በገጠር መሬት የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝና አርሶ አደሩ

 

መሬት ካለው ተፈጥሮዋዊ ባሕርይም ሆነ ግዙፍነት የተነሳ በሃገራችን ፖለቲካል ኢኮኖሚ ማዕከል ሆኖ እስካሁን ዘልቋል፡፡ በተለይም አብዛኛው ሕዝብ በእርሻ  የሚተዳደር ባለበት ሃገር የመሬት ጉዳይ የኢኮኖሚያዊ መሣሪያ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ የሆነ ጠቀሜታ አለው፡፡ የሃገሪቱን የመሬት ስሪት (land tenure) ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከተው በእያንዳንዱርዓት የተለየ ባሕርይ ይዞ እናገኘዋለን፡፡

1966 . በፊት የነበረው የመሬት ስሪት የራሱ ሆነ ባሕርይ የነበረው ሲሆንየርስት ጉልትግንኙነትን ያማከለ ነበር፡፡ መሬት በአብዘኛው የቤተ ክርስቲያን ይዞታ፣ የርስት ጉልት ይዞታ በሚል የተከፋፈለ ነው፡፡ ይህ የመሬት ስሪት በሃገሪቱ አብዛኛውን ክፍል በሚሸፍነው እና መተዳደሪያ መሬት ያለውን አርሶ አደሩን የሚያገል፣ የባለቤትነትም ሆነ የመጠቀም መብትን ዋስትና በማይሰጥ መልኩ የተዋቀረ እንደመሆኑ መሬት በጥቂቶች እጅ እንዲሆን ያደረገ ነበር፡፡

1966 . ተከትሎ የመጣው ለውጥ ቀደም ሲል የነበረውን የርስት ጉልት ግንኙነት በመሻር በመሬት ላይ አዲስ መዕራፍ ከፍቷል፡፡ በጊዜው ወደ ሥልጣን የመጣው የደርግ ሥርዓት ይከተል በነበረውን የሶሻሊስት ርዮተ ዓለም በመመራት ኢኮኖሚውን የሚመሩትን ዋና ዋና ነገሮች ከግል ባለቤትነት ወደ ሕዝብ ባለቤትነት ሲያሸጋግር መሬትም የገጠር መሬትን የሕዝብ ኃብት ለማድረግ በሚል አዋጅ ቁጥር 31/67 የሕዝብ ኃብት በሚል ታወጀ፡፡ አዋጁም መሬት አይሸጥም አይለወጥም የሚለውን ጥብቅ የሆነና የመሬት ጉዳይን ከሌሎች ንብረቶች የሚለየውን ገደብ ይዞ ብቅ ብሎ ነበር፡፡ 

ምንም እንኳን እንደ አዲስ የተደረገው የመሬት ስሪት ለውጥ ከገባር ሥርዓት አውጥቶ ወደ ሕዝብ ያሸጋገረ ክስተት ቢሆንም መሬት ተጠቃሚውን መብት ያጣበበ ነበር፡፡ የገጠር መሬትን የሕዝብ ለማድረግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 31/67 አንቀጽ 5 አንድ የመሬት ተጠቃሚ  በይዞታ የያዘውን መብት መሸጥ፣ መለወጥ፣ በስጦታ ማስተላለፍ፣ በማስያዝ፣ በወልድ አገድ ወይም በሌላ ሁኔታ ማስተላለፍ እንደማይችል ገደብ ያስቀምጣል፡፡

Continue reading
  28046 Hits

የተሻሻለው የአማራ ክልል የገጠር መሬት አዋጅ እና አከራካሪው የይርጋ ድንጋጌ

የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 133/98 የተካው የተሻሻለው የገጠር መሬት አዋጅ ቁጥር 252/2009 ቀደም ሲል በሕግ ደረጃ ሽፋን ያላገኙ አዲስ ነገሮችን ይዞ እንደወጣ ይታወቃል፡፡ አዲስ ከሚባሉ ነገሮች አንዱ በገጠር መሬት ላይ በሚነሱ ክርክሮች ላይ የይርጋ መቃወሚያ ተፈፃሚ ሊሆን እንደማይችል ያስቀመጠው ነገር ነው፡፡ ይህ የይርጋ ድንጋጌ በሕጉ የተካተተ አዲስ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ገና ከጅምሩ አከራካሪ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል፡፡ አከራካሪነቱም በባለሙያዎች መካከል ሁለት ጫፍ የያዙ አቋም እንዲኖር ከማድረግ አልፎ አዲስ የክርክር ምክንያትም እየሆነ ነው፡፡ አዋጁ ስራ ላይ ከዋለ ጀምሮም የገጠር መሬትን ተከትሎ የሚቀርቡ ክሶች ላይ የይርጋ መቃወሚያ ተፈፃሚነት የለውም በሚል  ብዙ ዶሴዎች ከተዳፈኑበት አቧራቸውን እያራገፉ በክስ መልክ  እየቀረቡ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶችም በባለሙያዎች መካከል በይርጋው ተፈፃሚነት ላይ  ባለ ሁለት ጫፍ የያዘ አቋም ምክንያት ከወዲሁ ተገማችነታቸውና ወጥነታቸው አደጋ ላይ እየወደቀ ነው፡፡ ስለዚህም በጉዳዩ ዙሪያ  የሚነሱ አቋሞችን እና ምክንያቶችን በማየት ሃሳቡን መመልከቱ አስፈላጊ እና ትኩረት የሚያስፈልገው ነው፡፡ የፁሁፉ ዋና ትኩረትም በተሻሻለው የገጠር መሬት አዋጅ ላይ የተቀመጠጠው የይርጋ ድንጋጌ ወሰን አለው ወይስ የለውም የሚል ይሆናል፡፡

