Font size: +
31 minutes reading time (6199 words)

በፍርድ ቤት አወዛጋቢ የሆኑ የውርስ ጉዳዮች እና መፍትሔዎቻቸው

ይህ ፅሑፍ “የኢትዮጵያ የውርስ ሕግ መሰረተ-ሐሳቦች” ከሚለው 3ኛ ዕትም መፅሐፍ በ10ኛ ምዕራፍ ላይ የተከተበ ሲሆን በዚህ መፅሐፍ በመጀመሪያ እና በ2ኛ ዕትም ያልነበር ነው፡፡ በዚህ መፅሐፍ በ3ኛ ዕትም በምዕራፍ 10 ላይ ከተነሱ በርካታ ጉዳዮች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ እነሆ ጀባ ብያለሁኝ፡፡

ማሳሰቢያ ይህ ፅሑፍ በመፅሐፉ በሕግ የሚጻፉ ጉዳዮችን የማጣቀሻ ሥነ-ሥርዓት (based on legal citation rule) ተከትሎ የተጻፈ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ፅሑፍ በበየነ-መርብ በሚለቀቅ በድህረ-ገፅ ላይ የሚነበብ በመሆኑ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ለአንባቢዎች ይህንን ፅሑፍ ሲያነቡ በሚመች አግባብ የማጣቀሻ ሁኔታዎች ከመፅሐፉ ከነበረው በሕግ የሚጻፉ ጉዳዮችን የማጣቀሻ ሥነ-ሥርዓት (based on legal citation rule) በተለየ መልኩ የተቀመጡ ለመሆኑ ለማሳሰብ እወዳለሁኝ፡፡

የውርስ ሐብት የሽያጭ ውልን የሚፍርስባቸው እና የማይፈርስባቸው ሁኔታዎች

1.     የውርስ ሐብት የሽያጭ ውልን የማይፈርስባቸው ሁኔታዎች

አንዳንድ ጊዜ ከወራሾች መካከል አንዱ የሌሎች ወራሾችን ፍቃድ ሳይጠይቅ የጋራ ሃብት የሆነውን የውርስ ሃብት የሆነ ቤትን በራሱ ስም በማዞር ይሸጣል፡፡ በዚህ ጊዜ ቤቱ እንዲሸጥ ፍቃዳቸውን ያልሰጡ ወራሾች የሽያጭ ውሉ እንዲፈርስላቸው ክስ ሲያቀረቡ በተግባር ይታያል፡፡ ይህንን በተመለከተ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በተለያዩ መዛግብት (በቅፅ 10 በሰ/መ/ቁ.41857፣ 46527 እና 47378) አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሰጠ ሲሆን በቅፅ 10 በሰበር መዝገብ ቁጥር 46527 ላይ በቀን 24/06/2002 ዓ.ም ሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

ገዢ ቤቱን በገዛበት ወቅት የቤቱ ስመ-ሃብት በሻጭ ስም ከነበረ እንዲሁም ሽያጩን ህጉ በሚጠይቀው የአፃጻፍ ስርዓት መሰረት ያከናወኑ ከሆነ ገዢ ቤቱን የገዙት በቅን ልቦና መሆኑን ስለሚያመለክት የቤት ሽያጩ መብቴን ይነካን የሚል ወራሽ ድርሻ አለው የሚባል ከሆነ ሻጭን ከሚጠይቅ በስተቀር ገዢው በህጋዊ መንገድ የገዛውን ቤት እንዲያስረክበው የሚደረግበት የህግ አግባብ የለም።

ይህንን በተመለከተ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ በተለያዩ መዛግብት የውርስ ሃብት ሳይከፋፈል ወራሾች በጋራ ይዘውት የሚገኝ ቤት ከወራሾቹ መካከል ሌሎቹ ወራሾች ሳያውቁ የቤቱን ስመ-ንብረት በስሙ አዙሮ ለሌላ ሰው ቢሸጠው ገዥው የሻጩን የማይንቀሳቀስ ንብረት የምስክር ወረቀት አይቶ ባለሃብት እንደሆነ ገምቶ የገዛው ስለሆነ የሽያጭ ውሉ ሊፈርስ አይገባም በማለት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል። ምክንያቱም ገዥው ሽያጩን ህጉ በሚጠይቀው የአፃጻፍ ስርዓት መሰረት ያከናወኑ ከሆነ ሻጭ የቤቱ የባለ ሃብትነት የምስክር ወረቀት መያዛቸው ንብረቱን የግል ሃብት እንደሆነ በፍ/ብ/ህ/ቁ.1195 መሰረት የሚያስቆጥር ሲሆን ይህን ማስረጃ በመመልከት ንብረቱን ውል ለማዋዋል ስልጣን ባለው አካል ፊት የሚገዛ ሰው ሽያጭን ያከናወነው በህግ መሰረት በመሆኑ ገዢ ቤቱን የገዙት በፍ/ብብህ/ቁ.1168 መሰረት በቅን ልቦና በመሆኑ እና በሕጉ ደግሞ የቅን ልቦና ገዥ ጥበቃ የሚደረግለት በሆኑ ነው፡፡ (ቅፅ 10፣ ሰ/መ/ቁ.41857፣ በቅፅ 10 በሰ/መ/ቁ. 46527 እና ቅፅ 10. ሰ/መ/ቁ.47378 ይመልከቱ)

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 10 በሰበር መዝገብ ቁጥር 46527 ላይ በቀን 24/06/2002 በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ላይ ሽያጩን ህጉ በሚጠይቀው የአፃጻፍ ስርዓት መሰረት ያከናወኑ ከሆነ ገዢ ቤቱን የገዙት በቅን ልቦና መሆኑን ስለሚያመለክት የሽያጭ ውሉ ሊፈርስ አይገባም የሚል በመሆኑ ከዚህ ላይ አንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ በሕጉ መሰረት ተደረገ የሚባለው ምን ምን ቅድመ-ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው የሚለውን ጉዳይ ውልን በውል አዋዋይ ፊት ከማረጋገጥ (authentication) እና ውሉን በሚመለከተው አካል ከማስመዝገብ (registration) አንጻር ያለውን ሂደትን እና ውጤትን እንመለከታልን፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 13 በሰ/መ/ቁ.71316 በሆነ በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ላይ ውል በውል አዋዋይ ፊት መደረጉ የሚጠቅመው በተዋዋይ ወገኖች መካከል ውሉ መደረግ አለመደረጉን ለማረጋገጥ እና የውሉን ይዘት በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮቹን ለማረጋገጥ (authentication) ነው፡፡የውልን ማረጋገጥ (authentication) በሕግ ፅንሰ-ሐሳቡ እና የሚያስከትለውን ውጤት በተመለከተ መልካም እና አለልኝ የሚባሉ የሕግ ፀሑፍት (Melkam B.Mogese and Alelegn W.Agegnehu, Issues on the Role of Formal Requirements for Validity of Immovable Transactions in Ethiopia: the Case of Amhara Region፣ Bahir Dar University Journal of Law, vol.6, No.1 (2015)፣ ገፅ.58 ላይ ይመልከቱ) እንደሚከተለው ያብራሩታል፡-

Authentication …establishes three things: namely, that an act was in fact so excuted, that the recital and agreements expressed in the act are accurate reports of the parties intentionals, and that any fact that the act recites to have occurred, did occur. The effect of authentication is fighting against fraudulent, that is illegal and immoral, activities. Further, authentication proves the date of conclusion of the instrument. Whe an instrument passes through the stage of authentication, it is referred to as an authentication act.

አንድን ንብረት በሽያጭ ውል ገዝቻለሁ፤ስለሆነም በዚህ ንብረት ላይ ያለ እኔ ሌላ ሶስተኛ ወገን መብት የለውም በማለት ማናቸውንም ሶስተኛ ወገን ለመመለስ ግን ቤቱ በሚገኝበት ሥፍራ በሚገኘው ንብረትን መዝግቦ ለመያዝ ስልጣን በተሰጠው ማዘጋጃ ቤት የምዝገባ ሥርዓቱ ሊከናወን እንደሚገባ በንብረት ህጉ እና በውል ህጉ ተደንግጓል በሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል የምዝገባ ሥርዓት (registration) በሕግ ያለው ትርጉም እና ውጤትን በተመለከተ መልካም እና አለልኝ (Melkam B.Mogese and Alelegn W.Agegnehu, Issues on the Role of Formal Requirements for Validity of Immovable Transactions in Ethiopia: the Case of Amhara Region፣ Bahir Dar University Journal of Law, vol.6, No.1 (2015)፣ ገፅ.58 ላይ ይመልከቱ) የሚባሉ የሕግ ምሁራን እንደሚከተለው ይተነትኑታል፡-

…Registration essentially means ‘transcription’ or ‘recordation’. It is the copying of an act relating to the disposion of a right…by an official usually known as the Registers or the Conservator of Registers when an act…is presented to him for registration, the Conservator makes a summary of the deed and records it in the special register…The systeme is essentially a registeration of owners rather than a registration of land. The registetrs are kept according to tha names of person and it is the list of the names of owners that forms the index of the Rigisters.

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ አመልካች ሲስተር ኮኮብ በቀለ እና ተጠሪዎች እነ አቶ ሰላም እስኮዳቮልፕ (በቁጥር 3 ሰዎች)፣የሰ/መ/ቁ. 173079፣ሐምሌ 29 ቀን 2012 ዓ.ም (ያልታተመ) በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በመነሳት የማይንቀሳቀስ ንብረትን ምዝገባን በተመለከተ ሁለት የምዝገባ ዓይነቶች እንዳሉ እንደሚከተለው ያብራራል፡-

 

…ስለማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ የሚደነግገዉ የፍትሐብሔር ህጋችን አንቀጽ 10 (Title 10) በመሠረታዊነት ሁለት የምዝገባ ዓይነቶች እንዳሉ የሚያስገነዝብ ነዉ፤ አንደኛዉ የህጋዉያን ተግባራት ምዝገባ (registration of juridical acts) ሲሆን ሁለተኛዉ የባለቤትነት ምዝገባ (registration of ownership) ናቸዉ፡፡ የመጀመሪያዉ ዓይነት ምዝገባ መያዣን ጨምሮ የማይንቀሳቀስ ንብረትን አስመልክቶ የሚቋቋሙበትን የተለያዩ መብቶችና ግዴታዎችን የሚመለከት ሲሆን (በህጉ ከአንቀጽ 1567-1574 ይመለከቷል)፣ ዓይነተኛ ዓላማዉም ንብረቱን የሚገዛ ወይም በንብረቱ ላይ ማናቸዉንም መብት ማቋቋም የሚፈልግ ሦስተኛ ወገን ንብረቱ ያለበትን ሁኔታ ወይም በንብረቱ ላይ አስቀድሞ የተቋቋመ መብትና ግዴታ መኖር አለመኖሩን እንዲያዉቅ ለማድረግ ነዉ፡፡ የፍትሐብሔር ህጉ በአንቀጽ 1561 ላይ የማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገቦች ለህዝብ ግልጽ መሆን እንዳለባቸዉ የደነገገዉም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ስለሆነም የማይንቀሳቀስ ንብረት የተመዘገበ መሆን አለመሆኑን በተመለከተ ክርክር ሲኖር፣ ምዝገባዉ ይህንኑ ዓላማ ማሳካት በሚችል መልኩ የተከናወነ መሆን አለመሆኑ አጽንዖት ተሰጥቶት መጣራት የሚገባዉ ጉዳይ ይሆናል፡፡ የተያዘዉን ጉዳይ ስንመለከት፣ ተጠሪዎች ከፍርድ ቤቱ የተሰጣቸዉን የእግድ ትዕዛዝ በሚመለከተዉ አካል ዘንድ ማስመዝገባቸዉ በንብረቱ ላይ የቅድሚያ መብት የሚያጎናጽፋቸዉ መሆን አለመሆኑን ቀጥሎ የምናየዉ ሆኖ አመልካች ከፍርድ ቤቱ የተሰጣቸዉን ትዕዛዝ ተጠሪዎችን ጨምሮ ማንኛዉም ሦስተኛ ወገን ንብረቱ ያለበትን ሁኔታ እንዲያዉቅ በሚያስችል መልኩ አስመዝግቧል ለማለት የሚቻለዉ የሚመለከተዉ የአስተዳደር አካል የዘረጋዉን የምዝገባ ሥርዓት ተከትሎ ንብረቱ በተመዘገበበት መዝገብ ላይ የተመዘገበ መሆኑ ሲረጋገጥ ነዉ (የፍትሐብሔር ህጉ አንቀጽ 1573 ይመለከቷል)፡፡ ይህም ማለት የእግድ ትዕዛዙ ንብረቱ በተመዘገበበት መዝገብ ላይ መመዝገቡ እስካልተረጋገጠ ድረስ አመልካች ትዕዛዙን ለሚመለከተዉ መስሪያ ቤት ሠራተኛ መስጠቱ መረጋገጡ እግዱ ተመዝግቧል ለማለት አይቻልም፡፡

በፍርድ ቤት የሚሰጡ የእግድ ሆነ ንብረቱን የማስከበር ትዕዛዝ፣ በፍርድ የተሰጡ ውሳኔዎች፣ የሽያጭ እና የስጦታ ውል፣ ኑዛዜ ካለ፣ የሃራጅ ሽያጭ፣ የመለዋውጥ ውል፣ ክስ፣ የኪራይ ውል፣ የመያዣ ውል ወ.ዘ.ተ ካሉ እነዚህ ሁሉ በማይቀሳቀስ ንብረት መዝገብ ላይ መመዝገብ ያለባቸው ሲሆን ምዝገባው ለህዝብ ግልፅ መሆን ያለበት ለመሆኑ የፍ/ብ/ህ/ቁ.1553 እስከ 1586 ያሉትን ድንጋጌዎች ላይ ለመረዳት ይቻላል፡፡ የእነዚህ ጉዳዮች ምዝገባ የህጋዉያን ተግባራት ምዝገባ (registration of juridical acts) የሚባለው ነው፡፡ በሌላ በኩል የማይቀሳቀስ ንብረቱ ገና ካርታ ያልወጣለት ከሆነ የባለቤትነት ምዝገባ (registration of ownership) አይኖርም፡፡ ይህም ማለት የማይቀሳቀስ ንብረቱ ገና ካርታ ያልወጣለት ከሆነ በማይንቀሳቀስ ንብረቱ ማህደር ሊመዘገብ የሚችለው ካሉ የሚመዘገቡት የህጋዉያን ተግባራት ምዝገባ (registration of juridical acts) ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ውልን ማረጋገጥ (authentication) ለውል ምዝገባ (registration) ቅድመ-ሁኔታ መሆኑን እና የሁለቱን ልዩነት የሕግ ምሁራኑ በአጭሩ “… authentication information is a private to the parties in the contract whereas registration information is public in lines with the principle of publicity” (Melkam B.Mogese and Alelegn W.Agegnehu) በማለት ያብራሩትል፡፡

ከዚህ የምሁራኑ ማብራሪያ እና ከሰበሩ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ለመረዳት የሚቻለው ውልን ማረጋገጥ (authentication) አሁን ላይ በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት የአዲስ አበባን እና የድሬደዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ውልን የማረጋገጥ (authentication) ስልጣን የተሰጠው በአዋጅ 922/2008 መሰረት ለፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጥ እና ምዝገባ አገልግሎት ለሚባል ተቋም ሲሆን ውጤቱ በተዋዋዮች ብቻ ሲሆን የውል ምዝገባ ግን መረጃው ለህዝብ ይፋ የሚሆን በመሆኑ ከተዋዋይ ውጭ ላሉት ለ3ኛ ወገን ጭምር ውጤት ያለው ለመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም አንድ የማይንቀሳቀስ ንብረትን በተመለከተ ተደረገ ውል በ3ኛ ወገን ላይ ውጤት እንዲኖረው ከተፈለገ በአዋዋይ ፊት መደረግ ብቻ ሳይሆን በአዋዋይ ፊት የተደረገውን ውል የማይንቀሳቀስ ንብረቱ በተመዘገበበት የመንግስት መስሪያ ቤት ማለትም ማዘጋጃ ቤት ወይም የመሬት አስተዳደር መስሪያ ቤቶች ተወስዶ ሊመዘገብ የሚገባ መሆኑን ነው፡፡

በመሆኑም ገዥው በውል አዋዋይ ፊት በተደረገ ውል መሰረት የውርስ ሃብት የሆነውን ቤት በስሙ ካስመዘገበው ወራሽ ላይ ከገዥ እና የሽያጭ ውሉም በሚመለከተው አካል ተመዝግቦ የቤቱ ስመ-ሃብት ወደ ገዥው ከዞረለት የሽያጭ ውሉ አይፈርስም፡፡ ፍቃድ ያልሰጡት የሌሎች ወራሾች መብት ሊሆን የሚገባው ውሉ ፈርሶ ቤቱን ተረክቦ እንከፋፈል የሚል ሳይሆን የሽያጩን ብር በየድራሻቸው ቤቱን ሽጦ ገንዘቡን ከተረከበው ሰው ላይ መጠየቅ ለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 10፣ ሰ/መ/ቁ.41857፣ በቅፅ 10 በሰ/መ/ቁ. 46527 እና በቅፅ 10 ሰ/መ/ቁ.47378 ከሰጣቸው የሕግ ትርጉሞች ለመረዳት ይሚቻል ነው።

2.    የውርስ ሐብት የሽያጭ ውልን የሚፈርስባቸው ሁኔታዎች

አንዳንድ ጊዜ የውርስ ሃብት የሽያጭ ዉሉን አንዱ ወይም ካንድ በላይ የሆነው ወራሽ የሌሎችን ወራሾች ፍቃድ ሳይጠይቅ የውርስ ሃብቱን ይሸጠዋል፡፡ ይህ በሚሆንብት ጊዜ የውርስ ሃብቱን የሽያጭ ውል ማስፈረስ የሚቻልበት ሁኔታ ያለ ለመሆኑ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 13 በሰበር መዝገብ ቁጥር 64371 ላይ በቀን 02/05/2004 ዓ.ም ሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

ውርሱ ወይም የውርሱ ሃብት የውርሱ አከፋፈል እስኪፈጸም ድረስ በወራሾቹ መካከል ሳይነጣጠል እንደሚቆይ በፍ/ብ/ህግ ቁጥር 1060/1/ ተደንግጓል። የጋራ ወራሾች የሆኑ ሰዎች ባልተካፈሉት የውርስ ንብረቶች ላይ ያላቸው መብትም በፍትሐብሔር ሕጉ በአንቀጽ 8 ስለጋራ ባለሃብትነት፣ በአላባ ስለመጠቀም እና ስለሌሎች ግዙፍ መብቶች በማመላከት በተቀመጡት ድንጋጌዎች መሠረት እንደሚወሰን በዚሁ ቁጥር 1060/2/ ተመልክቷል። በዚህ አግባብ የወራሾቹ ሁሉ የጋራ ሃብት የሆነውን ንብረት ለመሸጥ፣ ለማስተላለፍ፤ ወይም በዋስትና ለማስያዝ ወይም የተመደበበትን አገልግሎት ለመለወጥ የጋራ ባለንብረቶቹ ሁሉ ስምምነት አስፈላጊ እንደሆነ በፍ/ብ/ህግ ቁጥር 1262 ተደንግጓል። በመሆኑም አንደኛዉ ወራሽ የዉርስ የጋራ ንብረት የሆነዉን ቤት ሲሸጥ ውሉን የተፈራረመው የጋራ ባለሃብት የሆኑትን ወራሾች ሁሉ ስምምነት ሳያገኝ ከሆነ ሌሎች የጋራ ባለሀብት ወራሾች ውሉ እንዲፈርስ ጥያቄ ሲያቀርቡ ውሉ እንዲፈርስ መወሰን አግባብ ነው።

በዚህ የሰበር መዝገብ ሃተታ ላይ እንደተቀመጠው ለክርክር መነሻ የሆነው እና የተሸጠው ቤት ወደ ሸጡት ሰዎች ስመ-ሃብቱ ያልዞረ ነው፡፡ በመሆኑም ለክርክር ምክንያት የሆነው ቤት ስመ-ሃብቱ ወደ ሻጭ ወደ ሆኑት ወራሾች ስም ያልዞረ ከሆነ እና ስመ-ሃብቱን ሳያዞር እና የሌሎችን ወራሾች ስምምነት ሳያገኘ የውርስ ሃብት የተሸጡ ከሆነ የሽያጭ ውሉ የሚፈርስ ለመሆኑ መረዳት ይቻላል፡፡

