Font size: +
10 minutes reading time (1981 words)

ስለ ሸሪኣ ፍርድ ቤቶች መልስ የሚሹ ጉዳዮች

በተደራጀ እና በብሔራዊ ሕግ ዕውቅና አይሰጣቸው እንጂ በኢትዮጵያ የሸሪኣ ሕግን መሠረት በማድረግ ውሳኔ መስጠት የቅርብ ታሪክ አይደለም፡፡ በታወቀ ሁኔታ እና በመንግሥት ድጋፍ የሸሪኣ ፍርድ ቤቶች የተቋቋሙት ግን በ1934 ዓ.ም. ነው፡፡ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሕጉ ከሁለት ዓመት በኋላ ተሻሻለ፡፡ ቀጥሎም አገሪቱ በፌደራል ሥርዓት መተዳዳር ከጀመረች በኋላ በ1992 ዓ.ም. እንደ አዲስ የፌደራል ሸሪኣ ፍርድ ቤቶች ተቋቋሙ፡፡ በፌደራል ብቻ ሳይወሰኑ በክልሎቹም እንዲሁ ተቋቋሙ፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋና መሠረቱ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ነው፡፡ በአንዳንድ ክልሎች፣ ከመደበኛው ፍርድ ቤት ጎን ለጎን በችሎትነት ሲቋቋሙ በፌደራል ደረጃ ግን ራሳቸውን ችለው የመጀመሪያ ደረጃ፣ ከፍተኛ እና ጠቅላይ ሸሪኣ ፍርድ ቤቶች በመባል ተቋቁመዋል፡፡

የፌደራሉን በአስረጂነት ብንወስድ በየእርከኑ ለሚገኙት ሸሪኣ ፍርድ ቤቶች ተጠሪ ያላቸው ሲሆን የሚያስተዳድራቸውም የጠቅላይ ሸሪኣ ፍርድ ቤት ዋና ቃዲ (ፕሬዚደንት) ነው፡፡ ከዚያ፣ በጥቅሉ ግን ተጠሪነቱ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ነው፡፡ የሚተዳደሩበትን በጀትም በተመለከተ ምንጩ በዋናነት ከመንግሥት ነው፡፡ ዳኞችም በእስልምና ምክር ቤት አቅራቢነት በፌደራል የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ይሾማሉ፡፡ የሚተዳደሩትም እንደሌሎች የመደበኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ሁሉ ነው፡፡

ዳኛ ለመሆን ደግሞ በዋናነት መስፈርቱ የሸሪኣ ሕግ ዕውቀት መኖር ነው፡፡ ፍርድ ቤቶቹ በተሠጣቸው የዳኝነት ሥልጣን ላይ ውሳኔ ለመወሰን የሸሪኣ ሕግን ይጠቀማሉ፡፡ ስለሆነም፣ ለሕጉ ምንጭ የሆኑትን ቁርኣንን፣ ሀዲስን እንዲሁም ዑለማዎች የተስማሙባቸውን ውሳኔዎች (ኢጅማ)፣ ከሌሎች መርሆች ጋር ማመሳስልን (ቂያስ) እንደ ነገሩ ሁኔታ ጥልቅና ግላዊ ነገር ግን ምሁራዊ ምርምሮችን (ኢጂቲሃድን) ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡

እንደየአገራቱ ሁኔታ የሸሪኣ ፍርድ ቤቶች የሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕጎችንም የሚጠቀሙ አሉ፡፡ በእኛ አገር ግን ክርክሮቹ የሚመሩት በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ መሠረት መሆን እንዳለበት በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ይህ ጽሑፍም አንዳንድ ያልተቀረፉ እና አሳሳቢ የሚባሉ ነጥቦችን ያነሳል፡፡ የተወሰኑት አጠር አጠር በማድረግ፣ሁለት ጉዳዮችን ግን ዘርዘር ተደርገው ይቀርባሉ፡፡

