድ ምልክት ምዝገባ ሊታደስ፣ ሊተውና በጥቅም ላይ ባለመዋሉ ምክንያት ስለሚሰረዝበትና በዚህ መብት የመጠቀም በሙሉ ወይም በከፊል መብት በመስጠት ወይም ፈቃድ በመስጠት ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ ስለሚቻልበት ስርዓትም በህጉ (በአንቀፅ 20፣ 25፣ 34፣ 35፣ 28) ላይ በዝርዝር ተደንግገው የምናገኛቸው ናቸው፡፡ የንግድ ምልክት እንደሌሎች የአእምሮ ንብረቶች የራሱ የሆነ ፀንቶ የሚቆይበት ዘመን ያለው ሲሆን አንቀፅ 24 ይህን በማስመልከት "በዚህ አዋጅ ከአንቀፅ 35 እስከ 37 የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ የንግድ ምልክት ምዝገባ ፀንቶ የሚቆየው የምዝገባው መመልከቻ ከቀረበበት ቀን ጀምሮ ለሰባት ዓመታት ይሆናል " ሲል የሚደነግግ ሲሆን አንቀፅ 35 ጥቅም ላይ ያልዋሉ የንግድ ምክቶች ስለሚሰረዙበት ሁኔታ የሚደነግግ ህግ እንደመሆኑ መጠን አንድ የተመዘገበ የንግድ ምልክት በስራ ላይ ባልዋለበት ግዜ የግድ ፀንቶ የሚቆይበት 7 ዓመት መጠበቅ ሳያስፈልግ ሊሰረዝ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ በአንቀፅ 36 እንደዚሁ አንድ የተመዘገበ የንግድ ምልክት ፈራሽ ስለሚሆንበት ሁኔታ የሚደነግግ በመሆኑ በዚህም ሁኔታ ፀንቶ የሚቆይበትን 7 ዓመት መጠበቅ አስፈላጊ ያለመሆኑን ይገልፃል፡፡ አንቀፅ 37 ስለፈራሽነት ውጤት የሚደነግግ በመሆኑ የንግድ ምልክቱ ፀንቶ ባይቀጥልም በመፍረሱ ምክንያት የሚኖረው ውጤት ወደ ኃላ ተመልሶ እንዳልተመዘገበ እንደሚቆጠርና በምዝገባው ምክንያት የተከፈለው ገንዘብ የማይመለስ ስለመሆኑ የሚደነግግ በመሆኑ የአንቀፅ 24 ሐሳብ ፀንቶ የሚቆየው ለሰባት ዓመታት ቢሆንም በመሀል ግን የንግድ ምልክቱ ምዝገባ ሊሰረዝ፣ ፈራሽ ሊሆንና የፈራሽነት ውጤት ሊኖው እንደሚችል የሚደነግግ ነው፡፡
የንግድ ምልክት ምዝገባን በማስመልከት መዝጋቢው ፅ/ቤት በሰጠው ውሳኔ ያልተስማማ ወገን በይግባይ ስልጣን ወዳለው ፍ/ቤት መሄድ ይችላል:: ስለዚህ የንግድ ምልክት ባለቤትነት መብት በሶስተኛ ወገኖች ለሚደርስ ጥሰት የፍታብሄር መፍትሄ (civil remedies) እና የወንጀል ቅጣት (criminal sanctions) በማስከተል የፍታብሄርና የወንጀል ተጠያቂነት እንዲኖር በማድረግ ህግ ከፍተኛ የአእምሮ ንብረት መብት ጥበቃ የሚያደርግለት መብት ነው፡፡(አንቀፅ 17፣ 40 እና 41)
