- Details
- Category: Property Law
የካሳ አከፋፈል ስርዓት
ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ከይዞታው የሚለቅ ሰው በቅድሚያ ተመጣጣኝ ካሳ የማግኘት መብት ሕገ- መንግስታዊ መብት ነው፡፡ የዚህን የህገ-መንግስቱ አንቀጽ 40(8) መርህ ተግባራዊ ለማድረግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 455/97 በአንቀጽ 7 ላይ የካሳ መሰረትና መጠን በሚል ርእስ ስርና በአንቀጽ 8 ላይ የማፈናቀያ ካሳ በሚል ስር ሁለት ዓይነት የካሳ ክፍያዎች እንዳሉ በሚገልጽ መልኩ ተደንግጓል፡፡
እነዚህን ሁለት ድንጋጌዎች ለየብቻ ማየት ኢትዮጵያ የምትከተለውን የካሳ አከፋፈል ስርዓት በግልፅ ለመረዳት ስለሚያስችል በሚከተለው መንገድ ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡
በአንቀፅ 7 መሰረት የካሳ መሰረት ሆኖ የሚወሰደው እንዲለቅ በሚመለከተው አካል የተወሰነበት ባለይዞታ በመሬቱ ላይ ለሚገኘው ንብረት እና በመሬቱ ላይ ላደረገው ቋሚ ማሻሻል የሚከፈል ካሳ ነው፡፡ በሚለቀቀው የመሬት ይዞታ ለሚገኝ ንብረት የሚከፈል ካሳ ንብረቱን ባለበት ሁኔታ ለመተካት የሚያስችል ሲሆን በመሬት ላይ ለተደረገ ቋሚ መሻሻል የሚከፈለው ካሳ መሰረቱ በመሬቱ ላይ የዋለው ገንዘብና የጉልበት ዋጋ የሚተካ የካሳ መጠን ነው፡፡ እንዲለቅ እየተደረገ ያለው ንብረት መልሶ በመትከል አገልግሎት ለመስጠት የሚችል በሚሆንበት ግዜ ከፍ ብለው ከተጠቀሱት ንብረቱን ባለበት ሁኔታ የሚተካ ካሳና በመሬቱ ለተደረገ ቋሚ መሻሻል የወጣ ገንዘብንና የጉልበት ዋጋ በካሳ መልክ ከሚከፈለው በተጨማሪ የንብረቱ ማንሻ፣ የማጓጓዣና መልሶ ለመትከል የሚጠይቀውን ወጪ እንዲሸፍን የሚከፈለው ካሳ ነው፡፡ ይህም ማለት ለሁሉም ሰው ከይዞታው በመልቀቁ ምክንያት በመሬቱ ለሚገኝ ንብረት ካሳ የማግኘት መብት ያለው ሲሆን ለተደረገ ቋሚ መሻሻልና መልሶ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የሚከፈል ካሳ ግን እንደየ ሁኔታውና የንብረቱ ዓይነት እየታየ የሚከፈል ካሳ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የመጀመሪያው የካሳ ዓይነት አንድ ሰው ባለይዞታ ከሆነበት መሬት በመልቀቁ ምክንያት ከዚያ መሬት ያገኝ የነበረውን ጥቅም የማግኘት መብት ስላለው ለሁሉም የሚሰጥ ሲሆን ሌሎቹ ግን አንድ ሰው በመሬቱ ያደረገው ቋሚ መሻሻል ከሌለ በዚህ መልኩ የሚገለፅ የሚያገኘው ካሳ አይኖርም ማለት ነው፡፡ እንደዚሁም እንዲለቅ የተደረገው የአገልግሎት መስጫ መልሶ በመትከል እንደገና አገልግሎት መስጠት የማይችል ከሆነ በመጀመሪያው የካሳ ስሌት ማለትም ንብረቱ አሁን ባለበት ሁኔታ ለመተካት የሚያስችል ካሳና ያደረገው ቋሚ ማሻሻ ካለ የነዚህ ካሳ ይሰጠዋል እንጂ የማንሻ የማጓጓዣና መልሶ መትከያ የሚወጣ ወጪ ስለማይኖር በዚህ መልኩ የሚከፈለው ካሳ አይኖርም ማለት ነው፡፡
