Font size: +
7 minutes reading time (1454 words)

የውርስ ኃብት ማጣራትን የተመለከቱ አንዳንድ ነጥቦች ከሰበር ውሳኔ ጋር ተገናዝቦ የቀረበ

የውርስ ህግ ክፍል በሆነው የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 826 ላይ እንደተመላከተው አንድ ሰው የሞተ አንደሆነ በሞተበት ጊዜ ዋናው መኖሪያው በሆነበት ስፍራ የዚህ የሟች የውርስ ሀብት ይከፈታል፡፡ የሟች ውርስ ሟች በሞተበት ቅጽበት የሚከፈት ቢሆንም የሟች የውርስ ሀብት እስከሚጣራ ድረስ የሟች ንብረት እንደ አንድ የተለየ ንብረት ይቆጠራል፡፡ ይህም ማለት የሟች ንብረት ከሌሎች ሰዎች ወይም ወራሾች ንብረት ጋር ሳይቀላቀል የባለቤትነት መብቱ ለወራሾች ሳይተላለፍ እንደ አንድ ልዩ ንብረት ሆኖ ሊያዝ እንደሚገባ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 942 ይደነግጋል፡፡

ስለዚህ የሟች የውርስ ሀብት ወደ ወራሾች ይተላለፍ ዘንድ እንዲሁም ከሟች የውርስ ሀብት ላይ እዳ ጠያቂ ወይም ለሟች እዳ ከፋይ ነን የሚሉ ወገኖች የየፍላጎታቸው እንዲፈጸም፤ የሟች ወራሾች ማንነታቸው እና የሚደርሳቸው ምጣኔ ድርሻ ይታወቅ ዘንድ፤ሟች ኑዛዜ የተናዘዙ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ የውርስ ሀብቱ ሊጣራ የሚገባው ስለመሆኑ በፍ/ብ/ህ/ቁ 946 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ላይ በግልጽ ተመላክቶ ይገኛል፡፡

ይህ የውርስ ማጣራት ተግባር በምን አግባብ እንደሚከናወን፤ የውርስ አጣሪው ስልጣንና ኃላፊነት እስከምን ድረስ አንደሆነ፤ የውርስ ኃብት ላይጣራ ሚችልባቸው ሁኔታዎች፤ የውርስ አጣሪ ሪፖርትን በማጽደቅ በፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ ህጋዊ ውጤቱ እስከምን ድረስ እንደሆነና በዚህ ውሳኔ ላይ የሚቀርብ ተቃውሞ በምን መልኩ ሊቀርብ እንደሚገባ በዚህ ጽሁፍ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ውሳኔዎች ጋር በማገናዘብ አጭር ዳሰሳ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ 

 

የውርስ ኃብት አጣሪ ስልጣንና ተግባር

 

የውርስ ኃብት አጣሪ ስልጣንና ተግባር በፍ/ብ/ሕ/ቁ 856 ላይ የተገለጸ ሲሆን በዚህም መሰረት የሟችን ውርስ እንዲያጣራ የተሾመ ሰው ሊከውን ሚገባው÷

1ኛ)  የሟችን ኑዛዜ መፈለግና የኑዛዜ ወራሾችን ከነ ምጣኔ ድርሻቸው ማጣራት፤

2ኛ) መከፈያቸው የደረሱ የውርስ እዳዎችን መክፈል፤

3ኛ) ሟቹ በኑዛዜ ያደረጋቸውን ስጦታዎችን መክፈል፤

4ኛ) የሟችና ያለኑዛዜ ወራሾችን መለየትና ምጣኔ ድርሻቸውን መጣራት፤

5ኛ) የሟች ንብረት ምን ምን እንደሆነ ማጣራት ፤ንብረቱ እዳ ወይም እገዳ ያለበት መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ በውርስ አጣሪ ከሚከወኑ ተግባሮች ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡

አንድ የውርስ አጠሪ የሟችን የውርስ ኃብት በሚያጣራበት ወቅት የሚጣራው ንብረት የሟች መሆን አለመሆኑ አከራካሪ ሆኖ ሲያገኘው ንብረቱ የሟች ንብረት ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመመስረት የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ በመመርመርና በመመዘን ውሳኔ የመስጠት ስልጣን የሌለው ስለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 83665 በቅጽ 15 ላይ በሰጠው የሰበር ውሳኔ ላይ ተመላክቷል፡፡ በመሆኑም የውርስ ኃብት እንዲያጣራ የተመደበ የውርስ አጣሪ ንብረቱ የሟች የግል ኃብት መሆኑ አለመሆኑን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ማስረጃዎችን በማደራጀት የግራ ቀኙን ክርክር ከማስረጃው ጋር መርምሮ ውሳኔ እንዲሰጥ ውርሱን እንዲጣራ ላዘዘው ፍርድ ቤት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በኑዛዜ በተጠቀሱትና ባልተጠቀሱት ንብረቶች የውርስ ሀብት መሆን ያለመሆን ላይ ወራሾች ያልተስማሙና ክርክር ያነሱ ከሆነ የአጣሪው ሥራና ኃላፊነት ወራሾች የተስማሙባቸውን ንብረቶች የውርስ ኃብት መሆናቸውን መመዝገብ፤ ወራሾች ያልተስማሙባቸውን ንብረቶችና እዳዎች ካሉ ደግሞ ማስረጃቸውን በማሰባሰብ ማስረጃው ምን ምን እንደሚያስረዳ በሪፖርቱ ላይ በማስፈር እንዲያጣራ ላዘዘው ፍርድ ቤት ማቅረብ እንጂ ክርክሩንና ማስረጃውን ከህግ ጋር በማገናዘብ በራሱ የውርስ በሀብት ነው ወይም አይደለም? የሚል ውሳኔ የመስጠት ስልጣን የሌለው መሆኑ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት/ በሰ/መ/ቁ 23322 በቅጽ 7 እና በሰ/መ/ቁ 66727 በቅጽ 11 በሰጠው ውሳኔ ላይ ተገልጿል፡፡  

 

የውርስ አጠሪ የውርስ ኃብቱን ሲያጣራ ጥሪ አድርጎላቸው ያልቀረቡ ወራሾችን በተመለከተ

 

የውርስ አጣሪው የውርስ ማጣራት ስራውን እንዲያከናውን በፍ/ቤት ከታዘዘ በኋላ መጀመሪያ የሚያከናውነው ተግባር የውርስ ኃብቱ እየተጣራ መሆኑን የሚገልጽ የማስታወቂያ ጥሪ በፍርድ ቤቱ ማህተብ በማረጋገጥ በሟች ቋሚ መኖሪያ ቤት ላይና በሟች መኖሪያ ቀበሌ(ወረዳ) ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ እንዲለጠፍ ማድረግ ነው፡፡

የዚህ ማስታወቂያ ጥሪ ዋና አላማው የሟች የውርስ ኃብት ይገባኛል ፤ከሟች የውርስ ኃብት ላይ እዳ ጠያቂ ነን ወይም ለሟች ወራሽ እዳ ከፋይ ነን የሚሉ ወገኖች እንዲቀርቡ እና የሟች ኑዛዜ በእጁ ያለ ወገን ይህንኑ ማስረጃውን ይዞ እንዲቀርብ የሟች ውርስ እየተጣራ መሆኑን በይፋ ለማሳወቅ ነው፡፡ በዚህ ማስታወቂያ ጥሪ መሰረት ጥሪ ተደርጎላቸው ያልቀረቡ ሰዎች የወራሽነት ድርሻቸው በተመለከተ በምን አግባብ ሊስተናገዱ ይገባል የሚለው ብዙ ግዜ በውርስ ማጣራት ሒደት አዳጋች እየሆነ መጥቷል፡፡ በአንድ አንድ ቦታዎች የሟች ህጋዊ ወራሾች የውርስ ሀብት እየተጣራ መሆኑ ተገልጾ በማስታወቂያ ጥሪ ተደርጎላቸው እነርሱ ባልቀረቡበት ሁኔታ  ሌሎች ወራሾች በመረዳጃ እድር ውስጥ የሟች ልጆች መሆናቸው ተመዝግቦ ይገኛል በማለት እነርሱ ባልቀረቡበት ከእድር በመጣው መረጃ መሰረት ድርሻቸው ተጠብቆ የውርስ ሀብቱ ይጣራ የሚል ሀሳብ ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት  ውሳኔ የሰጠ ሲሆን፡፡ በውሳኔውም ላይ “የውርስ አጣሪው ጥሪ አድርጎላቸው ያልቀረቡ ሰዎች ሌላ ቦታ ይኖራሉ ተብሎ ስለመኖራቸው ከመረዳጃ እድር መዝገብ ላይ ተዘርዝርው ስለተገኙ ውርስ አጣሪው የወራሽነት ድርሻ አላቸው በማለት የሚያቀርበው የውሳኔ ሀሳብ አግባብነት ያለው አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከየትኛውም ቦታ የሚቀርቡ ማስረጃዎች ሁሉ ዋጋ የሚሰጣቸው ስላልሆኑ በመረዳጃ እድር መዝገብ ይገኛል የተባለው ሰነድ የሟች ወራሽነት ለጊዜው ለመወሰን ብቃት የሌለው ማስረጃ በመሆኑን የፍ/ብ/ሕ/ቁ 962(2) ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ያስገነዝበናል፡፡ ሌሎች ወራሾች አሉ ከተባለም ተጠሪው የክርክሩ ተከፋይ መሆን አለባቸው” በማለት ወስኗል፡፡  