ስለቃዲዎች፤

የመጀመሪያው ነጥብ ከዳኞች (ቃዲዎች) ጋር የሚገኛኝ ነው፡፡ የሸሪኣ ፍርድ ቤት ዳኛ ለመሆን ዋነኛው መለኪያ የሸሪኣ ሕግ ዕውቀት ነው፡፡ ይኼን ደግሞ ሊያረጋግጥ የሚችለው የእስልምና ምክር ቤቱ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ መሠረታዊ የሕግ ዕውቀትን አይጠይቅም፡፡ ይሁን እንጂ በአጠቃላይ ችሎቱ እና ክርክሩ የሚመራው በመደበኛው የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በተለይ ይህንን የሚመለከቱ ሕጎችን ማወቅ የሚገባ ነው፡፡

በተጨማሪም፣ የሸሪኣ ፍርድ ቤቶች ሕገ መንግሥቱን እና የራሳቸውንም ሥልጣን መጠንቀቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለሆነም፣መሠረታዊ የሕግ ዕውቀትን መለኪያ ማድረግ የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ መረሳት የሌለበት ጉዳይ የእስልምና ምክር ቤቱ ከግምት ማስገባት ያለበት የሸሪኣ ሕግ ምንጮችን እንዲሁም አተረጓጎሞችን የሚመለከቱ የተለያዩ አስተምህሮዎች (መዛሂብ) ስላሉ በአገሪቱ ውስጥ በወጥነት ለመጠቀም ሊያስቀምጣቸው የሚገቡ መርሆች የመኖራቸው ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ውጤቱ ላይ የተለያየ ስለሚሆን ነው፡፡

እርግጥ አዋጁ ይሄንን በማሰብ ይመስላል በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ትርጓሜዎች ካጋጠሙ ጠቅላይ ሸሪኣ ፍርድ ቤቱ ከአምስት ባለነሱ ቃዲዎች (ዳኞች) ውሳኔ ይሠጣል፣ያለው፡፡ ይህ እንግዲህ በፌደራልም በክልሎችም ሊያጋጥም የሚችል ጉዳይ ነው፡፡

በመደበኛ ፍርድ ቤት የዳኞችን ሹመት የሚያጸድቀውም ይሁን ከሹመት የሚያነሳው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምመላው የሚከናወነው በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ነው፡፡ ቃዲዎቹን በተመለከተ ግን የእስልምና ምክር ቤት ጉባኤው ያቀርብና የሚሾሙት በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ነው፡፡ ስለምን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አልተሾሙም? እንደሌሎች ዳኞችሥ ያለመከሰስ መብት አላቸው ወይ? ጥቅምና ጉዳቱ ጭምር ሊታይ የይገባዋል፡፡ ለምሳሌ በእስራኤል በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ነው የሚሾሙት፡፡

የፍርድ ቤቶቹ ተጠሪነትና አወቃቀር፤

የፍርድ ቤቱን አወቃቀርም በተመለከተ እንዲሁ የተወሰኑ መነሳት ያለባቸው ነጥቦች አሉ፡፡ አንዳንድ አገራት እንደ ግልግል ዳኝነት ብቻ ይቆጠራሉ፡፡ ግለሰቦች በራሳቸው ተስማምተው በግልግል የሚዳኙባቸው ተቋማት ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ በእንግሊዝ እንዲህ ዓይነት ተግባር ላይ የተሰማሩ ከ85 ያላነሱ ተቋማት አሉ፡፡ ነገር የሚሰጧቸው ውሳኔዎች በፍርድ ቤት አስገዳጅ አይደሉም፡፡ ባለጉዳዮቹ በራሳቸው በእነዚህ ተቋማት ከጨረሱ ችግር የለውም፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን የአስገዳጅ ባሕርይ የላቸውም፡፡ በካናዳ እና ሕንድም ተመሳሳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን የሸሪኣ ፍርድ ቤቶች የሚሰጧቸው ውሳኔዎች እንደማንኛው የፍርድ ቤት ውሳኔ አስገዳጅ ናቸው፡፡