የገጠር መሬት የካሳ አከፋፈል
በአዋጁ አንቀጽ 8 መሰረት የሚከፈል የማፈናቀያ ካሳ ከፍ ብለን አንቀጽ 7 መሰረት በማድረግ እያየናቸው ከመጣን የካሳ አከፋፈሎችና (modes of compensation) የካሳ መሰረቶች (Bases of Compensation) በተጨማሪ አንድ ሰው ከይዞታው በመፈናቀሉ ብቻ የሚከፈል የሁሉም ባለይዞታዎች መብት ነው፡፡ አፈፃፀሙን ማለትም የካሳ አከፋፈል ስሌቱንና ለማፈናቀያ ካሳ መሰረት የሚሆነውን መሰረት በማድረግ የተለያየ አካሄድን የሚከተል ሲሆን ዝርዝሩም እንደሚከተለው ነው:: በቋሚነት እንዲለቀቅ የሚደረገው የገጠር መሬት ባለይዞታ ሲሆን እንዲለቅ ከመደረጉ በፊት በነበሩት አምስት ዓመታት የነበረውን ገቢ በአስር ተባዝቶና በአዋጁ አንቀጽ 7 ማግኘት የሚገባው ካሳ ታክሎበት ካሳ ይከፈለዋል፡፡ በአጭሩ የካሳው አከፋፈል ቀመር :-
- ቋሚ የማፈናቀያ ካሳ = ባለፈው 5 ዓመት ያገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ x በ10 + ንብረቱ ባለበት ሁኔታ መተክያ ወይም
- ቋሚ የማፈናቀያ ካሳ = ባለፈው 5 ዓመት ያገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ x በ10 + ንብረቱ ባለበት ሁኔታ መተክያ + የቋሚ ማሻሻያ ገንዘብና የጉልበት ዋጋ ወይም
- ቋሚ የማፈናቀያ ካሳ = ባለፈው 5 ዓመት ያገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ x በ10 + ንብረቱ ባለበት ሁኔታ መተክያ + የቋሚ ማሻሻያ ገንዘብና የጉልበት ዋጋ + የንብረቱ ማንሻ፣ ማጓጓዣና መልሶ መትከያ ወጪ የካሳ አከፋፈል ቀመርን የሚከተል ነው፡፡
ለተወሰነ ጊዜ ከገጠር መሬት ይዞታው ለሚለቅ ባለይዞታ ወይም ለወል መሬት ባለይዞታዎች (Holders of Common land) እንዲለቁ ከመደረጉ በፊት በነበሩት አምስት ዓመታት ያገኙት አማካይ ዓመታዊ ገቢ መሬቱ እስኪመለስ ባለው ግዜ ታስቦ በአንቀጽ 7 የሚከፈለው ካሳ ተጨምሮበት የመፈናቀያ ካሳ ይከፈላቸዋል፡፡ ይህም ማለት፡-
- የተወሰነ ጊዜ ማፈናቀያ ካሳ = ባለፈው 5 ዓመት ያገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ ተፈናቅሎ የሚቆይበት ዓመት + ንብረቱ ባለበት ሁኔታ መተክያ ወይም
- የተወሰነ ጊዜ ማፈናቀያ ካሳ = ባለፈው 5 ዓመት ያገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ x ተፈናቅሎ የሚቆይበት ዓመት + ንብረቱ ባለበት ሁኔታ መተክያ + የቋሚ ማሻሻያ ገንዘብና የጉልበት ዋጋ ወይም