በመሆኑም በሕጉ በተደነገገው መሰረት የቤቱ ሽያጭ ካልተከናወነ እና ቤቱ እንዲሸጥ ፍቃዳቸውን ያልሰጡ ወራሾች ቤቱ የተሸጠው ሕጉን ሳይከተል ያላግባብ ነው የሚል እምነት ካላቸው ውሉ የሚፈርስበትን ምክንያት በመዘርዘር ውሉ ሊፈርስበት የሚችልብትን ምክንያት ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል እንጅ ውሉ ፀንቶ ባለበት እና ባልፈረሰበት ሁኔታ ገዥው በቤቱ ላይ መብት የለሌው በመሆኑ ለወራሾች ይለቀቅ የሚባልበት ምክንያት የለሌ ለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 7 በሰ/መ/ቁ.23332 ከሰጠው ይህ ትርጉም ለመረዳት ይቻላል፡፡ ይህም ማለት የውርስ ሃብት ቤቱ ሽያጭ በሕግ መሰረት የሚፈርስበት ምክንያት ካለ በመጀመሪያ የሽያጩን ውል ማስፈረስ ከዚያ ቀጥሎ ውሉ በፍ/ቤት ከፈረሰ በኋላ ቤቱን የገዛው ሰው የውርስ ሃብት የሆነው ገዝቶት የነበረውን ቤት እንዲያስረክባቸው መጠየቅ አለባቸው ማለት ነው፡፡

በወራሽነት ማስረጃ ላይ የሚቀርብ የመቃዎሚያ ክስ

አንድ የሟች ወራሽ ውርሱ ከተጣራ በኋላ የሚጠይቀው ዳኝነት በፍ/ብ/ህ/ቁ.996 መሰረት የሟች ወራሽ ለመሆኑ የሚያስረዳለትን እና የድርሻ መጠን የሚገልፅ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ነው፡፡ ከዚህ በተቃራነው አንዳንድ ሰዎች የሚጠይቁት የወራሽነት የምስክር ወረቀት የማስረጃ ውሳኔ (declaratory judgment) ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ የማስረጃ ውሳኔ (declaratory judgment) ብቻ የሆነ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ከሆነ ምንም እንኳን ሌላ ሕጋዊ ወራሽ እያለ ቢሆንም የማስረጃ ውሳኔ ሊሰጣቸው የሚገባ ለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ.162698 በሆነ መዝገብ ላይ በቀን 28/03/2011 ዓ.ም የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

ወራሽ የሆነው ሰው ለሟቹ ወራሽ መሆኑ እና ከውርሱ ላይ የሚያገኘውን ድርሻ የሚያመለክቱ የወራሽነት የምስክር ወረቀት እንዲሰጡት ዳኞችን ለመጠየቅ የሚችል ስለመሆኑ የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 996(1) ይደነግጋል። በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከተው ድንጋጌም የሟች ወራሽ መሆኑን የሚገልፅ ማስረጃ ብቻ እንዲሰጠው ወይም ደግሞ ከውርሱ ላይ የሚያገኘውን ድርሻ ጭምር የሚያመለክት የወራሽነት ማስረጃ እንዲሰጠው መጠየቅን ነው።  ይህን አማራጭ የመጠየቅ መብት የተተው ለጠያቂው ወገን ነው። 

የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ ወይም ልጆች እያሉ ሁለተኛ ደረጃ ወራሽ የወራሽነት ማስረጃ ቢወስዱ ሊሰረዝ አይገባም። ሁለተኛ ደረጃ ወራሹ እንዲሰጣቸው ጥያቄውን ያቀረቡት የወራሽነት ማስረጃ ብቻ ከሆነ እና ከውርሱ ላይ የሚያገኙትን ድርሻ የሚያመለክት የምስክር ወረቀት እንዲሰጣቸው ያቀረቡት ጥያቄ ከሌለ ሊታይ የሚገባው የወራሽነት ማስረጃን ብቻ መሠረት በማድረግ ነው እንጂ ከውርስ ላይ የሚያገኙትን ድርሻን መሰረት በማድረግ ሊሆን አይገባም። የቀረበውን አቤቱታ መሠረት በማድረግ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ጥያቄን ትክክለኛነትንና ህጋዊነትን በማረጋገጥ የማስረጃነት ውሳኔ / declaratory Judgment/ ከመስጠት ውጭ ሌላ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ክርክሮች ሁሉ ማስተናገድ አግባብነት ያለው አይደለም።

ሰበሩ በዚህ መዝገብ ላይ “ስለሆነም የወራሽነት ማስረጃ ብቻ እንዲሰጠዉ የጠየቀ አባት ሟች ልጆች ስላሉት ልትወርስ አትችም በሚል ከማስረጃዉ የዘለለ ዉሳኔ መስጠት ተቀባይነት የለም። ለአባት የሟች ልጆች ቢኖሩትም የወራሽነት ማስረጃ እንዲሰጠዉ ከጠየቀ ሊሰጠዉ ይገባል”  ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡

እንደዚህ መፅሐፍ አዘጋጅ በፍ/ብ/ህ/ቁ.996 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች ለመረዳት የሚቻለው የወራሽነት የመስክር ወረቀት የሚሰጠው ወራሽ ለሆነ ሰው ነው፡፡ አንድ ሰው የሟች ወራሽ የሚሆነው ደግሞ በሕግ ወይም በኑዛዜ ሲሆን በዚህ የሰበር መዝገብ ላይ የሟቹ አንደኛ ደረጃ ወራሽ የሆኑ ልጆች እያሉ ለአባት ገላጭ የወራሽነት የምስክር ወረቅት (Declatory Heir Certificate) እንዲሰጠው መወሰኑ አንደኛ ደረጃ ወራሽ የሆኑ ልጆች የሟች አባት ልጆች እያሉ መውርስ የማይችል ሆኖ እያለ የወራሽነት እንደሰጠው መውሰኑ ከሕጉ በተቃራኒ እና ከወራሽነት የምስክር ወረቀት ከሚሰጠበት ዓላማ አንጻር ተገቢነት ያለው ውሳኔ አይደልም፡፡

በሌላ በኩል የወራሽነት የምስክር ወረቀት በሃሰት የተሰጠ ከሆነ እና ተቃውሞ ከቀረበበት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.358 መሰረት የሚቀርብ የመቃወሚያ ክስን አከራክሮ የመወሰን ሥልጣን የፌዴራል ፍ/ቤት እንጅ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ.216496 በሆነ መዝገብ ላይ በቀን 24/09/2014 ዓ.ም የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

የአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤቶች በከተማው የዳኝነት አካል ተደራጅተው በተሻሻለው የከተማ አስተዳደሩ ቻርተር አዋጅ ቁጥር 408/1996 አንቀጽ 2 [1] መሰረት የወራሽነት ፣ የባልና ሚስትነት፣ የሞግዚትነት የምስክር ወረቀት ለማግኘት የሚቀርብ አቤቱታ የማየት የሥረ ነገር ስልጣን እንዳላቸው የሚደነግግ ቢሆንም ይህ ሥልጣናቸው ማስረጃ በተመለከተ የቀረበውን ጥያቄ ትክክለኛነቱን እና ሕጋዊነቱን በማረጋገጥ በማስረጃነቱ ውሳኔ [Declaratory Judgement] ከመስጠት ውጪ ማስረጃው የተሰጠበትን ውሳኔ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 358 መሰረት ተቃውሞ የሚቀርበውን አቤቱታን ተቀብሎ ሙሉ እና ውስብስብ የሆነውን ክርክር ማየትን እንደማይጨምር የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 171061 ፣ 190769 ፣195227 ፣ 196567 እና ሌሎችም በርካታ መዛግብት ላይ ውሳኔ ሰጥቷል። በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች የወራሽነት ውሳኔን በመቃወም የቀረበን ክርክር የማየት የሥረ ነገር ሥልጣን የላቸውም።

የወራሽነት የምስክር ወረቀትን በተመለከተ መቃዎሚያ መቅረብ የማይችል ለመሆኑ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 15 በሰ/መ/ቁ.79871 በሆነ መዝገብ ላይ በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በሌላ በኩል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/ጥር 358 መሰረት የሚቀርብ የፍርድ መቃወሚያ ወራሽነትን ለማረጋገጥ በሚሰጥ ማስረጃ ላይ ሊቀርብ እንደማይችል፤ ይልቁንም በማስረጃውም ምክንያት መብቴ ተነክቷል የሚል አካል ካለ ተገቢን ዳኝነት ከፍሎ ተጓደለብኝ የሚለውን መብት ማረጋገጥ እንዳለበት ወስኗል፡፡

በሌላ በኩል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ.181999 በሆነ መዝገብ ላይ በቀን 27/01/2013 ዓ.ም በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ላይ በገጠር የእርሻ መሬት ላይ የተሰጠን የወራሽነት የምስክር ወረቀት ላይ የመቃዎሚያ ክስ የሚቀርብ ለመሆኑ የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/ጥር 358 መሰረት የፍርድ መቃወሚያ ማቅረብ የሚችለው አካል ቀድሞ በተደረገው ክርክር የሙግቱ አካል ሊሆን ይችል የነበረ ሆኖ እርሱ ተካፋይ ባልሆነበት ክርክር በተሰጠው ውሳኔ መብቱ የሚነካው ማናቸውም አካል ስለመሆኑ እና መቃወሚያውም ሊቀርብ የሚገባው ፍርድ ከመፈፀሙ በፊት ስለመሆኑ ከድንጋጌው ይዘት መረዳት ይቻላል።በሌላ በኩል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/ጥር 358 መሰረት የሚቀርብ የፍርድ መቃወሚያ ወራሽነትን ለማረጋገጥ በሚሰጥ ማስረጃ ላይ ሊቀርብ እንደማይችል፤ ይልቁንም በማስረጃውም ምክንያት መብቴ ተነክቷል የሚል አካል ካለ ተገቢን ዳኝነት ከፍሎ ተጓደለብኝ የሚለውን መብት ማረጋገጥ ያለበት ስለመሆኑ ይኸው ችሎት በሰ/መ/ቁ/79871 ላይ የካቲት 11/2005 ዓ.ም በዋለው ችሎተ አስገዳጅ የህግ ትርጉም ሰጥቷል።

በሰ/መ/ቁ/79871 ላይ ቀርቦ ትርጉም የተሰጠበት ጉዳይ ወራሽነታቸውን በፍርድ ቤት አረጋግጠው ማስረጃውን መሰረት በማድረግ የውርስ ሃብት ነው በሚል የያዙትን ንብረት የሚመለከት ክርክር እንጂ የውርስ ሀብቱ ተለይቶ በሀብቱ ላይ የተሰጠ የወራሽነት ምስክር ወረቀትን የሚመለከት አይደለም። እናም በሁለቱ ጉዳዮች መካከል ተመሳሳይ የህግ እና የፍሬ ነገር ክርክር የለም። ስለሆነም በገጠር የእርሻ መሬት ላይ የተሰጠው የወራሽነት ማስረጃ ሌሎች ተከራካሪዎች በፍርድ መብት ባገኙበት ይዞታ ላይ የተሰጠ ማለትም የወራሽነት ማስረጃ የወሰዱበት ሀብት ሌላ ሰው በፍርድ መብቱን ባረጋገጠበት ሀብት ላይ ከሆነ በንብረቱ ላይ የተሰጠው የወራሽነት ማስረጃ መሰረዝ ያለበት በመሆኑ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 358 ታቃዉሞ አይቀርብበትም ሊባል አይገባም።