እነዚህ ፍርድ ቤቶች በመጨረሻ ተጠሪነታቸው ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ሸሪኣ ፍርድ ቤቶች የሚሰጧቸው ውሳዎችም በፌደራሉ ጠቅላይ ፈርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሊከለሱ ይችላሉ፡፡ በሰበር መከለስን በተመለከተም አሁንም የተወሰኑ መጥራት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የሸሪኣ ፍርድ ቤቶቹ የሰጧቸው ውሳኔዎች መሠረታዊ የሕግ ስህተት አላቸው የሚባለው ሥነሥርዓትን በተመለከተ ብቻ ነው ወይንስ መሠረታዊ ሕጉንም የሚለው ነው፡፡ መሠረታዊ ሕጉ፣ መነሻው ቁርኣንና ሌሎች ከላይ የተጠቀሱት ሲሆኑ እነሱን ይመለከታል ወይ? በተለይ ደግሞ እነዚህ ሕጎች ከሕገ መንግሥቱና ከዓለም አቀፍ የሰብኣዊ መብት ስምምነቶች ጋር የሚጣረሱ ቢሆንስ? ሕገ መንግሥቱ ፈቅዶ ከተቋቋሙ በኋላ ከእንደገና በሕገመንግሥትና በሠብኣዊ መብት ሰነዶች መለካት ይጠበቅባቸዋል ወይ? ያሰኛል፡፡ እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ዞሮ ዞሮ በሃይማኖት መሠረት ሳይሆን በሌሎች ሕግ መሠረት ይሆናል ውሳኔ የሚሠጠው፡፡

የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕጎች፤

የሸሪኣ ፍርድ ቤቶች የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉን የመጠቀም ግዴታ አለባቸው፡፡ ይሁን እንጂ የማስረጃ ጉዳይን በተመለከተ በግልጽ የተባለ ነገር የለም፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጉ የተወሰኑ የማስረጃ ደንቦችን ቢይዝም ቅሉ፣ በቂ ግን አይደለም፡፡ አንድንድ ጉዳዮችን በሚመለከት መሠረታዊ ሕጎቹ የማስረጃ ሕግንም ጨምረው ይዘዋል፡፡ ሸሪኣ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ለመስጠት ማስረጃ ስለሚስፈጋቸው በተለይም ምስክርነትን በሚመለከት ሸሪኣን የሚከተሉ ብዙ አገራት የሴቶች የምስክርት ቃል ከወንድ ያነሰ ወይንም የሁለት ሴቶች እንደ አንድ የወንድ ምስክርነት ስለሚታይ እልባት ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ዙሪያ መጥራት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ በተለይም ሕገመንግሥታዊነታቸው ስለሚያሳስብ፡፡ 
የሸሪኣ ፍርድ ቤቶቹ ችሎት በሚመሩት ጊዜ የሚያጋጥማቸውን ችሎት መድፈርና የፍትሕ ሥራን የማደናቀፍ ተግባር በተመለከተ የተሠጣቸው ሥልጣን ከመደበኛው ያነሰ ነው፡፡ ችሎት የደፈረን ሰው ቅጣት መወሰን የሚችሉት ከአንድ ወር በማይበልጥ እስራት ወይንም ከአንድ ሺ ብር ባልበለጠ የገንዘብ መቀጮ ነው፡፡ መደበኛ ፍርድ ቤቶች ሲሆኑ ግን እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ እስራት መቅጣት ይችላሉ፡፡ የልዩነቱ ምንጭ የሚያሰምን አይደለም፡፡ የትኩረት ማነስም ይመስላል፡፡

የትምህርት ሁኔታ፤

በአገሪቱ ባሉት ዩኒቨርሲቲዎች፣የሸሪኣ ሕግ መማርን የወደደ ተማሪ የሚወስደው አንድ ኮርስ አለ፡፡ ከዚህ ያለፈ ሌላ ትምህርት የለም፡፡ ሸሪኣ በዋናነት በየመድረሳዎቹ የሚሰጥ ትምህርት ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች ቢኖሩም፣በየባንኮቹ የሚሰጡት አገልግሎቶች እየጨመሩ ቢሄዱም በየዩኒቨርሲቲዎቹ የሚሰጠው ኮርስ አልጨመረም፡፡ ወይንም ደግሞ፣ እስልምና ምክር ቤቱ የተወሰኑ የመደበኛ ሕግ ትምህርቶችን ጨምሮ ሥልጠና የሚሰጥበት ተቋም ማቋቋም ይጠበቅበታል፡፡ ይሁን እንጂ ቃዲዎቹ ቢያንስ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጎቹን ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የጥብቅና አገልግሎት፤