በቅድሚያ የተሻሻለው የገጠር መሬት አዋጅ ቁጥር 252/2009 አንቀፅ 55 ስለይርጋ ያስቀመጠውን የድንጋጌውን ሙሉ ይዘት መመልከት ተገቢ ነው፡፡

አንቀፅ 55 ስለይርጋ

የገጠር መሬትን በወረራ ወይም በሌላ በማናቸውም ህገ ወጥ መንገድ ይዞ በመገልገል ላይ የሚገኝ ማንኛውም ሰው መሬቱን እንዲለቅ በማንኛውም ሌላ ሰው ወይም ሥልጣን ባለው የመንግሥት አስተዳደር አካል ሲጠየቅ ወይም በመደበኛ ፍርድ ቤት ሲከሰስ የይርጋ ጊዜ ገደብን በሥነ ስርዓት መቃወሚያነት ሊያነሳ አይችልም፡፡

የድንጋጌው ይዘት በተጠቀሰው መልኩ የቀረበ ሲሆን አንደኛው አቋም ይህ የይርጋ ድንጋጌ  በማንኛውም ከገጠር መሬት ላይ የሚነሳ ክርክርን የይርጋ መቃወሚያ እንዳይቀርበበት እና ይርጋን መቃወሚያ ማድረግ እንደማይቻል ተደርጎ እንደተደነገገ የሚገልፅ ነው፡፡ እንደዚህ አቋም አራማጆች ሕጉ በግልፅ የገጠር መሬትን በወረራ ወይም በማናቸውም ሕገ ወጥ መንገድ የያዘ ሰው የይርጋ መቃወሚያ ሊያነሳ እንደማይችል ስለሚናገር በመሬት ክርክር ይርጋ ተፈፃሚ ሊሆን አይገባም በማለት ይገልፃሉ፡፡  በድንጋጌው “በማናቸውም ሕገ ወጥ መንገድ መያዝ” የሚለው ሃረግ  የሚያመለክተው የገጠር መሬት ሊያዝ ከሚችልባቸው መንገዶች ማለትም (በድልድል፣ በስጦታ፣ በውርስ፣ በኪራይ) ውጪ የገጠር መሬትን ይዞ መገኘት እንደሆነ ተደርጎ የተቀመጠ ነው፡፡ በተሻሻለው አዋጅ አንቀፅ 2(39) በተቀመጠው የትርጓሜ ክፍል “ህገ ወጥ ይዞታ” ማለት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የተያዘና አግባብ ባለው አካል እውቅና ያልተሰጠው ማናቸውም የገጠር መሬት ይዞታ ስለመሆኑ ይናገራል፡፡  ይሕ የትርጓሜ ክፍል በሕጉ መሬት ከሚገኝባቸው መንገዶች ወይም ሥርዓት ውጪ የሚያዙና አግባብ ባለው አካል እውቅና ያልተሰጠው የገጠር መሬት እንደ ሕገ ወጥ ይዞታ የሚቆጠር ስለሆነ የይርጋው ድንጋጌም ሕገ ወጥ ይዞታ ከሚለው ትርጉም ጋር ተናዝቦ ሊታይ የሚገባ ነው፡፡ በይርጋ ድንጋጌውም የተቀመጠው በማናቸውም መንገድ በሕገ ወጥ መንገድ መያዝ የሚለው በሕግ ከተቀመጠው መሬት ከሚያዝበት ውጪ መያዝ ስለሆነ ከሕግ ውጪ የገጠር መሬትን ይዞ ይርጋን መከራከሪያ ማድረግ አይቻልም፡፡ በማናቸውም ሕገ ወጥ መንገድ የሚለውም ሁሉንም ከሕግ ውጪ የሚያዙበትን መንገዶች ክፍተት እንዳኖራቸው ዝግ አድርጎ ያስቀመጠ ስለሆነ የይርጋ መቃወሚያ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም፡፡ በተጨማሪም የመሬት ክርክር ይርጋ ሊያግደው እንደማይገባ የፌደሬሽን ምክር ቤት ሳይቀር ውሳኔ የሰጠ ስለሆነ በመሬት ክርክር በሁሉም ጉዳዮች ይርጋ ተፈፃሚነት ሊኖረው አይገባም በማለት መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡

Continue reading
  42433 Hits