በተደራጀ እና በብሔራዊ ሕግ ዕውቅና አይሰጣቸው እንጂ በኢትዮጵያ የሸሪኣ ሕግን መሠረት በማድረግ ውሳኔ መስጠት የቅርብ ታሪክ አይደለም፡፡ በታወቀ ሁኔታ እና በመንግሥት ድጋፍ የሸሪኣ ፍርድ ቤቶች የተቋቋሙት ግን በ1934 ዓ.ም. ነው፡፡ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሕጉ ከሁለት ዓመት በኋላ ተሻሻለ፡፡
ቀጥሎም አገሪቱ በፌደራል ሥርዓት መተዳዳር ከጀመረች በኋላ በ1992 ዓ.ም. እንደ አዲስ የፌደራል ሸሪኣ ፍርድ ቤቶች ተቋቋሙ፡፡ በፌደራል ብቻ ሳይወሰኑ በክልሎቹም እንዲሁ ተቋቋሙ፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋና መሠረቱ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ነው፡፡ በአንዳንድ ክልሎች፣ ከመደበኛው ፍርድ ቤት ጎን ለጎን በችሎትነት ሲቋቋሙ በፌደራል ደረጃ ግን ራሳቸውን ችለው የመጀመሪያ ደረጃ፣ ከፍተኛ እና ጠቅላይ ሸሪኣ ፍርድ ቤቶች በመባል ተቋቁመዋል፡፡
የፌደራሉን በአስረጂነት ብንወስድ በየእርከኑ ለሚገኙት ሸሪኣ ፍርድ ቤቶች ተጠሪ ያላቸው ሲሆን የሚያስተዳድራቸውም የጠቅላይ ሸሪኣ ፍርድ ቤት ዋና ቃዲ (ፕሬዚደንት) ነው፡፡ ከዚያ፣ በጥቅሉ ግን ተጠሪነቱ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ነው፡፡ የሚተዳደሩበትን በጀትም በተመለከተ ምንጩ በዋናነት ከመንግሥት ነው፡፡ ዳኞችም በእስልምና ምክር ቤት አቅራቢነት በፌደራል የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ይሾማሉ፡፡ የሚተዳደሩትም እንደሌሎች የመደበኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ሁሉ ነው፡፡
ዳኛ ለመሆን ደግሞ በዋናነት መስፈርቱ የሸሪኣ ሕግ ዕውቀት መኖር ነው፡፡ ፍርድ ቤቶቹ በተሠጣቸው የዳኝነት ሥልጣን ላይ ውሳኔ ለመወሰን የሸሪኣ ሕግን ይጠቀማሉ፡፡ ስለሆነም፣ ለሕጉ ምንጭ የሆኑትን ቁርኣንን፣ ሀዲስን እንዲሁም ዑለማዎች የተስማሙባቸውን ውሳኔዎች (ኢጅማ)፣ ከሌሎች መርሆች ጋር ማመሳስልን (ቂያስ) እንደ ነገሩ ሁኔታ ጥልቅና ግላዊ ነገር ግን ምሁራዊ ምርምሮችን (ኢጂቲሃድን) ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