የሸሪኣ ፍርድ ቤቶች አወቃቀር እንደ መደበኛው ፍርድ ቤት ሁሉ የፌደራል ሥርዓቱን የተከተለ ነው፡፡ ለነገሩ የሸሪኣ ፍርድ ቤቶች ብቻ ሳይሆን የእስልምና ምክር ቤቶቹም ቢሆን እንዲሁ ፌደራላዊ ናቸው፡፡ ስለሆነም፣ የፌደራል እና የክልል ሸሪኣ ፍርድ ቤቶች አሉ ማለት ነው፡፡ በእነዚህ ፍርድ ቤቶች የሚደረጉ ክርክሮችም በሌሎች ፍርድ ቤቶች እንደሚደረገው ሁሉ የጠበቃ ርዳታ ማስፈለጉ አይቀሬ ነው፡፡ ጉዳዩን የበለጠ አስፈላጊ የሚያደርገው ደግሞ በሸሪኣ ሕግ ጠለቅ ያለ ሥልጠና ያላቸው ጠበቆች ያለመኖሩ ጉዳይ ነው፡፡ ይኽ እንደተጠበቀ ሆኖ በእነዚህ ፍርድ ቤቶች በመቅረብ ክርክር ማቅረብ የሚችሉ ጠበቆችን የሚገዛ ሕግም የለም፡፡ በተለምዶ ግን በፌደሬል የመጀመሪያ ፍርድ ቤቶች ወይንም ሁለተኛ ደረጃ የጥብቅና ፍቃድ ያላቸው በአንጻሩ ባሉት የሸሪኣ ፍርድ ቤቶች እንዲሁም በማናቸውም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ወይንም አንደኛ ደረጃ የጥብቅና ፍቃድ ያለውም በትዩዩ ባሉት ሸሪኣ ፍርድ ቤቶች በመቅረብ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

የዳኝነት ሥልጣናቸው

የፌደራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን ከመደበኛው ፍርድ ቤቶች የሚጋሯቸው የወል ሥልጣን እንጂ የራሳቸው የተለየ ሥልጣን የላቸውም፡፡ በመሆኑም በማቋቋሚያ አዋጁ ቁጥር 188/1992 በአንቀጽ 4 መሠረት በማናቸውም ደረጃ የሚገኙ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን አይተው የመወሰን የዳኝነት ሥልጣን ያላቸው የጋብቻና የፍች፣ የቀለብ አወሳሰን፣ አካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት ሞግዚትነት እና የቤተሰብ ዝምድና ላይ የሚነሱ ጉዳዮችን በተመለከተ ሲሆን ጥያቄ ያስከተለው ጋብቻ በእስልምና ሃይማኖት ሥርዓት መሠረት የተፈፀመ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ ባለጉዳዮቹ በእስልምና ሃይማኖት ሥርዓት ለመዳኘት ሲመርጡ ነው፡፡

በተጨማሪም የወቅፍና (ከንብረትን አላባ ሌሎች እንዲጠቀሙበት መሥጠት) ስጦታ /ሂባ/፣ ውርስ ወይም ኑዛዜ ጉዳዮችን በተመለከተ አውራሹ ወይም ስጦታ አድራጊው ወይም ተናዛዡ ሙስሊም የሆነ እንደሆነ ወይም ሟች በሞተበት ሰዓት ሙስሊም ሆኖ የሞተ እንደሆነ፤ እንዲሁም እንዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ክርክር ቀርቦ ኪሣራ የሚመለከት ውሳኔ የመስጠት የዳኝነት ሥልጣን አላቸው፡፡