ከእነዚህ ሶስት የሰበር ውሳኔች ለመረዳት የሚቻለው ሰበሩ የወራሽነት የምስክር ወረቀትን በተመለከተ ሁለት ፍፁም ተቃራኒ የሆኑ ውሳኔዎችን ማለትም በአንድ በኩል በፍ/ቤት የተሰጠን የወራሽነት የምስክር ወረቀትን በተመለከተ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.358 መሰረት ተቃወሞ ሊቀርብበት አይገባም የሚል ሲሆን በሌላ በኩል በፍ/ቤት የተሰጠን የወራሽነት የምስክር ወረቀትን በተመለከተ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.358 መሰረት ተቃወሞ ሊቀርብበት ይገባል በሚሉት ናቸው፡፡

የተሻለው የትኛው አቋም ነው የሚለውን በተመለከተ አንባቢያን የየራሳቸውን አቋም የሚወስዱት እንደተጠበቀ ሁኖ እንደዚህ መፅሐፍ አዘጋጅ እይታ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.358 ላይ በዚህ ድንጋጌ የመቃዎሚያ ክስ ማቅረብ የሚቻለው የተቃዎሞ ክስ የሚቀርብበት ውሳኔው ከመፈፀሙ በፊት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ደግሞ መብት ገላጭ ውሳኔ እንጅ በቀጥታ ለአፈጻፀም የሚቀርብ ውሳኔ ባለመሆኑ በፍ/ቤት የተሰጠን የወራሽነት የምስክር ወረቀትን በተመለከተ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.358 መሰረት ተቃወሞ ሊቀርብበት አይገባም የሚል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 15 በሰ/መ/ቁ.79871 በሆነ መዝገብ ላይ በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ነው፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ.182152 በሆነ መዝገብ ላይ በቀን 26/01/2013 ዓ.ም በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ላይ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ላይ ተገቢነት የለውም በማለት ክርክር ለማቅረብ የሚችለው የወራሽነት የምስክር ወረቀት ሲሰጥ ተከራካሪ ያልነበር ሰው ለመሆኑ የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

የውርስ አጣሪ ሥልጣን የሟችን ንብረት ማጣራት እና መፈለግ፣ ከሟች ንብረት መብት አለን ባዮችን ወይንም ወራሾችን መወሰን፣ በኑዛዜው መሠረት ተጠቃሚዎችን መለየት፣ የኑዛዜ ስጦታዎችንና ዕዳ መክፈል እና የውርስ ሀብቱን ማስተዳደር መሆኑን ከፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 944 እና 956 ድንጋጌ መገንዘብ ይቻላል። ውርስ ከተጣራ በኋላ የውርስ አጣሪው ሪፖርቱን ለወራሾች እና ፍርድ ቤት ማቅረብ ያለበት መሆኑን የፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 960 ላይ ተመልክቷል። ተጣርቶ የቀረበውን የውርስ አጣሪ ሪፖርት መሠረት በማድረግ ወራሾች የወራሽነት የምስክር ወረቀት ከፍርድ ቤት ማግኘት የሚችሉ መሆኑን የፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 996 ያስገነዝበናል። በወራሽነት የምስክር ወረቀቱ በተለየው መሠረት ወራሾች የውርስ ድርሻ ክፍፍል መጠየቅ የሚችሉ መሆኑን የፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 1062 ያስረዳናል። በክፍፍል ረገድ አለመግባባት ቢፈጠር የወራሽነት የምስክር ወረቀቱ ክሱን ለማቅረብ መብት ወይንም ጥቅም የሚሰጣቸው በመሆኑ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ክስ ለማቅረብ ይችላሉ። በሌላ በኩል በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 999 በተደነገገው መሠረት አንድ ሰው ዋጋ ያለው የወራሽነት ማስረጃ ሳይኖረው ውርሱን ወይንም ከውርሱ አንዱን ክፍል በእጁ ያደረገ እንደሆነ እውነተኛ ወራሽነቱ እንዲታወቅለት የተወሰደበት የውርስ ሀብት እንዲመለስለት የወራሽነት ጥያቄ ክስ ለማቅረብ እንደሚችል ተመክቷል። በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 996(1) መሠረት የሚሰጥ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ለሟቹ ወራሽ የሆነውን ሰዉ እና ከውርሱ የሚያገኘውን ድርሻ የሚያመለክት ማስረጃ እንጅ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ በተደነገገው መሠረት ከሌሎች ሰዎች ጋር ክርክር ተደርጎበት በፍርድ እንዳለቀ ውሳኔ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም። የሟች ትክክለኛ ወራሽ ማን ነው? የሚለው ጭብጥ አከራካሪ በሆነ ጊዜ በተቃራኒ ማስረጃ ሊስተባበል የሚችል እና ተጣርቶ ውሳኔ ሊያገኝ የሚችል ጉዳይ ነው።

የውርስ ንብረት ክፍፍል ጥያቄ በቀረበበት ጊዜ የቀረበውን የውርስ አጣሪ ሪፖርት መቃወም የሚችለው ማስረጃውን ያወጣው ሰው እራሱ ሳይሆን ይህ ማስረጃ መውጣቱን የማያውቅ ነገር ግን ማስረጃው ቀድሞ በመውጣቱ ብቻ ያለው መብት እና ጥቅም እንዳይቀርብበት ለማድረግ ታስቦ እንጅ አምኖ ማስረጃውን ያወጣው ወገን ሃሳቡን በቀየረ ቁጥር የቀደመውን ማስረጃ በሌላ ማስረጃ በማስተባበል ዋጋ ማሳጣት የህጉ ዓላማ አይደለም።ማስረጃ የሚያስፈልገውም ተከራካሪ ወገኖች ያልተስማሙበት እና የተከራከሩበት ፍሬ ነገር ሲኖር ነዉ።

ሰበሩ በዚህ መዝገብ ላይ ከሚከተለው ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡-

በመሆኑም በራሳቸው ፈቃድና ተነሳሽነት ያለማንም አስገዳጅነት ዉርሱን በማጣራት እና የልጅቱ ሞግዚት በመሆን ልጅቷ የሟች ባለቤቴ ልጅ እና ወራሽ ናት በመሆኑም በቤት ግማሽ የሟች ድርሻ ወራሽ ናት በማለት ማስረጃ ወስዶ እራሳቸው የወሰዱትን የወራሽነት ማስረጃ በሌላ ተቃራኒ ወገን እንደቀረበ በማስመስል በክፍፍል ጊዜ የወራሽነት ማስረጃዉ ቢኖርም ልጅቷ የሟች ልጅ አይደለችም ፣የወራሽነት የምስክር ወረቀት ማስረጃ ስለሆነ ሊስተባበል ይችላል፣ ልጅቷም ያሳደግናት እንጂ የሟች ሚስቴ ልጅ አለመሆኗን አምናለች በማለት የሚያቀርበዉ ክርክር ተቀባይነት የለዉም።

ከዚህ የሰበር ውሳኔ ለመረዳት የሚቻለው አብሮ ሰዎች የወራሽነትን ካሳወጁ በኋላ በሌላ ጊዜ የወራሽነት የምስክር ወረቀትን ተቃዎሞ መከራክር የማይቻል ለመሆኑ ሲሆን ይህም ከሙግት አመራር እና ከፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ አንጻር ተገቢነት ያለው ውሳኔ ነው፡፡

 በወራሽነት የምስክር ወረቅ ላይ የዳግም ዳኝነት ክስ ማቅረብ የማይቻል ስለመሆኑ

በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.6 መሰረት አንድ ውሳኔ የተሰጠው በወንጀል ቀመስ ማስረጃዎች ከሆነ ውሳኔውን የሰጠው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ እንደገና ለመከለስ ያከራክራቸዋል፡፡ የወራሽነት የምስክር ወረቀትን በተመለከተ ግን የዳግም ዳኝነት የምይቀርብበት ለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ.228124 በሆነ መዝገብ ላይ በቀን 29/03/2015 ዓ.ም የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

የወራሽነት ማስረጃ አንድ ሰዉ የሟች ወራሽ መሆኑን በማረጋገጥ በፍርድ ቤት የሚሰጥ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ማስረጃዉን የሚሰጠዉ በእርግጥም ማስረጃዉ የተሰጠዉ ሰዉ የሟች ወራሽ መሆን አለመሆኑን አስመልክቶ ተከራካሪ ወገኖችን የሚያቀርቡትን ክርክር መሠረት በማድረግ ጭብጥ ይዞ እና መርምሮ አለመሆኑ ይታወቃል። ይልቁንም የወራሽነት ማስረጃ አንድ ሰዉ የሟች ወራሽ መሆኑን ለማረጋገጥ እንጂ በፍትሐብሔር ሥ/ሥርዓት ህጉ አንቀጽ 3 ላይ በተመለከተዉ አግባብ እንደ ፍርድ የማይቆጠር እና ከወራሽነት ጋር በተያያዘ በፍርድ ቤት በሚደረግ ክርክር በሚቀርብ ተቃራኒ ማስረጃ ሊስተባበል የሚችል ነዉ። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሰ/መ/ቁጥር 18576 ጨምሮ በሌሎች መዝገቦች ላይ የህግ ትርጉም ሰጥቷል።

በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ህጉ አንቀጽ 6 መሠረት የሚቀርብ የዳግም ዳኝነት ጥያቄ አስቀድሞ የተሰጠን ፍርድ ለማስለወጥ ሲሆን፣ የድንጋጌዉ አቀራረጽም በግራ ቀኝ መካከል የቀረበዉን ክርክር መሠረት በማድረግ የፍሬ ነገር ጭብጥ ተይዞ ክርክር ተደርጎበት ፍርድ ያረፈበት ጭብጥ መኖርን ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑ ከድንጋጌዉ ይዘት መገንዘብ ይቻላል። ዓላማዉም ለፍርድ ቤት ቀርቦ መብቱን ለማስከበር ክርክር አድርጎ ክርክሩንም ሊያስረዳ የሚችል ማስረጃ ለማቅረብ ተገቢዉን ትጋት እና ጥረት አድርጎ ነገር ግን በድንጋጌዉ ላይ የተመለከቱት ድርጊቶች በመፈጸማቸዉ ምክንያት ማስረጃዎቹን በወቅቱ ማግኘት ያልቻለን ወይም ክርክሩን ለማስረዳት በሌላኛዉ ተከራካሪ ወገን የቀረበዉ ማስረጃ በሐሰት የተዘጋጀ መሆኑን በወቅቱ ለማወቅ ያልቻለ ተከራካሪ ወገን በዚህ መልኩ አቤቱታዉን አቅርቦ መብቱን በማስከበር እንዲችል በማድረግ ፍትሕ የማግኘት መብቱን ለማረጋገጥ ነዉ።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ.228124 በሆነ መዝገብ ላይ በቀን 29/03/2015 ዓ.ም በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ላይ በወራሽነት የምስክር ወረቀት ላይ የዳግም ዳኝነት ሊቀረብ የማይገባ ለመሆኑ በሚከተለው አግባብ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡-