እስከ አሁን ያየናቸውን አጠር ባለ መንገድ ለማስቀመጥ የንግድ ምልክት እንደሁሉም የአእምሮ ንብረቶች ከምዝገባ በኃላ የሚገኝ የግዙፍነት የሌለው የንብረት መብት ሆኖ በሂደት ሊሰረዝ፣ ፈራሽ ሊሆን፣ ሊተውና ሊታደስ የሚችል መብትና ግዴታ ያለበት በመጨረሻም ከ7 ዓመት በኃላ ካልታደሰ መብቱ ቀሪ የሚሆንና ህግ የፍታብሄርና የወንጀል ጥሰት እንዳይገጥመው በፍትህ ስርዓቱ ከፍተኛ የሆነ ጥበቃ ተሰጥቶት የአገር ኢኮኖሚ ጤናማ በሆነ የግብይት ስርዓት ላይ እንዲመሰረትና የሸማቶችን መብት ከማሳከር (confusion) ነፃ በሆነ መንገድ በነፃ ፍላጐት ላይ የተመሰረተ የዕቃ ወይም የአገልግሎት ምርጫ እንዲካሄድ የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት ለኢኮኖሚ ልማቱ ስኬት የግብይት ስርዓቱ የነፃ ገበያ መርህን ተከትሎ እንዲሄድ የማድረግ አለማና ግብ ያለው ነው፡፡
የመብት ጥሰት መፍትሄዎች (Remedies)
የንግድ ምልክትን መሰረት በማድረግ ክርክር በሚነሳበት ጊዜ ፍ/ቤት እና የጉምሩክ ባለስልጣን ጊዜያዊ መፍትሄዎች ሊሰጡ እንደሚችሉና ዘላቂ መፍትሄም በፍ/ቤት ሊሰጥ እንደሚችል ይኸውም የፍ/ብሄር እና የወንጀል መፍትሔ ብሎ ማስተናገድ እንደሚቻል አዋጁ በግልፅ ይደነግጋል፡፡
የፍ/ብሄር መፍትሔ
በዚህ አዋጅ መሰረት በጊዜያዊ የፍ/ብሄር መፍትሔነት የሚወስዱት ጊዜያዊ እርምጃዎች ጉዳዩ እልባት እስኪያገኝ ድረስ የሚሰጥ ጊዜያዊ እግድ (interim injuction) ሲሆን ይኸውም አዋጁ በአንቀፅ 39(4) (ሀ)ላይ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ155 (1) ከተደነገገው በተሻለና ግልፅ በሆነ መንገድ እግድ ለመስጠት አደጋ ላይ የወደቀው ጥቅም በካሳ ሊሸፍን የማይችል ሲሆን፣ አደጋው የማይቀር መሆኑ ሲረጋገጥ፣ የክሱን ጥንካሬና ውሳኔ መስጠት በእያንዳንዱ ተከራካሪ ወገን ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በመመርመር እግድን መስጠት እንደሚቻል የሚደነግግ በመሆኑ በፍ/ቤት ስልጣን ላይ ልጓም ያበጀ ነው፡፡
የሁለቱ ተከራከሪዎች አቋም ተመሳሳይ በሚሆንበት ጊዜም ፍ/ቤት ጠለቅ ያለ ምርመራ (deep investigation) ማካሄድ እንዳለበት አዋጁ በአንቀፅ 39 (4) (ሐ) ላይ ግዴታ የሚጥል በመሆኑ በዚሁ አዋጅ የሚሰጥ እግድ ስለተጠየቀ ብቻ የሚሰጥ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
የንግድ ምልክት ክርክር በሚኖርበት ጊዜ ሌላው ሊወሰድ የሚችል መፍትሔ ንብረቱ ዋስትና ተደርጐለት ለ1ዐ ቀናት በጉምሩክ ተይዞ እንዲቆይ ማድረግ ሲሆን ከሳሽ ወይም መብቴ ተጣሰ በማለት አቤቱታውን ለጉምሩክ ባለስልጣን ያመለከተ ሰው በዚያ 10 ቀን ውስጥ ከፍ/ቤት ትዕዛዝ ካላመጣ በዋስትና የተያዘው ገንዘብ ገቢ ሆኖ ንብረቱ ለሌላው ወገን ይመለስለታል:: (አንቀፅ 42(1)) የዚህ ህግ ፋይዳም ባለመብቱ የእፎይታ ጊዜ(breathing time) አግኝቶ ጉዳዮን ወደ ፍርድ ቤት እንዲያቀርብና መመዘኛዎቹን አሟልቶ ከተገኘ ከፍ/ቤት የእግድ ትዕዛዝ በማውጣት በመብቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ጊዜ መስጠት ነው፡፡ ሌላው በአዋጁ ያለ ጊዜያዊ መፍትሔ ፍ/ቤት ከንግድ ምልክት ጋር በተያያዘ ምክንያት አንደኛው ወገን መብቴ ተጥሷል በማለት ያመለከተ እንደሆነ በአንቀፅ 39(1) (ለ) እና 39(5) መሰረት ለክርክር መነሻ የሆነው ንብረት በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 161(1) (ሀ) እና በወ/ሰ/ሰ/ህ/ቁ32 መሰረት እንዲበረብርና እንዲያዝ እንዲሁም እንዲታሰር ወይም እንዲታቀብ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ለፍ/ቤቱ ስልጣን የሚሰጥ በመሆኑ አንድ የንግድ ምልክት ባለቤት መብቱ እንዲሁ እንዳይጣስ የህግ ከለላ የሚሰጠውና በዘላቂነትም በፍ/ቤት ውሳኔ መብቱን እንዲያስከብር የሚያስችል ነው፡፡ እስካሁን ያየናቸው አንድ የንግድ ምልክት ባለቤት መብቴ ተጥሷል ባለበት ጊዜ ስለሚያቀርበው ክስና ጊዜያዊ መፍትሔ:: ቀጥለን ስለሚኖሩት ዘላቂ መፍትሔዎች (Final Remedies) እናያለን፡፡
አንዱ መፍትሔ በፍ/ ቤት ከሶ ለደረሰበት ጉዳት ካሳ እንዲያገኝ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው የንግድ ምልክት ባለቤቱን መብት መጣሱ ከታወቀ በዚያ ጊዜ ውስጥ ያገኘውን ትርፍ( Account of Profit) እንዲመለስ ማድረግ ሲሆን የዚህ ዓይነቱ መፍትሔ በአፈፃፀም ላይ አንድ ህገ ወጥ ስራን የሚሰራ ሰው የንግድ ሒሳብ ደብተር ይይዛል ተብሎ ስለማይገመት ስሌቱ ለማወቅ አስቸጋሪ የሆነ የመፍትሔ አገባበ ነው፡፡ ገንዘባዊ ጥቅም ካላቸው መፍትሔ በተጨማሪ ፍ/ቤት የእንዲታወቅ ፍርድ (declaratory judgment) በመስጠት የንግድ ምልክት መብት በሶስተኛ ወገኖች እንዳይጣስ ሊያደርግ ይችላል፡፡ አዋጁ በፍ/ብሄር መፍትሔነት ያስቀመጣቸው እግድ (injuction) እና ካሳ (compensation) ሲሆኑ በአንቀፅ 40(2) ያለው የካሳ አከፋፈል ስርዓት በፍ/ብ/ህ/ቁ 2091 ከተደነገገው ጉዳት ካሳ = የጉዳት መጠን ከሚለው መርህ ማፈንገጥ (deviation) የሚስተዋልበት ነው፡፡ ይኸውም የንግድ ምልክት መጣስን ተከትሎ የሚመጣ የካሳ አከፋፈል ስርዓት መሰረቱ ጉዳት (damage) መሆኑ ቀርቶ መብት ጥሷል የተባለው ሰው መጣሱ ከተረጋገጠ በዚያ ንግድ ምልክት ጥሶ በመነገድ ያገኘውን የተጣራ ትርፍ በሙሉ እንዲከፍል በማድረግ ወይም ፈቃድ ተሰጥቶት ቢነግድ ይከፈል ከነበረው ኪራይ(royalty) የሚበልጥ እንዲከፍል በማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም ስሌቱ “Compensation