- = x ተፈናቅሎ የሚቆይበት ዓመት + ንብረቱ ባለበት ሁኔታ መተክያ + የቋሚ ማሻሻያ ገንዘብና የጉልበት ዋጋ + የንብረቱ ማንሻ ሟጓጓዣና መትኪያ እንደ ስሌት የሚጠቀም ሲሆን ህጉ ለተወሰነ ጊዜ የሚደረግ ከይዞታ መልቀቅን በተመለከተ ለቋሚ መልቀቅ ከተከተለው ስሌት ጋር ሲታይ ከተወሰነ የብዜት መሰረት (base) ለውጥ ውጨ ሌላ ልዩነት የሌለው ቢመስልም በአንቀፅ 8(2) መጨረሻ ላይ በአንቀፅ 8(1) ያልተጠቀመበትን “… ሆኖም ይህ ክፍያ በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ (1) መሰረት ከሚከፈለው ካሳ መብለጥ የለበትም፡፡” ሲል የካሳ ክፍያውን ጣርያ ገድቦታል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለውም ለተወሰነ ጊዜ የሚደረግ መልቀቅ በአንቀፅ 8(1) ለካሳው ብዜት መሰረት ከሆነም 10 ዓመት ለሚበለጥ ጊዜ በጊዚያዊነት ከይዞታው ለቆ መቆየት እንደሌለበት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ከመሬቱ ለቆ የሚቆይበት ጊዜ ከ10 ዓመት በላይ ከሆነ ለተወሰነ ጊዜ ከገጠር መሬት ይዞታ መልቀቅ መሆኑ ቀርቆ እንደ ቋሚ ከገጠር መሬት ይዞታ መልቀቅ ይቆጠራና የካሳ አከፋፈሉም በቋሚ መልቀቅ አከፋፈል ስርዓትን የተከተለ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ህጉ ከፍ ብለን እያየናቸው ከመጣን የካሳ አከፋፈል ስሌቶች በተጨማሪ አንድ ሰው ካለው የገጠር መሬት ይዞታ ለህዝብ ጥቅም ሲባል እንዲለቅ በሚደረግበት ጊዜ ሌላ አማራጭ የካሳ አከፋፈል ስርዓትን በአንቀፅ 8(3) ይደነግጋል:: ይሄውም ተመጣጣኝ ገቢ የሚያስገኝና በቀላሉ ሊታረስና ምርት ሊያስገኝ የሚችል ተተኪ መሬት እና መሬቱ እንዲለቅ ከመደረጉ በፊት በነበሩት 5 ዓመታት ያገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢውን ያህል በካሳነት ይከፈለዋል ይላል፡፡
ስለዚህ ህጉ የገጠር መሬት ይዞታን ለህዝብ ጥቅም ሲባል ማስለቀቅንና የካሳ አከፋፈሉን በተመለከተ በቋሚነት ለሚለቅ በመሬት ላይ ለሚገኘው ንብረት የተደረገ ቋሚ መሻሻል ካለ ለዚህ የተደረገን ወጪና እንደየ ሁኔታው የንብረት ማንሻ፣ ማጓጓዣና መልሶ መትክያ ወጪን የሚሸፍን ካሳና ከዚህ በተጨማሪ እንደየ ሁኔታው የሚከፈል የመፈናቀያ ካሳን የመክፈል ስርዓትን (compensation schem) የያዘ ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም ቋሚ መልቀቅንና ለተወሰነ ጊዜ መልቀቅን መሰረት በማድረግ የተለያየ የማፈናቀያ ካሳ አከፋፈል ስርዓትን የሚከተልና ተተኪና የሚመጥን መሬት ባለበት ሁኔታም ለየት ያለ የካሳ አከፋፈል ስርዓት የሚከተል ህግ ነው፡፡
የከተማ ቦታ ካሳ አከፋፈል
