መሬት ካለው ተፈጥሮዋዊ ባሕርይም ሆነ ግዙፍነት የተነሳ በሃገራችን ፖለቲካል ኢኮኖሚ ማዕከል ሆኖ እስካሁን ዘልቋል፡፡ በተለይም አብዛኛው ሕዝብ በእርሻ የሚተዳደር ባለበት ሃገር የመሬት ጉዳይ የኢኮኖሚያዊ መሣሪያ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ የሆነ ጠቀሜታ አለው፡፡ የሃገሪቱን የመሬት ስሪት (land tenure) ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከተው በእያንዳንዱ ሥርዓት የተለየ ባሕርይ ይዞ እናገኘዋለን፡፡
በ1966 ዓ.ም በፊት የነበረው የመሬት ስሪት የራሱ ሆነ ባሕርይ የነበረው ሲሆን “የርስት ጉልት” ግንኙነትን ያማከለ ነበር፡፡ መሬት በአብዘኛው የቤተ ክርስቲያን ይዞታ፣ የርስት ጉልት ይዞታ በሚል የተከፋፈለ ነው፡፡ ይህ የመሬት ስሪት በሃገሪቱ አብዛኛውን ክፍል በሚሸፍነው እና መተዳደሪያ መሬት ያለውን አርሶ አደሩን የሚያገል፣ የባለቤትነትም ሆነ የመጠቀም መብትን ዋስትና በማይሰጥ መልኩ የተዋቀረ እንደመሆኑ መሬት በጥቂቶች እጅ እንዲሆን ያደረገ ነበር፡፡
የ1966 ዓ.ም ተከትሎ የመጣው ለውጥ ቀደም ሲል የነበረውን የርስት ጉልት ግንኙነት በመሻር በመሬት ላይ አዲስ መዕራፍ ከፍቷል፡፡ በጊዜው ወደ ሥልጣን የመጣው የደርግ ሥርዓት ይከተል በነበረውን የሶሻሊስት ርዮተ ዓለም በመመራት ኢኮኖሚውን የሚመሩትን ዋና ዋና ነገሮች ከግል ባለቤትነት ወደ ሕዝብ ባለቤትነት ሲያሸጋግር መሬትም የገጠር መሬትን የሕዝብ ኃብት ለማድረግ በሚል አዋጅ ቁጥር 31/67 የሕዝብ ኃብት በሚል ታወጀ፡፡ አዋጁም መሬት አይሸጥም አይለወጥም የሚለውን ጥብቅ የሆነና የመሬት ጉዳይን ከሌሎች ንብረቶች የሚለየውን ገደብ ይዞ ብቅ ብሎ ነበር፡፡
ምንም እንኳን እንደ አዲስ የተደረገው የመሬት ስሪት ለውጥ ከገባር ሥርዓት አውጥቶ ወደ ሕዝብ ያሸጋገረ ክስተት ቢሆንም መሬት ተጠቃሚውን መብት ያጣበበ ነበር፡፡ የገጠር መሬትን የሕዝብ ለማድረግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 31/67 አንቀጽ 5 አንድ የመሬት ተጠቃሚ በይዞታ የያዘውን መብት መሸጥ፣ መለወጥ፣ በስጦታ ማስተላለፍ፣ በማስያዝ፣ በወልድ አገድ ወይም በሌላ ሁኔታ ማስተላለፍ እንደማይችል ገደብ ያስቀምጣል፡፡