equals to damage” መሆኑ ቀርቶ የዚህ አዋጅ መርህ ለየት ባለ መንገድ ስለቱ “Compensation equal to net Profit or royalty +” ነው፡፡ በመሆኑም የንግድ ምልክት አዋጅ ቁጥር 501/98 የሚከተለው የካሳ አከፋፈል ክልሰ ሓሳብ (theory) ያለአግባብ መበልፀግን the theory of unlawful enrichment ክልስ ሐሳብ ሲሆን የፍ/ብሄር ህጉ የሚከተለው የጉዳት ካሳ አከፋፈል the theory of damages ክልስ ሓሳብን የተከተለ ነው::
ከዚህ በተጨማሪ አዋጁ በአንቀፅ 40(1) ላይ ልክ በፍ/ብሄር ህጉ አንቀፅ 2121 ላይ እንደተደነገገው ዘላቂ እግድ (permanent injuction) ሊሰጥ ስለሚችልበት ሁኔታ “ ተከሳሹ የመብት መጣስን ድርጊት እንዲያቆም ሊወሰን ይችላል በማለት ስለሚደነግግ ለባለ መብቱ ከፍተኛ የአእምሮ ንብረት መብት ጥበቃ የሚሰጥ ነው፡፡
የፍ/ብሄር መፍትሔን በማስመልከት ስለሚኖሩ ጥሰቶችና መፍትሄዎቻቸው እንደተገለፀው ሆኖ የንግድ ምልክት ባለቤቱን መልካም ስምና ዝናን (reputation of honor) እንዲመለሰልት ፍ/ቤት ፍ/ብ/ህ/ቁ 2120 እና ን/ህ/ቁ/134(2) (ሀ) በሚያዙት መሰረት በማስታወቂያ እንዲወጣና ህዝቡ እንዲያውቀው እንዲደረግ ለማዘዝ ስለሚችል የንግድ ምልክቱ ባለቤት በዚህ ራሱን መልሶ ወደ ገበያው በማስገባት ለበለጠ ጥቅም ሊሰራ የሚያስችለውን ሁኔታ እንዲመቻችለት ያደርጋል፡፡
የወንጀል ቅጣት
በመጨረሻም አዋጁ የንግድ ምልክት ጥሰትን መሰረት በማድረግ የፍ/ብሄር መፍትሄዎች እንደሚደነገግ ሁሉ በአንቀፅ 41 ላይ ወንጀልን በማስመልከት የንግድ ምልክት መብት ጥሷልተብሎ የተጠረጠረው ሰው ድርጊቱ መፈፀሙ ሲረጋገጥ በወ/ህ/ቁ 720 መሰረት ሆነ ብሎ የጣሰ ከሆነ ከ5 ዓመት በማያንስና ከ15 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡ ድርጊቱን የፈፀመው በቸልተኛነት ከሆነም ከአንድ ዓመት በማያንስና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡ አንዲሁም ወንጀሉን ለመፈፀም ያገለገሉ ቁሳቁሶችና መሳሪያዎችና መብት የተጣሰባቸውን ዕቃዎች መያዝ፣ መውረስና እና ማስወገድን ያጠቃልላል ሲል ይደነግጋል፡፡ ይህ የሚያሳየው የንግድ ምልክት መጣስ የቱን ያህል እንደሚያስቀጣ ብቻ ሳይሆን ህጉ ህዝቡ በህጋዊ የንግድ ምልክት ባልተጠቀሙ ግለሰቦች እንዳይታለልና ያልሆነ ዕቃ ወይም አገልግሎት በመግዛት ሊደርስበት ከሚችል ጉዳት ለመጠበቅ የቱን ያህል ክብደት እንደሰጠ ነው:: ከዚህ ህግ በስተጀርባ ያለው ህዝባዊ ፖሊስ ስግብግብ ነጋዴዎችን ከድርጊታቻው እንዲታቀቡ በማድረግ ህ/ሰቡን የነፃና ፍትሐዊ ግብይት ስርዓት ተጠቃሚ ማድረግም ጭምር ነው::