እንደሚታወቀው በአገራችን የከተማ ቦታን በሊዝና ከሊዝ ውጭ ባሉ የከተማ ቦታ ይዞታ የማግኛ መንገዶች እንደ በግል የከተማ ቦታ ምሪትና የቆየ የከተማ ቦታ ይዞታ ወዘተ ባሉ የባለይዞታነት መብት ማግኘት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው ህጉ በአንቀፅ 7(3) ላይ እንዲለቅ የተደረገው ባለይዞታ የከተማ ነዋሪ በሚሆንበት ጊዜ የሚሰጠው ካሳ ክልሎች በሚያወጡት ስታንዳርድ የሚወሰን ቢሆንም አንድ የቁጠባ ክፍል ሊያሰራ ከሚችል የገንዘብ መጠን ግን ማነስ እንደሌለበት የሚደነግገው፡፡ አንቀፅ 8(4) ይህን ሀሳብ በማጠናከር “በዚህ አዋጅ መሰረት የመሬት ይዞታው እንዲለቅ ለተደረገ የከተማ ነዋሪ ለንብረቱ ከሚከፈለው ካሳ በተጨማሪ ማለትም ንብረቱን ባለበት ሁኔታ ለመተካት የሚያሰችል ካሳ ከሚከፈለው በተጨማሪ መጠኑ በከተማው አስተዳደር የሚወሰን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ምትክ የከተማ መሬት ይሰጠዋል፡፡ እንዲሁም የፈረሰው የመኖሪያ ቤት የአንድ ዓመት ኪራዩ ግምት ተሰልቶ የመፈናቀያ ካሳ ይከፈለዋል ወይም የከተማው አስተዳደር ንብረት የሆነ ተመጣጣኝ ቤት ለአንድ ዓመት ያለ ኪራይ ክፍያ እንዲኖርበት ይደረጋል፡፡ “ ሲል ይደነግጋል
ስለዚህ ከሊዝ ውጪ በሆነ መንገድ የከተማ ቦታ ባለይዞታ የሆኑ ሰዎች ለህዝብ ጥቅም ሲባል እንዲለቁ በሚደረጉበት ጊዜ የሚኖረው የካሳ አከፋፈል ስርዓት የከተማ ነዋሪ የይዞታ ማስለቀቅያ ካሳ ንብረቱን ባለበት ሁኔታ የሚተካ ካሳ + ምትክ የከተማ መሬት + የአንድ ዓመት ኪራይ የመፈናቀያ ካሳ ወይም ያለኪራይ ክፍያ የአንድ ዓመት በመንግስት ቤት መገልገል ይሆናል፡፡ ይህ መብት ለመንግስት መስሪያ ቤትም ተፈፃሚነት ያለው የካሳ አከፋፈል ነው፡፡
ለህዝብ ጥቅም ሲባል ከይዞታው የሚለቅ የሊዝ ባለይዞታን በሚመለከት ህጉ ለየት ባለ ሁኔታ በአንቀፅ 8(6) እስካሁን እያየነው የመጣነውን በአንቀፅ 7 እና 8 ያለው የማስለቀቅያ ካሳ አከፋፈል ስርዓት እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ በተጨማሪ ለቀሪው የሊዝ ዘመን የሚጠቀምበት ተመጣጣኝ የመሬት ኪራይ ከመጀመሪያው የመሬት ኪራይ ያነሰ በሚሆንበት ጊዜም በመሬቱ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲጠቀምበት በማድረግ ያካካስለታል፡፡ ሌላው አማራጭም የሊዝ ባለይዞታው በምትክነት የተሰጠውን መሬት መረከብ ካልፈለገ የቀረው የሊዝ ዘመን ኪራይ ተሰልቶ እንዲመለስለት በማድረግ የሊዝ ግንኙነቱ እንዲቋረጥ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የአንድ በሊዝ የከተማ ቦታ ባለይዞታ የሆነ ሰው ከይዞታው እንዲለቅ በሚወሰንበት ጊዜ ከይዞታው የመልቀቅያ ካሳ አከፋፈል ሰርዓት በአጭሩ ያየን እንደሆነ:-