ለእነዚህ የዳኝነት ሥልጣን መነሻቸው ደግሞ ሕገመንግሥቱ የግልና የቤተሰብ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ለባለጉዳዮቹ በሃይማኖታዊ ፍርድ ቤቶች የመዳኘት መብትን ስለሚሰጥ ነው፡፡ ቀድሞ በሥራ ላይ የነበረው ሕግም ቢሆን የዳኝነት ሥልጣኑ ከአሁኑ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ኢስላሚ ሪፐብሊክ ከሆኑ አገራት ውጭ ያሉትና በሸሪአ ፍርድ ቤቶች መዳኘተን የሚፈቅዱ ባብዝኃኛው ለፍርድ ቤቶቹ የፈቀዷቸው ተመሳሳይ ጉዳዮችን ነው፡፡

እርግጥ ነው የቤተሰብ የሚለውም ይሁን የግል ጉዳዮች የሚሉት ለትርጉም የተጋለጡ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የዳኝነት ሥልጣንን በተመለከተ የጠራ አመለካከት የለም፡፡ አንድ ምሳሌ እናንሳ፡፡ በሰበር የታየ እና እልባት ያገኘ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ፍርድ ቤቶቹ ያላቸውን ሥልጣንም እንዲሁም ጉዳዩን የተመለከቱት ቃዲዎች ለሸሪኣ ፍርድ ቤት ያላቸውን አመለካከት ያሳያል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉንም ፍርድ ቤቶች የሚመለከት ነው ማለት ግን ፍጹም አይደልም፡፡

ጉዳዩ እንዲህ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ድሬዳዋ ከተማ ያለው የናኤባ ፍርድ ቤት የሚከተለውን ውሳኔ ያስተላልፋል፡፡ የይዞታ ክርክር ነው፡፡ አመልካችና ተጠሪ የአንድ ሰው ወራሾች በመሆናቸው ምክንያት የቀረበ የውርስ ንብረት ክርክር ይምሰል እንጂ መነሻው ቦታው የማን ይዞታ ነው የሚል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ የፌደራሉ ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤትም የዴሬዳዋ ናኢባ ፍርድ ቤት ቦታውን አስመልክቶ ከፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያላነሰ ሥልጣን እንዳለቸው በመግለጽ ጉዳዩን በማከራከር ይወሰናል፡፡

የናኢባ ፍርድ ቤቱም፣ አመልካች ያቀረበችውን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ፣ ክርክርና ማስረጃ ከሰማ በኋላ አመልካች ይዞታውን ለተጠሪ እንድትለቅ በማለት ወስኗል፡፡ አመልካች በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ለከፍተኛ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርባ ከተከራከሩ በኋላ የሥረ ነገር ሥልጣን ክርክሩን በመተው ወስኗል፡፡

በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ተጠሪ ይግባኝ ለፌደራሉ ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት አቅርባ ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤቱም የናኢባ ፍርድ ቤቱ ከፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የማያንስ ሥልጣን አለው ካለ በኋላ በፍሬ ነገሩ ላይ ወሳኔ ሰጥቷል፡፡ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የይዞታ ጉዳይን ማየት እንደማይችል፣ እንዲሁም ከፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያላነሰ ሥልጣን እንዳለው የገለጸውን በመተቸት ውሳኔውን ሽሮታል፡፡

ለመዳኘት ፍቃድን መስጠት፤

በሸሪኣ ፍርድ ቤት ለመዳኘት ተካራካሪ ወገኖች በዚሁ ፍርድ ቤት ለመዳኘት ፍቃደኛ መሆን አለባቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱም ይሁን አዋጁ ይህንኑ መሥፈርት በግልጽ ያስቀምጣሉ፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 4(2) የበለጠ በማረጋገጥ ዓይነት ፍርድ ቤቶቹ ሥልጣን የሚኖራቸው ተከራካሪ ወገኖች በእስልምናው ሃይማት ሥርዓት ለመዳኘት ግልጽ በሆነ መንገድ በፈቃዳቸው ከመረጡ አልበለዚያም ደግሞ መጥሪያ በአግባቡ የደረሰው ተከሳሽ መልስ ሳይሰጥ ከቀረ እንደተስማማ ይቆጠራል በማለት ነው፡፡