በመሆኑም በመረዳጃ እድር ውስጥ ስም ተጠቅሶ መገኘት ወራሾች ጥሪ ተደርጎላቸው ባልቀረቡበት ሁኔታ ያለኑዛዜ ወራሽነት ለማረጋገጥ ብቃት ያለው ማስረጃ አይደለም የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡

 

የውርስ ሀብት ማጣራት የግድ የማይሆንበት የሕግ አግባብ

 

ወራሾችም ሆነ የውርስ ሀብቶች ተለይተው በግልጽ በሚታወቁት ወቅት ከወራሾች መሀከል አንዱ በግልጽ ተለይቶ የሚታወቀው የውርስ ኃብት በሌሎች ወራሾች የተያዘ እንደሆነ የውርስ ሀብቱ ሳይጣራ ድርሻቸው ያካፍሉኝ የሚል ቀጥተኛ ክስ በድርሻቸው ግምት ልክ ጉዳዩን ለማየት የሥረ ነገር ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላሉ፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 946 ጀምሮ የተደነገጉ ደንጋጌዎች ስንመለከት ወራሾች በራሳቸው ወይም በተመረጠ ሌላ ሰው ውርስ እንዲጣራ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት ማመልከት እንዲችሉ ቢመላከትም በቀጥታ የክፍፍል ክስ የውርስ ሀብቱ ሳይጣራ የመመስረት መብት የላቸውም የሚል ክልከላ ግን በህጉ አልተቀመጠም፡፡

 

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 34703 በቅጽ 8 ላይ በሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ ላይ እንደተገለጸው “ወራሾችና የውርስ ሀብቱ በግልጽ ተለይቶ የሚታወቅ በሚሆንበት ጊዜ ከውርስ ሀብቱ ድርሻዬን ልካፈል ለሚል አመልካች የውርስ ሀብት መጣራት እንደ ቅድመ ሁኔታ አድርጎ መውሰድ አይገባም፡፡ በመሆኑም የውርስ ሀብት ከፍፍልን መነሻ ያደረገ ክስ የግዴታ ውርስ ካልተጣራ በኋላ መቅረብ የለበትም ሊባል አይገባም” ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ከዚህ ጋራ ተያይዞ ሊነሳ የሚችል ጥያቄ ቢኖር በዚህ የውርስ ሀብት ሳይጣራ በሚቀርብ የክፍፍል ክስ ላይ ከውርስ ሀብቱ ላይ የሚፈለግ ዕዳ ካለ በምን አግባብ ሊጣራ እና ሊስተናገድ ይችላል?  የሚለው ነው፡፡ ይህን በተመለከተ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዚህ በላይ በጠቀስኩት የሰበር ውሳኔ ላይ እንደገለጸው “ ከውርስ ሀብቱ የሚፈለግ እዳ ክሱ በቀረበበት ፍርድ ቤት መሪነት በማስረጃ ተጠርቶ ሊታወቅ የሚችል ነው” በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ ወራሾች የውርስ ሀብቱ በግልጽ ተለይቶ በታወቀበት ወቅት የውርስ ሀብቱን ማጣራት ሳያስፈልግ ድርሻዬን ልካፍል በማለት በሚጠየቀው የንብረት ግምት ልክ የሥረ ነገር ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት ቀጥተኛ የክፍፍል ክስ ማቅረብ የሚቻል ሲሆን ከውርስ ሀብቱም የሚፈለግ እዳ ካለ በዚሁ መዝገብ ሊስተናገድ ይገባል የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡

 

የውርስ አጣሪ ሪፖርት የጸደቀበት የፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ መቃወሚያ ስለሚቀርብበት የሕግ አግባብ

 

የውርስ አጣሪ የውርስ ማጣራት ተግባሩን ካከናወነ በኋላ የሪፖርቱን ሰነድ እንዲያጣራ ትዕዛዝ ለሰጠው ፍርድ ቤት ያቀርባል፡፡ በዚህም መሰረት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 960 እና 996 በተጠቀሰው አግባብ ችሎቱ የሪፖርቱን ይዘት አግባብ ከሆነው ህግ አንጻር መርምሮ በማጽደቅ ወራሾች ሪፖርቱ የጸደቀበትን የውሳኔ ግልባጭ የሚያገኙ ይሆናል፡፡  

የውርስ ማጣራት ውጤት እያንዳንዱ ወራሽ የሚደርሰው ድርሻ ተለይቶ የምስክር ወረቀት የሚሰጥ ይሆናል፡፡

በመሆኑም የውርስ አጣሪ ሪፖርት በማጽደቅ የሚሰጥ የፍርድ ውሳኔ እርሱን ችሎ እንደ መጨረሻ ፍርድ የማይቆጠር በመሆኑ ዋነኛ ሚናውም እንደ ማስረጃነት የሚያገለግል ነው፡፡ ስለዚህ ከማስረጃነት ዋጋ ውጭ ሌላ ዋጋ የሌለውን የውርስ አጣሪ ሪፖርት መብቴን ነክቷል የሚል ወገን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 መሰረት መቃወሚያ ሊቀርብ አይችልም፡፡

ስለዚህ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 45905 በቅጽ 11 በሰጠው ውሳኔ መሰረት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 መሰረት መቃወሚያ ማቅረብ የሚቻለው በውርስ ሀብት ክፍፍል ላይ ውሳኔ ለሰጠ ፍርድ ቤት ነው እንጂ የውርስ አጣሪ ሪፖርቱን ላጸደቀው ፍርድ ቤት አይደለም፡፡    

 

የውርስ አጣሪ ሪፖርት የጸደቀበት የፍርድ ውሳኔ በቀጥታ የአፈጻጸም አቤቱታ የማይቀርብበበት ስለመሆኑ

 

ከዚህ በላይ እንደተገለጸው የውርስ አጣሪ ባለው ስልጣን መሰረት ከውርስ ሀብቱ መብት አለን የሚሉ ወይም ወራሾች በመወሰን ፤የሟች ኑዛዜ ካለ በማፈላለግ፤በዚህም ኑዛዜ መሰረት ተጠቃሚዎችን በመወሰን ፤ውርሱን በማስተዳደር፤የውርሱን ተከፋይ ገንዘብ መሰብሰብና እዳዎችን በመክፈል፤የሟችን ንብረት ማጣራት ፤የኑዛዜ ስጦታዎችን በመክፈል የውርስ ማጣራት ሥራውን ያጠናቅቃል፡፡