ስለሆነም ተጠሪ የሟች ወራሽ ስለመሆናቸዉ ማስረጃ የተሰጣቸዉ ቢሆንም በእርግጥም ከሟች የተወለዱ መሆን አለመሆኑን በተመለከተ ክርክር ቀርቦ፣ ጭብጥ ተይዞ እና ተመርምሮ የመጨረሻ ዉሳኔ ያልተሰጠበት በመሆኑ አመልካች በሌላ አግባብ ክርክራቸዉን አቅርበዉ መብታቸዉን ማስከበር የሚችሉበት ዕድል አለ። ስለሆነም በወራሽነት ማስረጃ ላይ የዳግም ዳኝነት አቤቱታ ማቅረብ የጉዳዩን ባህርይ፣ ከዳግም ዳኝነት ጋር በተያያዘ በፍ/ብ/ሥ/ሥርዓት ህጉ አንቀጽ 6 ላይ የተመለከተዉን ድንጋጌ ይዘት እና ዓይነተኛ ዓላማ መሠረት ያላደረገ ነዉ።              

የቁም ስጦታ፣ ኑዛዜ፣ የኑዛዜ ሥጦታ እና የክፍያ ደንብ ልዩነት

1.    የኑዛዜ ስጦታ (Legacy) እና የክፍያ ደንብ (Rule of Partition) ልዩነት

በተግባር በፍርድ ቤት ከሚቀርቡ ክርክሮች ለመረዳት እንደሚቻለው የኑዛዜ ስጦታ እና የክፍያ ደንብ በሙግት ሂደት በመደበላለቅ የሚታቱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ የኑዛዜ ስጦታ እና የክፍያ ደንብ በፍርድ ቤት በክርክር ሂደት እጅግ ውስብስብ በሆነ አግባብ ለችሎት የሚቀርቡ በመሆናቸው እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በርከት ባሉ መዛግብት ክርክር ተደርጎባቸው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ተመሳሳይነታቸውን እና አንድነታቸውን በዝርዝር እንደሚከተለው እንቃኛለን፡፡

የኑዛዜ ስጦታ እና የክፍያ ደንብ የሚባሉት ፅንሰ-ሐሳቦች የሁለቱም ተመሳሳይነት ሁለቱም በሟች ኑዛዜ የሚደረግ የግል ተግባራት መሆናቸው ነው፡፡

የኑዛዜ ስጦታ እና የክፍያ ደንብ ልዩነታቸው የሚከተሉት ናቸው፡-

1ኛ ኑዛዜ የተደረገለት ሰው በሕግ የሟች ወራሽ መሆን/አለመሆን

ከፍ/ብ/ህ/ቁ.913 እና 1117 እስከ 1123 ያሉትን ድንጋጌው በማንበብ መረዳት የሚቻለው የኑዛዜ ስጦታ ሟች በኑዛዜ ካሉት የግል ንብረቶች መካከል አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆነ ንብረት ወራሽ ላልሆኑ ሰዎች ንብረቱን ከሞተ በኋላ እንዲተላለፍለት የሚያደርግበት መንገድ ነው፡፡ በሌላ በኩል የክፍያ ደንብ ደግሞ ሟች በኑዛዜው ላይ ከውርስ ሃብቱ መካከል አንዱ ወይም ከአንድ በላይ የሆነውን በሕግ የሟች ወራሽ ለሆነ ሰው እንዲወስድ የሚያደርግበት አሰራር ነው፡፡

2ኛ በኑዛዜ በተሰጠው ገንዘብ መጠን ልክ ከውርስ ሃብቱ ላይ የሚቀነስ መሆን/አለመሆን

በኑዛዜ ላይ የተደረገ የክፍያ ደንብ ጥቅሙ በኑዛዜው ላይ ለአንዱ ወራሽ እንዲወስድ የተገለፀውን ንብረት የሚወስደው በኑዛዜው ላይ የተገለፀው ወራሽ ሲሆን የሌሎቹ ወራሾች መብት በዚህ በኑዛዜ ለአንዱ ወራሽ በተሰጠው ግምት ልክ ከሌላው የውርስ ሀብት የመወሰድ እንጅ ይህንን በድንብ ክፍያ መሰረት የተሰጠውን ወራሽ ንብረት ወደ ውርሱ እንዲመለስ እና የውርስ ሃብት እንዲሆን የመጠየቅ መብት የላቸውም፡፡ በመሆኑም በክፍያ ደንብ መሰረት ንብረቱን እንዲወስድ የተደረገ ወራሽ በምትኩ ከሌላው የውርስ ሃብት ላይ በክፍያ ደንብ በተሰጠው የንብረት የገንዘብ መጠን ልክ ከውርስ ሃብቱ ላይ የሚቀነስበት ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል የኑዛዜ ስጦታ ሲሆን ስጦታ ተቀባዩ በሚወስደው ንብረት ልክ ከውርስ ሃብቱ የሚቀነስበት ገንዘብ የለም፡፡ ምክንያም የኑዛዜ ስጦታ ተቀባዩ ከጀምሩ የሟች ወራሽ ባለመሆኑ ሊወስድ የሚችለው ሟቹ በኑዛዜ የሰጠውን ንብረት ብቻ በመሆኑ እና ከውርሱ ሃበት ላይ መብት የሌለው በመሆኑ ነው፡፡

3ኛ የኑዛዜ ሥጦታ ተቀባዩ ከክፍያ ደንብ ወራሹ ቀድሞ ንብረቱ የሚሰጠው ስለመሆኑ

የኑዛዜ ስጦታ በውርስ ማጣራት ሂደት እና የክፍያ ደንብ ደግሞ በውርስ ሃብት የድርሻ ክፍፍል አግባብ ተፈጻሚነት ያላቸው ለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ በቅፅ 08 በሰ/መ/ቁ.18394 ላይ የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

ከፍ/ብ/ህ/ቁ.1047 ድንጋጌ እንደምንገነዘበው በመርህ ደረጃ ማንም ሰው ምንም መብት በሌለው ንብረት ላይ የተናዘዘ እንደሆነ የተሰጠው ኑዛዜ ዋጋ አይኖረውም። ነገር ግን በልዩ ሁኔታ ሟች ኑዛዜ በሚያደርግበት ንብረት ላይ ምንም መብት የሌለው መሆኑን እያወቀ ስጦታ የሰጠው እንደሆነ የስጦታው ህጋዊነት የፀና ይሆናል። በመሆኑም የተናዘዘበት ንብረት ላይ መብት ባይኖረውም የኑዛዜ ስጦታው የተደረገው ይህ መብት እንደሌለው እያወቀ ከሆነ ኑዛዜው ሊፈርስ የሚገባው አይሆንም። አንድ ሰው በአንድ ንብረት ላይ መብት እንደሌለው እያወቀ የተናዘዘ እንደሆነ ኑዛዜው የሚፀና ከመሆኑም ባሻገር የውርስ አጣሪው ከውርሱ ሃብት በዋጋ ተመጣጣኝ የሆነ ንብረት ወይም ገንዘብ ለስጦታ ተጠቃሚው መስጠት አለበት። ነገር ግን ይህ ደንብ ተፈፃሚ የሚሆነው ለውርስ ስጦታ/Legacy/ ብቻ ነው እንጅ ለክፍያ ደንብ/rule of partiton/ አይደለም። አንድ ሰው ከውርስ ሃብቱ መካከል አንድን ንብረት ለወራሹ መስጠቱ የኑዛዜ ስጦታ አያሰኘውም። ይህ ዓይነት ኑዛዜ እንደ አንድ የክፍያ ደንብ ነው። አንድ አውራሽ ለወራሹ አንድን ንብረት ቢናዘዝለት የኑዛዜው አፈፃፀም የስጦታ /Legacy/ አፈፃፀምን በመከተል ሳይሆን የክፍያ ደንብ /partion/ በመከተል የሚከናወን ይሆናል። ይህም ከፍ/ብ/ህ/ቁ 913 ላይ የምንረዳው ነው። ተናዛዡ የተናዘዘለት ሰው ወራሽ ከሆነ ኑዛዜው የስጦታ ውል ሳይሆን የክፍያ ስርዓት የያዘ ነው ማለት ነው። ኑዛዜው ስጦታን/ Legacy/ የሚመለከት ከሆነ ከፍ/ብ/ህጉ አንቀጽ 942 ጀምሮ ባሉ አንቀጾች መሰረት በማጣራት/liquidation/ ስርዓት የሚከናወን ሲሆን የክፍያ ደንብ ክፍፍል /Partition/ ግን ከአንቀጽ 1060 ጀምሮ ባሉ ድንጋጌዎች መሰረት የሚስተናግድ ነው። ኑዛዜው የኑዛዜ ስጦታ ነው ወይስ የክፍያ ደንብ የሚለውን ለመለየት የኑዛዜው ተጠቃሚ የተናዘዙ ወራሽ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ማየት ነው። ተናዛዡ ሃብቱን ለወራሾች በኑዛዜ ሲያከፋፍል ተወላጅ የሆነ ሰው ከሩብ በላይ ጉዳት የደረሰበት እንደሆነ ክፍፍሉ /ኑዛዜው/ እንዲቀር ለመጠየቅ ይችላል።

ከዚህ የሰበር አስገዳጅ የሕግ ትርጉም እና የውርስ ድንጋጌዎች ለመረዳት የሚቻለው በዚህ መፅሐፍ በምዕራፍ 7/ሰባት/ ላይ በዝርዝር እንደተቀመጠው ለኑዛዜ የስጦታ ተቀባይ የተሰጠው ንብረት ልክ እንደ ውርስ ዕዳ ተቆጥሮ በሟች የውርስ ዕዳ አከፋፈል ቅደም ተከተል መሰረት በውርስ አጣሪው የሚከፈል/የሚሰጥ ሲሆን ለወራሽ በክፍያ ደንብ የተሰጠው የውርስ ሃብት የሚከፈለው የውርስ ሃብቱ ተጣርቶ ካበቃ በኋላ በድርሻ ክፍፍል በሚቀርብ ክስ ወይም ስምምነት ነው፡፡ በመሆኑም በክፍያ ደንብ የተሰጠው የሟች የሕግ ወራሽ ንብረቱ የሚሰጠው የኑዛዜ ስጦታ ተጠቃሚ የሆነው ሰው በኑዛዜው መሰረት የተሰጠው ንብረት ከተሰጣ በኋላ የተረፈ የውርስ ሃብት ካለ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑ በክፍያ ደንብ ከተሰጠው ወራሽ ይልቅ የኑዛዜ ስጦታ የተሰጠው ወራሽ ከውርስ ሃብቱ በኑዛዜው መሰረት ሥጦታው ቀድሞ የሚከፈለው ይሆናል፡፡