የከተማ ሊዝ ይዞታ መልቀቅያ ካሳ = የአዋጁ አንቀፅ 7 እና 8 የሚያስገኙት የካሳ መብት + ለቀሪ ዘመን የሚጠቀምበት ምትክ መሬት መስጠት ሲሆን ሌሎቹ የአፈፃፀም ስርዓቶች እንደየ ሁኔታው የሚፈፀሙ ስሌቶች ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡
ስለዚህ በአገራችን ያለውን የመሬት ይዞታ ለህዝበ ጥቅም ሲባል ማስለቀቅያ ህግ የገጠር መሬትና የከተማ መኖሪያና የሊዝ ኪራይ ባለይዞታነትን መስረት በማደረግ ንብረቱን ባለበት ሁኔታ የመተካት አሰራርን እንደ መሰረታዊ ለሁሉም ከይዞታቸው እንዲለቁ የተወሰነባቸው ሰዎች የንብረት ካሳ ማስግኛ መብት በመውሰድ ሌሎች ተጨማሪ ክፍያዎች እንደየ ሁኔታው የሚወሰኑ በርካታ የካሳ አከፋፈል ስርዓቶችን (Compensation Schems) ያካተተ ህግ ነው፡፡ ይህም በደንብ ቁጥር 135/1999 ላይ በዝርዝር የምናገኘው ነው::
ከደንብ ቁጥር 135/99 አንፃር
ከፍ ብለን እንዳየነው የመፈናቀያ ካሳ አተማመንና ቀመር በደንቡ ላይ በዝርዝር የተደነገገ ስለሆነ የደንቡን ይዘት በሚከተለው መልኩ ለማካተት ተሞክሯል::
የካሳ አተማመን
ሀ. የቤት ካሳ አተማመን
1. የቤት ካሳ የሚሰላው ተመጣጣኝ ደረጃ ያለውን ቤት ለመስራት የሚየስፈልገውን የወቅቱን የካሬ ሜትር ወይም የነጠላ ዋጋ በማውጣት ይሆናል፡፡
2. የቤት ካሳ ተመን
2.1 ከቤቱ ጋር ተያያዥነት የላቸውን የግቢ ንጣፍ፣ ሴፕቲክ ታነክና ሌሎች ስትራክቸሮች ለመስራት የሚያሰፈልገውን የወቅቱን ዋጋ እና
2.2 ቤቱ በመነሳቱ ምክንያት የተገነቡ የአገልግሎት መስመሮችን ለማፍረስ ለማንሳት መልሶ ለመገንባት፣ ለመትከልና ለማገናኘት የሚያስፈልጉትን ወጭዎች ግምት ይጨምራል::
3. ቤቱ የሚፈርሰው በከፊል ሲሆን የቤቱ ባለቤት ቦታውን ለመልቀቅ ከመረጠ ለቤቱ ካሳ
የማግኘት መብት አለው፡፡
4.ቤቱ የሚፈርሰው በከፊል ሲሆንና የቤቱ ባለቤት በቀሪው ቦታ ላይ ለመቆየት ከመረጠ ለፈረሰው የቤት አካል ብቻ ተሰልቶ ካሳ ይከፈለዋል፡፡ ሆኖም የቤቱ ባለቤት በቀሪው የቤቱ አካል የመቆየት ምርጫ አግባብ ባለው የከተማው ፕላን ተቀባይነት ያለው መሆን አለበት፡፡
ለ.የአጥር ካሳ አተማመን
የአጥር ካሳ የሚሰላው ከሚፈርሰው አጥር ጋር በዓይነቱ ተመጣጣኝ የሆነ አጥር ለመስራት የሚያሰፈልገውን የወቅቱን የካሬ ሜትር ወይም የነጠላ ዋጋ በማውጣት ይሆናል፡፡
ሐ. የሰብል ካሳ አተማመን
1. የሰብል ካሳ የሚሰላው ሰብሉ ለመሰብሰብ ደርሶ ቢሆን ኖሮ ሊሰጥ የሚችለውን ምርት መጠንና ምርቱ ሊያወጣ ይችል የነበረውን የአካባቢውን የወቅቱ የገበያ ዋጋ መሰረት በማድረግ ይሆናል፡፡
2. ሰብሉ ለመሰብሰብ የደረሰ ከሆነ ባለንብረቱ በካሳ ክፍያ ፋንታ በአዋጁ አንቀጽ 4 መሰረት በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማለትም በ90 ቀን ውስጥ ሰብሉን ሰብስቦ መውሰድ ይችላል፡፡
መ. የቋሚ ተክል ካሳ አተማመን