የውርስ ማጣራት ስራው እንደተጠናቀቀ የውርስ አጣሪ ሪፖርቱን አጣሪው ለወራሾች እና ለፍርድ ቤቱ የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡ ሪፖርቱ የደረሳቸው ወራሾች በሪፖርቱ ላይ የተመላከተው ነገር መብትና ጥቅማቸውን የሚነካ ከሆነ ለፍርድ ቤቱ አስተያየት የሚያቀርቡ ሲሆን ችሎቱም የግራ ቀኙን አስተያየት ከሪፖርቱ አንጻር አገናዝቦ መሻሻል የሚገባውን ነገር ያለ እንደሆነ የሪፖርቱን ይዘት በማሻሻል በውሳኔ የሚያጸድቀው ይሆናል፡፡  ይህ በፍርድ ቤት የጸደቀው የውርስ አጣሪ ሪፖርት ከነ ማጽደቂያው የውሳኔ ግልባጭ ጋር ለወራሾች የሚደርሳቸው ሲሆን ወራሾቹም በዚህ ውሳኔ መሰረት የወራሽነት ምስክር ወረቀት( certificate of succession) የሚያገኙ ይሆናል፡፡ በመሆኑም የውርስ ማጣራት ውጤት እያንዳንዱ ወራሽ ከውርሱ የሚደርሰውን ድርሻ ተለይቶ የወራሽነት ምስክር ወረቀት ማስገኘት ነው፡፡ እያንዳንዱ ወራሽ የወራሽነት ምስክር ወረቀት ካገኘ በኋላ በወራሽነት መካከል አለመግባባት ሲፈጠር የውርስ አጣሪ ሪፖርቱን መሰረት በማድረግ ቀጥተኛ የአፈጻጸም ክስ ሊያቀርብ አይችልም፡፡ ከዚህ  ጋር በተያያዘ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 18576 በቅጽ 7 ላይ በሰጠው ውሳኔ “የውርስ ማጣራት ተግባር ተፈጽሞ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ማግኘት አላማው የእያንዳንዱ ወራሽ ድርሻን በመለየት መብቱን ማረጋገጥ ስለሆነ በዚሁ መልክ መብት ከተረጋገጠ በኋላ በወራሽነት የምስክር ወረቀቱ መሰረት ወራሾች ድርሻቸውን በስምምነት መከፋፈል ካልቻሉ በድርሻቸው መጠን ዳኝነት ከፍለው ይሔው መብታቸውን በፍርድ እንዲረጋገጥ ዳኝነት መጠየቅ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በዚህ መልኩ ዳኝነት ሳይጠይቅ በውርስ አጣሪው ሪፖርት መሰረት እንዲፈጸም የአፈጻጸም አቤቱታ ማቅረብ ፍርድ ያላረፈበትን ነገር ለማስፈጸም እንደመጠየቅ የሚቆጠርና የህጉን አላማ የሳተ ነው” ሲል ወስኗል፡፡ በመሆኑም የውርስ አጣሪ ሪፖርት የጸደቀበትን ፍርድ መሰረት በማደረግ የሚቀርበው የአፈጻጸም ክስ ሳይሆን ተገቢውን ዳኝነት ተከፍሎ ቀጥተኛ ክፍፍል ክስ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡    

 

መደምደሚያ

 

አንድ የውርስ አጣሪ የሟች ወራሾች እነ ማን እንደሆኑ፤ሟች ኑዛዜ የተው መሆን አለመሆኑን በማጣራ ፤መከፈያቸው የደረሰ እዳዎችን በመከፍል፤ለውርስ ሀብቱ የሚከፈል እዳ ካለ በመሰብሰብ፤የውርስ ማጣራት ሒደቱን በማጠናቀቅ ሪፖርቱን ለሾመው ፍርድ ቤት የሚያቀርበ ይሆናል፡፡ በተለየ ሁኔታ የውርስ ሀብቱና ወራሾች ተለይተው በሚታወቅበት ወቅት የውርሱን ማጣራት ሳያስፈልግ ቀጥተኛ የክፍፍል ክስ ማቅረብ ይቻላል፡፡

አንድ የውርስ አጣሪ የሟችን የውርስ ሀብት በሚያጣራበት ወቅት የውርስ ሀብት መሆን አለመሆኑ ክርክር የሚነሳበትን ንብረት የገጠመው እንደሆነ በዚህ ንብረት ላይ ተገቢውን ማስረጃ ሰብስቦ ማስረጃው በምን አኳያ እንደሚያስረዳ በሪፖርቱ ላይ በመመዝገብ ለፍርድ ቤቱ  ማስተላለፍ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ባለፈ አከራካሪው ንብረት ላይ የግራ ቀኙን ክርክር ከማስረጃው አንጻር መዝኖ ውሳኔ ሊሰጥ አይገባም፡፡

የውርስ አጣሪ ባጸደቀው የውሳኔ ክፍል ላይ ቀጥተኛ የአፈጻጸም ክስም ሆነ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 መሰረት መቃወሚያ ሊቀርብበት አይችልም፡፡

ድርሻውን ለመካፈል የፈለገ ወራሽ በድርሻው ግምት ልክ ቀጥተኛ የክፍፍል ክስ የሚያቀርብ ሲሆን ተቃውሞ ያለውም ወገን በዚሁ የክፍፍል መዝገብ ላይ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 መሰረት ተቃውሞ ማቅረብ ይቻላል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Ethiopian Public Private Partnership Framework
Permanency Rule Dilemma To Designate Grave Willful...

Related Posts

 

Comments 1

Abebe
Guest - Haftom tikue (website) on Monday, 18 September 2023 11:04

So far so good your website

So far so good your website
Already Registered? Login Here
Abebe
Tuesday, 23 July 2024