2.     የኑዛዜ ስጦታ እና የክፍያ ደንብ ከውርስ መነቀል እና በክፍያ ስጦታ ከሚደርስ ጉዳት ጋር ያላቸው ግንኙነት

በዚህ መፅሐፍ በተለያዩ ምዕራፎች ውስጥ ከውርስ መነቀለ እና በክፍያ ስጦታን በተመለከት በጥልቀት ተዳሷል፡፡ በዚህ ንዑስ ርዕስ ደግሞ እነዚህ ፅንሰ-ሐሳቦች ከኑዛዜ ሥጦታ እና ከክፍያ ደንብ ጋር ያላቸውን ቁርኝት ተዳሷል፡፡ የኑዛዜ ስጦታ እና የክፍያ ደንብ የሚሉትን ሁለት የውርስ ሕግ ፅንሰ-ሐሳቦች የሚፈጠሩት በሟች ኑዛዜ በመሆኑ ከውርስ መነቀል እና ከክፍያ ማነስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ በቅፅ 11 በሰ/መ/ቁ.57836 ላይ የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

በኑዛዜ የሚከናወኑ ተግባሮች የኑዛዜ ስጦታ(legacy) ወይም የክፍያ ደንብ (rule of partiton) ሊሆኑ ይችላሉ። በመርህ ደረጃ አንድ ሰው ከውርስ ሀብቱ መካከል አንድን ንብረት ለወራሾቹ መስጠቱ የኑዛዜ ስጦታ አያሰኘውም። ይህን አይነት ስጦታ ህጉ የሚቀበለው እንደ አንድ የክፍያ ደንብ ነው። በመሆኑም አንድ አውራሽ ለወራሹ አንድ ንብረት ቢናዘዝለት የኑዛዜው አፈጻጸም የስጦታ (legacy) አፈጻጸም በመከተል ሳይሆን የክፍያ ደንብ (partition) በመከተል የሚከናወን ነው። ሆኖም በኑዛዜው ላይ የሚሰጠውን ክፍያ መጠን በመገለጹ ብቻ ሁል ጊዜ የክፍያ ደንብ ነው ሊባል የሚቻል አይሆንም። የተሰጠው የንብረት መጠን ከሟቹ የውርስ ሀብት ግምት ጋር ታይቶ ውጤቱም በዚህ እረገድ መለየት አለበት። በሌላ አነጋገር ሟቹ በኑዛዜው ላይ የሚያሰፍረው የንብረት መጠን ከሟቹ የውርሰ ንብረት መጠን ጋር እየታየ የመነቀል ጉዳይ ነው ወይስ የክፍያ ማነስ? የሚለው ነጥብ የሚለይ ይሆናል። የባልና ሚስት የጋራ በሆነ ንብረት ላይ አንደኛው ወገን በኑዛዜው ንብረቱን በሰጠ ጊዜ በኑዛዜው ፍርስ መሆን አለመሆን ላይ ተናዛዡ በንብረቱ ላይ መብት ያለው መሆን አለመሆኑን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ንብረቱ የጋራ መሆን አለመሆኑ ላይ የነበረው ግንዛቤ ውጤት ይኖርዋል። ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1047 (1) እና (2) መገንዘብ የሚቻለው ኑዛዜ ፍርስ ሊሆን የሚችለው ተናዛዡ ስጦታ ባደረገበት ንብረት ላይ መብት እንደሌለውና ይህንም ያውቅ እንዳልነበር ሲታወቅ ብቻ ነው። በኑዛዜ የተሰጠን ስጦታ የክፍያ ደንብን በመከተል ለመፈጸምና እና የክፍያ ማነስ ነው በማለት በክፍያ ደንብ ድንጋጌዎች ለማስተካከል በፍ/ብ/ህ/ቁ 1117 እና 1123 ጥምር ንባብ መሰረት ኑዛዜ የተደረገለት ሰው የሟቹ ተወላጅ ወይም ወደ ላይ የሚቆጠር ዘመድ መሆን አለበት።

የኑዛዜ ስጦታ እና የክፍያ ደንብ በሙግት ሂደት በመደበላለቅ የሚምታቱ ጉዳዮችን የሚከተሉትን ምሳሌዎችን የሚያስረዱ በመሆኑ ምሳሌዎቹን በስርዓት መመርመሩ ተገቢ ነው፡፡

ለምሳሌ 1፡- አንድ ሟች የግል ንብረቱ የሆኑ አንደ ቤት ግምቶ 80 ሚሊዮን ብር፤ ሁለት መኪናዎች ግምታቸው 3 ሚሊዮን እና 5 ሚሊዮን ብር የሆኑ ንብረቶች ብቻ ያሉት ሲሆን አራት ልጆች እያሉት ቤቱን እኔ ከሞትኩኝ በኋላ ቤቱን በሕግ ወራሽ ላልሆነ ጓድኛው ይሰጣቸው በማለት በኑዛዜው ላይ የተገለፀ ቢሆን ይህን ኑዛዜን ልጆች ከውርስ የነቀልን በመሆኑ ይፈረስልን ማለት ይችላሉ ወይስ አይችሉም?

ለምሳሌ 2፡- አንድ ሟች የግል ንብረቱ የሆኑ አንደ ቤት ግምቶ 80 ሚሊዮን፤ ሁለት መኪናዎች ግምታቸው 3 ሚሊዮን እና 5 ሚሊዮን ብር የሆኑ ያሉት ሲሆን ሶስት ልጆች እያሉት በስጦታ ማከፋፈል በተደረገ ኑዛዜ ቤቱን በኑዛዜ ለበኩር ልጁ በተለየ ሁኔታ ስለሚወደው በኑዛዜ ቢሰጣቸው እና ለሴቷ ልጅ የ5 ሚሊዮን ብር መኪናውን እና ለቀሪው አንድ ውንድ ልጅ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመተውን መኪና እንዲሆን በኑዛዜው ላይ ቢገልፅ ይህን ኑዛዜን ልጆች በስጦታ መጎዳት መኪና የተሰጣቸው ልጆች ኑዛዜውን ይፈረስልን ማለት ይችላሉ ወይስ አይችሉም?

ከእነዚህ ምሳሌዎች ላይ ለመረዳት እንደሚቻለው በምሳሌ አንድ ላይ የኑዛዜ ስጦታው ተደረገው የሟች ሕጋዊ ወራሽ ላልሆነ ግለሰብ ልዩ የኑዛዜ ሥጦታ በማድረግ ከውርስ መንቀል የማይቻል ለመሆኑ በዚህ መፅሐፍ በምዕራፍ ሰባት ላይ በዝርዝር እንደተመለከትነው ሟች ወራሽ ላልሆነ ጓድኛው 80 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቤት በመስጠት ወራሽ ልጆቹን ከውርስ ሊነቅል የማይገባ በመሆኑ ኑዛዜው ፈራሽ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል በምሳሌ ሁለት ደግሞ በተደረገ የስጠታ ክፍያ መኪና የተሰጣቸው ልጆች በሕጉ መሰረት ከሩብ በታች የሚደርሳቸው በመሆኑ ኑዛዜውን በፍ/ብ/ህ/ቁ.1123 መሰረት እንዲፈርስ መጠየቅ ይችላሉ፡፡

3.     የኑዛዜ (Will) እና የቁም ስጦታ (Donation enter vivos) መምታታት 

ከፍ/ብ/ህ/ቁ.2427 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች ለመረዳት እንደሚቻለው የስጦታ ውል አንድ ሰው በሕይወት እያለ ንብረቱን ለሌላ ሰው እንዲተላለፉ የሚፈፅማቸው ተግባት ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በዚህ መፅሐፍ በተለያዩ ምዕራፎች ከላይ በስፋት እንደተመለከትነው ኑዛዜ አንድ ሰው ከሞት በኋላ ንብረቱን ለሚፈልገው ሰው የሚያስተላልፍበት የሚያርገው ግላዊ የሆነ የሕግ ተግባር (personal juridical act) ነው፡፡ የሁለቱ ተመሳሳይነት ሁለቱም አንድ ሰው የራሱን ንብረት ራሱ ወዶ እና ፈቅዶ ያለማም አስገዳጅነት ለሌላ ሰው የሚያስተላልፍበት መንገዶች መሆናቸው ነው፡፡ ሁለቱም ተግባራት በነጻ ያለምንም ዋጋ ንብረትን ለሌላ ሰው በስጦታ የማስተላለፊያ መንገዶች ናቸው፡፡

የኑዛዜ እና የቁም ስጦታ ልዩነታቸው ኑዛዜ የሚፈፀመው ኑዛዜ አድራጊው ከሞት በኋላ ሲሆን የቁም ስጦታ የሚፈፀመው ንብረት ሰጭው ከመሞቱ በፊት በሕይወት እያለ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሁለቱ ልዩነት ኑዛዜ በሕግ ፊት የፀና ለመሆን የኑዛዜ ተቀባዩን ፍቃድ የማይጠይቅ ሲሆን የስጦታ ውል በሕግ ፊት የፀና ለመሆን የሥጦታ ተቀባዩን ፍቃድ የሚጠይቅ ነው፡፡ ምክንያቱም በፍ/ብ/ህ/ቁ.1678(ሀ) እና 1679 መሰረት የቁም ስጦታ ከውል መካከል አንዱ በመሆኑ እና ውል ደግሞ የሚደረገው ሁለት እና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል ሁኖ ውሉ በሕግ ተቀባይነት ያለው እና የፀና እንዲሆን ተዋዋዮቹ ፍቃዳቸውን ወድ እና ፈቅደው የሰጡ መሆን አለባቸው፡፡ ከቁም ሥጦታ በተቃራኒ ኑዛዜ በሕግ ፊት የፀና ለመሆኑ ኑዛዜ ሲደረግ የኑዛዜ ተቀባዩ( ኑዛዜ የተደረገለት ሰው) ፍቃዱን መስጠት የማይጠበቅበት ሲሆን ኑዛዜ የተደረገለት ሰው ካለፈለገ ኑዛዜ አድራጊው ሲሞት በኑዛዜ ወራሽ ቢሆንም የሟችን ውርስ መተው (renounciation of succession) ያደርጋል፡፡