1. የቋሚ ተክል ካሳ የሚሰላው ተክሉ ፍሬ መስጠት ያልጀመረ ሲሆን ተክሉ በሚገኝበት ደረጃ ለማድረስ የሚያስፈልገውን ወጪ ግምት በማስላት ይሆናል፡፡
2. ቋሚ ተክሉ ፍሬ ለመስጠት የጀመረ ከሆነ ካሳው የሚሰላው ተክሉ በአንድ ዓመት የሚያስገኘውን ምርት በወቅቱ የአካባቢውን የገበያ ዋጋ በማባዛት እንዲሁም የመሬት ቋሚ ማሻሻያ ወጪን በመደመር ይሆናል፡፡
የዛፍ ካሳ አተማመን
1. የዛፍ ካሳ የሚሰላው በዛፋ የዕድገት ደረጃ ላይ ተመስርቶ የወቅቱን የነጠላ ወይም የካሬ ሜትር ዋጋ በማውጣት ይሆናል፡፡
2. ባለንብረቱ በካሳ ክፍያ ፋንታ በአዋጁ አንቀጽ 4 መሠረት በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማለትም በ90 ቀናት ውስጥ ዛፋን ከመሬቱ አንስቶ መውሰድ ይችላል፡፡
ረ. የጥብቅ ሳር ካሣ አተማመን
- የጥብቅ ሳር ካሳ የሚሰላው የመሬቱን የሳር ምርታማነትና የሳሩን የወቅቱን የካሬ ሜትር የገበያ ዋጋ መሠረት በማድረግ ይሆናል፡፡
- ባለንብረቱ በካሳ ክፍያ ፋንታ በአዋጁ አንቀጽ 4. መሠረት በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማለትም በ90 ቀናት ሳሩን ከመሬቱ ላይ አንስቶ መውሰድ ይችላል፡፡
ሸ. በገጠር መሬት ላይ የተደረገ ቋሚ ማሻሻያ አተማመን
በገጠር መሬት ላይ ለተደረገ ቋሚ ማሻሻያ ካሳ የሚተመነው ለምንጣሮ፣ ለድልደላና እርከን ለመስራት እንዲሁም ውኃ ለመከተርና ለሌሎች የግብርና መሰረተ ልማት የወጡትን የመሳሪያ፣ የጉልበትና የዕቃዎች የወቅቱ ዋጋ በማስላት ይሆናል፡፡
ቀ. ተዛውሮ የሚተከል ንብረት ካሳ አተማመን
ተዛውሮ ለሚተከል ንብረት የሚከፈለው ካሳ ለንብረቱ ማንሻ፣ ማዛወርያና መልሶ መትከያ የሚያስፈልጉ የባለሙያ፣ የማቴሪያልና የማጓጓዣ ወጭዎችን ግምት በወቅቱ የገበያ ዋጋ መሠረት በማስላት ይሆናል፡፡
በ . ለማዕድን ባለፈቃድ ስለሚከፈል ካሳ አተማመን
ለማዕድን ስራ በማዕድን ባለፈቃድ የተያዘ መሬት በአዋጁ መሠረት የሚለቀቅ ሲሆን የሚከፈለው ካሳ አግባብ ባለው የማዕድን ህግ መሠረት የሚፈፀም ይሆናል፡፡
ተ. ለመካነ መቃብር ስለሚከፈል ካሳ
1. ለመካነ መቃብር ስለሚከፈል ካሳ መካነ መቃብሩን ለማንሳት፣ ተለዋጭ ማረፊያ ቦታ ለማዘጋጀት፣ አፅሙን ለማዘዋወርና ለማሳረፍ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለሚደረግ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓት ማስፈጸሚያ የሚያስፈልጉት ወጪዎች ያጠቃልላል፡፡
2. ከፍ ብለው በተራ ቁጥር 1 የተጠቀሱት ወጪዎች የአካባቢውን የዕቃ፣ የትራንስፖርት አገልግሎትና የጉልበት የወቅቱን የገበያ ዋጋ መሠረት በማድረግ ይሰላሉ፡፡
የካሳ ስሌት ቀመር
በአዋጁና በዚህ ደንብ መሠረት የሚከፈል የንብረት ካሳ መጠን የሚሰላበት ቀመር እንደሚከተለው ይሆናል፣