የሃማኖት ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣናቸውን ለመተግበር አስቀድመው የባለጉዳዮቹን ፈቃደኝነት ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እዚህ ላይ የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ግን ሁለት ነጥበችን ብቻ እናንሳ፡፡ የመጀመሪያው መጥሪያ ደርሷቸው ነገር ግን መልስ ሳይሰጡ ቢቀሩ እደተስማሙ የሚሠጠው ግምት አጠያያቂ ነው፡፡ በእርግጥ ማንም ሰው በመደበኛ ፍርድ ቤት የመዳኘት ግዴታ እንዳለበት የታመነነ እና የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ በሃይማኖታዊ ፍርድ ቤት ለመዳኘት ግን የተከራካሪውን ወገን ስምምነት ይጠይቃል፡፡ ለዚያው፣ስምምነቱን በግልጽ እና በጽሑፍ የመግለጽ ግዴታ አለበት፡፡ በዚህ ሁኔታ ግዴታ የተጣለበትን ሰው መጥሪያ ደርሶት መልስ ካልሰጠ እንደተስማማ ግምት የመወሰዱ ተገቢነት ተጠየቃዊ አይመስልም፡፡

ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ ጣልቃ ገብ ወይንም ሦስተኛ ወገን ተከራካሪዎችን የሚመለከት ነው፡፡ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ ከከሳሽና ተከሳሽ በተጨማሪ የሚሳተፉ ባለጉዳዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ ክርክር የቀረበበት ጉዳይ የሌሎች ሰዎች ጥቅም ላይ ተጽእኖ በሚኖረው ጊዜ ጥቅማቸው የሚነካባቸው ሰዎች በራሳቸው አነሳሽነት የክርክሩ አካል ለመሆን ለፍርድ ቤቱ በማመልከት ጣልቃ ለመግባት በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 41 መሠረት ፍርድ ቤቱን ሊያስፈቅዱ ይችላሉ፡፡

ከተፈቀደላቸው የክርክሩ አካል ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ አልበለዚያም ተከራካሪዎቹ በሚያቀርቡት ማመለከቻ መሠረት ፍርድ ቤቱ ሌሎች ሰዎች የክርክሩ አካል እንዲሆኑ ሊያሳውቃቸው ይችላል፡፡ አስቸጋሪው ነገር የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡ በተለይም በሸሪኣ ፍርድ ቤት በመታየት ላይ ያለው ጉዳይ ጥቅማቸውን የሚነካባቸው ሰዎች ጣልቃ ለመግባት በምን መንገድ ፍቃደቸው ይረጋገጣል? የሚለው መልሥ ያስፈለገዋል፡፡

የሸሪኣ ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ አዋጁ ስምምነትን በሚመለከት ከግምት ያስገባው ከሳሽና ተከሳሽን እንጂ እንዲህ ዓይነት ጣልቃ ገቦችን አይደለም፡፡ በመሆኑም መቼ ላይ ፍቃደኝነታቸው ይጠየቅ? የተለያዩ መልሶችን ማሰብ ይችላል፡፡ አንደኛው አካሄድ ፍርድ ቤቱ በግልጽ መጠየቅ ሳያስፈልገው ባለጉዳዩ ጣልቃ ለመግባት ሲያመለክት ለመዳኘት እንደተስማማ ሊወሰድ ይችላል የሚለው ነው፡፡ ችግሩ ግን፣ የክርክሩ ተካፋይ እንዲሆን ሳይፈቀድለት አስቀድሞ ፈቃዱን በምን ሁኔታ እና መቼ ይገልጻል? የሚለው ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የክርክሩ አካል እንዲሆን ከተፈቀደለት በኋላ በዋናው ጉዳይ ላይ ከመሳተፉ አስቀድሞ በሸሪኣ ለመዳኘት ስለመፈለጉ ወይንም አለመፈለጉ ስምምነቱን መግለጽ አለበት የሚለው ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ሁለት ጉዳዮች አሉ፡፡

የመጀመሪያው ጣልቃ ገቡ በሸሪኣ ፍርድ ቤት ለመዳኘት አለመስማማቱ ዋናዎቹ ባለጉዳዮች ላይ የሚኖረው ውጤት ነው፡፡ ማለትም በአጠቃላይ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ከማከራከርና ውሳኔ ከመስጠት ማቆም አለበት ወይንስ የለበትም? የሚለው እልባት ያስፈልገዋል፡፡ ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ፣ ጣልቃ ገቡ በሸሪኣ ፍርድ ቤት ለመዳኘት ካልፈለገ እና ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ማየቱን የሚቀጥል ከሆነ ጣልቃ ገቡ ሌላ ፍርድ ቤት ክስ እንዳያቀርብ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ስለማይፈቅድለት መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡

ይህንን ዓይነቱን ጉዳይ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር ቀርቦለት የሰጠውን ውሳኔ እንመልከት፡፡ ጉዳዩ በሸሪኣ ፍርድ ቤቶች ታይቶ የመጨረሻ ውሳኔ ስላገኘ ወደ ሰበር ችሎት ቀርቧል፡፡ መነሻውም፣ የሸሪኣ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በማየት ላይ እያለ ሌሎች ሰዎች የክርክሩ ተካፋይ ለመሆን አቤቱታ ሲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ ይቀበላቸዋል፡፡ ከዚያም መቃወሚያቸው በሸሪኣ ፍርድ ቤት ለመዳኘት ፈቃደኛ ስላልሆኑ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን የማየት ሥልጣን የለውም የሚል ነው፡፡ ፍርድ ቤቶቹም ጣልቃ ለመግባት የቀረበውን ማመልከቻ እንደመስማማት በመውሰድ ተቃውሞውን ውድቅ በማድረግ እና በዋናው ጉዳይም ላይ ፍርድ ስለተሰጠ ለሰበር ቀርቧል፡፡

ሰበር ሰሚ ችሎቱም ጣልቃ ገብ አመልካች በሸሪዓ ሕግ መሠረት በሸሪዓ ፍርድ ቤት ለመዳኘት ፍቃድ አልሰጠሁም በማለት ክርክር ቢያቀርብም እንደሥር ፍርድ ቤቶቹ ሁሉ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ፣ አመልካቹ በሸሪዓ ህግ ለመዳኘት ፍቃዱን መስጠት ወይንም አለመስጠቱን ለማረጋገጥ የመረጠው የሸሪዓ ፍርድ ቤት ተከራካሪ ሆኖ የገባበትን ሁኔታ በማየት ነው፡፡ ለውሳኔው ደግሞ፣ አመካካች በሸሪዓ ፍርድ ቤት ተከራካሪ ሆኖ ከገባ በኋሊ የሸሪዓ ፍርድ ቤት ያቀረበውን ጥያቄና ክርክር ይዘት በቅድሚያ መርምሮታል ፡፡

በዚህም መሠረት አመልካች አመልካች በፍትሐ ብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ቁጥር 41 መሠረት ጣልቃ ገብቶ ለመከራከር ሲጠይቅ በክርክሩ ሒደት በአዋጅ ቁጥር 188/1992 አንቀፅ 6(1) መሠረት የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች የውሣኔአቸው መሠረት ሊያደርጉት በሚገባው በሸሪዓ ሕግ መሠረት ለመዳኘት ፍላጎትና ፍቃዱ አስቀድሞ ያለው መሆኑን ያመለክታል በሚል ነው፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ አመልካች በሸሪዓ ሕግ መሠረት በሸሪዓ ፍርድ ቤት ለመዳኘት ፍቃዱን የሰጠ መሆኑን ወይም አለመሆኑን አመልካች በክርክሩ ጣልቃ እንዲገባ የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ከፈቀደለት በኋሊ ያቀረበውን ክርክር ይዘትና የሸሪዓ ፍርድ ቤት በዳኝነት በማየት እንዲወሰንለት ያቀረበውን ጭብጥ በመመርመር ውሣኔ መስጠት እንጂ ለመዳኘት አለመፈለጉን ሊሆን አይችልም የሚል ይዘት አለው፡፡ እንግዲህ የሰበር ውሳኔው እና በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ አስገዳጅነት ያለው ይህ አቋም ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ከላይ ያነሳናቸውን ጥያቄዎች በድጋሜ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ድጋፍ የተሳነው እና እየተዘነጋ የመጣው የኮንስትራክሽን ውሎች አማራጭ የግጭት አ...
የዘገየ ፍርድ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Tuesday, 23 July 2024