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ፍ/ቤቶች ከኑዛዜ ጋር በተያያዘ ለፍ/ቤት ክርክር መነሻ እየሆነ ያለው ተከራካሪዎቹ ሰነዱን ኑዛዜ ነው ወይስ ስጦታ በሚል ሲሆን በእርግጥም አንዳንድ ጊዜ የቀረበውን ሰነድ ስጦታ ነው ወይስ ኑዛዜ የሚለውን ለመለየት ብዥታ እየፈጠሩ አስቸጋሪ ሲሆን በተጨባጭ/በተግባር ይታያል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች የስጦታ ውሉን ኑዛዜ ነው በማለት የሚከራከሩት በተለይ በተራ ክፍያ ልጆች ከሆኑ ያለምክንያት ከውርስ ነቅሎኛል በማለት የቀረበውን ሰነድ ፈራሽ እንዲሆን ካላቸው ሃሰብና ፍላጎት የተነሳ ነው፡፡ በመሆኑም የቁም ሥጦታን ተከራካሪዎች ኑዛዜ ነው በማለት ለክርክር የሚያቀርቡት ኑዛዜ ከሆነ ከውርስ ሟች ነቅሎኛል ብሎ ለማስፈረስ እና በቁም ሥጦታ ከተላለፈው ንብረት ላይ ተጠቃሚ ለመሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም በሰ/መ/ቁ.193046 በቀን 28/11/2013 ዓ.ም እና በሰ/መ/ቁ.236850 በቀን 29/09/2015 ዓ.ም ከተሰጡ ውሳኔዎችን ለመረዳት እንደሚቻለው እና በዚህ መፅሐፍ በዚህ ምዕራፍ ከዚህ ዝቅ ብለን በዚህ ንዑስ ርዕስ በስፋት እንደተዳሰሰው በቁም ሥጦታ ሕጋዊ ወራሽን ከወራሽነት መንቀል የሚቻል በመሆኑ ነው፡፡

ይህ የኑዛዜና የስጦታ መምታታት እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት/ሰ/ሰ/ችሎት ድረስ ቀርቦ ሰበር ችሎቱም በቅፅ 5 በሰ/መ/ቁ.32337 በሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉም ስጦታ ሁለት አይነት ሲሆኑ ሟች በህይወት እያለ ተፈጻሚ የሚሆን ስጦታ (Donation enter vivos) እና ሟች ከሞተ በኋላ ተፈፃሚ የሚሆን ስጦታ (donation martis causa) ሲሆኑ በኢትዮጵያ ህግ እውቅና የተሰጠው ሟች ሳይሞት ተፈጻሚ የሚሆነው የስጦታ ውል ነው በማለት ወስኗል፡፡

ከዚህ የሰበር ውሳኔ  ላይ ለክርክር የቀረበው ሰነድ ርዕሱ የሚለው “የቁም ኑዛዜ ስጦታ” ሲሆን ይህ ማለትም ይህ ስጦታ የሚፈፀመው ሟች ከሞተ በኋላ በመሆኑ “ኑዛዜ” የሚለው ቃል ስለሚያሳይ ይህ ሰነድ ኑዛዜ ነው በማለት ሰበሩ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ በእርግጥ ይህ ሰነድ በቁም ሲታይ እና ሲነበብ “ኑዛዜ” እና “ስጦታ” የሚሉ ቃላትን አጣምሮ የያዘ በመሆኑ ለትርጉም ቢጋለጥና ቢያምታታ አስገራሚ አይሆንም፡፡

ከዚሁ የሰበር ውሳኔ ላይ ለመረዳት እንደሚቻለው ኑዛዜ እና ስጦታ እንዲምታቱ ካደረጉት ምክንያቶች አንድ ሟች የሚያደርገው ተራ የደንብ ክፍያ (an assignment of portion of succession or property forming part of sucession) የሚለው የውርስ ህግ ጽንሰ ሀሳብ ነው፡፡ ከላይ በዚህ መፅሐፍ በዚህ ምዕራፍ በስፋት እንደተዳሰሰው ተራ የደንብ ክፍያ ማለት አንድ ኑዛዜ አድራጊ በኑዛዜው ላይ አንድን ንብረት ከሌሎቹ የሕግ ወራሾች በተለየ መልኩ አንዱ የሕግ ወራሽ እንዲወስዱ (በውርስ ሃብት ክፍፍል ጊዜ ለእርሱ እንዲሰጠው) የሚያደርግበት የኑዛዜ ቃል ሲሆን የሌሎቹን ድርሻ በሌላ ንብረት በዓይነት ወይም የዋጋውን ግምት ብር በመክፈል በማካካስ ንብረቱን ቅድሚያ የሚወስድበትን መብት (The right of Priority) የሚሰጥ ነው፡፡ ከላይ በዚህ መፅሐፍ በዚህ ምዕራፍ በስፋት እንደተመለከትነው እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበሩ ሰሚ ችሎትም በቅፅ 5 በሰ/መ/ቁ.32337 ላይ ትርጉም እንደሰጠው ሆነ በፍ/ብ/ሕ/ቁ.913 ላይ እንደተደነገገው ተራ የደንብ ክፍያ ሌሎቹን ወራሾች ከውርስ የሚነቅል አይደለም፡፡

ምሳሌ፡- አንድ ሟች አንድ ትልቅ ህንፃ እና ኢንዱስትሪ ብቻ ቢኖረውና 3 ልጆች ቢኖሩት ህንጻውን የበኩር ልጅ ይወስድ ቢል እና ኢንደስትሪው የህንፃው 2 (ሁለት) እጥፍ ዋጋ ቢኖረው ሌሎቹ ልጆች ኢንደስትሪውን ወስደው መከፋፈል ይችላሉ እንጂ ለታላቅ ወንድማቸውን የተሰጠውን ህንጻውን መጠየቅ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም  አባታቸው ህንፃውን በተራ ደንብ ክፍያ መርህ መሰረት ለታላቅ ወንድማቸው ቅድሚያ የመውሰድ መብት ሰጥቶታል፡፡

የኑዛዜ እና የስጦታ ጉዳይ በቀረበው የሟች ሰነድ ላይ ክርክር ሲነሳ የሰነዱን አጠቃላይ ይዘት እና ሟች ሰነዱ መቼ መፈጸም እንደሚፈለግ ማለትም በህይወት እያለ ከሆነ ስጦታ መሆኑን ከሞተ በኋላ ከሆነ ኑዛዜ መሆኑን እና በሕይወት እያለ ከሆነ ስጦታ ለመሆኑ አጢኖ ዕልባት መስጠቱ ተገቢና ምክንያታዊ ነው፡፡

የቁም ስጦታ ከውርስ መንቀል እና ከስጦታ መጎዳት ጋር ያለው ግንኙነት

በፍርድ ቤት ክርክር በተግባር ሙግት የሚቀርበው አንድ ሟች ለሕጋዊ ወራሾቹ ሆነ ለኑዛዜ ስጦታ ተቀባዩ የቁም ስጦታ አድርጎ ከሞተ በኋላ ከሟች ምንም ንብረት ያላገኙ ወይም ከሟች የውርስ ሃብት ከአንድ አራተኛ በታች በኑዛዜ የተሰጣቸው የሟች ሕጋዊ ወራሾች በሟች የቁም ስጦታ ከውርስ የተነቀልን በመሆኑ የሟች የቁም ስጦታ ይፈረስልኝ የሚል ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ሟች በሕይወት እያለ ባደረገው የቁም ስጦታ ንብረቱን ለሌላ ሰው ቢያስተላለፍ የሟች ሕጋዊ ወራሾች ከውርስ ተነቅለናል ወይም በመጎዳት (Lesion) መልኩ በሚያቀረቡት ክስ የቁም ስጦታው የሚፈርስበት የሕግ መሰረት አለ ወይስ የለም የሚለውን ማየቱ እና ምላሽ መስጠቱ የግድ የሚል ነው፡፡ ይህንን አከራካሪ ነጥብ በተመለከት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተለያዩ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሰጠ በመሆኑ እንደሚከተለው እንቃኘዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ በሰ/መ/ቁ.193046 በሆነ መዝገብ ላይ በቀን 28/11/2013 ዓ.ም በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በቁም ስጦታ የተላለፈ ንብረትን በተመለከተ ከሟች ወደ ስጦታ ተቀባዩ የቤቱ ስመ-ሃብት ባይዛወርም የውርስ ሃብት ሊሆን የማይገባ ለመሆኑ ተከታዩን ውሳኔ ሰጥቷል፡-

በስጦታ ውሉ መሰረት በስጦታ የተላለፈዉ የቤቱ ስመ-ሀብት ወደ ስጦታ ተቀባይ አለመዞሩ ስጦታውን ከሟች ሞት በኋላ ተፈፃሚ እንዲሆን የሚያደርግ አይደለም። ሟች ያደረጉት ስጦታ መሆኑ ከተረጋገጠ፤ ስለኑዛዜ የተነገሩት ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት የሌላቸው በመሆኑ ስጦታው ከውርስ ነቅሎናል በማለት የሚቀርብ ክርክር የሕግ ድጋፍ ያለው አይደለም። የማይንቀሳቀስ ንብረት ስጦታ የግልፅ ኑዛዜ አሰራርን ከመከተል ባለፈ በውል አዋዋይ ፊት አቅርቦ ማስመዝገብን ሕጉ ግዴታ ስለማያደርገው የምዝገባ ሥርዓቱን በተመለከተ የሚቀርብ ክርክር ተቀባይነት ያለው አይደለም። በመሆኑም ሟች የፍትሐብሔር ሕጉን ቁጥር 881 መሰረት አድረገዉ በአራት ምስክሮች ፊት አድርጎ እና ተነቦ ምስክሮች ከፈረሙበት በኋላ የነበራቸውን ብቸኛ ንብረት አከራካሪውን ቤት በሕይወት እያሉ በስጦታ ያስተላለፉት ከሆነ ከሞቱ በኋላ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 826(2) መሰረት የሚተላለፍ መብት ባለመኖሩ ወራሾች የሚያቀርቡት የውርስ ድርሻ ጥያቄ ተቀባይነት የለዉም።

ከዚህ የሰበር አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ለመረዳት የሚቻለው ሟች በቁም ስጦታ ንብረቱን ካስተላለፈ የሟች ሕጋዊ ወራሾች ከውርስ በሥጦታ ውል ስለተነቀልን የሥጦታ ውሉ ፈራሽ ይደረግልኝ ማለት አይቻልም፡፡ ይህንን በተመለከተ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ በሰ/መ/ቁ.236850 በሆነ መዝገብ ላይ በቀን 29/09/2015 ዓ.ም በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በቁም ስጦታ ንብረትን በማስተላለፍ ከውርስ መንቀል የሚቻል ለመሆኑ የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