1. የቤት ካሳ = የግንባታ ወጭ (በወቅቱ ዋጋ)
+ የመሬት ቋሚ ማሻሻያ ወጪ
+ የቀሪ ዘመን የመሬት ሊዝ ተመላሽ ክፍያ
2. የሰብል ካሳ = የቦታው ስፋት (በካሬ ሜትር)
x የሰብል የገበያ ዋጋ በኪሎ ግራም
x በአንድ ካሬ ሜትር ስፋት ላይ የሚገኝ ምርት በኪሎ ግራም
+ የመሬት ቋሚ ማሻሻያ ወጪ
3. ፍሬ መስጠት ያልጀመረ ቋሚ ተክል ካሳ = የተክል ብዛት (በእግር)
x በአንድ እግር የወጣ ወጪ ግምት
+ የመሬት ቋሚ ማሻሻያ ወጪ
4. ፍሬ መስጠት የጀመረ ቋሚ ተክል ካሳ = ተክሉ በአንድ ዓመት የሚያስገኘው ምርት
ብዛት (በኪሎ ግራም)
x የቋሚ ተክሉ ምርት የወቅቱ የገበያ ዋጋ
+ የመሬት ቋሚ ማሻሻያ ወጪ
5. ተዛውሮ የሚተከል ንብረት ካሳ = የንብረቱ ማንሻ ወጪ
+ የማዛወሪያ ወጪ
+ የመልሶ መትከያ ወጪ
6. የጥብቅ ሳር ካሳ = ሳሩ የሸፈነው ቦታ በካሬ ሜትር
X የሚመረተው የሳር ምርት ወቅታዊ የገበያ ዋጋ በካሬ ሜትር ይሆናል::
ምትክ ቦታና የመፈናቀያ ካሳ
- ለከተማ ቦታ ምትክ ስለመስጠት
ለህዝብ ጥቅም ሲባል ይዞታውን እንዲለቅ ለተደረገ የከተማ ነዋሪ የሚሰጠውን ምትክ ቦታ በአዋጁ አንቀጽ 14 (2) መሰረት ክልሎች በሚያወጡት መመሪያ መሰረት ይወሰናል፡፡
- ለገጠር መሬት ምትክ ስለመስጠት
ለህዝብ ጥቅም ሲባል የሰብል፣ የጥብቅ ሳር ወይም የግጦሸ መሬት እንዲለቀቅ ሲደረግ ለተመሳሳይ አገልግሎት የሚውል ምትክ መሬት በተቻለ መጠን ይሰጣል፡፡
- ለሰብልና ቋሚ ተክል መሬት ስለሚከፈል የመፈናቀያ ካሣ
1 እንዲለቀቅ የተደረገ የሰብል ወይም የቋሚ ተክል መሬትን በተመለከተ በዚህ ደንብ አንቀጽ 15 መሠረት ምትክ መሬት የተሰጠ ከሆነ፣
ሀ. ከሰብሉ የሚገኘውን አማካይ ዓመታዊ ገቢ የሚያህል፣ ወይም
ለ. ከቋሚ ተክሉ የሚገኘውን አማካይ ዓመታዊ ገቢ ተክሉ የደረሰበት የዕድገት ደረጃ ለማድረስ በሚወስደው ዓመታት ቁጥር ተባዝቶ የሚገኘውን መጠን የሚያህል፣ የመፈናቀያ ካሣ ይከፈላል፡፡
2. እንዲለቀቅ የተደረገ የሰብል ወይም የቋሚ ተክል መሬትን በተመለከተ በዚህ ደንብ አንቀጽ 15 መሰረት ምትክ መሬት መስጠት ካልተቻለ የሚከፈለው የመፈናቀያ ካሳ ሰብሉ ወይም ተክሉ ያስገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ በ10 ተባዝቶ የሚገኘው መጠን ይሆናል፡፡
3. የሰብል ወይም የቋሚ ተክል አማካይ ዓመታዊ ገቢ የሚሰላው፣
ሀ. መሬቱ ከመለቀቁ በፊት በነበሩት አምስት አመታት በተገኘው ገቢ ላይ፣ ወይም
ለ. ሰብሉ ወይም ቋሚ ተክሉ ገቢ ያስገኘው ከአምስት ዓመት ላነሰ ጊዜ ከሆነ በነዚሁ ዓመታት በተገኘው ገቢ ላይ፣ ወይም
ሐ. ሰብሉ ወይንም ተክሉ ዓመታዊ ገቢ መስጠት ያልጀመረ ከሆነ በአካባቢው ባለው ተመሳሳይ የይዞታ መጠን ከተመሳሳይ ሰብል ወይም ቋሚ ተክል በአምስት ዓመታት በሚገኝ ገቢ ላይ፣ ተመስርቶ ይሆናል፡፡