የኑዛዜ አድራጊው ለተወላጅ አስቀድሞ በስጦታ ንብረትን ማስተላለፉ የስጦታ ተጠቃሚን በኑዛዜ ከውርስ ሐብት ለመንቀል እንደበቂ ምክንያት ሊወሰድ የሚችል ነው። ባዶ መሬት የመንግስት እና የህዝብ ሐብት መሆኑ በሕገ-መንግስቱ እና በሌሎች ሕጎች የተገለጸ ጉዳይ ነው። ይህ ማለት ግለሰቦች በመሬት ላይ የሚኖራቸው መብት የመጠቀም እንጂ የባለቤትነት መብት አይደለም። በዚህም መሰረት ሟች የራሳቸው ይዞታ የነበረን መሬት ለወራሽ መስጠታቸው ሟች በይዞታው ላይ የነበራቸውን የመጠቀም መብት ማስተላለፋቸውን የሚያሳይ ነው። ስለዚህ ወራሽ በሟች እናታቸው ባዶ መሬት ተሰጥቷቸው ቤት መስራታቸውን ሳይክዱ ባዶ መሬት መሰጠቱ ንብረት እንደተሰጣቸው ተደርጎ ሊቆጠር እንደማይችል አድርገው የሚያቀርቡት ክርክር ተቀባይነት የለውም፡፡

ከላይ ከተሰጡት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በተጨማሪ ሰበሩ የጋራ የሆነ ቤትን አንድ ወላጅ ሲሞት ሌላኛው ወላጅ የሟች ድርሻ ጭምር የቁም ሥጦታ ካደረገ የሟችን ድርሻ በተመለከተ የሟች ወራሾች የቁም ስጦታውን በማስፈረስ መጠየቅ የሚችሉ ለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ በሰ/መ/ቁ.186715 በሆነ መዝገብ ላይ በቀን 30/06/2013 ዓ.ም የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

አስቀድሞ የእናት እና የአባታቸዉ የነበረ ቤት አባታቸዉ ሲሞት የንብረቱ ተጋሪ የሟች ሚስት ለአንደኛ ልጇ በስጦታ  ስለሰጡ እና ስመ-ሃብቱ በዚችዉ ስጦታ ተቀባይ ልጅ ስም ተመዝግቦ የሚገኝ እንዲሁም ስጦታ ሰጪዋ እናታቸዉ የስጦታ ውሉ ፈራሽ ነው ተብሎ እንዲወሰን ጠይቀው ክሳቸው በይርጋ ቀሪ የተደረገባቸዉ ቢሆንም የሌሎች ወራሾች የልጆች ሞግዚት የሆኑት እናታቸዉ በስጦታ ካስተላለፉ እንኳ የራሳቸውን ድርሻ ብቻ ከመሆኑ አንጻር በስጦታ ተሰጥቶ በአንደኛዋ ልጅ በስማቸው ተመዝግቧል በማለት በቤቱ ላይ የውርስ ድርሻ ያላቸው ልጆች ሌላዋ ወራሽ በንብረቱ ላይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ይዘዋል ስመ-ሃብቱንም ወደ ራሳቸው አዙረዋል ስለሆነም ሊጠይቋቸው አይገባም የሚባልበት የህግ አግባብም የለም። የስጦታ ሰጪዋ እናት የስጦታ ውሉ ፈራሽ ነው ተብሎ እንዲወሰን ጠይቀው ክሳቸው በይርጋ ቀሪ ሆኗል ቢባል እንኳ ሌሎች ልጆች የአባታቸዉ ዉርስ እንዲጣራ ክርክር እንዳያቀርቡ አስቀድሞ እናት በስጦታ ተቀባይዋ ልጅ ላይ የስጦታ ውሉ ፈራሽ ነው እንዲባል አቅርበዉ ክሳቸው በይርጋ ቀሪ ሆኗል መባሉ እንቅፋት የሚሆን አይሆንም። እናት በስጦታ ተቀባይዋ ልጃቸዉ ላይ የስጦታ ውሉ ፈራሽ ነው እንዲባል ባቀረቡት ክስ የሌሎች ወራሾች መከራከሪያ መቅረብ ነበረበት የሚባልበት የህግ ምክንያትም የለም።

ስለሆነም አከራካሪው ይዞታና ቤት የወራሾች አባት እና እናታቸዉ የነበረ መሆኑ አከራካሪ ባልሆነበት፤ ሟች አባታቸዉ ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ አካለ መጠን ያላደረሱት ወራሾች በህግ በተወሰነው ጊዜ ውስጥ በሞግዚታቸው በእናታቸዉ በኩል ወራሽ መሆናቸውን ያስወሰኑ ከሆነ፤ የልጆች ሞግዚት የሆኑት እናት በሞግዚትነት የሚያስተዳድሯቸውን ልጆች ሃብት ለልጆቹ መልካም አስተዳደግ ሊያውሉት ከሚችሉ በቀር የውርሱን የጋራ ንብረት እንደራሳቸው ንብረት በስጦታ ሊያስተላልፉ የማይችሉ በመሆኑ፤ እንዲሁም የሟች ልጆች እስካሁንም ድረስ በአከራካሪው የውርስ ቤት የሚኖሩ መሆኑ ባልተካደበትና በተረጋገጠበት ሁኔታ፣ የውርሱን ሃብት እናታቸዉ በስጦታ ለአንደኛ ልጃቸዉ አስተላልፈዋል፤ በስጦታ ውሉ መሰረት ስመ-ሃብቱ በአንደኛዋ ልጅ ስም ተመዝግቧል፤ እንዲሁም እናት ያደረጉት የስጦታ ውሉ ፈራሽ እንዲባል ያቀረቡት ክስ በይርጋ ቀሪ ተደርጎ ይኸው ውሳኔ እንደፀና ነው በማለት ከሟች አባታቸዉ የተለላፈላቸዉ ድርሻ የውርስ ሃብት ሊሆን እንደማይገባ መወሰን ስህተት ነዉ።

በሌላ በኩል የጋራ የሆነ ቤትን አንድ ወላጅ ሲሞት ሌላኛው ወላጅ የሟች ድርሻ ጭምር የቁም ሥጦታ ካደረገ የስጦታ አድራጊው ድርሻን በተመለከተ የሟች ወራሾች የቁም ስጦታው በሕግ የፀና ከሆነ የቁም ሥጦታ አድራጊው ከሞተ በኋላም መጠየቅ የማይቻል ለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ በሰ/መ/ቁ.186715 በሆነ መዝገብ ላይ በቀን 30/06/2013 ዓ.ም “ነገር ግን እናት በቤቱ ላይ የነበራቸውን መብት በስጦታ ያስተላለፉ በመሆኑ እና ስጦታው እንዲሻርላቸው ጠይቀው ውድቅ የሆነባቸው በመሆኑ ስጦታው የእናት ድርሻን በተመለከተ ዋጋ የሚያጣበት ምክንያት የለም የሚል አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡

ምሳሌ 1፡- አንድ ሟች የግል ንብረቱ የሆኑ አንደ ቤት ግምቶ 80 ሚሊዮን፤ ሁለት መኪናዎች ግምታቸው 3 ሚሊዮን እና 5 ሚሊዮን ብር የሆኑ ያሉት ሲሆን አራት ልጆች እያሉት ቤቱን እኔ ቤቱን ሳይሞት ለአንዱ ልጅ ቢሰጠው እና ሟች ከመሞቱ በፊት ስመ-ሃብቱ ስጦታ ለተሰጠው ልጅ የዞረ ቢሆን ይህን ሌሎቹ ልጆች በቤቱ ላይ የተደረገው ስጦታ ከውርስ የነቀልን ወይም ሊደርሰን ከሚችለው ከአንድ አራተኛ በታች የደረሰን በመሆኑ ይፈረስልን ማለት ይችላሉ ወይስ አይችሉም? የቤት ስጦታ የተደረገለት ልጅስ ሟች ኑዛዜ ሳያደረግ የሞቱ በመሆኑ ከመኪናዎቹ ድርሻውን የወራሽነት በማረጋገጥ ሲጠይቅ በስጦታ የተሰጠውን ቤት ካልመለሰ ሊካፈል አይገባም የሚል ክርክር በሌሎቹ ወራሾች ቢቀርብ ውጤቱ ምን ይሆናል?

ምሳሌ 2፡- አንድ ሟች የግል ንብረቱ የሆኑ አንደ ቤት ግምቶ 80 ሚሊዮን፤ ሁለት መኪናዎች ግምታቸው 3 ሚሊዮን እና 5 ሚሊዮን ብር የሆኑ ያሉት ሲሆን አራት ልጆች እያሉት ቤቱን ሳይሞት በሕግ ወራሽ ላልሆነ ጓድኛው ቢሰጠው እና ስመ-ሃብቱ ሟች ከመሞቱ በፊት ስመ-ሃብቱ ስጦታ ለተሰጠው ጓድኛው የዞረ ቢሆን ይህን ስጦታ ልጆች ከውርስ የነቀልን በመሆኑ ወይም በሕጉ መሰረት እስከ አንድ አራተኛ ድረስ ከውርስ ሃብቱ የማግኘት መብታችን ያሳጣን በመሆኑ የስጦታ ውሉ ይፈረስልን ማለት ይችላሉ ወይስ አይችሉም

እነዚህ ሁለቱም ምሳሌዎች ከላይ ሰበሩ በተለያዩ መዛግብት በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም እና ከቁም ሥጦታ ሕግ አንጻር ሲታዩ ሟች በምሳሌ አንድ ለሕጋዊ ወራሹ ማለትም ለልጁ እና በምሳሌ ሁለት ሕጋዊ ወራሽ ላልሆነው ለጓድኛው ያደረገው የቁም ስጦታ በህይወት እያለ እንዲፈፀም ያደረገው(ማለትም የቤቱን ስመ-ሃብት ከሟች ወደ ስጦታ ተቀባዮቹ በሕይወት እያለ ያዞረላቸው በመሆኑ) የቁም ስጦታ ስለሆኑ የሚፈርስበት የሕግ ምክንያት የለም፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በይርጋ የማይታገዱ የውርስ ጉዳዮች እና ከኑዛዜ ጋር የተያያዙ ይርጋዎች
በኢትዮጵያ ከሕግ አገልግሎት የሚሰበሰብ የተጨማሪ እሴት ታክስና የተርን ኦቨር ታ...

Related Posts

 

Comments 1

Abebe
Guest - ነግ on Friday, 26 April 2024 08:15

መጽሐፉ የት ይገኛል?

መጽሐፉ የት ይገኛል?
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 13 November 2024