- ለጥብቅ ሳር ወይም የግጦሽ መሬት ስለሚከፈል የመፈናቀል ካሣ
1. እንዲለቀቅ የተደረገ የጥብቅ ሳር ወይም የግጦሽ መሬትን በተመለከተ በዚህ ደንብ አንቀጽ 15 መሰረት ምትክ መሬት የተሰጠ ከሆነ፣ ከጥብቅ ሳሩ ወይም የግጦሽ መሬቱ የተገኘውን አማካይ አመታዊ ገቢ የሚያህል የመፈናቀያ ካሳ ይከፈላል፡፡
2. እንዲለቀቅ የተደረገ የጥብቅ ሳር ወይም የግጦሽ መሬትን በተመለከተ በዚህ ደንብ አንቀጽ 15 መሰረት ምትክ መሬት መስጠት ካልተቻለ የሚከፈለው የመፈናቀያ ካሳ ጥብቅ ሳሩ ወይም የግጦሸ መሬት ያስገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ በ10 ተባዝቶ የሚገኘው መጠን ይሆናል፡፡
3. የዚህ ደንብ አንቀጽ16 ንዑስ አንቀጽ 3 ድንጋጌዎች የጥብቅ ሳር ወይም የግጦሽ መሬት አማካይ ዓመታዊ ገቢን ለማሰላት በተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡
- ለተወሰነ ጊዜ ለሚለቀቅ የገጠር መሬት ስለሚከፈል የመፈናቀል ካሣ
የገጠር መሬት እንዲለቀቅ የተደረገው ለተወሰነ ጊዜ ከሆነ የመፈናቀያ ካሳው ስሌት ማባዣ መሬት እስኪመለስ ድረስ ያሉት ዓመታት ቁጥር ይሆናል፡፡ ሆኖም በዚህ መንገድ ተሰልቶ የሚገኘው ካሳ በዚህ ደንብ አንቀጽ 16 ወይም 17 መሠረት ከሚከፈለው መጠን መብለጥ የለበትም፡፡ እስካሁን ካሳ የሚከፈልበትን ስርዓትና የምንጠቀምበትን ቀመር እያየን መጥተናል ይህ ማለት ግን ሁሌ ካሳ ይከፈላል ማለት አይደለም ለምሳሌ በአዋጁ መሰረት መሬቱ የሚለቀቅ ስለመሆኑ የተሰጠው ውሳኔ ለባለይዞታው ከደረሰ በኋላ ለተሰራ ወይም ለተሻሻለ ቤት: ለተዘራ ሰብል ለተተከለ ቋሚ ተክል ወይም በመሬት ላይ ለተደረገ ቋሚ ማሻሻያ ካሳ አይከፈልም:: ስለዚህ በህገ መንግስቱ የተረጋገገጠው ቅድሚያ ካሳ የማግኘት መብት ቀጥሎ በወጣ አዋጅና ደንብ በዝርዝር እንዴት መፈፀም እንዳለበት ከፍ ብሎ ባየነው መልኩ የተደነገገ ቢሆንም ህግ ከሚፈቅደው ውጭ በመሆን ማለትም ለህዝብ ጥቅም ሲባል ከቦታው እንደሚለቅ እየተነገረው በዚህ መሬት ላይ ለሚያፈራው ንብረት ካሳ የማይከፈልበት መሆኑን ከግምት ውስጥ ማስገባት የግድ ይላል ምክንያቱም እንደዚህ ባለ ሁኔታ ለተገኘ ንብረት ካሳ መክፈል ማለት ከህግ ልእልና (rule of law) መርህ ጋር የሚፃረር ስራን መስራት ነው የሚሆነው :: ስለዚህ አሁን ባለው ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ለህዝብ ጥቅም ሲባል ከቦታው የሚፈናቀል የገጠርም ሆነ የከተማ ነዋሪ ካሳ የማግኘት መብት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህግ-መንግስት የተረጋገጠ መብት ሲሆን ዝርዝር አፈፃፀሙ የህግ-መንግስቱን መርህ ተከትለው በወጡ አዋጅ ቁጥር 555/97 እና ደንብ ቁጥር 135/99 ተደንግጎ የምናገኘው የዜጎች መብት ነው::